×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Friday, 14 April 2017

ደብረብርሃን ሚያዝያ 6/2009 በሰሜን ሸዋ ዞን ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንበታ ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ከሕብረተሰቡ መሰብሰቡን የዞኑ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ እንዳለው፣ ገንዘቡ የተሰበሰበው ሕብረተሰቡ ለግድቡ በቦንድ ግዥና በልገሳ ካደረገው ድጋፍ ነው።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አወቀ ዘነበ ለኢዜአ እንደገለጹት ሕዝቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል።

ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ በቦንድ ግዥና በልገሳ ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ከሕብረተሰቡ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

የግድቡ ግንባታ ዳር እንዲደርስም ሕብረተሰቡ በገንዘብ እያደረገ ካለው ድጋፍ በተጨማሪ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ 422 ሚሊዮን ብር የሚገመት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ማከናወኑንም ነው የጠቆሙት።

ለግድቡ ግንባታ ቀደም ሲል የጀመሩትን ድጋፍ የበለጠ አጠናክረው ለመቀጠል መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ስንታየሁ ደምሴ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከሁለት ወር ደመወዛቸው በተጨማሪ የ300 ብር ቦንድ በመግዛት ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በመንግስት ሥራ አመራርነት ሲያገለግሉ ከሕብረተሰቡ በልገሳ ያገኙትን ስድስት ግራም ወርቅ ለግድቡ ግንባታ እንዲውል በልገሳ መስጠታቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ዘበነ ማንደፍሮ የተባሉ የደብረ ብርሀን ከተማ ነዋሪ ናቸው።

"በዚህ ዓመት በአንድ ወር ደመወዜ ቦንድ በመግዛት ቀደም ሲል የጀመርኩትን ድጋፍ አጠናክሬ ለማስቀጠል አቅጂያለሁ" ብለዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አማረ ገብረዮሐንስ በበኩላቸው፣ "ግድቡ አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ከመሆኑም በተጨማሪ በአባይ ወንዝ ላይ በፍትሀዊነት የመጠቀም መብታችንን ያረጋገጥንበት ነው" ብለዋል።

የከተማው ንግድ ማህበረሰብ በተለያየ ጊዜ ካደረገው ድጋፍ በተጨማሪ የሕዳሴው ዋንጫ ወደከተማው በመጣበት ወቅት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

የግድቡ ግንባታ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ለማድረግ የንግዱ ማህበረሰብ በተያዘው በጀት ዓመትም የ100 ሺህ ብር ቦንድ ለመግዛት መወሰኑን ጠቁመዋል።

በሰሜን ሽዋ ዞን ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ከመንግስት ሠራተኛው፣ ከነጋዴው፣ ከባለሀብቱና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክልፍሎች  ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በማሰባሰብ ለግድቡ ግንባታ እንዲውል ተደርጓል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ሚያዝያ 6/2009 በሙስና ድርጊቱ ተሳታፊ ሆነው በተገኙ አካላት ላይ ተገቢ እርምጃ እንደሚወሰድ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ 59 ወረዳዎችና 12 ዋና ዋና ከተሞች በሙስናና በሕብረተሰቡ ግንዛቤ ላይ አተኩሮ ያካሄደውን ጥናት ትናንት ይፋ አድርጓል። 

የጥናቱ ውጤት ትናንት በአዳማ ከተማ ይፋ በተደረገበት ወቅት የተገኙት የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ እንደገለጹት በክልሉም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ሙስና መልኩን እየቀየረና እየተስፋፋ መጥቷል።

በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ወረዳዎች የተካሄደው ጥናትም ሙስና በክልሉ ለሕብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ዕድገት ማነቆ መሆኑን በግልጽ ያሳየ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሙስና በክልሉ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ከመሆኑ በተጨማሪ ህዝብን ለምሬትና ለቅሬታ እየዳረገ በመምጣቱ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ጥናቱ ጠቃሚ መሆኑን ነው የገለጹት።        

"የጥናቱ ውጤት በዋናነት ችግሩ የት ላይ እንደሆነ አሳይቶናል" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የፍትህ አካላት በሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ፍትህ በማጓደል በሕብረተሰቡ ላይ ተደራራቢ ወንጀል እየፈጸሙ ስለመሆኑ ጥናቱ ማመላከቱን አስታውቀዋል።

ችግሩን ለማስወገድ የጥናቱን ውጤት መሰረት በማድረግ በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት አባቶችና መላውን ሕብረተሰብ ያሳተፈ ሥራ እንደሚከናወን አስረድተዋል።

ሙስና ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማነቆ ከመሆን ባለፈ የመልካም አስተዳደር እጦት መንስኤ እየሆነ በመምጣቱ በድርጊቱ ተሳታፊ ሆነው በተገኙ አካላት ላይ ተገቢ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።

እንደ አቶ ለማ ገለጻ በፍትህ ተቋማት፣ በገቢዎች፣ በግብርና ታክስ፣ በግዥ አስተዳድር፣ በመሬት፣ በመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በሌሎች ተያያዥ ሴክተሮች ላይ ሕብረተሰቡ አገልግሎትን በገንዘብ እየገዛ ስለመሆኑ ጥናቱ አመልክቷል።

በተጨማሪም "ጥናቱ ሙስናን የማይሸከም ተተኪ ትውልድ ማፍራት እንደሚገባ የጠቆመ ጥናት ነው ሲሉም " ተናግረዋል።

የጥናቱን ውጤት ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የምርምር ቢሮ ዲን ዶክተር አለሙ ዲሳሳ፣ ጥናቱ ሙስና በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የማወቅና ለቀጣይ መፍትሄ የማፈላለግ ዓላማ አንዳለው አመልክተዋል።

በአመለካከትና በተግባር  ችግሩ በስፋት የሚታይባቸው አካባቢዎች ላይ ሕብረተሰቡ ያለውን ዕውቀት፣ ግንዛቤና አመለካከትን በመለየት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመፍታትም ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል።

ዶክተር አለሙ እንዳሉት፣ ጥናቱ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎች፣ የችግሩን ምንጭ እንዲሁም ሙስና የሚያስከትለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ  ጉዳቶችን  አመላክቷል።

በዚህም የፍትህ፣ የገቢዎች፣ የመሬት አስተዳድር፣ የግዥ ዘርፍ፣ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት፣ የጤና ተቋም፣ የልማት ድርጅቶችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙስና በስፋት የሚታይባቸው ተቋማት እንደሆኑ መለየታቸውንና በመንግስት ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ሴክተሮች መሆናቸው ተረጋግጧል።

ሕብረተሰቡም በሙሰኞች ላይ አስተማሪ እርምጃ ሲወሰድ አለማየቱ "ለውጥ አይመጣም" የሚል ተስፋ የመቁረጥ አዝማሚያ በስፋት እየያዘ መምጣቱ በጥናቱ በግልጽ መለየቱንም ጠቁመዋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራ ጎን ለጎን የሥርአቱ አደጋ የሆነውን ሙስናን ለማስወገድ በሚደረግው ጥረት ውስጥ ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን በጥናት የተደገፉ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥናቱ በራሱ ግብ እንዳልሆነ የተናገሩት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሁሴን ኡስማን ናቸው።

"በጥናቱ ሙስና ይስተዋልባቸዋል ተብለው በተለዩ ዘርፎች ላይ በአሰራርና አደረጃጀት የተደገፉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥና ጠንካራ ህጋዊ እርምጃዎች መወሰድ ይገባል" ብለዋል ።

ጥናቱ የክልሉ መንግስት በመደበው አምስት ሚሊዮን ብር የተካሄደ ሲሆን የጥናቱ ውጤት ትናንት በአዳማ ከተማ ይፋ ሲደረግ ከ800 በላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ መንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የዞንና የከተማ አስተዳድርና ከንቲባዎች ተገኝተዋል።

Published in ፖለቲካ

አክሱም ሚያዝያ 6/2009 በአክሱም ከተማ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ132 አቅመ ደካሞች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ድጋፉ ከተደረገላቸው መካከል ችግረኛ የሆኑ  አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች እንደሚገኙበት የከተማው የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ገልጿል፡፡

በጽሕፈት ቤቱ የማህበረሰብ ጥምረትና እክብካቤ ባለሙያ ወይዘሮ ስላስ ብርሃነ ለኢዜአ እንደተናገሩት አቅመ ደካሞቹ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ታስቦ ድጋፍ ከተደረገው ውስጥ 24 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ ነው፡፡

በተጨማሪም 24 ሺህ ብር ግምት ያላቸው የምግብ እህልና አልባሳት እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡

ድጋፉ የተገኘው በከተማው በተደራጀው  የማህበረሰብ ጥምረት ማህበር አማካኝነት ከነዋሪው ህዝብ ተዋጥቶ የተሰባሰበ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በከተማው የክንደያ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሰፈሩ ወልደማረያም ድጋፍ ከተደረገላቸው አካል ጉዳተኞች መካከል አንዱ ሲሆኑ ምንም አይነት ገቢ እንደሌላቸውና በበዓሉ  ምክንያት  በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

" 60 ኪሎ የስንዴ ዱቄትና 300 ብር ተሰጥቶኛል " ብለዋል።

የከተማው ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ህብረተሰቡን በማስተባባር  ለችግር ለተጋለጡ ሁለት ሺህ 453  ሰዎች  አምስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የገንዘብና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማደረጉም ተመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

ዲላ ሚያዚያ  6/8/2009 ተገቢ ያልሆነ የበዓል ወጪዎችን በመቀነስ የቁጠባ ባህልን ማዳበር እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

 ነዋሪዎቹ እንዳሉት በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ በሚል ምክንያት ብዙ ሰዎች ያለዕቅድ ብድር ውስጥ ጭምር ገብተው በቀላሉ ለማይወጡት ዕዳ ይዳረጋሉ።

 የከተማዋ ነዋሪ አቶ ማርያም ጎበና እንዳሉት ሕብረተሰቡ አውዳመትን ምክንያት በማድረግ ለአንድ ቀን ብዙ ገንዘብ በማውጣት ከበዓል በኋላ ሲቸገር ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡

 " በወጪ ብዛት የማመጣው ደስታ የለም፤ ከበዓል በኋላ ላለው ጊዜም አርቄ ስለማስብ ለፍቼ ያገኘሁትን ገንዘብ አላግባብ አላባክነውም " ብለዋል፡፡

 ለአንድ ቀን በዓል በሚል ብድርና ዱቤ በመውሰድ ዕዳ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ሕብረተሰቡ ከሚያገኘው ገንዘብ ላይ በመቆጠብ ለነገ መሰረት የሚሆን ነገር ማቆየት እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

 የዲላ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ታምራት ወያ በበኩላቸው፣ በአካባቢያቸው ለበዓል ወጪ ተብሎ ከወራት በፊት በእድርና በእቁብ መልክ በየሳምንቱ ገንዘብ የማሰባሰብ ልምድ መኖሩን አስታውሰዋል፡፡

 " የበዓል ወጪን አስቀድሞና አስቦ ማጠራቀሙ ጥሩ ተሞክሮ ቢሆንም ገንዘቡን ለበዓል ብቻ ማዋሉ ብክነት ስለሚሆን ቀንሶ በመጠቀም ቁጠባው ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል" ብለዋል፡፡

 በከተማው የበዴቻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ የምስራች ከበደ በበኩላቸው በዓሉን ከጎረቤቶቻቸው ጋር እንዲሁም በአካባቢያቸው ካሉ ወላጆቻቸውን ካጡ ሕጸናት እና ጧሪ ከሌላቸው አረጋውያን ጋር ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

 ሁሌም አቅማቸው በፈቀደ መጠን ከችግረኞች ጋር በዓልን እንደሚያከብሩና ይህም ደስታ እንደሚፈጥርላቸው የገለጹት ወይዘሮ የምስራች፣ ይህንን የሚያደርጉት የአብሮነትና መረዳዳት ባህልን ለማስቀጠል ብለው እንደሆነ ገልጸዋል።

 የወንዶች ፀጉር በማስተካከል ሥራ የሚተዳደረው ወጣት ማቴዎስ ቴማ በበኩሉ ከቤተሰቦቹ ርቆ እንደሚኖርና በዓሉን የተለያየ እምነት ተከታይ ከሆኑ ጓደኞቹ ጋር በጋራ እንደሚያሳልፍ ተናግሯል፡፡

 ብዙ ወጣቶች በዓላትን ከልክ በላይ በመጠጣት እና ገንዘባቸውን ያለአግባብ በማጥፋት በቀጣይ ቀናት ወደ ብድር ሲገቡ ታዝቢያለሁ ያለው ማቲዎስ፣ ወጣቶች ለበዓል አላስፈላጊ ወጪዎችን በመቀነስ የቁጠባ ባህልን ቢያዳብሩ የተሻለ መሆኑን

Published in ማህበራዊ

ደሴ ሚያዝያ 6/2009 በደሴ ከተማ ህገ ወጥ የጎዳናና የቤት ውስጥ ንግድ ለማስቆም በተደረገ እንቅስቃሴ ከአንድ ሺህ በላይ ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደህጋዊ መስመር ማስገባት ተቻለ።

የከተማዋ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ እንዳስታወቀው ለአንድ ወራት በተደረገ የንቅናቄ ዘመቻ ነጋዴዎቹን በማስተማር ህጋዊ መስመሩን እንዲከተሉ ማደርግ ተችሏል።

የመምሪያው ምክትል ኃለፊ አቶ ሳሙኤል አሰፋ እንዳስታወቁት በከተማዋ ህገ ወጥ የጎዳናና የቤት ውስጥ ንግድ መስፋፋቱ በከተማዋ ገቢ ላይ ተጽእኖ ፈጥሮ ቆይቷል።

ህገወጥ ንግዱ የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ ከመግታት ባለፈ ጽዳት እና ውበቷ እየተበላሸ እንዲመጣ ማድረጉንም አስታውሰዋል።

በተጨማሪም ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴው ህግ አክብረው በሚሰሩ ነጋዴዎች ህልውና ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደነበረው ነው አቶ ሳሙኤን የገለጹት፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ካለፈው የካቲት 15 ቀን 2009 ዓ ም ጀምሮ በተደረገ ንቅናቄ በዋና ዋና የከተማዋ መንገዶች ላይ ይካሄድ የነበረውን ህገወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ሙሉ በሙሉ ማስቆም መቻሉን ገልጸዋል።

በእዚህም በህገ ወጥ ንግድ ተሰማርተው የነበሩ ከ1 ሺህ 200 በላይ ግለሰቦች ውስጥ 38ቱ በራሳቸውና በተከራዩት ሱቅ ንግድ ፈቃድ አውጥተው ሲሰሩ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ አማራጭ የመሸጫ ቦታ ተዘጋጅቶላቸው ህጋዊ የንግድ ቀረጥ እየከፈሉ እንዲሰሩ ማድረግ ተችሏል።

ንግድ ፈቃድ ሳይኖረቸውና ፈቃዳቸውን ሳያድሱ በራሳቸው ቤት በንግድ ሥራ ተሰማርተው የነበሩ 398 ነጋዴዎች ከጽሁፍ ማስጠንቀቂ ጀምሮ እስከ 4ሺህ ብር በሚደርስ ቅጣት እንዲቀጡ መደረጉንም አቶ ሳሙኤል ስረድተዋል። 

“የተወሰደው ርምጃ ቢዘገይም ለህጋዊ ነጋዴዎች ዋስትና የሰጠ በመሆኑ እንደግፈዋለን” ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማሕበራት ዋና ፀኃፊ ወይዘሮ አረጋሽ ደምሴ ናቸው፡፡

“በከተማዋ ህገ ወጥ የጎዳና ንግድ መስፋፋቱ ህጋዊ ነጋዴው ዘመናዊ የግብይት ስርአቱን ተጠቅሞ ገቢውን እናዳያሳድግ አድርጎት ነበር” ብለዋል።

ህገወጥነትን መከላከል ለአንድ ሰሞን ብቻ የሚከናወን ሳይሆን ተጠናክሮ የሚቀጥል ሥራ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የጎዳና ላይ ንግድ ከዋና ዋና መንገዶች ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ መደረጉ የትራፊክ እንቅስቃሴው አደጋን መቀነስ በሚያስችል መልኩ የተሻለ ፍሰት እንዲኖረው ማስቻሉን ዋና ሳጅን መስፍን መናገራቸውን የዘገበው የኢትዮያ ዜና አገልግሎት ነው።

Published in ኢኮኖሚ

አዲሰ አበባ  ሚያዚያ  6/2009 የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል በዛሬው ዕለት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ተከብሮ ውሏል።

 ዕለቱ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን የተቀበላቸው መከራዎችን በማሰብ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና በዝማሬ ተከብሯል።

 በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያና ምዕመናን "ኪራላይሶን፣ አቤቱ ጌታ ይቅር በለን" በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅለትን በስግደት አስበውታል።

 የክርስትና እምነት ተከታዮች ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያሳየውን ትህትናና ፍቅር እርስ በእርስ በመዋደድ በዕለት ተእለት ኑሯቸው እንዲተገብሩት የአብያተክርስቲያናቱ የእምነት አባቶች አሳስበዋል።

 ክርስቶስ ለሰው ልጆች ስላየው ስቃይ፣ ግርፋትና መስዋትነት እንዲሁም ስላሳየው ፍቅርና ትህትና በመስበክ ምዕመኑ እርስ በእርሱ መደጋገፍና መተሳሰብን ሊማር ይገባል ነው ያሉት።

 በህዝቦች መካከል ልዩነት ሳይኖር ይቅር በመባባል፣ በመጠያየቅና በመቻቻል ክርስቶስ ያሳየው ቻይነት በህይወታችን መገለጽ አለበት ብለዋል።

 ምዕመኑ የክርስቶስን ትንሳኤ ሲያከብርም በምግብና በመጠጥ ብቻ ሳይሆን የተቸገሩትን በማሰብ ጭምር ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 6/2009 ከሰሞኑ አብዛኞቹ የአዲስ አበባ ነዳጅ ማደያዎች ቤንዚን ለመቅዳት በተሰለፉ ተሽከርካሪዎች ተጨናንቀው ታይተዋል።

በዛሬው ዕለትም በሜክሲኮ፣ በብሔራዊ ቴአትር፣ በካዛንቺስ፣ በፒያሳ፣ በአራት ኪሎና በሌሎችም የከተማዋ ክፍሎች የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች የቤትና የንግድ ተሽከርካሪዎችን ረጅም ሰልፍ ሲያስተናግዱ ውለዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች ነዳጅ ለማግኘት መቸገራቸውን ገልጸዋል።

ከአያት ነዳጅ ለመቅዳት ካዛንቺስ አካባቢ ባለው ማደያ ወረፋ ሲጠብቅ ያገኘነው አሽከርካሪ ዳግም ስንታየሁ በየማደያዎቹ ነዳጅ ለማግኘት መቸገሩንና ረጅም ጊዜ ለመጠበቅ መገደዱን ይገልጻል።

በየነዳጅ ማደያው የቤንዚን እጥረት እንዳለና በዚህም ምክንያት አሽከርካሪዎች ለእንግልትና መጉላላት እየተዳረጉ መሆኑንም ተናግሯል። 

ከቡልጋሪያ ማዞሪያ አካባቢ ነዳጅ ለመቅዳት የመጣው ሌላው ወጣት ዘመተ ንጉሱ በበኩሉ አሽከርካሪዎች ብዙ ጊዜ የነዳጅ እጥረት የሚያጋጥማቸው በየወሩ መጀመሪያ ላይ ነው ይላል።

ጉዳዩን አስመክልቶ በስልክ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሚካኤሌ ገብረህይወት በመዲናዋ የነዳጅ ማደያዎች የሚታየው የአሽከርካሪዎች መጨናነቅ የተከሰተው ከሱዳን ነዳጅ ይዘው የሚመጡ ተሽከርካሪዎች "ከጎንደር -ባህርዳር" ያለው መንገድ ጥገና ላይ ስለሆነ ቤንዚን በወቅቱ መድረስ ባለመቻሉ ነው ብለዋል።

ነዳጁን ወደ አዲስ አበባ ለማድረስ ሌላ አማራጭ መፍትሔ አልወሰዳችሁም ወይ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ችግሩን ለመፍታት በጊዜያዊነት የነዳጅ ቦቴዎች በደብረ ታቦርና በደሴ በኩል ያለውን አማራጭ መንገድ ተጠቅመው እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የመንገድ ጥገናውን አስመልክቶ "በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንና በአማራ ክልል መንገዶች ቢሮ መካከል የተፈጠረ የመረጃ ክፍተትና አለመናበብ'' በነዳጅ ማመላለስ አገልግሎት ላይ ችግር ማስከተሉን ተናግረዋል።

በወቅቱ የደረሰው ቤንዚን ከኢታኖል ጋር ፈጥኖ እንዲደባለቅና ለገበያም እንዲቀርብ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አንድ የቁጥጥር ቡድን በማቋቋም እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ችግሩ በነገው ዕለት ይፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅና አሽከርካሪዎች በትዕግስት እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ባህርዳር የሚገኘው የአባይ ድልድይ ጥገና ላይ በመሆኑ ነዳጁን አማራጭ መንገድ በመጠቀም ወደ አዲስ አበባ እንዲያስገባ በደብዳቤ በመጻፍ መግለጹን ለኢዜአ አስታውቋል።

ነዳጁን የሚያመላልሱት ተሽከርካሪዎች የደልጊ፣ ቁንዝላና ዱርቤቴ መንገዶችን እንዲሁም የኮምቦልቻ፣ መካነሰላምና ግንደወይን መንገዶችን እንዲጠቀሙ ማሳወቁንም እንዲሁ።

የድልድዩ ጥገና በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆንም ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ከሳምንት በፊት ባለስልጣኑ የሰጠውን መረጃ ዋቢ በማድረግ ባህርዳር የሚገኘው የአባይ ወንዝ ድልድይ ጥገና ላይ መሆኑንና ከ20 ቶን በላይ ክብደት ያላቸውን ተሽከርካሪዎች ሌሎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ማሳሰቡን መዘገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትን በተደጋጋሚ በስልክ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

የኢዜአ ሪፖርተር በካዛንቺስና አራት ኪሎ የሚገኙ አንዳንድ ነዳጅ ማደያዎች ለአሽከርካሪዎች ቤንዚንና ናፍጣ የለም በማለት አሽከርካሪዎችን ሲመልሱ የተመለከተ ሲሆን፤ የተወሰኑትም ከነጭራሹ አገልግሎት እንደማይሰጡ ታዝቧል።

Published in ኢኮኖሚ

ጅማ  መጋቢት 6/2009 በ23ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ጅማ ከተማ ላይ ትናንት የተገናኙት ጅማ አባ ቡናና  አዳማ ከተማ አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ተለያዩ ።

 በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ደግሞ ጅማ ከተማ ተጋጣሚው ናሽናል ሲሚንቶን 5ለ2 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል፡፡

 ጅማ አባ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ሲጠናቀቅ ዳዋ ሁቴሳ በ34ኛው ደቂቃ ለአዳማ ከተማ ሲያስቆጥር በድሉ መርዕድ ደግሞ ለጅማ አባ ቡና በ87ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥሯል።

 ጅማ አባቡና የመጀመሪያውን ግማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተጋጣሚው አዳማ ከነማ     የበላይነት ተወስዶነበት ነው፡፡

 ተጭነው የተጫወቱት አዳማዎች በ34ኛው ደቂቃ ባስቆጠሩዋት  አንድ ግብ  በመሪነት ለእረፍት መውጣት ችለው ነበር ።

 በ39ኛው ደቂቃ ላይ ክርስቶፈር ኒታንቢን በዳዊት ፍቃዱ ቀይረው ያስገቡት ጅማ አባቡናዎች የጨዋታውን ሚዛን ለማመጣጠን ያደረጉት ጥረት ሰምሮላቸው የማታ ማታ ውጤት ተጋርተው ለመውጣት ጠቅሟቸዋል።

 ጅማ አባቡና  በሁለተኛው ግማሽ ስህተቶችን አርሞና ተጠናክሮ ወደ ሜዳ  በመግባቱ መጠነኛ የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ችሏል፡፡

 በተለይ የአጥቂ መስመር ተጨዋቹ መሃመድ ናስር ያለቀላቸው ሁለት ጎል የሚሆኑ  ኳሶችን ያገኘ ቢሆንም ሳይጠቀምበት የቀረበት ክስተት የአባቡና ደጋፊዎች ያስቆጨ ነበር፡፡

 በ80 ደቂቃ መሃመድ ናስርን ቀይሮ የገባው በድሉ መርዕድ በ87ኛው ደቂቃ ለራሱ የመጀመሪያውን ክለቡን ደግሞ አቻ ያደረገው ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

 አባቡና 1 ነጥብ ማግኘቱን ተከትሎ በ24 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ አዳማ ከነማ በ36 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

 በ18ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ጅማ ላይ ጨዋታውን ያደረገው ጅማ ከተማ በተመስገን ገብረኪዳን ሃትሪክ፣ በሮቤል አስራትና በሄኖክ መሀሪ አንዳንድ ጎል ናሽናል ሲሚንቶን   5ለ2 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ መሪነቱን ያጠናከረበትን ውጤት አስመዝግቧል፡፡

 የናሽናል ሴሜንቶ  ሁለት ጎሎች የተቆጠሩት በፈረሃን ሰይድ  አማካኝነት ነው፡፡

 ጅማ ከተማ በከፍተኛ ሊግ ምድብ "ለ"ን  በ30 ነጥብ እየመራ ይገኛል፡፡

Published in ስፖርት

ድሬደዋ ሚያዝያ 6/2009 በድሬዳዋ አስተዳደር አራት ቢሊዮን ብር በሚጠጋ በጀት እየተገነባ የሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርክ ለወደብ ቅርብ መሆኑ ተመራጭነቱ እንደሚያጎላው  የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ፡፡

በኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ የተመራ የፌደራል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና  የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ባለፈው መጋቢት በድሬዳዋ የተጀመረው የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታን ትናንት ተመልክተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ እንደገለጹት የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ  በእቅዱ መሰረት  እየተካሄደ ነው፡፡

" ፓርኩ ለወደብ ቅርብ በመሆኑ የሀገርና የውጭ ሀገር ባለሃብቶችን ቀልብ እየሳበ  ተመራጭነቱን ያጎላዋል" ብለዋል፡፡

የግንባታው የመጀመሪያ ምዕራፍ በመጪው ታህሳስ ተጠናቆ 15 ግዙፍ ማምረቻዎች ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆኑ የጠቆሙት አቶ  ፍፁም "ይህም ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ በመግባት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጉዞ እንዲሳካ ያግዛሉ "ብለዋል፡፡

በድሬዳዋ መልካ ጀብዱ ቀበሌ አራት ቢሊዮን ብር በሚጠጋ በጀት በሶስት ምዕራፍ ተከፍሎ በ4ሺህ 100 ሄክታር መሬት የሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርኩ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በ150 ሄክታር መሬት ላይ ነው እየተከናወነ የሚገኘው፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው "ፓርኩ ድሬዳዋ የሀገሪቱ የምሥራቅ ክፍል የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ ያስችላል" ብለዋል፡፡

በተለይ ፓርኩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቆ አገልግሎት ሲጀምር ለብዙ ሺህ ዜጎች ከሚፈጥረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ የቴክኖሎጂ ሽግግርን  ለማስፋት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ አይነተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ፓርኩ ለጅቡቲና ለበርበር ወደቦች ቅርብ መሆኑ ተመራጭነቱ የጎላ ነው፡፡

ግንባታውን በሚያካሂደው የቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን (ሲሲኢሲሲ) አመራሮች የፓርኩን የስራ  ሂደት ለተመለከቱት የስራ ሃላፊዎች  ገለጻ አድርገዋል፡፡

የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ እስካሁን ለ1ሺህ 500 ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን  ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም 65 ሺህ ለሚሆኑ  ዜጎች የሥራ እድል እንደሚያስገኝ ይጠበቃል፡፡

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት መታቀዱን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ኢኮኖሚ

ሚያዝያ 6/2009 4ኛው የኢትዮ-አልጀሪያ የሚኒስትሮች የጋራ ጉባኤ በአልጀርስ በተካሄደበት ወቅት ሁለቱ ሃገራት አምስት የጋራ የትብብር ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡

የአልጀሪያ ፕረስ አገልግሎት እንደዘገበው ስምምነቱ የተፈረመው በኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እና በአልጀሪያው የውጭ ጉዳይና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራ መካከል ነው፡፡

ከስምምነቶች መካከል ሶስቱ በንግድ፣ በኮሙኒኬሽን፣ የአትክልትና የእጽዋት ዘር እንዳይበላሹ አስቀድሞ መከላከል በሚቻልበት ዙሪያ ሁለቱ ሃገራት በጋራ መስራት የሚያስችሉ ናቸው፡፡

ሁለቱ ስምምነቶች ደግሞ በእንስሳት፣ በአሳና  በውሀ  ሃብት ላይ ሃገራቱ በጋራ መስራት የሚያስችላቸው ነው ፡፡

የአልጀሪያ የውጭ ጉዳይና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራ በዚሁ ጊዜ የስምምነቶቹ መፈረም የኢትዮጵያ እና የአልጄሪያን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማሳደግ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትና የፖለቲካ ግንኙነታቸውንም የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡ የሁለቱን ሃገራት ሁለንተናዊ ግንኙነትና አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስም ስምምነቶቹ ወሳኝ መሆናቸውን አንስተዋል ሚኒስትሩ፡፡

ለስምምነቶቹ ውጤታማነት መትጋት የያስፈልጋል ያሉት ላማምራ የግል ባለሃብቱን በማሳተፍ በሁለቱ ሃገራት መካከል የልምድ ልውውጥ በማድረግ በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታዎች የሁለቱ ሃገራት መንግስታት ሊያመቻቹ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው 4ኛው የሚኒስትሮች የጋራ ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረገው የሃገሪቱ መንግስት ምስጋናቸውን አቅርበው በጋራ ጉባኤው ላይ የሁለቱን ሃገራት ሁለንተናዊ አጋርነትና ወዳጅነት ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችሉ ፍሬያማ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

አምስቱ ስምምነቶቹም በሃገራቱ ያሉ ህዝቦችን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን  አረጋግጠዋል፡፡

 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን