አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 01 March 2017

አዲስ አበባ የካቲት 22/2009 የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለመግዛት ካቀድኩት የ5 ሚሊዮን ብር ቦንድ 70 በመቶውን አሳክቻለሁ አለ።

የቦንድ ግዥውን የፈጸመው የግድቡ መሰረት የተጣለበትን 6ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መሆኑንና የዕቅዱ ቀሪ 30 በመቶ ከነገ በስቲያ እንደሚጠናቀቅ አስታውቋል።

የቢሮው የወጣቶች ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ዮናስ አረጋይ እንደተናገሩት የመላ ኢትዮጵያውያን አሻራ የሆነውን የህዳሴ ግድብ ከዳር ለማድረስ ከቦንድ ግዥ ባሻገር ለወጣቶች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ ነው።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በመዲናዋ በሚገኙ 107 የወጣትና የስፖርት ማዕከላት፣ በቢሮው ሠራተኞችና በስፖርት ፌደሬሽኖች የቦንድ ግዥ እየተፈጸመ ነው።

በተጨማሪም ወጣቶች ስለ ግድቡ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው በእኔነት ስሜት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የማስገንዘብ ስራ እየተሰራ ነው።

በከተማዋ ከሚገኙ 117 ወረዳዎች የሚውጣጡና ግድቡን ያልጎበኙ 585 ወጣቶች እንዲጎበኙ ይደረጋልም ብለዋል አቶ ዮናስ።

የግድቡ መሰረት የተጣለበትን 6ኛ ዓመት በተለያዩ የስፖርት ውድድሮች ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

መቐለ የካቲት 22/2009 በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን መደባይ ዛና ወረዳ በ39 ሚሊዮን ብር ወጪ  የትምህርት፣ የጤናና የመስኖ ልማት ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት ተዘጋጁ፡፡

ተቋማቱ  በክልሉ ርዕሰ  መስተዳድር  አባይ ወልዱ ተመርቀዋል።

የተገነቡትም  በመንግስት ፣ በትግራይ ልማት ማህበርና በሌሎች መንግስታዊ ባልሆኑ  ድርጅቶች ትብብርና ድጋፍ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በምረቃው ስነስርዓት ላይ  የትግራይ ልማት ማህበር ፈፃሚ ዳይሬክተር ዶክተር ታደለ ሓጎስ እንደገለጹት ተገንብተው ለአገልግሎት ከተዘጋጁት መካከል አራት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ሁለት የህክምና ተቋማት ይገኙበታል፡፡

ተቋማቱ ከ40 ሺህ በላይ የሚበልጡ  የወረዳውን ነዋሪዎች የተጠቃሚነት የሚያድርጉ ናቸው።

ርዕሰ መስተዳድር አባይ ወልዱ በበኩላቸው  መንግስት ከህዝቡና መንግስታዊ ካልሆኑ ደርጅቶች ጋር በመተባበር በአካባቢው ያለውን የመሰረተ ልማት እጥረት ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በቅርቡ ለህዝቡ አገልግሎት የሚውል አዲስ አንቡላንስ  እንደሚሰጥም ቃል ገብተዋል።

አይካ የተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ዳይሬክተር ሚስተር ፔሪ ሄቬን ለተቋማቱ ግንባታ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው በቀጣይ በሚካሄዱ የልማት ተግባራት ላይ ከመንግስትና ከህብረተሰቡ ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በወረዳው  የኩብርቶ ቀበሌ ነዋሪዋ  ወይዘሮ  ዓደይ አርአያ በሰጡት አስተያየት  በአቅራቢያቸው የጤና ተቋም ባለመኖሩ ስምንት ሰዓት በእግር ተጉዘው ይታከሙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አሁን  በአቅራቢያቸው በመሰራቱ ይደርስባቸው የነበረውን እንግልትና ችግር  እንደሚያስቀርላቸው ተናግረዋል፡፡ 

ተማሪ አባዲት ተክሉ የዓዲ ባዕረድ  ቀበሌ ነዋሪ ስትሆን  አቅራቢያቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ  ትምህርቷን በወረዳው ማዕከል ሰለኽለኻ ከተማ ለመማር መገደዷን ተናግራለች፡፡

በአቅም ችግር ምክንያት ርቀው መማር ያልቻሉ ደግሞ  ከስምንተኛ ክፍል በኋላ ትምህርታቸውን እንደሚያቋርጡ  ጠቅሳ አሁን በአቅራቢያቸው በመከፈቱ  የነበረው ችግር እንደሚፈታ ተናግራለች፡፡

ወይዘሮ አልጋነሽ ካህሳይ በበኩላቸው" በቀበሌያችን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ሁለት ሴት ልጆቼ ከስምንተኛ ክፍል በኋላ አቋርጠው  እንዲዳሩ አርጌያለሁ "ብለዋል፡፡

ትዳር እንዲመሰርቱ ያደረጉት  ከቤተሰብ ተለይው ርቀው ከሄዱ ተታለው እንዳይጎዱባቸው  በማሰብ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

"ዛሬ በአቅራቢያችን  ትምህርት ቤት በመሰራቱ ወላጆች ስጋት የለባቸውም፤ ሴት ልጆቻቸውን ከአጠገባቸው ሳይለዩ ያለምንም ስጋት ለማስተማር ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል" ብለዋል

Published in ኢኮኖሚ

አክሱም  የካቲት 22/2009 የአድዋ ከተማና አካባቢዋን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በሦስት እጥፍ ለማሳደግ የሚያስችል ተጨማሪ የውሃ ማጣሪያ ግንባታ ሥራ እየተካሄደ ነው።

የውሃ ማጣሪያ ግንበታ ሥራ እየተከናወነ ያለው ቀደም ብሎ በተገነባውና ለከተማዋ አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኘው ምድማር ግድብ አቅራቢያ ነው።

የከተማው የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ገብረእግዝአብሔር ለኢዜአ እንደገለጹት የውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክቱ እየተከናወነ ያለው የክልሉ መንግስት በመደበው 300 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ነው፡፡

አሁን ያለው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ከከተማው ነዋሪ ህዝብ ብዛትና በአካባቢው ካሉ የጨርቃ ጨርቅ፣ የእምነበረድና ሌሎች ፋብሪካዎች ፍላጎት አንጻር በቂ አይደለም ፡፡

አቶ ካሳሁን እንዳሉት፣ የአክሱም ከተማ ነዋሪዎችም የንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት የሚያገኙት 23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው ምድማር ግድብ ነው፡፡

በመሆኑም የግድቡን ውሃ በማጣራት የሚያሰራጨው ነባሩ የውሃ ማጣሪያ አቅሙ ውስን በመሆኑ የከተማዋን ዕድገት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተጨማሪ የማጣሪያ ፕሮጀክት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ አሁን ነበሩ ማጣሪያ በሰዓት የሚያጣራውን 380 ሜትር ኩብ ውሃ ወደ 875 ሜትር ኩብ ከፍ እንደሚያደርገው ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ይህም አሁን በአድዋ ከተማና አካባቢው ያለውን  የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት እንደሚፈታ ነው ያመለከቱት ፡፡

በ2007 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ፕሮጅክት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ የነበረበት ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የግንባታው አፈጻጸም 75 በመቶ ብቻ መሆኑን አቶ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡

ከውጭ የሚመጡ የመገጣጠሚያና የውሃ ቱቦዎች በተለያዩ ምክንያት በወቅቱ ወደአገርውስጥ አለመድረሳቸው ለግንባታው መዘግየት ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሮመካኒካል ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ጠቁመው፣ ማጣሪያው በሚቀጥለው ዓመት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አመልክተዋል፡፡

በእዚህም የአድዋና የአክሱም ከተማ ነዋሪዎችን ጨምሮ በአካባው የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በቂ የንፁህ መጠጥ ውሀ ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የነዋሪውን የነፍሰወከፍ የውሀ አቅርቦትም በቀን አሁን ካለበት 52 ሊትር ውሃ ወደ 80 ሊትር ከፍ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ካሳሁን አስረድተዋል።

በአድዋ ከተማ የምዕባለ ቀበሌ ነዋሪ መምህርት ሽሻይ ብርሃኑ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የሚኖሩበት አካባቢ ዳገታማ በመሆኑ ውሃ በበቂ ሁኔታ እያገኙ አይደለም፡፡

እየተሰራ ያለው የውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የውሃ አቅርቦቱ ይሻሻል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

"ከግድቡ ነዋሪውን ጨምሮ የተለያዩ ፋብሪካዎችና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ተጠቃሚ በመሆናቸው የማጣሪው ፕሮጀክቱ ቀድም ብሎ ሊሰራ ይገባ ነበር" ያሉት ደግሞ በከተማው የአሉላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገዛኢ በላይ ናቸው።

የውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክቱ እስካሁን ተጠናቆ ለአገልግሎት ባለመብቃቱ  እርሳቸውን ጨምሮ በሕብረተሰቡ ላይ ቅሬታ መፍጠሩን ተናግረዋል  ፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 22/2009 ዘላቂ የትምህርት ቤቶች ምገባ ፕሮግራምን እውን ለማድረግ የባለ ድርሻ አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ አሳሰቡ።

የአፍሪካ ትምህርት ቤት ህጻናትና ወጣቶችን የመመገብ ቀን "በአገር በቀል የትምህርት ቤቶች ምገባ፣ በወጣቶችና በህጻናት ላይ ኢንቨስት በማድረግ የስነ-ሕዝብ ትሩፋቶችን እንቋደስ" በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል።

ቀዳማዊት እመቤቷ በአፍሪካ ለ2ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮከበ ጽባህ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህትር ቤት በተከበረው ዓመታዊ በዓል ታድመዋል።

"ትምህርት ቤቶቻችን ደረጃቸውን የጠበቁና ምቹ አካባቢዎች እንዲሆኑ ወጣቶችና ህጻናትን በዘላቂነት መመገብ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ተማሪዎችን የመመገብ ሂደትን ዘላቂነትን ለማረጋገጥ በአንድነት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሺፈራው ተክለ ማርያም በበኩላቸው "ዛሬ ለተማሪዎች በምናወጣው ወጪ የነገ አገር ተረካቢዎች ጤናማና ምርታማ እንዲሆኑ መስራት አቻ የሌለው ተግባር ነው" ብለዋል።

በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናቸውን ያላረጋገጡ ዜጎች በመኖራቸው አገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራምን መተግበር ተገቢ መሆኑንም አመልክተዋል።

"የአፍሪካ የትምህርት ቤቶች ምገባ ቀንን ስናከብር በራስ አቅም፤ በአገር በቀል ኃብት ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የሚረባረቡበትን ስልት በመቀየስ እንሰራለን" ብለዋል ሚኒስትሩ።

በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የትምህርት ቤት ምግባ ፕሮግራም እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ናቸው።

በአዲስ አበባ በሚገኙ 206 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 20 ሺህ 46 ተማሪዎች ከእናት ወግ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር የምግብ አቅርቦት ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የትምህርት ቤት ምገባው ቀጣይነት እንዲኖረው አገር አቀፍ የትምህርት ቤት ምገባ ስትራቴጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

"በአገር ውስጥ የተመረተ ምግብ በትምህርት ቤቶች ማቅረብ ዘላቂና ብሄራዊ የትምህርት ቤት ምገባ እንዲኖር ያስችላል" ያሉት ደግሞ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ ናቸው።

ይህም ለአርሶ አደሮች የገበያ ትስስር በመፍጠር ገቢያቸውንና የምግብ ዋስትናቸውን በማረጋገጥ ለኢኮኖሚያዊ እድገቱ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

አገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሙን ከግብርናው ጋር በማስተሳሰር ዘላቂ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 22/2009 ወደ ደቡብ ሱዳን ለግንባታ የሚውል ብረት ጭነው ገብተው የነበሩ 23 ሲኖትራክና ገልባጭ ተሽከርካሪዎች ከሶስት ዓመት ተኩል በኋላ ለባለንብረቶቹ ተመለሱ።

ተሽከርካሪዎቹ ለባለንብረቶቹ የተመለሱት በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን መንግስታት ጥረት መሆኑን ባለንብረቶቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ተሽከርካሪዎቹ ወደ ስፍራው የተጓዙት የግንባታ ብረት ለማድረስ ቢሆንም በወቅቱ ደቡብ ሱዳን ውስጥ በተፈጠረው የእርስ በእርስ ግጭት ሳቢያ መመለስ ሳይችሉ ቆይተዋል።

ከባለንብረቶቹ አንዱ የሆነው ወጣት ደምሴ ጽጌ በኮንስትራክሽን መሳሪያዎች ማከራየት ስራ ለመሰማራት ከአንድ ባንክ ብድር ወስዶ  ሲኖትራኮችን በመግዛት ወደ ስራ መግባቱን ተናግሯል።

በወቅቱ ተሽከርካሪዎቹ በጭቃ ተይዘው ለማስወጣት ጥረት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ በአካባቢው የእርስ በእርስ ግጭት በመቀስቀሱ ሊመለሱ እንዳልቻሉ ነው የገለጸው።

በዚህ ምክንያት ለባንኩ ብድሩን መመለስ ባለመቻሉ ቤትና ንብረቱን ለመሸጥ በመገደዱ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያው ችግሮች መጋለጡን ነው የተናገረው።

መንግስት ተሽከርካሪዎቹን ለማስመለስ ከባለሃብቶቹ ጎን በመቆም ላደረገው ያላሰለሰ ጥረትም ምስጋና አቅርቧል።

ሌላው ባለንብረት አቶ ካሳ ኑሩ በበኩላቸው በተጠቀሰው ዓመት ንብረታቸውን ለማስመለስ በገጠማቸው ውጣ ውረድ ራሳቸውንና አገራቸውን የሚጠቅሙበትን ጊዜ ማባከናቸውን ገልጸዋል።

የተሸከርካሪዎቹ መመለስ የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጎልበት ያሳያልም ብለዋል፡፡

በመንግስት ድጎማ ከቀረጥ ነጻ ሲኖትራክ ገዝተው ወደ ስራ ቢገቡም ህይወታቸውን በተረጋጋ ሁኔታ መምራት ተስኗቸው እንደነበር የሚናገሩት ሌላዋ ባለንብረት ወይዘሮ ማርታ ኃይሌ ናቸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች አካላት ባደረጉት ጥረት ንብረታቸው መመለሱን ተናገሩት ባለንብረቷ "በተናጠል ያደረግነው ጥረት ንብረቶቻችንን ለማስመለስ ረጅም ጊዜ ወስዶብናል" ብለዋል።

ባለንብረቶቹ ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣባቸውን ተሽከርካሪዎች ለማስመለስ በተለያየ ጊዜ ወደ ደቡብ ሱዳን በመመላለስ ገንዘብና ጊዜያቸውን ማጥፋታቸውን ጠቁመዋል።

በእርስ በእርስ ግጭቱ ሶስት ተሽከርካሪዎች የተቃጠሉ ሲሆን ያልተመለሱ ሁለት ተሽከርካሪዎች መኖራቸውም ተገልጿል።

ባለንብረቶቹ ካርቱምና ጁባ ለሚገኙ ኤምባሲና ሚሽነሪዎች፣ ለገቢዎችና ጉምሩክ፣ ለገንዘብና ኢኮኖሚና ለሌሎቹ ተቋማት የትብብር ደብዳቤ ተጽፎላቸው ንብረታቸው እንዲመለስ መደረጉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

Published in ኢኮኖሚ

አክሱም የካቲት 22/2009 የቁጠባና የብድር ህብረት ስራ ማህበራት የሚሰጧቸው አገልግሎት ሀብት ለማፍራት እገዛ እንዳደረገላቸው የትግራይ ማዕከዊ ዞን  አንዳንድ አርሶ አደሮች ገለፁ፡፡

በዞኑ አድዋ  ወረዳ  የወረርባ የቁጠባና የብድር ህብረት ስራ ማህበር መልካም ተሞክሮውን በሶስት ወረዳዎች ለሚገኙ ተመሳሳይ ማህበራት አካፍሏል፡፡

ዲያቆን ወልደሃወርያ አረጋዊ  በአድዋ ወረዳ  የደብረ ገነት ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት ወረርባ በተባለው ማህበር በኩል  በየወሩ ዘጠኝ ብር በማስቀመጥ የጀመሩት ቁጠባ እያደገ ውጤታማ እንዳደረጋቸው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡ 

በወቅቱ ምንም ጥሪት እንዳልነበራቸው የገለፁት አርሶ አደሩ አሁን 24 ፍየሎችና አራት የወተት ላሞች ባለቤት እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡

የነበረባቸውን የብድር ገንዘብ ለማህበሩ በመመለስ  አሁን  ከ15ሺህ ብር በላይ ተቀማጭ እንዳላቸውም ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም  በንብ ማነብ ሰራ ለመሰመራት ለዘመናዊ የንብ ቆፎ መግዣ ከማህበሩ 10ሺህ ብር ለመበደር  ዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በመረብ ለኸ ወረዳ የበሪሀ ቀበሌ ገበሬ  ነዋሪ ወይዘሮ ሓረጉ ገብረማርያም በበኩላቸው ከስድስት ዓመታት በፊት በ20 አባላት የተመሰረተው ማርታ የቁጠባና ብድር ማህበር አባል መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአስር ብር የጀመሩት ቁጠባ እየጨመሩ በተጓዳኝም ከማህበሩ ብድር ወስደው በተሰማሩበት የንግድ ስራ በሚያገኙት ገቢ  አራት ልጆቻቸውን በተገቢው  ለማስማር እንዳገዛቸው ገልፀዋል፡፡

" መቆጠብ ባልጀምር   ልጆቼን  ለማስተማር ያቅተኝ ነበር፤ አሁን በቁጠባ ያስቀመጥኩት ገንዘብ  ከ14ሺህ ብር በላይ  ሆኗል"ብለዋል፡፡

በወረዳው የአዲፍታው ቀበሌ  ነዋሪ አርሶ አደር ይሕደጎ ታረቀ እንዳሉት ደግሞ  ከስምንት ዓመታት  በፊት በአስራ አንድ  አርሶ አደሮች የተመሰረተው  የሸዊት የቁጠባና ብድር  ማህበር አመራር ኣባል መሆናቸውን ተናግረው  አሁን  ህፃናት ቆጣቢዎችን ጨምሮ ዘጠኝ መቶ አባላት እንዳሏቸው ገልጸዋል፡፡

እሳቸውን ጨምሮ የማህበሩ አባላት  በቆጠቡት ገንዘብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው ማህበሩ ገዝቶ የሚያቀርባላቸው የምርት ማሳጊያ ግብአት ረዥም መንገድ  መጓዝን እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል፡፡

የእርሻ በሬ የሌላቸው አርሶ አደሮች ማህበሩ በሚያመቻችላቸው ብድር የእርሻ በሬ በመግዛት  ማህበሩ የሃብት ባለቤት እንዲሆኑ እያገዛቸው መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የወረርባ የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበርን እንቅስቃሴ የጎበኙት አርሶ አደሮች እንዳሉት ቋሚ የሂሳብ ሰራተኛ፣የሂሳብ መዝገብና ሌሎች አሰራሮች  በማህበራቸው ያልተለመዱ ስራዎች ናቸው፡፡ 

በጉብኝታቸው ወቅት ያገኟቸውን መልካም ተሞክሮዎች ወደ ራሳቸው በመውሰድ  እንደሚጠቀሙባቸውም ተናግረዋል፡፡

በአድዋ ወረዳ የህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት የህብረት ሰራ ማህበራት ባለሙያ አቶ ሳምሶን አለም በበኩላቸው  ወረርባ ማህበር ከሌሎች ለየት የሚያደርገው  የካፒታል መጠኑን ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ማሳደጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በወረዳው የሚገኙ የ1ሺህ 565 የቀበሌዎች  አርሶ አደሮች የማህበሩ አባላት ሆነው ባስመዘገቡት ውጤት ጭምር የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ማህበሩ  ከፌደራል እና ክልል መንግስት ሞዴል በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ነው፤ ልምዱንም ወደ ሌሎች ተመሳሳይ ማህበራት ለማስፋት የሶስት ወረዳ ህብረት ስራ ማህበራት አመራር አባላትን ተሞክሮ እንዲወስዱ መደረጉን አቶ ሳምሶም ገልፀዋል፡፡

ማህበሩ ባለው የተሻለ ካፒታል በአከባቢው ለሚገነቡ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች፣ ለተቸገሩ ህፃናት እርዳታ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ  በ100ሺህ ብር  ለህዳሴ ግድብ  ግንባታ ቦንድ በመግዛትም  ቀዳሚ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በዞኑ  አስተዳደር የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ተክለጀወርግስ አሰፋ  በዞኑ ከሚገኙ  238 የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ባለፉት ስድስት ወራት  ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ከአባል አርሶ አደሮች መቆጠቡን  ተናግረዋል፡፡

ለአባላትም ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ  ብድር ማከፋፈላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ   የካቲት  22/2009  በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመኑ ማጠቃለያ አገራዊውን የግብርና ምርት መጠን 594 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር ገለጸ።

ለዕቅዱ ስኬት አርሶ አደሮች በዘመናዊ የማምረቻ መሳሪያዎች እንዲጠቀሙ ማድረግ ትኩረት ተሰጥቶታል ተብሏል። 

ይህ የተባለው የመጀመሪያው የግብርና ሜካናይዜሽን ቀን "የግብርና ሜካናይዜሽን ለላቀ፣ መሬት የጉልበትና የሌሎች ግብዓቶች" በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው አውደ ርዕይ መክፈቻ ላይ ነው።

ሚኒስትሩ ዶክተር እያሱ አብርሃ እንደተናገሩት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተከናወነው ተግባር አገራዊ የምርት መጠኑን 270 ሚሊዮን 396 ሺህ ኩንታል ማድረስ ተችሏል።  

በሁለተኛው የዕድገትና ትራስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ የምርት መጠኑን 594 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስም በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ዕቅዱን ለማሳካት አሁን ያለውን የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሻሻል ይገባል" ያሉት ሚኒስትሩ መንግስት ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል። 

የምርት ብክነትን በመከላከል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ስልቶች ተቀይሰው እየተተገበሩ መሆኑን ነው ዶክተር እያሱ ያብራሩት።

50 በመቶ የማሳ ዝግጅት በትራክተር፣ 60 በመቶ የምርት አሰባሰብ በኮምባይነርና በሞተር በሚሰሩ አነስተኛ መውቂያ መሳሪያዎች መጠቀምን ከሚተገበሩ ስልቶች መካከል ጠቅሰዋል።

በዘርፉ ለተቀመጠው ግብ ስኬት ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል ሚኒስትሩ።

የሚኒስቴሩ የግብርና ሜካናይዜሽን ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ሀብቴ በበኩላቸው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የአመራረት ሂደት የምርት ብክነትን በመቀነስ መጠኑን በ30 በመቶ ያሳድገዋል ይላሉ። 

"በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በግብርና ሜካናይዜሽን ዘርፍ ጨቅላ የሚባል ደረጃ ላይ ነች" ሲሉም ገልጸውታል።

ችግሩን ለማቃለል በግለሰብ እጅ የሚገኙ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን በተለያዩ ክልሎች በማዘዋወር አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

እንደ አቶ ታምሩ ገለጻ በሚቀጥሉት ዓመታት የምርት ብክነት መጠንን ወደ አምስት በመቶ ለማውረድ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች መደራጀታቸውንና በተያዘው የምርት ዘመን የሙከራ አገልግሎት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ወጣቶቹ የሜካናይዜሽን ኢንጂነሪንግ፣ የኢኮኖሚክስ፣ የአግሮኖሚና በቴክኒክና ሙያ የአውቶ መካኒክ ባለሙያዎች እንደሆኑም ጠቅሰዋል አቶ ታምሩ።

የዘመናዊ ግብርና መሳሪያ አቅርቦት እጥረቱን ለማቃለል ከባለኃብቶች፣ ዩኒየኖችና ክልሎች ጋር በጥምረት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።

"በዘርፉ አርሶ አደሩን በስፋት ተጠቃሚ ለማድረግ ለአነስተኛ ይዞታ የሚሆኑ መሳሪያዎች በምርምር በማውጣት ተደራሽ ማድረግ ይገባል" ያሉት ደግሞ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ታፈሰ ገብሩ ናቸው። 

ኮርፖሬሽኑ ለአርሶ አደሮች የሜካናይዜሽን መሳሪዎችን ለማቅረብ ከእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር ጋር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ዘመናዊ ትራክተሮች፣ የሰብል መውቂያ፣ መዝሪያ፣ መስመር ማውጫና ሌሎች መሳሪያዎች ለእይታ የቀረቡበት አውደ ርዕይ ለሦስት ቀናት ክፍት ሆኖ ይቆያል። 

በአውደ ርዕዩ 20 የግል አነስተኛ የግብርና ሜካናይዜሽን አምራቾች፣ ዩኒየኖች፣ አስመጪዎችና የውጭ ኩባንያዎች እየተሳተፉ ነው።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ የካቲት 22/2009 የአገሪቱን የሕዳሴ ጉዞ በማረጋገጡ ሂደት ውስጥ መንግስትና የሃይማኖት ተቋማት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን በማክበር፣ በማስከበርና የሰላም እሴቶችን በማጎልበት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የፌደራልና አርብቶአደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አሳሰበ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በበኩሉ የጋራ እሴቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ ለሰላም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አመልክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሃይማኖት ተቋማት አመራሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ፈጻሚ አካላት የተሳተፉበት በሰላምና ልማት ላይ ያተኮረ የሦስት ቀናት የአሰልጣኞች ስልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት በፌደራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የብዙሃን፣ የሙያ ማህበራት፣ የሃይማኖትና እምነት ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አወል ወገሪስ ናቸው።

በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የአገሪቱን ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታንና የዜጎችን ሁለንተናዊ ደህንነት በመፈታተን ላይ የሚታወቁት የትምክህት፣ የጠባብነት፣ የጽንፈኝነትና የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦችና ድርጊቶችን መከላከል ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ።

የሃይማኖት ተቋማት ህገ መንግስቱ ያጎናጸፋቸውን መብት ጠብቀውና አክብረው በመንቀሳቀስ ለአገራቸው ሕዳሴ መረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ተቋማቱ በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶቻቸውንም እንዲያጎለብቱ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ፀሐፊ አቶ ሕሉፍ ወልደስላሴ በበኩላቸው፣ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ለዘመናት የዘለቀውን የሰላምና የአብሮነት ታሪክ የሚሸረሽሩና የሚፈታተኑ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መስተዋላቸውን ገልጸዋል።

"ችግሩ የሚያስከትለውን ጉዳት በማስተዋል የህዝቡን አኩሪ ባህልና ታሪክ ሊጎዳ የሚችል ተግባር እንዳይፈጸም የሃይማኖት ጽንፈኝነት አመለካከትና ተግባርን በልዩ ትኩረት መከላከል ይገባል" ብለዋል።

የሰላም ግንባታ ሥራ ለአንድ ወገን እንደማይተው ጠቁመው፣ የሃይማኖት ተቋማትና መንግስት በጋራ ተቀናጅተው በመንቀሳቀስ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሥራ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገሰሰ ረታ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ስልጠናው የሃይማኖት ጽንፈኝነትን በጋራ በመከላከል የአገሪቱን ሰላምና የህዝቦችን ደህንነት በጋራ ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል።

 

Published in ፖለቲካ

ሀዋሳ የካቲት 22/2009 የአድዋን ገድል ድህነትን ድል በመንሳት ለመድገም የድርሻቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

ነገ የሚከበረውን የአድዋ ድል መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ ወጣቶቹ እንዳሉት በቅኝ ግዛት ዘመን በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል በተደረገው ፍልሚያ አውሮፓውያን ለመጀመሪያ ጊዜ እጃቸውን ለጥቁር የሰጡበት ጦርነት ነው አድዋ፡፡

የቴፒ ከተማ ነዋሪው ወጣት ብዙአየሁ ተስፋዬ ያለፉት ጀግኖች አባቶች ወራሪውን ሃይል በጦርና በጋሻ መክተው  ሀገራቸውን በማስከበር አኩሪ ገድል መፈጸማውን ተናግሯል፡፡

ጀግኖች አባቶች " እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ ድል እንደተቀናጁ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን ደህነት ተረባርቦ በማሸነፍ ታሪክን መድገም አለበት"ብሏል፡፡

በሸካ ዞን የማሻ ከተማ ነዋሪው ወጣት ባንተአየሁ አበራ በበኩሉ ወጣቱ በትምህርት የሚያገኘውን እውቀትና ክህሎት በመጠቀምና አቅምን በማሳደግ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክቷል፡፡ 

"ቴክኖሎጂ  በፈጠረው ምቹ ሁኔታ እየተካሄደ ያለውን ዘመናዊ ቅኝ አገዛዝንና የባህል ወረራን ተጽዕኖ ማስተዋል ይገባናል፤ ወደ ውስጣችን ተመልክተን ለመልካም ነገሮች ትኩረት መስጠት አለብን "ብሏል፡፡

የሙዚቃ፣የፊልም፣የሚዲያና የፋሽን ኢንዱስትሪው የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ በመከላከልና ጠቃሚውን በመውሰድ በአድዋ ድል የተገኘውን የኢትዮጵያዊነት ኩራትና ድል  በልማቱም ላይ ማስመስከር እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡

"ወጣቶች መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ያመቻቸላቸውን እድል በመጠቀም የመላ አፍሪካውያን ኩራት የሆነውን የአድዋ ድል መድገም አለብን" ያለው ደግሞ በደቡብ ኦሞ ዞን የጂንካ ከተማ ነዋሪው ወጣት ሳሙኤል ገዛኸኝ ነው፡፡

የየም ልዩ ወረዳ ነዋሪው ወጣት ማህደር ዘሪሁን በበኩሉ የአሁኑ ትውልድ አባቶች በአድዋው ድል በአንድነት ጠላትን ያሸነፉበትን ልምድ በመቅሰም በተባበረ ክንድ ድህንትን ለመርታት  መትጋት እንዳለበት አመልክቷል፡፡

ዘመኑ የደረሰበትን አስተሳሰብና የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው የአድዋን ገድል ድህነትን ድል በመንሳት ለመድገም በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ወጣቶቹ ተናግረዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 22/2009 የኦሮሚያ ክልል መንግስት በልዩ ልዩ መስኮች አሰልጥኗቸው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች በቂ የብድር አገልግሎትና የገበያ ትስስር አለመኖሩ በሥራቸው ላይ ጫና እንዳስከተለባቸው ገለጹ።

የክልሉ መንግስት በበኩሉ “የብድር አቅርቦት ችግር ስለሌለ የሚፈለገውን መስፈርት አሟልተው ከመጡ የፈለጉትን ያህል መውሰድ ይችላሉ” ብሏል።

በኦሮሚያ ክልል ሰበታና ቡራዩ ከተማዎች የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ወጣቶች በእንጨት ስራና በዶሮ እርባታ ዘርፎች የተሰማሩ ናቸው።

ወጣቶች በቂ ስልጠና ወስደው ወደ ስራ መሰማራታቸውን ይገልጻሉ። ሆኖም የቦታ ጥበት፣ የኤሌትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ የገበያ ትስስር አለመኖር እና የብድር አቅርቦት እጥረት በስራቸው ላይ ጫና ፈጥሮባቸዋል።

በሶሾሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪ የያዘው ወጣት ግዛቸው በቀለ የሰበታ ከተማ አስተዳደር ባመቻቸው መሰረት በቂ ሥልጠና ወስዶ በብረታ ብረትና የእንጨት ስራ ተደራጅቶ እየሰራ ነው።

እንደ ወጣት ግዛቸው ገለጻ፤ የገበያ ትስስር አለመኖሩ ለስራቸው ውጤታማነት ችግር እየፈጠረባቸው ነው።

በእንስሳት ህክምና የመጀመሪያ ዲግሪ ያለውና በዶሮ እርባታ ስራ ላይ የተሰማራው ዶክተር በሻዳ ተስፋዬ እንደተናገረው፤ የብድር አገልግሎት እጥረትና የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ ውጤታማ እየሆነ አይደለም።

"መንግስት ወጣቱ በሚፈልገው ስራ ላይ ስልጠና ወስዶ ወደ ስራ እንዲገባ ማድረጉ ጥሩ ነው። ነገር ግን የኤሌትሪክ ኃይል ችግር አለመቃለሉ  በስራችን ላይ ጫና እየፈጠረብን ነው" ያለው ደግሞ በቡራዩ ከተማ አስተዳደር በእንጨትና የቤት ስራ እቃዎች ስራ ላይ የተሰማራው ወጣት  መንግስቱ ገረመው ነው።

በጨርቃጨርቅና ልብስ ስፌት ስራ የተደራጀው ወጣት አብረሃም  ደበሌም ተመሳሳይ ሀሳብ አለው።  “ለስራው ግብዓት የሚሆኑ ነገሮችን በማሟላት ውስንነቶች አሉ"  በማለት ሀሳቡን ይገልጻል።

የክልሉ የስራ እድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌታቸው ገለታ በበኩላቸው እንደገለጹት፤  የክልሉ መንግስት የገበያ ትስስር ችግርን ለመፍታት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።

ክልሉ ለወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ስድስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በመመደቡ የገንዘብ እጥረት አለመኖሩን ገልጸው፤ “መስፈርቱን አሟልተው የሚመጡ ወጣቶች በመመሪያው መሰረት ብድር መውሰድ ይችላሉ” ብለዋል።

የኤሌትሪክ ኃይል ችግርን ለማቃለል አስፈላጊው ክፍያ መከፈሉን ገልጸው፤  “ወጣቶች ያነሱት የገበያ ትሰስርና ሌሎች ቅሬታዎች በቅርቡ መፍትሔ ያገኛል” ሲሉ ነው ያረጋገጡት።

ለስራ እድል ፈጠራው ከተመደበው ገንዘብ መካከል ሦስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ከፌዴራል መንግስት ተንቀሳቃሽ ፈንድ የተሰጠ ሲሆን፤ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮኑ ከኦሮሚያ ቁጠባና ብድር ተቋም ፣ ከክልሉ መንግስት አንድ ቢሊዮን ብር ፣ ቀሪው ደግሞ ከልማት ባንክና ከልማታዊ የመንግስት ድርጅቶች የተገኘ መሆኑ ታውቋል።

በተያዘው ዓመት በክልሉ በአጠቃላይ ለ1ሚሊዮን 273 ሺ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን