አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 06 March 2017

አዲስ አበባ የካቲት 27/2009 የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ቢኖረንም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በሚከናወኑ የልማት ተግባራት ላይ በጋራ እንሰራለን ሲሉ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ የሚውል የሴቶች ስድስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ትናንት አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም የክልል ከተሞች መካሄዱ ይታወቃል።

በውድድሩ ሲሳተፉ ያገኘናቸው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ እንዲሁም የአዲስ ትውልድ ፓርቲ የስራ ኃላፊዎች በአገሪቱ የፖለቲካ አስተሳሰብና የዓላማ ልዩነት ቢኖርም ለአገር ዕድገት በሚውሉ ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ በጋራ ለመስራት እንደማይደራደሩ ገልጸዋል።

የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የህግና ጥናት ምርምር ክፍል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወይሻ "አገሪቱን በሁሉም አቅጣጫ ከጫፍ እስከ ጫፍ ላነቃነቀውና አንድ ላደረገውን የህዳሴ ግድብ ድጋፍ በሚዘጋጀው ውድድር የተሳተፈው ህዝብ  ሊበረታታ ይገባል" ይላሉ።

ፓርቲው ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስም ቦንድ በመግዛትና ለገቢ ማሰባሰቢያ በሚዘጋጁ መድረኮች ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

''የፖለቲካ ፓርቲዎች በዓላማና በፖለቲካ አስተሳሰብ እንለያይ እንጂ ለአገር ዕድገት በሚያመጡ ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ በተለይም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ እስኪጠናቀቅ የበኩላችንን እንወጣለን'' ብለዋል።

"የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን የማይዋጥላቸውና ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ የውጪ ጠላቶችን በመመከትና በማጋለጥ ፓርቲው የራሱን ድርሻ ይወጣል" ብለዋል። 

የአዲስ ትውልድ የፖለቲካ ጉዳይ ዋና ኃላፊ አቶ አለማየሁ ደነቀ በበኩላቸው ድርጅቱ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለመደገፍ የህዳሴው ምክር ቤት አባል መሆኑን ጠቁመዋል።

ምክር ቤቱ በሚያዘጋጃቸው የገቢ ማሰባሰቢያ የድጋፍ  ውድድርም ላይም 45 አባላትን ማሳተፋቸውን ጠቅሰው ግድቡ ዘር፣ ኃይማኖት፣ ፖለቲካ ልዩነት ሳይለይ ሁሉንም በአንድነት ያስተሳሰረና የልማቱ ተካፋይ የሚያደረግ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ድርጅቱ አገራዊ በሆኑ ልማቶች ላይ አብሮ ለመስራትና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት በበኩሉ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ህዝቡ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስቧል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ግድቡ እንደሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች በውጭ እርዳታ የማይሰራ በመሆኑ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች እንዲቀጥሉ ይደረጋል ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ እንዲፋጠን የፋይንስ አቅሙ ወሳኝ በመሆኑ የግንባታው ሂደት እንዳይቀዛቀዝ ድጋፉን አጠናክረን መቀጠል ይገባል ነው ያሉት።

ለገቢ ማሰባሰቢያ በተዘጋጀው የሩጫ ውድድር የተካፈሉ ሴት ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለግድቡ በሚደረግ ተሳትፎ ላይ የሴቶች ድርሻም የላቀ መሆኑን አውስተዋል።

ግንባታው እስኪጠናቀቅም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት።

በአዲስ አበባ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመትና የሴቶች ቀንን በማስመልከት የተዘጋጀው የስድስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ ነበር የተካሄደው።

"ጊዜ የለንም እንሮጣለን! ለህዳሴ ግድባችን እንቆጥባለን" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባና በሁሉም የክልል ከተሞች መደረጉም ይታወቃል።

Published in ፖለቲካ

ነቀምቴ  የካቲት 27/2009 በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ ከተማ ከ560 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ  ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች  በመካሄድ ላይ ናቸው።

የከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ጆቴ ለኢዜአ እንደገለጹት የልማት ሥራው እየተከናወነ ያለው ከከተማው ማዘጋጃ ቤት፣ ከክልሉ መንግሥት እና ከፌዴራል መንግሥት በተመደበ 560 ሚሊዮን 666 ሺህ ብር ነው።

ግንባታቸው እየተካሄደ ካለው የመሠረተ ልማት ሥራዎች መካከል የ12 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድ ግንባታ፣ የሁለት ኪሎ ሜትር የኮብል ድንጋይ ንጣፍ፣ የሁለት ኪሎ ሜትር የመንገድ ዳር መብራት ዝርጋታ ይገኙበታል።

የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ፣ የመናክሪያ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የደምቢ ዶሎ አውሮፕላን ማረፊያን አስፋልት የማልበስ ሥራ ከሚከናወኑት የልማት ሥራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

በተጨማሪም የተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ግንባታ፣ የጥቃቅና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ማዕከላትና ሌሎችም እንደሚገኙበት አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል።

የመሠረተ ልማት ግንባታዎቹ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ ዓመት አካባቢ የተጀመሩና በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ የቆዩ መሆናቸው ተመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት የመሰረተ ልማት ሥራዎቹ አፈጻጸም ከ35 እስከ 91 በመቶ የደረሰ መሆኑን የገለጹት አቶ ፍቃዱ፣ አብዛኞቹ እስከ 2009 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ይበቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ቄለም ወለጋ ዞን በዞን ደረጃ የተሰየመውና የደምቢ ዶሎ ከተማም ወደመካከለኛ ከተማነት ያደገው በቅርብ መሆኑን አስታውሰው፣ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ሲበቁ ለከተማው ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ከእዚህም ነዋሪው ተጠቃሚ እንደሚሆን አስረድተዋል።

አቶ ፍቃዱ እንዳሉት፣ በከተማው እየተከናወነ ባለው የመንገድ ሥራ 45 ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው የድንጋይ ንጣፍ ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ።

ከእዚህ በተጨማሪ ግንባታው እየተካሄደ ያለው የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግንባታም በማህበር ለተደራጁ ከ400 በላይ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አቶ ፍቃዱ ጨምረዉ ገልጸዋል፡፡

በከተማው የቀበሌ 05 ነዋሪ ወጣት ጆሮጎ ኢተፋ በበኩሉ ፣ በከተማው እየተገነቡ ባሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረለት ተናግሯል።

የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን ማጠናቀቁንና በአሁኑ ወቅት እየተገነባ ባለው የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ በቀን ሠራተኝነት ተቀጥሮ በሚያገኘው ገንዘብ ራሱን በማስተዳደር ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል የቀበሌ 03  ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ቶላ ፣ በከተማው  በርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውንና እርሳቸውም ለልማቱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

"ለከተማው ከ127 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ሲበቃ አሁን ያለብንን የዉሃ ችግር በማቃለል ተጠቃሚ ያደርገናል" ሲሉ ገልጸዋል።

በከተማው በተለያዩ አቅጣጫዎች መንገዶች ከመሰራታቸው በፊት ክረምት በጭቃ ፤ በበጋ ወቅት በአቧራ ይቸገሩ እንደነበር የገለጹት ደግሞ የቀበሌ 07  ነዋሪ ወይዘሮ አዲሴ ወዬሣ ናቸው ።

በሕብረተሰቡ ተሳትፎ ጭምር ተሰርተው አገልግሎት መስጠት በጀመሩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ባጃጆች እንደልብ መመላለስ በመጀመራቸው  ገበያ በቀላሉ ደርሶ ለመምጣት መቻላቸውን አመልክተዋል።

በከተማው የመንገድ ዳርቻ እየተዘረጋ ያለዉው የመብራት መስመርም ሕብረተሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ወይዘሮ አዲሴ ገልጸዋል።

በደምቢ ዶሎ ከተማ ከ65 ሺህ ሰው በላይ የሚኖር ሲሆን ከተማዋ  ወደ መካከለኛ ከተማነት በቅርቡ  አድጓል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 27/2009  የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ በ40/60 የገነባቸውን 1 ሺህ 292 ቤቶች በመጪው ቅዳሜ እንደሚያስመርቅ አስታወቀ፡፡

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ በመዲናዋ የተገነቡ ከ39 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በይፋ እንደሚያስመርቅ ገልጿል፡፡

የኢንተርፕራይዙ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኃይሉ ቀንአ ዛሬ በተለያዩ ሳይቶች የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተጎበኙበት ወቅት እንዳሉት ኢንተርፕራይዙ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሳይቶች ከ39 ሺህ በላይ ቤቶችን በመገንባት ላይ ነው፡፡

ከአራት ቀናት በኋላ የሚመረቁት የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሰንጋተራና በክራውን ሳይቶች ያሉ ሲሆን ግንባታቸው 98 በመቶ መጠናቀቁን ነው የገለጹት፡፡

ኢንተርፕራይዙ የቤቶቹን ምርቃት ካካሔደ በኋላም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ርክክብ በማድረግ የዕጣ ማወጣትና ለዕድለኞች የማስተላለፍ ስራም እንደሚካሔድ ተናግረዋል፡፡

የአስተዳደሩ የቤቶች ልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀረጎት ዓለሙ በበኩላቸው በመጪው ቅዳሜ በይፋ የሚመረቁት ቤቶች በሐምሌ 2008 ዓም ለሕዝብ በዕጣ የተላለፉ ናቸው።

የሚመረቁት በ20/80 እና በ10 /90 የተገነቡ 39 ሺህ 260 ቤቶች ሲሆኑ ከነዚህ መካከል 1 ሺህ 111 የሚሆኑት ለልማት ተነሺዎች እንደሚሰጡም ነው የተናገሩት፡፡

''የልማት ተነሺዎች የማሕበራዊ ግንኙነት እንዳይቋረጥ ለማድረግም ቀድሞ አንድ አካባቢ የነበሩ ነዋሪዎች በጋራ እንዲኖሩ ይደረጋል'' ነው ያሉት፡፡

መንገድን ጨምሮ አብዛኛው የመሰረተ ልማትና የማሕበራዊ ተቋማት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑንና በአሁኑ ወቅትም የቤት ዕድለኞቹ ከአስተዳደሩ ቤታቸውን በመረከብ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

እነዚሁ ቤቶች በቦሌ አራብሳ፣ በኮየፈቼና በቂሊንጦ ሳይቶች የሚገኙ ሲሆን የትምህርት ቤት፣ የጤና ጣቢያ የቴክኒክና ሙያን ጨምሮ ሌሎች ማሕበራዊ አገልግሎቶች እንደሚኖራቸው ነው የተናገሩት፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 27/2009 የአፍሪካን ኢኮኖያዊ ዕድገት አካባቢያዊ ጉዳት በማያስከትል መንገድ ዕውን ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል ተባለ።

በአፍሪካ የመልከዓምድር አያያዝ ላይ የሚመክር የምክክር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

አፍሪካ በፍጥነት እያደገች ያለች አህጉር ብትሆንም አካባቢያዊ መመናመኗም በዚያው ልክ እየጨመረ እንደመጣ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ተገልጿል።

በመሆኑም አፍሪካ ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ የምታደርገው ግስጋሴ የመልከዓምድር ገፅታዋን የሚያወድም መሆን እንደሌለበት ነው የተነገረው።

አረንጓዴ፣ ንፁህና ፅዱ የአፍሪካ መልከዓምድርን በመፍጠር የአህጉሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስቀጠል እንደሚገባም የውይይት መድረኩ መክሯል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የአካባቢ ደህንነት መቃወስ ችግር መቅረፍ የአንድ ሰው ተግባር አይደለም ያሉት የአካባቢና ደን ሚኒስትሩ ዶክተር ገመዶ ዳሌ ናቸው።

በአፍሪካ የውኃ ችግር፣ የምግብና የብዝሃ ሕይወት መመናመን፣ ቀጣይነት ያለው የምግብ ዋስትና ችግሮች ጎልተው የሚስተዋሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በመሆኑም እነዚህ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ አለባቸው ነው ያሉት።

መንግስት፣ አርሶናአርብቶ አደሩ፣ ግለሰቦች፣ ማኅበራዊ ተቋማትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ በመረባረብ የአፍሪካ ግስጋሴ ተፈጥሮን የሚያመናምን እንዳይሆን መታደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከፌዴራል መንግስት እስከ ወረዳ ሁሉን አሳታፊና ተግባራዊ የሚደረግ የተቀናጀ የመልከዓ ምድር አያያዝ ትልቅ ዋጋ እንዳለውም አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢያዊ ማዕከል መረብ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ረታ በቀጠናው የሚስተዋሉትን የመልከዓ ምድር ገፅታ ለውጦች ለመቅረፍ ከበርካታ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።

ከመንግስት፣ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ ከሚሰሩ አካላትና አግባብነት ያለው የመሬት አጠቃቀምን ተግባራዊ ለማድረግ ከሚሰሩ ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህ አካላት ብቻ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ስለማይችሉ ሁሉም ባለድርሻ በሚያደርገው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አካባቢው ላይ ችግር መፍጠር እንደሌለበት ሊገነዘብ ይገባል ነው ያሉት።

አፍሪካን ስናሳድግ አካባቢያዊ መመናመን ሊኖር አይገባም ያሉት ዳይሬክተሩ ባለድርሻ አካላትን የተቀናጀ የመሬት አያያዝ ዕውን ይሆን ዘንድ  እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

Published in አካባቢ

ቦረና የካቲት 27/2009 በድርቁ ምክንያት አደጋ የተጋረጠባቸውን ከብቶች ሸጠው ለመጠቀም የገበያ ችግር እንዳጋጠማቸው የቦረና ዞን አርብቶ አደሮች ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል ድርቅ ከበረታባቸው አካባቢዎች መካከል በእንስሳት ሃብታቸው የሚታወቁት የቦረናና ጉጂ ዞኖች ይገኙበታል።

የኢዜአ ሪፖርተር በአካባቢው እንደተመለከተው፤ በድርቁ ምክንያት በተከሰተው የውሃና መኖ እጥረት ከብቶች ከመጎሳቆላቸውም በላይ የሞት አደጋ ተጋርጦባቸዋል።

በቦረና ዞን ሚዮ ወረዳ የህዲ ገበያ ላይ ያገኘነው አርብቶ አደር ቁሩጡ ኡኑሴ ወደ ገበያ ይዘዋቸው የሚወጡት ከብቶች የተጎሳቆሉና የከሱ በመሆናቸው ዋጋ ሊያወጡላቸው አልቻሉም።

''ከብቶች ቢከሱም ከዚህ በፊት ከ10 ሺ ብር በላይ የምንሸጠው ሰንጋ በሬ ዛሬ ዋጋው ወደ 4 ሺ ዝቅ ብሏል፤ ረከሰብኝ። ይዤ ብገባም የማበላቸው ነገር የለም” ብለዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በወር መንግስት ለከብቶች የሚቀርበው መኖ ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ብቻ ያገለግላል። ይህ በመሆኑ ቤት የቀሩትም እንሰሳት ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው።

ለከብቶቹ መኖ ማቅረብ ባይቻል እነኳን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸጥ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል።

ከብቶቹ በመክሳታቸው ነጋዴዎች የቦረናን ከብቶች እየመረጡ አለመሆኑን የሚገልጹት ደግሞ በከብት ንግድ ላይ የተሰማሩ የአካባቢው ነዋሪ አቶ ጌቱ ዋቆ ናቸው።

ከዚህም በፊት ከብቶቻቸውን የሚረከቧቸው የያአበሎ፣ አዳማና የአዲስ አበባ ነጋዴዎች መሆናቸውን አስታውሰው፤ አሁን የሚረከባቸው ባለመኖሩ እነርሱም ለመግዛት መቸገራቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም በአካባቢው “አሁን ባለው ሁኔታ የከብቶች ዋጋ በግማሽ ያህል ቀንሷል” ብለዋል።

የኦሮሚያ አርብቶ አደር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናስር ሁሴን እንደገለጹት፤ ችግሩ የተፈጠረው ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ተወጣጥቶ የተቋቋመው ኮሚቴ ስራውን ባለመስራቱ ነው።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የአርብቶ አደሩን የመሸጥ ፍላጎት መሰረት አድርጎ፣ የድርቅ ተጋላጮችን ለመጥቀምና የቦረናን ከብት ዘር ለማስቀጠል ሲባል ከኮሚሽኑ፣ ከንግድ ቢሮና ከጥቃቅንና አነስተኛ የተወጣጣ አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል።

ኮሚቴው ነጋዴዎች ወደ አካባቢው እንዲመጡ የማድረግና በራሱም በመግዛት ወደ ሌሎች አካባቢዎች በተለይ አምና በኢልኒኖ ተጎድተው የነበሩ የምዕራብ ሃረርጌ ወራዳዎች በመውሰድ የቦረና ከብት ዘሩ እንዲቀጥል የማድረግ ኃላፊነት እነደተሰጠው አመልክቷል።

ለዚህ የሚውል "ገንዘብም መንግስት በብድር መልክ መድቧል" ያሉት አቶ ናሲር፤ ሆኖም ግን “ኮሚቴው የሚፈለገውን ውጤት ባለማምጣቱ አርብቶ አደሩ እየተጎዳ ነው” ብለዋል።

የቦረና ዞን ከአራት ሚሊዮን በላይ የእንስሳት ሃብት ያለው ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በድርቁ ምክንያት የሞቱ ከብቶች ቁጥር በውል እንዳልታወቀ ተገልጿል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 27/2009 ኢትዮጵያ ለውጭ ባለኃብቶች የምታቀርበው የኢንቨስትመንት ማበረታቻና የሕግ ከለላ በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳሳደረባቸው ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ባለሃብቶች ተናገሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከደቡብ አፍሪካ የኢንቨስትመንት ልዑካን ቡድኖች ጋር በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን ማፍሰስ በሚችሉበት ሁኔታ ዙሪያ ምክክር አድርጓል።

በውይይቱ ወቅት ለባለሃብቶቹ በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭና በመንግሥት ለውጭ ባለሃብቶች ስለሚቀርቡ ሕጋዊ ከለላዎች ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ኢትዮጵያ ለውጭ ባለኃብቶች የምታቀርበው የኢንቨስትመንት ማበረታቻና ጥበቃ አስተማማኝ በመሆኑ በዘርፉ ለመሰማራት እንደሚፈልጉ ነው ባለሃብቶቹ የገለጹት። 

የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ላይ የተሰማሩት ሳንዲሌ ንድሎቩ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት የመሰማራት ፍላጎት ነበረን ብለዋል። 

ይህም የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ባለኃብቶች ወደ አገሪቱ እንዲመጡ ስለሚፈልግና በአገሪቱም በርካታ የገበያ ዕድል መኖሩን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

የአገሪቱ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥም በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ገበያ ለመጠቅም እንደሚያስችልና በመንግሥት የሚቀርበው ማበረታቻም ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ፍላጎት ያሳድራል ብለዋል።

በግብርና ምርቶች ላይ የተሰማራችው ኤልሳቤ ፍርይ በበኩሏ በዛሬው ዕለት በአገሪቱ በመስኩ ለመሰማራት የምንፈልጋቸውን ዋና ጉዳዮች በዝርዝር ገለጻ ሲደረግ ለማግኘት ችለናል ብለዋል። 

በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እንደሚያደርጉና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ስምምነት እንደሚፈጽሙ ገልጸው በአገሪቱ ምቹ ሁኔታ መኖሩን ነው የተናገሩት።   

''በእንስሳትና በእንስሳት ውጤቶች ላይ ለሚሰመራ የውጭ ባለሃብት የአገሪቱ በር ክፍት ነው'' ያሉት ደግሞ ሌላው በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሃብት አዴሌ ፋዉል ናቸው።

በአገሪቱ በዘርፉ አምርቶ ምርቶችን ወደ ጎረቤት አገራት ለመላክም ዕድል መኖሩንና የሚቀርቡት ማበረታቻዎችም በተመሳሳይ ለመሥራት ምቹ መደላድል እንደሚፈጥሩ ነው ያስረዱት። 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቢዝነስ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው የውጭ ባለሃብቶች ከአፍሪካ አገራትም ጭምር ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ይህንም ለማድረግ በተለይም በአገሪቱ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች የመለየትና የማስተዋወቅ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።  

''በደቡበ አፍሪካ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ባለኃብቶቹ ወደ ዚህ እንዲመጡ አድርጓል'' ያሉት ዳይሬክተሩ ይህም በቀጣይ እንደሚጠናከር ነው ያረጋገጡት።

በኢትዮጵያና በደቡበ አፍሪካ ባለኃብቶች መካከል የተደረገው ይህ ስብሰባ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን በውይይቱ ላይ ከ20 በላይ የደቡብ አፍሪካ ባለሃብቶች ተሳታፊ ነበሩ።

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር የካቲት 27/2009  የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመሩ ግንባር ቀደም ሆነው ለመውጣት እንደሚሰሩ ተናገሩ። 

የሊጉ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ያለፉትን ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ በባህር ዳር ከተማ እየመከሩ ነው።

የወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሊቀመንበር ወጣት ሙቀት ታረቀኝ እንደገለጸው ሊጉ የወጣቶች ቁርጠኛ የመታገያ መድረክ ሆኖ እንዲያገለግል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

በየደረጃው የሚገኙ የሊጉ አበላት ብአዴን በሚያስቀመጠው የልማት ፕሮግራምና አቅጣጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ መብትና ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ አቅማቸውን በስልጠና የመገንባት ሥራ መሰራቱን ተናግሯል።

ለእዚህም በግማሽ ዓመቱ ከ800 በላይ የሚሆኑ የሊጉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም በአዲሱ የወጣቶች የለውጥና የተጠቃሚነት ፓኬጅ ላይ ያተኮረ ስልጠና እንዲሰጣቸው መደረጉን አመልክቷል።

ይህም ወጣቶች ስለ ሥራና ህገ ወጥ ስደት ያላቸውን አመለካት ከማስቀየር ባለፈ ሁሉንም ከመንግስት እንዳይጠብቁና በአደረጃጀት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ወጣት ሙቀት እንዳለው፣ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ሁከትና ግርግር የሊጉ አባላትና አመራሮች የድርጅቱን መስመር ይዞ ከመታገል ይልቅ በአሉባልታና ውዥንብር የመነዳት አዝማሚያ ታይቶባቸዋል።

ይህን ለማስተካከል ብአዴን ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረትም በየደረጃው የሚገኘው ከ80ሺህ በላይ የወጣቶች ሊግ አመራሮች በሂስ ግለ ሂስ የታገዘ የተሃድሶ ንቅናቄ እንዲያካሂዱ መደረጉን ጠቁሟል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የሊጉ አመራሮችና አባላት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመሩ ግንባር ቀደም መሆን እንዳለባቸው የገለጸው ወጣቱ በለይ ተተኪ አመራር የማፍራት ሥራው ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል በትኩረት እንደሚሰራ አስረድቷል።

ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወጣት ታምራት ማለደ በበኩሉ ባለፉት ዓመታት በሥራ ዕድል፣ በትምህርት፣ በጤና በሌሎችም  ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ገልጿል።

ከወጣቱ ቁጥር አንጻር በቂ አለመሆኑ ወጣቱ ወደአልተገባ ተግባር እንዲያመራ ማድረጉን አስታውሶ፣ ወጣቱን ተጠቃሚ የማድረጉ ጥረት በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክቷል።

ከሰሜን ሸዋ ቀወት ወረዳ የብአዴን ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ውብአንች ተረፈ በበኩሏ እንደገለጸችው "ወጣት ተተኪ ኃይል በመሆኑ በተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ሥራ ማየት ይፈልጋል" ብላለች።

በመሆኑም የአካባቢውን ጸጋ በመለየትና የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ አመራር መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁማለች።

ለተግባራዊነቱም መንግስትና መሪ ድርጅቱ ለወጣቱ የሰጡት ትኩረት ስኬታማ እንዲሆንና በእዚህም ወጣቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ግንባር ቀደም ሆና ለመስራት መዘጋጀቷን ገልጻለች።

የብአዴን ወጣቶች ሊግ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሜቴ አባላት በዛሬው ዕለት የ15 ሺህ ብር ቦንድ የገዙ ሲሆን ይህም በግማሽ ዓመቱ መላ አባላቱ በቦንድ ግዥ አስተዋጽኦ ያደረጉትን 315 ሺህ ያደርሰዋል፡፡  

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 27/2009 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሃድሶ ንቅናቄ የደረሰበት ሁኔታ እና የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አፈፃፀም ሪፖርት መገምገም ጀመረ።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት በመግለጫው እንዳስታወቀው፤ ኮሚቴው ሪፖርቱን ከገመገመ በኋላ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ ጀምሯል።

ኮሚቴው ኢህአዴግ በይፋ የጀመረውን በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ከአመራር አባላቱና ከአባሉ አልፎ ወደ ሲቪል ሠራተኛውና ህዝቡ እንዲወርድ የተቀመጠው አቅጣጫ የታሰበለትን ዓላማና ግብ በትክክል ማሳካት አለማሳካቱን በዝርዝር ይገመግማል።

በመግለጫው እንደተጠቀሰው፤ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ወኪል የሆኑት ትምክህት፣ ጠባብነትና የኃይማኖት አክራሪነት እንዲሁም ሥልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል አመለካከትና ተግባር የድርጅቱና አገራዊ የህዳሴ ጉዞ የሚፈታተኑ አደጋዎች መሆናቸው ታውቋል።

የኮሚቴው አባላት እነዚህ ተግባራት ህዝብን ጨምሮ በየደረጃው ትግል እንዲደረግባቸው የተቀመጠው አቅጣጫ የደረሰበት ሁኔታ በዝርዝር እንደሚገመግሙ ነው የተመለከተው።

ዴሞክራሲያዊ የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን ይበልጥ ከማጠናከር አኳያም በሕጋዊ መንገድ ከተደራጁ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር እየተደረገ ያለው ውይይትም እንደሚገመገም ያመለከተው መግለጫው፤ በቀጣይ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ጠቁሟል።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በየደረጃው ህዝቡ ሲያነሳቸው የነበሩ እና "ፈጣን ምላሽ ያሻቸዋል" ተብለው የተለዩ ጉዳዮች አፈፃፀም በዝርዝር ይገመግማል።

ኮሚቴው በግምግማው የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የሁለተኛው ዓመት አጋማሽ አፈፃፀም ሪፖርትንም በዝርዝር እንደሚገመግም ተመልክቷል።

በዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ልማት ዘርፎች፣ የልማታዊ መልካም አስተዳደር እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውይይት ተደርጎበት አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ተገልጿል።

በተጨማሪም ኮሚቴው የሴቶችና የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በተመለከተም የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ እንቅስቃሴው አፈፃፀሞችን በዝርዝር በመፈተሽ ቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ በነገው ዕለትም ቀጥሎ እንደሚውል የጽሕፈት ቤቱ  መግለጫ ያመለክታል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 27/2009 የሰባት ወራቱ የጨርቃጨርቅና ስፌት ኢንዱስትሪ ዘርፍ አፈጻጸም ከዕቅድ በታች መሆኑን የጨርቃጨርቅና አልባሳት ልማት ማህበር አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት 100 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የታቀደ ቢሆንም የተገኘው 47 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ነው።

የአስተዳደርና የቴክኒክ አቅም ውስንነት፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መንጓተት፣ ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖርና የግብይት አቅም ውስንነት ለአፈጻጸሙ ማነስ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቦጋለ ፈለቀ ቀደም ሲል ምርቶችን በብዛት ወደ ውጪ በሚልኩ ኩባንያዎች ላይ በተያዘው ዓመት የታየው መቀዛቀዝ ዕቅዱ እንዳይሳካ አድርጓል ብለዋል።

የአገር ውስጥ ባለሃብቶች የግብዓትና የገበያ ችግርም ሌላው ምክንያት ነው።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋለው ችግርም ዕቅዱ እንዳይሳካ ካደረጉ መንስኤዎች መካከል ነው።

በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የገቡ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች በሚፈለገው ፍጥነት ማምረት አለመጀመራቸውም እንዲሁ።

በዘርፉ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች የወጪ ንግድ አፈጻጸሙ በሚፈለገው መጠን እንዳይሆን ማድረጉን የገለፁት አቶ ቦጋለ ችግሮቹን ለመፍታት መንግስት የተለያዩ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ማስቀመጡን አስታውቀዋል።

በኢንቨስትመንት ሂደት ላይ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች የመሰረተ ልማት የብድርና ከቀረጥ ነፃ ማበረታቻ ማድረግ፣ የቴክኒክና የማማከር አገልግሎት፣ የግብይት አቅም ግንባታ፣ የምርት ጥራትና ምርታማነት ማሻሻያ ትግበራ የሚጠቀሱ ናቸው።

የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅና አልባሳት ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ፋሲል ታደሰ በበኩላቸው የወጪ ንግዱ አትራፊ እንዲሆንና በሚፈለገው መጠን እንዲፈፀም መንግስትና የግል ባለሃብቱ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

የልማት ባንክ ወለድ መጨመር፣ የግብዓት እጥረትና የገበያ እጦት ባለፉት ሰባት ወራት ከዘርፉ የተገኘው ገቢ ከዕቅድ በታች እንዲሆን ያደረጉ ናቸው ሲሉም አክለዋል።

የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታትም መንግስት ከዘርፉ ተዋንያን ጋር ውይይት መጀመሩ ተስፋ ሰጪ መሆኑንም አመልክተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከጨርቃጨርቅና ስፌት ኢንዱስትሪ ምርቶች 271 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በሰባት ወራት መፈፀም የተቻለው 47 ሚሊዮን ዶላሩን ብቻ ነው።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 27/2009 በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል የኃይማኖት ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ።

የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ጥቃቱን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራሁ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአገሪቱ ለ41ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሴቶች ቀን (ማርች 8) ዛሬ በፓናል ውይይት አክብሯል።

የጉባኤው የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አባኃይለማርያም መለሰ "በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ማንኛውም አይነት ጥቃት ለመከላከል የኃይማኖት አባቶች በየቤተ-እምነቱ ምዕመኑን ማስተማር አለባቸው" ብለዋል።

ኅብተረሰቡም ሴቶች ከወንዶች እኩል መሆናቸውን አምኖ እንዲቀበልና ጥቃቱን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የቤተ-እምነቶች ሚና የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

የኃይማኖት አባቶች በተከታዮቻቸው ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር አባኃይለማርያም "ሴቶች የአገሪቱ ልማትና ሰላም አንድ አካል መሆናቸውን መስበክ አለባቸው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል በአገሪቱ ከሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ጋር ውይይት ያደርጋል ነው ያሉት።

በሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ጉዳይ ግንዛቤና ንቅናቄ ባለሙያ አቶ ምንያምር ይታይህ ጥቃቱን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል። ከሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው ጋር የሚሰሩትን ለአብነት በማስታወስ።

ወንዶች ለሴቶች ያላቸው አጋርነት ዝቅተኛ መሆን፣ ኅብረተሰቡ ለሴቶች እኩልነት የሰጠው አናሳ ግምት፣ የሴቶች ተሳተፎ ዝቅተኛነት የጥቃት መንስኤዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩም ይህን አመለካከት ለመቀየር ከኃይማኖት ተቋማት፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።

በአንዳንድ ክልሎች ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሴት ልጆች ግርዛት የነበረ ቢሆንም ከፍትህ አካላት፣ ከኃይማኖት ተቋማትና ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በትብብር የግንዛቤ ትምህርት በመስጠት ችግሩን መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት።

የሴት ልጅ ግርዛት ከ15 እስከ 49 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ከ65 ነጥብ 2 በመቶ በላይ እንደሆነ የ2008 ዓመተ ምህረት ጥናት ያሳያል።    

የሴቶች ቀን በዓለም ለ106ኛ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ41ኛ ጊዜ "የሴቶች የቁጠባ ባህል ማደግ ለህዳሴያችን መሰረት ነው" በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን