አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 12 April 2017

አዲስ አበባ ሚያዝያ 4/2009 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአፍሪካ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ዋና ፀሃፊ ተናገሩ።

የድርጅቱ ዋና ፀሃፊ ዶክተር ፍራንግ ሊዩ የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽና አየር ትራንስፓርት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተወያይተዋል።

ዶክተር ፍራንግ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አንድ የአፍሪካ የኢኮኖሚያዊና የፖለቲካ ትስስር መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው።

አየር መንገዱ የአገሪቷን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ከመደገፍ ባሻገር የአህጉሩን አገራት በማስተሳሰርም ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ትራንስፖርትን በማሳደግ የአገሪቷን ክልሎች ለማገናኘትና ከዓለም ጋር ለመገናኘት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርትና በሲቪል አቪዬሽን ዕድገት ከአፍሪካ መሪ መሆንዋን የገለፁት ዶክተር ፍራንግ በዘርፉ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ መቀጠል አለባት ብለዋል።

የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ደህንነትና ነፃነት እንዲጠበቅ በአህጉሩ የወጣው የሲቪል አቪዬሽን ደህንነትና ነፃነት አዋጅ እንዲተገበር ኢትዮጵያ እንድታግዝም ጠይቀዋል።

አዋጁ የአፍሪካ አየር መንገዶች እርስ በእርስ በነፃነትና ያለምንም ችግር መንቀሳቀስ እንዲችሉ ስለሚያደርግ ለተግባራዊነቱ በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ በማውጣት የአየር ትራንስፖርትና የሲቪል አቪዬሽን በማሳደግ ያመጣውን ለውጥም አድንቀዋል።

መንግስት በዚህ ቁርጠኝነቱ ከቀጠለ ዘርፉ የበለጠ በማደግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ያሳድጋል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በበኩላቸው ኢትዮጵያ ቀዳሚነቷን በማረጋገጥ የአፍሪካን ሲቪል አቪዬሽን ለማሳደግ እየሰራች መሆኗን መግለጻቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሟላ የአቪዬሽን አካዳሚና ሌሎች ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያሟላ በመሆኑ አፍሪካዊያን ወደ ሌላ አህጉር መሄድ ሳይጠበቅባቸው በኢትዮጵያ እንዲጠቀሙ እንፈልጋለን ማለታቸውንም አክለዋል።

ለዚህም ድርጅቱ በሚያግዝበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን አቶ ተወልደ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሩዋንዳ፣ ሞዛምቢክ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ካሜሮን፣ ዚምባብዌና ቶጎ አየር መንገዶች ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ተወልደ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት እ.አ.አ በ1947 የተመሰረተ ሲሆን ኢትዮጵያ አቪዬሽኑን ከመሰረቱ 52 አገራት አንዷ ነች።

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ሚያዝያ 4/209 የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) ባለፉት ሶስት ዓመታት  ባከናወናቸው የልማት ስራዎች 2 ነጥብ 6  ሚሊዮን ህዝብን ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ።

ድርጅቱ ባለፉት ሶስት ዓመታት ባከናወናቸውን የልማት ስራዎችና ቀጣይ ተግባራት ላይ  በባህርዳር ከተማ ተቋማዊ ውይይት አካሂዷል።

አመልድ  አቅሙን በየጊዜው በማሳደግ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ምንልኩ በውይይቱ ላይ ገልጸዋል፡፡ 

ባለፉት ሶስት ዓመታት  ባከናወናቸው የልማት ስራዎች ድርጅቱ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

ከተከናወኑት የልማት ስራዎች መካከል  የተዘጋጀ  ከ92 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በ25 ሺህ 800 ሄክታር የተራቆተ መሬት ላይ በመትከል መልሶ እንዲያገግም የተደረገው  ይገኝበታል፡፡

ከአንድ ሺህ 700 በላይ አባል አርሶ አደሮችን በ15 አሳታፊ የደን አስተዳደር ቡድኖች በማቋቋም ከ65 ሺህ 800 ሄክታር በላይ የሚሸፍን የተፈጥሮ ደንን ከልሎ በመጠበቅ ከጥፋት መታደግ ተችሏል።

እንዲሁም የመጠጥ ውሃ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች የተለያየ አቅም ያላቸው 858 የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን ገንብቶ ለአገልግሎት በማብቃትም ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን   አቶ ደጀኔ ተናግረዋል፡፡       

በክልሉ ዘመናዊ የመስኖ ልማት እንዲስፋፋ ድርጅቱ የጀመረውን ስራ ይበልጥ በማጠናከር 85 አነስተኛ የመስኖ ግድቦችን ገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል።

በዚህም ከ22 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች ከስድስት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት የዘመናዊ መስኖ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

ኤልኒኖ ያስከተለውን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም ከ43 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለተጠቃዎች ማቅረቡን የገለጹት  ደግሞ የድርጅቱ የኢንተርፕራይዞች ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰጥቷል ደባልቄ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ  ነው።

ድርጅቱ ከመንግስት ጎን በመሆን ባቀረበው ምርጥ ዘር አርሶአደሩ ድርቁን በመቋቋም ከችግሩ ፈጥኖ በመውጣት ራሱን እንዲችል የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል።

በንብ ማነብ፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ በወተት ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት  ከአንድ ሺህ 630 ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠሩም ተመልክቷል።

የሚቀረፁ ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ጥራት አለማደግ፣ የሙያተኞች በየጊዜው መልቀቅና የሚከናወኑ የልማት ስራዎች የአጋር ድርጅቶችን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አለመሆን እንደዋና ችግር ተጠቅሰዋል።

እነዚህን ችግሮች በቀጣይ ለይቶ ለመፍታትም ድርጅቱ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተገልጿል። 

ከድርጅቱ ሰራተኞች መካከልም ከዋግህምራ ዞን ድሀና ወረዳ የመጡት ወይዘሮ መሰረት አለባቸው ድርጅቱ ከውጭ ሀገር ጠቃሚ ልምዶችን እያመጣ ተግባራዊ ማድረጉ የተሻለ አፈፃፀም እንዲያስመዘግብ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

" እኔም  የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን ግንባር ቀደም ሆኜ በመስራት የተጣለብኝን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነኝ"ብለዋል።

ሰራተኛው ተቀናጅቶ በመስራት ያመጣው ውጤት በመሆኑ ይህንኑ ተግባር በቀጣይ አጠናክረው ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የድርጅቱ ሰራተኛ አቶ ድረስ ምህረቴ ናቸው።

 

" ድርጅቱ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ በመጀመሩም ህዝቡን የልማቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩሌን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል፡፡  

 

ድርጅቱ ያለፉትን ዓመታት የልማት ስራ ክንውኖች በመገምገምና ቀጣይ  የዕቅድ አቅጣጫዎችን በማመላከት ከሚያዚያ 2/2009ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት ያካሄደውን ውይይት ዛሬ  አጠናቋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ድሬዳዋ ሚያዝያ 4/2009 በድሬዳዋ  ከተማ አስተዳደር ዘንድሮ 14 ሺህ  የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የከተማ የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡

የከተማዋ አስተዳደር  የሥራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ  ኃላፊ አቶ  ወጋየሁ ጋሻው ለኢዜአ እንደገለፁት በመርሀ ግብሩ ታቅፈው ከሚጠቀሙት ውስጥ 11 ሺህ 760ዎቹ የደሃ ደሃ ተብለው የተለዩ ናቸው።

እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በከተማ ውበትና ፅዳት፣በደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ፣ በከተማ ግብርና፣ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና መሰል የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ተደርጓል።

ሌሎች ረዳት የሌላቸውና መስራት የማይችሉ 2ሺህ 240 አዛውንቶች ደግሞ በመርሀ ግብሩ በመታቀፍ በቀጥታ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል ።

እንደ አቶ ወጋየሁ ገለፃ ዘንድሮ ለመርሀ ግብሩ ማስፈፀሚያ 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተመድቧል ።

በከተማው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በሚካሄደው የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ከ43 ሺህ 600 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል።

በከተማው የቀበሌ ዜሮ አምስት ነዋሪ ወይዘሮ  የራሴወርቅ ታምራት በሰጡት አስተያየት አልፎ አልፎ ልብስ በማጠብና እንጀራ በመጋገር በሚያገኙት ገቢ ሶስት ልጆቻቸውን ማሳደግ ተስኗቸው እንደነበር ተናግረዋል ።

" መንግስት ለድሆች አስቦ በፈጠረልኝ የከተማ ፅዳት ሥራ ከችግሬ ስለሚያወጣኝ ተደስቻለሁ " ብለዋል ።

በተመሳሳይ ስራ የተሰማሩት ወይዘሮ ሃምዲያ አብደላ በበኩላቸው "በተፈጠረልኝ የሥራ እድል ከማገኘው ገቢ በመቆጠብ ወደ ጥቃቅን ስራ ለመግባት አስቢያለሁ" ብለዋል።

መንግስት ድህነትንና ሥራ እጥነትን ለመቀነስ የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል ።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 4/2009 የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳዩ 25 የመንገድ ፕሮጀክቶችን በልዩ ትኩረት እንዲሰራ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።      

ባለሥልጣኑ በበኩሉ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ሦስት ተቋራጮች ውል እንዲቋረጥ አድርጌያለሁ ብሏል።

የምክር ቤቱ የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባለስልጣኑን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል።    

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ካሚል አህመድ "በግንባታ ላይ ከሚገኙ 216 አዲስና ነባር የመንገድ ፕሮጀክቶች 25ቱ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያስመዘገቡ በመሆናቸው ልዩ ትኩረት ያሻቸዋል" ብለዋል።  

ከፍተኛ የአፈጻጸም ክፍተት የሚስተዋልባቸውን ሁለት የውጭና ስድስት አገር በቀል ተቋራጮችን የችግር ምንጭ በመለየት ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግም አሳስበዋል።     

ከታቀደው በላይ፣ በዕቅዳቸው ልክና መካከለኛ አፈጻጸም ያስመዘገቡ 189 የመንገድ ፕሮጀክቶች ተቋራጮች አፈጻጸም 91 በመቶ መሆኑን በጠንካራ ጎን አንስተዋል። 

ባለሥልጣኑ ከሦስት ወራት በፊት ባቀረበው ሪፖርት የ43 ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰው አሁን ወደ 23 ዝቅ እንዲል ማድረጉ ጥሩ ክትትልና ድጋፍ ለማድረጉ አመላካች ነው ብለዋል።  

የጀመረውን የክትትልና ድጋፍ ስርዓት በማጠናከር የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በታቀደላቸው ጊዜና ወጪ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣም ነው አቶ ካሚል ያሳሰቡት።        

የባለሥልጣኑ ዋና ዳሬክተር አቶ አርዓያ ግርማይ በሰጡት ምላሽ ለተመዘገበው ዝቅተኛ አፈጻጸም የመንገድ ፕሮጀክት ተቋራጮች የማኔጅመንትና የፋይናንስ አቅም ክፍተቶች ምክንያት መሆናቸው በጥናት ተለይቷል ብለዋል። 

ባለሥልጣኑ ኃላፊነቱን ለመወጣት በመስክ ምልከታ ጭምር የታገዘ የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከወሰን ማስከበር ጋር ለተያያዙ ሥራዎች ቅድሚያ በመስጠት እንዲፈቱ ከማድረግ ባለፈ የፋይናንስና ተያያዥ ችግሮችን የማቃለል ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።        

ድጋፍ ተደርጎላቸው ማሻሻል ያልቻሉ ኮንትራክተሮች የተወሰነ ክፍል አቅም ላላቸው ኮንትራክተሮች እንዲሸጋገር መደረጉንም ገልጸዋል።

ድጋፍ ተደርጎላቸው መሻሻል ባላሳዩ ሁለት የውጭና አንድ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ላይም ውል የማቋረጥ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

በዘጠኝ ወራት 1 ሺህ 60 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ለማከናወን ታቅዶ 954 ኪሎ ሜትር መከናወኑን የባለሥልጣኑ መረጃ ያመለክታል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 4/2009 የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ባለሥልጣን የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ እንደሚያሻሽል አስታወቀ።

አዋጅ ቁጥር 813/2006ን በዋነኝነት ለማሻሻል ያስፈለገው ከፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ መቋቋሚያ አዋጅ ጋር ለማገናዘብ ነው ተብሏል።

ባለሥልጣኑ ስለአዋጁና የመሥሪያ ቤቱ የበጀት ዓመት ሦስተኛ የሩብ ዓመት አፈጻጸምን በማስመልከት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

በባለሥልጣኑ የሕግ ባለሙያ አቶ ዮናስ አበበ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ባለሥልጣኑ በአዋጁ ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት ውስጥ የሸማቾች መብትን መጠበቅና መከላከልን ያካትታል።

በዚህም መሰረት በአዋጁ የተጠቀሱትን ድንጋጌ በመተላለፍ ጥፋት በሚፈፅሙ ነጋዴዎች ላይ የወንጀል ምርመራ የማድረግና የወንጀል ክሶችን የመመስረት ሥልጣን እንዳለው መጠቀሱን አውስተዋል።

በተጓዳኝ የንግድ ውድድርን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን በመጣስ በሚፈጸሙ አስተዳደራዊ ጥፋቶች ላይ የአስተዳደሪዊ ምርመራ ክሶችን የመመሥረት ሥልጣን እንዳለው ነው የተናገሩት።

ይሁን እንጂ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ሥራ ላይ ከመዋሉ ጋር ተያይዞ የባለሥልጣኑ የወንጀል መመርመርና ክሶችን የመመስረት ሥልጣን መቅረቱን ገልጸዋል።

በዚህም የወንጀል ጉዳይ የመመርመር ለፌዴራል ፖሊስ እንዲሰጥ መደረጉን ነው ያስታወሱት።

በመሆኑም ባለፉት ሦስት ዓመታት ሥራ ላይ የዋለውን የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ  ከፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ጋር "የተጣጣመ ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል" ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ባለሥልጣኑ በረቂቅ አዋጁ የተሰጠውን ፀረ- ውድድር ተግባራት ላይ አስተዳደራዊ ምርመራና ክሶችን የመመስረት ሥልጣን በማያሻማ መልኩ እንደሚያስቀምጥ ነው የተናገሩት።

አሁንም ከንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ ጋር ተያይዞ የሕግ ድንጋጌዎች ላይ ግልፅነት እንዲኖር ማድረግ አዋጁን ለማመሻሻል ካስፈለጉበት ምክንያቶች መካከል አንዱ ተደርጎ መወሰዱን ነው የገለጹት።

የአዋጁ መሻሻል በሕግና በአሰራር ክፍተት በንግዱ ሥርዓት ውስጥ ይፈጠሩ የነበሩ ችግሮችንና በተለይም በሸማቹ መብት ላይ የሚደርሰውን ተፅእኖ ያቃልለዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት በማድረግና ግብዓቶችን በመጨመር በያዝነው ዓመት መጨረሻ ለማጽደቅ እቅድ መያዙ ተመልክቷል።

Published in ኢኮኖሚ

ማይጨው ሚያዝያ 4/2009 በትግራይ ክልል በመጪው መኽር በሚከናወነው የሰብል ልማት ሥራ የምግብ ዋስትናን ለሚያረጋግጡና ለኢንዱስትሪ ግብአት ለሚሆኑ ሰብሎች ትኩረት እንደሚሰጥ ተጠቆመ።

የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ እንዳመለከተው በክልሉ በዘንድሮው መኸር በተለያዩ ሰብሎች ከሚሸፈነው አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ግማሽ ያህሉ ለምግብ ዋስትናና አግሮ ፕሮሰሲንግ ግብአት በሚውሉ ሰብሎች ይሸፈናል።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን በመኸር እርሻው ዋና ዋና ሰብሎችን በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ለማልማት እንዲቻል ለ385 የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በማይጨው ከተማ ሲሰጥ የቆየው የአምስት ቀናት የአሰልጣኞች ስልጠና  ተጠናቅቋል።

በስልጠናው መዝጊያ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍሰሃ በዛብህ እንዳሉት፣ በክልሉ የሚገኙ አርሶአደሮች ለመጪው የመኸር እርሻ ሥራቸው የማሳ ዝግጅት፣ የአፈር ዕቀባና እርጥበትን ይዞ የማቆየት ሥራ በማከናወን ላይ ናቸው።

በክልሉ የማሽላ፣ የስንዴ፣ የበቆሎ፣ የጤፍና የሰሊጥ ሰብሎችን በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ለማልማት አካባቢዎች የተለዩ ሲሆን፣ አርሶአደሮች ሙሉ የግብርና ፓኬጆችን ተጠቅመው ለማልማት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

እንደ አቶ ፍሰሀ ገለጻ፣ በክልሉ ከሚለማው አጠቃላይ የእርሻ መሬት 630 ሺህ ሄክታሩ ከፍተኛ ምርት በሚሰጠው የማሽላ ሰብል ይሸፈናል።

"ይህም ከሰብሉ ብዙ ምርት በማምረት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ማሽላን በግብአትነት ለሚጠቀሙ ቢራ ፋብሪካዎች አገልግሎት በማቅረብ አርሶአደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛል" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ ለኩታ ገጠም (ክላስተር ) የአስተራረስ ዘዴ በተመረጡ አስር ወረዳዎች ከ130 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዳቦ ስንዴ ሰብል እንደሚሸፈን  ነው አቶ ፍሳሃ የተናገሩት።

"ከሚገኘው የዳቦ ስንዴ ምርትም 40 በመቶው የሚሆነው ለገበያ እንዲቀርብ ይደረጋል" ያሉት አቶ ፍስሃ፣ ምርቱ በክልሉ ለሚገኙ የዱቄት ፋብሪካዎች ግብዓት እንደሚውል ገልጸዋል።

በተለይ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከዳቦ ስንዴ በሄክታር እስከ 40 ኩንታል ለማምረት ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመው፣ በዚህም ለአርሶአደሩ የገበያ ትስስር በመፍጠር የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የጤፍ፣ የበቆሎና የሰሊጥ ሰብሎች ከምግብ እህል ፍላጎት በተጨማሪ ለግብርና ምርቶች ማቀናበሪያ ኢንዱስትሪዎች ግብዓትነት ፋይዳቸው የላቀ በመሆኑ በኩታ ገጠም የማልማቱ ሥራ ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል።

ለዚህም በምርት ዘመኑ ከእርሻ መሬት ዝግጅት ጀምሮ ምርትን ለገበያ እስከማቅረብ ያለውን ሙሉ የግብርና ፓኬጆችን ተጠቅሞ የኩታ ገጠም ልማቱን ለመተግበር የሚረዳ ስልጠና በስፋት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በስልጠናው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በበቆሎ፣ በስንዴና በሌሎች ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ ፀረ አዝርዕት ተባዮች ሲከሰቱም ጉዳቱን አስቀድሞ መከላከል በሚያስችሉ ዜዴዎች ላይ ያተኮረ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የአምባላጌ ወረዳ የአዝርእት ጥበቃ ባለሙያ ወይዘሪት ለምለም ህሉፍ፣ "ስልጠናው ከአዳዲስ የእርሻ ልማት ዜዴዎችጋር በመተዋወቅ ተጨማሪ አቅም ፈጥሮልኛል" ብላለች።

አካባቢያቸው የስንዴ ክላስተር ሆኖ መመረጡን ገልጻ፣ አርሶአደሩ ሁሉንም የግብርና ፓኬጆች ተጠቅሞ በኩታ ገጠም ልማት ምርታማነቱን እንዲያሳድግ አስፍላጊውን የሙያ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቷን ገልጻለች።

በእንዳመሆኒ ወረዳ የአዝርዕት ልማት ባለሙያ አቶ ኃይለ አዲስ በበኩላቸው ፣ ከስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ወደ አርሶአደሩ በማስተላለፍ በምርት ዘመኑ የገበሬውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በቁርጠኘነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 4/2009 የኢትዮጵያ የወጣቶች አትሌቲክስ ውድድር ለአምስተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ውድድሩ ሚያዝያ 14/2009 ዓ.ም እንደሚጀመር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ውድድሩ በመጪው ሐምሌ በአልጄሪያ ለሚካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና አገራቸውን የሚወክሉ አትሌቶች የሚመረጡበት ነው።

በዘንድሮ ዓመት በሚካሄደው ውድድር 335 አትሌቶች እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን 137ቱ  ሴቶች ናቸው።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እንደገለጸው ውድድሩ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ስፖርተኞችን ተሳትፎ ከማስፋት አኳያ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

ወጣት ተተኪ አትሌቶችን በማፍራት ረገድም ጉልህ ሚና ይጫወታል።

ውድድሩ ከ20 ዓመት በታች የሆኑ አትሌቶችን የሚያሳትፍ ሲሆን ከመቶ እስከ 10 ሺህ ሜትር የሩጫና የእርምጃ ውድድሮችና ሌሎች የሜዳ ላይ ተግባራት የሚከናወኑ ይሆናል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሚያዝያ 4/2009 የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር በጋምቤላ ክልል ለሚስተዋለው የሰው ሃብት አስተዳደር ችግር ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት መስራት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈፃፀም ተመልክቷል።

ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የሶማሌ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና አፋር ክልሎች የሰው ሀብት አስተዳደርና የባለዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ሪፖርትም ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባዬ ገዛኽኝ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ በ2009 ዓ.ም እቅዱ የጋምቤላን ክልል የሰው ሃብት አስተዳደር ችግር በዘላቂነት እፈታለሁ ቢልም ችግሩ አሁንም አለ።

የክልሉ የአሰራር ስርዓት በመንግስት ንብረት፣ ጊዜና በሰው ሃብት ላይ ብክነት እያስከተለ በመሆኑ ሚኒስቴሩ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ምልከታ ባደረገባቸው ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎችና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ኦሮሚያ ክልሎች አርብቶ አደር አካባቢዎች የጥቅማ ጥቅም፣ የበረሃ አበልና የደመወዝ ክፍያ ፍትሃዊነት የጎደለው እንደሆነ ከአካባቢው የመንግስት ሰራተኞችና የግብርና ተመራማሪዎች አረጋግጠናል ብለዋል።

ሚኒስቴሩም የጋምቤላ ክልል የሰው ሃብት አስተዳደር በሰራተኞችም ሆነ በአገሪቷ ላይ የሚያስከትለውን ችግር በማጤን አፋጣኝ ምላሽና ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት በትጋት እንዲሰራ አስገንዝበዋል።

በእቅድ ዘመኑ አሳካዋለሁ ያለውን ማከናወን አንዳለበት በመጠቆም።

የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር የሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አዳሙ አያና የቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቢያ ትክክል መሆኑን ገልጸው "በክልሉ ያለው የሰው ሃብት አስተዳደር ችግር በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ምላሽ ያገኛል" ብለዋል።

"በአንድ ሰው ደመወዝ ሁለትና ሶስት ሰራተኛ ይቀጠራል፤ 10 ዓመትና ከዚያ በላይ በሚጠይቅ የስራ መደብ ጀማሪ ባለሙያ ይቀጠርበታል፤ ይህም በሰራተኛውም ሆነ በመንግስት መዋቅርና አሰራር ላይ ችግር ሲፈጥር ቆይቷል" ነው ያሉት።

በአንድ የስራ መደብ ከ10 በላይ ባለሙያዎች የሚቀጠሩበትን አሰራር ለማስቀረት የመደብ መታወቂያ ቁጥር እንዲወጣ ተደርጓል ብለዋል።

በክልሉ ያሉ ደንብና መመሪያዎች ተፈትሸው ደጋፊ የስራ ሂደት የሚባለው መደብ ጥናት የተጠናቀቀ ሲሆን ዋና የስራ ሂደት የሚባሉ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃሉ ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

ከሁለት ወር በኋላ ተግባራዊ ሲደረግ በዚህ ሳቢያ የሚባክነው የመንግስት ንብረትና በሰራተኞች ላይ የሚደርሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምላሽ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

አዳማ ሚያዝያ 4/2009 በኦሮሚያ ክልል ህዝቡ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ሁለገብ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበትን 6ኛ ዓመት በማስመልከት በክልል ደረጃ ዛሬ በሻሸመኔ ከተማ የፓናል ውይይት ተካሂዷል። 

የጽህፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ አማን አሊ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የክልሉ ህዝብ የህዳሴ ግድብን በራስ አቅም ለመገንባት በገባው ቃል መሰረት የነቃ ተሳትፎ እያደረገ ነው።

በተለይ ባለፈው ዓመት በክልሉ የጸጥታ ፣የዝናብ እጥረት፣ የኤልኖና ሌሎች ችግሮች ቢያጋጥሙም ችግሮችን ተቋቁሞ ከራሱ የሚጠበቀውንና ቃል የገባውን ለመፈጸም የድርሻውን መወጣቱን አመልክተዋል።

''የህዳሴ ዋንጫው ሲዘዋወር 500 ሚሊዮን ብር በቦንድ ግዥና በልገሳ እናሰባስባለን ብለን አቅደን 607 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ችለናል'' ብለዋል። 

የግድቡ ግንባታ 6ኛ ዓመት ሲከበር ህብረተሰቡ የገባውን ቃል በማደስ እስከ ፍጻሜው   በማንኛውም መልኩ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ ይበልጥ እንዲያጎለብት ጠይቀዋል።

የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን እንደገለጹት የከተማዋ ነዋሪዎች በቦንድ ግዥና በስጦታ የሚያደርጉት ድጋፍ እንዲስፋፋ አስተዳደሩ የእቅዱ አካል አድርጎ እየሰራ ነው።

ግድቡ ሀገሪቱን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ በሚደረገው ጥረት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው የከተማዋ  ህዝብ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

በመድረኩ ላይ ''የአባይ ወንዝና የህዳሴ ግድብ'' በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ምሁር ዶክተር ብርሃኑ በላቸው እንዳመለከቱት ግድቡ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ከፍተኛ መነሳሳትን ፈጥሯል ።

ምሁሩ አያይዘውም ''ግድቡ ህጻን አዋቂ ሳይል ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በአንድነት በማሰለፍ የቁጠባ ባህላችንን በማዳበር የተሻለ ደረጃ ላይ አድርሷል'' ብለዋል።

ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ከፍተኛ የኢኮኖሚ ትስስር ከመፍጠሩም ባለፈ የወጣበትን የግንባታ ወጪም በአጭር ጊዜ እንደሚመልስ ተናግረዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በሻሸመኔ የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አሰለፈች ጸጋዬ እንደተናገሩት የግንባታው መጀመር ይፋ በሆነበት በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ የአንድ ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት ተሳትፏቸውን ጀምረዋል።

የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮዋ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመግለጽ ለተለያዩ ጉዳዮች በሚንቀሳቀሱበት ቦታ ሁሉ ህብረተሰቡ የቦንድ ግዢ እንዲፈጽም የማነቃቃት ስራ እንደሚሰሩም  አስረድተዋል።

በአነስተኛ ችርቻሮ ንግድ የሚተዳደሩት ወይዘሮዋ እስከ አሁን ድረስ የ52 ሺህ ብር ቦንድ የገዙ ሲሆን ቀደም ሲል የህዳሴ ዋንጫው ከኦሮሚያ ወደ ደቡብ ክልል በተሸኘበት ወቅት ዋንጫና የእውቅና የምስክር ወረቀት የተሸለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዓሉ ዛሬ በከተማዋ የተደረገውን የፓናል ውይይት ጨምሮ ለሁለት ቀናት በማርሽ ባንድ እንቅስቃሴ፣በሰርከስ፣በሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት እንዲሁም የከተማውን ህዝብ ባሳተፈ መልኩ  በስታዲየም እንደሚከበር ከበዓል አዘጋጅ ኮሚቴው የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

Published in ኢኮኖሚ

ማይጨው ሚያዝያ 4/2009 ከትግራይ ደቡባዊ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የዞኑ መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።  

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ጀምበር ሐድጉ ለኢዜአ እንደገለጹት ገንዘቡ የተሰበሰበው በዞኑ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በስጦታና በቦንድ ግዥ ባለፉት ሰባት ወራት ካደረጉት ድጋፍ ነው።

ሕብረተሰቡ ድጋፍ ያደረገው የግድቡ ግንበታ መሰረት የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ የቦንድ ግዥ ሳምንትና የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ በተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ ስነ ስርአት ላይ ነው።

በተለይ በቦንድ ግዥው የመንግስት ሠራተኞች፣ ሞዴል አርሶ አደሮችና ነጋዴዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

እንደ ወይዘሮ ጀምበር ገለጻ፣ በበጀት ዓመቱ ለግድቡ ግንባታ ከቦንድ ሽያጭና ከተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀግብሮች ለማግኘት የታቀደውን 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት እየተሰራ ነው።

የማይጨው ከተማ ነዋሪው አቶ አብርሃም ስዩም በሰጡት አስተያየት የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ እስካሁን የአምስት ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

"ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊነታችንና የአንድነታችን መገለጫ በመሆኑ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፌን አጠናክሬ እቀጥላለሁ " ብለዋል ።

በዞኑ የራያ አዘቦ ወረዳ ነዋሪው አቶ ህንደያ ባራኪም ለግድቡ ግንባታ ለሦስት ጊዜ ሙሉ የወር ደሞዛቸውን በመለገስ ድጋፍ ማድረጋቸውንና በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን የዞኑ ሕዝብ በቦንድ ግዥና በስጦታ ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓ።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን