አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 19 April 2017

ጎንደር ሚያዚያ 11/2009 በጎንደር ከተማ በሚካሔደው 7ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን በመቀበል ለፎረሙ መሳካት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ በከተማዋ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ዛሬ ለመንግስት ሰራተኞች ባዘጋጀው መድረክ ላይ የፎረሙን ዋና አላማ፤እየተደረገ ያለውን ቅድመ ዝግጅትና የአፈጻጸም ደረጃ አስመልክቶ ገለጻ አድርጓል።

ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ብስራት ጋሻው ፎረሙ ተቀዛቅዞ የቆየውን የከተማውን የንግድ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዘርፍ በማነቃቃት በኩል ታላቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

"ለፎረሙ ዝግጅት ተብለው የተጀመሩ የመንገድ፤ የጽዳትና ውበት፤ የመዝናኛ ስፍራዎች ግንባታ፤ የኮብል ስቶን የድንጋይ ንጣፍ የልማት ስራዎች የከተማውን መልካም የልማት ገጽታ የሚያጎሉ በመሆናቸው ዘላቂና ቀጣይነት ባለው መንገድ ሊገነቡ ይገባል" ብለዋል፡፡

አቶ አደራጀው  አዳነ የተባሉ የመንግስት ሰራተኛ በበኩላቸው "ከተማዋ የምትታወቅባቸውን የቱሪዝም ሀብቶች በማስተዋወቅ የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር አጋጣሚውን መጠቀም ተገቢ ነው" ብለዋል፡፡

የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ጽዳት በመጠበቅና ጎብኚዎችን በተገቢው መንገድ ማስተናገድ እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም የሚሳተፉበት ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል።

"ፎረሙ የከተማዋን መልካም ገጽታ ለመገንባት ትልቅ ድርሻ አለው" ያሉት ደግሞ ሌላው የመንግስት ሰራተኛ አቶ መርከብ እሸቴ ናቸው፡፡

ፎረሙን ምክንያት በማድረግ በከተማው እየተሰሩ ያሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የነዋሪውን የረጅም አመታት የልማት ጥያቄ ምላሽ በመስጠት በኩል የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የመሰረተ ልማት ስራዎቹ ከፎረሙ ማብቂያ በኋላም ቀጣይነት ሊኖራቸው እንደሚገባና ዘላቂ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ ጥራታቸው ተጠብቆ ሊካሄዱ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ለፎረሙ ስኬታማነትም ወደ ከተማው የሚመጡ እንግዶችን ከመቀበል ጀምሮ ፎረሙ ያለ አንዳች ስጋት በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑም አቶ መርከብ ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል ፎረሙን በማሳካት በኩል የከተማ አስተዳደሩ አደረጃጀቶችን ፈጥሮ ወደ ተግባር በመግባት የተጀመሩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በአብዛኛው በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የልማት ስራዎቹ ምንም እንኳን ፎረሙን ምክንያት በማድረግ የተጀመሩ ቢሆንም በበጀት አመቱ በከተማው ሊሰሩ የታቀዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለፎረሙ መሳካትም የመንግስት ሰራተኛው ከመላው የከተማው ህዝብና ከከተማ አስተዳደሩ  ጋር በመሆን እንዲረባረብም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡  

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ አየልኝ ሙሉአለም በበኩላቸው የከተማውና የዞኑ አስተዳደር 7ኛውን የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም በስኬት ለማጠናቀቅ የጋራ ሃላፊነትና ተልዕኮ ወስደው በርካታ ተግባራትን በቅንጅት እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ፎረሙ ከተማዋና ዞኑ ለተሳታፊው የሚተዋወቁበት ፣እንግዶችም ከፎረሙ መልስ የጎንደር አምባሳደር በመሆን መልካም ገጽታዋን ለሌሎች የሚያካፍሉበት ምቹ አጋጣሚ በመሆኑ የመንግስት ሰራተኛው ለስኬታማነቱ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ፎረሙን አስመልክቶ ለግማሽ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ በከተማው ከሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

"የከተሞች ዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር ለህዳሴአችን" በሚል መሪ ቃል በሚካሔደው የከተሞች ፎረም ላይ ከ200 በላይ የሀገር ውስጥና 40 ያህል የውጪ ሀገር እህት ከተሞች፤የንግድ ኩባንያዎች፤ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከ15ሺ በላይ እንግዶችም እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

Published in ማህበራዊ

ደሴ ሚያዚያ 11/2009 የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደርና የንግድ ዘርፍ ማኅበራት በጋራ ያዘጋጁት አገር አቀፍ የንግድ ትርኢትና ባዛር ተከፈተ፡፡

በኮምቦልቻ ከተማ ትናንት ማምሻውን የተከፈተው  የንግድ ትርኢትና ባዛር " የኮምቦልቻ ስፖርት ትራንስፎርሜሽን" በሚል መሪ ሃሳብ ነው፡፡

የከተማዋ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊና የባዛሩ ሰብሳቢ ወይዘሮ ተሚማ እንድሪስ እንደገለጹት የንግድ ትርኢትና ባዛሩ የኢንዱስትሪ ከተማ የሆነችውን ኮምቦልቻን የበለጠ ለማስተዋወቅ ያግዛል።

አምራች ኢንዱስትሪዎችንና ሸማቹን ማህበረሰብ በቀጥታ  በማገናኘት የገበያ ትስስር ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የንግድ ትርኢትና ባዛሩን የከፈቱት የአማራ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍሰሀ ወልደ ሰንበት ዝግጅቱ አምራቾች ምርታቸውን ለገበያ የሚያቀርቡበት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የመቀሌ ከተማ አስተዳደር መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመንፈስ ቅዱሥ ፍስሃ  በበኩላቸው  በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለውን ወዳጅነትና የእግር ኳስ ቡድኑን ለማጠናከር የከተማዋ አስተዳደር የ200 ሺህ  ብር ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል የኪዳኔ ጋርመንት ባለቤት አቶ ኪዳኔ ከበደ በሰጡት አስተያየት  የንግድ ትርኢትና ባዛሩ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት በተካሄዱ ባዛሮች በመሳተፍ በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስርም ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የውጭ ገበያ ጥያቄ ቀርቦላቸው በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከአዲስ አበባ የመጡትና በጠቅላላ ንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ መሐመድ ይማም  ከዚህ ቀደም በተደረጉት ተመሳሳይ ዝግጅቶች ላይ መሳተፋቸውን ጠቅሰው በዚህም  ምርታቸውን በማስተዋወቅ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እስከ ሚያዚያ 19/2009ዓ.ም  በሚቆየው በዚሁ ዝግጅት ላይ  ከውጭ ከህንድና ከፍሊፒንስ ከሀገር ውስጥ ደግሞ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ከአንድ መቶ በላይ አምራቾች፣ አከፋፋዮችና ነጋዴዎች ተሳትፈዋል፡፡

ከንግድ ትርኢቱና ባዛሩ የመግቢያ ትኬት ሽያጭና ከሌሎች የገቢ ማስገኛዎች ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የሚጠበቅ ሲሆን ገቢውም  የወሎ ኮምቦልቻ እግር ኳስ ቡድንን የገንዘብ  አቅም ማጠናከሪያ ይውላል፡፡

በኮምቦልቻ ከዚህ ቀደም በተደረጉ  ሁለት ተመሳሳይ ዝግጅቶች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱም  ተመልክቷል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 11/2009 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባቀረበው ሪፖርት መሰረት "በየደረጃው በሚገኝ የመንግስት መዋቅር ተጠያቂ በሆኑት አካላት ላይ እርምጃ ይወስዳል" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዛሬ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ባቀረበው የምርመራ ሪፖርት መሰረት በሁከትና ብጥብጡ ወቅት በተለያየ መልኩ የተሳተፉና ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለይቶ አቅርቧል።

በዚህም መሰረት መንግስት "በየደረጃው በሚገኘው የመንግስት መዋቅር ተጠያቂ በሆኑት አካላት ላይ እርምጃ ይወስዳል" ብለዋል።

ይህም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮሚሽኑን ሪፖርት መርምሮ በሚሰጠው የውሳኔ ሓሳብ መሰረት ተግባራዊ እንደሚሆን ገልፀዋል።

ሪፖርቱ በሁሉም ደረጃ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን መለየቱን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስት እርምጃ ለመውሰድ አመቺ መሆኑንም ተናግረዋል።

እስካሁን በርካታ ሰዎች “ተጠያቂ መሆን ጀምረዋል”  ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስት የሚወስደውን ህጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንደገለፁት፤ የኮሚሽኑ ሪፖርት በአገሪቷ የተጠያቂነት ደረጃ እያደገ መምጣቱን ያሳያል። ይሄም በስርዓቱ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ እየጎለበተ መምጣቱን ያረጋግጣል።

ሪፖርቱም የተቋሙን ተአማኒነት እንደሚያሳይ አመልከተዋል።

ኮሚሽኑ ችግሮችን በተሻለ መልኩ እየመረመረ መምጣቱ የጥልቅ ተሃድሶ ውጤት መሆኑንም እንዲሁ።

“ተቋሙ ተዓማኒና ገለልተኛ አይደለም ይባላል?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ “የውጭ ተቋም ቢሆን ከዚህ የዘለለ ሪፖርት አያቀርብም” ብለዋል።

ኮሚሽኑ በክስተቱ ‘የመንግስት አካላት ተጠያቂ ናቸው’ ማለቱን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የውጭ ተቋማትም ቢሆን “ከዚህ የተለየ አይደሉም ነው” ያሉት።

የውጭ አጣሪዎች እንዲገቡ መንግስት ያልፈቀደው የአገር ውስጥ ተቋማትን የማጣራት አቅም ለመፍጠር ታስቦ መሆኑን ገልጸው፤ ይሄ በመደረጉ የሰብዓዊ መብት ጠያቂነት እያደገ መምጣቱን የኮሚሽኑ ሪፖርት በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የጥልቅ ተሃድሶው አንዱ ዓላማ የቁጥጥር ተቋማት እንዲጎለብቱ ማድረግ መሆኑን ገልፀው፤ በሰብአዊ መብት ኮሚሽን የቀረበው ሪፖርት ዓላማው እንደሚሳካ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

የቁጥጥር ተቋማቱ ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የማድረግ ሥራዎችም እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የዴሞክራሲ ስርዓቱን ለማጎልበት ከስቪክ ማህበራት ጋር የተጀመረው ውይይት፣ “በፓርቲዎች የተጀመረው የድርድር እና ሌሎች መድረኮችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው” ያሉት።

ጥልቅ ተሃድሶው በርካታ ለውጦች ያመጣ ቢሆንም አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ባለመድረሱ ጥልቀት እንዲኖረው የማድረግ ሥራዎች እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

Published in ፖለቲካ

ድሬደዋ ሚያዚያ 11/2009 በድሬዳዋ አስተዳደር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡና ለመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት በሆኑ 167 የመንግስት ሠራተኞችና 110 አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ተናገሩ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሒም ዑስማን ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ እርምጃው የተወሰደው ባለፉት ሦስት ወራት ከከፍተኛ አመራር እስከ ሠራተኛው ድረስ በተካሄደው ጥልቅ የተሃድሶ ግምገማ ላይ የተለዩ ችግሮችን መሰረት በማድረግ ነው፡፡

እንደ መንግስት፣ እንደ ድርጅት እንዲሁም በየደረጃው ከሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተካሄደው ጥልቅ የተሃድሶ ውይይት መድረክ ላይ አመራሩ በተሰጠው ሥልጣን ሕዝብን  ከማገልገል ይልቅ ራሱን ሲጠቅም መቆየቱ ተመልክቷል፡፡

የትምክህት፣ የጠባብነት፣ የአካባቢያዊነት፣ የአድርባይነት አልፎ አልፎም የሃይማኖት አክራሪነት ችግሮች ይስተዋሉበት እንደነበር በተሃድሶ መድረኮቹ መለየቱን ከንቲባ ኢብራሒም አስረድተዋል።

ከእነዚህ በተጨማሪ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር ህዝቡን ለከፋ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲዳርጉት መቆየታቸውን በግምገማው ተለይቷል፡፡

በአንዳንድ ተቋማት ሠራተኛውም ለሕዝብ የአገልግሎት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ብልሹ አሠራርና ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሰፍን የራሱ ሚና መጫወቱ በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው መለየቱን ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

በእዚህ በኩል 110 አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱንና ከነዚህም ውስጥ 13 አመራሮች ከስልጣናቸው እንዲነሱ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ሌሎች 22 አመራሮች ከከባድ አስከ ቀላል ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን 31 የቢሮና የሴክተር መስሪያቤት አመራሮች እንዲሸጋሸጉ ተደርጓል።

በተጨማሪም 30 የቀበሌና 14 የገጠር ክላስተር አመራሮች በሚመጥናቸው ሥፍራ እንዲመደቡ መደረጉን ነው የገለጹት።

ከንቲባ ኢብራሒም እንዳሉት፣ አንድ ሶስተኛ በሚሆኑ የአስተዳደሩ አመራሮች ላይ ከተወሰደው እርምጃ በተጨማሪ ሕዝብን ለምሬትና ለመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲዳርጉ የነበሩና በሙስና ተግባራት የተሰማሩ 42 ሠራተኞች ከሥራ እንዲሰናበቱ ተደርጓል፡፡

75 ሠራተኞች ከቀላል እስከ ከባድ የዲሲፒሊን ቅጣት እርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን 29ኙ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሸጋሸጉ ተደርጓል።

በ21 ሠራተኞች ላይ መረጃ የማጥራት ሥራ እየተሰራ መሆኑንና በዘጠኙ ቀበሌዎች ደንብ በማስከበር ሥራ ላይ የተመደቡ ሁሉም በፈጠሩት ከፍተኛ ችግር ውላቸው ተቋርጦ እንዲሰናበቱ መደረጉን አስረድተዋል።

የተወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች መንግስት የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎች ለመፍታት በተቀናጀ መንገድ ያካሄደው የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ የተሻለ ለውጥ ይመጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡    

በአስተዳደሩ ምክር ቤት አዳራሽ  ነዋሪዎች ባካሄዱት የጥልቅ ተሃድሶ ውይይት ማጠቃለያ ላይ የተገኙት ወይዘሮ አሚና አሊ " እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ጥሩ ነው፣ ነገር ግን ህዝቡን ለብሶት የዳረጉ አመራሮችና ሠራተኞች አሁንም አሉ፤ መንግስት እነዚህንም እየተከታተለ መስመር ማስያዝ አለበት" ብለዋል፡፡

አቶ አብዱሸኩር አሰፋ በበኩላቸው መንግስት ያለበትን ችግር ለይቶ ከሕዝብ ለተነሱ የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት የወሰደው እርምጃ ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። 

"እርምጃው ወቅታዊና አስፈላጊ ነው፤ ለሠላም ለልማትና ለብልጽግና አጋዥ በመሆኑ እንደ አስተዳደር የተወሰደው እርምጃ ፈር ቀዳጅና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት›› ብለዋል።

የነዋሪዎቹን አስተያየት አስመልክተው ምላሽ የሰጡት ከንቲባ ኢብራሂም "የተጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ ግቡን እንዲመታ ሕብረተሰቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል፡፡

ህዝቡን ለብሶት የሚዳርጉና በአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንዳለባቸው የተለዩ ቢሮዎችና ሴክተሮች ሥር ነቀል ለውጥ እንዲያመጡ ልዩ ትኩረት ከመሰጠቱ በተጨማሪ በአስተዳደሩ ያሉ መገናኛ ብዙሃንን በማጠናከር ለተጀመረው ለውጥ መሳካት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ የሚሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዚያ11/2009 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች  ድርድሩን የሚመሩ፣ አጀንዳ የሚያደራጁና የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ተግባራትን የሚያከናውኑ የኮሚቴዎች አባላት መረጡ።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በደረሱት ስምምነት መሠረት በዛሬ ውይይታቸው ድርድሩን የሚመሩ ሦስት አባላት መርጠዋል።

በዚህም መሠረት አቶ አሰፋ ኃብተወልድን ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬን ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እንዲሁም አቶ ዓለማየሁ ደነቀን ከአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) ተመርጠዋል።

የተመረጡት አባላት ፓርቲዎቹ ድርድር ሲያካሄዱ ከሰዓት አመዳደብ ጀምሮ ፍትሃዊና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ድርድሩን የመምራት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ዛሬ ኢህአዴግን ጨምሮ 17 ፓርቲዎች ዘጠነኛውን ዙር ውይይት ሲያካሂዱ በተጨማሪነት አጀንዳ የሚያዘጋጁ፣ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ስራ የሚያከናውኑ ሶስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ሰይመዋል።

የኮሚቴ አባላቱ አቶ ገብሩ በርሄ ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኢዴህ)፣ አቶ መላኩ መለሰ ከኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) እንዲሁም አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ ከኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ናቸው።

ኮሚቴው ከነገ ሚያዚያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ከየፓርቲዎቹ የድርድር አጀንዳዎችን የሚሰበስቡ ሲሆን፤ ይህም በ15 ቀን ውስጥ ለፓርቲዎቹ ለድርድር የሚቀርብ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

አጀንዳዎቹ ተሰብስበው ከተደራጁ በኋላ ኮሚቴው ለድርድሩ አመቺ የሆነ ቀን በመወሰን ለየፓርቲዎቹ ቀኑን እንደሚያሳውቅና ድርድሩን እንደሚጀመር ታውቋል። 

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር  የድርድር አሰራር ደንብ ለማውጣት የተካሄዱ ዘጠኝ የውይይት ዙሮች በፓርቲዎቹ ይሁንታ መምራቱ ይታወቃል። ከአሁን በኋላ በሚካሄደው ድርድር ፓርቲዎቹ ከመካከላቸው በመረጧቸው የሚመራ ይሆናል።

 

 

 

 

 

Published in ፖለቲካ

 መቀሌ ሚያዚያ 11/2009 የመሰቦ  ሲሚንቶ ፋብሪካ  የአየር ብክለትን የሚከላከል አዲስ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ማዋሉን አስታወቀ።

 ቀደም ሲል ፋብሪካው በካይ የአፈር ብናኝን ወደ ከባቢ አየር በመልቀቅ በአየር ንብረት ላይ ተፅዕኖ ያስከትል የነበረው አሰራር በአዲስ ቴክኖሎጂ መተካት ችሏል።

 በፋብሪካው የፕሮጀክቶች አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ነጋሽ ትናንት ለኢዜአ እንደገለፁት፣ ፋብሪካው በሰዓት  አምስት ቶን የአፈር ብናኝ  ወደ ከባቢ አየር በመልቀቅ ችግር ሲያስከትል ቆይቷዋል።

 "ብናኙ በአካባቢው በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖሪያ ቤት፣በእንስሳት ግጠሽና መጠጥ ውሀ ላይ እያረፈ ችግር ያስከትል ነበር "ብለዋል፡፡

 ብናኙን  ለመቆጣጠርና መልሶ  ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ ከሁለት ሳምንት በፊት አገልግሎት ላይ ማዋላቸውን አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡

 ቴክኖሎጂው በመስፍን ኢንዳስትሪያል ኢንጂነሪንግና በአንድ የቻይና ተቋራጭ የተሰራ ሲሆን፣፣ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡

 ቴክኖሎጂው ወደ ከባቢ አየር ይለቀው የነበረውን የአፈር ብናኝ አፍኖ ከማስቀረቱ በተጨማሪም መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ ነው፡፡

 አቶ ሳሙኤል እንዳመለከቱት በተጨማሪም ፋብሪካው የስሚንቶ ግብአትን ለማምረት ሲጠቀምበት የነበረውና አከባቢውን የሚረብሽው የደማሚት ፍንዳታ  ድምፅ መቀነስም ተችሏል፡፡

 ፋብሪው ከሚጠቀምበት ንፁህ ውሀ ተጣርቶ ወደ አርሶ አደሮች መንደር ይለቀቅ የነበረው ጨዋማ ውሀም በአንድ ጉድጓድ እንዲጠራቀም በማድረግ ብክለቱን መቆጣጠር መቻሉንም ጠቁመዋል።

 ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች ግን ፋብሪካው የአፈር ብናኙ በመቆጠጣጠሩ የተወሰነ እፎይታ እንዳስገኘላቸው ገልጸዋል፡፡

 በፋብሪካው አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደር አያሌው ሀይሉ "ብናኙ በመኖሪያ ቤት፣በግጦሽና በወራጅ ወንዝ ላይ እያረፈ በሰውና እንስሳት ጤና ላይ ችግር ያደርስብን ነበር "ብለዋል፡፡

 አሁን ፋብሪካው የጀመረው የአፈር ብናኙን የመቆጣጠር ስራ ዘላቂ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡

 ሆኖም ግን የስሚንቶ መጥበሻ ከሚጠቀሙበት የድንጋይ ከሰል በክረምት ወቅት ከፋብሪከው ታጥቦ ወደ ወንዝና ሰብላቸው የሚፈስ በመሆኑ  ውሀውን የመበከልና  ሰብልም የማቃጠል ችግር እያስከተለባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

 አርሶ አደር ካሕሱ አለማየሁ በበኩላቸው፣ፋብሪካው ተራራውን ለማፍረስ ይጠቀሙበት የነበረው የደማሚት ድምፅ አሁን የቀነሰ ቢሆንም አልፎ አልፎ ሌሊት እንደሚረብሻቸውም አመልክተዋል፡፡

 በፋብሪካው የፕሮጀክቶች አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ነጋሽ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ፣ ሲሚንቶ ለመጥበስ የሚጠቀሙበት የከሰል ድንጋይ በሌላ  ለመተካት እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

 ይሄውም  ዘንድሮ 13 በመቶ ያህል የሰሊጥ ተረፈ ምርት ጥቅም ላይ ማዋላቸውን ጠቅሰው፣ በቀጣዩ ዘመንም  ወደ 40 በመቶ ለማድረስ ማቀዳቸውንም ጠቁመዋል፡፡

 በአካባቢው የሚገኙ የሰሊጥና ሌሎች ተረፈ ምርት በመጠቀም የከሰል ድንጋይ የአገልግሎት ድርሻ ዝቅ በማድረግ የህብረተሰቡን ቅሬታ በዘላቂነት ለመፍታት ጥረቱ  ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅሰዋል፡፡

 የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከመቀሌ ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኝ ነው፡፡

ሶዶ ሚያዚያ 11/2009 የ24ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ በሜዳው ሀዋሳ ከነማን የገጠመው ወላይታ ዲቻ አንድ ለዜሮ አሸነፈ።

የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ የተጨመረው ደቂቃ ሊያልቅ የዳኛ ፉሽካ በሚጠበቅበት ጊዜ 13 ቁጥሩ ዳግም በቀለ የወላይታ ዲቻዎችን ጎል አስቆጥሯል።

በመጀመሪያዉ የጨዋታ ክፍሌ ጊዜ  ኳስ  አደራጅቶ በመጫወት ሜዳዉን በመቆጣጠርና ወደ ጎል የቀረቡ ሙከራዎችን በማድረግ የሃዋሳ ከነማ ቡድን የተሻለ ነበር።

ወላይታ ዲቻዎች ያገኙትን ኳስ ወደ ተቃራኒው ቡድን ሜዳ በማድረስ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ኢላማቸውን የጠበቁ ባለመሆናቸዉ ወደ ጎልነት ሳይቀየሩ እስከ 47ኛ ደቂቃ ሊጠብቁ ግድ ብሏቸው ነበር።

በሁለተኛዉ የጨዋታ ክፍሌ ጊዜ ባለሜዳዎች ተጭነዉ በመጫወት ሜዳውን ቢቆጣጠሩም ተጨማሪ ጎል ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል፡፡

ሃዋሳዎች በሁለተኛው አጋማሽ ተጫዋቾችን ቀይረው በማስገባት ወደ ጨዋታው ለመመለስና ልዩነቱን ለማጥበብ ቢሞክሩም በተጋጣሚያቸው ተበልጠው አምሽተዋል፡፡

በርካታ ደጋፊ በስታዲየሙ ተገኝቶ ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ ቡድኑን ሲያበረታታና ሲደግፍ ነበር።

የሃዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ “የልጆቼ ያለመረጋጋት ያገኙትን አጋጣሚ ወደ ጎል ለመቀየር ያለመቻላችንና የሜዳው አለመመቸት የሽንፈታችን ምክንያት ነው” ብለዋል፡፡

“በመጀመሪያዉ ክፍለ ጊዜ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሞክረናል በሁለተኛዉ ግን መድገም አልቻልንም ድቻ የተሻለ ነበር ማሸነፍ ይገባቸዋል” ሲሉ ለተጋጣሚያቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

የደጋፊውን የድጋፍ አሰጣጥና ስነ-ምግባር ያደነቁት አሰልጣኝ ውበቱ የፍጹም ቅጣት ይገባን ነበር ሲሉ በዳኝነቱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ተናግረዋል፡፡

የወላይታ ዲቻ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በበኩላቸው ቡድናቸው በማሸነፉ መደሰታቸውን ገልጸው “ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም ብንችል የጎል ልዩነቱ ሊሰፋ ይችል ነበር” ብለዋል፡፡

ተጋጣሚያችን ጥሩ ኳስ  ፍልስፍና የሚከተል በመሆኑ እስከ መጨረሻው ድረስ በማስጨነቅና አጥቅቶ ለመጫወት መግባታቸውን የተናገሩት አሰልጣኙ ከምንም በላይ በጨዋታው ሙሉ ነጥብ ይዘው መውጣታቸው አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

 

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሚያዚያ11/2009 ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር መስክ እያከናወናቸው ያለውን ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠየቀ።

የምክር ቤቱ የከፍተኛ ትምህርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲን የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጦ ግብረ መልስ ሰጥቷል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ዩኒቨርሲቲው ያከናወናቸውን ሥራዎች ቋሚ ኮሚቴው አበረታች ሲል ገልጾታል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ እያሱ ወርቅነህ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የተቀላጠፈ የተማሪዎች ቅበላና ምዝገባ በማከናወን ትምህርት በወቅቱ እንዲጀመር ያደረገረው ጥረት በአዎንታ የሚታይ ነው።

ዩኒቨርስቲው ከዓመት ዓመት የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥን ለመቀነስ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ለውጥ እያመጣ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የዩኒቨርሲቲው ምሩቃን ወደ አምራች ዘርፍ እንዲገቡ ለማድረግ ከፋብሪካዎች ጋር ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስርን ለማጎልበት የጀመረው ሥራ አበረታች እንደሆነም ምክትል ሰብሳቢው አስረድተዋል።

በአንፃሩ በአስተዳደራዊ ቦታዎች የሴት አመራሮችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ ወጥነት ያለው የግዢ ሥርዓት መዘርጋትና በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ የሚያስተምሩ መምህራንን ቁጥር በማሳደግ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ በቋሚ ኮሚቴው የተሰጠው ግብረ መልስ ለቀጣይ የዩኒቨርስቲው ሥራ የሚጠቅም በመሆኑ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

በየደረጃው ከሚገኙ የተማሪዎችና መምህራን አደረጃጀቶች ጋር ውይይቶች በማድረግ የመማር ማስተማሩ የተቀላጠፈ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በተለያዩ የትምህርት መስኮች 39 ሺህ 927 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ በዚሁ ጊዜ ተገልጿል።

Published in ማህበራዊ

አሶሳ ሚያዚያ 11/2009 የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ወደ ክልሉ ሰርገው የገቡ ፀረ ሠላም ኃይሎችን አድኖ በመያዝና አሳልፎ በመስጠት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ሰጠ።

በአሶሳ ከተማ ትናንት በተካሄደው የእውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን እንደገለፁት ሠላምና የህዝብ ደህንነት በተረጋገጠበት ባለፉት 25 ዓመታት ፈጣን እድገት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

በዚህም " የሰላምን ውድ ዋጋ ከኛ በላይ ሊረዳና ሊያስረዳ የሚችል አካል የለም" ብለዋል፡፡

የሀገሪቱ ልማትና እድገት እረፍት የሚነሳቸው የውስጥና የውጭ ፀረ ሠላም ኃይሎች ነውጥና ብጥብጥ በመፍጠር የህዳሴውን ጉዞ ለማሰናከል ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም፡፡

አመቺ ጊዜና ወቅት እየጠበቁ የሽብር ተግባራቸውን ለመፈፀም የሚያደርጉት ሙከራ በፀጥታ ኃይሎች ጥምረትና በህዝብ ተሳትፎ እየከሸፈ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል፡፡

የክልሉን ሠላም ለማናጋትና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ጥቃት ለማድረስ በተያዘው ዓመት የገቡትን እራሱን የቤንሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን) ብሎ የሚጠራው ቡድን አባላት መደምሰስ መቻሉን አስታውሰዋል።

የፀረ ሠላም ኃይሎችን ለመደምሰስ በተደረገው ትግል ከፀጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ የትግል አጋርነታቸውን ላረጋገጡ የየአካባቢው ነዋሪዎች ላቅ ያለ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል፡፡

"ከክልሉ ጋር በስፋት የሚዋሰነው የሱዳን ብሉ ናይል ግዛት መከላከያ ሠራዊት አባላትና ህዝብ በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን አድኖ በመያዝና አሳልፎ በመስጠት ወንድማዊ አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል "ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የ12ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዲየር ጀነራል ብርሃኑ ጥላሁን በበኩላቸው  ፀረ-ሠላም ኃይሎችን ለመደምሰስ የተደረገው ትግል የአንድ አካል ብቻ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡

" በየደረጃው ያለ አመራር ልማት ሲያመጣና መልካም አስተዳደር ሲያሰፍን ህዝቡ ያለው አመኔታ ስለሚያድግ እንኳን ሽፍታ ንፋስ አይገባም " በማለት የመስተዳድር አካላት ከህዝቡ ጋር በቅርበት መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል

የክልሉ የፀጥታ አካላት ፣ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በመቀናጀት ፀረ-ሠላም ኃይሎች መደምሰሳቸውን የገለጹት ደግሞ የክልሉ የፀረ ሽምቅ፣ ልዩ ጥበቃና አድማ ብተና ዋና መምሪያ ኃላፊ  ኮማንደር ፈረደ ቦጂ ናቸው፡፡

በቅርቡ በተደረገው ግዳጅ በየአካባቢው የሚኖረው ህዝብ መረጃ በመስጠትና ፀረ ሠላም ኃይሎች የሚገኙበትን በመጠቆም ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ 82 የክልልና የፌደራል ተቋማት እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን የላቀ አስተዋጽኦ ለነበራቸው  የክልሉ የፀጥታ አባላት ከገንዘብ ስጦታ እስከ ማዕረግ እድገት የደረሰ እውቅና ተሰጥቷል።

 

Published in ፖለቲካ

ጋምቤላ ሚያዚያ 11/2009 በጋምቤላ ክልል አበቦ ወረዳ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማራው የሳውዲ ስታር የእርሻ ኩባንያ የአሌሮ ግድብን በመጠቀም ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ በበኩሉ ኩባንያው የጀመረው ዘመናዊ የመስኖ ግብርና ልማት ለአካባቢው አርሶአደሮች ትልቅ ልምድና ተሞክሮ የሚሰጥ መሆኑን አስታውቋል ።

በኩባንያው የአበቦ እርሻ ልማት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በድሉ አበራ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዝናብ መቆራረጥ የሚታየውን የምርት መቀነስ ችግር ለማቃልል ኩባንያው የመስኖ ልማትን በስፋት ለመጠቀም እየተንቀሳቀሰ ነው።

"በአሁኑ ወቅትም የአሌሮ ግድብን በመጠቀም ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ በመስኖ ሩዝ ለማልማት የ32 ኪሎ ሜትር የውሃ መተላለፊያ ቦይ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ ነው " ብለዋል ።

በሚቀጥለው ዓመት የውሃ ቋቶችና የውሀ መተላለፊያ ቦይ ግንባታ በማጠናቀቅ ኩባንያው የተረከበውን 10 ሺህ ሄክታር መሬት ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማት ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ነው ስራ አስኪያጁ የገለጹት።

ከዚሁ ጎን ለጎን በተያዘው የበጋ ወራት ወንዙን በመጥለፍ ከአንድ ሺህ 500 ሄከታር በላይ መሬት በሩዝ ሰብል መሸፈኑን ጠቅሰዋል ።

እንደ አቶ በድሉ ገለጻ በመጪው የመኸር ወቅት በዝናብና በመስኖ በመታገዝ ልማቱን ወደ ስድስት ሺህ ሄክታር ለማስፋት የማሳ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ነው ።

" ኩባንያው እያካሄደ ያለውን  ዘመናዊ የመስኖ ግብርና በአካባቢው ማህበረሰብ እንዲለመድ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል አቶ በደሉ።

የከልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ  ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡብ " ኩባንያው የጀመረው ዘመናዊ የመስኖ ግብርና ለአካባቢው አርሶ አደሮች ትልቅ ልምድና ተሞክሮ ይሰጣል" ሲሉ ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ በተለይም በክልሉ ያለውን ሰፊ የውሃ ሀብት በመጠቀም በጋ ከክረምት በማምረት የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋገጥ የመስኖ ልማትን የማስፋት ሥራ ተጠናከሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በኩባንያው የግብርና ልማት ባለሙያ ወጣት ዲው ማርያል በሰጠው አስተያየት በኮሌጅ ቆይታው ያላገኛቸውን አዳዲስ እውቀቶችና ልምዶች በኩባንያው እያዳበረ መሆኑን ተናግሯል።

"ድርጅቱ በአካባቢው በግብርና ልማት በመሰማራቱ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከመሆኔም በላይ ሙያዬን በማጎልበትና በማሻሻል ተጠቃሚ ሆኛለሁ " ያለው ደግሞ ወጣት ለገሰ ላፒሶ ነው።

" ስቀጠር የትራክተር ኦፕሬተር ነበርኩ፤ በሂደት ወደ ዶዘር፣ ከእዚያም ወደ ኮምባይነርና ስካባተር ኦፕሬተርነት ተሸጋግሬያለሁ።" ብሏል።

ከዚህ ቀደም ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንዲያለማ በመንግስት ተገንብቶ የነበረው የአሌሮ ግድብ ከሁለት አስርት ዓመት በላይ ለተፈለገው ዓላማ ሳይውል ቆይቷል።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው በክልሉ የተለያዩ ወንዞችን በመጠቀም ከ780 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት ይቻላል፡፡

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን