አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Friday, 17 March 2017

መቱ  መጋቢት 8/2009  የኢሉአባቦር ዞን ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ተግባራዊ ያደረገው የአሰራር ማሻሻያና ለውጥ ልማትን በተነሳሽነት ለማከናወንና የቡድን ሥራን ለማጎልበት እንዳስቻላቸው የህግ ታራሚዎች ገለጹ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የህግ ታራሚዎች እንደገለጹት፣ በማረሚያ ቤቱ በዚህ ዓመት ተግባራዊ በሆነው አዲስ አሰራር መሰረት በአንድ ለአምስት በመደራጀት ችግሮቻቸውን በራሳቸው መፍታት ጀምረዋል።

አደረጃጀቱ በልማቱ የተሻለ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

የህግ ታራሚ ፈድሉ አህመድ እንዳለው፣ በማረሚያ ቤቱ የአካባቢ ንጽህናን ለመጠበቅና በተለያዩ ልማቶች ታራሚዎች እያደረጉት ያለው ተሳትፎ በጋራ ውይይትና በቡድን የሚከናወን ነው።

ይህም ከዚህ ቀደም ከአካባቢ ንጽህና ጀምሮ በተለያዩ ጉዳዮቻቸው ላይ የማረሚያ ቤቱን አስተዳደር መፍትሄ ብቻ ይጠብቁ የነበረውን አሰራር ከማስቀረት ባለፈ ችግሮቻቸውን በራሳቸው እንዲፈቱ ያደረጋቸው መሆኑን ገልጿል።

በማረሚያ ቤቱ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን በኃላፊነት ተረክበው መስራታቸው ከዚህ ቀደም በተናጠል ከሚሰሩት ይልቅ ይብልጥ ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑንም አመልክቷል፡፡

"ማረሚያ ቤቱ የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን ማከናወን እንድንችል በአንድ ለአምስት እንድንደራጅ ማድረጉ የቡድን ሥራ ያለውን ፋይዳ በተሻለ እንድንገነዘብ አድርጎናል" ያለው ደግሞ ሌላኛው የህግ ታራሚ አርገኔ ኖኖ ነው፡፡

በማረሚያ ቤቱ ስለ ቁጠባ ትምህርት ማግኘታቸውን ገልጾ፣ በአሁኑ ወቅት ሰርቶ የሚያገኘውን ገንዘብ በመቆጠብ ቤተሰቡን እየደገፈ መሆኑን ተናግሯል።

የኢሉአባቦር ዞን ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኃላፊ ኮማንደር ተናኜ ወልዱ በበኩላቸው በማረሚያ ቤቱ ሠራተኞችና የህግ ታራሚዎች አሰራርና አያያዝ ላይ ማሻሻያና ለውጥ  መደረጉን ገልጸዋል።

ይህም በታራሚው ዘንድ የቡድን መንፈስ ከማጎልበት ባለፈ ለችግሮቻቸው ራሳቸው መፍትሄ እንዲያፈላልጉ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮማንደር ተናኜ እንዳሉት፣ ታራሚዎች የአካባቢያቸውን የጽዳትና የልማት ሥራዎች በአንድ ለአምስት አደረጃጀቶቻቸው በባለቤትነት ማከናወን ጀምረዋል፡፡

በተጨማሪም ለመቱ ከተማ ሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ የመናፈሻ ስፍራ በራሳቸው ተነሳሽነት መገንባታቸውንና ይህም ለከተማው ወጣቶች መዝናኛ ስፍራ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ታራሚዎቹ በአንድ ለአምስት አደረጃጀቶቻቸው አማካይነት ስለ ስነምግባርና ቁጠባ አስፈላጊነት ትምህርት እንዲያገኙ ተደርጓል።

ይህም የማረሚያ ቤት ቆይታቸውን ጨርሰው ወደሕብረተሰቡን ሲቀላቀሉ በልማት ሥራዎች ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡ አቅም እንደሚፈጥርላቸው መሆኑን ነው ኮማንደር ተናኜ የገለጹት።

የአሰራር ማሻሻያው ከታራሚዎች በተጨማሪ በማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ሠራተኞች ላይ ተግባራዊ መደረጉን ጠቁመው፣ ይህም በሠራኞች መካከል የቡድን ሥራና የውድድር መንፈስ እንዲጎለብት ማድረጉን አስረድተዋል።

 

 

 

Published in ማህበራዊ
Friday, 17 March 2017 23:43

የተዋጡ ነፍሶች!

Published in ቪዲዮ

አዲስ አበባ መጋቢት 8/2009 መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከደረሰው አደጋ የተረፉ ሰዎችን በቋሚነት ወደ ተረጋጋ ሕይወት እንዲመለሱ እያመቻቸ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

ጽሕፈት ቤቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው ሳምንታዊ መግለጫ እንዳመለከተው፤ መንግስት ለዘላቂ መፍትሄ ትኩረት በመስጠት የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ አውጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

ሳምንታዊ መግለጫው እንደሚያመለክተው፤ መንግስት ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን በቋሚነት ወደ ተረጋጋ ህይወት ለመመለስ እያመቻቸ ነው።

መግለጫው አያይዞ፤ በአገሪቷ ተመሳሳይ አደጋዎች እንዳይከሰት አስቀድሞ መተንበይ እና ሲከሰትም በቅድመ ትንበያ ላይ ተመስርቶ ጉዳቱን ለመቀነስ እንዲቻል በፖሊሲ፣ በህግና በተቋም ደረጃ አቅሙን እያጎለበተ እንደሚገኝ ገልጿል።

የአደጋው መድረስ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት፣ ባለሀብቶች፣ ወጣቶች እና መላው  ህብረተሰብ  እስካሁን ድረስ ለተጎጂዎች እያሳዩ ያሉት ተቆርቋሪነት፣ ትብብር እና ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን የአቋም መግለጫው ያሳያል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ተጎጂዎችን ለመለየት፣ ለመደገፍና ለማቋቋም ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።

ጉዳቱ ለደረሰባቸው እርዳታና ድጋፍ ለማድረግ ዜጎች ያሳዩትን ፍላጎት ለማቀናጀትና ትርጉም ባለው መልኩ ስራ ላይ ለማዋል የባንክ አካውንት ተከፍቷል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በድጋሚ ገልጾ፤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝቷል።

 

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ

ሳምንታዊ አቋም መግለጫ

መጋቢት 8 ቀን 2009 .

አደጋን የመከላከል እና የመቀነስ አቅማችንን እያጎለበትን ነው!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የደረሰው አደጋ አስደንጋጭ እና የመላው ኢትዮጵያውያንን ልብ በሃዘን የሰበረ ነው።

አደጋው መከሰቱ እንደተሰማ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በአካባቢው ተገኝተው የህይወት አድን ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ጉዳተኞች በአፋጣኝ ህክምና እንዲያገኙ እና በህይወት የተረፉትም በፍጥነት በጊዜያዊ መጠለያ ተሰባስበው አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል። የፌዴራል ህዝብ ተወካዮች ም/ቤትም ለሦስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሀዘን አውጇል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ተጎጂዎችን ለመለየት፣ ለመደገፍና ለማቋቋም ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል፡፡ ለጉዳቱ ተጠቂዎች እርዳታና ድጋፍ ለማድረግ ዜጎቻችን ያሳዩትን ፍላጎት ለማቀናጀትና ትርጉም ባለው መልኩ ሥራ ላይ ለማዋልም ኦፊሴላዊ የገንዘብ ማሰባሰቢያ የባንክ አካውንት ከፍቷል።  በአጠቃላይ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት፣ ባለሃብቶች፣ ወጣቶች እና መላው ህዝባችን አደጋው መድረሱ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ለተጎጂዎች እያሳዩት ያለው ተቆርቋሪነት፣ ትብብር እና ድጋፍ ፍጹም የሚደነቅ  ነው፡፡ በመሆኑም የኢፌዴሪ መንግሥት ለዚህ አኩሪ ኢትዮጵያዊ ተግባር ምሥጋናውን ያቀርባል። 

መንግሥት ከሁሉ በላይ ለዘላቂ መፍትሄ ትኩረት በመስጠት የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በአንድ በኩል ከአደጋው የተረፉት ወገኖቻችን በቋሚነት ወደተረጋጋ ህይወት የሚመለሱበትን ሁኔታ እያመቻቸ ነው። በሌላ በኩል በአገራችን ተመሳሳይ አደጋዎች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ መተንበይ እና  ሲከሰቱም በቅድመ ትንበያ ላይ ተመስርቶ የወገኖቻችንን ጉዳት ለመቀነስ እንዲቻል በፖሊሲ፣ በህግና በተቋም ደረጃ አቅማችንን  ይበልጥ እያጎለበትን እንገኛለን።

በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ መንግሥት ህይወታቸውን ባጡት ወገኖቻችን የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በድጋሚ እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ይመኛል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 8/2009 በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ በደረሰው አደጋ ለተጎጂዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ገለጸ።

ማህበሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በአደጋው የተረፉ እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን በማቋቋሙ ሂደት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

በመጪው እሁድ አባላቱን በማስተባበርና አደጋው በደረሰበት ቦታ በአካል በመገኘት የተጎጂ ቤተሰቦችን ለማፅናናት እንዲሁም ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አብርሃም ስዩም አስታውቀዋል።

ማህበሩ በአደጋው ምክንያት ህይወታቸውን ባጡ ዜጎች የተሰማውን ሀዘንም ለኢዜአ በላከው መግለጫ ገልጿል።

በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ በደረሰው አደጋ የሟቾች ቁጥር 113 ደርሷል።

በአደጋው ለህልፈተ-ህይወት ከተዳረጉት ውስጥ 38ቱ ወንዶች ሲሆኑ፤ 75 ደግሞ ሴቶች ናቸው።

አደጋው የደረሰው መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም ምሽት ላይ እንደነበር ይታወሳል።

Published in ማህበራዊ

አክሱም  መጋቢት 8/2009  በትግራይ ክልል አድዋ ከተማ ለህክምና አገልግሎት  የተገነባው  የፋሻ ማምረቻ  ፋብሪካ  የማምረት ስራ   ጀመረ፡፡

በመንግስት ሆስፒታሎች ብቻ የፋሻ ምርትን ከውጭ ለመግዛት   በዓመት የሚጠይቀውን ከ60 ሚሊዮን ብር ወጪ ለማዳን የፋብሪካው መገንባት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የኢትዮጵያ የመድኃኒት  ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ገልጿል፡፡

የፋብሪካው  ባለቤት አቶ አብርሃም  ገብረእግዚአብሔር  ለኢዜአ እንደገለፁት በአድዋ ከተማ ከአራት ዓመታት በፊት ያስጀመሩት የፋሻ ማምረቻ ፋብሪካ  ግንባታ ለማጠናቀቅ 53 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገውበታል፡፡

በአሁኑ ወቅት  ወደ ማምረት ስራ በመሸጋገር  ለ54 ሰዎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠራቸውን ጠቁመው ፋብሪካው ለህክምና አገልግሎት የሚውል ያለቀለት ፋሻ ከነግብአቱ  በማምረት  በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

"በፋብሪካው በተተከሉ ሶስት ማሽኖች አማካኝነት በቀን ለስምንት ሰዓታት እንደሚሰራና በዚህም  ጊዜ  ውስጥ ከ2ሺህ600 በላይ ጥቅሎችን ያመርታል" ብለዋል፡፡

የፋሻ ምርቱን አሁን መቀሌ ለሚገኘው  የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል  እያቀረቡ መሆኑን ያመለከቱት አቶ  አብርሃም  በቀጣይ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ለመላክ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የፋሻ  ምርት በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን እጥረት ከማቃለል ባሻገር  ሀገሪቱ  ምርቱን ለመግዛት የምታወጣውን  የውጭ ምንዛሪ በመቀነስ በኩልም አስተዋጽኦ እንደሚኖረው  አመልክተዋል።

ምርቱ በአገር ውስጥ ካለው ፍላጎት  አንጻር አነስተኛ በመሆኑ  ተጨማሪ ሶሰት ማሽኖችን  በመግዛት አቅርቦታቸውን በእጥፍ ለማሳደግ  ዝግጅት ላይ  መሆናቸውን የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የመድኃኒት  ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የመቀሌ  ቅርንጫፍ  ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ገብረማሪያም በበኩላቸው   የፋሻ  ፋብሪካው  የሚያመርተው ለቀዶ ህክምና፣ ለማዋለጃ ፣የደም  መፍሰስ ላጋጠማቸው ህሙማን  መሸፈኛ ሆኖ የሚያገለግል ግብአት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመንግስት ሆስፒታሎች ብቻ የፋሻ ምርትን ከውጭ ለማቅረብ   በዓመት የሚጠይቀውን ከ60 ሚሊዮን ብር ወጪ ለማዳን የፋብሪካው መገንባት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አመልክተዋል፡፡ 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 8/2009 መንግሥት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርገውን ውይይት የአውሮፓ ኅብረት በአድናቆት እንደሚመለከተው የኅብረቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ፌደሪካ ሞግኸሪኒ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከአውሮፓ ኅብረቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ፌደሪካ ሞግኸሪኒ ጋር በስትራቴጂካዊ አጋርነት ዙሪያ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

የኅብረቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ፌደሪካ ሞግኸሪኒ እንደተናገሩት ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ባለው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ዙሪያ ሠፋ ያለ ውይይት ተደርጓል።

ኅብረቱ በሁሉም ዘርፎች በሚባል ደረጃ ከኢትዮጵያ ጋር አጋርነት እንዳለውና ይህንንም ይበልጥ ለማጠናከር ሥምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት በአገሪቱ ባለው የፖለቲካ ጉዳይ በጋራ ለመሥራት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየታቸውን ነው የተናገሩት።

በመሆኑም በፖለቲካው መስክ መንግሥት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያደረገው ውይይት የሚበረታታና የሚደነቅ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም በፖለቲካው መስክ ትክክለኛ መንገድ መሆኑን አንስተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይም በዚህ ረገድ ለሚያደርጉት ጥረት ከጎናቸው እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከድርቁ ጋር በተያያዘ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የምትሰራውን ሥራ አድንቀዋል።

በዚህም ሳትወሰን በአፍሪካ ቀንድ አገራት ላለው የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ኢትዮጵያ የድርሻዋን በመወጣት ያበረከተችው አስተዋጽዖ ምስጋና ሊቸረው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ተቀብላ በማስተናገድም እንደ አገር የተጣለባትን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣች መሆኑን ነው የገለጹት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው መንግሥት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች  ሠፋ ያለ ውይይት ማድረጉን ገልጸውላቸዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን አገሪቱ ባጋጠማት የጸጥታ ችግር የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም የሰላም መሻሻል በመታየቱ በመመሪያዎቹ ላይ መሻሻል መደረጉን ተናግረዋል።

ይሁንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮም በሰብዓዊ መብት ላይ ምንም አይነት ጥሰት አለመከሰቱን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያረጋገጡት።

ለዚህም ደግሞ ከዓመት በፊት በኅብረቱና በኢትዮጵያ መካከል የተደረሰውን የስትራቴጂክ አጋርነት ሥምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እንደምትሰራ ጠቁመዋል።

በቀጣይ በቤልጂየም ርዕሰ-መዲና ብራሰልስ የሚካሄደው የቢዝነስ ፎረም ግንኙነቱን ወደላቀ ደረጃ በማድረስ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል እየሰራች ያለውን ሥራ እንደምታጠናክርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ካሳ ገብረዮሃንስ ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ

ባህርዳር 8/2009 በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ሞጋች ህብረተሰብ ለመፍጠር  የብዙሃን መገናኛ ሃላፊነት  ጎልቶ መውጣት እንዳለበት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ አሳሰቡ፡፡

የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ባለፉት ዓመታት ያካሄደውን የከተሞች መድረክ ውጤታማነት የገመገመ  አውደ ጥናት ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተካሄዷል፡፡

ሚኒስትሩ በአውደ ጥናቱ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ እንደገለጹት  ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን የሚሆነው በነቃ የህዝቦች ተሳትፎ ነው።

የብዙሃን መገናኛ ሚናም ትክክለኛ ፣ ሚዛናዊና ወቅታዊ ዘገባ  ለህዝብ በማቅረብ  በመረጃ የበለጸገ ማህበረሰብ መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።

በፓርቲዎች መካከል ነጻ ውድድር፣ ምቹ የመወዳደሪያ መድረክና ነጻ ፖለቲካዊ መብቶች የተረጋገጠለት ህዝብ እንዲኖር የዴሞክራሲ ምስሶዎችን መርህ አድርጎ መስራት እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

" የሃይማኖት፣ የባህልና የቋንቋ ብዝሃነት ባለባት ሀገራችን ብቸኛው የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት መላው የኢትየጵያ  ህዝቦች ናቸው" ብለዋል፡፡

" የአማራ  ብዙሃን መገናኛ  ህዝቡ በቀጥታ የሚናገርበትና ችግሮቹን የሚፈታበት፣ አመራሩም ችግሮቹን የሚያይበት የከተሞች መድረክ በማዘጋጀት ሞጋች ህብረተሰብ ለመፍጠር ያደረገው እንቅስቃሴ በአርአያነት የሚታይ ነው" ብለዋል።

ይህንን መልካም ተሞክሮ በማስፋት በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ጠያቂና ሞጋች ህብረተሰብ በመፍጠር ረገድ የብዙሃን መገናኛ ሃላፊነት  ጎልቶ መውጣት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ አለባቸው የሱፍ በበኩላቸው መንግስት ለዴሞክራሲያዊ  ስርዓት መጎልበት ከወሰደው እርምጃ ዋናው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በህግ አስደግፎ መፍቀዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድርጅታቸው ከተቋቋመ ጀምሮ ህዝቦች ሃሳባቸውን የሚለዋወጡበት፣ የሚመክሩበትና በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች የጋራ መግባባት የሚፈጥሩበት እንዲሆን በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዓላማውም በየደረጃው የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት  የክልሉ ህዝቦች ልማትና ዴሞክራሲያዊ የአስተሳሰብ ልዕልና እንዲጎለብት በሚያስችል አግባብ ለመፈጸም መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት ያካሄደውን የከተሞች መድረክ በብዙሃን መገናኛ ጥሪ በማስተላለፍ አሳታፊነቱ እንዲረጋገጥ ማድረግ እንደቻለ ስራ አስኪያጁ  ጠቁመው  በብሄራዊ ሬዲዮ ፣  በኤፍ ኤምና በቴሌቪዥን በቀጥታ ስርጭት  የሌላውም ማህበረሰብ  ንቃተ ህሊና እንዲጎለብት የድርሻውን መወጣቱንም ጠቅሰዋል፡፡ 

በአማራ ቴሌቪዥን ምክትል ዋና አዘጋጅ አቶ  ደምሳቸው ፈንታ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንደገለጹት መድረኩ ሲጀመር በከተማ መስተዳድሮች በኩል በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለማደናቀፍ ጥረት ተደርጎ ነበር።

በጊዜ ሂደት መንግስትና ህዝብ ፊት ለፊት በመወያያት ችግሮችን በመለየትና በአፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የጋራ መግባባት መፍጠር  መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ድርጅቱ ባለፈው ዓመት ብቻ በ19 ከተሞች ባካሄዳቸው መድረኮች  የተጣለበትን ሃገራዊና ህዝባዊ ሃላፊነት መወጣቱን አቶ  ደምሳቸው ገልጸዋል።

በባህር ዳር ከተማ አባንቴ ሆቴል በተካሄደው አውደ ጥናት ላይ የክልልና የፌዴራል የስራ ሃላፊዎች ፣ የ35 ከተሞች አስተዳደር አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ  መጋቢት 8/2009  የትብብር ዘርፎችን በማስፋት የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ የኢትዮጵያና ጅቡቲ መሪዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ላይ የሚገኙት የጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

የሁለቱ አገራት ልዑካን ቡድንም የሁለትዮሽ ውይይት አካሂዷል።

መሪዎቹ ከምክክር በኋላ በሰጡት መግለጫ የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር አዳዲስ የትብብር መስኮች ላይ በትኩረት ይሰራሉ።

''የሁለቱ አገራት ግንኙነት ዘርፈ-ብዙና የተጠናከረ እንደመሆኑ አንዳችን ከለአንዳችን መኖር አንችልም'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በዚህ እሳቤ አብሮ ለመልማትና ቀጣናዊ ትስስሩን ለማጠናከር የተሰሩ ስራዎች ለሌሎችም ጭምር ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።

''ይህንኑ የትብብር ልምድ ወደላቀ ደረጃ ለማድረስና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ የበለጠ ተቀራርበን መስራት አለብን'' በማለት የፕሬዝዳንቱ ጉብኝትም ይህን ለማድረግ ልዩ አጋጣሚ ነው ሲሉ አክለዋል።

በዛሬው ዕለትም በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ አብሮ በመስራት አገራቱን የቀጣናው ብሎም የአህጉሪቱ የኢንዱስትሪ ማዕከል ማድረግ የሚቻልበት አጋጣሚ ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ በበኩላቸው የእርስ በእርስ ንግድ መጠንን ማስፋት፣ ኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ ልማት ላይ የተጠናከራ ስራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ዛሬ የተደረጉ ውይይቶችና የተደረሱ ስምምነቶችም ለዚህ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራሉ ሲሉ ተናግረዋል።

መሪዎቹ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲፈታና የቀጣናውን ሰላም ለማስጠበቅ የጋራ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በጋራ የደህንነት ስራዎች፣ በንግድ፣ በመሰረት ልማት ዝርጋታና በሌሎችም የልማት መስኮች ላይ የተጀመሩትን ስራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል የአገራቱን ህዝቦች ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚተጉ አስረድተዋል።

በቅርቡ የተመረቀው የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መሰረተ ልማትም ፈጥኖ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንዲገባ እየተሰራ ነው ብለዋል ።

በቀጣናው የተከሰተው ድርቅም በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) አባል አገራት በጋራ እንዲሰሩም አሳስበዋል።

ሁለቱ መሪዎች ድርቁ ጠንከር ያለ መሆኑን አመልክተው አለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ ከጉርብትናቸው ባሻገር ለቀጣናው አገራት ምሳሌ የሚሆን ወዳጅነት መመስረት ችለዋል።

 

 

 

Published in ፖለቲካ

ድሬዳዋ መጋቢት 8/2009 በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ በተባለው ቦታ በደረሰው አደጋ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን መልሶ ለማቋቋም የድሬዳዋ አስተዳደር የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ድሬዳዋ ያላትን ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም የአስተዳደሩ ከንቲባ ኢብራሒም ዑስማን ተናግረዋል፡፡

በደረሰው አደጋና በጠፋው የሰው ሕይወት አስተዳደሩ በእጅጉ ሀዘን እንደተሰማው የገለጹት ከንቲባው፣ በአስተዳደሩና በነዋሪው ስም ለተጎጂዎችና ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

በደረሰው አደጋ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም አስተዳደሩ አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

"አስተዳደሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው" በተለይ ከ10 ዓመት በፊት በድሬዳዋ በደረሰው አደጋ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ 10 ሺህ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የተከናወኑ ውጤታማ ተሞክሮዎችን ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሐምሌ 29 ቀን 1998 ዓ.ም ምሽት ላይ በድሬዳዋ በተከሰተው ጎርፍ ከቤት ንብረታቸው ከተፈናቀሉ ሰዎች መካከል አቶ ዩሱፍ ዑስማን አንዱ ናቸው፡፡

በአሁን ወቅት እርሳቸውና ሌሎች የችግሩ ተጋላጮች በተሰራላቸው መኖሪያ ቤት ውስጥ ያለፈውን ጥቁር ጠባሳ ረስተው እየኖሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አሁን ላሉበት የተረጋጋ ሕይወት መንግስትና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያደረጉላቸው ድጋፍና ርብርብ የጎላ እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ቆሼ በተባለ ስፍራ በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ልባዊ ሃዘን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአደጋው የተፈናቀሉ ቤተሰቦችን ለማቋቋም እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተማጽነዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 8/2009 የአገር በቀል ከብቶችን ከተሻሻሉ ዝርያዎች ጋር በሰው ሰራሽ ዘዴ በማዳቀል የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል አዲስ መርሃ ግብር ይፋ ሆነ።

"የግሉና የመንግስት አጋርነት የሰው ሰራሽ እንስሳት ማዳቀል አገልግሎት (ፔይድ)” የተሰኘ መርሃ ግብር ዛሬ ይፋ ሆኗል።

መርሃ ግብሩን ይፋ ያደረገው ላንድ ኦላክስ የተሰኘ ዓለም አቀፍ የልማት ፈንድ ከእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ሚኒስቴርና ከብሔራዊ ሰው ሰራሽ እንስሳት ማራቢያ ቴክኖሎጂ ማዕከል ጋር በመሆን ነው። 

መርሃ ግብሩ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን ከብቶች ከአገር በቀል ከብቶች ጋር በማዳቀል የወተት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ትኩረት ያደረገ ነው። 

ይህ መርሃ ግብር ተግባራዊ የሚደረገው የተሻለ የወተት ምርት ይሰጣሉ ተብለው በተመረጡ  አማራ፣  ኦሮሚያ፣  ትግራይና ደቡብ ህዝቦች በሚገኙ ከ100 በላይ ወረዳዎች ነው።

የመርሃ ግብሩ አስተባባሪ ዶክተር ዘላለም ይልማ እንደገለጹት፤ በነዚህ ወረዳዎች ከ140 ሺ በላይ አርሶ አደሮች ተደራሽ ይሆናሉ።

ከአምስት ዓመት በኋላ ሲጠናቀቅ ለአንድ ሚሊዮን ከብቶች ሰው ሰራሽ የማዳቀል አገልግሎት በመስጠት 320 ሺ የተሻሻሉ ጥጃዎችን ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከ50 ሚሊዮን በላይ የዳልጋ ከብቶች ቢኖሩም፤ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ከሁለት በመቶ እንደማይበልጥ ባለሙያው ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ በዘጠኝ  ሚሊዮን ዶላር የሚተገበር ሲሆን፤ 500 የግልና የመንግስት ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ የእንስሳት ማዳቀል ተግባር ከተጀመረ ከ60 ዓመት በላይ ማስቆጠሩም በዝግጅቱ ወቅት ተነግሯል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን