አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 16 March 2017

መቀሌ መጋቢት 7/2009 የይሓ ጥንታዊ ቤተመቅደስና መካነ ቅርሶች ኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ እንዳላት ይበልጥ ምስክርነት የሚሰጡ መሆናቸውን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በጀርመን የአርኪኦሎጂ ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች ላለፉት ስምንት ዓመታት ዕድሳት ሲደረግለት የቆየው የይሓ ቤተ መቅደስ (ቤተ ሙክራብ) በመጠናቀቁ ከትናንት ጀምሮ ለቱሪስት አገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡

14 ሜትር ከፍታ ያለው ቤተ መቅደስ ስነ ሕንጻው የተለየና ሲሚንቶም ሆነ ሌላ የማያያዣ ግብአት ሳይኖረው ጥርብ ድንጋዮች እርስ በራሳቸው ተሳስረው ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ነው፡፡

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ትናንት በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት፣ የይሓ ቤተመቅደስና መካነ ቅርስ የቅድመ አክሱም ታሪኮችን፣ ሀብት፣ እውቀትና ብዙ ሚስጥር የያዘ ታሪካዊ ስፍራ ነው፡፡

አሁን በጀርመን ባለሙያዎች እየተደረገ ያለው የጥናትና ምርምር ሥራ ቅርሱና ታሪኩ ለቀጣዩ ትውልድ ተጠብቆ እንዲቆይ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቤተመቅደሱና ቅርሱ ኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ታሪክ እንዳላት ምስክር መሆኑን ጠቁመው፣ ከጥገና ሥራው ጎን ለጎን እየተካሄደ ያለው የመካነ ቅርስ ጥናትና ምርምር ሥራ ሳይቋረጥ  መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ከአሁን በፊት በይሓ ከተማ ግንባታው ቢጀመርም እየተጓተተ ያለው ሙዚየም ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ባለስልጣኑ ድጋፍ እንደሚያደርግም አቶ ዮናስ አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት የይሓ ታሪካዊ ስፍራን በቀን በአማካይ 17 ጎብኚዎች እየተመለከቱት መሆኑን ገልጸው፣ "የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች ከተሟሉ የጎብኚዎችን ቁጥር ከዚህም በላይ ከፍ ማድረግ ይቻላል" ብለዋል፡፡

"በይሓ ጥንታዊ ቤተ መቅደስ በጥናትና ምርምር የተገኙ ቅርሶች ኢትዮጵያ በጥንት ጊዜ በእርሻ፣ በንግድ፣ በስነ ሕንጻና ቤተ መንግስት  ደርሳበት የነበረውን እድገት የሚያመላክቱ ናቸው" ያሉት ደግሞ የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይለ ናቸው፡፡

በተ-መቅደሱ የስነ ሕንጻ ጥበብ ቴክኖሎጂ ባደገበት በአሁኑ ዘመን እንኳ ሊሰራ የማይችል መሆኑን  የፖርቹጋል ተመራማሪዎችም ምስክርነት የሰጡበት ታሪካዊ ሥፍራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ዳዊት እንዳሉት፣ ግንቡ በዕድሜ ብዛት ምክንያት በላዩ ላይ እጽዋት በቅለው የመሰነጣጠቅ አደጋ ደርሶበት ነበር፡፡

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ከጀርመን ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ቅርሱን ከአደጋ ለማትረፍ ላከናወኑት ሥራም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በምረቃው ላይ የተገኙ የጀርመን አርኪኦሎጂካል ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳሬክተር ፕሮፌሰር ፍሬደሪክ መልስ በበኩላቸው፣ በይሓ የጀመሩት የጥናትና ምርምር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡

የቅርስ ዕድሳቱንና የጥናትና ምርምር ሥራው ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ጋር በመሆን እንደሚያካሂድ ገልጸዋል፡፡

የይሓ ታሪካዊ ቦታ ከአባ ገሪማ ጥንታዊ ገዳምና ከአድዋ ተራራዎች ጋር በአንድ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ የሚመለከተው አካል ጥረት እንዲያደርግ የጠየቁት ደግሞ የአካባቢውን ማህበረሰብ ወክለው ንግግር ያደረጉ አባ ተክለመድህን ሀጎስ ናቸው፡፡

" ወደ ታሪካዊ ሥፍራ የሚያስገባ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ የሌለው በመሆኑ ቤተመቅደሱ የታሪካዊነቱን ያህል እየተጎበኘ አይደለም" ብለዋል፡፡

የይሓ ጥንታዊ ቤተ መቅደስ ዕድሜ በታሪክ ተመራማሪዎችና በመፅሀፈ ገድል መካከል ልዩነት እንዳለው ጠቁመው፣ የታሪክ ተመራማሪዎች በ800 ዓመተ ዓለም መገንባቱን ቢገልጹም በመፅሀፈ ገድል በ3 ሺህ 610 ዓመተ ዓለም  መገንባቱን የሚገልፅ የፅሁፍ ማስረጃ መኖሩንና ይህም ትክክለኛው መሆኑን ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 8/2009 እንግሊዝ በተለያዩ የልማትና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር መስራት እንደምትፈልግ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቦሪስ ጆንሰን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ እንግሊዝ ኢትዮጵያ በልማትና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የምታደርገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ በጋራ መስራት ትፈልጋለች።

አገሪቱ የምታከናውነውን የልማት እንቅስቃሴ ያደነቁት ሚስተር ጆንሰን ይህንን ተግባር በመደገፍ "የእንግሊዝ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ- ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ ከመንግስትም ባለፈ በግሌም እጥራለሁ" ብለዋል።

በቀጣይም ሁለቱ አገሮች በልማት፣ በኢንቨስትመንት፣ ጸጥታና መሰል ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ አገራቱ ግንኙነታቸውን በማጠናከር የእንግሊዝ ባለኃብቶች በአገሪቷ መዋዕለ-ነዋያቸውን ቢያፈሱ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መግለጻቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተናግረዋል።

የሁለቱን አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት መደረጉንም  ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና መመረጧን ተከትሎ በጎረቤት አገራት መካከል ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት እንግሊዝ ድጋፏን ትቀጥላለች ብለዋል።

በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን አካባቢ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታትና ሰላም ለማምጣት ኢትዮጵያ ለምታደርገው ጥረት ድጋፏን እንደምትቀጥል  የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጆንሰን ቃል መግባታቸውንም አውስተዋል።

የኢትዮጵያና እንግሊዝ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከሌሎች የአለም አገራት የላቀ መሆኑንና በአገሪቱ በልማትና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ግንባር ቀደም ድጋፍ ሰጪ እንደሆነች ተገልጿል።

ኢትዮጵያና እንግሊዝ ከ70 ዓመታት በላይ ባስቆጠረው የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው የንግድና የኢንቨስትመንት ምጣኔያቸው ከ700 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 7/2009 የኦሮሚያ ክልል መንግሥትን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶች በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ በተለምዶ ቆሼ በተባለው አካባቢ አደጋ ደርሶባቸው ለተጎዱ ነዋሪዎች የ45 ሚሊዮን 150 ሺ ብር ድጋፍ አደረጉ።

የገንዘብ ድጋፉን በከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ ድረባ ኩማ ጽህፈት ቤት በመገኘት በቼክ አስረክበዋል።

ድጋፍን ያደረጉት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያንና ሚድሮክ ኢትዮጵያ  ናቸው።

የሚድሮክ ኢትዮጵያ ተወካይና የደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ኃይሌ አሰግዴ የ40 ሚሊዬን ብር ድጋፍ አስረክበዋል።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽነር መኮነን ሌንጂሳ በበኩላቸው፤ የክልሉ መንግሥት ያደረገውን የአምስት ሚሊዬን ብር ድጋፍ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ፕሬዚዳንት ፓስተር ይልማ ዋቄ፤ ቤተክርስቲያኗ ያበረከተችውን 150 ሺ ብር አስረክበዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ የአደጋው ሰለባ የሆኑትን ለመደገፍ ያሳዩትን የወገን ደራሽነት አመስግነዋል።

የከተማው አስተዳደር ቀጥታ የአደጋው ተጎጂ ለሆኑት ቤተሰቦች ጊዜያዊ ድጋፍ ለማድረግ እና ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም መጠለያ የመለየት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ትናንት መገለጹ ይታወቃል፡፡

አስተዳደሩ ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ አካላትም የባንክ አካውንት መከፈቱም ተገልጿል።

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ መጋቢት 7/2009 የመሰረተ ልማት አቅርቦትና ተደራሽነት ችግር እንዳለባቸው በከፋ ዞን ሳይለም ወረዳ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ እንግዳው ዳራሽ እንዳሉት በወረዳው ዋና ከተማ ያዶታ ከ1999ዓ.ም ጀምሮ የመብራት ምሰሶ እየተቀያየረ ከመትከል ባለፈ የኤሌክትሪክ መብራት ማግኘት አልቻሉም፡፡

ባለባቸው የመንገድ ችግርም ትራንስፖርት ለማግኘት ከፍተኛ ውጣ ውረድና አላስፈላጊ ወጪም እየጎዳቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አቶ ካሳሁን ወርቁ ያዶታ ነዋሪ በበኩላቸው ለ37 ዓመታት በከተማዋ እንደኖሩ ጠቁመው እስካሁን ድረስ ያለባቸው የመብራት፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የመንገድ ችግር እንዳልተፈታላቸው ተናግረዋል፡፡

በተለይ በመንገድ ችግር ምክንያት ምርታቸውን የተሻለ ገበያ ወዳለበት ወስደው መሸጥና  ምጥ የጠናባቸው እናቶች  ወደ ህክምና ተቋም ፈጥኖ  ማድረስ እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡

በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተገነቡ የተለያዩ የልማት ተቋማት በመብራት ችግር ምክንያት በቂ አገልግሎት እንደማይሰጡ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ታምሩ ወዳጆ ናቸው፡፡

ነዋሪዎቹ ይህንን ችግር ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ አቅርበው እንዲፈታላቸው ቢጠይቁም ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉም ጠቁመዋል፡፡

የሳይለም ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ግችሎ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ  "ችግሩ ሳይፈታ የቆየው በቂ ክትትልና ድጋፍ ባለመደረጉና ተቀናጅቶ ካለመስራት የመጣ ነው "ብለዋል፡፡

የመንገዱ ችግር በዞን ደረጃ ተገምግሞ  በዞኑ የገጠር መንገድ ዲስትሪክት ጉድለት ስራው መጓተቱ  ቢታወቅም የመብራት ችግር ግን እስከ ዓመቱ  መጨረሻ እንደሚፈታ ተናግረዋል፡፡ 

የከፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስራት መኩሪያ በበኩላቸው የጌሻ ሳይለም ገጠር መንገድ ችግሩን በጊዜያዊነት እንዲፈታ የተጀመረ ቢሆንም "ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በተያዘው በጀት ዓመት ፕሮጀክት ተቀርጾ  ወደ ስራ ተገብቷል" ብለዋል፡፡

"ከህብረተሰቡ የተነሳው ቅሬታ ተገቢ ነው" ያሉት አቶ አስራት  የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል፡፡

የወረዳውን የመብራት ችግሩ ለመፍታት ለጊዜያዊ መፍትሄ በ2ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ጄኔሬተር መገዛቱን ጠቁመው  በዘላቂነት ደግሞ የክልሉ ገጠር ኤሌክሪፊኬሽን ቢሮ ከተቋራጭ ጋር  ውል ገብቶ ወደ ስራ መገባቱንም አመልክተዋል፡፡

ቡናን ጨምሮ በተለያዩ ቋሚ ሰብሎችና በማር ምርት  የሚታወቀው  ሳይለም  በካፋ ዞን ከሚገኙ 10 ወረዳዎች አንዱ ሲሆን ከዞኑ  ማዕከል  ቦንጋ በ160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

Published in ማህበራዊ

ድሬደዋ መጋቢት 7/2009 መንግስት የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት የመደበውን በጀት አስተዳደሩ ወደተግባር በመለወጥ በአፋጣኝ ወድ ሥራ እንዲያስገባቸው የድሬዳዋ ወጣቶች ጠየቁ።

አስተዳደሩ በበኩሉ ወጣቶቹን ወደ ሥራ ለማሰማራት የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች በመጠናቀቃቸው በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምሩ ተናግሯል፡፡

አስተያየታቸውን ለኤዜአ የሰጡት ሥራ አጥ ወጣቶች እንደገለጹት መንግስት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በፈቀደው 10 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቃሽ ፈንድ እነርሱም ተጠቃሚ መሆናቸው አስደስቷቸዋል፡፡

ይሁንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአስተዳደሩ ተቋማት ወጣቶችን በየጊዜው በስብሰባ ከማሰልቸት በስተቀር ለወራት ተግባራዊ ሥራ አለመጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህም መሰላቸትና ተስፋ መቁረጥ ሊያመጣ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀው ወጣት ተመስገን የኋላሸት መንግስት ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በመደበው በጀት ቢደሰትም በአስተዳደሩ በኩል በጀቱን ወደተግባር በመለወጥ በኩል መዘግየት እንዳለ ተናግሯል፡፡

" ስብሰባ አስፈላጊ ቢሆንም ሲበዛ ያሰለቻል፤ ወጣቱ የሚፈልገው ተግባራዊ ሥራ በመሆኑ በፍጥነት ወደ ሥራ መሰማራት እንፈልጋለን " ብሏል፡፡

ሌላዋ ከዩኒቨርሲቲ መመረቋን የገለጸችው ወጣት እልፍነሽ መንግስቱ " ባለን እውቀትና በሚሰጠን የገንዘብ ብድር ተጠቅመን ራሳችንን ለመለወጥ ተዘጋጅተናል፤ ሁሉንም በአንዴ ወደ ሥራ ለማሰማራት ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም የጠራ ማህደር ያላቸውን ግን ፈጥኖ ወደ ሥራ ማስገባት ይገባል" ብላለች፡፡

ወጣት አዲስአለም ሰይፈገብረኤል በበኩሉ፣ አስተዳደሩ ሥራ አጥ ወጣቶችን ቤት ለቤት መዝግቦ ሥራ ለማሲያዝ ያደረገው ጥረት ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ተናግሯል።

"የተጀመረው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ወጣቱን ከማደራጀትና ሙያዊ ሥልጠና ከመስጠት ባለፈ የሥራ ቦታ በማመቻቸት ፈጥኖ ወደ ሥራ ማስገባት ይገባል" ብሏል፡፡

"እኔና ጓደኞቼ የቤት ውስጥ ጌጣጌጥና የማስዋብ ሙያ ቢኖረንም ገንዘብና የመሸጫ ቦታ የለንም፤ መንግስት ይህን አመቻችቶ ወደ ሥራ ብንገባ በፍጥነት እንደምንለወጥ አምናለሁ።" ያለው ደግሞ ወጣት መሐመድ እድሪስ ነው፡፡

በተመሳሳይ ዜና ወጣቶች በቀጣይ በሚሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ላይ ለመምከር ትናንትና ዛሬ በተዘጋጁ መድረኮች ላይ የተገኙ ወጣቶችም አስተዳደሩ በፍጥነት ወደ ሥራ የሚገቡበትን መንገድ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኘው ወጣት ዘመድኩን ታፈሰ " የዛሬ ሰብሰባ ጥሩ ነው፤ በዚህ ሳምንት ወደ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ገብተን እንሰለጥናለን፤ በምናገኘው እውቀት ተደራጅተን ወደ ሥራ ለመግባት ጓጉተናል" ብሏል፡፡

የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ከድር ጁሃር በበኩላቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ወጣቶቹ ውጤታማና ቀጣይነት ያለው ሥራ እንዲያከናውኑ የሚሰማሩበትን የሥራ ዘርፎችና አማራጮችን የመለየት ሥራ ተሰርቷል።

ወጣቱን ወደ ተግባር ለማስገባት ጉዳይ የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያቤቶች ተቀናጅተው እየሠሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ወጣቶቹን በፍጥነት ወደ ሥራ በማስገባት በኩል ክፍተት መኖሩን አመነው፣ ሥራ እጥ ወጣቱን በትክክል ለመለየትና ውጤታማ ሥራ የሚሰሩበትን የሥራ ዘርፎች ከወጣቶቹ ጋር ለመመካከር የተደረገው ጥረት ጊዜ መፍጀቱን ገልጸዋል።

ለወጣቶቹ ያሉትን የገበያ አማራጮችና ትስስሮች ከወዲሁ ለማመቻቸት የተከናወኑ ስራዎችም የተወሰነ ጊዜ መውሰዳቸውን ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።

ባለፈው ሁለት ሳምንት ብቻ ከአራት መቶ በላይ ወጣቶች በድሬደዋ ባሉ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ሥልጠና እንዲወስዱ መላካቸውን ኮሚሽነር ከድር ገልጸው፣ እስከ መጋቢት መጨረሻ 3 ሺህ 500 ወጣቶች የስልጠናው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።

" ስልጠና መስጠትና የሥራ አማራጮችን መለየት የሥራው አካል ነው" ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ስልጠናውን አጠናቀው አስቀድመው የተደራጁ ወጣቶችን ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ የከተማ የምግብ ዋስትናና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወጋየሁ ጋሻው ወጣቶች በከተማ ግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በምግብ ሥራ፣ በኮንስትራክሽንና በመሳሰሉት ዋና ዋና ሰባት የሥራ መስኮች እንደሚሰማሩ ገልፀዋል፡፡

ኤጀንሲው አስቀድሞ በገነባቸውና በተጠናቀቁ የማምረቻና የመሸጫ ማዕከላት ወጣቶቹ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢደረግም አስተዳደሩ ለሁሉም ወጣቶች የማምረቻ ሥፍራ የማዘጋጀት አቅም እንደሌለው ጠቁመዋል።

የወጣቶቹ ቤተሰብ ለልጆቻቸው ውጤታማነት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የድሬ ብድርና ቁጠባ ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ይመር በበኩላቸው መንግስት ከበጀተው 10 ቢሊዮን ብር ለድሬዳዋ  አስተዳደር 55 ሚሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል።

"በዘንድሮ ዓመት ወጣቶቹን በተለያዩ የሥራ መስኮች ለማሰማራት 27 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ብድር ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል" ብለዋል፡፡

ተቋሙ ጉዳዩን ከሚያስተባብሩ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን አቶ ጌታቸው ተናግረው፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ከፋብሪካዎች፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከክበባት ጋር ሊፈጠሩ የሚችሉ ትስስሮችም መለየታቸውን አስረድተዋል።

"በፌደራል መንግስት በድሬዳዋ በተጀመሩት ልዩ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እና የድሬዳዋ መልካ ጀብዱ የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ወጣቶቹ ተደራጅተው የሚጠቀሙበት መንገድም ይመቻቻል" ብለዋል፡፡

እነዚህን ቅድመ-ሁኔታዎችለማከናወን ሲባል መጓተት ቢፈጠርም ወጣቶች ተስፋ ሳይቆርጡ የተሻለ ውጤት ለማምጣት መትጋት እንዳለባቸው አቶ ጌታቸው አስገንዝበዋል፡፡

በድሬዳዋ ቤት ለቤት በተካሄደ ምዝገባ ዕድሜያቸው ከ18 እስክ 34 ዓመት የሆኑ ከ14 ሺህ በላይ ወጣቶች በሥራ እጥነት መመዝገባቸው ለማወቅ ተችሏል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስአበባ መጋቢት 7/2009 የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌድሬሽን(ኢሰማኮ) በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማውን ሃዘን ገለጸ።

ኮንፌድሬሽኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ለተጎጂ ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝቷል።

ኮንፌድሬሽኑ በዚህ አጋጣሚ በሕይወት ለተረፉ ዜጎች የበኩሉን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም አስታውቋል።

በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ  በተለምዶ ቆሼ በተባለው አካባቢ መጋቢት 2 ቀን ከምሽቱ 2:00 ሰዓት ገደማ በደረሰው አደጋ ተጎጂ ለሆኑ ነዋሪዎች፣ ለሟች ቤተሰቦችንና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን የሚመኙ መልዕክቶች እንደቀጠሉ ናቸው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎችን ለማሰብ የሶስት ቀናት ብሔራዊ የሐዘን ቀን ማወጁ ይታወቃል።

 

Published in ማህበራዊ

ባህርዳር መጋቢት 7/2009 የአማራ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ የ15 ዳኞችን ሹመትና የተለያዩ አዋጆችን በማጽደቅ  ማምሻውን ተጠናቀቀ።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ የኔነህ ስመኝ የተሿሚዎችን ሁኔታ ሲያቀርቡ እንደገለጹት የትምህርት ዝግጅት፣ ወቅታዊ አፈጻጸማቸውና በነበራቸው መልካም ስነ ምግባር በዳኞች ጉባኤ ጭምር የታዩ ናቸው።

እንዲሁም ከፌደራል በመጡ መያተኞች ተፈትነው ጥሩ ውጤት ያመጡና በየሰሩበት አካባቢ በህዝብ አሰተያየት ተሰጥቶባቸው  ምስጉን መሆናቸው መረጋገጡንም አመለክተዋል።

ከተሿሚዎቹ መካከል 11 የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፣ ሶስት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችና  አንድ ደግሞ የሰሜን ጎንደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑ ናቸው፡፡

ዳኞቹን መሾም ያስፈለገው  የተወሰኑት ለፌደራል ተሹመው በመሄዳቸው፣ በመልቀቅና ከመጀመሪያም በቂ ዳኞች ባለመመደባቸው የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

ከቀረበው የዳኝነት ሹመት ውስጥ ሴቶች ሁለት ብቻ መሆናቸው የጾታ እኩለነትን ያረጋገጠ አይደለም ተብሎ ለተነሳው ጥያቄ ከወጣው መስፈርት በመውረድ በልዩ ውሳኔ ማግኘት የተቻለው እነዚህን በመሆኑ ነው በማለት  ምላሽ ተሰጥቷል።

የተሾሙ ዳኞችም በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው  ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

የማህበራዊ ፍርድ ቤትን፣ የገጠር መንገዶች፣ የማህበረዊ ዋስትናን፣ የከተሞችን አደረጃጀት ለማሻሻል የወጡና ሌሎች አዋጆችን ምክር ቤቱ ተወያይቶ በማጽደቅ ለአራት ቀናት ሲካሄድ የቆየውን ጉባኤ  ማምሻውን ተጠናቋል።

Published in ፖለቲካ
Published in ቪዲዮ

አዲስአበባ መጋቢት 7/2009 ኢትዮጵያ በቀጣናና በአህጉር ደረጃ ሰላም ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ እንግሊዝ ገለጸች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ ወቅት ሁለቱ አገሮች የጋራ አቋም በሚይዙባቸው አለም አቀፍ ጉዳዮች፣ በልማት፣ በጸጥታ፣ በኢኮኖሚ ትብብር፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ አብሮ ለመስራት መስማማታቸው ነው የተገለጸው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት የእንግሊዙ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድንቀዋል። ለአፍሪካና ሌሎች የዓለም አገሮች ወሳኝ ሚና እየተጫወተችም መሆኑን ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበርና ሌሎች ዘርፎች ትልቅ አቅም እንዳላት ነው የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆንሰን የገለጹት።

አገሪቷ እንደ ጎረቤት አገርና ኢጋድ መሪነቷ የሶማሊያ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ያደረገችው ጥረት እንግሊዝ እንደምታደንቅ በመግለጽ በጋራ ለመስራት አገራቸው ዝግጁ መሆኗን አብራርተዋል።

አገራቱ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አብረው ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ዙሪያም መወያየታቸው ነው የተገለጸው።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን አየር መንገድ የጎበኙ ሲሆን፤ "በአየር መንገዱ ያየሁት ነገር የኢትዮጵያን ትልቅ ስኬት የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ እንደገለጹት፤ ሁለቱ ሚኒስትሮች ያደረጉት ምክክር የአገሮቹን ግንኙነት ለማስፋት መንገድ የቀየሰ ነው።

የእንግሊዝ ባለሃብቶች በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ በቢራ ምርትና ሌሎች ዘርፎች መሰማራታቸውን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፤ በትምህርት ዘርፍም እንዲሳተፉ ዶክተር ወርቅነህ መጠየቃቸውን ነው የገለጹት።

የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ስትራቴጂያዊና በአርአያነት ሊጠቀስ እንደሚችል ይነገራል። አገሮቹ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እኤአ በ1897 መጀመራቸው ይታወቃል።

 

Published in ፖለቲካ

ጂግጂጋ መጋቢት 7/2009 በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከድርቅ ጋር ተያይዞ የተከሰተው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታን ለመከላከል ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አሚር አማን የተመራ ቡድን በክልሉ ጨረር ዞን አተት በተከሰተባቸው ቢርቆድና ደጋህቡር ወረዳዎች ትናንት የመስክ ምልከታ አደርገዋል፡፡

ዶክተር አሚር በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንዳሉት ድርቁን ተከትሎ በተከሰተው የአተት በሽታ የተጉዱ ሰዎችን ለማከምና ለማዳን  ከክልል እስከ ፌዴራል መንግስት እንዲሁም አጋር ድርጅቶች እየተሰጠ ያለው ምላሽ አበረታች ነው፡፡

ጤና ተቋማት በአተት የተያዙ ህሙማንን  በተለየ ትኩረት የማከም ስራ እያካሄዱ መሆናቸውን ጠቁመው የጤና ተቋማቱ  ከባለሙያ እጥረት፣ ከመረጃ  አያያዝና ከህክምና ቁሳቁስ እጥረት ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ችግሮች ለመፍታት ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡

እስካሁን በበሽታው የተያዙ 13 ሺህ ሰዎች በተደረገላቸው የህክምና እርዳታ መዳን እንደቻሉ ምልከታ ባደረጉበት ወቅት መገንዘብ እንደቻሉ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

በሽታውን ለመቆጣጠር  የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸውም  አመልክተዋል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሀሰን ኢስማኤል በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሰው ሃይል በማንቀሳቀስ ከ158 ሺህ በላይ አርብቶ አደሮች ስለ አተት በሽታ መከላከል ግንዛቤ እንዲኖራቸው ትምህርት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

በመከላከሉ ስራ ላይ የቢሮ ሰራተኞች፣  የዞንና የወረዳ አስተዳደር አካላት እንዲሁም  268 የጤና ባለሙያዎችና  የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ጭምር በመሳተፍ ርብርብ እያደረጉ ናቸው፡፡

በተለይ የህክምና ቁሳቁሶችን እና አልሚ ምግብ የሚያመላልሱ 75 ከባድ ተሸከርካሪዎች መሰማራታቸውንም ሃላፊው ገልጸዋል፡፡

ከድርቅ ጋር በተያያዘ እስከ አሁን በቆራሃይ፤ በፊቅና በጨረር ዞኖች በሚገኙ   አስራ አራት ወረዳዎች በሽታው መከሰቱንም አመልክተዋል፡፡

በድርቁ የተነሳ ህፃናትና ወላድ እናቶች በቀላሉ በበሽታ የመጋለጥ እድላቸው የሰፋ መሆኑን የተናገሩት ሃላፊው ከበሽታው ለመከላከልም ትኩረት ሰጥተው  እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በደጋሀቡር ወረዳ ለቢጋ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሀቢባ ሙሀሙድ ልጃቸው በአተት በሽታ ተይዞባቸው እንደነበር አመልክተው ወደ ጤናተቋም በመውሰድ በተደረገለት የህክምና እርዳታ መዳኑን ተናግረዋል፡፡

 ''ልጄ ሲድን  እኔ በበሽታው ተያዝኩ፤  አሁን በተሰጣኝ የህክምና እርዳታ እየተሻለኝ ነው፤  በፍጥነት ከበሽታው ለማገገም እንድችል አልሚ ምግብ ድጋፍ ያስፈልገኛል " ብለዋል፡፡

የዚሁ  ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ መርያማ አብዲ በበኩላቸው ልጃቸው  በበሽታው ተይዞ  በቀበሌው በሚገኘው ጤና ጣቢያ እያሳከሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን