አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 13 April 2017

አሶሳ ሚያዝያ 5/2009 የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በክልሉ ተደራሽ መሆኑ ከመልካም አስተዳደርና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን በአፋጣኝ ለማረም እንደሚያግዝ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳደር አስታወቁ።

ተቋሙ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ሰባተኛ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን ከፍቷል።

የጽህፈት ቤቱን መከፈት ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የፓናል ወይይት ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሃሰን እንደገለጹት፣ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባልተከበሩበት ሁኔታ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው አገራዊ እድገት ማምጣት አይቻልም።

ስለሆነም መንግስት የሕዝብ እንባ ጠባቂና መሰል የዴሞክራሲ ተቋማትን በማቋቋም ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በህግ የበላይነት የሚመራ፣ ዴሞክራሲያዊና ግልጽነትን የተላበሰ የመንግስት አስተዳደር ስርዓት ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ለሚመዘገቡ ውጤቶች የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ሚና የጎላ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል፡፡

ተቋሙ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን በክልሉ መክፈቱ በየደረጃው የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች በማረም አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት ለሚደረገው ጥረት አጋዥ በመሆኑ በክልሉ በኩል ጽህፈትቤቱን ለማጠንከር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የሕዝብ ዋና እንባ ጠባቂ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው መንግስት ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ስርዓት እንዲረጋገጥ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመታት የመልካም አስተዳደር ጉዳይን ዋንኛ አጀንዳ አድርጎ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ የተደረገው ጥልቅ የተሃድሶ ግምገማ መልካም አስተዳደርን ማስፈን የሚያስችሉ እርምጃዎች የተወሰዱበት እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

"በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር መፍታት ከተቻለ አስፈጻሚ አካላት ለህብረተሰቡ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት በመስጠት የዜጎችን እርካታ በማሳደግ አገራዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል" ብለዋል፡፡

የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከአሶሳ ከተማ በተጨማሪ በመቀሌ፣ በባህር ዳር፣ በሃዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በጋምቤላና በኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከፍቶ እየሰራ ነው፡፡

በቅርቡም ስምንተኛ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን በአፋር ክልል ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዳማ ሚያዝያ 5/2009 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በአንድነት በማሰለፍ ለልማት ተነሳሽነት መጎልበት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የጨፌ ኦሮሚያ አፈጉባኤ ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የህዳሴ ግድብ የመሠረተ ድንጋይ የተቀመጠበት ስድስተኛ ዓመት የማጠቃለያ  መርሃ ግብር ዛሬ በሻሸመኔ ስታዲዮም በልዩ ልዩ ዝግጅት ተከብሯል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት አፈ ጉባኤው አቶ እሼቱ ደሴ እንደገለጹት  በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁሉም  ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እያደረጉት ያለው ተሳትፎ የሚደነቅ ነው። 

የግድቡ መገንባት የሀገሪቱን የድህነት ታሪክ በመሻር ወደ እድገት ማማ የሚያሸጋግራትና በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ እውቅናን የሚያሰጣት መሆኑንም ተናግረዋል።

ህዝቦችን በአንድነት በማሰለፍ ለልማት ተነሳሽነት መጎልበት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸው በክልሉም የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን ቀን አስመልክቶ ተከታታይ የሆኑ  ህዝባዊ የንቅናቄ ስራዎች  በየደረጃው መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው አፈጻጸሙም ከእቅዱ በ300 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

አፈ ጉባኤው እንዳሉት ክንውኑ ከእቅድ በላይ የሆነው በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚ አካላት ተቀናጅተው ጠንካራ ቅስቀሳ በማድረጋቸውና የክልሉ ህዝብ ለግድቡ ላቅ ያለ ትርጉም በመስጠት ነቁ ተሳትፎ በማድርጉ ነው።

የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ እውን መሆን የሀገሪቱን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሃይል ማመንጫ ግድቡ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው ባሻገር የአይቻልም መንፈስ በመስበር  የትኛውንም ከባድ አገራዊ የልማት አጀንዳ  ከህዝብ  ጋር መወጣት እንደሚቻል  ማሳያ መሆኑን አውስተዋል።

"የሻሸመኔ ከተማ ህዝብ በከተማውም ሆነ በአገር ልማት ላይ በጎ አስተዋዕኦ በማድረግ የሚታወቅ ነው " ያሉት ከንቲባዋ ይህንኑ መልካም  ልምድ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በከተማው የአቦስቶ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ከድር በሰጡት አስተያየት እንደዚህ ዓይነቱ ዝግጅት መካሄዱ ለግድቡ ግንባታ አሻራቸውን እንዲያሳርፉና የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ ያነሳሳቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በማስመልከት በግላቸው ለሶስተኛ ጊዜ የሁለት ሺህ ብር የቦንድ ግዥ መፈጸማቸውንም ጠቅሰዋል።

ተማሪዎችን ጨምሮ በርካታ የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት በዓሉ በኦሮሚያ ማርሽ ባንድ፣በሰርከስ ትርኢትና በሌሎችም ዝግጅቶች ታጅቦ በደምቀት ተከብሯል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ሚያዚያ 5/2009 በአማራ ክልል ከቱሪዝም ሃብት የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲዎች አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ለይቶ ለማልማት የሚያስችሉ ምርምሮችን ማካሄድ እንደሚጠበቅባቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አስታወቁ ።

የክልሉ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ትናንት ተጠናቋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርና የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደገለጹት ክልሉ የበርካታ የቱሪስት መስህቦች ባለቤት ቢሆንም ከዘርፉ የሚፈለገው የኢኮኖሚያዊ ጥቅም እየተገኘ አይደለም ።

በተለይ ታሪካዊ ይዘት ያላቸውን አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በመለየትና በማልማት ለአገልግሎት እንዲውሉ በማድረግ በኩል ያለው ክፍተት ለችግሩ ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች ክፍተቱን ለመሙላት ያላቸውን ሃብት፣ እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ለዘርፉ እድገት የሚበጁ አዳዲስ ጥናትና ምርምሮችን ቀጣይነት ባለው መልኩ ማካሄድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የቱሪስት መስህብ ሀብቶችን እውቀትን መሰረት ባደረገ መልኩ ለማስተዋወቅ ተቋማቱ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

"ክልሉ የበርካታ ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች ባለቤት እንደመሆኑ ዘርፉን ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለገቢ ማስገኛ ኢንዱስትሪነት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ያሉት" አቶ ገዱ፣ በዚህ በኩል የትምህርት ተቋማቱ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል ።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሒሩት ካሳው  በበኩላቸው ወደክልሉ የሚመጡ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስት ፍሰትና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል ።

በዚህም ባለፈው ዓመት  በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ከጎበኙ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚጠጉ ቱሪስቶች ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል።

በየመዳረሻ ቦታዎች ለጎብኚዎች የሚመጥኑ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች መገንባታቸውና የተሻለ አገልግሎት መኖሩ ለዘርፉ እድገት አስተዋጾ ማድረጉን ጠቁመዋል ።

"በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ የጎብኚዎችን ቁጥር ወደ 12 ሚሊዮን ለማሳደግና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለማድረስ እየተሰራ ነው" ብለዋል ።

የቱረዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ተቋቁሞ የመስህብ ሀብቶችን የመለየትና የማልማት ክፍተቶችን በቅንጅት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል ።

ከዚሁ ጎን ለጎን ለሀብቱ ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ነው ዶክተር ሂሩት የገለጹት።

የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳነት ዶክተር ዓለማየሁ ከበደ በበኩላቸው የኒቨርስቲው 22 አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በመለየት እንዲለሙ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም አጼ ቴዎድሮስ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋፋት መድፍ የሰሩበትን ቦታ በማልማት ለጎብኚዎች ክፍት አንዲሆን መንገድ በመስራትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

"የዘረፉን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር የታገዘ ሥራ መስራት  አለብን" ሲሉም ተናግረዋል።

በጉባኤው ላይ የክልልና የከተማ አስተዳደር አካላት፣ በክልሉ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ በለሀብቶችን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 5/2009 በመደበኛ የህግ አሰራር ህግና ስርዓት ማስከበር የሚቻልበት ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣቱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ

የፀጥታ ኃይሎች በአንድ ኮማንድ ፖስት ዕዝ መስራታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የሥራ ክፍፍል ለማድረግ መወሰኑንም ገልጿል።

ኮማንድ ፖስቱ የአዋጁን የ6 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ዛሬ ገምግሟል።

የኮማንዱ ፖስቱ ሴክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ እንደገለፁት ባለፉት 6 ወራት በመደበኛ የህግ አሰራር ህግና ስርዓት ማስከበር የሚቻልበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው።

ኮማንድ ፖስቱ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ መተማመን እንዲኖር የሚያስችል ሥራም ሰርቷል።

እንደ አቶ ሲራጅ ገለፃ የአገር ውስጥና የውጭ የሽብርና የፀረ ሠላም ኃይሎች ግንባር በመፍጠር ሁከትና ብጥብጡን ለማስቀጠል ያደረጉት ጥረት መክሸፉ በስኬት ተገምግሟል።

ይህም በአገሪቷ አጠቃላይ መረጋጋትና ሠላም እንዲፈጠር አስተዋፅኦ አድርጓል ነው ያሉት።

በሁከትና ብጥብጡ የተጠረጠሩ አብዛኞቹን በቁጥጥር ሥር በማዋል ተሃድሶ የሚያስፈልጋቸው የሚገባቸውን ተሃድሶ ወስደው እንዲለቀቁ፣ በህግ መጠየቅ የሚገባቸውም በህግ አግባብ የሚጠየቁበትን ሁኔታ በመፍጠር የተሻለ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በመሰረተ ልማቶች፣ በዋና ዋና መስመሮች፣ በኬላዎችና ተቋማት ላይ በተሰሩ ሥራዎች በሁከትና ብጥብጡ የተከሰተው ችግር እንዳይደገም መደረጉም በስኬት ታይቷል።

ሠላምና መረጋጋት ከመፍጠር ባሻገር በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ አካላትን ማጥራት፣ ማደራጀትና ማሰልጠን ላይ ስኬታማ ሥራ መሰራቱንም ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የፀጥታ ኃይሎች በአንድ ኮማንድ ፖስት ዕዝ የሚሰሩት ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ የሥራ ክፍፍል ለማድረግ መወሰኑን አቶ ሲራጅ አስታውቀዋል።

የነበረው ችግር በመቀነሱ ሁሉም የፀጥታ አካላት ሥራ ተከፋፍለው ወደ ስምሪት እንዲሄዱ ተደርጓል ብለዋል።

በሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈው በቁጥጥር ሥር ያልዋሉትን በቁጥጥር ሥር በማዋል ህዝቡን ለማሳተፍና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ያለውን እምነት ለማጠናከርም አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት።

የተጀመረውን ዋና ዋና የመሰረተ የልማት አውታሮች፣ ኬላዎች፣ የመንግስት ተቋማትንና ኢንቨስትመንት ጥበቃ አጠናክሮ ለመሄድም እንዲሁ።

የፀጥታ አካላትን የማጥራት፣ የማሰልጠንና መልሶ የማደራጀት ሥራዎችን እስከ ወዲያኛው የማጠናቀቅና የማብቃት ሥራ መሰራት እንዳለበትም ተቀምጧል።

በቂ ትኩረት ሰጥቶ ያለመስራትና ከህግ ውጪ ህግ ለማስክበር የመስራት ችግሮች ታይተዋል ያሉት አቶ ሲራጅ ችግሩን ለመቅረፍ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቀዋል።

 

Published in ፖለቲካ

ጊምቢ ሚያዝያ 5/2009 የምዕራብ ወለጋ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ባለፉት ስምንት ወራት ከ25 ሺህ ለሚበልጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረጉን ገለጸ።

የስራ እድሉ ተጠቃሚ የሆኑት እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ጊምቢና መንዲ ከተሞችን ጨምሮ በ19 ወረዳዎች የሚኖሩ ናቸው።

መንግስት በነደፈው የእድገት ፕሮግራም መሰረት በማድረግ ጽህፈት ቤቱ በግንባታ፣ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በአገልግሎትና በሌሎች የስራ ዘርፎች በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ አድርጓል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ሃብታሙ ለገሰ  ለኢዜአ እንደገለጹት ተጠቃሚዎቹ በተሰማሩባቸው የስራ መስኮች ውጤታማ እንዲሆኑ  ከ32 ሚሊዮን 574 ሺህ ብር በላይ ብድርና የመስሪያ ቦታ ተመቻችቶላቸዋል፡፡

ከተጠቃሚዎቹ መካከል 42 በመቶ ሴቶች ናቸው።

በተሰማሩባቸው የስራ መስኮች  ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ በገንዘብ አያያዝና አጠቃቀም፣ በሂሳብ አሰራርና በውስጣዊ አደረጃጀት ዙሪያ ተከታታይ ስልጠናና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወጡ ወጣቶች ያላቸውን እውቀት ተጠቅመው በግንባታ፣በዶሮ እርባታ፣ እንስሳት ማደለብና በንብ ማነብ ላይ በመሰማራት ውጤታማ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ጽህፈት ቤቱ በከተማው የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለማቃለል ከተለያዩ የግልና የመንግስት መስሪያ ቤት ጋር የገበያ ትስስር  መፍጠሩንም አመልክተዋል፡፡

ሃላፊው እንዳሉት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከቴክኒክና ሙያ ተመርቀው የስራ እድል ያላገኙ 1 ሺ 421 ወጣቶችን በማደራጀትና ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ብድርና የመስሪያ ቦታ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል።

ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ለከተማው እድገት መፋጠንና ለኢንዱስትሪው ልማት ዘርፍ ዋነኛ ግበዓት መሆኑን መሰረት በማድረግ ዘንደሮ ከ15 በላይ ማህበራትን ወደ መካከለኛ ባለሃብትነት ለማሸጋገር መታቀዱንም ጠቅሰዋል።

እነዚህ ማህበራት በአማካይ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረት ያላቸው ናቸው።

በጊምቢ ከተማ ዘንድሮ በማህበር ተደራጅተው በእንጨት ስራ ከተሰማሩት ወጣቶች መካከል ወጣት ደጉ ተስፋዬ አንዱ ነው።

" ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ያገኘሁትን እውቀት ተጠቅሜ ከአቻ ጋደኞቼ ጋር በማህበር ተደራጅተን  በእንጨት ስራ ላይ ተሰማርተናል" ብሏል።

ከመንግስት  ስልጠና፣ የብድር አገልግሎትና የመስሪያ ቦታ ማግኘታቸውን ያመለከተው ወጣት ደጉ " ውስጣዊ የስራ መነሳሰት ስላለን በአጭር ጊዜ ሃብት አፍርተን ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን አቅደን እየሰራን ነው" ብሏል።

ሌላው በጫማ መገጣጠም ስራ የተሰማራው ወጣት ጫላ ዴኮ በበኩሉ ከሌሎች ሰዎች ጋር በመደራጀት ለሚሰሩበት  መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንዳደረገላቸው ተናግሯል፡፡

" ከጠባቂነት ተላቀን የራሳችን ስራ በመፍጠር በቀን ከ30 በላይ ጫማዎችን በዘመናዊ መልኩ እየገጣጠምን ለገበያ እያቀረብን ነው" ሲልም ወጣቱ ገልጿል።

ወጣቱ እንዳለው በአከባቢው ህብረተሰብ ተፈላጊ የሆኑ ጫማዎችን ከማምረት አልፈው ወደ ሌሎች አከባቢዎች ለማቅረብ አቅደው እየሰሩ ናቸው።

በተመቻቸላቸው የብድርና የመስሪያ ቦታዎች ታግዘው  ከድህነት ለመላቀቅ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግሯል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 5/2009 በተቋማት ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ተግባራትን ለማጠናከር በእንግሊዝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር ኢንስቲትዩት የሚከናወኑ ድጋፎች እንዲቀጥሉ በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽህፈት ቤታቸው የእንግሊዝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየርን ዛሬ አነጋግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ቀልጣፋና ውጤታማ ሥራ በማከናወን የአገልግሎት ተደራሽነት ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት በእንግሊዝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር ብሌየር ኢንስቲትዩት የተጀመሩ የድጋፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጠይቀዋል።

ኢንስቲትዩቱ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለማቃለል በኢንቨስትመንት ቦታዎችና በኢንዱስትሪ ፓርኮች የተለያዩ የድጋፍ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ተጠቁሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንደተናገሩት፤ በአገሪቷ ውጤታማና ቀልጣፋ የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማምጣት የሌሎች አገሮች ተሞክሮ በመቀመር ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።

ለዚህም በኢንስቲትዩቱ የተጀመሩ የድጋፍ ተግባራት ተጠናክረው እንደቀጥሉ ኢትዮጵያ ፍላጎት እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም መግለጻቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እውነቱ ብላታ ተናግረዋል።

የእንግሊዝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር በበኩላቸው እንደገለጹት፤ አገሪቷ በኢንዱስትሪው መስክ እድገት እያስመዘገበች ነው።

ይህን ለውጥ በመደገፍ “ውጤታማ፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ማረጋገጥ ያስፈልጋል” ብለዋል።

በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የአቅም ግንባታ ሥራ ማከናወንና የመሰረተ ልማትን ማሟላት ለአገሪቷ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚሰጥም ገልጸዋል።

በኢንስቲትዩቱ የተጀመሩ የድጋፍ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አውስተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ሚያዝያ 5/2009 ዓ.ም በሁሉም ንግድ ባንኮች 1 የአሜሪካን ዶላር በ22 ብር 8012ሳንቲም እየተገዛ በ23 ብር ከ2572ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡የእንግሊዝ ፓውንድ ስተሪሊንግ በ28 ብር ከ4947 ሳንቲም እየተገዛ በ29 ብር ከ0646 ሳንቲም እየተሸጠ ነው፡፡ 
የወርቅ ዋጋን ስንመለከት ደግሞ 24 ካራት አንድ ግራም ወርቅ በ980 ብር ከ7739ሳንቲም ሲሸጥ ባለ14 ካራት ደግሞ 572 ብር ከ1181ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡የሌሎችን ሃገራት የምንዛሬ ዋጋና የወርቅ ዋጋ በተከታዩ ሰንጠረዥ ይመልከቱ፡-

No automatic alt text available.

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 5/2009 የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ የአገሪቷ ዜጎች ሰኞና ረቡዕ ባህላዊ አልባሳትን ብቻ እንዲለብሱ ትዕዛዝ አስተላለፉ።

መመሪያው የአገሪቷን የጨርቃጨርቅና ፋሽን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ታስቦ መውጣቱን ፕሬዚዳንቱ ለቻይናው ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ጥምረት ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ተናግረዋል።

አልባሳቱ ለበዓላትና ለአዘቦት ቀናት እንዲመቹ ሆነው እንዲሰሩና አገር በቀል ኢንተርፕራይዞችን በማበረታታት ለውጭ አገር አልባሳት ሸመታ የሚወጣውን ወጪ መቀነስ ያስችላል ተብሏል።

መመሪያው አስገዳጅ ባይሆንም በምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

እ.አ.አ  ከ2010 ጀምሮ በልብስ ስፌት ሙያ የቆየችው ፓውላ ሳይመን መመሪያውን ከአገሪቷ መንግስት የተሰጣት ስጦታ አድርጋ ቆጥራዋለች።

"ይህ በጣም ጥሩ ማበረታቻ ነው፤ ደንበኞቼን ያበዛልኛል፤ አዋጁን ተከትሎ በየሶስት ሠዓት ልዩነት 15 ደንበኞች የባህል ልብስ ፈልገው ወደ እኔ እየመጡ ነው" ብላለች።

ናይጄሪያ ያለቀላቸው የውጭ አገራት አልባሳትን ከሚያስገቡ የአፍሪካ አገራት መካከል ቀዳሚዋ ስትሆን በዓመት 4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ታደርጋለች።

ዘርፉ የነዳጅ መገኘትን ተከትሎ እየቀዘቀዘ ቢሆንም በ80ዎቹ መጨረሻ በዓመት ለ350 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ሁለተኛውን ድርሻ የሚይዝ ነበር።

አሁን አሁን አብዛኞቹ የጨርቃጨርቅ ኩባንያዎች ኪሳራ ላይ በመውደቃቸው አዲሱ መመሪያ ዘርፉን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክቷል ተብሎለታል።

ለባህላዊ አልባሳት ልዩ ፍቅር ያላቸው ፕሬዝዳንት ቡሃሪ ዘርፉን ለማሳደግና ኪሳራ ላይ ያሉትን ኢንዱስትሪዎች ለመታደግ እርምጃ መውሰድ የጀመሩ ሲሆን በርካታ ናይጄሪያዊያንም በፕሬዝዳንቱ ውሳኔ በመደሰት በየጎዳናዎቹ ላይ በአልባሳቱ ማሸብረቁን ተያይዘውታል።

Published in ኢኮኖሚ

ደብረማርቆስ /አክሱም ሚያዚያ 5/2009 በምስራቅ ጎጃም ዞን ለመጪው የመኸር እርሻ የሚያገለግል 900 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ቀርቦ ለአርሶአደሩ እየተሰራጨ መሆኑን የዞኑ ሕብረት ሥራ ማህበራት መምሪያ አስታወቀ።

በሌላ በኩል በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ከመኸር እርሻ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጿል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ሕብረት ሥራ መምሪያ የብድርና ስርጭት ባለሙያ አቶ ኃይሉ ምህረቴ ለኢዜአ እንደገለጹት ለምርት ወቅቱ ከቀረበው ማዳበሪያ ውስጥ 530 ሺህ 560 ኩንታሉ በመሰረታዊ ሕብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ለአርሶአደሩ እየተሰራጨ ይገኛል።

ለምርት ወቅቱ የቀረበው ማዳበሪያ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተሰራጨው ጋር ሲነጻጸር በ120 ሺህ ኩንታል ብልጫ አለው።

በማቻከል ወረዳ  የግራቅዳማን ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር መርዕድ ቢምረው በሰጡት አስተያየት "ለምርት ወቅቱ የሚያስፈልገው ማዳበሪያ ቀድሞ በመድረሱ ፈጥነው የሚዘሩ ሰብሎችን በወቅቱ ለመዝራት አስችሎናል " ብለዋል ።

ሌላው የደባይ ጥላትግን ወረዳ የናብራ ሚካኤል ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አስማረ አዘነ በበኩላቸው፣ ባለፈው አመት "ዩሪያ" ማዳበሪያ በወቅቱ ባለመሰራጨቱ ከሄክታር ማግኘት የነበረባቸውን 50 ኩንታል የበቆሎ ምርት በ10 ኩንታል መቀነሱን ጠቁመዋል።

በዚህ ዓመት ማዳበሪያው ቀድሞ በመቅረቡ ሁለት ኩንታል "ዩሪያ" እና "ቦሮን" ማዳበሪያ ወስደው ግማሽ ሄክታር ማሳቸውን በድንች ዘር መሸፈናቸውን ጠቅሰዋል።

ቀሪው ማሳቸውን ሌሎች ፈጥነው በሚደርሱ ሰብሎች ዘር ለመሸፈን እየተዘጋጁ ነው።

በሌላ በኩል በትግራይ ማዕከላዊ ዞን 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም የዞኑ አስተዳደር ገልጿል ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተከለጊዮርጊስ አሰፋ እንዳሉት፣ ዕቅዱን ለማሳካት ለተሳታፊ አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች ስልጠና እንዲሰጥ ተደርጓል።

የምርት ማሳደጊያ ግብአቶችን በወቅቱ የማቅረብ፣ የአርሶአደሮች የልማት አደረጃጀቶችን የማጠናከርና መሰል ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

አንደ አስተዳዳሪው ገለጻ፣ እስካሁን ለሰባት ሺህ 600 የግብርና ባለሙያዎች በሰብል ልማት ማዕቀፍ ትግበራና ንቅናቄ ላይ ያተኮረ የአምስት ቀን ስልጠና ተሰጥቷል ።

ከእዚህ በተጨማሪ በምርት ወቅቱ ለሚሳተፉ የዞኑ አርሶአደሮች በገበሬ ማሰልጠኛ ማዕከላት አማካኝነት በአዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና በግብአት አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ለምርት ማሳደጊያ የሚያገለግል 140 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና 7 ሺህ 200 ኩንታል ምርጥ ዘር ቀርቦ እየተሰራጨ መሆኑን  ነው የገለጹት።

እንደ አቶ ተከለጊዮርጊስ ገለፃ በምርት ወቅቱ በሁሉም የሰብል አይነቶች በሄክታር 35 ኩንታል አማካኝ ምርት ለማግኘት ታቅዷል።

በዞኑ በመኸር ወቅት 192 ሺህ 296 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በዞኑ የጣንቋ አበርገለ ወረዳ የግብርና ኤክስቴሽን ባለሙያ ወይዘሮ ለቱ ገብረመድህን በሰጡት አስተያየት በስልጠና ያገኙትን ተጨማሪ እውቀት ወደ አርሶአደሩ ለማውረድ እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የታሕታይ ማይጨው ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ነጋሽ ገብረሕይወት በበኩላቸው፣ በማሰልጠኛ ማዕከሉ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ላይ በግብርና ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አርባምንጭ ሚያዚያ 5/2009 አርባ ምንጭ ከተማ ላይ በተካሔደው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ባለሜዳው አርባምንጭ ከነማ በድሬዳዋ ከነማ ሁለት ለባዶ ተሸነፈ፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በ40ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከነማው ዮሴፍ ዳሙዬ ባስቆጠራት ግብ አንድ ለባዶ እየመራ ለእረፍት ወጥተዋል።

ከዕረፍት መልስም በ82ኛው ደቂቃ የድሬዳዋ ከነማ 18 ቁጥሩ በረከት ይስሃቅ ሁለተኛውን ጎል በማስቆጠር ቡድኑ የጨዋታ የበላይነቱን እንደያዘ ውድድሩን እንዲያጠናቅቅ አደርጓል።

ውድድሩ ድሬዳዋ ከነማዎች ፍጹም የጨዋታ የበላይነትን ያሳዩበት ሲሆን በአንጻሩ አርባምንጭ ከነማ ደግሞ በሜዳው በተከታታይ ሁለት ጊዜ በመሸነፍ ስጋት ውስጥ ገብቷል ፡፡

 

Published in ስፖርት
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን