Items filtered by date: Saturday, 01 April 2017

መንበረ ገበየሁ ከሃዋሳ ኢዜአ

ገነት ወጣትነቷ ስቃይዋን የቀነሰላት ትመስላለች ። በማዕከሉ ህክምና ከሚያገኙ እንስቶችም በእድሜ ትንሿ ናት፡፡

ሌንደዴ ሌራ ደግሞ ገምታ ከነገረችን እድሜዋ ጋር ለአስራ አምስት ዓመታት የተሰቃየችበት የፌስቱላ ህመም ተዳምሮ የመውለድ ህልሟን እንዳያጨልመው ስጋት ውስጥ ገብታለች፡፡

በይርጋለም ሃምሊን የፌስቱላ ማዕከል ያገኘናቸው እነዚህ  እንስቶች ከተለያየ አካባቢ ከተለያየ ማህበረሰብ ውስጥ የመጡ ቢሆንም ከማህበረሰቡ የሚደርስባቸው መገለልና በደል የተነሳ የሚያመሳስላቸው በርካታ ነገሮች አሉዋቸው፡፡

እነሱን ጨምሮ በህክምና ማዕከሉ 47 እናቶች በተፈጥሮ የታደሉትን የእናትነት ጸጋ ለመቀበል በሚያልፉበት ሂደት የገጠማቸው ረዥም ምጥ ለፌስቱላ ህመም ዳርጎዋቸው ወልደው መሳም አልቻሉም፡፡

ከህመሙ ባለፈ በፌስቱላው ምክንያት የሚፈጠረው መጥፎ  ጠረን  ከማህበረሰቡ እንዲገለሉ በማድረጉ የደረሰባቸው የስነ ልቦና ጫና በህክምና የሚድን አይደለም፡፡

ትናንት በፍቅር በአንድ ጎጆ አብረዋቸው የነበሩ የትዳር አጋሮቻቸው ጭምር ፊታቸውን አዙረውባቸዋል ። አንዳንዶቹም በሌላ የትዳር አጋር የተኳቸው በመሆኑ ሰው ይፈልጋሉ ። ችግራቸውን ተቀብሎ በሽታው በህክምና እንደሚድን አምኖ አይዟችሁ የሚል፡፡

የ17 ዓመቷ ገነት አሰፋ ከብዙዎቹ እድለኛ ሴቶች መካከል አንዷ ትመስላለች ። አለሁልሽ የሚላት የትዳር አጋሯ ላለፈው አንድ ዓመት በህመሙ ምክንያት በተፈጠረው መጥፎ ጠረኗ ሚስትነቷን ተቀብሎ አስታሟታል ።  ህክምና እንድታገኝም ወደ ማእከሉ አምጥቷታል፡፡

ከቤተሰቦቿም አባቷ ተስፋ ቆርጠው ምን ዋጋ አለሽ አሏት እንጂ እናቷ ከጎኗ ናቸው፡፡ ለዚህም ይመስላል ገነት ተስፈኛ ሆና ፍልቅልቅ የምትለው፡፡

በከምባታ ጠምባሮ ዞን በአንዲት የገጠር መንደር ውስጥ በጨቅላ ዕድሜዋ የመሰረተችው ትዳር ፍሬ አፍርቶ ልጅ አላሳቀፋትም፡፡

ያለእድሜ ጋብቻ ሲደመር 3 ቀናትን የፈጀ ምጥ ለፌስቱላ ህመም አጋልጧት በይርጋለም ሃምሊን የፌስቱላ ማዕከል ትገኛለች፡፡

በህመሙ ምክንያት ሽንቷን መቆጣጠር እንደማትችል የገለጸችው ገነት በዚህ መጥፎ ጠረን ሳቢያ ላለፈው አንድ ዓመት ከሰዎች ተቀላቅላ እንደማታውቅ ነው የነገረችን፡፡

ዛሬ በማዕከሉ በሚደረግላት ህክምና ከህመሟ እያገገመች ቢሆንም ፊኛዋ አካባቢ በተፈጠረ ችግር ሙሉ በሙሉ ሽንት መቆጣጠር አላስቻላትም፡፡ ለዚህም ወደ አዲስ አበባ ሄደው ህክምና ከሚያገኙ እንስቶች አንዷ ሆናለች፡፡

እንደ ትናንቱ ሽንት ባለመቆጣጠሯ ምክንያት የሚፈጠር ጠረን የለም ። ህመሙ ቀንሶላታል። ግን ደግሞ ከበሽታው ሙሉ በሙሉ ድና ወደ ትውልድ ቀየዋ -ወደ ልጅነት ትዳሯ መመለስ ናፍቃለች፡፡

ተገቢውን ህክምና አግኝታ የእናትነት ህልሟን እንደምታሳካም እምነቷ የጸና ነው፡፡

ለአስራ አምስት ዓመታት በህመሙ መሰቃየቷን የምትናገረው ሌንደዴ ሌራ ደግሞ ከወላይታ ዞን ዳሞት ጋሌ ወረዳ ነው የመጣችው፡፡

በልጅነት ትዳር መስርታ የልጅ እናት የመሆን ህልሟን ልትኖር ስትጠብቅ በገጠማት የቀናት ምጥ ጽንሱ በሆዷ ውስጥ ጠፍቷል ። እሷም ለፌስቱላ ህመም ተጋልጣለች፡፡

በዚህ ምክንያት ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት ከማህበረሰቡ ተገላለች ። የትዳር አጋሯም  አላውቅሽም ብሏት ስቃይ የተሞላበት ህይወት አሳልፋለች፡፡

ሌንደዴ ከአስራ አምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ በዞኑ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ፅህፈት ቤት አማካይነት ባገኘችው መረጃ በሃምሊን የፌስቱላ ማዕከል ተገቢውን ህክምና አግኝታ መዳኗን ትናገራለች፡፡

ስቃዩን ረስታ ከቆየች ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ማህጸኗ አካባቢ የተፈጠረው ጠጣር ነገር በቀዶ ህክምና ሲወጣ ህመሙ በድጋሚ ተከስቶ በፌስቱላ ማዕከሉ መጥታ ነው የተገናኘነው፡፡

በማዕከሉ የሚደረግላት ህክምናና እንክብካቤ በማህበረሰቡ ምክንያት የደረሰባትን ስነልቦናዊ ጫና ከማስቀረቱ ባለፈ እርስ በርስ የመወያየት እድሉን ፈጥሮ  ከበሽታው የተፈወሱትን በማየቷ ነገን በተስፋ እንድትጠብቅ አድርጓታል፡፡

በግምት ሰላሳዎቹ አጋማሽ ላይ የደረሰችው ሌንደዴ እድሜና ጤና ሰጥቶ የልጅ እናት የመሆን ተስፋዋ እውን ሲሆን እስከ አራት ልጆች እንዲኖራት ትፈልጋለች፡፡

ይህ የአብዛኞቹ  በማዕከሉ የሚገኙ እንስቶች እናትነት የመናፈቅ  ጥሪ ነው፡፡ እናትነትን ናፍቀው ህጻናቱን ሳያቅፉ፣ እንደገናም ለፌስቱላ ተጋልጠው በዚህ ምክንያት ከማህበረሰቡና ከትዳር አጋሮቻቸው ጭምር ተገለው ለመኖር የተገደዱ እናቶች፡፡  

ሌላኛዋ በማዕከሉ ያገኘናት ከሌሎቹ በተለየ እናት ሆናለች፡፡ ለችግሩ የተጋለጠችው በሶስተኛ ልጇ ወሊድ ወቅት ነው፡፡ ከህመሙ በላይ የሁለት ልጆቿ መበተን አሳዝኖዋታል፡፡ የትዳር አጋሯ የሁለት ልጆቿ አባት ከሌላ ሴት ጋር ሌላ ጎጆ መመስረቱና ወላጆቿን በሞት ማጣቷ አንገቷን አስደፍቷታል፡፡

ወጣት ያቤቴ ሽኩሬ ትባላለች ። ከሃላባ ልዩ ወረዳ ነው የመጣችው፡፡ ሶስተኛ ልጇን ስትወልድ በገጠማት ረዥም ምጥ ምክንያት ለፌስቱላ ህመም ተጋልጣ ላለፉት ሁለት ዓመታት በበሽታው ተሰቃይታለች፡፡   

ያቤቴ ወጣት ናት  ። ከህመሙ በላይ ብቸኝነቱ ጎድቷታል። የትዳሯ አጋር የልጅነት ፍቅረኛዋና የልጆቿ አባት በሌላ ሴት ተክቶአታል፡፡ በበሽታው ምክንያት ያገለሉዋትን ሰዎች ቁጥር ብዙ ናቸው ፡፡ በመሆኑም ማዕከሉ ተገቢውን ህክምና አድርጎላት ሙሉ በሙሉ ከህመሙ መዳንና አዲስ ህይወት አዲስ ማንነት እንዲኖራት ትፈልጋለች፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በቅርቡ የተካሄደ ጥናትን ዋቢ አድርጎ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ከ36 ሺህ እስከ 39 ሺህ የሚደርሱ ሴቶች በተራዘመ ምጥ ምክንያት የፌስቱላ ተጠቂዎች ሆነዋል፡፡ በየዓመቱም 3 ሺህ 750 የሚሆኑ አዳዲስ እናቶች በፌስቱላ ይያዛሉ፡፡

እንደ ባለሙያዎች ገለጻ በተራዘመ ምጥ ምክንያት የሚፈጠረው ፌስቱላ በማህጸንና በፊኛ ወይም በሰገራ መውጫ /ደንዳኔ/ መካከል የሚፈጠር ቀዳዳ ነው፡፡

የተራዘመ ምጥ ያጋጠማት እናት በሰለጠነ ባለሙያ ካልታገዘች ምጡ ቀናትን ያስቆጥራል፡፡ በዚህ ጊዜ የህጻኑ ጭንቅላት በማህጸን በር ለመውጣት በሚያደርገው ግፊት ምክንያት የፊኛ ከረጢትና የሰገራ መውጫ /ደንዳኔ/ ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር የደም ዝውውር እንዲቋረጥ ያደርጋል፡፡

በዚህ ወቅት በአካቢቢው የሚገኙ ስስ የስጋ ክፍሎች እንዲጎዱ በማድረግ ፌስቱላ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡

ለፌስቱላ መንስኤ ከሚሆኑ ምክንያቶች ቀዳሚው የተራዘመ ምጥ ሲሆን በጤና ተቋማት በሰለጠነ ባለሙያ አለመውለድና የድንገተኛ ቀዶ ህክምና የማዋለድ አገልግሎት በበቂ ደረጃ ያለመኖርም ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ያለእድሜ ጋብቻን የመሳሰሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትና ድህነት ለፌስቱላ መከሰት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡

በይርጋለም ሆስፒታል የሃምሊን የፌስቱላ ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ ደስታ ፌስቱላ በህክምና መዳን የሚችል መሆኑን ገልጸው 600 ህሙማንን የማከም አቅም ባለው ማዕከል ውስጥ ላይ 300 ብቻ እንደሚያክሙና የበሽታው ተጠቂዎች በማህበረሰቡ በሚደርስባቸው መገለል ምክንያት ህክምናውን ፈልገው እንደማይመጡ ተናግረዋል ።

በማዕከሉ 20 እና ከዚያም በላይ ዓመታት በህመሙ የሚሰቃዩ አብዛኞቹ ሴቶች ከትዳር አጋሮቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ጭምር መገለል ደርሶባቸው ለበሽታው ጊዜያዊ መፍትሄ እየሰጡ ከቤታቸው መቀመጥን የሚመርጡ በመሆናቸው ለከፍተኛ የአእምሮ ጭንቀት እንደሚጋለጡም ገልፀዋል፡፡

መንግስት በ2020 ፌስቱላን ከሃገር ለማጥፋት በነደፈው ስትራቴጂ ቤት ለቤት በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙና ባለሙያዎች አማካይነት የሚሰራው ስራ ከተጠናከረ ግን በርካታ እናቶችን የማግኘት እድሉ ከፍተኛ በመሆኑ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያምናሉ ። የሚሰሩበት ተቋምም ከቀደመው በተሻለ ከመንግስት ጋር ይሰራል ፡፡

በሃገሪቱ በሚገኙ ስድስት የሀምሊን ህክምና ማዕከላት አገልግሎቱ በነጻ እንደሚሰጥና በደቡብ ክልል ይርጋለም ሆስፒታል በፈረንጆቹ 2006 ዓ.ም መጨረሻ ህክምና መስጠት ከተጀመረ ወዲህ ከክልሉ ብቻ ከ1ሺሐ በላይ እናቶች ህክምና ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁን ወቅትም 47 የሚደርሱ እናቶች ከደቡብና ኦሮሚያ ክልል መጥተው ህክምናውን በማግኘት ላይ ሲሆኑ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥም ሙሉ ወጪያቸውን ችሎ ወደ አዲስ አበባ እንደሚላኩ ገልጸዋል፡፡

አቶ አማረ በረጅም ጊዜ በማዕከሉ የቆይታ ልምዳቸው የገጠማቸውን ሲናገሩ የፌስቱላ ተጠቂ እናቶች ስቃይ ከባድ በመሆኑ የሁሉም ወገኖች  ድርሻ ይጠይቃል ። በተለይም የቤተሰብና የትዳር አጋር ሚና ከፍተኛ ነው ይላሉ፡፡

ህክምናውን አግኝተው ሙሉ በሙሉ ድነው የሚወጡ እናቶችም ከባድ ስራዎችን ባለመስራት፣ ወደ ግብረስጋ  ግንኙነት ፈጥኖ ባለመግባትና ቢያንስ ለሁለት ዓመት ከመውለድ ቢታቀቡ ይመረጣል ብለዋል፡፡

የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም እ.ኤ.አ በ2020 በተራዘመ ምጥ ምክንያት የሚፈጠረውን ፌስቱላ ከሃገር ለማጥፋት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የድርጊት መርሃ ግብር አዘጋጅቷል፡፡

በደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶችና ህጻናት ጤናና ስርዓተ ምግብ አገልግሎት ዋና ስራ ሂደት ባለቤት አቶ ሽመልስ ዋንጋሮ እንደገለጹት እቅዱን ለማሳካት ስራው በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካይነት የሚከናወን ይሆናል፡፡

በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካይነት የሚተገበረው የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ በሃገሪቱ መከላከልን መሰረት ያደረገው የጤና ፖሊሲ ውጤታማ እንዲሆን ካደረጉ እቅዶች ቀዳሚው መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሽመልስ በእናቶችና ህጻናት ጤና ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል፡፡

በመሆኑም ፌስቱላን በ2020 ከሃገር ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካይነት የፌስቱላ ህመምተኞችን የመለየት ስራ ይሰራል፡፡

በተጨማሪም ቤት ለቤት ከሚደረጉ የኩፍኝና ፖሊዮ ክትባት ዘመቻዎች በተጓዳኝ  የበሸታውን ተጠቂዎች በመለየት ህክምናውን እንዲያገኙ እንደሚደረግና በዘንድሮው ዓመትም በወላይታ ዞን ብቻ 30 እናቶች መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ቤት ለቤት በሚደረግ ክትትል የተለዩ እናቶች በአቅራበያቸው ወደሚገኝ ጤና ተቋም ሄደው በትክክል የፌስቱላ ተጠቂዎች መሆናቸውን ለመለየት በየጤና ጣቢያው ለሚገኙ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ያስረዳሉ ፡፡

በክልሉ በሴቶች ልማት ቡድን የተደራጁ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ሴቶች በጤናው ዘርፍ በሚወያዩባቸው የኤክስቴንሽን ፓኬጆች ላይ በፌስቱላ ተጠቂ የሆኑ እናቶች መኖራቸውን ለይተው እንዲሰሩባቸው አቅጣጫ በመቀመጡ ፌስቱላን ለማጥፋት የተያዘውን እቅድ ማሳኪያ መሳሪያዎች ናቸው፡፡

ቀድሞ የተያዙትን ወደ ህክምና በማምጣት ነጻ አገልግሎት አግኝተው እንዲታከሙ ሲደረግ አዳዲስ እናቶች የበሽታው ተጠቂ እንዳይሆኑ ደግሞ የጤና ተቋማት በተገቢው መሳሪያ ማደራጀትና የእናቶች የወሊድ አገልግሎት በሰለጠነ ባለሙያ እንዲታገዝ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት ፡፡

ሃምሊን የፌስቱላ ህክምና ማዕከል በስድስት ማእከላቱ ላለፉት 50 ዓመታት በህመሙና በህመሙ ምክንያት በሚፈጠረው ጠረን ከማህበረሰቡ የሚገለሉ፣ የስነ ልቦና ጫና ለደረሰባቸው ከ45 ሺህ  በላይ እናቶች የፌስቱላ ቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠቱን ከማእከሉ የተገኘው መረጃ ያስረዳል ።

Published in ዜና ሓተታ

ሰመራ መጋቢት 23/2009 በአፋር ክልል የከተሞችን ዕድገት ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው  ክልል አቀፍ የከተሞች ቀንን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሰመራ ከተማ አክብሯል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር መሀመድ እንደተናጉት ከሃያ ዓመት በፊት በክልሉ የነበሩ ከተሞች ከአምስት የማይበጡ ነበሩ።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎችና በተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች በአሁኑ ወቅት የከተሞቹ ቁጥር ከ40 በላይ መድረሱን ተናግረዋል።

ይሁንና ከተሞቹ ደረጃቸውን የጠበቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አደረጃጀትና ማስተር ፕላንን ተግባራዊ በማድረግ በኩል ችግሮች በስፋት መኖራቸውን አስረድተዋል።

ችግሩን ለመፍታት፣ ቢሮው የክልሉን ከተሞች አደረጃጀት በማጥናት የክልሉን ከተሞች በደረጃ በመክፈል በከንቲባ፣ በማዘጋጃና በመሪ ማዘጋጃ ደረጃ እንዲቋቋሙ የሚያስችል የአደረጃጀት ማንዋል አዘጋጅቶ ወደሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

እንደ አቶ አብዱልቃድር ገለጻ፣ ማስተር ፕላንን ተግባራዊ የማድረግ ሥራው በባህሪው ከካሳ ክፍያና መሰረተ ልማት ዝርጋታ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ በጀት ይጠይቃል።

በመሆኑም ክልሉ እስካሁን ድረስ ያለውን ውስን ሃብት ለማህበራዊ ልማት ቅድሚያ ስለሚሰጥ በሙሉ አቅም ወድስራ አለመግባቱን  አስረድተዋል

በቀጣይ የከተሞቹን ማስተር ፕላን ወድመሬት በማውረድ ከተሞቹ ከሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪና ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የሰመራ-ሎግያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አህመድ ኢቦ በበኩላቸው፣ ከተማዋ በአስተዳደር ደረጃ ከተቋቋመች አጭር ግዜ ቢሆናትም መሪ ፕላኑን መሰረት ያደረገ ፈጣን እድገት እያሳች መሆኗን ተናግረዋል።

በቀጣዮቹ ዓመታት የሎግያ-ሰመራ ከተማን ማስተር ፕላን ተግባራዊ ለማድረግና የውስጥ ለውስጥ መንገዶችንና ተያያዥ መሰረተ ልማቶችን ለማከናውን ሰፊ ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል። 

ከዚህ በተጨማሪ በጥልቅ ተሃድሶ የተለዩና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተስተዋሉ መልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን ለመፍታት አስተዳደሩ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ አህመድ እንዳሉት፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር የተያያዙ ችግሮችንም ደረጃ በደረጃ ለመፍታት አስተዳደሩ እየሰራ ይገኛል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሃመድ ሁሴን በበኩላቸው እንዳሉት፣ አገሪቱ የተከተለችው የፌዴራል ሥርአት ባለፉት ዓመታት በክልሉ ተጨማሪ ከተሞች እንዲፈጠሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

ይሁንና ከተሞቹ ዘርፈ ብዙ የመሰረተ-ልማትና ተያያዥ ችግሮች ያሉባቸው በመሆኑ እነዚህን ችግሮች በመፍታት ከተሞቻችን ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ አመልክተዋል።

በዚህ ረገድ ባለድርሻ አካላት የበለጠ ተቀራርበው በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ለሁለት ቀን የተካሄድው ክልል አቀፍ የከተሞች ቀን መድረክ የከተሞች ተወካዮችና ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ከ150 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ በክልሉ ያሉ ከተሞችን የእድገት ጉዞ ሚያሳይ መነሻ ፅሁፍ ቀርቦ ሰፊ ውይይት መደረጉ ተገልጿል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ነቀምቴ ጊምቢ መጋቢት 23/2009 ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማምክን በሚደርገው ትግል ውስጥ በንቃት በመሳተፍ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በነቀምቴና በጊምቢ ከተሞች የሚገኙ የኦህዴድ አባላትና ደጋፊዎች ገለጹ፡፡ 

27ኛው የኦህዴድ ምስረታ በዓል ትናንት በነቀምቴ ከተማ በፓናል ውይይት በተከበረበት ወቅት ከተሳተፉት መካከል ወይዘሮ ቦጋለች መንገሻ እንደተናገሩት ድርጅቱ ባደረገው ትግል የሴቶች እኩልነትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ ችሏል።

በተለይ ድርጅቱ ለድሃውና ለአቅመ ደካማ ህብረተሰብ ክፍል የቆመ መሆኑን ጠቅሰው ከድርጅቱ ጎን በመሰለፍ ጸረ-ሙስና ትግሉ ውስጥ በንቃት በመሳተፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

ሌላው የበዓሉ ተካፋይ ወጣት ደሳለኝ በኮንጃ በበኩሉ " ግለኝነትንና በአቋራጭ የመበልጸግ አባዜ ተረባርበን ልንመክት ይገባል" ብሏል።

የክራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባር ለመግታት በሚደረገው ጥረት በንቃት በመሳተፍ ለኦህዴድ ያለውን ድጋፍ  በተግባር  ለማሳየት ዝግጁ መሆኑንም ጠቅሷል።

በከተማዋ የዜሮ ሶስት ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አሰለፈች ታደሰ ድርጅቱ ከድል ወደ ድል በመሸጋገር ላይ ቢሆንም በሂደት ያጋጠሙትን ፈተናዎች ትኩረት ሰጥቶ መፍታት እንደሚገባው ጠቁመዋል።

በተለይ በተሃድሶ መድረክ ከህዝቡ የተነሱትን ቅሬታዎች ጊዜ ሳይወስድ ለመፍታት በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀው ከሳቸው የሚጠበቀውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አስመራ እጃራ በበኩላቸው "  በዓሉን  ስናከበር ኪራይ ሰብሳቢነት ለማስወገድ  የጀመርነውን ርብርብ ከዳር ለማድረስ የመነሳሳት መንፈስ በመላበስ ነው "ብለዋል።

በተመሳሳይ በዓሉ በጊምቢ ከተማ በተከበረበት ወቅት የተሳተፉት የድርጅቱ ደጋፊ አቶ ቡልቲ ደሳለኝ እንዳሉት በዓሉን  ሲያከብሩ በድርጅቱ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሙስናን ለመታገል ዝግጁነታቸውን በማረጋገጥ ነው።

ወይዘሮ ጫሌ ተሬሳ  የተባሉት የከተማው ነዋሪ  በበኩላቸው ድርጅቱ ለክልል ህዝብ የሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ምንጭ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚደግፉት ተናግረዋል፡፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል፡፡

የምዕራብ ወለጋ ዞን  ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሁንደሳ ሊካሳ እንደገለጹት የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት ከጨቋኝ ስርዓት እራሱን ነጻ ለማውጣት ሲታገል ቆይቷል።

ኦህዴድ በተበታተነ መልኩ ሲያካሂድ የነበረውን ትግል በተደራጀ መንገድ በመምራት የኦሮሞ ህዝብ የሚኮራበትን ድል ከማስመዝገቡም ባለፈ  ህዝቡን የልማት ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

Published in ፖለቲካ

መቀሌ መጋቢት 23/2009 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፊል የግንባታ ስራ በራስ አቅም እየተካሄደ መሆኑ ሊመጣ የሚችለውን የውጭ ጫና እንዳቃለለ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አስታወቁ።

የትግራይ ብዙሀን መገናኛ ተቋም የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በመቀሌ ከተማ ያዘጋጁት የፓናል ውይይት ዛሬ ተካሂዷል፡፡

ሚኒስትሩ በፓናል ውይይቱ ወቅት እንዳሉት፣ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ግንባታ ሲታሰብ አብሮት ሊመጣ የሚችል የፋይናንስ፣ የዲፕሎማሲና ሌሎችንም ተፅኖዎች አስቀድሞ መለየት ተችሏል፡፡

በግልገል ጊቤ ሶስት ግድብ የግንባታ ፕሮጀክት ላይ ካጋጠሙት ፈተናዎች ትምህርት በመውሰድ ሥራውን ሙሉ በሙሉ ለውጭ ተቋራጮች ከመስጠት ይልቅ ከፊል ስራዎች በራስ አቅም እየተካሄደ በመሆኑ የተለያዩ ጫናዎችን መቀነስ አስችሏል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳመለከቱት ሳሊኒ የሲቪል ስራዎች እንዲያከነውን ሲደረግ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ደግሞ በሃገር መከላከያ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ይህም ያጋጥም የነበረው የግንባታ መስተጓጎልና የውጭ ምንዛሪን ከመቀነስ ባለፈ ሌሎች ሜጋ ግድቦችን ለመገንባት የቴክኖሎጂና የእውቀት አቅም መገኘቱንም ጠቁመዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ አሁን 57 በመቶ የደረሰ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ደብረጽዮን ፣ " የፕሮጀክቱ አካል የሆኑ የሳድል ግድብ፣የኤሌክትሮ ሜከኒካል ስራዎችና ሌሎችን ጨምሮ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ከተጠናቀቁትም መካከል የሳብስቴሽንና ባለ 500 የሀይል ማስተላለፊያ ግንባታ ይገኝበታል፡፡

የግድቡ ግንባታ በጥሩ ፍጥነትና ምቹ በሆነ ሁኔታ መቀጠሉን ጠቅሰው እስከ አሁንም 50 ቢሊዮን ብር ወጪ መሆኑን ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

ዳሬሰላም መጋቢት 23/2009 "ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ታላቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ መገንባቷ አገሬ የተፈጥሮ ሃብቷን በአግባቡ እንድትጠቀም መንገድ አሳይታለች" ሲሉ የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ጆን ፖምቤ ጆሴፍ ማጉፉሊ ዳሬሰላም ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በተለይም ግንባታው ከተጀመረ ነገ ስድስተኛ ዓመት ስለሚሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲገልጹ "ከኢትዮጵያ አልፎ ለታንዛኒያም ትርጉም አለው" ነው ያሉት  ፕሬዚዳንቱ።

“የአባይ ውሃ የጋራ ሃብት በመሆኑ አጠቃቀሙ ሁሉንም አገሮች ያማከለና የማንንም ጥቅም የማይነካ መሆን አለበት” ብለዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታላቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እየገነባች "መንገዱን አሳይታናለች" ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የማመንጨት አቅም ወደ 6 ሺ 450 ሜጋ ዋት አድጓል።

ታንዛኒያ እስካሁን 1 ሺ 500 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ነው ያላት፤ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ሃይል ሚያስፈልጋት በመሆኑ “የኢትዮጵያን ተሞክሮ መውሰድ አለብን” ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ።

“ተፈጥሮ አድሎናል፤ ነገር ግን አልተጠቀምንበትም፤ እናንተ ስትራቴጂና ቴክኒክ አላችሁ። እኛም ሃብታችንን በአግባቡ እንድንጠቀምና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እንድንገነባ የባለሙያ እገዛ ልታደርጉልን ይገባል” በማለት ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ታላቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ መገንባት በመጀመሯ “አገሬ የተፈጥሮ ኃብቷን በአግባቡ እንድትጠቀም መንገድ አሳይታለች” ሲሉም ነው ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ የገለጹት።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሌሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ አገራቸው 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛት እንደምትፈልግ ጠቁመዋል።

በኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ ታንዛኒያ ከኢትዮጵያ ተሞክሮ በመውሰድ የአገሪቷን የኃይል እጥረት የማቃለልና ዘርፉንም ተወዳዳሪ የማድረግ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ፕሬዚዳንቱ ማጉፉሊ፤ ታንዛኒያ በቴሌኮም ዘርፍም የኢትዮጵያን ተሞክሮ መጋራት እንደምትፈልግ መግለጻቸውንም ነው ኢዜአ ከስፍራው የዘገበው።

“በታንዛኒያ በርካታ የቴሌኮም ኩባንያዎች አሉ፤ ኢትዮጵያ ያላት ግን አንድ ነው፤ ይሁንና የእኛዎቹ ተደምረው የሚያስገኙት ውጤት ከኢትዮጵያ ጋር አይወዳደርም፤ የእነርሱ የቴሌኮም ዘርፍ ውጤታማ፣ ትርፋማና የአገሪቷን ኢኮኖሚ በመደገፍ ላይ የሚገኝ ነው” ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ትልቅ የሆነውን የካርጎ ማዕከል በታንዛኒያ ዳሬሰላም ለመክፈት መዘጋጀቱ ለአገሪቷ መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

“አየር መንገዱ በርካታ አውሮፕላኖችና መዳረሻዎች ያሉት ስኬታማ ተቋም ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ፤ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ የሆነ ትልቅ ኩባንያ መሆኑን ገልጸዋል።

በታንዛኒያ የካርጎ ማዕከል ማቋቋሙ ቱሪዝም፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ከማስፋፋት ባለፈ ኢትዮጵያንም የአማራጭ ወደብ ተጠቃሚ ያደርጋታል።

በተለይም “ሁለቱ አገሮች በቀንድ ከብት ውጤታማ ስለሆኑ የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማስፋት ያግዛል” ብለዋል።

እናም የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመጠቀም “በወጪ ንግድ ያለንን ተሳትፎ ማሳደግ እንችላለን ነው” ያሉት።

ፕሬዝዳንቱ “ሁለቱ አገሮች ተመሳሳይ ራዕይ ያላቸው በመሆኑ አዲሲቷ ታንዛኒያንና አዲሲቷ ኢትዮጵያ ለመገንባት በጋራ እንሰራለን” በማለትም ነው ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩት።

 

Published in ፖለቲካ

ነቀምቴ መጋቢት 23/2009 በምስራቅ ወለጋ ዞን ከመደበኛ የእርሻ ሥራቸው በተጨማሪ በንብ ማነብ ሥራ የተሰማሩ አርሶአደሮች ሀብትና ንብረት በማፍራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ።

የዞኑ እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ ባለፉት ሰባት ወራት ሁለት ሺህ  ቶን የሚጠጋ ማር መመረቱን ገልጿል።

በዞኑ ጉቶ ጊዳ ወረዳ ኡኬ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር ገበየሁ ኤጀታ ከመደበኛ የእርሻ ሥራቸው በተጓዳኝ በንብ ማነብ ፓኬጅ በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አርሶአደሩ እንደሚሉት ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ በ28 ባህላዊና ዘመናዊ ቀፎ 700 ኪሎ ግራም ማር አምርተው ለሽያጭ በማቅረብ ከ70 ሺህ ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል።

ባለፉት ዓመታት ከማር ምርት፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባገኙት ገቢም በነቀምቴ ከተማ በ400 ሺህ ብር ወጪ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት መገንባታቸውን ነው የገለጹት።

ከእዚህ በተጨማሪ "ሁለት ልጆቼንም በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ከፍዬ እያስተማርኩ ነው" ብለዋል።

በወረዳው የጋዲሣ ቶኩማ የንብ አርቢዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ጉደታ ሃምቢሳ እንዳሉት 74 የማህበሩ አባላት በሰባት ቡድን ተከፋፍለው የንብ እርባታ ሥራ እያካሄዱ ነው።

ማህበሩ በ155 ባህላዊ፣ የሽግግርና ዘመናዊ ቀፎ በመታገዝ የንብ ማነብ ሥራ እያካሄደ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህ ዓመት ብቻ ባደረጉት እንቅስቃሴ አንድ ሺህ 620 ኪሎ ግራም ማር ለማምረት መቻላቸውን ተናግረዋል።

አቶ ጉደታ እንዳሉት፣ ከምርት ሽያጩ ማህበሩ ከ160 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።

የጊዳ አያና ወረዳ ኮኖጂ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ገመቹ ዊርቱ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት 32 ዘመናዊ፣15 የሽግግር እና 24 ባህላዊ ቀፎዎች እንዳላቸዉ ጠቁመዋል።

በዚህ ዓመት በአንድ ዙር ካመረቱት ማር 80ሺህ ብር ማግኘታቸውን ገልጸው የሁለተኛው ዙር ምርታቸውን ገቢያቸውን በእጥፍ እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ገቢያቸውን በማጠናከር በሁለት ሄክታር መሬት ላይ የቡና ልማት ሥራን እያስፋፉ መሆናቸውንና በቀጣይም ይህን በማጠናከር ገቢያቸውን ለማሳደግ ማቀዳቸውን አብራርተዋል ፡፡

በተመሳሳይ በሌቃ ዱለቻ ወረዳ የባንዲራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ታደሰ ነጋሽ ፣ ባለፉት ወራት ያመረቱትን 620 ኪሎ ግራም የማር ምርት በመሸጥ ገቢያቸውን ማሳደጋቸውን ተናግረዋል፡፡

አርሶአደሩ ከማር ባገኙት ገቢ ወደ እንስሳት ማድለብ ሥራ መግባታቸውንና ያደለቧቸውን ከብቶች ለገበያ አቅርበዉ ኑሯቸውን እያሻሻሉ  መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የምስራቅ ወለጋ ዞን የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የንብ እርባታ ባለሙያ አቶ ደረጀ ከበደ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ከዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት ሁለት ሺህ ቶን የሚጠጋ የማር ምርት ተገኝቷል።

ምርቱ የተሰበሰበው በ17 ወረዳዎች ውስጥ ከሚገኙት ከ189 ሺህ ከሚበልጡ ባህላዊ፣ የሽግግርና ዘመናዊ ቀፎዎች ነው።

እንደ አቶ ደረጀ ገለጻ፣ የማር ምርቱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ357 ቶን ቅናሽ አሳይቷል።

ባለፈው ታህሳስ ወር የተከሰተው ውርጭ በዕጽዋት ላይ ጉዳት ማድረሱና በእዚህም ንቦች በሚፈለገው መጠን አበባ መቅሰም አለመቻላቸው ለቅናሹ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

በዞኑ እስካሁን ከ12 ሺህ  የሚበልጡ አርሶአደሮች በንብ ማነብ ሥራ በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ በተያዘው ዓመት እስካሁን 60 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ከማር ሽያጭ መገኘቱን አብራርተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2009 በቆሼ በደረሰው የአፈር መደርመስ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውና ኃብትና ንብረታቸውን ላጡ ወገኖች የመኖሪያ ቤት ተበረከተላቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ነዋሪዎች በንፋስ ስልክ ላፍቶና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ውሰጥ በ24 ሚሊዮን ብር ወጪ የተሰሩ 110 የመኖሪያ ቤቶች ለተጎጂዎች አስርክቧል።

የከተማዋ ከንቲባ ዲሪባ ኩማ የቤቱን ቁልፍ ለተጎጂዎች ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት "የከተማ አሰተዳደሩ በተቻለ አቅም ተጎጂዎቹን የመርዳትና የማቋቋም ስራው ይቀጥላል" ብለዋል።

ቤቶቹ የተገነቡት ለኑሮ ተስማሚ በሆኑ አካባቢዎች በመሆኑ ተጎጂዎች ከህዝቡ ድጋፍ በተጎዳኝ ጠንክሮ በመስራት ኑሯቸውን ማሻሻል አለባቸው ነው ያሉት።

በቆሼ በደረሳው አደጋ ኮልፌ ቃራኒዮ ክፍለ ከተማ አስኮ አዲስ ሰፈር አካባቢ በ16 ሚሊዮን ብር የተገነቡ ቤቶች ለተጎጂ ቤተሰቦች ተብርክተዋል።

በሌላ በኩልም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍል ከተማ በ8 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነቡ ቤቶች ለተጎጂዎቹ የተሰጠ ሲሆን ቤቶቹ የውሃ፣የኤሌክትሪክ፣የመጸዳጃና የምግብ ማብሰያ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው መሆኑ በርክክብ ወቅት ተገልጿል።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎችም ህዝብና መንግስት ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አርቅበዋል።

በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻች እስካሁን በተካሄደው የድጋፍ ማሰባሰብ ስራ 60 ሚሊዬን 998 ሺህ ብር በጥሬ ብር እና ከስድስት ሚሊየን ብር በላይ በዓይነት ድጋፍ ተሰብስቧል።

Published in ማህበራዊ

መቀሌ መጋቢት 23/2009 የደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የወጣቶችን የብድር አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በብድር የወለድ መጠን ላይ ቅናሽ ማድረጉን አስታወቀ።

የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግስት የሰጠውን ልዩ ትኩረት ተከትሎ ተቋሙ በብድር የወለድ መጠን ላይ ቅናሽ ማድረጉን ነው የገለጸው።

የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሕሸ ለማ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ በተቋሙ ተሻሽሎ የወጣው የብድር አሰጣጥ መመሪያ ከትናንት መጋቢት 22 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ ውሏል።

በተቋሙ የብድር አሰጣጥ ማሻሻያ ከተደረገበት አሰራር አንዱ ከ12 እስከ 15 በመቶ የነበረው የተቋሙ የወለድ መጠን ለወጣቶች ወደ ስምንት በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል ።

በዚህም ለወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሲባል በተሰጠው ልዩ ትኩረት ተቋሙ ቅናሽ ላደረገው የወለድ መጠን ለማካካስ የክልሉ መንግስት ለተቋሙ የ320 ሚሊዮን ብር ድጎማ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

"ወጣቶች ከተቋሙ የብድር አገልግሎት ለማግኘት ውጣ ውረድ ይበዛል" በሚል ሲያነሷቸው የነበሩ ቅሬታዎችን መሰረት በማድረግ አሰራሩን የመፈተሽና የማስተካከል ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል ።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመደገፍ በተያዘው ዕቅድ መሰረት በመቀሌና በአክሱም ከተሞች የሙከራ ሥራ ተጀምሯል ።

ተቋሙ በዚህ ዓመት ለወጣቶች ብድር ለመስጠት ካቀደው ሦስት ቢሊዮን ብር ውስጥ  እስካሁን አንድ ቢሊዮን ብር ለሁሉም የተቋሙ ቅርንጫፎች ተሰራጭቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል ።

የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጎይቶኦም ይብራህ በበኩላቸው ወጣቶች  የክልሉ መንግስት ያመቻቸላቸውን የብድር አቅርቦት ለመጠቀም የራሳቸውን የሥራ እቅድ ማቅረብ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

"ወጣቶች በብድር እጦት ምክንያት ስራአጥ አይሆኑም"ያሉት አቶ ጎይቶኦም፣ የክልሉ መንግስት ወጣቶችን በመሰረታዊነት ተጠቃሚ ለማድረግ ከደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አክስዮን ማህበር ጋር በመሆን መመሪያ ማውጣቱን ጠቁመዋል ።

"የብድር አገልግሎት የሥራ መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅት ያስፈልጋል" ብለዋል።

የደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ለወጣቶች ካዘጋጀው የብድር ገንዝብ በተጨማሪ ከፌዴራል መንግስት የተመደበው 527 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ለወጣቶች የብድር አገልግሎት እንደሚውል አቶ ጎይቶኦም ተናግረዋል።

የደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አክስዮን ማህበር ባለፉት ዓመታት ሦስት ቢሊዮን ብር ብድር ከሰጣቸው 460 ሺህ ተጠቃሚዎች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው ።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2009 የፈተና ስርቆትና ኩረጃን ለመከላከል ከመምህራን፣ ወላጆች፣ ተማሪዎችና ከፖሊስ ጋር የበለጠ ተቀራርበው እንደሚሰሩ ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልል የትምህርት ቢሮ ሃላፊዎችና የጸጥታ አካላት ገለፁ።

የአገር አቀፍ ትምህርትና ፈተናዎች ምዘና ኤጀንሲ ከየክልሉ የትምህርት ቢሮዎች ሃላፊዎችና የፖሊስ አባላት ጋር ላለፉት ሁለት ቀናት ሲያካሄድ የነበረው ውይይት ዛሬ አብቅቷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች እንደገለጹት፤ ኩረጃና የፈተና ስርቆትን ለማስቀረት ከጸጥታ አካላት ጋር አብረው እየሰሩ ነው።

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ተሰማ ዲማ እንዳሉት ባለፈው አመት በክልሉ የኩረጃና የፈተና ስርቆት ችግር አጋጥሟል።

በዚህ አመት ይህ ተግባር እንዳይደገም መምህራን፣ተማሪዎችንና ወላጆችን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ ነው።

''በፈተና ወቅት የተሰረቀ ፈተና ነው በማለት በየሱቁ የሚሸጡ ሃሰተኛ ወረቀቶች አሉ'' ያሉት ምክትል ሃላፊው፤ ይህንንም ለመከታተል ከክልሉ ፖሊስ ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ተማሪዎችም በሃሰተኛ መረጃ እንዳይሸበሩ ከወዲሁ የማስተማርና የግንዛቤ ማስጨበጥ መጀመሩን ነው የገለጹት።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ይልቃል ከፍያለ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ተማሪዎች ፈተና አቅም መገምገሚያ መሆኑን ተገንዝበው በራሳቸው እንዲሰሩ ለማድረግና ኩረጃን ለማሰቀረት ክልል አቀፍ ውይይት እየተደረገ ነው።

ከፈተና ስርቆት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመከላከል ከፈተና አቀማመጥ፣ ደህንነት፣ ከፈተና ወረቀቶች አሰረጫጨት፣ ከተማሪዎች አደላደልና አቀማመጥ ጋር የተያያዙ አስተዳደራዊ መፍትሄዎችም ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመተባበር በቅርበት ለመስራት መዘጋጀታቸውንም ገልፀዋል።

የሱማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የመጡት ምክትል ኮማንደር አደነ ኢብራሂም በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም በክልሉ አንዳንድ መምህራን ኩረጃ እንዲካሄድ ሲተባበሩ በክትትል ተደርሶባቸው ለህግ እንዲቀርቡ ተደርገዋል። ይሄው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ከዚህ በተጨማሪም ፈተናዎቹ በየትምህርት ቤቱ በሚሰራጩበት ወቅት በቂ ክትትልና የደህንነት ስራ ለመስራት ከወዲሁ በቂ ዝግጅትእየተደረገ መሆኑን ገለጸዋል።

"በፈተና ስርቆትና ኩረጃ ላይ ያለው ችግር በየጊዜው እያደገና ስልቱን እየቀየረ በመሆኑ በትምህርት ሃላፊዎች፣ በወላጆችና በተማሪዎች መካከል ያለው ጥምረት የበለጠ መጠናከር አለበት" የሚሉት ደግሞ የአማራ ክልል የፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮማንደር ያሬድ አበበ ናቸው።

ለዚህም ችግሩን ለመከላከል ከህብረተሰቡ ጋር በሚካሄድ ውይይትና ለተማሪዎች በሚሰጠው ተከታታይ የስነ ምግባር ትምህርት መሰረታዊ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ አመልክተው፤ ከዚህ በተጨማሪም የቁጥጥሩን ስራ የበለጠ መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።

 

Published in ማህበራዊ

ማይጨው መጋቢት 23/2009 በባለሙያ ድጋፍ እጦት ከእንስሳት እርባታ የሚያገኙት ጥቅም አነስተኛ መሆኑን በትግራይ ደቡባዊ ዞን የራያ አዘቦ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ

አርሶ አደሮቹ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በግብርና ልማትና ችግሮች ዙሪያ  ተወያይተዋል።

አርሶ አደሮቹ በውይይቱ ላይ እንዳሉት  ከሰብል ልማት በተጓዳኝ እንስሳትን በማርባት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ጥረት ቢያደርጉም  በእርባታው ዘዴ ኋላቀርነት የሚያገኙት ጥቅም ዝቅተኛ ነው ።

ከወረዳው አርሶ አደሮች መካከል ወይዘሮ ባህፍታ መሃሪ በሰጡት አስተያየት፣ ከመንግስት የብድር ገንዘብ ወስደው 16 ፍየሎችና በጎችን ገዝተው በማርባት ኑሯቸውን  ለመለወጥ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም  የወረዳው እንስሳት ህክምና ባለሙያዎች ድጋፍ ስለማይሰጧቸው የሚያረቧቸው እንስሳት  በበሽታ በመጠቃት እያለቁባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

" በቅርቡ ባለሙያዎች  ወደ አካባቢያችን መጥተው ክትባት ጀምረዋል " ያሉት ወይዘሮ ባህፍታ እንስሳቱ ካለቁና ኪሳራ ከደረሰባቸው በኋላ አሁን ክትባት መስጠቱ  ትርጉም እንደሌለው አመልክተዋል፡፡

" ዘግይቶም ቢሆን የእንስሳት ክትባት መልካም ቢሆንም አገልግሎቱ ለማግኘት ከአካባቢያችን ርቀን ስለምንጓዝ  እንግልት እየደረሰብን ነው" ያሉት ደግሞ  አርሶ አደር ሙላት አብርሃ ናቸው።

በሚኖሩበት የገጠር ቀበሌ  የእንስሳት ህክምና ማዕከል በማቋቋም በአቅራቢያቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲመቻቸላቸውም ጠይቀዋል።

አርሶአደር ሓዱሽ ገብረመድህን በበኩላቸው ካሏቸው  እንስሳትና እንስሳት ተዋፅኦ የሚያገኙት  ምርት ውስን በመሆኑ  ከተሻሻሉ  ዝርያዎች ጋር ማዳቀል እንዲችሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸው አመልክተዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ቋሚ ኮሚቴ  ሰብሳቢ አቶ አረጋዊ አፅባሓ  በውይይቱ ላይ  " የአከባቢው አርሶአደር  ለረጅም ዓመታት በእንስሳት እርባታ ስራ የተሰማራ ቢሆንም የዘርፉ ልማት ለማዘመን የሚያስችለው ድጋፍ እያገኘ አለመሆኑን  መገንዘብ ችለናል" ብለዋል።

" አርሶአደሩ በእርሻ ስራ ብቻ ኑሮውን ለመለወጥ አደጋች ነው " ያሉት አቶ አረጋዊ፣ በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የእንስሳት ቁጥር መጥኖ በመያዝና እርባታውን  በማሻሻል ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም  አሳስበዋል፡፡

በአካባቢው የሚታየውን የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎች እጥረት ችግር በመፍታት  አርሶአደሩ ከእንስሳት ሃብቱ የተሻለ ጥቅም እንዲያገኝ መሰራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተለይ አርሶአደሩ የእንስሳት ማዳቀል አገልግሎት በመስጠት ረገድ የታየውን ክፍተት ለማስወገድ የባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስራ በስፋት መከናወን እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የእንስሳት ሃብት ልማት ቡድን መሪ አቶ አማረ መሃሪ  አርሶአደሩ ያቀረበው ቅሬታ ተገቢ መሆኑን ገልጸው ችግሩን ለማስተካከል  የተጠናከረ  ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

" በተለይ በአካባቢው ያለውን የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎች እጥረት ለማስተካከል የስልጠና ድጋፍ ይሰጣል " ያሉት አቶ አማረ፣ የእንስሳት ማዳቀልና የተሻሉ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን በአቅራቢያው እንዲያገኝ ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ቋሚ ኮሚቴ አባላት ሰሞኑን በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር በግብርና ልማት፣  በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ችግሮችና መፍትሄዎ ቻቸው  ዙሪያ ከአርሶ አደሩና ከአመራሩ ጋር ተወያይቷል፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን