አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 05 March 2017

መቀሌ የካቲት 26/2009 የተገነባላቸው ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከተጨማሪ ጉዞና ድካም እየታደጋቸው መሆኑን በደቡባዊ ምስራቅ ትግራይ ዞን የሕንጣሎ ዋጅራት ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

ማህበረ ረድኤት ትግራይ ግሊመር ኦፍ ሆፕ ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በመተባበር በፀሀይ ሀይል የሚሰራ ፓምፕ የተገጠመለት ንፁህ የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክት ገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል።

በወረዳው የ’’ጎነቐ’’ ቀበሌ ነዋሪና የ10ኛ ክፍል ተማሪዋ ፍረውኒ በላይ እንደገለፀችው ውሀ ከምንጭ ለመቅዳት ራቅ ወዳለ ስፍራ ሌሊት ተነስታ መጓዝና ወረፋ መጠበቅ የዘወትር ስራዋ ነበር።

በዚህ ምክንያትም በተደጋጋሚ ከትምህርት ቤት ለመቅረት እንደምትገደድ ገልጻ አሁን በአካባቢዋ የቀረበው የውሃ አገልግሎት ሁሉንም ነገር በጊዜው ለማከናወን እንዳስቻላት ተናግራለች።

ውሀ የሞላ ጀሪካን ጀርባቸው ላይ ተሸክመው ከሁለት ሰዓት በላይ የእግር መንገድ በመጓዝ  የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን የውሃ ፍላጎት ያሟሉ እንደነበረ የተናገሩት ደግሞ የ60 አመቷ አዛውንት ወይዘሮ ሃሪፈያ አስገዶም ናቸው።

ቀደም ሲል ለውሃ ፍለጋ በጠዋት ሲወጡ ልጆቻቸው ቁርስ ሳይበሉ ወደ ትምህርት ቤት እንደሚሔዱ ገልጸው አሁን የውሃ አገልግሎት በአቅራቢያቸው በመኖሩ ችግራቸው ስለተፈታላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የአከባቢው ነዋሪ አርሶ አደር ገዛኢ ተስፋይ በበኩላቸው እንደገለጹት ተራራውን አቆራርጦ ወደ ሰፈሩበት መኖሪያ ቤታቸው ውሀ ይጓጓዛል የሚል እምነት ፈፅሞ አልነበራቸውም።

ተዳፋትና ዳገታማ በሆነው ሰፈራቸው በርቀት ከሚገኝ ወንዝ ውሃ ለመቅዳት ሲቸገሩ ዘመናትን እንዳሳለፉ በመግለጽ የቀረበላቸው የውሃ አገልግሎት አኗኗራቸውን እንዳቀለለላቸው ተናግረዋል።

የማህበረ ረድኤት ትግራይ ዋና ዳሬክተር አቶ ተክለወይኒ አሰፋ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በደብባዊ ምስራቅ ዞን የሕንጣሎ ዋጅራት ወረዳ የ’’ጎነቐ’’ ቀበሌንና  በአፋር ክልል የአብዓላ ወረዳ ተጎራባች ቀበሌዎች የሚገኙ አርብቶ አደሮችን በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

ከትላንት በስቲያ የተመረቀውን ይህን ፕሮጀክት ልዩ የሚያደርገው በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ  በፀሃይ ሃይል የሚሰራ የውሃ ፓምፕ የተገጠመለት ከመሆኑ ባለፈ ፈታኝ የሆነውን የአካባቢውን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ተቋቁሞ በመገንባቱ ነው።

ውሃውን ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ ስምንት ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የውሀ መስመር የተዘረጋለት ሲሆን ከ3ሺህ በላይ የአካባቢውን ነዋሪዎች ችግር ከማቃለሉም በተጨማሪ የአጎራባች የአፋር ወረዳ አርብቶ አደሮችንና እንስሳትንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

ለውሀ ፕሮጀክቱ ማሰሪያ በግሊመር ኦፍ ሆፕ በኩል ድጋፍ ያደረጉት አሜሪካዊት ሚሲስ ሊዛ  ሄረስ "በዚህ ስፍራ ውሀ ቀድቶ መመለስ በጣም አስቸጋሪ መሆኑ አይቸዋለሁ "ብለዋል፡፡

የሴት ልጅ እናት በመሆናቸውም ይሄንን የእናቶችን ችግር ማቃለል ለልጆቻቸውና ለቤተሰባቸው ተጨማሪ ጊዜ እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ማህበረ ረድኤት ትግራይ ከፈረንጆቹ 2010 ጀምሮ በሕንጣሎ ወጀራት ወረዳ 222 የተለያዩ የውሃ ፕሮጀክቶች በመገንባት በአስር ሺህዎች የሚቆጠር ህዝብ የንፁሀ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል።

 

Published in ማህበራዊ

ጅግጅጋ / መቀሌ የካቲት 26/2009 ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስድስተኛ ዓመትና ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በጅግጅጋ ከተማ የስድስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሄደ።

ግድቡ የልማትና የዕድገት መሰረት በመሆኑ እስኪጠናቀቅ ድረስ ደጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የመቀሌ ከተማ ሴቶች ገልጸዋል።

'' ጊዜ የለንም እንሮጣለን! ለሕዳሴ ግድባችን እንቆጥባለን '' በሚል መሪ ቃል ዛሬ ከጧቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ በጅግጅጋ ከተማ በተካሄደው የስድስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድደር በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና ወንዶች ተሳትፈዋል።

ውድድሩ በከተማው ከሰይድ መሀመድ አዳራሽ እስከ ፍትህ ቢሮ በደርሶ መልስ የተካሄደ ሲሆን፣ ወጣት ዝናሽ ትዕግስቱ አንደኛ በመውጣት የአምስት ሺህ ብር ቦንድ ተሸላሚ ሆናለች።

ወጣቷ ከውድድሩ በኋላ ''በሽልማት መልክ ያገኘሁትን አምስት ሺህ ብር ለግድቡ ግንባታ መቆጠብ በመቻሌ ድስተኛ ነኝ " ብላለች፡፡

በውድደሩ ሁለተኛ በመውጣት የሁለት ሺህ ብር ተሸላሚ የሆነችው ወጣት አስቴር ግርማ ናት።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንና የግድቡ ስድስተኛ ዓመት በጋራ መከበሩ ሴቶች ለግድቡ የሚያበረከቱትን አስተዋፅኦ እንዲያሳድጉ ዕድል ይሰጣል።እኔም በተሰጠኝ ሁለት ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት የራሴን አሻራ ማሳረፍ ችያለሁ" ስትል ተናግራለች።

የክልሉ ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ራህማ መሀሙድ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በሩጫ ውድድሩ ሠራተኞችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ለውድድሩ የተዘጋጀውን ቲሽርት በመግዛት ለግድቡ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር እድሪስ ኢስማኤል በዛሬው ዕለት ብቻ ሴቶች ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ ቦንድ መቆጠባቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደኃላፊዋ ገለጻ፣ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ስድስት ዓመታት የክልሉ ነዋሪዎች 300 ሚሊዮን ብር በስጦታና በቦንድ ግዥ ለግድቡ ድጋፍ አድርገዋል።

በተመሳሳይ ዜና በቀብሪደሀር፣ በደገህቡር፣ በቀብሪበያህ፣ ጎዴ፣ ቶጎጫሌ ከተሞች ከ16 ሺህ በላይ ሴቶችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳፉበት የሩጫ ውድድር  ተካሂዷል፡፡

ከዛሬ ጀምሮ በቀጣይ ሰባት ቀናት የፓናል ውይይቶች፣ የቦንድ ሳምንትና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።

በሌላ ዜና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የልማታችንና የዕድገታችን መሰረት በመሆኑ እስኪጠናቀቅ ድረስ ደጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የመቀሌ ከተማ ሴቶች ገልጸዋል።

ዛሬ በመቀሌ ከተማ ለግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመትና ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ከሁለት ሺህ በላይ ሴቶች የተሳተፉበት የስድስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሂዷል።

አትሌት ጎተይቶም ገብረስላሴና አምበሴ ቶሎሳ በክብር እንግድነት ተገኝተው ውድድሩን አስጀምረዋል።

በሩጫ ውድደሩ ህሪት አጽብሃ፣ አለምብርሃን ገብሩና ተፈታዊት ደሳለኝ ውድድሩን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ በመውጣት አጠናቀዋል።

በውደድሩ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ለወጡት ተሳታፊዎች ከሦስት ሺህ እስከ አንድ ሺህ ብር የቦንድ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ወጣት አለምብርሃን ገብሩ በሰጠችው አስተያየት "ግድቡ ለአገሪቱ ዕድገትና ልማት መሰረት በመሆኑ በቀጣይም ቦንድ በመግዛትና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ድጋፌን አጠናክሬ እቀጥላለሁ" ብላለች።

በውድድሩ የአራተኛ ደረጃን ያገኘችው ወጣት መቅደስ እሸቴ በበኩሏ፣ ሴቶች ታሪክ መስራት በጦርነት ብቻ እንዳልሆነ አውቀው ድህነትን ለማሸነፍ መጣር እንዳለባቸው ተናግራለች።

ሀገሪቱ የጀመረችውን የልማት እንቅስቃሴ በማፋጠን ግድቡ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ግድቡ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ የጀመረችውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጻለች።

ለአሸናፊዎቹ ሽልማቱን የሰጡት የትግራይ ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር የትምወርቅ ገብረመስቀል በበኩላቸው፣ ሴቶች በሁሉም ዘርፍ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ በቀጣይም አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

Published in ስፖርት

ጅማ/ነቀምቴ የካቲት 26/2009 በጅማ ከተማ ዛሬ በተካሄደው 17ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ጨዋታ  ጅማ አባቡና አዲስ አበባ ከተማ አቻውን አንድ ለዜሮ  በሆነ ውጤት አሸነፈ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ  የመላው ምስራቅ ወለጋ ዞን ዓመታዊ የልዩ ልዩ የስፖርት ውድድር ተጠናቋል፡፡

በጅማ ከተማ በተካሄደው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ጨዋታ ለጅማ አባቡና ብቸኛውን የማሸነፊያ ጎል በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ኪዳኔ አሰፋ ጨዋታው በተጀመረ በ21 ደቂቃ ላይ ማስቆጠር ችሏል፡፡

የጅማ አባቡና አሰልጣኝ ገበረመድህን ሃይሌ " ጨዋታውን በማጥቃት ጫና ፍጥረን ለመጫወት የሞከርን ቢሆንም ወደ ጎል ለመቀየር ያደረግነው ሙከራ ግን አስዳሳች አልነበርም " ብለዋል፡፡

ቀጣይ ሳምንት ልምድ ካላው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ሲጫወቱ ጎል የማግባት ክፍተቶቻቸውን በማስተካከለ ሶስት  ነጥብ ይዘው ለመውጣት እንደሚዘጋጁም ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አሰልጣኝ አስራት አባተ በበኩላቸው "ተመጣጣኝ ጨዋታ በሁለቱም በድኖች በኩል ታይቷል፡" ብለዋል፡፡

በመጀመሪያው ግማሽ በሰሩት ስህተት  ቢያንስ ነጥብ ተጋርተው መውጣት እንዳልቻሉ ተናግረው "  ቡድኔ በመከላከሉ ላይ ያሳየው ብቃት አስደስቶኛል "ብለዋል፡፡

ጨዋታው በዳኝነትም  ሆነ በደጋፍ አሰጣጥ በኩል የተዋጣ እና ስፖርተዊ ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ መካሄዱንም አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከየካቲት 19/2009 ዓ. ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የሰነበተዉ የምስራቅ ወለጋ ዞን የልዩ ልዩ የስፖርት ውድድርም ዛሬ ተጠናቋል፡፡

ወድድሩ በሁለቱም ጾታ እግር ኳስ፣ ቦሊቦል፣ አትሌቲክስ፣ ቼዝ፣ ዳርት በፓራ ኦለምፒክ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣እና ባድሜንቴን አካቶ   17 ወረዳዎችን የወከሉ 637 ስፖርተኞችን አስትፏል፡፡

አሸናፊ ወረዳዎችም የተዘጋጀላቸውን ዋንጫ ከዕለቱ የክብር እንግዳ የዞኑ  አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ከአቶ ያደታ ጭምዴሳ እጅ ተቀብለዋል፡፡

በቅርቡ ባሌ ሮቤ በሚካሄደዉ የመላው ኦሮሚያ የስፖርት ውድድር ላይ  ምሥራቅ ወለጋን ወክለው የሚሳተፉ  92 ስፖርተኞች ተመረጠዋል፡፡

Published in ስፖርት

ሰሜን ሸዋ የካቲት 26/2009 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የገቢ አቅማቸውን ያሳደጉ አርሶአደሮች የምርት ማሳደጊያ ግብዓትን በቀጥታ ክፍያ መግዛት መጀመራቸውን የዞኑ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡                  በጽህፈት ቤቱ የሰብልና ኤክስቴንሽን ቡድን መሪ አቶ ደረጄ ኤጀታ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ 13 ወረዳዎች የሚገኙ ከ175 ሺህ 500 የሚበልጡ አርሶአደሮች ገቢያቸው እያደገ መጥቷል።

በዚህም የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በቀጥታ ገንዘብ ከፍለው መረከብ መጀመራቸውን ነው የገለጹት።

አርሶአደሮቹ ከሦስት ዓመት በፊት በበልግ፣ በመኸርና በመስኖ ለሚያለሙት ሰብል የምርት ማሳደጊያ ግበዓት የሚያገኙት በብድር ከሚቀርብላቸው ነበር።

ከአንድ ዓመት በፊት ለምርት ግብዓት መግዣ ከዋለው 42 ሚሊዮን 572 ሺህ ብር ውስጥ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው አርሶአደሩ ያለብድር እጅ በእጅ የከፈለው መሆኑን ጠቅሰዋል።

አቶ ደረጄ እንዳሉት 22 ሺህ የሚሆኑ አርሶአደሮች ከነበረባቸው 29 ሚሊዮን ብር የቆየ የማዳበሪያ ተዘዋዋሪ ዕዳ ውስጥ ከታህሳስ 2ዐዐ9 ዓ.ም ጀምሮ 27 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን በመሰረታዊ ሕብረት ሥራ ማህበራት በኩል ለዩኒየኖች ገቢ አድርገዋል።

የዞኑ አርሶአደሮች የገቢ አቅማቸውን በማሳደግ የምርት ማሳደጊያ ግብዓት መግዛት የቻሉት ከመደበኛ እርሻ ጎን ለጎን የመስኖና የእንስሳት ልማትን በማስፋፋታቸው መሆኑን አቶ ደረጄ ተናግረዋል።

በ2ዐዐ8/ዐ9 የመኸር ምርት ዘመን 183 ሺህ ኩንታል ዩሪያ እና ዳፕ ማዳበሪያን ጨምሮ የባዮ ፈርትላይዘር ማዳበሪያም ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸው፣ ለቀጣይ የምርት ዘመን ተመሳሳይ መጠን ያለው ማዳበሪያ በቀጥታ ክፍያ ለማሰራጨት ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ መንግስትን ጨምሮ የቢፍቱ ሰላሌ ገበሬዎች የሕብረት ሥራ ዩኒየን እንዲሁም ሌሎች መሰረታዊ ማህበራት የግብአት አቅርቦቱን እያከናወኑ መሆናቸውን አቶ ደረጄ ተናግረዋል፡፡

ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ በተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያም ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህ ዓመትም 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶአደሩ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ እንዲውል እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ የቁንዴ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ሀብታሙ ታዬ በሰጡት አስተያየት፣ ምርትና ምርታማነታቸውን በየዓመቱ እያሳደጉ በመምጣታቸው ካለፈው ዓመት ወዲህ ማዳበሪያ በብድር ከመውሰድ መታቀባቸውን ገልጸዋል።

ማዳበሪያ ያለብድር መግዛታቸው ከዋጋ ጭማሪም ሆነ ከወለድ ክፍያ ነጻ እንዳደረጋቸው ጠቁመው፣ ሌሎች አርሶአደሮችም የሚያገኙትን ገንዘብ በመቆጠብና የሥራ ባህላቸውን በማሳደግ ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

መደበኛ የእርሻ ሥራቸውን ከእንስሳት እርባታ ጋር አጣምረው እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በግራር ጃርሶ ወረዳ የወርጡ ቀበሌ አርሶአደር  ብርሃኑ ሊቼ  ናቸው።

"የቁጠባ ባህል እያዳበርኩ ስለመጣሁ የምርት ማሳደጊያ ግበዓት ካለምንም ችግር እጅ በእጅ ከፍዬ መግዛት ችያለሁ" ብለዋል።

ከጥቂት ዓመት በፊት በብድር ማዳበሪያ ይገዙ እንደነበር አስታውሰው ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በተለያየ መንገድ ገቢያቸው እያደገ በመምጣቱ ግዢውን በቀጥታ እያከናወኑ መሆኑን ተናገረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ቦረና መጋቢት 26/2009 በአባ ገዳነት ቦረናን ለስምንት ዓመታት ሲያስተዳድሩ የቆዩት አባ ገዳ ጎዮጎባ ለ71ኛው አባ ገዳ ኩራ ጃርሶ ሥልጣናቸውን ሥርዓቱ በሚፈቅደው ባህልና ደንብ መሠረት አስተላለፉ።

የሥልጣን ርክክቡን በያቤሎ ከተማና በአሬሮ ወረዳ በተለያዩ ዝግጅቶች በመከናወን ላይ ይገኛል።

የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ህዝብ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች መከወኛ ሆኖ ለዘመናት ኖሯል።

ቦረናዎችም በገዳ ስርዓት ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው ዘመናትን አስቆጥረዋል።

የሥልጣን ርክክብ ሂደቱ ለስምንት ተከታታይ ቀናት የሚደረግ ሲሆን፤ ይህም በገዳ ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለውና የስርዓቱ ዲሞክራሲያዊነት መገለጫ ነው።

በዚህም መሠረት የዘንድሮው 71ኛው የቦረና አባገዳ የስልጣን ርክክብ በልዩ ልዩ ባህላዊ ስርዓቶች፣ በስፖርታዊ ውድድሮችና በፓናል ውይይት በመከበር ላይ ይገኛል።

የኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሊበን አሬሮ ስለሥርዓቱ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ የልዩ ልዩ ዝግጅቶቹ ዓላማ በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የገዳ ስርዓት እሴቶችን ምንነትና ፋይዳ ለማስተዋወቅ ነው። በተጨማሪም ተተኪው ትውልድ ስርዓቱን የበለጠ በማጠናከር የየድርሻውን እንዲወጣ ታስቦ የተደረገ ነው።   

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 26/2009 በአዲስ አበባ ከተማ በሥራ ጥራታቸውና ፍጥነታቸው የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ 77 ኢንተርፕራይዞች የመስሪያ ቦታ ተሰጣቸው።

ኢንተርፕራይዞቹ ቦታውን ሊያገኙ የቻሉት ከ1 ሺ 139 አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መካከል ስራቸውን የሚያከናውኑት በፍጥነትና በጥራት መሆኑ በአጣሪ ኮሚቴ ከተረጋገጠ በኋላ ነው።

የኢንተርፕራይዞቹ ባለቤቶች እንደገለጹት፤ በአፈጻጸም ብቃታቸው ተለይተው የመስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው መደረጉ በሙሉ አቅማቸው ስራቸውን ለማከናወን ያስችላቸዋል። በተጨማሪም ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ያግዛል።

የአዲስ አበባ ከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የመስሪያ ቦታዎች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ለኢንተርፕራይዞቹ የመስሪያ ቦታ ያስረከበው በተመጣጣኝ ክፍያ መሆኑ ታውቋል።

ኢንተርፕራይዞቹ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በብረታ ብረትና እንጨት ሥራ፣ በጨርቃጨርቅና ልብስ ሥራ እና በቆዳና የቆዳ ውጤቶች የስራ መስኮች የተሰማሩ ናቸው።

የሜቱኬ የጨርቃ ጨርቅና ልብስ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ማህሌት ተሰማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተቋማቸው እየሰራ ያለው በ280 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ባረፈ ሼድ ነው። በአሁኑ ወቅት ሥራቸው እየሰፋ በመምጣቱ  የቦታ እጥረት አጋጥሟቸዋል፤ ለማስፋፋትም ተቸግረዋል።

ኢንተርፕራይዙ ለ45 ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሩን ገልጸው፤ ኤጀንሲው 360 ካሬ ሜትር የሚሆን የመሥሪያ ቦታ ስለሰጣቸው ስራቸውን በሰፊው ለማከናወን መታቀዱን ነው የተናገሩት።

ኢንተርፕራይዙ በሚያስፋፋበት ወቅት ተጨማሪ 55 ወጣቶችን ለመቅጠር እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

የደብረ ወርቅ ቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ አክሊሉ ወርቁ  እንደተናገሩት፤  ተቋማቸው በበለጠ ጥራትና ፍጥነት ስራውን ለማከናወን  ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያስፈልገዋል። ለቴክኖሎጂው ተስማሚ የሆነ የመስሪያ ቦታ ለማግኘትም ለዓመታት ተቸግረው ቆይተዋል።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በጥራት፣ በፍጥነትና በብዛት ለማምረት በቂ የሰው ሃይል እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ አሁን በተሰጣቸው ቦታ “ለእኛም እንጠቀማለን፤ ለወጣቶች የሥራ እድል እንፈጥራለን።  በጥራትና በፍጥነት እያመረትን የአገሪቷን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ እንሰራለን” ብለዋል።

የቢዜድ ጨርቃ ጨርቅና ልብስ ሥራ ኢንተርፕራይዝ አባል አቶ ዘለቀ ያደሳ እንደሚሉት፤ ተቋማቸው እስከአሁን በቂ የመስሪያ ቦታ ባለማግኘቱ አቅሙን አሟጦ ለመጠቀም ሲቸገር ቆይቷል።

የከተማዋ የመስሪያ ቦታዎች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር  አቶ ግዴና ኃይለየሱስ  እንደገለጹት ደግሞ፤  በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በአሰራራቸው የተሻሉ ኢንተርፕራይዞችን የሚለይ ገለልተኛ ኮሚቴ ተቋቁሞ የማጣራት ሥራ ካከናወነ በኋላ የመስሪያ ቦታ እንዲያገኙ ተደርጓል።

የሥራቸውን ጥራትና ፍጥነት  ከግምት በማስገባት ቦታው መሰጠቱን ያብራሩት አቶ ግዴና፤  ለሌሎች ኢንተርፕራይዞች አርአያ እንዲሆኑና ከዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች የሚመረቁትን ተማሪዎች ሥራ እንደሚያሲዙና  መንግሥትን የማገዝ ተግባር እንደሚያከናውኑ ታሳቢ መደረጉን ጠቁመዋል።

በቀጣይ ለሌሎች ግንባር ቀደም ኢንተርፕራይዞች የሥራ ቦታ የሚሆኑ ግንባታዎችን ለማከናወን የቦታ መረጣ እንደተጠናቀቀ ታውቋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ  የካቲት 26/2009  ህወሓት ከሌሎች ብሔራዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን ባደረገው ትግል የተገኘውን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የተመሰረተበት 42ኛው ዓመት  በዓል በአዳማ ከተማ በድምቀት ተከብሯል ።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ነጋ በርሔ በበዓሉ ላይ እንደገለጹት ደርግን በመገርሰስ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲባል ከ60 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶችን የህይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል ።

ከድርግ ውድቀት በኋላ የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክሩና ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡ በርካታ አንፀባራቂ ውጤቶች መመዝገበባቸውንም ተናግረዋል፡፡

" አሁንም ህዝቡ ከድህነት እንዳልወጣ ፣ ዴሞክራሲው ገና በጅምር ያለና የመልካም አስተዳደር ችግር ያልተፈታ በመሆኑ ትግሉ  መቀጠል አለበት "ብለዋል ።

ህወሓት ከሌሎች ብሔራዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን ባደረገው ትግል የተገኘውን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል፡፡ 

በተለይ ወጣቱ  የሰማእታትን አደራ ተቀብሎ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እስኪረጋገጥ ድረስ በፀረ ድህነት ፣ በትምክህት ፣ በጠባብነትና በፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ውስጥ ተሳትፎውን  አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል ።

የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ አባልና የአዳማ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ በበኩላቸው ህወሓት/ ኢህአዴግ ከሌሎች ብሔራዊ ድርጅቶች ጋር ህብረት በመፍጠር  ባካሄደው ትግል በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤቶች መመዝገቡን ተናግረዋል።

ሆኖም በመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት በተፈለገው ፍጥነት መጓዝ እንዳልተቻለ ጠቁመው የተካሔደው ጥልቅ ተሃድሶ በፅናት በማስቀጠል የህዝቡን እርካታ ለማረጋገጥ ትግሉን በአንድናት ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

"ለህዝቡ ጥያቄ ተገቢና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በአዳማ ከተማ ሰፊ የልማት ስራ ተጀምሯል" ያሉት ከንቲባዋ በዚህ ላይ በከተማዋ የሚኖሩ ህዝቦች ፣ የድርጅት አባላትና ደጋፊዎች በአንድነት መንፈስ ተሳትፏቸውን እንዲቀጥሉበት ጥሪ አቅርበዋል።

በበዓሉ ላይ ህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ በንባብ የቀረበ ሲሆን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችም አጋርነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ተወላጆች ፣ የብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች ፣ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች በተገኙበት በዓሉ በድምቀት ሲከበር ለትግሉ ሰማእታት የህሊና ፀሎትና የሻማ ማብራት ስነስርዓት ተካሄዷል፡፡

Published in ፖለቲካ

ጋምቤላ የካቲት 26/2009 በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ይዞታ ውስጥ ድንብር ዘለል አርብቶ አደሮች የቤት እንስሳትን ይዘው በመግባታቸው ጉዳት እያስከተሉ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አሰታወቀ።

አርብቶ አደሮቹ በፓርኩ መጠለያ እያደረሱት ካለው ጉዳት በተጨማሪ የፀጥታ ስጋትም እየሆኑ በመምጣታቸው ወደ መጡበት የመመለስ ሥራ መጀመሩን የክልሉ ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ገልጿል።

የፓረኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋልዋክ ጋርኮት ለኢዜአ እንደገለጹት ድንብር ዘለል አርብቶ አደሮች በርካታ የቀንድ ከብቶቻቸውን በመያዝ ወደ ፓርኩ በመግባት በእንስሳት መጠለያው ላይ  ከፍተናኛ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ።

ፓርኩ ሰፊ የቆዳ ስፋትና ውስን የጥበቃ ኃይል ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አርብቶ አደሮቹ እያደረሱት ያለውን ችግር በጽፈት ቤቱ አቅም ብቻ ማቃለል አለመቻሉንም ገልጸዋል።

ብሔራዊ ፓርኩ በተደጋጋሚ ጉዳት ባይደትርስበት ኖሮ በስፋትም ሆነ በብዝሃ ህይወት ሀብቱ በሀገሪቱ ከሚገኙ ፓርኮች ሁሉ የተሻለ እንደሆነም አቶ ጋልዋክ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በፓርኩ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ላይም በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የሚፈለገውን ያህል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የክልሉ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር አቶ ፒተር ጋርኮት በበኩላቸው ድንበር ዘለል አርብቶ አደሮች በአካባቢው ከፍተኛ የግጦሽ ችግር ከመፍጠራቸውም ባለፈ ድንበር ዘለል በሽታ ሊያመጡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የክልሉ ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት እንደገለጹት ድንበር ዘለል አርብቶ አደሮች በፓርኩ መጠለያ ላይ እያደረሱት ካለው ጉዳት በተጨማሪ የአካባቢውን አርብቶ አደሮች በግጦሽ መሬት እየተሻሙ ስለሆነ ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ተናግረዋል።

በየጊዜው የሚከሰተውን መሰል ችግር ለመከላከል ከራሳቸው የጎሳ መሪዎች ጋር ውይይት በመደረጉ በአሁኑ ወቅት ወደ መጡበት አካባቢ የመመለስ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

ድንበር ዘለል አርብቶ አደሮቹ ከሱዳን ደማዚን ከሚባለው አካባቢ እንደመጡ የታወቀ ሲሆን ከ500 ሺህ በላይ የሚገመቱ የቀንድ ከብቶችን ይዘው ፓርኩን ጨምሮ በአኝዋሃና ኑዌር ዞኖች እንደገቡ ከክልሉ ጸጥታ አሰተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in አካባቢ

ደብረ ማርቆስ የካቲት 26/2009 አቶ ገዳሙ ጥበቡ በምስራቅ ጎጃም ዞን ጎዛምን ወረዳ የቸር ተከል ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ቀደም ሲል ብርሀን ለማግኘት ናፍጣና እንጨት ይጠቀሙ እንደነበር ይገልጻሉ።

ይህም ለከፍተኛ ወጪ ዳርጓቸው እንደነበረና ከናፍጣውና ከእንጨቱ የሚወጣው ጭስ በእርሳቸውና በቤተሰባቸው ዓይንና የመተንፈሻ አካላት  የጤና ችግር ሲያስከትል መቆየቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት  ከ18ሺሀ ብር በላይ በማወጣት አሥር አምፖል የማብራት አቅም ያለው በፀሐይ ኃይል የሚሰራ ቴክኖሎጅ እየተጠቀሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህን አማራጭ የኃይል ቴክኖሎጂ መጠቀም ከጀመሩ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ቀደም ሲል ብርሃን ለማግኘት ለናፍጣና እንጨት ያወጡት የነበረው ከፍተኛ ወጪ ቀርቶላቸዋል።

"ከዚህ በተጨማሪ የእጅ ባትሪን እና  የሞባይል ባትሪ ለማስሞላት በየሳምንቱ ወደ ከተማ  በመመላለስ አጠፋው የነበረውን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ለልማት ሥራ እንዳውለው አስችሎኛል" ብለዋል።

የእርሳቸውና የቤተሰባቸው ጤናም እየተሻሻለ መምጣቱን ነው የገለጹት።

የደብረማርቆስ ዙሪያ ወረዳ የብራጌ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አስራደ ያረጋል ከመንግስት በተደረገላቸው ድጋፍ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ በመገንባት የኃይል ቴክኖሎጅ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ በግንባታው ወቅት ከፍተኛ ወጪ እንደማይጠይቅ ገልጸው የከብት እዳሪ በመጠቀም ብቻ መብራትና መግብን ለማብሰል የሚያስችል ኃይል ማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል

"ቀደም ሲል ማታ ማታ በቤት ውስጥ ብርሀን ለማግኘት ስንል ነጭ ጋዝ እንጠቀማለን በእዚህም ቤቱ በጭስ ስለሚታፈን ልጆቼ ለማጥናት ይቸገሩ ነበር" ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆናንቸው ወጪን በመቆጠብና የቤተሰባቸውን ጤና ከመጠበቅ ባሻገር ከባዮ ጋዝ የሚወጣውን ተረፈ ምርት ለመሬት ማዳበሪያነት በመጠቀም  ምርታማናታቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጎዛምን ወረዳ የዳሊጋው ዮሃንስ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ የልፍዋጋሽ ምህረት የማገዶ ቀጣቢ ምድጃዎችን መጠቀም ከጀመሩ አምስት ዓመት አልፏቸዋል።

ቀደም ሲል የእንጨት ማገዶን ምግብ ለማብሰል ስለሚጠቀሙ በጭስና በእሳቱ ሙቀት ምክንያት በየጊዜው ጤናቸው ሲታወክ መቆየቱን ገልጸዋል።

የእንጨት ማገዶ ለማምጣት ከአካባያቸው ርቀው በሚሄዱበት ጊዜም በሸክም ምክንያት ወገባቸው ለጉዳት ተዳርጎ እንደነበር ያስታውሉ።

"ማገዶ ቆጣቢ ምድጃን  መጠቀም ከጀመርኩ ወዲህ ይህ ሁሉ ቀርቷል" የሚሉት ወይዘሮ የልፍዋጋሽ፣ በአሁኑ ወቅት ጤንነታቸው መስተካከሉንና የማገዶ ወጪያቸው መቀነሱንም ተናግረዋል።

በማሳቸው ላይ ያለውን ዛፍና በአካባቢያቸው የሚገኘውን ደን በየጊዜው በመቁረጥ ለአደጋ የሚጋለጥበት ሁኔታም መቅረቱን ነው የገለጹት።

"ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ መጠቀም ከጀመርኩ ወዲህ በትንሽ ማገዶ ብዙ ምግብ ማብሰል ችያለሁ" ብለዋል።

በዞኑ የውሃ፣ የማዕድንና ኢነርጂ ሃብት መምሪያ የውሃ ሀብት ተቋማት አስተዳደር ግባት አቅርቦት ባለሙያ አቶ መግባር መንግስት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ የዞኑ ማህበረሰብ በአዳዲስ አማራጭ የኃይል ምንጮች የመጠቀም ባህሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከ160 ሺህ በላይ የተለያዩ አማራጭ የኃይል ምንጭ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ በተከናወኑ ተግባራት በግማሽ ዓመቱ ብቻ ከ90ሺህ በላይ የሚሆነውን ማካነወን እንደተቻለ ተናግረዋል።

አቶ መግባር ለሕብረተሰቡ ከተሰራጩ የኃይል አማራጮች ውስጥ 33ሺህ በፀሐይ ኃይል፣ 50 በባዮጋዝ የሚሰሩ ሲሆን ቀሪዎቹ የተለያዩ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ መሆናቸውን አመልክተዋል።

እንደባለሙያው ገለጻ፣ ያለፉት ስድስት ወራት አፈጻጸምም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ17 በመቶ በላይ ብልጫ አለው።

አማራጭ የኃይል ምንጮች ያላቸውን ጠቀሜታ ማህበረሰቡ እየተገነዘበ መምጣቱ ለታየው ብልጫ ምክንያት መሆኑ ተመልክቷል።

በዞኑ ባላፈው ዓመት 140 ሺህ የተለያዩ የኃይል አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶአደሩ ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ ተመልክቷል።

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ ባህርዳር ነገሌ የካቲት 26/2009 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት ስድሰተኛ ዓመትና አለም አቀፍ የሴቶች ቀን  ምክንያት በማድረግ በ33 የክልል  ከተሞች ዛሬ የሩጫ ውድድር ተካሄደ፡፡

ውድድሩ የተካሄደው በደቡብ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል ሀዋሳን ጨምሮ 31 ከተሞች እንዲሁም  በአማራ ባህርዳርና በኦሮሚያ ደግሞ ነገሌ ከተሞች ነው፡፡

በሃዋሳ ከተማ በተካሄደው ውድድር ላይ የክልሉ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ጌታቸው እንደገለጹት በክልሉ 31 ከተሞች በተካሄደው የሩጫ ውድድር 350ሺህ ያህል  ሴቶችና ወንዶች ተሳትፈዋል፡፡

የክልሉ ሴቶች በህዳሴው ግድብ ግንባታ ተሳትፏቸው እያደገ መሆኑንና በአደረጃጀቶቻቸው አማካይነት ቦንድ በመግዛት ድጋፋቸው አጠናክረዋል፡፡

የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን በበኩላቸው የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ የተደረገው ሩጫ የሴቶችን የቁጠባ ባህል በማሳደግ ለህዳሴ ግድቡ ተሳትፏቸውን የሚያሳዩበት ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት ስድሰተኛ ዓመትና አለም አቀፍ የሴቶች ቀን  ምክንያት በማድረግ  ከሚከናወነው የቦንድ ግዥ  140 ሚሊየን ብር በሴቶች ቁጠባ ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ቴዌድሮስ ገቢባ በከተማው  በሃምሳ አምስት ቡድኖች የተደራጁ ሴቶች ለከተማዋ እድገት አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሩጫ ውድድሩ ከተሳተፉ ሴቶች የሀዋሳ ነዋሪዎች መካከል  ወይዘሮ ታዬች አረጋ በግል 7ሺ ብር መቆጠባቸውን ተናግረው በማህበር ተደራጅተው የቆጠቡት  70ሺ መድረሱንና ለግድቡ ግንባታም ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሀዋሳው የሩጫ ውደድር ላየ ተዋቂዎቹ አትሌቶች ብርሃኔ አደሬና ገዛኸኝ አበራን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ ባለስልጣናት የተገኙ ሲሆን በውድድሩ ለተሳተፉ የሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል፡፡

በአማራ ክልል ደግሞ ባህር ዳር ከተማ  35ሺህ ያህል ህዝብ የተሳተፈበት የስድስት ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር ተካሄዷል፡፡

" ጊዜ የለንም እንሮጣለን፤ ለህዳሴ ግድባችን እንቆጥባለን!" በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የሩጫ ውድድር  ሃብቴ ፈጠነ፣ ደሳለኝ ምናለና ሃብታሙ ገበየሁ ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል።

በሴቶች ውድድርም  ሃይማኖት ገደፋው፣ መሰረት ሙጨና ወርቅነሽ ስንሻው እንዲሁም በዊልቸር ደግሞ  ድንቅነሽ አውደው፣ እመቤት ተናኘና ዳሳሽ በሪሁን  በቅደም ተከተል ማሸነፍ ችለዋል፤ ሁሉም አሸናፊዎች እንደየደረጃቸው የቦንድና የምስክር ወረቀት ተሸልመዋል፡፡

በሁለቱም ጾታ አንደኛ ለወጡት ተወዳዳደሪዎች የህዳሴው ግድብ ማስታወሻ ዋንጫ ከአትሌት መሰለች መልካሙና አትሌት ሙስነት ገረመው እጅ ተረክበዋል።

ከባህርዳር ከተማ አትሌቲክስ ፕሮጀክት በመምጣት አንደኛ የወጣችው ሃይማኖት ገደፋው በሰጠችው አስተያየት " ውድድሩ ሁሉም ህዝብ የተሳተፈበት ቢሆንም ለህዳሴው ግድብም የበኩሌን አስተዋጽኦ እንዳደረኩ እቆጥረዋለሁ" ብላለች።

በግሉ ተወዳድሮ አንደኛ የወጣው ሃብቴ ፈጠነ በበኩሉ ለውድድሩ በግሉ በቂ ዝግጅት በማድረግ ለማሸነፍ መብቃቱን ተናግሯል።

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አየነው በላይ እንደገለጹት የህዳሴውን ግድብ ምስረታ ምክንያት በማድረግ ህዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ በመቀጠል ያሳየው ተነሳሽነት የሚበረታታ ነው።

በተመሳሳይም በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን  ነገሌ ቦረና ከተማ  በተካሄደው  የስምንት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ላይ  750 የሚደርሱ ሴቶችና ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡

የዞኑ  ሴቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ ወይዘሪት ረሂማ መሀመድ  በዚሁ ወቅት ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በውድድሩ አንደኛ በመውጣት ያሸነፈው ወጣት ብርሀኑ ሙላት በሰጠው አስተያየት  በህዳሴው ግድብ ግንባታ የድጋፍ ጥሪ ተቀብሎ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተወድድሮ በማሸነፉ  መደሰቱን ተናግሯል፡፡

ከኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ ጋር የምትኖረውና በሴቶች ወድድር  ሁለተኛ በመውጣት ተሸላሚ የሆነችው ወይዘሪት ፋጤ መሀመድ በበኩሏ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ውስጥ  ሁሉም ዜጋ አሻራውን የማሳረፍ   የውዴታ ግዴታ አለበት ብላለች፡፡  

በውድድሩ በማሸነፍ በሁለቱም ጾታ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ለወጡ  ተወዳዳሪዎች  የቦንድ ፣ የወርቅ ፣የብርና የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

Published in ስፖርት
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን