×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Monday, 10 April 2017

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2009 የኳታር ባለኃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን በማፍሰስ የአገሪቷን ልማት እንዲደግፉ ፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ ጠየቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው የኳታር ባለኃብቶች በግብርና ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንቱ የኳታር አሚር ሼህ ታሚም ቢን ሃማድ አል-ትሃኒን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በኢትዮጵያና ኳታር መንግሥታት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቅርቡ መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያና ኳታር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2008 መቋረጡ የሚታወስ ነው።

ለግንኙነታቸው መቋረጥ መነሻ የሆነው ደግሞ ኢትዮጵያ የኳታር መገናኛ ብዙኃን በተለይም አል-ጄዚራ አሸባሪ ተብለው የተሰየሙ ድርጅቶችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንደሚደግፉ ይፋ ማድረጓ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ድርጊቱን በመቃወም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ እንዲቋረጥ አድርጓል።

የኳታሩ አሚር ሼክ ሀማድ ቢን ካሊፋ አል-ታኒ ከሦስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ግን አገራቱ ግንኙነታቸውን ዳግም እንዲያድሱ በር የከፈተ ሆኗል።

በዚህም ኢትዮጵያና ኳታር በትብብር መስራት የሚያስችሏቸውን በርካታ የሁለትዮሽ ስምምነቶች መፈራረም ችለዋል።

ይህን ተከትሎም በተለያዩ የትብብር መስኮች እስካሁን 11 የሚደርሱ የመግባቢያ ሠነዶችና ሥምምነቶች መፈረም ችለዋል።

ፕሬዚዳንት ሙላቱም አሚሩን ባነጋገሯቸው ጊዜ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ሥራ ያስፈልጋታል።

ለዚህ ደግሞ የኳታር ባለኃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ አገሪቷ የምታደርገውን የዕድገት እንቅስቃሴ በመደገፍ ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል።

ለዚህም አሚሩ የበኩላቸውን መጫወት እንደሚገባቸው ነው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ያሳሰቡት።

በሌላ በኩል በሁለቱ አገራት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መካከል የተደረሱ ሥምምነቶችን ገቢራዊ በማድረግ ምጣኔ ኃብታዊ ውህደቱን ማፋጠን እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ጠይቀዋል። 

በተመሳሳይም በፖለቲካው መስክ በቀጣይ ይበልጥ በመሥራት ግንኙነቱ አሁን ካለበት ደረጃ ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባም ገልጸውላቸዋል።

የኳታር አሚር ሼህ ታሚም ቢን ሃማድ አል-ትሃኒ በበኩላቸው የአገራቱን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

በምጣኔ ኃብታዊ ዘርፍ፤ በተለይም በኢትዮጵያ የሚመረቱ የግብርና ውጤቶች በኳታር የገበያ እድል አንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሠላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች እያደረገች ያለውን አበረታች ጥረት በአድናቆት እንደሚመለከቱት ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ለመመከት የሠብዓዊ ዕርዳታ ቡድን በመላክ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸውም አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም በአገራቱ ባለሙያዎች መካከል የሚደረጉ ድርድሮች አሁን ላይ በሚኒስትሮች አሊያም ደግም በመሪዎች ደረጃ ሊቀጥል እንደሚገባ ተነጋግረዋል።

አሚሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኢትዮጵያን ቀዳሚ ማድረጋቸው ለአገሪቷ ያላቸውን አክብሮት የሚያሳይ መሆኑ ተጠቅሷል።

የአሁኑ የአሚሩ ጉብኝትም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ከውጭ ጉዳይና ከፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የኳታር ባለኃብቶች በግብርና ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ጎን ለጎንም በማዕድንና በአገልግሎት ዘርፍ በሥፋት በመሰማራት የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያና ኳታር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1995 ነው።

Published in ፖለቲካ

አዳማ ሚያዝያ 2/2009 አዳማን ከጎርፍ ስጋት ነፃ በማድረግ ልማቷን ለማፋጠን በሚደረገው እንቅስቃሴ የባለሀብቶችና የነዋሪዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች ሀቤቤ አስታወቁ፡፡

በቅርቡ የተቋቋመው የአዳማ ከተማ ባለሀብቶችና ነዋሪዎች የሚገኙበት የባለድርሻ አካላት ምክር ቤት የልማት እቅድ ዛሬ በገልማ አባገዳ አዳራሽ ለህዝብ ይፋ ተደርጓል።

ከንቲባዋ በዚህ ወቅት "የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታት ጎን ለጎን የከተማዋን ልማትና እድገት ለማፋጠን እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንሰራ ይገባል" ብለዋል።

በተለይ ከተማዋ ከጎርፍ አደጋ ስጋት ነፃ ሆና ልማቷን በማፋጠን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ ነዋሪዎችና ባለሀብቶች ከአስተዳደሩ ጎን ተሰልፈው ድጋፋቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ከንቲባዋ እንዳመለከቱት አስተዳደሩ በተያዘው በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ከተማዋን ከጎርፍ የመከላከልና የሞጆ- አዳማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታን ጨምሮ 60 የልማት ፕሮጀክቶችን እያካሄደ ነው።

እነዚህንና ሌሎችንም የልማት ስራዎች ለማሳካት  በየደረጃው የሚገኙ ባለሀብቶች፣ ነዋሪዎችና የሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የአዳማ ከተማ ባለሀብቶችና ነዋሪዎች የሚገኙበት የባለድርሻ አካላት ምክር ቤት የልማት እቅድ ያቀረቡት አቶ ጌታቸው ሂርጶ እንዳሉት ከከተማዋ አስተዳደር በተጨማሪ በ921 ሚሊዮን ብር የተለያዩ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ታቅዷል።

በተለይ ከተማዋን ከጎርፍ ስጋት ለመታደግ በባለሀብቱ፣በአርሶ አደሩና በሌላውም ህብረተሰብ ተሳትፎ በአዳማ ዙሪያ በሚገኙ ተራሮችና በ870 ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ማካሄድ ዋነኛ የእቅዱ አካል ነው።

የከተማዋን ጽዳት ለማስጠበቅ የቆሻሻ ማሰባሰቢያና ማንሻ በየቦታው እንዲቀመጥ ይደረጋል፤  ከመኖሪያ ቤትና  ከንግድ ድርጅቶች አካባቢዎች   ቆሻሻ እንዳይጣል ገደብን የሚያሳይ  የርቀት ሁኔታም በእቅዱ ውስጥ ተካቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የልማት ስራውን ለማስፈጸም የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት በ120 ሺህ ብር ወጪ የውስጥ ቁሳቁስ ተሟልቶለት መደራጀቱም ተመልክቷል፡፡

በምክር ቤቱ 11 ዋናና አምስት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች እንዲሁም በ18ቱም ቀበሌዎች የህብረተሰቡን ተሳትፎ የሚመሩ አካላት ተሰይመው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመጀመር  መዘጋጀታቸውም ተጠቅሷል።

በልማት እቅዱ ላይ የመከሩት የከተማዋ ነዋሪዎች እቅዱን ለማሳካት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ የድርሻቸውን ለመወጣት  ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2009 ለግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጥሬ እቃ በጥራት ለማቅረብ እንዲቻል የአራት ዓመት እቅድ እየተዘጋጀ ነው።

እቅዱ ከ2009 እስከ 2012 ዓ.ም ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፤ ፓርኮች በሚገነቡባቸው አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦች ክልሎች የጥሬ እቃ አቅርቦትን በገበያ ተኮር ክላስተር ለማስተሳሰር ያለመ ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዛሬ በመነሻ እቅዱ ላይ ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት አድርጓል።

በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳሬክተር አቶ አብዱልሰመድ አብዱ የእቅዱን መነሻ ሀሳብ ለውይይት ባቀረቡበት ወቅት፤ ለግብርና ምርት ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጤታማነት የማይቆራረጥ የግብዓት አቅርቦት አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል።

በመሆኑም በተመረጡ ዞኖች በሚገኙ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከላት የሚሰበሰቡ የግብርና ምርት በተደራጀ ሁኔታ ለማቅረብ የሚያስችል እቅድ እየተዘጋጀ ነው።

የእቅዱ ዓላማ በተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለግብዓትነት የሚውሉ ሰብሎችንና የእንስሳት ተዋጽኦ በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ማስቻል ነው።

ለፓርኮቹ የጥሬ እቃ አቅርቦት በጥራት ላይ ትኩረት በማድረግ የሚሰራ ሲሆን፤ የግብርና ምርትንም 20 በመቶ ያሳድጋል ተብሏል።

የህብረት ስራ ማህበራትን የግብይት ፍጥነት አሁን ካለበት 13 በመቶ ወደ 40 በመቶ በማሳደግ የግብአት አቅርቦት ችግር እንዳይከሰት እንደሚያግዘም ነው የተመለከተው።

የሰብልና የእንስሳት ግብአትን በሚፈለገው መጠንና ጥራት በወቅቱ ማቅረብ፣ ግብይትን ማሳለጥ፣ የግብርና ምርት ገበያ ማስፋት፣ የእንስሳት ዝርያን ማሻሻል፣ አቅም ግንባታና ሌሎች በእቅዱ ተካተዋል።

እቅዱ ተግባራዊ በሚሆንባቸው አራት ክልሎች ውስጥ “239 ወረዳዎችን ለይቻለሁ” ያለው ደግሞ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ነው።

የኤጀንሲው ዳሬክተር ዶክተር ተሾመ ዋለ የልየታ ጥናቱን ሲያቀርቡ እንደገለጹት፤ አስር ዋና ዋና ገበያ ተኮር የግብርና ምርቶች ተለይተዋል። ከነዚህ መካከል ስድስቱ የሰብል፣ ሶስት የእንስሳትና የአበባ ምርት ናቸው።

በዓመት ከሚለማው 12 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ስምንቱ ላይ ስንዴና ሌሎች አምስት የሰብል ዓይነቶች በማምረት ከሚያስፈልገው ግብዓት 75 በመቶውን መሸፈን እንደሚቻል አመልክተዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መብራቱ መለሰ እንደገለጹት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የግብአት ፍላጎት ለማሟላት የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ያስፈልጋል።

በግብርናው ዘርፍ ከምርት ጥራት ጀምሮ የተለዩ ችግሮች መኖራቸውን ያነሱት ሚኒስቴር ዴኤታው፤  ለፓርኮች ግብዓት የሚውሉ ምርቶችን በልዩ ሁኔታ ለማምረት ከሚመለከታቸው ጋር እየተሰራ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

”ጥሬ እቃ ማምረት ስራ ለመጀመር ዘግይቷል” ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢንዲስትሪዎች ወደ ስራ ገብተው በግብአት እጥረት እንዳይቆሙና ከውጭ የሚገባውን ለማስቀረት ፍጥነትና ቀጣይነት ባለው መልኩ መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል።

ይህንንም ለማሳካት ለአርሶ አደሩ የተለየ ድጋፍና ስልጠና በመስጠት በፍጥነት ወደ ምርት እንዲገባ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2009 የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን "ስፖርታዊ ጨዋነት አጉድላለች" ሲል አትሌት አማረች ታደሰን ከማንኛውም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለሶሰት ወር  ማገዱን አስታወቀ።

አትሌቷ በበኩሏ ''ውሳኔው አሳዝኖኛል" ብላለች።

ፌዴሬሽኑ  በ34ኛው የፔፕሲ አዲስ አበባ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ላይ "የዲስፕሊን ጉድለት አሳይታለች" ሲል ነው አትሌት አማረች ላይ የእግድ  ቅጣት የጣለው።

በአንደኛና በሁለተኛ ዲቪዚዮን ሲካሄድ የነበረው የክለቦች ሻምፒዮና በአንደኛ ዲቪዚዮን በመከላከያ በዲቪዝዮን ሁለት ደግሞ በካራማራ ክለብ አጠቃላይ አሸናፊነት ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ተጠናቋል።

በዚህ የፍጻሜው ውድድር የመድሃኒዓለም አትሌቲክስ ክለብን በመወከል የአጭር ርቀት ተወዳዳሪዋ አትሌት አማረች ታደሰ  "የአትሌቲክሱን ህግና ደንብ በመጣስ ያለተገባ ባህሪ አሳይታለች" በማለት ለሶስት ወር ያህል በማነኛውም የስፖርት እንቅስቃሴ እንዳትሳተፍ በፌዴሬሽኑ እገዳ ተጥሎባታል።

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢና የክስ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ግርማ አስራት ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አትሌትዋ እገዳ ሊጣለባት የቻለው በ ተንቀሳቃሽ ምሰለ (ቪዲዮ) የተረጋገጠውን ውሳኔ አልቀበልም" በማለት በሜዳሊያ ሽልማት ወቅት የአትሌቲክሱን መርህ በመጣስዋ ነው።

"ዳኞች ሁለተኛ ነች ብለው ውጤቱን ቢያቀርቡም የቤቴል ቲቺንግ ጠቅላላ ሆስፒታል ክለብ ውጤቱ ትክክል አይደለም በማለት ቅሬታ በማቅረቡ  ቪድዮ ለማየት ተገደናል" ብለዋል።

ከተንቀሳቃሽ ምስሉ በተደረገው ማጣራት  አትሌት አማራች ሁለተኛ ሳትሆን ሶስተኛ መውጣትዋን ተረጋግጧል፤ ስለሆነም የአትሌትዋ ደረጃ ሶስተኛ መሆኑን በኮሚቴው ውሳኔ ማግኘቱን ተናግረዋል።

የሶስተኝነት ደረጃን ያገኘችው አትሌት አማረች በሜዳሊያ ሽልማት ስነ ስርዓት ላይ "አንደኛና ሁለተኛ ከወጡ አትሌቶች ጋር ፎቶግራፍ አልነሳም" በማለትና የስፖርቱን ዲስፕሊን በመጣስዋ ሜዳሊያዋን ልትቀማ ችላለች ሲሉም አብራርተዋል።

የአትሌቲክሱ ደንብ ባለማክበሯም ለሶስት ወር ያህልም ከማንኛውም ስፖርትዊ እንቅስቃሴ ተሳትፎ መታገዷንም አስታውቀዋል።

ክለብዋን በመወከል በ200 ሜትር የተወዳደረችው አትሌት አማረች በበኩሏ ''በውድድሩ ሁለተኛ ወጥቼ እያለሁ ተገቢ ባለሆነ መንገድ ውጤቴ ተሰርዞብኛል'' ብላለች።

እንደ አትሌትዋ ገለጻ "ሁለተኛ መውጣቴ በዳኞች ቢመሰከርልኝም ዓመት ሙሉ የለፋሁበትን ውጤት ተሰርዞ በማላውቀው መንገድ የሶስት ወር እገዳ መጣሉ አሳዝኖኛል" ብላለች።

የክለቡ አሰልጣኝ ዓለሙ አኩዙ "አትሌቶቻችን ዓመቱን ሙሉ ለፍተው ነው ለዚህ ውድድር የቀረቡት። ነገር ግን ያመጣናውን ውጤት ተሽሮ እገዳ ተጥሎብናል" ብለዋል።

ፌዴሬሽኑ የዳኞች ውሳኔ ሽሮ "ለሀገር ትጠቅማለች" ተብላ የምትጠበቀው አትሌት ለሶስት ወር ማገዱ አግባብነት የለውም" ሲሉም ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

አሰልጣኙ የተጣለው እገዳም ሆነ የተሻረው ውጤት የአትሌትዋን ብቻ ሳይሆን የክለቡን ሞራል የሚጎዳ መሆኑን ነው የገለጹት።

Published in ስፖርት

 

 አዲስ አበባ ሚያዚያ 2/2009 በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የአገር ባለሃብቶችን በስፋት ለማሳተፍ በበቂ ጥናት የተደገፈ ሥራ ማከናወን እንደሚገባ ተጠቆመ። 

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ባለሃብቶችን በፍጥነት ወደ ሥራ ማስገባት በሚቻልበት ዙሪያ ከፌዴራልና ክልሎች ከተውጣቱ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።        

በዘርፉ ያሉ መልካም አጋጣሚዎች፣ ችግሮች፣ የመፍትሄ ሀሳቦችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።    

የአማራ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የአገር  ውስጥ ባለሃብቶች የሚገጥማቸውን ችግሮች በበቂ ጥናት ለይቶ መፍታት ላይ ክፍተት ይስተዋላል።  

ይህም ባለሃብቱ በስፋት እንዳይሳተፍ ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ነው የገለጹት።   

በተለይም  የሚቀርቡ ማበረታቻዎች የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጡ በጥናት የተደገፈ ዘላቂነት ያለው ተግባር ሊከናወን እንደሚገባ አመልክተዋል።

“የቴክኖሎጂ መረጣና ማላመድ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል” ብለዋል።

የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደሴ አሰሜ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የአገር ውስጥ ባለሃብቱን በብዛት ለማሳተፍ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ዙሪያ የክልሎች ግንዛቤ መስፋት አለበት።    

በሚኒስቴሩ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ትራንፎርሜሽን ዳይሬክተር አቶ ሁነኛው አበባው እንደገለጹት፤ የአገር ውስጥ ባለሃብትን ተሳትፎ ለማሳደግ በቢዝነስ ፕላን ዙሪያ ሚኒስቴሩ መነሻ የሚሆኑ አስር የአዋጭነት ጥናት አካሂዷል።      

ጥናቱ “ባለሃብቶች እንዴትና በምን ዙሪያ ቢያቅዱ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ” የሚሉ ምክረ ሀሳቦችን የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

ጥናቶቹ የተደረጉት በቡና፣ ሰሊጥ፣ በቆሎና በቁም እንስሳት ሃብት ዙሪያ መሆኑን ጠቁመው፤ ሚኒስቴሩ ጥናቱን መሰረት በማድረግ “ለባለሃብቶች የምክር አገልግሎት እየሰጠ ነው” ብለዋል።    

ክልሎች በእውቀት ላይ ተመስርተው ለባለሃብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ለማስቻል በቢዝነስ ፕላን ዙሪያ  ለክልል ኢንዱስትሪ ቢሮዎች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

በገንዘንብ አቅርቦት በኩል የሚታየውን ችግር ለመፍታትም ሚኒስቴሩ ከልማት ባንክ ጋር በመተባበር ለባሃብቶች የሊዝና የፕሮጀክት ፋይናስ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማደረጉን ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ጎንደር ሚያዝያ 2/2009 የከተሞች ፎረም ልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በከተሞች በማጠናከር አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ፋይዳው የጎላ መሆኑን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን ተናገሩ፡፡

ሰባተኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በምታዘጋጀው ጎንደር ከተማ ሕዝባዊ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ መክፈቻ ላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አምባቸው እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም የከተሞችን በጎ ገጽታ በማስተዋወቅ ከተሞች የኢንቨስትመንትና የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

የከተማ ነዋሪዎች በከተማቸው የልማት ዕቅዶችና አተገባበር ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑና ህዝባዊ ንቅናቄን ለመፍጠር አመቺ መድረክ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

"በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የተካሄዱ ፎረሞች ከተሞች በልማት ሥራዎቻቸው ያስመዘገቧቸውን መልካም ተሞክሮዎችና ልምዶችን በአግባቡ ቀምረው እንዲያስፋፉ በማድረግ በኩልም ጠቃሚ ውጤት ተገኝቶበታል" ብለዋል፡፡

ሰባተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ አዘጋጅነት " የከተሞች ዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር ለሕዳሴያችን" በሚል መሪ ቃል ለማክበር ዝግጅቱ መጠናቀቁንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል በበኩላቸው ፎረሙ የከተማዋን ጥንታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶቿን ጨምሮ የንግድ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ሀብቶቹዋን ለማስተዋወቅ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ፎረሙን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የድርጊት መርሃግብር በመንደፍ፣ የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በመክፈትና ባለሙያዎችን በመመደብ የቅደመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፎረሙ በሚካሄድበት ቦታ የመዝናኛ ፓርክ፣ የኤግዚቪሽንና የፈጠራ ሥራዎች ማሳያ፣ የእንግዶች ማረፊያና ማስተናገጃ እንዲሁም የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተፋጠኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በሰባተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከ200 በላይ ከተሞች፤ 20 ታላላቅ የንግድ ኩባንያዎችና አራት የውጪ አገር እህት ከተሞች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከሚያዚያ 21 እስከ 28 ለአንድ ሳምንት በሚቆየው የከተሞች ፎረም ከ10ሺህ በላይ እንግዶች ታዳሚ እንደሚሆኑ ከከተማ አስተዳደር የተገኘውን መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 2/2009 ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት 'ትሬይነር ፕላስ' ሙሉ አባል ሆነች።

አቪዬሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ የ'ትሬይነር ፕላስ' አባል መሆን አገሪቷ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን በመስጠት የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ያስገኝላታል ብሏል።

የአቪዬሽን ቴክኖሎጂዎች እየተስፋፉና እያደጉ በመምጣት ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተጨማሪም የአየር ትራፊክ መጠን እየጨመረ በመሄዱ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሙያዎችን በብዛትና በጥራት ማሰልጠን ወሳኝ ጉዳይ አንደሆነም ይነገራል።

በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የስልጠና ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በቀለ ማዕከሉ ቀደም ሲል በተለያዩ የአቪዬሽን ሙያዎች ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ይገልጻሉ።

"አሁን የሙሉ አባልነት ማረጋገጫ የተገኘበት የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት 'ትሬይነር ፕላስ' አገሪቷ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን መስጠት ያስችላታል" ብለዋል።

በዚህም "የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይቻላል" ነው ያሉት አቶ ተሻለ።

አባልነቱ የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የአቪዬሽኑን የስልጠና ማዕከል አሰራር በመገምገም በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጠው አስተያየትና የግምገማ ውጤት መሰረት የተሰጠ ነው ብለዋል።

የማዕከሉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ያዘጋጁት ደረጃውን የጠበቀ የስልጠና ሰነድና መርሃ-ግብርም ደረጃውን ካስገኙ መስፈርቶች መካከል ናቸው።

የስልጠና ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ለ20 ጅቡቲያዊያን ስልጠና እየሠጠ ሲሆን ባለፈው ዓመት ለሶማሌ ላንድ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ስልጠና መሥጠቱን የባለስልጣኑ መግለጫ አመልክቷል።

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ ሚያዝ 2/2009 ሙስናና ብልሹ አሰራር ሲፈጸም ፊትለፊት የሚጋፈጥ አመራርና ሕዝብ ለመፍጠር በትኩረት መሰራት እንዳለበት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ፡፡

ከሙስና የጸዳች አገር ለመገንባት ሕጻናትና ወጣቶችን በመልካም ስነምግባር በማነጽ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ የኢፌድሪ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ገልጿል፡፡

በስነምግባራዊ አመራርና ተቋማዊ የጸረ ሙስና ስትራቴጂ አዘገጃጃት ላይ ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በሃዋሳ ከተማ ለአንድ ቀን የተዘጋጀ ስልጠና ዛሬ ተሰጥቷል።

በስልጠናው ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ እንዳሉት፣ በተጀመሩ የልማት ሥራዎች የተገኙ ውጤቶች በሙስናና ብልሹ አሰራር እንዳይደናቀፉ አመራሩ ከማንም በላይ ራሱን አጽድቶ መገኘት ይኖርበታል፡፡

በክልሉ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በተደረገ ጥረት አመርቂ ውጤት ቢመዘገብም መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ልማትን ለማምጣት በሚደረገው ርብርብ ውስጥ ዛሬም ሙስናና ብልሹ አሰራር ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

አቶ ደሴ እንዳሉት፣ በክልሉ የልማትና የስርዓቱ አደጋ ተብለው ከተለዩ ተግባራት ውስጥ ጠባብነት፣ የሃይማኖት አክራሪነት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር እንዲሁም የመልካም አስተዳደር እጦት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

ለእነዚህ ሁሉ በዋናነት የሚጠቀሰው ምክንያት ለስልጣን ያለው አተያይ በመሆኑ አመራሩ ራሱን ከዚህ አስተሳሰብ ነጻ በማድረግ በጥልቅ ተሀድሶው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢፌድሪ ስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አሊ ሱሌማን፣ ሙስናን መከላከል በዋናነት የጸረ ሙስና ኮሚሽን ሥራ ብቻ አድርጎ የማየቱ ልምድ ሊቀየር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሙስናን መከላከል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን በመረዳት በተለይ የነገ አገር ተረካቢ የሆነውን ትውልድ በመልካም ስነምግባር በማነጽ ከሙስና ነጻ የሆነች አገር ለመገንባት በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ባለፉት ዓመታት በመንግስት መስሪያቤቶችና የልማት ድርጅቶች ውስጥ ለሙስናና ብልሹ አሰራር አጋላጭ የሆኑ ምክንያቶችን በመለየት ብልሹ አሰራርን የማስተካከል ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በተለይ በመንግስት ግዥዎችና በመሬት አስተዳደር ላይ ትኩረት በማድረግ በተከናወኑ ተግባራት የመንግስትና የሕዝብ ሀብትን ከምዝበራ መከላከል እንደተቻለ ኮሚሽነር አሊ አስረድተዋል።

የደቡብ ክልል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አባይነህ አዴቶ በበኩላቸው፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በ49 የመንግስት መስሪያቤቶችና የልማት ተቋማት በተለያዩ ምክንያቶች ሊመዘበር የነበረ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን እንደተቻለም ገልጸዋል።

ያለ አግባብ ተመዝብሮ የነበረ 146 ሚሊዮን ብር በክስና በድርድር እንዲመለስ መደረጉንም ነው የጠቆሙት።

"በምመራው ተቋም ውስጥ ከብልሹ አሰራር የጸዳና መልካም ስነ ምግባር ያለው ሠራተኛ የመፍጠር ኃላፊነት እንዳለብኝ ከስልጠናው ግንዛቤ እግኝቺያለሁ" ያሉት ደግሞ የክልሉ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን ናቸው።

ለአገሩ የሚቆረቆር ዜጋ ከማፍራት አንጻር የተለያዩ የሴት አደረጃጀቶችን በመጠቀም እናቶች ልጆቻቸው ሙስናና ብልሹ አሰራርን የሚጠየፉ አድረግው እንዲያሳድጉ የማስገንዘብ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው ስልጠና ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  ሚያዝያ  2/2009 ትልቅ የህዋ ተወርዋሪ ዓለት /አስሮይድ/ ወደ ምድር አቅጣጫ እየተምዘገዘገ በመምጣት ላይ መሆኑን የአሜሪካን የጠፈር ምርምር ተቋም/ናሳ/ አስታወቀ።

ናሳን ጠቅሶ ሲ. ኤን. ኤን እንደዘገበው በጠፈር ውስጥ በመጓዝ ወደ ምድር አቅጣጫ በመምጣት ላይ ያለው ግዙፍ አለት/አስሮይድ/ ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ለምድር ቢቀርበም የመጋጨት እድል ስለሌለው የሚያደርሰው አንዳች ጉዳት አይኖርም።

ይሁን አንጂ ወደ ምድር ከቀረቡ ተመሳሳይ ሰማያዊ ዓለቶች መካከል የአሁኑ በግዝፈቱ ከቀደሙት የላቀ መሆኑን ናሳ አስታውቋል፤ ሆኖም ከምድር ጋር የመላተም ዕድል ስለሌለው የሚያሰጋ እንዳልሆነም ገልጿል።

ናሳ'ኒዎ ዋይዝ ስፔስፐሮብ' በተሰኘ ሳይንሳዊ ዘዴ ተወርዋሪ ዓለቱን ለክቶ ግዝፈቱ ሁለት ሺ ፊት/650 ሜትር/ እንደሆነም አስታውቋል። ይህም የአንድ እግር ኳስ ሜዳ ስፋት እንዳለው ጠቁሟል።

ተወርዋሪው ዓለት "መሬትን በምን ያህል ርቀት ይቀርባታል?" የሚለውን ጥያቄ ናሳ ሲመልስ፤ ሁለት ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ያህል እንደሚቀርብ ይህም ከጨረቃ ጋር ካለው  ርቀት ጋር ሲነጻጸር ጨረቃ ከምድር ካላት 384ሺ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት በአራት ነጥብ ስድስት ጊዜ የሚበልጥ ነው።

በዚህ ርቀት በሳምንት ውስጥ ብዛት ያላቸው ትናንሽ የህዋ አለቶች በጥቂቱ የሚያልፉ  ቢሆንም፤  ከ13 ዓመታት በፊት እ.አ.አ. 2004 ከተከሰተው ቱታቲስ ከተሰኘ የህዋ ተወርዋሪ ትልቀ አለት ቀጥሎ ይህ በጣም የቀረበና ትልቁ ነው። 

አዲስ አበባ ሚያዝያ/2009 ትምህርት ሚኒስቴር ልዩ ድጋፍ በሚሹ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ክልሎች የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሰራ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል።

ልዩ ድጋፍ በሚሹ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ክልሎች በርካታ ሥራዎች ቢሰሩም የትምህርት ጥራት ከማረጋገጥ አንጻር ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ገዛኸኝ ጠቁመዋል።

ለደረጃው የሚመጥኑ የሰለጠኑ ርዕሰ መምህራን አለመኖር፣ የመማሪያ መፅሃፍት እጥረትና ስርጭት ችግር፣ የተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ከምዝገባ ባለፈ አለመተግበር ቅንጅታዊ አሰራር ከሚጠይቁ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።

ሴቶችን አስልጥኖ ወደ አመራርነት ያለማምጣት፣ ለትምህርት የደረሱ ህጻናትን ወደ ትምህርት ቤት አለመላክና የልማት ሠራዊት አደረጃጀት በሙሉ ቁመና ላይ አለመገኘትም ለትምህርት ጥራት አለመረጋገጥ ምክንያቶች ናቸው።

ፕላዝማዎች የሚያጋጥማችው የኃይል አቅርቦትና የኔትወርክ ችግር ተማሪዎች ከቴክኖሎጂ ጋር እንዳይዛመዱ ብቻ ሳይሆን ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ነው ሲሉ ምክትል ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

በመሆኑም ልዩ ድጋፍ በሚሹ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ክልሎች የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ፓኬጁን ውጤታማ ለማድረግ ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ ይገባል።

ሚኒስቴሩ የድርቅ አደጋ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ህፃናት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ለምገባ መርሃ-ግብር አስፈላጊ ግብዓት እንዲሟላ ማድረጉን አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።

በአርብቶ አደር ክልሎች የትምህርት ጥራት ውስብስብ ባህሪያት ቢኖሩትም ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረገ ልዩ ስልት ነድፎ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የማስተሳሰር ተግባር ተከናውኗል።

ይህም ዝቅተኛ የነበረው አገር አቀፍ የፈተና ውጤት ከፍ እንዲል ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጠው አስተያየትና ግብረ-መልስ ገንቢና በግብዓትነት የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።

በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ክልሎች የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ደረጃውን የሚመጥኑ የሰለጠኑ ርዕሰ መምህራን እንዲኖሩ ለማድረግ ልዩ ድጋፍ ከሚሹ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ክልሎች ርዕሰ መምህራን ያለ ኮታ እንዲሰለጥኑ እየተደረገ ነው።

የተማሪ መፅሃፍት ጥምርታ በደረጃው መሰረት እንዲሆን ለማድረግ ጥረት ቢደረግም የክልሎች መፅሃፍቶችን በወቅቱ ያለማሳተምና የታተሙትንም ያለማሰራጨት ችግሮች እንደሚስተዋሉ አመልክተዋል።

ለጎልማሶች ትምህርት አለመተግበር የክልሎች ግንዛቤ ማነስ፣ የአመራሩ የባለቤትነት ስሜት ማጣት፣ ድጋፍ ከማዕከል ብቻ መጠበቅ፣ በቂ በጀት ያለመመደብና መፅሃፍት ያለማሳተም ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ችግሩን ለመፍታትና የትምህርት ልማት ሠራዊት ለመገንባት እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት ባሻገር ቅንጅታዊ አሰራሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በፕላዝማ ትምህርት ወቅት የሚያጋጥመውን የኤሌክትሪክና ኔት-ወርክ መቆራረጥ ችግር ለማስወገድም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በራሱ የሚተማመንና ኩረጃን የሚጠየፍ ትውልድ ለማፍራት የሚሰጠው የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን