አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 04 March 2017

ኡጋንዳ ካምፓላ የካቲት 25/2009 "አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በኡጋንዳ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከፕሬዚዳንት ዮዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ከሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር አካባቢያዊና አህጉራዊ ጉዳዮችም በመሪዎቹ ውይይት ተዳስሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከውይይቱ በኋላ እንደገለጹት፤ በሶማሊያ ሰላም ለማስፈን የተደረገው ጥረት ውጤት አስመዝግቧል።

ለዚህም በጥምረት የተደረገውን ጥረት አድንቀው፤ ኡጋንዳም ለከፈለችው መስዋዕትነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያና ኡጋንዳ የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በአገሪቷ ማሰማራታቸው የሚታወቅ ነው።

“ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት የተሰራው ስራ እና የተገኘው ውጤት አፍሪካ ችግሮቿን በራሷ አቅም ለመፍታት የምታደርገው ጥረት ማሳያ ነው” ብለዋል።

በተመሳሳይ የደቡብ ሱዳንን ሰላም ለመመለስ በኢጋድ በኩል እየተከናወነ ያለው ተግባር ውጤታማ እስኪሆን ድረስ እንደሚቀጥል ነው የጠቆሙት።

“በጥምረት ለመስራት፣ ለምጣኔ ሃብታዊ ብልጽግና እና ለንግድ ልውውጥ ሰላም ያስፈልገናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ በቀጣይም አህጉሪቷ ያሉባትን በርካታ ችግሮች በራሷ ልጆች የተባበረ ክንድ መፍታት እንደሚገባት ነው አጽንኦት የሰጡት።

የዓባይ ውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በተመለከተም “ሃብቱ የጋራ እንደመሆኑ ለጋራ ተጠቃሚነት በትብብር መስራት ይገባል” ብለዋል።

በኢትዮጵያና ኡጋንዳ መካከል የንግድ መግባባት መደረጉም ከእነርሱ አልፎ የአካባቢውን አገራትም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በአገሪቷ ስላደረጉት ጉብኝት አመስግነው፤ የሁለቱ መሪዎች ቆይታ ውጤታማ እንደነበር ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ቀዳማይ እመቤት ሮማን ተስፋዬና የጉብኝቱ ተሳታፊ ሚኒስትሮች በመካከለኛው የአገሪቷ አካባቢ ኪሶዚ የሚገኘውን የፕሬዚዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ የከብት እርባታ ጎብኝተዋል።

በኡጋንዳ ስለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበልና ሽኝት ያመሰገኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ የሶስት ቀናት ጉብኝታቸውን አጠናቀው ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 25/2009 አፍሪካውያን የሚያጋጥማቸውን ፈተናዎች አልፈው ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር በጽናትና በአንድነት መታገልን ከአድዋ ድል መማር እንደሚገባቸው የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ታቦ ኢምቤኪ ገለጹ።

121ኛውን የአድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ከአድዋ ድል ጋር በተያያዘ ድሉ ለአፍሪካ ነጻነት የነበረው ሚና፣ አፍሪካውያን ከድሉ ምን ሊማሩ ይችላሉ? የአፍሪካን ህዳሴ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን ለታቦ ኢምቤኪ ሰንዝረዋል።

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኢምቤኪ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያውያን ቅኝ ግዛት ለማስፋፋት ባህር አቋርጦ በመጣው የጣልያን ጦር ላይ የተቀዳጁት ድል የራሳቸው ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንም ጭምር መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት።

''ድሉ በቅኝ ግዛትና ኢምፔሪያሊዝም ቀምበር ስር ለነበሩ የአፍሪካ አገሮች የማንቂያ ደውል ነበር'' ያሉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት፤ ድሉ የአፍሪካውያንን በራስ የመተማመን መንፈስ የገነባ እንደነበር አስታውሰዋል።  

''ለዚህም ነው አፍሪካና ኢትዮጵያ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ተደርገው የሚወሰዱት” ብለዋል።  

አፍሪካ በአዝጋሚ የለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኗን የተገሩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኢምቤኪ፤ “የአህጉሪቷን ህዳሴ በማረጋገጥና የሚጠበቀውን ለውጥ በማምጣት አፍሪካውያን ከአድዋ ታሪካዊ ድል አንድነትን መማር ይገባቸዋል” ብለዋል።

ድህነት አሁንም የአፍሪካውያን ፈተና መሆኑን ገልጸው፤ ሥር የሰደደ ሙስና አህጉሪቷ ለውጥ እንዳታመጣ ተብትበው ከያዙዋት ችግሮች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን አውስተዋል። 

“የአድዋ ድል በዚህ በኩል የዓላማ ጽናት የሚያስተምር በመሆኑ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ለጋራ ለውጥ ከድሉ መማር ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።

ድሉ ለአፍሪካውያን ነጻነት የተጫወተውን ሚናም በሁሉም አፍሪካውያን ዘንድ በአግባቡ ለማስገንዘብ የጋራ ጥረት መደረግ እንዳለበት አመልክተዋል። ድሉን የመዘከር ሂደትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም እንዲሁ።  

''አድዋ፣ ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ነጻነትና አንድነት የተሳሰሩ ጉዳዮች ናቸው'' ያሉት ደግሞ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደ ማሪያም ናቸው።

የአድዋ ድል ለጥቁር ህዝቦች ያለውን ትርጉም በስፋት የማስገንዘቡ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል። 

በፓናል ወይይቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ተማሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

Published in ፖለቲካ

ሚዛን የካቲት 25/2009 የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ በእንስሳት፣ በእጽዋትና በተፈጥሮ ሳይንስ በደረጃ አራት ዲፕሎማ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 631 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ፡፡

ለሶስት ዓመታት ሰልጥነው ለምረቃ ከበቁት ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ሴቶች ናቸው፡፡

በምረቃው ስነስርዓት ላይ በክብር አንግድነት የተገኙት የቤንች ማጂ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምትኩ ታምሩ "ተመራቂዎቹ ያስተማራቸውን ህዝብ በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል ይኖርባቸዋል "ብለዋል፡፡

በእንስሳት ሳይንስ የተመረቀው ወንድሙ ሁንዴ  በሰጠው አስተያየት "በትምህርት ቆይታዬ የቀሰምኩትን በተግባር ለማዋል ተዘጋጅቻለሁ" ብሏል፡፡

ኮሌጁ ከተቋቋመበት 1994ዓ.ም  ጀምሮ ሀገሪቱ የነደፈችውን ግብርና መር ኢኮኖሚ ከግብ ለማድረስ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱን የኮሌጁ ዲን አቶ ገብሬ አቶምሳ ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ የዛሬዎቹ ተመራቂዎችን ጨምሮ  ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ 3ሺህ 471 ተማሪዎችን ማሰልጠኑም ተመልክቷል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

ነገሌ የካቲት 25/2009 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የወጣቱን የሱስ ተጠቂነት ለመከላከል ቀጣይነት ያለው ክትትልና ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዶላ ወዩ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በዞኑ ወጣቱን ለአደንዛዥ እጽ ሱሰኝነት የሚዳርጉና ለወንጀል የሚያነሳሱ ተግባራትን ለመከላከል 117 የሽሻ ማጨሻ እቃዎችንና ግብአቶችን በህዝብ ፊት እንዲወገዱ መድረጉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቋል።

የአዶላ ወዩ ከተማ ነዋሪው አቶ ጥላሁን ሳራ እንደገለጹት በሺሻና ጫት ቤቶች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር የአንድ ወቅት ብቻ ስለሚሆን የበርካታ ወጣቶች ስነ-ምግባር እየተበላሸ መጥቷል።

በመሆኑም ለሱስና ለስነ-ምግባር ጉድለት የሚያነሳሱ ተግባራት ላይ ፖሊስ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

የሺሻ ማስጨሻ እቃዎችን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን የተከለከሉ ተግባራትን በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ አስተማሪና ህጋዊ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት የገለጸው ደግሞ የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወጣት ብሩክ አየለ ነው።

የረጅም አመታት የሺሻ ሱስ ተጠቂ የነበረው ወጣት ወንድሙ ደምሴ በበኩሉ፣ ሺሻ የሚያስከትለው ጉዳት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን የስነ-ምግባርና የጤና ጭምር እንደሆነ ከህክምና ባለሙያዎች እንደተነገረው ጠቁሟል።

በህክምና ባለሙያ ምክር በብዙ ጥረት ከሺሻ ሱስ የተላቀቀው ወጣቱ አሁን ላይ ሌሎች ጓደኞችን በመምከርና በማስተማር ለመመለስ የራሱን ድርሻ እየተወጣ እንደሆነ አስረድቷል።

መሰል ድርጊቶችን ለመከላከልም የወጣቶች የጊዜ ማሳለፊያና መዝናኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሊስፋፉ እንደሚገባም ተናግሯል።

በጉጂ ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን ዲቪዥን ሀላፊ ኢንስፔክተር በቃሉ በለጠ በበኩላቸው ችግሮችን ለማቃለል 117 የሺሻ ማስጨሻ እቃዎችን ጨምሮ ከ50 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ እጽ እንዲወገድ ተደርጓል።

ሰሞኑን የተወገደው አደንዛዥ ዕጽ በአዶላ ከተማ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ከሻሸመኔ ወደ አዶላ ወዩ ከተማ ሲጓጓዝ የተያዘ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሺሻ ማስጨሻ እቃዎቹ በአዶላ ወዩ ከተማ በሰባ ቦሩ ወረዳ ደርሚና ቀንጢቻ ከተሞች በህዝብ ጥቆማ የተያዙ ሲሆን ሺሻ የሚያጨሱና ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ ለሚያሳልፉ ሰዎችም ትምህርት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

Published in ማህበራዊ

ጅማ የካቲት 25/2009 የአጋሮ ከተማ አስተዳደር በጥልቅ የተሀድሶ ግምገማ ወቅት ሕብረተሰቡ ያነሳውን የመንገድ ችግር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

አስተዳደሩ በአምስት የከተማ ቀበሌዎች 27 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድና 20 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ መስራቱን አስታውቋል፡፡

የአጋሮ ከተማ ከንቲባ አቶ ነጅብ ሁሴን እንደገለጹት መንገዱና የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዩ የተሰራው የከተማ አስተዳደሩና የኦሮሚያ ከልላዊ መንግስት በመደቡት 10 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

የመንገድ ሥራው የተከናወነው የከፋ የመንገድ ችግር ባለባቸውና አዳዲስ በተቋቋሙ መንድሮች መሆኑን ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡ በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት ያለበት የመንገድ ችግር እንዲፈታለት በዋናነት ሲያነሳ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባው፣ የከተማ አስተዳደሩ ለጥያቄው ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በከተማው 113 መንገዶችን መለየቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት 110 መንገዶችን ሰርቶ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉንም ከንቲባው አስረድተዋል።

እንደአቶ ነጅብ ገለፃ፣ የመንገድ ሥራው የነዋሪውን ጥያቄ ከመፍታት ባለፈ ከተለያዩ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው በ17 ማህበራት ለተደራጁ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ወጣት ጃሃድ ሻፊ እንዳለው የአጋሮ ከተማ አስተዳደር ለከተማዋ ልማት በሚያደረገው ጥረት ሥራ በማግኘቱ ለሥራና ለልማቱ ያለው ፍላጎት እንዲነሳሳ አድርጓል፡፡

"በቀጣይም አሁን ያገኘሁትን ልምድ በመጠቀም የበለጠ ለመስራትና ለመለወጥ ጠንክሬ እሰራለሁ" ብሏል።

የአጋሮ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሸምስያ ኑረዲን የከተማ አስተዳደሩ ጥያቄያቸውን ሰምቶ መንገድ በመስራቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"የተሰራው የጠጠር መንገድ እንዳይበላሽ በየጊዜው ጥገና እና እንክብካቤ የሚያስፈልገው በመሆኑ መንግስትና ሕብረተሰቡ ተቀናጀተው መስራት ይኖርባቸዋል" ብለዋል።

አቶ ኑረዲን አባፎጊ የተባሉ ሌላው ነዋሪ በበኩላቸው አሁን የተሰራው መንገድ መንግስት የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ቃል የገባውን በተግባር እያሳየ ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ መንገዶችን በመስራት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የጀመረውን ጥረት ሌሎች የልማት ሥራዎችንም በማከናወን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ሃዋሳ የካቲት 25/2009 ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሟላ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን በማመቻቸት ባለሃብቶች ተቀናጅተው የሚሰሩበትን ሁኔታ እንደሚፈጥሩ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃ ጨርቅ ምርት የተሠማራው ኤፒክ የተባለ ድርጅት ምርቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ለውጭ ሃገር ገበያ ልኳል ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንዱስትሪ ፓርክ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር በላቸው መኩሪያ እንደገለጹት አገሪቱ እያሳየች ባለው የኢንዱስትሪ ልማት እድገት የተነሳ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እየጨመረ መጥቷል።

በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃ ጨርቅ ምርት የተሠማራው ኤፒክ የተሰኘ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ምርቱን ለመጀመሪያ ጊዜ  ዛሬ ለውጭ ገበያ  ማቅረቡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ዘርፍ የተመዘገበ ታሪካዊ ስኬት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ለዚህም በዘርፉ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተጀመረው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት እንዲሁም መንግሥት የሚያደርገው ድጎማ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ተናግረዋል ፡፡

መንግሥት በኢንዱስትሪ ፓርኮች የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲፈጠር በማድረጉ ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሠሩ ማስቻሉ፣ መሠረተ ልማት ማመቻቸቱና የግብር እፎይታ መስጠቱ ለኢንቨስትመንት ልማት ትልቅ ማበረታቻ መሆኑንም ገልፀዋል።

"ከገበያ ትስስር አንፃር አጉዋ የሚያደርገው ድጋፍም የራሱ የሆነ ሚና ይጫወታል” ያሉት  ምክትል ኮሚሽነሩ  ፓርኩ ተገንብቶ ወደ ስራ በገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ አምርቶ  ለውጭ ገበያ ምርቱን ማቅረቡ የሚያስደስት ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

"በሚቀጥለው ሳምንትም ሸሚዝ አምራቹ ታል ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያን ጨምሮ ሌሎችም ድርጅቶች እግር በእግር  ምርታቸውን ወደ አሜሪካ ፣ ካናዳና ኖሮዌይ ይልካሉ " ብለዋል።

በተለያዩ የጨረታ ሂደቶች የተመረጡ 15  የአገር ውስጥ አምራቾች በፓርኩ እንዲገቡ ከውጭ ባለሃብቶች ጋር የማስተሳሰርና የባንክ ብድር የማመቻቸት ስራ ማለቁንም አስረድተዋል፡፡

መቀመጫውን ሆንግኮንግ ያደረገው የኤፒክ ድርጅት ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር ቻንዳና ሎኩግ (Chanfana lokuge) ምርታቸውን ኤክስፖርት በማድረጋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የህፃናት አልባሳት የሚያመርተው ኩባንያቸው ፓርኩ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮችን በአንድ ላይ በመያዙ ለስራቸው ተስማሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአጉዋ ስምምነትን ጨምሮ ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የቀረጥና ግብር እፎይታ መስጠቱ  ፣ከሌሎች ሃገራት አንጻር ርካሽ የሰው ሃይል መገኘቱና የመብራት ክፍያ ዝቅተኛ መሆኑ በሃገሪቱ  ለመስራት ምቹ እንዳደረገላቸው አስረድተዋል።

በመጀመሪያው ዙር 40 ሺህ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳት አሜሪካን አገር እንደሚልኩ የተናገሩት ቻንዳና እለቱ ህልማቸው እውን የሆነበት ቀን መሆኑን በመግለጽ በመንግሥትም ሆነ በፓርኩ ሠራተኞች ለሚደረግላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኩ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ሰዎች መካከል ወጣት ዘመንይሻ ባዴቦ ባገኘችው መልካም አጋጣሚ ተጠቅማ የሙያ ባለቤት ለመሆን መብቃቷን ገልጻለች።

ወጣቷ ቀደም ሲል ምንም ስራም ሆነ የሞያ ክህሎት እንዳልነበራት ገልጻ በፓርኩ ውስጥ ስራ በጀመሩት ባለሃብቶች አማካኝነት የተረጋጋ ኑሮዋን ለመምራት እንደቻለች ተናግራለች።

ሌላዋ በኢንዱስትሪ ፓርኩ የስራ እድል የተፈጠረላት ወጣት እድገት ታዲዮስ በበኩሏ በባለሃብቱ በተፈጠረላት የስራ እድል የዕለት ገቢዋን ማሳደግ መቻሏን ተናግራለች።

እሷ የምትሰራበት ድርጅትም የመጀመሪያ ምርቱን ወደ ውጭ ሃገር ገበያ መላኩን ስትመለከት ደስታዋን እጥፍ እንዳደረገው ገልጻለች።

ኢንዱስትሪ ፓርኩ ባለፈው ዓመት ተመርቆ ወደ ስራ የገባ ሲሆን ከ60 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎችም የስራ እድል የመፍጠር አቅም ያለው ነው።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ሽሬእንዳስላሴ የካቲት 25/2009 በትግራይ ምዕራባዊ ዞን  በ270 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ ያለው  የ" ሰባራዝጊ"  የመጠጥ ውሀ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ በመገባደድ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

የአዲ ረመፅ ከተማን  የንፁህ መጠጥ ውሀ ችግር ለመፍታት ታስቦ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የተጀመረው የፕሮጀክቱ ግንባታ የሚካሄደው የክልሉ መንግስት በመደበው በጀት ነው፡፡ 

በክልሉ ውሀ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሽመንዲ ከዋኒ ለኢዜአ እንደገለፁት የግድቡ ግንባታና ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎች እስከ መጪው ሰኔ ወር ተጠናቀው ለአገልግሎት ይበቃል፡፡

ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ  በላይ የመያዝ  አቅም ያለው የ" ሰባራዝጊ" ግድብ ግንባታ በዕቅዱ መሰረት ቀጥሎ አሁን ላይ  አፈፃፀሙ 95 በመቶ ደርሷል፡፡

" የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ የዓዲ ረመፅ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሀ ችግር ከመፍታት ባሻገር ለመስኖ ልማት ጭምር ማዋል ያስችላል" ብለዋል፡፡

እየተገነባ ያለው የግድቡ ስራ  የከተማ ነዋሪ በሚቀጥሉት ሀያ ዓመታት ሊኖር የሚችል የህዝብ ብዛት ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

ግድቡ በደለል ተሞልቶ  የአገልግሎት እድሜው እንደያጥር ደግሞ  የአካባቢው ማህበረሰብ የአከባቢ ጥበቃ ስራዎች ከወዲሁ ማከናወን እንደሚጠበቅበትም የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ጠቁመዋል፡፡

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል  ወጣት ብርሃኑ ንጉሰ በሰጠው አስተያየት በንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ምክንያት የሚጠቀሙት ንፅህና ከጎደለው የወንዝና የጉድጓድ ውሃ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ለውሀ ወለድ  በሽታ መጋለጣቸውን ያመለከተው ወጣቱ   ግድቡ ሲጠናቀቅ ችግራቸውን ይፈታል ብለው በተስፋ  እየጠበቁ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

ወይዘሮ የኔነሽ ስለሺ የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው ንፅህናው ካልተጠበቀ የጉድጓድ ውሀ ለመቅዳት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ወረፋ ለመያዝ እንደሚገደዱ ተናግረዋል፡፡

" ችግራቸውን  ለመፍታትም መንግስት የጀመረው የውሃ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደምንሆን ተስፋ እናደርጋለን "  ብለዋል።

አሁን ያለው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ከከተማው ህዝብ ብዛት አንጻር የሚመጥን ባለመሆኑ ያጋጠመውን እጥረት ለመፍታት በመገንባት ላይ ያለው ፕሮጀክት ዘለቄታዊ መፍትሄ እንደሚሆንም ተመልክቷል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 25/2009 ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተግባር በመተርጎም የጸረ ድህነት ትግሉን በስኬት ለመወጣት በየክልሎቹ የሚዘዋወረው የትውልድ ቅብብሎሽ ማሳያ የሆነው አዲስ የንቅናቄ ችቦ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚያስችል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ "ጊዜ የለንም እንሮጣለን! ለህዳሴ ግድባችን እንቆጥባለን!" በሚል መሪ ሀሳብ ነገ በሚካሄደው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሩጫ መላው ህዝብ እንዲካፈል ጥሪ አድርገዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 6ኛ ዓመት አስመልክቶ በተለይ ከኢዜአ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ የአድዋ ድል ታሪክ ጥልቅ ሀሳብ በትውልድ ቅብብሎሽ በጸረ ድህነት ዘመቻው በመረባረብ ውጤታማነቱ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም በ121ኛ የአድዋ ድለ መታሰቢያ በዓል በታሪካዊው ቦታ በተከበረበት ወቅት የትውልድ ቅብብሎሹ ማሳያ የንቅናቄ ችቦ ርክክብ ተደርጓል።

“የታላቁ ህዳሴ ግድባችን ብሄራዊ መግባባት መሰረት የተጣለበት አንድ ብርቅዬ ፕሮጀክታችን ነው” ያሉት አቶ ደመቀ፤ ክልሎች በየተራ የሚረከቡትን ችቦ ጨምሮ ህብረተሰቡ ግለቱን አጎልብቶ ለላቀው ምዕራፍ በቦንድ ግዥና በምክረ ሀሳብ የባለቤትነት ተሳትፎውን ማጠናከር የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

“የችቦ ቅብብሎሹን በቦንድ ግዥ፣ በአጋርነትና በባለቤትነት አጠናክሮ ለመቀጠል ይፋ ሆኖ በሚወጣው መርሃ ግብር መሰረት ተረካቢ ክልሎች ለኩሰው ይቀጥላል” ብለዋል።

የዚህ ዓይነቱ ንቅናቄ የህዝቡን ግለት ወደ ጋራ መድረክ የሚያወጣ ተሳትፎን የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የብሄሮች ብሄረሰቦችና ሕዘቦች ዋንጫ በየክልሉ በተንቀሳቀሰበት ወቅት ህዝብ ከህዝብ ከማስተሳሰር ባሻገር በቦንድ ግዥ ታሪክ መሰራቱን አስታውሰው፤ አሁንም ዋንጫው እንደቀጠለ የንቅናቄው ችቦ በአዲስ መልክ ጉዞ እንደሚጀምር ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ በጸረ ድህነት ዘመቻው በሁሉም መስክ የድርሻን በማሳካት የአድዋን ገድል የትውልድ ቅብብሎሽ አደራ መወጣት አስፈላጊ ነው።

የ121ኛ አድዋ ድል በዓል በታሪካዊው ስፍራ በተከበረበት ዕለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የንቅናቄውን ችቦ ለፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ለአቶ ያለው አባተ ማስረከባቸው ይታወሳል።

በሌላ በኩል "ጊዜ የለንም እንሮጣለን! ለህዳሴ ግድባችን እንቆጥባለን!" በሚል መሪ ሀሳብ ነገ በሚካሄደው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሩጫ መላው ህብረተሰብ እንዲሳተፍ ጥሪ አድርገዋል።

የዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በሚካሄደው ሩጫ ላይ ሁሉም ተሳትፎ በማድረግ አጋርነቱን ማሳየት እንዳለበት አስገንዝበዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ።

የዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ106ኛ በአገራችን ለ41ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሃ ግበሮች ይከበራል።

ታላቅ አገራዊ የሩጫ መርሃግብር የተዘጋጀው ሴቶች የግድቡ ባለቤትነታቸው፣ ፋና ወጊነታቸው፣ ቀጣይነታቸውና ተሳትፏቸውን የበለጠ ለማጠናከር መሆኑን ገልጸዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሩጫ በመላው አገሪቷ ከተሞችና ዞኖች የሚካሄድ ሲሆን፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ከሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴርና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተዘጋጀ ነው።

Published in ፖለቲካ

ጅማ ሃዋሳ የካቲት 25/2009 የጅማና የሃዋሳ ዩኒቨርስቲዎች  መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች  የጥልቅ ተህድሶ ግምገማ ጀመሩ፡፡

በጅማው የግምገማ መድረክ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ እንደገለጹት በልማታዊ መንግስት ምንነት፣ ባህሪያት፣ እንዲሁም ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ  የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎን ላይ  ውይይት ይደረጋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ለህዳሴው ጉዞ ስኬታማነት የበኩሉን ለመወጣት በመድረኩ መሳተፉ  አስፋላጊ ነው፡፡

"ብቁና ውጤታማ መምህር ፣ተመራመሪ እና ፈጻሚ ለትምህርት ጥራትና  ለህዳሴ ጉዞ  መረጋገጥ  በፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ግልጽ ግንዛቤ መያዝ አስፈላጊ ነው "ብለዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ተገኝተው ገለጻ ያደረጉት የጅማ ከተማ አፈ ጉባኤ አቶ ሰለሞን ቀኖ  በከተማም ሆነ በገጠር የሚታዩ አበረታች የልማት ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የዩኒቨርሲቲው  ማህበረሰብ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ከእርስ በርስ ጦርነት ወጥተን ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ህዝባችንን እያስተማርን ጎን ለጎን ፈጣን ዕድገት እያሰመዘገብን እንገኛለን" ያሉት አፈ ጉባኤው ውጤቱ የተገኘውም ልዩነቶችን  በዲሞክራሲያዊ አግባብ አጣጥሞ ማስኬድ በመቻሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

" የሀገሪቱን የህዳሴ ጉዞ  አጠናክርን በመቀጠል  ታሪክ ለመስራት እንዘጋጅ "ብለዋል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ዶክተር ታመነ አዱኛ በሰጡት አስተያየት በቆይታቸው የነበሩባቸውን ደካማና ጠንካራ ጎኖች በመፈተሽ ለተሻለ ለውጥ ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ግብርና ኮሌጅ የአስተዳደር ስራተኛ  የሆኑት አቶ ስለሽ ዳምጠው በበኩላቸው መንግስት ጠንካራ ሰራተኛ  ለመፍጠር እያደረገ ባለው ሂደት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የድርሻው መወጣት እንዲችል የተሀድሶ መድረኩ መዘጋጀቱ  አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በሀዋሳ  ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ባለው መድረክ ላይ የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ እንዳሉት የመድረኩ ዓላማ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አገሪቱ የምትከተለውን የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሚገባ እንዲገነዘብ ለማስቻል ነው፡፡ ፡

"የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ብቁና ውጤታማ መምህራንና ፈፃሚ መፍጠር ያስፈልጋል " ያሉት አቶ ሚሊዮን የተገኙ ውጤቶችንና ጉድለቶችን በመለየት በቀጣይ  ተቋሙ  ብቁ ዜጋ በመፍጠር ለሀገር  የሚጠቅም የምርምር ስራዎችን ማጠናከር እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አቶ አያኖ በራሶ በበኩላቸው "መድረኩ በመልካም አስተዳደር፣ በኪራይ ሰብሳቢነት፣ ፣ በትምክህትና በጠባብነትን  ችግሮች ዙሪያ በመነጋገር የመፍትሔ አቅጣጫ ያስቀምጣል" ብለዋል፡፡

የተቋሙ ሁሉም ሰራተኛ  በአፈፃፀምና በአመለካከት በኩል ያሉበትን  ጉድለቶች በመለየት በሂስ ግለ ሂስ ተገምግሞ ደረጃ እንደሚሰጠውም አመልክተዋል፡፡

በመምህራን ዘንድ የሚስተዋሉ የሥነ ምግባር ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት መድረኩ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል

በዩኒቨርሲቲው ትናንት በተጀመረውና ለአራት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ  7ሺህ የሚጠጉ  መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች እንደሚሳተፉም ተመልክቷል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 25/2009 ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከመቶ ሺህ ብር በላይ ለቆጠቡ የሴቶች የልማት ቡድኖች የሽልማት ፕሮግራም እንደሚዘጋጅ የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ዓለምፀሀይ ኤልያስ እንዳሉት ፕሮግራሙ የሚካሄደው ባለፉት ሁለት ወራት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በተካሄደው ንቅናቄ በተደራጀ የሴቶች የልማት ቡድን በቦንድ ግዥና በቁጠባ ለተሳተፉ ነው።

የተሻለ የቆጠቡና ቦንድ የገዙ ቡድኖች በከተማና በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳድረው ተሸላሚ ይሆናሉ ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የቁጠባና የቦንድ ግዥ በግልም ሆነ በቡድን ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዋ በተያዘው ወር መጨረሻ የሽልማት ፕሮግራሙ ይፋ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የሴቶች የልማት ቡድኖች በንቅናቄው ተሳትፏቸው መጠናከሩ የቁጠባ ባህልን በማዳበርና ኢኮኖሚያቸውን በማሳደግ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑንም ገልፀዋል።

'ቁጠባ ለቤተሰብም ሆነ ለህዳሴ ስኬት መሰረት ነው' በሚል መርህ የልማት ቡድኖች በግልና በቡድን ቁጠባቸውን እያሳደጉ እንደሚገኙና ንቅናቄውም በቋሚነት እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን