አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 21 March 2017

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2009 የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር በግብርና ግብዓቶች አቅርቦትና ጥራት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን እንዲያስወግድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአገሪቷን የመስኖ አቅም አሟጦ ለመጠቀም መስራት እንዳለበትም አስገንዝቧል።

የምክር ቤቱ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይህን ያለው የሚኒስቴሩን የ2009 በጀት ዓመት የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ካደመጠ በኋላ ነው።

ሚኒስቴሩ በግብርናው ሽግግር መፋጠን፣ በልማት ሠራዊት ግንባታ እንዲሁም በግብርና ግብዓቶች አቅርቦትና ጥራት ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን መፍታት እንዳለበት ተነግሯል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መሰለ አገሪቷ ካላት እምቅ የመስኖ አቅም አንጻር በሚፈለገው መጠን አለመሰራቱን ተናግረዋል።

"ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተለይም በግብርና ግብዓቶች አቅርቦትና ጥራት ላይ ክፍተቶች የሚስተዋሉ በመሆኑ በቀጣይ ችግሮቹ ሊፈቱ ይገባል" ብለዋል።

አርሶ አደሩ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆን የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አመልክተዋል።   

ሴቶች ከግብርና ማቀነባበሪያ ሥራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ሚኒስቴሩ የተጠናከረ ሥራ ሊሰራ ይገባልም ተብሏል።

ሚኒስቴሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና መረጃዎችን በማውጣት ረገድ ያከናወናቸውን ተግባራት ምክር ቤቱ በጠንካራ ጎን አስቀምጧቸዋል።

የተፋሰስ ሥራን በተቀናጀ የሕብረተሰብ ንቅናቄ መከወኑና ለውጥ ማምጣቱንም እንዲሁ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢያሱ አብርሃ “ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት በበጀት ዓመቱ ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በአነስተኛ መስኖ ለማልማት ታቅዶ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር ለምቷል” ብለዋል በሪፖርታቸው።

በዚህም ከስድስት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ1 ሚሊዮን 470 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን ከውጭ የሚገዛ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት በዓይነትና በመጠን ተሰብስቧል።

እንደ ዶክተር ኢያሱ ገለጻ በአገሪቷ ያጋጠመውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ስርጭት ችግር ለመፍታት ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም የዘር ስርጭት የመፍትሄ ሰነድ ተዘጋጅቷል።    

የአፈር ኃብትና ለምነትን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም የሚፈልገውን ምጥን ማዳበሪያ ለማቅረብ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች ከሚገኙ 58 ወረዳዎች የአፈር ናሙና መሰብሰቡንም ዶክተር ኢያሱ ተናግረዋል።

በእስካሁን ሂደት "የ655 ወረዳዎች የአፈር ናሙና ተሰብስቧል" ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት በቴክኖሎጂ መረጃ አቅርቦት 92 የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችና መረጃዎችን ለማውጣት ታቅዶ 91ዱን ማሳካት ተችሏል።

ኢትዮጵያ በከርሰና ገጸ ምድር ውሃ በመስኖ ሊለማ የሚችል ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ያላት ቢሆንም በተገቢው መንገድ አልምቶ ጥቅም ላይ ማዋል ላይ ክፍተቶች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ።  

በሌላ ዜና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው መደበኛ ስብሰባው በኢትዮጵያና ቻይና መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳይ ግለሰቦችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ለህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በአገራቱ መካከል በፍትሃ ብሄርና በንግድ ጉዳዮች ላይ በተደረገው የትብብር ስምምነት  የቀረበውን ረቂቅ አዋጅም እንዲሁ።

Published in ኢኮኖሚ

ሆስዕና መጋቢት 12/2009 በሀዲያ ዞን 4ሺ700 ሄክታር  መሬት የሚሸፍን  አዲስ የቡና ችግኝ ተከላ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን  የዞኑ  የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በጽህፈት ቤቱ የቡና ሻይ ቅመማ ቅመም ባለሙያ አቶ አስራት ሽፈራው ለኢዜአ እንደገለፁት ተከላው የሚካሄደው ልማቱን ለማስፋፋት በመጪዎቹ ሚያዝያና ሰኔ ወራት ሲሆን  17 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ተዘጋጅቷል፡፡

በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የተዘጋጁት እነዚህ የቡና ችግኞች  ከምርምር ማዕከላት የወጡና በሽታ ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"አዲስ ለሚካሄደው የቡና ችግኝ ተከላ ከወዲሁ የጉድጓድ ቁፋሮና ተጓዳኝ የማሳ ዝግጅት ስራዎች በመካሄድ ላይ ናቸው" ብለዋል።

አዲስ የሚተከሉት ችግኞች የዞኑን  የቡና ልማት ሽፋን ወደ 20 ሺህ 700 ሄክታር ከፍ እንደሚያደርጉት የሚጠበቅ መሆኑን ባለሙያው አመልክተዋል፡፡

በዞኑ በሶሮ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ደምሴ አረጋ በሰጡት አስተያየት ነባር ማሳቸውን በተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች መተካት ከጀመሩ ወዲህ  በሄክታር ያገኙት የነበረው አራት ኩንታል የቡና ምርት በእጥፍ መጨመሩን ተናግረዋል።

ዘንድሮም በተጨማሪ ማሳ ላይ ቡና ለመትከል የሚያስችላቸውን 100 ጉድጓድ ቆፍረው የዝናቡን መጣል በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።

ሌላው የወረዳው አርሶአደር ልሳኑ ጥላሁን በኩላቸው "'በዚህ ዓመት አዳዲስ የቡና ዝርያዎችን ለመትከል 144 ጉድጓዶችን ቆፍሬያለሁ" ብለዋል ።

በዞኑ 44 ሺህ የሚሆኑ ቡና አምራች አርሶ አደሮች እንዳሉ ከዞኑ የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2009 የስትራቴጂክ መጠባበቂያ ምግብ ክምችት ኤጀንሲ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም 600 ሺህ ዶላር ዋጋ ያላቸው የእህል ጥራት መጠበቂያ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገለት።

የእህል ጥራት መፈተሻ፣ ማበጠሪያና ማሸጊያ፣ መሰላል፣ ሚዛን፣ የተባይ ማጥፊያ መድሃኒት መርጫ፣ የአፍላቶክሲን መለኪያ፣ የደህንነት መጠበቂያና ሶስት ተሽከርካሪዎች ለኤጀንሲው ከተሰጡ መሳሪዎች መካከል ናቸው።

በኤጀንሲው የጥራት ቁጥጥር ስራ አመራር ዳይሬክተር አቶ አለም ወልዴ "ኤጀንሲው ከተቋቋመ ረጅም ዓመት ቢሆነውም በአቅም ውስንነት ሳቢያ ረጅም ጊዜ ያገለገሉ የጥራት መፈተሻ መሳሪያዎቹን መቀየር አልቻለም" ብለዋል።

በድጋፍ የተገኙት መሳሪያዎች ዘመናዊ በመሆናቸው ከውጭ የሚገቡና የአገር ውስጥ እህሎች ወደ መጋዘን ከመግባታቸው በፊትና ከገቡም በኋላ ጥራታቸው መጠበቁን ለማረጋገጥ ያግዛሉ።

መሳሪያዎቹ የኤጀንሲውን የእህል ክምች ጥራት አስተማማኝ ለማድረግ እንደሚያግዙም ገልጸዋል።

መሳሪያዎቹ አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሽንሌ፣ ኮምቦልቻ፣ ወረታና መቀሌ ለሚገኙት የኤጀንሲው መጋዘኖች ይከፋፈላሉ ተብሏል።

በኢትዮጵያ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ተጠሪ ጆን አይሊፍ መሳሪያዎቹ ኤጀንሲው ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ  የሚያከማቸውን እህል ጥራት ማስጠበቅ እንደሚያስችለው ተናግረዋል።

በቀጣይም "ከኤጀንሲው ጋር በሰው ሃይል ልማትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በጋራ እንሰራለን" ብለዋል።

የኤጀንሲው ሰራተኞች ስለ መሳሪያዎቹ አጠቃቀም ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ ከስዊዘርላንድና ቤልጂየም በመጡ ባለሙያዎች ስልጠና እንደሚሰጣቸው ከኤጀንሲው የተኘው መረጃ ያመለክታል።

ኤጀንሲው ብሄራዊ የስትራቴጂክ መጠባበቂያ ምግብ ክምችት አቅምን ለማሳደግ በ2010 ዓ.ም በሻሸመኔ፣ ፍኖተ-ሰላም፣ ባሌ ሮቤ፣ ነቀምት፣ ሆሳዕና፣ ነገሌ ቦረናና ቀብሪደሃር መጋዝኖች ለመገንባት አቅዷል።

አዲስ የሚገነቡት መጋዘኖች ከ892 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ እህል ማከማቸት የሚችሉ ሲሆን የነበረውን ብሄራዊ የእህል ክምችት አቅም ወደ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ያሳድጉታል።

Published in ኢኮኖሚ
Tuesday, 21 March 2017 22:34

የጋዜጠኛው ገመና

ገብረህይወት ካህሳይ

ጋዜጠኝነት ዋናው ባህሪው ትክክለኛነት ፣ ሀቀኝነት ፣ ፍትሃዊነት ፣ ሚዛናዊነት ህዝባዊ አገልጋይነት ፣ ለተበደለው ወገን ጥብቅና መቆምንና የተደበቀውን ገሃድ በማውጣት የህዝብን የመረጃ ጥማት ማርካት ነው ።

የዚህ ፅሁፍ መነሻ የጋዜጠኝነት ሀሁ መስበክ ሳይሆን የጋዜጠኝነት ካባ ለብሰን የምንፈፅማቸው ጥፋቶችን በመጠቆም ሙሉ በሙሉ ባይቀረፉም ለመቀነስ ይረዳል ከሚል መነሻ ነው ።

ጋዜጠኝነት የራሱ የሆነ የስነ ምግባር መርህ ያለው ክቡር ሙያ መሆኑን ከትምህር ቤት ጀምሮ እስከ ስራ ስምሪት ድረስ ተደጋግሞ ቢነገርም  ቅጥ በአጣ መልኩ ሲጣስ ተመልክቻለሁ ።

የጋዜጠኛው በራስ የመተማመን መንፈስ የተልፈሰፈሰ ሆኖ  የሚታይበት አጋጣሚም ይስተዋላል ። በሚሰራበት ተቋም አለአግባብ በደል ሲደርስበት ፊት ለፊት ተጋፍጦ ችግሩን መፍታት እየቻለ አንገቱን ደፍቶና አቀርቅሮ የሚወጣ ብዙ ነው ።

በረንዳ ከበረንዳ እየዘለልን ወሬ ማራገብ ግን እንችልበታለን ።  ለመሆኑ ለመብታችን መቆም ካቃተን እንዴት የህዝቡን መብት ለማስከበር አጀንዳ ቀርፀን ፣ ቴፕ ፣ ማስታወሻና ካሜራ ይዘን ወደ ህዝቡ እንገባለን ? ።

እራሱን ከህግ አውጪው ፣ ህግ ፈፃሚውና ህግ ተርጓሚው አካል ቀጥሎ 4ኛው የመንግስት አካል እንደሆነ ሲተነትን እየዋለ በተግባር ግን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ስራ ቀምቶ የሚመለስ ጋዜጠኛ ብዙ ነው ።

በናይጀሪያ ተስፋፋ የተባለው የቡናማ ኢንቮሎፕ  (Brown Envolop)  ጋዜጠኝነት መጠኑ የገነነ ባይሆንም በአገራችንም ግን እየተዛመተ መምጣቱን የሚጠቁሙ ምልክቶች  አሉ ። ቡናማ ኤንቨሎፕ በዋነኛነት ከባለ ጉዳዩ ደህና አበል ሲከፈልህ  ዜናና ፕሮግራም ሞቅ አድርጎ መስራት ያካትታል ። ክፍያዋ ቀዝቀዝ ካለች ደግሞ የሚዲያ ሽፋኑን ማሽመድመድ ያካትታል ።

በሀገራችን የጋዜጠኝነት ዘርፍም አበል መውሰድ እንደ መብት እየተቆጠረ ነው ። እንዲያውም  “ ብጨ” የሚል ስም ተለጥፎባታል ። በአንድ ታዋቂ ሚዲያ የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ ላይ አበል እንደ መብት ወስዶ መጠየቅ ተገቢ አይደለም የሚል ሃሳብ ተነስቶ ነበር ።

ጥቂት ጋዜጠኞች የሰጡት ሃሳብ ግን አሳዛኝም አስቂኝም ነበር  ። “ ብጨ” ብሄራዊ ጨዋነት ብለው አቆላመጥዋት ። ያለ ብጨማ መኖር ከባድ ነው “ በማለት አበልን ህጋዊ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ ነበረው ።

ከተወሰኑ ጥቂት ሚዲያዎች የሚመጡ ጋዜጠኞች ደግሞ ዓይን ያወጣ መንገድ ይከተላሉ ። ለአንድ ስራ አራትና አምስት ሆነው ይመጣሉ ። በእርግጠኝነት ተቋሙ የሰው ሀይል ተትረፍርፎበት እነዚህን ሁሉ ጋዜጠኞች አይልክም ። በድብቅ “ ብጨ” ለማሳደድ በጓደኝነት የተጠራሩ ናቸው ።

በአንዳንድ ትላልቅ ሆቴሎች ትላልቅ አገራዊ አጀንዳ የያዙ ዓውደ ጥናቶች ፣ የምክክር መድረኮችና ስልጠናዎች እንደሚካሄዱ ይታወቃል ። የሚዲያ ተቋማት ዜና አሊያም ፕሮግራም እንዲያመጡላቸው ጋዜጠኞችን መላክ የተለመደ ነው ። ጥቂት ከሙያው ስነ ምግባር ያፈነገጡ ጋዜጠኞች የሆቴሉን ዋይፋይ (Wi-Fi) ሲጠቀሙ ይውሉና የሃላፊዎችን ንግግር ብቻ ተቀብለው ተራ ሪፖርት ያቀርባሉ ።

ሌላው በትላልቅ ሆቴሎች በሚዘጋጁ ስብሰባዎች ከስራው ይልቅ ሆዳቸውን የሚያስቀድሙ ጋዜጠኞች መታየታቸው ነው ። እነዚህ (Cocktail journalists) እራሳቸውን ትእዝብት ውስጥ ጥለው የመጡበትን ተቋም የሚያሰድቡ ናቸው ።

ገንዘብ ብቻ እንጂ የጋዜጠኝነት ሙያ ይዘት ጠንቅቀው ሳያውቁ የተቀላቀሉ አንዳንድ ጋዜጠኞች ደግሞ “No Money No News ” በሚል የተዛባ እሳቤ በጅምር ያለውን ክቡር ሙያ ከድጡ ወደ ማጡ ሲያወርዱት ይስተዋላል ።

ሙያዊ አቅም አንሷቸው የሚንገዳገዱ አንዳንድ ጋዜጠኞች አሰሪው ተቋም ኢንቨስት አድርጎ በሚያዘጋጀው ስልጠና ላይ አካላቸውን ብቻ አስቀምጠው የሞባይል ጌም ሲጫወቱ ውለው የሚወጡም ታይተዋል ።

ታዲያ ! እኛው ጋዜጠኞች እንዲህ ከሆንን በእኛው ላይ የምርመራ ጋዜጠኝነት ስራውን ማን ይሰራው ይሆን ?። ወይስ አይናችንን የምናይበት ሌላ ዓይን ይመጣ ይሆን ?።

ማሳሰቢያ፡-ይህ አስተያየት ከራሴ የ25 ዓመታት ቆይታ የታዘብኩት እንጂ የምሰራበት ተቋምን አይወክልም ። እራሳችንን አይተን መውቀስ ብንጀምር ግን ሊጠቅመን ይችላል ።

 

 

Published in ዜና ሓተታ

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2009 በአርብቶ አደር ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ተቋማትን የሚያስተባብር የፖሊሲና ስትራቴጂ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ገለጸ። 

ሚኒስቴሩ እየተዘጋጀ ባለው ማዕቀፉ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል። 

የሚኒስቴሩ የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ጄኔራል ሻንቆ ደለለኝ እንደተናገሩት ማዕቀፉ በአርብቶ አደር ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ተቋማትን በአንድ ላይ ለማሰባሰብ ያለመ ነው። 

ማዕቀፉ ከተለያዩ ምንጮች የሚገኝ ገንዘብና ሌሎች ኃብቶች በአንድ ቋት የሚተዳደሩበትና ለፕሮጀክቶች ፈሰስ የሚሆንበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም ይረዳል።

"ይህም ተቋማቱ እርስ በእርስ እንዲናበቡና እንዲደጋገፉ በማድረግ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ዘላቂነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ እገዛ ያደርጋል" ብለዋል። 

እንደ ዳይሬክተር ጄኔራሉ ገለጻ በማዕቀፉ ውስጥ 13 ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ሲኖሩ ከመካከላቸው የውኃ እቀባን መሰረት ያደረገ የመስኖ ልማት ተጠቃሽ ነው።

የመስኖ ልማት ሥራው የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውኃን በአግባቡ መጠቀምን ያካትታል።

በአርብቶ አደሩ መልካም ፍቃድ ላይ በመመርኮዝ የመንደር ማሰባሰብ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠልም አዲሱ ማዕቀፍ ያካተተው ሌላው ጉዳይ ነው።

በተጓዳኝም ዘላቂ ልማት ማፋጠን የሚያስችል የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ማሟላት የሚያስችሉ ሥራዎች ይተገበራሉ።

ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ ማዕድናትና ሌሎች የተፈጥሮ ኃብቶችን መጠቀም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ላይ ትኩረት እንደሚደረግም ዳይሬክተር ጄኔራል ሻንቆ ገልጸዋል።

በአርብቶ አደር አካባቢዎች ያሉ ሥራዎች በጥናትና ምርምር መታገዝ እንዳለባቸው ጠቅሰው በዚህ ረገድም ተጨባጭ ሥራ ለመከወን ማዕቀፉ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

ማዕቀፉ ስራዎችን ለባለድርሻ አካላት ከፋፍሎ በመስጠት በታቀደላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲጠናቀቁ የሚያስችል መሰረት እንደሚጥል ታምኖበታል። 

ይህም በብሄራዊ ደረጃ የሚስተዋለውን የኃብት ብክነትና የሥራ ድግግሞሽ እንደሚያስቀር ዳይሬክተር ጄኔራሉ ጠቁመዋል። 

በኢትዮጵያ የጀርመኑ ፍሬድሪች ኢበርት ስቲፍቱንግ ተቋም ተወካይ ኮንስታንቲን ግሩንድ በበኩላቸው "ዘርፉ በጥናትና ምርምር መታገዝ አለበት" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመስኩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በስፋት እንዲከናወኑ ተቋሙ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ አምስት ክልሎች 149 ወረዳዎች 12 ሚሊዮን አርብቶ አደሮች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ መጋቢት 12/2009 በሀገሪቱ የቁም እንስሳት ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን  ለማስወገድ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊረባረቡ እንደሚገባ  የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ሚኒስቴር አሳሰበ።

ሚኒስቴሩ ከኦሮሚያ ክልል ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት " በቁም እንስሳትና በጥሬ ቆዳና ሌጦ የግብይት የህግ ማዕቀፍ" ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያዘጋጀው መድረክ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለባቸው ንጉሴ እንደገለጹት በሀገሪቱ በአርብቶ አደሩና በሌሎችም አካባቢዎች የቁም እንስሳት ግብይት ላይ በርካታ ችግሮች  አሉ።

ከችግሮቹም መካከል ቅድሚያ የሚሰጠው የግብይት ሥርዓቱ ሃገሪቱ ስለ ቁም እንስሳት ግብይት ባወጣችው ህግና የአፈፃጸም አቅጣጫ መሠረት ስራ ላይ አለመዋሉን ጠቅሰዋል።

በግብይት ስርዓቱ ላይ የግልፅነት መጓደል ፣ የግብይት አዋጁን ለመተግበር ቁርጠኝነት ማነስ፣ በተዋናዮቹ፣ በአገልግሎት ሰጪው፣ በተቆጣጣሪ እና በህግ አስከባሪው ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት በስፋት መኖሩና ይህን ታግሎ ለማስተካከል አለመድፈር ሚኒስትር ዴኤታው  ያመለከቷቸው ሌሎቹ ችግሮች ናቸው።

ዘርፉ ለአገር እድገትና ልማት፣ ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ  ከፍተኛ ሆኖ እያለ በአስተሳሰብ ደረጃ  የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች መካከል በንግድ ፈቃድ፣ መሸኛ፣ ህጋዊ ግዥ ደረሰኝ  አሰጣጥና በሌሎችም ተመሳሳይ አሰራርና ቁጥጥር አለመኖርም ተጠቁሟል።

ሚኒስትር ዴታው እንዳሉት በተለይ አርብቶና አርሶ አደሩ ስለ እንስሳቱ ትክክለኛ የዋጋ መረጃ የሚያገኝበት ወጥነትና ግልጽነት ያለው አሰራር አለመኖር በአካባቢው ባገኘው ዋጋ ለመሸጥ ይገደዳል።

የኮንትሮባንድና ህገ ወጥ የእንስሳት ንግድ በመስፋፋቱም አርቢው ማህበረሰብ የልፋቱን ያህል ተጠቃሚ እየሆነ አይደለም።

" በነዚህ ምክንያቶች ወደ ውጭ የምንልካቸው የቁም እንስሳትና ለኤክስፖርት ቄራዎች የምናቀርባቸው  የእርድ እንስሳት የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ እየሆነ አይደለም " ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ለዚህ ማሳያ ያደረጉት ባለፉት ስምንት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የቁም እንሰሳት የተገኘው ገቢ 48 ሚሊዮን ዶላርና ይህም የእቅዱን 18 በመቶ ብቻ መሆኑን ነው።

በተጠቀሱት ወራት ለውጭ ገበያ የቀረበው የሥጋ ምርት አፈፃፀሙም የእቅዱን 60 በመቶ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለማስወገድ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትና የግብይቱ ተዋናዮች ተቀናጅተው በቁርጠኝነት መረባረብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ዓላማም የሚመለከታቸው አካላት ግዴታቸውን እንዲወጡ፣ አርሶና አርብቶ አደሩ በቀጣይ ከእንስሳት ሀብቱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ ጠንካራ የግብይት ስርዓት ለመዘርጋትና ህገወጥነትን በጋራ ለመከላከል ያለመ መሆኑም ጠቁመዋል።

ይሄው መድረክ በሌሎች ክልሎች እንደሚቀጥል ተመልክቷል፡፡ 

በኦሮሚያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የቁም እንስሳትና እንስሳት ተዋፅኦ ግብይት ሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ለማ አጀማ በበኩላቸው በእንስሳትና በእንስሳት ተዋጽኦ ግብይት ላይ ማነቆ የሆኑ የአመለካከትና የግንዛቤ ችግሮችን በመለየት  ለውጥ ለማምጣት የተደራጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ ከኦሮሚያ ክልል አርብቶ አደር ዞኖች የተውጣጡ የዘርፉ ተዋናዮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2009 እየተስፋፋ የመጣውን የስኳር ህመም ለመከላከል ሕብረተሰቡ ወቅታዊ የጤና ምርመራና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር እንዳለበት የኢትዮጵያ ስኳር ሕሙማን ማኅበር አሳሰበ።

ከአገሪቷ ሕዝብ ከአምስት እስከ ሰባት በመቶ የሚሆነው የስኳር ህመም እንዳለበት በመስኩ የተካሄዱ ጥናታዊ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የማኅበሩ የፕሮግራሞች ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ምስራቅ ታረቀኝ ለኢዜአ እንደገለጹት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመላ አገሪቷ የስኳር ህመምተኞች ቁጥር እየጨመረና አሳሳቢ የጤና ችግር እየሆነ ነው።

በሽታው በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እየጎዳ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ማኅበሩ ከጤና ተቋማት ጋር በመተባበር ከ3 ሺህ 500 በላይ ለሆኑ ህጻናት ኢንሱሊን እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በአገሪቷ በብዛት የሚታየው ሁለተኛው አይነት የስኳር ህመም መሆኑንና ይህም ቆሽት የተባለው የሰውነት ክፍል በቂ ኢንሱሊን ማምረት ሲያቆም ወይም በአግባቡ ሳይሰራ ሲቀር የሚከሰት እንደሆነ ጠቁመዋል።

የስኳር ሕመም ሐኪም ዶክተር አህመድ ረጃ በበኩላቸው በሽታው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና በዓለም በከፍተኛ ፍጥነት  አየተስፋፋ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያም በህጻናት ላይ ጭምር በስፋት እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

የኅብረተሰቡ የአኗኗርና የአመጋገብ ዘይቤ መቀየር እንዲሁም በቂ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ ከበሽታው መስፋፋት መንስኤዎች መካከል ጠቅሰዋል።

ከአርባ ዓመታት በፊት በዓለም ላይ 30 ሚሊዮን ያህል የስኳር ሕሙማን እንደነበሩ ያስታወሱት ዶክተር አህመድ ይህ አሃዝ በአሁኑ ወቅት ወደ 400 ሚሊዮን ማሻቀቡን ገልጸዋል።

በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ ወቅታዊ የጤና ምርመራና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሊያዘወትር እንደሚገባ ዶክተር አህመድ መክረዋል።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቡድን ባለሙያ ዶክተር ሙሴ ገብረ ሚካኤል የስኳር ህመም በአገሪቷ አሳሳቢ የጤና ችግር በመሆኑ ሚኒስቴሩ በሽታውን አስቀድሞ ለማወቅና ለማከም የሚረዳ የመረጃ መመሪያ አዘጋጅቶ በህትመት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የበሽታውን መስፋፋት ለመቀነስ ኅብረተሰቡ ጣፋጭ ምግቦችን አብዝቶ እንዳይመገብና በየዕለቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርግም ዶክተር ሙሴ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ከናጄሪያና ደቡብ አፍሪካ በመቀጠል በስኳር ህመም መስፋፋት ከአፍሪካ በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ጥናቶች ያመለክታሉ።

Published in ማህበራዊ

መጋቢት 12/2009 ዓ.ም በሁሉም ንግድ ባንኮች 1 የአሜሪካን ዶላር በ22 ብር 7084ሳንቲም እየተገዛ በ23 ብር ከ1626ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡የእንግሊዝ ፓውንድ ስተሪሊንግ በ28 ብር ከ1107 ሳንቲም እየተገዛ በ28 ብር ከ6729 ሳንቲም እየተሸጠ ነው፡፡ 
የወርቅ ዋጋን ስንመለከት ደግሞ 24 ካራት አንድ ግራም ወርቅ በ942ብር ከ8218ሳንቲም ሲሸጥ ባለ14 ካራት ደግሞ549ብር ከ9794ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡የሌሎችን ሃገራት የምንዛሬ ዋጋና የወርቅ ዋጋ በተከታዩ ሰንጠረዥ ይመልከቱ፡-

No automatic alt text available.

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ መጋቢት 12/2009 ባለፉት ስምንት ወራት ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን  አስታወቀ፡፡

በኮሚሽኑ የስምንት ወራት የስራ አፈጻጸም ላይ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ውይይት ተካሄዷል።

የኮሚሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባስ መሀመድ በዚሁ ወቅት  እንደገለፁት ፈቃድ የተሰጠው  በክልልና በፌደራል ደረጃ ቀርበው ለተመዘገቡ 153 ባለሀብቶች ነው፡፡

ከእነዚህም ውስጥ በግብርና ፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ የገቡ ባለሀብቶች እስካሁን ከ50 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡

በግብርና መስክ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከተዘጋጀው  6ሺህ 483 ሄክታር የገጠር መሬት ውስጥ  ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ ለሚሆነው የይዞታ ማረጋገጫ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ አባስ ገለፃ  ለባለሀብቶች ለስራ አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎችን  ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ።

በገቡት ውልና በተቀመጠላቸው ጊዜ ወደ ስራ ያልገቡ 46 ባለሀብቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመው  ሶስት ባለሀብቶች ደግሞ የተሰጣቸው የመሬት መጠን እንዲቀነስባቸው መደረጉንም ጠቁመዋል።

"በግብርና መስክ የተሰማሩ ስምንት ባለሀብቶችም የተሰጣቸው የመሬት ኪራይ ውል ተሰርዟል" ብለዋል።

በክልሉ በገጠርና በከተማ ለኢንቨስትመንት አገልግሎት የሚውል መሬት በመለየት ለባለሀብቶች የማስተዋወቅ ስራ እየተካሄደ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

                                       ገብረህይወት ካህሳይ (ኢዜአ)

በዓለማችን  ከ15 እስከ 24 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል የሚገኙ 1ነጥብ 2 ቢሊዮን ወጣቶች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ ። ይህ ቁጥር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ 2030 ድረስ በየዓመቱ 7 በመቶ እያደገ ይሄዳል ተብሎም ተገምቷል ።

 

በአህጉራችን አፍሪካም ቢሆን 880 ሚሊዮን ከሚጠጋው አጠቃላይ ህዝብ ውስጥ 226 ሚሊዮን የሚጠጋው  ከ15 እስከ 24 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሃይል ነው ፣ ይህ ቁጥር ከዓለማችን የወጣቶች ቁጥር አንፃር 19 በመቶውን ይይዛል ።

 

የአፍሪካ የወጣቶች ቀጥር እስከ 2030 ድረስም 42 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል ። እስከ 2055 ደግሞ በእጥፍ ይጨምራል የሚሉ ጥናቶች እየወጡ ነው።

 

በአገራችን ኢትዮጵያ ወጣቶች ተብለው የሚጠሩት ከ15 እስከ 29 ዓመት የእድሜ ክልል የሚገኙ ሲሆን ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥር 34 በመቶ ድርሻ አላቸው። በየዓመቱ 2 ሚሊዮን ህፃናት ወደ ወጣትነት የእድሜ ክልል ይሸጋገራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

 

ይህ ሰፊ የሰው ሀይል በአግባቡ ከተያዘና ከለማ በሀብት ላይ ሀብት እየጨመረ የሚሄድ የኢኮኖሚው ዋና መዘውር ነው። የዴሞክራሲና የልማት አንቀሳቃሽ መሰረትም ሆኖ ያገለግላል። በአግባቡ ካልተያዘ ግን ድንገት ሊፈነዳ የሚችል ቦንብ መሆኑን በአረቡ ዓለም በተለይ ደግሞ በየመን ፣ በግብፅ ፣ በቱኒዝያና በአፍጋኒስታን  የቀለም አብዮት እንቅስቃሴ በግልፅ ታይቷል ።

 

በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የወጣቶች ማካተትና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ማትያስ አሰፋ መጠኑ ይለያይ እንጂ በአገራችንም  ቢሆን መታየቱ አልቀረም ይላሉ ። ወጣቱ የሚገባውን ያህል ሳያገኝ የቆየ የህብረተሰብ ክፍል ነው። የወጣቱ ፍላጎት የተለያየና በየጊዜው ሊለዋወጥ የሚችል በመሆኑ ተከታተሎ  ጥያቄዎቹ በፍጥነት  እንዲመለሱለት ይፈልጋል።

 

ወጣቱ ሀይል ስራ መስራት ይፈልጋል። የመማር ጉጉት አለው። መዝናናት ያስደስተዋል። ደህንነቱ ተጠብቆ ተሳትፎውን ማጎልበት ይሻል። እውቅና ማግኘት ይናፍቃል። በሰላም ተረጋግቶ መኖር የምንጊዜም ምርጫው ነው።  የጤና አቅርቦት እንዲሟሉለት ይመኛል። ፍትህና እኩልነትን አጥብቆ  ይፈልጋል። እነዚህ ሲጓደሉበት ደግሞ ይከፋል ።

 

የነገ ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳይሆን የዛሬው አገር አንቀሳቃሽ ጭምር በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው  ግድ ይላል ። ለዚህም ነው  መንግስት የወጣቶች የልማትና የእድገት ስትራተጂ ቀርፆ ወደ ተግባር የገባው ።

 

 ለዚህም ነው ካለችው ውሱን  ሀብት 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መድቦ ስራ አጥ ወጣቶች ወደ ስራ ለማስገባት ደፋ ቀና እያለ ያለው።

 

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ እርስቱ ይርዳው ለኢዜአ እንደገለፁት የወጣቶች የልማትና የእድገት ስትራቴጂ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ ወደ ትግበራ ተሸጋግሯል ።

 

በስትራቴጂው የዝግጅት ምእራፍ  በህብረተሰቡና በወጣቱ ዘንድ በቂ ግንዛቤ የመፍጠር ፣ ምን ያክል ስራ ፈላጊ ወጣቶች እንዳሉና በምን ስራ መሰማራት እንደሚፈልጉ የመለየት ፣ ለስትራተጂው ማስፈፀሚያ የተመደበውን በጀት ደልድሎ ወደ ታች የማውረድና የመስሪያና የመሸጫ ፍላጎት ለይቶ የማወቅ ስራዎች ተከናውነዋል ።

 

በእስከ አሁኑ ሒደት በሁሉም ክልሎች 3 ሚሊዮን ስራ ፈላጊ ወጣቶች ተመዝግበዋል። የማደራጀትና ስልጠና የመስጠት ተግባርም እየተከናወነ ነው። ወደ ስራ የማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ሚኒስትሩ  ተናረዋል። በዚህ ዓመት ብቻ በገጠር  1ነጥብ 7 ሚሊዮን ወጣቶች  በከተማ ደግሞ 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣቶች የስትራቴጂው ተሳታፊና ግንባር ቀደም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል።

 

ስጋቶች ግን አሉ። ለተራቡ ወገኖቻቸው የተላከ የእርዳታ እህል ሰርቀው የሚበሉ አመራሮች ባለባት አገር ገንዘቡን ዘርፈው እንደማይበሉት ምን ዋስትና አለው? ተጠቃሚውስ ወጣት ብቻ መሆኑን ምን ማረጋገጫ አለ? ፍትሃዊነቱንስ እንዴት መመዘን ይቻላል? የሚሉ  ጥያቄዎች  በተደጋጋሚ ይነሳሉ ።  ሚኒስትሩ ግን የመከላከያ መፍትሄ ተበጅቶለታል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

 

“የተመደበው ገንዘብ ሳይሸራረፍ  ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል  የህግ ማእቀፍ ተዘጋጅቶለት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስተዳዳሪነት በየክልሉ ለተመረጡ 11 የፋይናንስ ተቋማት እንዲደርስ ተደርጓል ። አንድም የመንግስት መዋቅር እጁ ላይ የሚደርሰው ገንዘብ የለም። ጎድሎ ቢገኝ እንኳን ተጠያቂ የሚሆኑት በሃላፊነት የተረከቡት የፋይናንስ ተቋማት ናቸው” ብለዋል።

 

እስከ አሁን ድረስ 3 ሚሊዮን ስራ አጥ ወጣቶች ተለይተው መመዝገባቸውን ፣ መደራጀታቸውንና ወደ ስራ ለመግባት ስልጠና መውሰድ መጀመራቸውን ያብራሩት ሚኒስትሩ ምልመላውን ፍትሃዊ ለማድረግ እስከ ታች ድረስ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ ምዝገባው መካሄዱን አስረድተዋል።

 

የበጀት ድልድሉም ቢሆን  ክልሎች ባላቸው ስራ ፈላጊ ወጣት ቁጥር ታሳቢ በማድረግ ተደልድሎ እስከ ታች ድረስ ወርዷል ነበር ያሉት ።

 

ከዚህ ባሻገር የመገናኛ ብዙሃን  ለወጣቶች ከተመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ  ሰባራ ሳንቲም እንኳን እንዳይባክን  መከታተል ፣ ተፈፅሞ ሲገኝ በአግባቡ ማጋለጥና ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዲሰፍን ሙያዊ ሃላፊነታቸው በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ይላሉ።

 

አዲሱ የወጣቶች የልማትና የእድገት ስትራቴጂ ቅድመ ዝግጅት ከማድረግ ጎን ለጎን በነባሩ የወጣቶች የልማት ፓኬጅ በዘንድሮው የመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት ለ600 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል እንደተፈጠረም ሚኒስትሩ አቶ እርስቱ ይርዳ ከሰጡት ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

 

በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የወጣቶች ማካተትና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ማቲያስ አሰፋ እንደገለፁት ደግሞ መንግስት በመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ ዘንድሮ በገጠር 1ነጥብ 7 ሚሊዮን በከተማ ደግሞ 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ቢታቀድም የተመዘገቡት ግን 3 ሚሊዮን ወጣቶች ብቻ ናቸው ። ስለዚህ እድሉ ተፈጥሯልና  ስራ ፈላጊዎች ሊጠቀሙበት ይገባል  ባይ ናቸው ።

 

በእስከ አሁኑ ድረስ በደረሳቸው መረጃ መሰረት ትግራይ ወደ ትግበራ መግባቱንና አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀው ሁሉም ክልሎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ይገባሉ  ብለዋል።

 

ተዘዋዋሪ ፈንዱ ወጣቶችን ማእከል አድርጎ ለወጣት ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ለማህበራዊ ቀውስ ለተጋለጡ ወጣቶችን ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ነው።

 

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ስራ አጥተው የሚውሉ ወጣቶች ቁጥር እየተበራከተ ነውና ስትራቴጂው ያስቀመጠው መፍትሄ ይኖር ይሆን ? ለሚለው ጥያቄ ደግሞ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ  የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ መልስ አላቸው ።

 

’’  በጣት የሚቆጠሩ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ የነበሯት አገር አሁን ከ40 በላይ ደርሰዋል ። ኢኮኖሚያዊ እድገታችንን ሊሸከም የሚችል የተማረ የሰው ሃይል መፍጠር በራሱ ሀብት ነው። ይህን ሀብት ወደ ተግባር ለማሸጋገርም የተለያዩ  እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። መፍትሄው ስራ ፈጠራን ከማበረታታት  እስከ ስራ  መፍጠር የሚደርስ ነው ።’’

 

በወጣቶች የልማትና የእድገት ስትራተጂው ስራ ፈላጊዎችን የመለየት ተግባር ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ማእከላት  የተመረቁ 211 ሺህ ወጣቶች ከዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ደግሞ 80 ሺህ ወጣቶች ተመዝግበዋል። ለመሰማራት የፈለጉበት የስራ መስክ ተጠንቶም ፕሮጀክት ፕሮፖዛል እየተሰራላቸው ነው ። ስለዚህ የእድሉ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ።

 

በአሁኑ ጊዜ እያበቡ የመጡ የኢዱስትሪ ፓርኮችም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚፈሩ ወጣቶችን ተቀብለው መሸከም የሚችሉና ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥሩ ናቸው ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታዋ ያብራራሉ ።

 

መንግስት የሀገራችን ወጣቶች ሀብት እንጂ ስጋት  ናቸው ብሎ አያስብም ። የዛሬ ልማቷን በማፋጠንና የነገዋን ሀገር በመረከብ  ታሪክ መስራት የሚችሉ ሀብቶች ናቸው ብሎ ያምናል ። የቤት ስራው ግን የመንግስት ብቻ መሆን የለበትም ። ሁሉንም የዛሬዋንና የነገዋን ሀገሩን በማሰብ ለወጣቶች ግንባታ የበኩሉን ማበርከት ይጠበቅበታል።

 

የአገራችን የመገናኛ ብዙሃንም ቢሆኑ  በሰፊ ግብረገብነት ከተገነባው ማህበረሰብ አብራክ የተፈጠሩ ወጣቶቻቸውን  በአገር ፍቅር ስሜት ለመቅረፅ  ጠንክረው መስራት አለባቸው። ከልብ ለወጣቱ ክብርና ፍቅር ሰጥተው ከሰሩ የታይዋንና የኮሪያ ሚዲያዎች ካስመዘገቡት አኩሪ ታሪክ በላይ የደመቀ ሌላ አዲስ ታሪክ ሊያፅፉ ይችላሉ ።

 

ለዛሬው ፅሁፌ መሰነባበቻ አንድ የሃይማኖት አባት ሲናገሩ የሰማሁትን ላካፍላችሁ ። ” ወቅቱ 1983 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ነበር ።  የደርግ ሰራዊት ፈርሶ የተበታተነበት  ነው ። የፈረሰው የጦር አባል ወደ ቤቱ ለመመለስ በእግር ረጅም መንገድ ተጉዞ ከተማ ላይ ሲደርስ  ሽጉጥ ፣ ክላሽና ቦንብ ታጥቆም ጭምር ወርቅ ቤት ሄዶ እባካችሁ ራበኝ  አንድ ብር ስጡኝ ብሎ ለመነ እንጂ ለመዝረፍ አልሞከረም “ ነበር ያሉት ።  የህብረተሰባችን የዘመናት የጨዋነት እሴት ውጤት  ነው ። ዛሬም ጨዋ ህዝብ ጨዋ ወጣት መቅረፅ አይሳነውም ። 

Published in ዜና ሓተታ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን