አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 11 March 2017

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2009 "የአገሪቱን ልማት የሚያፋጥን አምራች ዜጋ ማፍራት እንዲቻል የቤት ጥያቄን ለመመለስ መስራት አለብን" አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቦሌ አራብሳና በቦሌ አያት ሶስት፣ አራት እና አምስት ሳይቶች ግንባታቸው የተጠናቀቁ የ20/80 የቤት ፕሮግራሞችን በስፍራው ተገኝተው መርቀዋል።

በሳይቶቹ የተመረቁ ቤቶች ለልማት ተነሺዎች የተላለፉ የቦሌ አያት ሶስት፣ አራትና አምስት 1ሺህ 811 እንዲሁም በቦሌ አራብሳ ሳይት 20 ሺህ 100 ቤቶች ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት መንግስት የተለያዩ ፖሊሲዎችን በመንደፍ ዘላቂነት ያለው ልማት አረጋግጦ፣ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው።

በዚህ ሂደት በከተሞች የሚንጸባረቁ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መነሻ የሆነው ድህነትን ለመግታት ያልተቋረጠ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በየዘርፉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተገኙ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለነዚህ ውጤቶች ተጠናክሮ መቀጠልና አገሪቱ የያዘቻቸውን የልማት ግቦች ለማሳካት ጤንነቱ የተጠበቀ አምራች ኃይል ማፍራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ይህን ለማድረግም ከሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎቶች አንዱ የሆነውን የመጠለያ ጥያቄ መመለስ ተገቢ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በአገሪቱ በዚህ ረገድ ያለውን አንገብጋቢ ጥያቄ ለመመለስ መንግስት በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍና የተቀናጀ የቤት ልማት ፕሮግራም ቀርጾ በመስራቱ በርካቶች ተጠቃሚ ሆነዋል ነው ያሉት።

እስካሁን በፕሮግራሙ በአዲስ አበባ ብቻ 175 ሺህ ቤቶች ለግማሽ ሚሊዮን ዕድለኞች በዕጣ መተላለፋቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት የተመረቁት ከ40 ሺህ በላይ ቤቶች ደግሞ የጥረቱን ውጤት የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

መንግስት ከ40/60፣ 20/80 እና 10/90 ፕሮግራሞች በተጨማሪ የመንግስት ሰራተኞችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በኪራይ መልክ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ፕሮግራም በመቅረጽም ወደ ስራ ገብቷል።

መንግስት የሚያጋጥሙትን የክህሎትም ሆነ የገንዘብ ችግር በማሸነፍ የዜጎችን የቤት ጥያቄ ለመመለስ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ቃል ገብተዋል።

በተጨማሪም በየከተሞቹ ያለውን የቤት ፍላጎት መንግስት ብቻውን ማሟላት ስለማይችል ዜጎች በተደራጀ መልኩ እንዲያግዙም ጠይቀዋል።

የአገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ በማድረግና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲሰማራ በማድረግ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎት ለማሟላት ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ የተሻለ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላትም እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

መንግስት ከፍተኛ መዋዕለ-ነዋይ በማፍሰስ ለህብረተሰቡ የሚያቀርባቸው ቤቶች የአገልግሎት ዘመናቸው እንዲረዝም ቤቶችን በመንከባከብና አካባቢውን ጽዱና አረንጓዴ በማድረግ ለመኖሪያ ምቹ አካባቢ መፍጠር ከነዋሪዎች ይጠበቃል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዛሬ ከተመረቁት ቤቶች በተጨማሪ 130 ሺህ ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ናቸው።

ከሚገነቡት መካከል የተወሰኑ ቤቶች በሚቀጥለው ዓመት ግንባታቸው እንደሚጠናቀቅም አስታውቀዋል።

በእስካሁኑ ሂደት የቤቶች ግንባታ የዜጎችን የቤት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ የከተማውን የተጎሳቆለ ገጽታ በመቀየር ጉልህ አስተዋጽዖ አበርክቷል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ ትልቅ ልምድ የተገኘበት በመሆኑ ለተያዙት ፕሮጀክቶች መፋጠን ጉልህ ሚና ይጫወታል ሲሉም ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2009 ወጣቱ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ግንዛቤ ቢኖረውም በሱስ መጠመድ በበሽታው የመያዝ ዕድሉ እንዳይቀንስ እንዳደረገው ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌደሬሽን እና የአዲስ አበባ ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት በጋራ ያዘጋጁት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።

የጽህፈት ቤቱ የፕሮግራሞች ዋና የስራ ሂደት መሪ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በዚህ ወቅት እንዳሉት "ኤች አይ ቪ/ኤድስን የተመለከቱ መረጃዎች በየጊዜው ተደራሽ ቢሆኑም ወጣቱ ጆሮ ዳባ ልበስ እያለ ነው"።

"የዚህ ምክንያቱ ወጣቱ በሱሶች በመጠዱ በስሜታዊነት ያለምንም ጥንቃቄ ልቅ የግብረ-ስጋ ግነኙነት መፈጸሙ ነው" ብለዋል።

ሲስተር ፈለቀች እንደሚሉት ስለ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ መተላለፊያ መንገዶች ግንዛቤ በየጊዜው ይሰጣል፤ ተግባራዊ የሚያደርግ ወጣት ግን ብዙ አይደለም።

ራሱን ለሱሶች ማስገዛቱ ዋነኛ ችግር መሆኑን ጠቁመው "ወጣቱ ስለ ኤች አይ ቪ/ኤድስ በተደጋጋሚ እንደተሰበከ ሁሉ ስለሱስ መጥፎ ባህሪያትም መድረክ ተፈጥሮ መማር አለበት" ብላዋል።

ይህ ካልሆነ የቫይረሱን ስርጭት መግታት አይቻልም፤ ተጠቂው ደግሞ በአብዛኛው ወጣቱ በመሆኑ ወጣቱ ላይ በስፋት መስራት ይገባል ብለዋል።

ጽህፈት ቤቱ በጎጂ ሱሶች ዙሪያ ወጣቱን ለማስተማር ከተለያዩ የወጣት ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ወጣት አባይነህ አስማረ በበኩሉ "ወጣቱ የልማት ኃይል መሆኑ ይታወቃል፤ ይሁንና ቀላል የማይባል ወጣት ራሱን ለሚጎዳ ነገር ተገዥ በማድረግ ለአገር ልማት  የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ እየቀነሰ ይገኛል" ብሏል።

ይህን ለማስተካከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች አማራጭ የሌላቸው መፈትሄዎች በመሆናቸው ፌደሬሽኑ በስፋት እየሰራ ነው ሲል ጠቁማል።

በአዲስ አበባ ከ86 ሺህ በላይ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች ሲኖሩ ከ2 ሺህ 900 በላይ የሚሆኑት በዚህ ዓመት አዲስ የተያዙ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፤ አብዛኛውም ወጣቱ ኃይል ነው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2009 የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌደሬሽን ለአካል ጉዳተኞች የቅርጫት ኳስ ውድድር የሚያገለግሉ የመጫወቻ ዊልቸሮችን ለክልሎች ድጋፍ አደረገ።

ፌደሬሽኑ ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በድጋፍ መልክ ያገኛቸውን 60 ዊልቸሮችና የመለዋወጫ መሳሪያዎች ነው ዛሬ በአዲስ አበባ የክልል ተወካዮች በተገኙበት ያከፋፈለው።

ድጋፉ የተደረገው ለአራት ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ነው።

የፌደሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይመር ኃይሌ ለኢዜአ እንደገለጹት ድጋፉ በአገሪቱ ካሉት የአካል ጉዳተኞች ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር በቂ ባይባልም ለስፖርቱ መነቃቃት መልካም ነው።

አካል ጉዳተኞችን በቅርጫት ኳስ እያሳተፉ የሚገኙ የተወሰኑ ክልሎች ለኦሮሚያና ደቡብ ለእያንዳንዳቸው 12 ዊልቸርና ከ300 ያላነሱ የመለዋወጫ መሳሪያዎች ተበርክቶላቸዋል።

በተመሳሳይ የአማራና የትግራይ ክልሎች ለእያንዳንዳቸው 10 ዊልቸሮች እና 150 የመለዋወጫ መሳሪያዎች ተሰጥቷቸዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አራት ዊልቸሮች እንዲሁም አዲስ አበባ 150 የመለዋወጫ መሳሪያዎችን አግኝተዋል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2009 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርክቴክተር ህንጻ ግንባታና ከተማ ልማት ተቋም በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ቴክኖሎጂና አርክቴክቸራል ዲዛይን በዲግሪ መርሃ-ግብር ያሰለጠናቸውን 203 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ።

ከተመራቂዎቹ መካከል 161ዱ ወንዶች ሲሆኑ 42ቱ ሴቶች ናቸው፤130ዎቹ በመደበኛ መርሃ-ግብር የተማሩ ሲሆን ቀሪዎቹ በማታው ክፍለ ጊዜ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

ተመራቂዎቹ በግንባታው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የቤቶች ዲዛይንና ኮንስትራክሽን ግንባታ ያላቸውን አቅም በመጠቀም ለዘርፉ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑም እንዲሁ።

የተማሩበት ዘርፍም ከስራ ጠባቂነት ይልቅ የራሳቸውን ስራ ፈጥረው ለመስራት የሚያስችላቸው መሆኑ ነው የተመለከተው።

ተቋሙ በዲግሪ መርሃ-ግብር ሲያስመረቅ ለ17ኛ ጊዜ ነው።

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በኪነ-ህንጻ ትምህርት በዲግሪ መርሃ ግብር ያስተማራቸውን 32 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

ተመራቂዎቹ ለአምስት ዓመት ከግማሽ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፤ ከተመራቂዎቹ 27ቱ ወንዶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሴቶች ናቸው።

በምርቃቱ ስነ-ስርዓት ላይ ተማሪዎቹ በግንባታው ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲኖርና ጥራት ላለው ግንባታ እየተደረገ ላለው ጥረት የጎላ ሚና ይጫወታሉ ነው የተባለው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2009 ሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን የበለጠ ለማጎልበት የተለያዩ የቁጠባ ዜዴዎችን በአግባቡ ሊጠቀሙ ይገባል ተባለ።

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን የሴቶችን የቁጠባ ባህል ሊያሳድጉ በሚችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ-ግብሮች  አክብሯል።

በኢትዮጵያ የሴቶችን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ የቁጠባ ማህበራት፣ የሴቶች ልዩ የቁጠባ መርሃ-ግብርና ሌሎች አማራጮች ተፈጥረዋል።

እነዚህን ዘዴዎች በመጠቀም በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በሴቶች መቆጠቡን በፕሮግራሙ ወቅት ተገልጿል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተካ አባዲ እንደተናገሩት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ መብት ለማረጋገጥ መንግስት እያከናወነ ከሚገኘው ተግባር አንዱ የቁጠባ ባህላቸውን ማሳደግ ነው።

በዚህም ኃብት በማፍራት፣ በመቆጠብና በመበደር በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው ራሳቸውንና አገራቸውን በመጥቀም ላይ ይገኛሉ።

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅትም በዓመት ሁለት ጊዜ በሚያደርገው የእድገት ደረጃ ሴቶች ከአንደኛው እድገት የሚያገኙትን ገንዘብ ቀጥታ እንዲቆጥቡ ለማድረግ እቅድ ተይዟል ነው ያሉት።

በድርጅቱ የቁጠባ ማህበር ውስጥ ሴቶች ገብተው እንዲቆጥቡም እየተደረገ ነው ብለዋል።

ሴቶች በአገሪቱ ዕድገት ውስጥ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ ቁጠባን እንደ ባህል ሊያደርጉት ይገባል ያሉት ደግሞ አስተያየት የሰጡ የድርጅቱ ሴት ሰራተኞች ናቸው።

ድርጅቱ የሴቶችን አቅም ለማሳደግ ትምህርት ለመማር ፍላጎት ያላቸው ሴቶችን ድጋፍ በማድረግ እንደሚያበረታታ፤ በሚወልዱበት ጊዜም የአራስ መጠየቂያ ገንዘብ እንደሚሰጥ ነው የተናገሩት።

በበዓሉ አከባበር የቁጠባ ባህልን የሚያሳድጉ መረጃዎች፣ የሴቶች የገንዘብ አጠቃቀም ባህል ጥንካሬ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ቁጠባ ያለውን ጠቀሜታ የተመለከቱና ሌሎችም ዝግጅቶች ቀርበዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ነቀምት መጋቢት 2/2009 በኦሮሚያ ክልል ሶስት ዞኖች  ከ693 ሺህ የሚበልጡ ሕፃናት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የክትባት መርሃ ግብር አስተባባሪ አቶ ጌታሁን ዘውዱ እንደገለጹት ከየካቲት21/2009 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በተካሄደ የክትባት ዘመቻ በዞኑ 342 ጣቢያዎች ዕድሜያቸዉ ከዘጠኝ ወር እስከ አምስት ዓመት የሆናቸዉ 190 ሺህ 164 ህፃናት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ደግሞ በ41 የክትባት መስጫ ጣቢያዎች 86 ሺህ 448 ሕፃናት መከተባቸውን በዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ዳኜ ቀነዓ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በቄለም ወለጋ ዞን  ከዘጠኝ ወር እስከ 15 ዓመት እድሜ ያላቸው  417ሺህ 146 ህጻናትና ታዳጊዎች በ277 የክትባት መስጫ ጣቢያዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ታምራት ዓለሙ ገልጸዋል፡፡

በነቀምቴ ከተማ 09 ቀበሌ 3 ልጆቻቸውን ያስከተቡት ወይዘሮ ትግሥት ካሣሁን በሰጡት አስተያየት የጤና ባለሙያዎችን ምክር በመቀበል የልጆቻቸውን ጤንነት ለመጠበቅ በወቅቱ ማስከተባቸውን ተናግረዋል፡፡

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እናት ወርቁ እንዳሉት  የክትባትን አስፈላጊነትና ጥቅምን በመረዳት ሁለት ልጆቻቸውን አስከትበዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ነገሌ መጋቢት 2/2009 ህገ መንግስቱ በሁሉም መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው በጉጂ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ ሴት አመራሮችና የመንግስት ሰራተኞች ተናገሩ፡፡

አመራሮቹና  ሰራተኞቹ የአለም የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ  ለኢዜአ እንደገለጹት  ህገ መንግስቱ ያረጋገጠው እኩልነት ሴቶችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

የጉጂ ዞን ሴቶችና ህጻናት  ጉዳይ ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ ወይዘሪት ረሂማ አብዱላሂ " በዞኑ ባለፉት 25 አመታት ሴቶች በሀብት ፣ በስልጣን ፣በትምህርትና በሌሎችም መስኮች እኩል ተጠቃሚ ሆነዋል" ብለዋል፡፡

የዞኑ ሴቶች ለመብትና ጥቅሞቻቸው መከበር ተደራጅተው ከመታገል ባለፈ ለህዳሴ ግድብና ለሌላውም የልማት ስራ የድርሻቸውን ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ በሁለት ወራት ብቻ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር የቆጠቡ ሶስት ሺህ 550 ሴቶችን በማሳያነት አመላክተዋል፡፡

የመደበኛ ትምህርት እድል ያገኙ 140 ሺህ ሴት ተማሪዎች እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

የዞኑ ሴቶች በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ በመንግስት ስራም ሆነ በህግ ፊት ከወንዶች እኩል ፍትህ እያገኙ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ በነገሌ ቦረና ከተማ የመንግስት ሰራተኛ   ወይዘሮ ጌጤነሽ ሀይሉ ናቸው፡፡

በህገ መንግስቱ ለሴቶች የተሰጠው መብት በዞኑ በርካታ ሴቶች የመንግስት ሰራተኞች እንዲሆኑና የሀላፊነት ቦታን እንዲያገኙ አስችሏል፡፡

ከዚህ በፊት  ሴቶች እንዳይማሩና ለአመራርነትም እንዳይበቁ የነበረው ተጽዕኖና የተሳሳተ አመለካከት ተለውጦ አሁን ላይ በሁሉም መስክ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆናቸውን ወይዘሮ ጌጤነሽ ተናግረዋል፡፡

"ለሴቶች አሁን የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ እኩል ፍትህ የሚያስገኝ ፣በመንግስት ስራ ቅድሚያ የሚያሰጥ ፣የሀብትና የመሬት ባለቤት ለመሆን ያስቻለ ነው "ብለዋል፡፡

የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ሰራተኛ የሆኑት  ወይዘሮ የኋላሸት ሀይሌ በበኩላቸው የሴቶች ችግር በህገ መንግስቱ ቢፈታም በአንዳንድ የዞኑ አካባቢዎች አሁንም ከጥገኝነት ያልተላቀቁ ሴቶች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የተጀመረውን የማብቃት ጥረት በማጠናከር እኩል ተጠቃሚነታቸውን ማጎልበት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የጉጂ ዞን ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ መአዛ አብደታ በዞኑ 150 ሴቶች በመካከለኛ አመራርነት ቦታ ላይ ተመድበው እንደሚገኙ  ገልጸዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ደሴ መጋቢት 2/2009 የላቀ የምግብ ይዘት ያላቸውና የተሻለ ምርት የሚሰጡ የበቆሎ ምርጥ ዘሮችን በመጪው የመኸር ወቅት ጥቅም ላይ እንደሚያውል የአማራ ክልል ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ አስታወቀ።

ኢንተርፕራይዙ ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በምስራቅ አማራ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር አዲስ በወጡ የበቆሎ ምርጥ ዘሮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

በኢንተርፕራይዙ የዘር ጥራትና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ደምለው አበበ ትላንት በደሴ ከተማ በተደረገው ውይይት ላይ እንደገለፁት ምርጥ ዘሩ መልካሳ 6 ኪው፣ ኤም ኤች 138 ኪውና ቢ ኤች ኪው ፒ ዋይ 545 የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ናቸው።

እርጥበት አጠር ለሆኑት የምስራቅ አማራ አካባቢዎች የሚስማሙና ድርቅን ተቋቁመው ከ120 እስከ 145 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ለምርት እንደሚደርሱ በጥናት መረጋገጡንም ተናግረዋል።

በተለምዶ ከሚመረተው የበቆሎ ዝርያ በሄክታር የሚገኘውን 15 ኩንታል ከአራት እጥፍ በላይ ከማሳደጋቸውም ባለፈ በተሻለ የምግብ ይዘታቸው በክልሉ ህፃናት ላይ የሚስተዋለውን የመቀንጨርና የመቀጨጭ ችግር እንደሚያቃልሉም ተናግረዋል።

በአርሶ አደሩና በባለሙያው ዘንድ በምርጥ ዘሮቹ ላይ ግንዛቤ ከተፈጠረ በኋላ በምስራቅ አማራ አምስት ዞኖች ውስጥ በጥናት በተለዩ 12 ወረዳዎች  አንድ ሺህ 425 ኩንታል ዘር ለማሰራጨት ከወዲሁ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል

በመጭው መኽር  የሚሰራጩት ምርጥ ዘሮች አምስት ሺህ 700 ሄክታር መሬት እንደሚያለሙ የገለፁት አቶ ደምለው ከሚለማው መሬት በአማካይ 205 ሺህ 200 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግሥቴ በበኩላቸው ቢ ኤች 545 የተባለ ምርጥ ዘር በምእራብ አማራ ለሚገኙ በቆሎ አምራች አርሶ አደሮች ተሰራጭቶ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ውጤታማ እንደነበር አስታውሰዋል ።

ክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመቀንጨር ችግር ከተጠቁ ክልሎች ግንባር ቀደም መሆኑን ያወሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው አዲስ የተዋወቁት ምርጥ ዘሮች የምግብ ይዘታቸው ከፍተኛ መሆን ችግሩን ለማቃለል አስተዋጽዖ እንዳለው ተናግረዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን የላስታ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማትና ጥበቃ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ብርሃነመስቀል በበኩላቸው እንደገለጹት አዲስ የተገኙት የበቆሎ ምርጥ ዘሮች የአርሶ አደሩን ምርታማነት የሚያሳድጉ ናቸው።

"ወረዳው ዝናብ አጠርና በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቃ በመሆኑ ምርጥ ዘሮቹ የአርሶ አደሩን ምርታማነትና የሰብሉን የምግብ ይዘት ለማሳደግ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል” ብለዋል።

መቐለ መጋቢት 2/2009 በትግራይ ከልል መቀሌ ከተማ  የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ለመጀመር የሚያስችለው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

የክልሉ የጥቃቅንና አነስተኛና የከተሞች ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ልማት ኤጀንሲ ሃላፊ አቶ ሃይላይ አረጋዊ ለኢዜአ እንደገለፁት ለመጀመሪያ ጊዜ በትግራይ መቀሌ  በሚጀመረው የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም  5ሺህ  ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ከተጠቃሚዎቹ መካከል 16 በመቶ የሚሆኑት ለመስራት አቅም የሌላቸው ወገኖች የቀጥታ ድጋፍ የሚያገኙ ናቸው፤ ቀሪዎቹ  በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ በማሳተፍ ድጋፍ ያገኛሉ፡፡

ሃላፊው እንዳመለከቱት የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሰዎች የደሀ ደሀ የህብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸው በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት አደረጃጀቶች ተለይተው መስፈርቱን ያሟሉ  ናቸው፡፡

በመስፈርቱ መሰረት የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሚሆኑት  በሀወልቲ፣በቀዳማይ ወያነና በሓድነት ክፍለ ከተሞች የአምስት ሺህ ነዋሪዎች ምልመላ መጠናቀቁን  አቶ ሃይላይ ገልጸዋል፡፡

በስራው ለሚሳተፉ ዘንድሮ የሚከፈል 50 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን አመልክተው ፐሮግራሙ በመጪው መጋቢት ወር አጋማሽ  እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡ 

" በፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለዩ  ሰዎች በየክፍለ ከተሞቹ ስም ዝርዝራቸው  በቀጣዩ ሳምንት ይለጠፋል" ብለዋል፡፡

የማይገባው ወገን የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ሆኗል የሚል የህዝብ ቅሬታ ከተገኘ ዳግም የማጣራት ስራ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል፡፡

የከተሞችን ስራ አጥነት ችግር ለመፍታት  ዋናው መፍትሄ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ተደራጅቶ መስራት መሆኑን የጠቀሙት ሀላፊው " የምግብ ዋስትና ፕሮግራምም የዚሁ አጋዥ አካል ተደርጎ ይወሰዳል "ብለዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2009 አዲሱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን አመራር ጅምር ተስፋ ሰጪ ነው ሲሉ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኞችና አትሌቶች ተናገሩ።

በሪዮ ኦሎምፒክ የአትሌቶች ምርጫና በኋላም ደካማ ውጤት መመዘግቡን ተከትሎ በሩጫው ዓለም ስኬታማ የሆኑ አትሌቶች ፌደሬሽኑ ላይ ተቃውሞ ማንሳታቸው ይታወሳል።

የበርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ጥያቄ የነበረውም አትሌቲክሱ በዘርፉ ባለፉ አትሌቶች መመራት አለበት የሚል ነበር።

ይህ ጥያቄም ጥቅምት 26 ቀን 2009 ዓ.ም በነበረው የፌደሬሽኑ 20ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ምላሽ በማግኘት አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በፕሬዚዳንትነት ተመርጧል።

አትሌት ገብረእግዚብሔር ገብረማርያም ደግሞ በምክትልነት ባለፉት አራት ወራት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን እየመሩት ይገኛሉ።

አዲሶቹ አመራሮች በስፖርቱ ያለፉና ልምድ ያላቸው ቢሆኑም በአጭር ጊዜ ጎልቶ የሚታይ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ ባይታሰብም፤ ችግሮችን ለመፍታት እያሳዩት ያለው ጥረት ገና ከጅምሩ ጥሩ የሚባል ነው ይላሉ የአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችና አትሌቶች።

አሰልጣኝ ሻምበል ጋሻው በዛ "በአትሌቲክስ ስፖርት ከዚህ በፊት በመካከለኛና በረጅም ርቀት ስፖርቶች ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ይታይ ነበር፤ አሁን ግን በሌሎች ስፖርቶችም በትኩረት እየሰሩ ነው" ብለዋል።

ለአብነትም እሳቸው በሚያሰልጥኑትና ከሜዳ ላይ የአትሌቲክስ ስፖርት ተግባራት አንዱ በሆነው የዝላይ ስፖርት ''ከዚህ በፊት ትኩረት ከተነፈጋቸው ስፖርቶች አንዱ ነበር፤ አሁን አመራሩ በየጊዜው ስልጠናውን በአካል እየመጣ ይከታተላል'' ሲሉ ነው የተናገሩት።

የብሄራዊ ቡድኑ የአጭር ርቀት አሰልጣኝ ዋና ኦፊሰር አብዱላዚዝ ሁሴን በክልልና በአዲስ አበባ የሚገኙ ባለሙያዎችን በማሰባስብ ችግሮችን ለመለየት ውይይት አድርገዋል፤ ይህም እንደ ጅምር ጥሩ ነገር ነው'' ብለዋል።

እነዚህ ስራዎች ተጠናከረው መቀጠል አለባቸው ሲሉም አሰልጣኙ አሳስበዋል።

አትሌቶችም በአጭር ጊዜ ችግሮች ሙሉ በሙሉ ይፈታሉ ብለው ባይጠብቁም አዲሱ አመራር ለአትሌቲክስ ስፖርት የተሻለ ነገር ያመጣል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።

ከዚህ በፊት በመካከለኛና በረጅም ርቀት ላይ ብቻ ትኩረት የነበረው አትሌቲክሳችን አሁን በአጭር ርቀትና በሜዳ ላይ ተግባራትም የተጀመሩ ስራዎች ትልቅ ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል።

"የአጭር ርቀት ተወዳዳሪው አትሌት ኢብራሒም ጄይላን ፌደሬሽኑ ትልቅ ተስፋ ሰጥቶናል፣ ያንንም በቅርብ ቀን እናያለን የሚል ተስፋ አለን" ሲል ተናገሯል።

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን አትሌቶች ለአገር ውስጥ ውድድር ትኩረት እንዲሰጡ አብዛኛው የአገር ውስጥ ውድድሮች ላይ የሽልማቱን መጠን በእጥፍ በማሳደግ አትሌቶችን እያበረታታ ይገኛል።

Published in ስፖርት
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን