አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 10 March 2017

አዲስ አበባ የካቲት 1/2009 በአቃቂ ከርሰ ምድር ውሃ ተጠቃሚ አካባቢዎች ያጋጠማቸውን የውሃ እጥረት ችግር መፈታቱን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአቃቂ ከርሰ ምድር ውሃና የመዲናዋን የውሃ አቅርቦት በተመለከተ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በውሃ አቅርቦት ችግር ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ ማሰማታቸው የተለመደ ሆኗል።

የከተማዋ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በበኩሉ ችግሩ የተከሰተው በከርሰ ምድር የውሃ መገኛዎች ላይ በተፈጠረ የምርት መቀነስ እና ከከተማዋ ዕድገት ጋር ተያይዞ የውሃ ፍላጎት እና አቅርቦቱ አለመጣጠን መሆኑን ገለጿል።

ከነዚህ መካከል ባለፉት ሶስት ወራት በመዲናዋ የተከሰተ የውሃ አቅርቦት ችግር ተጠቃሽ ነው። በደቡብ፣ በምዕራብና በመዲናዋ ማዕከላዊ ስፍራ በውሃ  ምንጭነት የሚያገለግለው የአቃቂ ከርሰ ምድር የውሃ መጠኑ በመውረዱ ችግሩ መከሰቱ ነው የተገለጸው።

ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለማሪያም እንደተናገሩት፤  ከባለፈው መስከረም ጀምሮ ለወራት የከርሰ ምድር ውሃ መጠን በመቀነሱ የውሃ እጥረት ተከስቷል። ሆኖም በጥናት ላይ የተመሰረቱ ማስተካከያዎች በመደረጋቸው ችግሩ እየተፈታ መጥቷል።

እንደ ዋና ስራ አስያጁ ገለጻ፤ በአቃቂ  አካባቢ ከተቆፈሩትና  ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ከሚያደርጉት አራት የከርሰ ምድር ውሃዎች መካከል ሶስቱ የውሃ መጠናቸው የመውረድ ችግር አጋጥሟቸዋል።

የዚህ መንስኤ ደግሞ የከርሰ ምድሩን ፕሮጀክት ያጠናው አማካሪ “የከርሰ ምድር ውሃ መጠኑ ለ10ና ለ15 ዓመታት ውሃው ሳይቀንስ ይቆያል” በሚል ሙሉ እምነት በፓፕ ተከላው ወቅት በተከሰተ የቴክኒክ ችግር መሆኑን አንስተዋል።

በቀን 70 ሺ ሜትሪክ ኩብ ውሃ የሚያመርቱ የከርሰ ምድር ጉድጓዶች የማምረት አቅማቸው ወደ 40 ሺ ሜትሪክ ኩብ ወርዷል።

ይህን ጥናት መነሻ በማድረግ ሙያዊ ግምገማ ተደርጎ በቀረቡ የመፍትሄ  አማራጮች የማስተካከያ ስራዎች መከናወናቸውን ነው የገለጹት።

በተከናወነው ማስተካከያ ከአቃቂ እስከ ሜክሲኮ አካባቢዎች ያሉ ሰፈሮችን የውሃ አገልገሎት የሚሰጠው ከወረደበት በቀን 40 ሺ ሜትሪክ ኩብ ወደ 55 ሺ ሜትሪክ ኩብ እንዲያመርት መደረጉን አብራርተዋል።

ጎተራ፣ ስቴድዬም፣ ጎፋ መብራት ኃይል አካባቢ ያሉ ሰፈሮች ከዚህ በፊት ያገኙት የነበረው መጠን መስተካከሉንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ከአቃቂ ተነስቶ ወደ ሃና ማሪያም፣ ጦር ኃይሎች የሚወስደው የአቃቂ ከርሰ ምድር ምዕራፍ ሶስት 'ለ' የተባለው መስመር ከነበረበት 70 ሺ ሜትሪክ ኩብ በቀን የማምረት አቅም ወደ 40 ሺ ሜትሪክ ኩብ ዝቅ ብሎ ነበር። በተደረገለት የማስተካከያ ተግባርም አሁን ወደ ቀድሞው የምርት አቅም መመለስ መቻሉን ነው የገለጹት።

የልደታ፣ የኮልፌና የንፋስ ስልክ ክፈለ ከተሞችም ከዚህ በፊት አገልግሎት ያገኙ ነበር፤ ችግሩም መፈታቱን አብራረተዋል።

በሌላ በኩል ያለውን የውሃ መጠን ለተጠቃሚዎች ለማድረስ የአቃቂ አካባቢን ጨምሮ በበርካታ አካባቢዎች የኤሌትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር ፈጥሮ እንደነበር አመልክተው፤ ከኤሌትሪክ ኃይል ጋር በተደረጉ ምክክሮች ችግሩ እየተፈታ መምጣቱንም ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ ምድር ባቡር ጋር ተያይዞ እንዲሁም የውሃ ማስተላለፊያ መስመሮች ካላቸው እድሜ አኳያም ለውሃ መቆራረጥ ምክንያት እንደነበሩ ተወስቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰሜን አዲሰ አበባ የውሃ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታትም የለገዳዲ ምዕራፍ ሁለት የተሰኘ የውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክት ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በቀን 79 ሺ ሜትሪክ ኩብ ውሃ በቁፋሮ የተገኘ ሲሆን፤ ተጨማሪ ጉድጓዶችን በመቆፈር ወደ 86 ሺ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በምስራቅ አዲስ አበባ ያለውን የውሃ ችግር በተለይም በአያት ኮንዶሚኒዬም ነዋሪዎችን የውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታትም በቀን 69 ሺ ሜትሪክ ኩብ የሚያምርት የጉድጓድ ውሃ ፕሮጀክት መጠናቀቁን አክለዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 1/2009 የበካይ ጋዝ ልቀትና የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ መጠንን የሚለካ ስርአት በኢትዮጵያ ሊተገበር መሆኑን የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ገለፀ።

ሬድ ፕላስ የተሰኘውን ይሕንን ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

በአገሪቷ ያለውን ደን በመጠበቅ ፣ አዳዲስ ችግኞችን በመትከልና የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ የአየር ንብረት ለውጥን  በመከላከል ላይ የሚሰራው የብሔራዊ የሬድ ፕላስ ፕሮግራምን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ተጠናቋል።

በሚኒሰቴሩ የሬድ ፕላስ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ይተብቱ ሞገስ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአገሪቷ የሬድ ፕላስ ፕሮግራምን ተግባራዊ ለማድረግ መሳሪያዎችን ከውጭ የማስገባትና ሌሎች የዝግጅት ስራዎች ተጠናቀዋል።

በአሁኑ ወቅት የሬድ ፕላስ ስርዓት ይዘት ጥናት ውጤት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተላከ ሲሆን፤ ልኬቱ በየሁለት ዓመቱ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የመለኪያ ስርአቱ የካርቦን ልቀትን መጠን በመቀነስ የሚገኙ ውጤቶችን የሚያሳይ በመሆኑ ከዘርፉ ተገቢውን ገቢ ለማግኘት የሚያስችል እንደሆነም ተጠቁሟል።

በመሬት፣ በአየርና በደን ላይ ያሉ መረጃዎችን በተደራጀ መንገድ ለመለየት የሚያስችለው የመለኪያ ስርአቱ፣ ለውጦችን በማሳየት አገሪቷ በምታስመዘግበው የካርበን ልቀት መጠንን ለመቀነስ በምታደርገው ልክ ገቢ እንድታገኝ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የመለኪያ ስርአቱ የደን ሽፋን፣ የአየር ንብረት ለውጥንና የካርበን ልቀት መጠንን በዝርዝር የሚያሳይ ነው።

ፕሮግራሙ የደን ይዞታዎች አካባቢ የሚገኝው የሕብረተሰብ ክፍል በራሱ ክልል ላይ የደን ልማት እንዲያካሂድና ከውጤቱም ተጠቃሚ እንዲሆን  ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ ፕሮግራሙን ከኦሮሚያ ክልል ጋር ተግባራዊ ለማድረግ ከክልሉ የደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

ፕሮጀክቱን በሌሎች አካባቢዎችም ተግባራዊ ለማድረግ ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ፤ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን በማስፋፋቷና የአየር ብክለትንም በመቆጣጠር ላይ በመሆኗ  ከካርቦን ንግድ ተጠቃሚ ትሆናለች።

ለረጅም ዓመታት ከመሬት መራቆት ጋር ተያይዞ የአገሪቷ የደን ሀብት በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰ ሲሆን፤ አሁን በማገገም ላይ በመሆኑ ሽፋኑ 15 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኢትዮጵያ ከሚለቀቀው 18 ሚሊዮን ቶን በካይ ጋዝ ውስጥ “አምስት ሚሊዮን ቶን የካርቦን ዳይኦክስድ ጋዝን በአገሪቷ ያለው ደን መጦ ያስቀረዋል” ብለዋል።

ዋናው ዓላማ ያለው ደን እንዳይጠፋ መከላከል ነው፤ አዳዲስ ደኖችን በማስፋፋት በአካባቢ  አየር ውስጥ ያለውን ካርቦን እንዲወስዱ ማድረግና በበካይ ጋዝ አማካኝነት የሚደርሰውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ማድረግ  መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ብክለትን ለመቀነስ በምታደርገው እንቅስቃሴ በግምባር ቀደምትነት የምትታወቅ አገር መሆኑዋንም ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል የደን፣ አከባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አራርሳ ረጋሳ በስልክ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፤ በሁለት ወራት ውስጥ ፕሮግራሙን በጅማ ፣ በጉጂ ፣ በቄለም ወለጋ ፣በቡኖ በደሌ ዞኖች 49 ወረዳዎች ውስጥ  ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ተጠናቋል።                                                                                                      

ክልሉ ከሚኒስቴሩ ጋር በመተባበር በካርቦን ልቀት ቅነሳና በፕሮጀክቱ አተገባበር ላይ የአቅም ግንበታ ስልጠና መስጠቱንም ነው የገለጹት።

ለዚሁ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያም በአለም ባንክ 18 ሚሊዮን ዶላር መመደቡንም አመልክተዋል።

በክልሉ ከዚህ በፊት በዓመት 38 ሄክታር መሬት ደን ይጨፈጨፍ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫም አኃዙ በመቀነስ ላይ ነው።

በዚህም “የደን ሽፋንን በመጨመር በዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

ሬድፕላስ የደን ምንጣሮና ብክነትን ለማስቀረትና ዕቅድን ከልሶ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወጣ ፕሮግራም መሆኑም ተገልጿል።

ባህር ዳር የካቲት 1/2009 የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተግባራዊ በሆነባቸው የአገሪቱ ወረዳዎች ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ በመሆኑ ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ከትናንት ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ እየገመገመ ነው።

የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አታክልቲ አብርሃ በጉባኤው ላይ እንደገለጹት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህንን ተደራሽ ማድረግ ከ80 በመቶ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ነው።

የጤና መድህን በ2004 ዓ.ም በአራቱ ዋና ዋና የአገሪቱ ክልሎች በሚገኙ 13 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ ቢተገበርም በአሁኑ ወቅት ፕሮግራሙ ከ300 በላይ ወረዳዎችን ተደራሽ ማድረጉን ተናግረዋል።

እንደ አቶ አታክልቲ ገለጻ፣ ፕሮግራሙ ተግባራዊ በሆነባቸው ወረዳዎች የማህበረሰቡ ግንዛቤ፣ ትብብርና ንቁ ተሳትፎ እያደገ በመምጣቱ ውጤታማነቱ ጎልቶ እየታየ ነው።

መንግስትም የጤና ተቋማትን ዝግጁነትንና የባለሙያውን አቅምና ክህሎት ከማሳደግ ባለፈ  የመድኃኒት አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ በስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል።

በምዕራብና ምስራቅ አማራ ፕሮግራሙ ያለበትን ሁኔታ መገምገሙን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ይህም ችግሮችን ከመለየት ባለፈ መልካም ልምዶችንና ስኬቶችን ቀምሮ ለማስፋት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ብዙአየሁ ጋሻው በበኩላቸው “የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን መደበኛ ባልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው” ብለዋል።

በክልሉም ከ2 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ መሆኑ የፕሮግራሙ ስኬት አንድ መሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህም የውስጥ አቅምን በማሳደግና ዘላቂ የሀብት ምንጭ እንዲጎለብት በማድረግ ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የተያዘውን አገራዊ ግብ ለማሳካት መሰረት እየጣለ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይም በዝቅተኛና በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቀድመው የሚቆጥቡት የገንዘብ አቅም ሳይገድባቸው ሕክምና የሚያገኙበት ዕድል የፈጠረ በመሆኑ አርሶአደሩም  በስፋት እየተቀበለውና ተጠቃሚ እየሆነ መሆኑን አብራርተዋል።

የጤና መድህን አባላት ጊዜውን ጠብቀው መታወቂያቸውን እንዲያድሱ፣ የሕክምና ተቋማት የአገልጋይነት መንፈስ እንዲያሳድጉ እንዲሁም የጤና መድህኑ አዳዲስ አባለትን በስፋት የማፍራት ተግዳሮቶች እንዲወገዱ መድረኩ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይኖርበታል ሲሉ አቶ ብዙአየሁ ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

መቱ የካቲት 1/2009 ባለፉት ዓመታት ባከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የመጣው ለውጥ  ልማቱን አጠናክረው ለመቀጠል መነሳሳት እንደፈጠረላቸው በኢሉአባቦር ዞን የዳሪሙ ወረዳ አንዳንድ አርሶአደሮች ተናገሩ፡፡

በዞኑ ባለፉት አምስት ዓመታት ተፋሰስን ተከትሎ በአርሶአደሩ ተሳትፎ በተከናወነው  የአፈርና ወሃ ጥበቃ ስራ  ከ713 ሽህ ሄክታር በላይ የተጎዳን መሬት ማልማት ተችሏል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዳሪሙ ወረዳ አርሶ አደሮች እንዳሉት ቀደም ባሉት ዓመታት  ባከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ  ደርቀው የነበሩ ምንጮች እንዲመለሱ ፣ እንስሳት በቅርበት መኖ እንዲያገኙ እና የአፈር መሸርሸር እንዲቀንስ አስችሏል፡፡

በወረዳው የወሌ ባምቢስ ቀበሌ አርሶ አደር ቡላ ኤጄርሶ ተፋሰስን ተከትለው ባካሄዱት የአፈርና ውሀ እቀባ ስራ ተጎድቶ የነበረው መሬታቸው  አገግሞ እርጥበት በመያዙ  ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመስኖ እያለሙ  መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

" በዚህ ዓመት በቆሎ ፣ቲማቲምና ጥቅል ጎመን እያለማሁት ካለው አራት ጥማድ መሬት ውስጥ አንድ ጥማድ የሚሆነው ከዚህ ቀደም ደርቆ የነበረ ነው” ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ይዞታቸው በሙሉ በመልማቱ  አካባቢያቸውን ከጉዳት ለመጠበቅ  የሚያካሄዱትን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ አጠናክሮ ለመቀጠል መነሳሳታቸውን  ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በዳገታማ አካባቢዎች የሚዘሩት ሰብሎች በአፈር  መሸርሸር የተነሳ የመሬት ለምነት በመቀነሱ ፍሬ ማፍራቱን  አቁሞ እንደነበር ያመለከቱት  ደግሞ የወረዳው ሌላው አርሶአደር ቄስ አበራ አለማየሁ ናቸው፡፡

በየዓመቱ እየተከናወነ ባለው የእርከን ስራ የአፈር መሸርሸር መቀነሱን ተናግረዋል፡፡

" የተፋሰስ ልማት ስራ ሲጀመር  ስለጠቀሜታው ብዙም ስለማላውቅ ተነሳሽነቴ አነስተኛ ነበር ያሉት "  አርሶ አደሩ   አሁን ላይ ጥቅሙን በመረዳት ከሌሎች አርሶአደሮች ጋር ስራውን ለማጠናከር በከፍተኛ ፍላጎትና ተነሳሽነት እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የተከሏቸው  የዛፍ ችግኞች ደርሰው  አካባቢያቸውን ልምላሜ ከማላበሳቸውም  በላይ በእርከኖች ዳርቻ የሚተክሉት የሳር ዝርያዎችም ከብቶቻቸው ከቤት ሳይርቁ መኖ እንዲያገኙ ማስቻሉንም አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል፡፡

ተጠቃሚነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ያለምንም ቅስቀሳ ስራውን ለማስቀጠል በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የዳሪሙ ወረዳ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ተማም ከድር በበኩላቸው  በወረዳው  ካለፈው ወር ጀምሮ  22ሺ 600 ሄክታር  መሬት ላይ የአፈርና ወሀ እቀባ ለማከናወን እየሰሩ  መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በስራውም ላይ ከ21ሺህ በላይ አርሶአደሮች እየተሳተፉ ሲሆን እስካሁን ከተከናወኑት መካከል በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዳ ከ2ሺ600 ሄክታር በላይ መሬት መከለሉ ይገኝበታል፡፡

"በክረምት ወቅቱ በተለያዩ የደን ችግኞችና የእንስሳት መኖ ለማልማት   ከ1ሺህ 800 ኪሎግራም በላይ የችግኝ ዘር ተዘርቶ እንክብካቤ እየተደረገለት ነው" ብለዋል፡፡

የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ  እንዳሉት በዞኑ የአፈርና ወሀ ጥበቃ ስራው ሳይጀመር በፊት ከአንድ ሄክታር የአርሶአደሩ ማሳ  በየዓመቱ እስከ 300 ኩንታል አፈር በጎርፍ ይሸረሸር ነበር፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ተፋሰስን ተከትሎ በአርሶአደሩ ተሳትፎ በተከናወነው  የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ  ከ713 ሄክታር በላይ የተጎዳን መሬት ማልማት ተችሏል፡፡

በዚህም   የአፈር መሸርሸርን በማስቀረት የመሬቱ ለምነት ከመጨመሩም በላይ  ከአርሶአደሩ የግብርና ፓኬጆችን የመጠቀም ባህል መዳበር ጋር ተደምሮ  በሁሉም ሰብሎች በአማካኝ ከ12 ኩንታል ወደ 30 ኩንታል አድጓል፡፡

በዞኑ   262 ቀበሌዎች  ካለፈው ወር አንስቶ እየተከናወነ ባለው   የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ከ200 በላይ ተፋሰሶችን ተከትሎ  130ሺ ሄክታር የሚሸፍን መሬት ለማልማት እየተሰራ ነው፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ  መጋቢት 1/2009 ሙስናን ለመቀነስ የወጣቶች የስነ ምግባር ማሻሻያ ስራዎችን ማከናወን ዋነኛ መሳሪያ መሆኑን የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።

ዛሬ አገር አቀፍ የጸረ ሙስና ጥምረት ስራ አስፈጻሚ መደበኛ ስብሰባ ተካሂዷል።

አገር አቀፍ የጸረ ሙስና ጥምረት የጸረ ሙስና ትግሉን ህዝባዊ ለማድረግ ታስቦ የተቋቋመ የኮሚሽኑ የህዝብ ክንፍ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ በ13 አደረጃጀቶች ስር 800 ጥምረትን ያቀፈ ነው።

የጥምረቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ 13ኛ መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሂድ አዲስ ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበሮችን ምርጫ አከናውናል። የ2008 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይም ተወያይቷል።

ኮሚሽነር አሊ ሱለይማን በወቅቱ እንደገለጹት፤ አንድ አገር ሙስናን ማስቀረት ባትችልም ለመቀነስ የሚከናወኑ ተግባራት ከተደራጀ የህዝብ ተሳትፎ ውጭ ውጤታማ ሊሆን አይችልም።

“አደረጃጀቶቹ በየዘርፉ ከራሳቸው አባላት ጀምሮ፣ መልካም ስነ ምግባር ላይ የሚሰጡት ትምህርትና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በየመድረኩ መሪውን ፊት ለፊት የሚጠይቅና ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚል ዜጋ እየፈጠረ ነው” ብለዋል።

ሆኖም ግን ችግሩን በዘላቂነት ለማቃለል ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ ለመፍጠር ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የበለጠ ስራ መሥራት እንዳለበት ገለጸዋል።

''የዚህ ዘመን ወጣት ጥሩ ሥነ ምግባር የተላበሰ አይደለም ብሎ ከመተቸት ባለፈ፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ መውረስ ያለባቸው ባህል ምንድን ነው፣ ምን ያህል ትምህርት ተሰጥቷቸዋል የሚለው ጉዳይ ብዙም ትኩረት አላገኘም'' ሲሉም ተናግረዋል።

ይህ እንዳይሆን ኮሚሽኑ ከጥምረቱ ጋር በመሆን ወጣቶች ላይ ያተኮሩ የተለያዩ መድረኮችን፣ ሥልጠናዎችንና የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮችን ለማዘጋጀት እቅድ መያዙን ተናግረዋል።

“አሁን በአገር ደረጃ እያስቸገረ ያለውን የመልካም አስተዳደርና የሙስና  ችግር ለመቀነስ የመጪው ትውልድ አስተሳሰብ ላይ መሰራት አለበት” የሚለውን ሃሳብ የተጋሩት የጥምረቱ የስራ አሰፈጻሚ አባላትም በተሰማሩበት የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።

በእስከ ዛሬ ሂደታቸውም አባሎቻቸውንም ሆነ ሰፊውን ህብረተሰብ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ቅድሚያ ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ በጥምረቱ አባላትም ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው የቁርጠኝነት ደረጃ ደግሞ ከዚህ በላይ መሆን አለበት ባይ ናቸው።

አገር አቀፍ የጸረ ሙስና ጥምረት ሙስናን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር የአመለካከት ለውጥን ለማምጣት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ስራዎችን በቅንጅት ለመስራት ታስቦ የተመሰረተ ነው። 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 1/2009 የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ውሳኔ ሰጭነት ለማሳደግ የሚያስችሉ መረጃዎችን በመስጠት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሴት ጋዜጠኞች ተናገሩ።

ሰራተኞቹ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን  አክብረዋል፡፡

ሰራተኞቹ በዓሉን ያከበሩት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ፣ አቅማቸውን ለማጎልበትና በተመደቡብት የስራ መስክ ተወዳዳሪ ሆነው መቀጠል በሚያስችሏቸው አቅጣጫዎች ላይ በመወያየት ነው፡፡

በርካታ ሴቶች የመስራትና የመለወጥ ዓቅም እያላቸው ምቹ ሁኔታዎች ባለማግኘታቸው ሰርተው ሳይለወጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ጋዜጠኛ አብነት ታደሰ የዘንድሮው የሴቶች ቀን ሲከበር "የሴቶች የቁጠባ ባህል ማደግ ለህዳሴያችን መሰረት ነው" በሚል መሪ ቃል በመሆኑ ለመቆጠብ የሚያነሳሳ በመሆኑ ሴቶች የራሳቸውን ኃብት እንዲያፈሩ የሚረዳ ነው ስትል ተናግራለች፡፡

"የቁጠባ ባህል ማደጉ ሰርተን አገራችንና ራሳችንን እንድንለውጥ በር የሚከፍት ነው" በማለት ሴቶች ያለባቸውን ተደራራቢ ኃላፊነት ለመወጣት የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ በር የሚከፍት ነው ብላለች፡፡

ሴቶች የመቆጠብ ልምዳቸው ትልቅ ቢሆንም ገንዘቡን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው በአብዛኛው የመረጃ እጥረት ይኖራል፤ ስለዚህም ወቅታዊና ጠቃሚ መረጃዎችን ለሴቶች በማድረስ እንሰራለን ነው ያለችው።

የሴቶችን አቅምና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም አርአያነትን የሚያሳዩ ዘገባዎችና ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማቅረብም በተሻለ ሁኔታ እንደምትሰራ ነው ቃል የገባችው፡፡

ሴት ልጅ በማንኛውም ዘርፍ ብትሰማራ መሪ፣ ውጤታማና አገርን ለመለወጥ የምትችል መሆኗን ለማመላከት እንደምትሰራም እንዲሁ።

ከመቆጠብ በፊት ገቢ ይቀድማል ያለችው ጋዜጠኛ አስቴር ታደሰ ደግሞ ሴቶች በመደራጀትና አሁን እየተፈጠሩ ያሉ የስራ እድሎችን በመጠቀም ራሳቸውን ከጠባቂነት ማውጣት የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚጠቁም መረጃ እንደምትሰጥ ነው የተናገረችው።

ሴቶች በማንኛውም የስራ መስክ ቢሰማሩ ውጤታማ ናቸው፤ ይህን ለማመላከት ደግሞ በስኬት ማማ ላይ የደረሱ ሴቶችን ልምድ በዘገባዬ ለማሳየት ጥረት አደርጋለሁ ብላለች፡፡

ሴቶች ወደ ውሳኔ ሰጭነት እንዲመጡና የመነሳሳት ስሜት የሚፈጥሩ መረጃዎችን በመስራት የውጤታማ ሴቶችን ተሞክሮ አሳያለሁ ስትል አክላለች።

በተቋሙ የውጭ ቋንቋዎች ዜና ዴስክ አስተባባሪ ቤተልሔም አበባው እንዳለችው የሴቶችን አቅም በትምህርት በማሳደግ የተለያዩ ስራዎች እንዲሰሩና እንዲለወጡ ለማድረግ ጅምር ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

 በተጨማሪ  በኤጀንሲው  የሚገኙ የሴት ጋዜጠኞችን አቅም በማሳደግ ወደ አመራርና ውሳኔ ሰጭነት ቦታዎች ለማምጣት እንደሚሰራም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ሙለታ በበኩላቸው መገናኛ ብዙኃን የሴቶችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የመፍታት ኃላፊነታቸው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።

በመሆኑም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በመከላከል ረገድ ሴት ጋዜጠኞች ያላቸውን አቅም ማጎልበትና ለውጥ ለማምጣት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

ሴቶችን የማብቃትና ወደ አመራር ሰጭነት ቦታዎች ማምጣት የሚያስችሉ ዘገባዎችን በጥራትና በተወዳዳሪነት መስራት እንደሚገባቸውም ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።

የዘንድሮው የሴቶች ቀን በዓል በዓለም ለ106 በኢትዮጵያ ደግሞ ለ41ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 1/2009 የመንገዶች ጥገና በሌሊት መካሄድ የትራፊክ ፍሰቱ እንዳይስተጓጎል በማድረጉ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል አሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው አንዳንድ የመዲናዋ አሽከርካሪዎች። 

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመንገድ ጥገናዎችን በሌሊት እያካሄደ ይገኛል።

በዚሁ መሰረት በተያዘው ዓመት ከመስከረም 26 ጀምሮ በሦስት ምዕራፍ በመከፋፈል የጥገና ስራው እየተከናወነ ነው። 

በመጀመሪያው ምዕራፍ የቀለበት መንገዱን መነሻ በማድረግ ሦስት አደባባዮች ፈርሰው 33 ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገና ተደርጓል።

በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከሳርቤት፣ ሜክሲኮ፣ ብሄራዊ ካዛንቺስ ስድስት ኪሎ፣ አራት ኪሎ እና አራዳ አካባቢ ያሉ መንገዶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

ከቄራ ጎፋ ላፍቶ ብሄር ብሄረሰቦች እንዲሁም ከኤድናሞል ወደ 22 የሚወስደው መንገድም በመጠገን ላይ ነው።

የኢዜአ ሪፖርተር በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች እንዳሉት የመንገድ ጥገናው በምሽት መደረጉ የትራፊክ ፍሰቱን እያሻሻለው ነው።

ጥገናው በሌሊት መደረጉ የትራፊክ ፍሰቱን ከማሻሻል ባለፈ በመኪና ዕቃዎች ላይ የሚደረሰውን ጉዳትም እንደቀነሰው ነው አሽከርካሪዎቹ የተናገሩት።

የመንገድ ጥገናው በምሽት መደረጉ የትራፊክ ፍሰቱ እንዲሳለጥ ከማድረጉ ባሻገር በመኪና አካሎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት እንዲቀንስ ማስቻሉን የሚናገሩት ደግሞ ሌላኛው የላዳ አሽከርካሪ አቶ ተፈሪ ወልደጊዮርጊስ ናቸው።

አሁን ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ለመፍታት የመንገድ ማስፋፊያ ግንባታ ላይ በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አመልክተዋል። 

የሚኒባስ ታክሲ አሽከርካሪ አቶ ሞጎስ ምህረቴ በበኩላቸው ከቦሌ ፒያሳ እንደሚሰሩ ገልጸው ''የመንገድ ጥገናው ሌሊት መደረጉ ጊዜና ነዳጅ መቆጠብ ያስችላል'' ነው ያሉት። 

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የራስ ኃይል መንገድ ጥገና ዳይሬክተር ኢንጂነር መኮንን ጥበቡ ጥገናው ከመጀመሩ በፊት የመንገድ ጉዳት መጠንን የሚያሳይ ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል።

በጥናቱ መሰረት የተለዩ ቦታዎች ላይ በቅደም ተከተል እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

''የምዕራፍ ሦስት የመንገድ ጥገናው ተጀምሯል'' ያሉት ዳይሬክተሩ ጥገናው መስቀል አደባባይ ቃሊቲ አቃቂ መስመር ዋና ዋና መንገዶችን ያካተተ ነው ብለዋል።

ጥገናውን ለማከናወን ሦስት ቡድን ተዋቅሮ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

''የመንገድ ጥገናው በአግባቡ እንዳይከናወን የትራፊክ መጨናነቅ ትልቅ እንቅፋት ፈጥሯል''ያሉት ኢንጂነር መኮንን ችግሩን ለመፍታት ከሰኞ እስከ አርብ ሌሊት እየተሰራ ነው፤ እሁድ ደግሞ በቀን ጥገናው እንዲከናወን እየተደረገ ነው ብለዋል። 

ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋቱ 1 ሰዓት ያለምንም ችግር ጥገናው እየተካሄደ መሆኑን የተናገሩት ኢንጂነሩ ስራው በተቀላጠፈ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ጥገናው ቀን በሚካሄድበት ወቅት በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት የሚደርሰውን አደጋ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።  

ጠጥተው የሚያሽከረክሩ ሹፌሮች መኖራቸው፣ የትራፊክ ምልክቱን አንስቶ ማለፍና ጥገናው በሚካሄድበት ቦታ ላይ መኪና አቁሞ መሄድ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ይገኙበታል።  

ለችግሮቹ እልባት ለመስጠት ባለሥልጣኑ የመንገድ ትራንፖርት ቢሮን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የመንገዶችን ጥገና ለማካሄድ ከመንገድ ፈንድና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 328 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን ተናግረዋል። 

በበጀት ዓመቱ 71 ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገና ለማድረግ ታቅዶ እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ እስካሁን 69 ኪሎ ሜትር ጥገና ተካሂዷል ብለዋል።  

ጥገናውን እስከ ግንቦት መጨረሻ ለማጠናቀቅ መታቅዱን በመጠቆም።

''በቀጣይ የመንገድ ጥገናውን በስፋት ለማከናወን የመንገድ ጉዳት መጠንን በጥናት የሚለይ ቡድን ተቋቁማል'' ያሉት ዳይሬክተሩ ጥገናው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 1/2009 ኢትዮጵያ ውስጥ ግንባታው ሲካሄድ የቆየውና መጠናቀቅ ካለበት ጊዜ ዘጠኝ ዓመት የዘገየው የካፍ አካዳሚ ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት ተመደበለት።

በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ሰሚት ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ (የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን) ካፍ አካዳሚ ግንባታው የተጀመረው በ1997 ዓ.ም ሲሆን፤ በእቅዱ መሰረት በሶስት ዓመት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቅ ነበር።

ይሁን እንጂ አካዳሚው በክትትል ማነስ ግንባታው እስከአሁን በመጓተት ላይ ነው።

ስራው ሲጀመር ካፍ የግንባታው ስራ ለግብፃውያን ተቋራጮች የሰጠ ቢሆንም፤ በተለያዩ  ምክያቶች ግንባታውን በማዘገየታቸውና በተፈለገው ጥራት ደረጃ ባለመስራታቸው ውሉ እንዲቋረጥ ተደርጓል። ከዚህ በኋላም ከአራት ዓመት በፊት ለኢትዮጵያውያን ተቋራጮች እንዲሰጥ ተደርጓል።

ኢትዮጵያውያን ተቋራጮች የጀመሯቸውን ህንጻዎች ያጠናቀቁ ቢሆንም የእግር ኳስ ሜዳው ግን “የውሃ ችግር ገጥሞናል” በሚል ምክንያት  ውላቸውን አቋርጠዋል።

አካዳሚው እስካሁን በነበሩት 12 ዓመታት የስፖርተኞች የመኝታ ክፍሎች፣ የስልጠና  ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ መጠናቀቅ ችለዋል።

ይሁን እንጂ  በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ ሳር ለመስራት የታሰበው ሁለቱ የእግር ኳስ ሜዳዎች ገና በጅምር ላይ ናቸው።

በኢትዮጵያ እየተገነባ ካለው የካፋ አካዳሚ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ የተጀመረው የካሜሮን አካዳሚ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ከገባ ከሁለት ዓመት በላይ አስቆጥሯል።

የካሜሮን አካዳሚ ሶስት የእግር ኳስ ሜዳ፣ የሥልጠና አዳራሽና የመኝታ ክፍሎች፣ ከጅምና መዋኛ ገንዳ በተጨማሪ ሳውና፣ ስቲም ጃኩዚ ሌሎች መሰል ነገሮችን ያሟላ ነው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ እንደገለጹት፤ አካዳሚው የዘገየው በካፍ ኃላፊዎችና እና በኢትዮጵያ የካፍ ተወካይ አቶ ሳህሉ ገብረወልድ የክትትል ማነስ የተፈጠረ ችግር እንደሆነ ነው የተናገሩት።

''አካዳሚው ከመዘግየቱም በተጨማሪ  የጥራት ችግር አለበት፤ ይህንም በካፍ በኩል የተማመንበት ነው'' ብለዋል።

አቶ ወንድምኩን እንደተናገሩት፤ በቀጣይ ይህን ለማስተካከልና ተጨማሪ  የውሃ መዋኛ ገንዳ፣ ጅምና ሌሎች ማዘውተሪያ ቦታዎች አካቶ ለመስራት በካፍ በኩል በጀት ተመድቧል።

ለዚህም በካፍ በኩል ከአራት ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞለታል።

በኢትዮጵያ የካፍ ተወካይ አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ከዚህ በፊት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ግንባታው የዘገየው በግብጻውያን ተቋራጮች ችግር ምክንያት መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵውያን ተቋራጮች በኩል ደግሞ በአካባቢው በነበረው የውሃ ችግር ምክንያት የእግር ኳስ ሜዳውን ሳይሰሩ ውላቸውን ማቋረጣቸውን ነው የተናገሩት።

ከዚህ በፊት "ምን ያህል ገንዘብ ወጪ ተደርጎበታል?" ላልናቸው ጥያቄ በካፍ ተወካይ በአቶ ሳህሉ ሆነ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በኩል የሚያቁት ነገር እንደሌለ ነው የተገለጸው።

ወጪው ምን ያህል እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም ሙሉ በሙሉ በካፍ የሚሸፈን መሆኑ ይታወቃል፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም የመሬት አቅርቦትና ለግንባታው የሚውሉ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ድጋፍ አድርጓል።

ካፍ በኢትዮጵያ እያስገነባው ያለው የስፖርት አካዳሚ ሲጠናቀቅ በዋናነት በመካከለኛውና ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የእግር ኳስ ውድድሮች ያደርጉበታል ተብሎ ይታመናል። እንዲሁም “የስፖርተኞች የዳኞችና የስፖርት አስተዳደር ስልጠና እና  ማደሪያ ይሆናል” ተብሎ ይጠበቃል።

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ  መጋቢት1/2009 አገራዊ የቴሌኮም ሽፋንና የኔትወርክ አገልግሎት በኃይል እጥረት እንዳይቋረጥ የተለያዩ አማራጮችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ።

አማራጮቹ ተቋሙ በፋይበር ኦፕቲክ ገመዶች ኤሌክትሪክ መቆራረጥና በኃይል ሰጪ አንቴናዎች ኃይል እጥረት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላሉ ተብሏል።

ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞቹ ቁጥር 52 ነጥብ 9 ሚሊዮን መደረሱንም ተጠቁሟል።

የኢትዮ- ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ አብዱራሂም አህመድ የተቋሙን የስድስት ወር አፈጻጸም አስመልክተው ለኢዜአ የእንደገለጹት፤ የአገሪቷ የቴሌኮም ሽፋንና የአገልግሎት ዓይነት እያደገ ቢመጣም በኃይል እጥረት የአገልግሎት መቆራረጥና የኔት ወርክ መጨናነቅ ያጋጥማል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ በ 35 አቅጣጫዎች የሚገኙ ከ 14 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የፋይበር ኦፕቲክ ገመዶች በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ “የኃይል እጥረት ሲያጋጥም አገልግሎቱ ይቋረጣል” ብለዋል።

በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ኃይል ሰጪ አንቴናዎች “የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያንሳቸው ለደንበኞች የሚሰጡት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ይቋረጣል" ነው ያሉት።

በፋይበር ኦፕቲክ ገመዶችና ኃይል ሰጪ አንቴናዎች በሚስተዋለው የኃይል እጥረት  ከደንበኞች የሚሰማውን ቅሬታ በዘላቂነት ለመፍታትና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ አማራጭ መንገዶች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

በመሆኑም የፋይበር ኦፕቲክ ገመዶችንና ኃይል ሰጭ አንቴናዎችን እንዲጠብቋቸው “ለክልሎች መንግስታት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል” ብለዋል።

“መስመሮቹ በማንኛውም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ተጠባባቂ መስመር አላቸው” ብለዋል አቶ አብዱራሂም።

በመሆኑም  በኃይል መቆራረጥ አገልግሎቱ ለተወሰነ ጊዜ የኔት ወርክ መጨናነቅ ይታይበት ይሆናል እንጂ ሙሉ በሙሉ እንደማይቆራረጥ  አቶ አብዱራሂም ተናግረዋል። 

ከኃይል መቆራረጥ በተጨማሪ ተቋሙንና አገሪቷን ገቢ ከማሳጣት ባለፈ የደህንነት ስጋት እየሆነ የመጣው የቴሌኮም ማጭበርበር መሆኑን አስረድተዋል።

የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሉ በዓመት ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዬን ብር በላይ ሊያሳጣት እንደሚችል የገለጹት አቶ አብዱራሂም፤ ችግሩን ለመከላከል ከኅብረተሰቡ፣ ከደህንነት መስሪያ ቤት፣ ጸጥታ ኃይሎች፣ ከክልል መንግስታትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮ ቴሌኮም በመላ አገሪቷ ከ52 ነጥብ 9 ሚሊዬን በላይ የሞባይል፣ የኢንተርኔት ዳታና የመደበኛ ስልክ ደንበኞች እንዳሉት ገልጸዋል።

ተቋሙ በአገልግሎትም በስድስት ወር ውስጥ 11 ነጥብ 9 ቢሊዬን ብር ያልተጣራ ትርፍ አግኘቷል።

ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ18 በመቶ እድገት ማሳየቱን ነው ከተቋሙ የተገኘው መረጃ የሚያሳየው። 

ኢትዮ - ቴሌኮም  ባለፉት  ስድስት ወራት 13 አዳዲስ ምርትና አገልግሎት ለተጠቃሚዎች አቅርቧል።

ከእነዚህም አዳዲስ አገልግሎቶች መካከል በመደበኛና በሞባይል ስልክ ገቢራዊ የሚደረጉ ወርኃዊ ጥቅል አገልግሎቶች ሲሆኑ፤ በዋነኝነት ድምጽን መሰረት ያደረጉ አገልግሎቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን ያመለከቱት ኃላፊው፤ የቴሌኮም ምርትና አገልግሎቶች ለተጠቃሚ ኅብረተሰብ በማዳረስ የቴሌኮም አማራጮችን የማስፋፋት ሥራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

ጅግጅጋ  መጋቢት 1/2009 ከአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ድርቅ በተከሰተባቸው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አካባቢዎች አስቿኳይ የሕክምና እርዳታ በበጎ ፈቃደኝነት ለመስጠት መሰማራታቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የበጎ ፍቃደኛ የጤና ባለሙያዎች ልኡካን ቡድኑ በደጋህቡርና ቆራሃይ ዞኖች ለሚገኙ በድርቁ ለተጎዱ ነዋሪዎች የሕክምና እርዳታ ለመስጠት ከትናንት ጀምሮ ወደተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መንቀሳቀሳቸውን ተናግረዋል፡፡

27 አባላትን የያዘው የልዑካን ቡድን ከትናንት በስቲያ ጅግጅጋ ከተማ ሲደርስ የክልሉ ምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ መሀመድ ረሼድና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

የቡድኑ አባላት ከዛሬ ጀምሮ በአራት ንኡሳን ቡድን በመከፈል በወረዳዎቹ በአካል በመገኘት የሕክምና ድጋፍ የማድረግ ሥራቸውን እንደጀመሩ  ተመልክቷል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀሰን ኢስማኤል ለኢዜአ እንደተናገሩት ከድርቅ አደጋ ጋር ተያይዞ ካለፈው ጥር ወር መጀመሪያ በክልሉ 14 ወረዳዎች የተከሰተው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) በሽታን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

በበሽታው እስካሁን 920  ሰዎች መጎዳታቸውን ገልጸው፣ የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከል ከሚሰጠው የጤና አገልግሎት በተጨማሪ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለእዚህም ከክልሉ ውሃ ቢሮ፣ ከእንስሳትና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች እንዲሁም ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የተውጣጡ አባላትን የያዘ ኮሚቴ ተቋቁሞ በተለያዩ ወረዳዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የበጎ ፍቃድ የሕክምና ቡድኑ አስተባባሪ አቶ መንበሩ ፍጹም እንዳሉት የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ግለሰቦችን ያቀፈው ቡድን ከአተት ጋር በተያያዘ ለሁለት ሳምንታት የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡

የሕክምና ቡድኑ በክልሉ በሚኖረው ቆይታም 12 ሺህ ሰዎችን ተደራሽ እንደሚያደርግ ተናግረው፣ እንደ በሽታው የመስፋፋት መጠን ከሁለት ሳምንት በላይ በክልሉ ሊቆይ እንደሚችልም አመልክተዋል።

"በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚከሰት ችግር የአማራ ችግር ነው" ያሉት አስተባባሪው፣ ቡድኑ ለአርብቶአደር ነዋሪዎች የሕክምና አገልግሎት በመስጠት በበሽታው የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ቡድኑ ከሕክምና ባለሙያዎች በተጨማሪ በክልሉ በሚቆይበት ጊዜ ድጋፍ ለማድረግ የሚያግዙትን አንድ አንቡላንስና አንድ የውሃ ማመላለሻ ቦቴ መኪና ይዞ መምጣቱን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

ከሕክምና ቡድኑ አባላት መካከል ከአማራ ክልል ዳንግላ ዙሪያ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የመጡት አቶ አልማ ገነት በሰጡት አስተያየት በፍቃደኝነት ሙያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት መምጣታቸውንና በእዚህም ደስታ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡

የሕክምና ቡድኑ  የአተት በሽታ በተከሰተባቸው የክልሉ ወረዳዎች ከመደበኛ የጤና ባለሙያዎች በተጨማሪ ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲና ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ 300 የጤና ባለሙያዎች የጀመሩትን ጥረት ያጠናክራል፡፡ 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን