አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Saturday, 18 March 2017

አዳማ መጋቢት 9/2009 የግብርና ሥራውን በማዘመን በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ዓመታዊ የግብርና ምርትን ወደ 500 ሚሊዮን ኩንታል ማሳደግ እንደሚቻል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር አስታወቀ።

በመጀመሪያ ደረጃ የአፈር ለምነት የንቅናቄ ሰነድ ዙሪያ የሚመክር አገር አቀፍ የውይይት መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዶክተር ኢያሱ አብርሃ የውይይት መድረኩን ሲከፍቱ እንደተናገሩት በአገሪቱ ትርፍ ምርት ማምረት እየተቻለ ግብርናን ማዘመን ባለመቻሉ ስንዴ፣ የብቅል ገብስ፣ ዘይትና የመሳሰሉ የግብርና ምርቶች ዛሬም ከውጭ እየመጡ ነው።

በአገር ውስጥ ትርፍ ምርት ማምረት እንዲቻል ሞዴል አርሶአደሮች የምርምር ውጤቶችን ተጠቅመው እንዲያመርቱ ከማድረግ ባለፈ ቁጥራቸውን አሁን ካለበት 22 በመቶ ወደ 50 በመቶ ማሳደግ ያስፈልጋል።

ዩኒቨርሲቲዎችንና የምርምር ማዕከላትን በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በመሰረት ልማት በማጠናከር ቴክኖሎጂ እንዲያፈልቁ ፣ እንዲያላምዱና እንዲያባዙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ነው የገለጸት።

ከእዚህ በተጨማሪ የዝናብ እርሻንና የመስኖ ልማት ሥራውን በክላስተር በማከናወን በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ዓመታዊ የአገሪቱን ምርት ከ400 እስከ 500 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት እንደሚቻል ዶክተር ኢያሱ አስረድተዋል።

"በግብርና ስራው ትርፍ ማምረት ብቻ ሳይሆን የሚመረተው ምርት የዓለም ገበያን ታሳቢ ያደረገ፣ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በግብአትነት የሚያገለግልና ከውጭ የሚገባውን በመተካት የውጭ ምንዛሬ የሚያድን መሆን ይኖርበታል" ሲሉም ተናግረዋል።

በአገሪቱ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዓመት መጨረሻ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት ዕቅድ መያዙንና እስካሁን ድረስ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር ለማልማት መቻሉን ገልጸዋል።

የአፈር ለምነት ሥራ የተጠናከረ ባለመሆኑ የአፈር አሲዳማነትና ጨዋማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል።

"የአፈር ለምነት ሥራውን አጠናክሮ መምራት ካልተቻለ ትርፍ ምርት ማምረት አይቻልም" ያሉት ሚኒስትሩ፣  ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት በዘርፉ እንዲረባረቡ አሳስበዋል።

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶከተር ካባ ዑርጌሳ በበኩላቸው፣ ከአገሪቱ የእርሻ መሬት 43 ከመቶ አሲዳማ፣ 19 ከመቶ ኮትቻ፣ አምስት በመቶ ጨዋማ መሬት መሆኑን ተናግረዋል።

የመሬቱን ለምነት በማሻሻል ምርታማነትን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

"የኮትቻ መሬትን አንጣፍፎ በመጠቀም በዓመት ሁለትና ከዚያ በላይ በማምረት ምርታማነት ማሳደግ እንዲሁም አሲዳማ መሬትን በማከም አሁን የሚሰጠውን ምርት በሦስት እጥፍ በመጨመር ዕቅዱን ማሳካት ይቻላል" ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ ተመራማሪዎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ዘርፉ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

ተሳታፊዎቹ በተለያዩ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ቴክኖሎጂዎች፣ አሰራሮችና ተሞክሮዎች ዙሪያ በመወያየት በዘንድሮው የእርሻ ወቅት የአፈር ለምነት ንቅናቄ ሰነዱን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመተግበር የሚያስችል አቅጣጫ ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ መጋቢት 9/2009 የአዳማ ከተማን የጎርፍ ስጋት በዘላቂነት ለመፍታት  የሚያስችል  65 ሺህ ነዋሪዎች የሚሳተፉበት የተራራ ላይ  የተፋሰስ ልማት ዘመቻ  ዛሬ ተጀመረ ።

ህዝቡ ከሚሰራቸው የተፋሰስ ልማት በተጨማሪ የአዳማ ከተማ አስተዳደር 150 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ ዘላቂ የጎርፍ መከላከል ተግባር እያካሄደ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ  አዳነች ሐቤቤ  ገልፀዋል ።

ከንቲባዋ የልማት ስራ ሲጀመር እንዳሉት  ዓመታትን ያስቆጠረውና ክረምት በመጣ ቁጥር የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ስጋት የሆነውን የጎርፍ አደጋ በዘላቂነት መከላከል ይገባል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት  መስተዳድሩ ፣ ባለሃብቶችና ነዋሪዎች የየድርሻቸውን ለይተው በማወቅ ወደ ተግባር ገብተዋል ።

አስተዳድሩ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ዘላቂ የጎርፍ መከላከያ ጥናት በማካሄድ ለመጀመሪያው ምዕራፍ 150 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን ከንቲባዋ አመለክተዋል፡፡

በተመደበው በጀትም " አዳዲስ የጎርፍ መውረጃ ቦዮች ግንባታ ፣ ነባር መውረጃዎች መጠገንና ማፅዳት ፣ የተደፈኑ ቦታዎች ከቆሻሻ ነፃ ማድረግና የአፈር መከላከል ስራ በማካሄድ ላይ ነው "ብለዋል ።

ዋነኛ የጎርፍ ምንጭ እንደሆኑ በሚታመንባቸው የሚጊራ ፣ ደንበላና ለከ አዲ ተራሮች ላይ ለ30 ቀናት የሚቆይ የተፋሰስ ስራ ዘመቻ ዛሬ የተጀመረው የከተማው ነዋሪ ህዝብ  " አዳማን ከጎርፍ ለመታደግ የላብ እንጂ የህይወት መስዋእትነት አይጠይቅም"  በሚል መርህ ነው፡፡

በዘመቻው 65 ሺህ የከተማው ነዋሪ ህዝብ የሚሳተፍ  ሲሆን ከበጋው የተፋሰስ ስራ በተጨማሪ በመጪው ክረምት 3 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል መታቀዱንም  ከንቲባዋ ተናግረዋል ።

"የጎርፍ ስጋቱ መፍትሔው በእጃችን ነው " ያሉት ከንቲባዋ ህዝቡ ዛሬ የጀመረውን የጎርፍ መከላከል ዘመቻ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል ።

የከተማዋ ባለሃብቶች በበኩላቸው በህብረትና በተናጠል ጎርፍ ሰብሮ ሊወጣባቸው ይችላል ተብለው የሚጠረጠሩ አካባቢዎችን  በማጠናከር የድርሻቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል ።

Published in አካባቢ

ባህር ዳር መጋቢት 9/2009 በገጠር መሬት ኢንቨስትመንት የሚፈጸሙ ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግሩን ማፋጠን እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ።

በገጠር ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚመክሩበት መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በክልሉ ሰሜንና ምዕራብ ወረዳዎች ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሰፋፊ መሬቶች መኖራቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የመሬት ሃብትን በተገቢው መንገድ በማልማት ለአገራዊ እድገቱ ማዋል እንደሚገባ አመልክተዋል።

የክልሉን ምርታማነት ለማሳደግ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች በዓለም ላይ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን፣ እውቀትንና ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችን በማምጣት የራሳቸውንም ሆነ የአርሶአደሩን የአመራረት ዘይቤ መለወጥ እንዳለባቸው እስገንዝበዋል።

አቶ ገዱ እንዳሉት መንግስትና ሕዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ ለሚገኙ ውሱን ባለሃብቶች የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል።

በሌላ በኩል የገቡትን ውል የማያከብሩ፣ ማህበራዊ ኃላፊነትን የማይወጡና በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር የተዘፈቁ ባለሃብቶችን በመለየት የማስተካከያ ርምጃ እንደሚወሰድ አመልክተዋል።

በተለይ በኢንቨስትመንት ስም የሚፈጸሙ ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግሩን ማፋጠን አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

የምክክር መድረኩ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችና የችግሮችን ምንጭ ከመለየት ባለፈ ለመፍትሄው በላድርሻ አካላት የጋራ መግባባት የሚፈጥሩበት እንደሆነም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጸጋ አራጌ በበኩላቸው በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ከአንድ ሺህ 900 በላይ ባለሃብቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ባለሀብቶቹ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ለሚደርሱ ሥራ አጥ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ነው ያስረዱት።

አቶ ጸጋ እንዳሉት፣ ባለሃብቶቹ ምርታማነትን በማሳደግ የክልሉ ልማት እንዲፋጠን፣ ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርና ልምድና ተሞክሮን በማምጣት ባለፉት ዓመታት የድርሻቸውን ተወጥተዋል።

በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደስራ ከገቡት ውስጥ ከ 97 በመቶ በላይ የሚሆኑት በሰብል ማምረት ሥራ መሰማራተቸውን ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ የገለጹት ደግሞ በቢሮው የገጠር ኢንቨስትመንት የሥራ ሂደት መሪ አቶ ኡመር ጣሂር ናቸው።

ባለፈው ዓመት ከአበባ ልማት ብቻ 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ጠቅሰው፣ ከሰብል ልማት ውጭ ያሉ ዘርፎች ውጤታማ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

በዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በሚያስገኙና ሰፊ የሥራ ዕድል በሚፈጥሩ የአበባ፣ የደን፣ የምርጥ ዘር ብዜት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የአግሮ ኢንዱስትሪ ልማት ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥራቸው ዝቅተኛ መሆኑንም አመልክተዋል።

በተጨማሪም "በውል የወሰዱትን መሬት አለማልማት፣ ለሌላ ማከራየት፣ ከአርሶ አደሩ የተለየ አመራረት ዘይቤን አለመከተል የተስተዋሉ ችግሮች ናቸው" ሲሉ በጥናቱ አቅርበዋል።

አቶ ኡመር እንዳሉት፣ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት መሰረት በግብርና ኢንቨስትመንት ከሚጠበቀው 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ባለይ ምርት በአሁኑ ወቅት የተመረተው 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነው።

በጎንደር ከተማ ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው ኮንፈረንስ  ባለሃብቶች፣ የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የዘርፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2009 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመደራደሪያ ረቂቅ ሰነድ "በድርድሩ ወቅት አደራዳሪ ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም?" በሚለው ሃሳብ ላይ በተጨማሪ ለመወያየት በቀጠሮ ተለያዩ።

በምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅና ያላቸው 21 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ከኢህአዴግ ጋር የሚደራደሩበት ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጅቷል።

በዚህ ረቂቅ ሰነድ ላይ እስካሁን "የድርድሩ አላማ" ከሚለው ውጭ በሰነዱ ስያሜ፣ በድርድሩ ሂደት እንዲሁም አደራዳሪ በሚሉ ይዘቶች ላይ ገና መስማማት ላይ አልደረሱም።

ኢህአዴግን ጨምሮ 22ቱ ፓርቲዎች በድርድር ወቅት "ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም" በሚለው ሃሳብ ላይ በሁለት ጎራ ተከፍለው ሲከራከሩ ቆይተዋል።

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድርድሩ በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት የሚኖረውና ድርድር የሚባለው ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ ሲኖረው ብቻ መሆኑን ይገልጻሉ።

ኢህአዴግ በበኩሉ ድርድሩ በህዝብ ዘንድ ተዓማኒ እና በግልጽ እንዲቀርብ ለማድረግ "ታዛቢ እንጂ አደራዳሪ አያስፈልገንም" የሚል አቋም አንጸባርቋል።

ፓርቲዎቹ "ሁለቱን የተለያዩ ሃሳቦች ማስታረቅ ካልተቻለ በሌላ ጉዳይ ላይ መወያየት አንችልም" በማለት ሃሳቡን በየግላቸው ዓይተው ለመወሰን ቀነ ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

በተመሳሳይ  ድርድሩ "በግል ወይስ በቡድን" ይካሄድ የሚለው ሃሳብም ሳይቋጭ በእንጥልጥል ቀርቷል።

ድርድሩ "በግል ወይስ በቡድን" ይካሄድ የሚለውን ለመወሰን የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻቸውን ተገናኝተው እንዲወስኑ እድል ቢሰጣቸውም በእለቱ ሁሉም ተሟልተው ባለመገኘታቸው ውሳኔ ላይ ሳይደርሱ መለያየታቸው ይታወሳል።

ኢህአዴግ  ባቀረበው በግል፣ ፓርቲዎች አንድ ሆነው ወይም የተለየ አጀንዳ አለኝ የሚል ፓርቲ በልዩ ሁኔታ መደራደር ይችላል በሚሉት ሶስት አማራጮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ በስተቀር 20ዎቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ አጀንዳ በጋራ፤ በተለያዩ አጀንዳዎች በግል ለመደራደር ተስማምተዋል።

ነገር ግን መድረክ "ከሌሎች የተሻለ ልምድ ስላለኝ ሁሉንም ወክዬ ልደራደር አሊያም በማንኛውም አጀንዳ በግሌ ነው የምደራደርው" የሚል ሃሳብ በማቅረቡ ጉዳዩ ሳይቋጭ ቀርቷል።

በመሆኑም መድረክ ጉዳዩን በግሉ ዓይቶ ሀሳቡን ይዞ እንዲቀርብና "አደራዳሪ"ን በተመለከተ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፓርቲ አመራር አባላት ጋር ተወያይተውበት እንዲመጡ ለመጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

Published in ፖለቲካ

ነቀምቴ መጋቢት 9/2009 በምሥራቅ ወለጋ ዞን ባለፉት ስምንት ወራት ስራ አጥ የነበሩ  ከ15ሺህ በላይ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን   የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

ወጣቶቹ ወደ ስራ የገቡት በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎች ከተማና ገጠር ውስጥ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ አባይ ተናግረዋል፡፡

ክንውኑም 27 ሺህ 243 ሥራ አጥ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ከተያዘው እቅድ ውስጥ ነው፡፡

አፈጻጸሙ ከእቅድ በታች የሆነው   ከዓመቱ መግቢያ  ጀምሮ በየደረጃ  የተካሄደው የጥልቅ ተሃድሶ  ፕሮግራም  ጊዜ በወስዱ ቢሆንም በቀጣይ ሁሉንም ለማሳካት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል፡፡

ወደ ስራ የገቡት ወጣቶች ከተሰማሩባቸውም መስኮች መካከል ግንባታ፣  ግብርና ፣ ንግድ፣ ማዕድን ማውጣትና አገልግሎት ይገኙበታል፡፡

አቶ ሙሉጌታ እንዳሉት እነዚህን ወጣቶች ከማደራጀትና የስራ አመራር ስልጠና ከመስጠቱ ሌላ ከ884 ሄክታር በላይ የሚለማ መሬት እንዲሁም 112 የመሸጫና የማምረቻ ቦታዎች ተመቻችቶላቸዋል፡፡ 

እንዲሁም መንግስት ለዞኑ የመደበው ከ147 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣቶች ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋል እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው አመራር እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ አክስዮን ማህበር የነቀምቴ ቅርንጫፍ የኦፕሬሽን ማኔጀር አቶ ከፍያለዉ ገብረኪዳን በበኩላቸው በዞኑ  ዘንድሮ ተደራጅተዉ ወደ ሥራ ለገቡ ወጣቶችና ለሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች  ከ14 ሚሊዮን  ብር በላይ በብድር መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ጎቡ ሰዮ ወረዳ  የአኖ ዜሮ አንድ  ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ኢዮብ ብርሃኑ ለኢዜአ  በሰጠው አስተያየት   11 ሆነው በመደራጀትና 25ሺህ ብር በመቆጠብ ጠጠር ማምረት መጀመራቸውን ተናግሯል፡፡

በመንግስት በኩል ጠጠር የሚያመርቱበት ማሽን በረጅም ጊዜ የብድር ክፍያ  እንዲያገኙ ያመቻቸላቸው መሆኑንም አመልክቷል፡፡

በዞኑ በበጀት ዓመቱ ከ40ሺህ ለሚበልጡ  ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር  ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

ባለፈው ዓመትም  ከ34ሺ በላይ  ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውም ከዞኑ  የሥራ ዕድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ማህበራዊ
Published in ቪዲዮ

አርባ ምንጭ መጋቢት 9/2009 ተደራጅተው መስራታቸው ለምርታቸው የተሻለ ገበያ በማግኘት ተጨማሪ ሀብት ማፍራት እንዳስቻላቸው በጋሞ ጎፋ ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሙዝ አምራች አርሶ አደሮች ተናገሩ።

አርሶ አደር በቀለ ደቻ  በዞኑ የጋንታ ካንቻማ ሰሌ አትክልትና ፍራፍሬ ግብይት መሠረታዊ ህብረት ሰራ ማህበር አባል ናቸው፡፡

ተደራጅተው ከመሰራታቸው በፊት ያጋጥሙ የነበሩ የገበያና የግብይት ችግሮች አሁን ላይ መወገዱን ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት በማህበራቸው  አማካኝነት ምርታቸውን ወደተሻለ ገበያ ወስደው  መሸጥ ችለዋል፤ የገበያ ችግራቸው  ከመቃለሉም በላይ የቁጠባ ባህላቸውም አድጓል።

የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ይመር ካይጸ በበኩላቸው የማህበሩ አባላት በአደረጃጀቱ በኩል ከመንግስት የምክር አገልግሎትና የሙያ ስልጠና  ድጋፍ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ማህበራቸው ከአራት ዓመት በፊት በ110 አባላትና በ200 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የተጀመረው  ግብይት በአሁኑ ጊዜ ካፒታሉን ወደ አስር ሚሊዮን ብር ማድረሱንና የአባላቱ ቁጥርም በእጥፍ ማደጉን አስታውቀዋል፡፡

ዘንድሮ በአካባቢዉ በተከሰተ አየር መዛባት ምክንያት ምርቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ቢያሳድርባቸውም  በአገር ውሰጥ የተሻለ ገበያ በመኖሩ ገቢያቸው  እምብዛም እንዳልቀነሰባቸው ጠቁመዋል።

ባለፋት አራት ዓመታት የቆጠቡትን ገንዘብ ጨምሮ  በ7 ሚሊየን ብር መለሰተኛ ሆቴል መክፈታቸውንና ተደራጅተው መሰራታቸው  እውቀታቸው፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን አስተባብረው  ለስኬት እንዳበቃቸውም ጠቅሰዋል።

በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የካንቻሜ ቀበሌ ነዋሪው  አርሶ አደር ቸካ ሸንደሮ  ተደራጅቶ መሰራት ጠቃሚ መሆኑን ከጓደኞቻቸው ውጤታማነት መማራቸውን ተናግረዋል።

እሳቸውም የሙዝ አምራች አርሶ አደር ቢሆኑም እስከ አሁን ባይደራጁም በቀጣይ እንደሌሎቹ ህብረት ፈጥረው ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸውም  ጠቁመዋል።

የዞኑ የህብረት ሰራ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢሳያስ ሽቱ በበኩላቸው በዞኑ በአትክልትና ፍራፍሬ ግብይት የተደራጁ 41 የህብረት ሰራ ማህበራት እንዳሉ ተናግረዋል።

በማህበራቱ አባል አርሶ አደሮች አማካኝነት ባለፋት ስድሰት ወራት ከግማሽ ሚለዮን  ቶን  በላይ የሙዝና የማንጎ ምርት ለአገር ውሰጥ ገበያ ቀርቦ ከሽያጩ 25 ሚሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የሙዝ ምርት ለመካከለኛዉ ምስራቅ ሀገሮች መላክ ተጀምሮ በዋጋ ያለመግባባት ምክንያት መቋረጡን ያስታወሱት ሃላፊው ከአሁን የተሻለ ገበያ ለማግኘት ከባለድርሻ አካላት የተወጣጣ ቡድን ተቋቁሞ ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2009 መንግስት ለአደጋ በተጋለጡ ቦታዎች የሚኖሩ ዜጎችን አስቀድሞ ከጉዳት የመከላከልና የመጠበቅ ስራዎች ለማከናወን ትኩረት እንደሚሰጥ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ ዛሬ ሰጥተዋል።

ሰሞኑን በቆሼ አካባቢ የደረሰው አደጋ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን አስቀድሞ ለማንሳት ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ያመላከተ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በወንዝ ዳርቻዎችና "ይናዳሉ" ተብሎ በሚታሰቡ ቦታዎች የሚኖሩ ዜጎች ችግር ሳይደርስባቸው፣ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ሳይከሰት  ከወዲሁ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወን ነው የገለጹት፡፡

በአሁኑ ወቅት በቆሼ አካባቢ  አደጋው ለደረሰባቸው ወገኖች አስፈላጊ የሆኑ የምግብ፣ የውሃ ፣ የብርድ ልብስና ሌሎች ድጋፎች እየተደረጉ መሆናቸውንም አውስተዋል።

በቆሼ የተነሳውን አደጋ መንስኤ ለማወቅም ከቴክሳስ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተውጣጣ ቡድን ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

ሌላው ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ያብራሩት፤ ሰሞኑን ከደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳዎች ድንበር ጥሰው ወደ ጋምቤላ አንዳንድ አካባቢ ገብተው በሰውና በንብረት ላይ አደጋ ያስከተሉትን ታጣቂዎች በተመለከተ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ "መንግስት ኃይል መጠቀመን አልመረጠም" ያሉት ዶክተር ነገሪ፤ የሰው ሕይወት እንዳያልፍና የተወሰዱ ሕፃናትም በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

መንግስት አካባቢውን በማልማት፣ የመሰረተ ልማቶችን በመዘርጋትና ዜጎችን በመንደር ምስረታ በማሰባሰብ በየወቅቱ የሚነሱ ግጭቶች እንዲቆሙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እነዚሁ ታጣቂዎች የደቡብ ሱዳን መንግስትን እንደማይወክሉ የገለጹት ዶክተር ነገሪ፤ እስካሁንም ስድስት ሕፃናትና 185 ከብቶችን ለማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ሰሞኑን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይም አደጋ ለመጣል የሞከሩ አካላትን አስመልክቶም ''እነዚህ አካላት እትብታቸው ኤርትራና አስመራ የሆነ የሚመራቸውም የኤርትራ መንግስት ነው ''ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት "ከየትኛውም ኃይል ይነሳል" ተብሎ የሚታስብ ስጋት እንደሌለ አመልክተው፤ እንደ አገር ግን ሉዓላዊነቷን ለማስከበር መከላከያ ሠራዊቷ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ብቃት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

 

Published in ፖለቲካ

ጂግጂጋ መጋቢት 9/2009 የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስት በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ በሚባለው ስፍራ በአፈር መደርመስ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ለማቋቋም የሚያግዝ የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡

የክልሉ  ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ  እንድሪስ እስማኤል ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት የካቢኔ አባላት ዛሬ ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ ገንዘቡ ለተጎጂዎቹ መልሶ ማቋቋሚያ እገዛ እንዲውል ወስኗል፡፡

የካቢኔ አባላቱ  በአደጋው ህይወታቸውን ባጡት ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽም የክልሉ መንግስት ለተጎጂዎቹ የሚያደርገውን ድጋፍ  አጠናክሮ እንደሚቀጥልም  አመልክተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግስትና ህዝብ ከዚህ ቀደምም በትግራይ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉም የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊው አስታውሰዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2009 የፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ ጉብኝት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ በማድረስ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተናገሩ፡፡

በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሲያካሂዱ የቆዩት የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ሸኝተዋቸዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት እንዲጠናከር ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ በግላቸው ላበረከቱት አስተዋጽዖም የኢትዮጵያ መንግሥት ምስጋና አቅርቧል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ በማድረስ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

ዘመናትን የዘለቀው የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት አሁን ላይ መድረሱ ጥንካሬውን እንደሚያሳይና ይህም በተለያዩ ዘርፎች ላይ መሰረት ማድረጉን ነው የጠቆሙት።

"በክፉ ጊዜም በደግ ጊዜም በጋራ የምንቆም አገር ነን፤ የሕዝብ ጥቅም ያስተሳሰረን መንግሥታት ሕዝቦች ነን" በማለት ያለውን አጋርነት ገልጸዋል።

ግንኙነቱ ያለምንም እንከን እዚህ ላይ ለመድረሱ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ አበርክቷቸው ትልቅ በመሆኑ ምሥጋና እንደሚገባቸው ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

"ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የወጪና የገቢ ምርት በጅቡቲ ወደብ የሚሄድ ነው" ይህም አጋርነታችንን ወሳኝ ያደርገዋል ብለዋል።

በቀጣይም በአገራቱ መካከል ቀሪ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ አጋርነቱን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ ቀንድ አገራትም ያላትን የግንኙነት አድማስ መልሳ በመመልከት ግንኙነቱን ለማንሰራራት ትሰራለችም ነው ያሉት።

በዚህም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ውህደትና ለዓለም ትስስር የበኩሏን ለመወጣት ጥረት እንደምታደርግ ጠቁመዋል።

ፕሬዚዳንቱ በቆይታቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለሁለቱ ምክር ቤት አባላቶች አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ግንኙነት ዙሪያ ንግግር አድርገዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋርም የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ሁለንተናዊ ትስስር ይበልጥ ሊጠናከርበት በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር በመሆን ለጅቡቲ አምባሳደሮች መኖሪያ የሚሆን የግንባታ መሰረት-ድንጋይ አስቀምጠዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ለማስመዝገብ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ ሥር ሆነው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን