አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Tuesday, 07 February 2017

አዲስ አበባ ጥር 30/2009 "ዋን ቤልት ዋን ሮድ" በተሰኘው የቻይና መሰረተ ልማት ፕሮጀክት ዙሪያ የዓለም መሪዎች በቤጂንግ ሊመክሩ መሆኑን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር አስታወቁ።

አምባሳደር ላ ይፋን ዛሬ በቢሯቸው ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርገዋል።

"ቻይና ከዓለም አገራት ጋር በተለያዩ የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች አማካኝነት ለመተሳሰር በዘረጋችው 'ዋን ቤልት ዋን ሮድ'  ፕሮጀክት ላይ መሪዎቹ በመጪው ግንቦት በቤጂንግ ይመክራሉ" ብለዋል።

በመድረኩ ከአንድ ሺህ በላይ የዓለም የተለያዩ ተቋማት ሚኒስትሮች፣ ፕሬዝዳንቶች፣ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ስራ አስኪያጆች የሚሳተፉ ሲሆን በፕሮጀክቱ አፈፃፀምና በዓለም አቀፍ ንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ይወያያሉ።

ፕሮጀክቱ መነሻውን ሼንጄን፣ በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ እስያ በማድረግ በምሥራቅ አፍሪካ በኩል ወደ ሜዲትራኒያን ባህር አውሮፓ በመድረስ 4 ቢሊዮን ህዝብ የሚኖርባቸውን አካባቢዎች ያቋርጣል።

በኢኒሼቲቩ የሚካተቱ አገራትን መለየት፣ አፍሪካ ምን ታገኛለች ምንስ ታጣለችና መሰል ጉዳዮች በምክክር መድረኩ መልስ እንደሚሰጥባቸው አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ቻይና የመንግስታቱ ድርጅት በ2030 እደርስበታለሁ ያላቸውን የዘላቂ የልማት ግቦች ለመፈፀም ለዓለም አበረከትኩት የምትለው ይህ ፕሮጀክት በተለይም በአፍሪካ ለሚተገበሩ የተለያዩ የልማት ስራዎች አማራጭ የገንዘብ፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንቨስትመንትና ሰፊ የገበያ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።

በሌላ በኩል አምባሳደር ላ ይፋን በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ሁከት ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው የቻይና ኩባንያዎች እንደነበሩ አንስተዋል።

ያም ሆኖ መንግስት አገሪቷን ወደ ቀድሞ ሠላሟ ከመመለስና ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ከመፍጠር አንፃር በወሰዳቸው እርምጃዎች ደስተኛ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ የህዝቡ ሰላም ወዳድነትና ከድህነት ለመውጣት የሚያደርገው ጥረት ዋነኛውን ድርሻ እንደሚወስድና ቻይናም ሰፊ ድጋፍ ማድረጓን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በህዝብ ለህዝብ፣ በፓርቲ ለፓርቲና በመንግስት ደረጃ ያላቸው ወዳጅነት መልካም መንፈስ የተላበሰ መሆኑ አገራቱ የሚተባበሩባቸው አጀንዳዎች እያደጉ እንዲሄዱ ማድረጉንም አውስተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ደሴ ጥር 30/2009 ወሎ ዩኒቨርሲቲ በደሴ ከተማ ለሚገኙ 18 ዓይነ ስውራን የመንግስት ሰራተኞች ኮምፒዩተርን በራሳቸው መጠቀም የሚያስችላቸውን ስልጠና ሰጠ፡፡

ዩኒቨርስቲው ዓይነ ስውራኑን ያሳለጠነው ለ15 ቀናት ሲሆን በጽህፈትና የንባብ ሶፍትዌር ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ባለፈው እሁድ በተካሄደው የስልጠናው ማጠናቀቂያ ፕሮግራም ላይ በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አስማረ ደጀን እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው አካል ጉዳተኞችን ለማብቃት የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲው ለዓይነ ስውራን የመንግስት ሰራተኞች ለአንድ ሳምንት ያህል መሰረታዊ የኮምፕዩተር አጠቃቀም፣ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የጽህፈትና የንባብ ክህሎት የሚሰጥ ስልጠና መስጠታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማርና ምርምሩ በተጓዳኝ በማህበረሰብ አገልግሎት በተለይም ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ዶክተር አስማረ አመልክተዋል።

ዘንድሮም ለዓይነ ስውራን መምህራን የሚያገለግሉ 20 ኮምፒዩተሮች ለደሴ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ማበርካታቸውን ጠቅሰዋል።

ወደ ፊትም ለሰልጣኝ ዓይነ ስውራን የመንግስት ሰራተኞች የላፕቶፕ ኮምፒዩተር ድጋፍ ለማድርግ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ከሰልጣኞቹ መካከል መምህር ዱባለ አባተ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው የሰጣቸው ስልጠና ራሳቸውን ችለው የዕለት ተዕለት ስራቸውን ለመፈጸም ያስችላቸዋል።

"የወሎ ዩኒቨርሲቲ በከፈተው እድል በነጻ የኮምፒተር ስልጠና ማግኘት በመቻሌ ስራዬን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በማስደገፍ በቀላሉ እንድሰራ ስላደረገኝ አመሰግናለሁ "ብለዋል።

በአማራ ክልል የደሴ ከተማ ቋሚ ምድብ ችሎት የክልል ዓቃቤ ህግ አቶ አማረ ሲሳይ በበኩላቸው ስልጠናው በስራቸው ላይ ተጨማሪ አቅም እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

ስልጠናው በስራ ቋንቋቸው በአማርኛ የመጻፍና የማንበብ ክህሎትን የሚያዳብር በመሆኑ የዕለት ተዕለት ስራቸውን ለማቀላጠፍ  ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግላቸውም ጠቁመዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ፍቼ ጥር 30/2009 በአካባቢያቸው በሚካሄዱ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የጸጥታ ሥራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች እንደገለጹት በተናጠልም ሆነ በጋራ  ከመንግስት ጋር ተቀራርበው በመስራት የአካባቢያቸውን ሰላም፣ ልማትና እድገት ለማፋጠን ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ናቸው።

በከተማው የሀገር ሽማግሌና የህግ ባለሙያ  አቶ ማሞ በላቸው በአካባቢያቸው እየተካሄዱ ያሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ያለ ምንም የፀጥታ ስጋት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም የድርሻቸውን አስተዋጽኦ ከማድረግ ባሻገር በአድልኦ፣ በወገናዊነትና በሙስና የሚፈጸሙ አፍራሽ ድርጊቶችን ለማጋለጥና በቁርጠኝነት ለመታገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

"በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ወጣቶች፣ ሴቶችና ምሁራን ማንኛውንም ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ አግባብ ብቻ በማቅረብ ለሀገሪቱ ሕዳሴ እውን መሆን ሊተጉ ይገባል" ብለዋል።

በተለይ ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢ እንደመሆናቸው በልማትና እድገት ጉዞ  የጎላ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በቅርቡ ወደ አመራርነት የመጡ ወጣቶችን ማበረታታት ሲያጠፉም በጊዜ በማረም በኩል የሕብረተሰቡ ተሳትፎ የጐላ መሆን እንዳለበትም አቶ ማሞ ጠቁመዋል።

"ሕዝብና መንግስትን የሚያቀራርቡ ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው" ያሉት ደግሞ የፍቼ ከተማ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ካባዬ መዝገቤ ናቸው።

ዴሞክራሲያዊ ሥርአት እንዲጐለብትና የሕዝብ የስልጣን ባለቤትነት እንዲረጋገጥ የሁሉም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የሀገር ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ጉዳይ የጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ብቻ ሳይሆን የሁሉንም የጋራ ጥረት የሚፈልግ መሆኑን ጠቁመዋል።

በከተማዋ የቀበሌ 04 ነዋሪ ወጣት ስንሻው አድማሱ በበኩሉ መብትና ግዴታ እንዲከበር በእኔነት ስሜት የራስን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንደሚገባ አመልክቷል።

"ለሀገሪቱ ሰላም ሁላችንም ሌት ተቀን ልንተጋ ግድ ይላል" የሚለው ወጣቱ በተለይ ዝምታ፣ ኪራይሰብሳቢነትና አደርባይነት በቀዳሚነት ሕዝብን እንደሚጎዳ ተናግሯል።

በህገ መንግስቱ የተጎናጸፈውን መብት ተጠቅሞ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከመንግስትና ከሕዝብ ጎን እንደሚቆምም ገልጿል።

ወጣት ስንሻው እንዳለው፣ በከተማው የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ የተወሰዱት እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።

ሕዝብን ሲያማርሩ የነበሩ አመራሮችን በአዲስ ለመተካትና ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ ለመስጠት የተኬደው ርቀት መልካም መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ የተጀመረው የተጠያቂነት አሰራር መጠናከር እንዳለበት አስረድተዋል።

በአካባቢው የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማስፋፋት እንዲሁም በነዋሪው የተነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለማቃለል በትኩረት እንደሚሰራ የገለጹት የፍቼ ከተማ ከንቲባ ተጫን ዋቅጅራ ናቸው።

በከተማዋ አሉ በተባሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ ከነዋሪዎች ጋር ውይይት መደረጉን ገልጸው፣ ለመፍትሄውም የጋራ ስምምነት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።

በቀጣይ የተለያዩ አደረጃጀቶችን ተጠቅመው ተጨባጭና ውጤታማ ሥራዎችን ለማከናወን በሙሉ አቅማቸው እንደሚንቀሳቀሱም ከንቲባው አረጋግጠዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥር 30/2009 ካንሰርን አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የአገሪቱ ህዝብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በየዓመቱ ጥር 30 የሚከበረውን የዓለም ካንሰር ቀን አስመልክተው የላኩት መግለጫ እንደሚጠቁመው የዘንድሮ መሪ ሃሳብ "እንችላለን፣ እችላለሁ" የሚል ነው።

በመግለጫው እንደተብራራው ካንሰርን ለመከላከል ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ቢሆንም አስቀድሞ ለመከላከል የኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

ስራ ላይ የዋለው ብሄራዊ የካንሰር መከላከል ዕቅድ ኢትዮጵያን በአፍሪካ አገር አቀፍ ዕቅድ አዘጋጅተውና በጀት መድበው በመተግበር ላይ ከሚገኙ አገራት መካከል አንዷ አድርጓታል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የካንሰር ህክምና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከ440 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የማስፋፊያ ስራዎች እየተከወኑም ነው።

የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያና መቆጣጠሪያ ደንብ ፀድቆ ስራ ላይ በመዋሉ በ120 የመንግስት ሆስፒታሎችና መንግስታዊ ባልሆኑ የህክምና ተቋማት ከ30 ሺህ በላይ ሴቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል።

ለ20 ዓመታት ሲካሄድ በቆየው የጤና ዘርፍ የልማት ፕሮግራም ከ15 ሺህ በላይ የጤና ኬላዎች፣ ከ3 ሺህ 200 በላይ የጤና ጣቢያዎችና ከ400 በላይ ሆስፒታሎች ሲገነቡ ከ38 ሺህ በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችም በየጤና ኬላዎቹ አገልግሎት እየሰጡ ነው።

በዚህም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ ውጤት ቢገኝም የህመሞቹ አሳሳቢነት እንዲሁም የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጫናው እየጨመረ ነው ሲል መግለጫው አትቷል።

በመሆኑም ካንሰርን አስቀድሞ ለመከላከል፤ ህመሙ እንደተከሰተ ወዲያው እንዲታወቅና ተገቢውን ህክምና በመስጠት የህሙማኑን ስቃይ ለመቀነስ፤ ታክመው የሚድኑበትን ሁኔታም ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ኅብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል።

የካንሰር ህመምን መቆጣጠር ካልተቻለ ከ20 ዓመታት በኃላ በየዓመቱ ለ24 ሚሊዮን ህዝብ ሞት ምክንያት እንደሚሆን ተመልክቷል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 30/2009 የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ በአየር ትንበያ ላይ ያተኮረ ስራ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።

አባል አገራቱ በአየር ንብረት ለውጥ ክስተት የሚደረሰውን ጉዳት ለመቀነስ አሁን እያደረጉት ካለው እንቅስቃሴ በተጨማሪ የአየር ትንበያን መሰረት በማድርግ መስራት ይኖርባቸዋል ተብሏል።

የኢጋድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ "በአፍሪካ ቀንድ በ2016/17 ለደረሰው አስከፊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ መስጠት" በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

በ45ኛው የኢጋድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ተወካይ ሚስ ሜካህ ሽሬትሳ እንዳሉት በየጊዜው የሚከሰተው አስከፊ ድርቅ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።

የኢጋድ አባል አገራት ይህን ችግር ለመቀነስ ከየአገራቱ የሚቲዎሮሎጂ ድርጅቶች የሚሰጠውን መረጃ በመቀበል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

አባል አገራቱ ኢትዮጵያ በሁለት ዓመታት ውስጥ በድርቅ የተጎዱ ዜጎቿን ቁጥር ከ10 ሚሊዮን ወደ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን የቀነሰችበትን ልምድ መውሰድ እንዳለባቸውም መክረዋል።

የመንግስታቱ ድርጅትም ከአገራቱ ጋር የጀመረውን ድርቅን የመቋቋም ስራ ይበልጥ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የኢጋድ የግብርናና የአካባቢ ልማት ዳይሬክተር ሚስተር ማሐመድ ሙሳ በበኩላቸው አገራቱ በሚቲዎሮሎጂና በዘርፉ ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር መቀበላቸው በአየር ንብረት ለውጥ ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት ለመቋቋም ይረዳቸዋል ብለዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በአየር ትንበያ ላይ የተመረኮዘ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታው ኢንጅነር ወንድሙ ተክሌም "አባል አገራት ከዘርፉ ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር በመቀበል በመጪዎቹ 3 ወራት ሊከሰት የሚችለውን ድርቅ ለመቋቋም በጋራ መስራት አለብን" ብለዋል።

"የኢትዮጵያ መንግስት ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ጋር በቅርበት እየሰራ ነው፤ እስከ ታችኛው መዋቅር ድርስ በማውረድም ከኤጀንሲው የሚገኘውን መረጃ ተግባራዊ እያደረግን ነው" ሲሉ አክለዋል።

ኤጀንሲውን ለማጠናከር የተለያየ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንና ዘለቂ የልማት ግቦችን ለማሳካትና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በ2010/11 በአፍሪካ ቀንድ 13 ሚሊዮን ዜጎች በድርቅ የተጠቁ ሲሆን ይህ ቁጥር በማሻቀብ በ2016/17 ወደ 17 ሚሊዮን ደርሷል።

Published in አካባቢ

ባህር ዳር ጥር 30/2009 በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከ17 ሺህ በላይ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ህጋዊ መሆናቸውን የክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በስፋት የሚስተዋለውን ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ለመከላከልና ህጋዊ መስመር ለማስያዝ እየተሰራ ነው፡፡

የንግድ እንቅስቃሴውን ህጋዊ ስርዓት ለማስያዝ በተደረገው የልየታ ስራ በክልሉ 19 ሺህ 714 ግለሰቦች ምንም አይነት ፈቃድ ሳይኖራቸው በህገ ወጥ መንገድ ሲሰሩ እንደነበር አውስተዋል።  

እነዚህን ግለሰቦች ወደ ህጋዊ የንግድ መረብ ለማስገባት በተደረገው እንቅስቃሴ ከ17 ሺህ 150 በላይ የሚሆኑት ፈቃድ አውጥተው በህጋዊ መንገድ እንዲሰሩ ተደርጓል።

ፈቃድ ለማውጣት ፈቃደኛ ያልሆኑትን ደግሞ ድርጊቱን እንዲያቆሙ መደረጉን ነው አቶ ተዋቸው የገለጹት።

''የንግድ ፈቃድ ሳይኖረው ሲሰራ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ ከሰባት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራትና በገንዘብ እንደሚቀጣ እያስተማርን ነው'' ብለዋል።

በባህርዳር ከተማ አስተዳደር በተዘጋጁ ልብሶች ንግድ ስራ የተሰማራው ወጣት መሀመድ አለቤ በሰጠው አስተያየት ህገወጥ ንግድን መንግስት መቆጣጠር ካልቻለ ህጋዊው ነጋዴ ተወዳዳሪ ሆኖ መዝለቅ እንደማይችል ገልጿል፡፡

መንግስት  በህገወጦች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ከማድረግ ባለፈ በህጋዊ መንገድ ሰርተው የሚለወጡበትን ሁኔታ ሊያመቻች እንደሚገባ ጠቁሟል።

“የመስሪያ ቦታ ተከራይቼ የምሰራበት የገንዘብ አቅም ስለሌለኝ ራሴን ለማስተዳደር ስል የተለያዩ ልብሶችን ጎዳና ላይ ዘርግቼ ለመስራት ተገድጇለሁ” ያለው ደግሞ የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወጣት አበበ ክንዱ ነው።

መንግስት በቀጣይ በቋሚነት ተረጋግቶ የሚሰራበት ቦታና ለመስሪያ የሚሆን ብድር ቢያመቻችለት ከህገ ወጥ ንግድ በመውጣትና ተረጋግቶ በመስራት ራሱንና ቤተሰቡን ለመጥቀም ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።

በክልሉ በተለያየ ደረጃ የንግድ ፈቃድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ ከ300 ሺህ በላይ ነጋዴዎች እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 30/2009 ከኃላፊነታቸው የሚነሱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሚያገኟቸውን መብቶችና ጥቅማጥቅሞች ለመወሰን የወጣው የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ።

በረቂቅ አዋጁ የመንግሥት መሪዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች መብትና ጥቅማጥቅም የሚገባቸው የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንደሆኑ ተቀምጧል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባ ረቂቅ አዋጁንና ሰባት የብድር ስምምነቶችን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ ቀደም ሲል ከኃላፊነት የሚነሱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን መብትና ጥቅማጥቅም ለማስከበር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 653/2001 ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።

በዚሁ መሰረት፤ ረቂቅ አዋጅ 8/2009 ሆኖ ለዝርዝር ዕይታና ምርመራ በዋናነት ለበጀትና ፋይናንስ እንዲሁም በተባባሪነት ለሕግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ተመርቶ ነበር።

ቋሚ ኮሜቴዎቹም በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ መሰረት በረቂቅ አዋጁ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባልደረቦች ጋር ጭምር ዝርዝር ውይይት ማካሄዳቸው ተገልጿል።

የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በተወሰኑ የአዋጁ ክፍሎች ላይ ብቻ መጠነኛ ማሻሻያዎችን በማድረግ እንዲሁም በመንግሥት በጀት ላይ የተለየ ተጽዕኖ የማይፈጥር መሆኑን ቋሚ ኮሚቴዎቹ አረጋግጠዋል።

በዚህም ከኃላፊነታቸው ለተነሱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተፈቀደው የመኖሪያ ቤት አገልግሎት ሁለት የምርጫ ዘመን ወይንም ከዚያ በላይ ላገለገሉ የምክር ቤት አባላት ተፈጻሚ እንደሚሆን ተደንግጓል።

አንድ የምርጫ ዘመንና ከግማሽ ያላነሰ አገልግሎት፤ በህመም፣ በአካል ጉዳት ወይንም ከአቅም በላይ በሆነ ሌላ ምክንያት ከኃላፊነት ከተነሳ ለራሱና ለቤተሰቦቹ ኪራይ እየከፈለ የሚኖርበት ቤት ይሰጠዋል ተብሏል።  

ከኃላፊነት የተነሳ የቀድሞ የምክር ቤት አባል ቀድሞ በነበረበት የመንግሥት መሥሪያ ቤት በአዋጁ አንቀጽ 9 መሰረት መመደብ ካልቻለ በሌሎች መሥሪያ ቤቶች በተመሳሳይ ክፍት የሥራ ቦታ ተመድቦ እንዲሰራም እንዲሁ።

ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል ከኃላፊነት ተነስቶ ጥቅሞችን ከማግኘቱ በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ ሊከፈለው የሚገባው የመቋቋሚያ አበል፣ የሥራ ስንበት ክፍያ፣ የመኖሪያ ቤት አበልና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ለቤተሰቡ እንዲሰጥም ተፈቅዷል።

ማሻሻያው ሌሎች ጉዳዮችንም ያሻሻለ ሲሆን የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተሰማሩበት የሥራ መስክ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አንዲወጡ ያስችላል ነው የተባለው።

ተሿሚዎች ከኃላፊነታችን ከተነሳን በኋላ ምን እንሆናለን ከሚል ስጋት ለማላቀቅ እንደሚረዳም ተጠቁሟል።

ወደ መንግሥት የሥራ ኃላፊነት የሚመጡ አዳዲስ ግለሰቦችን ከማበረታታት በዘለለ በመንግሥት ተቋማት ያለውን የአሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት የማጎልበት ሚናው ከፍተኛ እንደሆነም ነው የተነገረው።

የቀረበው የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የሥራ ኃላፊዎች ከሥራቸው ከተሰናበቱ በኋላም ያካበቱትን ልምድና እውቀት ለአገር ልማት ለማዋል የሚያስችል መሆኑ ላይም ሥምምነት ተደርሶበታል።

በዚሁ መሰረት የበጀትና ፋይናንስ እንዲሁም የሕግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በጋራ በመሆን የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ እንዲጸድቅ ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበዋል።

ምክር ቤቱም በቋሚ ኮሚቴዎቹ የቀረበውን የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው በአገሪቷ የተጀመሩና አዳዲስ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ፋይናንስ ማድረግ የሚያስችሉ ሰባት የብድር ስምምነቶችን አጽድቋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 30/2009 የጭነት ማመላለሻ ዋጋ ከፍተኛ መሆን የአገሪቷን የውጭና የውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ በማዳከም ኢኮኖሚውን ጎድቶታል ሲል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት አመለከተ።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር በጭነት ማመላለሻ አገልግሎት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስወገድና ፈጣንና በዋጋ ተመጣጣኝ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ችግሮቹን እንዲያጠናለት ከአንድ ዓመት በፊት ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተስማምቶ ነበር።

በዚሁ መሰረት ጥናቱን ያካሄደው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ትምህርት ክፍል ዛሬ ውጤቱን ይፋ አድርጓል።

ጥናቱ እንዳሳየው በጭነት ትራንስፖርቱ ዘርፍ ያለው ከፍተኛ ዋጋ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምር ያደርጋል።

አገሪቷ ወደ ውጭ አገራት የምትልካቸው ምርቶችም በትራንስፖርት ዋጋው መናር ሳቢያ ከሌሎች ዓለማት ምርቶች ጋር እንዳይወዳደሩ ያደርጋል።

ጥናቱ በጭነት ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ የሚስተዋሉ በርካታ ተግዳሮቶችን ዘርዝሯል።

በአገሪቷ የሚገኙ የጭነት ተሽከርካሪዎች ውስንነት፣ ያሉትንም በአግባቡ ማስተዳደር አለመቻል፣ በአገር ውስጥ አጭር ርቀት የሚጓዙት ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ የአገልግሎት ዋጋ መጠየቅና የዋጋ ትመናው በዘፈቀደ መካሄድ ከተጠቀሱ ተግዳሮች መካከል ናቸው።

በተጨማሪም ድንበር አቋራጭ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች ለብዙ ቀናት የሚዘልቅ የወደብ ላይ ወረፋ ጥበቃና ለጉዞ ከሚያጠፉት ጊዜ የበለጠውን የሚወስደው የፍተሻ ቆይታ የዋጋ ጭማሪው ምክንያቶች ተብለዋል በጥናቱ።

የእነዚህ በርካታ ችግሮች መኖር የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎቱ ዋጋ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጓል ሲል ጥናቱ ጠቅሷል።

"ይህ በጭነት ትራንስፖርት ዘርፉ የሚስተዋል የዋጋ ጭማሪ አገሪቷ ከሰብል ማጓጓዝና ወደ ውጭ አገራት በመላክ ልታገኘው የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዳታጣጥም አድርጓታል" ሲሉ የጥናቱ አቅራቢ ዶክተር መሃመድ ሰዒድ ተናግረዋል።

በጊዜና በዋጋ ተመጣጣኝ የሆነ የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖሩ አገሪቷ ወደ ውጭ በመላክና በማስገባት የምታገኘውን ጥቅም በአሉታዊ መንገድ ጎድቶታል።

ዓለም ከደረሰበት የትራንስፖርት አቅም ጋር የአገሪቷን የጭነት ትራንስፖርት ዘርፍ ለማጣጣም በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የጠቆሙት ደግሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አብዲሳ ያደታ ናቸው።

የጥናቱን ውጤት እንደ ግብዓት በመውሰድ ችግሮችን የመፍታት ስራዎች ይከወናሉ ነው ያሉት።

"ከአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታና ሕግ ጋር የማይቃረኑ የጥናቱን ውጤቶች እንደ ፖሊሲ ግብዓት በመጠቀም የተሻለ የጭነት ትራንስፖርት ዘርፍ ለመገንባት እንጠቀምባቸዋለን" ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

Published in ኢኮኖሚ

ድሬዳዋ ጥር 30/2009 የሀገሪቱን ሰላም ፣ እድገትና ልማት የሚጎዱ ተግባራትን ለመከላከል የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ፡፡

ጉባኤው ከፌደራልና አርብቶአደር ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሰላም እሴት ግንባታ  ላይ ለባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው  የአሰልጣኞች ስልጠና በድሬደዋ ተጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ፀሐፊ አቶ ሑሉፍ ወልደ ሥላሴ ስልጠናው ትናንት ሲጀምር እንደገለጹት ኃይማኖቶች በሙሉ የፈጣሪ ፀጋ  የሆነው ሰላም በሰዎች መካከል ትልቅ ስፍራ እንዲኖረው በትኩረት ያስተምራሉ፡፡

" በተለይም የሀገርን አንድነትና ልማት የሚጎዱ ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴዎችን በተናጠልና በተቀናጀ መንገድ በመመከት የተጀመሩ የፀረ-ድህነት ዘመቻዎች እንዲሳኩ የኃይማኖት ተቋማት የጀመሯቸውን  ተግባራት ያጠናክራሉ "ብለዋል፡፡

አቶ ሑሉፍ እንዳመለከቱት በአንዳንድ አካባቢዎች ከተከሰቱት ግጭቶችና የሰላም እጦቶች ትምህርት በመውሰድ  መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ ጉባኤው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለመፍትሄዎቹ ቀድሞ ይንቀሳቀሳል፡፡

" ህዝባችንን ስለ ሰላምና አብሮነት በስፋትና በጥልቀት በማስተማር ነዋሪው ለሰላም ግንባር ቀደም ሆኖ እንዲሰለፍ ማድረግ ይጠበቅብናል" ብለዋል፡፡

የሀገሪቱን ሰላም ፣ እድገትና ልማት የሚጎዱ ተግባራትን ለመከላከል ጉባኤው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀል የተናገሩት ፀሐፊው በድሬዳዋ የተዘጋጀው ሥልጠና ይህንኑ ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን ጠቀስዋል፡፡

በፌደራልና አርብቶ አደሮች ጉድይ ሚኒስቴር የኃይማኖትና የእምነት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሐጂ አሊ በበኩላቸው የሀገሪቱ የኃይማኖት ተቋማትና ተከታዮቻቸው በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶችን ማጎልበት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ጠንቅቀው በማወቅና በማሳወቅ አክራሪነትንና ፅንፈኝነትን በጋራ መመከት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ 

አቶ ሐጂ እንዳሉት የኃይማኖት ተቋማት በኃይማኖት ሽፋን የሚካሄድ ፀረ- ሰላምና ፀረ- ልማት እንቅስቃሴዎችን በመከላከል  ረገድ እያከናወኑ የሚገኙት ተግባራት አበረታች ውጤት እያስገኘ ነው፡፡

ይህንን ከማጠናከር በተጓዳኝ በተለይ ሴቶችና ወጣቶች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሀገርን ዕድገትና አንድነት በማይፈልጉ ኃይሎች አጀንዳዎች እንዳይጠለፍ  ማስተማር እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡

በየጊዜው የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች በሰላም እሴቶችና በሀገር እድገት ላይ የጋራ መግባባት እንዲኖር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው ናቸው፡፡

ሶስት ቀናት በሚቆየው የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ  የኢትዮጵያና የድሬዳዋ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ አመራሮች፣ የድሬዳዋ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ተጠሪዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ናቸው፡፡

በሠላም እሴት ግንባታና በሴኩላሪዝም ፅንሰ ሃሳብ ላይ  ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድም ተመልክቷል፡፡፡

Published in ፖለቲካ

ሰመራ ጥር 30/2009 በአፋር ክልል ስፖርቱን ለማሳደግ የሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።

በኮሚሽኑና በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ትብብር በአምስት የስፖርት አይነቶች ለ10 ቀናት ሲሰጥ የቆየው የዳኝነትና አሰልጣኝነት ስልጠና ትናንት ተጠናቋል።

የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሺነር አቶ መአር አሊሴሮ እንደገለጹት በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ክልሉንና ሃገርን መወከል የሚችሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት በታዳጊ ወጣቶች ስልጠና ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ወጣቶች ወቅቱ የሚጠይቀውን ሳይንሳዊና ዘመናዊ ስልጠና እንዲያገኙና የውስጥ ውድድሮችን በብቃት መዳኘት እንዲቻል በዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ጠቅሰዋል።

ከፌደራል ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በክልሉ በየጊዜው ለአሰልጣኞችና ዳኞች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ሲሰጥ ቢቆይም፣ የሚፈለገውን ያህል የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል አሁንም ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል።

በተለያዩ የስፖርት አይነቶች አሰልጣኞችንና ዳኞችን በጥራትና በብዛት ለማፍራት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ እቶ ሲሳይ ሳሙኤል በበኩላቸው፣ መስሪያ ቤታቸው ዘንድሮ በአምስት የስፖርት አይነቶች 600 ለሚሆኑ የታዳጊ ክልል ባለሙያዎች የዳኝነትና አሰልጣኝነት ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በስልጠና መርሀ ግብሩ በቮሊቮል፣ በጠረቤዛ ቴኒስ፣ በቦክስ ዳኝነት እንዲሁም በዳርትና በክብደት ማንሳት አሰልጣኝነት 150 የሚሆኑ የአፋር ክልል ባለሙያዎች ስልጠና ማግኘታቸውንም አመልክተዋል ።

መንግስት በስፖርት ዘርፍ በአገሪቱ የሚታየውን የባለሙያ እጥረት በመፍታት በዘርፉ በክልሎች መካከል ተቀራራቢ እድገት እንዲኖር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ስልጠናው መሰጠቱን ተናግረዋል።

በስልጠናው በክልሉ ስር የሚገኙ 32 ወረዳዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

Published in ስፖርት
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን