አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 07 March 2017

አዲስ አበባ የካቲት 28/2009 ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች መንግስት ምግብ፣ ምግብ ነክና የመኖ አቅርቦት በአስተማማኝ ሁኔታ በወቅቱ እንዲደርስ እየሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ ድርቅ በተከሰባቸው በደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች የምግብ፣ ምግብ ነክና መኖ አቅርቦት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።

የሰው ሕይወት የመታደግ፣ የእንስሳቱን ጉዳት የመቀነስና የእንስሳት ኃብቱን ጠብቆ የመዝለቅ አማራጭ ተይዞ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

የዘንድሮው የድጋፍ ፍላጎት አዲስ ካጋጠመው ድርቅና ካለፈው ዓመት ከመጣው የእርዳታ ፈላጊ ህብረተሰብ ጋር የተዳመረ መሆኑን አስታውሰው፤ በሁለቱ ድምር ውጤቶች ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ርብርብና ትኩረት እንደሚጠይቅም ነው የተናገሩት።

መንግስት የድርቁን የጉዳት መጠን ጥልቀትና ስፋት በዝርዝር በማጥናት የአንድም ሰው ሕይወት እንዳይጠፋ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በእንስሳት ላይ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም "በቀጣይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል አቅጣጫ ተግባራዊ እየተደረገ ነው” ብለዋል።

ድርቁ በተከሰተባቸው በተለይም በኦሮሚያ ቦረና፣ በባሌና ጉጂ ዞኖች ቆላማ አካባቢዎች፣ በሶማሌ ክልል፣ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ አካባቢዎች  ጉዳቱ ከባድ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ዘንድሮ በአጠቃላይ እርዳታ የሚሹ ዜጎች ቁጥር ከአምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ሲሆኑ፤ ባለፈው ዓመት በተከሰተው ድርቅ ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለድርቅ አደጋ ቢጋለጡም በራስ አቅም መታደግ መቻሉ ይታወሳል።

መንግስት ከየትኛውም ጉዳይ በላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅዱን የፕሮጀክቶችና የልማት መርሃ ግብሮች ሳይጎዳ የሚያስፈልገውን ሀብት የመመደብና በወቅቱ ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የተዘጋጁ የውሃ ጉድጓዶች በጥልቀት ተቆፍረው ውሃ ቶሎ እንዲወጣ የማድረግና የተለያዩ አማራጮችን የመጠቀም ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ የአርብቶ አደሩን እንስሳት ህይወት ለመታደግ የሚያስችሉ ስራዎችም ተግባራዊ እየሆኑ በመምጣታቸው የሚያበረታታ ውጤት መታየቱን አመልክተዋል።

መንግስት የሚያደርገው ድጋፍ በተቻለ መጠን ብክነትና ጥፋት ሳይደርስበት ተጠቃሚዎቹ ዘንድ በወቅቱ ለማድረስ የሚያስችል ክትትልና ያንንም ሊያረጋግጥ የሚችል ስርአት መዘርጋቱን አረጋግጠዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ የመንግሥታቱ ድርጅት መጠየቁ ይታወሳል።

Published in ማህበራዊ

ጅግጅጋ የካቲት 28/2009 ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የቦንድ ሽያጭ በጅግጅጋ ከተማ ተጀመረ።

የክልሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እንደገለጸው፣ የቦንድ ሽያጩ እየተከናወነ ያለው ጽህፈት ቤቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ተንቀሳቃሽ ድንኳኖች አማካኝነት ነው።

በእዚህም ከ25 ብር ጀምሮ እስከ 100 ሺህ ብር ዋጋ ያላቸው ቦንዶች ለሽያጭ መቅረባቸው ተመልክቷል።

ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ በተጀመረው የቦንድ ሽያጭ ሥነስርአት ላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የመንግስት ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በሥነስርአቱ ላይ የመጀመሪያውን ቦንድ ግዥ የፈጸሙት የክልሉ ምክር ቤቱ አፈጉባኤ አቶ መሀመድረሺድ ኢሳቅ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ዝግጅቱ የክልሉ ሕዝብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ የሚያጠናክር ነው።

እንደአፈጉባአው ገለጻ፣ የክልሉ ሕብረተሰብ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ይፋ ከሆነበት ማግስት ጀምሮ በቦንድ ግዥ፣ በስጦታና በተለያየ መንገድ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

የግድቡ መገንባት የአገሪቱን የኃይል እጥረት ከማቃለሉም ባሻገር ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚደረገውን ጉዞ እንደሚያፋጥን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ሕብረተሰቡ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ በቦንድ ግዥና በስጦታ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አፈ ጉባኤው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለሕዳሴው ግድብ የታየው ሕዝባዊ ንቅናቄ በሌሎች የልማት መስኮችም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ምክር ቤት ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አፈጉባኤው ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር እድሪስ እስማኤል"ግድቡ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችን በአንድነት እያሳተፈ ያለ ልዩ ስጦታ ነው" ብለዋል ፡፡

ፕሮክጅቱ በአባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት ነግሶ የቆየውን የአይቻልም አስተሳሰብ የሰበረ መሆኑን ገልጸው፣ የተጀመረው የቦንድ ሽያጭ ሳምንት የክልሉ ሕዝብ የገባውን ቃል በቁርጠኝነት እንዲወጣ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ኢንጂነር እድሪስ እንዳሉት የክልሉ ነዋሪዎች እስካሁን በቦንድና በልገሳ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ለግድቡ ድጋፍ አድርገዋል።

የቦንድ ሽያጭ ሳምንቱ ከዛሬ ጀምሮ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች እስከ መጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም እንደሚቆይ ገልጸው፣ በእዚህም ሕብረተሰቡ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለውን ድጋፍ እያሰየ መሆኑን ተናግረዋል።

በዝግጅቱ ላይ የአራት መቶ ብር የቦንድ ግዥ የፈጸሙት አቶ አያን መሀሙድ በሰጡት አስተያየት፣ የቦንድ ሽያጭ ሳምንቱ በተለያዩ ወቅቶች ለግድቡ ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ዛሬም በአቅሜ ቦንድ መግዛት በመቻሌ ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ አዲስ ታሪክ እየሠራሁ ነው ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል'' ሲሉም ተናግረዋል።

" የአንድ መቶ ብር ቦንድ ግዢ  መፈጸማቸውን የገለጹት የጅግጅጋ ከተማ ቀበሌ 12 ነዋሪ አቶ አደን ዩሱፍ ናቸው።

በቀጣይም የግድቡ ግንባታ ፕሮጅክት ስኬታማ  እንዲሆን የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ጅግጅጋ የካቲት 28/2009 በኢሶህዴፓ አመራር ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተመዘገቡት የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራ ውጤቶችን ለማጠናከር  የድርሻቸውን እንደሚወጡ በጅግጅጋ ከተማ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ገለጹ፡፡

አባላትና ደጋፊዎች ፓርቲው የተመሠረተበትን 19ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ዛሬ በፓናል ውይይት አክብረዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ) አባላትና ደጋፊዎች እንደገለጹት በድርጅቱ መሪነት በክልሉ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

ከአባላቱ መካከል አቶ አደን ዩሱፍ በሰጡት አስተያየት ኢሶህዴፓ የሚመራው የክልሉ መንግስት በየደረጃው ባለው  የአስተዳደር እርከን  ህብረተሰቡን በማሳተፍና በማስተባበር ባለፉት ዓመታት ውጤታማ ስራዎች ተፈጻሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ  በተደጋጋሚ የተከሰተውን ድርቅ  በዘላቂነት ለመከላከል በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የተለያዩ ግቦች ተቀምጠው እየተተገበሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የድርጅቱ ደጋፊ አቶ አብዲከሪም ቀልንሌ ናቸው፡፡ 

ኢሶህዴፓ በተለይ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመረውን  የልማት ስራ አጠናክሮ ለማስቀጠል ከፓርቲው አባላትና ደጋፍዎች ብዙ እንደሚጠብቅም ጠቁመዋል፡፡

ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬታማ ለማድረግ እያደረጉት ያለውን ድጋፍ   ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንደሚቀጥሉበትም  አባላቱና ደጋፊዎቹ በሰጡት አስተያየት አረጋገጠዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች የተገኙ  ውጤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡

የኢሶህዴፓ ሊቀ መንበር አቶ መሐመድ ረሺድ በበኩላቸው "ፓርቲው ከኢህአዴግና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ መቻቻልና መከባበር የሰፈነበት ክልል እንዲገነባ አስችሏል" ብለዋል፡፡

ድርቅ ባጠቃቸው የክልሉ አካባቢዎች የምግብ፣ መዳሐኒትና የእንስሳት መኖ ለማቅረብ ኢሶህዴፓ እየሰጠ ያለው ቆራጥ አመራር ተጠናክሮ እንሚቀጥል ሊቀ መንበሩ አረጋግጠዋል፡፡

"ፓርቲያችን የሚመራው የክልሉ መንግስት ለ530 ሺህ አርብቶ አደሮች በየቀኑ የተዘጋጀ ምግብ እያቀረበ ይገኛል" ያሉት ሊቀመንበሩ በክልሉ የተከሰተው ድርቅ ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡፡

የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች በክልሉ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ የሚያደርጉትን ድጋፍ ማጠናከር እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

በጅግጅጋ ከተማ ሰይድ መሀመድ አብዲሌ ሐሰን የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተከበረው የኢሶህዴፓ 19ኛው ምስረታ በዓል ላይ የሻማ ማብራት ስነ ስርዓትም ተካሄዷል፡፡

Published in ፖለቲካ

ሽሬእንዳስለሴ የካቲት 28/2009 ከሑመራ በሱዳን ወደብ በኩል  ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ44 ሚሊዮን በላይ  የአሜሪካን ዶላር ላይ ገቢ ተገኘ፡፡

በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን  የሑመራ ጉምሩክ መቅረጫ ጣቢያ ተወካይ  አቶ ሃይሌ ገብረማርያም ለኢዜአ እንደገለጹት ገቢው የተገኘው በዘንድሮ ግማሽ የበጀት ዓመት ከተላከው ሰሊጥና ሌሎችም የግብርና  ምርቶች ነው፡፡

በዚህም  ወደ እስራኤልና ቻይና የተላከው ከ350ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥና በዚህም የተገኘው  ከ38 ሚሊዮን በላይ  ዶላር ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡

ገቢው በእቅድ ከተያዘውና  ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር  በሰባት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያነሰ መሆኑን አቶ ሃይሌ ተናግረዋል፡፡

ለገቢው ማነስ በምክንያትነት ከተጠቀሱት መካከል በዓለም ገበያ የሰሊጥ ዋጋ መቀዛቀዙን ተከትሎ  ዋጋ ይጨምራል በሚል አብዛኛው  ምርት ወደ ገበያ አለመውጣቱ ይገኝበታል፡፡

ሰሊጥ በማምረት ወደ  ውጭ ከሚልኩ ነጋዴዎች መካከል  አቶ ወላይ በርሄ  በሰጡት አስተያየት በዓለም ገበያ የሰሊጥ ዋጋ በመውረዱ ምክንያት  ባለፉት ስድስት ወራት ምርት  ወደ ውጭ እንዳላኩ ተናግረዋል፡፡

የሰሊጥ ምርት በአሁኑ ወቅት ያለው የአገር ውስጥ ዋጋና ሰሊጥን ለማምረት የሚወጣው ወጪ የሚያካክስ ባለመሆኑ አምራቹና ነጋዴው ለጉዳት እየተዳረገ መሆኑም ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ከሌሎች አምራቾች ጋር   በማህበር በመደራጀትና   ገበያን በማፈላለግ የተከማቸ ምርታቸውን ወደ ውጭ ለመላክ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም አመልክተዋል፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት በዓለም ገበያ የሰሊጥ ዋጋ እየወረደ በመምጣቱ ምርቱን ወደ ውጭ መላክ ማቆማቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አምራችና ላኪ አቶ ተኪኤ ባህታ ናቸው፡፡

" በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ ጉዳቱ እያመዘነ ይሄዳል" ያሉት አቶ ተኪኤ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የባዕኬር አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ  ስራ ሲጀመረ ምርታቸውን እሴት ጨምረው ለመላክ ተስፋ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመትም በሑመራ በኩል ወደ ተለያዩ አገራት  ከተላኩት  የግብርና ምርቶች  ከ154 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 28/2009 አስረኛው የአዲስ አበባ ከተማ መሪ ፕላን ለመኖሪያ ቤቶችና ለአረንጓዴ ቦታዎች ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን የመሪ ፕላኑ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ በመሪ ፕላኑ ዙሪያ ከተማ አቀፍ የነዋሪዎች ማጠቃለያ መድረክ አካሂዷል።

10ኛው የ2017 እና የ2032 ዓ.ም መሪ ፕላን ይዘት ምን እንደሚመስልና ከቀደሙት መሪ ፕላኖች ጋር ያለው ልዩነት እንዲሁም ሊያመጣ በሚችለው ለውጥ ላይ እስካሁን ከ500 በላይ የህዝብ ውይይት መድረኮች መካሄዳቸው ተገልጿል።

የከተማ አስተዳደሩ ፕላን ኮሚሽነርና የጽህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ማቴዎስ አስፋው እንደተናገሩት፣ ከነዚህ ውይይት መድረኮች የተገኙ ግብዓቶች የተካተቱበት ይህ መሪ ፕላን በቅርቡ በከተማዋ ምክር ቤት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

"መሪ ፕላኑ የአዲስ አበባ ከተማን እድገት በሚመጥን፣ የከተማዋን ዓለም ዓቀፋዊ ሚና የሚያሳድግና የዲፕሎማቲክ መዲናነቷን በማያሻማ መልኩ የሚያስቀጥል ነው" ብለዋል።

ከተማዋ የታዳሽ ኃይል ምንጭ እንድትሆን፣ የቱሪዝምና የኮንፍረንስ መዕከል እንዲሁም የአፍሪካ የባህል ማዕከልና ሙዚየም እንዲኖራት እድል ይፈጠራልም ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ነዋሪ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን መሆኑን የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ መሪ ፕላኑ በ2017 ከአምስት ሚሊየን በላይ የሚሆነውን ነዋሪ ማስተናገድ በሚችል መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።

መሪ ፕላኑ መዲናዋ በደረጃቸው የተከፋፈሉ የንግድ፣ የአስተዳደር፣ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ዋና ማዕከላት፣ የወረዳ ማዕከላትና የሰፈር ወይም የአጥቢያ ማዕከላት ያሉት ነው።

በመሆኑም መዲናዋ 30 በመቶ አረንጓዴ ቦታ፣ 30 በመቶ የመንገድ መሠረተ ልማትና 40 በመቶ ደግሞ የግንባታ ቦታዎች እንዲኖሯት ተደርጓል ብለዋል

ከዚህ በተጨማሪ ከተማዋ በአራት ዞኖች የተከፋፈለች ሲሆን ዞን አንድ የከተማ መዕከል፣ ዞን ሁለት ዋና ዋና ጎዳናዎች፣ ዞን ሶስት ከቀለበት መንገድ ርቀው ያሉ ቦታዎችና ዞን አራት ደግሞ አዲስ አበባ ዙሪያ ናቸው።

በዚሁ መሠረት ዞኖቹ 30 በመቶ፣ 40 በመቶ፣ 50 በመቶና 60 በመቶ እንደ ቅደም ተከተላቸው ለመኖሪያ ቤት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ እንደሚደረግ ተገልጿል።

በመዲናዋ ቅይጥ መኖሪያ በሚባል ስልት ለንግድ ተብለው የሚገነቡ ሕንጻዎች ከአራተኛ ፎቅ በላይ ለመኖሪያ እንዲያገለግሉ የሚያስገድድ ደንብ ተዘጋጅቷል ብለዋል አቶ ማቴዎስ።

በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ የሕዝቡን ኑሮ እያወኩ የሚገኙ የመንገድ ላይ የእንጨትና የብረት መስሪያ ቦታዎች፣ ጫት ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶችና መሰል ቤቶች ወደ ዋና መንገድ ብቻ ተቃርበው ስራቸውን እንዲሰሩ ይደረጋል።

ፕላኑ የከፍለ ከተሞችን ቁጥር ወደ 13 የሚያሳድግ ሲሆን የወረዳዎች ቁጥርም ይጨምራል ተብሏል።

መሪ ፕላኑን ለማስተግበርም የመዲናዋ ፕላን ኮሚሽን የበላይነት በመያዝ የልማትና ግንባታ ባለስልጣንና የማዕከላትና ኮሪደሮች ልማት ኮርፖሬሽን የተባሉ ቢሮዎች ይፈጠራሉ ነው ያሉት።

በተጨማሪም የአረንጓዴ ቦታዎችን በአግባቡ ለማስተዳደር ይቻል ዘንድ የተፋሰስና የአረንጓዴ ልማት ኤጀንሲ ቢሮ ይቋቋማል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መሪ ፕላኑ ሰፊና በቀላሉ ለመፈጸም የማይቻል በመሆኑ የማስፈጸም አቅም ታሳቢ ተደርጓል ወይ? የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም እቅዱ ሲተገበር ነዋሪዎች እንዳይፈናቀሉ ለማድረግ፣ ከተፈናቀሉም ለችግር ሳይጋለጡ እዛው አካባቢ ሰርተው መኖር የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸቱን የተመለከተ ጥያቄ አንስተዋል።

በመሪ ፕላኑ መሠረት የሚሰሩት ሕንጻዎች ረጃጅም በመሆናቸው የተፈጥሮ አደጋን መቋቋም ስለመቻላቸውና ሌሎች ስጋት አዘል ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል።

በጥቅሉ ነዋሪዎቹ የተዘጋጀው መሪ ፕላን ጥሩና ከተማዋን በተሻለ መልኩ ይለውጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው መሪ ፕላኑን ለማስፈጸም ከፍተኛ የአመራር ቁርጠኝነት መኖሩን ገልጸው ሕዝቡም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል። 

ፕላኑ ለከተማዋ ነዋሪዎች ተስፋ ሰጪ እንጂ የስጋት ምንጭ ባለመኆኑ ሕብረተሰቡ ጥርጣሬ ውስጥ መግባት የለበትም ብለዋል።

''የመዲናዋ ነዋሪዎች በባለቤት ስሜት ከመሪ ፕላኑ ውጪ የሚደረጉ ነገሮች ሲኖሩ የአስፈጻሚውን አካል በመከታተል የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርባቸዋል'' ብለዋል።

በረቂቅ ደረጃ ሳለ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ሲተገበር የቆየው መሪ ፕላን በቅርቡ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንደሚገባ ተመልክቷል።

መሪ ፕላኑ የአዲስ አበባን የመጪዎቹን 10 እና 25 ዓመታት እጣ ፈንታ የሚወስን ነው ተብሏል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 28/2009 የሞጆ - ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ምዕራፍ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት ማንጠፍ ስራ እየተከናወነ ነው።

የአዲስ አበባ - ሞያሌ - ናይሮቢ- ሞምባሳ የመንገድ ኮሪደር አካል የሆነው የሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ምዕራፍ አንድ የሞጆ - መቂ የ56 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር መንገድ ከተጀመረ ዓመት አልፎታል።

ፕሮጀክቱ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የመንገድ ልማት ዘርፍ መርሃ ግብር ውስጥ የተካተተ ነው፡፡

ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው ''ቻይና ሬል ዌይ  ሰቨንዝ ግሩፕ'' የተባለ የቻይና ዓለም አቀፍ ስራ ተቋራጭ ሲሆን፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ለመገንባት ካቀደው 10 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ውስጥ ዘጠኝ ነጥብ ዘጠኙን አከናውኗል።

የተቋራጩ ኃላፊ ኢንጅነር ሱን ጂአንጉኦ እንደገለጹት፤ የአስፋልት የማንጠፍ ስራው ሶስት ደረጃዎች አሉት። በእስካሁኑ ሂደት በመጀመሪያው ዙር አስፋልት የማንጠፋ ስራ ሶስት ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር ለማጠናቀቅ ተችሏል ፡፡

በመቀጠልም ሁለተኛውና የመጨረሻው አስፋልት ማንጠፍ ተግባር እንደሚከናወን ጠቁመው፤ በተያዘው ዓመት ይሄንኑ ስራ ከግማሽ በላይ ለማድረስ  እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ከሞጆ - አዋሳ የሚገነባው የፍጥነት መንገድ አዲስ አበባን ከደቡብና ከኦሮሚያ የሚያገናኝ በመሆኑ የከተሞችን የእርስ በርስ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው።

የመንገዱ መገንባት የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቃሜታ ከግምት በማስገባት በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በሦስት ዓመት ተኩል እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው የሞጆ - መቂ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ሦስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር የተመደበለት ሲሆን፤ ወጪው በኢትዮጵያ መንግስት በተመደበ በጀትና ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ብድር የሚሸፈን ይሆናል።

የሞጆ - ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ 208 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ታውቋል። ሞጆ - መቂ፣  መቂ - ዝዋይ፣ ዝዋይ - አርሲ ነገሌና አርሲ ነገሌ - ሐዋሳ በመባል በአራት ምዕራፎች ተከፍሎ ነው የሚከናወነው።

በመንገዱ ግንባታ ከ700 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል ተፈጥሯል።

መንገዱ በአንድ ጊዜ  በግራና በቀኝ አራት ተሽከርካሪዎችን ለማስተናገድ የሚችል ሆኖ ነው የሚገነባው።

የፕሮጀክቱ ምዕራፍ ሁለት መቂ - ዝዋይ የዲዛይን፤ የአፈር ጠረጋና ሌሎች ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

ቀሪዎቹ ሁለት ምዕራፎችን ስራ ለማስጀመር በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ የባለስልጣኑ መረጃ ያሳያል።

 

Published in ኢኮኖሚ

የካቲት 28/2009 የዘንድሮ የሴቶች ቀን የተለያዩ የልማት ንቅናቄዎችን በመፍጠር እየተከበረ መሆኑን  የኢፌዲሪ  የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡

ዘንድሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ106ኛ ጊዜ በኢትዮጲያም ለ41ኛ ጊዜ”የሴቶች የቁጠባ ባህል ማደግ ለህዳሴያችን መሰረት ነው “ በሚል የልማት ንቅናቄ ቀኑ ይከበራል፡፡

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን አስፋው ለኢዜአ እንደገለፁት ዘንድሮ በሃገር አቀፍ  ደረጃ በሚከበረው የሴቶች ቀን  ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን የሚያበቁበት ሁኔታ እንዲፈጠር  ከቀበሌ እስከ ወረዳ ባሉ አደረጃጀቶች የሴቶች የቁጠባ ባህል ከመሰረቱ ተጠናክሮ ለወደፊቱም እንዲቀጥል ንቅናቄ ተፈጥሯል፡፡

ሴቶች በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ በነበራቸው ሚና “በአንደኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን  2.82 ቢሊየን ብር መቆጠብ ችለዋል” ብለዋል፡፡

ሆኖም አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመድረሱ የቁጠባ ባህላቸውን ለማሳደግ  ንቅናቄው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

ሴቶችን በአረንጓዴ ልማትና የከተማ ውበት  ከከተማ እስከ ገጠር  ማሳተፍ የንቅናቄው አካል መሆኑን ገልፀው መስኩ ለሴቶች የስራ እድል የሚፈጥር በመሆኑ አሟጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡    

ያሳለፍነው እሁድ የካቲት 26/2009 ተካሂዶ በነበረው " ጊዜ የለንም እንሮጣለን፤ ለህዳሴ ግድባችን እንቆጥባለን!"በተሰኘው የሴቶች ሩጫም በሃገር አቀፍ ደረጃ 500 ሺህ ያህል ሴቶች እንደተሳተፉበትና  “ለስራም መሮጥ አለብን የተሻለ እድገት ያስፈልገናል” የሚል መልእክት እንደተላለፈበት ነው አቶ ሰለሞን የገለፁት፡፡

አሁን እየተካሄደ ባለው የቦንድ ሽያጭ ሳምንትም አባቶች ለሴት ልጆቻቸውና ለሚስቶቻቸው ወንድሞች ለእህቶቻቸው ያላቸውን አጋርነት የሚገልፁበት የቦንድ ግዢ በማከናወን “ያጋመስነውን የህዳሴ ግድብ በሁሉም የህብረተሰብ ተሳትፎ እናጠናቅ” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡   

በነገው እለትም ከ2500  በላይ ሴቶች በሚገኙበት መድረክ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጋር በሴቶች  ችግሮች ዙሪያ ውይይት ይደረጋል ብለዋል፡፡

በዚህም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ የሚቀመጥ ሲሆን ተደራጅተው በቁጠባ ውጤታማ የሆኑና የተበደሩትን በጊዜ የመለሱ ስኬታማ ሴቶች እንደሚሸለሙ ገልፀዋል፡፡

Published in ማህበራዊ
Tuesday, 07 March 2017 22:45

ሌላ ፕላኔት

Published in ቪዲዮ

አዲስ አበባ የካቲት 28/2009 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ  ተሾመ አቶ ጀማሉዲን ሙስጠፋ ዑማርን በሶማሊያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣንና ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር አድርገው ሾሙ።

የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ለአምባሳደሩ ሹመቱ የተሰጠው በዛሬው ዕለት ነው።

ለረጅም ዓመታት ሰላምና መረጋጋት ርቋት የቆየችው ሶማሊያ በቅርቡ ምርጫ ማካሄዷና ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ በፕሬዚዳንትነት መመረጣቸው ይታወሳል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 28/2009 እንስሳትን ከማርባት ጎን ለጎን በመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ ለማምረት በመሞከራቸው ድርቁ በተከሰተበት ወቅት ራሳቸውን ለመደጎም መቻላቸውን የቦረና እና ጉጂ ዞኖች አንዳንድ ነዋሪዎች ገለጹ።

የዞኖቹ አስተዳደሮችም የተከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት ለመቋቋም እንዲቻል በአካባቢው የሚገኘውን የውሃ ሃብት ለመጠቀም ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በተከሰተው ድርቅ 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎቿ ለእለት እርዳታ ተጋልጠው እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ መንግስት ባደረገው ሁሉን አቀፍ ርብርብ ችግሩን ለመቋቋም ተችሏል።

ዘንድሮ ቁጥሩ ወደ አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዝቅ ያለ ሲሆን፤ ከነዚህ ተረጂዎች መካከል ሁለት ሚሊዮኖቹ በኦሮሚያ ክልል የቦረና፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ባሌ እንዲሁም ምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ ውስጥ ይገኛሉ።

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ቅኝት ባደረገባቸው የቦረና ሁሉም ወረዳዎች፣ በጉጂ ደግሞ ካሉ ሰባት ወረዳዎች አምስቱ ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ እንስሳት በተለይም ከብቶች ለአደጋ እየተጋለጡ ናቸው።

በድምሩ ከ637 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎችም የምግብ፣ የመጠጥ ውሃና የተጨማሪ ምግብ እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።

ከዘላቂ መፍትሄ አኳያ አርብቶ አደሩ እንስሳት ከማርባት ጎን ለጎን በዞኖቹ ያሉ ወንዞችንና የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም የእርሻ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት።

ለዚህ ተግባር በጉጂ ዞን የባሮ እና ደዋ ወንዞች፣በአካባቢው ያለው የከርሰ ምድር ውሃ ጥቅም ላይ ውለዋል። በቦረና ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች በቀላሉ የሚወጡ የከርሰ ምድር ውሃ መኖሩም ተመልክቷል።

አሁን በተፈጠሩት እድሎች ተጠቅሞ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት የጀመሩ የዞኖቹ ነዋሪዎችም ራሳቸውን መደጎም መቻላቸውን ይናገራሉ።

የጉጂ ዞን ጎሮ ዶላ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አሚኖ አሊ እና በቦረና ዞን ሚዮ ወረዳ ነዋሪ አርብቶ አደር ራቾ ኮንሶሌና ዱብ ኮንሶሌ ተመሳሳይ ሀሳብ ያቀርባሉ።

አርብቶ አደሩ “ከብት ከማርባት ጎን ለጎን የኤክስቴንሽ ስራ በመከናወኑ ለውጥ እየመጣ ነው” የሚሉት የጉጂ ዞን አርብቶ አደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወርቁ ዱሎ ናቸው።

የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሊባን ኤሬሮ በበኩላቸው፤ ''በአካባቢው በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ድርቅ ለመቋቋም አርብቶ አደሩን ሌሎች ተጨማሪ የግብርና ስራ ላይ ማሰማራት ግድ ነው'' ብለዋል።

“የዞኑን የከርሰ ምድር ውሃ አውጥቶ መጠቀምና በክረምት ወቅት የሚፈሰውን የዝናብ ውሃ አቁሮ ማቆየት ድርቅ በሚመጣበት ጊዜ እንስሳቱን ለማጠጣት፣ ከዚያም አልፎ በመስኖ ለማምረት ይረዳን ነበር ግን ይህ ባለመሆኑ አሁን ለችግር እየተጋለጥን ነው” ሲሉም አክለዋል።

Published in አካባቢ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን