አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 03 March 2017

መቱ ነቀምት   የካቲት 24/2009 የግብርና ፓኬጆችን መጠቀማቸው ምርታማነታቸው በማሳደግ ተጠቃሚ መሆናቸውን  በኢሉአባቦርና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች  አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

በሁለቱ ዞኖች በ2008/2009 የምርት ዘመን ታርሶ ከለማው የእርሻ መሬት  14 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱም ተመልክቷል፡፡ 

አርሶ አደር  አለማየሁ አበራ በበኢሉአባቦር ዞን ዳሪሙ ወረዳ ወሌ የባምቢስ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው ፡፡

ባለፈው መኸር ወቅት ከአንድ ሄክታር መሬት ላይ ማዳበሪያን ተጠቅመው በመስመር የዘሩት በቆሎ  ከ35 ኩንታል በላይ ምርት ሰብስበዋል፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት ከዚህ ቀደም  እነዚህን የግብርና ፓኬጆችን ሳይጠቀሙ በተለምዶ በሚያካሄዱት የእርሻ ስራ በሄክታር የሚያገኙት ምርት  ከአስር ኩንታል አይበልጥም ነበር፡፡

በዚሁ ዞን አሌ ወረዳ ይቢ ማሪ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ከድር ሀይሌ በበኩላቸው  ባለፈው የመኸር ወቅት በቆሎ በሄክታር ጤፍ ደግሞ በግማሽ ሄክታር ላይ ማዳበሪያን ተጠቅመው በመስመር መዝራታቸውን ተናግረዋል፡፡

" የግብርና ፓኬጆችን  በመጠቀም ማልማቴ ምርታማነቴን ከማደጉም ባለፈ በብተና ስዘራ የማባክነውን የዘር መጠንም ቀንሶልኛል" ብለዋል፡፡ 

በሄክታር  ካለሙት በቆሎ ከ30 ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰባቸውና ይህም ከዚህ ቀደም በተለመደው አስራር ሲያገኙ ከነበረው ከሶስት እጥፍ ብልጫ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ ወረዳዎች  ባለፈው የመኸር ወቅት ከለማው 133ሺህ ሄክታር   ከአራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የገለጹት ደግሞ የዞኑ እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ናቸው፡፡

አብዛኛው የዞኑ አርሶአደር የግብርና ፓኬጆችን መጠቀም በመጀመሩ የምርታማነት መጠኑ  ከ10  ወደ 32 ኩንታል ማደጉንም ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይም በሆሮ  ጉዱሩ ወለጋ የሆሮ ወረዳ  ግትሎ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገደፈ አብድሳ እንደተናገሩት የግብርና ባለሙያዎች  የሚሰጧቸውን ምክርና ሙያዊው ድጋፍ  ተጠቅመው በመስመር መዝራት ከጀመሩ ወዲህ ምርታማነታቸው አድጓል፡፡

በተለምዶ የእርሻ ስራ ጤፍ  ከ10 ኩንታልና  ባቄላ ከአምስት ኩንታል  በታች በሄክታር ያገኙ የነበረው  ከሶስት እጥፍ በላይ በማሳደግ ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደሩ ተናግረዋል፡፡

የዚሁ ቀበሌ ሌላው አርሶ አደር  ወይዘሮ ኩሉለ አራሩ በበኩላቸው ከዚህን ቀደም በመስመር ባለመዝራት የልፋታቸውን ያህል ውጤት ሳያገኙ መቆየታቸውን ጠቁመው  የግብርና ፓኬጆች መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ  የተሻለ ምርት እያገኙ መጠቀማቸውን ተናግረዋል።

የተሻሻሉ የግብርና አስራሮችን መጠቀማቸው ስንዴ 60 ኩንታል ፣ ጤፍ 20  ኩንታል እና ባቄላ ደግሞ ከ15 ኩንታል በላይ በማግኘት ምርታማነታቸው በከፍተኛ ደረጃ ማደረጉን የተናገሩት ደግሞ  አርሶ አደር ተረፈ አለማየሁ ናቸው፡፡

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ባለፈው የመኸር ወቅት  ከለማው 309ሺህ 388 ሄክታር መሬት  9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል፡፡

በዞኑ እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የእቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ኢታላይ ሙጬ እንደገለጹት በመስመር መዝራትን ጨምሮ አርሶ አደሩ የተለያዩ  የግብርና ፓኬጆችን ተጠቅሞ በማልማቱ በዘመኑ የተገኘው ምርት ከባለፈው ዓመት ጋር ብልጫ ያለው ነው።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 24/2009 የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማሰባሰብ ማቀዱን ገለፀ።

ቢሮው ገቢውን ለማሰባሰብ ያቀደው ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ማርች 8 ምክንያት በማድረግ ከሚዘጋጁ የተለያዩ ፕሮግራሞች ነው።

ከሴቶች የልማት ቡድን ቁጠባ ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ማቀዱንም ገልጿል።

ቢሮው ይህን የገለጸው ማርች 8 እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ መሰረት የተጣለበትን 6ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከመዲናዋ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ጋር በሰጠው መግለጫ ነው።

የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ዓለም ፀሐይ ኤልያስ እንደተናገሩት ገንዘቡን ለመሰብሰብ የታቀደው ከቦንድ ግዥ፣ ከቲሸርት ሽያጭና ከተለያዩ ስጦታዎች ነው።

በገቢ ማሰባሰቡ ፕሮግራም ከ60 ሺህ በላይ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የተለያዩ አደረጃጀቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

ማርች 8 ከሴቶች ቁጠባና ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ጋር ተያያዥነት እንዲኖረው በማድረግ እንደሚከበርም አስረድተዋል።

በዓሉ የሴቶችን ቁጠባ በማሳደግ፣ መዲናዋን ፅዱና አረንጓዴ በማድረግና ለግድቡ ግንባታ በተዘጋጀ የቦንድ ግዥ ሳምንት እየተከበረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከየካቲት 20 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለአስር ቀን በሚካሄደው የቦንድ ግዥ ሳምንት ከወረዳ ጀምሮ የተደራጀ ንቅናቄ በመፍጠር አመራሩን ያሳተፈ የቦንድ ግዥ እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል።

ወንዶች ለሴቶች ያላቸውን ክብር ለመግለፅ ለእናቶቻቸው፣ ለባለቤታቸው፣ ለእህቶቻቸውና ለልጆቻቸው ቦንድ በመግዛት አጋርነታቸውን ማሳየት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሽታዬ መሀመድ በበኩላቸው በመዲናዋ በተዘጋጁ 71 ማዕከላት ባለፉት ሶስት ቀናት ከተሸጠ ቦንድ ከ10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል።

በቀሪዎቹ የሽያጭ ቀናት የመዲናዋ ነዋሪዎች፣ ወጣቶችና አደረጃጀቶች ለግድቡ ግንባታ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ የማስቀጠል ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀንና የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን 6ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ህብረተሰቡ የሚሳተፍበት የሩጫ ውድድር እሁድ የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም እንደሚካሄድም ኃላፊዋ ጠቁመዋል።

በዓሉን አስመልክቶ ለተዘጋጀው የሩጫ ውድድር ከተሸጠው 60 ሺህ ቲሸርት ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱንም ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 24/2009 የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ አዋጆችን በማፅደቅና ሹመቶችን በመስጠት ተጠናቋል።

የጨፌው አምስተኛ የሥራ ዘመን ሁለተኛ ዓመት አምስተኛ መደበኛ ጉባኤ በአዳማ አባ ገዳ አዳራሽ ለሁለት ቀናት ተካሂዷል።

ጉባኤው ከመጠናቀቁ በፊት የጨፌውን አሰራር፣ አደረጃጀት፣ የአባላትና የስብሰባ ሥርዓትን የሚወስን አዋጅ አሻሽሎ አጽደቋል።

ተሻሽሎ የጸደቀው አዋጅ የጨፌውን ቋሚ ኮሚቴዎች በተሻለ መልኩ ለማደራጀትና ውጤታማ ለማድረግ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።

በተጨማሪም የክልሉን ገቢ ግብር ማሻሻያ እንዲሁም የክልሉን መንግስት ታክስ አስተዳደር አዋጆችንም አፅድቋል።

ሁለቱ አዋጆች የክልሉን የታክስ አሰባሰብ ስርአት ለማጠናከር እንደሚያስችሉ የተጠቆመ ሲሆን፤ የክልሉን ገቢ ከኪራይ ሰብሳቢነትና መልካም አስተዳደር ችግሮችም የፀዳ ለማድረግ እንደሚረዳ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት ያደረገውን ጥልቅ ተሃድሶ ውጤታማ ለማድረግ ያስችላሉ ተብሎ የታመነባቸው ስድስት የካቢኔ አባላትን ሹመት አጽድቋል።

በዚሁ መሰረትም ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ  አዲሱ አረጋ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዩች ቢሮ ኃላፊ፤ አቶ አህመድ ቱሳ የገቢዎች ባለስልጣን ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል፡፡

አቶ አብዱ ገለቶ የመንገዶች ባለስልጣን፣ አቶ ተክሌ ኡማ የትራንስፖርት ባለስልጣን  እንዲሁም አቶ አውሉ አብዲ የስራ እድል ፈጠራና የከተሞች ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ኃላፊዎች ሆነዋል፡፡

የክልሉን የፍትሕ ዘርፍ በአግባቡ ለመምራትም 70 የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሹመትና አንድ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የተሾሙ ሲሆን፤ ለኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ስምንት አባላት ያሉት ቦርድም ተሰይሟል።

Published in ፖለቲካ

አዲሰ አበባ የካቲት 24/2009 የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን / የሕዝብ ችግሮችን ለመፍታት የሚታዩ ተግዳሮቶችን በየደረጃው በመፈተሽ መፍትሔ ለመስጠት ቁርጠኛ አቋም በመያዝ እየሰራ መሆኑን ገለፀ፡፡

ከክልሉ ውጪ የሚገኙ የፊዴራልና የሌሎች ክልሎች የብአዴን አመራር አካላት የተጀመረውን ጥልቅ ተሃድሶ በማስቀጠልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ሂደት አባላቱ ተልዕኳቸውን የበለጠ አጠናክረው በሚቀጥሉበት ስልት ላይ ውይይት እያካሄዱ ናቸው።

ሥልጠናው የድርጅቱን ጥልቅ ተሐድሶ በንድፈ ሐሳብ በሚደገፉ ርእሰ ጉዳዩች ላይ እንደሚያተኩር ነው የተገለፀው፡፡

ከአማራ ክልል ውጭ የድርጅቱ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ እሸቴ አስፋው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት፤ ድርጅቱ እስካሁን የሕዝብ ችግሮችን የማዳመጥና የመፍታት ሥራዎችን በተግባር ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

በሥልጠናው ላይ በሚደረጉ ውይይቶች እስካሁን አመራሩ ያደረገውን ጥልቅ ተሐድሶ በንድፈ ሐሳብ ለማበልጸግ እንደሚያስችል አመልክተው፤ ይህም አባላቱ በተሻለ ቁመና ለአፈፃፀም በሚተጉበት አቅጣጫ ላይ እንደሚያተኩርም ተናግረዋል።

ድርጅቱ በጥልቅ ተሐድሶ መድረኮች የተለዩትን አንገብጋቢ የሕዝብ ችግሮች መፍታት  መጀመሩን የጠቆሙት አቶ እሸቴ፤ ድርጅቱ ትምክህትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመዋጋት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ድርጅቱ በጥልቅ ተሐድሶ የተነሱትን ችግሮችን የሚፈታበትን መንገድ አቅዶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን አመልክተው፤ አፈፃፀማቸውን በመከታተልና በመቆጣጠር ውጤታቸውን እየገመገመ እንደሚሔድም ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 24/2009 የላይቤሪያዋ ፕሬዝዳንት አሌን ጆንሰን ሰርሊፍ ጉብኝት የኢትዮጵያና ላይቤሪያን ግንኙነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር የሚያስችል መሰረት የተጣለበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ በሳምንቱ በዲፕሎማሲው መስክ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንት አሌን ጆንሰን ሰርሊፍ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሳደግ ያለመ የሦስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገው ዛሬ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

ፕሬዝዳንቷ በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝና ከፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋር የተወያዩ ሲሆን በአምስት ዘርፎች በትብብር መስራት የሚያስችል ስምምነትም ተፈርሟል።

የኢንዱስትሪና የዓሣ ሃብት ልማት እንዲሁም ትምህርት ስምምነት ከተደረሰባቸው መስኮች መካከል እንደሆኑ አቶ ተወልደ ጠቅሰዋል።

የፕሬዝዳንቷ ጉብኝት የሁለቱን አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ለማሸጋገር መሰረት የተጣለበት እንደነበር በማውሳት። 

ፕሬዝዳንት ሰርሊፍ የሀዋሳና ዱከም ኢንዱስትሪ ፓርኮችን መጎብኘታቸውንና አገራቸው በዘርፉ የኢትዮጵያን ልምድ መቅሰም እንደምትሻ መናገራቸውንም ገልጸዋል አቶ ተወልደ።

በላይቤሪያ የተከሰተውን ግጭት ለማረጋጋትና የኢቦላ ወረርሽኝ ለመከላከል ኢትዮጵያ ላደረገችው ድጋፍ ፕሬዝዳንቷ ምስጋና ማቅረባቸውንም ተናግረዋል። 

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኬር ማያርዲት ጉብኝት ሌላው የሳምንቱ አበይት ጉዳይ መሆኑንም አቶ ተወልደ አንስተዋል። 

በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን መካከል ከተፈረሙ ስምንት ስምምነቶች መካከል ንግድ፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የመንገድ ልማትና ትምህርትን ጠቅሰዋል። 

"በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ኢትዮጵያ በኢጋድ በኩል ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች" ያሉት አቶ ተወልደ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተፈረሙ ስምምነቶች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ ሚናዋን መወጣቷን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የተመራ የልዑካን ቡድን በጄኔቭ ስዊዘርላንድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ስብሰባ ለመታደም ወደ ስፍራው ማቅናቱም ሌላው የሳምንቱ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል። 

ሚኒስትር ዴኤታዋ በስብሰባው ላይ በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ማብራሪያ መስጠታቸውንም ገልጸዋል።

በተለይም በአገሪቷ ተከስቶ በነበረው ግጭት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጥረው ከሆነ የሚያጣራ ቡድን መቋቋሙንና በወቅቱ የነበረውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ የሚዳስስ ሪፖርት ለተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን መናገራቸውንም አክለዋል።   

የግለሰብና የቡድን መብቶችን ለማስከበር አገሪቷ እየተከተለችው ባለው አሰራርና በተገኙ ውጤቶች ዙሪያ ማብራሪያ መስጠታቸውንም እንዲሁ። 

በህዳሴው ግድብ ላይ ጥቃት ለማድረስ 20 የሚደርሱ ጸረ ሠላም ኃይሎች ያደረጉት ሙከራ መክሸፉም ሌላው የሳምንቱ መነጋገሪያ ጉዳይ እንደነበር አስታውሰዋል። 

መንግሥት በወሰደው እርምጃ 13ቱ ሲገደሉ ሰባቱ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ መዘገቡ ይታወሳል።

አቶ ተወልደ ስለ ጉዳዩ በሰጡት ማብራሪያ "ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት ድርጊቱ መክሸፉ ኢትዮጵያ ሁሌም ዝግጁ መሆኗን ያመላከተ ነው" ብለዋል። 

የጸረ ሠላም ኃይሎቹ ድርጊት መክሸፍ አገሪቷ ሠላምና መረጋጋቷን ለማስቀጠሏ ማሳያ መሆኑን የተናገሩት ቃል አቀባዩ ይኸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። 

ዜጎች ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአገሪቷ ሠላም እንዳይደፈርስ የጀመሩት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል።

Published in ፖለቲካ

ነቀምት የካቲት 24/2009 በቄለም ወለጋ ዞን በተያዘው የበጋ ወራት በመስኖ ከለማው መሬት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን አስታወቀ ፡፡

በባለስልጣኑ የመስኖ ውሃ አቅርቦት የሥራ ሂደት አስተባባሪና ምክትል ኃላፊ አቶ ኤልያስ አዲሱ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በዞኑ በባህላዊ፣ በዘመናዊ፣ በውሃ መሳቢያ ሞተርና በጉድጓድ ውሃ 28 ሺህ 706 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል። 

ከዚህም ሦስት ሚሊዮን 562 ሺህ 892 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ እስካሁን ከአንድ ሚሊዮን 880 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ ኤልያስ ገለጻ፣ አርሶአደሩ በመስኖ ልማት የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባሻገር በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማምረት ገቢውን በማሳደግ ላይ ይገኛል።

ይህም የመስኖ ተሳታፊ አርሶአደሮች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ እንዲመጣ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዞኑ በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት ከ52 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ምርጥ ዘርና 318 ኩንታል የምርት ማሳደጊያ ግብአቶች አገልግሎት ላይ መዋላቸውን ጠቁመው፣ በመስኖ ልማቱ 82 ሺህ 372 አርሶአደሮች መሳተፋቸውን አመልክተዋል፡፡

በዞኑ በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ከሆኑ አርሶ አደሮች መካከል በሰዮ ወረዳ የቆሬ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ወንድሙ ተስፋ በሰጡት አስተያየት፣ በሁለት ሄክታር መሬታቸው ላይ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ አትክልቶችን አልምተው በመሸጥ እየተጠቀሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር 30 ኩንታል ምርት ለገበያ በማቅረብ ከሰባት ሺህ ብር በላይ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ ለገበያ ከሚያቀርቡት 600 ኩንታል ከ150 ሺህ ብር በላይ ገቢ አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመትም ከመስኖ ልማት ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውንም አርሶአደሩ አስታውሰዋል።

በሐዋ ገላን ወረዳ የመደ ጀለላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ሼህ ሙህዲን መሐመድ በበኩላቸው እንዳሉት በሰጡት አስተያየት በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት ሽንኩርት 60 ኩንታል ለገበያ አቅርበዋል።

በአካባቢያቸው የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ ስድስት ብር መሆኑን ጠቁመው በመንግስት የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ በገበያው ብዙም ትርፋማ እየሆኑ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

ከሽንኩርት ልማቱ በተጨማሪ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት ቲማቲም ከ20 አስከ 30 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ አመልክተዋል፡፡

አርሶአደር ሼህ ሙህዲን በ2008 ዓ.ም በመስኖ ካለሙት ሽንኩርት ከ36 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውንና ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 24/2009 አገር አቀፉ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽን ለገበያ ትስስርና ምርታቸውን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ  ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ተሳታፊዎች ገለጹ።

የበጀት ዓመቱ 1ኛ ዙር አገር አቀፍ ሞዴል የጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችና ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውጭ ያሉ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር ዛሬ በአዲስ አበባ ተከፍቷል።

የኢዜአ ሪፖርተር በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ለመሳተፍ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ አንቀሳቃሾችን አነጋግሯል።

ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ወረዳ የመጡትና ከቀንድ ጌጣጌጥ የሚያመርቱት አቶ ጥላሁን አየነው በኤግዚቢሽኑ መሳተፋቸው ሰፊ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ያምናሉ።

ለሌሎች ተሳታፊዎች ምርታቸውን በማስተዋወቅና የገበያ አድማሳቸውን በማስፋት የተሻለ ገቢ እንደሚያስገኝላቸውም ገልጸዋል።

ከጅማ ከተማ የመጡት ወይዘሮ መሰረት አስታጥቄም የተለያዩ የእንጨት ምርት ውጤቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል።

በኤግዚቢሽኑ ሲሳተፉ የመጀመሪያቸው መሆኑን ገልጸው ምርታቸውን ለተለያየ የህብረተሰብ ክፍል ለማስተዋወቅና ገበያ ለማግኘት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል። 

የሞሪንጋ ምርቱን ለህብረተሰቡ ለማስተዋወቅና ለመሸጥ በኤግዚቢሽንና ባዛሩ የታደመው የአርባ ምንጭ ከተማው ወጣት አቡሽ ሚልኪያስም በዚህ ሃሳብ ይስማማል።

"ኤግዚቢሽኑ ምርቶቼን ከመሸጥ ባሻገር፤ የሚፈጥርልኝ የገበያ ትስስር ለቀጣይ ስራዬ የጎላ ጥቅም ይኖረዋል" ነው ያለው።

የፌደራል የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ ኤግዚቢሽኑ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞቹ የገበያ ትስስር ከመፍጠርና ምርቶቻቸውን ከማስተዋወቅ አንጻር የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በክልሎች ለሚገኙ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራዞች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

መዋቅራዊ አደረጃጀት በመዘርጋት ኢንተርፕራይዞቹ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በየደረጃው እንዲፈቱ የማድረግ ስራ እየተከናወነ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሰባት ቀናት የሚቆየው ኤግዚቢሽንና ባዛር "ዘላቂነት ያለው የገበያ ትስስር ለኢንተርፕራይዞች ልማት መሰረት ነው" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚካሄደው።

በኤግዚቢሽኑ የሸማ፣ የቆዳ፣ የእንጨት፣ የፈሳሽ ሳሙናና ሌሎች ምርቶችን የያዙ ከ220 በላይ ኢንተርፕራይዞች እየተሳተፉ ነው።

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ የካቲት24/2009 ሴቶችን ማዕከል ያደረጉ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ዘላቂነት ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ፡፡

የደቡብ ክልል ሴቶች ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ  ከርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ደሴ ዳልኬ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል፡

በውይይቱ መክፈቻ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተሰራው ሥራ ዘርፈ ብዙ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

በቀጣይም ሴቶችን ማዕከል ያደረጉ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ዘላቂነት ያለው ለውጥ ለማምጣት የለውጥና የልማት ፓኬጆችን በተገቢው መንገድ መተግበር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

አቶ ደሴ እንዳሉት፣ ሴቶች በልማቱ ያላቸውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ በተናጠል ከሚያደርጉት እንስቅሴ ባለፈ አደረጃጀቶችን ተጠቅመው በመንቀሳቀሳቸው ለሕዳሴ ጉዞ ስኬት የድርሻቸውን እየተወጡ ነው።

በአደረጃጀቶቻቸው የሚያደርጉት የቁጠባ እንቅስቃሴም ለውጥ እየታየበት መሆኑን ጠቁመው፣ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሴት ባለሀብቶችን ማፍራት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል።

ከመሰረተ ልማት አለመሟላት ጋር በተያያዘ ቀጥተኛ ተጎጂዎች ሴቶች በመሆናቸው በቀጣይ በየደረጃው ተገቢ ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

የገጠር ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙ ሴቶችን ከወንዶች እኩል ተጠቃሚ ባለማድረጉ ለለውጥና ለልማት ፓኬጁ ተፈጻሚነት የተቀናጀ አመራርና ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አቶ ደሴ ጠቁመዋል፡፡

በኮንስትራክሽን ዘርፍ ሴቶች ተመጣጣኝ ክፍያ እያገኙ አይደለም ለሚለው ቅሬታም ተመጣጣኝና እኩል ክፍያን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሴቶች አደረጃጀቶቻቸውን በመጠቀም የራሳቸውን ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስረድተዋል።

በመሸጫና መስሪያቦታ እንዲሁም በብድር አቅርቦቱ ላይ ያለባቸውን ችግር ለመፍታትም  በቀጣይ ሴቶችን ማዕከል ያደረገ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፣ ባለፉት ዓመታት የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማረጋገጥ በተሰራው ሥራ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸውን በርካታ ሴቶች ማፍራት ተችሏል።

በቀጣይም በአርብቶአደር አካባቢ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ በተለየ ዕቅድ ተይዞ እንደሚሰራ ነው የጠቆሙት፡፡

የአመራር ሰጪነት ሚናቸውን ለማሳደግ በተሰራው ሥራም በፌደራል ፓርላማ 40 ከመቶ ሴቶች ክልሉን መወከላቸውን ተናግረዋል።

በክልልና በየደረጃው ባሉ ምክር ቤቶች ተሳትፏቸው በማደጉ ተጨባጭ ለውጦች መምጣቻውን ገልጸዋል፡፡

በመልካም አስተዳደርና በፍትህ፣ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና በሌሎች ጉዳዮች ለተነሱላቸው ጥያቄዎችም ርዕሰ መስተዳድሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የክልሉ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሂክማ በበኩላቸው፣ የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሴቷን በኢኮኖሚ ለማብቃትና ተሳትፎዋን ለማሳደግ ታስቦ የሚከበር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"በቀጣይም ፈጣንና ተግባራዊ ምላሽ በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ በንቃት በመሳተፍና የልማት አቅሞችን በማቀናጀት የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት መሳዳግ ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡

በመድረኩ አቅማቸውን በማሳደግ የተሸለ ገንዘብ የቆጠቡ የልማት ቡድኖችና አደረጃጀቶች እንዲሁም ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ሴት ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በክልሉ ምክር ቤት አዳራሽ በተካሄደው ውይይቱ ሴት አርሶአደሮች፣ አመራሮች፣ ምሁራን፣ ሴት ተማሪዎችና በተለያየ ዘርፍ ውጤታማ የሆኑ ሴቶች ጨምሮ 800 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 24/2009 ኢህአዴግን ጨምሮ 22 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚደራደሩበት አጀንዳ ዓላማ ዙሪያ ስምምነት ላይ ደረሱ።

ኢህአዴግ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ለመደራደር ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል

በዚህም 21 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ከኢህአዴግ ጋር እየተወያዩ ይገኛሉ።

ዛሬ 22ቱ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች "የምንደራደረው ከዚህ ግብ ለመድረስ ነው" ብለው ባነሱት ጉዳይ ላይ ተወያይተው ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በዚሁ መሰረት "በድርድር ወቅት የሚነሱ የተለያዩ ሃሳቦችን እንደ ግብዓት በመጠቀም መሰረታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን የሚሻሻሉ ህጎችን ማሻሻል የአፈፃፀም ጉድለቶችን ማስተካከል" በሚል ሀሳብ ላይ ተስማምተዋል።

ቀደም ብሎ በደረሱት መግባባት መሰረት ውይይቱን የመሩት የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ  "በአገራችን የፖለቲካ ምህዳርና የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ያጋጠሙ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሄ እንዲሰጥ ማስቻል" የሚለውን ጨምሮ በአምስት የድርድር ዓላማዎች ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

"ሥልጣን በምርጫ ሥርዓት ብቻ አሸናፊ ለሆነው የፖለቲካ ፓርቲ  የሚተላለፍበትን ወሳኝ ምዕራፍ በሀቀኝነትና በቁርጠኝነት ተነስተን እውን እንዲሆን የድርሻችንን ለመወጣት ነው" የሚለው ሃሳብ የድርድሩ አጀንዳ እንዲሆን ተወስኗል።

ፓርቲዎቹ ከዚህ በፊት ባደረጉት ስምምነት መሰረት የዛሬው ውይይት በኢህአዴግ የተመራ ሲሆን፤ መገናኛ ብዙሃንም በስብሰባው እንዲገኙ ተደርጓል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባደረገው የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ማጠቃለያ ላይ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል በአገሪቷ በህጋዊ መንገድ ከተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት፣ ክርክርና ድርድር ማድረግ የሚለው ይገኝበታል።

ፓርቲዎቹ በቀሪዎቹ ጉዳዮች ላይ ለመወያየትና ረቂቅ ደንቡን ለማፅደቅ ለየካቲት 30 ቀን 2009 ዓ.ም ቀነ ቀጠሮ ይዘዋል።

Published in ፖለቲካ

የካቲት 24/2009 በህንዳውያን የእደ ጥበብ ባለሙያዎች በእጅ የተሰሩ አልባሳት ኤግዚቢሽን ዘ ሲንቴቲክ ኤንድ ራዮን ቴክስታይል ኤክስፖርት ፕሮሞሽን ካውንስል በተሰኘ የህንድ ኩባንያ በኢትዮጵያ ሊካሄድ መሆኑን ያርን ኤንድ ፊበር ድረ ገፅ አስነብቧል፡፡

ኤግዚቢሽኑ የህንድ መንግስት የወጪ ንግድ ማበረታቻ የ 2016-17 ፕሮግራም አካል መሆኑ ተነግሯል፡፡

ኤግዚቢሽኑ በኢትዮጵያ በሚገኘው የህንድ ኤምባሲ፣በህንድ የንግድና የጨርቃ ጨርቅ ሚኒስቴር፣በአገር ውስጥ ነጋዴዎችና በኢትዮጵያ መንግስት እገዛ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቲዩት፣የንግድ ምክር ቤት፣የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ማህበር የጋራ ትብብር የሚዘጋጅ መሆኑን ድረ ገፁ ጠቅሷል፡፡

ተሳታፊዎቹ ብዛት ያላቸው በእጅ የተሰሩ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን ለእይታ የሚያቀርቡ ይሆናል፡፡ከምርቶቹ መካከል የተዘጋጁ የሹራብ ክሮች፣ቀሚሶች፣ሙሉ ልብስ፣ሸሚዞች እና የስፌት መሳሪያዎች ይገኙበታል፡፡

ዝግጅቱ በኢትዮጵያ ለሚገኙ አስመጪዎች ፣ገዢዎችና ወኪሎች ትልቅ እድል የሚፈጥር ሲሆን የሚፈልጉትን አልባሳት የምርት መመዘኛቸውን መሰረት በማድረግ ከህንድ የጨርቃ ጨርቅ እደ ጥበብ ባለሙያዎች ለማግኘት እንደሚረዳቸው ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ቢ2ቢ የተሰኘ መርሐ ግብር በማዘጋጀት በህንድ ላኪዎችና በኢትዮጵያ አስመጪዎች መካከል በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ግንኙነት ለመመስረት ጥረት እንደሚደረግ ድረ ገፁ አስነብቧል፡፡

ከህንድ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርት ውስጥ በእጅ የተሰሩ ልብሶች 10 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡ከኤምባሲው የተገኘ መግለጫ እንደሚያሳየው ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የህንድ አልባሳት ምጣኔ መጨመር ቢያሳይም በእጅ የተሰሩ አልባሳት ድርሻ ግን ዜሮ ነው፡፡

 ዘ ሲንቴቲክ ኤንድ ራዮን ቴክስታይል ኤክስፖርት ፕሮሞሽን ካውንስል የህንድ ጨርቃ ጨርቅ ላኪዎችን ባህር ማዶ ከሚገኙ ገዢዎች ጋር በማገናኘት በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ኤምባሲው አስታውቋል ፡፡

ካውንስሉ በኢትዮጵያ የሚገኙ ገዢዎችንና አስመጪዎችን የመደገፍ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቆ በመጪዎቹ አመታት በሁለቱ አገራት የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን በንግድ የማስተሳር ስራዬን አሳድጋለሁ ማለቱ ተገልጿል፡፡

ኤግዚቢሽኑ የካቲት 27 እና 28 -2009 በሼራተን አዲስ ላሊበላ አዳራሸ እንደሚከናወን ከድረ ገፁ ያገኘነው ዘገባ ያሳያል፡፡

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን