አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 19 March 2017

ሶዶ መጋቢት 10/2009 በ19ኛው  የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በወላይታ ሶዶ ስታዲየም ዛሬ  በተካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ ወላይታ ድቻና ሲዳማ ቡና አቻ ዜሮ ለዜሮ ተለያዩ፡፡

በመጀመሪያዉ የጨዋታ ክፍሌ ጊዜ ኳስ  በማደራጀት፣ በመከላከልና የመሃል ሜዳዉን በመቆጣጠር የሲዳማ ቡና  ቡድን ሲበልጥ ወደ ጎል በመድረስና አጋጣሚዎችን በመፍጠር ድቻ የተሻለ  ነበር፡፡

በሁለተኛዉ የጨዋታ ክፍሌ ጊዜ የወላይታ ድቻ ቡድን ራሱን አደራጅቶ በመግባት በመከላከል፣  በማደራጀትና በማጥቃቱም የተሻለ ብልጫ የነበረው ቢሆንም ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡

የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ "ከሽንፈት የተመለስን በመሆናችን አንድ ነጥብ ማግኘታችን የሚያስከፋ ባይሆንም የፈጠርናቸው የጎል አጋጣሚዎች መጠቀም አለመቻላችንና በሜዳችን ሙሉ ነጥብ ያለመውሰዳችን ያስቆጫል" ብለዋል፡፡

በአጨራረስ  ክፍተት እያስከፈላቸውን ያለውን ዋጋ ለመመለስ ተኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ (አለኮ) " በመጀመሪያው የጨዋታ ከፍለ ጊዜ መጨረስ ሲገባን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም ያለመቻላችን ነጥብ እንድንጥል አድርጎናል" ብለዋል፡፡

ከሜዳቸው ውጭ  ተጫውተው አንድ ነጥብ ማግኘታቸው መልካም መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ዳኝነቱም የተሻለ መሆኑን ጠቁመዉ በሜዳዉ የተመለከቱት የስፖርታዊ ጨዋነት የተላበሰ የድጋፍ አሰጣጥ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ 

 

Published in ስፖርት

መቱ መጋቢት 10/2009 በኢሉአባቦር ዞን ባለፉት ሰባት ወራት ከ13ሺህ 500 ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ከእቅድ በላይ መከናወኑን የዞኑ ቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን ገለጸ፡፡ 

በባለስልጣኑ የቡና ጥራት ቁጥጥር የስራ ሂደት መሪ አቶ በላቸው ለገሰ  ለኢዜአ እንደገለጹት ቡናው ለማዕከላዊ ገበያ የቀረበው በዞኑ  አስራ አንድ ወረዳዎች በሚገኙ 76 የደረቅና  የእሸት ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ተዘጋጅቶ ነው፡፡

የኢንዱስትሪዎቹ ባለቤት በሆኑት 428 ቡና አቅራቢ ነጋዴዎችና 65 የህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ከቀረበው የቡና ምርት ውስጥ 12ሺ400 ቶን ደረቅና ቀሪው የታጠበ መሆኑ ተናግረዋል፡፡

ከንውኑ ከእቅዱ በ700 ቶን  ብልጫ ያለው  ነው፡፡

ለአርሶአደሩ ፣ለአቅራቢዎችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት በተሰጠው ተከታታይነት ያለው ስልጠና ምርቱ በጥራትና በብዛት እንዲቀርብ መነሳሳት መፍጠሩንና  ለክንውኑ ብልጫ መሆን የስራ ሂደቱ መሪ  በምክንያትነት  ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም የቡና ልማት ግብይትና ጥራትን በተለየ ትኩረት ለማካሄድና የዘርፉን ጠቀሜታ ለማሳደግ የቡና እና ሻይ ልማት ዘርፍ ከግብርናው ሴክተር ተለይቶ ራሱን ችሎ መቋቋሙም ሌላው አስተዋጽኦ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ አሌ ወረዳ በቡና ምርት ግብይት የተሰማሩት አቶ አማረ በቀለ እንዳሉት ዘንድሮ  ምርቱን በአንደኛ ደረጃ የግብይት ማዕከላት ብቻ በመግዛት  ለምርቱ ጥራት መጠበቅ  በትኩረት መስራታቸውን ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ ያሰባሰቡትን ስምንት ኩንታል የቡና ምርት ለገበያ ማቅረባቸውን የተናገሩት  ደግሞ በዚሁ ወረዳ የይቢ ማሪ ቀበሌ ነዋሪ  አርሶአደር  ከድር ሁሴን  ናቸው፡፡

የተሰጣቸውን ስልጠና ተከትለው ከምርት ስብሰባ እስከ ገበያ ለጥራቱ  ትኩረት መስጠታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በኢሉአባቦር በቡና ልማት የተሸፈነ ከ160ሺህ  ሄክታር በላይ መሬትና  በልማቱም ላይ የተሰማሩ 150ሺህ ያህል አርሶአደሮች እንደሚገኙ  ከዞኑ ቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ጅማ  መጋቢት  10/2009 የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) በጥልቅ ተሀድሶ ውቅት ህዝቡ ያነሳውን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ የአጋሮ ከተማ አንዳንድ  ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የድርጅቱ 27ኛው ዓመት የምስረታ በዓል በአጋሮ ከተማ የልማት ስራዎችን በመጎብኘትና በፅዳት ዘመቻ ማክበር ተጀምሯል፡፡ 

በጉብኝቱና በጽዳቱ ላይ  ከተሳተፉት ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሜሮን ሃሰን  በሰጡት አስተያየት የከተማው ጽዳት ቅንጅትን የሚጠይቅ ሥራ በመሆኑ  ጽዳቱን ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንሚቀጥሉበት ገልጸዋል፡፡

ለድርጅቱ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት የልማት ስራዎች በመጎብኛትና በጽዳት ዘመቻ  በዓሉን እያከበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሙዲን አባፊጣ የተባሉት ነዋሪ እንዳሉት  በከተማው በአጭር ጊዜ ውስጥ  የተገነባው የጠጠር መንገድ በቀጣይ ሌሎችንም የልማት ስራዎች በተመሳሳይ ለውጤት ማብቃት እንደሚቻል የሚያመለከት ነው፡፡

"የጠጠር መንገድ ከተሰራ በኋላ የትራንስፖርት አገልግሎት በቀላሉ ማግኘት በመቻላችን ውጣ ውረድን በማስቀረት  ጊዜያችንን ለመቆጠብ አስችሎናል" ያሉት ደግሞ የከተማው ዜሮ አራት ቀበሌ ነዋሪ  አቶ ጀሃድ አባዱራ ናቸው፡፡

በቀጣይም  በዓል የሚያከብሩት ኦህዴድ የሚመራው መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚያካሄዳቸውን የልማት ስራዎች በጥራትና በፍጥነት እንዲፈጸሙ የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

የአጋሮ ከተማ አስተዳር ኦህዴድ ጽህፈት ቤት  ተጠሪ አቶ ነዚፍ መሀመድ አሚን " በዓሉን በማስመልከት የተጀመረው የመስረተ ልማት ጉብኝትና የየፅዳት ዘመቻ ከተማዋን ውብ እና ጽዱ ለማድረግ  በነዋሪው ዘንድ መነቃቃትን ለመፍጠር ያለመ ነው" ብለዋል፡፡

ባለፉት  27 ዓመታት በኦህዴድ መሪነት በርካታ ልማቶች የተከናወኑ ቢሆንም  በነበሩ ከፍተቶች ህዝቡ ጥያቄ እንዲያነሳ ምክንያት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሃላፊ አቶ ኤሊያስ ሸረፉ ናቸው፡፡

እንደከተማው በቀጣይ የህዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጠልም አመልክተዋል፡፡

 

Published in ፖለቲካ

ሀዋሳ መጋቢት 10/2009 እየጨመረ የመጣውን የኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራሩን ማጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

ሀገር አቀፍ የኮንትሮባንድና  ህገ ወጥ ንግድ የመከላከል ግብረ ሃይል ያለፉትን ሰባት ወራት እቅድ አፈጻጸም በሃዋሳ ገምግሟል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጫኔ በግምገማው ወቅት እንደገለጹት ኮንትሮባንድና  ህገ ወጥ ንግድ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመከላከል ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው፡፡

ግብረ ሃይሉ ከሶስት ወር በፊት አዳማ ላይ በነበረው የግምገማ መድረክ ክልሎች እንደአካባቢያቸው ሁኔታ እቅድ አውጥተው እንዲንቀሳቀሱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሰባት ወራት ከ414  ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችና የብር ኖቶች በኮንትሮባንድ ከውጭ ሲገቡ መያዛቸውን አመልክተዋል፡፡

ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር የ28 ነጥብ 7 በመቶ የጨመረ ነው፡፡

ከ54 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ ምርቶችና ሌሎችም ከሃገር  ሊወጡ ሲሉ መያዛቸውን አቶ ከበደ ጠቅሰዋል፡፡

የቁም እንስሳት በሚወጡባቸው አካባቢዎች ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ እንቀስቃሴ በመደረጉ ለውጥ መምጣቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ በጠረፍ አካባቢ በሚካሄድ  ንግድ ላይ የሚያግባባ የጋራ መመሪያና ስምምነት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

እየጨመረ የመጣውን ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል በክልሎችና በጎረቤት ሃገራት መካከል ቅንጅታዊ አሰራሩን ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

"ከሃገሪቱ እድገት ጋር ተያይዞ እየተስፋፉ የመጡ መንገዶችን ተከትሎ የሚገቡ ኮንትሮባንድ እቃዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም በመፍጠር በቀጣዮቹ ወራት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ይሰራል "ብለዋል፡፡

በመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች የሚደረገውን ፍተሻ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን ከማጠናከር ባለፈ ህብረተሰቡም ችግሩን እንዲገነዘብ ለማስቻል ሰፊ ንቅናቄ መፍጠር ያስፈልጋልም ተብሏል፡፡

በባለስልጣኑ የህግ ማስከበር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘመዴ ተፈራ በበኩላቸው በኮንትሮባንድ ከሚገቡ እቃዎች 33 በመቶ አልባሳት እና 21 ከመቶ ደግሞ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ቅድሚውን ቦታ እንደሚይዙ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ  አቶ ገመችስ መላኩ እንዳሉት ደግሞ ግብረ ሃይሉ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ መርካቶን የርብርብ ማዕከል በማድረግ በተከናወነው ስራ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

ከተለያዩ የኤሌክትሮክስ መሸጫ ሱቆች 2ሺህ ሞባይሎች፣ በሆቴል ስም በኮንትሮባንድ በሚገቡ ጨርቃጨርቅ ንግድ  ከተሰማራ የሆቴል ድርጅት ከ10 መኪና የሚበልጥ አልባሳት መያዙን ጠቁመዋል፡፡

በምግብ መጠጥና መድሃኒት ዘርፎች ድርጅቶችን ለይቶ በመንቀሳቀስ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው  እቃዎች መወገዳቸውንም አመልክተዋል፡፡

በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የሃዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት  የህግ ማስከበር የስራ ሂደት ባልደረባ ኮማንደር አበበ ሚሻሞ በበኩላቸው ግብረ ሃይሉ ችግሩን ለመከላከል ከሌላው ጊዜ በተለየ መንቀሳቀሱን   ገልጸዋል፡፡

በኬንያ በኩል የሞያሌን አቅጣጫ ይዞ ከሚገቡ አልባሳትና ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች በተጨማሪ የሚገቡ ህገ ወጥ የሞተር ብስክሌቶች  ቁጥር  እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

"የሞተር ብስክሌቶች  ህገ ወጥ ተግባር ለትራፊክ አደጋም እያጋለጡ በመሆናቸው ከጸጥታ አካላት ጋር  በትኩረት በመስራት መፍትሄ የሚበጅላቸው ናቸው "ብለዋል፡፡

በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው  የግምገማ መድረክ ላይ  አዲስ አበባ፣ ትግራይና አማራ የተሻለ አፈጻጸም በማሳየት በርካታ ህገ ወጥ ተሸከርካሪዎች የሚገቡባቸው ደቡብ ህዝቦችና  አሮሚያ  እንዲሁም ቤንሻንጉልና ጋምቤላ ደግሞ በአነስተኛ አፈጻጻም የተመለከቱ ናቸው፡፡

ለሁለት ቀናት የተዘጋጀውና ትናንት በተጠናቀቀው በዚሁ መድረክ ላይ ከፌዴራል ፣ ከዘጠኙም ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የገቢዎችና ጉምሩክ ፣ የጸጥታና ሌሎችም የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች የስራ ሃላፊዎችና ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡ 

 

Published in ኢኮኖሚ

 አዲስ አበባ  መጋቢት  10/2009  በአዲስ አበባ ከተማ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ በተለምዶ ቆሼ በተባለው አካባቢ የተከሰተውን አደጋ ተከትሎ ለተጎጂዎች ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግላቸው የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ገለጸ።

የማህበሩ አባላት ዛሬ በአካባቢው በመገኘት በአደጋው የተጎዱ ነዋሪዎችን ጎብኝተዋል፤ ሐዘን ላይ ያሉ ቤተሰቦችንም አጽናንተዋል።

በአደጋው ሳቢያ 113 ሰዎች ሕይወታቸውን  አጥተዋል። ብዙዎቹ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ ለመኖር ተገደዋል።

እነዚህን ተጎጂዎች ለመታደግና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ከከተማው አስተዳደር ጀምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ተቋማትና ድርጅቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።

በተለያዩ ጊዜያት በአካባቢው ላይ ተገኝተው ጉብኘት ያደረጉና አጋርነታቸውን ያሳዩ የህብረተሰብ አባላት ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋምና ዘላቂ መፍትሄ የመስጠት ጉዳይ በርብርብ እንዲሰራ ይጠይቃሉ።

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ዳይሬክተር አቶ አብረሃም ስዩም እንደተናገሩት፤ አደጋው አስደንጋጭና አስከፊ በመሆኑ የኢትዮጵያን ህዝብ በእጅጉ አሳዝኗል።

በተከሰተው  አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ርብርቡ መቀጠል እንዳለበት ያመለከቱት አቶ አብርሃም፤ ማህበሩ ተጎጂዎችን መልሶ በማቋቋም ተግባር ከመንግስት ጎን በመቆም ድጋፍ  እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት።  

እንደእርሳቸው ገለጻ፤ ማህበሩ ከመንግስት ጎን በመሆን ለተጎጂዎች ሁለገብ ድጋፍ ለማድረግ አቅዷል።

በማህበሩ የሴቶች ፎረም አስተባባሪ ወይዘሮ ኤፍራታ ለማ በበኩላቸው፤ በአደጋው የተጎዱ ሰዎችን መልሶ ለማቁቁም በሚደረገው ጥረት በውጪ የሚገኙና በአገር ውስጥ ያሉትን ዲያስፖራዎች በማስተባበር ገቢ የማሰባሰብ ስራዎችን እየተሰራ መሆመኑን ተናግረዋል።

በዚህም የሚደረገው ድጋፍ ተጎጂዎችን ከማጽናናት ባለፈ መልሶ በማቁቁምና ረገድ ማህበሩ የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚችል  ጠቁመዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2009 ቅዱስ ጊዮርጊስ  በአዲስ አበባ ስታዲየም ከኮንጎው ኤሲ ሊዮፓርድስ ጋር ያደረገውን  የመልስ ጨዋታ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ለመጀመሪያ ጊዜ በሻምፒዮንስ ሊጉ የምድብ ድልድሉ ውስጥ ገብቷል ፡፡  

ቅዱስ ጊዮርጊስ በደርሶ መልስ ጨዋታ ተቀናቃኙን 3 ለ 0 በሆነ ድምር ውጤት አሸንፎ ነው ቀጣዩን ምድብ የተቀላቀለው፡፡

ሳልሃዲን ሰይድ በ16ኛውና በ93ኛው ደቂቃ  ሁለት ግቦችን በስሙ በማስመዝገብ  የሻምፒዮንስ ሊግ  ግቦቹን ወደ አምስት ከፍ አድርጓል፡፡

ፈረሰኞቹ ከሳምንት በፊት ከሊዮፓርድስ ጋር ከሜዳቸው ውጪ አሸናፊ ያደረገቻቸውን ጎል ያስቆጠረው ምንተስኖት አዳነ ቀይ ካርድ በማየቱ በዛሬው ጨዋታ አልተሰለፈም፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ የሻምፒዮንስ ሊጉን የምድብ ድልድል በመቀላቀሉ 550 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ያገኛል፡፡

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2009 "ተጎጂ ቤተሰቦችን መልሶ ለማቋቋም ሕብረተሰቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚያኮራ ነው" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ከሌሎች ሚኒስትሮችና የአስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ዛሬ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ በተለምዶ ቆሼ በተባለው አካባቢ ተገኝተው መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም ምሽት ላይ በደረሰው አደጋ ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦችን አጽናንተዋል።

አቶ ደመቀ፤ ሕብረተሰቡ አደጋው ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ በስፍራው ተገኝቶ ተጎጂዎቹን መልሶ ለማቋቋም እያደረገ ያለው ርብርብ የሚያኮራና የሚያበረታታ መሆኑን ነው የገለጹት።

''አደጋው የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ልብ የሰበረና አሳዛኝ ነው'' ያሉት አቶ ደመቀ፤ በተለይ ደግሞ ሴቶችና ህጻናት ከተጎጂዎቹ መካከል ከፍተኛ ቁጥር መያዛቸው የበለጠ አሳዛኝ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስትም ይህንኑ በመገንዘብ ብሔራዊ የኃዘን ቀናት ከማወጅ ባለፈ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም በከተማ አስተዳደሩ አማካኝነት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል።

ህይወታቸው ያለፉ ዜጎችንም በተቻለው ሁሉ ስርዓተ ቀብራቸው እንዲፈጸም ማድረጉን ገልጸው፤ በቀጣይ የሚጠረጠር ቦታ ካለ "ፍለጋው ይቀጥላል ነው" ያሉት።

"መንግስትና ሕብረተሰቡ ተባብረው ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ይረባረባሉ" ብለዋል።

በተለይ ደግሞ አስከሬን በመለየትና በመፈለግ በጣም ፈታኝ የሆነ ስራ በመስራት የዜግነት ግዴታቸውን ሲወጡ የቆዩ የአካባቢው ወጣቶች፣ ነዋሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ምስጋና እንደሚገባቸው በአጽንኦት ገልጸዋል።

በአካባቢው ያሉ ቤቶች በጥናት ላይ በተመሰረተ መንገድ እንደሚነሱ ገልጸው፤ "ዜጎች የተረጋጋ ህይወት እንዲመሰርቱ የማስቻል ስራም ይከናወናል" ነው ያሉት።

በአደጋው ምክንያት ችግር ያጋጠማቸው ሕጻናትም ትምህርታቸውን ጨምሮ ሌሎች መደበኛ ሕይወታቸውን የሚመሩበት መንገድ እንደሚመቻች ተናግረዋል።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በተወሰነ መልኩ የጀመረው ስራ መኖሩን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአደጋው መንስኤ ምን እንደሆነ የከተማ አስተዳደሩ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አስጠንቶ ዘላቂ መፍትሄ የማዘጋጀት ስራም በትኩረት እያከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል።

ኃዘኑ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ተጎጂዎቹን በዘላቂነት ማቋቋም እስከሚቻል ድረስ ሁሉም ሰው የድርሻውን ርብርብ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2009 በአዲስ አበባ የብስክሌት ክለቦች ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አሸናፊ ሆኑ።

በአዲስ አበባ ብስክሌት ፌደሬሽን የተዘጋጀው ሻምፒዮና ዛሬ ሲጠቃለል 40 ኪሎ ሜትር የሸፈነ ውድድር በስታዲየም አካባቢ ተካሂዷል።

በዚሁ የአጠቃላይ ውጤት የወንድ ኮርስ ውድድር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እና በማውንቴን ውድድር የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የዋንጫ አሸናፊ መሆን ችለዋል።

ለአንድ ዓመት ያህል በሁለቱም ፆታ በማውንቴንና በኮርስ የብስክሌት ውድድር ታዳጊዎችን ጨምሮ በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች  ተካሂደዋል።

በዚህ ሻምፒዮና የቡድን  ወንዶች ማውንቴን ውድድር የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የዋንጫ አሸናፊ ሆኗል።

የካ ክፍለ ከተማና ጋራድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስፖርት ክለብ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ማሸነፍ ችለዋል።

በተመሳሳይ በቡድን የወንድ ኮርስ ውድድር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አሸናፊ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና የአፍሪካ ስደተኞች ስፖርት ክለቦች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ረዘነ በየነ እንደገለጹት፤ አምስት ክለቦችን ያሳተፈው የአዲስ አበባ ክለቦች ሻምፒዮና የብስክሌት ውድድር ዋና ዓላማው ታዳጊዎችን ማፍራት ነው።

የብስክሌት ስፖርትንም ለማስፋፋት ውድድሮችን የማብዛት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ለአንድ ዓመት ያህል ሲካሄድ የቆየው ይኽው ውድድር ታዳጊ ወጣቶችን ጨምሮ  አምስት ክለቦች የተሳተፉበት ከ16 ጊዜ በላይ ውድድሮች መካሄዳቸው ተውቋል።

በግልና በቡድን ከአንድ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ለወጡ ተሳታፊዎችም የሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

Published in ስፖርት

አዳማ መጋቢት 10/2009 አስር  ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ የተመደበለት የወጣቶች የልማትና የእድገት ስትራቴጂ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ  ወደ ትግበራ ምዕራፍ መሸጋገሩን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳ ገለፁ ።

ሶስት ሚሊዮን ስራ አጥ ወጣቶች ወደ ስራ ለመግባት ተመዝግበዋል።

ሚኒስትሩ ለኢዜአ እንደገለፁት በስትራተጂው የዝግጅት ምዕራፍ  በህብረተሰቡና በወጣቱ ዘንድ በቂ ግንዛቤ የመፍጠር ፣ የስራ ፈላጊ ወጣቶች ብዛትና በምን ስራ መሰማራት እንደሚፈልጉ የመለየት ስራ ተከናውኗል፡፡

ለስትራተጂው ማስፈፀሚያ የተመደበውን በጀት ደልድሎ ወደ ታች የማውረድና የመስሪያና የመሸጫ ፍላጎት ለይቶ የማወቅ ስራዎችም እንዲሁ።

በእስካሁኑ ሒደት በሁሉም ክልሎች 3 ሚሊዮን ስራ ፈላጊ ወጣቶች ተመዝግበው በማደራጀትና ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ የማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ሚኒስትሩ ተናግረዋል ።

የተመደበው ገንዘብ  ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል  የህግ ማእቀፍ ተዘጋጅቶለት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስተባባሪነት በየክልሉ ለተመረጡ  11 የፋይናንስ ተቋማት እንዲደርስ ተደርጓል።

ሚኒስትሩ እንዳመለከቱት የበጀት ድልድሉ ክልሎች ባላቸው ስራ ፈላጊ ወጣት ቁጥር ተደልድሎ እስከ ታች ድረስ ወርዷል፤ስትራቴጂው የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ ወደ ትግበራ ተሸጋግሯል ።

በአዲሱ የወጣቶች የልማትና የእድገት ስትራቴጂ ቅድመ ዝግጅት ከማድረግ ጎን ለጎን በነባሩ የወጣቶች የልማት ፓኬጅ በዘንድሮው የመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት ለ600 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል እንደተፈጠረም ጠቁመዋል።

በሚኒስቴሩ የወጣቶች ማካተትና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ማቲያስ አሰፋ በበኩላቸው  መንግስት በመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ ዘንድሮ በገጠር 1ነጥብ 7 ሚሊዮን በከተማ ደግሞ 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

ከታቀደው ውስጥ የተመዘገቡት  ወጣቶች  3 ሚሊዮን ናቸው ።

እስካሁን በደረሰው መረጃ መሰረት ትግራይ ወደ ትግበራ መግባቱንና አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመው " ሁሉም ክልሎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ይገባሉ "ብለዋል ።

ተዘዋዋሪ ፈንዱ  ወጣቶችን ማዕከል አድርጎ ሴቶችን ፣አካል ጉዳተኞችንና ለሌላም ችግር  የተጋለጡ ወጣቶችን ለማብቃት ልዩ ትኩረት ይሰጣል ተብሏል።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ለፌደራልና ለክልል መገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች  በወጣቶች ዘገባ ላይ ለሁለት ቀናት በአዳማ ከተማ ያዘጋጀው ስልጠና ትናንት ተጠናቋል።

Published in ኢኮኖሚ
Sunday, 19 March 2017 16:21

ያልገታነው “ናዳ”

በረከት ሲሳይ (ኢዜአ)

ፀሀይ ንዳዷን ጨርሳ ቀኑ ማለፉን ለማብሰር ስታዘቀዝቅ፤ ጀንበር መጥለቋን ተንተርሶ ሠማዩ ሲቀላ፤ ከዚህ ሠማይ ሥር ቀኑን ሙሉ ላይ ታች ሲል ኑሮን ለማሸነፍ ሲዋትት የዋለው የአዲስ አበባ ነዋሪ አንዳንዱ በባቡር፣ ሌላኛው በአውቶብስ፣ ገሚሱ በታክሲ፤ አንዱ በአንዱ ላይ ተደራርቦ አልያም ደግሞ በእግሩ እየተጓዘ “ዞሮ ዞሮ ከቤት” እንዲሉ ማልዶ የወጣበትን ቤቱን ከአመሻሹ ዳግም ለመመለስ የሚያደርገው ትግል ሁሌም የምንታዘበው የከተማችን ማኅበራዊ  ትዕይንት ሆኗል።

 

ከዚህ ሁሉ ትርምስና ግርግር ጀርባም በርካታ አዛውንቶች፣ ሕጻናት፣ አቅመ ደካሞች በሌላቸው አቅም ከጉልበታሙ ወጣት ከተሜ ጋር መሳ ለመሳ ቆመው የአቅማቸውን ተፍጨርጭረው ከቤታቸው ደጃፍ ይደርሱ ዘንድ የሚያደርጉትን ትንቅንቅ በአንክሮ ለሚመለከት ትካዜ የሚጭር ሌላኛው የአደባባይ ክስተት ነው።

 

ከዚሁ ሁሉ በኋላ፤ በለስ ቀንቶት የተሳፈረ ምንም እንኳን በሙሉ መቀመጫ ሳይቀመጥ፣ በኩርሲና ባለቀ የመኪና ባትሪ ፕላስቲክ ላይ ተቀምጦ፤ ከከፈለው ገንዘብ የሚገባውን መልስ ሳይቀበል ጉዞውን እንዲገፋ ይገደዳል።

 

እንደ ጀት እየበረረ በሚሄደው በዚሁ ተሽከርካሪ ወስጥም ግራና ቀኙን እያማተረ ነፍስና ስጋው ተላቆ “ኧረ! ሹፌር ቀስ ብለህ ንዳ እንጂ” ብሎ በኃላፊነት መንፈስ ላቀረበው ማሳሰቢያ “ምን አገባህ?” የሚል “ዱቄት ላበደረ አመድ” ዓይነቱ መልስ ይሰነዘርበታል። በዚኅ መሰሉ በተለያዩ ተዕይንቶች በታጀበ ጉዞ  ከቤቱ! ከቀዬው! ይደርሳል። ይህ አኳሀኋን በራሱ እንግልት ቢሆንም፤ በሰላም ከቤቱ መድረስ መቻሉን ሲያስብ ለአምላኩ ምስጋና አቅርቦ ነገ የተሻለ እንዲሆን ከመመኘት ውጪ ሌላ ነገር የማድረግ አቅም የሚኖረው አይመስለኝም። ለምን ቢሉ? የዕለት ጉርስ ፍለጋ ደፋ ቀና ብለው ቤታቸው ለመመለስ ወጥነው በትራፊክ አደጋ ምክንያት ወጥተው የቀሩ ወገኖች በርካታ መሆናቸው ነው። ጎበዝ! አያሌዎች ደግሞ ለከባድ አካል ጉዳት ተዳርገው ከሥራ ገበታቸው ርቀው፤ ከቀለም ትምህርታቸው ተስተጓጉለው በአንድ ጀንበር የአልጋ ቁራኛ በመሆናቸው ተስፋቸው ነጥፎ አዲስ ነገር ሳይታያቸው ዘመናቸውን ይቆጥራሉ። ከእነዚህ ሰዎች ጀርባም፤ በርካታ ሰዎችም የዕለት ተዕለት ኑራቸው  ሲመሰቃቀልባቸው፣ ያረፉ እጆች ያሏቸው እናቶችና አባቶች ደግሞ ጧሪ ቀባሪ አጥተው ሞታቸውን ይማጸናሉ።

ይህን ኩነት ተግ ብሎ ለሚከታተለው አስተዋይ ሰው፤ ጉዳዩ የሚያስተክዝ በንጹህ ህሊና ሲታይም የስንቱን ቤት ደስታ ገፎ ማቅ ያጎናጸፈ በመሆኑ እንባ ያራጫል። እውነት ለመናገር፤ ዛሬ በአገራችን ተሽከርካሪ ማሽከርከርም ሆነ ተሳፍሮ መሄድ በሞት ጥላ መካከል የመሄድ ያክል አስፈሪነቱን እኔ ከማስነብባችሁ በላይ ራሳችሁ ታውቁታላችሁ።

በየቀኑ በሚደርሱ አደጋዎች ልክ ተቆጥሮና ተሰፍሮ እንደሚሰጥ ያክል ገና ማልደን ስንነሳ በራዲዮ ከምንሰማው ቀዳሚ ንጋት ፈንጣቂ ክፉ ዜና ከሆነ ሰነባብቷል። በጣም የሚገርመው ደግሞ የትራፊክ አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ “ኧረ በእውነቱ ወዴት እየሄድን ነው ጎበዝ” ያሰኛል። ለምሳሌ ያክል ያለፈውን ዓመት እንኳን መረጃ ብናጣቅስ 4 ሺ 352 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ከ13 በላይ ደግሞ ለቀላልና ለከፋ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል። “ለችግሩ ዋነኛ መንስኤ ምንድን ነው?” ተብለው ለሚቀርቡት ጥያቄዎች በዋነኝነት በአገሪቷ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት አለመሟላት፣ የግንዛቤ ማነስ፣ የአሽከርካሪዎች ሙያና ሥነ - ምግባር ጉድለት - ለዚህም ደግሞ የተጠናከረ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት አለመኖር፣ ለመንገድ ደኅንነት ተብለው የሚወጡ ሕጎችና ደንቦች ተፈጻሚነት አለመኖር፣ የአስፈጸሚ አካላት የሥራ ግድፈትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ይነሳሉ።

ይሁን እንጂ ለበርካታ የትራፊክ አደጋዎች በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የአሽከርካሪዎች የሙያና የሥነ - ምግባር ጉድለት መሆኑን ልብ ይሏል። ይህ ምክንያት እኔም እንደ አንድ ዜጋ ለሚከሰቱት አደጋዎች ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን በሙሉ ልቤ አምናለሁ። ይህ ከሁለት መልኩ ሊመጣ የሚችል ችግር መሆኑንም እገነዘባለሁ፤ አንድም በቸልተኝነትና ሌላም በግንዛቤ ማነስ ብዬ ለማስረደት እሞክራለሁ። ቸልተኝነት ስል በርካታ የአሽከርካሪ ፍቃድ ማረጋገጫ ከሚመለከተው ህጋዊ አካል የያዙና ነገር ግን በትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በተገቢው መልኩ የማይፈጽሙ ናቸው። ለምን ብለን እራሳችንን ከዚያም እነኚሁ አሽከርካሪዎችን በምንጠይቃቸው ጊዜ መልሱ ያለ ምንም ምክንያት መሆኑን ስንረዳ ጉዳዩ ቸልተኝነት መሆኑን እናውቃለን። ኧረ እንደው አንድ ግለሰብ በፍጥነት ማሽከርከር አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል እያወቀ፤ የትራፊክ የመንገድ ዳር ምልክቶች፣ የትራፊክ መብራቶች  እንዲሁም ትራፊክ ፖሊስ አለማክበር የሚያመጣው ጉዳት የከፋ መሆኑን እያወቀ፣ ለእግረኞች ቅድሚያ አለመስጠት ህይወት እንደሚቀጥፍ እያወቀ እንዴት ሰው ተጠንቅቆ አያሽከረክርም? ለምንስ እርሱ አጥፍቶ ለሌሎች የጥፋት ሳንካ ምክንያት ይሆናል? ያው ቸልተኝነት ነው፤ ሌላ ምክንያት ያለው አይመስለኝም።

በሁለተኛ ደረጃ የግንዛቤ ማነስ ነው ብዬ የማነሳው በሁለት መንገዱ ቢታይ መልካም ይመስለኛል። አንደኛው ግንዛቤ ሊመጣ የሚችለው በሚሰጡ የትምህርትና የሥልጠና መርኃ ግብሮች እንጂ ግንዛቤ በራሱ እንደ ውቃቢ ሊሰፍር የሚችል ነገር አይደለም። በመሆኑም በአሽከርካሪዎች ላይ የሚስተዋለው የግንዛቤ ማነስ በቂ ትምህርትና ሥልጠና ባለመውሰዳቸውና ወደ ሙያው የገቡት በልምድ መሆኑ ነው። ይህስ እንዴት ነው ቢሉ? በአሁኑ ወቅት በትክክለኛው መንገድ ተከትለው የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ የሚወስዱት ምን ያክል ናቸው? የሚል ጥያቄ ቢነሳ የሚገኘው ምላሽ “በጣም ትንሽ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች” የሚል ይመስለኛል። በርካታ ሰው ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ በሰው በሰው ሕጋዊ ፍቃድ ያላቸው እንዲሁም ሕገ-ወጥ ፍቃድ ያላቸው መሆኑን ነው የምንረዳው። ቀላል የማይባሉ ደግሞ ያለ አሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ የሚያሽከረክሩ መሆናቸው ሌላኛው ሁኔታዎችን በትክክል የሚገልጽልን እውነታ ነው። ለምሳሌ ያክልም ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ ብቻ ከ700 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ሳይኖራቸው ሲያንቀሳቅሱ ተገኝተዋል፤ በዚህች መዲና 15 ግለሰቦች ደግሞ በጥር 2009 ዓ.ም ብቻ ሕገ-ወጥ የአሽከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ይዘው ተገኝተዋል። 

 

በሁለተኛ ደረጃ ያለው የግንዛቤ ማነስ ሊመነጭ የሚችለው በአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት የሚሰጡት ትምህርቶች ጠንክራ ካልመሆናቸው አልያም ደግሞ ለሥልጠናው የሚጠየቀው የትምህርት ደረጃ አነስተኛ በመሆኑ ግለሰቦች ጉዳዩን በቅጡ ካለማጤናቸው ነው ባይ ነኝ። አንዳንድ የማሰልጠኛ ተቋማት በቂ ሥርዓትን የተከተለ የሥልጠና መርኃ ግብር እንደሌላቸው በሥፋት የሚነገር ሲሆን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድም በቀላሉ እንደሚሰጡ ነው የሚነገረው። በሌላ በኩል አንድ ግለሰብ “አራተኛ ክፍል ከጨረሰ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም ገብቶ መሰልጠን ይችላል” የሚለው መርህ በራሱ በሥልጠናው ወቅት በሠልጣኞች ረገድ የጋራ መግባባት ወይንም ተግባቦት እንዳይኖር ያደረገ ሌላው ምክንያት ይመስለኛል። ይህም ወደ ሙያው ተቀላቅለው በሥራ ላይ የሚገጥማቸውን የቴክኒክና የሙያ ሥነ-ምግባራት ከማወቅ በዘለለ በገቢር ጥቅም ላይ አውለው ሊደርስ የሚችለውን የትራፊክ አደጋ መከላከል አለመቻላቸው ይህንኑ ያሳያል።

 

በቀላሉ ይህንን ለማጠናከር በአሽከርካሪዎች ሥልጠና መርህ መሰረት አንድ አሽከርካሪ ሊያደርገው የሚገባ ጥንቃቄ ተብሎ ከተዘረዘሩ መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል አንድ አሽከርካሪ፤ ተሽከርካሪ ውሰጥ ከመግባቱ በፊት፣ የተሽከርካሪውን ኮፈን ከፍቶ፣ ተሽከርካርካሪ ውስጥ ከገባ በኃላና በእንቅስቃሴ ወቅት ተገቢውን ፍተሻ ማድረግ እንዳለበት ያስገድዳል። ምን ያክሉ አሽከርካሪ ይሆን ይህንን የሚያደርገው ? እኔ በበኩሌ በዚህ ረገድ ጥርጥር አለኝ። ከዚያ በዘለለ በከተማና በሌሎች በደረጃ አንድ ሁለት እንዲሁም ሦስት ተብለው እንደ አሽከርካሪ ዓይነቶቹ የተጠቀሱት የመንገድ የፍጥነት ወሰን የሚያከብሩት ሹፌሮች ምን ያክሉ ናቸው? እነዚህንና በመንገድ ደህንነት ዙሪያ የሚነሱትን ጥያቄዎች እያሰላሰላችሁ ለራሳችሁ መልስ ከመስጠት በዘለለ የበኩላችሁን ትወጡ ዘንድ ምኞቴ ነው። ይሁንና እኔም በአገራችን ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በቀዳሚነት የአሽከርካሪዎች የሙያና የሥነ-ምግባር ጉዳይ በቅጡ ሊጤን እንደሚገባ ነው የማስበው።

 

ይህ በተለይም ለአሽከርካሪዎች የሚሰጠው የብቃት ማረጋገጫ ሥልጠና አሁን ካለበት የጊዜ ሰሌዳ ሊራዘም እንደሚገባና ቴክኒካል የሆኑ ጉዳዮች ላይ ትክክለኛ ገንዛቤ መፈጠሩን ማረገጋገጥ ተገቢ ይመስለኛል።  ከዚህ ጎን ለጎን፤ በሥልጠና ተቋማት የሚሰጡት የሥነ-ባህሪ ትምህርቶች በአሽከርካሪዎች ላይ ለውጥ እንዲያመጣ ከተፈለገ የተመደበው ጊዜም እንደ ቴክኒክ ክፍሉ ሊጠናከር ይገባል። በሌላ በኩል የሚጠየቀው የትምህርት ደረጃ አሁን ካለበት አራተኛ ክፍል እንደው ቢያንስ ከስምንተኛ ጀምሮ ቢሆን ይህም ግንዛቤ ለመፍጠር ቀላል የሚያደርገው ይመስለኛል። እነዚህ ከላይ የተደረጉት ጉዳዮች የሚሟሉ ከሆነ ቀሪው ለትራፊክ መንገድ ተብለው የሚወጡትን ሕጎችና ደንቦች በመጀመሪያ ከሚመለከተው አካል ጋር ስለ አስፈላጊነቱ መግባባት በመፍጠር ለተግባራዊነቱ መረባረብ ያስፈልጋል። በተለይም ሕግን- ተላልፈው በሚገኙ አሽከርካሪዎች ላይ ተገቢውን ቅጣት መጣልና ከድርጊታቸው እንዲማሩ ማድረግ ለነገ የማይባል መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። በአሽከርካሪዎች ላይ የሚካሄደው ፍተሻም በኃላፊነት ስሜት የሚደረግ መሆኑን ማረጋገጥም እንዲሁ ትኩረት ያሻዋል።

 

ኅብረተሰቡም ህግንና ደንብን በማወቅ፣በማክበር እንዲሁም ሊጣሱ ሲሉ በመከላከል እንዲሁም ተጥሰው ሲገኙም ለአስፈላጊ እርምት እርምጃ መተባበር ይገባል። ሌላው በረጅም ጊዜ እቅድ፤ የከተማዋን የመንገድ መሰረተ ልማት ማሟላትና የትራንስፖርት አቅርቦቱንም በማሻሻል ዘርፉን የተሻለ ማድረግ እንደሚገባ ይሰማኛል።  የትራፊክ አደጋ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን በየዓመቱ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን በላይ ሰዎችን ህይወታቸውን የሚነጥቅ ነው፤  በአሁኑ ወቅት እድሜያቸው ከ15 አስከ 29 የሆኑ ወጣቶች በቀዳሚነት ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉት በትራፊክ አደጋ መሆኑንም የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። ከእነዚህም አደጋዎች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት አደጋዎች የሚከሰቱት በእድገት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ባሉ የዓለም አገሮች ሲሆን፤ በአንጻሩ በእነዚህ አገሮች ያለው የትራንስፖርት አቅርቦት ደግሞ ዝቅተኛ መሆኑን ነው የተመለከተው። ለችግሩ ምንም ዓይነት መፍትሄ የማይሰጠው ከሆነ የትራፊክ አደጋ ተባብሶ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030  ዓለም ላይ ካሉ ገዳይ በሽታዎች መካከል ሰባተኛ ደረጃን ይቆናጠጣል ተብሏል።  ይህም የችግሩን ግዝፈትና ለመፍትሄውም የሁሉም ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው።

 

ይግረማችሁና ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ምከንያት የሆነኝ ከሳምንታት በፊት ቤተሰብ ጠይቀው ከጎጃም ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ በተሽከርካሪ አደጋ ህይወታቸውን ባጡት ባለትዳሮች ነበር። ከዚህም በመቀጠል ከቀናት በፊት በትራፊክ አደጋ መንስኤና መፍህትሄ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በተካሄደው ስብሰባ ላይ የትራፊክ አደጋ የደረሳባት አንዲት ወጣት ስላለችበት ህይወት የተናገረችው ንግግር እኔን ብቻ አይደለም ብዙዎች የስብሰባው ታዳሚዎችን ቅስም የሚሰብር መሆኑም ሌላው ለመጻፌ ገፊ ምክንያት ነው።  በሚያሳዝን መልኩ ይህንን ጽሁፍ በማዘጋጅበትም ወቅት አራት የካቶሊክ ደናግላን ህይወታቸውን በትራፊክ አደጋ ማጣታቸውን ስሰማ ስለጉዳዩ አውርተን አፍታም ሳንቆይ ሌላ አዲስ አደጋ ተቀባይ መሆናችን የችግሩን ግዝፈት የሚያሳይ ነው።

 

የትራንስፖርት ሚኒስትር  ዴኤታ አቶ አብዲሳ ያደታ እንደተናገሩት፤ የጊዜ ጉዳይ ነው አንጂ የትራፊክ አደጋ ኃይ ባይ የማባይባል ከሆነ የሁሉንም በር ያንኳኳል። ትምህርት አዘል መልዕክት “እኽ” ብሎ በመስማት ነገን የተሻለ ለማድረግ እንረባረብ።

Published in መጣጥፍ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን