አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 20 March 2017

ከሰለሞን ተሰራ

በኬኒያና ኢትዮጰያ ድንበር ሞያሌና ቦረና አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች በግጭት፣ ድህነትና  ለአካባቢ ጉዳት ተጋልጠው ለረዠም ጊዜ የኖሩ ህዝቦች እንደነበሩ ሮይተርስ የተባበሩት መንግስታት ያወጣውን ፅሑፍ መሰረት በማድረግ ዘግቧል፡፡

አአአ ከ2012 እስከ 2013 በሞያሌ ከተማ በተፈጠረው ግጭት ለበርካታ ሰዎች ሞትና ንብረት ጥፋት  ሆኖ እንደነበር አመልክቷል፡፡

ይህ ችግር ደግሞ ማህበራዊ ተጽእኖውን በማጉላት ነዋሪዎቹን ከመኖሪያ ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉና ፣ ለወንጀልና ለአክራሪዎች መፈጠር ምክንያት ሆኖም እንደነበር ጠቅሷል፡፡

ነገር ግን  በኢጋድና በተባበሩት መንግስታት አጋርነት በኢትዮጵያና በኬንያ መንግስት መካከል በተከታታይና ስር ነቀል በሆነ መንገድ በተከናወነ የድንበር ተሻጋሪ ፕሮግራም ችግሮቹን መቅረፍ ተችሏል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒ ጉቴሬዝ በቅርቡ በኬንያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮ ኬንያ ድንበር ተሻጋሪ ፕሮግራም የተጠቃለለው አካባቢን መሰረት ያደረገ የልማት ፕሮግራም በሌሎች አካባቢዎች ቢተገበር ውጤታማ ተግባር ለማከናወን እንደሚያስችል መናገራቸውን ዘገባው ገልጿል፡፡

የፕሮግራሙ ጅማሮ አካባቢውን ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ተስፋ እንዳላቸው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ለዋና ፀሐፊው ገልጸውላቸዋል፡፡ “ፕሮግራሙ ሞያሌን የአፍሪካ ዱባይ ያደርጋታል”  ብለዋል፡፡

የሁለቱን አገራት ቁርጠኛነት የሚያሳየው መዘርዝር በኢትዮጵያና ኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አዘጋጅነት

ሰላምና ልማትን ለማፋጠን የኢትዮጰያና ኬኒያ ድንበር ተሻጋሪ ኢኒሼቲቭ በሚል ርዕስ  የቀረበ ጽሁፍ ለንባብ በቅቷል፡፡

ኢኒሼቲቩ ድንበር ተሻጋሪ በሆኑት መርሳቤት ካውንቲ ኬንያ እና በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ በቦረና ዳዋ ዞኖች ያለውን ሰላምና ብልፅግና ለማረጋገጥ ያለመ ነው፡፡

በኬንያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ዶክተር ስቴፋኖ ኢጃክ “ እኔ አዎንታዊ ለውጦችን ተመልክቻለሁ፡፡ እናም የአውሮፓ ህብረት ከኢጋድና ከተባበሩት መንግስታት ጋር በመተባበር ድንበር ተሻጋሪ ፕሮግራሙን ለመደገፍ ወስኗል፡፡ፕሮግራሙን ወደ ማንዴራ ሶስት ማዕዘን (ኬንያ-ኢትዮጵያ-ሶማሊያ) ወደ ኦሞ (ኬንያ-ደቡብ ሱዳን) ወደ ካራሞጃ  (ኬንያ-ኡጋንዳ)  ክላስተር ማሳደግ እንሻለን”.ብለዋል፡፡

ከታዩት አዎንታዊ ምልክቶች መካከል በአካባቢው ሰላምን በማስፈን የትብብር መሰረት መጣሉ ይጠቀሳል፡፡ ከተለያዩ ጎሳዎች የተውጣጡት የአካባቢው የሰላም ኮሚቴ አባላት ሰላምና አብሮነት እንዲጎለብት ደከመን ሰለቸን ሳይሉ እየሰሩ መሆናቸውን ዘጋቢው ጽፏል፡፡

በአክራሪነት መንፈስ የተሞሉትን ወጣቶች ከጥፋታችው እንዲቆጠቡ ለማድረግ የአካባቢው ሽማግሌዎች እውነታውን እንዲገነዘቡ እያደረጓቸው ነው፡፡ በዚህም አክራሪና አሸባሪ ድርጅቶችን የሚቀላቀሉ ወጣቶች ቁጥር በእጅጉ መቀነሱን ከፅሑፉ መገንዘብ ችለናል፡፡

የአካባቢውን ባለስልጣኖችና ማህበረሰቡን በማብቃት የድህነት ምጣኔውንና በመርሳቤት ካውንቲ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በመሰራት ላይ መሆኑም ተገልጿል፡፡የኢሶሎ-ሜርሊ-መርሳቤት-ሞያሌ መንገድ በመጠናቀቁ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረውና ድንበር ተሻጋሪ ንግዱንም እንደሚያሳልጠው ዘጋቢው ጠቅሷል፡፡

በተጨማሪ መንገዱ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ግብጽ የሚዘልቀውን   መንገድ ግንባታ  እውን ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ተብራርቷል፡፡

በቀጠናው ያለው እምቅ የማህበራዊ ኢኮኖሚ ልማት እራሱን የቻለ ሐብት ነው፡፡ያልተነካው የቀንድ ከብት ሐብት ለቆዳ  ፣ ለስጋና ለወተት ኢንዱስትሪ መሰረት ነው፡፡በሁለቱ አገራት የድንበር አካባቢ ነዋሪዎች መካከል የሚከወናወነው ድንበር ተሻጋሪ ንግድ  ለሁለቱም አገራት ከፍተኛ ገቢ ያስገኝላቸዋል፡፡

በከተሞቹ ያለው የማህበረሰቦቹ ባህላዊ፣ታሪካዊና አካባቢያዊ ስብጥር የቱሪዝም ሐብትና ያልተበረዙ የኑሮ እውነታዎች የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈ አሰተማማኝ የሆነው የታዳሽ ሐይል እምቅ ሐብት ለአገራቱ ብልፅግና መሰረት መሆን የሚችል መሆኑን ፀሐፊው ጠቅሷል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ይህንኑ ያልተነካ ሐብት በመጠቀም በአካባቢው የሚታየውን ድህነት ለመቀነስ እና በተለያዩ መስኮች ልማትን ለማምጣት እየሰራ ነው፡፡ በተለይ በድንበር ዘለሉ ንግድ በስፋት ተሳታፊ የሆኑትን ሴቶች ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻልም በፀሐፊው ተገልጿል፡፡

የተባበሩት መንግስታት በቅርቡ ይፋ የሚያደርገው “He for She” ኢኒሼቲቭ ሴቶችን ለማብቃት የጾታ መበላለጥ ችግርን ለማስወገድና በሁለቱም አገራት የሚገኙ ሴቶችን በልማት ስራው ተሳታፊ ለማድረግ ያግዛልም ተብሏል፡፡

ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር የተደረገው ጥናት በድንበር አካባቢው ለግጭት ምክንያት የሆኑትን መንስኤዎች ለመለየት ከማስቻሉ በላይ ባለድርሻ አካላት በቦታው የሚታየውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የሚያደርጉትን እገዛ የሚያጠናክርላቸው መሆኑን ፀሐፊው በዘገባው አካቶታል፡፡

ይህ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት ሰላምንና ደህንነትን ለማስፈን የያዘውን አጀንዳ 2063 ራዕይ እውን ለማድረግ መንደርደሪያ እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡

በድንበር ከተሞቹ አካባቢ ያለው የንግድ ዝውውር ዝቅተኛ ሲሆን ወደፊት ከፍተኛ እድገት እንደሚያስመዘገብ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡

የፕሮግራሙ አስተባባሪና የኬንያ ፕሬዝዳንት ቢሮ ሐላፊ የሆኑት ወይዘሮ ሩት ካጊያ   “ኢኒሼቲቩ በአግባቡ ተግባር ላይ ከዋለ የድንበር ግጭቱን በማስወገድ የአዲስ አማራጭ ድልድይ በመሆን ያገለግላል፡፡ በተለይ የተዘነጉትንና በድህነት ውስጥ ያሉትን ማህበረሰቦች በ2030 ከድህነት ለማውጣት ያስችለናል ”.ማለታቸውን ጠቅሶ ፀሐፊው ዘገባውን ድምድሟል፡

 

 

 

 

 

Published in ዜና-ትንታኔ

አዲስ አበባ   መጋቢት  11/2009  የኢትዮጵያና ቻይና ትብብር ለአፍሪካ-ቻይና ግንኙነት በአርአያነት የሚወሰድ መሆኑን የቻይና ፕሬዚዳንት የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች አማካሪ ያንግ ዬቺ ገለፁ።

በአማካሪው ያንግ ዬቺ የተመራው የልዑካን ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በሁለትዮሽ፣ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል።

ያንግ ዬቺ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የኢትዮጵያና ቻይና ትብብር ለቻይና-አፍሪካ ግንኙነት መጠናከር በአርአያነት የሚወሰድ ነው።

በአሁኑ ወቅት “ኢትዮጵያ በፈጣን ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገት አፍሪካን እየመራች ነው” ያሉት ያንግ ዬቺ "ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት አለን" ብለዋል።

ያንግ ዬቺ እንዳሉት ቻይና እያደገ ለመጣው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የምታደርገውን ድጋፍና ትብብር ታጠናክራለች።

በተለያዩ ፕሮጀክቶች ከኢትዮጵያ ጋር ስትሰራ መቆየቷንና በተለይም በባቡርና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት የምታደርገውን ድጋፍ ይበልጥ እንደምታጠናክር ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ለማሳካት የቻይና ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ቻይና በኢትዮጵያ የልማት ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዳላት ገልፀው ድጋፏን እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የቻይና ድጋፍ እየተስፋፋ ባለው የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የአገሪቷ ባለሀብቶችም በተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በስፋት እየተሰማሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቻይና ፕሬዚዳንት የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች አማካሪ ያንግ ዬቺ በተመሳሳይ ከፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋር ባካሄዱት ውይይት አገራቸው የአፍሪካ ግንኙነቷን በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማስተሳሰር ድጋፏን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

በአፍሪካ አገራትና ህዝቦች መካከል ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ውህደትን ለማጠናከር እንደምትሰራም ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው ቻይና ለኢትዮጵያ ልማት የምታደርገውን ድጋፍ እንድታጠናክር ጠይቀዋል።

ያንግ ዬቺ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምና ከፕሬዝዳንት ሙላቱ ጋር ሁለቱ አገራት በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች የሚያደርጉት ትብብር በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ተለዋጭ አባል በሆነችበት የፀጥታው ምክር ቤት በጋራ እንደሚሰሩ ተነጋግረዋል።

በመጪው ግንቦት ቻይና በምታካሄደውና ከ60 በላይ አገራት በሚሳተፉበት ዋን ቤልትና ሮድ ፎረም ኢትዮጵያ ጠንካራ ተሳትፎ በምታደርግበት ሁኔታ ዙሪያም ተወያይተዋል።

Published in ፖለቲካ

መጋቢት 11/2009 የአለም ባንክ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት በቀጣዮቹ ሶስት አመታት ተግባር ላይ የሚውል  57  ቢሊዮን ዶላር ፋይናንስ  እንደሚያደርግ ማስታወቁን ሲጂቲን ዘገበ፡፡ 

አጠቃላይ ፋይናንስ ከሚደረገው 45 ቢሊየን ዶላር ከአለም አቀፍ ልማት ማህበር የሚገኝ ነው ተብሏል፡፡

የአለም ባንክ የሚሰጣቸው እርዳታዎችና ብድሮች ያለወለድ  ለአለማችን ድሃ ሃገሮች የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል፡፡   

የአለም ባንክ ፕሬዚዳንት ጂም ዮንግ ኪም እንደገለፁት  የአለም ባንክ ፋይናንስ ከሚያደርገው በጀት 8 ቢሊየን ያህሉ ለግሉ ሴክተር የሚውል ሲሆን ገንዘቡ ከአለም አቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን የተገኘ ነው፡፡

ከገንዘቡ 4 ቢሊዮን ያህሉ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሃገራት ላይ ከሚሰራውና  የአለም ባንክ አካል ከሆነው  ከአለም አቀፍ የመልሶ ግንባታና ልማት ባንክ የተገኘ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ፕሬዚደንቱ እንደሚሉት አዲስ የሚቀርበው ፋይናንስ  ለትምህርት ማስፋፊያ ፕሮግራሞች፣ ለመሰረታዊ የጤና አገልግሎቶች ፣ለንፁህ ውሃና የፅዳት አገልግሎት ፣ ለግብርና፣ ለስራ ፈጠራ ፣ለመሰረተ ልማት እና ለተቋማዊ ለውጥ ስራዎች ይውላል ፡፡

ከአለም አቀፍ ልማት ማህበር የሚለቀቀው  አዲሱ  ፋይናንስ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት  የተጀመሩ  448 ፕሮጀክቶችን  የሚደግፍ ይሆናል ፡፡  

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2009 ምርትና ምርታማነትን በማረጋገጥ የልማት ፍላጎቱን መሸከም የሚችል አዲስ የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት መዘርጋትና መተግበር እንደሚያስፈልግ ተነገረ።

የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አገሪቷ ላቀደችው የግብርና ልማት ሁሉ-አቀፍ የትራንስፎርሜሽን ስኬት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የታመነበትን አገር አቀፍ የግብርና ኤክስቴንሽን ስትራቴጂ ሰነድ ይፋ አድርጓል።

ሚኒስትሩ ዶክተር እያሱ አብርሃ “የግብርና ኤክስቴንሽን የሰውን አስተሳሰብ፣ ባህሪይና አመለካከት ከመቀየር ጎን ለጎን ኋላቀር አሠራሮችን በዘመናዊና በአዋጪ አሠራሮች በመተካት የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ወሳኝ ነው” ብለዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥም የልማት ፍላጎቱን መሸከም የሚችል አዲስ የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት መዘርጋትና መተግበር ያስፈልጋል።

ምርቶችን በሚፈለገው ጥራትና መጠን በማምረት፣ የውጭ ምንዛሪ በማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በማቅረብ፤ የሸማቹን ፍላጎት በማርካትና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በነበረው የግብርና ኤክስቴንሽን የአርሶና አርብቶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላትን ምርምርና ተጠቃሚውን በማገናኘት ረገድ ተገቢውን አገልግሎት የመስጠት ውስንነቶች እንደነበሩበት ተጠቅሷል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ከ500 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማምረት ግብ መጣሉን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ግብርናው እየዘመነና የኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ እየተጠናከረ የሚሄድበት መዋቅራዊ ሽግግር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ለዚህም አሁን ያለውን የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት በመቀየር አዲስ ስትራቴጂ መንደፍ የወቅቱ ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል።

አዲሱ የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓተ ፆታ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስና ሥርዓተ ምግብን በተመለከተ የተለየ ትኩረት የሰጠ እንደሆነ ተነግሯል።

በ1956 ዓ.ም 132 የነበረው የልማት ሠራተኞች ቁጥር አሁን በሁሉም ክልሎች የአርሶና አርብቶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ከ60 ሺህ በላይ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች በቀበሌ ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ ነው።

የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓቱን ለማዘመን በሁሉም ቀበሌዎች ከ12 ሺህ በላይ የአርሶና አርብቶ አደር ማሰልጠኛ ጣቢያዎች የተቋቋሙ ሲሆን በቀጣይም ከአምስት ሺህ በላይ ይገነባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከኢትዮጵያ አርሶ አደሮች 22 በመቶ የሚሆኑት የግብርናን ምክረ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ በሞዴልነት ተፈርጀዋል፤ እነዚህ አርሶ አደሮች እያንዳንዳቸው ሁለት አርሶና አርብቶ አደሮችን በማስተማር ወደ ሞዴልነት ቢያመጡ ቁጥሩ ወደ 66 በመቶ እንደሚያድግ ጥናቶች ያመለክታሉ።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር  መጋቢት 11/2009  በአማራ ክልል በግብርና ኢንቨስትመንት ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑ 19 ባለሃብቶችና ድርጅቶች ተሸለሙ፡፡

ሽልማቱ የተሰጠው በጎንደር ከተማ ለሁለት ቀናት የተዘጋጀው የግብርና ኢንቨስትመንት ኮንፈረንስ ትናንት ሲጠናቀቅ ነው፡፡

የክልሉ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ሃላፊ አቶ ጸጋ አራጌ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የክልሉ መንግስት የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርና ኢንቨስትመንት ለመደገፍ እየሰራ ነው።

በዚህም በዘርፉ ከተሰማሩ 1ሺህ 915 ባለሃብቶች መካከል ውጤታማ ለሆኑ 19 ባለሃብቶችና ድርጅቶች የምስክር ወረቀትና የልማት አርበኝነታቸውን የሚገልጽ ስጦታ እንደተበረከተላቸው ተናግረዋል፡፡

የእውቅና ሽልማት መስጠቱ ሌሎችም ተበረታተው ለግብርናው መዘመን የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚያነሳሳ ነው።

ውጤታማ የሆኑ ባለሃብቶችን በማደረጃትም ሆነ በግል እንደየአቅማቸው በቀጣይ በሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመረጡት የስራ ዘርፍ እንዲገቡ ለማበረታታት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

ከተሸላሚዎቹ መካከል በሰሜን ጎንደር መተማ ወረዳ የመጡት አቶ ተስፋ ወርቁ በሰጡት አስተያየት ከ1ሺህ  ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ሰሊጥ፣ ጥጥና  ማሽላ  በማምረት ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለ40 ቋሚና ከእርሻ ዝግጅት እስከ  ሰብል መሰብሰቢያ ወቅት ደግሞ ከ700 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች  ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠራቸውን  ተናግረዋል።

" ኢንቨስትመንቴ በሁለተኛና መጀመሪያ ዲግሪ ባላቸው የሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲመራ ማድረጌ ለውጤት እንድበቃና በክልሉ መንግስት እውቅና እንዲሰጠኝ አብቅቶኛል" ብለዋል።

በቀጣይም የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ልማት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለላቸውም ጠቁመዋል፡፡

በአራት ሄክታር መሬት በጥምር ግብርና በመሰማራታቸው ውጤታማ ሆነው ለመሸለም መብቃታቸውን የገለጹት ደግሞ ከኦሮሞ  ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ደዋ ጨፋ ወረዳ የተመረጡት ባለሃብት አቶ መስፍን ክፍሉ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለው የገበያ ሁኔታ ያልተረጋጋ በመሆኑ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ በመሰማራት እሴት ጨምረው ወደ ውጭ በመላክ ተወዳዳሪ ለመሆን  በአካባቢያቸው ከሚገኙ ሌሎች ባለሃብቶች ጋር እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

በምዕራበ ጎጃም  የጃቢጠናን ወረዳ ነዋሪው ወጣት ተስፋሁን የኔዓለም እንዳለው ከ12 የዩንቨርሲቲ ተመራቂዎች ጋር ተደራጅተው በ2004 ዓ.ም በ25 ሄክታር መሬት ላይ የግብርና ልማት ጀምረዋል፡፡

" ከራሳችን በማዋጣት በ60ሺህ ብር የጀመነው ልማት በየዓመቱ በርበሬ፣ በሎቄ፣ አኩሪ አተርና በቆሎ አምርተን በመሸጥ ዛሬ ላይ ከ2 ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር በላይ በባንክ ማስቀመጥ ችለናል" ብሏል።

ወረዳውና ዞኑ የብድር አቅርቦትና ሌሎችንም ድጋፎች ካደረጉላቸው በአጭር  ጊዜ ውስጥ ወደ ከፍተኛ ባለሃብትነት በማደግ ተሸላሚ ለመሆን እንደሚጥሩም ተናግሯል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ  መጋቢት 11/2009 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለችግር የተጋለጡ ደቡብ ሱዳናዊያንን ለመደገፍ በጁባ የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ሊያካሂድ ነው።

መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም በአገሪቷ መዲና ጁባ የሚካሄደው ውድድር በድርቅና በተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች ድጋፍ ማሰባሰብን ዓላማ ማድረጉን አዘጋጆቹ ተናግረዋል።

ውድድሩ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያና ነዋሪነቱን በደቡብ ሱዳን ባደረገው ኢትዮጵያዊ ባለሀብት አቶ አይሸሹም ተካ ነው የተዘጋጀው።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የቦርድ ሰብሳቢ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ "ስፖርት የፍቅርና የመረዳዳት መሳሪያ በመሆኑ የተቸገሩ የጎረቤት አገር ዜጎችን ለመርዳት አስበናል" ብሏል።

ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ከመርዳት ባሻገር ስለ ሠላም አስፈላጊነት መልዕክት ማስተላለፍና የኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳንን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ሌላው የውድድሩ ዓላማ መሆኑን ገልጿል።

"ሠላም ከሁሉም ይበልጣል" ያለው ኃይሌ "የጎረቤት አገር ሠላም አለመሆን እኛንም የሚነካ በመሆኑ ደቡብ ሱዳን ወደ ቀድሞ ሠላሟ እንድትመለስ በጋራ መስራት ይገባል" ብሏል።

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ውድድሩ ተጎጂዎች ድጋፍ እንዲያገኙና አገራቸው የተሻለ ሠላም እንዲኖራት ከማድረጉ በላይ የሁለቱን አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።

ደቡብ ሱዳን ወደ ቀድሞ ሠላሟ እንድትመለስ የኢትዮጵያ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል በጋና እና ሊቢያ የሩጫ ውድድሮችን ማዘጋጀቱ ይታወቃል።

Published in ስፖርት

መቀሌ መጋቢት11/2009 በትግራይ ክልል የእጣን ዛፍን ከጥፋት ለመታደግ በምርምር የተደገፈ ጥረት እየተደረገ መሆኑን  የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ገለጸ።

በቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ እንክበካቤና ደን ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሀፍቱ ኪሮስ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብና ማዕከላዊ ዞኖች 384 ሺህ 200 ሄክታር   መሬት  በእጣን ዛፍ የተሸፈነ ነበር፡፡

በሂደት በደረሰበት ጉዳት እየተመናመነ ሽፋኑ አሁን ላይ ወደ  267ሺህ 88 ሄክታር ዝቅ ብሏል።

የህገ ወጥ እርሻ መስፋፋት፣ ልቅ ግጦሽ፣ ደን ጭፍጨፋ፣  ቃጠሎና ስርዓት የሌለው የምርት አጠቃቀም ለተክሉ መመናመን በምክንያትነት ከተጠቀሱት ውስጥ ይገኙበታል፡፡

"በየዓመቱ ይገኝ የነበረው 50 ሺህ ኩንታል ምርት በማሽቆልቆሉ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም እየቀነሰ መጥቷል "  ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ሀፍቱ ገለፃ አሁን ያለውን የእጣን ዛፍ ሀብት ባለበት ደረጃ ለማቆየትና በሂደት ሽፋኑን ወደ ነበረበት ይዞታ ለመመለስ ዝርያዎቹን በሳይንሳዊ ዘዴ በማባዛት  ለመጠበቅና ለማልማት  የሚያስችል ምርምር እየተካሄደ ነው።

በተጓዳኝም  ከ20 እስከ 30 አባላት ያሏቸው  86 ማህበራት ተቋቁመው የእጣን ዛፍ ይዞታዎችን በመረከብ እንዲንከባከቡና ችግኝ እንዲተክሉ እየተደረገ መሆኑንም አስተባባሪው  አመልክተዋል።

"የእጣን ዛፍ ሀብቱ ለመጪዎቹ ሶስት ዓመታት ከምርት ነፃ ሆኖ እንዲቆይ ይደረጋል፤ በይዞታው ላይም የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች እየተካሄደ ነው  "ብለዋል ።

በትግራይ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ምርምር ምክትል አስተባባሪ አቶ ክንፈ መዝገበ በበኩላቸው የእጣን ዛፉን ከጥፋት ለመታደግ  በዘርና በግንድ ቆረጣ ዘዴ ዝርያዎችን ለማራባት የሚያስችል ምርምር እየተካሄደ  መሆኑን ገልጸዋል።

የማይፀብሪና ሽሬ ግብርና ምርምር ማዕከላት ተክሉን በሰርቶ ማሳያዎች  ቆርጠው በመትከል ባደረጉት  የሙከራ ምርምር ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱንና ይህንኑ የማስፋፋት ስራ መጀመሩን ጠቅሰዋል ።

በአየር ሁኔታ ለውጥ ምከንያት በተክሉ እድገትና ምርታማነት ላይ የሚፈጠር አሉታዊ ተፅእኖ እንዳይኖር ቀጣይነት ያለው ጥናትና ምርምር እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል፡፡

የበዝሒ ህብረት ሸርክና ማህበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ንጉሰ ነጋ  ከዚህ ቀደም 150 ሄክታር የእጣን ዛፍ ይዞታ በመረከብ  በየዓመቱ  እስከ 300 ኩንታል ምርት በመሰብሰብ ለገበያ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

የእጣን ምርቱን ለሀገር ውስጥ ገበያ ኩንታሉን እስከ 4000 ብር ይሸጡ እንደነበርም  አስታውሰዋል ።

ይሁንና የሚገኘው ምርት በሂደት እየቀነሰ በመምጣቱ ባለፈው ዓመት 60 ኩንታል ብቻ ማግኘታቸውን ጠቁመው  ዘንድሮ  ማምረቱን  በማቆም ለሶስት ዓመታት የሚቆይ  እንክብካቤ የማድረግ ስራ መጀመራቸውን  አመልክተዋል፡፡

የዕጣን ዛፍ  ለመድኃኒት፣ ለመስታወት፣ ለፕላስቲክ ቀለም፣ ለሽቶና ለተለያዩ ኬሚካሎች መስሪያ እንደሚውል ከትግራይ  የግብርና ምርቶች  ገበያ ፕሮሞሽን ኤጀንሲ  የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር መጋቢት 11/2009 የሴቶችን ሰብአዊ መብትና እኩልነት  ለማስከበር  በተደረገው ጥረት ለውጥ ቢኖርም አሁንም ችግሮች እንዳሉ ተመለከተ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን  ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የአለም የሴቶች ቀንን በባህር ዳር ከተማ  በፓናል ውይይት አክብሯል።

" የዘንድሮው በዓል የሚከበረው የሴቶችን ገቢ ማሳደግ ለሰብአዊ መብቶቻቸው መከበር መሰረት ነው"  በሚል መሪ ሃሳብ መሆኑን በኮሚሽኑ  የሴቶችና ህጻናት ኮሚሽነር ወይዘሮ ኡባህ መሃመድ በበዓሉ ላይ ገልጸዋል፡፡ 

ይህም የሀገሪቱ  ሴቶች ህገ መንግስቱ ያጎናጸፋቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ በንቃት የመሳተፍና የመጠቀም መብት ለማጎልበት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽነሯ እንዳመለከቱት ባለፉት ዓመታት በሴቶች የትምህርት ተሳትፎ፣ የመሬትና የሌላም  ሃብት ባለቤትነት መብቶችን ማስከበር ላይ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡

ሆኖም አሁንም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ  የመብት ጥሰቶችና ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

የሴቶችን ሰብአዊ መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር  ኮሚሽኑ ስምንት ቅርንጫፎችን ከፍቶ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ላይ ያተኮረ  ግንዛቤ የማስጨበጥ   ስራ እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ  በበኩላቸው ባለፉት ስርዓቶች በሴቶች ላይ ይደርስ የነበረውን ጭቆና  ለማስወገድ ሴቶች ከወንድ  አጋሮቻቸው ጋር  በመሆን ታግለው ማታገላቸውን ተናግረዋል።

ባስመዘገቡት ድልም የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የፖለቲካዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት  እየጎለበተ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኮሚሽነር አቶ አበረ ሙጨ እንዳሉት ደግሞ  የሴቶችን የመብት ጥሰት ለማስወገድ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ነጻ የህግ አገልግሎት እንዲያገኙ ድጋፍ እየተደረገ ነው።

ከዓለም ጤና ድርጅት የመጡት ዶክተር ፍቅር መለሰ በበኩላቸው በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን የጾታና ሌሎች የመብት ጥሰት ለማስወገድ ራሳቸው ሴቶች ደፍረው መታገል እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

ከባህርዳር ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ማዕከል  ወጣት ዘመኑ አጥናፉ በሰጠው አስተያየት የሴቶችን መብት ለማስከበር ያለው ክፍተት የህግ ማዕቀፍ ችግር ሳይሆን የህብረተሰቡ  ግንዛቤ ማነስና  የፍትህ አካሉ ቁርጠኝነት መጓደል  መሆኑን ተናግሯል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በዓመት አንድ ጊዜ በሚከበር በዓል ብቻ ሳይሆን በየመስሪያ ቤቱ፣ በትምህርት ቤቶችና በሌሎችም የስራ አካባቢዎች የዕለት ተዕለት አጀንዳ መሆን እንዳለበት ጠቁሟል።

በባህር ዳር ከተማ በተከበረው የሴቶች ቀን በዓሉ ላይ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች፣ የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተወካዮች ፣የሃይማኖት አባቶችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

 

 

Published in ማህበራዊ

ጅማ  መጋቢት  11/2009  በ19ኛው ሣምንት የኢትዮጵያ ፕሪመየር ሊግ ጅማአባቡና ከአርባምንጭ ከተማ  ትናንት ያደረጉት ጨዋታ የለምንም ግብ ተጠናቀቀ፡፡

በጅማ ከተማ ስታዲዮም በተካሄደው  በዚሁ የእግር ኳስ ውድድር አባቡና ተጭኖ በመጫወት በርካታ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክርም ወደጎል ሊቀይር አልቻለም፡፡

" ሶስት ነጥብ ለማግኘት ካለን ፍላጎት አንጻር ጫና ፈጥረን ለመጫወት ብንሞክርም ባለመቻላችን ነጥብ ተጋርተን ልንወጣ ተገደናል" ሲሉ  የጅማ አባቡና አሰልጠኝ ገብረመድን ሃይሌ ተናግረዋል፡፡

አሰልጣኙ አያይዘውም ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪመየር ሊግ ከተጀመረ በኋላ አባቡና ሁለት ጊዜ አሸንፎ ሶስት ጊዜ አቻ ከመውጣቱም በላይ ምንም አይነት ግብ  ሊቆጠርበት አለመቻሉ መሻሻሉን እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

" ቀጣይ በምናድረጋቸው ጨዋታዎች ግብ ያለማግባት  ድክመታችንን በማሻሻል ወደ አሸናፊነት ለመመለስ  እንሞክራለን" ብለዋል፡፡

የአርባምንጭ ከተማ አስልጣኝ ጳውሎስ ፀጋዬ በበኩላቸው " በመልሶ ማጥቃት አሸንፈን ለመውጣት ያሰብነው ባይሳካም ከሜዳ ውጭ ነጥብ ተጋርቶ መመለስ እንደስኬት ይቆጠራል "ብለዋል፡፡

አስልጣኙ አክለውም  ተጫዋቾቻቸው  ከሶስት ቀን በፊት በመኪና በመጓዝ  ወልድያ  ከተማ ጋር ከተጫወቱ በኋላ በድካም ስሜት ያደረጉት በመሆኑ ውጤቱ  የሚያስከፋ እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡

አስልጣኝ ጳውሎስ " የዕለቱ ዳኛ   ካለባቸው የአካል ብቃት ችግር የተነሳ የተሳሳተ ውሳኔ ሲወስኑ በማየቴ አዝኛለሁ "ብለዋል፡፡

Published in ስፖርት

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን