አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 04 February 2017

አዲስ አበባ ጥር 27/2009 በአገራዊ የህዳሴ ጉዞ የሴቶች ተሳትፎ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

የምክር ቤቱ የተመራጭ ሴቶች ኮከስ አገራዊ የሴቶች የምክክር መድረክ ማስፈጸሚያ የድርጊት መርሃ ግብር ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

የመድረኩ ዓላማም በሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዙሪያ በሚያጋጥሙ ፈተናዎች ግንዛቤ በመያዝ በቀጣይ በጋራና በተናጠል የሚሰሩ ተግባራትን የመለየት ንቅናቄ መፍጠር ነው ተብሏል።

የኮከሱ ሰብሳቢና ምክትል አፈ-ጉባዔ ሽታዬ ምናለ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በአገራዊ ህዳሴው የሴቶች ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሴቶች ኃላፊነታቸው ሊወጡ ይገባል።

ይህን ማሳካት የሚቻለው ሴቶች በቂ ግንዛቤ በማዳበርና በግንባር ቀደም መንቀሳቀስ ሲችሉ ነው ብለዋል።

የሴቶች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለድህነት ቅነሳና ለአገራዊ ሠላም ወሳኝ በመሆኑ በዚህ ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ምክትል አፈ-ጉባዔዋ ጠይቀዋል።

በዚህ በኩል የሴት አመራሮችና አደረጃጀቶች ድጋፍ መኖር እንዳለበት ነው ወይዘሮ ሽታዬ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።

በመድረኩ ለመወያያ መነሻ የሚሆን ጽሁፍ ቀርቦ በተሳተፊዎች ውይይት ተደርጎበታል።

ሚኒስትሮች፣ የፌዴራልና የክልል አመራሮች እንዲሀም ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በመድረኩ ተሳታፊ ሆነዋል።

 

 

Published in ማህበራዊ

መቀሌ 27/2009 የጥልቅ ተሀድሶ መድረኩ በየደረጃው መካሄዱ በቀጣይ ከየተቋማቱ የተሻለ አገልግሎት እንድንጠብቅ አድርጐናል ሲሉ በትግራይ ክልል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

በየወረዳዎችና ቀበሌዎች እየተካሄደ ያለው የጥልቅ ተሀድሶ መድረክ ከተጠበቀው በላይ የህዝብ ችግሮች የተጋለጡበት መሆኑን ገልጿል፡፡

በሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በፀገዴ ወረዳ የአውረራ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ኣቶ በሪሁ ሐጎስ እንዳሉት፣ መድረኩ የተሰጣቸውን የህዝብ አደራ ወደ ጎን በመተው የራሳቸውን ጥቅም ሲያሳድዱ የነበሩ የወረዳና የቀበሌ አመራሮችን ያጋለጠ ነው፡፡

የኢህአዴግ ጥልቅ ታሃድሶ ተከትሎ በቀበሌያቸው የተካሄደው የህዝብ መድረክ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እንደየጥፋታቸው በህግ የመጠየቅ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ውሳኔ የተላለፈበት እንደነበር አቶ በሪሁ ተናግረዋል።

‘‘ለህዝብ እምነትና የተለየ ክብር የሰጠ የግምገማ መድረክ በማየቴም በኢህአዴግና በመንግስት የነበረኝን ቅሬታ እንዳነሳ ረድቶኛል‘‘ ያሉት አቶ በሪሁ በቀጣይም ተቋማቱ ችግሮችን በማስተካከል የተሻለ አገልግሎት ይሰጣሉ ብለው እንደሚጠብቁ ገልፀዋል፡፡

በመቀሌ ከተማ የሴቶች ልማት ቡድን አስተባባሪ ወይዘሮ ፀጋ ገብረመድህን በበኩላቸው የውይይት መድረኩ ''የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የቀበሌ የነዋሪነት መታወቂያ በህግ ወጥ መንገድ ሲሰጡ የነበሩ አመራሮች እንዲጋለጡ አስችሏል'' ብለዋል።

የራስን ጥቅም በማስቀደም ህዝብና ሃገርን ሲበድሉና ህዝብን ሲያጉላሉ የቆዩ ግለሰቦች እንዲጋለጡና በህግ እንዲጠየቁ ያስቻለ መድረክ እንደነበርም ተናግረዋል።

መድረኩ ሠራተኛው በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበሩበትን ችግሮች በግልጽ እንያይ ያስቻለ በመሆኑ በቀጣይ የተሻለ አገልግሎት ከየተቋማቱ እንደሚጠብቁ ገልፀዋል፡፡

በትግራይ ደቡባዊ ዞን የራያ አላማጣ ወረዳ ነዋሪ አቶ ካልአዩ አለ በበኩላቸው፣ ፀረ ሰላም ቡድኖች ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል ለመናድ ሲሞክሩት የነበረውን አፍራሽ እንቅስቃሴ እልባት እንዲያገኝ መድረኩ ትልቅ ድርሻ መጫወቱን ተናግረዋል።

''የውስጣችንን ችግር ሳናፀዳ ከውጭ የሚመጣውን መከላከል አይቻልም'' ያሉት አቶ ካልአዩ ፣''የተጀመረው ራስህን የማደስ ትግል ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል'' ብለዋል።

በትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ ከፍተኛ የህግ ባለሙያ አቶ እያሱ ገብረስላሴ እንዳሉትም፣   ''የህግ የበላይነትን በማክበርና ለሀገር ተቆርቋሪ ዜጋ ለመፍጠር መድረኩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል'' ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ  ምክትል ኃላፊ አቶ አረጋይ ገብረእግዚአብሄር ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፣ በየወረዳዎችና ቀበሌዎች እየተካሄደ ያለው የጥልቅ ተሀድሶ መድረክ ከተጠበቀው በላይ የህዝብ ችግሮች እንዲጋለጡና የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲቀመጥላቸው አስችለዋል፡፡

እየተካሄደ ባለው የግምገማ መድረክ ህዝብና አገርን በድሏል ተብለው የተገመገሙና በማስረጃ የተደገፈ ጥፋት ፈጽመው ተገኝቷዋል የተባሉ በርካታ ተጠርጣሪዎች ደግሞ በህግ እንዲጠየቁ እየተሰራ መሆኑ ምክትል  ቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል።

በትግራይ ክልል በሚገኙ ሰባት ዞኖችና 52 ወረዳዎች በሚገኙ  ከ800 በላይ ቀበሌዎች ህዝባዊ መድረኮች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 27/2009 በመዲናዋ ቀለበት መንገዶች መብራት ባለመኖሩ በምሽት አደጋ የሚያደርሱ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ የትራፊክ መብራት በተገቢው ቦታ አለመኖሩም ችግሩን እንዳባባሰው ነው የገለጸው።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በቀለበት መንገዶች የመንገድና የትራፊክ መብራት ባለመኖሩ በምሽት አደጋ የሚያደርሱ አሽከርካሪዎችን ለመያዝ  አዳጋች ሆኗል።

በቀለበት መንገድ የሚያሽከረክሩ በሰዎች ላይ አደጋ ካደረሱ በኋላ እንደሚሰወሩ አመልክተው፤ የትራፊክ ፖሊሶች በአካባቢዎቹ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ጫና እየፈጠረባቸው መምጣቱን ነው የገለጹት።

በአዲስአበባ ዋና ዋና መንገዶች በተለይም ከመካኒሳ-ጀሞ-ሀናማሪያም ወደቃሊቲ የሚወስደው የቀለበት መንገድ መብራት ባለመኖሩ ለትራፊክ አደጋ መጨመር ምክንያት እየሆነመምጣቱን ነው የተናገሩት ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ።

ምክትል ኢንሰፔከተር አሰፋ የትራፊክ መብራት የሚያስፈልግባቸው ቦታዎችን ለይቶ አለማወቅ አንዱ ለትራፊክ አደጋ መጨመር ምክንያት መሆኑን ነው የተናገሩት። የሚያስፈልግበት ቦታ እያለ ከማያስፈልግበት ቦታ እየተተከለ መሆኑንም ገልፀዋል።

ምክትል ኢኒስፔክተር አሰፋ እንዳሉት ከሜክስኮ ጀምሮ እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ የትራፊክ መብራት ያስፈልጋል። ነገር ግን የለም፤  ገነት ሆቴል መታጠፊያ ላይ እንዲሁም የቀድሞው ጉምሩክ አካባቢ ለጊዜው አያስፈልግም፤ ግን የትራፊክ መብራት ተገጠሞለታል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት የመንገድ መብራቶችን በየወቅቱ እየፈተሸ  ችግሮችን  በፍጥነት ከመፍታት አኳያ ጉድለት እንዳለበት ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብረእግዚአብሄር ታፈረ  እንደተናገሩት፤ በመንገድ መብራቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በግምገማ ተለይተው ታውቀዋል።

ከአዲሱ ገበያ ወደ ዊንጌት የሚወስደው የቀለበት  መንገድም  የመብራት ተከላ ስራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ነው የተናገሩት።

ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ የቀለበት መንገዶችንም ግንባታቸው እንደተጠናቀቀ የመብራት ተከላውን ስራ ለማከናወን  አስፈላጊ ማቴሪያሎች መሟላታቸውን ነው የተናገሩት።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በበኩሉ እንደገለጸው፤ መስሪያ ቤቱ አዲስ በመሆኑ ትራፊክ መብራት የሚያስፈልጋቸውንና  የማያስፈልጋቸውን መስመሮች የመለየት ሥራ እየሰራ ነው። ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮችን ለማስተካከል የጥናት ስራዎች መጠናቀቃቸውንም ገልጿል።

የአዲስ አበባ መንገዶች ትራፊክ ማኔጅመንት ዋና ዳይሬከተር  አቶ ገነቱ ደሳለኝ፤ መስሪያ ቤቱ ከተቋቋመ አንድ ዓመት መሆኑን ገልጸው። 

ከመካኒሳ -ጀሞ-ቃሊቲ የሚወስደው መንገድ ትራፊክ መብራት ያልተገጠመለት መንገዱ ባለመጠናቀቁ ምክንያት ነው።

ለአገልግሎት ክፍት የሆነበት ምክንያት የመንገድ መጨናነቅ በመኖሩ "መጨናነቁን ይቀንሳል በሚል አማራጭ ነው" ብለዋል።

የመንገዱ  ግንባታ እንደተጠናቀቀ በሚያስፈልግበት ቦታ ላይ የመግጠም ስራ ወዲያውኑ ይከናወናል ነው ያሉት ።

አዳዲስ የመንገድና ትራፊክ መብራት የሚያስፈልጋቸውን ለመለየትም ጥናት እየተደረገ መሆኑን ነው ያረጋገጡት።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 27/2009 ለቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ ግንባታ ሲጠቀሙበት የነበረውን መሬት የሰጡ አርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ እንደዘገየባቸው ገለጹ።

አርሶ አደሮቹ በተወሰደባቸው መሬት ምትክ ቦታ፣ የካሳ ግምትና ከካሳ ክፍያ በሚያገኙት ገንዘብ አዋጭ ጥቅም የሚያስገኝላቸውን "የንግድ ዕቅድ" አዘጋጅቶ መጨረሱን የምዕራብ ጎጃም ዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን በቡሬ ከተማ በአንድ ሺህ ሄክታር ላይ የሚያርፈው የቡሬ የተቀናጀ ግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ባለፈው ሐሙስ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።

ፓርኩ ከሚገነባበት አንድ ሺህ ሄክታር መሬት 260 ሄክታሩን በተያዘው ዓመት ግንባታውን ለማጠናቀቅ የታሰበ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 165 ሄክታር መሬት መኖሪያ ቤት የተገነባበትና የግለሰቦች እርሻ እንደነበር ተገልጿል።

ይሁንና መሬቱ በግለሰቦች ቢያዝም የህዝብን ጥቅም ለሚያስከብር የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ በመፈለጉ የክልሉ መንግሥት የመሬት ካሳ ግምት፣ ምትክ መሬትና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ በመስማማት መሬቱን ተረክቧል።

የፓርኩ የግንባታ መሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ መርሃ ግብሩን ለመዘገብ ወደ ስፍራው ያቀናው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የጋዜጠኞች ቡድን አርሶ አደሮቹ ከፓርኩ ግንባታ ጋር ተያይዞ ያላቸውን አስተያየት ጠይቋል።

በግብርና ሥራ የሚተዳደሩት አቶ አበበ መኖር፣ አቶ ኃያሉ ምንባና አቶ ብርሃኔ እንግዳ እንደገለጹት፤ ፓርኩ የአካባቢው ህዝብና እነሱን የሚጠቅም መሆኑን ተረድተው ይጠቀሙበት የነበረውን መሬት ለመንግሥት ሰጥተዋል።

ነገር ግን መንግሥት በወቅቱ ቃል በገባው መሰረት የካሳ ክፍያ፣ ምትክ መሬትና ሌሎች ድጋፎች እስካሁን እንዳላገኙ ነው የሚናገሩት።

የቡሬ ከተማ ከንቲባ አቶ አግማሴ እሸቴ እንደገለጹት፤ ፓርኩ ከ 260 ሄክታር መሬት ላይ 296 አርሶ አደሮች ከሚሰሩበት ቦታ ተነስተው ወደ ሌላ አካባቢ ይዛወራሉ።

"አሁን ላይ ለተፈናቃይ አርሶ አደሮቹ ተገቢው የካሳ ክፍያና ድጋፍ ካልተደረገላቸው በቀጣይ ለፓርኩ ልማት የሚያስፈልገው 740 ሄክታር ተጨማሪ መሬት የማፈላለግ ስራችንን እጅግ አስቸጋሪ የሚያደርግብን በመሆኑ የካሳው ጉዳይ ቶሎ ሊፈታ ይገባል" ብለዋል።

ለፓርኩ ልማት ተብሎ ከአርሶ አደሮቹ የተወሰደው መሬት የካሳ ክፍያ ለሚፈልግ ተገቢውን ክፍያ፣ የመኖሪያ ቤት መስሪያና ምትክ መሬት ለሚፈልጉ ተለዋጭ መሬት የማዘጋጀት ተግባር የክልሉና የዞን ባለሙያዎች ማጠናቃቃቸውን የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳደር ገልጿል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጎሹ እንዳላማው እንዳሉት የካሳ ስሌትን መሰረት በማድረግ ክፍያው ለአርሶ አደሩ እንዲከፈል ይደረጋል ብለዋል። 

ከምትክ የእርሻ መሬትና መኖሪያ ቤት ቦታ መስጠት በተጨማሪም መንግስት ከሚሰሩበት አካባቢ የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች ያገኙት የካሳ ክፍያ ገንዘብ እንዳይባክን በአዋጭና የረጅም ጊዜ ጥቅም ሊያስገኝላቸው የሚችል ዕቅድ ማዘጋጀቱን ምክትል አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ በተያዘው ዓመት ግንባታው ተጠናቆ ባለኃብቶች በ 2010 ዓ.ም ወደ ፓርኩ ገብተው ማምረት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር ጥር 27/2009 በአማራ ክልል የተፋሰስ ልማት በተካሄዳባቸውና የደን  አካባቢዎች የሚተከል  ከሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለማዘጋጀት እየተሰራ ነው፡፡

በክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ አጠቃቀም የስራ ሂደት መሪ አቶ ጌታቸው እንግዳየሁ እንደገለጹት  በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግር  የጠፋውን ደን መልሶ ለመተካት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅትም በመጪው የክረምት ወቅት  የሚተከል የዛፍ ችግኝ የማፍላትና የሚለማበት  ቦታ የመለየት ስራ እየተካሄደ  ነው፡፡

እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴም 119 ሺህ 500 የሚሆኑ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎችን በማዘጋጀት ለተከላ የሚውል ከ15 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ችግኝ ማፍላት ተችሏል፡፡

ቀሪውን ችግኝ ለማዘጋጀት በሂደት ላይ የሚገኝ  ሲሆን ከ312 ኩንታል በላይ ዘር ተሰባስቦ ተሰራጭቷል።

አቶ ጌታቸው እንዳሉት የሚዘጋጀው ችግኝ  በበጋው ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ በተሰራባቸው ተፋሰሶችና  የደን አካባቢዎች የሚተከል ነው፡፡

በዚሀም  ከ523 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መሸፈን የሚያስችል እንደሆነም  ጠቁመዋል።

የሃገር ውስጥና የውጭ ዝርያዎችን ጨምሮ እየተዘጋጁ ካሉት የዛፍ ችግኞች መካከል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ዋንዛ፣ ግራር፣ ወይራ፣ ፅድ፣ ብሳና፣ ዋርካ ይገኙበታል፡፡

በክልሉ  ቀደም ሲል ሰባት ነጥብ ስምንት በመቶ ደርሶ የነበረው  የደን ሃብት ሽፋን  የችግኝ ተከላ፣ ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ አሁን 14 በመቶ ማድረስ መቻሉም ተመልክቷል፡፡

ወጣት ፈቃዱ ሙሉጌታ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ የአቢዎት ፋና ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን  በመጪው የክረምት ወቅት  ለአካባቢው ተስማሚ የሆነ 60 ሺህ የዛፍ  ችግኝ ለማፍላት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ተናግሯል፡፡

በሚፈላው ችግኝም 700  የሚሆኑ ወጣቶችን በማስተባበር ከ12 ሄክታር በላይ መሬት በደን ለመሸፈን የተደራጀ እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም ጠቁሟል።

እንደ ወጣቱ  ገለፃ በግሉም ስድስት ሺህ 500 የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የአቦካዶና የማንጎ ችግኞችን እያፈላ ነው፤  ከአትክልት ችግኝ ሽያጭ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሰራ ይገኛል፡፡

በዚሁ ወረዳ የአማሪት ቀበሌ  የአይተነውና ጓደኞቹ የአትክልትና ፍራፍሬ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት አይተነው ገነት በበኩሉ በቀጣዩ  ክረምት   15 ሺህ ችግኝ ለመትከል የማፍላት ስራ መጀመራቸውን ገልጿል፡፡

በቀበሌው ለማህበራቸው በተሰጣቸው 15 ሄክታር መሬትም ባለፉት አራት  ዓመታት ከ300 ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል ለአካባቢው ደን ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ጠቅሷል፡፡

በክልሉ ባለፈው የክረምት ወቅትም ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተተክሎ እንክብካቤና ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑንም የክልሉ ግብርና ቢሮ አመልክቷል።

Published in አካባቢ

ድሬዳዋ ጥር27/2009 በየቀበሌያቸው መልካም አስተዳደር በማስፈን የበደሉትን ህዝብ ለመካስ መዘጋጀታቸውን በጥልቅ የመታደስ የግምገማና ሥልጠና መድረክ ላይ የተሣተፉ የድሬዳዋ ቀበሌ ሠራተኞች ገለፁ፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር ከጥር 22 ቀን 2009 ጀምሮ ለአምስት ቀናት በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ የተሣተፉ የቀበሌ ሠራተኞች ለኢዜአ ዛሬ እንደገለፁት ሀገሪቱ የምትመራበትን መሠረታዊ ልማታዊ አቅጣጫዎች፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ላይ ተገቢውን ዕውቀትና ግንዛቤ ጨብጠዋል፡፡

ባለፉት 15 ዓመታት በተመዘገቡ የልማት፣ የሠላም እንዲሁም የማህበራዊና የምጣኔ ሃብታዊ ዕድገቶች ላይ የድርሻቸውን ቢያበረክቱም የሚጠበቅባቸውን ተልዕኮና ኃላፊነት በሙሉ አቅም ከመፈፀም አንጻር ክፍተት መኖሩን ገልፀዋል፡፡

በተለይ የህዝቡን የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት ጥያቄዎች በሚያረካና በተገቢው መንገድ ከመፍታት አንፃር መሠረታዊ ክፍተት እንደነበረባቸው በጋራና በተናጠል ባካሄዱት ግምገማ መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

እነዚህን ክፍተቶች ለማረምና የበደሉትን ህዝብ ለመካስ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የቀበሌ 07 ሠራተኛ አቶ ሱሌይማን አሊ ህዝቡ እየተማረረ የሚገኝባቸውን ዘርፎች መለየታቸውን ገልፀው ''እኔም ሆንኩ የሥራ ባልደረቦቼ ህዝቡን ያማረሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመፍታት ተጋልጋዩን ለመካስ ተዘጋጅተናል'' ብለዋል፡፡

ከሥልጠናው መሠረታዊ እውቀት ጨብጫለሁ ‹‹ በአመራሩም ሆነ በሠራተኛው ውስጥ ያሉ ክፍተቶች ተለይተዋል፤ በቀጣይ ህዝቡን በመካስና በሙሉ አቅሜ ለማገልገል ተዘጋጅቻለሁ ያሉት ደግሞ የቀበሌ 06 ሠራተኛ አቶ በቀለ አበበ ናቸው፡፡

የቀበሌ 02 የደንብ ማስከበር ሠራተኛ ወይዘሮ ሰላም ፍቅሬ በበኩላቸው  ተሃድሶው በኪራይ ሰብሳቢነት፤ በህገ-ወጥ ግንባታና ብልሹ አሠራሮችን ለመፍታት መሠረታዊ እውቀት ያስጨበጠና ሊጠናከር የሚገባው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኪራይ ሰብሳቢነት በመሳተፍ ህገ-ወጥ ቤቶች እንዲበራከቱ ሠራተኛው የራሱ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው ይህን በመታገልና በመከላከል ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ተመሣሣይ ሃሳብን ያራመዱት አቶ ገብሬ ትኩ በበኩላቸው ''ሠራተኛው ራሱ ምን ላይ እንዳለ ተረድቷል፣ በቀጣይ እኔም ብልሹ አሠራሮችን በመታገል ኪራይ ሰብሳቢነትን በመመከት የህዝቡ እንባ እንዲታበስ እሰራለሁ'' ብለዋል፡፡

መድረኩ በመንግስት ፖሊሲዎችና ስታራቴጂዎች ላይ የጠራ ግንዛቤ እንዲፈጠር ያስቻለና ባለፉት 15 ዓመታት የተመዘገቡ ለውጦችና የተስተዋሉ ችግሮች በውል ሠራተኛውና አመራሩ እንዲገነዘብ አስችሏል ያሉት ደግሞ አቶ ሲራጅ ሁሴን ናቸው፡፡

''እኔም የተስተዋሉትን ክፍተቶች ሥር ነቀል በሆነ መንገድ እንዲፈታ ኃላፊነቴን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ''

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን የሚፈለገውን ሁለንተናዊ የልማት፤ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄዎች ለመመለስ ከሠራተኛው የተሃድሶ መድረክ በመቀጠል ከህብረተሰቡ ጋር ተመሣሣይ ውይይት እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ጅጅጋ ጥር 27/2009 በአገሪቱ የሚታየውን ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ አስታወቁ፡፡

10ኛው  ሀገር አቀፍ የግብር እና ቀረጥ ሳምንት ትናንት በጅግጅጋ ከተማ በፓናል ውይይት መከበር ጀምሯል፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ  በውይይቱ ላይ እንደገለፁት ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የአገር ኢኮኖሚን ይጎዳል፡፡

ባለፉት ዓመታት በተለይ የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ህብረተሰብ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል ባካሄደው ጥረት በመጠኑም ቢሆን ህጋዊ የግብይት ስርዓት እንዲይዝ ማገዙን ገልፀዋል፡፡

አሁንም ግን የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴ እንዳልቆመ የጠቆሙት  ሚኒስትሩ "በህገ ወጥ መንገድ ወደ መሃል አገር የሚገቡ ሸቀጦች የአዲስ አበባ ገበያን እያጥለቀለቁት ነው "ብለዋል፡፡

ይህ ደግሞ በህጋዊ መንገድ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘውን የንግድ ህብረተሰብ እየጐዳው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በአግባቡ ለህብረተሰቡ እየደረሰ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ለኦሮሚያ ክልል ከፊል ዞኖች የተፈቀዱ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በኢትዮዽያ ሶማሌ ክልል ከተሞች ሲሸጥ መገኘቱን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

ህገ - ወጥ ነጋዴዎቹ በክልሉ ነዋሪዎች ስም ለማህበራት የተሰጠውን ፈቃድ ከማህበራቱ በመከራየት እየተጠቀሙ  መሆናቸውን ጠቁመው ይህም በየክልሎቹ የሚገኙ ፈቃድ ሰጪ መስሪያ ቤቶች ክትትል እንዳላደረጉ እንደሚያመላክት ተናግረዋል፡፡

ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከልና የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት የተናበበ እቅድ በማዘጋጀት የጀመሩትን ቅንጅታዊ ስራ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሀሙድ ከቀረጥ ነፃ መፈቀዱ የህብረተሰቡን ችግሮች እንዲፈቱ እያገዘ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አቅርቦቱን በተመለከተም ለተፈቀደላቸው አርብቶ አደሮች በጊዜና በአግባቡ እንዲቀርብ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ቀጣይ ክትትል እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

በክልሉ የጠረፍ አካባቢ ነዋሪዎችን ወደ ህጋዊ ንግድ እንቅስቃሴ እንዲገቡ የሚደርግ አሰራር አለመኖሩን የገለፁት ርእሰ መስተዳድሩ የፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከንግድ ሚኒስትር ጋር በመነጋገር ችግሩን መፍታት እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የክልል ገቢዎች ተወካዮች የክልሉ ጠረፋማ ወረዳዎች አመራሮች የባለስልጣኑ አመራሮችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡

የግብር እና ቀረጥ ሳምንት በፓናል ውይይቶች፣ በፎቶ እግዚብሽን እና በእግር ጉዞ መርሃ - ግብሮች እስከ የካቲት 1 ቀን 2009 ይከበራል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 27/2009  በአዲስ አበባ ከተማ በዋና ዋና አደባባዮች እግረኞች መስመራቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ለማድረግ በአዲስ መልክ የመንገድ አካፋይ አጥሮች ተሰርተዋል። የመንገድ አካፋዮቹ መኖር ለእግረኞች የተመቸ ቢመስሉም ተሽከርካሪዎች ከፈጣን እንቅስቃሴ  ተገድበው ይታያል።

የኢዜአ ሪፖርተር በሜክሲኮ አደባባይ፣ ስታዲየምና መገናኛ አደባባይ ተዘዋውሮ እንደተመለከተው የመንገድ አካፋይ አጥሮቹ በተተከሉበት የመገናኛ አደባባይ የትራፊክ መጨናነቅ ተከስቶ አስተውሏል።

በየስፈራው ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደተናገሩት፤ የመንገድ አካፋይ አጥሮቹ ለእግረኛ ጥሩ ቢሆኑም ለተሽከርካሪ መጨናነቅን ፈጥሯል።

የትራፊክ ፖሊስ ዋና ሳጅን በላይ ወልዴ እንደሚገልጹት፤ የመንገድ አካፋይ አጥሮቹ እግረኛው መንገዱን ጠብቆ እንዲጓዝ አድረጓል። ተሽከርካሪዎችም  ስርዓት ጠብቀው ለመጓዝ ቢችሉም "ተሽከርካሪ በብዛት ስላለ እንቅስቃሴውን ይገድባል" ነው ያሉት።

ከነዚህ የመንገድ አካፋይ አጥሮች ይልቅ የእግረኛ መሻገሪያ ድልድዮች ቢኖሩ የትራፊክ ፍሰት የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመው፤ ይህም ለትራፊክ አደጋ መቀነስ ምክንያት እንደሚሆን ነው የገለፁት።

ሌላው አስተያየት ሰጪ የላዳ አሽከርካሪ አቶ አብደላ አህመድ በትራፊክ ፖሊሱ የተሰነዘረውን ሃሳብ ይጋራሉ።

የመንገድ አካፋይ አጥሮቹ ለእግረኛ ጥሩ መሆናቸውነ አመልከተው፤ ለተሽከርካሪዎች ግን መንገዱ ይበልጥ የትራፊክ መጨናነቅ እንዲኖር  ማድረጉን ነው ያከሉት።

የመንገድ አካፋይ አጥሮቹ እግረኛው መንገዱን ጠብቆ እንዲጓዝና የእግረኛ አስተባባሪዎችን ስራ እንዳቃለለላቸው የገለፀው ደግሞ በጎፈቃደኛ እግረኛ አስተባባሪ ወጣት ዘሪሁን ከበደ ነው።

የአዲስ አበባ የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በበኩሉ እንደገለጸው፤ የመንገድ አካፋይ አጥሮቹ እግረኛውን አቅጣጫ የሚያሳዩና የተሽከርካሪ ፍሰቱን ለማሳለጥ የሚያስችሉ ናቸው።

የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታመነ በሌ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በአንድ ሳምንት ክንውን ሜክሲኮ አደባባይ፣ ስታዲየም፣ መገናኛ እንዲሁም ሲኤምሲ አካባቢዎች ላይ መሰራቱን ነው የገለጹት።

በቀጣይም ቄራ መጋጠሚያና ቡናና ሻይ ፊት ለፊት እንዲሁም በጥናት በተለዩ የትራፊክ መጨናነቅ በሚስተዋልባቸው አደባባዮችና መጋጠሚያዎች ላይ ይተከላል።

የመንገድ አካፋይ አጥሮቹን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ማቅረቡን ገልፀው፤ በውሃ የሚሞሉት ፕላስቲክ የመንገድ አጥሮች ከ560ሺህ ብር በላይ ተገጣጣሚ የብረት የመንገድ አጥሮቹ ደግሞ ከ180 ሺ ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸዋል።

አቶ ታመነ የከተማዋ ነዋሪ የተቀመጡትን የመንገድ አካፋይ አጥሮች በመንከባከብና የእግረኛ አስተባባሪ በጎ ፍቃደኞችን በመተባበር ለትራፊክ አደጋ መቀነስ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት 250 በውሃ የሚሞሉ የፕላስቲክና 145 ተገጣጣሚ የብረት የመንገድ አካፋይ አጥሮች የትራፊክ መጨናነቅ በሚስተዋልባቸው የተለዩ ቦታዎች ላይ መተከላቸው ታውቋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 27/2009  በኢትዮጵያ የኬሚካል አወጋገድ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ ለኢዜአ እንዳተናገሩት፤ ቀደም ሲል አገልግሎቱ ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት በ21 የፌዴራል መንግስት ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ጊዜዉ  ያለፈበት የኬሚካል ክምችት መኖሩ ታውቋል።

ይህም የሆነበት ምክንያት "በአገሪቷ ኬሚካሎች የሚወገዱበት ሥርዓትና የሚያስወግዳቸው ራሱን የቻለ ባለቤት ባለመኖሩ ነው" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን በአካባቢ ላይ ጉዳት ሳያደርሱ የሚወገዱበትን ስርዓት ለመዘርጋት ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመስራት ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

የኬሚካሉ ክምችት መጠንና ዓይነት በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መታወቁ ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው ኬሚካሎቹ የሚወገዱበትን መንገድ አጥንቶ ውጤቱን እንዲያሳውቅ ከስምምነት ላይ ተደርሶ ወደ ስራ መገባቱንም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ጥናቱን ከሚከታተሉት አንዷ ዶክተር አዳም መኮንን በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ጥናቱን ለማካሄድ ለሚመለከታቸው ኮሌጆች ደብዳቤ  በመጻፍ ከየትምህርት ክፍሉ የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያሉበት አጥኚ ኮሚቴ እያዋቀረ መሆኑን ገልፀዋል።

ጥንቱም በተያዘው አመት እንደሚጠናቀቅ ገልፀዋል።

ጥናቱ የኬሚካሎቹ ባህሪና መጠን  ላይ ተመስርቶ የሚደረግ መሆኑን አመልክተው፤ የሌሎች አገሮች ተመክሮ በመቀመር ወጥ የሆነ የኬሚካል አወጋገድ ሥርዓት በአገሪቷ እንዲኖር እንደሚያግዝ ተነናግረዋል።

ኬሚካሎቹ ካላቸው የተለያዬ ባህሪ አኳያ ከፍተኛ የሆነ ሙያዊ ጥናት እንደሚያስፈልገውና በኬሚካሎቹ አሰባሰብና አያያዝ ላይም ለሚመለከታቸው ተቋማት ስልጠና መስጠት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በአገሪቷ ውስጥ የሚገኙ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎች መጠንና ዓይነት ለማወቅ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጥናት አካሂዶ እንደነበር   ይታወሳል።

በዚህም በ21 የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ውስጥ  ማዳበሪያዎች፣ አረም ማጥፊያዎችንና የላቦራቶሪ ኬሚካሎችን ጨምሮ የተለያዩ መጠንና አይነት ያለቸው የኬሚካል ክምችት መኖሩ ተለይቷል።

በኬሚካሎቹ አያያዝና ክምችት ላይ ጥንቃቄ እየተደረገ አለመሆኑንና በወቅቱ ካልተወገዱ በአካባቢ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉም ይፋ መደረጉ የሚታወስ ነው።

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ጥር  27/2009  የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት የስኳር ፕሮጀክት የምርት ሙከራ በመጪው መጋቢት እንደሚጀምር የስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ኢትዮጵያ የሕዝቡን የስኳር ፍላጎት ለማሟላት 300 ሺህ ቶን ስኳር ከውጭ ለማስገባት ባለፈው ዓመት ውል መፈጸሟ የሚታወስ ነው።

አገራዊ የስኳር ፍላጎትን በአገር ውስጥ አቅርቦት ለማሟላት አሥር የስኳር ፕሮጀክቶች መንግሥት እየገነባ ይገኛል።

በደቡብ ክልል የኦሞ ወንዝን ተከትለው በቀን 60 ሺህ ቶን ሸንኮር አገዳ የመፍጨት ዓቅም ያላቸው አራት የስኳር ፕሮጀክቶች በ 1 ነጥብ 465 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገነቡት የፕሮጀክቱ አካል ናቸው።

ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ኦሞ አንድና ሁለት የስኳር ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ በሙሉ ዓቅማቸው ወደ ምርት እንደሚገቡ ይጠበቃል።

ሁለቱ የስኳር ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምሩ በዓመት 650 ሺህ ቶን ስኳር እንደሚያመርቱ ነው ኮርፖሬሽኑ የገለጸው።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ እንዳወቅ አብቴ ለኢዜአ እንደገለጹ በቻይና ኩባንያ በመገንባት ላይ ያለው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት የስኳር ፕሮጀክት በበጀት ዓመቱ ወደ ምርት ይገባል።

በአሁኑ ጊዜ የፋብሪካው የማሽነሪ ግንባታና ተከላ ሥራ ተጠናቅቆ አፈፃጸሙ ከ 90 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን ቀሪው የፋብሪካው ሲቪል ሥራም በቅርቡ እንደሚጠባቀቅ ገልጸዋል።

የማሽነሪ፣ የኃል ማመንጫ ክፍል ሌሎች ማሽነሪዎች ፍተሻ ሥራዎች በማካሄድ ስኬታማ መሆኑን ተረጋግጦ በመጪው መጋቢት የምርት ሙከራ እንደሚጀምር ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የገለጹት።

ኩባንያው በገባው ውል መሰረት በሁለት ዓመታት ውስጥ ግንባታውን አጠናቀቆ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ማስረከብ የነበረበት ቢሆንም በተደረገው የዲዛይን ማሻሽያ ምክንያት የማጠናቀቂያ ውሉን እስከ የካቲት 2009 ዓ.ም እንዲራዘም ተደርጓል።   

በአገር ውስጥ ኩባንያ እየተገነባ ያለው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ስኳር ፕሮጀክት ሙሉ የማሽነሪ ፍተሻ በማጠናቀቅ በቀጣይ ወር ወደ ምርት የሚያሸጋግረውን የሙከራ ሥራ እንደሚጀምርም አቶ እንዳወቅ ጠቁመዋል።

የኦሞ አንድና ሁለት የስኳር ፕሮጀክቶች ወደ ምርት መሸጋገር የአገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ለውጭ ገበያ የሚተርፍ ምርት ይኖሯቸዋል ብለዋል።

"የኦሞ ቁጥር ሦስት የስኳር ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት እየተፋጠነ ነው" ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው እስካሁንም ከ 60 በመቶ በላይ ግንባታው መጠናቀቁን አመልክተዋል።

ከአንድ እስከ ሦስት ያሉት የስኳር ፕሮጀክቶች እያንዳንዳቸው በቀን 12 ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት ዓቅም ያላቸው ሲሆን ኦሞ አራት ግን በቀን 24 ሺህ ቶን በመፍጨት ዓቅሙ ልዩ ያደርገዋል ይላሉ።

ኦሞ ሁለት፣ ሦስትና አራት የስኳር ፕሮጀክቶች ከቻይና በብድር በተገኘ 1 ነጥብ 13 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር እና የኢትዮጵያ መንግሥት በመደበው 197 ሚልዮን የአሜሪካ ዶላር ነው የሚገነቡት።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን