አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 02 March 2017

አዲስ አበባ የካቲት 23/2009 ከኢትዮጵያ የቅርስ አጠባበቅ ሥርዓት ላይቤሪያ ልምድ እንደምትቀስም ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ሰርሊፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየምን ዛሬ ጎብኝተዋል።

በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፤ ሙዚዬሙ ውስጥ የሚገኙትን ጥንታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ፕሬዚዳንቷ፤ በሰው ልጅ አመጣጥ ታሪክ ታላቅ ስፍራ ያላቸውን ቅሪተ አካሎች፣ የአርኪኦሎጂና የታሪክ  ስብስብ ቅርሶች አጠባበቅ እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለቅርስ አያያዝና አጠባበቅ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠች መሆኗን መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቷ የሶስት ቀን ይፋዊ ጉብኝታቸውን ጨርሰው ነገ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያና የላይቤሪያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ1959 ጀምሮ ነው።

 

 

Published in ፖለቲካ

ኡጋንዳ የካቲት 23/2009 ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ የሚያከናውቸውን ተግባራት አጠናክረው ለመቀጠል ተስማሙ።

ሁለቱ አገሮች በሴቶችና ህጻናት እንዲሁም በወጣቶችና ስፖርት ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ኡጋንዳ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስፍራው የተጓዙት የአገሪቷ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት ነው።

ዛሬ ኢንተቤ የገባው የኢትዮጵያ መንግስት የልዑካን ቡድን ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ያካተተ ነው።

የልዑካን ቡድኑ በኢንተቤ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሰ በአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳም ኩቴሳ፣ በቤተ መንግስትም በፕሬዚዳንት ሙሴቬኒና በቀዳማዊት እመቤት ጃኔት ሙሴቬኒ አቀባበል ተደርጎለታል።

ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በተለያዩ ጉዳዮች በተለይም በአካባቢያዊ ሰላምና ጸጥታ በጋራ በመስራት ላይ ይገኛሉ።

በዛሬው ዕለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ በሁለትዮሽ፣ በአካባቢያዊ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።

አገሮቹ በሴቶችና ህጻናት እና በወጣቶችና ስፖርት ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችሏቸውን ስምምነቶች የተፈራረሙ ሲሆን፤ ቀደም ሲል በተለያዩ መስኮች የተፈረሙ ስምምነቶች ተግባራዊነት ላይም ተወያይተዋል።

ሁለቱ አገሮች ከዚህ ቀደም በጸጥታ፣ በትራንስፖርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በቱሪዝምና በሌሎችም መስኮች በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ይታወሳል።

ሁለቱ መሪዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ አገሮቹ ለፈረሙት ስምምነቶች ተግባራዊነት በትኩረት ይሰራሉ።

የሁለቱን አገሮች የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ፣ በመሰረተ ልማት ለመተሳሰር የተወያዩ ሲሆን፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በጋራ መስራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይም መክረዋል።

ሁለቱ አገሮች በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር ከስምምነት ደርሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ገልጸው፤ ጉብኝቱ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማሳደግ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ተናግረዋል።

ሁለቱ አገሮች ከድህነት ለመውጣት ያላቸውን ሀብትና አቅም በማስተባበር መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በሶማሊያ ሰላም ለማስፈንና አልሸባብን ለመዋጋት ወደ አገሪቷ የሰላም አስከባሪ ሠራዊት በመላክና በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማስፈን በመስራት ላይ ይገኛሉ።

አገሮቹ ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት አሁንም በጋራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ ለአዲሱ የሶማሊያ መንግስት እገዛ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒም ፤ ኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅና በቆዳ ዘርፍ ለውጥ እያመጣች ያለች አገር መሆኑዋን ገልጸው፤ ከአገሪቷ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በጋራ መስራት አዋጭ መሆኑን አመልክተዋል።

በዛሬው ዕለት የተከበረውን 121ኛው የአድዋ ድል በዓል አስመልክቶም "የእንኳን አደረሳችሁ" መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከአፍሪካ አንጋፋ መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ በ2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተመሳሳይ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በቆይታቸውም ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች ስምምነት ሲያደርጉ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ የግልገል ጊቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን፣ የአርባ ምንጭ አዞ እርባታና ሌሎችንም ስፍራዎች መጎብኘታቸው የሚታወስ ነው።

 

 

 

Published in ፖለቲካ

ነገሌ የካቲት 23/2009 በቦረና ዞን አርብቶ አደሩ አካባቢ ከስድስት ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች አዲስ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በበጀት ዓመቱ ወደ ሥራ ከገቡት መካከል ስድስት መቶ የሚሆኑት የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ ትምህርት ያጠናቀቁ ወጣቶች መሆናቸውን በጽህፈት ቤቱ የእቅድና በጀት ባለሙያ አቶ ዳንኤል ዴኮ ገልጸዋል፡፡

በግብርና፣ በግንባታ፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በሸማቾችንና በሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ወደ ሥራ ከገቡት መካከል 950 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

በዚህ ዓመት 24 ሺህ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ዕቅድ ቢያዝም በገንዘብ አቅርቦት ችግር፣ በቅርቡ በተከሰተ ድርቅ ምክንያትና በተጠቃሚዎች የተሳሳተ አመለካከት የታሰበውን ያክል መሳካት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

በዞኑ የያቤሎ ከተማ ነዋሪ ወጣት ንጉሴ ምህረት በተፈጠረው የሥራ ዕድል ከአራት ጓደኞቹ ጋር በ20 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የብረታ ብረት ሥራ መጀመራቸውን ተናግሯል፡፡

ሥራው ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ቢሆንም የማምረቻና የመሸጫ ቦታ የሌላቸው መሆኑ እርሱና ጓደኞቹ የሚፈለገውን ያክል ውጤት እንዳይሆኑ እንቅፋት የሆነባቸው መሆኑን አስተውቋል፡፡

በዚሁ ከተማ ከ11 ጋደኞቹ ጋር የብረታ ብረት ሥራ የጀመረው ሌላው ወጣት አብረሀም ጀልዴሳ በበኩሉ ፣ የገንዘብ ብድር ባለማግኘታቸው የሚፈልጉትን ያክል ምርታማ መሆን እንዳልቻሉ ገልጿል፡፡

"የገበያ ትስስር እንዲፈጠርልን፣ የገንዘብ ብድር እንዲመቻች፣ የማምረቻና የመሸጫ ቦታ እንዲሰጠን ለሚመለከተው አካል ጥያቄ አቅርበን መልስ እየጠበቅን" ብለዋል፡፡

በወጣቶቹ የቀረቡትን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑንና እስካሁንም 15 ሺህ ካሬ ሜትር የመሸጫና የማምረቻ ቦታ ለመስጠት መዘጋጀቱን አቶ ዳንኤል ገልጸዋል

በኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ አክሲዎን ማህበር የቦረና ዞን ጽህፈት ቤት በበኩሉ፣ በዚህ ዓመት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ለመስጠት ዕቅድ ይዞ ወደሥራ መግባቱን አስታውቋል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ተወካይ አቶ ባህሩ ግራቫ እንዳሉት፣ እስካሁን 587 ወጣቶችን ጨምሮ 22 ሚሊዮን ብር ለቆጠቡ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች 17 ሚሊዮን ብር ብድር ተሰጥቷል፡

በቦረና ዞን በ778 ማህበራት የተደራጁ ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች ወደሥራ መግባታቸውን የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ደሴ የካቲት 23/2009 በደቡብ ወሎ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል የቦንድ ግዥ ሳምንት ፕሮግራም ተዘጋጀ፡፡

ፕሮግራሙ የተዘጋጀው  የህዳሴው ግድብ ግንባታ የተጀመረበት ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ነው፡፡

የዞኑ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ አቶ ተስፋዬ መንግሥቴ ዛሬ ለጋዜጠኞች አንደገለጹት የህዳሴው ግድብ ግንባታ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ የዞኑ ህዝብ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ድጋፍ ካደረገው የዞኑ ህዝብ መካከል የመንግሥት ሰራተኛው፣ አርሶ አደሩ፣ የንግዱ ማኅበረሰብና  የከተማ ነዋሪ ይገኝበታል፡፡

ሃላፊው እንዳሉት የህዳሴው  ዋንጫ በክልሉ በቆየበት ዓመትም የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገቡ ዞኑ የዋንጫ ተሸላሚ  ሆኗል፡፡

መልካም ተሞክሮን  በማስፋት ለግድቡ የሚደረገውን አስተዋጽኦ ለማስቀጠልም ከትናንት ጀምሮ የቦንድ ግዥ ሳምንት ፕሮግራም ተዘጋጅቷል።

ከዞን እስከ ቀበሌ በሚካሄደው በዚሁ ፕሮግራም 50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታስቦ ወደ ስራ መገባቱንም አቶ ተስፋዬ አስታውቀዋል።

ቦንድ ከመግዛት ባሻገር የፓናል ውይይት፣ የሙዚቃና ስነጽሁፍ ዝግጅት፣ ኪነጥበባዊና ስፖርታዊ ውድድሮች በማካሄድ ህብረተሰቡ በግድቡ ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማስፋት ይሰራል።

"በቦንድ ግዥና በስጦታ ለተሳተፉ አካላት የክብር መዝገብ እንደሚዘጋጅ፣ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የህዳሴው ግድብ ክበባት እንደሚቋቋሙ፣ ቦንድ ላልተሰጠቸው እንዲሰጣቸው ፣ ያልተጠናቀቁ ስራዎችን የመፈጸም  ተግባራት ይከናወናሉ" ብለዋል፡፡

በዞኑ ኩታበር ወረዳ የመሆነኛ አምባ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ለህዳሴው ግድብ እያንዳንዳቸው እስከ 400 ብር የሚደርስ  የቦንድ ግዥ ለመፈጸም ቃል መግባታቸውን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ኡመር ሰይድ ተናግረዋል፡፡

በወረዳው የትምህርት ቤቶች የጉድኝት ሱፐር ቫይዘር አቶ እሸቱ በላይ ለአራተኛ ጊዜ ቦንድ በመግዛት ከስምንት ሺህ ብር በላይ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

 "የህዳሴው ግድብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥና አገራዊ እድገታችንን የሚያፋጥን በመሆኑ እንደ ዜጋ  የሚጠበቅብኝን ለማድረግ ጥረት እያደረግሁ ነው" ብለዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ሃዋሳ የካቲት 23/2009 የፍትህ አካላት የህዝብን ጥቅም የሚጎዱ የወንጀል ድርጊቶችን በመከላከል የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አሳሰቡ።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግና የክልል ፍትህ ቢሮዎች በፍትህ ስርዓት ዙሪያ የጋራ ምክክር መድረክ በሃዋሳ ከተማ እየተካሔደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ እንደተናገሩት የፍትህ ስርዓቱን ውጤታማ፣ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የፍትህ አካላት ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱንና የህዝብን ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ሽብርተኝነት፣የሃይማኖት አክራሪነት፣ህገ ወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውርንና ሌሎችንም የወንጀል ስጋቶች ለማስወገድ መታገል እንደሚገባ ተናግረዋል።

"በክልሎችና በፌደራል ጠቅላይ አቃቢያነ ህጎች መካከል የርስ በእርስ ትብብርና መደጋገፍን በማጠናከር በፍትህ ዘርፍ የተመጣጠነ አፈጻጸም እንዲኖር የምክክር መድረኩ ትልቅ ድርሻ  አለው" ብለዋል።

በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ በበኩላቸው ለልማቱ መሰረት የሆነው ሃገራዊ ሰላም አስተማማኝ እንዲሆን ከአጎራባች ክልሎች ጋር የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በክልሉ መንግስት፣ በባለድርሻ አካላትና በህብረተሰቡ ቅንጅት የፍትህ አገልግሎት አሰጣጡ እየተሻሻለ ቢሆንም ገና ብዙ መስራት እንደሚገባ ገልጸው መድረኩ የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን አመልክተዋል።

የሁሉም ክልል ፍትህ ቢሮ ሃላፊዎች፣ ተጠሪ ተቋማት፣አመራሮችና የፌደራል አቃቢ ህግ ከፍተኛ ባለሙያዎች በሚሳተፉበት የሶስት ቀን ውይይት በፌደራል አቃቢ ህግ የአሰራር ማንዋልና በአዲስ የማቋቋሚያ አዋጅ፣በክልሎች የጋራ ስምምነት ሰነድና የግማሽ ዓመት አፈጻጸም

ለሶስት ቀናት በሚቆየውና ትላንት በተጀመረው መድረክ ላይ በፌደራል አቃቢ ህግ የአሰራር ማንዋልና በአዲስ የማቋቋሚያ አዋጅ፣በክልሎች የጋራ ስምምነት ሰነድና የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ላይ የሚመክር ሲሆን የሁሉም ክልል ፍትህ ቢሮ ሃላፊዎች፣ ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና የፌደራል አቃቢያነ ህግ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 23/2009 በአድዋ ድል ከታየው የአንድነትና የቆራጥነት መንፈስ ለአገሪቷ ህዳሴ በህብረት መስራት ስኬታማ እንደሚያደርግ ሊገነዘቡ መቻላቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በበኩላቸው፤ "ወጣቱ ትውልድ አገሪቷ የጀመረችውን የልማትና ህዳሴ  ጉዞ በማስቀጠል የአድዋን ድል መድገም ይጠበቅበታል" ብለዋል።

የአድዋ የድል በዓል ዛሬ ለ121ኛ ጊዜ በአጼ ምኒሊክ አደባባይ ተከብሯል።

የኢዜአ ሪፖርተር በአጼ ምኒሊክ አደባባይ በዓሉን ለማክበር የመጡ ወጣቶችን አነጋግሯል።

ወጣቶች እንደገለጹት፤ ቀደምት አባቶች ጠላትን ድል የነሱት በህብረትና በአንድነት መንፈስ በመንቀሳቀሳቸው መሆኑን ተገንዘበዋል። ከዚህም ለአገር እድገት በጋራ መስራት እንዳለብን እምነት አሳድረናል ነው ያሉት።

ከኡራኤል አካባቢ የመጣችውና በበዓሉ ላይ የታደመችው ወጣት ይፍቱ ስራ እንደተናገረችው፤ በአድዋ የታየውን የአንድነት መንፈስ በመላበስ ለአገር እድገት መስራት ያስፈልጋል።

በልማት ስራዎች ላይ በመረባረብ የአገሪቷን እድገት ማስቀጠል ይጠበቅበናል ያለችው ወጣት ይፍቱ፤ አገሯን ለማሳደግ ባላት እውቀትና አቅም ለማገልገል በቁርጠኝነትና በአሸናፊነት መንፈስ እንደምትሰራ ተናግራለች።

ወጣት ዮሴፍ ገላው ከፒያሳ አካባቢ በዓሉን ለማክበር ታድሟል። ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ሆነው ጠላትን ድል እንዳደረጉ ሁሉ የስራ ባህልን በማሳደግ ለአገር እድገት ተግቶ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ነው ያመለከተው።

ከመንግስት ጋር በጋራ በመሆን የአገሪቷን ቀጣይነት ላለው እድገትና ልማት ለማስቀጠል ወጣቱ በጥንካሬ መንፈስ መስራት እንዳለበትም መልዕክቱን አስተላልፏል።

በአድዋ የተሰራውን ገድል "የአገራችን ሰላም በማስከበር መድገም አለብን" የሚለው ደግሞ ከሳሪስ አካባቢ በዓሉን ለማክበር የመጣው ወጣት ዮሐንስ መንገሻ ነው።

ድሉ ከምንም በላይ ያስተማረን "ለአገራችን ሰላም ዘብ መቆም ነው" ይላል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ወጣቱ ትውልድ አገሪቷ የጀመረችውን የልማትና ህዳሴ  ጉዞ ለማስቀጠል በመረባረብ የአድዋን ድል መድገም ይጠበቅበታል።

በቀጣይ የአድዋ ታሪክ በትውልዱ በአግባቡ እንዲዘከር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባውም አሳስበዋል።

121ኛው አድዋ የድል በዓል በአዲስ አበባ ሲከበር የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማን ጨምሮ ጀግኖች አርበኞች በአጼ ምኒሊክ ሐውልት ስር የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

በዓሉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ አባት አርበኞች እና በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት ተከብሯል።

Published in ማህበራዊ

ድሬደዋ የካቲት 23/2009 በድሬዳዋ አስተዳደር የባህል ስፖርትን ለማሳደግ ከቀበሌዎችና ከትምህርት ቤቶች ጋር በቅንጅት እየተሳራ መሆኑን የአስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ገለጸ።

ለአሥር ቀናት በሰባት ባህላዊ ስፖርቶች በድሬደዋ ሲካሄድ የሰነበተው ውድድር ተጠናቋል፡፡ 

ከድሬዳዋ ስድስት ቀበሌዎች፣ ከተለያዩ ድርጅቶችና ትምህርት ቤቶች የተወከሉ ከ300 በላይ ስፖርተኞች ከየካቲት 10 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በሰባት ባህላዊ ስፖርቶች ውድድራቸውን ሲያኪያሂዱ ቆይተዋል።

በኮርቦ፣ በሻህ፣ በቡብ፣ በትግል፣ በቀስት፣ በገና፣ እንዲሁም በገበጣ ባህላዊ ስፖርቶች ሲካሄድ የሰነበተው የስፖርት ውድድር ከትናንት በስቲያ በተኪያሂዱ ውድድሮች ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡

የሶማሌ ባህላዊ ስፖርት በሆነው የሻህ ውድድር በሴትና ወንድ ድምር ውጤት ቀበሌ 07 ፣ በኮርቦና በቀስት ደግሞ ቀበሌ 04 አሸናፊ ሆነዋል፡፡

በቡብ እና በገና ጨዋታዎች ኬር እስኩየር ሥጋ ቤት ክለብ፣ በትግል ባህላዊ ውድድር ዘመን ፈርኒቸር አሸናፊ ሲሆኑ በባለ 12 እና 18 ጉድጓዶች በተኪያሂደ የገበጣ ጨዋታ የቀበሌ 05 በድምር ውጤት አሸናፊ ሆኗል፡፡

አሸናፊዎቹ የተዘጋጀላቸውን የዋንጫና የገንዘብ እንዲሁም የምስክር ወረቀት ሽልማት ከዕለቱ እንግዶች ተቀብለዋል፡፡

በውድድሩ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ስፖርት ኮሚሽን የባህል ስፖርት ፈደሬሽን ፀሐፊ ወይዘሮ ጽዮን በለጠ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ ውድድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመጪው ሚያዝያ ወር አክሱም ላይ ለሚካሄደው የባህል ስፖርቶች ውድድር አስተዳደሩን የሚወክሉ ስፖርተኞችን መመልመል አስችሏል፡፡

ሀገራዊ ማንነትንና የርስ በርስ ትስስርን የሚያጎለብቱትን የባህል ስፖርቶች ለማሳደግም ከቀበሌዎች፣ ከድርጅቶችና ከትምህርት ቤቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታትም ስለስፖርቱ እየተፈጠረ የሚገኘው ግንዛቤ የሚበረታታና የሚጠናከር መሆኑን እንዳለበት ወይዘሮ ጽዮን ገልፀዋል፡፡

በስድስት ትምህርት ቤቶች መካከል የባህል ስፖርት ውድድር መኪያሄዱን አስታውሰው በዚህ ውድድር የተሳተፉት ተማሪዎች ዛሬ ደግሞ ቀበሌያቸውን ወክለው መጫወታቸውን ገልፀዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ጽዮን ገለጻ፣ የባህል ስፖርት በቀጣይ በአስተዳደሩ በሚካሄደው የትምህርት ቤቶች ጨዋታ አንዱ የመወዳደሪያ ዘርፍ እንዲሆን እየተሰራ ነው፡፡

የባህል ስፖርት አሰልጣኝ መምህርት ኢትዮጵያ አማረ በበኩሏ፣ ቀበሌዎች ለባህል ስፖርቱ እድገት ኃላፊነታቸውን መወጣት ያለባቸው ቢሆንም አንዳንድ ቀበሌዎች ለስፖርቱ የተመለመሉ ስፖርተኞችን ጭምር ለመደገፍ ፍላጎት እንደሌላቸው መታዘቧን ገልጻለች፡፡

የባህል ስፖርቶችን የፍፃሜ ጨዋታዎች በድሬዳዋ ሳቢያን ሜዳ ተገኝተው የተከታተሉ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ ለባህል ስፖርቱ ማደግና የተሻለ ደረጃ መድረስ ያልተበረዘ የባህል ጨዋታ ባለቤት የሆነው የገጠሩን ክፍል ማካተት አስፈላጊ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

Published in ስፖርት

ባህር ዳር/ደብረማርቆስ የካቲት 23/2009 121ኛው የአድዋ ድል በዓል በባህር ዳር ከተማ በውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ።

የአማራ ክልል ጥንታዊት አባት አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ዳኝነት አየለ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ጀግኖች አባቶች በአንድነታቸውና በጽናታቸው ወራሪውን የኢጣሊያን ጦር አሳፍረው መመለሳቸውን አስታውሰዋል።

አባቶቻችን አገርን ሊወር፣ ሊያጠፋና ሕዝብን ሊጎዳ የሚመጣ ጠላትን በየዘመናቱ አሳፍረው የመመለስ ጠንካራ መንፈስ እንደነበራቸው ገልጸዋል።

"በጦር፣ በጎራዴና በሌሎች ኋላ ቀር መሳሪያዎች ለአገራቸው ነጻነት የከፈሉት መስዋዕትነት ለዓለም ጭቁን ሕዝቦች ጭምር አርአያ ሆኖ ይጠቀሳል" ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን የውስጥ ጉዳያቸውን ወደ ጎን በመተው ለዳር ድንበራቸው መከበር በጋራ የመቆም ጠንካራ መንፈስ እንዲኖራቸው ለአዲሱ ትውልድ አውርሰው ማለፋቸውንም አስታውሰዋል።

የአገሪቱ ሕዝቦች ሕብረት ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ ስኬታማ እንደሚሆኑ የአድዋ ድል ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፣ የአሁኑ ትውልድ የአገሪቱን ታሪክና የአባቶቹን ጀግንነት ጠንቅቆ ማወቅና ማሳወቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያየህ አዲስ በበኩላቸው " ወጣቱ ትውልድ ከአባቶች ጀግንነትን በመማር በተጀመረው ድህነትን የማጥፋት ዘመቻ ላይ የራሱን ታሪክ መስራት አለበት" ብለዋል።

ቀደምት አባቶች የአገሪቱን ሉአላዊነት ጠብቀው እንዳቆዩ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም መንግስት በነደፈው የልማትና የዴሞክራሲ ሥራዎች በንቃት ተሳትፎ የሕዳሴውን ጉዞ ማፋጠን እንዳለበት አመልክተዋል።

ለዚህም "የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ አባት አርበኞችና ወላጆች ታዳጊ ሕጻናት ስለ አገራቸው ታሪክ፣ ባህልና ወግ አውቀው እንዲያድጉ ማድረግ ይኖርባቸዋል" ብለዋል።

የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት አንተነህ መላኩ በበኩሉ ያልተነገሩ የጀግኖች አባቶች ታሪክ በአግባቡ ሊነገሩ እንደሚገባ ነው የገለጸው።

በዓሉም ወጣቱ ትውልድ ስለአድዋ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ጭምር መከበር እንዳለበት አስገንዝቧል።

ሌላዋ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት ትዕግስት ዘለቀ በበኩሏ፣ "ጀግኖች አባቶቻችን ዳር ድንበራቸውን አስጠብቀው እንዳስረከቡን ሁሉ እኛም ድህንትን ድል በመንሳት የአገሪቱን ክብር ከፍ ማድረግ አለብን" ብላለች።

ዛሬ በቀድሞ የክልሉ ምክር ቤት አዳራሽ በተከበረው በዓል ላይ አባት አርበኞች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ ወጣቶችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና በአድዋ ጦርነት የተገኘውን ድል ለወጣቱ ትውልድ ማስተማርና መሳወቅ ይጠበቅብናል ሲሉ በደብረማርቆስ ከተማ የሚገኙ የጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት ተናገሩ።

121ኛው የአድዋ ድል በዓል ዛሬ በከተማው ንጉስ ተክለሃይማኖት አደባባይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላትና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተከብሯል።

በከተማዋ የሚኖሩት አባት አርበኛ ከበደ አየለ የአድዋ ድል በዓል በየዓመቱ መከበር የአባቶችን ታሪክ ለማስታወስና ለመዘከር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በበዓሉ የተገኘው ድል ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የዛሬው ትውልድም በልማት ላይ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ ስለአድዋ በሚገባ ማስተማር እንደሚገባ አመልክተዋል።

ለእዚህም ከአባት አርበኞች ብዙ እንደሚጠበቅ ነው የጠቆሙት።

ወይዘሮ ጽጌ ዮሐንስ የተባሉ የማህበሩ አባል በበኩላቸው፣ በዓሉ ቅድመ አያቶቻችን ለአገራቸው የሚሰጡትን ክብርና ፍቅር የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

"የእኛ ልጆች ይህን አውቀው ለአገራቸው ታሪክ እንዲሰሩ የአድዋ ድልን በሚገባ በማስተዋወቅ በኩል ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል" ብለዋል።

በበዓሉ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፀሐፊ አሥር አለቃ ዕድል ፈንታ ድሮ ጥንታዊ ጀግኖች አባቶች የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ላለማስደፈር ተጋድለው ጠላትን ድል መንሳታቸውን አስታውሰዋል።

በእዚህም ነጭ በጥቁር አይሸነፍም የሚለውን አመለካከት በመስበር ለጥቁር ህዝብ ጭምር አርአያነት ያለው ተግባር መፈጸሙን ነው የገለጹት።

ዛሬ ያለው ተተኪ ትውልድ የጦርነት ሳይሆን የልማት አርበኛ በመሆን ድህነትን ድል ሊነሳ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 23/2009 በኢትዮጵያ አቅም የማሳደግና የማሻሻል ሥራ የተከናወነላቸው 63 የኤሌትሪክ ኃይል የማሰራጫና ማከፋፋያ ጣቢያዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የውጭና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተደጋጋሚ የሚከሰትን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር ለማቃለል በማሰራጫና ማከፋፈያ ጣቢያዎች አቅም የማሳደግና የማሻሻል ስራዎች ተከናውነዋል።

የእነዚህን የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫና ማከፋፋያ ጣቢያዎች አቅም የማሳደግና የማሻሻል ሥራ የተከናወነው በአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ወጪ ነው።

በማሳደግና በማሻሻል ስራዎች የመስመሮቹ ኃይል የማስተላለፍ አቅም ከ132 ኪሎ ቮልት ወደ 230 ኪሎ ቮልት እንዲሁም ከ230 ኪሎ ቮልት ወደ 400 ኪሎ ቮልት ማደጉን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ አቅም የማሳደግና የማሻሻል ሥራዎች ከተከናወነባቸው ቦታዎች መካከል በቃሊቲ አንድና ሁለት፣ በሰበታ፣ በገፈርሳ፣ በኮተቤ፣ በሰሜን ቃሊቲና ንፋስ ስልክ የማሰራጫና የማከፋፈያ ጣቢያዎች ተጠቃሽ ናቸው።

በክልሎች ደግሞ ድሬደዋ ፣አርባ ምንጭ፣  ሀዋሳ፣ አላማጣ፣ ማይጨው፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣  ወረገኑ፣ ዳባትና ደብረ ማርቆስ ይጠቀሳሉ።

በተለይ በኦሮሚያ ለሚገኙ 24 የኃይል ማከፋፋያ ጣቢያዎች የመልሶ መከላከያ ግንባታ ሥራ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አቶ ምስክር አክለዋል።

በአገሪቷ እየተገነቡ ያሉትን ትልልቅ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች የኤሌክትሪክ የኃይል አቅርቦት ለማማሻል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የኤሌትሪክ ኃይል አቅረቦት 4 ሺ 260 ሜጋ ዋት መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 23/2009 የአሁኑ ትውልድ አባቶቹ በአድዋ ተራሮች ላይ ያሳዩትን የአገር ፍቅርና የአይበገሬነት መንፈስ በመላበስ ለቀጣይ ትውልዶች የበለጸገች ኢትዮጵያን ማውረስ እንዳለበት የኢፌዴሬ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ።

መጋቢት 17 ቀን 2009 ዓ.ም በይፋ የሚለኮስ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አገራዊ የንቅናቄ ችቦ ርክከብ ተካሂዷል። 

121ኛው የአድዋ ድል በዓል ዛሬ በአድዋ ከተማ ተከብሯል።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የቀደምት አባቶች በጥልቅ የአገር ፍቅር፣ በነጻነትና ጀግንነት መንፈስ ጠላትን ድል ነስተዋል። በዚህም የዛሬው ትውልድ በኢትዮጵያዊ ማንነቱ እንዲኮራ አስችለዋል።

“ይህ ትውልድም ሆነ ቀጣዩ ትውልድ የአገር ፍቅርና የአይበገሬነት መንፈስ ሊወርስ ይገባዋል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ድህነትን ከኢትዮጵያ ምድር በማጥፋት ታሪክ ሰርቶ ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን የአመራር ጥበብ በተግባር የታየበት፤ የሁሉም ኢትጵያዊያን ዘመን የማይሽረው የአንድነትና የመተባበር ውጤት የተንጸባረቀበት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ክንድ የአድዋን ድል ታሪክ በልማትም መድገም ይጠበቅባቸዋል።

በዕለቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ አገራዊ ሕዝባዊ ንቅናቄ የችቦ ርክክብ ተካሂዷል።

አገራዊ የንቀናቄ ችቦ በመጪው መጋቢት 17 ቀን 2009 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በይፋ ይለኮሳል ተብሎ ይጠበቃል።

በዕለቱም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የንቅናቄ ችቦውን ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ለአቶ ያለው አባተ አስረክበዋል።

"ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ሀገራዊ ህብር ዜማ የህዳሴያችን ማማ" በሚል መሪ ሀሳብ መጋቢት 17 ቀን 2009 ዓ.ም ይፋ የሚሆነው የንቅናቄ መድረክ በሚቀጥሉት 11 ወራት በመላው አገሪቷ ተግባራዊ እንደሚሆን ታውቋል።

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን