አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 09 March 2017

መቐለ የካቲት 30/2009 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት  በአስተሳሰብና በተግባር የሚገለፅ የህዝብ አገልጋይነትን የሚጎዳ ችግር እንደሚስተዋል ተገለጸ፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አምስቱም ኮሌጆች መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የተሳተፉበት የተሃድሶ ግምገማ   ዛሬ ተጀምሯል፡፡

በዩኒቨርሲቲ የአዲ ሀቂ የትያትር አደራሽ  በተጀመረው  የግምገማ  መድረክ   የማህበራዊ ሳይንስ  መምህር ዶክተር  ተክላይ ተስፋዬ ባቀረቡት የመነሻ ሃሳብ ላይ እንደገለጹት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲና በሌሎችም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአስተሳሰብና በተግባር የሚገለጹ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡

እነዚህም ችግሮች ትምክህት፣  ጠባብነትና የሃይማኖት አክራርነት መሆናቸውን ጠቁመው ይህም  የህዝብ አገልጋይነትን የሚጎዳና ለሀገሪቱ የህዳሴ ጉዞ መሳናክል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኪራይ ሰብሳብነት አስተሳሰብ ፣የስነምግባር መጓደል፣ ህግና ስርዓት በተከተለ መንገድ ስራን በማከናወን ረገድ ክፍተቶች እንደሚታዩም ጠቅሰዋል፡፡

ዶክተር  ተክላይ እንዳመለከቱት የተቋሙ ማህበረሰብም በእነዚህ  ችግሮች መግባባት ላይ ከደረሰ   በጋራ መታገል ያስፈልጋል፡፡

ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሃሳብ ትግል በማድረግ የትምህርት ስርዓቱ በላቀ ደረጃ እንዲፈፀም  የማድረግ የውይይቱ   አንድ አካል እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

" የሀገሪቱ   የህዳሴ ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖረው የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ የተጣለበትን ሀላፊነት እንዲወጣ  ለማድረግ የተሃድሶ ገምገማው መድረክ የጎላ ሚና ይኖረዋል "ብለዋል፡፡

እስካሁን በታየው ሀገራዊ ለውጥ   ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተጫወቱት ሚና ቢኖርም   የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የትምህርት ጥራት መጓደል  እንደሚታይባቸውም ተመልክቷል፡፡

ይህ ደግሞ  የተሟላ ስብዕና ያለው ዜጋ ለማፍራት አሉታዊ ተፅኖ የሚያስከትል በመሆኑ በፍጥነት ለማረም ግምገማው ዋሳኝ ነው ተብሏል፡፡

በዩኒቨርስቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ምህረት ብርሃኑ በበኩላቸው ግምገማው የዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ በአፈፃፀሙ ያለበት ደረጃ በግልፅ ይገመግማል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር መምህር ዶክተር ደረጀ ተክለማርያም እንዳሉት " ራሳችንን በጥልቅ ተሃድሶ ገምግመን ቀጣይ ስራዎቻችን በጥራት ለመስራት ቃላችን የምናድስበት የውይይት  መድረክ ይሆናል" ብለዋል።

እያንዳንዱ ተሳታፊ በዩኒቨርስቲው ያሉ ችግርችን ከማውጣት ባለፈ ምን ሰርቻለሁ የሚል አስተሳሰብ በመያዝ ራሱን ለመገምገም  በንቃት መሳተፍ እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል።

 

Published in ፖለቲካ

ጂግጂጋ የካቲት 30/2009 በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በፖለቲካው መስክ የሴቶች ተሳትፎ እያደገ መምጣት ስለራሳቸው የነበራቸውን አመለካከት እንደቀየረው አስተያየታቸውን ለአዜአ የሰጡ የጅግጅጋ ከተማ ሴቶች ገለጹ፡፡

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን "የሴቶች ቁጠባ ባህል ማደግ ለሕዳሴያችን መሰረት ነው" በሚል መሪ ቃል በጅግጅጋ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡ 

በጅግጅጋ ከተማ ቀበሌ 11 ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አሻ ሙሴ በውይይቱ ላይ በሰጡት አስተያየት የክልሉ ሴቶች በፖለቲካ መስክ የተሻለ ቦታ እንዲያገኙ የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑ መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

''ሴቶች በየዘርፉ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ ቀደም ሲል ስለራሴ የነበረኝን አመለካከት እንድቀይር አድርጎኛል" ያሉት ወይዘሮ አሻ፣ ሴት ልጆች ከተማሩ የተሻለ የአመራር ቦታ ላይ መድረስ እንደሚችሉ ባለፉት ዓመታት ማስተዋላቸውን ገልጸዋል። 

ወይዘሮ ዴቃ መሀመድ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው፣ በጅግጅጋ ከተማ ሴቶች ከነበረባቸው ጭቆና ተላቀው በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስኮች ላይ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አመልክተዋል።

ይህም የጾታ እኩልነትን በበለጠ ለማስፈን ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩ በተጨማሪ በፍትህና በተለያዩ ዘርፎች የሴቷ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። 

"በተማርኩበት ሙያ በመንግስት መስሪያቤት ተቀጥሬ በመስራቴ ደስተኛ ነኝ። ቀደም ሲል ለሴቷ በአደባባይ ለመስራት ይቅርና ለመማር እንኳ አስቸጋሪ ነበር። አሁን ይህ ቀርቶ ሴቶች ከፍተኛ ደረጃ ላይ እየደረሱ ነው፤ የተሻለ ቦታ ለመድረስም የራስ ጥረት ወሳኝ እንደሆነ ተረድቺያለሁ" ብለዋል፡፡

ሴቶች ላይ ይደርስ የነበረውን ጭቆና ለማስቀረት የተደረገውን ሁለንተናዊ የትግል እንቅስቃሴና የተገኙ ወጤቶችን መዘከር የበዓሉ ዓላማ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፋጡማ መሀመድ ናቸው፡

በከተማው በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖሊቲካዊ መስኮች የሴቶችን ተሳትፎ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማጠናከር በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሁሉም ዘርፍ ለሴቶች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለግማሽ ቀን በተካሄደው መድረክ ስለ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አጀማመርና ሂደት፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ተሳትፎ እንዲሁም ስለተገኙ ለውጦችና ሴቶች በኢትዮጵያ ሕዳሴ ላይ እያበረከቱት ስላለው አስተዋጽኦ ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ ላይ ከከተማው የተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ 200 የሚሆኑ ሴቶች ተሳትፈዋል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 30/2009 በአዲስ አበባ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራትን ዓላማ ያደረገው ስድስተኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎች ስፖርታዊ ውድድር ቅዳሜ ይጀመራል።

የመዲናዋ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር የሚዘጋጀውና በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው ውድድር መክፈቻውን በመጪው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደርጋል።

በመዲናዋ ከመንግስትና ከግል የተውጣጡ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አራት ሺህ የቀን ተማሪዎች በውድድሩ እንደሚካፈሉ ነው አዘጋጆቹ በሰጡት መግለጫ ያሳወቁት።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ በረከት በላይ እንደተናገሩት በመዲናዋ 4 ሺህ ተማሪዎችን በ17 የስፖርት ዓይነቶች በማሳተፍ ምርጥ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ያለመ ውድድር ነው።

በስፖርት የተሳትፎ ንቅናቄ መፍጠር፣ በተማሪዎች ዘንድ የእርስ በእርስ ቅርበት መፍጠር፣  በተለያዩ ስፖርቶች በአገር አቀፍ ውድድሮች ላይ መዲናዋን የሚወክሉ ተሳታፊዎችን መምረጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የውድድር እድል በመፍጠር ስፖርተኞች በተለያዩ ክለቦች እንዲመረጡ ማስቻልና ተማሪዎቹ  ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ ያግዛል ብለዋል ኃላፊው። 

ውድድሮቹ ስኬታማ እንዲሆኑ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን ጨምሮ ምቹ ሁኔታ፣ አስፈላጊ ቁሳቁሶችና ባለሙያዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ውድድር ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ደረስ  ሰላማዊ እንዲሆን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል። 

የመዲናዋ ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ በአምላኩ ተበጀ በበኩላቸው በተማሪዎች ውድድር ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲሰፍን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

ውድድሩም የተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ በማይሻማ መልኩ ቅዳሜና እሁድ እንደሚካሄድ ገልጸው በውድድር ምክንያት ትምህርቱ ቢያልፋቸው እንኳ የሚካካስበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል። 

ውድድሩ መክፈቻውንና መዝጊያውን በአዲስ አበባ ስታዲየም በማድረግ ጃንሜዳ፣ ራስ ኃይሉ ጅምናዚየም፣ በአራት ኪሎ ትምህርትና ስልጠና ማዕከልና በተለያዩ የመዲናዋ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ይደረጋል።

ወድድሩም በተለያዩ ስፖርቶች በእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስ፣ በቮሊቦል፣ በእጅ ኳስ፣ በጠረጴዛ ቴኒስ፣ በሜዳ ቴኒስ፣ በቴኳንዶ፣ በቼዝ፣ ቅርጫት ኳስና በሌሎችም ከመጋቢት 2 እስከ 17 ቀን 2009 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገልጿል።  

ቀደም ሲል በየወረዳውና ክፍለ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የውስጥ ውድድሮችን በማካሄድ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ምርጥ ስፖርተኞች ናቸው በማጠቃለያው ውድድር የሚካፈሉት። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በየትምህርት ቤቶች ያሉትን የስፖርት ማዘውተሪያዎች በማመቻቸት ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰሩ የመዲናዋ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮና የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ያለውን የስፖርት የማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት ለማቃለል ካሉትና እየተገነቡ ከሚገኙት የማዘውተሪያ ስፍራዎች በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች በአማራጭነት ለመጠቀም ሁለቱ ቢሮዎች በጋራ እየሰሩ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ በረከት በላይ እንዳሉት ትምህርት ቤቶቹ ምርጥ ስፖርተኞች የሚፈሩበት በመሆኑ ያሉትን ሜዳዎች በመጠገን፣ በማደስና በማስተካከል ምቹ ሜዳዎች ለመፍጠር እየተሰራ ነው። 

የማዘውተሪያ ስፍራዎች በመገንባት ሁሉንም ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግም የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ ቢሮው ከመዲናዋ ኮንስትራክሽን ቢሮና የመሬት ልማት አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።

ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ በተለይ በትምህርት ቤቶች የማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የትምህርት ቢሮ በበኩሉ ከወጣቶችና ስፖርት በመተባባር በየትምህርት ቤቱ ያሉትን የማዘውተሪያ ስፍራዎች ለአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ብሏል።

 

Published in ስፖርት

የካቲት 30/2009 ከማርስ ጋር ተመሳሳይነት ባለው አነስተኛ ሳተላይት”ኪዩብ ሳት” ላይ በተሞከረ ጥናት ድንች ማርስ ላይ ሊበቅል እንደሚችል አንድ ጥናት አረጋገጠ ፡፡

የጥናቱ ግኝት ድንች በከፋ የአየር ፀባይ ሊያድግ እንደሚችልም አመላካች ነው ተብሏል፡፡

በፔሩ የሊማ የኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ኢንጂነሮች ዲዛይን ባደረጉትና ከአለም አቀፍ የድንች ጥናት ማእከል ጋር ባዘጋጁት የማርስ መሰል አነስተኛ የሳተላይት ሳጥን ውስጥ ድንች መብቀል ችሏል፡፡     

የሳተላይት ሳጥኑ የማርስን ቀንና ሌሊት ፣የሙቀት ሁኔታ ፣የአየር ግፊት እና የከባቢ አየር ሁኔታ የሚመስልና ይህንንም የሚቆጣጠር ሴንሰር የተገጠመለት ሲሆን የድንቹንም እድገት ሁኔታ ይቆጣጠራል ፡፡

"ማርስ መሰል የአየር ሁኔታ ላይ ማብቀል መቻላችን የዚህ ሙከራ ትልቅ ስኬት ነው”  ያሉት የዩኒቨርስቲው ተመራማሪና የጥናቱ ተሳታፊ  ጁሊዮ ቫልዲቫ ሲልቫ ናቸው፡፡

“ተክሎች በሳተላይት ሳጥን ውስጥ የማርስን አይነት የአየር ፀባይ ተቋቁመው ማደግ ከቻሉ በማርስም የመብቀል ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው ፤ በመሆኑም የትኞቹ የድንች ዝርያዎች በመብቀል የተሻሉ እንደሚሆኑ ተደጋጋሚ ጥናት እናደርጋለን ፣ ይህም ድንች ለማደግ የሚያስፈልገውን አነስተኛ ሁኔታ እንለያለን”ብለዋል፡፡

የድንች ዘረ መል ተለዋዋጭ(dynamic) በመሆኑ የትኛውንም አየር ፀባይ የመለማመድ ሁኔታ ይኖረዋል።በመሆኑም ተመራማሪዎች ቀደም ሲል በጨዋማ አፈርና  ድርቅ ባለበት ሁኔታም የሚበቅል ድንች በምርምር ማግኘታቸውን የዘገበው ዩፒአይ ነው፡፡

 

አዲስ አበባ የካቲት 30/2009 በሰንጋ ተራና ክራውን ሳይቶች የተጠናቀቁ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማግኘት ሙሉ ክፍያ ያጠናቀቁ ግለሰቦች ብቻ በዕጣ እንደሚወዳደሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በመዲናዋ እየተገነቡ ካሉት 39 ሺህ 229 የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 1 ሺህ 292 ቤቶች ሙሉ ለሙሉ በመጠናቀቃቸው በመጪው ቅዳሜ እንደሚመረቁ ነው የተገለፀው፡፡

ከንቲባ ድሪባ ኩማ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የተጠናቀቁት ቤቶች የፊታችን ቅዳሜ ከተመረቁ በኋላ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲተላለፉ ቅድሚያ የሚሰጣቸውና እጣ ውስጥ የሚካተቱት ሙሉ ክፍያቸውን ያጠናቀቁ ዜጎች ይሆናሉ፡፡

ቀሪዎቹ ደግሞ የሚጠበቅባቸውን ክፍያ እየፈፀሙ ቆይተው እንደ አከፋፈል ቅደምተከተላቸው በዚሁ ፕሮጀክት ስር በሚገነቡት የ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም ውስጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ነው የገለጹት፡፡

''የዚህ የ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም በመንግስት ሲጀመር ዋነኛ አላማው ቁጠባን ለማበረታት ሲሆን መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ያላቸውንም ዜጎች የቤት ባለቤት ማድረግ ነው'' ብለዋል፡፡

መንግስት በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል የተለያዩ ስትራቴጂዎች ነድፎ እየሰራ እንደሆነ የገለጹት ከንቲባው እስካሁን በ10/90 እና በ20/80 ብቻ 175 ሺህ ቤቶች ለተጠቃሚው ተላልፈዋል፡፡

በዚሁ ፕሮግራም ሌሎች 94 ሺህ የሚደርሱ ቤቶች ደግሞ በግንባታ ላይ እንደሆኑ ነው የተናገሩት፡፡

መንግስት የሚያካሂደው የቤት ልማት ፕሮግራም የመኖሪያ ቤት እጥረትን ከመፍታት ጎን ለጎን ጉልበት ተኮር በመሆኑም በየዓመቱ ከ 60ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እየተፈጠረ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

''የ40/60 ፖሊሲውም ስትራቴጂውም ቁጠባን ፖሊሲ ያደረገ ስለሆነ ቤቱን ለነዋሪ የምናስተላልፈው መንግስት ቤት ለመስራት የሚያስፈልገውን ወጪ ለመቀነስ ሲባል ከፍተኛ ገንዘብ የቆጠቡ ሰዎች ቀድመው ቤቱን ያገኛሉ'' ብለዋል ከንቲባ ድሪባ፡፡

በአሁኑ ወቅት በመገንባት ላይ ያሉት ቤቶች እስከ 2011 ዓም ድረስ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለተጠቃሚው እንደሚተላለፉም ነው የገለጹት፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ የካቲት 30/2009 ስኬታማና ሞዴል አርሶአደሮች የሚጠቀሙበትን የግብርና አሰራር ለሌሎች አርሶአደሮች በማስተላለፍ አገራዊ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገበ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ተናገሩ።

በደቡብ ክልል በተከበረው 8ኛው የከፊል አርሶ እና አርብቶ አደሮች ፌስቲቫል ከአንድ ነጥብ ሁለት እስከ 21 ሚሊዮን ብር ሃብት ያስመዘገቡ አርሶአደሮች ተሸልመዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ደሴ ዳልኬ በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ግብርናው የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢንዱስትሪ ልማትና ለኤክስፖርት ዘርፍ ዋነኛ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡

የክልሉ አርሶአደሮች ምርትና ምርታማነትን መነሻ በማድረግ በአነስተኛ ማሳቸው ላይ ገበያ ተኮር ምርቶችን የማምረት አቅማቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ግብርናው እየዘመነ መሆኑን የገለጹት አቶ ደሴ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አርሶአደሮች ከኋላ ቀርነት አስተራረስ ወጥተው ከራሳቸው ፍጆታ ባለፈ ለገበያ የማምረት አቅም ማጎልበታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ከአርሶአደርነት ወደ ባለሀብትነት ተሸጋግረው ለሽልማት የበቁ አርሶአደሮች ማረጋገጫ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል፡፡

"የማስፋት ስትራቴጂን ተግባራዊ በማድረግ ስኬታማና ሞዴል አርሶአደሮች የሚጠቀሙበትን የግብርና አሰራር ለሌሎች አርሶአደሮች በማስተላለፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል" ብለዋል።

የግብርና ኤክስቴንሽን ተግዳሮቶችን ለመፍታትም አርሶአደሩንና ከፊል አርብቶአደሩን አቀናጅቶ በአደረጃጀት መምራት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል

ተሸላሚ አርሶአደሮች የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ እንዱስትሪ ለማሸጋገር በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራም መላው አርሶአደር የተግባሩ ባለቤት በመሆን ዘላቂነት ያለው ልማት ለማስመዝገብ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በመስኖ ልማት ዘርፍና በገጠር የተቀናጀ ልማት ከእንስሳት የሚገኘው ጥቅም በሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳደሩ በቀጣይ በዘርፉ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፣ ግብርናው የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እንዲችል እየተተገበረ ባለው የአረንጋዴ ልማት ስትራቴጂ የክልሉ የደን ሽፋን 19 ከመቶ ደርሷል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንም 25 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዛሬዎቹ ተሸላሚዎች ድህነትን  በጥረታቸው የተሻገሩና የምግብ ዋስትናቸውን ያረጋገጡ ከመሆናቸው በላፈ በሚሊዮን የሚቆጠር ሃብት ያፈሩ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

ከተሸላሚዎቹ መካከል አቶ ደንጋሞ ዳኖሌ 21 ሚሊዮን ብር በማፍራት ከሲዳማ ዞን የተሸለሙ ሞዴል አርሶአደር ሲሆኑ ሽልማቱ ልዩ ደስታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂን መጠቀም መቻላቸውና ከግብርና ባለሙያ የሚሰጣቸውን ድጋፍ በአግባቡ መተግበራቸው ለሽልማት ያበቃቸው  መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሌላኛዋ ተሸላሚ ሞዴል አርሶአደር ገነት መንግስቱ ለመጀመሪያ ጊዜ መሸለማቸውን ገልጸው፣ ዘመናዊ የግብርና ዘዴዎችን ቀስመው ተግባራዊ ማድረጋቸው ስኬታማ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡

በፌስቲቫሉ ከአንድ ነጥብ ሁለት እስከ 21 ሚሊዮን ብር ሃብት ያስመዘገቡ 387 አርሶአደሮችን ጨምሮ ለ624 የግብርና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ተሸልመዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ነገሌ የካቲት 30/2009 በዶሎ እና ሞያሌ በኩል ከውጭ የገባ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የኮንትሮባንድ እቃ  ተያዘ፡፡

እቃዎቹ የተያዙት  በህብረተሰቡ ጥቆማ ከየካቲት 28/2009ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት  በተደረገው ክትትል በጉጂ ዞን ነገሌ ቦረና ከተማ እንደደረሱ ነው፡፡

በከተማው ፖሊስ ጽህፈት ቤት የሰላም ማስከበር አስተባባሪ ሳጂን ካባ ነጋሳ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተያዙ የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል የመጋረጃ ጨርቆች፣ 103 በፀሓይ ሃይል የሚሰሩ የመብራት መሳሪያዎችና ሶስት ሺህ 576 የሞባይል ስልኮች ይገኙበታል፡፡

የሞባይል ስልኮቹ  በታርጋ ቁጥር ኮድ 2 አዲስ አበባ 83498 የቤት መኪና ላይ ተጭኖ ነገሌ ቦረና ከተማ አስፋልት መንገድ ዳር እንደቆመ የታያዙ ናቸው፡፡

ቀሪዎቹ እቃዎች የተያዙት ደግሞ በሌላ ተሽከርካሪ ከሞያሌ አካባቢ ተጓጉዘው ከተማው ደርሰው ሲራገፉ ተደርሶባቸው ሲሆን የድርጊቱ ፈጻሚዎች ሸሽተው አምልጠዋል፡፡

የቤት መኪናው አሽከርካሪ ለጊዜው በመሰወሩ ፖሊስ  መኪናውን በቁጥጥር ስር አውሎ ጉዳዩን በማጣራት ላይ እንደሆነም ሳጂን ካባ ጠቁመዋል፡፡

ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት ያሳየውን  ትብብር ወደፊትም በመቀጠል  በሀገር ውስጥ ለሚካሄደው ፍትሀዊ የንግድ ውድድር መሳካት የድርሻውን እንዲወጣ  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የከተማው ፖሊስ ህገ ወጥ እንቅስቃሴን ለመከላከል ከሌሎች  ባለድርሻ አካላት ጋር  በመተባበር እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 30/2009 አዲስ አበባ ከተማ የእግረኞችን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል ስትራቴጂ ይፋ አደረገች።

በከተማዋ አስተዳደር ካቢኔ የጸደቀው ''የእግረኞች ደህንነት ስትራቴጂ'' ለ13 ዓመት የሚሰራበት መሆኑም  ተገልጿል።

የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ  ሰጥተዋል።

ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ፣ አለም አቀፍ የመንገድ ዳሰሳ ጥናት ተቋም እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን  “የእግረኞችን የትራፊክ አደጋ ተጋላጭነት” በተመለከተ ያደረጉት ጥናት በወቅቱ በሪፖርት መልክ ቀርቧል።

የከተማዋ ካቢኔ “ችግሩን ለመፍታት ያስችላሉ” ያላቸውን የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ በማጽደቅ ለቀጣይ 13 ዓመታት በቁረጠኝነት የሚሰራባቸውን አቅጣጫዎች አስቀምጧል።

ከስትራቴጂዎች መካከልም የእግረኞች ቁጥር በሚበዛባቸው አካባቢዎች የተሽከርካሪዎችን ሕጋዊ የፍጥነት መጠን መቀነስ፣ የተሻሻሉ የመንገድ ዲዛይኖችን ማዘጋጀት፣ የትራፊክ ህጎችን በአግባቡ ማስፈጸም ተጠቃሾች ናቸው።

ህግ በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ ቅጣቱን መጨመር፣ ተደራሽ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን  ዘመቻ ማካሄድ እና የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሂደትን ማጥበቅ የሚሉትም ይገኙበታል።

ከንቲባ ድሪባ በሰጡት ማብራሪያ፤ ስትራቴጂውን ተግባራዊ በማድረግ አደጋ በሚበዛባቸው ዋና ዋና መንገዶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል።

ለእግረኞች ቅድሚያ መስጠት፣ በግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በመታገዝ ቁልፍ የደህንነት ህጎችን የማስከበር ስራዎች በትኩረት ይከናወናሉ።

የትራፊክ አደጋ እና  የአካል ጉዳት መረጃ  አስተዳደር ስርዓትንና የድህረ አደጋ የህክምና አገልግሎትን ማጠናከር  “ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግባራት ናቸው” ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የተካሄደ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በ2008 ዓ.ም በከተማዋ በትራፊክ ሳቢያ 463 የሞት አደጋ ተከስቷል። ይህ ደግሞ ከ100 ሺ ህዝብ 13 ነጥብ 8 በመቶው የሞት አደጋ እንደሚደርስበት ያመለክታል።

Published in ማህበራዊ

ነገሌ /ነቀምቴ የካቲት 30/2009 በአዶላ ወዩ ከተማ ለተከታታይ 12 ቀናት ሲካሄድ የሰነበተው መላው የጉጂ ዞን የስፖርት ውድድር በሻኪሶ ከተማ አስተዳደር አሸናፊነት ትናንት ማምሻውን ተጠናቀቀ፡፡

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ዓመታዊ የልዩ ልዩ ስፖርት ጨዋታዎችም በሻምቡ ከተማ አስተዳደር አሸናፊነት ተጠናቋል።

በመላው የጉጂ ዞን የስፖርት ውድድር የሻኪሶ ከተማ አስተዳደር አሸናፊ የሆነው ለውድድሩ ከተዘጋጁት 12 ዋንጫዎች ሰባቱን በማንሳት እንደሆነ የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ገመቹ ገልጸዋል፡፡

የቦሬ ወረዳ በአትሌቲክስ አራት ዋንጫ፤ የነገሌ ከተማ አስተዳደር ደግሞ በቴኳንዶ፣ በቅርጫትና በእጅ ኳስ በማሸነፍ ሦስተኛና ሁለተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።፡

ከዞኑ 13 ወረዳዎችና ከሦስት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ አንድ ሺህ 200 ስፖርተኞች በ12 የስፖርት አይነቶች መሳተፋቸውን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

እንደአቶ ተስፋዬ ገለጻ፣ የውድድሩ ዓላማ በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ ለሚካሄደው የመላው ኦሮሚያ ጫዋታዎች ላይ የጉጂ ዞንን በመወከል የሚሳተፉ ስፖርተኞችን መምረጥ ነው፡፡

በእዚህም 115 ተወዳዳሪዎች በመላው ኦሮሚያ ጨዋታዎች ላይ እንዲሳተፉ መለየታቸውንም አቶ ተስፋዬ አስታውቀዋል፡፡

አሸናፊ ለሆኑ ስፖርተኞች የዋንጫ ሽልማት የሰጡት የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ዋደራ የወጣቱን ስፖርታዊ ክህሎት ለማሳደግ መሰል ውድድሮች እንደሚዘጋጁ ገልጸዋል፡፡

የውድድሩ አሸናፊ ሆነው በመላው ኦሮሚያ ጨዋታዎች ለመሳተፍ ዕድል ያገኙ ስፖርተኞች የጉጂ ዞንን ባህልና እሴት በማስተዋወቅ ጭምር ውድድራቸውን ማካሄድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በተመሳሳይ ዜና የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ዓመታዊ የልዩ ልዩ ስፖርት ጨዋታዎች በሻምቡ ከተማ አስተዳደር አሸናፊነት ተጠናቋል።

የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቶለሳ ጨመዳ እንዳሉት ከየካቲት 22 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለስምንት ቀናት ሲካሄድ በቆየው የዞኑ ዓመታዊ የልዩ ልዩ ጨዋታዎች  የስፖርት ውድድር 834 ስፖርተኞች ተሳትፈዋል።

በአትሌቲክስ፣ በጠረጴዛ ቴኒስ፣ በፓራ ኦለምፒክ፣ በዳርት፣ በቼዝ፣ በእግርና መረብ ኳስ በተካሄደው ውድድር ከዘጠኝ ወረዳዎችና ከአንድ የከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ስፖርተኞች ተሳትፈዋል፡፡

ውድድሩ በሻምቡ ከተማ አስተዳደር የበላይነት የተጠናቀቀ ሲሆን አስተዳደሩ አጠቃላይ አሸናፊ ሊሆን የቻለው በወንዶችና ሴቶች አትሌቲክስ፣ በፓራ ኦሎምፒክና በጠረጴዛ ቴኒስ አራት ዋንጫዎችን በማግኘቱ ነው፡፡

በሌሎች ጨዋታዎች የአባይ ጮመን ወረዳ በወንዶች መረብ ኳስ፣ የጉዱሩ ወረዳ በሴቶች የመረብ ኳስ  እና በዳርት አሸናፊ በመሆን የተዘጋጀላቸውን ዋንጫ ከዕለቱ የክብር እንግዳ እጅ ተቀብለዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት በሻምቡ ከተማ አስተዳደርና በጃርደጋ ጃርቴ የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል የተካሄደው የዋንጫ ፍልሚያ ቡድኖቹ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መሸናነፍ ባለመቻላቸው በተሰጠው የመለያ ምት የጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ የእግር ኳስ ቡድን 5ለ4 በሆነ ውጤት በመርታት የጨዋታው አሸናፊ ለመሆን በቅቷል፡፡

እንደ  አቶ ቶለሳ ጨመዳ ገለጻ፣  በዓመታዊ የልዩ ልዩ ስፖርት ጨዋታዎች ውድድር ዞኑን የሚወክሉ 72 ስፖርተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

ለአሸናፊ ወረዳዎች ዋንጫና የምስክር ወረቀት የሰጡት የዞኑ ስፖርት ምክር ቤት ተወካይ አቶ ዓለማየሁ ሀብቴ ናቸው፡፡

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ የካቲት 30/2009 21ዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር በሚያደርጉት ክርክርና ድርድር ማን ይሳተፍ፤ ማንስ ያደራድር በሚሉት ሃሳቦች ላይ ሳይግባቡ በቀጠሮ ተለያዩ።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ዛሬ ለአምስተኛ ጊዜ ተገናኝተው በቀጣይ በሚያካሂዱት ክርክርና ድርድር ላይ ማን ይሳተፍ እንዲሁም ማን ያደራድር በሚሉት ሃሳቦች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም ኢህአዴግን ጨምሮ አብዛኞቹ ፓርቲዎች በአገር አቀፍ ደረጃ በህጋዊነት የተመዘገቡና ምርጫ ቦርድ እውቅና የሰጣቸው ፓርቲዎች በድርድሩና ክርክሩ ላይ ይሳተፉ የሚል ሃሳብ አቅርበዋል።

መድረክ በበኩሉ ራሱ ከኢህአዴግ ጋር ዋና ተከራካሪ እንዲሆን ወይም ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች በጋራ በመሆን ክርክርና ድርድሩ ላይ እንዲሳተፉ ሃሳብ አቅርቧል።

ሆኖም የመድረክን የመጀመሪያ ሃሳብ አብዛኞቹ ፓርቲዎች ተቃውመዋል።

ኢህአዴግ በበኩሉ ገዥው ፓርቲ ለ21ዱም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል እውቅና እንደሚሰጥና በድርድሩ እኩል የመሳተፍ መብት እንዳላቸው ገልጿል።

ፓርቲዎቹ በጋራ መድረክ ያልተነሱ ሃሳቦች ላይ በተናጠል ለመከራከርና ለመደራደር ከፈለጉም እድሉ አላቸው ብሏል ኢህአዴግ።

ፓርቲዎቹ በቀጣይ የሚያካሄዱት ክርክርና ድርድርን ማን ይምራው ወይም ማን ያደራድር በሚሉ ሃሳቦች ላይም በርካታ አስተያየቶችን አንስተው መግባባት ላይ ሳይደርሱ በቀጠሮ ተለያይተዋል።

አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ክርክርና ድርድሩን ነጻ፣ ገለልተኛና በቂ እውቀትና ልምድ ባላቸው ሰዎች ይመራ የሚል ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን ሶስት ፓርቲዎች ደግሞ ራሳቸው ፓርቲዎቹ በዙር ይምሩት ሌላ አደራዳሪ አያስፈልግም የሚል ሃሳብ አቅርበዋል።

ኢህአዴግ በበኩሉ ድርድሩ የሚካሄደው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እንደመሆኑ ከፖለቲካ ፓርቲዎች በላይ ችግሩን የሚያውቅና ለችግሩ መፍትሄ የሚያመጣ  ሌላ አደራዳሪ አያስፈልግም የሚል ሃሳብ አቅርቧል።

ኢህአዴግ ቀደም ሲል ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ሲያካሂድ አደራዳሪ እንዳልነበርና በአሁኑ ክርክርና ድርድርም አደራዳሪ ሳያስፈልግ ራሳቸው ፓርቲዎቹ በተራ መድረኩን ይምሩት ብሏል።

መድረኩን የሚመራው ፓርቲ በዚያን ወቅት የራሱን ሃሳብ የሚያንጸባርቅ ሌላ ሰው ይወክላል እንጂ ሲያደራድር የታዛቢነት ሚና ነው የሚጫወተው የሚል ሃሳብ አንስቷል።

21ዱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር ማን ይደራደር እንዲሁም ድርድሩን ማን ይምራው በሚሉት ጉዳዮች አስቀድመው ተገናኝተው የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱና ውሳኔያቸውን ለቀጣዩ ቅዳሜ ይዘው ለመምጣት ቀነ ቀጠሮ ይዘዋል። 

ፓርቲዎቹ ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ስብሰባ በክርክና ድርድሩ ዓላማ ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን