አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 02 February 2017

ደብረ ብርሃን ጥር 25/2009 የተሃድሶ ንቅናቄ መድረኩ  የአመለካከት ችግሮችን በመፍታት ህዝቡን በተገቢው ማገልገል እንዲችሉ  ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ።

በዞኑ  ከ39ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች  የተሳተፉበት የተሃድሶ ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

ከሰራተኞቹ መካከል የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የፕላንና ፕሮግራም ባለሙያ አቶ ደረጀ ጌታነህ  መድረኩ የመንግስት ሰራተኛው ለራሱና ለአካባቢው አስፈላጊ ነው ብሎ ያመነበትን ጥያቄ በግልፅ እንዲያነሳ እድል የፈጠረለት መሆኑን ለኢዜአ  ተናግረዋል፡፡

ባለፉት 15 ዓመታት በዞኑ በሁሉም መስኮች ለውጦች እንደተመዘገቡ ሁሉ በአስተሳሰብ ችግር የህዝብ ጥያቄን መመለስ ያልቻለ አመራርና ፈፃሚ እንደነበርም  ጠቅሰዋል ።

"በየደረጃው ያለው ሰራተኛ ከተሀድሶ  ባገኘው ሙያ ተኮር ስልጠናና ግምገማ የህብረተሰቡን ጥያቄ በፍጥነት ለመመለስ  የሚያስችል ቁርጠኝነትና መነሳሳት ፈጥሯል" ብለዋል፡፡

የዞኑ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሐብት መምሪያ ባለሙያ ወይዘሮ አስቴር ታደሰ በበኩላቸው "ቀደም ሲል በእቅድ አፈፃፀም ምዘና መሰረት ይደረግ የነበረው ውጤት አሰጣጥ ስራን ሳይሆን ጓደኝነትን መሰረት ያደረገ ነበር " ብለዋል።

የመንግስት ሰራተኛውን የአገልጋይነት ስሜት ለማሳደግና ተገቢውን የአገልግሎት ምዘና ለማድረግ የጥልቅ ተሐድሶ መድረኩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

የዚሁ የመስሪያ ቤቱ ባልደረባ አቶ ግርማ ጌታቸው በበኩላቸው "መድረኩ በሰራተኛው ዘንድ እንደ ባህል የሚቆጠረውን የስራ ሰዓት መሸራረፍና በስምሪት ወቅት የነበሩትን የአፈፃፀም ችግሮች እንድናያቸው አስችሎናል " ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

በስራ ክፍላቸው  የሚነሱ ችግሮችን የራሳቸው አድርገው ወስደው በመፍታት ለህብረተሰቡ  ቀልጣፋ  አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ግንዛቤ  ከመድረኩ መጨበጣቸውን ተናግረዋል፡፡

ሰራተኞቹ እንዳሉት የተሃድሶ ንቅናቄ መድረኩ  የአመለካከት ችግሮችን በመፍታት ህዝቡን በተገቢው  ለማገልገል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

በዞኑ የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሐብት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሲሳይ ወንድምአገኘሁ እንደገለፁት በመድረኩ  ሰራተኛው እቅድን ያለመተግበር፣ የአመለካከትና የተጠያቂነት መንፈስ ማጣት ችግር እንደነበረበት ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

በመንግስት በኩልም የሚስተዋሉ  የአቅም ክፍተቶችን ለይቶ ያለመሙላት ችግሮች በቀጣይ መስተካከል እንደሚገባቸው መመልከቱን ጠቁመዋል።

በዞኑ 22 የገጠር ወረዳዎችና በአምስት የከተማ አስተዳደሮች እየተካሄደ ያለው የተሀድሶ ንቅናቄ መድረክ እስከ ጥር 30 ቀን 2009ዓ.ም እንደሚቆይም ተመልክቷል፡፡

 

 

Published in ፖለቲካ

ሀዋሳ መቱ ጥር 25/2009 የአፍሪካ ኀብረት የአህጉሪቱን ገፅታ በመገንባት የተሻለች አፍሪካ ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን ተናገሩ፡፡      

የመቱ ዩኒቨርስቲ ምሁራን  በበኩላቸው ህብረቱ  በአፍሪካ የእርስ በእርስ ጦርነትና ግጭት ለማስቆም የያዘው እቅድ የአፍሪካውያንን የወደፊት ብሩህ  ተስፋ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት 28ኛው የመሪዎች ጉባኤ በርካታ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ፣ አዲሱን የኀብረቱን መሪ በመምረጥና ከ30 ዓመታት በኋላ ሞሮኮን ከእንደገና አባል አገር በማድረግ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

ይህንን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ምሁራን እንዳሉት አህጉሪቱ ራሷን ችላ እንዲትቆም ህብረቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ሽመልስ አሻግሬ አፍሪካ በኢኮኖሚያዊ ፣ በፖለቲካዊና በማህበራዊ ጉዳዮች ከሌሎች የአለም አገራት ወደኋላ የቀረች አህጉር እንደነበረች ተናግረዋል፡፡

" መገለጫዋ የሆነው ድህነት ፣ ረሃብና የእርስ በርስ ጦርነት የቅርብ ጊዜ ታሪኳ ነው"  ያሉት አቶ ሽመልስ አሁን አህጉሪቷ በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

" አፍሪካ አሁን ለያዘችው ቅርፅ የአፍሪካ ኀብረት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል"ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ኀብረት የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ካመጣቸው ለውጦች በተጨማሪ በአፍሪካዊያን ዘንድ የራስን ችግር በራስ አቅም የመፍታት ብቃት እየፈጠረ ነው፡፡

"  በየቀጠናው እየጠፋ ብቅ የሚለውን ግጭትና ጦርነት በማርገብ በኩልም ሆነ የአፍሪካን ገፅታ በማስተካከል ረገድ ህብረቱ ትልቅ ድርሻ ነበረው" ሲሉም ምሁሩ ተናግረዋል፡፡

የተሻለች አህጉር ለመፍጠር ፈተና የሚሆኑ እንደ ሙስና ፣ ሽብርተኝነትና ስደትን በመቀነስ በኩልም ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መኖሩን ጠቁመው የዴሞክራሲውን ስርዓት መገንባትና በድህነት ላይ በትብብር መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ለአህጉሪቱ ህልውና ስጋት ይሆናሉ የተባሉ የናይጄሪያውን ቦኮሃራም ፣የሶማሌውን አልሻባብ ፣ የኡጋንዳውን ሎርድ ሬዝስታንስና የኮንጎውን ኤም 23 የሽብር ቡድን ከአህጉሪቱ ማጥፋት የቀጣይ የኅብረቱ የቤት ስራ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ 

በ28ኛው የኅብረቱ ጉባኤ ላይ የተገኙት አዲሱ የተመድ ዋና ፀሐፊ  ጉቴረዝ አፍሪካን  ለመደገፍ ቃል መግባታቸው ኀብረቱ በአለም አቀፍ ድርጅቶችና በበለፀጉ አገራት ጭምር ለዓላማው ስኬት እንዲታገዝ የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ ኀብረት በ2063 የተሻለች አፍሪካ ለመፍጠር ለሚያደርገው እንቅስቃሴ አድናቆት እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ  በዩኒቨርሲቲው የህግና መልካም አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ወይዘሪት ፌቨን አብርሃም ናቸው፡፡

" ቀጠናውን በ2020 ከጦርነት ስጋት ነፃ በማድረግ ሠላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ ለተቀመጠው ግብ ስኬት እንደ አህጉራዊ ተቋም  ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት"ብለዋል፡፡

አፍሪካውያን ከአፍሪካውያን ጋር የማቀራረብና የእርስበርስ ትስስር የማጠናከር ስራ እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው በህግና መልካም አስተዳደር ትምህርት ክፍል የአፍሪካ ኀብረት ህግና የሰብዓዊ መብት ትምህርት መምህር አቶ ዮሐናን ዮካሞ በበኩላቸው የአፍሪካ ኀብረት ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የተቋቋመ እንደመሆኑ ሰላምንና ፀጥታን በማስፈን ፣ ኢኮኖሚያዊ እድገት በማምጣትና አዲስቷን አፍሪካ የመፍጠር ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
ኀብረቱ አንደኛው አገር በሌላኛው ችግር ውስጥ ጣልቃ እየገባ እንዲደጋገፉ ስለሚፈቅድ ከሌሎች የአለም ኀብረቶች ልዩ እንደሚያደርገው አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኀብረት አባል አገራት የምታካፍላቸው ተሞክሮዎች እንዷላትም ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ ከመቱ ዩኒቨርስቱ ምሁራን መካከል  አቶ አዲሱ ቀነአ በሰጡት አስተያየት የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ግጭትና ጦርነትን በማስቆም አህጉሪቱን  ወደ ተሻለ እድገት እንዲሸጋገሩ ለወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ትልቅ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

አህጉሪቱ ያላትን እምቅ ሀብት በሚገባ እንድትጠቀም ወጣቶችን በማደራጀት በልማቱ ማሳተፍና መልካም አስተዳደር ማረጋገጥ  አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርስቲው ድህረ ምረቃ መርሀ ግብር አስተባባሪ አቶ ሱሌይማን አብደላ በበኩላቸው "ለአህጉሪቱ እድገት እንደ ትልቅ ማነቆ ሆኖ የቆየው  የእርስ በእርስ ግጭቶችና የሽብር ተግባራትን ለማስወገድ የተያዘው እቅድ  ሀገራት ወደ ተሻለ የእድገት ጎዳና ለመሸጋገር ተስፋ ሰጪ ነው"  ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአካባቢዋ የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራትን በኤሌትሪክ ሀይል አቅርቦት ለማስተሳሰርና በጋራ ለማደግ የምታደርገውን ጥረት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሊማሩባት ይገባል፡፡

 

 

 

Published in ፖለቲካ

ከኢዜአ ሞኒተሪንግ

በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደዉ በ27ኛዉ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የሩዋንዳዉ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በአፍሪካዊያን አቻዎቻቸው የአፍሪካ ህብረትን የሚያሻሽልና ህብረቱን በ2018ዓ.ም ራሷን እንድትችል የሚያግዛት እቅድ እንዲያዘጋጁ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዉ ነበር፡፡ 

ፕሬዚዳንት ካጋሜም ስራውን ለማስጀመር ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴን ያዋቀሩ ሲሆን በኮሚቴ አባልነትም አሚና ጄ ሞሓመድ የናይጄሪያ የቀድሞ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር፤ማሪያም መሃመት ኑር የቻድ የኢኮኖሚ ፕላንና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር፤የኬፕ ቬርዴዋ የቀድሞ የፋይናንስና ፕላን ሚኒስትር ክርስቲና ዱአርቴና የካሜሩን ኢኮኖሚስትና የምዕራብና መካከለኛ አፍሪካ ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ከባቢያዊ ዳይሬክተር  ቬራ ሶንግዌ ተሳትፎ አድርገዋል።

የአፍሪካ ህብረት መሰረታዊ ውድቀት መነሻዉ የአፍሪካ ህብረት መሪዎች የሚወስኑዋቸዉ ዉሳኔዎችን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ አለመቻሉና አፍሪካዊያን በአፍሪካ ህብረት ዙሪያ ያላቸዉ የተዛባ አመለካከት፤የአፍሪካ ህብረት ለአፍሪካዊያን አስፈላጊ አይደለም የሚል አስተሳሰብ ዋንኛ ችግሮች መሆናቸውን ካጋሜ በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የተበታተነ፤ በበርካታ ጉዳዮች የተተበተበና በአጋር ድርጅቶች የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ጥገኛ የሆነ ድርጅት መሆኑን ካጋሜ በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡ "ተቋማዊ ለውጡን ተግባራዊ ማድረግ በአጋጣሚ ወይንም ያልተጠበቀ ግብዣ አድርገን ልንወስደው አይገባም፡፡ የለውጥ አጀንዳውን በመሪዎች ጉባዔና በህብረቱ ኮሚሽን ደረጃ ሀላፊነትን በግልፅ በማከፋፈል ተግባራዊ እንዲሆን መደረግ አለበት" ማለታቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንን ዋቢ በማድረግ የኬቲ ድረ ገፅ  ዘገባ ያመለክታል፡፡

ፕሬዚዳንት ካጋሜ አፍሪካዊያን አቻዎቻቸው በአህጉሪቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ፤የአፍሪካ ህብረት ተቋማትም ቅድሚያ ለተሰጣቸው ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት መስራት፤የአፍሪካ ህብረትን በፖለቲካዉ ዘርፍም ሆነ ተልዕኮን ለማስፈጸም በሚያስፈልጉ ደረጃዎች ሁሉ በብቃት ማስተዳዳርና አፍሪካዊያን በራሳቸዉ  የዉስጥ አቅም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንን ፋይናንስ ማድረግ እንዳለባቸው አጥብቀው አስገንዝበዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር ኢራስተስ ምዌንቻ"አፍሪካ በተፈጥሮ ሃብቷ፤ የአፍሪካ ህብረት ጠቅላላ የስራ ማስኬጃ በጀቷን፤ 75 ከመቶው የልማት መርሃ ግብሮቿና 25 ከመቶ የሰላምና ፀጥታ ወጪዋን በራስዋ መሸፈን አለባት"በማለት ለመገናኛ ብዙሃን መግለፃቸውን ኬቲ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ከዚህ ቀደም የህብረቱ ከ60 እና ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጪ በውጭ ሃገር ለጋሾች ይሸፈን እንደነበር የጠቆመው መረጃው ይህም ሁኔታ ህብረቱን ለተለያዩ ጣልቃ ገብነቶች አጋልጦት እንደነበር አመልክቷል።

ይህንን ከግምት ያስገባው የማሻሻያ ሰነዱ ሁሉም አባል ሃገራት ከገቢ ንግድ ከሚያገኙት ዜሮ ነጥብ ሁለት በመቶውን ለህብረቱ እንዲያስገቡ የሚል ሃሳብ በማቅረብ ህብረቱ ላለበት የፋይናንስ ችግር መላን ዘይዷል። ይህም ለህብረቱ በአመት ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንዲያገኝ በማስቻል ራሱን ከውጭ ጥገኝነት ነፃ እንዲሆን ያደርገዋል።

የቀረበውን የማሻሻያ ሃሳብ ገለፃን ተከትሎ አፍሪካዊያን መሪዎች የቀረበውን የለውጥ ሀሳብ  ህብረቱን  ወደ አዲስና ትክከለኛ ጎዳና የሚወስደው፤ለህብረቱ ሀይል የሚያጎናፅፍና የተቋሙን አጀንዳ ከህዝቡ ጋር በማስተሳሰር አፈጻጻሙን የሚያሻሽል በመሆኑ በደስታ ተቀብለዉታል ብሏል፡፡

በተያያዘም ጉባኤው የአፍሪካ ህብረት አቅሙን በማሳደግ በራሱ እንዲቆም የሚያስችሉ ውሳኔዎች የተላለፉበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መግለፃቸውን ኢዜአ በዘገባው አመልክቶ በፕሬዚዳንት ካጋሜ መሪነት የተዘጋጀው የማሻሻያ ሰነድ ኋላቀር የነበረውን የህብረቱን አሰራር ለማሻሻል የሚያስችል እንደሆነና በሁሉም አገሮች ስምምነት መፅደቁ አንዱ የጉባኤው ስኬት መሆኑን መናገራቸውን አሰቀምጧል።

 

"በርግጥ ሰነድ መፅደቁ ብቻ በቂ አይደለም ወደ ተግባር መሸጋገር አለበት" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለተግባራዊነቱ እንታገላለን” ብለዋል።

 

በዘንድሮውና ለ28ኛ ጊዜ በተሰናዳው ጉባኤ ላይ መራሄ መንግስታቱ በቀረበው የማሻሻያ ሰነድ ላይ ስምምነት ላይ ከመድረሳቸው በተጨማሪ የህብረቱን ኮሚሽን ሊቀመንበር በመምረጥ እንዲሁም ሞሮኮን ከ33 አመታት በኋላ ያቀረበችውን የህብረቱ አባልነት ጥያቄን የመቀበል ውሳኔን በማሳለፍ ቆይታቸውን በስኬት በማጠናቀቅ ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል።    

 

Published in ዜና-ትንታኔ

አዲስ አበባ  ጥር 25/2009  እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ 1972 ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላት ሲሪላንካ ኤምባሲዋን ዛሬ በአዲስ አበባ ከፍታለች።

ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ሲሪላንካና ሌሎች አገራት ኤምባሲያቸውን በአዲስ አበባ መክፈታቸው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተደማጭነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው።

አዲስ አበባ ከኒው ዮርክና ጄኔቫ ቀጥሎ የዲፕሎማሲ መዲና መሆኗን የገለጹት ዶክተር ወርቅነህ ሲሪላንካ ኤምባሲዋን መክፈቷ የሁለቱን አገሮች የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ የሚረዳ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ስትመረጥ ሲሪላንካ ላደረገችው ድጋፍም ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል።

ሲሪላንካ በሻይ ልማት ዘርፍ የተሻለ ልምድ ያላት አገር በመሆኗ ኢትዮጵያ ከአገሪቷ ጋር በቅንጅት መስራት ትፈልጋለችም ብለዋል።

የሲሪላንካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማንጋላ ሳማራዊራ በበኩላቸው የአፍሪካ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ኤምባሲ መከፈቱ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሚያሳድገው ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ኤምባሲ መክፈታቸው በግብርና፣ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ በቅንጅት በመስራት የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያና ሲሪላንካ የሁለትዮሽ ግንኙነት የተጀመረው ደግሞ ከ 40 ዓመት በፊት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥር 25/2009 በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች መጠነኛ ዝናብ እንደሚጠበቅ ብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ለኢዜአ እንዳስታወቀው በአብዛኛው የአገሪቷ ክፍሎች የሚስተዋለው የአየር ፀባይ ደረቅና ፀሃያማ ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል።

በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደቡባዊ ክፍል ጥቂት ስፍራዎች ላይ የሚከሰተው መጠነኛ ዝናብ በአፈር እርጥበት፣ በመጠጥ ውኃና  በግጦሽ ሣር የነበረውን አቅርቦት ሊያሻሽለው እንደሚችል ጠቁሟል።

በተቀሩት የአገሪቷ ክፍሎች የሚኖረው ደረቅና ፀሃያማ አየር የሰብል ስብሰባ ያላጠናቀቁ አካባቢዎች አመቺ ቢሆንም በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች በመጠጥ ውኃና በግጦሽ ሣር አቅርቦት አሉታዊ ተጽእኖ ሊያስከትል እንደሚችል በትንበያው ገልጿል።

ወቅቱ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ዝናብ የሚጀምርበት ቢሆንም አነስተኛ ዝናብ የሚኖረው በታችኛው ኦሞ፣ በጊቤና ደቡባዊ ምስራቅ ባሮ አኮቦ አዋሳኝ አካባቢዎች እንዲሁም በጥቂት የታችኛው ስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች መሆኑን ነው ኤጀንሲው ያስታወቀው።

በአብዛኞቹ የተፋሰስ አካባቢዎች የሚያመዝነው የአየር ሁኔታ ደረቅና ፀሃያማ ሆኖ እንደሚቆይም የኤጀንሲው ትንበያ ያሳያል።

በሚቀጥለው አንድ ወር ደረቅ ሆነው የቆዩ አካባቢዎች የሚያገኙት ዝናብ ከመጠጥ ውኃ፣ ከግጦሽ ሣር አቅርቦት መሻሻል ባለፈ ለማሳ ዝግጅት የሚረዳ የአፈር እርጥበት እንደሚኖራቸው ኤጀንሲው ገልጿል።

በተፋሰስ አካባቢዎችም በመጠንና በሽፋን አነስተኛና ያልተስተካከለ ዝናብ እንደሚኖር ትንበያው ጠቁሟል።

ኤጀንሲው እየተጠናቀቀ ባለው ጥር ወር የነበረው ደረቃማ የአየር ፀባይ በቋሚና የፍራፍሬ ተክሎች የውኃ ፍላጎት፣ የግጦሽ ሣርና የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እጥረት እንደሚፈጠር ገልጿል።

ሌሊትና ጠዋት የነበረው ቅዝቃዜ በዕጽዋት ዕድገትና በእንስሳት ምርት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደነበረውም አብራርቷል።

ቅዝቃዜው በወሩ የመጨረሻ አስር ቀናት እየቀነሰ መምጣቱንም የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ትንበያ አስታውቋል።

 

Published in አካባቢ

ወልዲያ  ጥር 25/2009  በወልድያ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተዘጋጀው አገር አቀፍ የንግድ ትርኢትና ባዛር ዛሬ በወልድያ ከተማ ተከፍቷል።

ባዛሩን የከፈቱት የከተማው ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ደሳለኝ እንደገለጹት ከዝግጅቱ የሚገኘው ገቢ ምክር ቤቱ ለሚያስገነባው ህንጻ አገልግሎት ይውላል።

የተዘጋጀው የንግድ ትርኢትና ባዛር ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ አምራችና አቅራቢ ድርጅቶች ምርታቸውን ለማስተዋወቅ፣ ለመሸጥና የቀጣይ ገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የወልደያ ከተማና የአጎራባች ወረዳ ህዝቦችም በርካታ የምርት ወይም የንግድ እቃ ዓይነቶች በአንድ አካባቢ በማግኘት በተመጣጣኝ ዋጋ ለመግዛት የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል።

ለተከታታይ 15 ቀናት በሚቆየው የንግድ ትርኢትና ባዛር ከአዋሳ፣ አዳማ፣ አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ከትግራይና ሌሎች አካባቢዎች የመጡ 120 የሚደርሱ የንግድ ድርጅቶችና አምራቾች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

በባዛሩ የቆይታ ጊዜ ከመግቢያ ትኬት ሽያጪ፣ ከቦታ ኪራይ፣ ከልዩ ልዩ ጨረታዎችና ከመሳሰሉት ከአንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

የሚገኘው ገቢም የከተማው ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በወልድያ ከተማ ላይ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ ለሚያስገነባው ሁለገብ ህንፃ እንደሚውልም አመልክተዋል።

ከባህርዳር ከተማ የመጡት የጣና ሳሙና ፋብሪካ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ አያሌው በሰጡት አስተያየት ባለፈው ዓመት ወልድያ ላይ በነበረው ባዛር ተሳትፈው ከጠበቁት በላይ ሽያጭ ማከናወናቸውን አስታውሰው ዛሬም ጥሩ ገበያ እንደሚያገኙ በመተማመን መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ የመጡት አቶ ጥላሁን ኮሌክሽን በበኩላቸው  ወልድያ ላይ ሲሳተፉ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው ይዘውት የመጡት የአጠቃላይ ኤሌክትሮኒክስ እቃም መልካም ገበያ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የወልድያና አካባቢው ማህበረሰብም መልካምና እንግዳ አክባሪ በመሆኑ በሽያጭ ከሚያገኙት ገቢ ባሻገር በንግድ ትርኢትና ባዘሩ እርካታ እንደሚሰማቸው አስገንዝበዋል።

በወልድያ ከተማ 06 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ አበበ ካሳው በበኩላቸው “ፈሳሽ ሳሙና ለመግዛት ነው የመጣሁት፤ በባዛሩ ሁሉም የሸቀጥ አይነቶች ባንድ ቦታ የሚገኙ በመሆናቸው ለሸማቹ ማህበረሰብ ጥቅሙ ከፍ ያለ ነው” ብለዋል።

ከጥር 25 ቀን ጀምሮ ለተከታታይ 15 ቀናት ለሚካሄደውን የንግድ ትርኢትና ባዛርን ዳሽን ቢራ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራና ሌሎች ድርጅቶች ድጋፍ ማድረጋቸው ታውቋል።

የወልድያ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከ4ሺ በላይ የንግድ ማህበረሰብን በማቀፍ ለፍትሃዊና ዘመናዊ የንግድ ስርዓት መስፈን እየሰራ እንደሚገኝ በዚሁ ጊዜ ተገልጿል፡፡---

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ  ጥር 25/2009 የመንግስት የፋይናንስ ግዥና አስተዳደር ኤጀንሲን የማስፈጸም አቅም ማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ በአምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሁለተኛ ዓመት  የስራ ዘመን 15 መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበ ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር  ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፤ የተቀላጠፈና ተጠያቂነት የሰፈነበት የግዥና ንብረት አስተዳደር አሰራር ለመፍጠር የኤጀንሲውን የማስፈጸም አቅም ማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው።

ኤጀንሲው ያለበትን የአቅም ችግር ለመፍታትና ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በሰው ሃይል አቅም ግንባታ ረገድ እንደሚሰራ አብራርተዋል።

በፋይናንስ፣ በንብረት አስተዳደርና በግዥ ሂደት በኩል ወጥ የፋይናንሰ ግዥና የንብረት አስተዳደር መዋቅር መዘርጋቱንም ተናግረዋል።

ዶክተር አብርሃም እንደገለጹት፤ የመንግስት ግዥና ፋይናንስ መስሪያ ቤቶች የተጠያቂነት አሰራር እንዲፈጠር የውስጥ ኦዲተር ሰራተኞች ተጠሪነታቸውን ለሚኒስቴሩ በማድረግ የተማከለ አሰራር ተመስርቷል።

"ሰራተኞቹ ተጠሪነታቸውን ለሚኒስቴሩ መሆኑ በነጻነት እንዲሰሩ ለማድረግና አስተዳደራዊ ተጠያቂነት ለማስፈን ያግዛል" ብለዋል።

አስተዳደራዊ ተጠያቂነትን ለማስፈንም ዝርዝር መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ነው ያብራሩት።

በሌላ በኩል ከወደብ የሚገቡ ንብረቶች በወቅቱ ያለመድረሳቸው በምጣኔ ሃብታዊ ተወዳደሪነት ላይ ከሚያሳድረው አሉታዊ ጫና ባሻገር አገሪቷን ተገቢ ላልሆነ ወጭ እየዳረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም በቅድሚያ ገቢ እቃዎች የሚታወቁበት አሰራር በመፍጠርና የንግድ ሎጂስቲኩን በማጠናከር በቅንጅት መስራት ዘላቂ መፍትሄ እንደሚሆንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 25/2009 የአዲስ አበባ ምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ደንብና መመሪያዎች ተፈፃሚ መሆናቸውን የመቆጣጠር አቅሙን እንዲያጠናክር ባለድርሻ አካላት ጠየቁ። 

ባለሥልጣኑ በ 2009 ዓ.ም የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃጸም ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

በዚሁ ጊዜ ባለሥልጣኑ የሚያወጣቸውን ደንብና መመሪያዎች ተፈፃሚ መሆናቸውን በአግባቡ ቁጥጥር እያደረገ አለመሆኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ፀጋዬ ፃዲቅ እንደገለጹት ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ትምባሆ ማጨስን የሚከለክል ሕግ ቢወጣም ተፈፃሚነቱ ግን ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገበት አይደለም።

በምግብ ላይ ባዕድ ነገር በመቀላቀል ለተጠቃሚ በሚያቀርቡ እንዲሁም ጊዜ ያለፈባቸውን ምግቦች በሚሸጡ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።

የባህል ህክምናን በሕግ ማዕቀፍ ለማስደገፍ የተወሰደ እርምጃ ቢኖርም በመስኩ የሚታየውን የግንዛቤ እጥረት ለማስወገድ ባለሥልጣኑ የሚጠበቅበትን ያህል እየሰራ አለመሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ተስፋዬ ገብረዮሃንስ ናቸው።

አቶ አየለ ሰዲ የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው በልማት ተነሺ አካባቢዎች በቆሻሻ ክምችት እየተሞሉ በመሆኑ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) በሽታ እንዳይከሰት ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።

በመዲናዋ በሚፈጸመው ሕገ-ወጥ እርድ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር የላላ መሆን በኅብረተሰቡ ጤና ላይ እክል እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕገ-ወጥ እርድና የጥራት ጉድለትን ለመከላከል የሚደረገው ቁጥጥር አናሳ በመሆኑ በዚህ በኩል ባለሥልጣኑ ያወጣውን ሕግ አክብሮ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በህገ-ወጥ መንገድ ጊዜ ያለፈባቸውን መድኃኒቶች ለተጠቃሚ በሚሹጡት ላይም ጠንከር ያለ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ከግል ሕክምና ማህበር የመጡት አቶ አበበ ዓለሙ ጠቁመዋል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ወረቲ በሰጡት ምላሽ በብቃት ማረጋገጥና ቁጥጥር ዘርፍ የሚታዩ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሰቢነት ዝንባሌዎችና ተግባራት ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በባለሥልጣኑ ያለአግባብ ጥቅም ለማግኘት በሕገ-ወጥ ተግባር በተሰማሩ ሠራተኞች ላይም እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የባለሥልጣኑ ሠራተኛ መስለው ኅብረተሰቡን የሚያጨበርብሩ ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉን ነው የገለጹት።

ማንኛውም ሕገ-ወጥ ተግባር ሲፈጸም ኅብረተሰቡ በ 8864 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጥ ዋና ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።

ባለሥልጣኑ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ መስራቱን እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

Published in ማህበራዊ

ደሴ ጥር  25/2009 የአፍሪካ ህብረት በ2020 ከአህጉሪቱ ግጭት እንዲወገድ የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት አባል ሀገራት አበክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው የአዲስ አበባ ፣ የመቀሌና የወሎ ዩኒቨርስቲዎች ፕሬዝደንቶች ገለጹ፡፡

ፕሬዝደንቶቹ ለኢዜአ እንዳሉት የአባል ሀገራቱ መሪዎች ሙስናንና ድህነትን ለማጥፋት ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ እንደገለጹት አፍሪካን ከእርስ በእርስ ግጭትና ከጦርነት ነጻ ለማድረግ የተያዘው እቅድ የሚበረታታ ነው።

" የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በቅድሚያ መንግስታቱ  በጋራና በተናጠል በሙስናና ድህነት ላይ መዝመት ይጠበቅባቸዋል" ነው ያሉት ፕሮፌሰር አድማሱ።

በአህጉሪቱ ጎልተው የሚታዩ የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ፍትሃዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል ችግሮችን ለማስገድም  መንግስታቱ በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሀገራቱ ይህንን ካደረጉ የተያዘውን ዕቅድ ይሰካል የሚል እምነት እንዳላቸው ፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሠላምና ደህንነትን አንድ የልህቀት ማዕከል  አድርጐ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ለህብረቱ ዕቅድ መሳካት የሚረዱ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ የአጋዢነት ሚናውን እንደሚጫወት ቃል ገብተዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ክንዳያ ገብረህይወት እንዳሉት ''ህብረቱ ያስቀመጠውን  ግጭት አልባ አህጉር የመፍጠር ዕቅድ አፍሪካ የራስዋን ችግር በራሷ አቅም ለመፍታት የምታደርገውን ትግል ወደ ፍሬያማነት መቃረቡን የሚያመላክት ነው'' ብለዋል።

ለዕቅዱ መሳካት የሁሉም አፍሪካዊ ጥረት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ በተለይ የዘርፉ ምሁራን  ጥራት ያላቸው ጥናትና ምርምሮች በማካሄድ መሪዎቹን ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

የሀገራቱ መሪዎችም ለግጭትና አለመግባባት መንሴ የሆኑትን እንደሙስና፣ ኢ-ፍትሃዊነት፣ ድህነትና ኋላቀሪነት የመሳሰሉ ችግሮችን መቅረፍ  እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል።

''በኢንዱስትሪያላይዜሽንና በዘመናዊ ግብርና ላይም ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰው ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ በተለይ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን ጥረት አጠናክራ መቀጠል አለባት'' ብለዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው በአህጉሪቱ ግጭትን በዘላቂነት ለማስወገድ በቅድሚያ መንግስታቱ ድህነትና ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

“ከሌላው ዓለም በተለየ መልኩ አፍሪካ የወጣቶች አህጉር ነች” የሚሉት ፕሬዝዳንቱ “የፍሪካ ሀገራት አምራች ሀይሉ ይበልጥ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችሉ ፖሊስና ስትራቴጂዎችን መከተል አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል” ነው ያሉት ።

''የራበውና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ያልተረጋገጠለት ህዝብ ወደ ግጭት መግባቱ አይቀሬ ነው'' ያሉት ዶክተር አባተ የአፍሪካ መሪዎች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ከተንቀሳቀሱ የተያዘው ዕቅድ ማሳካት ይቻላል ብለዋል።

ከላይ ከተገለጹት ችግሮች ጎን ለጎን የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቋቋም መንግሰታቱ ከወዲሁ ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል

በአህጉሪቱ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ሀይሎች ሆን ብለው የእርስ በእርስ ጦሪነትና ግጭቶችን እንዲቀጥሉ  ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ መሆኑን በመገንዘብ የአፍሪካ ሀገራት አንድነታቸውን በማጠናከር ሊመክቱት እንደምገባም አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ህብረት ራዕይን በኢትዮጵያ ለማሳካት በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት ዩኒቨርሲቲዎች በሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት፣ በቴክኖሎጅና እውቀት ሽግግርና በጥናት የተደገፈ የህዝብ ተጠቃሚነት አተኩረው እንደሚሰሩ ፕሬዝዳንቶቹ አስታውቀዋል።

Published in ማህበራዊ

ባህር ዳር ጥር 25/2009  በግንባታ ላይ የሚስተዋሉ የዲዛይን፣ የግንባታ መጓተትና የጥራት መጓደል ችግሮችን ለመፍታት የተሀድሶ ግምገማው እንደሚያግዝ የአማራ ክልል የውሃ፣ መስኖና ኢነርጁ ልማት ቢሮ ሰራተኞች ገለጹ።

ሰራተኞቹ  ላለፉት አምስት ቀናት ሲያካሄዱት የቆየው የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ መድረክ ትናንት አጠናቀዋል፡፡ 

አቶ አስራት ካሴ በተሃድሶው ግምገማው ከተሳተፉት የቢሮው ሰራተኞች መካከል አንዱ ሲሆኑ በቆይታቸው በተቋሙ ውስጥ የሚስተዋሉ የስራ መሰናክሎችን በግልፅ  መለየት እንደቻሉ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

ይህም በአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ህዝቡን ሲያማርሩ የነበሩ የመልካም አስተዳደር መጓደሎችን አምነው በመቀበል ለመፍትሄው ዝግጁ አድርጓቸዋል፡፡

በተለይም የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድግ በርካታ ስራዎች ቢከናወኑም  አሁንም የግንባታ ጥራትና የግንባታ መጓተት ችግሮች በተደራሽነቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን  ጠቁመዋል።

የተሀድሶው መድረክም እነዚህን ችግሮች ነቅሶ በማውጣትና ሰራተኛው የችግሮቹ ባለቤት መሆኑን በግልፅ በማሳየት ሃላፊነቱን በአግባቡ  መወጣት እንዳለበት ማሳየት ያስቻለ መሆኑን አቶ አስራት ጠቅሰዋል፡፡

መድረኩ "ሰራተኛው በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ያለበትን ተጨባጭ ክፍተት በማሳየት በአዲስ መንፈስ ለለውጥ እንዲነሳሳ እድል የፈጠረ ነው " ያሉት ደግሞ አቶ ጥላሁን አልማው ናቸው።

የመስኖ ተቋማት ግንባታ በዲዛይን ችግርና በስራ  መጓተት መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረጋቸውም በላይ በህዝቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጥረዋል።

በችግሮቹ ዙሪያ በተደረሰው መግባባት መሰረት የህዝብ አገልጋይነትን ስሜት በመላበስ በቀጣይ ለሚከናወኑ የተቋማቱ ተግባራት ስኬታማ ሆነው እንዲጠናቀቁ የበኩላቸውን ለመወጣት ተሀድሶው ዝግጁ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አብረሃም መንገሻ በበኩላቸው" የጥልቅ ተሀድሶው ለስራ እንቅፋት የሆኑ የአመለካከት ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ለመስጠት ያግዛል "ብለዋል።

በተለይም የስነ ምግባር መጓደል፣ የአገልጋይነት መንፈስ መጥፋት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ፣ የጠባብነትና ትምክህት አመለካከቶችን ሰራተኛው ከራሱ የእለት ከእልት ተግባር ጋር አዋህዶ በጥልቀት እንዲያቸው መደረጉን ገልፀዋል።

አቶ አብረሃም እንዳሉት ከውሃና መስኖ ተቋማት የጥናት፣ የዲዛይን፣ የግንባታ ጥራት መጓደል፣ ግንባታዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ ያለመጠናቀቅና መሰል ችግሮች ባለሙያው መፍታት ያለባቸው ቁልፍ ጉዳዮች እንደሆኑ መግባባት ላይ  ተደርሷል።

ተህድሶውም ተቋሙ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ያስቀመጣቸውን ግቦች በቀጣይ በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ለማከናወን ተደማሪ ጉልበት እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

የተጀመረው በጥልቀት የመታደስ ግምገማ እንደተቋም የሚቀጥል መሆኑንም አቶ አብረሃም  አስታውቀዋል።

በአማራ ክልል " ብቁና ውጤታማ ሲቪል ሰርቫንት ለአገራዊ ህዳሴ"  በሚል መሪ ሀሳብ  እየተካሄደ ባለው የጥልቅ ተህድሶ ግምገማ  193 ሺህ የመንግስት ሰራተኞች እየተሳተፉ መሆናቸውን ቀደም ሲል ተገልጿል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን