አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 16 April 2017

ሚያዝያ 8/2009 አሜሪካ አልሸባብን ለማጥቃትሚያስችል ወታደራዊ ስልጠና ለሶማሊያ ወታደሮች ልትሰጥ መሆኑ ተነገረ፡፡ 

የአሜሪካ ወታደሮች ስልጠናውን የሚሰጡት  በሱማሊያ ተሰማርተው ለሚገኙት የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ሀይላት ጭምር ነው፡፡ 

ስልጠናውን ለመስጠት በርከት ያሉ የአሜሪካ ብሄራዊ ሰራዊት አባላት ወደስፍራው ማቅናታቸውንና ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሰራዊት አሜሪካ በስፍራው ስታሰማራ የመጀመሪያው መሆኑም ተጠቁማል፡፡

አሜሪካ በተጨማሪም በሶማሊያ ለሚገኘው የደህንነት ሀይል እርዳታና ድጋፍ እንደምታደርግ መገለጹን  የዘገበው አልጀዚራ ነው፡፡

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 8/2009 የሕንድ ኤምባሲ ያዘጋጀውና ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው የክሪኬት ስፖርት ውድድር ፍጻሜውን አገኘ።

የክሪኬት ስፖርት ውድድር ዋነኛ ዓላማ ስፖርቱን በኢትዮጵያ ለማስተዋወቅና የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከር መሆኑም ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ቦሌ የማህበረሰብ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ሲካሄድ በቆየው በዚህ ውድድር በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሕንዳዊያን ተሳትፈዋል።

በፍጻሜ ጨዋታውም በአዲግራት ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩ ሕንዳዊያን መምህራንና የህንድ ኤምባሲ ሰራተኞች ለዋንጫ ተፎካክረዋል።

በውድድሩም የአዲግራት ዩኒቨርስቲ መምህራን በማሸነፍ ዋንጫውን ወስደዋል።

የዚህ ውድድር ኮሚቴ አባል ሀራሽ ኩታሬ እንደተናገረው፤ ውድድሩ መካሄዱ በኢትዮጵያ የክሪኬት ስፖርትን ለመጀመር በር ይከፍታል።

በዚህ ዓመት በውድድሩ የተካፈሉት በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሕንዳዊያን ሲሆኑ፤ በቀጣይ ዓመት “ኢትዮጵያዊያንም ይሳተፈሉ” ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።

ውድድሩ ባለፈው ዓርብ ተጀምሮ ዛሬ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ቀን በርካታ የአዲስ አበባ ወጣቶች  ጨዋታውን ለመከታተል ታድመው ነበር።

የሕንድ ኤምባሲ የክሪኬት ስፖርት ውድድር ኢትዮጵያ ውስጥ ሲያዘጋጅ የመጀመሪያው ነው።

Published in ስፖርት

ሚያዝያ 8/2009 በቱርክ ዛሬ ለሚካሄዱት ህዝበ ውሳኔ 55 ሚሊዮን ቱርካዊያን ድምፅ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ህዝበ ውሳኔው የፕሬዘዳንት ሬሲፕ ጣሂር ኤርዶጋንን ስልጣን የሚጨምር አልያም ፓርላሜንታዊ ስርአቱን የሚያስቀጥል ይሆናል፡፡

ለህዝበ ውሳኔው መካሄድም የቱርኩ ፕሬዘዳንት ኤረዶጋን አሁን ያለው ፓርላሜንታዊ ስርዓት ወደ ፕሬዘደንታዊ አስተዳደር እንዲቀየር በጠየቁት መሰረት መሆኑ ተነግሯል፡፡

ፕሬዘዳንታዊ ስርዓቱ ሀገራችንን ወደ ዘመናዊ አስተዳደር ስርዓት ይለውጣታል የሚሉ ቱርካዊያን የፕሬዘዳንቱን ሀሳብ ደግፈው ድምጽ ይሰጣሉ፡፡

በተፃራሪው የቆሙ ወገኖች ደግሞ ፕሬዘዳንታዊ ስርኣት አምባገነንነትን ያመጣል የሚል ስጋት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡

ፕሬዘደንታዊ ስርዓቱ ለፕርዘዳንቱ ካቢኔ አፍርሶ መገንባት ፓርላማ እስከ መበተን የሚደርስ ስልታንና የመሳሰሉ ሃላፊነቶችን እንደሚሰጠም ተነግራል፡፡

በዚሁ ህዝበ ውሳኔ ላይ 55 ሚሊዮን ቱርካዊያን ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ለህዝበ ውሳኔው ከ167 ሺህ በላይ ድምፅ መስጫ ጣቢዎች መዘጋጀታቸውን ቢቢሲ በድረገጹ አስነብቧል፡፡

 

Published in ፖለቲካ

መቱ ሚያዝያ 8/2009 በኢሉአባቦር ዞን የቅመማ ቅመም ሰብል ልማት ለማስፋፋት እየተደረገ ያለው ጥረት የዞኑ ዓመታዊ ምርት እንዳሳደገው የዞኑ ቡና ሻይና ቅመማቅመም ልማት ባለስልጣን ገለጸ፡፡

ለቅመማ ቅመም ሰብል ልማት ትኩረት በመስጠት ገቢያቸውን ለማሳደግ  በመስራት ላይ መሆናቸውን በዞኑ  የበቾና መቱ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

በባለስልጣኑ የቅመማ ቅመም ልማት ባለሙያ አቶ ቡላ ገብሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ 13 ወረዳዎች የሚገኙ ከ25 ሺህ በላይ አርሶአደሮች   ኮረሪማ፣ ዝንጅብል፣እርድ ፣በርበሬና ለሌሎችም  የቅመማ ቅመም ሰብሎችን በማልማት ላይ ተሰማርቷል፡፡

አርሶ አደሮቹ ባለፈው መኸር ወቅት ከ5 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በቅመማ ቅመም ሰብሎች በመሸፈን  ከ25 ሺህ 100 ኩንታል በላይ ምርት ሰብሰበዋል፡፡

በወቅቱ የሰበሰቡት ምርት መጠን ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ13 ሺህ ኩንታል በላይ ብልጫ ያለው ነው።

የምርት መጠኑን  ሊጨምር የቻለው አርሶአደሮች የሚደረግላቸውን ድጋፍና እገዛ በመጠቀም ከደንና ከቡና ልማት ጋር አቀናጅተው ቅመማቅመም የማምረት ስራቸውን በማስፋፋታቸው መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል።

አርሶአደሮች ገበያ ተኮር የቅመማቅመም ሰብሎች በስፋት በማልማት ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ የግብርና ባለሙያዎች በቅርበት የሙያ ድጋፍና እገዛ እያደረጉላቸው መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ፡

"ምርቱን ይበልጥ ለማስፋፋት ሁለት የችግኝ ጣቢያዎች ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡ ከ70 ሺህ በላይ ችግኞች አርሶ አደሮቹ እየተባዙ ናቸው " ብለዋል፡፡

አዳዲሶቹ የቅመማቅመም ዝሪያዎች በሔክታር  ይገኝ የነበረው የእርድ ምርት ከ70 ኩንታል ወደ 125 ኩንታል ፣ የኮረሪማ ምርት ደግሞ ከ6 ኩንታል ወደ 8 ኩንታል ከፍ የማድረግ አቅም እንዳላቸውም ተመልክቷል፡፡

አርሶ አደር ጌታሁን ገብረሚካኤል በበቾ ወረዳ ወልጋይ የቁብሳ ቀበሌ ነዋሪ  ሲሆኑ  ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ ከቡና ጋር በጥምር  ኮረሪማ በማልማት ላይ መሆናቸውን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

" ዘንድሮ ከልማቱ 18 ኩንታል እርጥብ ኮረሪማ ሰብስቤያለሁ" ያሉት  አርሶ አደሩ በደንብ ሲደርቅ ከስድስት ኩንታል በላይ እንደሚሆንና  በዚህም  ከ40ሺህ ብር በላይ ገቢ አገኝብታለሁ ብለው እንደሚጠብቁም ጠቁመዋል፡፡

በመቱ ወረዳ የሳርዶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር  ምትኩ ሞርካ በበኩላቸው ከሌሎች ውጤታማ አርሶአደሮች ባገኙት ልምድ በመነሳት በመጪው ክረምት ሩብ ሄክታር የሚሆን መሬት በእርድ ለመሸፈን ዝግጅት ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

በመጪው ክረምት የተሳታፊ አርሶአደሮችን ቁጥር ወደ 35 ሺህ በማሳደግ 6ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት በቅመማቅመም ለማልማት መታቀዱን የዞኑ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ባለስልጣን አመልክቷል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 8/2009 ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገር ስደተኞች የምታደርገው ድጋፍና እንክብካቤ የሚደነቅ መሆኑን የሶስት አጎራባች አገሮች የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።

የሶማሊያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፕላን፣ፖሊሲና ትብብር ኃላፊ፣ የሱዳን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእቅድና ፖሊሲ ዳይሬክተር እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ ጤናና ጉዳይ አስተባባሪ ዳይሬክተር ጄኔራል ናቸው።

ኃለፊዎቹ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገር ስደተኞች የችግር ጊዜ መጠጊያ በመሆን በጎ ስራዋ ለሌሎች ተምሳሌት ያደርጋታል።

በሶማሊያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፕላን፣ ፖሊሲና ትብብር ኃላፊ ሙሃመድ አብዱላሂ እንደገለጹት፤ በሶማሊያ የእርስ በእርስ ግጭት ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮም ሆነ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት በርካታ ቁጥር ያለው ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ በመሰደድ መጠለያ አግኝተዋል። 

''በሌሎች አገሮች የተጠለሉ የሶማሊያ ስደተኞች እንዲወጡ ሲገደዱ የኢትዮጵያ መንግሥት ልክ እንደ ራሱ ህዝብ ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ ማደረጉ የሚያስመሰግነው ነው'' ብለዋል። 

ስደተኞቹ በጦርነቱ ምክንያት ወደ መጡበት መመለስ ሲያቅታቸውም የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ ተቀብለው ከዜጎቻቸው እኩል በማየት መንከባከባቸውን ተናግረዋል።  

በአሁኑ ወቅት የሶማሊያ መንግሥት በአሸባሪው ቡድን አልሻባብ ተይዘው የነበሩ አብዛኛው ቦታዎችን መቆጣጠር በመቻሉ የአገሪቷ ሠላምና ደህንነት መሻሻሉን ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት በጎረቤት አገሮች የሚገኙ የሶማሊያ ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታወቀዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የሶማሊያ ስደተኞች "በዚህች  አገር የእንግድነት ቆይታቸው የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጋቸው ከመልካም ጎረቤት የሚጠበቅና አድናቆትም ሊቸረው የሚገባ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። 

የሱዳን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእቅድና ፖሊሲ ዳይሬክተር ዶክተር ሰኢድ ሞሃመድ  እንደተናገሩት፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሱዳን ስደተኞች ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።

እነዚህ ስደተኞች በቆይታቸው ተገቢ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰው፤ እንክብካቤው በጤና አገልግሎት ብቻ ሳይሆን "የትምህርት ዕድል ማግኘትና ሙሉ ሰብዓዊ  መብታቸው መከበሩ የሚጠቀስ ነው" ብለዋል።    

በዚህም ኢትዮጵያ ለሱዳን ህዝቦች ባለውለታ በመሆኑዋ ምስጋና የሚገባት አገር እንዳደረጋትም ገልጸዋል።    

በደቡብ ሱዳን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ ጤናና ጉዳይ አስተባባሪ ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ኬዲአንዳ ቾንግ፤ ኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ናቸው።   

"ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ነጻነት ትግል ጀምሮ የላቀ  አስተዋጽኦ እያደረገች ያለች አገርናት" ያሉት ዶክተር ቾንግ፤ በአሁኑ ወቅት እርቅ እንዲወርድና ዘላቂ ሠላም እንዲሰፈን የምትጫወተው ሚና ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጠው ተናግረዋል።

በጦርነት ወቅት የተጠለሉባትን ኢትዮጵያን የደቡብን ሱዳን ህዝቦች እንደ ሁለተኛ አገራቸው እንዲያዩዋት ማድረጉንም ገልጸዋል።   

ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን በርካታ ቁጥር ያለው ስደተኞች ተቀብላ ድጋፍና እንክብካቤ እያደረገች ነው።     

ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ ከማስተናገድ ባሻገር ለምታደርገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 

በኢትዮጵያ ከ800 ሺ በላይ ስደተኞች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 8/2009 የአገሪቷን ቱሪዝም አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር መመደቡን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም አቅም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች የማስተዋወቁ ስራ በቀሪው ሩብ ዓመት እንደሚከናወንም ገልጿል።

የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላትም ቱሪዝሙን በማስተዋወቅ የአገሪቷን መልካም ገጽታ ለመገንባት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበጀቱ ኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ባላቸው መገናኛ ብዙሃን የማስተዋወቅ ስራ ይሰራል።

አዲሱን የቱሪዝም መለያ የአማርኛ አቻ ትርጓሜ "ምድረ-ቀደምት" ደግሞ ለአገር ውስጥ ቱሪስቶች እናስተዋውቃለን" ብለዋል።

አዲሱን የቱሪዝም መለያ 'ላንድ ኦፍ ኦሪጅንስ' በተለያዩ ቁሳቁሶችና የስጦታ እቃዎች ላይ በማተም ለማስተዋወቅ ሶስት ሚሊዮን ብር መበጀቱንም ገልጸዋል።

የአማርኛ አቻ ትርጓሜውን ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች ለማስተዋወቅና ህዝቡም ይገልፀኛል ብሎ እንዲይዘው ለማድረግም ታቅዷል።

የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ያዕቆብ መላኩ  እንደገለጹት፤ የቱሪስት ፍሰቱና ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ እስካሁን በመጣበት ሂደት ሳይሆን አመርቂ ውጤት እንዲመጣ ያስፈልጋል ።

በመሆኑም አዲሱን መለያ መሠረት በማድረግ የማኀበሩ አባላት አገሪቷን ለማስተዋወቅና ስነ ምግባርን ጠብቀው ለመስራት የበለጠ መነሳሳት መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

የሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዜናዊ መስፍን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለቱሪስቱ የሚመጥኑ ሆቴሎች እየተስፋፉ እንደሆነ ገልጸው፤ ይህን በማስተዋወቅ ሂደት ማህበሩ "የሆቴል ጋይድ" አዘጋጅቶ በተለያዩ አገሮች እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

አዲሱ የቱሪዝም መለያ አገሪቷን በሚገባ እንደሚገልጻት የተናገሩት አቶ ዜናዊ፤ ይህን መለያ ስያሜ ለውጭው ዓለም በማስተዋወቅና ገጽታዋን በመቀየር በኩል "የሆቴል ባለንብረቶች ማህበር የድርሻውን ይወጣል" ብለዋል።

በተጨማሪም በፈጣን እድገት ላይ ያለው የሆቴል ቱሪዝም በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲቀናጅ በአገር ውስጥ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ ከውጭ ባለሙያዎችን በማስመጣት ስልጠናዎች እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

ሚያዝያ 8/2009 በዓለማችን የረጅም እድሜ ባለጸጋ የሆኑት ጣሊያናዊት ኤማ ሞራን  በ117 ዓመታቸው ማረፋቸው ተነገረ፡፡

ኢማ ሞራን የተወለዱት እንደአውሮፓዊያን አቆጣጠር ህዳር 29 1899 ዓመተ ምህረት እንደተወለዱም ይነገራል፡፡

በጣሊያን ሰሜናዊ ቨርቤንያ ከተማ ውስት በመኖሪያ ቤታቸው ህይወታቸው ያለፈው ኤማ ማሮን ስምንት እህትና ወንድሞች እንደነበራቸው ዘገባው ያትታል፡፡

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሁዋላ ከነበሩት 90 ያህል የጣሊያን ዜጎች መካከል  አንዷ እንደነበሩ ተጠቁማል

የዘር ሀረጋቸው ረጅም እንደሆነ የሚነገርላቸው ኤማ ቤተሰቦቻቸው የረጅም እድሜ ባለጸጎች እንደነበሩም ይነገራል፡፡

ለአብነት የተጠቀሱት የኤማ ወላጅ እናት በ91 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉንም አስታውሷል፡፡

የኤማ ሞሮን የቅርብ ሀኪም የሆነው ካርሎ ባቫ በበኩሉ ኤማ ለረጅም ኣመታት እንቁላል ፡ አትክልትና ፍራፍሬ ተመጋቢ እንደነበሩ ተናግራል፡፡

                                       

     ምንጭ ፡- ቢቢሲ

 

Published in ማህበራዊ

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን