አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 12 March 2017

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2009 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ በደረሰው አደጋ የሰው ሕይወትና ንብረት በመጥፋቱ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገለጸ።

በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ  በተለምዶ ቆሼ በተባለው አካባቢ አደጋው የደረሰው ትናንት ከምሽቱ 2:00 ገደማ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ፤ አስተዳደሩ በተከሰተው አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች የተሰማውን ልባዊ ሐዘን በራሱና በከተማዋ ነዋሪዎች ስም ገልጿል።

Published in ማህበራዊ

ጅማ መጋቢት 3/2009 የጥልቅ ተሀድሶ ዓላማን በስኬት ለማጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በጅማ ከተማ የሚገኙ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) አባላት ገለጹ፡፡

ከ1ሺ200 በላይ የድርጅቱ አባላት በልማትና መልካም አስተዳደር ዙሪያ ዛሬ በጅማ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊ አባላት መካከል  አቶ ጥላሁን አየለ ደኢህዴን/ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት የዘረጋው የጥልቅ ተሀድሶ እንቅስቃሴ በየደረጃው ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለስኬታማነቱም  የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸው "ልማት በአንድ አገር የሚረጋገጠው በጋራ በመስራት በመሆኑ  የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት መትጋት ይጠበቅብናል" ብለዋል፡፡

ወይዘሮ አስናቀች አኔቦ በበኩላቸው በጅማ ከተማ በርካታ የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከሌሎችም ጋር ተከባብረው  በሰላም ፣ በፍቅር እና በእኩልነት አብረው እየኖሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በጅማ ከሚገኙ የደኢህዴንና የእህት ድርጅት  አባላት ጋር በመሆን ለአካባቢያቸው  ሰላምና ልማት በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

"ለአብነትም ባለፈው ዓመት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች  ግርግር  በነበረበት ውቅት ጅማ ከተማና አካባቢው ሰላም ሊሆን መቻሉ የዚሁ ማሳያ ነው "ብለዋል፡፡

በቀጣይ የአካባቢያቸውን ሰላምና ልማት በጋራ በማጠናከር የጋራ ጠላት  የሆነውን ድህነት  ለማሸነፍ የጥልቅ ተሀድሶው አስፈላጊ በመሆኑ  ለስኬታማነቱ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

" ጥልቅ ተሀድሶ ክራይ ሰብሰቢነትን በማጥፋት ህዝቦች ተቻችለው እንዲኖሩ የሚያደርግ በመሆኑ በስኬት ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት  የበኩሌን እወጣለሁ" ያሉት ደግሞ  አቶ ተስፋዬ በቀለ ናቸው፡፡ 

የደኢህዴን  ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ተመስጌን ጥላሁን ደኢህዴን ከሌሎች አህት ደርጅቶች ጋር የተደራጀው ድህነትንና ኋላቀርነትን በጋራ ለመናድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

" በጅማ ከተማ የምትገኙ የደኢህዴን አባላት ከኦህዴድ እና ከሌሎች እህት ድርጅቶች ጋር  እያደረጋችሁት ያለው የአካባቢን ሰላም የመጠበቅና የልማት  ተሳትፏችሁን አጠናክራችሁ መቀጠል አለባችሁ" ብለዋል፡፡

ጅማን ከአጎራባች የደቡብ ህዝቦች  ክልል ጋር በመሰረተ ልማት ለማገናኘት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ  ከክልል ውጭ የደኢህዴን ጽህፈት ቤት ሃላፊ  አቶ አግዞ ገብረመድህን ናቸው፡፡

የመሰረተ ልማት ስራው በቀጣዩ ዓመት እንደሚጠናቀቅና ይህም  የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንደሚያጠናክርም አመልክተዋል፡፡

 

 

Published in ፖለቲካ

አዳማ መጋቢት 3/2009 ሞዴል አርሶ እና ከፊል አርብቶ አደሮች በግብርናው ዘርፍ ያገኙትን ልምድና እውቀት በተመሳሳይ ዘርፍ ለተሰማሩ እንዲያካፍሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠየቁ።

ስምንተኛው አገር አቀፍ የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች በዓል በአዳማ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ ከ550 በላይ አርሶና ከፊል አርብቶአደሮች በግብርና ዘርፍ ባስመዘገቡት የላቀ አፈጻጸም ከቦንድ ጀምሮ እስከ ዘመናዊ ትራክተር ድረስ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ለሽልማት የበቁት አርሶና ከፊል አርብቶአደሮች የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ጉልበት ተጠቅመው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ናቸው። 

በተጨማሪም የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን የሙያ አቅጣጫ በመቀበል ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣት ግንባር ቀደም መሆናቸውን በተግባር ማረጋገጣቸውን ነው ያመለከቱት።

በቀጣይም የእነርሱን አርዓያ የሚከተሉ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ቁጥር እንዲጨምር በሚደረገው ጥረት የመሪነት ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው ነው የገለጹት።

“በአገሪቷ ካሉት 14 ሚሊዮን አርሶ አደሮች መካከል 22 በመቶ የሚሆኑትን ለሞዴልነት ማብቃት ችለናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም የሚያበረታታ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

“ሞዴል አርሶ አደር አንድ አልያም ሁለት ከተቻለም ሶስት አርሶ አደሮችን በማብቃትና በመከታተል” ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪያቸውን ያቀረቡት።

ይህ ከተደረገ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመንና የዘርፉን እድገት በዘላቂነት ማስቀጠል እንደሚቻል አረጋግጠዋል።

ተሸላሚ አርሶ አደሮቹ የተሰጡትን አደራ ተቀብለው እንደሚተገብሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እምነታቸውን ገልጸዋል። 

በሌላ በኩል የግብርናው ዘርፍ ባለፉት 15 ዓመታት በአማካይ የዘጠኝ በመቶ እድገት በማስመዝገብ ለአገሪቷ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት መሰረት መጣሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

መንግሥት በአነስተኛ ማሳ ላይ የተሰማሩ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱን እንደ ዋነኛ የእድገቱ መነሻ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ከሚመረተው ምርት 90 በመቶ የሚሆነው ከአነስተኛ ማሳ የሚገኝ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በአግባቡ በመተግበርና ለእንስሳት መኖ አቅርቦት በማመቻቸት በእንስሳት እንክብካቤ ዘርፍም አመርቂ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

አገሪቷ የገጠማትን ድርቅ ለመመከት የሚያስችሉ የቅድመ ድርቅ መከላከያ ስልቶች አርሶ አደሩ ቀድሞ ገቢራዊ ማድረጉን አስታውሰው፤ ይህም ድርቁን በራስ አቅም ለመመከት ካስቻሉ ዘዴዎች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ገቢራዊ የተደረጉት የቴክኖሎጂ ግብዓቶችም ለእስካሁኑ ውጤት ያለው አበርክቶ ቀላል አለመሆኑን ነው የገለጹት።

ይህም አገሪቷ ለምትፈልገው የመጀመሪያ ደረጃ የካፒታል ክምችት እድል የፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ ለሚፈለገው መዋቅራዊ ሽግግር አበርክቶ ቀላል አለመሆኑን ገልጸዋል።

ግብርናው በተጠናከረበት መልኩ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እንዲጠናከር በማድረግ ከፍተኛ የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ ያለው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አስረድተዋል።

“በዚህም ደግሞ እናንተ አርሶና ከፊል አርሶ አደሮች ያበረከታችሁት አስተዋጽዖ ከፍተኛ በመሆኑ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ” ብለዋል።

ከእነርሱም ጎን በመሆን ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት የድርሻቸውን የተወጡ የግብርና ባለሙያዎች ምስጋና ሊቸራቸው እንደሚገባም ተናግረዋል።

የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር ዶክተር እያሱ አብርሃ በበኩላቸው፤ ግብርናውን ለማዘመን የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ነው ያረጋገጡት።

ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የቴክኖሎጂ ግብዓት አቅርቦት ሥርዓት እንዲኖር ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራና ገበያ መር የኤክስቴንሽን ሥርዓትም ገቢራዊ እንደሚሆን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ገበያን መሰረት ያደረገ የምርት ሂደት ውስጥ እንዲሆን ለማስቻልም የግብርና ሥራ ማኅበራትን የማጠናከር ሥራም እንዲሁ ትኩረት እንደሚደረግበት ጠቁመዋል።

ይህንንም በአግባቡ ለማስኬድ የግብርና ባለሙያዎችና የምርምር ተቋማት የማደረጃት ሥራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስረዱት።

ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ የግብርና ልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ ለማድረግ የውሃ እቀባና የአፈር ጥበቃ ሥራዎች በስፋት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2009 በኢንዱስትሪ የሚመረቱ ምርቶችን በፍጥነት ወደ ውጪ ለመላክ እንዲቻል በኢንዱስትሪ ፓርኮች አቅራቢያ የደረቅ ወደቦች ግንባታ ሥራን የማስፋፋት ተግባር እንደሚያከናውን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ።

ደርጅቱ ትናንት ለመገናኛ ብዙሃንና ለፌዴራል ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የባቦጋያ ማሪታይም ማሰልጠኛ፣ የሞጆና የገላን ደረቅ ወደቦች ተርሚናሎችን ያሉበትን ሁኔታ አስጎብኝቷል።

የድርጅቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ገብረሕይወት እንደተናገሩት፤ አሁን ያሉትን ሰባት የደረቅ ወደቦች ከማስፋፋት ጎን ለጎን በኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢም ደረቅ ወደቦች ይገነባሉ።

እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻ፤ ድርጅቱ በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አቅራቢያ የደረቅ ወደብ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው። በአማራ ክልል በወረታ ከተማ ሌላ የደረቅ ወደብ ለመገንባት የጥናት ሥራ እየተካሄደ ይገኛል።

የደረቅ ወደቦች ግንባታ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚወጡ ምርቶችን በፍጥነት ወደ ውጪ ለመላክ እንደሚያስችሉ ምክትል ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።    

የድርጅቱ ተጠባባቂ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ተፈራ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ከውጪ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ ኮንቴነሮች መካከል 80 በመቶውን የሚይዘው የሞጆ የደረቅ ወደብ ተርሚናል ነው። ለዚህ ተርሚናል የበለጠ አቅም ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ የማስፋፊያ ስራ እየተከናወነለት ይገኛል።

የደረቅ ወደቡ ማስፋፊያ የሚከናወነው አሁን ካለው የ60 ሄክታር መሬት ስፋት ወደ 140 ሄክታር ለማድረስ መሆኑን ነው አቶ መስፍን ያስረዱት።

ከጂቡቲ የሚጫኑ ኮንቴነሮችን በባቡር በማጓጓዝ ለማራገፍ የሚያስችል በስድስት ሄክታር ላይ ያረፈ የባቡር ሐዲድ ግንባታም እየተፋጠነ መሆኑን ነው የገለጹት።

ለሚራገፉ ዕቃዎች ማቆያ የሚሆኑ ሁለት ትላልቅ መጋዘኖች  እየተሰሩ ሲሆን፤ በቀጣይም ሁለት እንደሚገነቡ ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ጅግጅጋ መጋቢት 3/2009 በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከ738 ሺህ በላይ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ማጠናቀቁን የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ መሀመድ ቢሌ እንደተናገሩት፣ የፌዴራል መንግስት የወጣቱን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ከፈቀደው ተዘዋዋሪ ብድር ውስጥ ለክልሉ የተመደበው 603 ሚሊዮን ብር ነው።

በአሁኑ ወቅት ገንዘቡ ለሥራ ዝግጁ መደረጉን ጠቁመው፣ የክልሉ መንግስት 40 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ገንዘብ መመደቡን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ወጣቶችን ወደሥራ ለማስገባት ከክልል እስከ ቀበሌ ከሚገኙ የመንግስት አካላትና ከወጣት አደረጃጀቶች ጋር በጋራ እየተሰራ  መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ መሀመድ እንዳሉት፣ በክልሉ በገጠርና በከተሞች የሚኖሩ ሥራ አጥ ወጣቶችን የመመልመል ሥራ የተከናወነ ሲሆን ወጣቶቹ ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ሊሰማሩባቸው የሚችሉ የተለያዩ የሥራ ዘርፎችም ተለይተዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች ከተዘዋዋሪ ፈንዱ ለቁሳቁስና ለሥራ ማስኬጃ በብድር እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደአቶ መሀመድ ገለጻ፣ በገጠር አካባቢ ወጣቶች በቁም እንስሳት ንግድ፣ በእንስሳት ማድለብና በእርሻ ልማት ሥራ ይሰማራሉ፡፡ በከተሞችም የወተት ማቀነባበሪያና የዘይት ማምረቻ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን እንዲያቋቋሙ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።

በተጨማሪም የትምህር ቤት ጠረንጴዛና ወንበር እንዲያመርቱ እንዲሁም በውበት ሳሎን፣ በዶሮ እርባታና በአገልግሎት ዘርፍ በመረጡት መንገድ ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ የሙያና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል።

የክልሉ ቴክኒክ ሙያ፣ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ናስር ሀሰን በበኩላቸው፣ በክልሉ በተለያዩ የሥራ መስኮች እንዲሳተፉ ከተለዩት ወጣቶች መካከል እስካሁን ለሁለት ሺህ 3 መቶ የሚሆኑት ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

አቶ ናስር እንዳሉት፣ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 34 ዓመት ክልል ውስጥ ያሉና በ93 የክልሉ ወረዳዎችና ስድስት የከተማ አስተዳደሮች የሚኖሩ ሥራ አጥ ወጣቶች የዕድሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

የሥራ ዕድል ከሚፈጠርላቸው ወጣቶች መካከል ሁለት ሺህ 100 የዲግሪ ምሩቃን ናቸው።

የክልሉ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት መህቡብ መሀሙድ፣ ማህበሩ ከክልሉ ስፖርትና ወጣቶች እንዲሁም ከክልሉ ቴክኒክ ሙያና ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የወጣቶች የሥራአጥነት ችግር እንዲፈታ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የፌዴራልና የክልሉ መንግስት የወጣቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጀመሩት ጥረት በፍጥነት ወደ ተግባር እንዲቀየር ጠይቋል።

በጅግጅጋ ከተማ ቀበሌ 18 ነዋሪ ወጣት አሊ ሳላህ ባለፈው ዓመት ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ ጥናት በመጀመሪያ ዲግሪ መመረቁን ገልጾ፣ በአሁኑ ወቅት ከሌሎች ሦስት ጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ ወደሥራ ለመሰማራት ለክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ፕሮፖዛል ማቅረባቸውን ተናግሯል።

በቅርቡም ከጅግጅጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በውጤታማ የሥራ ዕቅድ አዘገጃጀትና በሒሳብ ሰነድ አያያዝ ላይ ለሁለት ሳምንት ስልጠና እንደተሰጣቸው ጠቁሟል፡፡

በጎዴ ከተማ ቀበሌ 01 የሚኖረው ወጣት አብዲቃድር አህመድ በበኩሉ፣ ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር በጋራ በማህበር መደራጀቱን ገልጿል።

በአካባቢው ተፈላጊ የሆነውን የሰሊጥ ዘይት ለማምረት በመንግስት በኩል ማምረቻ መሳሪያ በብድር ተገዝቶ እንዲቀርብላቸው ጠይቀው መልሱን እየተጠባበቁ መሆናቸውን አመልክቷል።

በመንግስት ለማምረቻ መሳሪያ፣ ለኪራይና ለሥራ ማስኬጂያ የሚለቀቅላቸውን ገንዘብ በአግባቡ ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግሯል።

ወደሥራ የሚገቡት ወጣቶች ሲመለመሉ በቀበሌው ተሰሚነት ያላቸው የጎሳ መሪዎችና ሌሎች የአስተዳደር አካላት ቤት ለቤት በመሄድ መሳተፋቸውንም አስረድቷል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2009 ’’የአማርኛ ሰዋሰው እና ስነ- ጽሑፍ’’ በሚል ርዕስ የታተመው አጋዥ መጽሐፍ ትናንት ተመረቀ።

መጽሀፉን ያዘጋጀው ጋዜጠኛ የኑስ መሐመድ ነው፡፡

መጽሀፉ በየአካባቢው የሚታየውን የአማርኛ የጽሕፈት ቋንቋ አጠቃቀም ችግር በተወሰነ ደረጃ ለማሰተካከል አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።

በከተሞች አካባቢ በግል ትምህርት ቤቶች የሚስተዋለውን የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም ችግርና ተማሪዎች በውጭ ቋንቋ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ማድረግ የሚያስከትለውን አገራዊ ተግዳሮት ለማመላከት መሞከሩ ነው በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገለጸው።

የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ደራሲና ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላት በመጽሐፉ የምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ’’ማናቸውም አንጋፋ የተባልን ደራሲያን ያላሰብነውን በማሰቡ የሚደነቅ ነው፤ አገራችን በኪነ-ጥበቡ ያለችበት ደረጃ ይታወቃል። በተለይ በቋንቋ አጠቃቀማችን ያለውን ግድፈት ለማቃናት ፍንጭ የያዘ መጽሐፍ ነው’’ ብለዋል።

ደራሲና ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ እንደሚሉት፤ በሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቋንቋ አጠቃቀም ላይ ችግሮች ተደቅነዋል። ትምህርት ቤቶችና ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በባዕድ ቋንቋ ብቻ እንዲገናኙ የመደረጉ ጉዳይ ፈታኝ እየሆነ መጥቷል።

’’በራሱ ቋንቋ ያልተማረ ህፃን የነገ አገር ተረካቢ ዜጋ ሊሆን አይችልም’’ ያሉት ደራሲና ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ፤ “ቀድመኸናል” ሲሉ ለመጽሀፉ አዘጋጅ አድናቆታቸውን ችረውታል።

ደራሲና ተርጓሚ አፈወርቅ በቀለ በበኩላቸው፤ የጽሕፈት ቋንቋ ካላቸው ጥቂት አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኑዋን አስታውሰው፤ የጽሕፈት ቋንቋ ደግሞ የአጻጻፍ ሥርዓተ-ህግ ወይንም ሰዋሰው ተከትሎ መጻፍ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

መጽሐፉ የግዕዝ ቋንቋን መነሻ በማድረግ አሁን በአለው የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ግድፈቶችን በመለየት ትክክለኛውን መንገድ ለማሳየት እንደሚሞክር ነው የተገለጸው።

ደራሲ የኑስ በበኩሉ ’’ትምህርት ቤቶች ውስጥ አማርኛና ጠጠር መወርወር ያስቀጣል እስከማለት ተደርሷል። አማርኛ ሲያወራ የተገኘ እኔ ደካማ ነኝ እያለ በተማሪዎች ፊት የስነ ልቦና ጫና እስኪደርስበት ይቀጣል’’ ብሏል።

አንዳንድ ሰዎች ስለማንነት ያላቸው አመለካከት የተዛባ መሆኑን ጠቁሞ፤ በሌላ በኩል ደግሞ “ትምህርት ቤቶች አጋዠ የአማርኛ መጽሐፍ እጥረት አለ” የሚሉ አካላትንም ምንም ሳይሰሩ መኮነን እንደሌለባቸው ነው የገለፀው።

መጽሐፉ ስለ ዘይቤ፣ ስርዓተ ነጥብ አጠቃቀምና የግጥም አፃፃፍ ስልቶች ላይ ደራስያን ትኩረት እየሰጡ እንዳልሆነ ይጠቅሳል።

ከዚህም ባለፈ መጽሐፉ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ሆሄያት ይቀነሱ የሚሉትንም ’’በርካታ ብሔሮች ብሔረሰቦች በሚኖሩባት ኢትዮጵያ የራሳችን ገላጭ የሆነውን ቋንቋ መቀነስ" ተገቢ አለመሆኑን በአጽንኦት ይገልጻል። 

በመጽሐፉ ምረቃ ስነ ስረዓት ላይ በሁሉም ዘርፍ ያሉ የኪነ - ጥበብ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞችና የስነ-ጽሑፍ አፍቃሪያን የተገኙ ሲሆን፤ የመጽሐፉን ይዘት የሚያጠናክሩ በግዕዝ ቋንቋ የቅኔ ዘረፋና፣ የአንጋፋና ወጣት ገጣሚያን ስራዎች ቀርበዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2009 በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የቆሻሻ ክምር በመናዱ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ።

የተናደው የቆሻሻ ክምር ከመዲናዋ ለበርካታ ዓመታት እየተሰበሰበ ሲከመር የነበረ ነው።

ትናንት የተከሰተው አደጋ የሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል ሃብት ንብረት አውድሟል።

አደጋው የተከሰተው በግምት ትናንት ምሽት ሁለት ሰዓት አካባቢ ሲሆን፤ ሰዎችን ከቆሻሻ ክምሩ የማውጣት ስራ እየተከናወነ ሲሆን በአደጋው ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች አስከሬን እየወጣ ይገኛል። 

ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም ወደ ሕክምና ተቋም ተወስደዋል። በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር፣ የወደመው ንብረትና የደረሰው አደጋ መጠን እየተጣራ ነው።

በአሁኑ ወቅት በአፈር ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለማውጣት እርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

የአካባቢው ሰዎች የደረሰውን አደጋ አስከፊነት ገልጸዋል።

የቆሻሻው መደርመስ አደጋው የተከሰተበት አካባቢ 18 ያህል ቤቶችን ሸፍኗቸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በስፍራው ተገኝተው የአደጋውን ስፋት ተዘዋውረው ተመልክተዋል። የተሰማቸውን ጥልቅ ኃዘን ገልጸዋል።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችና የአካባቢው ሰዎች ባደረጉት ርብርብ የብዙ ሰው ሕይወት ለማዳን እንደተቻለ ያብራሩት ከንቲባው፤ የተሰማቸውን ጥልቅ ኃዘን ገልጸዋል።

በአካባቢው የመሬት መንሸራተት ስለሚደርስ የአካባቢው ነዋሪዎችን በዘላቂነት ሕይወት የማዳንና መልሶ የማቋቋም ተግባር የከተማ አስተዳደሩ እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

 

Published in ማህበራዊ

ነገሌ መጋቢት 3/2009 የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ኑሯቸውን በእቅድ በመምራት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የሊበን ወረዳ አንዳንድ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ወይዘሮ ሀቢባ መሀመድ በወረዳው  የሲሚንቶ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የቀደሙ ወላጆች  ልጅ በእድሉ ያድጋል የሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ  ለችግር ዳርጓቸው መቆየቱን ለኢዜአ  በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡ 

ከዚህ በመማር ከባለቤታቸው ጋር ተማክረው የቤተሰብ ምጣኔ በመጠቀማቸው ኑሯቸውን  በእቅድ መምራት እንዳስቻላቸው  ተናግረዋል፡፡

የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት አራርቆ በመውለድ የእናትና የህጻናትን ጤንነት ለመጠበቅ ብሎም  የኑሮ ጫናን ለመቀነስ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል፡፡

በወረዳው  የመሊሶ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ስኳሬ ተሜ በበኩላቸው  የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ማግኘታቸው አራርቆ ለመውለድ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል ፡፡

አራርቀው ከወለዷቸው ሶስት ልጆች መካከል ሁለቱን ያለችግር በመንግስት ትምህርት ቤት መደበኛ ትምህርት እየተከታተሉ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ፡

" የእርግዝና  መከላከያ መድሀኒት መውሰድ በመውለድና በጤና ላይ ችግር  የሚያስከትል  እየመሰለኝ ስጋት ነበረኝ " ያሉት ደግሞ የዚሁ  ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አዲ ጎዳና ናቸው፡፡

ስለጥቅሙ ትምህርት ካገኙ በኋላ ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡

ሌላዋ የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ ዋሬ ጎሎምቦ እንዳሉት ደግሞ  በግንዛቤ ጉድለት 11 ልጆችን  አለእቅድ አከታትለው  ወልደዋል፡፡

በእሳቸው ዘመን ኑሮን በእቅድ ለመምራት የጤና ተቋም ባለመስፋፋቱ  እንደዛሬው የቤተሰብ ምጣኔ  አገልግሎት  አልነበረም፡፡ 

የወይዘሮ ዋሪ ባለቤት አቶ ጃተኒ ጎለምቦም ኑሮን በእቅድ ለመምራት ቤተሰብን መመጠን አማራጭ የሌለው እንደሆነ አቅምን ባለማገናዘብ የቤተሰብን ቁጥር በማብዛት ከደረሰባቸው የኑሮ ጫናና ችግር መማራቸውን ተናግረዋል፡፡

በቤተሰብ ብዛት የሚፈጠር የኑሮ ጫና የሴቶች ችግር ብቻ  ሳይሆን የወንዶችም  እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በጉጂ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት 67 ሺህ 944 እናቶች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የእናቶችና ህጻናት ጤና አስተባባሪ አቶ ካሱ ዳዴ እንዳሉት" የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑት እናቶች  ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅትጋር ሲነጻጸር  በሰባት ሺህ 994 ይበልጣል"ብለዋል፡፡

የጤና ተቋማትም በመስፋፋታቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ   የዞኑ አጠቃላይ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ሽፋን ከ45 ወደ 51 በመቶ ማደጉን ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ በሚገኙ ሁለት ሆስፒታሎች ፣ 325  ጤና ጣቢያዎች እና  ጤና ኬላዎች የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት እየተሰጠ  መሆኑም ተመልክቷል፡፡ 

 

Published in ማህበራዊ

ባህርዳር  መጋቢት3/2009 በባህርዳር ከተማ የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች የተሳተፉበት የጤና ስፖርት ውድር ዛሬ በአጼ ቴዎድሮስ ስታድየም ተጀመረ።

በመክፈቻው ላይ በተካሄደው የእግር ኳስ ውድድር ባህርዳር ዩንቨርሲቲ ኢትዮ ቴሌኮምን 3ለ2 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

የተስፋ ኮከበ የበጎ አድራጎት ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንትና የውድድሩ አስተባባሪ ወጣት አምሳሉ እስመለዓለም እንደገለጸው በውድድሩ  21 የመንግስት መስሪያ ቤቶች  በአራት ምድብ ተከፍለው ይሳተፋሉ።

የውድድሩ ዓላማም በመንግስት መስሪያ ቤቶች መካከል ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ሰራተኛው የእረፍት ጊዜን በስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማሳለፍ ጤናውን እንዲጠበቅ ለማስቻል ያለመ ነው።

የመንግስት ሰራተኞች የጤና ስፖርት ውድድር ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ በመካሄድ ዛሬ ላይ መድረሱን አስተባባሪው ተናግረዋል።

ውድድሩ  በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ ቀጥሎ ከየምድቡ  አንደኛና ሁለተኛ የወጡትን ለሁለተኛው ዙር ውድድር በማሰለፍ ሰኔ 30/2009ዓ.ም  በሚካሄደው የዋንጫ ጨዋታ መርሃ ግብሩ ይጠናቀቃል ተብሏል።

ከባህርዳር ዩንቨርሲቲ የኬሚስትሪ መምህርና የእግር ኳስ ስፖርት ተወዳደሪ  ወልደ ጊዮርጊስ ህሉፍ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በየዓመቱ በሚካሄደው የመንግስት ሰራተኞች ስፖርት ውድድር መሳተፉ ጤናማ ህይወት እንዲኖረውና ማህበራዊ ትስስርን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡

ዛሬ በተካሄደው ውድድርም ጎል በማስቆጠር ቡድኑ እንዲያሸንፍ የድርሻቸውን እንደተወጡ  ጠቁመው ይህም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ለፍጻሜ በመድረስ ዋንጫ ለመውሰድ እንደሚያበረታታቸው አመልክተዋል።

በሰሜን ምዕራብ ሪጅን የኢትዮ ቴሌኮም እግር ኳስ ቡድን አምበል ደግነት አድማሱ በበላቸው  ቡድናቸው አሁን ቢሸነፍም በቀጣይ አሻሻሎ ለዋንጫ ተፋለሚ ለመሆን ጥረት እንደሚያደረግ ተናግረል።

"የጤና ስፖርት ውድድሩ ጤናን ከመጠበቅ በሻገር በሌሎች መስሪያ ቤቶች የሚሰሩ በርካታ ጓደኞች እንዳፈራ አስችሎኛል" ብለዋል።

ሰኔ 30 በሚጠናቀቀው  ውድድር ለአሸነፊው ቡድን ዋንጫ፣ የኮከብ ተጫዎቾች፣ የጸባይና ሌሎችም ሽልማቶች እንደሚኖሩ ተገልጿል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ  መጋቢት 3/2009 ቅድሚያ ለሴቶች የአምስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር አትሌት ደጊቱ አዝመራው አሸናፊ ሆነች። በውድድሩ 11 ሺ ሴቶች ተሳትፈዋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመሆን ያዘጋጁት የቅድሚያ ለሴቶች የአምስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድርን ዛሬ ተካሂዷል።

ውድድሩ "ስለምትችል" በሚል መሪ ሀሳብ ነው ዛሬ ለ14ኛ ጊዜ የተካሄደው።

ውድድሩ መነሻና መድረሻውን አትላስ ሆቴል በማድረግ የተካሄደ ሲሆን፤ በሴቶች የሩጫ ውድድር ከአዲዳስ ፕሮጀክት የተገኘችውና ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው አትሌት ደጊቱ አዝመራው በአንደኝነት አጠናቃለች።

አትሌት ደጊቱ አሸናፊ የሆነችው ውድድሩን 15 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ ከ8 ማይክሮ ሰከንድ በመጨረስ ነው ።

አትሌት አበባ እጅጉ ከአዲዳስ ፕሮጀክት ሁለተኛ ስትወጣ፤ አትሌት ምህረት ተፈራ ከሱር ኮንስትራክሽን ሶስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

ከውድድሩ በኋላ አትሌት ደጊቱ በቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ በመጀመሪያ ተሳትፎዋ አሸናፊ በመሆንዋ መደስትዋን ገልጻለች።

በቀጣይ በዓለም አቀፍ ወድድሮች አገሯን ለማስጠራት ጠንክራ እንደምትሰራም ተናግራለች።

"ቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ ለሴቶች ትልቅ ትርጉም ያለው ውድድር ነው" ያለች ደግሞ የዘንድሮ የሴቶች ሩጫ ውድድር አምባሳደር አትሌት መሰረት ደፋር ነች።

እንደ አትሌት መሰረት ገለጻ፤ ውድደሩ ሴቶች ጤንነታቸውን ጠብቀው እንዲዝናኑ ከማድረጉም ባሻገር ችሎታቸውን የሚያሳዩበት መድረክ ነው።

በዚህ ውድድር በርካታ አትሌቶች ማፍራት መቻሉ ነው ያመለከተችው። አሁንም ተተኪ አትሌቶች እየተገኙበት መሆኑን ነው አትሌት መሰረት የገለጸችው።

ዛሬ አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ውድደራቸውንያጠናቀቁ አትሌቶች የተገኙት አትሌት መሰረት ደፋር ካቋቋመችው አዲዳስ ፕሮጀክት ነው።

ይህ ፕሮጀክት ከተቋቋመ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ውጤታማ አትሌቶች መገኘታቸው “አስደሳች ነው” ብላለች አትሌት መሰረት።

በውድድሩ አንደኛ ሆና ላጠናቀቀቹ 15 ሺ ብር ሽልማት ሲበረከትላት፤ ሁለተኛ ለወጣችው 10 ሺ ብር፤ ሶስተኛ ለወጣችው ደግሞ የሰባት ሺ ብር ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

በውድድሩ ከ35 ደቂቃ በታች ለገቡ ተወዳዳሪዎች  የሴቶች ሩጫ አምባሳደር አትሌት መሰረት ደፋር የፈረመችበት የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

በሴቶች ሩጫ አትሌት አሰለፈች መርጊያ ሁለት ጊዜ፣ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ ሶስት ጊዜ ደጋግመው ያሸነፉ ሲሆን፤ አትሌት ቲኪ ገላና፣ ማሚቱ ዳስቃና ሱሌ ኡቱራ አንድ አንድ ጊዜ ማሸነፍ የቻሉ አትሌቶች ናቸው።

Published in ስፖርት
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን