አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 06 February 2017

አዲስ አበባ  ጥር 29/2009 የሴቶችን ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደቡብ ሴቶች ማህበር ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ዛሬ ተካሂዷል።

በጉባዔው ላይ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ባደረጉት ንግግር በተደራጀ አካሔድ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

በሴቶች ላይ ለዘመናት ሰፍኖ የቆየውን የተዛባ አመለካከት ለማስወገድ በተባበረና በተቀናጀ መልኩ መታገል እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

ሴቶች ሕገ-መንግሥቱ ያጎናጸፋቸውን መብቶች ተጠቅመው በአገሪቱ ልማት ውስጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ እንደሚያስችልም ነው የጠቆሙት።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች በሚታየው ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዕድሜያቸው ለአካለ መጠንና ለትምህርት ያልደረሱ ህፃናት ወደ ከተማ እየፈለሱ ይገኛሉ።

የማህበሩ አባላት አደረጃጀታቸውን ተጠቅመው ችግሮችን ለማቃለል ትኩረት በመስጠት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል።

''በህፃናት ላይ የሚደርሰውን የጉልበት ብዝበዛ ለመቀነስና ድህነትን መዋጋት ዋነኛ ተግባር ነው'' ያሉት ቀዳማዊት እመቤቷ "ሴቶች ደግሞ የችግሩ ጥምር ተጎጂዎች በመሆናቸው ይህም ትኩረት ይሻል" ነው ያሉት።

እነዚሁ የኅብረተሰብ ክፍሎች በቤት ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን በመዋጋት ረገድም የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የደቡብ ሴቶች ማህበር የአዲስ አበባ ቅርንጫ ሰብሳቢ ወይዘሮ ውዴ ቴሶ በበኩላቸው በመዲናዋ በርካታ ሴቶች በጥቃቅንና አነስተኛ  ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ተጠቃሚ ሆነዋል።

በየደረጃው በሚገኙ የምክር ቤቶችም አባል በመሆን ሚናቸውን በመወጣት ላይ ሲሆኑ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ደግሞ  በተለያዩ መዋቅሮች ወደ አመራር ሰጭነት ቦታ መጥተዋል ብለዋል።

በተፈጠረው የዴሞክራሲ ሥርዓት ሴቶች የተለያዩ ድሎችን ያጣጥሙ ቢሆንም በክልሉ በሴቶች ላይ በርካታ ጥቃቶች፣ በደሎችና ጭቆናዎች ይደርሰባቸዋል ብለዋል።

''በመዲናዋ የክልሉ ተወላጅ ሴቶች ተደራጅተው ባለመንቀሳቀሳቸው በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ እንቀስቃሴ ላይ ያላቸው ተሣታፊነትና ተጠቃሚነት የተሟላ ነው ማለት አያስደፍርም፤ ችግሩን ለመቅረፍ ማህበሩ ወደ ተግባር እንቀስቃሴ ገብቷል'' ነው ያሉት።

የደቡብ ሴቶች ማህበር ሊቀ መንበር ወይዘሮ አስቴር ይርዳ እንደሚሉት የክልሉ ሴቶች በሕገ-መንግሥቱ የተረጋገጠላቸውን መብቶቻቸውን በማስከበር ተሳትፎ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በማህበራት ተደራጅተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።

የክልሉ ሴቶች እንዲቆጥቡ፣ የልማት ቡድን አጀንዳ በማድረግ በገጠርም ሆነ በከተማ ወደ ሥራ በመግባታቸው ውጤት በማስመዝገብ ከራሳቸው አልፈው ለህዳሴው ግድብ የቦንድ ግዢ እየፈፅሙ ይገኛሉ ብለዋል።

የማህበሩ አባላት ቁጥርም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

በማህበር ተደራጅቶ መንቀሳቀስ ከተጠቃሚነት በላይ ከጠባቂነትና ከጥገኝነት በመላቀቅ ራስን ለማብቃት ጠቀሜታው የጎላ ነው ሲሉ የጉባዔው ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 29/2009 የእንግሊዝ የታዳሽ ኃይል ኩባንያዎች ከ 850 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የገናሌ ዳዋ ቁጥር 6 የኃይል ማመንጫና የመስኖ ፕሮጀክቶችን ሊገነቡ ነው።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ የእንግሊዝ የታዳሽ ኃይል ኩባንያዎች ግሎብሌክና አጋሮቹ የልዑካን ቡድንን ዛሬ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ተቀብለው አነጋግረዋል።

የካምብሪጅ ኢንዱስትሪዎች የኮርፖሬት ጉዳዮችና ዋና አማካሪ የሆኑት አሌክስ ስቴዋርት ለጋዜጠኞ  እንደገለጹት ኩባንያዎቹ 250 ሜጋ ዋት የሚያመነጨውን ገናሌ ዳዋና የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታን ያከናውናሉ።

የመስኖ ፕሮጀክቱ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች 27 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።

እናም ኩባንያዎቹ ባለፉት ሦስት ዓመታት በገናሌ ዳዋ 6 የኃይል ማመንጫ ግንባታ በማህበራዊና አካባቢያዊ ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ተጽዕኖ የዳሰሳ ጥናት ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።

ለሁለቱም ፕሮጀክቶች ግንባታ ከ 850 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገንዘብ የተመደበ ሲሆን ለ 55 ሺህ ሰዎች የሥራ ዕድል ያስገኛል ብለዋል።

የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በዚህ የበጀት ዓመት የሚጀመር ሲሆን በአምስት ዓመት ውስጥም ይጠናቀቃል ነው የተባለው።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ በዚሁ ጊዜ በኃይል ዘርፍ ልማት ለሚሰማሩ ኩባንያዎች መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በተለይ በታዳሽ ኃይል ልማት ለሚሰማሩ እንደ ግሎብሌክ ያሉ ኩባንያዎች መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው ያረጋገጡት።

የገናሌ ዳዋ 6 የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ ከእንግሊዙ ሲ.ዲ.ሲ ፈንድና ከኖርዌይ መንግሥት በተገኘ ድጋፍ የሚከናወን ነው።

Published in ኢኮኖሚ

ደሴ ጥር 29/2009 በደሴ ከተማ  ሆጤ ስታዲዮም ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በሁለቱም ጾታ በአዲስ አበባ ፖሊስ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

ከጥር 24/2009 ጀምሮ ለአምስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው ውድድር  ከአምስት ክልሎች የተውጣጡ 87 ወንድና ሴት ተወዳዳሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡

በውድድሩም በወንዶች  አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ማራቶንና  ፌዴራል ፖሊስ  እንደቅደም ተከተላቸው ባስመዘገቡት  ነጥብ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በሴቶችም አዲስ አበባ ፖሊስ በ12 ነጥብ አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ማራቶንና አካዳሚ ክለቦች ደግሞ ተከታዩን ቦታ ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ሃላፊ አቶ ዮሐንስ  ብርሐኔ እንደገለጹት ውድድሩ የደሴና አካባቢው ማህበረሰብ ለቦክስ ስፖርት ያለውን ፍቅር ያረጋገጠበት ሆኖ አልፏል።

"ውድድሩም ደማቅና ፉክክር የተስተዋለበት፣ ስፖርታዊ ጨዋነት የተረጋገጠበት፣ በርካታ ተመልካች የተከታተለው በመሆኑ ስኬታማ ነበር" ብለዋል፡፡

የዘንድሮው ሻምፒዮና ውድድር ከዚህ ቀደም  ተሳትፎ ያልነበራቸው ክለቦች በማካተት ፍጻሜውን ማግኘቱንም ጠቁመዋል።

የቀድሞ የቦክስ ስፖርት ተወዳዳሪና የደሴ ከተማ ቦክስ ክለብ አሰልጣኝ እሸቱ ጨርቆሴ "ውድድሩ በደሴ ከተማ መካሄዱ በአካባቢው ተቀዛቅዞ የነበረውን የቦክስ ስፖርት ውድድር እንዲነቃቃ ያደርገዋል "ብሏል፡፡

ለአሸናፊ ክለቦች ሽልማት ያበረከቱት የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ላቀው ከበደና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ናቸው፡፡

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ጥ 29/2009  ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ ወደ ቱርክ አንካራ አቀኑ።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ከቱርኩ አቻቸው ሬሲፕ ጣይፕ ኤርዶጋን በቀረበላቸው ግብዣ መሰረት ነው ወደ አንካራ ያመሩት።

የሁለቱ አገራትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ማጠናከር የጉብኝቱ ዓላማ እንደሆነም ተገልጿል።

ፕሬዚዳንቱ በአንካራ ቆይታቸው ከፕሬዚዳንት ኤርዶጋንና ከሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ንግድና ኢንቨስትመንት ማሳደግ በሚቻልበት ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

አገራቱ በባህልና በትምህርት ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከርም ሌላው ትኩረት የሚያደርጉበት እንደሚሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፍ የቱርክ ኢንቨስትመንት መዳረሻ አገር እንደሆነችም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ከ 350 በላይ የሚሆኑ የቱርክ ኩባንያዎች 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረጋቸውንም በማሳያነት ጠቅሷል።

ይህ ደግሞ ቱርክ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከምታደርገው ኢንቨስትመንት 50 በመቶ ያህሉን የሚይዝ ነው።

ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በጉብኝታቸውም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለፕሬዝዳንቱ የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል።

ኢትዮጵያና ቱርክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1896 ነው።

Published in ፖለቲካ

አክሱም  ጥር 29/2009 በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ባለፉት ስድት ወራት ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በመትጋት ላይ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የታሕታይ ማይጨው ወረዳ ወጣቶች ገልፀዋል።

በዞኑ አስተዳደር የወጣቶች ተሳትፎ አስተባባሪ አቶ ለአከ አባይ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፣ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ከተሞች የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ከ12 ሺህ በላይ ሴቶች ናቸው፡፡

ወጣቶቹ ከተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች መካከልም ግብርና፣ ኮንስራክሽን፣ ማእድንና ኢንዱስትሪ የሰራ ዘርፎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በዞኑ በተደረገው ጥናት አሁንም ከ95 ሺህ 500 በላይ ስራ አጥ ወጣቶች መኖራቸውን የገለጹት አስተባባሪው ፣ ''እነዚህን ወጣቶች ወደ ስራ ለማስገባት የተለያዩ አማራጮች እየተጠኑ ነው'' ብለዋል።

በሁሉም ወረዳዎችና ከተሞች የወጣቶች ኮንፈረንስ መካሄዱን የተናገሩት አቶ ለአከ ''በኮንፈረንሱ ላይ ወጣቶች ራሳቸው የተለያዩ አማራጭ መንገዶችን እንዲያስቀምጡ እድል ተሰጥቷቸዋል'' ብለዋል።

በቂ የብድር አቅርቦትና የማምረቻና መሸጫ ቦታ መዘጋጀቱን ገልፀው፣ ወጣቶች የሚያነሷቸውን ችግሮች በቅርበት በመከታታል ለመፍታት የሚረዱ የወረዳ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውን ተናግረዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ ሞዴል ወጣቶች ከሰራ አጥ ወጣቶች ጋር ተገናኝተው የልምድና የተሞክሮ ልውውጥ ማድረጋቸው ተቁሟል።

መንግስት ያስቀመጠውን የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ፓኬጅ ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውና ተሳታፊነታቸውን ለማረጋገጥ በትጋት በመስራት ላይ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ገልፀዋል፡፡

በታሕታይ ማይጨው ወረዳ የማይብራዝዮ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት በርሄ ገብረሚካኤል እንደሚለው፣ ከሁለት አመት በፊት ምንም ስራ እንዳልነበረው አስታውሷል፡፡

አሁን ግን በሚኖርበት አከባቢ ያለውን የውሃ ሃብት ተጠቅሞ የመስኖ ልማት በማካሄድ በሚያገኘው ገቢ ከጥገኝነት መላቀቁንና ሞዴል ወጣት ለመሆን መብቃቱን ተናግሯል።

ከሚያካሂደው የመሰኖ ልማት  ከ12 ሺህ ብር በላይ በቁጠባ ያስቀመጠ ከመሆኑም በላይ ባለሁለት ክፍል የቆርቆሮ ክዳን መኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን መብቃቱን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም መንግስት የተለያዩ የውሃ አማራጮችን አዘጋጅቶልናል ያለው ወጣቱ፣ አማራጮቹን በመጠቀም የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን በትጋት እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡

ከሞዴል ወጣቶች በርካታ ጠቃሚ ተሞክሮ እንደወሰደና ለቀጣይ በግልና በማህበር ተደራጅቶ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንደሚሆን የተናገረው ደግሞ ወጣት ክብሮም ወልደትንሳኤ ነው።

ትምህርቱን አቋርጦ ላለፉት 4 አመታት የቤተሰብ ጥገኛ መሆኑን የተናገረው ወጣት ክብሮም፣ በአካባቢው በተካሄደው ኮንፈረንስ በመካፈል ከሞዴል ወጣቶች ካገኘው ልምድ ያለበትን የስራ ጠባቂነትና የአስተሳሰብ ችግር ማስወገዱን ገልጿል፡፡

መንግስት ባመቻቸለት የብድር አገልግሎትም ሰርቶ ራሱን ለመለወጥ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

''እስካሁን ያጠፋሁት ወርቃማ ጊዜ ይቆጨኛል'' ያለው ወጣት ክብሮም፣ ''ባጭር ጊዜ ውስጥ  ሞዴል ወጣት ሁኜ ሌሎች ወጣቶችን ፈለጌን እንዲከተሉ አደርጋለሁ'' ብሏል።

የታሕታይ ማይጨው ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ብርሃነ በበኩላቸው፣ በወረዳው የሚገኙ ሰባት ሺህ የሚጠጉ ስራ አጥ ወጣቶችን በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለማሰማራት 11 ሚሊዮን ብር መመደቡን ተናግረዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 29/2009 አራተኛው አገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ማህበራት ዓውደ ርዕይ በኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚካሄድ የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ገለጸ።

ዓውደ ርዕዩ  "የኅብረት ሥራ ማኅበራት ግብይት ለዘላቂ ልማታችን ስኬት" በሚል መሪ ሃሳብ ከየካቲት 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት ለእይታ ክፍት ይሆናል።

በአገሪቱ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ለማጠናከርና ለማደራጀት በተደረገው እንቅስቃሴ ከ 79 ሺህ በላይ መሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን መፍጠር ተችሏል።

በዚህም ማኅበራቱ ከ 15 ሚሊዮን በላይ አባላትን ማፍራት እንደቻሉ ነው ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ የሚያሳየው።

እነዚህ ማኅበራት በአጠቃላይ ከ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ሲሆን 370 የኅብረት ሥራ ማህበራትና ዮኒየኖችም በአገር አቀፍ ደረጃ ተደራጅተዋል።

እናም የኅብረት ሥራ ማህበራት ምርትና አገልግሎታቸውን በዓውደ ርዕዮች በማቅረብ እንዲያስተዋውቁ በማድረጉ የገበያ ትስስር እንዲፈጠረላቸው እየተሰራ ይገኛል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ሱሩር እንደሚሉት ዓውደ ርዕዩ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ያላቸውን ምርትና አገልግሎት ለተጠቃሚዎች ለማስተዋወቅ የሚረዳ ነው።

ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ የኅብረት ሥራ ማህበራት በዓውደ ርዕዩ መሳተፋቸው የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና ተሞክሮን እንዲቀስሙ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ነው የገለጹት።

ማኅበራቱ ምርትና አገልግሎታቸውን ለሸማቹ ኅብረተሰብ ከማቅረብ ባለፈ ከሌሎች አምራቾች ጋርም የገበያ ትስስር መፍጠር ያስችላቸዋል ብለዋል።

ሸማቹም የሚቀርቡለትን ምርትና አገልግሎቶች ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ በመግዛት ተጠቃሚ እንደሚሆንም አመልክተዋል።

በአውደ ርዕዩ ላይ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ 260 የሚደርሱ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

  

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 29/2009 ዜጎች ሕገ-ወጥ ስደትን እንደ አማራጭ እንዳይወስዱ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ኤጀንሲ ገለጸ።

ኤጀንሲው እንደገለጸው ዜጎች የሥራ ዕድል የሚያገኙባቸውን ሁኔታዎች በማመቻቸት ስደትን እንዳያማትሩ እያደረገ ነው።

ኤጀንሲው ከአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመሆን በሕገ-ወጥ ስደት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ''የስደት መንስኤውና ውጤቶቹ'' በሚል ርዕስ በኤጀንሲው ስምሪትና ሥልጠና ባለሙያ በአቶ ግርማ ሙሉጌታ ሰነድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል።

በክልሉ በዓመት ከ 31 ሺህ በላይ ዜጎች በሕገ-ወጥ መንገድ ከአገር ወጥተው እንደሚሰደዱ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን ሃዲያ፣ ከንባታ ጠምባሮ፣ ስልጤ፣ ሀላባ፣ ወላይታና ጋሞጎፋ ዞኖች ደግሞ የስደተኞች መነሻ አካባቢዎች ናቸው።

እናም አቶ ግርማ እንደሚሉት ዜጎች ከመሰደድ ይልቅ በአገር ውስጥ የልማት ተቋማት በጊዜያዊነት ተቀጥረው እንዲሰሩ ኤጀንሲው እያደረገ ነው።

በዚሁ መሰረት ባለፉት ስድስት ወራት ከ 84 ሺህ በላይ የሚሆኑ የክልሉ ተወላጆች በክልሉና ከክልሉ ውጭ በሚገኙ የልማት ተቋማት ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።

''ይህ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ዜጎች የተወሰነ ገንዘብ አጠራቅመው ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው ብድር ጠይቀው የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ መነሻ እየሆናቸው ይገኛል'' ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ ኤጀንሲው ከገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በመቀናጀት ቋሚ ሥራ ለመፍጠርም ሁኔታዎችን እያመቻቸ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እንዲያም ሆኖ ኅብረተሰቡ ስለስደት ያለውን የተዛባ አመለካከት ለመለወጥ አሁንም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ ነው የሚገልጹት።

የኤጀንሲው ዳይሬክተር አቶ በልጉዳ ባጢሶ በበኩላቸው ወጣቶች በአገራቸው ሰርተው ለመለወጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።

ዜጎች በአገራቸው የተመቻቸላቸውን ሁኔታ ተጠቅመው ራሳቸውን እንዲቀይሩ እንዲደራጁ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዳሉት የስደትን አስከፊነት ከግንዛቤ ማስጨበጥ ባለፈ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሥራ ዕድል ማመቻቸት አለበት ።

Published in ማህበራዊ

ደሴ ጥር 29/2009 በስጋ ደዌ በሽታ ላይ የሚስተዋለውን የአመለካከት ችግር በመቅረፍ የተጠቂዎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ዓለም አቀፉ የስጋ ደዌ ቀን ለ18ኛ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ “በስጋ ደዌ ምክንያት ከሚመጣ የአካል ጉዳት ነጻ የሆነ ትውልድ እንገንባ!” በሚል ቃል በደሴ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ታደለች ዳሌቾ በበዓሉ ላይ እንደገለጹት በሽታው በዘር የማይተላለፍና በህክምና የሚድን በመሆኑ ተጠቂዎች ፈጥነው ወደ ህክምና በመሄድ የህክምና እርዳታ እያገኙ ነው።

በዚህም የበሽታውን ስርጭት መቀነስ ቢቻልም አሁንም በየዓመቱ ከሶስት እስከ አራት ሺህ ሰዎች በበሽታው ተይዘው ወደ ህክምና ተቋማት እንደሚመጡ አስረድተዋል፡፡  

በበሽታው ተጠቅተው በህክምና የዳኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች የስራ እድል ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ግን አሁንም ውስንነት እንዳለ ገልጸዋል።

''ብዙዎች ሰርተው መለወጥ፣ ሃብት ማፍራትና በኢኮኖሚው ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን እየቻሉ ለልመና ተዳርገዋል'' ብለዋል፡፡

''ችግሩን ለመቅረፍም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመቀናጀት የስጋ ደዌ ህሙማንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ ነው'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ጫንያለው መንግስቱ በበኩላቸው የአመለካከት ችግሩ በህዝቡ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአመራሩና የተማረው ሃይል ውስጥም እንደሚንጸባረቅ ጠቁመዋል፡፡

በስጋ ደዌ ህሙማን ላይ የሚደርሰው መገለል ቢቀንስም መስራት ለሚችሉ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ እጥረት እንዳለ አመልክተዋል፡፡

እንደ ሰብሳቢው አሁንም በተለይ በገጠር አካባቢዎች በስጋ ደዌ ህሙማን ላይ የሚደርሰው አድሎ ከፍተኛ በመሆኑ ተጠቂዎች ከኅብረተሰቡ እየተገለሉ ለልመና ተዳርገዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ልዑልሰገድ ንጉሴ በአማራ ክልል የስጋ ደዌ ስርጭት ከፍተኛ ከሆነባቸው አካባቢዎች አንዱ ደቡብ ወሎ መሆኑን ጠቁመዋል።

''ችግሩን በመገንዘብም በ2020 በአካባቢው በበሽታው የተያዘ አንድም ሰው እንዳይኖር ግብ ተይዞ ሁሉን አቀፍ ርብርብ እየተካሄደ ነው'' ብለዋል።

ለዚህም በዞኑ የሚገኙ ሁሉንም የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በማሰልጠን በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዓለም አቀፉ የስጋ ደዌ መከላከል የኢትዮጵያ ተወካይ ወይዘሮ ካኒ ሃንሰንስ የኢትዮጵያ መንግስት የስጋ ደዌ በሽታን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው።

የተጠቂዎች ቁጥር ከፍተኛ ከሆነባቸው የአፍሪካ አገራት አንዷ ኢትዮጵያ በመሆኗ አሁንም ችግሩን ለመቅረፍ የተጠናከረ ስራ መሰራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

"የቤት ለቤት ትምህርት በመስጠት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መጠናከር አለባቸው፤ መገናኛ ብዙሃንም ሰፊ ትምህርት መስጠት ይገባቸዋል" ብለዋል፡፡

ከ40 ዓመት በፊት የስጋ ደዌ ተጠቂ የሆኑትና የቦሩ ሜዳ ስጋ ደዌ ጉዳተኞች ማህበር አባል ወይዘሮ ደሞዝ ተካ የስጋ ደዌ ተጠቂዎቹ ልመናን በመጠየፍ ራሳቸውን በስራ መደገፍ እንደሚችሉ አረጋግጠዋል፡፡

ሌላው የማህበሩ አባል አቶ ወልደየሱስ መሐመድ በበኩላቸው የስጋ ደዌ በሽታ ከየትኛውም ስራ እንደማያግዳቸው ጠቁመው በእንስሳት እርባታ፣ በምንጣፍ ስራና በሂሳብ ሰራተኛነት ማህበሩን በማገልገል ራሣቸውንም ተጠቃሚ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ እንደሚያስረዳው በአገሪቱ በሚገኙ 93 ወረዳዎች ከፍተኛ የስጋ ደዌ ስርጭት እንዳለ ተመልክቷል።

Published in ማህበራዊ

መቱ ጥር 29/2009 በኢሉአባቦራ ዞን ባለፈው የመኸር ወቅት ከለማው መሬት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ምርቱ የተሰበሰበው በወቅቱ በአገዳ፣ በብርዕና ቅባት እህሎች ከለማው 134 ሺህ ሄክታር ከሚጠጋ መሬት ላይ ነው።

ዘንድሮ የተገኘው ምርት ከቀዳሚው  የምርት ዘመን ጋር ሲነፃፀር በ500 ሺህ ኩንታል ብልጫ ማሳየቱን ጠቁመዋል።

የተሻለ ምርት የተሰበሰበው የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ በዋና ዋና ሰብሎች በሄክታር የሚገኘውን አስር ኩንታል ምርት ወደ 32 ኩንታል ማሳደግ በመቻሉ ነው።

እንዲሁም የአርሶ አደሩ የግብአትና ቴክኖሎጂ  አጠቃቀም መሻሻልና ባለፉት አመታት የተከናወነው የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ እርጥበትና የአፈር ለምነት መጨመሩም ሌላው ለምርቱ ማደግ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በዞኑ ሁሩሙ ወረዳ ባሮ ቀበሌ አርሶ አደር  ታምሩ ኢፋ ለኢዜአ እንደገለፁት በመኸር እርሻ አንድ ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ያለሙትን  ሰብላቸውን ሰብስበው ጎተራ አስገብተዋል፡፡

በአንድ ተኩል ሄክታር ላይ ያለሙትን የበቆሎና ማሽላ ምርት መሰብሰባቸውን የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ዋቅጅራ አጋ ናቸው፡፡

አርሶ አደር መሀመድ ሼህ ሙሳ በበኩላቸው በዚህ አመት  በመስመር የመዝራት ቴክኖሎጂና ግብአት በአግባቡ በመጠቀም ምርታማነታቸውን በእጥፍ ማሳደግ እንደቻሉ ተናግረዋል።

በዞኑ ባለፈው መኸር በተካሄደው የግብርና ልማት ላይ ከ200 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆናቸው ተመልክቷል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 29/2009 የብሔራዊ ኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ በኤክስፖርት ዘርፍ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ማነቆዎችን ማስወገድ የሚያስችሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ ኮሚቴው በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰብሳቢነት በዘርፉ በሚታዩ ማነቆዎች ዙሪያ ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

በዘርፉ የሚታዩ ዋና ዋና ማነቆዎችን ለመፍታት በመንግሥትና ባለኃብቶች በኩል ምን ምን ተግባራት መከናወን እንዳለባቸውም በሰፊው   ተመክሮበታል።

በመሆኑም የአቅርቦት፣ የሎጂስቲክስ፣ የፋይናንስና የቅንጅት ችግሮችን ለማስወገድ የሚያስችሉ የመፍትሄ አቅጠጫዎች ተሰጥተዋል።

በዚህ መሰረት በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የሚታየውን ከብክለት የጸዳና ጥራት ያለው ጥጥ በምርምር ተደግፎ የሚቀርብበት ሁኔታ እንዲመቻችና የቫት ተመላሽ ለላኪዎች በሰባት ቀናት እንዲከፈላቸው መግባባት ላይ ተደርሷል።

በተጨማሪም ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከሰነድ ጋር የተገናዘበ ገንዘብ (CAD) ጥሬ ዕቃ ሲጠየቅ ያለምንም ገንዘብ ማስያዣ እንዲያስገቡና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለኃብቶች የቅድመ ጭነት አገልግሎት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚሰጥ ይሆናል።

ኮሚቴው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በኢንዱስትሪ ልማት ዕድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችና ተግዳሮቶችን በማስወገድ የተፋጠነ መዋቅራዊ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው ቅድሚያ በተሰጠባቸው ዘርፎችም ውይይት ተካሂዷል።

ከእነዚህ መካከል የጥጥ ልማት መስክን ጨምሮ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው እንደሆነም ተመልክቷል።

ኮሚቴው የአገሪቱን ኤክስፖርት እንቅስቃሴ ለማሳደግ አዲስ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በዘርፉ ቀጥተኛ ተሳታፊ ከሆኑ የአገር ውስጥና የውጪ ባለኃብቶች፣ የማህበራት አባላት፣ ዘርፉን ከሚመሩ አስፈፃሚ አካላትና ከተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ነው ውይይቱን ያደረገው።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን