አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 15 April 2017

ጅግጅጋ ሚያዚያ 7/2009 የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያን ከአደጋ ስጋት ለመታደግ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል፣ ቱሪዝም መገናኛ ብዙሃን ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የባህል ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ቋሚ ኮሚቴ አባላት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የመገናኛ ብዙሃን የሥራ እንቅስቃሴና የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ያለበትን ሁኔታ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ቡድን መሪ አቶ ታሪኩ ታደሰ በወቅቱ እንደገለፁት፣ በመጠለያው የሚገኙ ዝሆኖችን ከአደጋ ስጋት መታደግና መንከባከብ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ "በመጠለያው የሚገኙ ዝሆኖች አደጋ ላይ ናቸው”።

"በመጠለያው ያሉ ዝሆኖች በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ በመሆናቸው የሚመለከታቸው የፌዴራል፣ የክልል አካላትና የአካባቢው ህብረተሰብ ከአደጋ ሊጠብቋቸውና ሊንከባከቧቸው ይገባል " ብለዋል ።

የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ኃላፊ አቶ ጀማል ሀሶ በበኩላቸው፣ ከሐምሌ 2008 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ማንነታቸው ያልታወቁና የታጠቁ ሰዎች ሰባት ዝሆኖችን ገድለዋል።

ሌሎች ዝሆኖችም ራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ ወደ መኖሪያ መንደሮች ውስጥ በመግባት የስድስት ሰዎች ሕይወት ማጥፋታቸውን አስታውሰዋል።

እንደ አቶ ጀማል ገለፃ የእርሻ መሬት ለማስፋፋት ሲባል የሚደረግ የደን ምንጣሮ፣ ሕገ ወጥ አደንና የግጦሽ ስምሪት በመጠለያው ላይ የተጋረጡ ዋና ዋና የአደጋ ስጋቶች ናቸው ።

በመጠለያው የሚገኙ 400 የሚሆኑ ዝሆኖች በአፍሪካ ደረጃ ዝሪያቸው በመጥፋት ላይ ያሉ ብርቅዬዎች መሆናቸውንም አቶ ጀማል ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ፈርዱሳ መሀሙድ በመጠለያው የአስተዳደር ህንጻዎች ግንባታና የሰው ኃይል የማሟላት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል ።

የክልሉ መንግስት ከፌዴራል ዱር እንስሳትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የጥበቃና የአስተዳደር ሠራተኞች እንዲቀጠሩ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

"ይሁን እንጂ በወቅቱ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የአካባቢው አርብቶአደሮች ግጦሽ ፍለጋና ከእርሻ መሬት ማስፋፋት ጋር ተያይዞ የመጠለያው ህልውና አደጋ ላይ ወድቋል " ብለዋል ።

እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ገለጻ ችግሩን ለመቅረፍ ከማህበረሰቡ ባህላዊ መሪዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል ።

የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ በ1962 ዓ.ም የተቋቋመና 6 ሺህ 982 ስኬር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

በሌላ በኩል የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ የክልሉን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ፣የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል ።

በተለይ የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አዲሱን የማስታወቂያ ህግ ለመተግበር የጀመረውን ጥረት በማጠናከር ለማስታወቂያ ፅሁፍ ቅድሚያ በክልሉ ቋንቋ እንዲያደርግ አመልክቷል።

በሁለተኛነትም የአገሪቱን የስራ ቋንቋ (አማርኛን) በአግባቡ ለመተግበር ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴው አባላት አስገንዝበዋል ።

የኢትዮጰያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲም በክልሉ 11 ዞኖች፣ 93 ወረዳዎችና ስድስት የከተማ አስተዳደሮች የሚከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎችን በመከታተል ለህዝብና ለመንግስት ለማሳወቅ የሚያደርገውን ጥረት በማድነቅ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡

በተጨማሪም የቋሚ ኮሚቴው አባላት "የኢትዮጵያ ብሮድካስትቲንግ ኮርፖሬሽን የስርጭቱን ጥራት ለማሻሻል አገልግሎቱን ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ለማሳደግ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል " ብለዋል ።

በተለይ በካራማርዳ ተራራ ላይ የሚገኘው የማሰራጫ ጣቢያ ከመብራት መቋረጥ ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን የስርጭት መስተጓጎል በአፋጣኝ መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 

 

Published in ማህበራዊ

ሀብታሙ ገዜ ከኢዜአ (ድሬደዋ)

የባህልና የበዓል መንታ መንገድ!

     ወደ አየር መንገድ በሚወስደው ጎዳና ትይዩ ላይ በሚገኘው የአስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ህንጻ ውስጥ ለበዓል የተዘጋጁ 12 ከፍተኛና ሁለት መካከለኛ ሰንጋዎች ተኮልኩለዋል፡፡ በዓሉን እያደመቁ ህልፈተ ቀናቸውን እየተጠባበቁ ናቸው፡፡

    ከነዚህ ሰንጋዎች መካከል አንዱ የእነ አቶ ሙሉጌታ ቆርቾና የስምንት የሥራ ባልደረቦቻቸው ነው፤ 17ሺህ ብር ወጥቶበታል፤ ምርጥ የሐረር ሰንጋ የተባለውን ልብ ይበሉልኝ !- ሻኛው ያብረቀርቃል፤ ከተቀመጠበት ድንገት ብድግ ሲል የተሸከመውን ሥጋ መሸከም የተሳናቸው የሰንጋው እግሮች ብርክ የያዛቸው ያስመስልባቸዋል፡፡

     ልክ እንደ ሰንጋው የአቶ ሙሉጌታ የፊት ገጽታ ላይ ፀዳል ይነበባል፤54 ቀናት በጾም በፀሎት የዛሉ አይመስሉም፡፡ የበዓሉ ዝግጅት እንዴት ነው የሚል መንደርደሪያ ሰነዘርኩኝ፡፡

‹‹ዘንድሮ ልዩ ነው፤ ከብት ትንሽ ያዝ ቢልም እንደተለመደው የተሻለ ከብት ገዝተናል!›› አሉኝ አቶ ሙሉጌታ በኩራት፡፡

   የቅርጫ ከብት በመግዛት የቅርጫ ተካፍይና ተዋንያን እየሆኑ የመጡ ሠራተኞች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ  ነው፡፡

       “ለምን መሰለህ የቅርጫ ሥጋ በዋጋ ደረጃ አዋጭ ነው፤ ከሥጋ ቤቶች ዋጋ ጋር አይነፃጸርም፤ ሌላው ደግሞ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህል ነው። ተሰባስቦ በጋራ መብላት መጠጣት እጅጉን የሚያስደስት ትዝታ የሚፈጥርበት በመሆኑ ሁሉም የዚህ ተካፋይ እየሆነ ይገኛል፡፡” በማለት የብዙ ሰው ምርጫ የሆነበትን ምክንያት ነገሩኝ።

      አቶ ሙሉጌታ ይህን ቢሉም የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎች ግን ያልበሰለና እሳት ያልነካው ጥሬ ስጋ መመገብ ለብዙ በሽታዎች መንስኤ እንደሚሆን ይናገራሉ፡፡

    በእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት የእንስሳት ሥጋ ምርመራ ቡድን አስተባባሪ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ደመቀ ተፈሪ  ‹‹በጥሬ ስጋ አማካይነት ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ ከ150 በላይ በሽታዎች በመኖራቸው ህብረተሰቡ በባለሙያ የተረጋገጠ ከብት በማረድ ጤናማ ሥጋ መመገብ ይኖርበታል›› የሚል ምክራቸውን ይለግሳሉ።

     እርሶ የቅርጫ ሥጋ ተካፋይ ሆነው አያውቁምን? አልኳቸው

        ‹‹ጥንት እንጂ አሁን ያልተመረመረ ሥጋ ተመግቤ አላውቅም›› አሉኝ

     እርሳቸው ይህን ይበሉኝ እንጂ  በየትምህርት ቤቱ፣ በየመስሪያቤቱ፣  በክልሉ መገናኛ ብዙሃን፣ በየሰፈሩ፣ብቻ ምን አለፋችሁ በተዘዋወርኩባቸው የድሬደዋ ቀበሌዎችና አካባቢዎች ዛሬ ማታ ለቅርጫ የሚውሉ ከብቶች ታስረዋል፡፡

        እነዚህን ትዕይንቶች ካስተዋልሁ በኋላ በቀጥታ ወደ ከብት ገበያ /ጀላባ/ ተጓዝኩኝ፡፡ በአብዛኛው  የመንግስት ሠራተኞች በሕብረት ሆነው በዋጋ ሲደራደሩ ይስተዋላል፡፡ አቅማቸው መለስ ያሉት የስጋ ቤት ባለቤቶችም የትዕይንቱ ተካፋይ ናቸው፡፡ በድሬደዋ ደረጃ አንድ የሆኑት የሥጋ ቤት ባለሃብት የከብት ግዥ የሚያከናውኑት ቁጥር አንድ የሐረር ሰንጋ በሚገኝባቸው የምሥራቅ ሐረርጌ ወረዳዎች ቁልቢ፣ወተር፣ደደር፣ቀርሳ… ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች በመሆኑ በድሬደዋ ገበያ ላይ እንኳን በዓል ሆኖ በአዘቦቱም የማይመጡ መሆኑ ልብ ይሏል፤አቅማቸውን የሚመጥን ሰንጋ አይገኝም የሚል እምነት አላቸውና

  በ14ሺህ ብር መካከለኛ ከብት ለ10 ሲገዙ ያገኘኋቸው አቶ ባንተግዜ አስፋውና ሌሎች የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ቅርጫ ማህበራዊ ፍቅርን ያፀናል፤ የተጣሉ ይታረቃሉ፣ ባህሉ ሊተውና ሊከለከል የማይገባ መሆኑን አጫወቱኝ፡፡

    ለበዓሉ  በከብት ገበያው የሚጠበቀውን ያህል ከብት አልገባም ፡፡ዞር ዞር ስል ያገኘኋቸው ደላሎችም፣ ነጋዴዎችም ፣ሸማቾችም በዚሁ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡

     የከብት ነጋዴው ተሾመ ወርቁ ትልቁ በሬ ከ21ሺህ እስከ 22 ሺህ፤ መካከለኛው ከ17ሺህ እስከ 18 ሺህ ብር ዝቅተኛው ደግሞ እስከ 13ሺህ ብር እየተሸጡ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

‹‹ገበሬው ከብቶችን ገበያ አላመጣም፤በዚህ የተነሳ ዋጋ ጨምሯል በአዲሱ ዓመት መግቢያ ከነበረው ዋጋ ከአራት እስከ 5ሺ ብር ጭማሪ አሳይቷል›› ብለዋል፡፡

   አቶ ዘሪሁን አበበ የከብት ነጋዴ ናቸው፤ የዘንድሮ የከብት ገበያ መሀል ላይ ነው ያለው ይላሉ፡፡ ዝናብ አለመኖሩ ከብት ያዝ ብሏል፤ በእዚህም ገበሬው ለእርሻ ሥራ ከብት ይፈልጋል እንጂ ወደገበያ አያመጣም ባይ ናቸው፡፡

   ‹‹ትልቁ ከብት እስከ 19 ሺህ ብር እየተሸጠ ነው፤መካከለኛው 16 ሺህ ብር ይገኛል” ብለዋል የዘንድሮ በዓል  አብዛኛው ሸማች የመንግስት ሠራተኛው በመሆኑ በመደነቅ።

      በዚህ የገበያ ትዕይንት ውስጥ አንድ የማውቀው ሰው ተመለከትሁ ፤አጠገቡ ሄድኩኝ ፤ሠላምታ አቅርቤ ስለገበያው ጠየቅሁት፤ በከንቲባ ጽህፈትቤት የጥበቃ ሠራተኛ ነው፤ አንደበተ ርዕቱ ነው፤አካባቢውን ተገንዝቦ በማስረዳት በኩል የተዋጣለት መሆኑን በሥራ አጋጣሚ ተመልክቻለሁ፡፡ አቶ መላኩ ይባላል፡፡

‹‹ይሄው ቢወደድም ሽምተናል፤11 ጥበቃዎች ነን የገዛነው›› አለኝ

          ዋጋውን እንዴት ቻላችሁት? ወዲያው የመጣልኝ ጥያቄ ነበር 

      ‹‹መንግስት የጨመረልን ደመወዝ ለእዚህ ወሳኝ ሰዓት በመድረሱ የከብቱን 

               ዋጋ እንድንቋቋም አስችሎናል›› አለኝ

      ቅርጫ ተሸክመህ እቤት ስትገባ ቤተሰብ ይደሰታል፤ እዚያ ተሰባስበህ በአዋዜ ተሻምተህ ስትበላ እንዴት  ያስደስታል መሰለህ፡፡ እስቲ የበዓሉ ቀን ማለዳ ተመልከተን አንተም እግረ መንገድህን ትቀምሳለህ

     ‹‹ሀብቴ በነገራችን ላይ  እንድ ታሪክ ሰምተህ ታውቃለህ? አለኝ›› መላኩ

                ምን?

             “ስለ ጥሬ ስጋና የኢትዮጵያ አርበኞች ገድል”

    አንድ ፀሐፊ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ  በአደዋ ጦርነት ወቅት የተከሰተ ነው ብሎ የፃፈው ወዲያው ትዝ ቢለኝም፤ እኔ ባለችኝ ጥቂት የንባብ ባህል እውነታውን ስላልደረስሁበት ትዝ ያለኝን ውጬ  አለማወቄን ተነፈስሁ፡፡

    “ጥሬ ስጋ እኮ ለአድዋ ድል መገኘት አስተዋፅኦ አድርጓል፤አርበኞቻችን ጥሬ ስጋ እየዘለዘሉ ሲመገቡ ያስተዋሉ የጣሊያን ወታደሮች እግሬ አውጭ ብለው የሸሹበትን ታሪክ አለማወቅህ ይገርመኛል!” አለኝ በመገረም፡፡

           አመስግኜው ተሰናበትኩት

       የከብት ገበያውን ለቅቄ ፊቴን ከሰባተኛ ወደ ሳቢያን ሰኢዶ  ታክሲ ተራ አቀናሁ፡፡ አካባቢው የበዓል ድባብ ተላብሷል፤ሰው ይተራመሳል፤ይህ የበዓል ስሜት በፍየል ገበያ አካባቢ ያይላል፤ ጩኸቱ ፣የሚገላበጠው ረብጣ ብር፣ ተቀበል -- አትቀበል ፣ውሰድ -- አትውሰድ ክርክሩ የበዓል ዋዜማ መሆኑን ያሳብቃል፡፡

    አቶ ዩሱፍ ሣሊህ የታወቁ የአሸዋ ፍየል ገበያ ደላላ ናቸው፡፡ ቁጥሩ የበዛ ሰው በፍየል ገበያው ተሣታፊ ሆኗል፡፡

   የትልቁን ፍየል ሽንጥ በመዳፌ ጨበጥ -ለቀቅ አደረኩኝ- ልምድ ያለኝ ይመስል፡፡ አስከትዬ ዋጋውን ጠየኩ ፡፡

       ‹‹ 30 ብቻ አምጣ›› ሦስት ሺህ መሆኑ ነው።

              20 ልስጥህ፤ አያዋጣም …እንዲህ ክርክራችን ቀጠለና ሳንግባባ ቀረ

      ከፍየሎቹ መሀል  መካከለኛ ፍየል ፍለጋ  ማማተር ያዝኩ፤ አገኘሁት፡፡ ጠየኩኝ፡፡ ተከራክሬ የመጨረሻው ዋጋ 1ሺህ 600 እንደሆነ ተነገረኝ፡፡ ዝቅተኛው ከዘጠኝ መቶ እስከ 1100 ብር መሆኑን ተዟዙሬ  አይቺያለሁ፡፡

    ታዋቂው ደላላ አቶ ዩሱፍም ስለገበያው ዋጋ ለማወቅ ብቻ መምጣቴን ካስረዳዋቸው በኋላ የነገሩኝ በበዓሉ ዋዜማ ማግስት የፍየል ዋጋ ወጥ አለመሆኑን ነው፡፡

    በዛሬው ገበያ ከፍተኛው እስከ 2400 ብር፣ መካከለኛ እስከ 1800 ብር፣ ዝቅተኛው 1000 ብር እየተሸጠ  መሆኑን ነገሩኝ፡፡

   ‹‹ካለፈው በዓል አንጻር ከሦስት እስከ አራት መቶ ብር የፍየል ዋጋ ላይ ጭማሬ ታይቷል››

    የፍየል ገበያ የተበታተነ ነው፡፡ በአንድ በተከለለ ስፍራ አይሸጥም፤ አስፋልት ዳር፤ የታክሲ መውረጃና መሳፈሪያ አካባቢ፣ በየጎዳናው ላይ ይካሄዳል፤ የሚመለከተው አካል ይህን የተዝረከረክ ገበያ ትዕይንትን ተቋማዊ ደርዝ ሊያሲዘው ይገባል፡፡

        አሁን ያለሁት ወደ ሐረር መውጫ ባለው የፍየል መገበያያ አስፋልት ዳር ላይ ነው፡፡ የማውቃቸው አባትና ዲያስፖራ ልጃቸው ፍየል እየገዙ አገኘኋቸው፡፡ ይህ ቤተሰብ ለቅርጫ ትዕይንትና ተሣትፎ ልዩ ፍቅር እንዳለው አውቃለሁ -ቤተኛም በመሆኔ፡፡ ‹‹እንዴት ፍየል ተራ›› ለራሴ አጉተመተምሁ፤ ትዝብቴንም ለዲያስፖራው ልጅ ሰነዘርኩኝ፡፡

           ቤተሰብ ላለው ሰው ቅርጫ አዋጪና ወጪን የማይጎዳ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያመጣ ባህል መሆኑን ገለፀልኝ፡፡

       ሙሉ ቅርጫ አንድ ሺህ 100 ብር ቢሆን ነው፤ በዚህ ገንዘብ ሥጋ ቤት ከአራት ኪሎ ሥጋ በላይ መግዛት አይቻልም፤ ቅርጫን እንደ ባህል በመንከባከብ የቱሪዝም መስህብ ማድረግ ይገባል፣ ጉዳዩ የሚመለከተው ሰው ሊያስብበት ይገባል ያለው የ26 ዓመቱ ወጣት ዲያስፖራና ኢንቨስተር ባራኪ ገብረ ህይወት ነው፡፡

          ‹‹አንተ የቅርጫ ተካፋይ ሆነህ ታውቃለህ››

      ‹‹ለቤተሰብ ገብቼ አውቃለሁ፣ በጣም የሚጣፍጥ ነገር ነው፤ ሰዎች ስለማህበራዊ ኑሯቸው፤ ስለ አገራቸው፤ስለአካባቢያቸው፤ ስለታመሙ ሰዎች ድጋፍ ለማሰባሰብ የልባቸውን የሚወያዩበት መድረክ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ››

                ዘንድሮስ ተካፋይ ነህ?

                 አይደለሁም

                 ለምን?

    ወዳጆቼ አንድ ፍየል በስጦታ አመጡልኝ፤ እኔም አንድ ደገምኩኝ

         እና ቤተሰብ ምን አለ?

     አባቴ ቅርጫ ባለመግባቱ አዝኗል፡፡

     አብዛኞቹ የክርስትና እምነት ተከታዮች ለበዓሉ በቅርጫ ሥጋ ትዕይንት ላይ በፍቅር እየተሳተፉ ቢሆንም የድሬዳዋ ቄራ አገልግሎት ድርጅት ግን ተግባሩ ለችግር የሚዳርግ መሆኑን ይመክራል፡፡

     በድርጅቱ የህገ-ወጥ እርድ ቁጥጥር ቡድን አስተባባሪ አቶ አሰበ ኮራ በዓል በደረሰ ቁጥር በየመስሪያ ቤቱ የሚፈጸም እርድ አሳሳቢ ከመሆኑ ሌላ ደምና ፈርስ በየግቢው ተከማችቶ ለተላላፊ በሽታ እያጋለጠ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

    ‹‹ቄራው በቀን 250 ከብቶች የማረድ አቅም አለው፤ የቅርጫ እርድ አገልግሎትም ይሰጣል፡፡ ለአንድ ከብት 150 ብር ነው የሚከፈለው ለቅርጫ አራጅ የሚከፈለው ግን 850 ብር ነው፤ሕብረተሰቡ የተመረመረና ጤናው የተረጋገጠ ስጋ ለመብላት የቄራ አገልግሎት መጠቀም ይገባዋል ›› ብለዋል፡፡

   ይህን ሃሳባቸውን ያልተቀበሉ ያነጋገርኳቸው የቅርጫ ተሣታፊዎች ንፁህና ምቹ በሆነ አካባቢ ከብቱን እንደሚያርዱና ፈርስና ደሙን በአግባቡ እንደሚያስወግዱ ተናግረዋል፡፡

     አቶ ሙሉጌታ ቆርቾ ‹‹ቅርጫው እኮ ከስጋ ጉዳይ የዘለለ ነው፤ አንድነትን መጠበቂያ ነው፤ ስለሀገርና ስለትብብር መመካከሪያ ነው፤ እንደፈረንጆች የተናጥል ሕይወትን ብቻ ይዞ ከመጓዝ በጋራ የጋራ እሴቶችን በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፊያ መድረክ መሆኑን መረዳት ይገባል›› ብለዋል፡፡

   ለበዓሉ ድምቀት ፤ደምቀውና ተውበው ደንበኞቻቸውን ለማስተናገድ ሰሞኑን በጥገናና በእድሳት ላይ የሰነበቱት የሥጋ ቤቶምች ተጠቃሾች ናቸው፤ ሊቃኙ የሚገባቸው ጭምር፡፡

    በምርጥ ሥጋቸው ከሚጠቀሱት መካከል ዋናዎቹ በከተማው የሉም፤ ወደር የሌለውን የሚንከባለል ምርጥ ሰንጋ ፍለጋ ተሰማርተዋልና፡፡

    ድንገት አንዱን ሥጋ ቤት አግኝቻለሁ ፤የቤቱ ነጭ ቀለም ደምቋል፤ የወለሉ  ሸክላ በአዲስ ተነጥፏል፤ የሥጋ ማስታወቂያም በደማቁ ተፅፏል፤ተስሏልም፡፡መቼም ሸማችና ተጠቃሚ የእድሳቱን ወጪ መጋራቱ አይቀርም አልኩ በልቤ

የቤቱ ባለቤት ባይኖርም የሥጋው ዋና ቆራጭ ወጣት ተመስገን ኃይሌን አገኘሁት፡፡

‹‹ለበዓል ሦስት ምርጥ ሰንጋ አርደን ደንበኞቻችንን ለማስደሰት ተዘጋጅተናል››

     የዋጋውስ ጉዳይ ተጠቃሚው ከወዲሁ ስጋት ገብቶታል፡፡

         ያን ያህል ጭማሬ ይኖራል ብዬ አላስብም፤

ባለቤቱ የለምና የአዱ ገነቱን ሥጋ ቤት ቆራጭ አመስግኜ ተሰናበትሁ፡፡

    ነገሬን ስጠቅለው ወዲህ የጥሬ ስጋና የቅርጫ ስጋ ባህል ፣ ወዲያ ያልተመረመረና ያልበሰለ ስጋ የጤና ጠንቅነት ፤መንታ መንገድ ፤ ተመልክተናል ፣አስተውለናል፤ የትኛው መንገድ  አዋጪ ይሆን!?

      የዛሬ አጀንዳዬ የከብት ገበያና የቅርጫ ጉዳይ ላይ ሆነና የታይዋንና የአሸዋ የአልባሳት ዋጋና መሳጭ የሰው ጎርፍ የሚስተዋልበትን ትዕይንት መቃኘት አልቻልሁም፤ ይበልጥኑ ደግሞ አሪቲና ቄጤማ ጎዝጉዛ በዓልን በዓል የምታደርገዋን የድሬዋን መርካቶ -- የቀፊራ ገበያ ባለመቃኘቴ ቅር ብሎኛል፡፡ የከርሞ ሰው ይበለን---------በሌላ ጊዜ ዳግም መምጣቴ አይቀርም፡፡

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የትንሳኤ በዓል! እንዲሆን እመኛለሁ፤ ቸር እንሰንብት!

Published in ማህበራዊ

ሚዛን ሚያዚያ 7/2009 በደቡብ ክልል የአማን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በመማሪያ ክፍልና ወርክሾፕ እጥረት ምክንያት የተሟላ ትምህርት መስጠት እንዳልቻለ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የኮሌጁ መምህራንና ተማሪዎች ገለጹ።

ኮሌጁ ችግሩን ለማቃለል ከ27 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የማስፋፊያ ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

በኮሌጁ የአይሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ዮናስ በቀለ እንደተናገሩት የተማሪ ቁጥር  ካለው የመማሪያ ክፍል ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ በሦስት ፈረቃ በማስተማር  ላይ ይገኛሉ።

ይሔም በመደበኛ የመማር ማስተማር ሒደቱ ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ ከማሳረፉም ባለፈ በመምህራን ላይም ጫና መፍጠሩ እንደማይቀር ተናግረዋል

የማሽነሪ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ጌታቸው አስናቀ በበኩላቸው በመማሪያ ክፍል ጥበት ምክንያት በርካታ ተማሪዎች በአንድ ክፍል ውስጥ እያስተማሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ተማሪዎችን በአግባቡ ለመከታተል አስቸጋሪ ከመሆኑ ባሻገር የሚሰጡ ሙከራዎችን መሰራታቸውን ተከታትሎ ለመየት እንቅፋት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክስ ትምህርት ክፍል አንደኛ አመት ተማሪ የሆነው ወጣት ጋሻው ሰጠ በበኩሉ ''በቂ መማሪያ ክፍል ባለመኖሩ በርካታ ተማሪዎች በተጨናነቀ ሁኔታ  ለመማር ተገደናል'' ብሏል፡፡

ትምህርቱ በፈረቃ መሆኑም የተግባር ትምህርቱ ላይ የሚሰጠው ጊዜ በቂ እንዳይሆንና የምናገኘውም ዕውቀት ውስን እንዲሆን ስለሚያደርግ መፍትሄ ሊፈለግለት እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡

የአማን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ መስፍን አለማየሁ እንደገለጹት ኮሌጁ ከፍተኛ የሆነ የመማሪያ ክፍል፣ የቤተ ሙከራና አስተዳደራዊ ቢሮ እጥረት አለበት፡፡

በዚህም ማስተናገድ ከሚችለው በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ገልጸው ''ችግሩ በትምህርት ጥራት ላይ ተጽዕኖ አለው ''ብለዋል፡፡

ኮሌጁ የራሱ የልምምድና ሰርቶ ማሳያ ስለሌለው እስካሁን በትውስት ተማሪዎችን እያሰለጠነ መሆኑንና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ቤተ ሙከራና ዎርክሾፕ ችግሩን እንደሚያቃልል አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡

የኮሌጁ የግንባታ ተቋራጭ አስተባባሪ አቶ ዋሲሁን ተሻገር እንደገለጹት የማስፋፊያ ሥራው ከዘጠና ስምንት ከመቶ በላይ መጠናቀቅ ችሏል። 

ግንባታው  የብረታ ብረት፤ የጨርቃ ጨርቅ ፤የግንባታ፤ ኤሌክትሪክና አውቶሞቲቭ ውርክሾፖች ፤ ሁለት የመማሪያ ህንጻ፤ ሦስት የአስተዳደር ህንጻ ፤አንድ ቤተ መጻህፍት የመጸዳጃና የመሰብሰቢያ አዳራሽን ጨምሮ አስራ ሁለት ህንጻዎችን የያዘ ነው፡፡

በ1994 ዓ.ም. የተመሰረተው የአማን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አንድ ሺህ 200 ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ሲሆን እስከ አሁን ድረስም ከአምስት ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያየ ሙያ ማስመረቁ ተመልክቷል።

Published in ማህበራዊ

ድሬደዋ ሚያዚያ 7/2009 የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን 400 ሺህ ብር ግምት ያላቸው ለመስኖ የሚያገለግሉ የውሀ መሳቢያ ሞተሮችና  ምርጥ የአትክልት ዘሮችን ለፈዲስ ወረዳ አርሶአደሮች በድጋፍ ሰጠች ።

ድጋፉ የተደረገው በወረዳው በአራት ቀበሌዎች ለሚገኙ 30 አባውራ አርሶአደሮች ነው ።

ቤተክርስቲያኗ ድጋፍ ያደረገችው 16 አነስተኛ የውሀ መሳቢያ ሞተሮች 18 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የወረዳው ግብርና ፅህፈት ቤት አስታውቋል ።

የወረዳው የመስኖ ልማት ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ሸምሰዲን መሐመድ ሰሞኑን በተደረገ የድጋፍ ርክክብ ስነ- ስርአት ላይ እንደገለፁት በአካባቢው በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚደርስን ተፅዕኖ መቋቋም እንዲቻል አርሶአደሩ በቡድን ተደራጅቶ በአነስተኛ መስኖ ልማት ሥራ እንዲሰማራ ተደርጓል ።

በዚህም በሺህዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች 2 ሺህ 300 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ተቋቁመው በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናቸውን እያረጋገጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

"ቤተክርስቲያኗ ያደረገችው ድጋፍ የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ለማስቀጠል ያግዛል " ብለዋል ።

በቤተክርስቲያኗ ከአደጋ ስጋት ነጻ የሆነ ማህበረሰብ የመፍጠር ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አንተነህ መላከ እንደገለፁት፣ ቤተክርስቲያኗ በምስራቅ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ አርሶአደሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም እንዲችሉ የሚደረገውን ጥረት እያገዘች ነው ።

ቤተክርስቲያኗ የሐረር ማህበራዊና ልማት ኮሚሽን ማስተባበሪያ ጽህፈትቤት አማካኝነት ከጥቅምት 2009 ዓ.ም ጀምሮ በምስራቅና በምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች፣ በድሬዳዋና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚቆይ የ1 ቢሊዮን ብር የልማት ፕሮጀክት ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን ጠቁመዋል ።

በፕሮጀክቱ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የመጠጥና የአነስተኛ መስኖ ተቋማት ግንባታና ምርትና ምርታማነትን የሚያጎለብቱ የእርሻ መሳሪያዎች አቅርቦት ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ለፈዲስ ወረዳ አርሶአደሮች ትላንት የተደረገው ድጋፍ የፕሮጀክቱ አካል ነው ።

የወረዳው ነዋሪ አርሶአደር ዲና መሐመድ በሰጡት አስተያየት ቤተ-ክርስቲያኗ የለገሰቻቸው የውሃ መሳቢያ ሞተር ከሌሎች አርሶአደሮች ጋር የመስኖ ልማታቸውን አጠናክረው በማስቀጠል የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል ።

"ከዚህ ቀደም የምግብ እህል ድጋፍ ተደርጎልናል፣ አሁን ደግሞ የምንፈልገውን የውሃ መሳቢያ ሞተር በማግኘታችን ከተረጂነት ለመውጣት ጠንክረን እንሰራለን " ብለዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ደሴ ሚያዚያ 7/2009 አዲስ ለሚመሰረተው የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በ457 ሚሊዮን ብር የተጀመረው የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ከ70 በመቶ በላይ መጠናቀቁ ተገለጸ።

ዩኒቨርሲቲው በመጭው ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ 1 ሺህ 500 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታምሬ ዘውዴ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ የሚገነቡ ህንጻዎች  የተጀመሩት በ2008 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ነው።

እነዚህም ለመማሪያ፣ ለመኝታ፣ ለመመገቢያ፣  ለቤተ መጻህፍትና ለሌሎች አገልገሎት መስጫ የሚውሉ ሲሆን እስከ መጪው ዓመት መጀመሪያ ድረስ ግንባታቸው ይጠናቀቃል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲው በ2010 የትምህርት ዘመን በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በማህበራዊ ሳይንስ፣ በግብርና እንደሁም በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጆች በሃያ የትምህርት ዓይነቶች 1ሺህ 500 ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ስራውን ለመጀመር አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችና የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ግዥ እያካሄደ ነው።

ለሚጀመሩት የትምህርት አይነቶች ስርአተትምህርት መዘጋጀቱንና የመምህራንና ድጋፍ ሠራተኞች ቅጥር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

የመጀመርያ ዲግሪ ምሩቃን የሆኑ 61 መምህራን በመጭው ክረምት ለሁለተኛ ዲግሪ የሚያበቃቸውን ትምህርት አጠናቀው በመጭው ዓመት ሥራ እንደሚጀምሩም አመልክተዋል ።

የዩኒቨርሲቲው የግንባታ ሥራ ከሁለት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል።

አቶ አህመድ አሊዬ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል ትምህርት ለማግኘት በርካታ ውጣ ውረድ ማለፍ፣ ብዙ ርቀት መጓዝና የደህና ቤተሰብ ልጅ መሆንን ይጠይቅ አንደነበር ገልጸዋል።

"በአሁኑ ወቅት መንግስት ለትምህርት ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተስፋፉ በመሆኑ ልጆቻችን ያለ ችግር እያስተማርን ነው" ብለዋል።

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ዓመት በአገሪቱ የግንባታ ሥራቸው ከተጀመሩ 11 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሲሆን፣ በግንባታ ላይ ያሉት ተቋማት አጠቃላይ በአገሪቱ የሚኖሩ ዩኒቨርሲቲዎችን ቁጥር 44 ያደርሰዋል፡፡

Published in ማህበራዊ
Saturday, 15 April 2017 20:16

የኃላፊነት ቅርጫ

አየለ ያረጋል -ኢዜአ

ዛሬ ላይ ዓለም ወደ አንድ መንደር እየተሰበሰበች ነው። በዚህ በሉዓላዊነት ዘመን ላይ ግን ዓለም እንጂ የግለሰቦች አብሮነት ወደ ብዙ ተናጠላዊ መንደሮች የተበታተነ ነው። አስተሳሰቡ፣ ሥነ ልቦናውና አጠቃላይ የህይወት ዑደቱ ከአንድ መንደር ነዋሪዎች መካከል ለብቻው መነጠል።

በርግጥ ውጥንቅጡ በወጣና የተናጠል ኑባሬ (individual culture) በነገሰበት ዘመን ኢትዮጵያዊያን ያላቸው የአብሮነት ኑባሬ (collectivism culture) እንደተጠበቀ ነው። ለምሳሌ እኔ ባደኩበት ማህበረሰብ ውስጥ አንድ ሰው ከልደቱ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በማህበረሰቡ ጥላ ስር ነው የሚኖረው። የልደቱ ቀን ከመወለዱ አስቀድሞ መንደርተኛው እናቱን ከብቦ ይሰበሰባል። እናቱ ከተገላገለች በኋላም ገንፎ ተገንፍቶ፤ ጭብጦ ተጨብጦ ጠላም ተጠምቆ ዓለምን ይቀላቀላል። ለአቅመ ስራ ሲደርስም በደቦ ይሰራል። ትዳር ሲመሰርትም ዘመድ ጎረቤት ተጠርቶ በፌስታ ሶስት ጉልቻው ይጎለትለታል። የዓለም “የኪራይ ዘመኑን” ሲያጠናቅቅም አገሬው ተሰብስቦ አዝኖ ተላቅሶ ይሸኘዋል። እንዲህ ነው። እንዲህ ነው የአንድ ግለሰብ የኑሮ ዑደቱ። በማህበረሰቡ መካከል ተወልዶ ከማህበረሰቡ መካከል ያልፋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ በማህበራዊ መስተጋብሩ ከእርሱነቱ ጋር ጎልተው የሚወጡ ክዋኔዎች አሉ። ለአብነት ከትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ በርካታ የአብሮነት ማህበረሰባዊ ክንዋኔዎችም ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል ጾሙን ለመፈሰክ  በሬ ገዝቶ  በ“ቅርጫ” ስርዓት መከፋፈል የተለመደ ነው።

ዛሬ ላይ ያለው የቅርጫ ክንዋኔ ምን እንደሚመስልም ፋይዳው ለመዳሰስ ሞከርኩ። በተለይ የተለያየ የህብረተሰብ ስብጥር ባለባት አዲስ አበባ።

ቅርጫ - በአዲስ አበባ

ጋሽ ስንታዬሁ አዳፋ ኮፍያቸውን አድርገው በጥዋት ጸሃይ ይሞቃሉ። ከእኛ ሰፈር "ደመቅ" ያለች ሱቅ ባለቤት ናቸው። ምናልባትም ከሱቁ ውጭ ያሉ ሸራ መሰል ነገሮችን ይሸጣሉ እንጂ፤ ከሱቃቸው ሽያጭ ላይ ብዙም አይደሉ። ሌሎች ወጣቶች ናቸው ሱቅ ውስጥ የሚቀመጡት። ያም ሆነ ይህ ጠዋት ማታ በዚያ ስናልፍ (ወደ ተከራየንበት ግቢ)ና ከሱቃቸው አንዳንድ ነገሮችን ስንሸምት ሠላምታ እንለዋወጣለን። ዛሬ ለዕለቱ ጉዳይ እፈልጋቸዋለሁና ሞቅ ያለ ሠላምታ አቅርቤ ተጠጋኋቸው።

'ጋሽ ስንታየሁ ሠላም ነዎት?' ብዬ እጄን ዘረጋሁላቸው።

"እግዚአብሔር ይመስገን ደህናህን አድርክ? በዚህ ሰሞን ሠላም ይባላል ብለህ ነው?" አሉኝ። ዘወትር ከዘራቸውን ጨብጠው ከሚቀመጡባት ከሱቃቸው ፊት ለፊት ካለችው ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ ከጎናቸው ተቀምጨ ወግ ጀመርን።

'ጋሽ ስንቴ የዘንድሮ ቅርጫ ሁኔታ እንዴት ነው?'

"ምንም አይልም ዘንድሮ ትንሽ በሬ ተወደደብን እንጂ" በፈገግታ ነው የመለሱልኝ።

እንደ ጋሽ ስንቴ አባባል ዘንድሮ ለቅርጫ የሚገዛ በሬ ከፍተኛው እስከ 30 ሺ ብር ይደርሳል። በርግጥ እንደየአቅሙ እንጂ ከ14 እስከ 15 ሺ ብር ጀምሮ በሬ ይገኛል። "እኛ ለምሳሌ ትናንትና (ጸሎተ ሃሙስ ዕለት) ወደ ሱልልታ ሰው ልከን በ30 ሺ ብር ነው ያስገዛነው" አሉኝ።

'ቆይ ግን ጋሽ ስንቴ የቅርጫ ሥርዓት ምን ይመስላል? ማለቴ አንድ በሬ ለስንት መደብ ነው የሚከፋፈለው? ስንት አባላት ነው ያሉት? የአንድ መደብ ዋጋ ስንት ገባ' የሚለውን ጥያቄ አስከተልኩ።

ያጣመሩትን እግራቸውን እየለያዩ "ብዙ ጊዜ ቅርጫ በአንድ ሰፈር ያሉ ሰዎች ናቸው የሚገቡት። ብዙ ጊዜ ስድስት፣ ስምንት ወይም አስር አባላት ይኖሩታል። በስራቸው ደግሞ ሌላ አባወራ ሊያስገቡ ይችላሉ። ወትሮ ሁሉ ነገር በቅጡ ነበር። የዘንድሮ የቅርጫ ዋጋማ ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው። አምና ለምሳሌ የአንድ መደብ ዋጋ እስከ ሁለት ሺ ነበር ዘንድሮ ግን ይሄው በአምስት መቶ ብር ጨምሯል" ጨዋታቸውን ቀጠሉ።

'በበዓል ዕለት ከቅርጫ ወይ ከልኳንዳ የትኛውን መጠቀም ደግ ነው?'

"ቅርጫ የተሻለ ነው እንጂ። ዛሬ ምን ይሁን ምን ይሁን በሚያስጠረጥር ጊዜ ቅርጫን የመሰለ የለም። አንደኛ ዋጋው ውድ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ጨጓራ ነገሮችን ከልኳንዳ አታገኝም። ቅርጫ ደሞ ሰብሰብ ብለህ በደስታ እየተጫወትክ ስለሆነ ጨዋታውስ ቢሆን ማን ይሆነዋል?" ነበር ያሉኝ።

'ጋሽ ስንቴ ስርዓቱ ከእርድ ስነ ስርዓት በኋላ መለያየት ነው? ማለቴ እንዴት ነው የሚበላ የሚጠጣ እንደ ጠላ ወይም አረቄ ነገርስ አለ?'

"እንዴታ! በደንብ ነው እንጂ። ጠላ ግን አዲስ አበባ ያው አታገኝም። አረቄና ቢራ ግን አለ። ምላስ ሰንበርና ለምለም ጉበት ተቋድሰን ነው የምንለያየው። ይሄ ግን አሁን የፋሲካ፣ እርዱ የሚፈፀመው ሌሊት አጠባብ ላይ ስለሆነ ዖም ስለሆነ እህል ውሃውን ሲነጋ ነው የምንቋደሰው..."

ጋሽ ስንቴ የቅርጫ ገንዘብ ሰብሳቢ መሆናቸውንም አጫወቱኝ። እናም ስለ ቅርጫ የተሻለ ልምድ እንዳላቸው ገመትኩኝና ብዙ አወራኋቸው። እንደ ጋሽ ስንቴ አባባል ቅርጫ ብዙ ጊዜ ለገናና ለበዓለ ትንሳኤ ነው የሚከወነው። ከነጋሽ ስንቴ አብዛኛው የቅርጫ አባላት ከቤተሰብ የተወረሰ ነው። ይህ የአብሮነት እሴታቸውና ማህበራዊ ትስስራቸው ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ መሆኑ ነው እንግዲህ። እኔም አመስግኜ ተሰናበትኳቸው።

ቅርጫ በተለይም በከተሞች አካባቢ ካለው የማህበረሰብ የዳራ ታሪክና ባህል፣ ከብዝሃነቱ አኳያ "በቀላሉ ለማከናወን" በሚል በውስጤ ሲመላለስ የነበረ ጥያቄ ነው። አንድ የስራ ባልደረባዬ ተከራይታ በምትኖርበት ግቢ ውስጥ አከራዩ ተከራይዎችን አስተባብሮ ቅርጫ እንዲገቡ እንደሚያደርግ ቀደም ብላ ነግራኝ ነበር። ይህ ነገር እንዴት ይሆን?

አቶ ግርማ አሰፋ በቅርጫ ጉዳይ የተሻለ ልምድ እንዳላቸው ሰማሁ። እኔ ከምሰራበት መስሪያ ቤት የካሜራ ባለሙያ ናቸው። እናም ስለ ነገረ ቅርጫ እባክዎ ያጫውቱኝ ማለቴ አልቀረም። ከሰዎች ጋር ቆመው ስለነበር ‘ይቅርታ አቶ ግርማ! ስለ ቅርጫ ላዋራዎት ፈልጌ ነበር’ አልኳቸው በለሆሳስ መጠየቅ።

“ውይ እርሱም እየጠየቀኝ ነበር” ከፊት ለፊታችን የቆመውን ሾፌር እየጠቆሙ።"ሞልቷል። ቀደም ብለህ ብትነግረኝ ኖሮ…" አቋረጥኳቸው።

'እኔ ቅርጫ ልገባ ሳይሆን ስለቅርጫ መረጃ ለመጠየቅ' መሆኑን ነገርኳቸው። ተሳሳቅንና ወደ ጉዳያችን ገባን።

"አሁን እኔ ለአዲስ አበባ ከተማ እንግዳ ነኝ። ሌሎችም ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ወደ ከተማ የሚፈልሱ ነዋሪዎች ቅርጫ ለመግባት አያስቸግራቸውም?" አልኳቸው።

"ቅርጫ የሚከናወነው'ኮ በቆዩ ጎረቤታሞችና ዘመዳሞች ብቻ አይደለም። ብዙ ጊዜ በአስተባባሪነት ሰርቻለሁ። እኛ ለምሳሌ ከመስሪያ ቤት አምስት አባላት አሉን። አሁን አንተ አዲስ ተከራይ ከሆንክ በተከራየህበት ግቢ ውስጥ የሚከናወን ቅርጫ አለ። እና ቅርጫ በመስሪያ ቤት፣ በንግድ ተቋማት፣ በጉርብትና ቅርበት ነው ብዙውን ጊዜ የሚደረገው" አሉኝ።

'የቅርጫ ማህበራዊ ፋይዳው ምንድን ነው?'

"እንዴ! በዓል'ኮ በዓልነቱ ዋናው ሳቅ ጨዋታው ነው። ባህላዊ ገጽታው ራሱ ለይት ያለ ነው። በቅርጫ ጊዜ እንዳልኩህ ትተዋወቅበታለህ። ከተማ ላይ በሬው የሚታረደው ባለሙያ ተፈልጎ ነው። አራት መቶ ወይም አምስት መቶ ይከፈላል። አባላቱ ግን ቅርጫውን በዓይነት በዓይነት እየመደብክ ቁጭ ብለህ መጨዋወት ነው። በዚያ ሠዓት ከጓዳ እስከ አደባባይ ያሉ ወሬዎች ይወራሉ። እርስ በርስ እየተቀላለዱ መጨዋወቱም እንደዚያው። በጎዳና ላይ ያሉ ወገኖችን ሰብስበን የምንመግብበት ሁኔታም አለ። በቅርጫ ወቅት ብዙ ገጠመኞችም ይከሰታሉ" ሲሉ አቶ ግርማ መለሱ።

'ለምሳሌ ምን ምን ገጠመኞች ያስታውሳሉ?'

"በሬ ሲገዛ ከደላሎች ጋር አለመግባባት ሊከሰት ይችላል። እና አንዳንድ ደላሎች ሰንጋውን ወስፌ ወይም መርፌ ነገር ይወጉታል። ያኔ በሬው ሲይዙት ይጎፋል። እኛንም ይህ ነገር ገጥሞን ያውቃል። ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ በቅርጫ ላይ የሚቀርቡ እንደ ጠጅና አረቄ ነገሮችም አሉ። እና አንዳንዴ የሞቅታ ስሜትም ይኖራል። በዚያው ልክ በስራ ተጠምደህ ከርመህ ለበዓል ስትገናኝ ጨዋታው ይጣፍጥሃል። እና ብዙ ጊዜ ጨዋታችንን ስንል የቤተሰብን ጉዳይ እየረሳን በጣም አርፍደን እንሄዳለን" እየሳቁ።

እርዱ የት እንደሚፈጸምም ጠየኳቸው። ቅርጫው በስራ ባልደረባነት ከሆነ እርዱም በመስሪያ ቤት፤ ካልሆነ ግን በየተራ በአባላቱ ቅጥር ግቢ እንደሚፈፀም አጫወቱኝ። እርዱ ከተፈጸመ በኋላ የራስን መደብ ለማስወሰድ ቤተሰብ ይጠራል። ያኔም ልጆች የመተዋወቅ እድሉን እንደሚያገኙ አቶ ግርማ ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ የቅርጫ ሁኔታ በወፍ በረር ቢሆንም ከላይ ተመልክተናል። ከጋሽ ስንቴና ከአቶ ግርማ ምናልባትም እኔ የገጠር ልጅ ስለሆንኩኝ በገጠር አካባቢ ስለሚከናወነው ቅርጫ (በአደኩበት አካባቢ) ጥቂት ልበል። በእኛ ሰፈር ቅርጫ ለበዓላት ብቻ አይደለም። አንድ ሰው አንድ በሬ ወይም ላም በገደል፤ በዋጅማ በሌላም እክል ከተጎዱና የመትረፍ እድል የላቸውም ተብሎ ከታመነ እርድ ይከናወንና የአካባቢው ማህበረሰብ ስጋውን በመደብ ይካፈለዋል። እያንዳንዱ አባወራ/እማወራ ማህበረሰባዊ ግዴታ ስላለበት ባይፈልግም ይቃረጠዋል። ምናልባት በቀጥታ (ገንዘብ) አይከፍልም። አዝመራው ሲደርስለት 'ገበያ ውዬ እመልሳለሁ' ብሎ ድርሻውን ይወስዳል። ይህ በዋናነት ለስጋው ተብሎ ሳይሆን ከብቱ ቢጎዳበት ኪሳራ የሚገባውን ግለሰብ ለመደገፍ የሚደረግ ነው።

ከዚህ ባለፈ በገና፣ በመስቀል (ክብከባ ይባላል)፣ በትንሳኤና በመሳሰሉ በዓላት ቅርጫ የግድ ነው። በጉርብትና፣ በእድር አልያም በማህበራት ተሰባስቦ። በግ ወይም ፍየል ገዝቶ ለብቻው በዓሉን ለመዋል ያልቻለ ሰው ቅርጫ ገብቶ በዓሉን በደስታ ያሳልፋል። እኔ እንኳን የእኛን ድርሻ 'የቅርጫ መደብ' ለማምጣት እሄድ ስለነበር ለበዓላት ወቅት ከሚናፍቁኝ ትዕይንቶች ልጆች ተሰባስበን የምናደርገው ጨዋታ ነው። የአካባቢው አባቶች የሚያደርጉት ለዛ ያለው ባህላዊ ጨዋታ ነው። ቅርጫ የፋሲካ ሌሊት ላይ ስለሚከናወን ብዙም ባይሆንም ለገና በዓል ግን ቅርጫ ትልቅ ማህበረሰባዊ ትርጉም አለው። በሰፈሩ በተለያዩ ምክንያቶች የተቀያየሙ ግለሰቦች ካሉ ለዚህ ቀን ሲባል ሽማግሌ ተፈልጎ ይታረቃሉ። ሁሉም የአካባቢው ነዋሪ የቅርጫ ተሳታፊ እንዲሆንም እንደየአቅሙ እንዲደራጅ እድሎች ይመቻችለታል። ዛሬም በዚህ መልኩ የቀጠለ ይመስለኛል።

እንግዲህ ከሁለቱ የመረጃ ምንጮቸ መገንዘብ እንደሚቻለው ቅርጫ የማይናቅ ማህበረሰባዊ ትውውቅን የመፍጠር እድሉ ሰፊ ነው። በቅርጫ የተጀመረ ግንኙነት ወደ እቁብና ማህበር መሰል የኅብረት ትስስሮች እንደሚያድግም ከጋሽ ስንቴም ሆነ ከአቶ ግርማ ንግግር ተገንዝቤያለሁ። በጥቅሉ ቅርጫ ያለው ባህላዊ የአብሮነትና የመተጋገዝ እሴትነቱ የጎላ ነው። ነገር ግን የሰንጋውን ጤንነት ከማስመርመርና ጤናማ የእርድ ሁኔታ ከማከናወን አኳያ ሊሰራ እንደሚገባ አምናለሁ። ቅርጫ ከጊዜ ጊዜ ያለው ሉዓላዊነት የህብረተሰቡ ባህል በምዕራባዊያኑ ባህል መፈተኑ አይቀርም። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያዊያኑ ያላቸውን የአብሮነትና የመረዳዳት ኑባሬ መሸርሸሩና ወደ ተናጠላዊ አኗኗር መምራቱ አይቀርም። ከጊዜ ጊዜ የአጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ለእንደዚህ ዓይነት ጠቃሚ ባህሎች መዳከም የራሱን አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድርም አስባለሁ።

አዋጁም ያትታል። ከ17 ዓመታት በፊት የወጣው የቅርስ ጥናትና አጠባበቅ አዋጅ። አዋጅ ቁጥር 209/92 አንቀጽ 3 ነጥብ 5 ላይ ስለ እነርሱ ያወራል። የኢንታጀብል ባህላዊ ቅርሶች (Intangible Heritages) በዓይን ሊታዩና በጆሮ ሊሰሙ ቢችሉም ግን አይዳሰሱም፣ አይጨበጡም፣ አይነኩም። ለአብነትም ማህበራዊ ክንዋኔዎች፣ ሥነ-ስርዓቶችና ፌስቲቫሎች ይጠቀሳሉ። ከነዚህ ማህበራዊ ክንዋኔዎች መካከል ክብረ በዓላት፣ ሠርግና ሞት ጋር የተያያዙ ሥነ-ስርዓቶች ባህላዊ የዳኝነትና የዕርቅ ስርዓቶች፣ ደቦና ዕድር የመሳሰሉ ነባር የሕብረት ሥራ ባህሎችና መረዳጃዎች ወግና ልማዶችን ይጠቅሳል።

ከማንነት ስሜት ጋር ያለመጻረር፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ከሰው ልጅ ፈጠራ ክብር ጋር፣ ከህዝቦች የእርስ በርስ ባህል ጋር የማይቃረኑ ከሆኑ እንደ ማይዳሰሱ ቅርሶች እንደሚቆጠሩም በዩኔስኮ የተቀመጡ ‘የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ኮንቬንሽን” መስፈርቶች ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ የድርጅቱን  የጠቅላላ ጉባኤ ስምምነት አሜን ብላ ተቀብላለች። እንደ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አካባቢያዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ነባራዊ ሁኔታ ቢለያይም በበዓል ወቅት ኢትዮጵያዊያንን አንድ የሚያደርጓቸው ባህላዊ ክዋኔዎች ሞልተዋል። ለአብነትም ከላይ የተመለከትነው የቅርጫ ስርዓት።

በኑሯችን ውስጥ የሚገጥሙንን የክፉ ቀናትም ሆነ የደስታ ጊዜያት በጋራ "እየተቃረጥን" ስናሳልፋቸው በባህላዊና በማህበራዊ ልማት ረገድ ብዙ እናተርፋልን። ካተረፍን ደግሞ ጸጸት የለብንም። ትርፋችንን እያጠነከርን እንጂ ኪሳራ አያጋጥመንም። 'ብሔራዊ መግባባትስ ከሰፈር  ይጀምራል' የሚል አባባል ቢተረትስ? ሕብረተሰቡ ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቆ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር የራሱ ፈንታ ነው። ጎልተው የወጡትን ማህበራዊ ክዋኔዎቻችንን በዩኔስኮ ማስመዝገብ ብቻ ሳይሆን ለአብሮነታችን ምሰሶ የሆኑ ባህላዊ እሴቶቻችንን በስነ ልቦናችን ማተም ያሻናል እላለሁ። ለእያንዳንዱ የማህበረሰብ ባህላዊ እሴቶችና የአብሮነት መገለጫዎች የሆኑ የማይዳሰሱ ቅርሶችን መጠበቅ “የኃላፊነት ቅርጫ” አለብን።

 

Published in ዜና ሓተታ
Saturday, 15 April 2017 18:53

የአይጥና ድመት ጨዋታ

መስፍን አራጌ- ኢዜአ

ከሰሞኑ እኔ በምኖርበት ደሴ አካባቢየደረሰው ሁኔታ የመነጋገሪያ ርዕስነቱ ሳምንታት አልፈው እንኳ አልቀዘቀዘም፡፡ ከከንፈር መጣጩ  የባስ አታምጣ እስከሚለው ሁሉም ጉዳዩን ከአፉ አላወጣውም ።

ሰላማዊት አንዳርጌ (እውነተኛ ስሟን ለማኅበራዊ ደህንነቷ ስንል ቀይረነዋል) የ29 ዓመት ወጣት ነጋዴ ናት፡፡ ኑሮዋን በደሴ 011 ቀበሌ ያደረገች፡፡

ጥር19/2009 ዓ.ም የቅዱስ ገብርኤልን ወርሃዊ በዓል በጧት ተነስታ መሳለም ባለመቻሏ ወደ ቅጽር ግቢው ያመራችው ፀሃይ መጥለቂያዋ አካባቢ ነበር፡፡ ግቢውን ጸጥታ ወርሶታል፡፡ በጸጥታው ውስጥ ለአምላኳ መልእክቷን ታደርሳለች፡፡ በተመስጦ ጸሎት ስታደርስ የነበረችው ሰላማዊት ግቢው ውስጥ ቀይ ቀለም ያላት የቤት መኪና መግባቷን ያወቀችው ዘግይታ ነበር፡፡

ድንገት አንድ የወንድ ድምጽ ፀጥታውን አደፈረሰው ፡፡ የመኪናው ሾፌር ነው፡፡

"እንዴት ዋላችሁ?"አለ ሰውዬው በትህትና፡፡

ሰላማዊት ሰውዬውን ባታውቀውም የእግዚአብሔር ቤት ሆና የእግዜሩን ሰላምታ አልነፈገችውም "እግዚአብሔር ይመስገን" አለች፡፡

ሰውየው ከጎኗ ለመቀመጥ ፈቃዷን አልጠየቀም ቤተክርስቲያን አይደል፡፡ ቁጭ እያለ ጥያቄ ቢጤ ወረወረ፡፡"ይሄ ቤተክርስቲያን ማን ይባላል?"

"ለአካባቢው እንግዳ ነህ?"

"አዎ ከአዲስ አበባ ነው የመጣሁት፡፡" አለ ሰውዬው ተረጋግቶ፡፡

"ቅዱሥ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ይባላል፡፡"

ጥያቄና መልሱ መለስተኛ መግባባት ፈጠረ፡፡ ስም ለስም ተዋወቁ፡፡ ሰላማዊት አለችው፡፡ አክሊሉ አላት- አክሊሉ ግሩም፡፡

አክሊሉ መኪና መያዙን ገልጾ ለመሸኘት ቢጠይቃትም ጥያቄውን አልተቀበለችውም፡፡ በእግሯ መሄድን እንደምትመርጥ ነገረችው፡፡ ተስፋ አልቆረጠም፡፡

"እሽ ስልክ ቁጥርሽን ስጭኝ" አላት፡፡ ሰጠችው፡፡

በዚህ መልክ የተጀመረው ትውውቅ በስልክ ልውውጥ ተጠናከረ፡፡ ይደውልላታል ። ብዙ ነገር ያጫውታታል፡፡

አክሊሉ በትዳር ተሳስሮ በአንድ ታዛ ስር መኖር እንደሚፈልግ ነገራት፡፡ የአወንታም የአሉታም ምላሽ አልሰጠችውም፡፡ እሱ ግን ጥያቄውን አላቋረጠም፡፡ ጓደኛዋ እንድታማልደው ለመነ፡፡ ወንድሞቿን ወተወተ፡፡ ቤተሰቦቸዋን ተማጸነ፡፡ ለትዳር የተጠማ መሆኑን የ49 ዓመቱ አክሊሉ በተሰበረ አንደበት ገለጸ፡፡ በመጨረሻም ጥያቄው ተቀባይነት አገኘ፡፡

በከተማው የተከበሩ የኃይማኖት አባቶችን ሽምግልና ላከ፡፡ ሽማግሌዎቹም የደስደሱን አበሰሩት፡፡ ጋብቻው የካቲት 11/2009ዓ.ም እንዲሆን ቀን ተቆረጠ፡፡

ጋብቻው ታላላቅ ሽማግሌዎች፤ የኃይማኖት አባቶችና እንግዶች ባሉበት ተካሄደ፡፡ አዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤትና ንብረት እንዳለው የሚናገረው አክሊሉ ከሁለት ግራም የጣት ወርቅ ውጭ ሌላ መስጠት አልቻለም፡፡ ሃብቴና ንብረቴ ባለበት አዲስ አበባ ፈታ ያለ ድግስ እደግሳለሁ ሲል ቃል ገባ፡፡

በሰርጉ እለት ዶፍ ዝናብ ይጥል ነበር፡፡ አስራ አንድ ሰዓት ገደማ ነው፡፡ ድንገት አንዳች ነገር ያሳሰበው ሙሽራው አክሊሉ ወደ ሙሽሪት ሰላማዊት ጠጋ ብሎ የሆነ ነገር ሹክ አላት፡፡

"ወደ ባንክ መሄድ ነበረብኝ፡፡ በዚህ ዶፍ ዝናብ መሄድ ግን አልችልም፡፡ ሰዎች ደግሞ እየደወሉልኝ ነው፡፡ አስር ሽህ ብር ካለሽ ባክሽ ስጭኝ" አላት፡፡ ሰላማዊት አላመነታችም፤ የትዳር አጋሯ ግማሽ አካሏ ለመሆን የህይወት ጉዞ ጀምሮ የለ፡፡ ሰዎቹ ለምን እንደሚደውሉለት አታውቅም፡፡ ገንዘቡን ለምን እንደሚፈልገውም አልጠየቀችውም፡፡ የጠየቃትን ብቻ ሰጠችው፡፡

አክሊሉ ገንዘቡን ተቀብሎ አመሻሽቶ ተመለሰ፡፡ በሰርጉ ጊዜ አምሽቶ ቢመለስም በሙሽራ ወግ ተስተናገደ፡፡

ጧት አራት ሰዓት ገደማ ሙሽራው አክሊሉ ሌላ ጥያቄ አስከተለ፡፡ የሚሄድበት ጉዳይ እንዳለው ነገራት፡፡ እሱን ያህል ሰው ግን አንገቱ ላይ ሃብል ሳያስር ጣቱ ላይ ቀለበት ሳያጠልቅ ሌጣውን ቢሄድ እንደማይመጥነው አስረዳት፡፡ እናም ወርቋን እንድታወሰው ጠየቃት፡፡ ሰላማዊት 16 ግራም የሚመዝን  የአንገትና ሀብልና የጣት ቀለበቷን ሰጠችው፡፡

አክሊሉ አነስተኛ ሻንጣውን አንጠልጥሎ በሰርጋቸው እለት የተለገሳትን ስጦታዎችና አምስት ብልኮ ሰብስቦ መጠቅጠቅ ጀመረ፡፡ ሁኔታው ያላማራት ሰላማዊት በድንጋጤ ታስተውለዋለች፡፡ ደርሶ የሚመጣበት ቦታ እንዳለ ነግሯት ከቤት ወጣ፡፡

እመጣለሁ ብሎ የወጣው አክሊሉ ደብዛው ጠፋ፡፡ የት እንዳለ የሚያውቅ አልነበረም፡፡ ስልክ መደወሉን ግን አላቋረጠም፡፡ አስቸኳይ ስራ ስላጋጠመው መምጣት አለመቻሉን ይነግራታል፡፡

የካቲት 12 በጋብቻው ማግስት ከቤት የወጣው አክሊሉ የውሃ ሽታ እንደሆነ መጋቢት ደረሰ፡፡

መጋቢት 5/2009ዓ.ም ደሴ ከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት ጉዳይ የነበራት ሰላማዊት ጉዳይዋን ጨርሳ ስትመለስ ፒያሳ አካባቢ አንድ መኪና አየች፡፡ ዓይኗን አላመነችም፡፡ ለአንድ ቀን አብሯት ያደረው ባለቤቷ የአክሊሉ መኪና ናት፡፡ አንዲት ትራፊክ የመኪናዋን ታርጋ እየፈታች ነው፡፡ የሆነች ሴት ደግሞ ሁኔታውን በሞባይሏ ትቀርጻለች፡፡ አንዳች ነገር እንዳለ ውስጧ ነገራት፡፡

ሰላማዊት ሞባይል ወደምትቀርጸው ሴት ጠጋ ብላ "አንችም እንደኔ ተዘርፈሽ ይሆን?" አለቻት፡፡

"አዎ የተዘረፍኩ ነኝ" አለች በእልህ ራሷን በመነቅነቅ፡፡

ሰላማዊት የአክሊሉ መኪና ሰው በመግጨቷ ባለችበት እንድትቆም መደረጓን አወቀች፡፡ ስልኳን አውጥታ ወደ አክሊሉ ደወለች፡፡ የውስጧን በውስጧ ይዛ አናገረችው፡፡ ተረጋግቶ ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰብ እንዲያሳክም ከነገረችው በኋላ እዚያው እንደምትጠብቀው ነገረችው፡፡ አክሊሉ መኪናው የቆመችበት ቦታ ሲመለስ ተዘርፈናል የሚሉ ሁለት ሴቶች ብቻ አልነበረም የጠበቁት ፖሊስ ጭምር እንጅ፡፡

የአክሊሉን መኪና በሞባይል ስትቀርጽ የነበረችውና ተዘርፊያለሁ ስትል የነበረችው ሴትስ ማን ናት?

የ38 ዓመቷ ምህረት ሲሳይ (እውነተኛ ስሟን ለማኅበራዊ ደህንነቷ ስንል ቀይረነዋል) በደሴ ከተማ በቀበሌ 10 የምትኖር የመንግሥት ሰራተኛ ናት፡፡ የካቲት 10 የመብራት ወርሃዊ ክፍያ ለመክፈል በጉዞ ላይ ሳለች ኪዳነምህረት አካባቢ አንድ መኪና ውስጥ የተቀመጠ ሰው በምልክት ይጠራታል፡፡ ወደ ጠራት ሰው ሄደች፡፡

"ለአገሩ እንግዳ ነኝ፡፡ ባክሽን እዚህ አካባቢ የኮምፒውተር ታይፕ የሚያደርጉ ወይም ፎቶ ኮፒ አገልግሎት የሚሰጡ ካሉ ብታሳይኝ" አላት፡፡

ሳታመነታ አሳየችው፡፡ ሰውየው ግን በቀላሉ የሚላቀቃት አልሆነም፡፡ ወደ ምትሄድበት ሊሸኛት እንደሚችል ጠየቃት፡፡ አልተቀበለችውም፡፡  ቅርብ ስለሆነ መሸኘት እንደማያስፈልጋት ነገረችው፡፡ በክርስትና እምነት ቅዱሳን የተባሉትን ሁሉ በስማቸው እየጠራ ተማጸናት፡፡ ምህረት ልመናውን መቃወም አልቻለችም፡፡ "ጻድቃኑን ረግጨ የምሄድ ያህል ተሰማኝ" የምትለው ምህረት መኪናው ውስጥ ገባች፡፡

አክሊሉ እንደሚባል ነገራት፡፡ በትዳር የተጎዳ፣ በብቸኝነት የተሰቃዬ መሆኑን አንጀት በሚበላ ትካዜ ገለጸላት፡፡ ለእምነቷ የምታድር እንደ እሷ ዓይነት ሴት እንደሚፈልግ ጠቆማት፡፡

"ፈጣሪ ልመናየን ሰምቶ አንችን የመሰለ የእምነት ሰው ሰጥቶኛል፡፡ ባክሽን እንጋባ" አላት አክሊሉ፡፡

"እንዴት ትዳርን ያህል ተቋም በጥድፊያ እንገነባለን፡፡ ባይሆን ፈጣሪ እንዲያሳካው በጸሎት እንለምን" ስትል ምላሽ ሰጠችው፡፡ እስከ ምጽአት ሊጠብቃት ዝግጁ መሆኑን አረጋገጠላት፡፡

አክሊሉ ምህረት ወደምትሰራበት ቢሮ ካደረሳት በኋላ በስራ መውጫ ሰዓት እንደሚመለስ ነግሯት ተሰናበታት፡፡ አክሊሉ እንዳለው አስር ሰዓት ገደማ ምህረት ወደምትሰራበት ቢሮ መጣ፡፡ ከስራ ሰዓት ስትወጣ ያልጠበቀችውን ስጦታ አበረከተላት - የአንገት ሃብልና የጣት ቀለበት፡፡  ምህረት ግን አልተቀበለችውም፡፡ የእሷ ሃቅ አለመሆኑን ገልጻ መለሰችለት፡፡ የትዳር ጥያቄውን ከማቅረብ ያልተቆጠበው አክሊሉ ያለውን የሃብት መጠን በመዘርዘር ለማማለል ሞከረ፡፡

"አዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ 480 ሄክታር ላይ የተንጣለለ ቪላ ቤት ከነሰርቪሱ፣ ሲኖ ትራክና ገልባጭ መኪና አለኝ፡፡" አላት፡፡

የምህረትን ልብ ለማሸነፍ አክሊሉ ወደ ስራ ቦታዋ በመምጣት አገኛት፤ ጓደኞቿንም ጋበዘ፡፡

በተዋወቁ በማግስቱ ሻይ ቡና ካሉ በኋላ እንደዘበት የባንክ አካውንት እንዳላትና እንደሌላት ጠየቃት፡፡ የጥያቄው ዓላማ ባይገባትም በቅንነት መለሰችለት፡፡

"ውጭ አገር የምትኖር እህቴ በስሜ ካስቀመጠችው 57 ሺህ ብር ውጭ የኔ የምለው የባንክ ሂሳብ የለኝም፡፡ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢ የምተዳደር የመንግስት ሰራተኛ ነኝ፡፡" አለችው፡፡ ለአክሊሉ ይሄ በቂ ነበር፡፡ የባንክ ቡኩን እንድታሳየው ጠየቃት፡፡

ከሁለት ቀናት በኋላ ተገናኝተው ምሳ ተገባበዙ፡፡ ምህረት የጊዜ ጉዳይ እንጅ አንድ ቀን እንደምታገባው አምናለች፡፡ አክሊሉ ደግሞ ይሄንን ተረድቷል፡፡ 

ግብዣው ሲጠናቀቅ በአክሊሉ ጥያቄ መሰረት የባንክ ደብተሯን አሳየችው፡፡ አክሊሉ ደብተሩን በአጽንኦት ከመረመረ በኋላ "ደብተርሽ ወጭ ገቢ እንዳለው ታውቂያለሽ? ወጭ አድርገሽ ነበር?" አላት፡፡

"ለእህቴ ቦታ ለመግዛት ለወንድሜ የተወሰነ ገንዘብ አውጥቼ ሰጥቼው ስለነበር ነው" ስትል መለሰች፡፡

አክሊሉ የራሱን ሁለት የባንክ ደብተሮቹን አውጥቶ አሳያት፤ አንዱ የንግድ ባንክ ሌላው የዳሸን ባንክ ነው፡፡ በደብተሮቹ ላይ ያለውን የገንዘብ መጠን ግን አላየችውም፡፡ የማየትም ፍላጎት አልነበራትም፡፡ ከሁለት የባንክ ደብተሮቹ ለስራ የሚያስፈልገውን አስቀርቶ ቀሪውን ገንዘቡን በእሷ ስም ከተቀመጠውን 57ሺህ ብር ጋር በመቀላቀል የጋራ አካውንት መክፈት እንዳለባቸው አሳሰባት፡፡ ማሳሰቢያው አሳብ የሆነባት ምህረት "ገንዘቡ የእህቴ እንዴት ሆኖ በጋራ አካውንት መክፈት እንችላለን?" ስትል ጭንቀቷን ገለጸች፡፡

"ምን መሆንሽ ነው ፍቅሬ እንኳንስ ገንዘባችን እኛ አንድ አካል አንድ አምሳል ልንሆን አይደል እንዴ?"

ምህረት በፍጹም ልቧ አመነችው፡፡ ዳሸን ባንክ በስሟ የተቀመጠውን 57ሽህ ብር አውጥታ ቆጥራ ሰጠችው፡፡ አካውንቱን በጋራ ለመክፈት መታወቂያ ስለሚያስፈልግ መታወቂያዋን እንድትስጠው ጠየቃት እሱንም አስረከበችው፡፡

የምህረት ስጋት ወንድሟ የእህቷን ቤት እያሰራ ስለሆነ ድንገት ገንዘብ ቢያጥረው እንዴት ይሆናል የሚል ነው፡፡ አክሊሉ ደግሞ ለዚህ ጥሩ ምላሽ አዘጋጅቷል፡፡ ብሩን በፈለገው ሰዓት ለወንድሟ እንደሚሰጡት አረጋገጠላት፡፡ ምህረት ስጋትም ፍርሃትም እየናጣት ይቅርብኝ አለች፡፡ በመሃላ ሊያረጋጋት ሞከረ፡፡

በየሰዓቱ ካላገኘሁሽ እያለ ፋታ ይነሳት የነበረው አክሊሉ ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ ደብዛው ጠፋ፡፡ ወትሮም ጥርጣሬ ውስጧን ሲያነጥረው የነበረው ምህረት ሰማይ ምድሩ ዞረባት፡፡ ደጋግማ ብትደውልለትም ስልኩ ጥሪ መቀበል አልቻለም፡፡

እምባና ጭንቀት፣ ፀፀትና ብስጭት እያብሰለሰሏት ሳለ መጋቢት አምስት የምትሰራበት ቢሮ አካባቢ ፒያሳ ላይ የአክሊሉን መኪና ታያታለች፡፡ ጊዜ አላጠፋችም፡፡ ቦርሳዋን ቢሮዋ ወርውራ ወደ ቆመችው መኪና ተንደርድራ ሄደች፡፡ አክሊሉ የለም፡፡ ባይኖርም ግድ አልሰጣትም፡፡ እንኳንም መኪናውን ያገኘቻት፡፡ ቢያንስ መኪናን ያህል ነገር ጥሎ አይሰወርም፡፡

ሞባይሏን አውጥታ መኪናዋን መቅረጽ ጀመረች፡፡ በዚህ ሰዓት ነበር ከሰላማዊት አንዳርጌ ጋር የተገናኙት፡፡

አክሊሉ ወደ መኪናው ሲመለስ ምህረትና ሰላማዊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውል አደረጉ፡፡ በአቅራቢያቸው ወዳለውም አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ተያይዘው አመሩ፡፡ ጉዳያቸውን ዘርዝረው አስረዱ፡፡ በዚህ መሃል ነበር ተጠርጣሪ ወደ ጊዜያዊ ማረፊያ ሲላክ ከኪሱ  የወጣ የአንዲት ሴት ፎቶና መታወቂያ የተመለከቱት፡፡ ሁለቱም ከሳሾች በመታወቂያ ላይ ያለችውን ሴት ያውቋታል፡፡ ምናልባትም የእነሱ እጣፈንታ የደረሰባት እንደሆነችስ ማን ያውቃል?... እውነቱን ለማረጋገጥ ባለመታወቂያዋ ጋር ስልክ ተደወለ፡፡

"ሃሎ" አለች ስልክ የተደወለላት ሴት

"እንግዳወርቅ ማስረሻ  ነሽ?" አለ ከወዲያኛው መስመር የሚሰማው ድምጽ፡፡ (እውነተኛ ስሟን ለማኅበራዊ ደህንነቷ ስንል ቀይረነዋል)

"አዎ ነኝ"

"አክሊሉ ግሩም የሚባል ሰው ታወቂያለሽ?" ተጠየቀች፡፡

አክሊሉ ግሩምን ታውቀዋለች እንጂ ፡፡ የእንግዳወርቅ ልብ ደረቷን ጥሶ ይወጣ ይመስል በድንጋጤ ይመታል፡፡ አዎ በእርግጥም አክሊሉን ታውቀዋለች፡፡ ያ ጊዜ እንዴት ይረሳል?!

በመንግሥት ስራ የምትደዳረው የ55 ዓመቷ እንግዳወርቅ ጎንደር በር አካባቢ ታክሲ እየጠበቀች ነበር፡፡ ቀኑ ደግሞ የካቲት 27/2009ዓ.ም፡፡

ታክሲዎች ከመነሻቸው ተሳፋሪ እየሞሉ ስለሚመጡ  መንገድ ዳር ላይ የትራስፖርት አገልግሎት ማግኘት ይከብዳል፡፡ በርካታ ታክሲ ጠባቂ የአስፋልቱን ዳር ይዞ ተደርድሯል፡፡

ድንገት አንዲት የቤት መኪና ቆመችና ሾፌሩ እንግዳወርቅን እንድትገባ ምልክት ሰጣት፡፡ በታክሲ እጥረት የተጉላላቸውና በድካም የዛለችው እንግዳወርቅ ትብብሩን አመስግና መኪናው ውስጥ ገባች፡፡ በጉዞው መሃል የሆድ የሆዳቸውን ተጨዋወቱ ከአክሊሉ ጋር፡፡ ነዋሪነቱ አዲስ አበባ መሆኑንና ቱርቦ የጭነት መኪናው ሃይቅ አካባቢ ተገልብጦበት እሱን ለማስነሳት መምጣቱን ነገራት፡፡ እንግዳወርቅ ለአገሩ እንግዳ ሆኖ ላደረገላት ትብብር አመስገነችው፡፡ እንግዳ ነውና ቤቷ ሻይ ቡና እንዲል ጋበዘችው፡፡ አላንገራገረም - ግብዣውን ተቀበለ፡፡

ቤተቦሰቿ የክብር እንግዳቸውን በአክብሮት ለማስተናገድ ሽርጉድ አሉ፡፡ መብራት ባለመኖሩ ከሰል ፍለጋ ወዲያ ወዲህ ሲሉ የተመለከተው አክሊሉ "መኪናዬ ላይ ከሰል ስላለ ኋላ አመጣልሻለሁ" አላት፡፡ እንግዳወርቅ ውለታው በዛባት፡፡ መልካምነቱ ከበዳት፡፡

ቤት ያፈራውን ቀማምሶ የተደረገለትን መስተንግዶ አመስግኖ ከቤት ሲወጣ የሞባይል ቁጥሯን ተቀበለ፡፡

ከቀኑ አስር ሰዓት ገደማ የእንግዳወርቅ ስልክ ጥሪ አሰማ፡፡ አንስታ አነጋገረች - አክሊሉ ነበር፡፡ የት እንደሆነች ጠየቃት፡፡ ወደ ቤት ለመግባት መንገድ ላይ መሆኗን ነገረችው፡፡ ከሰሉን ይዞ እየመጣ መሆኑን ጠቁሞ "ጠብቂኝ" አላት፡፡ ጠበቀችው፡፡ ስጦታውንም ይዘው ወደ ቤት ገቡ፡፡ የእንግዳወርቅ እናት በአንድ ቀን ትውውቅ ይሄን ያህል ቸርነት ላሳያቸው እንግዳ ምስጋናቸውን አቀረቡ፡፡

አክሊሉ አንዳንድ ግለሰባዊ ጥያቄዎችን ጠየቃት፡፡ እንግዳወርቅ በምትችለው መጠን መለሰችለት፡፡ እምነትሽ ምንድን ነው አላት፡፡ ፕሮቴስታንት መሆኗን ነገረችው፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ የጠበቀ ቅርርብ መፍጠር የቻለው አክሊሉ ወደ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እንዲሄዱ ለእንግዳወርቅ ጥያቄ አቀረበ፡፡ በእምነቷ ፕሮቴስታንት ብትሆንም እንግዳወርቅ ጥያቄውን ለመግፋት አልደፈረችም፡፡ አብራው ሄደች፡፡ በጉዟቸው ላይ ስለ ግል ህይወቱ አንድ ሁለት አላት፡፡

"እኔ በሚስት የተጎዳሁ ሰው ነኝ፡፡ 250ሺህ ብርና አንድ ሚኒባስ ለሚስቴ ሰጥቼ ተፋትቻለሁ፡፡ አሁን በሃዘን የተጎዳውን ጎኔን የምትጠግንልኝ ሴት እፈልጋለሁ፡፡ ያች ሴት ደግሞ አንች ነሽ፡፡ ታገቢኛለሽ?"አላት፡፡

ጥያቄው ዱብዳ ቢሆንባትም ተረጋግታ ለመመለስ አልተቸገረችም፡፡ "ትዳር ጥሩ ነበር ግን እንዴት ሁለት የተለያዬ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች በአንድ ጣራ ሊኖሩ ይችላሉ? አይከብድም?" ስትል መለሰችለት፡፡

"ምንም የሚከብድ ነገር የለውም፡፡ ከፈለግሽ እኔ ሃይማኖቴን እቀይራለሁ፡፡ የምፈልገው ትዳር ብቻ ነው" ሲል ወተወተ፡፡

የእንግዳወርቅን ልብ በተወሰነ ደረጃ ማሸነፍ የቻለው አክሊሉ የተገለበጠብኝን መኪና ተሳቢ ላሳይሽ በማለት ወደ አንድ ጋራዥ ወስዶ የሆነ ተሳቢ አሳያት፡፡  አመነችው፡፡

ከጋራዥ መልስ የእንግዳወርቅን እጅ በእጆቹ አጥብቆ ያዘ፡፡ እንግዳወርቅ ምንም አላለችም፡፡ በጣቷ ላይ ያለውን የወርቅ ቀለበት አውጥቶ እሱ ጣት ላይ አደረገው፡፡ እንግዳወርቅ ድርጊቱን እንደ መድረክ ተውኔት በትኩረት ትከታተላለች፡፡ ከዚያም የእሱን ቀለበት አውጥቶ እሷ ጣቶች ላይ ሰካው፡፡ አንገቱ ላይ ያለውንም ሃብል አውጥቶ በስጦታ ዘረጋላት፡፡

በማግስቱም ተቀጣጥረው ተገናኙ፡፡ አሁንም የጋብቻ ጥያቄውን አቀረበላት፡፡

"በሃብት ደረጃ ከ3.5 ሚሊዮን ብር በላይ ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ እኔ ካንች የምፈልገው 70 በ30 ነው"አላት

"እንዴት?" ጠየቀች እንግዳወርቅ፡፡

"ሰባ በመቶ እንደ እናት የት ገባህ የት ወጣህ ብላ የምትቆረቆርልኝ ሰላሳ በመቶ እንደ ሚስት አካሌ ብላ የምታስብልኝን ሴት ነው የምፈልገው፡፡ እኔ ባለኝ ሃብት የተንደላቀቀ ኑሮ መምራት እንችላለን፡፡ አንች ጋር ስንት ብር ይኖራል?"ሲል እንደዘበት ጥያቄውን

ወረወረ፡፡

"አንድ ሰላሳ ሺህ ብር አላጣም" አለች በለሆሳስ እሱ አለኝ ካለው ብር ጋር ስታነጻጽረው የእሷ መጠኑ አንሶባት፡፡አክሊሉ በፍጥነት የጋራ አካውንት መክፈት እንዳለባቸው አሳሰባት፡፡ እናም መታወቂያና ፎቶዋን እንድትሰጠው አግባባት፡፡

የእሷ ሚስትነት የእሱ ባልነት የሚረጋገጠው የጋራ ሃብታችው መገለጫ የሆነ የጋራ አካውንት ሲከፍቱ እንደሆነ አስረዳት፡፡

እንግዳወርቅ ቆም ብላ ለማሰብ እንኳን ፋታ አላገኘችም፡፡ መታወቂያና ሁለት ጉርድ ፎቶ ግራፍ ከቤቷ አፈላለጋ ሰጠችው፡፡

10 ሺህ ብር ከብርሃን ባንክ 20 ሽህ 900 ብር ደግሞ ከንግድ ባንክ አውጥታ ታስረክበዋለች፡፡ የጋራ ሃብት በጋራ አካውንት ሊከፈት ያለ የሌለ ጥሪት ተሟጥጦ ተሰጠው፡፡

አክሊሉ ታማኝነቱንና ለእንግዳወርቅ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ግማሽ ኩንታል ጤፍ ገዝቶ ለቤተሰቡ አስረከበ፡፡ አንድ ጆንያ ከሰል ለእህቷ በመለገስ  በልቧ ውስጥ ማህተሙን አሳረፈ፡፡

በጋራ አካውንት እንከፍታለን ብሎ 30 ሺህ 900 ብር ከወስደ በኋላ መታወቂያና ፎቶ ሰብስቦ ፎርም መሙላቱን ነገራት፡፡

"እኔ በሌለሁበት የጣምራ ፊርማ እንዴት ሊፈረም ይችላል?" የሚል ጥያቄ አነሳችለት፡፡

ችግር እንደሌለው በመግለጽ ጥያቄዋን ያጣጣለው አክሊሉ ብሩ እንዳይባክን በእሱ አካውንት ውስጥ እንዲገባ ማድረጉንና ነገሮች ሲመቻቹ የጋራ አካውንቱን ባንክ ድረስ በመሄድ እንደሚከፍቱ ያብራራላታል፡፡ ውስጧ  ቢጠረጥርም ማመኗ ሚዛን ደፋና የተናገረውን ተቀበለችው፡፡

ገንዘቡን እጁ ውስጥ ያስገባው አክሊሉ በቀን ሁለትና ሶስቴ የሚያያትን ሴት ዘነጋት፡፡ ዱካው ተሰወረ፡፡ አልፎ አልፎ ብቻ ለስራ ከከተማ ውጭ እንደሆነ በአፍታ የስልክ መልእክት ያስተላልፍላታል፡፡

በዚህ ወቅት ነበር ከአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ተደውሎ አክሊሉ የሚባል ሰው ታውቅ እንደሆነ የተጠየቀችው፡፡ አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ስትገሰግስ ሄደች፡፡ ምህረትና ሰላማዊት አዚያው ጠበቋት፡፡

እንግዳወርቅ ከአክሊሉ በስጦታ የተበረከተላትን የአንገት ሃብልና የጣት ወርቅ አውጥታ ለፖሊስ አስረከበች፡፡ በጋብቻዋ ማግስት የአንገትና የጣት ቀለበቷን በአስገራሚ ሁኔታ ተነጥቃ የነበረችው ሰላማዊት  ንብረቷን አገኘች፡፡ የትዳር ፈላጊው አስገራሚ የፈጠራ ድርጊትና የማጭበርበር ጉዞ በአስገራሚ ቅጽበት ተገታ፡፡

ፖሊስ ባደረገው ማጣራትም ግለሰቡ ሁለት መኪኖችን ከአዲስ አበባ በመከራየት ለዚሁ ስራ ሲጠቀምባቸው እንደነበር ደርሶበታል፡፡

አከሊሉ ግሩም የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት በ1996 የወጣውን የኢፌድሪ የወንጀል ህግ ቁጥር 6921/1/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ በቀረበበት የማታለል ክስ ድርጊቱን መፈጸሙ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ተረጋገጠበት፡፡ ጉዳዩን ሲከታተል የቆየውም የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ብሎ ውሳኔ አሳለፈበት፡፡

ፍርድ ቤቱ መጋቢት 13 በዋለው ችሎት ተከሳሹን ጥፋተኛ በማለት እጁ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ የሚታሰብ የሰባት ዓመት ጽኑ እስራት አሳልፎበታል፡፡

Published in መጣጥፍ

ከአረጋዊ መዝገበ (ኢዜአ )

በኢኮኖሚ የበለፀጉ ተብለው የሚጠሩት የዓለም ሃገራት አሁን የደረሱበትን የእድገት ደረጃ ላይ እንዲገኙ  ቁልፍ ሚና ከተጫወቱ ዘርፎች መካከል በግብርና ላይ የተመሰረተ የህብረት ስራ ማህበራት እንቅስቃሴ አንዱ መሆኑን  መረጃዎች ይጠቁማሉ ።

ግብርና ዘርፈ ብዙ ሰብሎች የሚያካትት ቢሆንም በአሁኑ ፅሁፍ ትኩረት ያደረግነው ግን ስኳር ድንችን ነው ። አገራት ህዝባቸውን  በህብረትና በግል እያንቀሳቀሱ ስኳር ድንች የፈጥኖ ደራሽ ሚናውን እንዲጫወትና በምግብ ሰብል ፈጥነው እራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ተጠቅመውበታል ።

በስኳር ድንች ልማት በስፋት ተንቀሳቅሰው ውጤታማ ከሆኑ 100 የዓለም አገራት መካከል ታላቋ ቻይና ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኗን  የኤርላንድ ዓለም አቀፍ የስኳር ድንች ምርምር ማእከል መረጃ ያመላክታል ።

ዜጎች የስኳር ድንች ምርትና ቅጠል ከተጠቀሙ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አልፈው ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ሆኖ ያገለግላቸዋል ። ሃይል ሰጪ ንጥረ ነገር እንዲያገኙም ይረዳል ። በቪታሚን ኤ ፤ ቢ፤ ሲና ኢ ንጥረ ነገር የበለፀገ ነው የሚሉት በአየርላንድ ዓለም አቀፍ የስኳር ድንች ምርምር ማእከል የመቀሌ ቅርንጫፍ ሀላፊ ዶክተር ሃይላይ ተስፋይ ናቸው ።

በሃገራችን የተለያዩ ክልሎች ውስጥ ህዝቡ የስኳር ድንች ልማትና አጠቃቀም ለምግብ ዋስትና መረጋገጥና ለገቢ ምንጭ ማሳደጊያ እንዲጠቀምበት መንግስትና ማእከሉ ለአራት አመታት ያክል እየሰሩ መቆየታቸውን ዶክተር ሃይላይ  ይናገራሉ ። ህዝቡንም በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ።

ማእከሉ ከትግራይ ክልል ዕርሻና ገጠር ልማት ቢሮ ጋር ተቀናጅቶ መስራት ከጀመረ አምስት ዓመታት አስቆጥሯል ።  በ13 ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኝ ህዝብ የስኳር ድንች አመራረትና አጠቃቀም የማላመድ ስራም ተከናውኗል ።

በተጠቀሱ ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ በሺህ ለሚቆጠሩ አባውራ አርሶ አደሮች የአሰልጣኞች ስልጠና እንዲወስዱም ተደርጓል።

በእንጀራ፤በቂጣ፤በገንፎ፤በወጥና በሌሎች መልክ እየተዘጋጀ ሊቀርብ እንደሚችል ህዝቡ እየተገነዘበ በመምጣቱ በአሁኑ ሰዓት በሁሉም አካባቢ እየተስፋፋ ይገኛል ነው ያሉት ።

በክልሉ በተደረገው የተቀናጀ ጥረት ዜጎች ድህነትን በማስወገድና ጤንነትን በማረጋገጥ ስኳር ድንች የሚኖረውን ፋይዳ እየተገነዘቡ እንዲመጡ ማስቻሉንም ያስረዳሉ ።

በተለይ በክልሉ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የስኳር ድንች ምግብ ፕሮግራም እንዲጀምሩ በመደረጉ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ከማድረግ አልፎ ንቁ አእምሮ ይዘው ትምህርታቸው እንዲከታተሉ አስችሏል ። ተጠናክሮ እንዲቀጥልም እየተሰራ ነው ሲሉ ዶክተር ሀይላይ አስረድተዋል።

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን ሃውዜን ወረዳ ውስጥ ‘‘መጋብ‘‘ ተብሎ በሚጠራው ገጠር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደር  ገብረህይወት ካህሳይ እንዳሉት ሁለት ጥማድ ማሳቸውን በስኳር ድንች ማልማትና መጠቀም ከጀመሩ ሶስት ዓመታትን አስቆጥረዋል።

በዓመት ከሁለት ጥማድ መሬታቸው በሁለት ዙር 100 ኩንታል የስኳር ድንች ምርት በማግኘት ገቢያቸውን እንዲያሳድጉና  በምግብ ሰብል እራሳቸውን እንዲችሉ ዋስትና ሆኖአቸዋል ።

ከሁለት ጥማድ መሬታቸው በዓመት ሁለት ዘር የስኳር ድንች ቁርጥራጭና ፍራፍሬ እያለሙ ገበያ ላይ አንድ ኩንታል ከ600 እስከ 700 ብር ድረስ እየሸጡ መሆናቸውንም ይናገራሉ።

የራሳቸውና የቤተሰቦቻቸው የተመጣጠነ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ በኣካባቢያቸው ለሚገኙ ከሁለት ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች ዘር በመስጠትና ልምዳቸውን በማካፈል ሞዴል ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው ።

እስከ ኤርላንድ ድረስ ተጉዘውም የስኳር ድንች ተማራማሪ አርሶ አደር ተብሎው እንዲጠሩና የገንዘብና ሌሎች ሽልማቶችን እንዲያገኙ መንገድ እንደከፈተላቸው አርሶ አደር ገብረይህወት ይገልፃሉ።

በደቡባዊ ምስራቅ ዞን የእንደርታ ወረዳ ልዩ ስሙ ‘‘የጨለቆት‘‘ ገጠር መንደር ነዋሪ አርሶ አደር ካልኣዩ ህሉፍ በስኳር ድንች ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ናቸው ።

ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በሱዳን አገር በስደት ላይ ቆይተው ወደ አገራቸው ከተመለሱ ሁለት ዓመት ሆኖአቸዋል ።   በስኳር ድንች ልማት ከተሰማሩ ወዲህ አዲስ ህይወት መምራት መጀመራቸውን ይናገራሉ ።

አሁን አንድ ጥማድ የእርሻ ማሳ በወር ሁለት ሺህ ብር ተከራይተው በቁርጥራጭ ስኳር ድንች እንዲሸፈን ሌት ተቀን በመስራት  በዓመት ከ65 ኩንታል በላይ ምርት እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኣካባቢያቸው ለሚገኙና ለመቀሌ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አንዱን  ኩንታል በ600 ብር ሂሳብ እያከፋፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ ከስኳር ድንች ምርትና ቁርጭራጭ በመሸጥ በአሁኑ ጊዜ 75 ሺህ ብር ቆጥበዋል ።

በአካባበቢያቸው ለሚገኙ 30 የሚሆኑ ሴት አርሶ አደሮች  የስልጠና  ድጋፍ ሰጥተዋል ። ሴት አርሶ አደሮቹ የስኳር ድንች ዘር እያለሙ ለገበያ እንዲያውሉና ህይወታቸውን እንዲለውጡ ድጋፍ ማድረጋቸውንም አርሶ አደር  ካልኣዩ ያስረዳሉ ።

በአርሶ አደሩ እገዛ በጨለቆት የገጠር መንደር  የሚገኙ ሴት አርሶ አደሮች በማህበር ተደራጅተው ወደ ስኳር ድንች ልማት ገብተዋል ። የማህበሩ  አስተባባሪ  ወይዘሮ  ትርሃስ ወልዱ  ቁርጥራጭ ስኳር ድንች ማልማት ከጀመሩ ሴት አርሶ አደሮች መካከል አንዷ ናቸው ።

ልማቱ ራሴንና ልጆቼን  የተመጣጠነ ምግብ እንድናገኝ ረድቶናል ። በየዓመቱም ከስኳር ድንች ሽያጭ 15ሺህ ብር ድረስ ገቢ ማግኘት ችያለሁ ብለዋል - ወይዘሮዋ ። ምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ኣልፎ  በተለይም ለህፃናት በሽታ የመከላከል አቅማቸው እንዲያድግና ንቁ  እንዲሆኑ እገዛ እንዳደረገላቸው ተናግረዋል፡፡

በኤርላንድ መንግስት ድጋፍ የሚደረግለት አለም አቀፍ የድንች ማእከል በክልሉ ስኳር ድንች ለማላመድ ላለፉት አምስት አመታት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በተለይም በምገባ ፕሮግራም የሚደገፉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  ስኳር ድንች በምግብነት እንዲለመድ ለህፃናት ተማሪዎች ቀቅሎ የመመገብ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ።

በትግራይ ክልል እርሻና ገጠር ልማት ቢሮ የመስኖ ልማት ንኡስ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ  እንደገለፁት የምግብ ዋስትና እጥረት ባለባቸው ወረዳዎች  አርሶ አደሮች  ስኳር ድንች እንዲያለሙ እየተደረገ ነው ።

በክልሉ የስኳር ድንች በስፋት በመስኖ ማልማት እንዲቻል በአሁኑ ወቅት  አራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ቁርጥራጭ ስኳር ድንች ችግኝ ማከፋፈል ተጀምሯል ብለዋል።

በዚህም  ከ14 ሺህ 600 በላይ የቤተሰብ መሪዎች የስኳር ድንች ምርት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል  ። ለቁርጥራጭ ስኳር ድንች ተክል መግዢያ የሚውል ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ከጀርመን ቴክኒክና ልማት ተራድኦ ድርጅት ድጋፍ ተገኝቷል ።

 ፀረ ድህነት ትግላችን ሊያፋጥኑ የሚችሉ ሀብቶች በእጃችን አሉ ። በአግባቡ ከተጠቀምንበት ያለጥርጥር ድህነት ይሸነፋል ። ስኳር ድንች እየጣፈጠ የህይወት መንገዳችን የሚያጣፍጥ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል ። አማራጩን በንቃት መጠቀም ደግሞ ከእኛ ይጠበቃል ።

Published in ዜና-ትንታኔ

መቀሌ ሚያዚያ 7/2009 በትግራይ ክልል ለህገ ወጥ ተግባር ህጋዊ ከለላ ለመስጠት ጥብቅና የሚቆሙ የህግ ባለሙያዎች በፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠሩ መሆኑን አንድ ጥናት አመላከተ።

ህጋዊነትን የሚጥሱ ጠበቆች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታውቋል፡፡

የክልሉ ፍትህ ቢሮ በ12 ከተሞች በጥብቅና ሥራ የሚተዳደሩ የህግ ባለሙያዎች የሥራ አፈጻጸምን ለመገምገም በቅርቡ ያካሄደውን የ45 ቀን የዳሰሳ ጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል ።

በክልሉ በሚገኙ ከተሞች በጥብቅና ስራ የሚተዳደሩ አንዳንድ የህግ ባለሙያዎች  የሀሰት ምስክሮችን  በማባበል ተጠርጣሪዎችን በነጻ ለማስለቀቅ እንደሚጠቀሙ ጥናቱ አመላክቷል ።

በተጨማሪም ሰዎችን  በማስኮብለል በከባድ ወንጀል የተከሰሱ ተጠርጣሪዎችን ነጻ ለማውጣት በሆስፒታል የተሰጠ የሀሰት የሕክምና ማስረጃዎችን ጠበቆቹ እንደሚጠቀሙ በጥናቱ ተለይቷል ።

ተጠርጣሪዎች ለተከሰሱበት ወንጀል ድርጊቱ በተፈጸመበት እለትና ቦታ እንዳልነበሩ ለማድረግ ያቀረቧቸው የሀሰት ማስረጃዎችም በጥናቱ መገኘታቸው ተመላክቷል።

በተለይ በመቀሌ ከተማ የሚገኙ አንዳንድ የግል ጠበቆች ንብረትና ቤት የሌለው ነጻ መሬት ቤት እንዳለው አስመስለው በማቅረብ የህዝብና የመንግስት ሀብት አላግባብ ወደ ግለሰቦች እንዲተላለፍ ማድረጋቸውን ጥናቱ አመላክቷል።

አንዳንድ ጠበቆችም ላስከፈሉት ገንዘብ ደረሰኝ አለመስጠትና በህግ ከተቀመጠው የቅድመ ክፍያ መጠን በላይ እንደሚያስከፍሉ በጥናቱ ታይቷል ።

እንደ ጥናት ውጤቱ ጠበቆች ደንበኞቻቸው የሚያቀርቡላቸውን መረጃ ለሥራቸው ቢጠቀሙበትም የማስረጃውን ትክክለኛነት የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ልኡል ካህሳይ በበኩላቸው እንደገለፁት "ህብረተሰቡ ባለፈው ዓመት በግል ጠበቆች ላይ ያነሳቸው የነበሩ ቅሬታዎች ዘንድሮ እየቀነሱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

የጥብቅና ሙያ የንግድ ሙያ አለመሆኑን የተናገሩት አቶ ልኡል፣ ጠበቆች ህግ የማስከበር እንዲሁም ፍትሀዊና ሚዛናዊ የህግ ስርአት የማስፈን ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ይህ ሳይሆን ቀርቶ ህገ-ወጥነትን በመከተል ፍትህን ለማደናቀፍ  የሚቆሙ ጠበቆች ካሉ ቢሮው ተገቢ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል ።

የክልሉ የግል ጠበቆች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አብዩ ገብረዋህድ በበኩላቸው "የዳሰሳ ጥናቱ በዝርዝርና በግልፅ መቅረቡ ለቀጣይ ሥራ ትምህርት እንድናገኝ አድርጎናል" ብለዋል፡፡

በጥብቅና ሙያ የሚተዳደሩት ቄስ በላይ ገብረስላሴ በበኩላቸው፣ ለያዙት ጉዳይ ሙያው ከሚፈቅደው ውጭ ክፍያ የሚያስከፍሉ አንዳንድ ጠበቆች በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባ ገልፀዋል።

ላለፉት ሦስት ቀናት በቆየውና የክልሉ ፍትህ ቢሮ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በክልሉ በጥብቅና ሥራ የተሰማሩ ከ300 በላይ የህግ ባለሙያዎች መሳተፋቸው ታውቋል ።

የዳሰሳ ጥናቱ በማረምያ ቤት የሚገኙ ፍርደኞችንና ተገልጋይ የሕብረተሰብ ክፍሎች አስተያየት በናሙናነት ማካተቱ ተመልክቷል።

በተጨማሪም የጠበቆችን የመዝገብና የጉዳይ አያያዝ በመፈተሽ የተካሄደ መሆኑን የክልሉ ፍትህ ቢሮ ባለሙያና የጥናት ቡድኑ አባል አቶ ምስጉን መለስ አስታውቀዋል።

Published in ማህበራዊ

ነቀምቴ ሚያዚያ 7/2009 ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ መረብ በማስገባት የዞኑን ገቢ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የምስራቅ ወለጋ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ።

በዞኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ258 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ታውቋል።

የባለስልጣኑ ምክትል ኃላፊና የግብር ከፋዮች ስልጠና የሥራ ሂደት መሪ ወይዘሮ ጀለኔ በንቲ እንዳስታወቁት፣ ባለስልጣኑ የዞኑን ገቢ ለማሳደግ በየደረጃው ለሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍል የግንዛቤ ትምህርት እየሰጠ ነው።

የሚፈለግባቸውን ግብር በወቅቱ በመክፈል ግንባር ቀደም ለሆኑ ግብር ከፋዮችም የምስክር ወረቀትና የማበረታቻ ሽልማት በመስጠት ሌሎች ግብር ከፋዮችን የማነቃቃት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚንቀሳቀሱ ሕገ ወጦችን ወደ ሕግ ለማቅረብ ከዞኑ ከገበያ ልማት ጽህፈት ቤትና የትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም ወይዘሮ ጀለኔ አመልክተዋል።

ግብርን በወቅቱ መክፈል አስፈላጊነት ላይ በየደረጃው ከሚገኙ የአመራር አካላት፣ የወረዳና የከተማ የገቢዎች ባለስልጣን ጽህፈት ቤቶች፣ የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ጋር በተደረገው ተከታታይ ውይይትም የዞኑ ዓመታዊ ገቢ እያደገ መጥቷል።

እንደ ምክትል ኃላፊዋ ገለጻ በተያዘው በጀት ዓመት ከ400 ሚሊዮን 453 ሺህ ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ የተሰበሰበው ከ258 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ዓመታዊ እቅዱን ማሳካት እንደሚቻል አመላካች መሆኑን ተናግረዋል።

ወይዘሮ ጀለኔ እንዳሉት፣ አብዛኛው ገቢ የተሰበሰበው ከሠራተኛ ደመወዝ ግብር፣ ከንግድ ትርፍ ግብር፣ ከአርሶአደሩ እንዲሁም ቀጥተኛና ቀጥተኛ ካልሆኑ የታክስ ግብሮች ነው።

ከዞኑ የተሰበሰበው ገቢ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ተቀራራቢ ሲሆን ገቢው ዓመታዊ የልማት ወጪን በ23 ነጥብ 74 በመቶ እንደሚሸፍን አመልክተዋል።

በነቀምቴ ከተማ የቀበሌ 03 ነዋሪና የቲጅ ካፌ እና ሪስቶራንት ተወካይ አቶ ተስፋዬ ረጋሳ በሰጡት አስተያየት ድርጅቱ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

"ግብርን በወቅቱ መክፈል ከእዳ ነጻ ከማድረጉም በላይ በመንግስት የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ አቅም ይሆናል" ብለዋል።

"ከግብር የሚሰበሰበው ገቢ ለአገር ልማትና ዕድገት የሚውል ስለሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የምሆነው እኔ ነኝ" ያሉት ደግሞ በከተማው የሙሉ ዳሜ ምግብ ቤት ባለቤት አቶ ጎሹ ዳሜ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ግብራቸውን በወቅቱ ሳይከፍሉ ቀርተው ቅጣት ሲጣልባቸው በመንግስት ላይ ምሬት ሲያሰሙ የነበረበት ሁኔታ ስህተት እንደሆነ በአሁኑ ወቅት መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

የግሎባል ሆቴል ባለቤት አቶ ታረቀኝ ኦላና በበኩላቸው፣ "አንዳንድ ግብር ከፋዮች የመንግስት ሕግና ደንብን ባለማክበር እራሳቸውን ችግር ላይ ሲጥሉ አስተውያለሁ" ብለዋል።

የተጨማሪ እሴት ታክስ ነጋዴውን የሚጎዳበት ሁኔታ እንደሌለ ገልጸው፣ ነጋዴው በእዚህ ራሱ እንደተጎዳ አድርጎ መንግስትን ማማረር አግባብ እንዳልሆነ አመልክተዋል።

እርሳቸው በተፈጠረላቸው ግንዛቤ ተጠቅመው ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ሕጋዊ መረብ ውስጥ እንዲገቡ የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን