አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Thursday, 09 February 2017

አዲስ አበባ የካቲት 2/2009 በበልጉ ወቅት ሊኖር የሚችለውን ውስን የዝናብ መጠን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ጋር በመሆን መጪውን በልግ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በመጪው በልግ ዝናቡ ዘግይቶ እንደሚጀምርና በመጠንም በሰሜንና ሰሜን ምስራቅ ስምጥ ሸለቆ እንዲሁም ደቡብና ደቡብ ምስራቅ የአገሪቷ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በታች እንደሚሆን መተንበዩ ተገልጿል።

ምዕራባዊ አጋማሽ የአገሪቷ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የበልግ ዝናብ ሊኖራቸው እንደሚችልም የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ የረዥም ጊዜ የአየር ፀባይ ትንበያ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዳዲሞስ ወንድይፍራው ተናግረዋል።

በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ አብዱሰመድ አብዶ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ትንበያውን ተከትሎ በቂ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የበልጉ ዝናብ ዘግይቶ እንደሚገባና በመጠንም ሊቀንስ እንደሚችል ያለውን መረጃ ለአርሶ አደሩ የማድረስና የተለያዩ ምክረ ሃሳቦችን የማቅረብ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የተገኘውን የዝናብ እርጥበት በወቅቱ እንዲጠቀሙ፣ መስኖና የውሃ ማቆር ስራዎችን እንዲከውኑና በአጭር ጊዜ የሚደርሱና ድርቅ መቋቋም የሚችሉ ሰብሎችን እንዲዘሩ የማስገንዘብ ስራም እንዲሁ።

በአሁኑ ወቅት ከ219 ሺህ ኩንታል በላይ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የተለያዩ ምርጥ ዘሮችና ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየደረሰ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው በልግ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ ከ93 ሚሊዮን 323 ሺህ ኩንታል በላይ ለማምረት የታቀደ ሲሆን ከ800 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ አራት ሺህ ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

Published in አካባቢ

መቐለ የካቲት 2/2009 የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ የኢንዱስትሪ ዘርፉ በቴክኖሎጂ መታገዝ እንዳለበት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ አስታወቁ፡፡

"ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል  ለሁለት ቀናት የሚቆይ አገር አቀፍ መድረክ ትናንት በመቀሌ ከተማ ተጀምሯል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን በቴክኖሎጂ የተደገፈው የኢንዱስቱሪ እድገት ፈጣንና ቀጣይነት እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚ ዕድገትን ከማምጣቱ ባለፈ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተደማጭነትን እንደሚያሳድግ ገልጸው፣ በመድረኩ የአገሪቱን ሀብቶች እሴት ጨምሮ በመላክ ተጠቃሚ መሆን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል።  

እንደ ሰሊጥ፣ ቡናና መአድን ያሉ የአገሪቱ ሀብቶች በቴክኖሎጂ የታገዘ እሴት ሳይጨመርባቸው ለገበያ በማቅረብ አርሶአደሮችም ሆነ አገሪቱን የተሻለ ተጠቃሚ ማድረግ እንደማይቻል ጠቁመዋል።

በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት እንዲኖረው የኢንዱስትሪ ዘርፉ በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆን እንዳለበት ሚኒስትሩ አመልክተዋል።       

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አምባሳዶር ደክተር አዲስዓለም ባሌማ  እንደገለጹት፣ ባለፉት ዓመታት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት የተሰጠው ትኩረት ውስን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ  ወጣት ተመራማሪዎችን ለማበረታት የተደረገው ጥረት አንስተኛ መሆኑ በዘርፉ እድገት ላይ አሉታዊ  ተጽዕኖ መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡

ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው የውይይት መድረክ  በእርሻ፣ በከተማ ልማት፣ በቱሪዝም ልማትና እድገት ላይ ያተኮሩ 14  ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው የተናገሩት ደግሞ የትግራይ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ደክተር አብራሃ ኪሮስ ናቸው፡፡

የምርምርና የፈጠራ ውጤታቸውን ገበያ ላይ በማዋል ሞዴል ለሆኑ 29 ተማራማሪዎችና የፈጠራ ባለቤቶች ሽልማት እንደሚሰጥ ተመልክቷል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ 280 ተመራማሪዎችና የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 2/2009 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ ሊደርስ ይችል የነበረውን ችግር ማስቀረቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት በአገሪቱ በተወሰኑ ቦታዎች ሁከት መድረሱን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባይታወጅ ኖሮ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንስ ነበር።

"ተፈጥሮ በነበረው ሁከት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባይታወጅና የባህልና ቱሪዝም ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ከአስጎብኚ ድርጅቶች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ ዲፕሎማቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ባይሰራ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ በእጅጉ ይቀንስ ነበር" ብለዋል።

"ህብረተሰቡ ሰላም ወዳድና ጎብኚዎችን የማይተናኮል መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ በተቀናጀ መንገድ በመሰራቱ ጎብኚዎች የያዙትን የጉዞ ፕሮግራም እንዳይሰርዙ፣ ኮንፈረንሶችም በተያዘላቸው ጊዜ እንዲካሄዱ ማድረግ ተችሏል" ነው ያሉት።

በዚህም በዘንድሮው ግማሽ በጀት ዓመት 439 ሺህ 359 የውጭ አገራት ቱሪስቶች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።

የጎብኚዎቹ የቆይታ ጊዜም በአማካይ 16 ቀናት እንደነበርና 1 ቢሊዮን 644 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በዘርፉ የተኘው ገቢና የጎብኚዎች ቁጥር ከ2008 ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በዘንድሮ በጀት ዓመት በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከት ምክንያት ወደ አገር ውስጥ የገቡ ጎብኚዎች ቁጥርና ገቢ ቅናሽ አሳይቷል።

በ2008 በጀት ዓመት ከ478 ሺህ 890 ጎብኚዎች 1 ቢሊዮን 789 ሚሊዮን 964 ሺህ 160 ዶላር ገቢ ተገኝቶ ነበር።

የዘንድሮው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የጎብኚዎች ቁጥር በ39 ሺህ 531 ሲቀንስ ገቢውም በ145 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል።

በተመሳሳይ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ዘርፍ ባለፉት ስድስት ወራት ከ15 ሺህ 600 በላይ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተካሄዱ ሲሆን በቀሪ ጊዜያት ተመሳሳይ ጉባኤዎች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል። 

ጎብኚዎች የፈለጉትን በየቦታው በነፃነት በሰላም እንዲጎበኙና ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ህብረተሰቡና የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለነበራቸው ሚና ምስጋና አቅርበዋል።

በተጠናቀቀው የጥር ወር የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና ለጥምቀት በዓል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እንግዶችና ጎብኚዎች መምጣታቸው፣ የኤርታሌ እሳተ ገሞራ አዲስ ክስተት፣ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች እየሰፉ መምጣትና ሌሎች መልካም ሁኔታዎች በቀጣይ የጎብኚዎችን ቁጥር እንደሚጨምሩ ይጠበቃል።

በዚህም በበጀት አመቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ጎብኚዎች ወደ አገር ውስጥ በመምጣት ከዘርፉ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት የተያዘውን እቅድ ማሳካት እንደሚቻል አቶ ገዛኸኝ ተናግረዋል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጠናቀቂያ 2012 ዓመት የጎብኚዎችን ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን በላይ ለማድረስና ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከዘርፉ ገቢ ለማግኘት ዕቅድ ተይዟል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 2/2009 ከገዢው ፓርቲ ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመወያየትና ለመደራደር መዘጋጀታቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ።

በአገር ውስጥ የሚገኙ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር የሚያደርጉትን ድርድርና ውይይት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ከገዢው ፓርቲ ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚወያዩና እንደሚደራደሩ ነው ያስታወቁት።

ውይይትና ድርድሩ የሚመራበት ስርዓት፣ ስነ ምግባርና ሁኔታ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ተሳትፎን የተመለከተ የጋራ ሃሳብ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረባቸውንም ገልጸዋል።

በጋራ ለመስራት የተሰባሰቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች በውይይትና ድርድሩ የአገር ውስጥና የውጭ ታዛቢዎች እንዲኖሩ ፍላጎት አለን ብለዋል።

የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ ኢህአዴግ በአገሪቷ ትልልቅ ጉዳዮች ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየትና ለመደራደር መወሰኑ ለፖለቲካ ችግሮች መፍትሄ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ይህን መነሻ አድርገው የተሰባሰቡት 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለውይይትና ድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ትግስቱ አወሉም ፓርቲዎቹ ከገዢው ፓርቲ ጋር የሚያካሄዱት ውይይትና ድርድር በሰጥቶ መቀበል መርህ እንዲሆን ተስማምተዋል ነው ያሉት።

ሂደቱ በባለሙያዎች የታገዘና በሰለጠነ አግባብ የሚካሄድ፤ ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮች የማይታዩበት እንዲሆንም እንሻለን ብለዋል።

"ውይይትና ድርድሩ በአገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን በማጥበብ በአገራዊ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት የሚያቀራርብ ነው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኢዴህ) ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ገብሩ በርሄ ናቸው።

የሚካሄደው ውይይትና ድርድር የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ፓርቲዎቹ ራሳቸውን ለህዝቡ በግልፅ የሚያቀርቡበት ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

ፓርቲዎቹ ያቀረቡት የድርድርና ውይይት ሞዳሊቲ ከገዢው ፓርቲና ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሞዳሊቲዎች ጋር ቀርበውና ውይይት ተደርጎባቸው የጋራ ሆነው ይፀድቃሉም ብለዋል።

ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው በአገሪቷ የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝባቸውንና የአገራቸውን ጥቅም በማስቀደም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፣ በመቻቻል ፖለቲካና በድርድር ችግሮችን ከአገር ጥቅም አንፃር ለመፍታት መዘጋጀት ለመሰብሰባቸው መንስኤ መሆኑንም ገልጸዋል።

ድርድሩ ለህዝቡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበትና ያለፉትን ችግሮች የማይደግም ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም አመልክተዋል።

ከገዢው ፓርቲ ጋር ለመወያየትና ለመደራደር አንድ ዓይነት አቋም ለያዙት 11 ፓርቲዎች አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሰብሳቢ፣ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኢዴህ) ፀሃፊ መሆናቸው ይፋ ተደርጓል።

በ1997 ዓ.ም ከተከሰቱ ችግሮች በመማር ግንኙነታቸውን በማጠናከር፣ ልዩነቶችን በማክበርና በማጥበብ በጋራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

በፓርቲዎቹ ስብስብ ውስጥ አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን)፣ የኢትዮጵያ ፍትህ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዲኃግ)፣ የወለኔ ህዝብ አንድነት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የወለኔ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የመላው ኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ይገኙበታል።

እስካሁን 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢህአዴግ ባቀረበው ውይይትና ድርድር ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን ቢያሳዩም የተለያዩ ሃሳቦችን በማንፀባረቅ ላይ ይገኛሉ።

Published in ፖለቲካ
Thursday, 09 February 2017 22:51

አውቶብሱ !!

ሚስባህ አወል /ኢዜአ/

የካቲት 2009 የመጀመሪያው ቀን ላይ ነው፡፡ ቢሮ በጠዋት ገብቼ የምሰራው ስራ ስላለ የጠዋቱን  የትራንስፖርት መጨናነቅ ለማምለጥ ከወትሮው ቀደም ብዬ ከቤቴ ወጣሁ!!

ይሁንና ያልቀረልኝ የተለመደው የትራንስፖርት ችግር ፊት ለፊቴ ተጋረጠ፡፡ ሰከንዶች ነጎዱ ደቂቃዎችም አለፉ !! ከአስኮ አካባቢ ትርፍ ሰው ጭነው የሚመጡ ታክሲዎች ዊንጌት ጋር ያሉ የትራፊክ ፖሊሶችን በመፍራት ቦታቸውን እያስተካከሉ መጓዛቸውን ቀጥለዋል፡፡

19 ቁጥር አውቶብስም በርካታ ሰው አሳፍራ በአወሊያ አካባቢ በሚገኘው ፌርማታ ላይ ተከስተች፡፡ ለመሳፈር ፍላጎት ቢኖረኝም ያሳፈረችው ሰው ብዛት የሚያጨናንቅ በመሆኑ አለፍኩዋት፡፡

አፍታም ሳይቆይ ሁለት አውቶብሶች በፌርማታው ላይ ደረሱ ካለፈችው አውቶብስ የማይተናነስ ሰው አሳፍረዋል፡፡

ደቂቃዎቹና ታክሲዎቹ ያለማቋረጥ በአጠገቤ መንጎዳቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከሰላሳ ደቂቃ በሁዋላ 94 ቁጥር ዳፍ አውቶብስ ሲምዘገዘግ መጣና ተሳፍረን ጉዞ ጀመርን፡፡

የተጨናነቀውን የዊንጌት አደባባይ በመከራ ያለፈው  አንበሳ ከአደባባዩ በላይ በኩል ወደ ሩፋኤል ፤ ሸጎሌና አዲሱ ገበያ የሚሄዱ ተሳፋሪዎችን ጠራርጎ ከጫነ በሁዋላ በሚመቸው የቀለበት መንገድ ላይ ሩጫውን ተያያዘው፡፡

ዊንጌት አካባቢ ያጠፋውን ጊዜም ለማካካስ ይመስላል በሚመቸው ጉዳና ላይ እየተምዘገዘገ ሳለ የፊት ጎማው መፈንዳቱን የሚገልጽ ድምፅ ተሰማ ተሳፋሪው በድንገጤ ውስጥ ወደቀ፡፡

ብዙም ሳይቆይ አውቶብሱ እንደ ሰከረ ሰው ይወዛወዝ ጀመር፡፡ ጠና ያሉት የአውቶብስ ሹፌር መኪናውን ለመቆጣጠር ትግል ጀመሩ፡፡

አውቶብስ ውስጥ የተሳፈሩ መንገደኞች በየእምነታቸው ፈጣሪያቸውን እየጠሩ መጮህና መማጸናቸውን ለሰከንዶች ቀጠሉ፡፡

አውቶብሱ የመንገዱን ጠርዝ እየታከከ መምዘግዘጉን ቀጠለ በዚህ ጊዜ የሚያሽከረክሩት ሹፌሩ ሳይሆኑ ወደፈለገበት ይዞን የሚወዛወዘው  አውቶብሱ ራሱ መሆኑን ተረዳሁ፡፡

አውቶብሱ አሁን የሚመቸውን አስፋልት ለቆ በአስፋልቱ ዳር ያሉ ታዳጊ የሆኑ ዛፎችን እየጨረጋገደ ከህዝቡ ጩህት ጋር መጓዙን ቀጠለ፡፡

ከመነሻው ተሯሩጦ ወንበር ይዞ የመጣው ተሳፋሪ ከፊሉ በአውቶብሱ ወለል ላይ የሙጥኝ አለ፡፡ አንዱ ባንዱ ላይ እየተደራረበ መጮህ ሆነ፡፡

አንድ አምስት የሚሆኑ ዛፎችን ያስተኛው አውቶብስ ለውሃ መውረጃ በተዘጋጀ ቱቦ ውስጥ በመግባት ወደጎን ተደግፎ ለመቆም ቻለ፡፡

አውቶብሱ ይቁም እንጂ በአውቶብሱ ውስጥ ያሉ ተሳፋሪዎች ግን ሊቆሙ አልቻሉም በመስኮት የወጡትን ትተን ከውስጥ በአውቶብሱ ወለል ላይ ተኝተው ፈጣሪን የሚማጠኑት መማጸናቸውን ቀጥለዋል፡፡ ‹‹ተርፈናል !!›› ‹‹አውቶብሱ ቆሟል!!›› የሚሉ ድምፆች ቢሰሙም ፈጣሪን ከመማፀን አላቆሙም፡፡ አላመኑማ! መትረፋቸውን፡፡

ግማሹም አዘንብሎ በከፊል ከተኛው አውቶብስ በተከፈተው በር ለመውጣት ትግሉን ተያይዟል፡፡

እዚህ ጋር በዛ ጠዋት ጎማው የፈነዳው ያንበሳው አውቶብስ የአገልግሎት ዘመኑ ከ30ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረ ለመሆኑ የአደባባይ ሚሰጥር ነው፡፡

አንበሳ በየፌርማታው የእርጅና ብዛት እያቃሰቱና ከፍተኛ ጩህት እያሰሙ ቆመው ያለበቃኝ የሚጭኑት አውቶብሶቹን የቴክኒክ ብቃት በየቀኑ ይመረምር ይሆን!!

ዳሩ አይመስለኝም፡፡ የአንበሳ አውቶብስ ተጠቃሚ እንደመሆኔ ከውስጣዊ ይዘቶቹ በርካታ የቴክኒክ ጉድለቶች እንዳሉት መናገር እችላለሁ የአውቶብሶቹ ወለል ተቀዶ አስፋልቱን እያየን የምንጓዝባቸው አውቶብሶች ጥቂት አይደሉምና!!፡፡

ከደቂቃዎች በሁዋላ በአዲሱ አስፋልት ላይ የተገኘው ተሳፋሪ ፈጣሪውንና ሹፌሩን እያመሰገነ ይነጋገር ገባ፡፡ ገሚሱም አካሉን ይመረምር ጀመር፡፡

‹‹ሹፌሩ ምራቁን የዋጠ ታጋሽ ባይሆን አልቆልን ነበር!!››  ‹‹በአካባቢው ሌላ መኪና ቢኖር ኖሮ …..››  ‹‹ሜዳማውን አልፎ ከደቂቃዎች በሁዋላ የሚደርስበት ገደላማ ስፍራ ቢሆን ኖሮ ….›› ብቻ በቢሆን ኖሮ ያልተባለ ያልመነጨ ሃሳብ አልነበረም፡፡ ለማለቃችን፡፡

ከዛ ሁሉ ሰው ሁለት ሴቶች ትንሽ በድንጋጤ ራሳቸውን እንደመሳት አድርጉዋቸው ነበር ፤ አንዲቷ ነፍሰጡር መሆኗን ተረድቻለሁ፡፡

በኢትዮጵያ ከሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች መካከል አብዛኛው በአሽከርካሪዎች ብቃት ማጣት መሆኑ ቢታወቅም ሶስት በመቶ የሚሆነው በተሸከርካሪዎች የቴክኒክ ችግር መሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

አንበሳ ይህን ተገንዝቦ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት በዘመናዊ መኪኖች ሊተካና የማይተካ አገልግሎቶቹን ለማሳካት ጥረት ሊያደርግ ይገባል እላለሁ፡፡

ያጋጣሚ ጉዳይ ቢሆንም ጥር 22 የተጀመረውና "ከትራፊክ አደጋ የጸዳ የትራንስፖርት አገልግሎት ለአገራዊ ህዳሴ" በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ንቅናቄ እስከ ግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም ይቀጥላል። ሚዲያዎች ሳምንቱን ለመዘከር በርካታ ሽፋን እየሰጡት እንዳለም ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ  በተሸከርካሪ ቁጥር ብዛት ከአፍሪካ አነስተኛ መሆኗ ቢታወቅም በአደጋ ግን ከፍተኛውን ቦታ ይዛ ትገኛለች፡፡

በአሁኑ ወቅት ገዳይ ከሚባሉ በሽታዎች ባልተናነሰ ሁኔታ የህዝባችንን ህይወት እየቀጠፈ ስላለው  የትራፊክ አደጋ መፍትሄ ለማምጣት በየመስኩና በሁሉም ህብረተሰብ ዘንድ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል፡፡

ለዚህም ይመስላል  የትራፊክ አደጋ አሳሳቢነት በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በሀገሪቱ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑ የተገለጸው፡፡

ታዲያ የትራፊክ አደጋን በመከላከሉ ረገድ ጥንቁቅ አሽከርካሪዎችን ማፍራት፣ የተሸከርካሪዎቻችንን የቴክኒክ ብቃት በየጊዜው መፈተሸና እግረኞች የትራፊክ ህግን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ በመምከር ተሰናበትኩ፡፡      

                                                                                                                             መልካም ቀን !

 

 

 

 

Published in ዜና-ትንታኔ

ዲላ የካቲት 2/2009 ምላሽ ሳያገኙ የቆዩ የመልካም አስተዳደርና  የልማት ጥያቄዎች  ቅድሚያ በመስጠት መፍታት ከአዲሶቹ አመራሮች እንደሚጠበቅ  የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

የአስተዳደሩ ምክር ቤት አዲሶቹን  የካቢኔ አባላት ከመሾሙ በፊት ነዋሪው ህዝብ  አስተያየት እንዲሰጥባቸው አድርጓል፡፡

በዚህ ላይ የተሳተፉት ነዋሪዎች እንዳሉት   አዲሶቹ አመራሮች  በከተማው መልስ ሳያገኙ የቆዩ የህዝብ ጥያቄዎች ቅድሚያ በመስጠት መፍታት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በተለይ በአካባቢው  ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለዘመናት ተቻችሎና ተዋዶ የኖረው ህብረተሰብ  መቃቃርን ትቶ  እርቀ ሠላም የማውረዱን ጉዳይ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡ ፡

መምህር ታዬ አለሙ በከተማው  የሀሮሬሳ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን  በጥቃቅን እና አነስተኛ የ የብድር ተቋማት  ላይ ከብድር አቅርቦት ፣ ከክትትልና ድጋፍ ጋር ተያይዞ የነበሩ ፍትሃዊ ያልሆኑ አካሄዶችን መስተካከል እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡

የሀሴ ዴላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አለማየሁ ሮባ በበኩላቸው በተሽክርካሪ መናኸሪያ ተሳፍረው ከወጡ በኋላ ከታሪፍ በላይ እንዲከፍሉ የሚገደዱበት ሁኔታ ስላለ  አዳዲሶቹ  አመራሮች እንዲፈቱላቸውም ጠይቀዋል፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነት  በከተማው ማዘጋጃ ቤት ላይ ተስፋፍቶ እንዳለ ያመለከቱት የከተማው ቦኢቴ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ለገሰ ጎበና በበኩላቸው  የቀበሌ ቤቶችን በዝምድና ማደል እና የግል ቤት ላላቸው ያለአግባብ ገንዘብ ተቀብሎ ቤት ማስተላለፍ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

እነዚህንና ሌሎችም ምላሽ ሳያገኙ የቆዩ የመልካም አስተዳደርና  የልማት ጥያቄዎች  ቅድሚያ በመስጠት መፍታት ከአዲሶቹ አመራሮች እንደሚጠብቁ   ነዋሪዎች ጠቁመዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በአካባቢው ተከስቶ የነበረው ግጭት ህዝቡን በማይወክሉ የጠባብነትና ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ባላቸው ጥቂት ግለሰቦች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ለዘመናት በፍቅር እና በመከባበር በኖሩ ህዝቦች መካከል ያለውን ትስስር የሚያላላ ክስተት መፈጠሩን ጠቅሰው ፤ የዞኑ አስተዳደር ለእርቀ ሰላሙ ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡

በተለይ በሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ የነበሩት ችግሮች በማስወገድ ወጣቱን የላቀ ተጠቃሚ ለማድረግ  አስተዳደሩ ከአዲሱ የከተማው አመራር ጋር በቅንጅት ይሰራል ፡፡

የደቡብ ክልል ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ አድማሱ አንጎ በበኩላቸው በዞኑ ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ ብሎም ወጣቱን የሀብት ባለቤት ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

አቶ አድማሱ እንዳመለከቱት  በዞኑ ሊገነባ የታቀደው የኢንዱስትሪ ፓርክ በታሰበለት ጊዜ መሰረት ለማከናወን ጥረት ይደረጋል፡፡

የከተማው አስተዳደር ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ  ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ በህዝቡ ተገምግመው ከሾማቸው የካቢኔ አበላት መካከል  22 ነባር ሲሆኑ 16 ደግሞ ከተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት በመወጣት የተመለመሉ ናቸው፡፡

ተሿሚዎችም በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

መቐለ የካቲት 2/2009 ከጥልቅ ተሃድሶው ግምገማ በኋላ  የህዝቡ የልማት ተነሳሽነት ቀጣይነት እንዲኖረው በትጋት እንደሚሰሩ የትግራይ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ከግምገማው በፊት በመንግስት ሰራተኛው ላይ በነበረው የአገልጋይነት መንፈስ መጓደል፣ የመልካም አስተዳደር ችግርና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ህዝቡ ተስፋ የመቁረጥ ዝንባሌ ይታይበት እንደነበር ጠቁመዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ወይዘሮ ዘይነብ ዓብደል ለጢፍ እንደገለጹት፣ ባለፉት 15 ዓመታት የተከናወኑት መልካም ስራዎችና የነበሩት ችግሮች በግምገማው እንዲታዩ መደረጉ እያንዳንዱ ሰራተኛ ችግሩን  እንዲመለከት መንገድ ከፍቷል።

" የተሃድሶ ግምገማው በክልሉ በመካሄድ ላይ ባሉት የልማት ስራዎች የህዝቡን ተሳትፎና ፍላጎት እንዲጠናከር መነሳሳት ፈጥሯዋል " ብለዋል፡፡

ሌላው የምክር ቤት  አባል አቶ አብርሃለይ ፍትዊ በበኩላቸው " የግምገማ መድረኩ የምክር ቤቱ አባላትም ወደ ታች ወርደን አስፈፃሚው አካል የሚያከናውናቸውን ስራዎች በመከታተልና በመቆጣጠር የነበራቸው ክፍተት እንዲታዩ አስችሏል" ሲሉ ገልጸዋል።

በክልሉ የተካሄደው የተሃድሶ ግምገማ የፈጠረውን አቅም በመጠቀም የተበደለውን ህዝብ   ለመካስና  የልማት ስራዎችን ለማፋጠን የመሪነት ሚናቸውን በተገቢው እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

የግምገማ መድረኩ ከመንግስት ሰራተኛው ጀምሮ እሰከ ገጠር ቀበሌ ድረስ ወዳለው ህዝብ መውረዱ በነበሩት ችግሮች ላይ እያንዳንዱ  ድርሻውን እንዲያውቅ ማስቻሉን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ አወጣሽ ይርገብ የተባሉት የምክርቤት አባል ናቸው።

ግምገማው ችግሮችን በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መጠናቀቁ ህዝብና መንግስት ይበልጥ ተቀናጅተው እንዲሄዱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

የልማት ስራዎች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት  እንዲጠናቀቁ የሚያስችል መሆኑን ወይዘሮ አወጣሽ ጠቅሰዋል።

አቶ ግርማይ ሃይሉ  እንዳሉት ደግሞ በግምገማው ወቅት እያንዳንዱ የመንግስት ሰራተኛ ችግሮቹን በሚገባ እንዲያይ በመደረጉ የአገልጋይነት ስሜት ተፈጥሯል፡፡

ህብረተሰቡ በተለያየ ወቅት ሲያነሳቸው የቆዩትን ጥያቄዎችና ችግሮች  ተከታትሎ ምላሽ  ለመስጠት መድረኩ  መማማሪያ እንደነበርም ጠቁመዋል።

የግምገማ መድረኮቹን ተከትሎም የምክር ቤቱ አባላት ባደረጉት የዳሰሳ ቅኝት በሁሉም ዘርፎች ተነሳሽነት እየተፈጠረ መሆኑን ማረጋገጥ እንደተቻለ የገለጹት  ደግሞ  የምክር ቤቱ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዕፃይ እምባየ ናቸው።

ህዝቡም  አመራሩን በግልፅ መድረክ መገምገሙና አመራሮቹም ድክመቶቻቸውን በቅንነት መቀበላቸውን ጠቁመው  መድረኩ ተቀናጅተው ለመሄድና ለልማት ያላቸውን ተነሳሽነት የሚያጎለብት ግብአት የተገኘበት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ጅማ የካቲት 2/2009 ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚወጣው የፍሳሽ ቆሻሻ አካባቢን በመበከል በጤናቸው ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አስተያየታቸውን ለአዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ ።

ችግሩን በተደጋጋሚ ለማሳወቅ ቢሞክሩም በዩኒቨርሲቲው በኩል የመፍትሄ እርምጃ አለመወሰዱ ቅሬታ እንደፈጠረባቸውም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት ከዩኒቨርሲቲው የሚለቀቀው ፍሳሽ ቆሻሻ አካባቢው ላይ እያስከተለ ያለው ብከለት መፍተሄ እንዲያገኝ ጥያቄ ማቅረብ ከጀመሩ ከሰባት ዓመት በላይ ሆኗቸዋል።

ይሁን እንጂ ችግሩ እየተባባሰና በነዋሪው ጤና ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት እየከፋ መምጣቱ ታውቆ ምላሽ አለማግኘታቸው ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል ።

ከነዋሪዎቹ መካከል የጤና ባለሙያ የሆኑት አቶ ገብረስላሴ ፋንታ እንደገለጹት ከዩኒቨርሲቲው በሚለቀቀው ፍሳሽ ቆሻሻ በተደጋጋሚ የጤና እክል ቢገጥማቸውም ችግሩ ለዓመታት እልባት አለማግኘቱ አካባቢው ለመኖር አደጋች ሆኖባቸዋል።

በአሁኑ ወቅት አቅም ያላቸው ነዋሪዎች ቤታቸውን ለቀው ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ መገደዳቸውንና ሌሎችም ከአካባቢው ለመልቀቅ እየተዘጋጁ መሆኑን  ጠቁመዋል።

በርካታ የአካባቢው ነዋሪች ለመተንፈሻ አካል የጤና ችግርና ከንጽህና ጉድልት ለሚመጡ በሽታዎች መጋለጣቸውን አመልክተዋል ።

በጅማ ከተማ በተለምዶ "ቆጪ" ተብሎ በሚጠራው ሰፍር የሚኖሩት አቶ ማርቆስ መጫ በበኩላቸው "የአካባቢው ነዋሪዎች ከቀድሞ የዩኒቨርሲቲው አመራር አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩ እንዲፈታ ጥረት ቢያደርጉም እስካሁን እልባት ማግኘት አልተቻለም " ብለዋል።

"ከዩኒቨርሲቲው የሚለቀቀው ፍሳሽ ቆሻሻ እንዲቆም በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም " የቆሻሻ ማብለያ ገንዳ ለመስራት በተሰጠው ቦታ ላይ ሰዎች በህገውጥ መንገድ በመስፈራቸው የተፈጠረ ችግር ነው " ከማለት ባለፈ ዘላቂ መፍትሄ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል። 

የጅማ የኒቪርሲቲ ምክትል ፕሬዜዳንት አቶ ኮራ ጡሽኔ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታ ተገቢ መሆኑን አምነዋል።

"ዩኒቨርሲቲው በ1995 ዓ.ም ለቆሻሻ ማብለያ በተረከበው ቦታ ላይ ህገወጥ ሰዎች በመስፈራቸው ግንባታውን እስካሁን ማካሄድ አልተቻለም" ሲሉ ምክንያቱን ገልጸዋል።

የፍሳሽ ቆሻሻው በዩኒቨርሲቲው አካባቢ ብክለት በማድረሱ የመኖሪያ አካባቢውን ለኑሮ አደጋች ማድረጉን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በቅጥር ጊቢው ውስጥ የቆሻሻ ማብለያ ግንባታ ሥራ መጀመሩንና ግንባታው ሲጠናቀቀቅ ችግሩ እንደሚፈታ አስታውቀዋል ።

የጅማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሻፊ ሁሴን አስተዳደሩ ለዩኒቨርሲቲው ፍሳሽ ቆሻሻ ማብላያ እንዲገነባበት በሰጠው ቦታ ላይ የተካሄደው ህገወጥ ሰፈራ የቆየና ስር የሰደደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አስተዳደሩ ለዩኒቨርሲቲው የፍሳሽ ማብላያ ግንባታ በተሰጠው ቦታ ላይ የሰፈሩ ነዋሪዎችን በማስነሳት ግንባታው የሚጀመርበትን ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት የሚያስችለውን አቅጣጫ አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አቶ ሻፊ አስታውቀዋል።

በጅማ ከተማ በቅርቡ በተካሄደው ጥልቅ የተሃድሶ መድረክ በነዋሪው ከተነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አንዱ "ለኑሮ ተስማሚና ጽዱ አካባቢ የመኖር መብታችን ይከበር" የሚለው እንደሆነ አቶ ሺፋ ገልጸዋል።

አስተዳደሩም የነዋሪዎችን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ ነው ብለዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 2/2009 መንግስት በአርብቶአደሩ አካባቢ የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም በ47 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የመጀመሪያ ዙር እርዳታ እያቀረበ መሆኑን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

በተያዘው ዓመት በሶማሌ ክልል ዘጠኝ ዞኖች፣ በምዕራብ ጉጂ፣ ቦረና፣ ባሌ ቆላማ አካባቢዎች፣ በደቡብ ኦሞና ሰገን ሕዝቦች አካባቢ የሚኖሩ አርብቶአደሮች ለከፍተኛ ድርቅ ተጋልጠዋል።

ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች እርዳታ ሲያገኙ መቆየታቸውን አስታውሶ በተያዘው ዓመት ደግሞ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎችን እየደገፈ መሆኑን ገልጿል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የዘንድሮው ዓመት የተረጂዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር በ44 በመቶ ዝቅ ብሏል።

መንግስት ያለፈውን ልምድ በመጠቀም ለተረጂዎቹ ከሚያስፈልገው 715 ሚሊዮን ዶላር አጠቃላይ በጀት በራሱና በአጋሮቹ ለመሸፈን እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ለአዲስ ተረጂዎች የሚውል 47 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት የምግብ እህል፣ አልሚ ምግቦችና ዘይት እያከፋፈለ ነው።

ዳይሬክተሩ እንደሚሉት መንግስት እንደ ባለፈው ዓመት ሁሉ ዘንድሮም ለተረጂዎች የሚያስፈልጉትን የምግብ እህል፣ አልሚ ምግብና ዘይትን ጨምሮ ሌሎችንም ቁሳቁስ እያቀረበ ይገኛል።

በአካባቢዎቹ ከ114 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል እየተከፋፈለ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ድርቁ በአርብቶአደሩ አካባቢ የተከሰተ በመሆኑ ኮሚሽኑ ለእንሰሳት ኃብቱም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ የእንስሳት መኖ አቅርቦቱም በተጠናከረ ሁኔታ እየተካሔደ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ኮሚሽኑ ከእንስሳትና አሳ ኃብት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የድርቁ አጠቃላይ አዝማሚያ የእንስሳት ህይወትን በስፋት ሊቀጥፍ እንደሚችል በመገመቱ ተጨማሪ የመኖ አቅርቦት እየተዘጋጀ ሲሆን ለገበያ እንዲቀርቡም እየተደረገ ነው ብለዋል።

በቀጣይ የሚጠበቀው የበልግ ዝናብ መጋቢት ወር ላይ ከጀመረ የተረጂዎች ቁጥር በተወሰነ ደረጃ ሊቀንስ እንደሚችል ተገምቷል።

በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በኤልኒኖ ሳቢያ በአገሪቱ ሰፋ ባለ አካባቢ በተከሰተው ድርቅ ለ10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች በራስ አቅም እርዳታ ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 2/2009 አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በውሃ እጦት ሳቢያ ለጤና እክልና ለማህበራዊ ቀውሶች እየተዳረግን ነው አሉ።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በከርሰ ምድር የውሃ መገኛዎች ላይ በተፈጠረው የምርት መቀነስና በፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ችግሩ መከሰቱን ገልጿል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የጉለሌና የየካ ክፍለከተማ ነዋሪዎች ውሃ በአካባቢው ከሁለት ወራት በላይ በመጥፋቱ ለጤና እክሎችና ማህበራዊ ቀውሶች መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ከናይጄሪያ ኤምባሲ ከፍ ብሎ በተለምዶ ካታንጋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሂሩት ጌራወርቅ፣ አቶ ተስፋዬ ማሞ እና ወይዘሮ አረጋሽ በሻህ በውሃ ችግር ምክንያት ህፃናትና አዋቂዎች ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በክፍለከተማው የጉቶ ሜዳ ጤና ጣቢያ የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆኑን የላብራቶሪ ቴክኖሎጂስቷ ወይዘሮ ፋንታዬ ሙላትና ፋርማሲስት አያሌው ታፈሰ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በየካ ክፍለከተማ ፈረንሳይ ጉራራ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ወርቅነሽ ደንድር እና ወጣት ትዕግስት ስሜ በውሃ ችግር ምክንያት ገላቸውንና የሚለብሱትን ልብስ ማጠብ ባለመቻላቸው ለጤና ችግር እንደተጋለጡ ነው የሚናገሩት።

በከተማው በተለያዩ ቦታዎች ለአብነትም በአዲሱ ገበያ፣ አስኮ አዲስ ሰፈር፣ ዓለምባንክ ልደታ ኮንዶሚኒየም፣ ቦሌ ቡልቡላ፣ ቦሌ መድሃኔዓለም፣ አፍንጮ በር እና በአራዳ ክፍለከተማ ዘበኛ ሰፈር እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች ውሃ በከፊልና ሙሉ በሙሉ የሌለባቸውን መሆኑን የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

ስለቀረቡት ቅሬታዎችም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የሚመለከታቸውን የስራ ኃላፊዎች አነጋግሯል።

በባለስልጣኑ የውሃ አቅርቦት ስርጭት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቃዱ ዘለቀ ችግሩ በከርሰ ምድር የውሃ መገኛዎች ላይ በተፈጠረ የምርት መቀነስ እና ከከተማዋ ዕድገት ጋር ተያይዞ የውሃ ፍላጎት እና አቅርቦቱ ባለመመጣጠኑ የመጣ ነው ይላሉ።

ከውሃ አቅርቦት አንፃር ባለፉት ሁለት ዓመታት ከገፀ-ምድር እና ከርሰ ምድር የውሃ መገኛዎች የልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም በ2006 ዓም በቀን ከነበረው የ350 ሺህ ሜትር ኪዩብ የውሃ አቅርቦት ወደ 608 ሺህ ሜትር ኪዩብ ማሳደግ በመቻሉ ቀድሞ በፈረቃ የሚያገኙ የኮልፌ፣ ልደታ፣ ቂርቆስና ቦሌ አካባቢዎች የ24 ሰዓት አገልግሎት ያገኙ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ፈረቃቸው ተሻሽሏል ብለዋል።

በከተማው ተገንብተው አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት የአቃቂ ሀ እና ለ እንዲሁም የደርቱ የውሃ ፕሮጀክቶች የታቀደላቸውን ምርት ሲያመርቱ ቢቆዩም አሁን ግን የምርት መቀነስ ችግር እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በሰሜን አዲስ አበባ በጉለሌ፣ አዲስ ከተማ እና ኮልፌ ክፍለከተሞች ዘላቂ የውሃ ምንጭ እስኪገኝ ድረስ በተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶች ምርት በመቀነሱ ስርጭቱ መቀነሱን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በሽሮ ሜዳ፣ፈረንሳይ ጉራራ፣ ጣሊያን ኤምባሲ አካባቢ ችግሩ በመከሰቱ ምትክ ጉድጓዶች እንዲቆፈሩ ተደርጓል ነው ያሉት።

በልደታ እና ሳር ቤት አካባቢ የተፈጠረውን የውሃ ችግር ለመፍታትም የ24 ሰዓታት አገልግሎት ከሚያገኙ አካባቢዎች በመቀነስ ችግሩን ተመጣጣኝ ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል "በምስራቅ አዲስ አበባ አካባቢ የውሃ አቅርቦት ችግር ባይኖርም ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በቀን ውስጥ ሁለት ሶስት ጊዜ ስለሚከሰት የውሃ ፓንፖች ለብልሽት በመዳረጋቸው ምክንያት የውሃ ችግሩ ሊፈጠር ችሏል" ብለዋል።

በዚህም የተበላሹትን የውሃ ፓንፖች በአዲስ ለመቀየር ከአምስት ቀናት በላይ ይጠይቃል፤ ይሄም በፈረቃ ያገኙ የነበሩ አካባቢዎች ፈረቃቸውን ጠብቀው እንዳያገኙ ችግር እየፈጠረ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የከተማዋ የውሃ ፍላጎት በቀን ወደ 974 ሺህ ሜትር ኪዩብ እንደሚያድግ ጥናቶች ያሳያሉ።

ይህንን መሰረት በማድረግ ባለስልጣኑ የከተማውን የውሃ አቅርቦት ወደ አንድ ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን