አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 08 February 2017

ድሬድዋ የካቲት 1/2009 በአገር አቀፍ ደረጃ በየመንግስት ተቋማት የተቀናጀ ሙስናን የመከላከል ስትራቴጂ ሰነድ በመተግበር የጸረ ሙስና ትግሉን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።
 
ስትራቴጂው ላይ ለምስራቅ ተጎራባች ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ፣ የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና  ኮሚሽን ሃላፊዎች  ግንዛቤ ለማስጨበጥ ኮሚሽኑ ያዘጋጀው ውይይት በድሬደዋ ተካሄዷል፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ እንደገለጹት  ባለፈው ዓመት በተመረጡ 99 የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ውስጥ ከግዥ ጋር ተያይዞ የሚፈጸም ሙስናን ለመከላከል በጥናት የተደገፈ አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

በዚህም  የመንግስትና የህዝብ ሀብት ከብክነትን መታደግ ተችሏል።
 
ከ118ሺ በላይ ነዋሪዎች የሙስና መታገያ ትምህርት በመስጠትና  አደረጃጀቶችን በመጠቀም ህዝቡን የጸረ ሙስና ትግሉ አካል በማድረግ  ሙስናን የማይሸከም ህብረተሰብ የመፍጠር ጅምር ስራ ተከናውኗል፡፡
 
በሙስና የተጠረጠሩ ከ3ሺ 600 በላይ ሰዎች ላይ ክስ ተመስርቶ ከመካከላቸውም በ1ሺ 500ዎቹ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ተደርጓል።
 
ይሁን እንጂ  ከሙስናና ብልሹ አሰራሮችጋር ተያይዞ የህዝቡን ፍላጎትና ጥያቄዎችን ከመመለስ አንጻር ብዙ መሰራት የሚጠበቅ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡  

ሙስና በልማቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ የሚችልባቸውን ዘርፎች በመለየት በመንግስት ተቋማት የተቀናጀ የሙስና መከላከል ስትራቴጂ ሰነድ በፌዴራል መንግስት ተቋማት መተግበር መጀመሩን ተናግረዋል።
 
ስትራቴጂው በሁሉም አገሪቱ ክፍል በተቀናጀ መንገድ በመተግበር የጸረ ሙስና ትግሉን ፍሬያማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

"ስትራቴጂው በጅምላ ሲካሄድ የነበረውን ሂደት በማስቀረት ከየተቋማቱ ነባራዊ ሁነቶችና ተጨባጭ አሰራሮች አንጻር በራስ አቅም ለመከላከል ያስችላል" ብለዋል።
 
ተቋም ተኮር የመከላከያ ስትራቴጂው ከተለያዩ አለም አገራት ልምድ የተቀሰመበትና በየተቋማቱ የሚታዩ የኪራይ ሰብሳቢነት ዝንባሌዎችንና ብልሹ አሰራሮችን በመናድ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጠቀሜታው የጎላ ነው።
 
ስትራቴጂው ተግባራዊ እንዲሆን አመራሩ ችግሩን በተግባር እየፈታ በመሄድ ለውጤተማነቱ  ቁርጠኛ መሆን እንደላበት ያመለከቱት አቶ ወዶ  "ህዝቡም መብቱን በገንዘቡ መግዛትና ችግሩን ዳርቆሞ ማየት ሳይሆን ለመፍትሄው መንቀሳቀስ አለበት "ብለዋል።
 
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አብደላ አህመድ "ስትራቴጂው የልማትና የመልካም አስተዳደር እንቅፋት የሆኑትን የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና  ተግባራትን ለመከላከል ያስችላል" ብለዋል።
 
ከስልጠናው የሚቀስሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ የመንግስት ሀብትና ንብረት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ክትትልና ቁጥጥሩን ለማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

ክትናንት ጀምሮ ለሁት ቀናት በተካሄደው ውይይት ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ፣የሐረሪ ፣ የአፋርና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አመራሮች፣ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ተጠሪዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

የካቲት 1/2009 እንግሊዝ ለሰብአዊ እርዳታ ጥበቃ ሊያደርጉ የሚችሉ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ደቡብ ሱዳን ልትልክ መሆኑን ሲጂቲን ዘገበ፡፡ 

እንግሊዝ 3 መቶ ሰራዊት ወደ ደቡብ ሱዳን የምትልክ ሲሆን አብዛኞቹም ኢንጂነሮች ናቸው፤ ሰራዊቱም በደቡብ ሱዳን የሚገኙ 12 ሺህ ጠንካራ ሰላም አስከባሪዎችን የሚደግፉ ይሆናሉ ብሏል ዘገባው ፡፡

የእንግሊዝ የውጪ ጉዳይ አለም አቀፍ ልማት ኃላፊ ፕሪቲ ፓትል አገራቸው ከሌሎች ጋር በጥምረት ሰብአዊ እርዳታው ላይ መስራቷ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሲጂቲን ስካይ ኒውስን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል ፡፡

እኤአ በ1990ዎቹ የታጠቁ የደቡብ ሱዳን ወታደሮች 80 ከመቶ የሚሆነውን የእርዳታ አቅርቦት በመዝረፍ ለራሳቸው ፍጆታ በማዋል ከሰሜን ሱዳንና እርስበርሳቸው ሲዋጉ ነበር ብሏል ሲጂቲን፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 1/2009 በኦሮሚያ ክልል ሕብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ችግሮች ምላሽ ለመስጠት ሕዝቡን ያሳተፈ የውይይት መድረክ መዘጋጀቱን የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።    

የጥልቅ ተሃድሶው ግምገማ በመጀመሪያው ምዕራፍ የ15 ዓመታት ጉድለቶችን በመለየት መጠናቀቁን ነው ቢሮው የገለጸው።

በክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በጥልቅ ተሃድሶው ምንነትና አስፈላጊነት ላይ ከስምምነት ተደርሷል።

"በግምገማውም የ15 ዓመታት ጥንካሬዎችና ጉድለቶች ምን ይመስሉ እንደነበር ለመለየት ተችሏልም ነው" ያሉት።

በሁሉም ደረጃ በተካሄደውም የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር አቶ አዲሱ ገልጸዋል። 

ይህን የሕዝብ ተሳትፎ ይበልጥ አጠንክሮ ለመቀጠልና በጥልቅ ተሃድሶው እንደ ዋና ዋና ክፍተቶች በተነሱትና ሕዝቡ የሚያነሳቸው ችግሮች ለመፍታትና ወደ ተግባር ለመግባት ሕዝቡን የሚያሳትፍ የውይይት መድረክ ማዘጋጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል።

በዚህም ክልሉ በ20 ዞኖችና በ10 የከተማ አስተዳደሮች የካቲት 5 ቀን 2009 ዓ.ም ሕዝቡን የሚያሳትፍ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል። 

"በውይይት መድረኩ የጥልቅ ተሃድሶው ውጤት ለሕዝቡ ይፋ ይደረጋል" ያሉት አቶ አዲሱ ሕዝቡም ድርሻውን ተረድቶ በተጀመረው ጥልቅ ተሃድሶ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። 

ውይይቱም ሕዝቡ ለሚያነሳው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ወደ ተጨባጭ ሥራ ለመግባት ያግዛል ብለዋል።   

 

Published in ፖለቲካ

አርባ ምንጭ የካቲት 1/2009 በጋሞ ጎፋ ዞን አራት ቆላማ ወረዳዎች በድርቅ ለተጎዱ ሰዎችና እንስሳት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቅና ምላሽ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ቃይሴ ቃዲላ ለኢዜአ እንደገለጹት በወረዳዎቹ ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ የዝናብ እጥረት አጋጥሟል፡፡

በዚህም ምክንያት ለአንድ ዓመት ያህል ምርት ካለመገኘቱም በላይ የእንስሳት መኖ እጥረት በመከሰቱ ከ143 ሺህ በላይ የቤተሰብ አባላትና 53 ሺህ እንስሳሳት ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡

ችግሩ ጎልቶ የታየባቸዉ ካምባ ፣ዛላ ፣ኡባደብረ ፀሐይና ቦንኬ ወረዳዎች ያሉ ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ከብቶቻቸዉን ይዘው በማዜ ብሔራዊ ፓርክ አቅራቢያ እንዲቆዩ ተደርጎ ነበር፡፡                                                                                                          

ነዋሪዎቹ በአሁን ወቅትም ወደ ቀያቸዉ መመለሳቸውንና ከነዚህ ውስጥ 71ሺ960 የቤተሰብ አባላት የምግብ እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡

እስካሁንም 40ሺህ የሚጠጋ ኩንታል ስንዴ፣ ጥራጥሬ፣  ዘይትና  አልሚ ምግብ ለተጎጂዎቹ መቅረቡንም ጠቅሰዋል፡፡

"ቀሪዎቹ ነዋሪዎች ደግሞ በቀጣዩ ሳምንት ድጋፉ የሚያገኙ ናቸው " ያሉት አቶ ቃይሴ የመኖ እጥረት ላገጠማቸዉ እንስሳት ደግሞ ከ38ሺህ በላይ  ጥቅል የመኖ ሣር እየተከፋፈለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት ላገጠማቸው ዛላ እና ኡባ ደብረ ፀሃይ ወረዳዎች በቦቴዎች  ውሃ እየቀረበላቸው እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በካምባ ወረዳ ማርታ ቦሄ ቀበሌ አርሶ አደር ዱርካ ዱንዴ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በአከባቢው የዝናብ እጥረት በማጋጠሙ ማምረት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

በዚሁ ምክንያት ለችግር መጋለጣቸውን ጠቁመው  በአሁኑ ወቅት መንግስት እያደረገላቸው ባለው  ድጋፍ በመጠኑም ቢሆን እፎይታ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በወረዳው የጎጋሌ ቀበሌ አርሶ አደር መልካሙ ገዱማጆ በበኩላቸው በድርቁ ምክንያት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ምርት ባለማግኘታቸው የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል፡፡

"መንግስት የሰውና የእንስሳትን ህይወት ለማትረፍ ፈጥኖ ድጋፍ እያደረገ በመሆኑ ከተወሰኑ ከብቶች ውጭ የጠፋ የሰዉ ህይወት የለም" ብለዋል ፡፡

አምርተው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ  መንግስት የጀመረውን ድጋፍ  አጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁት ደግሞ  በዞኑ የቦንኬ ወረዳ ኮሻለ ቀበሌ አርሶ አደር አቶ በቀለ ጋውላ ናቸው፡፡

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ የካቲት 1/2009 ቱርክ በኢትዮጵያ የምታካሂደውን የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አጠናክራ እንድትቀጥል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጠየቁ።

ፕሬዚዳንቱ የቱርክና የኢትዮጵያን ግንኙነት "ወደከፍተኛ ደረጃ ያደርሳል" ተብሎ የታመነበትን ጉብኝት በቱርክ አንካራ እያደረጉ ናቸው።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው ዶክተር ሙላቱ ከቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይፕ ኤርዶጋን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ቃል አቀባዩ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ በስልክ እንደገለጹት፤ ቱርክ ኢትዮጵያ ውስጥ የምታካሂደውን የኢንቨስትመንት ተግባራት አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ቱርክ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት የተጓዙት ጥር 29 ቀን 2009 ዓም ነው።

ኢትዮጵያ እያካሄደችው ለምትገኘው የልማትና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ቱርክ የበኩሏን ድጋፍ እንድታደርግ በጉብኝታቸው ጠይቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ350 በላይ የቱርክ ኩባንያዎች ሦስት ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ-ነዋይ በማውጣት በልማት እየተሳተፉ ናቸው።

ይህ ደግሞ ቱርክ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከምታደርገው ኢንቨስትመንት 50 በመቶ ያህሉን እንደሚሸፍን ነው የተመለከተው።

ኢትዮጵያ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ በሁለተኛው የእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅድ በኢንዱስትሪው በተለይም በማምረቻው ዘርፍ ለሚደረገው እንቅስቃሴ ሚናዋ የጎላ እንዲሆን መጠየቃቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 ቱርክ ወደ ኢትዮጵያ የ385 ሚሊዮን ዶላር ግብይት ያደረገች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ወደ ቱርክ የምትልከው የንግድ መጠን ግን 35 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይህን የንግድ ግንኙነት በማሳደግ በ2020 ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ መግባባት ላይ መድረሳቸውንም ነው አቶ ተወልደ የተናገሩት። 

ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በውይይታቸው፤ በየአገሮቹ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች የቋንቋ ፋኩልቲ ለማቋቋም ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ተስማምተዋል። ይህም በኢትዮጵያ የቱርክ፣ በቱርክ አማርኛ ቋንቋዎችን ለመስጠት ይችላሉ።

በአሁኑ ወቅት 400 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን በቱርክ ነጻ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸው ተወስቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ቱርክ በመሰረተ ልማትና በወልድያ ሀራ የባቡር መስመር ግንባታ እየተሳተፈች ሲሆን፤ የቱርክ ኤግዚም ባንክ ለዚሁ ፕሮጀክት የ300 ሚሊዮን ዶላር ብድር መስጠቱ ይታወቃል።

ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይፕ ኤርዶጋን ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በጉብኝታቸውም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለፕሬዚዳንቱ የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል።

ኢትዮጵያና ቱርክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1896 ነው።

Published in ኢኮኖሚ

የካቲት 1/2009 በአዲስ አበባ አሸዋ ሜዳና ቡራዩ የገበያ ማእከላት ዛሬ የዋለውን  የእህል ዋጋ  መረጃ  የኦሮሚያ ግብርና ምርት ገበያ ድርጅት አድርሶናል፡፡   

No automatic alt text available.

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 1/2009 የኅብረት ሥራ ማኅበራት አርሶና አርብቶአደሩን በገበያ በማስተሳሰርና ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ሚናቸው የጎላ እንደሆነ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

አራተኛው አገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚዬም “የህብረት ሥራ ማህበራት ግብይት ለዘላቂ ልማታችን ስኬት” በሚል መሪ ቃል በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ተከፍቷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤግዚቢሽኑን ሲከፍቱ እንዳሉት መንግስት ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ለቀረጻቸው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተግባራዊነትና ለተመዘገበው ፈጣን ዕድገት ስኬት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሚና የጎላ ነው።

ማህበራቱ ቀጣይነትና ተከታታይነት ያለው ኢኮኖሚ እንዲገነባና የአርሶና የአርብቶአደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የግብርና ግብአቶችን፣ ምርጥ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን በተቀላጠፈና በጥራት በማቅረብ ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት አዎንታዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ለተመዘገበው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት የኅብረት ሥራ ማኅበራት አርሶና አርብቶአደሩን በገበያ በማስተሳሰርና ተጠቃሚ በማድረግ የላቀ ሚና እንደነበራቸው ነው ያብራሩት።

የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና በዘላቂነት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ አቅም ለመገንባት የኅብረት ሥራ ማኅበራት የጎላ ፋይዳ አላቸው ነው ያሉት።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖርና ተወዳዳሪ የወጪ ንግድ ለመገንባት ማህበራቱ በግብርና ምርቶች እሴት ጭማሪ ላይ መሳተፍ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስትር ዶክተር እያሱ አብርሃ በበኩላቸው ገበያ ተኮር የአመራረት ስርዓት በመከተል የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪውን በመመገብ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው የኢኮኖሚ ሽግግር ማህበራቱ በግብይት ስርዓቱ ላይ የድርሻቸውን እንደሚያበረክቱ ገልፀዋል።

በመሆኑም ከውጭ የሚገቡ ልዩ ልዩ ምርቶችንና ቴክኖሎጂዎችን በመተካት የውጭ ምንዛሬን የማስቀረት ስትራቴጂና ዘመናዊ የግብርና ግብይት ሥርዓት ውጤታማ እንዲሆን በአግሮ ፕሮሰሲንግ የሚሰማሩ የኅብረት ሥራ ማህበራትን ቁጥር ማሳደግ ቁልፍ ተግባር መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ነው ያሉት።

ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚዬሙ ኅብረት ሥራ ማኅበራት አብረዋቸው ከሚሰሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ከግብርና ግብዓት አቅራቢዎች፣ ከማምረቻና የፍጆታ ዕቃ አቅራቢዎችና ከፋይናንስ አገልግሎት ተቋማት ጋር ትስስር ለመፍጠር ያለመ ነው።

መክፈቻው ላይ ሞዴል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተሞክሮና ስኬቶቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን ከውጭ የመጡ ኅብረት ሥራ ማኅበራትም ተሞክሯቸውን አቅርበዋል።

አራተኛው የህብረት ሥራ ማኅበራት ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚዬም ከየካቲት 1 እስከ የካቲት 8 ቀን 2009 ዓም በኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል።

ባለፉት ዓመታት ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ለማደራጀትና ለማጠናከር በተደረጉ ተግባራት ከ79 ሺህ በላይ ኅብረት ሥራ ማኅበራት 373 የህብረት ሥራ ዩኒየኖችና አራት የህብረት ሥራ ፌዴሬሽኖች ተቋቁመዋል።

በዚህም 15 ነጥብ 4 ሚሊዮን አባላትን በማፍራት ከ17 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማፍራታቸውን ከፌደራል የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ይጠቁማል።

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ የካቲት 1/2009 በአዳማ ከተማ ሥራ አጥነትን ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ ወደ ሥራ መገባቱን የከተማዋ አስተዳድር አስታወቀ።

በዚህም ስምንት ሺህ የሚጠጉ ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የአዳማ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ ገልጸዋል።

ከንቲባዋ እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል።

እስካሁንም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተመረቁትን ጨምሮ ከሰባት ሺህ 900 በላይ ለሚሆኑት በቋሚነትና በጊዚያዊነት የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወጣቶችን የመለየት ሥራ መሰራቱን አመልክተዋል።

ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ከወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ክፍተቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ለሥራ አጥ ወጣቶች የተገነቡ የማምረቻ፣ የመሸጫና መስሪያ ቦታዎች እንዲሁም የገበያ መዕከላትና የማምረቻ ክላስተሮች በህገ ወጥ መንገድ ወደ ባለሀብቶችና ግለሰብ ይዞታነት የተዛወሩ መሆኑን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ማዕከላቱን ወደ መንግስት ይዞታነት ለማስመለስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ እስካሁንም 28 ማዕከላትን ለማስመለስ መቻሉን ጠቁመዋል።

የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባና የጥቃቅን አነስተኛ ማይክሮ እንተርፕራይዝ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ጎፌ በተደረገው የማጣራት ሥራ ከ6 ሺህ 500 በላይ ሥራ አጣቶችን መለየት እንደተቻለ ገልጸዋል።

በሚቀጥሉት አምስት ወራት 5 ሺህ 900 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሙሉ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱን የገለጹት አቶ ካሳሁን፣ ሁለት ሺህ ሊሚሆኑት ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርም አስረድተዋል።

ወጣቶቹ ከሚሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች መካከል የምግብ ዝግጅት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የልብስ ስፌትና ዲዛይን፣ ብረታ ብረትና የእንጨት ስራ፣ መዕድን፣ ግንባታ፣ የከተማ ግብር፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የዶሮና እንስሳት እርባታ፣ የከተማ ጽዳትና ውበት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አቶ ካሳሁን ገልጸዋል።

ለዕቅዱ ማስፈፀሚያ ከ21 ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን አቶ ካሳሁን ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ የአዳማ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ፉፋ ቶላ በበኩላቸው  ከስልጠናና የንግድ ዕቅድ ጀምሮ የቁጠባ፣ የብድርና የዋስትና ማናቆዎች ከወዲሁ እንዲፈቱ ከአስተዳደሩ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚህ ቀደም ለማህበራት ማነቆ የሆኑትን ሙያዊ ስልጠናን ጨምሮ የንግድ ዕቅድ፣ የንግድ ፍቃድ፣ የግብር መለያ ቁጥር፣ የመስሪያና መሸጫ ቦታዎች እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮችን ቀድመው እንዲሟሉም በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ለወጣቶች የተመደበው በጀት ለተፈለገው ዓላማ እንዲውል ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ወጣቶችን የመመልመል ሥራ መከናወኑን የገለጹት ደግሞ በአዳማ ከተማ የቀበሌ 08 ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ ሰብለወንጌል ደቻሳ ናቸው።

ወጣቶችን ብቻ ማደረጀት በቂ አለመሆኑን ገልጸው ሙያዊ ስልጠና፣ ብድር፣ የመስሪያና መሸጫ ቦታዎች ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።

ትናንት በተካሄደው የአዳማ ከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ምክርቤት አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከልማትና ንግድ ባንክ፣ ከኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ እንዲሁም ከከተማ አስተዳድሩ የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 1/2009 በቅርቡ በአፋር ክልል ደቡብ ምስራቅ ኤርታሌ ተከስቶ የነበረው እሳተ ገሞራ በሰውም ሆነ በአካባቢ ላይ የከፋ ጉዳት የማስከተል አቅም እንደሌለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።   

በዩኒቨርስቲው የሥነ-ምድር ትምህርት ቤት የስትራክቸራል ጂኦሎጂ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ኪዳኔ እንደገለጹት በኤርታሌ ዙሪያ ተከስቶ የነበረው እሳተ-ገሞራ አነስተኛ በመሆኑ ወደፊት ጉዳት የማያስከትል ነው።

የኤርታሌ፣ የታታሌ፣ የአላይታና የማህደሮ ሰንሰለታማ እሳተ-ገሞራዎች ከቀይ ባህር ተነስተው እስከታች የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ የሚዘልቁ ናቸው። 

በእሳተ ገሞራ ሂደት የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የመሬት መዛነፍና መስመር የሚሰሩ የመሬት ቅርጾች የመፈጠር ምልክቶች እንደሚታዩ የገለጹት ፕሮፌሰሩ ይህም የአፍሪካና የዓረቢያ ልሳነ ምድር የመነጣጠል ውጤት ነው ብለዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ መሐመድ ከድር እንደተናገሩት የኤርታሌ አዲስ እሳተ ገሞራ ክስተት ከቱሪስት መስህብነቱ ባሻገር የዘርፉን ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ቀልብ ለመሳብ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል። 

የኤርታሌ እሳተ ገሞራ ትዕይንት በዓለም አስደናቂ በመሆኑ በርካታ ዘጋቢ ፊልሞች ተሰርተውበታል።

"በሌላው የዓለም ክፍል የሚፈጠር እሳተ ገሞራ ከፈነዳ በኋላ ጥቂት ጊዜ ቆይቶ የሚከስም ነው የኤርታሌ ትዕይንት ግን ከዓለም የተለየ የሚያደርገው ለረጅም ጊዜ መቆየቱ ነው" ብለዋል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ያዬ በበኩላቸው እንደገለጹት "አዲሱ የኤርታሌ እሳተ ገሞራ ክስተት የተለየ ትዕይንት የሚያሳይና የቱሪስቶችን ትኩረት የሚስብ ነው"።

በኤርታሌ ቅርብ ርቀት ላይ የታየው አዲስ እሳተ ገሞራ እስካሁን በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ምንም ዓይነት አደጋ አለመፍጠሩ ታውቋል።

ባለፈው ጥር ወር አጋማሽ በኤርታሌ የተከሰተውን እሳተ ገሞራ ተከትሎ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ክስተቱ ለአካባቢው አስጊና አደጋን የሚያስከትል ነው በማለት መዘገባቸው ይታወሳል።

 

Published in አካባቢ

የካቲት 1/2009 ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ ከወል ስትሪት ጆርናል ጋር ባደረጉት ቆይታ የአሜሪካ መንግስት የቻይናን ተሞክሮ በመውሰድ በአገር ውስጥ ሥራ ፈጠራ ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ ገለጹ፡፡

"ቻይና ሞዴል የሆነችው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ለአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደርም ነው," በማለት ለዘጋቢው ተናግረዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ቁልፍ የንግድ አጋርነትና ሽብርተኛነትን በመዋጋት ትብብራቸውን ማሳደግ አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል፡፡ “ቻይናውያን በአገራቸው እያስፋፉ ያሉት የማምረቻ ዘርፍ ለአሜሪካ ሞዴል ሊሆን ይገባል፡፡,"

የኢትዮጵያ ስፋት፣ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እና ጠንካራ ወታደራዊ አቅም አገሪቱን ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ከፍ ወዳለ ደረጃ አሸጋግረዋታል፡፡ በድርቅና በእርዳታ የምትታወቀው አገር ገፅታ አሁን ፍፁም ተለውጧል ብለዋል፡፡

አገሪቱ ጦሯን የአህጉሪቱን ግጭት ለማስወገድ በማሰማራት የማይናቅ ሚና እየተጫወተች ነው፡፡ከቻይና ፣ከባህረ ሰላጤው አገራትና ከአሜሪካ ጋር ያላት አጋርነት የአህጉሪቱን አለመረጋጋት ለማስወገድና ድህነትን ለመቅረፍ እየተጠቀመችበት ነው፡፡

አገሪቱ የተመረጡ የኢኮኖሚ ዘርፎችን መቆጣጠሯን ምእራባውያን የማይቀበሉት ጉዳይ ቢሆንም አገሪቱን እንደጠቀማት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዘጋቢው ነግረውታል፡፡

እአአ ከ2012 አንስቶ አገሪቱን እየመሩ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ  በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን አለመረጋጋት ለመከላከልና ጂሐዲስቶችን ለመዋጋት ከዋሺንግተን ጋር በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በጦርነት በሚታመሱት ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን በሺዎች የሚቆጠር ጦሯን አስፍራ አህጉራዊ ግዴታዋን እየተወጣች ነው፡፡

አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ ሸቀጥ የማስገባት እድል ወይም አጎዋን ለማስቀረት የያዙትን ውጥን እንዲያጤኑት ጠይቀው 17 አመት የቆየው ስምምነት በባራክ ኦባማ የአስተዳደር ዘመን በ 2015 ታድሷል፡፡ በስምምነቱም 40 የአፍሪካ አገራት ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን የንግድ ልውውጥ እንዲያሳድጉ አግዟቸዋል ብለዋል፡፡

"የአጎዋ ደንብ ለመጪዎቹ አስር አመታት እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ,"  በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ ተናግረው የሚስተር ትራምፕ "ቅድሚያ ለአሜሪካ" መልእክት የቤጂንግን ሞዴል መከተል አለበት ብለዋል፡፡

ጂሐዲስቶችን በመዋጋት በኩል ከሚስተር ትራምፕ ጋር በጥልቅ ትብብር እንደሚሰሩ ተስፋቸው መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ለአስርት አመታት የተመዘገበው ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት የአገሪቱን በራስ መተማመን ከፍ አድርጎታል፡፡የአለም የገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡አገሪቱ በሀምሳ አመት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የድርቅ አደጋ ቢገጥማትም እድገቷ አልተቋረጠም፡፡

በአገሪቱ የተተገበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሌሎች እንደሚሉት ሳይሆን የመርህ ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዘጋቢው አውግተውታል፡፡

መንግስት የተቆጣጠራቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ እንቅፋት አለመሆኑንም ጨምረው ገልጸውለታል፡፡ከ200 የበለጡ የመንግስት የንግድ ድርጅቶች ባለፉት ሀያ አምስት አመታት ለባለሐብቶች ተላልፈዋል፡፡ኬኬአር ኤንድ ኩባንያው በአበባ ምርት ፣የቱርክ፣የቻይና እና የአሜሪካ ኩባንያዎች በጨርቃ ጨርቅና ጫማ ማምረት ዘርፍ በመሰማራት በሺ ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል አስገኝተዋል፡፡

በ2011 ሶስት የመንግስት ቢራ ፋብሪካዎች ለዲያጆና ሔኒከን ኢንተርናሽናል በግማሽ ቢሊዮን ዶላር  የተሸጡ ሲሆን ባለፈው አመት የጃፓኑ ሲጋራ አምራች በ510 ሚሊዮን ዶላር የመንግስትን የትንባሆ ማምረቻ 40 በመቶ ድርሻ ገዝቷል፡፡

መንግስት አሁንም የውጭ ባለሐብቶችን በገንዘብ ተቋማት በችርቻሮ ንግድ እንዲሳተፉ አይፈቅድም በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስታቸውን አቋም ይፋ አድርገዋል፡፡

መንግስት ከነዚህ ዘርፎች በሚያገኘው ትርፍ በመታገዝ የባቡር መስመር ዝርጋታንና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ይደግፍበታል፡፡የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሐብቶች ክፍት ቢሆን በአገሪቱ ያሉትን ባንኮች ይውጧቸዋል በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም እውነታውን ግልፅ አድርገውታል፡፡" ባንኮቻችን ጡንቻቸውን እስኪያፈረጥሙ ድረስ በሩን አንከፍተውም፡፡"

የኢትዮጵያ መንግስት የሚያከናውናቸው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የኢትዮጵያ የእድገት ስትራቴጂ ዋነኛ መሰረት ሆነው ይቀጥላሉ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

በቻይና መንግስት ድጋፍ የተገነባው የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር መስመር አገልግሎት በአይነቱ በአፍሪካ የመጀመሪያው ሲሆን ባለፈው አመት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

በ 4.2 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስድስት ሺ ሜጋዋት ሐይል እንደሚያመነጭና በመጪው አመት እንደ ዝናቡ ሁኔታ ወደ ስራ እንደሚገባ መናገራቸውን ጠቅሶ ዘጋቢው ሐሳቡን ቋጭቷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን