አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Tuesday, 18 April 2017

ነቀምቴ ሚያዝያ 10/2009 የነቀምቴ ከተማ የስራ እድል ፈጠራና የከተማ ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ባለፉት ስምንት ወራት በመደበኛ መርሃ ግብር ከአንድ ሺህ 800 ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል ማመቻቸቱን ገለጸ።

ከተማዋ ምክትል ከንቲባና የኤጀንሲው ሃላፊ አቶ አለማየሁ ደረሰ እንዳሉት የስራ እድሉ የተመቻቸው በ563 ማህበራት ለተደራጁ ወጣቶች ነው።

ከስራ እድሉ ተጠቃሚ ወጣቶች መካከል 829 ከዩኒቨርስቲ እንዲሁም ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ሰልጥነው የተመረቁ ይገኙበታል።

ወጣቶቹ የተሰማሩባቸው መስኮች አነስተኛ ንግድ፣ የከተማ ግብርና፣አገልግሎትና ማኒፋክቸሪንግ ሲሆን ለስራቸው መንቀሳቀሻም ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር እንዲያገኙ ተደርጓል።

በተጨማሪ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት አንድ ሺህ 700 ወጣቶችን በ338 ማህበራት በማደራጀት ስራ ውስጥ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ምክትል ከንቲባው እንዳሉት ወጣቶቹ  ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ በገበያ ትስስር፣በንግድና ሂሳብ መዝገብ አያያዝ እንዲሁም በስራ አመራር ዙሪያ  ስልጠና እየተሰጣቸው ይገኛል።

ስልጠናቸውን እንዳጠናቀቁ በቅርቡ ከፌዴራልና ከክልል መንግስታት የተመደበ ከ94 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኤጀንሲው እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ 6 ሺህ 500 ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት አቅዶ እየሰራ ነው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ 10/2009 ካናዳ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል በካናዳ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ተጠሪ ሚስተር ኦማር አልግሃብራ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በካናዳ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ተጠሪ ሚስተር ኦማር አልግሃብራ የተመራ ልኡካን ቡድንን በቢሯቸው ተቀብለው ዛሬ አነጋግረዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ፍሊፕ ቤከር እንደገለጹት፤ ልኡካን ቡድኑ አገሮች ካሁን በፊት የነበራቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ በካናዳ የልማት መርሃ ግብር ድጋፍ ከሚደረግላቸው አገሮች አንዷ መሆኑዋን ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ የልዑካን ቡድኑ መሪ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን አብራርተዋል።

ሁለቱ አገሮች ከልማት ትብብር በተጨማሪ የፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በሚጠናከሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን የተናገሩት ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ተበጀ በረሄ ናቸው።

በተለይም ሁለቱ አገሮች የፌዴራሊዝም ስርዓት የሚመሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ “በዘርፉ ልምድ የሚለዋወጡበትን ሁኔታዎች ለማጠናከር መክረዋል” ብለዋል።

በኢትዮጵያ በኃይልና ማዕድን ዘርፍ የሚታዩ የአቅም ውስንነትን ለመፍታት ካናዳ የምታደርገውን ትብብር በምትቀጥልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን አመልክተው፤ በንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ያላቸውን ግንኙነትም በሚያጠናክሩበት ስልት ላይም መምከራቸውን ዳይሬክተር ጄኔራሉ ገልፀዋል።

ካናዳ ለኢትዮጵያ በአቅም ግንባታ፣ በግብርና፣ በማዕድንና ሃይል ዘርፍና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚውል ድጋፍ ከምታደርግባቸው ዘርፎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ካናዳ በየዓመቱ ለኢትዮጵያ ልማት የሚውል ከአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ እንደምታደርግ ታውቋል።

Published in ፖለቲካ

ደብረ ማርቆስ ሚያዝያ 10/2009 በምስራቅ ጎጃም ዞን  በገጠር መሬት ጉዳይ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ፡፡ 

የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በኮንፍረንሱ ላይ እንዳሉት የገጠር መጠቀሚያ መሬቶችን ፍትሃዊ  የሆነ አሰራር በማስፈንና ህጋዊነትን በማረጋገጥ  የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቷል።

ለዚህም የነበሩ ክፍተቶችን ነቅሶ በማውጣት ከቀበሌ መሬት አስተዳደር ጀምሮ እስከላይኛው መዋቅር ድረስ ሁሉም ሀላፊነቱ እንዲወጣ  የየራሱን ድርሻ እንዲወስድ  ይደረጋል። 

ወደ ህግ ከሚቀርቡት ጉዳዮች ከ80በመቶ በላይ ከመሬት ጋር የተያያዙ ክሶች መሆናቸውን ያመለከቱት አስተዳዳሪው ይህም በፍትህ ዘርፉ ትኩረት የሚሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዙሪያ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የዞኑ መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም መምሪያ ሀላፊ አቶ ዳንኤል ደሳለኝ በበኩላቸው ዘመናዊ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት በመዘርጋቱ አርሶአደሩ በመሬቱ ላይ ዘላቂነት ያለው ዋስትና እንዲያገኝ ማስቻሉን  ገልጸዋል፡፡

" ነገር ግን መሬት ነክ ቅሬታዎች፣ አቤቱታዎች ከጊዜ ጊዜ እየተበራከቱ ለግጭት  መንስኤ እንዳይሆኑ ተከታታይ ስራ መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።

የኮንፈረንሱ ዓላማም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳትና  የጋራ አቅጣጫ በማስቀመጥ በቀጣይ መሰል ችግሮች እንይኖሩ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት አጋር አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ መነሳሳትን ለመፍጠር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የወል መሬት ወራራን፣ የአቅመ ደካሞች መሬት አለአግባብ  የመነጠቅና  የሀሰት ምስክር በዘርፉ በስፋት የሚታዩ ክፍተቶች መሆናቸውን በኮንፍረንሱ ላይ ተነስቷል፡፡

የፍትህ አካላት የሚቀርብላቸውን መረጃዎች ደጋግመው አለማጣራት፣ ፖሊስም ከመሬት አስተዳደር ጋር ተናቦ አለመስራት እንዲሁም አንዳንድ የዘርፉ  ባለሙያዎች በጥቅማጥቅም ሀላፊነታቸውን ያለመወጣት  ችግሮች እንዳሉም ተመልክቷል።

በዞኑ እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር  የተወጣጡ ከ560በላይ  የፍትህ አካላት ፣ የሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ እንዲሁም የመሬት አጠቃቀም  ባለሙያዎች በኮንፍረንሱ ተሳትፈዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ባህርዳር ሚያዝያ 10/2009 በአማራ ክልል አባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር ከ16 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ 22 ታላላቅ ኢንዱስትሪዎችን ሊገነባ መሆኑን የክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የቢሮው ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት በክልሉ ልማት የኢንዱስትሪውን ድርሻ ለማሻሻል የሚያስችል እቅድ ተይዞ እየተተገበረ ይገኛል።

በግል ባለሃበቱና በመንግስት የልማት ድርጅቶች ትብብር ባለፈው ዓመት የተቋቋመው የአባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር በክልሉ ያለውን ጥሬ እቃ የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችን በጥናት ለይቶ ለመግባት እንቅስቃሴ ጀምሯል።

"የፋብሪካዎችን ግንባታ ለመጀመር ከሚያስፈለግው አጠቃላይ ወጪ በአክሲዮን ማህበሩ መሸፈን ካለበት አራት ቢሊዮን ብር ውስጥ ከሦስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚበልጠው የተፈረመና ቃል የተገባ ሲሆን አንድ ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል" ብለዋል።

ገንዘቡ የተሰበሰበውም 516 የልማት ድርጅቶችና ባለሃበቶች ከገዙት አክሲዮን ሲሆን አሁንም ያልተሸጡ ቀሪ ሰባት ሺህ 490 አክሲዮኖች በመኖራቸው ባለሃብቶች ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ቀሪው 75 በመቶ የግንባታዎቹ ወጪ በባንክ ብድር የሚሸፈን መሆኑን ጠቁመው"በአሁኑ ወቅትም ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚገነቡ ሰባት ኢንዱስትሪዎችን የመሰረት ድንጋይ ለማሰቀመጥ ዝግጅት ተደርጓል"ብለዋል

በቀዳሚነት ወደ አፈፃፀም ከሚገቡት ኢንዱስተሪዎች ውስጥም በደጀን የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ በባህር ዳር የብረታ ብረት ፋብሪካ፣ በጎንደር ቴክስታይልና ጋርመንት እንዲሁም በደብረ ታቦር፣ ወልዲያ፣ ደሴና ደብረ ብርሃን የእንጨት ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪአካዎች ይገኙበታል

እነዚሁ ፋብሪካዎች እስከ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ መጨረሻ ግንባታቸው ተጠናቆ ማምረት ይጀምራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ተስፋዬ ገልፀዋል።

ኢንዱስትሪዎቹ በክልሉ ያለውን እምቅ ጥሬ እቃ በመጠቀም፣ የስራ እድል በመፍጠር፣ በኢንዱስትሪ ምርት ውጤቶች ያለውን የገበያ እጥረትና የዋጋ ውድነት ለማረጋጋት ታልሞ የሚከናወኑ ሲሆን ሌሎች ፋብሪካዎች በቀጣይ የሚገነቡ ናቸው።

"በተቻለ መጠን ከዚህ በፊት በሃገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን የሚደግሙ ሳይሆን የተሻለ ጥራትና ተመራጭነት ያላቸውና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ "ይደረጋሉ ብለዋል።

በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ሸሽተው የነበሩ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ባለሃብቶችን የመመለስና በፕሮጀክቱ የማሳተፍ ጥረት እየተደገ እንደሚገኝም ሃላፊው አስታውቀዋል።

"ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ለሚገነቡት ኢንዱስትሪዎች ከመጭው ሃሙስ ጀምሮ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስራ የሚከናወን ሲሆን ፕሮጀክቶቹ ማምረት ሲጀምሩም ከአምስት ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ይፈጥራሉ "ብለዋል።

የአባይ ኢንዱስትሪያል ልማት አክሲዮን ማህበር የተቀመጠለትን ግብ በመምታት የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ ባለሃብቱ አክሲዮኖችን በመግዛት በየደረጃው የሚገኘው አመራር ደግሞ በመሸጥ ግንባር ቀደም ሊሆኑ እንደሚገባ አቶ ተስፋዬ አሳስበዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ጎንደር ሚያዝያ 10/2009 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግምታቸው ከስድስት ሚሊዮን ብር የሚበልጥ የህክምና አልጋዎችና   ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶችን በሰሜን ጎንደር ለሚገኙ አምስት  ሆስፒታሎች ሰጠ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ ድጋፉን በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት የእርዳታው ዋና አላማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችን  አቅም  በማሳደግ  በዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ ላይ የሚደርሰውን ጫና መቀነስ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ለሆስፒታሎቹ ያደረገውን የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ያገኘው ስዊድን ሀገር ከሚገኘው "ሂውማና ብሪጅ" ከተባለ አለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አኒሳ በፈቃዱ በበኩላቸው ድጋፍ የተደረገላቸው በመተማ፣ በደባርቅ፣ በጭልጋ፣ በደንቢያና  ወገራ ወረዳዎች የሚገኙ ሁለት ነባርና ሶስት አዳዲስ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ናቸው።

ለሆስፒታሎቹየተሰጡት131 የህሙማን አልጋዎች፣ 54 ወንበሮች፣ 126 ፍራሾች፣  ስድስት ዊልቸሮችና 68  ጠረጴዛዎች  ከጅቡቲ  ወደብ  ለማስገባት ዩኒቨርሲቲውከ365ሺህ ብር በላይ ማውጣቱን ጠቁመዋል።

"ሂውማን ብሪጅ ኢትዮጵያ" ከተባለው አለም አቀፍ በጎአድረጊ ድርጅት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት በቀጣይም ሆስፒታሎቹ  ተመሳሳይ  የህክምና  ቁሳቁስ  ድጋፍ የሚያገኙበት  ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል፡፡

የመተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ታጀበ ዘየደ በተለይ የህሙማን አልጋዎቹ ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

"በወር እስከ 200 የሚደርሱ ህሙማን በሆስፒታላችን ይስተናገዳሉ "ያሉት ደግሞ የአይከል የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኘው ለውጤ ናቸው፡፡

ሆስፒታሉ በቂ የህሙማን አልጋ ስለሌለው ተኝተው የሚታከሙ ሰዎች በወረፋ ይንገላቱ እንደነበረ ገልጸው አሁን የተደረገላቸው ድጋፍ አገልግሎታቸውን እንዲያሻሽሉ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።

ድጋፉ በቀን ከአንድ ሺህ 500 በላይ ታካሚዎችን ከዞኑ ሆስፒታሎች ለሚቀበለው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስራ ጫና መቃለል እገዛ እንደሚያደርግ ተመልክቷል።

Published in ማህበራዊ

ሀረር ሚያዝያ 10/2009 በሐረር ከተማ የሚገኘው የጀጎል ሆስፒታል ከበጎ ፈቃደኛ የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር የአጥንት በሽታ ላለባቸው ከአራት መቶ በላይ ዜጎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሰጠ።                 

በአካባቢያቸው የነጻ ሕክምና አገልግሎት በማግኘታቸው በጤናቸው ላይ ለውጥ ማየታቸውን ተጠቃሚዎቹ ገልጸዋል።      

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር አቶ ያሲር ዮኒስ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ ሆስፒታሉ ነጻ የሕክምና አገልግሎቱን የሰጠው ከሚያዚያ 2 ቀን  ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት ነው።   

የነጻ ሕክምናውን ያገኙት በተፈጥሮና በአደጋ ምክንያት የአጥንት ጉዳት ደርሶባቸው በአቅም ማነስ ምክንያት ለረጅም ዓመታት መታከም ሳይችሉ የቆዩ ሕሙማን ናቸው።

ለአንድ ሳምንት በተሰጠው ነጻ የጤና አገልግሎትም በሕመሙ እየተሰቃዩ የነበሩ 476 የሐረርና የአጎራባች ክልል ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

አቶ ያሲር እንዳሉት በሆስፒታሉ በተሰጠው ነጻ የአጥንት ሕክምና 416 ዜጎች የመድኃኒትና መርፌ አነስተኛ የሕክምና አገልግሎት ሲያገኙ የከፋ ጉዳት ያለባቸው 60 ሕሙማን ደግሞ ከፍተኛ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተሰጥቷቸዋል።

በሕክምና አገልግሎቱ የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስት  ዶክተር ኤልያስ አህመድን ጨምሮ ከአዲስ አበባ ስድስት ከፍተኛ የአጥንት ህክምና ባለሙያዎች አስፈላጊውን የሕክምና ቁሳቁስ በመያዝ ተሳትፈዋል።

ከእነሱ በተጨማሪ የክልሉ መንግስት 11 ተጨማሪ ከፍተኛና ረዳት የሕክምና ባለሙያዎችን በመመደብ ተጎጂዎቹ አስፈላጊውን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን አቶ ያሲር ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአጥንት ሕክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ኤልያስ አህመድ በበኩላቸው፣ የሕክምና አገልግሎቱን ወደ አዲስ አበባ ሄደው መታከም ለማይችሉ አቅመ ደካማ ዜጎች መሰጠቱን ገልጸዋል።

በሆስፒታሉ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወነው ነጻ የአጥንት ሕክምና የዘንድሮውን ጨምሮ ከአንድ ሺህ 200 በላይ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውንና ለሕሙማኑ አነስተኛና ከፍተኛ የቀዶ ሕክምና መሰጠቱን አስረድተዋል።

የሕክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የሐረር ከተማ ቀበሌ 03 ነዋሪ አቶ ሰለሐዲን ቶፊቅ እንደተናገሩት ከሦስት ዓመት በፊት በደረሰባቸው ድንገተኛ የትራፊክ አደጋ የግራ እግራቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

"በወቅቱ የተሻለ ሕክምና አላገኘሁም ነበር፤ በሌላ ጊዜ ቆይቼ ስታከምም በአጥንቴ ውስጥ ብረት ስለገባ ሁል ጊዜ ህመም ይሰማኝ ነበር።" ብለዋል።

አሁን ባገኙት ነጻ የሕክምና አገልግሎት ብረቱ በቀዶ ሕክምና ወጥቶላቸው ምንም ዓይነት ሕመም እየተሰማቸው እንዳልሆነና ለተደረገላቸው የሕክምና ድጋፍም ምስጋናቸው የላቀ መሆኑን አስረድተዋል።

"ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ወድቄ ከደረሰብኝ የአጥንት ስብራት ለመዳን ብዙ ጊዜ ሕክምና ባደርግም ሊሻለኝ አልቻለም ነበር" ያሉት ደግሞ የሸንኮር ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ቦጋላች አባተ ናቸው።

በከተማው ወደሚገኙ የሕክምና መስጪያ ተቋማት ደጋግመው መሄዳቸውንና ወደ አዲስ አበባ ሄደው እንዲታከሙ የተገለጸላቸው ከመሆኑ ውጪ መፍትሄ እንዳላገኙ ገልጸዋል።

"አቅመ ደካማ በመሆኔ ወደአዲስ አባበ ሳልሄድ ከሕመሜ ጋር ሰነበትኩ" ያሉት ወይዘሮ ቦጋለች፣ በተሰጣቸው ነጻ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በጤናቸው ላይ ለውጥ እያዩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዶክተር ኤልያስ አህመድ የሚመራው የሕክምና ቡድን በሆስፒታሉ ለሦስት ዓመታት በሰጠው ነጻ የሕክምና አገልግሎት ከአንድ ሺህ 200 በላይ አቅመ ደካማ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል።   

Published in ማህበራዊ

አዳማ ሚያዝያ 10/2009 የሕብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት በቴክኖሎጂ እና በጥናትና ምርምር የልህቀት ማዕከላትን ከፍቶ እየሰራ መሆኑን የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።

ዩኒቨርሲቲው ለአዳማ ከተማ እድገት ገንቢ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በሳይንስና ቴክኖሎጂ አገሪቷ ያለባትን የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የሕብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚፈቱ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ዩኒቨርሲቲው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከከፈታቸው ስምንት የቴክኖሎጂ፣ የጥናትና ምርምር የልህቀት ማዕከላት መካከል የሲሚንቶ፣ የኬሚካል፣ የብረታ ብረት፣ የማኑፋክቸሪንግና የህዋ ምርምር ማዕከላት ይገኙበታል።

ከእዚህ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው በ10 ክልላዊና ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ጥናትና ምርምር ከማድረግ ባለፈ የማማከር አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ልምድ እያጎለበተ መምጣቱን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፣ በመለስተኛና  አነስተኛ አንቀሳቀሾች የፈጠራ ችሎታ፣ የቴክኖሎጂ መቅዳት፣ ማላመድና ማስተዋወቅ ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመለየት በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ያካሄደውን ጥናት በቅርቡ ለክልሉ መንግስት እንደሚያስረክብ ገልጸዋል።።

በማሕበረሰብ አገልግሎት ዙሪያ በተለይ ትውልዱ በስነ ምግባር የታነጸ እንዲሆን ከማድረግ አንጻር በአዳማ ከተማና ምስራቅ ሸዋ ዞን የሚገኙ የወጣቶች ማዕከላትን በቁሳቁስና በገንዘብ እያጠናከረ መሆኑን አስረድተዋል።

ከተማዋን በየጊዜው እያስቸገረ ካለው የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ከመስተዳድሩ ጋር በመቀናጀት የወራጅ ውሃ መቀልበሻ ቦዮችን መገንባቱን ገልጸዋል።

ከእዚህ ጎን ለጎን የከተማዋን ማስተር ፕላን በአዲስ መልክ ለማሻሻል በተደረገው ጥረት ሙያተኞችን በማሳተፍ የበኩሉን ድጋፍ ማድረጉን ነው የገለጹት።

ከአዳማ ከተማ አስተዳደር ቦታ በመረከብ ለአካባቢው ሥራ አጥ ወጣቶች የመሸጫና የማምረቻ ማዕከላትን ገንብቶ ማስረከቡንም ዶክተር ለሚ ገልጸዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የከተማዋንም ሆነ የአካባቢውን ሕብረተሰብ ለመደገፍ በማህበረሰብ አገልግሎት ዙሪያ እየሰራ ያለውን በጎ ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

"በከተማዋ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የሚስተዋሉ ችግሮችንና አስተዳደሩ ያልደረሰባቸውን መስኮች በመለየት የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ነው" ብለዋል።

በዘንድሮ ዓመት ብቻ የወራጅ ውሃ መቀልበሻ ቦዮችንና ለመለስተኛና አነስተኛ ተቋማት የመሸጫና ማምራቻ ማዕከላት ገንብቶ ማስረከቡንም ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ ተናግረዋል።

አዲሱ የከተማዋ ማስተር ፕላን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማሻሻል በተደረገው ጥረትም ተቋሙ  ሙያተኞችን በማሳተፍ ወሳኝ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል።

የሕብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲጎለብትም በአገልግሎት፣ በኢንዱስትሪ ትስስር፣ በመለስተኛና አነስተኛ ተቋማት፣ በጥናትና ምርምር ዙሪያ የዩኒቨርሲቲው ተባብሮ የመስራት ባህል እየዳበረ መምጣቱን አስረድተዋል ።

የአካባቢውን ሕብረተሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት በቁሳቁስ፣ በአይነትና በገንዘብ የሚያደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የምርምር ቢሮ ዲን ዶክተር አለሙ ዲሳሳ ናቸው።

በመልካም አስተዳደር፣ በሙስና፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ስርፀት ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችና ምርምሮች በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

የአዳማ ከተማ የወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊና የከተማው እግር ኳስ ቡድን ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ ቱሉ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለክለቡ የአስር ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ድጋፉ ቡድኑ በአገር አቀፍ ደረጃ የያዘውን ውጤት አስጠብቆ ለመቆየትና ለተሻለ ውጤት እንዲሰራ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን  አመልክተዋል።

የገንዘብ ድጋፉ ለአምስት ዓመት መሆኑን የጠቆሙት አቶ አለማየሁ፣ ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ብር ለቡድኑ እንደሚለቅ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ለከተማዋ አራት የወጣት ማዕከላት አገልግሎት የሚውል የጀነሬተርና ሌሎች ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው ከከተማው መስተዳድር ጋር በመተባበር ከተራራው የሚወርደውን ጎርፍ ጉዳት እንዳያስከትል ለማድረግ ቱቦ በመገንባቱ ከስጋት ነጻ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 10/2009 የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት የሚፈለገውን ውጤት አለማምጣቱን አንድ ጥናት አመለከተ።

ጥናቱ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ስርዓተ ትምህርት እንዲከለስ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "በትምህርት ተቋማት የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ግንባታና ዴሞክራሲያዊነት፣ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች" በሚል ርዕስ የተካሄደ ጥናት ዛሬ ውይይት ተደርጎበታል።

የጥናትና ምርምር ማዕከሉ ባካሄደው ጥናት ግኝት መሰረት "ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ሲሰጥ የቆየው የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት በአመራር ድክመት የሚጠበቅውን ውጤት አላስገኘም"።

የትምህርት ዘርፉ የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር መምራት አለመቻሉን ነው ጥናቱ ያመለከተው።

በቀረበው ጥናት መሰረት የመማሪያ መፅሐፉ ይዘት የተደጋገመ መሆን፣ አቀራረቡ ከዓላማው ጋር መቃረኑ እና የትምህርቱ መርሀ ግብር የሚመራበት በቂ አደረጃጀትና አሰራር አለመኖሩ በቁልፍ ችግርነት ተጠቅሷል።

የተማሪዎችን ስነ ምግባር ለመከታተል የሚያስችል አሰራርና አደረጃጀት እስካሁን አለመዘርጋቱን ጥናቱ ይፋ አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪ የስነ ምግባር ትምህርትን ጉዳይ የመምህራን ኃላፊነት ብቻ አድርጎ መቁጠር፣ በመምህራን፣ በተማሪዎችና ወላጆች መካከል ያለው ግንኙነትም መላላት ተገልጿል።

የስነ ዜጋና ስነ ምግባር አስተማሪዎች የብቃትና የአቀጣጠር ችግር መኖሩም በጥናቱ ላይ ተጠቁሟል። ትምህርቱን ለሚሰጡ መምህራን ከፍተኛ ትኩረት መስጠትና ማብቃት እንደሚያስፈልግም ነው የተመለከተው።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይ ፀሀየ፤ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት የሚፈለገውን ውጤት ያለማምጣት ቁልፍ ችግር የአመራሩ ድክመት መሆኑን ነው የገለጹት-ዋናውን ችግር መፍታት ያለበት አመራሩ መሆኑን በመጠቆም።

አቶ በረከት ስምዖንም  ችግሩ የአመራር ውድቀት መሆኑን ገልፀው፤ "የማስተካከል ፈጣን እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል" ብለዋል።

"መምህሩ ለለውጥ የተዘጋጀ ኃይል ነው" ያሉት አቶ በረከት፤ እሰካሁን ለውጥ ያልመጣው የአመራር ሁኔታው ችግር ስላለበት መሆኑን አመልክተዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም በሰጡት አስተያየት፤ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ ያስፈልጋል።

የመገናኛ ብዙሃን እና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተሳትፎ ደካማ መሆኑ በጥናቱ ውስጥ መገለፁን ያደነቁት ዶክተር ሂሩት፤ "አሁን ያላቸውን ሚና ለማሳደግ መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው፤ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ስርዓተ ትምህርትን በማሻሻል "በሚቀጥለው ዓመት ወደ ተግባር" እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደገለጹት፤ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት 'በአመራር ድክመት የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም' የሚለው የጥናቱ ውጤት ተቀባይነት አለው።

ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የተቀናጀ ስራ ባለመሰራቱ የሚፈለገው ውጤት ያለመምጣቱን ነው ያረጋገጡት።

በጥናቱ የቀረበው ችግር በስነ ዜጋና ስነ ምግባር የታየ ችግር ብቻ ሳይሆን በትምህርት ጥራት ላይም ችግር እየፈጠረ መሆኑን ነው የገለጹት።

በጥናቱ የቀረቡ ችግሮችን በመያዝ "መፍትሔ የመስጠት ሥራ መሰራት አለበት ነው" ያሉት።

ጥናቱ የሸፈናቸው አካባቢዎች የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ብሄር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ሶማሌ ክልሎች እና አዲስ አበባ አስተዳደር ናቸው።

የጥናትና ምርምር ማዕከሉ ላለፉት ሦስት ዓመታት ባካሄደው እንቅስቃሴ በተለያዩ ዘርፎች ወደ 14 የሚጠጉ ጥናቶችን አካሂዷል።

Published in ማህበራዊ

ባህርዳር ሚያዝያ 10/2009 የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በፍርድ ቤት ቀርበው መከራከር ለማይችሉ  የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድሮ ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የነፃ የህግ ድጋፍ አደረገ።

በዩኒቨርስቲው የነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ምክትል አስተባባሪ መምህር ደሳለኝ ጥጋቡ እንደገለጹት ተቋሙ ድጋፉን ያደረገው ለዚሁ ተግባር ተብለው በተቋቋሙ 6 ማዕከላት ነው።

በገንዘብ እጥረት ምክንያት ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት ቀርበው የመከራከር አቅም የሌላቸው 312  ህፃናት፣ ሴቶች፣አረጋውያን፣ጎዳና ተዳዳሪዎችና መሰል የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፉን እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ከተደረገው ድጋፍ መካከል  የህግ ምክር አገልገሎት፣ ክስ መመስረት፣ መልስ ፣አቤቱታና ይግባኝ መፃፍ፣ ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እስከ ሰበር ድረስ ጉዳዩን በጥብቅና ይዞ በመከራከር መብቶቻቸውን የማስጠበቅ ስራ ይገኝበታል፡፡

ቀርበው ክርክር የተደረገባቸውም የባልና ሚስት ፍች፣ የልጆች ቀለብ፣ የሃብት ክፍፍል፣ የውርስ፣ አሰሪና ሰራተኛ የመሳሰሉት ጉዳዮችም ናቸው፡፡

የአገልግሎት ድጋፍ  የተሰጠውም በህግ መምህራንና የተሻለ ውጤት ባላቸው ተማሪዎች አማካኝነት እንደሆነም አስተባባሪው ጠቅሰዋል።

የነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎቱ መሰጠቱም ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በገንዘብ እጥራት ምክንያት የተጠቃሚነት መብቶቻቸው እንዳይጣስ አግዟል፡፡

አስተባባሪው እንዳመለከቱት አገልግሎቱን በማስፋፋት ተመሳሳይ ችግር ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ለማዳረስ የነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ክፍሉን በሰው ሃይል  የማጠናከር ስራ እየተካሂደ ነው፡፡

ድጋፉን ከሚሰጡት መካከል የአምስተኛው ዓመት የህግ ተማሪ አቦበከር አብረን  "የሰዎች መብት አለአግባብ  ሲጣስ መመልከት ህሊናን እረፍት ይነሳል በተለይም የህግ ሰው ስትሆን ደግሞ ነገሩን ድርብርብ ያደርግብሃል" ብሏል።

የህግ  ድጋፉን ከሶስተኛ  ዓመት ጀምሮ እየሰጠ እንደሚገኝና በዚህም የብዙ ችግረኛ ሰዎችን መብት በህግ ፊት ተከራክሮ ማስጠበቅ እንደቻለም  ተናግሯል።

የነፃ አገልግሎት መስጠት በመቻሏ የንድፈ ሃሳብ ትምህርቱን በተግባር በመደገፍ የተሻለ ልምድና የህግ እውቀት ማግኘት እንዳስቻላት የተናገረችው ደግሞ በዩኒቨርስቲው  የአምስተኛው ዓመት የህግ ተማሪ የምስራች በላይ ናት።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት ውስጥም የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አባዲት ወላይ  በሰጡት አስተያየት የባለቤታቸውን ጡረታ ባለመብትነት እንዲከበርላቸው በዩኒቨርስቲው ነፃ የህግ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልጸዋል፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ባለፈው በጀት ዓመትም ከ800 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የነፃ የህግ ድጋፍ መስጠቱም ተመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 10/2009 ኢትዮጵያና ስፔን በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በስፔን አቻቸው ሚስተር ኢልዴፎንሶ ካስትሮ የተመራውን የልዑካን ቡድን በፅህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አቶ መለስ ዓለም አገሮቹ በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ነው የተናገሩት።

በንግድ፣ ኢንቨስትመትና ቱሪዝም ማስፋፋት መስክ ሁለቱ አገሮች ተባብረው ለመስራት የጋራ መስማማት ላይ ደርሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ለልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችና እድሎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የስፔን ባለሃብቶችም በኢትዮጵያ ባሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችና እድሎች እንዲጠቀሙ ወይዘሮ ሂሩት ለስፔኑ አቻቸው መግለጻቸውን አቶ መለስ ተናግረዋል።

የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሚስተር ኢልዴፎንሶ ካስትሮ አገራቱ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳይ ላይ መወያያታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት የሚሆን የህግ ማዕቀፍና የተመቻቸ ሁኔታ እንዳላት ገልጸው ስፔን ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የልማት እርዳታ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

አቶ መለስ ዓለም እንዳሉት አገራቱ በዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳይ ላይም ተወያይተዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ አገራቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ መግለጻቸውንም ነው አቶ መለስ ያብራሩት።

ኢትዮጵያና ስፔን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1951 ነው።

የስፔን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በመንገድ ግንባታ፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች መዋዕለ-ነዋያቸውን በማፍሰስ ላይ ይገኛሉ።

አገሪቱ በትምህርት፣ በጤና፣ በስነ-ቅሪት ምርምር እና በሌሎችም መስኮች የልማት ትብብርና እርዳታ ለኢትዮጵያ ታደርጋለች።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን