አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 17 April 2017

ጊምቢ ሚያዚያ  9/2009 በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማ የጎርፍ መከላከያን ጨምሮ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ገለጸ፡፡

 የማዘጋጃ ቤቱ  ስራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ በንቲ ለኢዜአ እንደገለጹት ስራዎቹ የተጀመሩት በተመደበ 15 ሚሊዮን ብር በጀት በዘንድሮ ዓመት የተለያዩ ጊዜያት ውስጥ ነው፡፡

 ከስራዎቹ መካከል 13 ኪሎ ሜትር የከተማው ውስጥ ለውስጥ ጠጠር መንገድ እና  ሁለት ኪሎ ሜትር  የድንጋይ ንጣፍ  እንዲሁም  የመንገድ ዳር መብራትና የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች ይገኙበታል።

 "ከከተማው ወጣ ገባ  የመሬት አቀማመጥ ጋር ተያይዞ በየጊዜው የሚያጋጥመውን የመሬት መንሸራተትና ከፍተኛ የጎርፍ አደጋን ለመቋቋም የእርከን ስራና  የውሃ መቀልበሻ ቦዮች ግንባታ እየተካሄደ ነው "ብለዋል ።

 የመሰረተ ልማት ስራዎቹ የሚካሄዱት በክልሉ መንግስት ድጋፍ ፣ በማዘጋጃ ቤት ገቢ፣  በህብረተሰቡ የገንዘብና የጉልበት አስተዋፅኦ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

 በእቅዳቸው መሰረት ስራቸው እየተፋጠነ ያለው እነዚህ የልማት ስራዎች በዓመቱ መጨረሻ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁም ተመልክቷል፡፡

 ከነዋሪዎቹ መካከል ወጣት አማዩ ቦሩ በሰጠው አስተያየት በውሃ መውረጃ ቦዮች ግንባታና በድንጋይ ማንጠፍ ልማት ላይ ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

 የመሰረተ ልማቱ ለከተማው እድገት ካላቸው ፋይዳ አንፃር ክረምት ከመግባቱ በፊት እንዲጠናቀቁ በገንዘብና በጉልበት የሚያበረክቱትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት ደግሞ አቶ ክፍሉ ሞሲሳ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው፡፡

 በከተማው የዜሮ አራት ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ መልካም አሰፋ በበኩላቸው ከዚህ በፊት መንገድ ባለመኖሩ በተለይ ነፍሰጡር እናቶችን ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

 አሁን በግንባታ ላይ ያለው መንገድ ችግራቸውን እንደሚፈታው ተስፋ  እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል፡፡

 የከተማውን እድገት ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ  ሚያዚያ 9/2009 በባህላዊ የወርቅ ምርት ስራ ውስጥ የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት ስጋት እንደፈጠረበት የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ።

 በሌላ በኩል 21 አዳዲስ  የወርቅ መገኛ ቦታዎች በጥናት በመለየታቸው ለባህላዊ ወርቅ አምራቾች ለመሥጠት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ገልጿል።

 የኮንትሮባንድ ንግድ በመስፋፋቱ ባለፉት ስምንት ወራት ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ ከሚገባቸው 6 ሺህ 638 ኪሎ ግራም ወርቅ ውስጥ 1 ሺህ 517 ኪሎ ግራም ብቻ መግባቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

 በዚህም 61 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብቻ ገቢ መገኘቱ ነው የተገለጸው።

 በሚኒስቴሩ የገበያ ልማት ትስስርና ትንበያ ዳይሬክተር አቶ ተወልደብርሃን አባይ እንደገለጹት በባህላዊ መንገድ ከታቀደው በላይ ወርቅ ተመርቷል፡፡

 ነገር ግን ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው የዕቅዱ 30 በመቶ ብቻ በመሆኑ የኮንትሮባንድ ንግድ በአሳሳቢ ደረጃ ለመስፋፋቱ ማሳያ ነው ብለዋል።

 በአሁኑ ወቅት በህገ-ወጥ ንግድ የተሰማሩ አካላት ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች ግብይት በመፈፀምና የውጭ ምንዛሪ ማግኛና ሃብትን ወደ ውጭ የማሸሽያ መንገድ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው።

 በአዲስ አበባም እንዲሁ ወርቅ ቤቶች ከባህላዊ አምራቾች በህገ-ወጥ መንገድ ግብይት በማካሄድ ወደ ውጭ የሚልኩበት ሁኔታ እያደገ በመምጣቱ ወደ ባንኩ የሚገባው የወርቅ ክምችት እንዲያንስ አድርጓል ብለዋል።

 የኮንትሮባንድ ንግድ ከተለመደው የጠረፋማ የአገሪቱ ከተሞች ከመስፋፋቱ ባለፈ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ በአየር መንገድ በኩል ወደ ውጭ የማውጣት ሙከራ እየታየ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

 ይሕን ሕገ-ወጥ የወርቅ ንግድ ለመቀነስና አምራቾቹን ለማበረታታት ብሔራዊ ባንክ ከዓለም የወርቅ ዋጋ የአምስት በመቶ ጭማሪ በማድረግ እየገዛ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

 የኮንትሮባንድ ንግዱን ለመከላከል ከፌደራል እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ያለውን አመራር፣ የፀጥታና የጉምሩክ አካላት የቅንጅት ስራ የሚጠይቅ መሆኑን ነው የገለጹት።

 የኮንትሮባንድ ንግዱን ለመከላከልና የሀገር ልማት ማነቆነቱን ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ፈጥሮ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የንቅናቄ መድረኮች ማዘጋጀት መጀመሩንም ነው ያብራሩት።

 በሌላ በኩል ባህላዊ የወርቅ አምራቾቹ የመፍጪያ/ክሬሸር/፣ ማበጠሪያና ማጠቢያ መሳሪያዎችን በማቅረብ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል አቶ ተወልደብርሃን።

 የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ  የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታምሩ መርሻ እንዳሉት በ2008 ዓ/ም በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በ18 ሺህ ስኩየር ካሬ ሜትር የወርቅ መገኛ ቦታዎች ላይ የጂኦ-ኬሚስትሪ፣ ጂኦ-ፊዚክስና ጂኦሎጂ ጥናት ተካሒዷል።

 በጥናቱ ላይ በአሁኑ ወቅት ሰባት የባለሙያዎች ቡድን ወደ መስክ ተሰማርቶ የዳሰሳ ጥናት እያካሄደ ይገኛል።

 ቡድኑ በዚሁ የዳሰሳ ጥናት 21 የወርቅ መገኛ ቦታዎችን በማካለል ለባህላዊ አምራቾች አስረክቦ እንደሚመለስ ነው የተናገሩት።

 የደለል ወርቅ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚገኝ በመሆኑ በእነዚህ አካባቢዎች ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

 ሰርቬዩ በቀሪው በጀት ዓመት ከሚከልላቸው 31 የማዕድን መገኛ ቦታዎች ውስጥ 21ዱ የወርቅ መገኛዎች እንደሚሆኑም ነው ያስረዱት።

Published in ኢኮኖሚ

አምቦ ሚያዚያ 9/2009 መንግስት ባመቻቸው የከተሞች የምግብ ዋስትና ልማት ፕሮግራም  ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች አመለከቱ።

 የ27 ዓመት ዕድሜ ያላት  ወጣት ብርሀኔ ያደሳ በልጅነቷ  ወላጆቿን አጥታ ያደገችው የተለያዩ  የህይወት ውጣ ውረዶችን በማለፍ ነው፡፡

 አሁን የሶስት ልጆች እናት መሆኗን የገለጸችው ወጣት  ብርሀኔ  የመስሪያ ቦታም ሆነ ገንዘብ  ስለሌላት ህፃናቱን ለማሳደግ በልመና ላይ መሰማራቷን ተናግራለች፡፡

 መንግስት የከተማ  የምግብ ዋስትና ልማት ፕሮግራም ተግባራዊ እንደሚያደርግ  ሰምታ ሰርቶ ለመለወጥና ልጆቿን  ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ አድርጋ በመውሰድ ተስፋ ሰንቃ ነበር፡፡

 "ፕሮግራሙ ስራ ላይ ቢውል እኔም ሆንኩኝ  ልጆቼን  ከልመናና ከጎዳና ህይወት እንድንወጣና ህይወታችን ሊለውጠው ስለሚችል በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን እፈልጋለሁ” ብላለች፡፡ 

 ሌላው የከተማው ነዋሪና የአካል ጉዳተኛ  የሆኑት አቶ ቀና ሞጋሳ በበኩላቸው " በዊልቸር እየተንቀሳቀስኩኝ ሊስትሮ እንድሰራ ወንበርና የመስሪያ ቦታ እንዲሰጠኝ ያቀረብኩት ጥያቄ ሰሚ በማጣቱ አማራጭ በማጣት ወደ ልመና ገብቻለሁ "ብለዋል ።

 አቶ ቀና እንዳመለቱት መንግስት ያመቻቸው የከተማ የምግብ ዋስትና ልማት ፕሮግራም  የመስሪያ ቦታና የመንቀሳቀሻ ገንዝብ ድጋፍ እንደሚያደረግ   ከሰሙ ወዲህ ከልመና ህይወት እወጣለሁ ብለው ተስፋ አድርገው ነበር።

 የ65 ዓመት እድሜ ያላቸው  ወይዘሮ  አስናቀች አዱኛ አይናቸው ታመው ሰርተው ራሳቸውን ለመርዳት  በማይችሉበት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል ።

 መንግስት ባመቻቸው እድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተስፋ ቢያደርጉም  ፕሮግራሙ በሩቁ ከሚሰሙት ውጪ ተግባራዊ ባለመሆኑ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡

 የአምቦ ከተማ የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ኦብሳ ኢንሰርሙ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ  ነዋሪዎቹ ያነሱት ቅሬታ ትክክል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 የደሃ ደሃ  የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀረፀው ፕሮግራም ተግባራዊ ሳይሆን መዘግየቱን ጠቁመው የበጀት አለመመደብ ፣ የአሰራር  አቅጣጫ  አለመቀመጡ፣  ቀድመው ወደ ትግበራ የገቡት የጅማና የአዳማ  ከተሞች ተሞክሮ ተቀምሮ አለመድረሱ ለመዘግየቱ በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡

 የከተማው አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ፍጹም አበበ በበኩላቸው የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎችን  የመለየት ስራ አጠናቀው ከክልል በጀቱ  እንደተለቀቀ ስራው  እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዳማ ሚያዚያ  9/2009  በአዳማ ከተማ ሁለት ባለሃብቶች  የፋሲካን በዓል አስመልክተው 173 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ ከ1ሺህ 500  ለሚበልጡ ችግረኞች ትናንት ድጋፍ አደረጉ፡፡

 የኪያ የምግብ ኮምፕሌክስ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤሊያስ ማስረሻና የኤፊ ኮነስትራክሽን ድርጅት ባለቤት አቶ ኤርሚያስ አሰፋ የተባሉት ባለሀብቶቹ ድጋፉን ያደረጉት በገንዘቡ ምሳ አዘጋጅተው በመጋበዝ ነው፡፡

 ባለሃብቶቹ አራት ሰንጋዎችን በማረድ የምሳ ግብዥውን  ያደረጉት ለጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለአቅመ ደካሞችና  ለአካል ጉዳተኞች መሆኑ በስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

 የከተማው አስተዳደር ድግሱን በማስተባበርና በማስተናገድ ሌሎች የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችም የታሸገ የመጠጥ ውሃና ለበዓሉ ድምቀት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች በማቅረብ  ተሳትፈዋል ።

 የአዳማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ጁንዲ ዓሊይ በወቅቱ እንደተናገሩት ዘንድሮ በከተማው ተግባራዊ በሆነው የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር   በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል ።

 በመንግስት ከሚካሄደው መርሀ ግብር በተጨማሪ ባለሃብቶች አቅመ ደካሞችን በመርዳት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸውም  ጠቁመዋል፡፡

 በአዳማ ከተማ በርካታ ባለሀብቶች እንዳሉ ያመለከቱት  ስራ አስኪያጁ "የሁለቱ በጎ አሳቢዎች  አርአያነት ሌሎችም ሊከተሉት ይገባል "ብለዋል፡፡

በግብዥው ከተሳተፉ አቅመ ደካሞች መካከል  ወይዘሮ ጥሩወርቅ መኩሪያ በሰጡት አስተያየት "ጧሪ የሌለኝ ቢሆንም   ወገኖቼ አስበው ባዘጋጁት ድግስ ተደስቻለሁ " ብለዋል ።

 በከተማው የቀበሌ 14 ነዋሪና የእድሜ ባለፀጋ አቶ ተሾመ መኩሪያ በበኩላቸው በዓሉን በደስታ ማሳለፍ እንዲችሉ ያሰቧቸውን  ባለሃብቶች አመስግነዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  ሚያዚያ  9/2009 በትንሳኤ በዓል ዋዜማና የበዓሉ ዕለት ወንጀል ሳይፈጸም በዓሉ በሰላም ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ።

 በተመሳሳይ በዋዜማውና በበዓሉ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ አለመድረሱን የከተማዋ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን አስታውቋል።

 የፖሊስ ኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለኢዜአ እንደገለጹት "የኮሚሽኑ አባላት ከህብረተሰቡ ጋር ባደረጉት እንቅስቃሴ ምንም አይነት ወንጀል ሳይፈጸም በዓሉ በሰላም ተከብሯል"።

 አባላቱን በተለያዩ ስፍራዎች በማሰማራትና ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎችና ከመዲናዋ ነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት ኮሚሽኑ የሰራው ስራ ውጤታማ እንደነበር ገልጸዋል።

 ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት ለኮሚሽኑ ጥቆማ በማድረግ ላሳየው ትብብርም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 የፖሊስ ኮሚሽኑ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ በበኩላቸው በበዓሉ ዕለት በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች ሁለት ከባድና አንድ ቀላል የአካል ጉዳቶች መድረሳቸውን ተናግረዋል።

 ከባድ የአካል ጉዳት የተመዘገበው በአቃቂ ቃሊቲ እና የካ ክፍለከተሞች ሲሆን ቀላል የአካል ጉዳቱ የደረሰው በአዲስ ከተማ ክፍለከተማ ነው።

 በበዓሉ ዋዜማ ሁለት የሞት፣ ሁለት ከባድ የአካል ጉዳትና 27 የንብረት አደጋ በድምሩ 31 አደጋዎች መድረሳቸውንም ጠቁመዋል።

 የሞት አደጋዎቹ የደረሱት ኮተቤ መምህራን ኮሌጅና ቦሌ አንበሳ ጋራዥ አካባቢ መሆኑን ነው ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ የገለጹት።

 አሁንም አሽከርካሪዎችና ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ አሳስበዋል።

 በዋዜማውና በበዓሉ ዕለት ምንም የእሳት አደጋ አለመድረሱን የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን ገልጿል።

 የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ባለፈው ዓመት የትንሳኤ በዓል ሁለት ሰዎች መሞታቸውን አስታውሰው በዘንድሮው በዓል ግን ምንም አይነት አደጋ አለመከሰቱን ተናግረዋል።

 የትንሳኤን በዓል ጨምሮ በዘንድሮው ዓመት በተከበሩ ኃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት ምንም አይነት የእሳት አደጋ አለመድረሱንም እንዲሁ።

 ህብረተሰቡ በባለስልጣኑ የሚተላለፉትን የቅድመ ጥንቃቄ መልዕክቶች ተግባራዊ ማድረጉ አደጋ እንዳይከሰት ወሳኝ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።

 አደጋ እንዳይከሰት ላደረገው ጥንቃቄም ምስጋናቸውን አቅርበው ህብረተሰቡ በበዓሉ ወቅት ያደረገውን ጥንቃቄ በቀሪ ጊዜያትም አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

Published in ማህበራዊ

 አዲስ አበባ ሚያዚያ 9/2009 አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በስፔን ሳባዴል በሁለት ሺህ ሜትር ያስመዘገበችው አዲስ ክበረ-ወሰን በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ጸደቀ።

 የክብረ-ወሰኑን መጽደቅ ተከትሎ አትሌት ገንዘቤ የክብረወሰኖቿን ቁጥር ስድስት አድርሳለች።

 ገንዘቤ ጥር 30 ቀን 2009 ዓም በስፔን ሳባዴል ከተማ በተደረገው የሁለት ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር አዲስ ክብረ-ወሰን በማስመዝገብ ማሸነፏ ይታወሳል።

 ርቀቱን 5 ደቂቃ 23 ሰከንድ 75 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመግባት ነበር ክብረወሰኑን የሰበረችው።

 ገንዘቤ የሰበረችው አዲስ ክብረ-ወሰን በስሟ መመዝገቡን ነው ዛሬ የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ይፋ ያደረገው።

 አትሌት ገንዘቤ በስሟ ያስመዘገበችው የ2 ሺህ ሜትር የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር ከ22 ዓመት በፊት በአየርላዳዊቷ አትሌት ሶኒያ ኦ ሱሊቫን 5 ደቂቃ ከ25 ሰከንድ 36 ማይክሮ ሰከንድ ተይዞ የነበረ ነው።

 አትሌት ገንዘቤ ክብረ-ወሰን ስታስመዘግብ ይህ ለስድስተኛ ጊዜ ሲሆን፤ ከስድስቱ አምስቱ በቤት ውስጥ ውድድር የተመዘገቡ ናቸው።

 አትሌቷ አዲስ ክብረ-ወሰን ካስመዘገበችባቸው ውድድሮች መካከል በ2015 ሞናኮ ላይ 1 ሺህ 500  ሜትር አንዱ ነው።  

 ሌሎች አምስቱ ደግሞ ዛሬ የፀደቀውን 2 ሺህ ሜትር ጨምሮ፤ 1 ሺህ 500 ሜትር፣ 3 ሺህ ሜትር፣  5 ሺህ ሜትር፣ የአንድ እና የሁለት ማይል የቤት ውስጥ ውድድር ርቀቶች ናቸው።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሚያዚያ 9/2009 ሁለተኛው ዓመታዊ የምሥራቅ አፍሪካ የሲሚንቶ፣ የኮንክሪትና የኃይል ጉባዔ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው።

 ጉባዔው ከሁለት ቀናት በኋላ በመዲናዋ በተባበሩት መንግሥታት የጉባዔ አዳራሽ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

 ጉባዔው አገራት ልምድ የሚለዋወጡበት፤ የቀጣናውን የሲሚንቶ፣ የኮንክሪትና የኃይል ኢንዱስትሪ ልማትን ለመደገፍ የሚጠቀሙበት መድረክ ይሆናል ነው የተባለው።

 

Published in ኢኮኖሚ

ነቀምቴ   ሚያዚያ 9/2009 በምስራቅ ወለጋ ዞን በዘንድሮ የመኸር አዝመራ 13 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ የእርሻ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

የዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዘውዴ መኮንን እንዳስታወቁት፣ በዘንድሮ የመኽር አዝመራ 405 ሺህ 93 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን እየተሰራ ነው።

በእርሻ ሥራውም የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም 13 ሚሊዮን 275 ሺህ ኩንታል የሚበልጥ  ምርት ለማግኘት መታቀዱን ነው የገለጹት።

 እስካሁንም ለ252 ሺህ 857 አርሶአደሮች በአዳዲስ የግብርና አሰራሮችና በቴክኖሎጂ አጠቃም ዙሪያ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

ስልጠናው አሲዳማ መሬትን በኖራ የማከም ፣ መሬትን ደጋግሞ ማረስና መለስለስ ስለሚሰጠው ጠቀሜታ፣ በመስመር የመዝራትና የፀረ አረምና ፀረ ተባይ መድኃኒቶች አጠቃቀምና የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አመጣጠን ያካተተ መሆኑን አቶ ዘውዴ አመልክተዋል።

አቶ ዘውዴ እንዳሉት፣ በዞኑ በ2008/2009 የምርት ዘመን የተገኘውን 11 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በመጪው የመኽር አዝመራ በሁለት ሚሊዮን ኩንታል የማሳደግ ግብ ተቀምጦ ወደ ማሳ ዝግጅት ሥራ ተገብቷል።

 በዞኑ በዲጋ ወረዳ የለሊሳ ዲምቱ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ግርማ ኢታና በሰጡት አስተያየት፣ በየደረጃው በሚገኙ የግብርና ባለ ሙያዎች በንድፈ ሀሳብና በተግባር ተደግፎ በሚሰጣቸው ሥልጠና ከተለመደው የግብርና አሰራር በመውጣት ዘመናዊ የግብርና አሰራር ለመጠቀም የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

 ከእዚሁ ቀበሌ አርሶአደር መርጋ ኢረቲ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ምክር በመጠቀም ባለፈው ዓመት ከአገልግሎት ውጭ የነበረውን ሩብ ሄክታር አሲዳማ መሬታቸውን በኖራ በማከም ዘንድሮ ታርሶና ለስልሶ ለዘር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

 በጅማ አርጆ ወረዳ የሂኔ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ኦላና ቶላሳ በሰጡት አስተያየት ደግሞ ቀደም ሲል ማዳበሪያን የሚጠቀሙት በግምት እንደነበር አስታውሰው፣ በሥልጠናው ለአንድ ሄክታር መሬት ምን ያህልና ምን ዓይነት ማዳበሪያ መጠቀም እንዳለባቸው ግንዛቤ መጨበጣቸውን ተናግረዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ማይጨው ሚያዚያ 9/2009 በትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው ከተማ በ264 ሚሊዮን ብር የተጀመረው የራያ  ዩኒቨርሲቲ የአንደኛው ምዕራፍ ግንባታ ከ76 በመቶ በላይ ተጠናቀቀ።

ዩኒቨርሲቲው በመጪው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ  1 ሺህ 500 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት እያደረገ ነው ።

 የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፈሰር ታደሰ ደጄኔ ለኢዜአ እንደገለፁት በሰኔ ወር 2008ዓ.ም. የተጀመረው የአንደኛው ምዕራፍ ግንባታ   የተማሪዎች  መኝታ ፣  የመመገቢያ፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ የቤተ-መጻሐፍት፣ የቤተ ሙከራና ሌሎችንም አገልግሎት መስጫዎችን ያካተተ ነው፡፡

 በመጪው ዓመት መግቢያ ላይ ለአገልግሎት ለማብቃት ግንባታው  እየተፋጠነ ሲሆን ስራው እስካሁንም ከ76 በመቶ በላይ ተጠናቋል፡፡

 በኢሁኑ ወቅትም የመጻሐፍት፣ የቤተ ሙከራና ለመማር ማስተማሩ ስራ የሚያገለግሉ  ቀሳቁሶች  ግዥ በመካሄድ ላይ ነው።

 ከዚሁ ጎን ለጎን የ45 መምህራን ቅጥር  እየተፈፀመ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

 በተያዘው የበጀት ዓመት   በተመደበ 364 ሚሊዮን ብር በጀትም የሌሎች 25 ህንፃዎች ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር አመላክተዋል ።

 "በህንፃ ግንባታ ስራው ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ጊዚያዊ የስራ እድል ተፈጥሯል" ብለዋል ።

 ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ መሃመድ ጀማል በሰጡት አስተያየት የዩኒቨርሲቲው መገንባት የአካባቢውን እድገት ለማፋጠን የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወጣት አሸናፊ ሐጎስ በበኩሉ ከሌሎች ጋደኞቹ ጋር በመደራጀት በብድር ባገኙት ግማሽ ሚሊዮን ብር ካፒታል ለግንባታ የሚውል ቁሳቁስ በማምረት  ለዩኒቨርሲቲው እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

 ዩኒቨርሲቲው በመጪው ዓመት በመጀመሪያ ዲግሪ መርሀ ግብር 1ሺህ 500 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱም ተመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

ሚዛን ሚያዚያ 9/2009 በቤንች ማጂ ዞን የተከሰተ ተምች 4 ሺህ 760 ሄክታር ላይ በነበረ የበቆሎ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡  

የመምሪያው ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ አስተባባሪ ወይዘሮ ደስታ ግርማዬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ ተምቹ  ለመጀመሪያ ጊዜ በዞኑ የታየው መጋቢት 6 ቀን 2009 ዓ.ም ሸዋ ቤንች ወረዳ ኩካ ቀበሌ ውስጥ ነው።

በአሁኑ ወቅት የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በዞኑ አስር ወረዳዎች በመሚገኙ በ221 ቀበሌዎች ላይ መዛመቱን አመልክተዋል።

ተምቹ ከ12 ሺህ የሚበልጡ አርሶአደሮች ማሳ ላይ በ4 ሺህ 760 ሄክታር መሬት የነበረ የበቆሎ ሰብልን ማጥፋቱን ጠቅሰዋል ።

የተምቹን ስርጭት ለመከላከል በ2 ሺህ 868  ሄክታር መሬት ላይ 5 ሺህ 764 ሊትር ጸረ -ተባይ መድኃኒት መረጨቱንም ተናግረዋል ።

"ተምቹን ለመከላከል ርብርብ እየተደረገ ቢሆንም ተምቹ በአንድ ጊዜ  እስከ 2ሺህ 500 እንቁላል በመጣል በፍጥነት የሚራባ መሆኑ በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎታል " ብለዋል ።

አርሶአደሩ በማሳው ላይ ክትትል በማድረግ ተምቹን በባህላዊ መንገድ በመግደል ጉዳቱን ለመቀነስ የራሱን ጥረት እንዲያደርግ መደረጉንም ወይዘሮ ደስታ ጠቅሰዋል ።

በደቡብ ቤንች ወረዳ የፋኒቃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ካህሱ አብርሃ በሩብ ሄክታር ማሳቸው ላይ ቀድመው የዘሩት የበቆሎ ሰብል ተምቹ  ባደረሰበት ጉዳት መጥፋቱን ጠቁመዋል ።

የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ጸጋዬ ተክለእግዚአብሄር  በበኩላቸው፣ ተምቹ በአካባቢያቸው ከተከሰተበት ቀን ጀምሮ የብዙ አርሶአደሮች ማሳ ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡

"ተምቹ ቀደም ሲል የዘራሁትን በቆሎ አውድሞብኛል፣ አዲስ በዘራሁት ማሳ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ክትትል እያደረኩ ነው’’ ብለዋል፡፡

"ከዚህ ቀደም በአካባቢያችን እንደዚህ ሰብልን በፍጥነት የሚያጠፋ ተባይ ተከስቶ አያውቅም፤ ይህ የመጀመሪያ ነው" ያሉት ደግሞ በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የሸሸቃ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ባስክን ወሽከራ ናቸው፡፡

በዞኑ የተከሰተው ተምች ፉል አርሚ የተሰኘ መጠሪያ ያለውና ያልተለመደ ዝርያ   መሆኑ  ነው፡፡

Published in አካባቢ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን