አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 15 March 2017

አዲስ አበባ  መጋቢት 6/2009 የፕሮፌሰር ዮሐንስ ክንፉ የቀብር ሥነ-ሥርዓት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዛሬ ተፈጸመ።

በቀብር ሥነ-ስርዓታቸው ላይ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና የስራ ባልደረቦቻቸው ተገኝተዋል።

በአክሱም ከተማ ሰኔ 23 ቀን1928 ዓ.ም ከደጃዝማች ክንፉ ኪዳኔና ከወይዘሮ ዋጋዬ ገብረ ሚካኤል የተወለዱት ፕሮፌሰር ዮሐንስ፤ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በተወለዱ በ81 ዓመታቸው መጋቢት 5 ቀን 2009 ዓ.ም ነው።

ፕሮፌሰር ዮሐንስ እ.ኤ.አ በ1960 የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ያገኙ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ1963 በአካውንቲንግ ዘርፍ ከአሜሪካው ዩታህ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።

በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአካውንቲንግ ዘርፍ በማስተማር እ.ኤ.አ በ1963 ዓ.ም ስራቸውን የጀመሩት ፕሮፌሰር ዮሐንስ፤ ከአሜሪካ ሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አስተዳደር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

በዩኒቨርስቲው ለ47 ዓመታት በመምህርነትና ተመራማሪነት አገልግለዋል።

እ.ኤ.አ በ1995 ዓ.ም የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙት ፕሮፌሰር ዮሐንስ፤ በኢትዮጵያ በአካውንቲንግ የሙያ ዘርፍ ''አባት'' በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ።

ፕሮፌሰሩ በሙያቸው ላይ ያተኮሩ ከ50 በላይ የምርምር ውጤቶች በታዋቂ መጽሔቶች ላይ ማሳተማቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

በ2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰጡት የረጅም ጊዜ አገልግሎት የኢመራተስ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኘተዋል።

የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ በሰሯቸው የምርምር ስራዎች የተለያዩ ዲፕሎማዎች ከአሜሪካና ከተለያዩ አገሮች ማግኘታቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

ፕሮፌሰር ዮሐንስ ባለትዳር፣ የአንድ ወንድና የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበሩ።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2009 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የቆሻሻ ክምር ተንዶ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች የቀብር ማስፈፀሚያ  ድጋፍ አደረገ።

የከተማዋ ከንቲባ ድርባ ኩማ በስፍራው ተገኝተው ለተጎጂ ቤተሰቦች የገንዘብ ድጋፉን አበርክተዋል።

የገንዘብ ድጋፉ የተበረከተው ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ ለሆኑት ለእያንዳንዳቸው ብር አስር ሺ ሲሆን፤ ከተለያዩ ክልሎች ለመጡት ደግሞ የትራንስፖርት ወጪን ጨምሮ የ15 ሺ ብር ድጋፍ ነው የተደረገው።

ከንቲባ ድሪባ ድጋፉን አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ መንግስት ልዩ ድጋፍ በማድረግ አደጋ የደረሰባቸውን ቤተሰቦች በጊዜያዊነት ለማገዝ የተቻለውን ጥረት እያደረገ ነው። በዘላቂነትም የተጎጂዎቹን ሕይወት ለመቀየር በከንቲባው የሚመራ ሶስት ኮሚቴ በተደራጀ አግባብ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

በተመሳሳይ ከንቲባው ዛሬ ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በደረሰው አደጋ የሟቾች ቁጥር 113 መድረሱን ገልፀዋል።

በአደጋው ህይወታቸውን ካጡት ውስጥ 38ቱ ወንዶች ሲሆኑ፤ 75 ደግሞ ሴቶች ናቸው።

"መላው የከተማው ነዋሪ እንዲሁም የተጎጂ ቤተሰቦች በተገኙበት የሟቾች የቀብር ሥነ ስርዓት በክብር በየእምነቱ ተቋማት  ተፈፅሟል" ያሉት ከንቲባው፤ የፍለጋ ሂደቱ ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ነው የሚል ግምት እንዳለቸውም ገልፀዋል።

የአካባቢው ህብረተሰብ በፍለጋ እና አስከሬን በማንሳት እያደረገ ላለው አስተዋጽዖ  ከንቲባው አመስግነዋል።

"የሟቋቋም ሥራው በሁለት መልኩ ነው የሚሰራው" ያሉት ከንቲባ፤ አንደኛው ቀጥታ የአደጋው ተጎጂ ለሆኑት ቤተሰቦች የሚደረገው ጊዜያዊ ድጋፍ እና በሁለተኛ ደረጃ  ደግሞ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለሟቋቋም መጠለያ የመለየት ሥራ እየተካነወነ መሆኑን ተናግረዋል።

አስተዳደሩ ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ አካላት የተለየ የባንክ አካውንት መከፈቱንም ከንቲባው ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  መጋቢት 6/2009 ከእንፋሎት ኃይልና በሴራሚክ ማምረት ስራዎች ለመሰማራት መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው የቱርክ ባለሃብቶች ገለጹ።

ባለሃብቶቹ ዛሬ ከፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር በፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ውይይት አድርገዋል።

ባለሃብቶቹ በእነፋሎት ኃይል፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች እንዲሁም በሴራሚክ ሥራ ላይ ለመሰማራት ነው ፍላጎት ያላቸው።

ለዚህ ደግሞ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ ለቱርክ ባለሃብቶች ያቀረበችው ማበረታቻና በሥራቸው ውጤታማ መሆናቸው መዋዕለ ንዋያቸውን ለማውጣት መፈለጋቸው እንደምክንያት ተጠቅሷል።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ፋቲህ ዩሉሶይ እንደተናገሩት፤ ባለሃብቶቹ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት ያለውን ምቹ ሁኔታ ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎት አላቸው።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ በቱርክ ከወራት በፊት ያደረጉት ጉብኝትም ባለሃብቶቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ካደረጉ ምክንያቶች  ተጠቃሽ መሆናቸውን አውስተዋል።

ዶክተር ሙላቱ ከቱርክ ኣቻቸው ፕሬዚዳንት ጣሂብ ኤርዶጋን ጋር የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማጠናከር መስማማታቸውም ሌላው መልካም እድል መሆኑን ነው ያመለከቱት።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ 440 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል።

ይሁንና ይህን አሃዝ ወደ አንደ ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ ሁለቱ አገሮች ተስማምተዋል።

ቱርክ በምስራቅ አፍሪካ በስድስት ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ሥራ እያካሄደች  እንደሆነ አምባሳደር ዩሉሶይ አመልክተው፤ ከዚህ ወስጥ ሁለት ነጥብ አምሰት ቢሊዮን ዶላሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በኢትዮጵያ ከ30 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል፤ ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስረዱት።

ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው፤ ባለሃብቶቹ በፈለጉት የኢንቨስትመንት ዘርፎች ቢሰማሩ ትርፋማ እንደሚሆኑ ነው የገለጹላቸው።

ፐሬዚዳንቱ ፤ " በአሁኑ ወቅት 60 በመቶ የሚሆነው የሴራሚክ ፍላጎት ከቻይና እንደሚመጣና ቀሪው ከቱርክና ከዱባይ ይመጣል፤ በዚህ ላይ ብትሰሩ ውጤታማ ትሆናላችሁ" ነው ያሏቸው።

ይህም ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ከፍተኛ መጠን ያለው የሴራሚክ አቅርቦት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እንደሚያስችላት በመጠቆም።

በሌላ በኩል "ኢትዮጵያ እየገነባች በአለው የኢንዱስትሪ ፓርክ ለኢንቨስትመንት ሥራቸው ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል" ብለዋል።

በኢትዮጵያም ለሴራሚክ የሚሆን የጥሬ እቃ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ መኖሩንም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ከቱርኩ አቻቸው ሬሲፕ ጣይፕ ኤርዶጋን በቀረበላቸው ግብዣ መሰረት በቅርቡ በቱርክ አንካራ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ጉብኝታቸው የሁለቱ አገሮችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ያለመ ነበር።

ፕሬዚዳንቱ በአንካራ ቆይታቸው ከፕሬዚዳንት ኤርዶጋንና ከሌሎች የአገሪቷ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ንግድና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች  ዙሪያ መወያየታቸው ይታወሳል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2009 ኢትዮጵያና ሩስያ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መከሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የሩስያ የተፈጥሩ ሃብትና አካባቢ ምክትል ሚኒስትር ኤቭጌኒ ኪስሌቭን ዛሬ አነጋግረዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ እንደገለጹት፤ ሁለቱ አገሮች በስድስተኛው የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ የተነሱ ጉዳዮችን ውጤታማ ማድረግ በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ መክረዋል።

በባህልና ቱሪዝም እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በማዕድንና ሌሎች ዘርፎች የተደረሱባቸውን ስምምነቶች ለማጠናከር በሚያስችል ጉዳይ ላይም ተወያይተዋል።

በተለይም ንግድና ኢንቨስትመንትን አስመልከቶ ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮችን በማንሳት የአገሮቹን ግንኙነት ለማጠናከር መክረዋል።

ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ ለሚያደርጉ ባለሃብቶች የምትሰጣቸውን ማበረታቻዎች ለሩስያ ባለሃብቶችም እንደምታደርግ ሚኒስትር ዴኤታዋ  አብራርተዋል።

የሩስያ የተፈጥሮ ሃብትና አካባቢ ምክትል ሚኒስትር ኤቭጌኒ ኪስሌቭ በበኩላቸው በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና ቱሪዝም  ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር መምከራቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ፍላጎት መኖሩን አንስተዋል።

የሩስያ ባለሃብቶችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ያሉትን አማራጮች እንደሚያስተዋውቁ ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያና ሩስያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1943 ነው የተጀመረው።   

Published in ኢኮኖሚ

መጋቢት 6/2009 በህገወጥ መንገድ ዜጎችን  ወደውጭ በመላክ ወንጀል ተሳትፈዋል ያላቸውን ሁለት ግለሰቦች እስከ 16 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት መቅጣቱን የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

በፍርድ ቤቱ የአራዳ ምድብ ችሎት አንደኛ ወንጀል ችሎት ትናንት የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው በህገወጥ መንገድ ዜጎችን ወደውጭ ልከዋል ባላቸው መሀመድ ሀሰን እና ሀይላይ ሀጎስ ላይ ነው፡፡

መዝገቡ እንደሚያስረዳው ነዋሪነቱ በዚሁ አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 20 የሆነው መሀመድ ሀሰን የተከሰሰው በስምንት የክስ መዝገቦች ሲሆን ዜጎችን ወደውጭ ለመላክ ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖረው የተለያዩ ግለሰቦችን ወደውጭ በመላኩ ነው፡፡

ግለሰቡ ወደ አውሮፓ በሊቢያ በኩል እልካችሁዋለሁ በማለት ዜጎች ከሀረር  ጂግጂጋና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ በማስመጣትና  ዜግነታችን ሱማሊያዊ ነን በሉ በማለት ፎርጂድ መታወቂያ በመስጠት ዜጎችን በህገወጥ መንገድ ወደውጭ በመላክ ተከሷል፡፡

በመሆኑም ችሎቱ የፌደራሉ አቃቤ ህግ ያቀረበውን የሰው፣ የሰነድና የኢግዚቢት ማስረጃዎችን በመመርመርና ግለሰቡ ያቀረበውን የክስ ማቅለያ ከግምት በማስገባት በ15 ዓመት ፅኑ እስራትና በሶስት ሺህ ብር እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡

ሌላው ሀይላይ ሀጎስ በተመሳሳይ ስምንት ክሶች የተመሰረተበት ሲሆን ነዋሪነታቸው በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ የሆኑ አምስት ነዋሪዎችን በሱዳንና በጂቡቲ በኩል ሳውዲ አረቢያ በማስገባት ስራ እንድታገኙ አደርጋለሁ በማለት ከያንዳንዱ 2ሺህ 500 ብር በአጠቃላይ 12 ሺህ አምስት መቶ ብር መውሰዱ ተረጋግጧል፡፡

የግል ተበዳዮቹን ወደ ኦሮሚያ አዳማ በማስመጣትና ለጊዜው በቁጥጥር ስር ካልዋለው ግብረአበሩ ጋር በመሆን በከባድ የጭነት ተሸከርካሪ በማሳፈርና ፖሊስ እንዳይዛችሁ በማለት በእቃ መጫኛ ኮንቴነር እንዲሳፈሩ በማስገደድ ግንቦት 7 /2008 ዓመተ ምህረት ከሎጊያ ወደ ጂቡቲ በመጓዝ ላይ ሳሉ ሰለሜ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በፀጥታ ሀይሎች በቁጥጥር መዋላቸውን መዝገቡ ያስረዳል፡፡

በመሆኑም ተከሳሹ የፈጸመውን የወንጀል ድርጊት ሲመረምር የቆየው ችሎቱ የአቃቤ  ህግን የሰነድ፣ የሰውና የኢግዚቢት መረጃዎችን መሰረት በማድረግና ተከሳሹ ያቀረበውን የክስ ማቅለያ ከግምት በማስገባት እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ በ16 ዓመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት እና በአራት ሺህ ብር እንዲቀጣ  ወስኗል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

ደብረ ማርቆስ ከመደበኛ የእርሻ ሥራቸው ጎን ለጎን በአፕል ልማት ሥራ  የተሰማሩ የምስራቅ ጎጃም ዞን አርሶአደሮች ገቢያቸው እያደገ መሆኑን ተናገሩ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የዞኑ አርሶአደሮች መካከል የስናን ወረዳ ደጋሰኝን ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ተዋቸው እሸቱ እንዳሉት፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ከእርሻ ሥራቸው በተጨማሪ በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ አፕል እያለሙ ነው።

በዚህም በየዓመቱ የሚያገኙት እስከ 20 ሺህ ብር የሚደርስ ተጨማሪ ገቢ ኑሯቸውን ለማሻሻል እየረዳቸው መሆኑን ተናግረዋል።

"የደጋ ፍራፍሬ ልማት የተሻለ ዋጋ የሚያወጣና በገበያም ተፈላጊ እንደሆነ አረጋግጫለሁ" ያሉት አርሶአደሩ፣ በቀጣይ ምርታቸውን በማሳደግ ይበልጥ ለመጠቀም እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በዚሁ ወረዳ የወንበብ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አጣናው አለበል እንዳሉት፣ የአፕል ልማት ገቢያቸውን በመጨመር ኑሯቸውን በተሻለ ለመምራት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

አካባቢያቸው ደጋ መሆኑን የገለጹት አርሶአደሩ፣ ከስድስት ዓመት በፊት ድንችና እንግዶ ብቻ ሲያለሙ የማዳበሪያ ወጪያቸውን እንኳ የማይሸፍንበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል።

"በአሁኑ ወቅት ግማሽ ሄክታር በማይሞላ ማሳዬ ላይ የአፕል ልማት በማካሄድ በዓመት ሦስት ጊዜ ምርቱን በመሸጥ እስከ 30 ሺህ ብር እያገኘሁ ነው" ብለዋል።

በዞኑ ቢቡኝ ወረዳ የጃርኪት ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ይታይህ መለሰ በበኩላቸው፣ አፕልን ቀደም ብለው ማልማት ከጀመሩ አርሶአደሮች ሲጠቀሙ አይተው ወደልማት ሥራው መግባታቸውን ተናግረዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት ፈጥነው ምርት ሊሰጡ የሚችሉ ዝርያዎችን ከግብርና ቢሮ ወስደው በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ መትከላቸውንና በአሁኑ ወቅት ተክሉ ምርት ለመስጠት መድረሱን ጠቁመዋል።

በዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ ሀብታሙ አህመድ፣ በጮቄ ተፋሰስ የሚገኙ ስምንት ደጋማ ወረዳዎችን በደጋ አትከልትና ፍራፍሬ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ለአዜአ ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት ከአራት ሺህ ሄክታር በሚበልጥ ማሳ ላይ በተሰሩ ሥራዎች ከ15 ሺህ በላይ አርሶአደሮችን በአፕልና በሌሎች የደጋ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት በማሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ የአፕል ምርት ተመርቶ ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱንና በዚህም አርሶአደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን በማሳያነት አቅርበዋል።

አቶ ሀብታሙ እንዳሉት፣ ከአርሶአደሮች ባሻገር በርካታ ወጣቶች ምርቱን ተረክበው አንዱን ኪሎ ከ50 ብር በላይ በመሸጥ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።

የዞኑ መስተዳድርም  የአፕል ምርትን ጥራት ለማስጠበቅ በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ምርት ለመስጠት የሚችሉ ዝርያዎችን ከደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች በማስመጣትና በማሰራጨት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናገረዋል።

ለመጪው ክረምት ጥቅም ላይ የሚውሉ ከ280 ሺህ በላይ የአፕል ግንዶችን በማስመጣት የማባዛት ሥራ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት ከ120 ሺህ በላይ የደጋ ፍራፍሬ ችግኞች ከ91 ሄክታር በላይ በሚሆን ማሳ ላይ መተከላቸውን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር መጋቢት 6/2009 ልማታዊ ባለሀብቶችን በአግባቡ ከማስተናገድ ባለፈ እውቀትና ልምድ በመቅሰም የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግሩን ማፋጠን እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አስታወቁ።

የክልሉ ምክር ቤት በስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ የዛሬ ውሎው በአስፈጻሚ አካላት ሪፖርት ላይ ሰፊ ምክክር በማድረግ ሪፖርቱን አጽድቋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በጉባኤው አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፣ ባለፉት ወራት በድርጅትና በመንግስት የተካሄደው የተሃድሶ ንቅናቄ ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር አስችሏል።

የተፈጠረው አደረጃጀት በክልሉ ለሰላም መታጣትና አለመረጋገት ምክንያት የነበረውን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ፈጥኖ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ወደክልሉ ለልማት የሚመጡ ባለሀብቶችን በአግባቡ ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚገባ የገለጹት አቶ ገዱ፣ በዚህም ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ እውቀትና ልምድ በመቅሰም የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግሩን ማፋጠን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሂደት መሰረተ ሰፊና አገር በቀል ኢንዱስትሪ ለመገንባት በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ወጣቶችን ውጤታማነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ተከታታይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

"ልማታዊ ባለሀብቶችን ፈጥነው የማያስተናግዱ አመራሮችና ባለሙያዎች ካሉ እያደናቀፉ ያሉት የህዝቡን የመልማት ፍላጎት፣ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ፈጠራና የገቢ እቅምን በመሆኑ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ርምጃ ይወስዳል" ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ በየዓመቱ ውስን ሞዴል አርሶአደሮችን ከመቁጠር ባለፈ በርካታ ሞዴሎች በየዘርፉ እንዲኖሩ የቀጣይ ተግባር መሆን እንዳለበትም አቶ ገዱ አሳስበዋል።

በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራው ባህል እየሆነ የመጣውን የቅንጅት፣ የነቃ ተሳትፎና በስፋት መተግባር ወደ ዘላቂነትና ሕዝባዊ ተጠቃሚነት ለማሸጋገር የምክር ቤት አበላት የመሪነት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

አቶ ገዱ እንዳሉት፣ በክልሉ ምዕራባማ ወረዳዎች የሚስተዋለው ሰፊ የደን ጭፍጨፋ የአየር ንብረት ለውጥን የሚያስከትል በመሆኑ ለማስቆም ተገቢ ርምጃ ይወሰዳል።

ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚነሱ የካሳና መሰል ችግሮችን ለመፍታትም አርሶአደሩ የመሬት ባለቤትነት መብቱ እንዲረጋግጥለት መንግስትን መጠየቅ እንዳለበት ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

በከተሞች የሚስተዋለው ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እንዲገታም ህጋዊ አማራጮችን በማስፋት ለሕገወጦች የማይደራደር የከተማ አመራር ለመፍጠር ተከታታይነት ያለው ሥራ እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

የወረዳና ቀበሌ ይከፈልልን እንዲሁም የከተማ ደረጃ ይደግልን በሚል ወደምክር ቤቱ የሚቀርቡ ጥያቄዎች "የክልሉ መንግስት ባለፈው ዓመት በጥናት ላይ ተመስርቶ ተገቢ ምላሽ በመስጠቱ በአሁኑ ወቅት ማስተናገድ አይቻልም" ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ይርሳው ታምሬ በበኩላቸው፣ የምክር ቤት አባላት አስፈጻሚ አካሉ ባቀረበው ዕቅድ መሰረት መፈጸም አለመፈጸሙን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሕብረተሰቡ ከዕቅድ ውጭ ጥያቄዎችን ሲያነሳም ከአካባቢው መስተዳድር ጋር በመሆን ከክልሉ አቅም ጋር እየተገናዘበ በሂደት የሚፈታ መሆኑን ማስረዳት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ምክር ቤቱ በከሰዓት ውሎው የዳኝነት አካሉን ሪፖርት ያዳመጠ ሲሆን በነገው ዕለትም የተለያዩ ሹመቶችንና አዋጆችን በማጽደቅ እንዲሁም ውሳኔዎችን በማሳለፍ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2009 በሚቀጥሉት 10 ቀናት በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የሰብሎችን የውሃ ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል ዝናብ እንደሚጠበቅ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በቀጣዮቹ 10 ቀናት አብዛኞቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ዝናብ ያገኛሉ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍሎች የተጠናከረና ሰፊ ዝናብ ማግኘት እንደሚጀምሩም ገልጿል።

ይህም ለበልግ ሰብሎች እድገትና ለቋሚ የውሃ ፍላጎት፣ ለአርብቶ አደሮችና ለከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለመጠጥ ውሃ እንዲሁም ለግጦሽ ሳር አቅርቦት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።

በአንዳንድ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ደግሞ በመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት የሚኖረው ደረቃማ አየር በቡቃያም ሆነ በእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰብሎችን የውሃ ፍላጎት ለማሟላት አሉታዊ ጎን እንደሚኖረው አመልክቷል።

አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የሚገኘውን ውሃ በአግባቡ በመያዝና ከብክነት በመከላከል ጥቅም ላይ እንዲያውል ኤጀንሲው አሳስቧል።

የባሮ አኮቦና ኦሞጊቤ፣ መካካለኛው ስምጥ ሸለቆ እንዲሁም የላይኛውና የመካከለኛው አዋሽ፣ የአባይ ደቡባዊና ምስራቃዊ አጋማሽ የላይኛው ተከዜና አፋር ደናከል ተፋሰሶች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።

በተጨማሪ በላይኛው ዋቢ ሸበሌና በላይኛውና መካከለኛው ገናሌዳዋ ተፋሰሶች በጥቂት ቦታዎቻቸው ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ጠቁሟል።

በተፋሰሶቹ ላይ የሚገኘው ዝናብ  የአካባቢውን አየር በማቀዝቀዝ በአፈር ውስጥ እርጥበት እንዲኖር ከማድረግ ባለፈ ለገጸ-ምድርና ለከርሰ-ምድር ውሃ ሃብት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ መግለጫው ጠቁሟል።

በቀሪዎቹ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖረው ደረቅና ፀሐያማ አየር የሰብል ስብሰባ ላላጠናቀቁ አካባቢዎች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመልክቷል።

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2009 በአገር አቀፍ ደረጃ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራምን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ ገለፁ፡፡

ፕሮግራሙን ለመደገፍ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማሕበር ጋር የአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ሮማን የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማሕበር የበላይ ጠባቂ ናቸው፡፡

ማህበሩ ላለፉት አራት ዓመታት በአዲስ አበባ በመንግሥት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ለጉዳት የተጋለጡ ህጻናት ትምህርታቸው ላይ እንዲቆዩና ውጤታማ እንዲሆኑ እየሰራ ነው፡፡

ማህበሩ በተያዘው በጀት ዓመት 20 ሺህ 135 ተማሪዎችን በምገባ ፕሮግራም ያካተተ ሲሆን 846 ለሚሆኑ እናቶች የሥራ እድል መፍጠሩም ተጠቁሟል፡፡

የማሕበሩ የበላይ ጠባቂ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት በአዲስ አበባ የተጀመረውን የምገባ ፕሮግራም ወደ ክልል ለማድረስ የትምህርት አካላት በፕሮግራማቸው አስገብተው የአቅማቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ የቅስቀሳ ስራ እየተሠራ ነው፡፡

ፕሮግራሙ በአገሪቱ እንዲዳረስና ዘላቂነት እንዲኖረው የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን እስካሁን የተገኘውን ልምድ ለማካፈልም ማሕበሩ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የተማሪዎች የምግባ ፕሮግራም በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚታዩ መማር ማስተማሩን የሚያስተጓጉሉ ሂደቶችን ለመቅረፍ አስችሏል፡፡

በዚህም ማርፈድ፣ መቅረት እና ትምህርት ማቋረጥ ላይ ለውጦች መታየታቸውን አመልክተው እንቅስቃሴው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያስረዱት፡፡

ከኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የተደረገው የአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ስምምነት የዚሁ ስራ አካል መሆኑና ሌሎች ድርጅቶችም ይህን አርአያነት እንዲከተሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ተፈራ ድርጅቱ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለአንድ አመት የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም የሚውል ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው 450 ተማሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡

ገንዘቡ የነገ አገር ተረካቢ የሆኑ ህጻናት በትምህርት ቤት ሆነው የምግብ ድጋፍ እንዲያገኙ ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት እገዛ ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡

የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ደብረወርቅ ልዑልሰገድ እንዳሉት ማህበሩ ከ2006 ዓ.ም ግማሽ ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ በሚገኙ 207 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎች በምገባ ፕሮግራም አቅፏል፡፡

ከምገባ ፕሮግራም ባለፈ በርካታ እናቶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል፡፡

ማህበሩ ዓላማውን እውን ለማድረግ ከተለያዩ የአገር ውስጥ ድርጅቶች ድጋፍ በማግኘት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2009 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ነገ በሚከፈተው አምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ።

ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቡትን የ2009 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ሪፖርት በማዳመጥ ጥያቄዎች ቀርበው ውይይት ያካሄድባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን ማዕቀፍ ለማሳካት የተያዘውን እቅድ መሰረት በማድረግ ዋጋን ለማረጋጋት የተሄደበትን ርቀት፣ የወጪ ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ይፈተሻሉ።

በማህበራዊ ዘርፍም ትምህርትና ጤና፣ ሴቶችና ወጣቶች እንዲሁም በአገሪቱ የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራት የውይይቱ አካል ይሆናሉ።

በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄው ያለበት ደረጃና የተገኘው ውጤት፣ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲን ለማጎልበት የተከናወኑ ተግባራት፣ አስቸካይ ጊዜ አዋጁ ያለበት ነባራዊ ሁኔታና የአገሪቱ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በዝርዝር እንደሚታዩም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢዜአ ያደረሰው መረጃ ያመለክታል።

 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን