አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Friday, 03 February 2017

ሀዋሳ ጥር 26/2009 በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በድርቁ ምክንያት የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ከ458 ሺህ በላይ  ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እህል ድጋፍ  እንደሚደረግ ተገለጸ፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የሚከፋፈል  ከ509 ሺህ  ኩንታል በላይ  የምግብ እህል እየተጓጓዘ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት የአየር ንብረት ለውጡን ተከትሎ በክልሉ ያጋጠመው ድርቅ ሰብአዊ ቀውስ ሳያደርስ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የመኸር ዝናብ በመዘግየቱና አነስተኛ በመሆኑ ተገቢውን ምርት ባለማግኘቱ 485 ሺህ 150 ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ  ያስፈልጋቸዋል፡፡

በተለይም ቸግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለህጻናትና እናቶች ጤና ትኩረት በመስጠት በጤና ተቋማት ማቆያዎች ተከፍተው የአልሚ ምግብ እንደሚቀርብ ሃላፊው ተናግረዋል፡፡ 

ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ከአምናው አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን የጠቆሙት ሃላፊው  ዝናቡ በዚሁ ከቀጠለና የውሃ መጠኑ ከቀነሰ  ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በመኸር ምርት መቀነስ ምክንያት አስቸኳይ ድጋፍ የሚደረግላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከጥር እስከ ሰኔ 2009ዓ.ም ድረስ የእለት ምግብ ያገኛሉ፡፡

የበልግ ምርት ማግኘት ሲጀምሩ ችግራቸው እንደሚቃለል ይጠበቃል፡፡

በምግብ እጥረት ምክንያት ሰብአዊ ቀውስ እንዳያጋጥም ተገቢው ትኩረት እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጥላሁን 509 ሺህ 234 ኩንታል  የተለያዩ የእለት ምግቦች እየተጓጓዙ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ  ስንዴ ፣ ጥራጥሬ ፣ ዘይትና አልሚ ምግብ ይገኝበታል፡፡

በክልሉ የምግብ ዋስትና ችግር ባለባቸው 79 ወረዳዎች የሚገኙ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ቋሚ የሴፍትኔት ተጠቃሚ መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

ወልዲያ ጥር 26/2009 የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ የራሳችንን ችግሮችና ጉድለቶች በግልጽ እንድናይ በማስቻሉ በቀጣይ ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት ያስችለናል ሲሉ በሰሜን ወሎ ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ።

የስራ ሰዓትን ለመንግስት ስራ ብቻ ያለማዋል፣ ሕዝብ የሚጠብቀውን ያህል አገልግሎት ያለመስጠትና  ኃላፊነትን በአግባቡ ያለመወጣት ችግር በየተቋማቱ መኖሩ በግምገማው ጎልቶ መታየቱንም አስተያየት ሰጪዎቹ አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ ገቢዎች ቅርንጫት ጽህፈት ቤት ሰራተኛ አቶ እንዳለ አማረ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው የእያንዳንዱን ሠራተኛና አመራር ችግሮች ነቅሶ ያሳየን ነው።

በአመራሩና ሠራተኛው ላይ የስራ ሰዓትን ለመንግስት ስራ ብቻ ያለማዋል፣ ሕዝብ የሚጠብቀውን ያህል አገልግሎት ያለመስጠትና  ኃላፊነትን በአግባቡ ያለመወጣት ችግር እንደሚታይ በግምገማው ጎልቶ መታየቱንም ተናግረዋል፡፡

የዞኑ መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ሰራተኛ አቶ ሲሳይ ደምሴ በበኩላቸው በተለይ የትራንስፖርት ዘርፉ ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚያነሳበት ቢሆንም አመራሩም ሆነ ሰራተኛው ችግሩን ለመፍታት እንዳልቻለ በግምገማው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

በቀጣይም የተስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ፍትሃዊ የመንግስት አገልግሎት እንዲሰፍን ለመስራት ቃል ገብተናል ሲል ገልጿል።

የዞኑ ሲቪል ሰርቢስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አራጌ ይመር እንደገለጹት ከዞን እስከ ቀበሌ ያሉ 18 ሺ 541 የመንግስት ሰራተኞች በዘጠኝ አጀንዳዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ዋና አላማውም ስህተቶችን አርሞ የተሻለ የስራ አፈጻጸም መፍጠርና እያንዳንዱ ሰራተኛ ያለበትን ደረጃ አውቆ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ማብቃት በመሆኑ ስኬቱ በተከታታይ ምዘና የሚረጋገጥ እንደሚሆን አስረድተዋል።

ደካማ የስራ አፈጻጸምና ብልሹ ሥነ ምግባር ያላቸውን ደግሞ  በማረምና በማስተካከል ያገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ የሚያስችል ውጤት ይጠበቃል ብለዋል፡፡  

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ጥር 26/2009 ከውጭ የሚገቡ የስኳርና የዘይት ምርቶች በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በአገር ውስጥ  ለመተካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ 

ላለፉት ሶስት ቀናት በመቀሌ ከተማ  ሲካሄድ የቆየውን አገር አቀፍ የንግድ ዘርፍ የምክክር መድረክ ዛሬ  ተጠናቋል፡፡

የንግድ ሚኒስትሩ ዶክተር በቀለ ጉላዶ በመድረኩ ላይ " መንግስት የስሚንቶ ምርቶችን እጥረትን  ለመፍታት የተከተለው መንገድ የዘይትና የስኳር ምርቶች እጥረት ለመፍታትም ይጠቀምበታል "ብለዋል፡፡

ለዚህም መንግስት በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች በማበረታታት በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ከውጭ የሚገቡ የስኳርና የዘይት ምርቶች በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት  ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከሚደረገው ጥረት ውስጥ   በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ አክስዮን ማህበር፣ዳብል ኤ የዘይት ማምረቻና ሌሎችም  ፋብሪካዎችን በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸው ይገኝበታል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በግንባታ ላይ የሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎችም ይጠቀሳሉ፡፡

"ፋብሪካዎቹ  በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት  ወደ ማምረት ደረጃ  ሲሸጋገሩ በከፍትኛ ውጭ ምንዛሪ የሚገቡ  የፓልም ዘይቶች ይቀራሉ "ብለዋል፡፡

እስከዚያ ድረስም በስርጭቱ ላይ የሚታዩ ችግሮች መፍታት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በአማራ ክልል ደብረማርቆስ ከተማ በ700ሚልዮን ብር ወጪ ግንባታ ሂደት ላይ የሚገኝ " ዳብል ኤ" የዘይት ማምረቻ ፋብሪካ በሚቀጥሉት ዘጠኝ ወራት ወደ ማምረት ስራ ይሸጋገራል፡፡

የፋብሪካው ስራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ ወርቁ አይተነው " ፋብሪካው ከአኩሪ አተር፣ሰሊጥ፣ኑግ፣በሎቄና ተልባን በመጠቀም  ዘይት ለማምረት የግንባታውን ሂደቱ ወደ ማጠናቀቅ ገደማ ደርሰዋል" ብለዋል፡፡

ፋብሪካው በቀን እስከ 155ሺህ ሊትር ዘይት በማምረት ግማሹ ለአገር ውስጥ ቀሪውን ደግሞ ወደ ውጭ ለመላክ እቅድ እንዳለቸውም ጠቅሰዋል፡፡

ላሉፉት ሶስት ቀናት የተደረገው ውይይትም  በንግድ ዘርፍ ላይ የሚታዩ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ትምህርት የተገኘበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

" ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በጥራትና በብዛት ለመጨመር  እንዲቻል  በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት ያሉትን ውስን  ላኪዎች የተያዘውን ቦታ መስፋት ይገባል " ያሉት ደግሞ የቢፍቱ አዱኛ አክስዮን ማህበር ስራ አስክያጅ አቶ ዱፌራ ሞቲ ናቸው፡፡

በምርት ገበያ ድርጅት ያሉት መገበያያዎች በውስን ላኪዎች በመያዛቸው በላኪነት ለመሰመራት የሚፈልጉ  አዳዲስ  ነጋዴዎች ማካተት እንዳልቻለም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ፀሀፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ በበኩላቸው " በአዲስ አበባ የሚካሄዱ የንግድ ባዛርና ትርኢት የኮንትሮባንድ  ምንጭ እየሆኑ ናቸው" ብለዋል፡፡

ንግድ ሚኒስቴር የሚካሄዱ የንግድ ባዛርና ትርኢት በሚገባ ሊፈትሻቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የንግድ ሚኒስትሩም የተነሱትን ጉዳዮች በግብአትነት በመጠቀም ለማስተካከል  እንደሚሰራ የገለጹ ሲሆን ከዘርፍ ማህበራት፣ከአስመጪዎችና ላኪዎች እንዲሁም ከክልል ንግድ ቢሮዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ ሁሉም ክልሎች ባቀረቡት የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርታቸው ላይ የጋራ ውይይት አድረገዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ወልዲያ ጥር 26/2009 በቀበሌ ማዕከላት የእንስሳት ጤና ባለሙያ ተመድቦ ክትባትና ህክምና መሰጠቱ የቤት እንስሳቶቻቸውን ጤንነት በመጠበቅ ተጠቃሚ እንዳደጋቸው የሰሜን ወሎ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዘንድሮው የመጀመሪያ ግማሽ የበጀት ዓመት ከ4 ሚሊዮን በላይ እንስሳት የበሽታ መከላከያ ክትባትና ህክምና መስጠቱን የዞኑ እንስሳት ሃብት ተጠሪ ጽህፈት ቤት አመልክቷል።

በዞኑ በመቄት ወረዳ የ034 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደምሌ ተስፋው በሰጡት አስተያየት በቀበሌው በተመደበች አንድ ባለሙያ ለእንስሳታቸው ክትባትና ህክምና በወቀቱ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

ያሏቸውን ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች የጤና መታወክ ሲገጥማቸው ወደ ክሊኒኩ ፈጥነው እንደሚወስዱ ጠቁመው የመድሃኒት እጥረትም ላለፉት ሶስት ዓመታት እንዳላጋጠማቸው ተናግረዋል፡፡

በራያ ቆቦ ወረዳ የ07 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መንገሻ አያሌው በበኩላቸው ባለው ነባር ክሊኒክ የማዳቀል፣ የህክምናና የክትባት አገልግሎት እንደሚያገኙ አረጋግጠዋል።

በተለይም ባለፈው ዓመት ባጋጠመው የድርቅ አደጋ የተጎዱ አካባቢዎችን በመለየት ነፃ የእንስሳት ህክምናና ክትባት እስካሁን እየተሰጠ በመሆኑ እርሳቸውም ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በጉባላፍቶ ወረዳ የ04 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጌታቸው በበኩላቸው የህክምና አገልግሎት ፈልገው ያጡበት ጊዜ አለመኖሩን ገልጸው በተለይ ከሁለት ዓመት ወዲህ የመድሃኒት አቅርቦት እጥረት በቀበሌው እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በበልግ ዝናብ መጥፋት የጀመረው ድርቅን ተከትሎ መንግስት ነጻ የእንስሳትን ክትባትና ህክምና ማቅረቡን በሰሜን ወሎ ዞን  የእንስሳት ሀብት ልማት ተጠሪ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በጽህፈት ቤቱ የእንስሳት ጤና ጥበቃና ቁጥጥር ባለሙያ ዶክተር አየለ አስማማው እንደገለጹት በዘንድሮው የመጀመሪያ ግማሽ የበጀት ዓመት ከ4 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ እንስሳት ክትባትና ህክምና መስጠቱን ገልጸዋል።

የጤና አገልግሎቱን ካገኙት እንስሳት መካከል ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት  የበሽታ መከላከያ ክትባት ያገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ ህክምና የተሰጣቸው ናቸው።

በግማሽ ዓመቱ የተመዘገበው አፈጻጸም ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር በክትባት በ595ሺ ፤ በህክምና ደግሞ ከ900 ሺህ በላይ እንስሳት ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ከእንስሳት የሚገኘውን ምርት በማሳደግ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንዲቻል  ባስተላለፈው መመሪያ እያንዳንዱ ወረዳ ለእንስሳት መድሃኒት ግዢ ብቻ የሚውል አንድ ሚሊዮን ተዘዋዋሪ በጀት ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ እንዲመድቡ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡

በተጨማሪም የእንስሳት ክሊኒክ የሌላቸው ቀበሌዎች ግንባታ በማከናወን አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 26/2009 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከወጣ በኋላ የተፈለገው ውጤት ቢመዘገብም "አሁን ይነሳል፣ ይራዘማል" የሚባልበት ጊዜ አለመሆኑን የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ገለፁ።

ሚኒስትሩ በህዝብ ተሳትፎ ታግዞ ጥልቅ ተሃድሶው የሚፈለገውን "ውጤት እያመጣ ነው" ብለዋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ የታወቀ ቢሆንም ዛሬ ላይ ሆነን ግን አዋጁ በዚህ ቀን ይነሳል፣ ይራዘማል፣ የሚባልበት ጊዜ አይደለም” ብለዋል።

ሚኒስትሩ እንደገለፁት፤ አዋጁ በመውጣቱ በወቅቱ የተፈጠሩ ችግሮችን በማቃለል ዜጎች ያለስጋት በሰላም መንቀሳቀስ ችለዋል። በተጨማሪም የልማት፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች ቀጥለዋል።

በዚህ መሰረት አዋጁ ዜጎች የሚጠብቁት በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የማድረግ ግቡን እየመታ መምጣቱን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

“አዋጁ በሚገመገምበት ጊዜ  ዓላማውን እያሳካ የመጣበት ሂደት አለ” ያሉት ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ነገሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በተለይ ወረቀቶችን የመበተን፣ ቅስቀሳ የማድረግ እና ቦምብ መጣል የመሳሰሉ ድርጊቶች መከሰታቸውን ገልፀዋል።

ይህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅመው የኮማንድ ፖስቱ "እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ለማቃለል መስራት እንዳለበት የሚያሳይ ነው"  ሲሉ ነው የገለጹት።

ይህ ግን "አዋጁ ይራዘማል ወይም ስድስት ወር ሳይሞላው ይነሳል ማለት አይደለም፤ ውጤቶችን በመገምገም የሚወሰን ነገር ነው" ብለዋል ሚኒስትሩ።

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለውን ጥልቅ ተሃድሶ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ተሃድሶው ህዝብ አምኖበት እየተሳተፈና የተፈለገው ውጤት እየመጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

"መንግስትና ዜጎች ከጥልቅ ተሃድሶው የሚጠብቁትን ውጤት ያውቃሉ" ያሉት ሚኒስትሩ፤ መንግስት ያሉትን ችግሮች በመዳሰስ ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ነው ያብራሩት።

ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ እየተካሄደ ባለው ጥልቅ ተሃድሶ የመንግስት ሠራተኛውና ህዝቡ በተዘጋጁላቸው መድረኮች መሪዎችን ፊት ለፊት በመገምገም የራሳቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው።

በተጨማሪም ሕዝቡ በተሳተፈባቸው መድረኮች መሪዎቹን ከመገምገሙ ባሻገር ጠንካራው እንዲቀጥል፣ መስተካከል የሚኖርባቸው ጉዳዮች እንዲስተካከሉና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ የበኩሉን ድረሻ መወጣቱንም ነው ያወሱት።

የበላይ አመራር አባላትን በመቀየር ብቻ ዜጎች የሚፈልጉትን ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንደማይቻል ጠቁመው፤ በፐብሊክ ሰርቪሱ ያለው ህዝብን የማገልገል አመለካከትና ችግር እንዲቃለል እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

መንግስት በተለዩት ችግሮች ላይ እርምጃዎችን እየተወሰደና በኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ተዘፍቀው የተገኙትን የመጠየቅ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለህዝብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በጥልቅ ተሃድሶው የሚወሰዱ እርምጃዎች እንደሚቀጥሉ ገልፀው፤ "የህዝብ አገልጋይነት አመለካከትን ለመፍጠር የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ" ብለዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥር 26/2009 የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ለመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ግንባታ የሚውል ከ270 ሚሊዮን ብር በላይ ስምምነት ዛሬ ከሥራ ተቋራጮች ጋር ተፈራረመ።

ስምምነቱን የፈረሙት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት እና የየተቋራጮቹ ዋና ሥራ አሥኪያጆች ናቸው።

የተፈረመው ስምምነት በሀዋሳና ሠመራ ኤርፖርቶች የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ለመገንባት የሚውል ነው።

የሀዋሳ ኤርፖርት ተርሚናል ዲዛይን በሃዋሳ ሀይቅ ብቻ የሚገኙ የአዕዋፋት ዝርያዎችን እንዲሁም በአካባቢው በስፋት የተለመደው የቤት አሰራር በሚያሳይ መልኩ የተዘጋጀ ነው።

ቤቱ በሳጠራ የሚሰራ ሆኖ ከጣሪያ ጀምሮ እስከ ወለል ድረስ እየሰፋ ወደታች በመውረድ ባህላዊ የቤት አሰራርና ሀይቁ ላይ የሚንሳፈፉ ወፎች የአካባቢው ልዩ መለያ በመሆናቸው በዲዛይኑ እንዲካተቱ ተደርጓል።

ግንባታው ሲጠናቀቅ አካባቢውን ለማስተዋወቅ የሚረዳ ከመሆኑም ባሻገር ለተርሚናሉ ተጨማሪ ውበት እንዲላበስ ያደርገዋል ነው የተባለው።

የሠመራ ተርሚናል ዲዛይን የአካባቢው ሴቶች የሚሰሩት ባህላዊ የቤት አሰራርን መሰረት አድርጎ አገራዊ ባህሉን ከዘመናዊ ግንባታ ጋር በማቀናጀት የሚገነባ ይሆናል።

ግንባታው ሲጠናቀቅ በውስጡ ሌሎች የአካባቢውን ባህል የሚያንጸባርቁ የተለያዩ ውብ ባህላዊ ሥዕሎች እንዲኖሩት በማድረግ የሠመራ ከተማን  የቱሪዝም መስህብነት እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን ነው የተገለጸው።

የሀዋሳ ኤርፖርት ተርሚናል በኤፍ ኢ ኮንስትራክሽን ማቴሪያል ሬንታል ፕሮዳክሽን ጄኔራል ኮንትራክተር ግንባታው የሚካሄድ ሲሆን የሠመራው ደግሞ በአፍሮ ፅዮን ኮንስትራክሽን ነው።

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት በስምምነቱ ላይ እንደተናገሩት የሀዋሳና ሠመራ ኤርፖርቶች የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ግንባታ የዝግጅት ሂደት ተጠናቋል ብለዋል።

ድርጅቱ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ለመንገደኞች ምቹ ለማድረግ ዝግጅቱን የጀመረው ባለፈው ዓመት ነው።

እንዲያም ሆኖ ከታሰበው በላይ በመጓተቱ ይህን ታሳቢ በማድረግ ከተቋራጮቹ ጋር ከሁለት ዓመት በላይ የሚወስደውን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መግባባት ላይ ተደርሷል።

የሁለቱም ኤርፖርቶች የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናሎች የወደፊቱን የአየር ትራንስፖርት ፍላጎት በማሟላት እስከ 20 ዓመት ድረስ እንዲያገለግሉ ታሳቢ ተደርጓል።

ድርጅቱ በ2007 ዓ.ም. የአምስት አዳዲስ ማለትም ሀዋሳ፣ ሠመራ፣ ሮቤ፣ ጂንካና ሽሬ እንዳሥላሴ ኤርፖርቶች ተርሚናል ዲዛይን አዘጋጅቷል።

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ ጥር 26/2009 ታላቁ የኢትዮጵያ  ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት በማጠናከር የእርስ  በእርስ የመተጋገዝ ልምድን ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን  የስልጤና ጉራጌ ዞኖች አስተዳዳሪዎች ገለጹ፡፡

የህዳሴው  ግድብ ዋንጫ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል  በሚኖረው ቆይታ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መዘረዲን ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት የህዳሴ ግድብ ዋንጫው በዞኑ በቆየበት 20 ቀናት ውስጥ 52 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል፡፡

የዞኑ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዥና በስጦታ እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ዋንጫው በዞኑ ወረዳዎች በተዘዋወረበት ወቅት የተለያዩ ስጦታዎችን በመለዋወጥ እርስ በእርስ ያለውን ግንኙነትና አንድነት እያጎለበተበት ነው፡፡

ከአንዱ ወረዳ ወደ ሌላው ወረዳ ሲዘዋወር የሀገር ሽማግሌዎች ከዋንጫው ጋር አብረው በመንቀሳቀስ ለግድቡ ግንባታ ህዝቡ የሚጠበቅበትን እንዲያወጣ በመቀስቀስና  በማስተባበር ጭምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ አቶ መዘረዲን  ገልጸዋል፡፡

የህዳሴ ዋንጫው ለግድቡ ገቢ ማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሀገራዊ አንድነታቸውንና ትስስራቸውን የበለጠ ለማጠናከር በመሆኑ የዞኑን ቆይታ ጨርሶ ወደ ጉራጌ ዞን ሲሸኝም የሀገር ሽማግሌዎች  ሰንጋ በስጦታ ማበርከታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሁለቱ ዞኖች ቀደም ሲል በአንድ ዞን ይተዳደሩ የነበሩ፣ ተመሳሳይ ባህል ፣ዕምነት ወግና ልምድ ያላቸው እንደመሆኑ ያቀረቡት ስጦታ አንድ ነን የሚል መልዕክት ያለው መሆኑን የገለጹት ደግሞ  የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ኮርንማ ናቸው፡፡

“የህዳሴ ዋንጫው ዓላማውም በሀገራችን ያለውን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ማጠናከር ከመሆኑ አንጻር ይህ አይነቱ ልምድ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያሳየና በልማት ያለውን አንድነት ያመላከተ ነው “ብለዋል፡፡

ዋንጫው በዞኑ በሚቆይበት ጊዜ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከዚህ ውስጥ  እስካሁን 82 በመቶ  ማሳካት መቻሉን ጠቁመው ከታቀደው በላይ  ማከናወን እንደሚቻልም  ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሩ የቤት እንስሳትን ጭምር በስጦታ እንዳበረከተ ያመለከቱት አቶ መሀመድ  የመንግስት ሰራተኛው ከጥር ወር ጀምሮ ከደመወዙ 60 ሚሊዮን ብር በአንድ ዓመት ለመክፈል መስማማቱንም አመልክተዋል፡፡

የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ጌታቸው እንዳሉት ዋንጫው ቀደም ሲል ከተዘዋወረባቸው ክልሎች መልካም ተሞክሮን በመውሰድ  በክልሉ በሚኖረው ቆይታ 500 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡

ዋንጫው ወደ ክልሉ ከገባበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከሁለት ዞኖች ብቻ ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አመልክተው “ በቀሪዎቹ 12 ዞኖችና አራት ልዩ ወረዳዎች ከዕቅዱ በላይ መሰብሰብ እንደሚቻል ያሳየ ነው “ብለዋል፡፡

አቶ ፋሲካ እንዳመለከቱት ባለፉት አራት ዓመታት 730 ሚሊዮን ብር ገቢ ከክልሉ ህዝብ ተሰብስቧል፤ በአምስት ዓመታት ውስጥ ለመሰብሰብ የታቀደውን አንድ ቢሊዮን ብር ዘንድሮ ማሳካት ይቻላል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 26/2009 የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያና የጡረተኞች አበል ጭማሬ ከጥር 1 ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆኑ ውሳኔ አሳለፈ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤቱ ዛሬ 22ኛ መደበኛ ስብሰባ አካሂዷል።

በስብሰባው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንን ለማቋቋም በተዘጋጀ ረቂቅ ደንብና  ኢትዮጵያ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በተስማማችባቸው የብድር ስምምቶች ላይም ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ ለመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ እንደሚደረግ ቃል በተገባው መሰረት ተጠንቶ የቀረበለትን ማስተካከያ ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል።

የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ለመንግስት ሠራተኞች ደመወዝ ማስተካከያ በተመለከተ ባቀረበው ጥናት ላይ ምክር ቤቱ ከተወያየ በኋላ ነው  ከጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን የወሰነው።

በተጨማሪም በመንግስትና በግል ሠራተኞች ጡረተኞች የአበል ጭማሪ ላይ ከተወያየ በኋላ ከጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑን መግለጫው አመልክቷል።

የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲን የአደረጃጀት፣ የአሰራርና የሰው ኃይል ችግሮችን በመፍታት ተቋሙ ተልዕኮውን በውጤታማነት ለመፈጸም እንዲችል ጥናት መደረጉን መግለጫው አመልክቷል።

በገበያ ሂሳብ ቤቶች የማልማት፣ የማከራየት፣ የመጠገንና የማስተዳደር ተልዕኮ ያለው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ መቅረቡንም አትቷል።

ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ማሻሺያዎችን በመጨመር ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣና በሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑንም መግለጫው ያሳያል።

ኢትዮጵያ በመስኖ ልማት፣ መጠጥ ውኃ፣ መንገድ ግንባታ፣ በኤሌትሪክ አገልግሎት እንዲሁም በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር ያደረገቻቸውን የብድር ስምምነቶች በተመለከተ መወያየቱ ተመልክቷል።

ምክር ቤቱ ከአገሪቷ የብድር ስምምነቶች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን ተቀብሎ ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ መወሰኑንም መግለጫው ያመለክታል።

Published in ፖለቲካ

ሶዶ ጥር 26/2009 በወላይታ ዞን ጥራትን መሰረት ያደረገ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሰፍን የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ወላጆች፣ ተማሪዎችና የትምህርት ባለሙያዎች ገለፁ፡፡

በሶዶ ከተማ የጮራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወላጅ መምህራን ህብረት ኮሚቴ አቶ ሰይፉ ሴታ  እንደተናገሩት ወላጆች በትምህርት ቤቱ የሚሰጠው ትምህርት ተመጣጣኝና ጥራቱን የጠበቀ ስለመሆኑ ክትትልና ጥቆማ እንዲሰጡ በመደረጉ በተማሪዎች ላይ ለውጥ መታየቱን ገልፀዋል፡፡

በዓመት ሶስት ጊዜ በሚካሄደው የወላጆች የምክክር መድረክ ላይም የተሻሉ መምህራንና ውጤታማ የሆኑ ሞዴል ፈጻሚዎች ማበረታቻ እንደሚያገኙ በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎች በክፍል ደረጃ በዓመታዊ፣ ወርሃዊና ሳምንታዊ ዕቅድ ዝግጅት ላይ እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በትምህርት ቤቱ የማህበረሰብ ሳይንስ መምህር ቶማስ ቶሩ ናቸው፡፡

''መምህራን የሚያደርጉት ክትትልና ድጋፍ፣ ግብረ መልስ መስጠት፣ ወላጅ የልጁን ውጤት እንዲያውቅ በማድረግና ኩረጃን የሚጸየፍ ዜጋ ለመፍጠር የተሰሩ ስራዎች በተማሪው ውጤት ላይ መሻሻሎችን እያመጡ ነው'' ብለዋል፡፡

በሶዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ የሆኑት ቤቴልሄም ግርማና ኩሪ ላካሞ በአንድ ለ አምስት አደረጃጀት የሚያደርጉት ጥናት የተሻለ ውጤት ማምጣት እንዳስቻላቸው ገልፀዋል፡፡

በወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ዋና የስራ ሂደት ባለሙያ አቶ ቦጋለ ብሩ እንደገለጹት ወላጆች፣ መምህራንና ተማሪዎች የግብ ስምምነት መፈራረማቸውንና ደረጃውን የጠበቀ ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም በግብረ መልስ የጥራት ጉዳይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሰራ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ጌታሁን ጋረደዉ በበኩላቸው ''የትምህርት ጥራት ተደራሽ ለማድረግ ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲመራው ቅንጅታዊ አሰራር መፈጠሩ ውጤት እያስመዘገበ ነው'' ብለዋል፡፡

በዞኑ በየደረጃው በሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች 583 ሺህ 767 ተማሪዎችና 9ሺ 658 መምህራን በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ሚዛን 26/2009 የአፍሪካ ህብረት የ28ኛ የመሪዎች ጉባኤ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰሩ ያስተላፉት ውሳኔ አህጉሪቱን ከጥፋት የሚታደጋት መሆኑን የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ሁለት ምሁራን ገለጹ።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በበኩላቸው ህብረቱ በ2020 አህጉሪቱን ከጦርነትና ከግጭት የጸዳች ለማድረግ የተያዘው እቅድ ይሳካል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ  የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና ስትራቴጂ ጥናት ተመራማሪ አቶ መሓሪ ዮሐንስ " ወጣቶች ሁለገብ ተሳታፊነታቸውና ተጠቃሚነታቸው ካልተረጋገጠ የአፍሪካ ቀጣይ ዕድል ጥያቄ ውስጥ  የሚያስገባ ይሆናል" ብለዋል፡፡

"አፍሪካውያን እርስ በርስ መጋጨትንና ሙስናን አስወግደው መልካም አስተዳደርና ዘላቂ ልማት በማስፈን ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል በማንገስ  ወጣቱ ትውልድ ሚናውን እንዲያበረክት የሚያደርግ ፖሊሲዎች ማውጣት አለባቸው" ብለዋል።

አፍሪካ በወጣት ልጆቿ መታነፅ እንዳለባት መሪዎቹ  አምነው ካልሰሩና ጠንካራ መሰረት ካልጣሉ አህጉሪቱ ውድቀት ሊያጋጠማት እንደሚችል ጠቁመዋል።

በአፍሪካ ያለው ትውልድ አብዛኛው ከ15 እስከ 64 ዕድሜ ክልል በመሆኑ የሙያ ስልጠና በመስጠት አቅሙን በማሳደግና በማደራጀት አምራች የሚሆንበት ደረጃ መፍጠር እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ በዩኒቨርስቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ሃላፊ አቶ አብርሃ ገብረስላሴ ናቸው።

ለዚህም " ትውልዱ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎዉ ማሳደግ ይገባል "ብለዋል።

"ወጣቱ በኢንዱስትሪ ዘርፍና በተለይ ደግሞ በትላልቅ የመንግስት ማኒፋክቸሪንግ ፕሮጀክቶች በማሳተፍ የተለያዩ ክህሎቶች ቀስሞ እንዲወጣ ጊዜና ጉልበቱን በስራ እንዲያሳለፍ ማድረግ ተገቢ ነው "ብለዋል፡፡

"የአፍሪካ አህጉር መሪዎች ወጣቶች በመንግስታዊ መዋቅር በማሳተፍ የስራ ልምድ እንዲቀስሙ በማድረግ ወደ አመራር እንዲመጡ ማስቻል ይጠብቃል ብለዋል።

በተመሳሳይ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ክፍል የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት መምህር አድማሱ አብራሮ በበኩላቸው  አህጉሪቱ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በሰላምና ጸጥታ ረገድ አንጻራዊ  መሻሻሎች ማሳየቷን ተናግረዋል፡፡

አህጉሪቱ በ2063 የበለጸገችና የለማች አፍሪካ ለማየት የነደፈችውን ራዕይ ለማሳካት በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ላይ ሰላምን ማስፈንና ማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥታ መስራት እንደሚገባት ጠቁመዋል፡፡ 

ህብረቱ በ2020 አህጉሪቱን ከጦርነትና ከግጭት የጸዳች ለማድረግ የተያዘው እቅድ ይሳካል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል፡፡

የህብሩቱ ጉባኤ በአህጉሪቱ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ወጣቶችን ለማሳተፍ መወሰኑ ለአህጉሪቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርስቲው ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የምጣኔ ሀብት መምህር የሆኑት አቶ  ጥምቀቴ ዓለሜ ናቸው፡፡

"በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ቢኖርም አብዛኛው ያልተማረና ያለስራ የሚኖር በመሆኑ የወደፊቷ  አፍሪካ ዕጣ ፈንታ ባለቤት የሆነው አምራቹ ሃይል ማዕከል ያደረገ ሥራ ሊሰራ ይገባል" ብለዋል፡፡

"ኢትዮጵያ ወጣቶችን ያሳተፈ ስራ በመስራት ቀድማ የምትጠቀስ ናት " ያሉት መምህሩ ለወጣቱ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የስራ ባለቤት ማድረግ ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል የአህጉሪቱ ተግባር መሆኑን  አመልክተዋል፡፡ 

በዩኒቨርስቲው የህግ መምህሩ አቶ ተግባሩ ተረፈ በበኩላቸው "አፍሪካ አንድነቷን የሚያረጋግጥ ፣ልማቷን የሚያፋጥን ሰላሟን የሚያሰፍን ጠንካራ አመራር ያስፈልጋታል" ብለዋል፡፡

አፍሪካ ከወትሮው በተሻለ  መነቃቃት ላይ እንደሆነችና የሌሎችን ቀልብ በመሳብ ዓለም ዓቀፍ ተደማጭነቷ እየጨመረ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡

የሞሮኮ ዳግም ወደ ህብረቱ አባልነት መመለሷና እንደ ቻይና ያሉ ያደጉ ሀገራት አፍሪካን  የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረጋቸው የአህጉሪቱን ትንሳኤ ማሳያ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን