አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 13 March 2017

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2009 በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የቆሻሻ ክምር ተንዶ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ።

በቆሼ አካባቢ በደረሰው ድንገተኛ  አደጋ ሕይወታቸው ያለፈና አስከሬናቸው የተገኘ ዜጎች ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ የፌዴራልና የአስተዳደሩ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል።

የኦርቶዶክሰ እምነት ተካታዮቹ በአቡነ አረጋዊ ቤተክርሰቲያን ቀብራቸው የተፈጸመ ሲሆን፤ የእስልምና እምነት ተከታዮች ደግሞ ኮልፌ ቀራንዮ በሚገኘው የእምነቱ ተከታዮች መካነ መቃብር ነው የተፈጸመው።

የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች የነበሩት ደግሞ ስርዓተ ቀብራቸው በለቡ መካነ መቃብር ተካሂዷል።

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ  በተለምዶ ቆሼ በተባለው አካባቢ አደጋው የደረሰው ከትናንት በስቲያ ከምሽቱ 2:00 ገደማ ነበር።

ከተማ አስተዳደሩ የአደጋው ተጎጂ ቤተሰቦች እንዲቋቋሙና አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንዲያገኙ የጀመረውን ተግባር በልዩ ትኩረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ማስታወቁ ይታወሳል። 

Published in ማህበራዊ

መቐለ መጋቢት 4/2009 በትግራይ ክልል ከተሞች  ነዋሪዎችን  ተጠቃሚ  የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን  የክልሉ  ምክትል ርዕስ መስተዳደር ገለጹ፡፡

ሰባተኛው የትግራይ ክልል የከተማች ፎረም ትናንት በአዲግራት ከተማ  ተካሄዷል፡፡

ምክትል ርዕስ መስተዳድሩና የንግድ ከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አዲስ አለም ባሌማ  በፎረሙ ላይ እንደገለጹት መንግስት በከተሞች የጀመራቸውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ግንባታና  የመሰረተ ልማት ስራዎችን እያካሄደ ነው፡፡

መኖሪያ ቤት ለሌላቸው ነዋሪዎች የክልሉ መንግስት በማህበር በማደራጀት የመኖሪያ ቤት እንዲገነቡ  ጥረት እየተደረገ ሲሆን የከተሞችን ጽዳትና ውበት ጠብቆ  በአረንጓዴ ልማት በማጠናከር  ለነዋሪዎች  ምቹ  ለማድረግ  እየተሰራ ነው፡፡

" ከተሞች በሃገራዊ እድገት  ያላቸውን ድርሻ ከፍ ለማድረግም የነዋሪዎች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ተሳስሮ መቀጠል አለበት "ብለዋል፡፡

ፎረሙ አስተማሪ የሆኑ ተሞክሮዎች እንዲስፋፉ ከማድረግ በተጨማሪ ከተሞችን የልማትና የዴሞክራሲ ማዕከል በማድረግ መልካም አስተዳደር እንዲያሰፍን አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ተብሏል።

በፎረሙ ላይ በአዲግራት  ከተማ  የተከናወነው  የከተማ ልማት፣ጽዳትና ውበት እንዲሁም በአላማጣ የታየው የህዝቦች የልማት ተሳትፎና የወጣቶች ተጠቃሚነት እንደተሞክሮ ቀርቧል።

የአዲግራት  ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተስፋልደት ደስታ  በከተማው  የቆሻሻ መድፊያ የነበሩ ቦታዎችን በነዋሪው ተሳትፎ ወደ ልማት በመቀየር ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው  እንዲጠቀሙ  ማድረጋቸውን  ለፎረሙ ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር ለፅዳትና ውበት አገልግሎት 13 ሚሊዮን ብር ከመመደቡ በላይ ነዋሪዎችና ባለሀብቶች  ተሳትፎ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ለሁለት መቶ ሴቶች  የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ከንቲባው አመልክተዋል፡፡

በድንጋይ ንጣፍ የመንገድ ግንባታ ፣ በከተማ ግብርና በንግድና በሌሎችም ዘርፎች ለ364 ወጣቶች የስራ እድል መፍጠራቸውን የተናገሩት ደግሞ የአላማጣ ከተማ ከንቲባ ረዳኢ ብርሀኑ ናቸው፡፡

የሽራሮ ከተማ አስተዳደር  ከንቲባ አቶ ዳኛው ውሬታ በበኩላቸው "ፎረሙ  በከተሞች የሚታዩ የመልካም አስተዳደርና የመሰረተ ልማት ችግሮችን የመፍታት ሚናው የጎላ ነው" ብለዋል።

በአዲግራት ከተማ ያለው የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት እንዲሁም ከተማው በአረንጓዴ ልማት እንዲሸፈን  መደረጉ ትምህርት እንደሆናቸውም ጠቅሰዋል፡፡

በፎረሙ   የ12 ከተሞች ከንቲባዎች  ፣የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ፣የመሰረተ ልማት ቢሮ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አርባ ምንጭ መጋቢት 4/2009 በጋሞ ጎፋ ዞን በከተማና በገጠር የሥራ ዕድል የሚፈጠርላቸው 54 ሺህ 582 ወጣቶች መለየታቸውን የዞኑ ወጣቶችና ስፓርት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ምክትል ኃላፊና የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራና ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዓለም ባበና እንደተናገሩት፣ በዞኑ የሥራ ዕድል ከሚፈጠርላቸው ወጣቶች መካከል 32 ሺህ 527 የሚሆኑት በገጠር የሚኖሩ ወጣቶች ናቸው።

ከእነዚህ ወጣቶች መካከል ሦስት ሺህ 133 የሚሆኑት የመጀመሪያ ዲግሪና የዲፕሎማ ምሩቃን ናቸው።

ምሩቃኑ የመሬት ይዞታና መነሻ ካፒታል የሌላቸው መሆኑን ገልጸው፣ስልጠና አግኝተው ወደ ሥራ እንዲገቡ በሕዝብ መድረኮች የተለዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መንግስት በአገርአቀፍ ደረጃ ለወጣቶች ከያዘው ተዘዋዋሪ ፈንድ 201 ሚሊዮን ብር ለጋሞ ጎፋ መመደቡን የተናገሩት ኃላፊው፣ 50 ከመቶ የሚሆነው በጀት በዚህ ዓመት ሥራ ላይ እንደሚውል ገልጸዋል።

አቶ ተስፋዓለም እንዳሉት፣ ከተፈቀደው ተዘዋዋሪ በጀት ከ121 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ለገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ የሚውል ሲሆን ቀሪው 80 ሚሊዮን ለከተማው ወጣቶች ይውላል።

ወጣቶች በብድር የሚሰጣቸውን ገንዘብ ተጠቅመው ወደሥራ የሚሰማሩበት 21 ሺህ 727 ሄክታር በተፋሰስ የለማ መሬት በገጠር ተለይቶ መዘጋጀቱንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በከተሞችም መሸጫና ማምረቻ ቦታዎችን ለይቶ የማካለል ሥራ እየተሠራ መሆኑን አቶ ተስፋአለም አመልክተዋል፡፡

በዞኑ ምዕራብ አባያ ወረዳ የአልጌ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ደሳለኝ ቲኮ እንደገለጸው፣ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ዋስትና ያለውና የወጣቱን ተጠቃሚነት በዘላቂነት የሚያረጋግጥ መሆን ይኖርበታል።

ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአካውንትንግ የመጀመሪያ ድግሪ ተመርቆ ከወረዳዉ በተደረገለት ድጋፍ በጓሮ አትክልት ሥራ መሰማራቱን የገለጸው ወጣቱ፣ አብዛኞቹ  የሥራ መስኮች በዘላቂ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ አለመሆናቸውን ጠቁሟል።

በአርባ ምንጭ ከተማ የቤሬ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት እንዳልካቸው ደጀኔ በበኩሉ፣ "ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ችግር የሆኑ ጉዳዮች በቀጣይ ተጠንተው ሊፈቱ ይገባል" ብሏል።

ከሁለት ዓመት በፊት በጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ሥራ ተሰማርቶ ባገኘው ገንዘብ ሥራውን ማሳደግ ቢፈልግም የመሰሪያ ቦታ ማግኘት ባለመቻሉ ያለሥራ መቀመጡን ተናግሯል፡፡

መንግስት ወጣቶችን ወደሥራ ለማሳማራት በቅርቡ ባካሄደው ምዝገባ መካተቱን የገለጸው ወጣቱ፣ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል የራሱንና የጓደኞቹን ኦኮኖሚያዊ ችግር በዘላቂነት ሊፈታ ይችላል የሚል ተስፋ አንዳለው ገልጿል።

በጋሞ ጎፋ ዞን በተያዘው በጀት ዓመት ወደስራ እንዲገቡ ከተለዩት 54 ሺህ 582 ሥራ አጥ ወጣቶች መካከል 21 ሺህ 274 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ከዞኑ ወጣቶችና ሰፓርት መምሪያ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ መጋቢት 4/2009 መንግስት በመደበው ከፍተኛ በጀት የተመቻቸውን የስራ እድል በአግባቡ በመጠቀም ሚሊየነር መሆን እንደሚቻል በተግባር ያረጋገጡ ወጣት ሞዴል አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

ወጣት ዘውዱ ዓለሙ በስምንተኛው አገር አቀፍ የሞዴል አርሶአደሮች ፌስቲቫል ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ እጅ የሜዳሊያ ሽልማት ከተቀበሉ ሚሊዮነር ወጣት አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ነው ።

እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ተምሮ ውጤት ስላልመጣለት ወደ ግብርና ስራ መሰማራቱን ገልጿል፡፡

በአንድ በኩል የግብርና ስራውን ጎን ለጎን ደግሞ የእንስሳት እርባታውን አቀናጅቶ በማከናወን በአጭር ጊዜ ውስጥ  9 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ሀብት ማፍራት እንደቻለ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ተናግሯል፡፡ 

ከሰሜን ሸዋ ዞን ቅንብቢት ወረዳ በስኬቱ ለአገር አቀፍ ሽልማት የበቃው ወጣት ዘውዱ 50 ለሚጠጉ ወገኖቹ የስራ እድል ፈጥሯል፡፡

ወጣቶች ሀብት አፍርተው እሱ የደረሰበት ደረጃ ደርሰው የማየት ፍላጎት እንዳለው ያመለከተው ወጣት ዘውዱ " ስራ በመፍጠርና  ጠንክሮ በመስራት ሀብት ማፍራት እንደሚቻል በተግባር አይቼዋለሁ፤ የእድሜ እኩዮቼም  እንደኔ እንዲሆኑ እመኛለሁ "ብሏል፡፡

ከባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ 7 ሚሊዮን ብር ሀብት በማፍራቱ ተመልምሎ ለሽልማት የበቃው ወጣት አርሶ አደር ሰለሞን ደገፋ በበኩሉ በመስመር መዝራትን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ በመጠቀም ለስኬት መብቃቱን ተናግሯል ።

ከእርሻው ስራ በተጓዳኝ በከተማ የመኖሪያ ቤትና ሁለት መጋዘኖች ገንብቶ ወደ ንግድ መግባቱን ገልፆ "ወጣቶች መንግስት የሚፈጥርላቸውን የስራ እድል በአግባቡ ከተጠቀሙበት ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ከእኛ ማረጋገጥ ይችላሉ" ብሏል ።

" የወጣት ሞዴል አርሶ አደሮች ስኬት ማስፋት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ወጣት ስራ ፈጣሪዎች ሲሸለሙ ማየት እንደምንችል እርግጠኛ ነኝ " ብሏል፡፡

ከምስራቅ ሸዋ ዞን ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ ተመልምሎ የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ወጣት አርሶ አደር ሹሚ ዱቤ  በበኩሉ  በግብርና ስራ የ8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ባለሃብት መሆን እንደቻለ ተናግሯል፡፡

"  የስራ እድል የፈጠረላቸው ከአስር የማያንሱ  ወጣቶች የስኬቴ ሚስጢር ናቸው " በማለት ይገልፃቸዋል ።

ተምረው ቤት የተቀመጡ በርካታ ወጣቶች የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ተአምር እንደሚሰሩ የሚገልፀው  ወጣት ሹሚ በአንድ በኩል መንግስት እድሉን ሊፈጥርላቸው በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቶቹ እድሉን በአግባቡ ተጠቅመው ከልብ መስራት እንዳለባቸውም ጠቁሟል፡፡

በተለይ የከርሰ ምድር ውሃን የሚጠቀሙና የመስኖ ልማትን የሚመርጡ ወጣቶች ጠንክረው ከሰሩ ስኬታማ እንደሚያደርጋቸውም ጠቁሟል።

መንግስት  ከፍተኛ በጀት በመመደብ ለይቶ ያመቻቸው  የስራ እድል በአግባቡ በመጠቀም ሚሊየነር መሆን እንደሚችል ወጣት ሞዴል አርሶ አደሮቹ የራሳቸውን የተግባር ውጤት በማመላከት ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ለሞዴል አርሶአደሮች ሽልማት በሰጡበት ወቅት  ባስተላለፉት መልእክት መንግስት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሴቶችና ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እየተረባረበ መሆኑን ተናግረዋል ።

በተለይም የወጣቶች ዘመናዊ የግብርና ልማት ተሳትፎ በአግባቡ ከተመራ የግብርናው ዘርፍ በማዘመን ታሪካዊ ተልእኮ የሚፈፅም እንደሚሆንም ገልፀዋል ።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2009 “በዲፕሎማሲው መስክ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሁሉም ድጋፍ ያስፈልጋል” አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰራተኞች የሴቶችን ቀን በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሂሩት እንደገለጹ፤ በዲፕሎማሲው መስክ የሴቶችን ቁጥር ለመጨመር የሁሉም ድጋፍ አስፈላጊ ነው።

ይህን ችግር ለመፍታትና የሴት ዲፕሎማቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሰው ሃብትና የስልጠና ክፍሎች በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

'ሴቶችን ወደ ዲፕሎማትነት ማምጣት የሚቻለው በቅስቀሳ ብቻ አይደለም' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ወደ ተለያዩ የስራ ክፍሎች በመሄድ ሴቶችን ማሳተፍና ወደ ሥልጠና ተቋማት እንዲገቡ ማድረግ የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።

ለውጭ ጉዳይ ጥንካሬ በእውቀትና በሙያ ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማት ማፍራት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በብዛት ሴቶች በዘርፉ ተሳታፊ ቢሆኑ ለስራው ውጤታማነት የጎላ ድርሻ እንደሚያበረክቱም ነው የገለፁት።

በህንድ የኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደር ዶክተር ገነት ዘውዴ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በአሁን ወቅት በአገሪቷ ያሉት ሴት ዲፕሎማቶች ቁጥር ሰባት በመቶ ብቻ ነው።

ለዚህ ምክንያቱ የባህል ተጽዕኖ፣  የተቋማት አሰራር፣ ሴቶች ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት ዋነኞቹ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

'ዲፕሎማሲ የወንድ ስራ ነው' የሚለውን አመለካከት ለመቀየር ተቋማት ለሴቶች ምቹ ሁኔታን መፍጠርና ሴት ዲፕሎማቶችን ማበረታታት እንዳለባቸውም አምባሳደሯ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ለ41ኛ ጊዜ የዓለም የሴቶች ቀን “የሴቶች የቁጠባ ባህል ማደግ ለህዳሴያችን መሰረት ነው” በሚል መሪ ሀሳብ መከበሩ ይታወሳል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2009 በአስረኛው የአዲስ አበባ መሪ እቅድ መሠረት የሚገነቡ መንገዶች የእግረኛ መንገድ በማስፋት ሽፋኑን ለማሳደግ ትኩረት የሰጠ መሆኑን የአዲስ አበባ መሪ ፕላን ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ። 

በመሪ እቅዱ የመዲናዋ የመንገድ መሠረተ ልማት 30 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው የእግረኛ መንገድ ነው ተብሏል።

ጽህፈት ቤቱ በመሪ እቅዱ ፕሮጀክት የመንገድ ዘርፍ አተገባበር ባስጠናቸው እቅዶች ላይ ከአስፈጻሚ አካላት ጋር ዛሬ አውደ ጥናት አካሂዷል።

በአውደ ጥናቱ ላይ በአምስትና በአስር ዓመቱ የአዲስ አበባ መሪ እቅድ ፕሮጀክት ስልታዊ የልማት እቅድ ትግበራ መካከል ቅድሚያ ከተሰጣቸው ተግባራት የመንገድና መጓጓዣ አንዱ መሆኑ ነው የተገለጸው።

የመዲናዋ የትራፊክ ፍሰት እንዲሳለጥና የትራፊክ አደጋን በግማሽ ለመቀነስ ከተቀየሱ ተግባራት መካከል ለእግረኛ መንገድ ሰፊ ሽፋን መስጠት እንደሆነም ተመልክቷል።

በፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ የትራንስፖርትና መንገድ ጥናት ባለሙያ አቶ ጋሻው አበራ፤ ከዚህ በፊት በተከናወኑ የመንገድ ግንባታዎች ለእግረኛ መንገድ ትኩረት ሳይሰጥ መቆየቱን ገልጸው፤ "በ10ኛው መሪ እቅድ የመንገድ የጎንዮሽ እይታን ማስፋት ትኩረት ተደርጎበታል" ብለዋል።

በዚህም በአዲሱ መሪ እቅድ በሚዘረጉ መንገዶች 60 በመቶው ለእግረኛ መንገድ ሽፋን የሚተው መሆኑን ገልጸዋል።

መርካቶን በመሳሰሉ ዋና ዋና የህዝብ መንቀሳቀሻ ማዕከላትና የገበያ ቦታዎችም የእግረኛ መንገዶች በጥናት መለየታቸውን ነው የተናገሩት። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመሪ እቅዱ የትራፊክ ፍሰቱን መጨናነቅ ለማቃለል ሰባት የጭነት ተሽከርካሪ ትራንስፖርት መነኸሪያዎች በጥናቱ ተለይተዋል።

የጭነት ተሽከርካሪዎች በየትኛው ሰዓት በከተማ ውስጥ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ በመደንገግ  የሰዓት ገደብ እንደሚበጅላቸውም ተገልጿል።

የህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ ማዕከላዊ መነኸሪያ፣ የከተማ ውስጥና የክልል የሕዝብ ትራንስፖርት መነኸሪያዎች ተብለው በጥናት ተለይተዋል።

ተሽከርካሪዎች በአውራ መንገዶች ላይ እንዳይቆሙ ለማድረግም በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች 66 የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ወይም ፓርኪንጎች በጥናቱ እንደተለዩም ተገልጿል። 

በአስር ዓመቱ መሪ እቅድ ፕሮጀክት 330 ኪሎ ሜትር መንገዶችና 47 ልዩ መንገዶች የሚገነቡ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ 27 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ ተገምቷል።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ተጓዥ የጉዞ ፍላጎት መኖሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

Published in ኢኮኖሚ
Monday, 13 March 2017 22:28

ጉዞ ወደ አባገዳ ምድር

                                                                  አብዱራዛቅ ጂማ (ኢዜአ)

የገዳ ስርዓት ምንጭ ብቻ አይደሉም፤ ይልቁንም ዛሬም ድረስ የኦሮሞን ባህል  ጠብቀው ማቆየት መቻላቸው መላያቸው ነው፤ ቦረናዎች። ዘንድሮ ግን ፈታኝ ጉዳይ ገጠማቸው፤ ቦረና እና ጉጂ በድርቅ ተጎብኝተዋል። ሊሸጡአቸው የሚሳሱላቸው፣ ከልጆቻቸው ለይተው የማያዩአቸው ከብቶቻቸው ዓይናቸው እያየ ሲሞቱም ተመልክተዋል። በዚህም ክፉኛ አዝነዋል። መንግስት እያደረገላቸው ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ይጠይቃሉ፣ ቦረናና የቦረና ምድር።

በቦረናና አከባቢው የተከሰተው ድርቅ ምን ጉዳት እንዳስከተለ፣ እንዴትስ ችግሩን ለማቃለል ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነ ለማወቅ የጋዜጠኞች ቡድን የካቲት 21 ቀን 2009 ማልዶ ተነሳ። ቡድኑን ወደ ስፍራው እንዲያመራና በመንግስትና ረድኤት ድርጅቶች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ምን ገፅታ እንዳለው እንዲዘግብ የጋበዘው የኦሮሚያ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ነው።

ቡድኑ የቪዲዮ  ካሜራና መቅረጸ ድምፁን  ታጥቆ በዕለቱ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት  አዲስ አበባን በመልቀቅ በፈጣኑ የአዳማ መንገድ ይምዘገዘግ ጀመረ። ፀሃይ ሳትበረታ ፈጣን መንገዱን በፍጥነት ለማለፍ የሚከንፈው ሾፌራችን የተሽከርካሪውን ፊት ወደ ደቡብ አቅጣጫ አዙሮ መሃል ለመሃል ተሰባብሮ እየተጠገነ ያለውን የሞጆ - ሀዋሳ መንገድ ተያያዘው፤ መዳረሻችን ሀዋሳ እስኪሆን ድረስ ፍጥነቱ እንደቀጠለ ነበር።

 ‘’ከባድ መንገድ ይጠብቀናል፤ ቶሎ ምግብ  በልተን እንውጣ’’ ተባብለን ከደቡቧ ምድር ሀዋሳ ለምሳ ቆይታ አደረግን። ከጥቂት ቆይታ በኋላ  ሀዋሳን ለቀን እንደወጣን፣ የመጣንበትን የፍጥነት መንገድ እያሰብን የሚያንገራግጨውን  የጠጠር መንገድ ጀመርን፤ መንገራገጩ አቦስቶ የሚባለው ትልቅ የፍተሻ ኬላ እስክንደርስ ድረስ ቀጥሏል።

ወደ አካባቢው ስሄድ የመጀመሪያዬ ነበርና ''እንዴ ይሄ መንገድ እኮ ለም፣ ብዙ ሃብት ያለበት፣ ትልቅ ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ አከባቢዎችን የሚያስተሳስር፣ ከዚያም አልፎ ወደ ጎረቤታችን ኬኒያ ጭምር የሚዘልቅ  ነው። እንዴት ፒስታ ሊሆን ቻለ?'' ስል ጠየቅኩኝ።

''አይ ፒስታ'' ''ገና መች አየህ'' አሉኝ፣ አብረውኝ እየተጓዙ ያሉ ጋዜጠኞች።  የመጀመሪያው የስራ ጉዞአችን ጉጂ በመሆኑ ወደ ቦረና ከሚወስደው  የተበላሸ መንገድ ለአፍታ ተለያየን። ለካ ወደ ነጌሌ  የሚዘልቀው መንገድ አስፋልት  ነበር።

ሆኖም ጉዞው ሲጨምር መንገዱም መለዋወጡን ቀጠለ።  የስራ ጓደኞቼ መንገዱ አርጅቶ በመቆፋፈሩ፣ በጣምም አስቸጋሪ መንገድ እንደሆነ ነገሩኝ። የሚያሳዝነው ግን መንገዱን የማደስ ስራ ከተጀመረ  ዓመታት ማለፋቸው ነው።  የምንጓዝበት ተሽከርካሪ እየከነፈ፣  እኛም የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን እያነሳን፣ በጉዟችን  ላይ የምናየውንም በካሜራችን እየወሰድን ፣ አለታ ወንዶ፣ አገረ ሰላምና ሌሎች የደቡብ ክልል ከተሞችን አቋርጠን መዳረሻችን ወደ ሆነችው ኦሮሚያ ክልል የጉጂ ዞን አዋሳኝ   ገባን። 

ጉጂ ዞን ከገባን  በኋላም ቢሆን  ስንደመምበት በነበረው አረንጓዴ ውበት ግራና ቀኝ ታጅበን ነበር። ጭራሽ ሌሎች አካባቢዎች ያላየናቸው ለየት ያሉ ዛፎችንም ማየት ጀመርን። ይህን ጊዜ ግራ ተጋባሁ። ድርቅ አለ የተባልነው ጉጂ ሆኖ እንዴት አረንጓዴ ውበት? ስል ራሴን ጠየቅኩ። ''ነው ወይስ ጉጂ አልደረስንም?'' አልኩ።

ጉዟችን ቀጥሎ ቦሬ ከተማ የሚል ታፔላ ተመለከትኩ።  እውነት ነው  ጉጂ ደርሰናል አልኩኝ - ለራሴ። ምክንያቱም ቦሬን በስሟ አውቃታለሁ። ለዘገባ እየሄድኩ ያለሁት ይህቺ ከተማ ወዳለችበት  ጉጂ ነው።

ጉጂ የገዳ ስርዓት የሚካሄድባት፣ አባ ገዳዎች በየስምንት ዓመቱ ስልጣን የሚረካከቡበት፣ የተከበረው ''የሚዔ ቦኮ አረንጓዴ ሜዳ''፣ ከዚያም አልፎ ጥቅጥቅ ያለው የአንፈራ ጫካ ያለባት ናት፤ እና በጉጂ ታሪካዊነት ተመስጬ  ፎቶ በማንሳትና ቪድዮ በመቅረጽ ተጠመድኩ።…

መንገዳችን ቀጥሏል፤ አዶላ ከተማን አለፍን፡፡ ወደ ነጌሌ የሚወስደውን መንገድ ተያይዘነዋል። እኔም ፎቶ ማንሳትና ቪዲዮ መቅረጼን ተያይዥዋለሁ። በካሜራዬ ወስጥ እያየው ለውጥ አስተዋልኩኝ፣ አረንጓዴው መሬት እየጠፋ፣ ቅጠላቸው የረገፈ ዛፎች፣ የተሰነጣጠቀና ውሃ የተጠማ መሬት ይታየኝ፣ ይከታተለኝም ጀመር። ይህን ጊዜ ውስጤ የተፈጠረው አረንጓዴ ቀለም እየጠፋብኝ መጣ።

የተጎሳቆሉ ግመሎች፣ አካላቸው የተጎዳ ፍየሎች፣ በተለይ ደግሞ እግራቸውን አንስተው  መራመድ የተሳናቸው የቦረና ከብቶችን የመንገዱ ግራና ቀኝ ያሳየን ጀመር። ድርቅ በከብቶቹ በርትቷል። ሃራ ቀሎና ወዳራ የሚባሉትን ከተሞች እያለፍን ወደ ነጌሌ እየተጠጋን ስንሄድ ጭራሽ መንገድ ዳር የሞቱ ከብቶች ይታዩን ጀመር። ሀዘኔ በረታ። ምስል መያዛችንን አላቆምንም። አሁን ችግሩ ምን ያህል የበረታ እንደሆነ ማሳየት ግድ አለን። ተሽከርካሪያችንን አቁመን ሁኔታውን ይበልጥ እንታዘብ ጀመር። 

ለአባ ገዳዎቹ ቦረና እና ጉጂ ምድር ኩራትና ክብራቸው የሆኑ፣ ገበያ እንኳን አውጥቶ በገንዘብ ለመለወጥ የሚሳሱላቸው፣ ስንት ዘመን ''ዳሌ ሎን ቦረና'' /የቦረና ዳለቻ ከብት/ እየተባለ የተዘፈነላቸው፣  የከብቶቹ ሥጋ አዲስ አበባን ያስደመሙ፣  ኢትዮጵያንም በቀንድ ከብት ከአፍሪካ አንደኛ ያስባሉ የቦረና ሰንጋና ከብቶች እንደ ቀልድ መንገድ ዳር ወድቀው ተመለከትኩ።

እዚያው ሳለን  እድሜው  15 ዓመት የሚሆን ታዳጊ  አጥንታቸው ወጣ ወጣ ያሉ ጎስቋላ ከብቶች እየነዳ መጣ። ተጠግቼው ስለሞቱት ከብቶች እንዲነግረኝ ጠየቅኩት፣ ''የነ ጣርሮ ናቸው'' አለኝ የእነ ጣርሮን ሰፈር  በእጁ ጣቶች እየጠቆመኝ። ''የኛም አንድ ሁለት ሞቶብናል ግን የነሱ ብዙ ከበቶች ናቸው ያለቁት'' አለኝ። ቀጠል አድርጎም ''ከብቶቹ አሁን ምንም የሚበሉት ነገር የላቸውም፣ ውሃም በጣም ረዥም መንገድ ተጉዘን ፈልገን ነው የምናጠጣቸው፣ ከባድ ነው'' አለኝ። በልጁ ገለፃ እያዘንን ጉዟችንን ቀጠልን።…ነገሌም ገባን። ለሁለት ቀናት እዚያው ከትመን የተለያዩ ወረዳዎች ላይ እየተንቀሳቀስን ቅኝት ስናደረግ ቆየን። በቆይታችን የተረዳነው አንዱ ነገር ድርቁ እንስሳትን በተለይ ደግሞ ከብቶችን በጣም የጎዳ መሆኑን ነው።

በመንግስት በኩል ለመኖ የሚሆን ሳር እየቀረበ ነው ቢባልም እኔ በቆየሁበት የአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አንድም ቦታ የተከመረ ወይም እየተከፋፈለ ያለ ሳር አላየሁም። የጠየቅኳቸው አርብቶ አደሮችም  በወር አንድ እስር ሳር ለአንድ ቤተሰብ እንደሚሰጥ፣ ነገር ግን ሳሩ ካላቸው የከብት ብዛት አኳያ እንኳን ለወር ለሳምንትም ስለማይበቃ ከብቶቻቸው እየሞቱባቸው መሆኑን ነው ያወጉኝ። የቀሩትንም ለማዳን ተስፋቸው እየተሟጠጠ መሆኑን ነው የገለጹልኝ።

መንግስት ለዚያ ሁሉ ከብት የሚበቃ ሳር ማቅረብ ስለማይችል አርብቶ አደሩ የሚከፋፈለውን  መኖ ለጥቂት ከብቶቹ ብቻ እየሰጠ ዘራቸው እንዳይጠፋ ቢያደርግ ጥሩ ነው የሚል ነገርም ከዞኑ የስራ ሃላፊዎች ሰምቻለው። እኔ ግን ለከብቶቻቸው ያላቸውን ልዩ ፍቅር እያሰብኩ ''እንዴት ነው አንዱ ከብት እንዲሞት ተፈርዶበት ሌላውን እያበላህ አቆይ  የሚባላው፣ ሌላ መፍትሄ ጠፍቶ ነው ወይ'' ብዬ እራሴን ጠየቅኩ። መፍትሄ ከጠፋ የቦረና ከብት ዘር እንዲቀጥል ያንን ማድረግ ግድ ይላቸው ይሆናል ብዬም አሰብኩ።

በዞኑ  በነበረኝ ቆይታ፣ ለድርቅ ተጎጂዎች መንግስት የሚያደርገውን የምግብና የመጠጥ ውሃ ድጋፍ ተመልክቻለሁ። ተረጂዎችም “ስለሚደርግላቸው ድጋፍ ትልቅ ምስጋና አለን” ይላሉ። ይህም ሆኖ “እጥረት መኖሩን መንግስት ይወቅልን” ሲሉ መልዕክታቸውን አክለው ነበር።

በቆይታዬ  ቀልቤን የሳቡና ''ለካ እንደዚህም ማድረግ ብዙ ችግር ያቃልላል'' ካሰኙኝ ነገሮች ህዝብ ለህዝብ የሚያደርገው የምግብና የከብት መኖ ድጋፍ ነው። የነጌሌ ነዋሪዎች በርካታ ተሽከርካሪዎችን አከታትለው የሰው ምግብና የከብት መኖ ጭነው የጉሚ ኤልደሎ ወረዳ ነዋሪዎችን በተወካዮቻቸው በኩል ''ችግራችሁ ችግራችን ነውና አይዞአችሁ፣ ከጎናችሁ ነን'' ሲሉ በስፍራው ተግኝቼ ስሰማ ደስ አለኝ። ወገን ለወገን ደራሽ ነው ማለትም ይሄ ነው።

“እንዴት ናት? ይች ነገር” ብዬ በመጠጋት እንዱን የወረዳ የስራ ሃላፊ ሳነጋግር ''ይሄ ብቻ አይደለም'' አለኝ፣ “ተመሳሳይ ድጋፍ ድርቅ ካልነካቸው አከባቢዎች ለሌሎች አምስት ወረዳዎች ሲደረግ ነበር” ብለውኛል። የመንግስት ሰራተኞችም የቻሉ ሙሉ የወር ደመወዛቸውን ያልቻሉ ደግሞ በመቶኛ እያሰሉ ነው አሉኝ። ይህን በጎ ተግባር  በሁለቱም ዞን  ተመልክቻለሁ። ታዲያ ይሄ ሁሉም አካባቢ ቢለመድ፣ በራስ አቅም ማለት ይሄ አይደለምን?

ሌላው ቀልቤን የሳበው ነገርና በሁለቱም ዞን ላይ የተመለከትኩት ሰናይ ነገር፣ በዚያ የበረሃ መሬት ፣ በክረምቱ ወቅት የታቆረውን ውሃ እና የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ ያመረቱ ነበሩ። እነዚህ በዚህ ክፉ ጊዜ የቤተሰባቸውን ህይወት መደጎም እንደሌሎቹ አልከበዳቸውም። በእርግጥ ቁጥራቸው ትንሽ ነው። ቢሆንም ይቻላል ብሎ ለማውራትና ለማሰብ ምሳሌዎች ናቸው ነው የምለው።

በዞኖቹ ገናሌና ደዋ የመሳሰሉ ትላልቅ ወንዞችን ጨምሮ ሁለት፣ ሶስት ሜትር ቢቆፈር የሚወጣ የከርሰ ምድር ውሃ አለ፣ ክረምት ሲፈስ የሚቆየውን የዝናብ ውሃም አቁሮ ማቆየት እኮ በአገሪቷ እየተለመደ መጥቷል። ስለዚህ የሰውም፣ የከብትም ምግብ ማምረት ይቻላል ማለት ነው። ''ከተሰራበት'' ።…

የሁለት ቀን ቆይታችንን ጨርሰን ወደ ቦረና ዞን ያቀናነው ከቀትር በኋላ ነበር። ወደ አዶላ ተመልሰን ነው በሻኪሶ አድርገን ወደ ቡሌሆራ፣ ከዚያም ያቤሎ ቀጥለን ደግሞ ሞያሌ ለመድረስ ያሰብነው። ከአዶላ እንደወጣን በጣም ከባድ ኮሮኮንች ወይም በተለምዶ ፒስታ መንገድ አጋጠመን። የሚገርማችሁ  አፈር ምድሩ ወርቅ የሆነበት፣ ሚድሮክን የሚያክል ግዙፍ ኩባንያ ወርቅ የሚዝቅበት፣ ሻኪሶን ከአዶላና ቡሌሆራ ጋር የሚያገናኘው ይህ መንገድ እንዲህ አይነት ደረጃ ያለው መሆኑ ነው። ለዚች መንገድ አሁን ሚድሮክ እራሱ አይበቃም?

የሆነው ሆነና ከአንድ ቀን ተኩል ጉዞ በኋላ ቀጣይ መዳረሻችን ወደ ሆነው ቦረና ዞን አቀናን። ለጉብኝት በተመረጡልን ወረዳዎችም ደርሰን ተዘዋውረን ተመለከትን። እዚያም ድርቁ ትንሽ ከፋ ይላል። ሁሉንም ወረዳዎች ነው ያዳረሰው፣ የከብቶች ሞትም ከጉጂው የከፋ ይመስላል። የዞኑ ሃላፊ ሲናገሩ እንደሰማሁት ብዙ ከብቶች ሞተው፣ የቀሩት ደግሞ ወደ ሌላ አካባቢ ተሰደው አንድም ከብት የሌለበት ወረዳ ጭምር አለ።…

ሚዮ የሚባል ወረዳ ላይ የገብያ ቀን ስለደረስን የከብቶች ገበያ የመጎብኘት እድሉ ነበረኝ። አርብቶ አደሩ ድርቁ የተጫጫናቸውን፣ አንገታቸውን እንኳን ቀና አድርገው መቆም ያቃታቸው፣ ካላቸው ከብቶች ግን የተሻሉ የሚላቸውን ገበያ አምጥቶ ነበር።

ቃለመጠየቅ ያደረግኩላቸው አርብቶ አደሮች፣ ''ገበያ የለም''  ''ገዥ ነጋዴ የለም'' ''ይዘን ወደ ቤታችን እንዳንመለስ ይሞቱብናል፣ የሚገዛን ደግሞ የለም'' “መንግስት አንድ ሊለን ይገባል” የሚል የእሮሮ ድምጽ ያሰማሉ።

መንግስት ለሰዎች እያደረገ ያለውን የምግብ፣ የመጠጥ ውሃና የተጨማሪ ምግብ እርዳታም ተመልክቻለሁ። እዚህ ግን ለከብቶች የሚቀርበው መኖ ይቀርባል ሲባል ሰማው እንጂ አላየሁም።

በዞኑ ተማሪዎች በድርቁ ምክንያት ትምህርታቸውን እያቋረጡ ነው ሲባልም ሰምቼ ስለነበረ፣ በሞያሌ ወረዳ  ከነዋሪዎቹ አንዳንዶቹን  ጠጋ ብዬ ለማነጋገር ሞክሬ ነበር። “አዎ እኔ ራሴ አቋርጬ ለዕለት ጉርስ የቀን ስራ እየሰራሁ ነው። አብረን ስንማር ከነበሩ ተማሪዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አሁን አይማሩም” የሚል አጋጥሞኛል። እንዲሁም “ሶስት ልጆቼ ትምህርት አቋርጠው ቤት ቁጭ ብለዋል” የሚሉ እናትም አጋጥመውኝ ነበር። አስደንጋጭ ነው።

ይህን ከሰማሁ በኋላ ትምህርት ሚኒስቴር “ተማሪዎች በድርቁ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ለዞኑ ብቻ 25 ሚሊዮን ብር መድቦ የምገባ ፕሮግራም አስጀምሯል” የሚል  መልካም ዜና ሰማሁ። ችግሩም ይፈታል፣ ከትምህርት የቀሩትም ወደ “ትምህርት ቤት ይመጣሉ” ብዬ አስባለሁ።

የተያዘልን ጊዜ እያለቀ ስለሆነ ፊታችንን ወደ አዲስ አበባ አዙረን መንገድ ላይ ያሉትን አንዳንድ ወረዳዎች እየጎበኝን ለመመለስ በማለዳ ከሞያሌ ስንወጣ ያየሁት የተሽከርካሪ አደጋ ግን በጣም አስደንጋጭ ነበር። ይህ ገጠመኝ ስራችንን ከጋዜጠኝነት ወደ ነብስ አድን የህክምና ባለሙያነት የቀየረው ነበር። ከፊታችን ከተፈቀደለት ፍጥነት በላይ  ሲከንፍ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ ቅጥቅጥ ተሽከርካሪ አንድ ሞተረኛ አድናለሁ ብሎ ያሳፈረውን  ህዝብ እንደያዘ ተገለበጠ።

በቅርብ የነበርነው እኛ ስለሆንን ደርሰን ሰዎችን ለማትረፍ እያወጣን፣ በያዝነው ተሽከርካሪ ወደ ሞያሌ ሆስፒታል ስናመላልስ ቆየን። በርካታ ሰዎች ክፉኛ ቆስለዋል፤ ደግነቱ በቦታው የሞተ ሰው አልነበረም።

የተሽከረካሪው ፍጥነት ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ “በርካታ እቃ አናቱ ላይ የጫነ መሆኑ መሰለኝ በቀላሉ እንዲወድቅ ያደረገው” ልል አሰብኩና የትራፊክ ባለሙያ ስላልሆንኩ ግምቴን ተውኩት። አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ድርቅን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ፈጥረን ተፈጥሮን እየታገልነው ነው። ታዲያ ልንቆጣጠረው በምንችለው  በሰው ሰራሹ ተሽከርካሪ አደጋ ለምን እንሙት?

Published in መጣጥፍ

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2009 ለሴቶች የተሰጠው ትኩረት ይበልጥ እንዲጎለብት የድርሻቸውን እንደሚወጡ በቅድሚያ ለሴቶች የሩጫ ውድድር የተሳተፉ ሴቶች ተናገሩ።

የቅድሚያ ለሴቶች አምስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር "ስለምትችል" በሚል መሪ ሀሳብ ትናንት ለ14ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በዚህ ውድድር ከተሳተፉ ሴቶች መካከል ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየት የሰጡት እንዳሉት አሁን ለሴቶች የተሰጠው ትኩረት ይበልጥ እንዲጠናከር ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፤ እኛም የዚሁ አካል እንሆናለን ብለዋል።

ውድድሩን ከቀዳሚዎቹ መካከል ሆነው የጨረሱት የ49 ዓመት አዛውንቷ ወይዘሮ አስካለ ታደሰ  "ሩጫውን በደስታ ነው የጨረስኩት ድካም አልተሰማኝም፤ ለመዝናናትና ጤንነቴን ለመጠበቅ እጠቀምበታለሁ" ብለዋል።

"ሴቶች ከተመሪነት ወደ መሪነት፣ ከማጀት ወደ ቢሮ የወጡበት ጊዜ በመሆኑ ችሎታቸውን በአግባቡ መጠቀም አለባቸው" ሲሉም መክረዋል ።

በበጎ ፈቃደኝነት በመላ አገሪቱ በብስክሌት በመዞር ላለፉት 15 ዓመታት ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ላለባቸው ወገኖች እንክብካቤና ድጋፍ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት ወይዘሮ ሂሩት ገድሉ ሴቶች ባለብዙ ችሎታ ናቸው፤ ይህን ችሎታቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በተለይም አሁን አሁን ለሴቶች እየተሰጠ ያለው ትኩረት በደንብ እንዲያብብ መስራት ይገባቸዋል ነው ያሉት ወይዘሮ ሂሩት።

ከስዊድን ኤምባሲ የመጣችው አና ሄክማን "ከዚህ በፊት ሴቶች ብቻ በሚወዳደሩበት ውድድር ተካፍዬ አላውቅም፤ ደስ የሚል ሩጫ ነው ያየሁት በዚህ ደስተኛ ነኝ" ብላለች።

ወደፊትም ለሴቶች መብትና እኩልነት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁማለች።

ሴቶችን በማበረታታት ያላቸውን እምቅ ኃብት መጠቀም ይኖርብናል ያለችው ደግሞ አርቲስት ቻቺ ታደሰ ነች።

ኢትዮጵያ የበርካታ ብቃት ያላቸው ሴቶች ባለቤት ስለሆነች እነዚህ ሴቶች ከጥሩ ቦታ እንዲደርሱ መስራት እንደሚገባና የበኩሏ እንደምትወጣ ነው የገለጸችው።

በትናንትናው ዕለት በተካሄደው ቅድሚያ ለሴቶች የአምስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር አትሌት ደጊቱ አዝመራው አሸናፊ የሆነች ሲሆን በውድድሩ 11 ሺህ ሴቶች ተሳትፈዋል።

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2009 የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የቤት ውሰጥ ስራዎችን በቴክኖሎጂ መደገፍ እንደሚገባ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት "ተግባራዊ ለውጥ ለሴቶች እኩልነት መረጋገጥ" በሚል የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚጎትቱ ልምዶች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዛሬ መክሯል።

ኦክስፋም የተሰኘው አለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት "የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና የእንክብካቤ ስራዎች" በሚል ያደረገው ጥናት ቀርቧል።

በድርጅቱ የስርዓተ-ጾታ ባለሙያ ወይዘሮ ህሊና አለማርዬ እንዳለችው ሴቶች በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተግባራት ይሳተፉ ሲባል በቤት ውስጥ የሚያከናውኗቸው ተጨማሪ ስራዎች የሚያሳድሩትን ጫና ለማወቅ ጥናቱን ማድረግ አስፈልጓል።

እንደ ባለሙያዋ ገለጻ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች 250 ቤቶችን በናሙና በመውሰድ ጥናቱ ተካሂዷል።

በዚህም ሴቶች የበለጠ ስራ እንደሚሰሩ፣ ወንዶች የሚሰሩት ስራ በክፍያ መሆኑን፣ ሴት ህጻናት ልጆች ከወንድ ህጻናት የበለጠ እንደሚሰሩ ጥናቱ አሳይቷል።

የሚያከናውናቸው ተግባራትም በባህላዊ መንገድ በመሆኑ ከጊዜ፣ ጤናና ሌሎች እንቅስቃሴዎች አንጻር ተጠቃሚነታቸውን የሚጎትቱ ናቸው ትላለች።

በጊዜ ሲታይም በኦሮሚያ ክልል ሴቶች ከመደበኛ ስራ ውጪ በቀን ከ6 እስከ 7 ሰአት ተጨማሪ ስራ ይሰራሉ።

መሰል ተግባራት በከተማ ውስጥ መኖራቸውን ለማረጋገጥ በተደረገው ጥናት የተማሩና በስልጣን ላይ ያሉ ሴቶች ከ3 እስከ 4 ሰአት እንደሚሰሩ ታውቋል።

ባለሙያዋ የእንክብካቤ ስራዎችን ለማቅለል ዘመናዊ አሰራሮችን መንግስት ለሴቶች ማቅረብ አለበት የሚል ሃሳብ ሰጥታለች።

ሴቶች በቤት ውስጥ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት እየተደረገ ያለው ጥረት እውን እንዲሆን በጥናቱ የተገኙ ውጤቶችን ለመንግስትና ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ በማቅረብ ግፊት ይደረጋል ተብሏል።

በሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ግንዛቤና ንቅናቄ ቡድን መሪ ወይዘሮ ማህደር ቢተው ባለፉት አመታት የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ ቢመጣም አሁንም ክፍተቶች ይስተዋላሉ ብለዋል።

በመሆኑም የተገኙ ውጤቶችንና ክፍተቶችን በመለየት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ሙሉ ለሙሉ ለማረጋገጥ የሚያስችል ፓኬጅ በሚኒስቴሩ እየተዘጋጀ መሆኑንም አስታውቀዋል።

እንደ ቡድን መሪዋ ከሆነ ሴቶችን ከተጠቃሚነት ወደኋላ የሚጎትቱ ጫናዎችን ማቃለልም የስትራቴጂው አንዱ ትኩረት ነው።

የቤት ውስጥ ስራን ሊያቃልሉ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለሴቶች ተደራሽ ማድረግ አንዱ ሲሆን የወንዶችን ተሳትፎ የሚያሳድግ ግንዛቤ መፍጠር ሌላኛው በስትራቴጂው የተቀመጠ መሆኑን አንስተዋል። 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2009 የአፍሪካ አገራት የተፈጥሮ ኃብት አስተዳደር አቅማቸውን ሊያጎለብቱ እንደሚገባ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንትና የጣና ፎረም ሊቀ-መንበር ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ገለጹ።

የጣና ከፍተኛ የአፍሪካ የደህንነት የምክክር መድረክ በሚቀጥለው ወር በሚያካሄደው ስድስተኛው ፎረም ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በዚህ ወቅት እንዳሉት አፍሪካውያን የተፈጥሮ ኃብትን በማስተዳደር ረገድ የአቅም ውስንነት አለባቸው።

የአቅም ውስንነቱ የሚመነጨው በተፈጥሮ ኃብት ማስተዳደር በቂ የሆነ እውቀት፣ ክህሎትና በዘርፉ የሚሰሩ የተቋማት አቅም በሚፈለገው መልኩ ባለመገንባቱ ነው ብለዋል።

በዚህም ምክንያት የአፍሪካ አገራት የተፈጥሮ ኃብታቸውን በሚጠበቀው መልኩ እንዳይጠቀሙ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።

በተለይም በተፈጥሮ ኃብት ፍለጋ በአህጉሪቷ የሚሰማሩ ድርጅቶች ጋር የመደራደር አቅም ችግር አፍሪካ ካላት ኃብት በሚፈለገው መልኩ እንዳትጠቀም እያደረጋት መሆኑን ነው ያስረዱት ሚስተር ኦባሳንጆ።

አፍሪካውያን አገራትም ይህንን በመገንዘብ የተፈጥሮ ኃብት አስተዳደር አቅማቸውን የሚያጎለብቱ ስራዎችን መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ለዚህም በተፈጥሮ ኃብት ዘርፍ ሙያተኞችን ማሰልጠንና ማብቃት፣ በዘርፉ ያሉትን ተቋማት አቅም መገንባት በዋነኛነት አገራቱ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ኃብት ማስተዳደርና መጠቀም የሚያስችሉ ህጎችን ማውጣትና ያሉትንም ህግና ደንቦች በአግባቡ ተፈጻሚ ማድረግ ሌላኛው ጉዳይ መሆኑን ሚስተር አባሳንጆ አስገንዝበዋል።

እነዚህን የመፍትሄ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ አፍሪካ ከተፈጥሮ ኃብቷ ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል አክለዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መስራት እንዳለበትም እንዲሁ።

የጣና ከፍተኛ የአፍሪካ የደህንነት የምክክር መድረክ በሚያካሂዳቸው ፎረሞችና ሌሎች እንቅስቃሴዎች የአፍሪካውያን ችግር በአፍሪካውያን መፍትሔ እንዲያገኝ የሐሳብ ድጋፍ በማድረግ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

ሚያዝያ 14 እና 15 ቀን 2009 ዓ.ም "የተፈጥሮ ኃብት አስተዳደር በአፍሪካ" በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የጣና ፎረም የአገር መሪዎች፣ አህጉራዊና ቀጠናዊ መሪዎች፣ የአፍሪካ የሲቪክ ማህበራት፣ የአፍሪካ የግሉ ዘርፍና ሌሎች አጋር አካላት ይሳተፋሉ።

የጣና ፎረም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናቶች ተቋምና በአፍሪካውያን መሪዎች አነሳሽነት ከስድስት ዓመት በፊት የተቋቋመ ነው፡፡

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን