አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 08 March 2017

ድሬደዋ የካቲት 29/2009 የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ) የክልሉን ሕዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ትርጉም ባለው መንገድ ለመፍታት እያከናወነ ያለውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠሉን የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ንግድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር አብዲ ተናገሩ።

ፓርቲው የተመሰረተበት 19ኛ ዓመት በዓል ዛሬ በድሬዳዋ አስተዳደር ተከብሯል፡፡

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የኢሶህዴፓ አባላትና ደጋፊዎች፣ የድሬዳዋ አስተዳደርና እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተማሪዎችና የድሬዳዋ ነዋሪዎች ለፓርቲው ያላቸውን ድጋፍ የሚገልጹ መፈክሮች አንግበው በዓሉን በሰልፍ አክብረዋል፡፡

በድሬዳዋ ስታዲዮም በተካሄደው በዓል ላይ የተገኙት አቶ ከድር አብዲ ፓርቲው ላለፉት 19 ዓመታት የክልሉን ሕዝብ ማህበራዊ፣ የምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ትርጉም ባለው መንገድ በመፍታት የክልሉን እድገት በማፋጠን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በመንደር ለተሰባሰቡት አርብቶአደሮች የመሠረተ ልማት አውታሮችን በማሟላት የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ለማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ ትምህርት፣ መንገድ፣ ጤናና መሰል ማህበራዊ አገልግሎቶችን በማዳረስ የክልሉ ነዋሪ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ለማድረግ መቻሉን አስታውሰዋል።

በክልሉ የሚገኙ ሥራ እጥ ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰራው ሥራም የተደራጁ ወጣቶች ሕይወታቸውን እንዲለውጡ የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎች እንዲያገኙ ከመደረጉ በተጨማሪ የብድርና የገበያ ትስስር እየተፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አቶ ከድር ገለጻ በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋምና ለችግር የተጋለጡ አርብቶአደሮችን ሕይወት ለመታደግ ክልሉ ከፌደራል መንግስት ጋር በመቀናጀት የምግብ እህል፣ የእንስሳት መኖና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ ነው፡፡

የድሬዳዋ ኢሶህዴፓ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰቡኔ አብዲ በበኩላቸው፣ ኢሶህዴፓ በክልሉ እያስመዘገበ ካለው የልማት ውጤቶች በተጨማሪ ድሬዳዋ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል እንድትሆን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች የሕብረተሰቡን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሥራ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ግንባር ቀደም ሚናቸውን ለመወጣት የተቀናጀ ጥረት እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በአስተዳደሩ የሚገኙ የፓርቲ ደጋፊዎችና አባላት ከፓርቲው ጎን በመሆን ብልሹ አሰራሮችንና የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርና አመለካከቶችን በፅናት እንዲታገሉም አቶ ሱበኔ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ያለፉ ሥርአቶችን ጭቆና አሜን ብለው ሳይቀበሉ ተቃውሟቸውን በይፋ ሲገልጹና ሲታገሉ ከነበሩ የአገሪቱ ሕዝቦች መካከል የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ አንዱ መሆኑን ያስታወሱት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራም ዑስማን ናቸው።

እርሳቸው እንዳሉት ኢሶህዴፓ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የድርሻውን እያበረከተ ይገኛል።

በዚህም የክልሉ ህዝብ ከሌሎቹ የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩል በሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻሉን አስታውቀዋል፡፡

የድሬደዋ ነዋሪዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ህገ-መንግስታዊ ምላሽ በመስጠትና ከእህትና አጋር ድርጅቶች ጋር ሆኖ ልማትና እድገት እንዲፋጠን የሚያከናውናቸውን ተግባራት እንዲያጠናክርም አስገንዝበዋል፡፡

"ፓርቲው ባለፉት 10 ዓመታት በክልሉም ሆነ በድሬዳዋ አስተዳደር ተጨባጭ የልማት ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል" ያሉት ደግሞ በድሬደዋ የቀበሌ 07 ነዋሪ ሐጂ ሐሰን ዑመር ናቸው።

ወጣት ሸኪብ ኢብራሂም በበኩሉ ፓርቲው በየፈረጁ ለወጣቱ ሥራ ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ጥረት ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት ጠቁሟል፡፡

የፓርቲው 19ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል "በጥልቅ ተሃድሶ ላይ የተመሰረተ ድርጅታዊ ለውጥ ለአንድነታችንና ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ሃሳብ ከወትሮው በተለየ ድምቀት ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የኢህአዴግ የድሬዳዋ ኮሚቴ ጽህፈትቤትና የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ የድጋፍ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡

Published in ፖለቲካ

 

 

አዲስ አበባ የካቲት 29/2009 የደቡብ ኮሪያ ቹንቡክ ግዛት ነዋሪዎች ኢትዮጵያ በደቡብ ኮሪያ ጦርነት ወቅት ላደረገችው ድጋፍ ምስጋናቸውን በተግባር እያረጋገጡ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከደቡብ ኮሪያ ቹንቡክ ግዛት የልዑካን ቡድን አባላት ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1950 በኮሪያ ጦርነት ወታደሮችን በመላክ ድጋፍ በማድረግ አጋርነቷን አሳይታለች። ከጊዜ ወደ ጊዜ አገራቱ በተለያዩ መስኮች ያላቸው ግንኙነት እየጎለበተ መጥቷል።

የቹንቡክ ግዛት ህዝቦች ይህንኑ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ የለጋሽ ቡድን አቋቁመው ገንዘብ በማሰባሰብ በኢትዮጵያ በገጠር ልማትና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ ድጋፍ እያደረጉ ነው።  

ለጋሾችን የሚያስተባብረው ደግሞ ኢትዮጵያ በደቡብ ኮሪያ ጦርነት ወቅት ስላደረገችው ድጋፍ የመጀመሪያውን ጽሁፍ ይዞ የወጣው ዶንግ ያንግ ዕለታዊ ጋዜጣ ነው።

የግዛቱ ህዝቦች በአዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ በመገንባት ላይ ለሚገኘው የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረግ ችለዋል። 

በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ በኩል የገጠር ልማት ስትራቴጂውን መደገፍ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወኑ ናቸው።    

የልዑካን ቡድኑ አባላት የግዛቱ ነዋሪዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ ይበልጥ በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ላይ ነው ከፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ጋር የተወያዩት።

የገጠር ልማት ሥራዎችን ድጋፍ ይበልጥ ለማጠናከር የግዛቱ ህዝቦች እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2017 ጀምሮ በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በኩል ድጋፍ ለማድረግ ከስምምነት መደረሱ በውይይቱ ላይ ተገልጿል።

የልዑካን ቡድኑ መሪና የዶንግ ያንግ ዕለታዊ ጋዜጣ ባለቤት ሚስተር ጆ ቺኦል ሆ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በትምህርቱ መስክ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የቹንቡክ ህዝብ ላለፉት 22 ዓመታት ሲደግፍ ቆይቷል።      

''የግዛቷ ህዝቦች ኢትዮጵያዊያን በጦርነቱ ወቅት ያደረጉትን ድጋፍ አይዘነጉትም'' ያሉት የቡድን መሪው፤ አገራቱ ካላቸው ታሪካዊ ቁርኝት አኳያ በተለያዩ መስኮች የሚኖራቸው ትስስር ሊሰፋ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ሁለቱ አገሮች የሚጋሩት ታሪክ በዚህኛው ትውልድ ብቻ ሊታወስ እንደማይገባው የተናገሩት የቡድኑ መሪ፤ የአገራቱ ታሪክ ተጠብቆ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የቹንቡክ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ተቀናጅቶ የመስራቱን ሂደት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ በበኩላቸው የግዛቱ ነዋሪዎች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተባብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን አድንቀዋል። 

''ከዚህ በፊት በደቡብ ኮሪያ ባደረኩት ጉብኝት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ጥልቅ መሆኑን ተገንዝቢያለሁ'' ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ አገር መሆኗን ለልዑካን ቡድኑ አባላት ያስረዱት ፕሬዚዳንቱ፤ የደቡብ ኮሪያ ባላሃብቶች ኢትዮጵያ ወስጥ በስፋት እንዲሳተፉ መንግስት እንደሚያበረታታ ገልጸዋል።

የልዑካን ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፤ በግዛቱ ህዝቦች የሚደገፉ የትምህርት ፕሮጀክቶችን እንደሚጎበኝ ይጠበቃል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 29/2009 መንግስት ለሥራ ወደ ተለያዩ አገሮች የሚሄዱ ሴቶች መብት እንዲከበር ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ106ኛ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ41ኛ ጊዜ የተከበረውን የሴቶች ቀንን አስመልክቶ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደር የተወጣጡ የሴቶች ተወካዮች ጋር በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ተወያይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ለስራ ወደ ተለያዩ አገሮች የሚሄዱ ሴቶች የመብት ጥሰት እንዳይደርስባቸው ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።

ሴቶቹ በሚሄዱባቸው አገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች መጠለያና በጉዟቸው በሚተላለፋባቸው ዋና ዋና ቦታዎች የማቆያ ስፍራዎች ለማዘጋጀት የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሴቶች ለስራ ከሚጓዙባቸው አገሮች መንግስታት ጋር የኢትዮጵያ መንግስት ውል ካልተፈራረመ እንዳይሄዱ እንደሚደረግም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገልጸዋል። 

ሴቶቹ በብዛት ከሚሄዱባቸው የባህረ ሰላጤ አገሮች መንግስታት ጋር ውል እንደተፈረመ ጠቁመው፤ ይህም ሴቶች የሚደርስባቸውን እንግልትና የመብት ጥሰት ለመቀነስ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

የተደረገው ውል በሴቶቹ ላይ ማንኛውም ችግር ቢከሰት አገሮቹን በህግ መጠየቅ  እንደሚያስችልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከባህረ ሰላጤው አገሮች መካከል ውል ያልተፈራረመችው ከሳዑዲ አረቢያ ጋር መሆኑን አስታውሰው፤ በቅርቡ ውሉ እንደሚፈረም ገልጸዋል።

በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚሰጠውን ስልጠና ያልወሰዱና ስምንተኛ ክፍል ያላጠናቀቁ ሴቶች ወደ ተለያዩ አገሮች ለስራ መሄድ እንደማይችሉም አመልክተዋል።

መንግስት ሴቶች ወደ ተላያዩ አገሮች ሳይሄዱ በአገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ የሚያደርገውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በቂ እንዳልሆነ አመልክተው፤ በዚህ ረገድም በቀጣይ ለጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ባለፈው ዓመት የካቲት ወር መውጣቱ የሚታወስ ነው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 29/6/2009 ጣሊያን ለኢትዮጵያ ለግል ዘርፍ ልማት የሚውል የአምስት መቶ ሺ ዩሮ ድጋፍ ሰጠች።

ድጋፉ በዓለም ባንክ የዓለም ዓቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን የልማት መርሃ ግብሮች መካከል አንዱ ለሆነው "ለግል ዘርፉ ልማት መርሃ ግብር" ማስፈጸሚያ የሚውል ነው።

ድጋፉ የተደረገው ከተለያዩ ለጋሽ አካላት ገንዘብ በማሰባሰብ ለታዳጊ አገሮች የግል ዘርፍ ድጋፍ በሚሰጠው "በመልቲ ዶነር ኢንሸቲቭ ፎር ፕራቬት ሴክተር ደቨሎፕመንት" በተሰኘው የጋራ ትብብር ማዕቀፍ በኩል ነው።

የድጋፍ ስምምነቱ ፊርማ ስነ ስርዓትም ከሶስቱም ወገን ተወካዮች በተገኙበት በጣሊያን ኤምባሲ ዛሬ ተካሂዷል።

ስምምነቱ ለግል ዘርፉ እድገት በተለይም ለአነስተኛና መካከለኛ የማምረቻ ኢንተርፕራይዞች ልማት የሚውል ነው።

የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን የሰሃራ በታች የልማት ትብብር ኃላፊ ኢቫ ባኮኒ እንደገለጹት፤ ድጋፉ ያስፈለገው ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለው ተከታታይ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ የማምረቻውን ዘርፍ ለማጠናከር ነው።

ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥሩ አነስተኛና መካከለኛ የማምረቻ ዘርፎች እንዲዳብሩ የአቅም ግንባታ ስራዎች ለመስራት እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ጁሴቴ ማስትሬት በበኩላቸው፤ የጣሊያን መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርገው የፋይናንስ ድጋፍ ከጊዜ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

"የፋይናንስ ድጋፉ የግሉ ዘርፍ እንዲዳብርና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ያለመ ነው" ብለዋል።

ይህም ወጣቶች በአገር ውስጥ ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸውና ስደትን ለመቀነስ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በትምህርትና በጤና መሰረተ ልማቶች ከምታደርገው ድጋፍ በተጨማሪ አገሪቷ ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ሽግግር የግሉ ዘርፉ እንዲዳብር ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ነው የተናገሩት።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ወክለው የተገኙት በሚኒስቴሩ የፖሊሲና ፕሮግራም ዳይሬክተርና የልማት አጋሮች ፕሮጀክቶች አስተባባሪ አቶ አህመድ ኑሩ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር በአነስተኛና መካከለኛ የማምረቻው ዘርፍ ላይ በትኩረት እየሰራች ነው።

በማምረቻው ዘርፍ የተሰማሩ የግል አምራቾች ካሉባቸው ማነቆዎች መካከል የፋይናንስ አቅርቦትና የመሬት ችግር እንደነበር ገልጸው፤ ድጋፉ በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ ያለውን ችግር ለማቃለል እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

የጋራ የልማት አጋሮች የመንግስትን የፖሊሲ አቅጣጫ ፈትሸው የሚያደርጉት ድጋፍ ተግባራዊ የሚሆነው በልማት ባንክ የፋይናንስ ሊዝ ስርዓት መሆኑን አመልክተዋል።

የመሬት አቅርቦት ችግርን ለመፍታትም በየወረዳው የኢንዱስትሪ ክላስተር ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን አቶ አህመድ ተናግረዋል።

የጣሊያን መንግስት በዓለም ዓቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን በኩል ለኢትዮጵያ ያደረገችው ድጋፍ የአሁኑን ጨምሮ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዩሮ ደርሷል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ደብረማርቆስ የካቲት 29/2009 ሴቶች በህዳሴው ግድብ ያላቸውን አስተዋጽኦ በማሳደግና የቁጠባ ባህላቸውን በማዳበር  ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ምሁራን በጥናትና ምርምር ማገዝ እንዳለባቸው ተጠቆመ።

የደብረማርቆስ ዩንቨርስቲ  አለም  አቀፍ የሴቶች ቀን  ዛሬ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።

የዩንቨርስቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ታደሰ ጤናው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ሴቶች በቀደምት ስርዓቶች ይደርስባቸው የነበረውን  ጭቆናና አድሎ ለማስወገድ በተደረገው ትግል ጉልህ አስተዋጽኦ አበረክተዋል።

የበዓሉ ዋና ዓላማም ጭቆናና አድሎን ለማስወገድ የተደረገውን ሁለተናዊ የትግል እንቅስቃሴ እና የተገኘውን ውጤት በመዘከር  ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ  እንዲያሳድጉ መነሳሳትን ለመፍጠር ነው።

"ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች ሴቶች ከወንዶች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሆኑበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል "ብለዋል።

በቀጣይም  የጾታ እኩልነት የበለጠ እንዲጎለብት፣ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲወገዱና በሀገሪቱ  የህዳሴ ጉዞ  ሴቶች ግንባር ቀደም ተዋናይ እንዲሆኑ ማጠናከር ያስፈልጋል።

በህዳሴው ግድብ ያላቸውን አስተዋጽኦ በማሳደግ እና የቁጠባ ባህላቸውን በማዳበር ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ምሁራን በጥናትና ምርምር ማገዝ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

ዩንቨርስቲው በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዘርፉ የሴቶች የቁጠባ ባህል ለማሳደግ እና ለሀገር የሚያበረክቱበትን አስተዋጽኦ ለማስፋት የሚያስችል የምርምር ስራ በቅርቡ  የሚጀምር በመሆኑ ምሁራን በንቃት እንዲሳተፉም ጠይቀዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ አዲሴ ጫኔ በበኩላቸው የዓለም የሴቶች ቀን መከበሩ የታለፉ ጭቆናዎችን ለመዘከርና አሁን ላይ በተገኘው ድል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚያገዝ ገልጸዋል፡፡

ዩንቨርስቲውም የበርካታ ሴት እህቶቻችን መገኛ እንደመሆኑ በዓሉን አስታውሶ መብትና ጥቅማቸው እንዲከበር  ግንዛቤ መፍጠሩ የሚበረታታ  መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል ተማሪ ደስታ ደመቀ ዕ የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ ያላቸውን  በመቆጠብ የወደፊት  ዓላማቸውን ለማሳካት ንቅናቄ መፈጠሩ እንዳስደሰታት ተናግራለች፡፡

" እኔም በትምህርት ዘርፉ ባስመዘገብኩት ውጤት የ2ሺ ብር ቦንድ ሽልማት መግኘቴ በህዳሴው ግድብ ላይ የራሴን አሻራ እንዳሳረፍኩ ያህል እንዲሰማኝ አድርጎኛል "ብላለች።

በዓሉ  ላይ ከፓናል ውይይቱ  ሌላ  የጥያቄና መልስ ውድድር  እንዲሁም  ድራማና የስነ ጹሁፍ ዝግጅቶች ተካሄደዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ደብረማረቆስ  የካቲት 29/2009 በምርጥ ዘር ብዜት መሰማራታቸው የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ያስቻላቸው መሆኑን በምስራቅ ጎጃም ዞን አንዳንድ አርሶአደሮች ገለጹ።

የደብረኤሊያስ ወረዳ የጉፍጭማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ጌትነት ጫኔ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘር ብዜት ሥራ ከተሰማሩ አራት ዓመት ሆኗቸዋል።

በእዚህም የሰብል ምርጥ ዘሮችን በማባዛት እና በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ገቢያቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ እንዳሉት፣ በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ የስንዴ ምርጥ ዘር አባዝተው ምርጥ ዘር ያልሆነው ስንዴ ከሚያወጣው ዋጋ በኩንታል 15 በመቶ ጭማሬ አድርገው እየሸጡ ናቸው።

"ምርጥ ዘር ማባዛት ከጀመርኩ አንስቶ በየዓመቱ እስከ 45 ኩንታል በማምረት ከ30 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘት ችያለሁ" ሲሉም ገልጸዋል።

በእዚሁ ወረዳ የጓይ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አዘነ ገደፋው በየዓመቱ የበቆሎና የስንዴ ምርጥ ዘሮችን በማባዛት በ15 በመቶ ጭማሪ ለሕብረት ሥራ ማህበራት ማስረከባቸውን ተናገረዋል።

ምርጥ ዘር ያልሆነውን ስንዴና በቆሎ አምርተው ሲሸጡ ከነበራቸው ገቢ ጋር ሲነጻጸር የአሁኑ የተሻለ መሆኑ የምርጥ ዘር ብዜት ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያደረጋቸው መሆኑን አስረድተዋል።

" ከሁለት ዓመት ወዲህ በምርጥ ዘር ብዜት በዓመት ከ130 ኩንታል በላይ ስንዴ እና በቆሎ በማምረትና በመሸጥ ትርፋማ መሆን ችያለሁ" ብለዋል።

በአዋበል ወረዳ ወጀል ቀበሌ የሚኖሩት አርሶአደር ሽፈራው ገዳሙ በበኩላቸው ፣ የሽንብራ ምርጥ ዘር በማባዛት ተጠቃሚ መሆን ከጀመሩ አምስት ዓመታት እንደሆናቸው ተናግረዋል።

በየዓመቱ በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ ከ12 ኩንታል በላይ የሽምብራ ምርጥ ዘር በማምረት በእያንዳንዳንዱ ኩንታል አራት መቶ ብር ጭማሬ እያገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የዞኑ ግብርና እና ገጠር ልማት መምሪያ የዘር ብዜት ባለሙያ አቶ እያለ ዳኘ ለኢዜአ እንደተናገሩት አርሶአደሩ ጥራት ያለው ምርጥ ዘር በማባዛት የዘር አቅርቦት ችግርን እየፈታ ነው።

በያዝነው የምርት ዘመን በዘር ብዜት ከተሸፈነ ሁለት ሺህ 900 ሄክታር በላይ ማሳ ከ170 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ማገኘት ተችሏል።

ባለሙያው እንዳሉት፣ በዞኑ የሚገኙ አራት ሺህ 800 አርሶአደሮችም በዳቦና ማካሮኒ ስንዴ፣ በጤፍ፣ በበቆሎና ሽንብራ ምርጥ ዘር ማምረት ሥራ ላይ ተሳትፈዋል።

ባለፈው ዓመት በዞኑ ከ120ሺህ ኩንታል በላይ ጥራቱን የጠበቀ ምርጥ ዘር በአርሶአደሩ ተባዝቶ በመቅረቡ በአካባቢው ይስተዋል የነበረውን የዘር አቅርቦት እጥረት እንዲቃለል ከማድረጉ ባለፈ የዞኑ ምርታማነት እንዲያድግ  አስችሏል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 29/2009 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከታኅሳስ አንድ እስከ የካቲት ሀያ ድረስ የተሻለ የሰሩ ሴቶችን ሸለሙ።

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን "ማርች 8" ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተከብሯል።

የዘንድሮው የሴቶች ቀን ማርች 8 "የሴቶች የቁጠባ ባህል መዳበር ለህዳሴያችን መሰረት ነው" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተከበረው።

ሴቶቹ ለሽልማት የበቁት "ጥሩ ቆጥበዋል" በሚል ነው። በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ በቁጠባ የአጠራቀሙት ሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም  የሸለሟቸው ሴቶች፤ በከተማ ግብርና፣ በማንፋክቸሪንግ፣ በሆቴልና ምግብ ዝግጅት ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች በእንጨት ስራና በከብት ማድለብ፣ በምግብ ማቀነባበርና በሌሎች ሙያዎች የተሰማሩ ቆጣቢና ውጤታማ የሆኑ ናቸው።

ሴቶቹ በሽልማት ካገኙት መካከል ትራክተር፣ የውሃ ማውጫ ፓንፕ፣ ሶላርና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ይጠቀሳሉ።

የተሸለሙት ሴቶች ከዘጠኙም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ናቸው።

 

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ የካቲት 29/2009 ተደራጅተው በተሰማሩባቸው ስራዎች ከሚያገኙት ገቢ በመቆጠብ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሴቶች ተናገሩ፡፡

በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የሴቶች አረጃጀቶች መካከል በጉራጌ ዞን እንደጋኝ ወረዳ ጎምታ ቀበሌ የታጀኔ ልማት ቡድን አንዱ ነው፡፡

የልማት ቡድኑ ሰብሳቢ ወይዘሮ አለምነሽ ሃብሌ እንደተናገሩት ቡድኑ በ2006ዓ.ም ሲደራጅ 27 ሴቶችን በአባልነት በማቀፍ እያንዳንዳቸው  በወር ሁለት  ብር በመቆጠብ ነው፡፡

ከወረዳው በተፈቀዳላቸው የጋራ መሬት በባለሙያዎች እየታገዙ ወደ እርሻ በመግባት በዓመት ሶስት ጊዜ በማምረት  የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ችለዋል፡፡

ያመሩቱትን 75 ሺህ ኩንታል ስንዴ ለምርጥ ዘር ድርጅት ማስረከባቸውን ያመለከቱት የቡድኑ ሰብሳቢ ከሚያገኙትም ገቢ በመቆጠብ ከ246ሺህ ብር በላይ የጋራ ተቀማጭ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪ አባላቱ በየግል የቁጠባ ደብተር እንዳላቸውና እሳቸውም 113ሺህ ብር መቆጠባቸውን ጠቅሰው ልማት ቡድኑ በወረዳው ሁሉም ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መልካም ተሞክሮውን እንደሚያካፍልም ተናግረዋል፡፡

አርባምንጭ ከተማ የናርዶስ ምግብ ዝግጅት ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ሄለን ታደስ በበኩላቸው ወደ ስራ የገቡት በ2004 ዓ.ም መንግስት ያመቻቸላቸውን 25ሺህ ብር የመነሻ ካፒታል በመጠቀም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ካፒታላቸው ወደ ግማሽ ሚሊየን ብር  በማደጉ ማህበሩ ተጨማሪ ሶስት ቅርንጫፎችን ከፍቶ እየሰራ ነው " ብለዋል፡፡

በማህበሩ ለ21 ሴቶች የስራ እድል በመፍጠር የተለያዩ የባልትና ውጤቶችን ለአርባምንጭ ሆስፒታልና ለተለያዩ ተቋማት እንደሚያቀርቡም ጠቁመዋል፡፡

የማህበሩ ቁጠባ ከ31ሺ በላይ መድረሱን የጠቀሱት ወይዘሮ ሄለን "ቁጠባ ለነገ የሚቀመጥ ቅርስ ነው " ብለዋል፡፡

የልማት ቡድን አባላት በተለያዩ የልማት ተግባራት ላይ ተሰማርተው ባለፈው አንድ ዓመት አስራ አምስት ሺህ ብር  መቆጠባቸውን የተናገረችው ደግሞ  በከምባታ ጠምባሮ ዞን ጠምባሮ ወረዳ ቦሄ ቀበሌ የሴቶች ልማት ቡድን ሰብሳቢ አስናቀች ጥላሁን ናት፡፡

ሴቶች ተደራጅተው በተሰማሩባቸው ስራዎች ከሚያገኙት ገቢ በመቆጠብ ተጠቃሚነታቸው እያደገ ከመምጣቱም ሻገር  በሚገጥማቸው ችግሮች ዙሪያ በጋራ እንዲወያዩና  ልምድ እንዲለዋወጡ እድል መፍጠሩንም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን በበኩላቸው "በክልሉ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሴቶች በልማት ቡድን ተደራጅተው በመንቀሳቀስ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውንና ተሳትፎዋቸውን እያሳደጉ ነው "ብለዋል፡፡

በቀጣይ በአደረጃጀት ያልታቀፉ ሴቶችን ለማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው "አደረጃጀቶቹ ሴቶች አቅማቸውን በተገቢው እንዲጠቀሙ እድል የፈጠረ ነው " ብለዋል፡፡

ለሴቶች የልማትና የለውጥ ፓኬጅ ተግባራዊነት በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 29/2009 የአፍሪካ ሴቶችን በየደረጃው ለማብቃት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ዶክተር ዲላሚኒ ዙማ ገለጹ።

ዛሬ በተካሄደው የሴቶች ቀን በዓል ላይ ተሰናባቿ የሕብረቱ ሊቀ መንበር ዶክተር ዲላሚኒ ዙማ እንደገለጹት፤ በሁሉም ዘርፍ ሴቶችን ለማብቃት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡

የአፍሪካ አገሮች ሴቶች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ከወንዶች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ "ይበልጥ መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።

አፍሪካ ህብረት የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8ን ''በሴቶች በተለይ ወጣት ሴቶች እየተለወጠ ባለው ዓለም ውሰጥ በ2063 ከወንዶች እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ይሰራል'' በሚል መሪ ሀሳብ አክብረዋል።

ዶክተር ዲላሚኒ ዙማ እንዳሉት፤ የሴቶችና ወጣት ሴቶችን እኩልነት በሁሉም ዘርፍ እውን እንዲሆን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል፡፡

በተለይ በአፍሪካ ኅብረት 28ኛው የመሪዎች ጉባዔ  ላይ"ከፍተኛ የአምራች ኃይልን ለመጠቀም በወጣቶች ላይ መዋዕለ ነዋይ እናፍስ" በሚል በተቀመጠው መርሕ መሰረት ወጣት ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሁኑ አገሮች በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

የቀኑ መከበር የሴቶች እኩልነትን ለማረጋገጥ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ለማስጠበቅና በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በተለይ በገጠሪቷ አፍሪካ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመቀነስ፣ የስራ ጫና ለማቃለል፣ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረትና ከኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የቦትስዋና አምባሳደርና የአፍሪካ ሴቶች ዲን ሚሲስ ማሞሳዲያና ሞሌፋ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ሴቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

እነዚህ የሕብረተሰቡን ግማሽ አካል ተጠቃሚ በማድረግና የጾታ እኩልነትን በማረጋገጥ የበለጸገች አፍሪካ መፍጠር እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

"በወጣት ሴቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግና በገጠር ያሉትን በማስተማር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድርግ መስራት አለብን" ብለዋል።

በቅርቡ በዓለም አቀፍ የሴቶች ሊደር ሺፕ አሸናፊ የሆኑት ደቡብ አፍሪካዊቷ ባለሀብት ሚስስ አዴላድ ሩተርስ  "እኔ በትንሽ ገንዘብ ጀምሬ ከፍተኛ የማዕድን አምራች ተቋም ባለቤት ሆኛለሁ፤ ሌሎች የአፍሪካ ወጣት ሴቶችም ይህን ልምድ መውሰድ አለባቸው" ብለዋል።

የአፍሪካ ሴቶች እየተለወጠች ባለችው ዓለም ውስጥ ጠንክረው መስራት እንደለባቸው አመልክተው፤ በአህጉሪቷ ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉና  ያላቸውን አቅም በመውጣት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

"የአፍሪካ ሴቶችን ለማብቃትና ወደ መሪነት ለማምጣት አገሮች መስራት አለባቸው" ያሉት ደግሞ የአፍሪካ ህብረት የሰው ሃብት ልማት ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ ኦድራውጎ ናቸው።

ሴቶችን በማሰተማር ለአፍሪካ ዕድገት የበለጠ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ማድርግ እንደሚያስፈልገ ተናግረዋል።

ህብረቱ በዛሬው እለት በዓሉን ሲያከብር በአጉሪቷ ተምሳሌታዊ ስራ የሰሩ ሴቶች ተዘክረዋል።

የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ106ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ41ኛ ጊዜ ተከብረዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 29/2009 "ከወጣት ተጫዋቾች ይልቅ ልምድ ያላቸው ላይ ትኩረት ሰጥቼ እሰራለሁ" ሲሉ ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ተናገሩ፡፡

ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ ከሁለት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን /የዋሊያዎቹ/ ዋና አሰልጣኝ ሆነው  መመረጣቸው ይታወቃል።

ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤ በብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውስጥ ልምድ ያላቸውና ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ ተጫዋቾችን በማፍራት ስራ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡

''የተመረጥኩት ወጣት ተጫዋቾችን ለማፍራት ሳይሆን ልምድ ያላቸውን በመጠቀም ውጤት ለማምጣት ነው። ስለዚህ በዚህ ተግባር ላይ አተኩሬ እሰራለሁ '' ብለዋል።

በርካታ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን በመያዝ ብሔራዊ ቡድኑን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

እንደ ዋና አሰልጣኙ ገለጻ፤ ትልቁ ዓላማቸው ህዝብንና መንግስትን የሚያስደስቱበት ውጤት ማስመዝገብ ነው።

''አሁን ባለሁበት ደረጃ ውጤት ያመጡልኛል ብዬ ያሰብኳቸውን ተጫዋቾች ይዥ ነው መስራት ያሰብኩት፤ ወጣት ተጫዋቾች ለማፍራት ከሆነ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ላይ ነው መቀጠር ያለብኝ'' ብለዋል።

ብሔራዊ ቡድኑን ውጤታማ ለማድረግም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ትብብርና ድጋፍ  እንዲያደርጉ አሰልጣኙ ጠይቀዋል።

''ለውጤታማነቱ እኔ ብቻዬን ምንም አላመጣም፤ አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ ፌዴሬሽኑና የመገናኛ ብዙሃን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን የሚወጣ ከሆነና ተባብረን ከሰራን ነው ለውጥ የሚመጣው'' ብለዋል። 

''ጠንካራና ውጤታማ ቡድንን ለመመስረት ለአሰልጣኞች ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል" ያሉት ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ፤ ባለፉት ዓመታት በብሔራዊ ቡድኑ የተቀጠሩ አሰልጣኞች በየጊዜው መለዋወጣቸው ጠንካራ ተጫዋቾችን ለማፍራት ተግዳሮት እንደሚፈጥረባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለብሔራዊ ቡድኑ አሸናፊ በቀለን ዋና አሰልጣኝ  አድረጎ ቢመርጥም፤ እስከሁን ግን የቅጥርና የስራ ስምምነቶችን አላከናወኑም።

Published in ስፖርት
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን