አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 05 February 2017

ዲላ ጥር 28/2009 በጌዴኦ ዞን ዘንድሮው በሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የቡና ጉንደላና መልሶ ማልማት ትኩረት እንደሚደረግ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት መምሪያ ገለጸ፡፡

ተፋሰስን መሰረት በማድረግ ለሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ 33 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ለመሸፈን ዝግጅት ተደርጓል፡፡

በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ከፍያለው ወሬራ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ ባለፉት 6 ዓመታት በ286 ንዑስ ተፋሰሶች ላይ 134 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተከናውኗል ፡፡

በዚህም የአፈር ለምነት በመጨመርና የተሻሻሉ አሰራሮችን በመከተል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ከመቻሉም በላይ  አርሶ አደሩ  የተፋሰስን ሥራ በባለቤትነት በመስራት ተሳትፎውን እያሳደገ መጥቷል፡፡

ዘንድሮም 421ሺ 322 አርሶ አደሮች በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው የሚሳተፉ ሲሆን በ134 ንዑስ ተፋሰሶች 33ሺህ 500 ሄክታር መሬት እንደሚለማ አቶ ከፍያለው ተናግረዋል ፡፡

"በዞኑ ዲላ ዙሪያና ወናጎ ወረዳዎች ከ40 ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ የቡና ዛፎች ምርታቸው እየቀነሰ በመምጣቱ ምርቱን ለማሻሻል ያረጁ ቡናዎች  ጉንደላ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል "ብለዋል፡፡

 የእርጥበት ማቆያ   ሥራዎችን በቡና ማሳዎች ውስጥ እንደሚሰራ ያመለከቱት ደግሞ በመምሪያው  የቡና ልማት ባለሙያ ወይዘሮ ማርታ ደምሴ ናቸው፡፡

ባለሙያዋ እንዳሉት ሁለት ሺህ 979 ሄክታር ላይ የቡና ጉንደላ ፣ አምስት ሺህ 543 ሄክታር ላይ ያረጁ ቡናዎችን በመንቀል በአዲስ ለመተካት የጉድጓድ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

"ዞኑ የሚታወቅበትን የቡና ምርትና ምርማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብና ግንዛቤ በማስጨበጥ ዝግጅት ተደርጓል "ያሉት  ወይዘሮ ማርታ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተመሳሳይ ተግባራት የቡና ምርት እንዲጨምር ማስቻሉን አብራርተዋል ፡፡

ምትኩ ጎበና በዞኑ ቡሌ ወረዳ  ሲካ ቀበሌ ነዋሪ  አርሶ አደር ሲሆኑ  በየዓመቱ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ስራው እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡ 

በዚህም "ለዓመታት ምርት  ባለመስጠት ትተውት የነበረው መሬት በተከናወነ  የአፈርና ውሃ ጥበቃ  ስራ ምርታማ ለመሆን "ችለዋል ፡፡

በእነዚህ ቦታዎች   የከብቶች መኖ በማልማት ከራሳቸው ባለፈ ለአካባቢው አርሶ አደሮች በሁለት ዓመታት ውስጥ እስከ 35 ሺህ ብር ድረስ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደሩ ጠቁመዋል፡፡   

በጌዴኦ ዞን የዘንድሮው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የሚካሄደው  " ተፋሰስን  ለቡና ልማታችን » በሚል መሪ ሀሳብ ነው፡፡

Published in አካባቢ

ጅማ ጥር 28/2009 በጅማ ከተማ ዛሬ በተካሄደው የ15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ጅማ አባቡና ድሬዳዋ ከተማን 3ለ0 በሆነ ውጤት አሸነፈ፡፡

ውጤቱም ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት አስችሎታል፡፡

ጅማ አባቡና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከተጀመረ ማሸነፍ የቻለው ሶስት ጨዋታ  ብቻ ሲሆን የቡድኑ አስልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ  ከያዙት ከሁለት ሽንፍት በኃላ የተመዘገበ ውጤት ነው፡፡

ድሬዳዋ በበኩሉ ከአራት ተከታታይ ድል በኋላ በዛሬው ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊሸነፍ ችሏል፡፡

ለጅማ አባቡና የማሸነፊያ ጎሎችን አሜ መሀመድ በ13ኛው ደቂቃ ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ በፍጹም ቅጣት ምት በ48ኛው እና ዩጋንዳዊው ክሪዚስቶፎር ንታምቢ 56ኛው ደቂቃ ላይ ማስቆጠር ችለዋል፡፡

የጅማ አባቡና አሰልጣኝ ገበረመድህን ሃይሌ " ቡድንን ማስልጠን ከጀመርኩ ከሁለት ሳምንት  ጀምሮ ውጤት ማስመዝግብ እንደምችል እገምት ነበር የገመትኩትም ተሳክቷል "ብለዋል፡፡

በውጤት ቀውስ ውስጥ የነበረ ቡድን ከጨዋታ ብልጫ ጋር 3ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፎ መውጣት ዋንጫ ከማንሳት ያልተናነሰ የደስታ ስሜት በሁሉም የቡድኑ ደጋፊ ዘንድ የሚፈጥር ነው፡፡

የመጀመሪያ ዙር የማጠናቀቂያ ጨዋታን በድል ማጠናቀቃቸው ለሁለተኛ ዙር የጨዋታ ጊዜ ከፍተኛ መነሳሳት የሚፈጥር ይሆናል፡፡

የድሬዳዋ አሰልጠኝ ዘላለም ሽፈራው  በጨዋታው ሙሉ በሙሉ መበለጣቸውን ተናግረው  ሁለተኛ ግማሽ ውጤት ለመቀየር ወደ ሜዳ ቢገቡም እንዳልተሳካለቸው ገልጸዋል፡፡

የሁለቱ ጨወታዎች ከመጀመሩ በፊት ለድሬደዋ ከነማ በድን መሪ እስከዳር ዳምጠው  በልጅነቱ ለተጫወተበት ለጅማ ሳሪስ ታዳጊ እግር ኳስ ቡድን 25 የስፖርት ትጥቅ በስጦታ አበርክቷል፡፡

የጅማ ሳሪስ እግር ኳስ ክለቡ ደግሞ በልጅነቱ ከቡድኑ አባላት ጋር የተነሳውን ፎቶ ግራፍ በፍሬም በማዘጋጀት በስጦታ አበረክተውለታል፡፡

በ2007ዓ.ም  የከፍተኛ ሊግ የወድድር ዓመት ድሬደዋ ከተማ ጅማ አባቡናን 3ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወደ ፕሪሚር ሊግ የተቃላቀለ ቡድን ነው፡፡

Published in ስፖርት

መቀሌ ጥር 28/2009 በትግራይ ክልል በሁሉም መስኮች የህዝቡን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች አበረታች ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን  የክልሉ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ሁለተኛ ቀኑን የያዘው የክልሉ ምክር ቤት  መደበኛ ጉባኤ በርዕሰ መስተዳድሩ የቀረበውን የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት  ላይ ተወያይቶ አፅድቋል ።

የምክር ቤቱ አባላት በጉባኤው ላይ እንደገለፁት በግብርናው ዘርፍ የኩታገጠም አስተራረስን መሰረት ያደረገ የአዝርእት ልማትና የመስኖ ስራ አመርቂ ውጤት አስገኝቷል።

የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በመከናወን ላይ ካሉ ተግባራት መካከል በትምህርት ቤቶች መምህራንን በማሳተፍ ለሴቶች እየተሰጠ ያለው ተጨማሪ የማጠናከሪያ ትምህርት በውጤታማነቱ ሌላው ማሳያ መሆኑን የምክር ቤቱ ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈለጉሽ አሳምነው ተናግረዋል።

ህገወጥ ስደትን በመቆጣጠር  ወጣቶች ታሪካቸውና ባህላቸውን እንዲያውቁ ለማድረግ ቀጣይነት ያለው ስራ ማካሄድ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

የምክር ቤቱ የህግና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ዘይነብ ዓብዱለጢፍ በበኩላቸው የክልሉ የሚሊሻና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በመተባበር የአካባቢያቸውን ፀጥታ ለማስጠበቅ እያደረጉት ባለው ጥረት በቅርቡ ከኤርትራ ሰርገው የገቡ የግንቦት ሰባት አባላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በፍትህ አካላት ዙሪያ በተካሄደው የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ መድረክ ህዝቡ በመሳተፈ መልኩ መከናወኑ ውጤታማ እንደነበር ጠቁመዋል ።

በዘርፉ ወንጀልን በመከላከል፣የትራፊክ አደጋ በመቀነስና የመሰረተ ልማቶችን ከአደጋ በመጠበቅ ዙሪያ ቀጣይነት ያለው ሰራ መሰራት እንዳለበት ወይዘሮ ዘይነብ አስገንዝበዋል ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ  "ህዝቡን የልማቱ ባለቤት አድርጎ መንቀሳቀስ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚያስችል  በግብርና፣ በጤናና በግብር አሰባሰቡ ዙሪያ እየታዩ ያሉትን ውጤቶች ማሳያዎች ናቸው" ብለዋል።

"በጥልቅ የተሃድሶ ግምገማ ራሳችን የበለጠ እንድናይና የነበሩን ጉድለቶች እንድናውቅ በማድረግ ረገድ ህዝቡ ያደረገው ተሳትፎና ጥረት የሚደነቅ ነው " ብለዋል፡፡

በቀጣይ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎቻችን ለማሳካት የበለጠ መስራት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል ።

የምክር ቤቱ አባላት በርዕሰ መስተዳድሩ የቀረበውን የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት በማዳበጥ ተወያይተው አፅድቀዋል ።

በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና በዋና ኦዲተር የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ምክር ቤቱ እየተወያየ ሲሆን ጉባኤው ነገ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

Published in ፖለቲካ

ደብረ ማርቆስ ጥር 28/2009 በምስራቅ ጎጃም ዞን ሊዳሩ የነበሩ ከ180 በላይ ህጻናት ጋብቻ እንዲቋረጥ መደረጉን የዞኑ ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሴቶች ማደራጃ ተሳትፎ ና ተጠቃሚነት ባለሙያ አቶ ጥላሁን ምህረቴ ለኢዜአ እንደገለጹት ያለእድሜ ጋብቻው እንዲሰረዝ  የተደረገው ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ነው፡፡ 

ከዞን እስከ ቀበሌ የተለያዩ የማስፈጸሚያ ዘዴዎችን በማመቻቸት ያለእድሜ ጋብቻን  በማስቀረት ሴት ህጻናት ጊዜያቸው  በትምህርት እንዲያሳልፉ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ 

በተያዘው የመጀመሪያው ግማሽ የበጀት ዓመት ብቻ 185 የሚሆኑ ህጻናት ጋብቻን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ማቋረጥ መቻሉን ባለሙያዋ አስታውቀዋል፡፡

"ጋብቻቸው ከተቋረጠው ህጻናት መካከል ከ100 በላይ ሴቶች ናቸው፤ ከነዚህ ውስጥ በ80 በመቶው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የነበሩ ናቸው" ብለዋል።

ባለሙያው እንዳሉት በቀጣይ  መምሪያው ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር የጠበቀ ትስስር በመፍጠር ህጻናት ልጆች  ለመሰል ችግሮች እንዳይጋለጡ የተጠናከረ ስራ ይካሄዳል፡፡

ወይዘሮ የዝቤ ጥበብደባይ ጥላት ግን ወረዳ የናዝሬት መዳሃኔዓለም ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን ባለፈው  ዓመት በቅደም ተከተል የዘጠኝ ዓመቱን ወንድ ልጃቸውንና የአምስት ዓመት ሴት ልጃቸውን ለመዳር ከደገሱ በኋላ ጋብቻው እንዳተቋረጠ ተናግረዋል።

በጎረቤቶቻቸው ጥቆማ የመንግስት አካላት ደርሰውባቸው ጋብቻው በመቋረጡ  ተበሳጭተው እንደነበርንም ተናግረዋል፡፡

" በተሰጠኝ  ምክር መሰረት በልጆቼ ላይ ይደርስ የነበረውን የጤናና ችግር እንዲሁም የቀጣይ ህይወታቸው መመሰቃቀል መገንዘብ በመቻሌ ዛሬ እኔም የነሱ ተባባሪ ለመሆን በቅቻለሁ " ብለዋል፡፡

ወይዘሩ የዝቤ እንዳሉት ያለእድሜያቸውን ለመዳር ያነሳሰቸውም በየጊዜው በሰርግ ሲያወጡ የነበረውን ወጭ ለማስመለስ፣ ልጆቻቸው ህጻን ቢሆኑም ቁሞ ቀር እናድይባሉ በመስጋት እንደሆነ ነው፡፡ 

ተዘጋጅቶ የነበረው  ድግስም በዱቄት ደረጃ ስለነበር ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ  መላ ቤተሰባቸውን  መመገብ እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል፡፡

በአነደድ ወረዳ የንፋሳም ትምህርት ቤት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ   ይሽጥላ ጌታ በዚህ ዓመት ጋብቻቸው ከተቋረጠባቸው መካከል አንዷ ስትሆን ጋብቻው የተቋረጠው  ጉዳዩን እንደሰማች ለርዕሰ መምህር በመንገረ  ለቤተሰቦቿ  ማስጠንቀቂየ በመሰጠቱ መሆኑን ተናግራለች፡፡

"እኔም በርትቼ በመማር የቀጣይ ህይወቴን ከማመቻት ባሻገር እድሜዬ ሲደርስ የፈለኩትን የማገባበት እድል በመፈጠሩ ደስተኛ ነኝ" ብላለች፡፡

Published in ማህበራዊ

ጅማ ጥር 28/2009 የአጋሮ ከተማ አስተዳደር የመልካም አስተዳደር ችግር በፈጸሙና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም ያላቸውን 14 የቀበሌ   አመራሮች ከኃላፊነታቸው ማንሳቱን አስታወቀ።

የቀበሌ አመራሮቹ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገው ከከተማ ነዋሪዎች ጋር በተደረገ የጥልቅ ተሃድሶ ውይይት የመልካም አስተዳዳር ችግር መፈጸማቸው በመረጋገጡ ነው።

በተነሱት አመራሮች ምትክ  በከተማው ነዋሪዎች አስተያየት ተሰጥቶባቸው ተቀባይነት ያገኙ አዳዲስ አመራሮች ትናንት  መመደባቸውን የአጋሮ ከተማ ከንቲባ አቶ ነዚሙ ሁሴን ገልጸዋል።

ከንቲባው እንዳሉት ነዋሪው በተፈጠረለት መድርክ በመጠቀም  መልካም የሰሩ አመራሮችን ዕውቅና በመስጠትና አጥፊዎችን በማጋለጥ ያደረገው ተሳትፎ የከተማው መልካም አስተዳደርን በማስፈን ልማትን ለማፋጠን እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ ነው፡፡

አስተዳደሩ ከአሁን በኋላ ከህዝብ ተደብቆ የሚሰራው የሌለው በመሆኑ በከተማው ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከነዋሪዎች ጋር የተጀመረውን ቅንጅት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል ።

በነዋሪው ፊት ቀርበውና አስተያየት ተሰጥቶባቸው አዲስ የተሸሙ የቀበሌ አመራሮች በትምህርት ዝግጅት  ፣ በስራ ቆይታቸው ውጤታማ የሆኑ፣ የመምራት ብቃት ያላቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው እንደሆኑም ጠቁመዋል።

በአጋሮ ከተማ የተምሳ ዲዳ ቀበሌ ነዋሪ  ወይዘሮ ኡሜ በድሩ በሰጡት አስተያየት በቀበሌ ደረጃ አመራሮች በህዝብ ፊት ቀርበው አስተያየት እንዲሰጥባቸው  መደረጉ ግልጽነትን የሚያሰፍን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም አመራሮች ከመታጨታቸው ጀምሮ  ህዝብ ፊት ቀርበው አስተያየት ቢሰጥባቸው የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪዎችን አስቀድሞ መከላከል ስለሚቻል ጅምሩ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ሌላው የብርቢሳ ዋሪቱ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አባ ሚልኪ አባፊራ በበኩላቸው "የመልካም አሰስተዳደር ችግር የፈጠሩ አመራሮች ተነስተው በምትካቸው ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ አመራሮች መመደባቸው የከተማውን እድገት ያፋጥነዋል " ብለዋል ።

" አስተዳደሩ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጠረው በቀበሌዎች መሆኑን በመገንዘብ ለህዝብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የወሰደው እርምጃ ተገቢና የሚበረታታ ነው " ያሉት ደግሞ  ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ሙሃመድ ጀማል ናቸው።

አዲስ ከተመደቡት የቀበሌ አመራሮች መካከል የተምሳ ፊራየ ቀበሌ አስተዳዳሪ  አቶ ዩሃኒስ አባፊራ በበኩላቸው በህዝብ አገልጋይነት መንፈስ በመንቀሳቀስ የህብረተሰቡን ይሁንታ አግኝተው የተጣለባቸውን  ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ባህርዳር ጥር 28/2009 የነበሩባቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች ለይተው ለማረም  በአዲስ መንፈስ እንዲዘጋጁ የተሃድሶ መድረኩ ያነሳሳቸው መሆኑን የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች ተናገሩ።

በተሃድሶው መድረኩ ከ2ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች መሳተፋቸውን የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ገልጸዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል የባህርዳር ከተማ አገልግሎት ጽህፈት የጉዳይ ተቀባይ ባለሙያ  ወይዘሮ ያልጋይቱ የኋላ በሰጡት አድተያየት "  ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የጥልቅ ተሃድሶ ውይይት እያደረግን ነው" ብለዋል።

መስሪያ ቤታቸው በአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ምክንያት አገልግሎት ፈላጊው ህብረተሰብ በሚያደርገው ምልልስ ለምሬት የተዳረገበት መሆኑን ጠቅሰዋል። 

" እያደረግን ያለነው የተሃድሶ ግምገማ ቀደም ሲል የነበሩብንን ክፍተቶች ለይተን እንድናይ ፣  ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት እንድናገለግል አስችሎናል" ብለዋል።

" ያደረግነው ጥልቅ ተሃድሶ ልናያቸው ያልቻልናቸውን ችግሮች ያየንበት ነው” ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ኮንስትራክሽን መምሪያ የተቋራጮች፣ ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ባለሙያ አቶ እንደሻው አበራ ናቸው።

ሰራተኞች ባላቸው አፈጻጸም የተለዩ  በመሆናቸው ተሞክሮም ለመለዋወጥ ያስቻለ መድረክ መሆኑን  ጠቁመው  "በግሌ መንግስትና ህዝብ የጣሉብኝን ሃላፊነት በአግባቡ እንድወጣ፤ ራሴን እንዳይና እንድፈትሽ አስችሎኛል" ብለዋል።

" ቀደም ሲል የሚፈጸሙ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራትን እያየሁ ከመታገል ይልቅ የማልፍበት ሁኔታ እንደነበርና ተቻችዬ የምኖርኩበትን ጊዜ አሁን ላይ መለስ ብዬ ሳስታውስ እንድቆጭ አድርጎኛል"ብለዋል።

በመድረኩ ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው አቅማቸው የፈቀደውን ያህል የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመታገልና ህዝቡን በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአገልግሎት ጽህፈት ቤቱ የከተማ አውቶብስ ሾፌር አቶ ክንደያ ሐለፎም በበኩላቸው ተሃድሶው ይስተዋሉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመድረኩ ተለይተው መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ክብረት መሀሙድ በበኩላቸው በተዘጋጁ 57 መድረኮች ከ2 ሺህ 100 በላይ የመንግስት ሰራተኞች በተሃድሶው መድረኩ መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለህዝቡ በተሟላ መልኩ ለመስጠትም የመንግስት ሰራተኛው በጥልቅ ተሃድሶው እንዲያልፍ ማድረግ  አስፈላጊና ወቅቱ የሚጠይቀው ሆኖ ተገኝቷልም ብለዋል።

ሰራተኛው የነበሩበትን ችግሮች በጥልቅ ተሃድሶ መድረኩ ለይቶ በማየቱም ህብረተሰቡን ለምሬት እየዳረጉ ያሉትን ችግሮች  በማረም ለላቀ አገልግሎት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 28/2009 የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የኢኮኖሚ አቅማቸውን የማጠናከር ተግባር ላይ ማተኮር እንደሚገባ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ ሴቶች አገር አቀፍ ኮከስ አባላት ሁለንተናዊ የሴቶችን ተሳተፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ምክክር አድርገዋል።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ ደሚቱ ሃምቢሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅም ሳይጠናከር የፖለቲካዊ ብቃታቸው ብቻ ቢያድግ ትርጉም ያለው ውጤት ሊመጣ አይችልም።

ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት የሚደረገው ትኩረት “የድሃ ድሀ ሴቶች ላይ ብቻ መሆን የለበትም” ያሉት ወይዘሮ ደሚቱ፤ በተለያዩ የንግድ ስራዎች ውስጥ  የተሰማሩትን  መደገፍ፣ ማሰልጠንና የገበያ ትስስር እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማጎልበት የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ ከተቋማት ለስራ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ተበድረው መስራት እንዲችሉ ግንዛቤ መፈጠር እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የከተማ ሴቶቸ በኢንዱስትሪ ዘርፎች እንዲደራጁ፤ በገጠር የሚኖሩት ደግሞ በእንስሳት እርባታና ጓሮ አትክልት ምርት ላይ ተሰማርተው የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ገቢ ማመንጨት እንዲችሉ አሰራሮች መዘርጋታቸውን ጠቁመው፤ ሴቶች ያሉትን ምቹ የሆኑ “ልዩ እድሎች ለመጠቀም እውቀቱ የላቸውም” ብለዋል።

ለዚህም የአመራር አባላት ለሴቶች ግንዛቤ የመፍጠርና የማስተባበር ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።   

ሴቶችን ተጠቃሚና ተሳታፊ የማድረግ ኃላፊነት በአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ላይ ብቻ የሚጣል እንዳልሆነ የገለጹት ወይዘሮ ደሚቱ፤ “የሁሉንም መስሪያ ቤቶች፣ የማህበረሰብ አደረጃጀቶችና የአጋር አካላትን ርብርብ ይጠይቃል” ያሉት።

''ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ማሳደግ  የአገሪቷን ህዳሴ ማረጋገጥ ነው'' ያሉት ወይዘሮ ደሚቱ፤ የህዳሴ ጉዞውን ለማሳካት ደግሞ በራሳቸው የሚተማመኑ አመራር ሰጭ ሴቶችን ማፍራት የሚጠበቅ መሆኑን ነው የገለጹት።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤና የሴቶች ኮከስ ሊቀመንበር ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ፤ ምክር ቤቱ ከህገ-መንግስቱ ጀምሮ የሴቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ህግና መመሪያዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ በመከታተልና በየጊዜው በመገምገም የተጣለበትን ሃላፊነት እንደሚወጣ ገልጸዋል።

ለሴቶች ስራ እድል ፈጠራ፣ በአደረጃጀቶችና በብድር አቅርቦት ዘርፍ የሴቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ምክር ቤቱ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በመጀመሪያው የምክር ቤት ዘመን ከ547 መቀመጫዎች ሴቶች የሚሸፍኑት 13 ብቻ መሆናቸውን ያስታወሱት ወይዘሮ ሽታዬ፤ በአሁኑ ወቅት በምክር ቤቱ የሴቶች ተሳትፎ 212 መድረሱን ተናግረዋል።

በአገሪቷ በ1987 ዓ.ም በምክር ቤት የነበረው የሴቶች ቁጥር ከ2 ነጥብ 38 በመቶ ወደ 38 ነጥብ 8 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል። 

''ኮከስ'' ማለት ተመሳሳይ ዓላማ፣ ፍላጎትና ጥያቄ ያላቸው አካላት ጥያቄዎቻቸውን፣ ዓላማና ፍላጎታቸው በተደራጀ መልኩ ለማንሳትና ለማሳካት የሚፈጥሩት አደረጃጀት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 28/2009 በአዲስ አባበ በተካሄደው የማራቶን ሩጫ ውድድር በወንዶች ታደሰ አሰፋ በአንደኝነት አጠናቀቀ።

በሴቶች ማራቶን ከፌዴራል ፖሊስ አመለወርቅ ፍቃዱ አሸናፊ ሆናለች።

21ኛው የፔፕሲ አዲስ አበባ የማራቶን የሩጫ ውድድር መነሻና መድረሻውን ሰሚት አድርጎ በዛሬው እለት ተካሂዷል።

በዚህ ውድድር በወንዶች የፌዴራል ማረሚያው ታደሰ አሰፋና በሴቶች አመለወርቅ ፍቃዱ ከፌዴራል ፖሊስ አንደኛ በመውጣት አሸናፊ ሆነዋል።

በላቸው አለሙ ከፌዴራል ፖሊስ ሁለተኛ እንዲሁም በግል የተወዳደረው አማኑኤል ተሾመ ደግሞ ሶስተኛ ሆነው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

እንዲሁም ከሴቶች ተስፋነሽ መርጋ እና ጽዮን አባቡ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን ተከታትለው ገብተዋል።

በዚህ ውድድር አሸናፊ ለሆኑ አትሌቶች የገንዝብና የሜዳሊያ ሽልማት ተሰጥቷል።

ውድድሩን በአንደኝነት ያጠናቀቀው አትሌት ታደሰ በሰጠው አስተያየት እንደገለጸው፤ መሰል ውድድሮች  በአለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለመካፈል እድል ይፈጥራሉ። በተጨማሪም አትሌቶች ያሉበትን አቋም ለመፈተሽ ያስችላቸዋል።

ከውድድሩ በኋላ በአንዳንድ አትሌቶችና ውድድሩን ባዘጋጀው የአዲስ አበባ አትሌቲክስ  ፊደሬሽን መካከል አለመግባባቶች ተከስተዋል።

ለአለመግባባቱ መነሻ ምክንያት የሆነው ደግሞ በውድድሩ ወቅት የጥቂት አትሌቶች ውጤት መሰረዝ ነው።

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ቴክኒክ ክፍል ዳይሬክተር አቶ አንዱአለም ያየህይራድ የአትሌቶች ውጤት የተሰረዘው "የቲ ሴራ" ወይም መታወቂያቸውን ሳያስመዘግቡ በመወዳደራቸው ነው።

ይህም  ደግሞ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌደሬሽን አሰራር ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፉ አትሌቲክስ ስፖርት ማህበር መመሪያ መሰረት ተግባራዊ የሆነ ነው።

በህጉና መመሪያው መሰረት የማይወዳደሩ አትሌቶች መመሪያውን ጥሰው ውጤታቸውን ሊያዝላቸው አይችልም።

የፔፕሲ አዲስ አባበ የማራቶን ውድድር በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ውድድሩ ከ16 ክለቦች የተውጣጡ 132 አትሌቶች፣ በግል የተወዳደሩ 80 አትሌቶችና የቀድሞ አንጋፋ አትሌቶች አካቶ በድምሩ 233 አትሌቶች ተሳትፈዋል።

Published in ስፖርት

ሀዋሳ ጥር 28/2009 በየአካባቢው የሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማምጣት በሚያስችል መልኩ መሆን እንዳለበት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚንስትር  ዶክተር እያሱ አብርሃ አስታወቁ፡፡

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተፋሰስ ልማት ስራ ትናንት በጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ ሚካኤሎ ቀበሌ በይፋ ተጀምሯል፡፡

በስፍራው የተገኙት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚንስትሩ  እንዳሉት የግብርና መር ስትራተጂው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት በማስመዝገብ የህዝቡንም ተሳትፎና ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ነው፡፡

"የተፋሰስ ልማት ስራውን ከመስኖ ልማትና ከእንስሳት እርባታ ጋር በማስተሳሰር ኤክስፖርትን መሰረት ያደረገ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ስራን ማከናወን በሚያስችል መልኩ መሰራት አለበት "ብለዋል፡፡

ልማቱ ህዝቡን ወደ ሀብታምነት መለውጥ እንዲያስችልና ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ በዚህ የተፋሰስ ልማት ስራው ላይ ተማሪዎች እንዲሳተፉ መደረጉ የሚያመላክት እንደሆነ  ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በስራው የማስፈጸም አቅም ውስንነቶችና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክፍተቶችን ለመሙላት በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቁመው ህዝብን የሚያሳትፍ ሰፊ ንቅናቄ ከመፍጠር አንጻር የተከናወነው ተግባር ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው በዚህ ስፍራ የተገኘው ህዝብ ቁጥር አመላካች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"በግብርናው መስክ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ ሽግግር ለማድረግ በተፋሰስ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የበለጠ መሰራት አለበት "ብለዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ በበኩላቸው ባለፉት አመታት በተከናወነው ተግባር  በጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ ሚካኤሎ ቀበሌ  የተገኘው ውጤት በምርታማነት እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በወረዳው የሚገኙ አርሶ አደሮች በበልግና በመኸር ከሚያለሙት ማሳ 80 በመቶውን በመስኖ በማልማት ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማጎልበት እንዲችሉ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

"የተፋሰስ ልማት ስራውን አጠናክረን እስከ ሰራን ድረስ የውሀ መገኛ አማራጮችን ለማስፋት ያስችሏል " ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በአካባቢው የሚገኘውን ሰንሰለታማውን የዘቢዳር ተራራ በተፋሰስ በማልማትና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በመስራት ከጉራጌ ዞን ባለፈ አጎራባች አካባቢዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

የተፋሰስ ልማት ስራው የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የበለጠ ማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ በዘቢዳር ተራራ ሊሚካሄደው የተፋሰስ ልማት ሰራ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

በክልሉ ከሶስት ሺህ ስድስት መቶ በላይ ተፋሰሶች ተጠንተው ፣ የዲዛይንና ቅየሳ ስራዎችን በማጠናቀቅ ለማልማት በታቀደው መሰረት ዛሬ ወደ ተግባር መገባቱን የገለጹት ደግሞ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ናቸው፡፡

ባለፉት ስድስት ዓመታት በተከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ የተሻለ ውጤት የመጣበት አካባቢ በመሆኑ ይህን ውጤት ለማስቀጠልና አርሶ አደሩን ለማበረታታት ስራው በሚካኤሎ ቀበሌ በይፋ እንዲጀመር መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ባለፉት ዓመታት ከአምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተፋሰስ በማልማት የተራቀቱ አካባቢዎች መልሰው ማገገም እንደቻለም  ጠቁመዋል፡፡

በተያዘው የበጋ ወራትም ከ3ሺህ 760 በላይ ተፋሰሶችን በመለየት 1 ሚሊዮን 128 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ለስራው የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችና የሰው ኃይል የመለየት ስራ መከናወኑን አቶ ጥላሁን አመልክተዋል፡፡

በዚህ የተፋሰስ ልማት ስራ ከአምስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ፣ ሴቶችና ወጣቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ጥር 28/2009 የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው የአንደኛ ዲቪ ዥን የሚሳተፉ ክለቦች በፋይናንስ አቅም ማነስ ምክንያት ከውድድር እየወጡ መሆናቸው ተመለከተ።

ፌዴሬሽኑ በተለያዩ ምክንያቶች ያዘገየውን የ2008 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ ባካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው፤ ለተተኪ ወጣት እግር ኳስ ተጫዋቾች የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው።

በክለቦች እንዳይታቀፉ ለውድድር መመዝገቢያ ክፍያ መጨመር ለክለቦቹ መፍረስ ምክንያት እየሆነ መጥቷል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች እንደገለጹት፤ ለተተኪ ወጣት እግር ኳስ ተጫዋቾች የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው። ይህም የኳስ ጨዋታ ክህሎት ያላቸው ተተኪ ተጫዋች ማግኘት እያስቸገረ ነው።

የኮልፌ ቀራኒዮ የወንዶች እግር ኳስ ክለብና የጉለሌ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ ያላቸው የፋይናንስ አቅም አነስተኛ እንደነበር ያመለከቱት ጉባዔተኞቹ፤ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ የሚጠይቀው የመመዝገቢያ ክፍያ በመጨመሩ ለመበተን ተገደዋል።

ቀዳም ሲል ይጠየቅ ከነበረው የምዝገባ ክፍያ መጠን መጨመሩን አመልክተው፤ በ2008 ዓ.ም የውድድር ዓመት የሁለት ሺ ብር ጭማሪ መደረጉን የክለብ ተወካዮች ገልጸዋል።

ፌዴሬሽኑ ተተኪ ወጣት ከማፍራት አኳያ ክፍተት እንዳለበት ጠቁመው፤ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።

በእድሜያቸው ከ17 ዓመትና ከዛ በላይ ለሆናቸው ተጫዋቾች የውድድር እድል በመፍጠር በኩልም ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል።

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ዓለሙ እንደተናገሩት፤ የክለቦች ክፍያ እንዲጨምር የተደረገው ከመንግስት የሚመደበው በጀት በመቋረጡ ነው።

ይሁን እንጂ የፋይናንስ አቅም የሌላቸው ክለቦችን “እንዲካፍሉ ከመጣሩም በላይ ከውድድሩ ውጪ እንዳይሆኑ አስተያየት ይደረጋል” ብለዋል።

ከክፍለ ከተሞችና ከሚመለከታቸው ጋር በመወያየት ክለቦች በፋይናንስ አቅም ማነስ እንዳይበተኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ “ህዝባዊ መሰረት እንዲይዙ ውይይት እያካሄድን ነው” ብለዋል ።

ተተኪ ወጣት እግር ኳስ ተጫዋቾች ላይም የክትትልና ድጋፍ አጥረት መኖሩን ያመኑት አቶ ጌታቸው፤ በቀጣይ “ክፍተቶችን ለማረም ጥረት ይደረጋል” ብለዋል። 

Published in ስፖርት
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን