አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 11 April 2017

ባህርዳር ሚያዝያ 3/2009 በአማራ ክልል የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ከ170 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዘር በመሸፈን እየለማ መሆኑን  የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የሰብል ጥበቃ ባለሙያ አቶ አሻግሬ እንዳየን ለኢዜአ እንደገለጹት በዘር የተሸፈነው መሬት በክልሉ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ በሰሜንና በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች ነው።

የዘንድሮው የበልግ ዝናብ መጣል ከሚገባው ጊዜ ከአንድ ወር በላይ ዘግይቶ ቢጀምርም አሁን ላይ ከአነስተኛ እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እየጣለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለማልማት በዕቅድ ከተያዘው ውስጥ እስካሁን ከ170 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ፈጥነው በሚደርሱ ቀይ ጤፍ፣ ማሾ፣ አተር፣ ምስር፣ ቦሎቄ፣ ሽምብራ፣ ስንዴና ገብስ ዘር ተሸፍኗል።

እየጣለው ያለው ዝናብ ከበልግ በተጨማሪ ለመኽር እርሻ ዝግጅት አመቺ በመሆኑ አርሶ አደሩ የሚጥለው ዝናብ ሳይባክን በማሳው ውስጥ በማስቀረት እንዲጠቀም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

እስካሁን በዘር ተሸፍኖ እየለማ ላለው መሬት ሶስት ሺህ 747 ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ባለሙያው ጠቁመው በበልጉ ለማልማት በዕቅድ የተያዘው 267 ሺህ ሄክታር መሬት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የምስራቅ አማራ አገልግሎት ማዕከል የትንበያ ባለሙያ ወይዘሮ ሉባባ መሀመድ በበኩላቸው የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች ዝናቡ መጣል የጀመረው ዘግይቶ መሆኑን ተናግረዋል።

ተለዋዋጭ የአየር ፀባይ በመስተዋሉም እስካሁን እየጣለ ያለው ዝናብ የሳሳና የተቆራረጠ፣ የስርጭት መጠኑም ከመደበኛ በታች ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል።

ከሚያዚያ 10 ጀምሮ የሚጥለው የዝናብ መጠንና ስርጭቱ እየተሻሻለ እንደሚሄድ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎች እንደሚያመልክቱ ባለሙያውን ጠቅሰው አርሶ አደሩ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎችን ለይቶ እንዲያለማም አሳስበዋል።

አርሶ አደር ዳዊት አካለስላሴ በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ አርማኒያ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ  እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ ለሰብል ምቹ በመሆኑ ባላቸው ግማሽ ሄክታር መሬት በአጭር ጊዜ የሚደርስ ሰብል እያለሙ መሆናቸውን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሩ እያለሙት ያለው የማሾ ሰብል በጥሩ የዕድገት ደረጃ ላይ ስለሚገኝ ከዚህም ባለፈው የመኸር ወቅት የሚበልጥ  ምርት ይጠብቃሉ፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ተንታ ወረዳ የዜሮ ስድስት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አስር አለቃ እሸቱ ተፈራ በበኩላቸው ካለፈው  የካቲት ወር ጀምሮ   የጣለውን ዝናብ በቂ ባይሆንም ያለውን ተጠቅመው  በግማሽ ሄክታር መሬታቸው ላይ  ገብስ መዝራታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮው የበልግ እርሻ ለማልማት ከታቀደው መሬት 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል  ምርት እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ አመልክቷል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አርባ ምንጭ ሚያዚያ 3/2009 መንግስት ባመቻቸላቸው  የስራ እድል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ መዘጋጀታቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የደቡብ ኦሞ ዞን ወጣቶች ተናገሩ፡፡

ከፌደራል መንግስት በተመደበ ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ ተጠቃሚ የሚሆኑ 5 ሺህ 388 ስራ አጥ ወጣቶች በዞኑ ተለይተዋል፡፡

የጅንካ ከተማ ነዋሪው ወጣት ጳውሎስ ጎሪሳ በሰጠው አስተያየት መንግስት ከመደበው ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ ለመጠቀም ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በማህበር መደራጀቱን ገልጿል፡፡

"በእንጨትና ብረታ ብረት ሥራ ለመሰማራት የሚጠበቅብንን 10 ሺህ ብር ቆጥበን የስራ ዕቅዳችንን ለሚመለከተው አካል አቅርበናል " ብሏል ።

በከተማው በመኪና እጥበት ሥራ ከተደራጁት መካከል ወጣት መሳይ አፍራሳ በበኩሉ ምልመላው ፍትሃዊና በሥራ አጦች ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑን ተናግሯል።

ሌላው የበና ጸማይ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ደለለኝ ስሌ  አስር የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን አባላት ያሉት ማህበር በመመስረት በግንባታ ስራ ለመሰማራት የሚጠበቅባቸውን 10 ሺህ ብር መቆጠባቸውን ገልጿል ።

"መንግስት ለወጣቱ በሰጠው ልዩ ትኩረት ተጠቃሚ በመሆን በህይወታችን  ለውጥ ለማምጣት ተዘጋጅተናል " ብሏል ።

የደቡብ ኦሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ባደገ እንዳሉት ለዞኑ ወጣቶች የስራ ማንቀሳቀሻ 67 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ ተመድቧል፡፡

በዞኑ ከስምንት ወረዳዎችና ከጅንካ ከተማ በስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ የሚሆኑ 5 ሺህ 388 ሥራ አጥ ወጣቶች ተለይተዋል።

ከእነዚህም መካከል  1ሺህ 186 ሴቶች ናቸው ።

ወጣቶቹ ከሚሰማሩባቸው መስኮች መካከል እንስሳት ማድለብ፣ ንብ ማነብ፣ የሰብል ልማት፣ የኦሞ ስኳር ፕሮጀክት ውስጥ ተጠቃሚ ማድረግ ይገኙበታል፡፡ 

በተዘዋዋሪ የብድር ገንዘቡ ወጣቶቹ ተጠቅመው በሚሰማሩባቸው የስራ መስኮች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማገዝ ለ74 አመራሮችና ባለሙያዎች ሥልጠና መሰጠቱን አቶ ታረቀኝ ተናግረዋል።

በመደበኛ መርሀ ግብር ደግሞ ዘንድሮ በዞኑ ከተማና ገጠር በ84 ማህበራት የተደራጁ ከ6ሺህ የሚበልጡ ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች መሰማራታቸው ተመልክቷል፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2009 የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ የሁሉም ችግሮች መፍቻ ተደርጎ እየተወሰደ ያለውን አስተሳሰብ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር መቀየር እንደሚገባው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርን የ2009 ዓ.ም የስምንት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል።

መንግስት የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ 10 ቢሊዮን ብር መድቦ የአፈጻጸም ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ለወጣቶች ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑ ይታወቃል።

ገንዘቡ በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ስራ አጥ ወጣቶች ወደ ስራ ለማሰማራት የጸደቀ ነው።

ይሁንና የተመደበው የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ የሁሉም ችግሮች መፍቻ ተደርጎ እየተወሰደ መሆኑን ነው በምክር ቤቱ የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ የተናገሩት።

የችግሮች ሁሉ መፍቻ ተደርጎ መወሰዱም በስራ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር እና ህብረተሰቡም የተመደበው ገንዘብ ብዙ ችግሮች ይፈታል ብሎ እንዲጠብቅ እያደረገው ነው ብለዋል።

በህብረተሰቡ፣ በአመራሩና በወጣቶች ዙሪያ የአመለካከት ችግር እየተስተዋለ ነው ያሉት ወይዘሮ አበባ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እነዚህን ችግሮች ሊፈታ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

ከቅድመ ዝግጅት ባለፈ ወጣቶች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ፣ የመስሪያ ቦታ ማመቻቸትና በቂ ስልጠና ከመስጠት አንጻርም በሚፈለገው ፍጥነት ስራዎችን እያከናወነ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ስለሆነም በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን የአመለካከት ችግር በቂ ግንዛቤ በመስጠት፤ ወጣቶችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ እንዲገቡ ትኩረት በማድረግ ሊሰራ ይገባል ብለዋል ወይዘሮ አበባ።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ እርስቱ ይርዳ በበኩላቸው በተዘረጋው የብድር አስተዳደር ማዕቀፍና መመሪያ ላይ ስራውን ለሚመሩ አካላት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

የተመደበው ገንዘብ  የሁሉንም ወጣቶች ችግር እንደማይቀርፍ የገለጹት አቶ እርስቱ፤ ወደ ስራ ለመግባት ለብድር ስርጭቱ የሚውል የመጀመሪያው ዙር ገንዘብ ክልሎች ባላቸው የወጣት ቁጥር መሰረት እንዲተላለፍ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም የተወሰኑ ክልሎች በዞንና በወረዳ በመደልደል የብድር ተቋማት በሚቀርቡላቸው ጥያቄ መሰርት እንዲያስተናግዱ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

ከተንቀሳቃሽ ፈንዱ በተጨማሪ በስምንት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ በገጠርና በከተማ ለዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች፣ ለቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ሌሎችም ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ተይዞ ነበር።

ከነዚህ ውስጥ ለ936 ሺህ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩን አቶ እርስቱ ተናግረዋል።

የተፈጠረው የስራ ዕድል ከተለየው የስራ ፈላጊ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር አፈጻጸሙ ዝቅተኛ በመሆኑ በቀጣይ ልዩ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

ወጣቶች በአገራቸው ያለውን ሃብት ከማየት ይልቅ ስደትን የተሻለ አማራጭ አድርገው በመውሰድ ለእንግልትና ሌሎች ተያያዥ አደጋዎች እየተጋለጡ እንደሆነም በወቅቱ አንስተዋል።

ለዚህ ዋነኛ ምክንያት የህገ-ወጥ ደላሎች የማታለል ተግባር እንደሆነም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍም ግንዛቤ ከመፍጠር በተጨማሪ ህገ-ወጥ ደላሎችን ለመያዝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የጋራ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

 

 

Published in ማህበራዊ

ፍቼ ሚያዚያ 3/2009 በፍቼና ገብረ ጉራቻ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የኘላዝማ ትምህርት ስርጭት በመቋረጡ በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ጫና መፍጠሩን  መምህራንና ተማሪዎች ገለጹ፡፡

ተማሪዎችና መምህራኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት በትምህርት ቤቶቻቸው ስርጭቱ ከተቋረጠ ሰባት ወራት ሆኖታል።

በፍቼ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ1ዐኛ ክፍል ተማሪ ብሌን ደረጄ በሰጠችው አስተያየት በአገር አቀፍ ደረጃ በፕላዝማ የሚሰጠውን የእንግሊዝኛና የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ባለመከታተሏ “በውጤቴ ላይ ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት አለኝ" ብላለች

"ትምህርቱን በአግባቡ ከተከታተሉ ሌሎች ተማሪዎች ጋር ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና መቀመጥ ተወዳዳሪ አያደርገኝም " ስትል ቁጭቷን ገልጻለች።

የፍቼ ቀለምና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪ ወጣት ምስጋናው አበበ በበኩሉ ትምህርቱን አለመከታተሉ በአገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ውጤት ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥርበት እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።

የፍቼ  ቀለምና መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ዱጉማ ሞሲሳ በበኩላቸው የፕላዝማ ቴሌቪዥኖች በመበላሸታቸው ምክንያት የፕላዝማ ትምህርት ስርጭቱ ሊቋረጥ መቻሉን ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቱ የተበላሹ ፕላዝማዎችን ለማስጠገን በጀት የሌለው በመሆኑ ችግሩን ለሚመለከተው አካል ቢያሳውቅም መፍትሄ አለመገኘቱን ተናግረዋል ።

በገብረ ጉራቻ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ ደመቀ ባጫ ትምህርትቤታቸው ተመሳሳይ ችግር እንደገጠመውና የትምህርት ስርጭቱን በመምህራን ለመሸፈን ባለመቻሉ ተማሪዎች የሚገባቸውን እውቀት ማግኘት አለመቻላቸውን ጠቁመዋል።

ይህም በተማሪዎች ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ነው መምህሩ የገለጹት።

የዞኑ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት የትምህርት ማሻሻያና ጥራት ቡድን ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ አበበ  ችግሩን ለመፍታት ከክልሉ ትምህርት ቢሮና ከኢትዮ- ቴሌኮም ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል

እንደ አቶ ገዛኽኝ ገለጻ፣ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተበላሹ ከዘጠና በላይ የኘላዝማ ቴሌቪዥኖችን በማስጠገን ሥራ ለይ ለማዋል አስፈላጊ የመለዋወጫ እቃዎችን ከውጭ አገር ለማስመጣት ግዥ እየተካሄደ ነው።

በአነስተኛ ብልሽት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የፕላዝማ ቴሌቪዥኖችን በማስጠገን ሥራ ላይ እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል ።

በዞኑ 13 ወረዳዎች በሚገኙ 59 ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ለትምህርት ስርጭት አገልግሎት ከዋሉ 313 የፕላዝማ ቴሌቪዥኖች ውስጥ 92ቱ ብልሽት ደርሶባቸዋል፡፡

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2009 በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት አባል አገሮች /ኢጋድ/ ድንበር አካበቢ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና ስደተኞችን የጤና ችግር ለመፍታት እንዲቻል "የተቀናጅ የጋራ የጤና ማስተባበሪያ ረቂቅ ማዕቀፍ" ተዘጋጀ።

የኢጋድ አባል አገሮች ተወካዮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አዲስ አበባ ውስጥ ዛሬ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።

በዚሁ ወቅት እንደተገለጸው፤ የተዘጋጀው የጤና ማስተባበሪያ ረቂቅ ማዕቀፍ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2018 እስከ 2020 ተግባራዊ የሚሆን ነው።

ረቂቅ ማዕቀፍ በቀጣናው የሚከሰተውን ቲቢ፣ ወባና ኤች. አይ. ቪ /ኤድስን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር፣ አስፈላጊውን የህክምና ድጋፍና እገዛ ለማድረግ እንዲቻል የሚያደርግ መሆኑ ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሸች ጉዳይ አስተዳደር ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዘይኑ ጀማል እንደገለጹት፤ ረቂቅ ማዕቀፉ በአባል አገሮች ድንበር አካባቢ የጤና መርሃ ግብሮችንና አገልግሎቶችን የተሻለ ለማድረግ ያስችላል።

ይህም በቀጣናው ወጥ የሆነ የጤና መርሃ ግብር ለመተግበርና የሚከሰቱትን በሽታዎች በጋራ ለመመከት የሚቻልበትን ሁኔታ እንደሚፈጥርም  ነው የተናገሩት።

በቀጣናው የሚከሰቱ ግጭቶችና ድርቅ ህብረተሰቡን ለተለያዩ በሽታዎች እያጋለጠ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ረቂቅ ማዕቀፉ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑትን ተላላፊ በሽታዎችን በጠንካራ የጤና ስትራቴጂ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የተቀናጀ የጤና ማስተባበሪያ ረቂቅ ማዕቀፉን ለተሳታፊዎች ያብራሩት ዶክተር ሞሀመድ ሀሰን በበኩለቸው እንደገለጹት፤ ሰነዱ በኢጋድ አባል አገሮች መካከል ለስደተኞችና ለአካባቢው ህብረተሰብ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል እንዲቻል ታልሞ የተዘጋጀ ነው።

አባል አገሮቹ ያላቸውን ብሔራዊ የቲቢ፣ ወባና ኤች. አይ. ቪ /ኤድስን መከላከልና መቆጣጠር ፕሮግራም ከሰነዱ ጋር አቀናጅተው ወጥ የሆነ የጤና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችልም ነው የጠቆሙት።

በተለይም ስነዱ አባል አገሮቹ ስደተኞችን በተመለከተ ሰፊና የተቀናጀ ትብብር እንዲያደርጉ፣ የጋራ እቅድ እንዲያዘጋጁ፣ የአቅም ግንባታ ሥራ እንዲሰሩ፣ የመረጃ ልውውጥ እንዲፈጥሩ ፣ ክትትልና ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ለማድረግ እንደሚያስችልም አብራርተዋል። 

የምክክር መድረኩ በነገው እለት የሚቀጥል ነው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2009 የተተኪ ወጣት ስፖርተኞች የምልመላ ስርዓትና የማዘውተሪያ ስፍራዎች ችግር ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርን የ2009 ዓ.ም የስምንት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል።

የአገሪቱን ስፖርት ለማሳደግ በመላ አገሪቱ ባሉ የማሰልጠኛ ጣቢያዎች በ17 የስፖርት ዓይነቶች 25 ሺህ ወንድና 25 ሺህ ሴት በድምሩ 50 ሺህ ታዳጊ ወጣቶች ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።

ዓላማው ለስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላትና ለክለቦች መጋቢ በመሆን በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሚሆን ብሄራዊ ቡድን መፍጠር ነው።

ሆኖም ከየጣቢያው ተመርጠው ወደ ማዕከል የሚገቡ የተተኪዎች ምልመላ ፍትሐዊ አለመሆኑ ብቃት ያላቸው ተተኪዎች እንዳይወጡ ምክንያት እየሆነ ነው ተብሏል።

በተለይም ብቃት ያላቸው ወጣቶችን ከመለየት ጀምሮ ወደ ማዕከላት፣ ክለብና ብሄራዊ ቡድን የማሸጋገር ከፍተኛ ችግር መኖሩንም ነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተናገሩት።

የአገሪቱ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ፖሊሲ  በአገር አቀፍ ደረጃ በከተማ ማስተር ፕላን መሰረት በገጠር ደግሞ አመቺ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት በእያንዳንዱ ቀበሌ አንድ የማዘውተሪያ ስፍራ ሊኖር እንደሚገባ ይደነግጋል።

ነገር ግን በከተማና በገጠር በቂ የማዘውተሪያ ስፍራ ባለመገንባቱ ወጣቶች በመለማመጃና በመዝናኛ ቦታዎች እጦት በአልባሌ ቦታ ሊውሉ ይችላሉ።

ስለሆነም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለነዚህ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት ብሏል ምክር ቤቱ። 

ብሄራዊ ፌዴሬሽኖችም ሆነ ክለቦች ከመንግስት ድጎማ ወጥተው ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ መፈጠር እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።

አብዛኛዎቹ ፌዴሬሽኖችና ክለቦች 95 በመቶ በመንግስት ድጎማ የሚተዳደሩ ናቸው።

ከዚህ በመውጣት የራሳቸውን ገቢ የሚያመነጩበት መንገድ በመፍጠር ስፖርቱ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው መስራት አንደሚያስፈልግም ነው የተገለጸው።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ እርስቱ ይርዳው እንደገለጹት በስልጠና ጣቢያዎችና ማሰልጠኛ ማዕከላት የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ  ደረጃቸውና አሠራራቸው ምን መሆን እንዳለበት የሚያሳይ  ማንዋል እየተዘጋጀ ነው።

ማዕከላትና የስልጠና ጣቢያዎች የታለመላቸውን ዓላማ እንዲያሳኩም ክልሎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።

"የተተኪ ወጣቶችን የምልመላ ችግር ለመቅረፍ ብቃት ያለው አሰልጣኝ በመመደብ ከግላዊ አሠራር በመውጣት በቡድን የሚሰራበትን ስርዓት እንዘረጋለን" ብለዋል።

ፌዴሬሽኖችም ከመንግስት ድጎማ በመውጣት ራሳቸውን እንዲችሉ ረጅም ጊዜ የሚያስፈልግ ቢሆንም ጅምር ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2009 በአገሪቱ በምርት ጥራት ቁጥጥር ዙሪያ የህግ ማዕቀፉ አተገባበር የላላ መሆን የምርጥ ጥራት ችግር እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል ተባለ።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚያስተባብረው የብሄራዊ ጥራት መሰረተ ልማት ፎረም ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።  

በስብሰባው ላይ ከፌደራል፣ ክልልና የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን የብሄራዊ የጥራት መሰረተ ልማት ስነ-ምህዳር በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የፎረሙ አባላት ወደ ውጭ የሚላኩ፣ አገር ውስጥ የሚገቡና ጥቅም ላይ የሚውሉ ምርቶች ላይ የሚታዩ የጥራት ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል። 

ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች ወደ አገር መግባታቸው፣ በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ ነጋዴዎች መኖራቸው፣ የምርት ፍተሻ ስራው የአቅም ክፍተት የሚታይበት መሆኑ ከተነሱ ችግሮች መካከል ናቸው።

በማር፣ ቅቤ፣ ጤፍን የመሳሰሉ ምርቶች ላይ ባዕድ ነገር እየተቀላቀለ የኅብረተሰቡ ህልውና አደጋ ላይ እየወደቀ መሆኑም ተነስቷል።

ወደ ውጭ አገር በሚላኩ ምርቶች ላይ ደግሞ በተለይ በአውሮፓና እስያ አገራት ደረጃን የሚያሟሉ ባለመሆናቸው ከገበያ ውጭ እየሆኑ መሆኑንም እንዲሁ።  

የደቡብ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ የንግድ ኢኒስፔክሽንና ሬጉሌሽን ዋና የሥራ ሂደት መሪ ወይዘሮ መስከረም ባህሩ እንዳሉት በተለይ በክልሎች የምርት ጥራት መፈተሻ ላብራቶሪዎች እጥረት ይስተዋላል።           

ይህም ምርቶችን ለማስፈተሽ ከፍተኛ ወጪ እንዲወጣ እያደረገ በመሆኑ ላቦራቶሪዎችን ተደራሽ ማድረግ እንደንሚገባ ጠቁመዋል።

የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የጥራት ማኔጅመንት ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ምናሉ ተሰማ በበኩላቸው በምርት ጥራት ዙሪያ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የግሉን ዘርፍ በብዛት ማሳተፍ ተገቢ መሆኑን አስምረውበታል።

''የጥራት ጉዳይ የህይወት ጉዳይ በመሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ሊያከናውኑ ይገባል'' ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ ከፍተኛ አማካሪ አቶ አዲሱ ተክሌ ናቸው።

የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ቃሬ ጫዊቻ ኅብረተሰቡ ስለሚጠቀመው ምርት የግንዛቤ ክፍተት እንዳለ አንስተው በዚህ ረገድ ለሸማቾች ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።      

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት የኅብረተሰቡን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት በቀጣይ በጥናት የተደገፈ ስራ ይሰራል።

''ህዝቡ በገንዘቡ በሽታ እየገዛ ነው ያሉት'' ሚኒስትሩ በጉዳዩ ዙሪያ ዘላቂ እልባት ለማምጣት ባላድርሻ አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

ጥራት የሌላቸው ምርቶች በመገናኛ ብዙሃን መተዋወቅ የለባቸውም፤ መገናኛ ብዙሃን በዚህ በኩል ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ከጥራት ጋር በተያያዘ የሚወጡ የህግ ማዕቀፎች ዙሪያ የአተገባበር ክፍተት እንደሚታይ የጠቆሙት ሚኒስትሩ በቀጣይ ሚኒስቴሩ ንግድ ሚኒስቴርን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ጠንካራ ህጋዊ ስርዓት ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የግሉን ዘርፍ በጥራት መረጋገጥ ስራው ለማሳተፍ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበር ስታራቴጂ መቀየሱንም ነው ያስረዱት።

በክልሎች የሚታየውን የምርት መፈተሻ ላቦራቶሪ እጥረት ለማቃለል ዩኒቨርሺቲዎች ላቦራቶሪዎች እንዲገነቡ ድጋፍ በማድረግ በያሉበት ማህበረሰብ የምርት ፍተሻና ማረጋገጥ አገልግሎት እንዲሰጡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል። 

ዩኒቨርሺቲዎች የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን አገራዊ እንቅስቃሴ በጥናትና ምርምር እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።

አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2009 የኢትዮጵያ መንግሥት የድርቅ አደጋ ላጋጠማቸው የሶማሊያ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ በድርቅ ለተጎዱ የሶማሊያ ዜጎች ሰባት ሺህ ኩንታል ሩዝ ድጋፍ አድርጋለች።

ከዚህም በተጨማሪ አምስት ሺህ ኩንታል ዱቄት፣ 30 ሺህ ጣሳ የዱቄት ወተትና 300 ኩንታል ኃይል ሰጪ ብስኩት ለሶማሊያ ድጋፍ ማድረጓ ነው የገለጸው።

በቅርቡ በሶማሊያ በተከሰተው ድርቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሶማሊያዊያን ለከፋ ችግር በመጋለጣቸው የአገሪቱ መንግሥት የድጋፍ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ለሶማሊላንድ አስተዳደርም የአልሚና የኃይል ሰጪ ምግቦች እርዳታ ማድረጓ አይዘነጋም።

ሁለቱ ድጋፎች ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ያላትን ወዳጅነትና የችግር ደራሽነት ያረጋገጠችበት መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ የሚመጡ ስደተኞችን በመቀበልም የመጠለያ እና የማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማቅረብ ላይ መሆኗ ይታወቃል።

ይህም ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገሮች ሕዝቦች ያላትን አክብሮትና ከአገራቱ ጋር ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ለመፍጠር ያላትን ፍላጎት ያመላክታል ነው የተባለው።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ800 ሺህ በላይ የጎረቤት አገራት ስደተኞችን ማስጠለል ችላለች።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ3/2009 መንግስት በአዳማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለሚገቡ የቻይና ሁናን ግዛት ባለሀብቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁናን ግዛት ምክትል አስተዳዳሪ ሚስተር ሂ ባኦዢያንግ የተመራ በአዳማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመሳተፍ የሚፈልግ የልኡካን ቡድንን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

የልኡካን ቡድኑ አዳማ በሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ የሁናን ኩባንያዎች በሚሳተፉበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርቧል።

ውይይቱን የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኤዥያና ኦሽንያ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ጸጋአብ ከበበው እንደገለፁት በኢንዱስትሪ ፓርኩ ተሳትፎ ለሚያደርጉ የሁናን ባለሀብቶች ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ተናግረዋል።

የአዳማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ሞዴል የኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሆን የመንግስት ፍላጎት መሆኑንም ገልፀዋል።

ይህን እውን ለማድረግ መንግስት በፓርኩ ለሚገቡ የሁናን ባለሀብቶች ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

የቻይና እና የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢንዱስትሪ ፓርኩ አንዱ የትብብሩ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የልኡካን ቡድኑ መሪና የሁናን ግዛት ምክትል አስተዳዳሪ ሚስተር ሂ ባኦዢያንግ ለአዳማው የኢንዱስትሪ ፓርክ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገናል ብለዋል።

የጥናት ሥራዎችን የሚያከናውን ቡድን ወደ ሥፍራው ልከናል ያሉት የቡድን መሪው የኢንዱስትሪ ፓርኩ የመጀመሪያ ፕላን ማለቁን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የመግባቢያ ስምምነቶችን አድርገናል፣ በቀጣይ ግንቦትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁናን በሚያደርጉት ጉብኝት የኢንዱስትሪ ፓርኩን የሚመለከቱ ስምምነቶች እንፈራረማለን ነው ያሉት።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ከፓርኩ በተጨማሪ በግብርና፣ ትምህርትና ስልጠና እንዲሁም የባህል ትብብር ለማድረግ መክረናል ብለዋል።

በፓርኩ የሚሳተፉ ባለሀብቶች ወደፊት በከተማ ልማት በተለይም በአዳማ አካባቢ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።

ከልኡካን ቡድኑ ጋር የመጡት ባለሀብቶችና ኩባንያዎች በመኪና መገጣጠም፣ በፋርማሲ፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪና በሌሎችም ዘርፎች የሚሰሩ ናቸው።

የኢትዮጵያ-ሁናን ሶስተኛውን ምዕራፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ ከ250 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ በአዳማ ለመገንባት ትላንት ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ በ122 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን ከ12 እስከ 18 ወራት በሚፈጅ ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ 365 ሄክታር የሚሸፍን ሲሆን በመጀመሪያው ምዕራፍ የአልባሳት፣ በሁለተኛው የጨርቃጨርቅና የሁናን ግዛት ድርጅቶች የሚሳተፉበት ሶስተኛው ምዕራፍ ደግሞ የተለያዩ ማምረቻ፣ መገልገያ፣ የግብርናና የግንባታ መሳሪያዎች ይመረቱበታል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 3 /2009 የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ተጠሪ ተቋማት በቤቶች ማስተዳደርና ማስተላለፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት ያለመስራት ተጽእኖ እንዳሳደረባቸው ገለጹ።

ቢሮው የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን በስሩ ከሚገኙ ተጠሪ ተቋማት ጋር ገምግሟል።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት የፕሮጀክት 14 ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብቶም ብርሃኑ በቤቶች ማስተዳደርና ማስተላለፍ የሚታዩ ችግሮችን ከመፍታት አንጻር ቢሮው ክፍተቶች እንዳሉበት ገልጸዋል።

የቅንጅት ችግር በቤቶች ግንባታ መጓተትና ዕጣ ወጥቶላቸው ለዕድለኞች የተላለፉ ቤቶች የመሰረት ልማቶች አለመሟላት ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት እክል እንደፈጠረ ገልጸዋል 

የሚስተዋሉትን ችግሮች ከተጠሪ ተቋማት ጋር በቅርበት በመስራትና የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ቅሬታዎች በተቀናጀ መልኩ ምላሽ መሰጠት አለበት ነው ያሉት አቶ ሀብቶም።

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለ ወርቄ በቢሮው በኩል ለግንባታ የሚውሉ እንደ ግብአት ግዥ ያሉ መዘግየቶች በክፍለ ከተማው የሚገነቡ ቤቶች በታቀደላቸው በጀትና ዓመት እንዳይከናወኑ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ከተጠሪ ተቋማት ጋር በቅንጅት የመስራት ክፍተትን ለማስተካከል ቢሮው የአሰራር ስርአት ሊዘረጋ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ቢሮው ከፅህፈት ቤቱ ጋር በሚፈለገው መልኩ በቅንጅት አለመስራት የጋራ መኖሪያ ቤቶች በታሰበው ጊዜ ለነዋሪው እንዳይተላለፉ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ሐረጎት ዓለሙ ናቸው።

ፅህፈት ቤቱ ግንባታ ለማካሄድ ከቢሮው የሚያስፈልገው በጀት የሚለቀቅበት ጊዜ መጓተትም የቤቶቹ ግንባታ በወቅቱ ተጠናቀው ለተጠቃሚዎቹ እንዳይተላለፍ ምክንያት እንደሆነም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ እንደገለጹት ቢሮው በቤቶች ማስተዳደርና ማስተላለፍ ላይ ያለው የአሰራር ቅንጅት ችግር በግንባታው ዘርፍ ማነቆ በመሆን በቢሮው የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ከተለዩ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል የሚጠቀስ ነው።

ለዚህም ከተጠሪ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ረገድ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ቅንጅታዊ የአሰራር መዋቅር ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ይህም በቤቶች ግንባታ የሚታየውን መጓተትና በታቀደው ጊዜ ለተጠቃሚው አለመድረስ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በተቀናጀ መልኩ ለመፍታት እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።

በቢሮው በኩል ለግንባታ የሚውሉ እንደ ግብአት ግዥ ያሉ መዘግየቶች መንስኤ መንግስት አብዛኛውን ግብአት እየገዛ የሚያቀርብ በመሆኑ ነው ብለዋል።

ይህም በግዥ ወቅት መጓተት እየፈጠረ በመሆኑ ቢሮው የግንባታ ስራ ተቋራጮች ግብአት እንዲያቀርቡ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት እያደረገ መሆኑን አቶ ይድነቃቸው ጠቁመዋል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን