አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 14 March 2017

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2009 ቆሼ አካባቢ በደረሰው የቆሻሻ መደርመስ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር 72 ደረሰ።

በአደጋው ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ስርዓተ-ቀብር በየእምነት ተቋሙ ተካሂዷል።

ዛሬ በደብረ አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ገብረክርስቶስ ቤተክርስቲያን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ የሆኑ ዜጎች ስርዓተ-ቀብር ተፈጽሟል።

በቤተክርስቲያኗ የፓትርያርኩ ተወካይ ብፁዕ አቡነ ያሬድ በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው የሙታን ወዳጆችና ቤተሰቦችን አጽናንተዋል።

በቀብሩ ስነ-ስርዓት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው፣ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ ዶክተር አምባቸው መኮንንና ሌሎችም የስራ ኃላፊዎች ተገኝተው ሀዘናቸውን ገልጸዋል።

አደጋው ያልታሰበና ሁሉንም ሰው ያሳዘነ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው አስተዳደሩ ለተፈናቃዮች ዘላቂ ማረፊያዎችን በማመቻቸት ከጎናቸው እንደሚቆም ገልጸዋል።

ኃላፊዎቹ ከስርዓተ-ቀብሩ በኋላ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የወጣቶች ማዕከል በጊዜያዊነት የተጠለሉ ተፈናቃዮችን ጎብኝተዋል።

በወጣት ማዕከሉ ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ 246 ዜጎች ተጠልለው ይገኛሉ።

በወረዳ አንድ ወጣቶች ማዕከል በጊዜያነት የሰፈሩ እናቶች፣ አባወራዎችና ህጻናት ናቸው።

ምክትል ከንቲባው ተዘዋውረው በማረፊያው ያሉ ዜጎች በጊዜያዊነት እንዲሟላላቸው የሚፈልጉትን ጠይቀዋል።

ከአደጋ ተርፈው በጊዜያዊ ማረፊያው ያሉ ሰዎችም መንግስት ዘላቂ ማረፊያ ይስጠን ብለዋል።

ምክትል ከንቲባው ተዘዋውረው በጊዜያዊ መጠለያው የሚገኙ ተፈናቃዮችን በጎበኙበት ወቅት ከተማ አስተዳደሩ ከአደጋው የተረፉ ወገኖችን፤ በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ቤተሰቦችን ለማቋቋምና ለመደገፍ ጥረት ያደርጋል ብለዋል።

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን ተፈናቃዮች ዘላቂ መኖሪያ እንዲያገኙ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2009 የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ለማሻሻል ለዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት የድርሻውን ለመወጣት እየሠራ መሆኑን ገለጸ።

አየር መንገዱ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት አጋማሽ ድረስ ስድስት አዳዲስ የበራራ መዳረሻዎችን ለመጨመር እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንደተናገሩት በአፍሪካ ያለው የአየር ትራንስፖርት ዕድገት ከሚፈለገው ደረጃ በታች ነው።

ለዚህም በዘርፉ የአቪዬሽን ዘርፍ የሠለጠኑ የቴክኒክ ባለሙያዎች፣ ኢንጂነሮች እንዲሁም የአውሮፕላን የበራራ ባለሙያዎች አለመኖርን በዋና ምክንያትነት አስቀምጠዋል። 

በዚህ የተነሳም አህጉሪቱ ለዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ዝውውር ከ300 በታች ድርሻ እንዳላትና ይህም ከአፍሪካ የሕዝብ ብዛት ጋር ሲተያይ አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁንና አንዳንድ የአፍሪካ አገራት አየር መንገዳቸው እንደገና እንዲያንሰራራ ወይም አዲስ በመክፈት ከዓለም ኅብረተሰብ ጋር ለመገናኘት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያም የዘርፉን የባለሙያ እጥረት ለማቃለል የአቪዬሽን አካዳሚ በመገንባት የደረሰችበት ደረጃ ለአፍሪካ ወቅታዊ ችግር መፍትሄ ስለሚሆን ተቀባይነት ይኖረዋል ነው ያሉት።

በዚህም አየር መንገዱ ለአፍሪካ የሠለጠነ የሠው ኃይል በማቅረብ የበኩሉን ለመወጣት እንደሚሰራ ነው የተናገሩት።

የአቪዬሽን አካዳሚው በአሁኑ ወቅት ከአውሮፕላን አብራሪዎች ትምህርት ቤት በስተቀር በሁሉም ዘርፎች ለውጭ አገር ዜጎች ክፍት መሆኑንም ነው ያስረዱት።

አካዳሚው የአውሮፕላን ቴክኒክ ጥገና፣ የአቪዬሽን አስተዳደር፣ የአውሮፕላን መስተንግዶና በሌሎችም የበራራ አገልግሎት ዘርፍ ላይ እንደሚያሰለጥን በመግለጽ።

ይህንንም በማስተዋወቅ ለአንዳንድ ተማሪዎችም ነጻ የትምህርት ዕድል በመስጠት አካዳሚው የአህጉሪቱን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ለማዘመን  ድርሻ እንዲኖረው አንሰራለን ነው ያሉት።

በሌላ በኩል የአየር መንገዱ የማስፋፊያ ፕሮጀክት መዘግየት ቢታይበትም በአሁኑ ወቅት ጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በመንገደኞች ላይ የተፈጠረው መጨናነቅ እንደሚቃለል እምነታቸውን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት አጋማሽ ማብቃያ ድረስ ስድስት አዳዲስ የበራራ መዳረሻዎችን ለመጨመር እየሰራ መሆኑንም ነው ሥራ አስፈጻሚው የተናገሩት።

እነዚህም አየር መንገዱ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ሁለንተናዊ ግንኙነት ለመፈጠርና ዲፕሎማቶችን በማጓጓዝ ለአፍሪካ ኅብረትም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 95፤ በአገር ውስጥ ደግሞ 20 መዳረሻዎች አሉት።

Published in ኢኮኖሚ

አዲሰ አበባ መጋቢት 5/2009 በአገሪቷ የሚገኙትን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች መጎብኘታቸው በትምህርት ቤት በንድፍ ሃሳብ ደረጃ የቀሰሙትን እውቀት ይበልጥ ለማበልጸግ እንደሚያስችላቸው ታሪካዊ ቦታዎችን የጎበኙ ተማሪዎች ገለጹ።

የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የመጀመሪያና ሁለተኛ ዓመት የቱሪስት አስጎብኚ እና የቱሪዝም ማኔጅመንት ዘርፍ ተማሪዎችን በትግራይና በአማራ ክልል የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን አስጎብኝቷል።

በአጠቃላይ 272 የሚሆኑ ተማሪዎች በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል የሚገኙትን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ጎብኝተዋል።

ተማሪዎቹ ከጎበኟቸው የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ አክሱም ሃውልት፣ የፋሲል ግንብ እና ጣና ሃይቅ ደሴቶች ላይ ያሉ ገዳማት ይገኙበታል።

በጉብኝቱ  ወቅት ከተማሪዎቹ መካከል መታሰቢያ እታለማ በሰጠችው አስተያየት በትምህርት ቤት በንድፍ ሃሳብ ደረጃ የተማረችውን ታሪክ በተግባር ማየቷ ወደ ስራ ስተሰማራ ብቁና ውጤታማ እንደሚያደርጋት ገልጻለች።

ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ የቱሪዝምና የካልቸራል አንትሮፖሎጂ መምህር አቶ ተፈሪ አቦሃይ እንደገለፁት፤ ጉብኝቱ ለተማሪዎቹ በንድፍ ሃሳብ የተማሩትን በተግባር ከማሳየት ባሻገር የአገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲስፋፋ ያደርጋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አሸብር ተክሌ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ትምህርት ቤቱ ብቃት ያለው ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለኢንዱስትሪው ለማፍራት በዋናነት የተግባር ተኮር ስልጠና ላይ በትኩረት እየሰራ ነው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2009 ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ የሆነ የአፍሪካ አገራት የአምባሳደር ሚስቶች ቡድን ኦሞ ቻይልድ አሶሴሽን ለተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት የ180 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ።

የቡድኑ ኃላፊና በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር ባለቤት ሚስ ኒሃል ፋውዚ የተሰበሰበውን ገንዘብ ለአሶሴሽኑ መስራችና ኃላፊ አቶ ላሌ ላቡኮ አስረክበዋል። 

በደቡብ ኦሞ ዞን በሐመር፣ በካራ እና በና ብሔረሰቦች የሚወለድ ህጻን የመጀመሪያ ጥርሱ በላይኛው ድዱ ከበቀለ የብሔሩ የጎሳ መሪዎች እንዲገደል ያደርጋሉ።

በጎሳ መሪዎቹ አመለካከት ጥርሱ በላይኛው ድዱ የበቀለ ህጻን እርግማን ያመጣል የሚል እሳቤ አላቸው፤ አሶሴሽኑ ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እንዲቀርና ህጻናቱ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ድጋፍ የሚያደርግ ነው።

የኦሞ ቻይልድ አሶሴሽን መስራችና ኃላፊ አቶ ላሌ ላቡኮ ቡድኑ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም ይኸው ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን በሐመር፣ በና እና ካራ ብሔረሰቦች የሚወለደው ህጻን  የመጀመሪያ ጥርሱ በላይኛው ድዱ ከበቀለ፤ "ሚንጊ” (እርጉም) ነው በሚል በብሔሮቹ የጎሳ መሪዎች እንደሚገደል ገልጸዋል።

አሶሴሽኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ባካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ ድርጊቱ በደቡብ ኦሞ ዞን ካራ ብሔር እንዲቆም ማድረጉን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት በሁሉም አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የቡድኑ ኃላፊ ሚስ ኒሃል ፋውዚ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የገንዘብ ድጋፉ በዞኑ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ህጻናቱ እንዳይገደሉ አሶሴሽኑ ለሚያደርገው ጥረት የሚውል ነው ብለዋል።

በአካባቢው ያሉ ህጻናትን ከዚሁ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለመከላከል፣ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ፣ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ ለምግባ ፕሮግራም፣ ለቁሳቁስ ድጋፍ እና ለግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንደሚውል ገልጸዋል።

በቀጣይም ቡድኑ ለአሶሴሽኑ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።

የኦሞ ቻይልድ አሶሴሽን በ2001 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በደቡብ ኦሞ ዞን ለሚገኙ 50 ህጻናት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የአፍሪካ የአምባሳደር ሚስቶች ቡድን ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ድጋፍ ለማድረግ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1990ዎቹ የተቋቋመ ነው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2009 በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ላይ የሚመክረው አራተኛው ዓለም አቀፉ የአቪዬሽን ድርጅት ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው።

በአፍሪካ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ሲምፖዚየም ከሚያዚያ 3 እስከ 6 ቀን 2009 ዓ.ም  ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንዳሉት ሲምፖዚየሙ በዘርፉ የሚሰሩ ባለሙያዎች እርስ በእርሳቸው እንዲቀራረቡ የማድረግ ሚና ይጫወታል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ያሉ ዘመናዊ መሣሪያዎችና ስልቶች እንዲተዋወቁ እንዲሁም ለዘርፉ የተሻለ አማራጭ ለማፈላለግ ዕድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

ይህም በዘርፉ ያለውን የካበተ ልምድ እርስ በእርስ በመለዋወጥ ዘርፉን ለማዘመን እንደሚረዳ ነው የጠቆሙት።

ሲምፖዚየሙ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱ፤ የአህጉሪቱ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ትኩረት እንዲያገኝና ሊያድግ በሚችልበት ጉዳይ ላይ ምክክር ለማድረግ እንደሚጠቅም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድን በሲምፖዚየሙ ይበልጥ ለማስተዋወቅ፤ በተለይም የአቪዬሽን አካዳሚውን ለማጠናከር ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል። 

ሲምፖዚየሙ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ አየር መንገድና በመንግሥታቱ ድርጅት የአቪዬሽን ድርጅት ትብብር ነው።

በሲምፖዚየሙ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ500 በላይ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሲምፖዚየሙ "በጋራ አቅምን ለመገንባት ሥልጠና እንጨምራለን" በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል።

Published in ኢኮኖሚ

መጋቢት 5/2009 ዓ.ም በሁሉም ንግድ ባንኮች 1 የአሜሪካን ዶላር በ22 ብር 6811ሳንቲም እየተገዛ በ23 ብር ከ1347ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡የእንግሊዝ ፓውንድ ስተሪሊንግ በ27 ብር ከ6914 ሳንቲም እየተገዛ በ28 ብር ከ2452 ሳንቲም እየተሸጠ ነው፡፡ 
የወርቅ ዋጋን ስንመለከት ደግሞ 24 ካራት አንድ ግራም ወርቅ በ924ብር ከ9814ሳንቲም ሲሸጥ ባለ14 ካራት ደግሞ 539ብር ከ5725ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡የሌሎችን ሃገራት የምንዛሬ ዋጋና የወርቅ ዋጋ በተከታዩ ሰንጠረዥ ይመልከቱ፡-

No automatic alt text available.

Published in ኢኮኖሚ

የኢፌዲሪ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን መጋቢት 5/2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች እለታዊ የገበያ ዋጋ መረጃ አድርሶናል፡፡

No automatic alt text available.

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ መጋቢት 5/2009 የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ እሴት የተጨመረበት ምርት ለሃገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ያደርገናል ብለው እንደሚጠብቁ  ቡና አቅራቢና ላኪ ባለሃብቶች ተናገሩ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ይሄው ፓርክ እውን ሆኖ ለውጤት እንዲበቃ በጉጉት የሚጠብቁት መሆኑን ባለሃብቶቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

የአማሮ ጋዮ ቡና ላኪ ድርጅት ስራ አስኪያጅና ባለቤት ወይዘሮ አስናቀች ቶማስ የኢንዱስትሪ ፓርኩ መገንባት ከምንም በላይ የስራውን ባለቤት አርሶአደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"የአርሶአደሩ ተጠቃሚነት በቂ ምርት እንዲያመርት ያግዘዋል"  ያሉት ባለሀብቷ  ከዚህ ቀደም በጥሬ የሚልኩት ቡና እሴት ተጨምሮበት የሚላክበት እድል የሚፈጥር በመሆኑ ምርታቸው ተገቢውን ዋጋ ያገኛል ብለው በተስፋ እንደሚጠብቁም ገልጸዋል፡፡

ምርቱ ከአርሶአደር ማሳ የሚሰበሰብ በመሆኑ በጥራት ለማምረት እንደሚያስችል ጠቁመው "ባለሃብቱ ከአርሶአደሩ ጋር በቅንጅት በመስራት የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ ተጠቃሚ መሆን አለበት" ብለዋል፡፡

በግብርና ምርቶች ላይ ትኩረት ያደረገው የፓርኩ ግንባታ ሙሉ በሙሉ መሰረተ ልማት ተሟልቶለት ስራው በአንድ ማዕከል መከናወኑ ጥራት ያለውን ምርት እንዲመረት ያግዛል " ያሉት ደግሞ የዳዬ በንሳ ቡና ላኪ ድርጅት ባለቤት አቶ አሰፋ ዱካሞ ናቸው፡፡

ባለሃብቱም እሴት የተጨመረበትን ምርት ወደ አለም ገበያ በማቅረብ ተገቢውን ዋጋ ከማግኘት ባለፈ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

ለአካባቢው የህብረተሰብ ክፍሎችም የስራ እድል በመፍጠር ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡

የኢንጅነር ዘላለም ቡና አቅራቢና ላኪ ድርጅት ባለቤት አቶ ዘላለም ወልደአማኑኤል ቡና እየነገዱ ባደጉበት የትውልድ ቀያቸው ፓርኩን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡

ባለሀብቱ እንደገለጹት ድርጅታቸው ከዚህ ቀደም በጥሬ ለሃገር ውስጥና ለአለም ገበያ የሚልካቸው ምርቶች በፓርኩ እሴት ተጨምሮበት መላኩ ሃገሪቱ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ያሳድጋል፡፡

የሃብቱ ባለቤት የሆነው አምራች አርሶአደር ተገቢውን ጥቅም አግኝቶ የአካባቢውን ስያሜ የያዘ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እድል የሚፈጥር መሆኑንም  ገልጸዋል፡፡

በዚህም እሳቸውን ጨምሮ በዘርፉ ለተሰማሩ የክልሉ ባለሃብቶች ትልቅ እድል የሚፈጥር በመሆኑ በስራ ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የፓርኩ ተገንብቶ እውን መሆን  እሴት የተጨመረበት ምርት ለሃገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ያደርገናል ብለው እንደሚጠብቁ  ባለሀብቶች ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች  ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደሴ ዳልኬ በበኩላቸው ፓርኩ የሚገነባበት ቦታ በአለም ደረጃ ታዋቂ የሆነው የሲዳማ፣ ጌዲኦና ይርጋጨፌ ቡና የሚመረትበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ እንደሉት የፓርኩ መገንባት ለዘመናት በጥሬ የሚላከው ቡና እሴት ተጨምሮበት የሚላክበት አቅም ይፈጥራል፡፡

በዚህም የዘርፉ ተዋናይ የሆኑ የክልሉ ባለሃብቶችም ሆነ ወደ ባለሃብትነት ለተሸጋገሩ ሞዴል አርሶ አደሮች ምቹና የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በፓርኩ ለሚገቡ ባለሃብቶች የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል፡፡

በሲዳማ ዞን ዳሌ ወረዳ ዌሬናታ ቀበሌ በሁለት መቶ አስራ አምስት ሄክታር ላይ የሚገነባው የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የእንስሳት ተዋጽኦ፣ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ ቡናና ማር ከአርሶአደሩ ተቀብሎ እሴት ጨምሮ በማቀነባበር ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለገበያ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2009 ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በካፍ የምስረታ በዓልና በጠቅላላ ጉባኤው ላይ በእንግድነት ለመገኘት ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉንና 39ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ያካሂዳል።

ከፕሬዝዳንቱ በተጨማሪ የፊፋ ዋና ጸሐፊ ፋትማ ሳሙራ ለዚሁ ጉባኤ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እና ፋትማ ሳሙራ በጉባኤው ላይ በእግር ኳስ ስፖርት ልማት ላይ ያተኮሩ የሃሣብ ልውውጦች እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በተለይም ዋና ጸሐፊዋ የፊፋ ክፍለ አህጉራዊ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በአዲስ አበባ በሚቋቋምበት አግባብ ዙሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ ጋር ለመምከር ኘሮግራም ይዘዋል፡፡

ፊፋ በአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት ከመክፈት በተጨማሪ ተከታታይ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር እርስቱ ይርዳ፣ ሚኒስትር ዴኤታው ተስፋዬ ይገዙ፣ እንዲሁም የካፍ ኘሬዝዳንት ኢሣ ሃያቱ እና ሌሎችም የስራ ኃላፊዎች ለእንግዶቹ አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው ይጠበቃል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ መጋቢት 5/7/2009 ተሰናባቿ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ አህጉሪቱን ለማስተሳሰር ያደረጉት ጥረት የሚበረታታ እንደነበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ።

የስራ ዘመናቸው በስኬት ይጠናቀቅ ዘንድ በየደረጃው የሚገኙ የኢትዮጵያ የስራ ኃላፊዎች ድጋፍ እንዳልተለያቸው ደግሞ ዲላሚኒ ዙማ ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንት ሙላቱ ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው የቀድሞ የሕብረቱን ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማን ሽኝት አድርገውላቸዋል።

ሽኝቱን የተከታተሉት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና በአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዋህደ በላይ እንደተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ''ሊቀ-መንበሯ በቆይታቸው የአህጉሪቱን ችግሮች በመፍታት ረገድ ትልቅ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል'' ብለዋል።

ለሕብረቱ መጠናከርና ሰላም የሰፈነባትና የበለፀገች አህጉር ለመፍጠር ያበረከቱት አስተዋጽኦ በአባል አገራቱ ዘንድ የሚያስመሰግናቸው መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በአህጉሪቱ ለመልካም አስተዳደር እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርና የህግ የበላይነትን ለማስፈንም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ቆይተዋል ሲሉ ገልጸዋል።

አህጉሪቱን በስኬት ሲመሩ መቆየታቸው በተለይም 'አይችሉም' ተብለው ለሚፈረጁት ሴቶች አርአያ እንደሚያደርጋቸው ፕሬዝዳንቱ መናገራቸውን አስረድተዋል።

የሴቶችን ተሳትፎ እና አቅም በማሳደግ በኩልም ዙማ በሊቀ-መንበርነታቸው ዘመን ጉልህ ድርሻ ሲያበረክቱ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።

በተለይም አጀንዳ 2063ን በማስፈፀም ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ነው የተናገሩት።

ደቡብ አፍሪካና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩበት መስክ ላይ የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደነበርም ነው የገለጹት።

ተሰናባቿ የሕብረቱ ሊቀ-መንበር ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ በበኩላቸው ''ኢትዮጵያ በቆየሁባቸው አራት ዓመታት ተኩል ከአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር የነበረኝ ትብብር ስኬታማ እንድሆን አድርጎኛል'' ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያን ተማሪ ከነበሩበት ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚያውቋት የተናገሩት ዙማ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያሳየችው ለውጥ "የተለየ ነው" ብለዋል።

ይኸም ለሌሎች የአፍሪካ አገራት በአርዓያነት የሚጠቀስ እንደሆነ ተናግረዋል።

''እንደ አገር በተለይም በአዲስ አበባ ያለው ምግብ፣ ሙዚቃውና አየሩ በጣም የሚያስደስት ነው፣ በቆይታዬም ስኬታማ ነበርኩ፤ ነገር ግን አሁንም ለአህጉሪቷ ዕድገት ብዙ መስራት ይጠበቅብኛል'' ብለዋል።

ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ የአራት ዓመት ተኩል የሕብረቱ ሊቀ-መንበርነታቸውን አጠናቀው ባለፈው ጥር ወር በትረ-ስልጣኑን ለቻዳዊው ሙሳ ፋቂ መሃማት ማስረከባቸው ይታወሳል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን