አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Friday, 17 February 2017
Published in ቪዲዮ

አዲስ አበባ  የካቲት 10/2009   የህዝባዊ ወያነ  ሃርነት ትግራይ /ሕወሃት/ ታጋዮች የከፈሉትን መስዋዕትነት የአገሪቷን ህዳሴ ለማረጋገጥ በመረባረብ መመለስ እንደሚገባ  አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተናገሩ።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሠራተኞች 42ኛውን የህወሃት ኢህአዴግ ምስረታ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል። 

የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አራቱን ብሄራዊ ድርጅቶች ወክለው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የህወሃት የትጥቅ ትግል የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የነጻነት፣ የእኩልነት፣ የፍትህና የማንነት ማረጋገጫ እሴትና ትሩፋት የተረጋገጠበት መሆኑንም በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።

"42 ሲቆጠር ቁጥር ነው፤ ነገር ግን በደም የተገነባ ትልቅ እሴት ያረጋገጡ፤ ፍትህ ዴሞክራሲና ሠላም የህዝቦች እሴት እንዲሆኑ ያደረጉ ውድ የመስዋዕትነት ውጤት ዓመታት ናቸው" ብለዋል።

ትግሉ አምባገነኑን የደርግ ስርዓት በማስወገድ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት የተረጋገጠበት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሽፈራው ለተገኘው ድል የትግራይ ህዝብና ህወሃት ውድ ዋጋ መክፈላቸውን ተናግረዋል።  

"የቀደሙት ታጋዮች ህዳሴዋ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመፍጠር መስዋዕት ሆነዋል" ያሉት አቶ ሽፈራው ታጋዮቹ የወደቁለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ዋነኛ ጠላት ድህነት መሆኑን በመጥቀስም ድህነትን ለማስወገድ ከህወሃት የትግል ታሪክ በጽናት መታገልን መማር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 

የብአዴን ተወካይ አቶ እሸቴ አስፋው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ህዝቡ ከህወሃት የትግል ታሪክ ፅናትን፣ አንድነትንና ይቻላል ባይነትን መማር ይኖርበታል ብለዋል። 

"ብአዴንና ህወሃት በደምና በአጥንት የተገነቡ፣ አንድ ዋጋ የከፈሉ ናቸው" ያሉት ተወካዩ ብአዴን ለኢትዮጵያ ህዳሴ ስኬት ከህወሃት ጋር ተባብሮ መስራቱን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ከህወሃት ኢህአዴግ የመጡት አቶ ይርጋለም መዓሾ በበኩላቸው የቀደሙት ታጋዮች የከፈሉት መስዋዕትነት አሁን ላለው ሠላም፣ ዕድገትና ዴሞክራሲ መሰረት መጣሉን ገልጸዋል።

ተተኪው ትውልድ የታጋዮችን አደራ በመረከብ ድህነትን ለማጥፋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ማጠናከር አለበት ብለዋል።

"አሁን የትጥቅ ትግል ጊዜ አልፏል፤ ጊዜው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የአስተሳሰብ ትግል የሚደረግበት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

የኪራይ ሰብሳቢት አመለካከትን መመከት የሚያስችል የአስተሳሰብ ትግል ማድረግ እንደሚያስፈልግም አክለዋል።

በበዓሉ ላይ ለታጋይ ሰማዕታት የህሊና ጸሎትና የጧፍ ማብራት ስነ-ስርዓት የተካሄደ ሲሆን በዓሉን በአስመልክቶ ከህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የወጣ መግለጫም በንባብ ቀርቧል።

Published in ፖለቲካ

ነቀምቴ የካቲት 10/2009 በነቀምቴ ከተማ በ64 ሚሊዮን ብር ወጪ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።

የከተማው ማዘጋጃ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደምሰው በላይ ትናንት ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የሚከናወኑት የልማት ሥራዎች መንገድ፣ የመብራትና የውሃ መስመር ዝርጋታ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ እየተከናወኑ ከሚገኙ የልማት ሥራዎች መካከል 5 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ ጥርጊያ መንገድ ግንባታ፣ 7 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍና የሁለት መካከለኛ ድልድዮች ግንባታ ሥራ ይገኝበታል።

ከእዚህ በተጨማሪ 570 ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም 5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የጎርፍ መውረጃ ቦይ ግንባታ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

የሰባት ኪሎ ሜትር የመንገድ ዳር መብራት ዝርጋታ ለማከሄድ በአሁኑ ወቅት ጨረታ መውጣቱን የገለጹት አቶ ደምሰው፣ የውሃ መስመር ዝርጋታው የ3 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር አጠቃላይ ርዝመት እንዳለው ጠቁመዋል።

አቶ ደምሰው እንዳሉት፣ በከተማዋ በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በተያዘው ዕቅድ መሰረት እስካሁን በ21 ኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ወጣቶችን ማሳተፍ ተችሏል።

በእዚህም ሁለት ሺህ 700 ወጣቶች በኮብል ስቶን ጠረባና ንጣፍ ሥራ ላይ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይ በመልካም አስተዳደር እጦትና በኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ይጓተት የነበረው የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፋጠነ መምጣቱን ገልጸዋል።

Published in ማህበራዊ

ጂግጂጋ  የካቲት  10/2009  በድርቅ ለተጎዱ አርብቶ አደሮች እንስሳትን  በመግዛት ለምግብነት እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የእንስሳትና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዓሊ ዑመር ለኢዜአ እንደገለጹት ለምግብነት እንዲጠቀሙ እየተደረገ ያለው የክልሉ መንግስት በመደበው 9 ሚሊዮን ብር በጀት  እንሰሳትን ከአርብቶ አደሩ በመግዛት  ነው፡፡

ድርቁ ባለባቸው ሽላቦ ፣ ሺኮሽና  ዋርዴር ወረዳዎች በሚገኙ ስድስት ቀበሌዎች  በእያንዳንዱ  60 በግና ፍየሎች ከአርብቶ አደሩ በመግዛት ገንዘቡን ለሌሎች ፍላጎታቸው ማሟያ እንዲያውሉት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም  በ47 የውሃ መገኛ  አካባቢዎችና አነስተኛ የህዝብ ቁጥር  ባላባቸው ጣቢያዎች ላይ በየቀኑ 30 ፍየሎችና በጎች በመግዛት ታርደው ስጋውን በቋንጣ መልክ በማዘጋጀት እንዲጠቀሙ እየተሰጣቸው እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

"ድጋፉ በተመሳሳይ ለአንድ ወር የሚቆይ ነው "ያሉት ሃላፊው በቀጣይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲረከቡ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

አርብቶ አደር አሊ ፊድ በሽላቦ ወረዳ  የአሊን ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የክልሉ መንግስት በየቀኑ 60 ፊየሎችን  በማረድ ፣ ሩዝና አልሚ ምግብ በማቅረብ  ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለመንግስት ፍየሎቹን በሸጡበት ገንዘብ ስኳር እና ሌሎች የቤት ወጪዎችን በመሸፈን ተጠቃሚ እንደሆኑ አርብቶ አደሩ ገልጸዋል፡፡ 

ከአስር ዓመታት በፊት ተመሳሳይ ድርቅ  በአካባቢያቸው ማጋጠሙን የተናገሩት አርብቶ አደሩ  አሁን መንግስት የሚያቀርበው የእርዳታ እህል ችግራቸውን ቢያቃልልም በቂ  ባለመሆኑ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል::

መንግስት በየቀኑ 30 ፊየሎችን በማረድ ሩዝና ስጋ በማቅረቡ ያጋጠማቸው የድርቅ ችግር ለመቋቋም ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በቢርቆድ ወረዳ የሆሳለ ቀበሌ ነዋሪ አርብቶ አደር  አብዲራን ሂርስ አህመድ ናቸው፡፡

ሆኖም የሚርብላቸው የእንስሳት መኖና መድሃኒት ካለው እንስሳት ቁጥር ጋር የሚመጣጠም  ባለመሆኑ አቅርቦቱ እንዲሻሻልላቸውም ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ድርቁ በክልሉ በመማር ማስተማሩ ላይ የሚያስከትለውን ተፅእኖ ለመቀነስ ችግሩ በተባባሰባቸው አካባቢዎች ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ 125ሺህ 446 ህፃናት የአስቸኳይ ጊዜ የትምህርት ቤት ምዝገባ መርሃ ግብር  ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ ነው ፡፡

በክልሉ ትምህርት ቢሮ የእቅድ ዝግጅት  ሃላፊ  አቶ ፈይሰል አብዲኑር እንደገለጹት ለምዝገባ መርሃ ግብር ማስፈያም ትምህርት ሚኒስቴር 22 ሚሊየን 452 ሺህ ብር  በጀት መድቧል፡፡ ፡

ከተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ለተማሪዎቹ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ድጋፍ እየተመቻቸ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ባህርዳር  የካቲት 10/2009  የአማራ ሴቶች ማህበር 6ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ እንደሚያካሂድ አስታወቀ።

ጉባኤው ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው " ኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራርን በተደራጀ ትግል በመታገል የሴቶች የነቃ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን እናረጋግጣለን " በሚል መሪ ቃል ነው።

የማህበሩ ሊቀመንበር ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ ጉባኤውን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጹት፣ በጉባኤው የማህበሩ ያለፉት ሦስት ዓመታት የሥራ እንቅስቃሴ ይገመገማል።

በተጨማሪም በማህበሩ የቀጣይ ሦስት ዓመታት ዕቅድ ላይ ተወያይቶ የአፈጻጸም አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ እንደሚያጸድቅ ሊቀመንበሯ ተናግረዋል።

የምክር ቤት አባላትንና ሥራ አስፈጻሚዎችን ምርጫ ያካሂዳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የገለጹት።

በተጨማሪም ማህበሩ በባህር ዳር ከተማ በሊዝ የመነሻ ዋጋ ባገኘው አራት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ለሚያስገነባው ሕንጻ የመሰረት ድንጋይ እንደሚቀመጥ ጠቁመዋል።

በየደረጃው ያለው አመራርና የመንግስት ሠራተኛው በጥልቅ ተሃድሶ ክፍተቶቹን በመለየት ለማስተካከል ቃል የገባበትና ለሴቶች ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ቁርጠኛ በሆነበት ወቅት ጉባኤው መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

ማህበሩ ከየካቲት 14 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚያካሂደው 6ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከ550 በላይ ተሳታፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በጥቂት በጎ ፈቃደኛ ሴቶች የተቋቋመው የአማራ ሴቶች ማህበር ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉት።

ማህበሩ የሴቶችን ሁለንተናዊ መብትና ጥቅም ለማስከበር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ  ነዉ፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 10/2009 የክልሎች ከ20 ዓመት በታች የቼዝ ሻምፒዮና ውድድር በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ እየተካሄደ ነው።

ውድድሩ ሁሉንም ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የሚያሳትፍ ቢሆንም የተገኙት አራት ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ብቻ ናቸው።

ትግራይ፣ አማራ፣ ደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮች በውድድሩ እየተሳተፉ ነው።

ትናንት በ20 ሴትና 30 ወንድ ተወዳዳሪዎች የተጀመረው ሻምፒዮናው ነገ ፍጻሜውን የሚያገኝ ሲሆን ታዳጊ ስፖርተኞችን ማፍራትና የልምድ ልውውጥን ዓላማ ያደረገ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሁሉም ተሳታፊዎች ክፍት የሆነ የግል የቼዝ ሻምፒዮና ውድድር በመጪው ሰኞ በአካዳሚው ይካሄዳል።

ውድድሩ በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያን ወክሎ በምስራቅ አፍሪካ የቼዝ ሻምፒዮና ላይ የሚካፈለው ብሔራዊ ቡድን ተወዳዳሪዎች የሚመረጡበት ነው።

ኢትዮጵያ 'የአፍሪካ ዞን አራት ነጥብ ሁለት' በመባል የሚታወቀውን የቼዝ ውድድር በመጪው መጋቢት 2009 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ እንደምታስተናግድ የኢትዮጵያ ቼዝ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

Published in ስፖርት

ባህር ዳር የካቲት 10/2009 የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮች የህብረተሰቡን ችግር በመፍታት ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር በላይነሽ ዘባድያ በበኩላቸው እስራኤል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላትን የካበተ ልምድና እውቀት ለኢትዮጵያ ለማካፈል በትብብር በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ 60 የጥናትና ምርምር ስራዎች የሚቀርቡበት 5ኛው ዓመታዊ የሳይንስ ዘርፍ አውደ ጥናት ዛሬ ተጀምሯል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ባይሌ ዳምጤ በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚከናወኑ ጥናትና ምርምሮች ጥልቀት ያላቸውና ለወቅታዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ የሚያበጁ እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው፡፡

በተለይ በዘርፉ የሚከናወኑ ጥናትና ምርምሮች የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱና ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ እንዲሆኑ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎችም በዓመታዊ የሳይንስና ምርምር አውደ ጥናቶች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ከዘርፍ ልምድ እንዲቀስሙና ትምህርታቸውን በትኩረት እንዲከታተሉ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር በላይነሽ ዘባድያ በበኩላቸው እስራኤል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላትን የካበተ ልምድና እውቀት ለኢትዮጵያ ለማካፈል በትብብር በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

እስራኤል አሁን ለደረሰችበት የእድገት ደረጃ ዜጎቿ ችግሮችን በምርምር በመፍታት አገራቸው ተወዳዳሪና ከበለፀጉ ሃገሮች ተርታ ማሰለፍ እንደቻሉ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ወደ ላቀ ከፍታ ለማድረስ የምታደገውን ጥረት ለማገዝ ምሁራንን ወደ እስራኤል በመላክ  በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አገራቸው ያላትን የካበተ ልምድና እውቀት እንዲቀስሙ እየተደረገ  መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ደለለ ወርቁ በበኩላቸው ዓመታዊ የጥናትና ምርምር አውደ ጥናቱ ተመራማሪዎችን እርስ በእርስ በማገናኘት ልምድና እውቀት የሚለዋወጡበት ነው።

በጥናትና ምርምር ኮንፈረንሱ የሳይንስ ዘርፉን የሚመለከቱ 60 የምርምር ውጤቶች ቀርበው ምክክር ይደረግባቸዋል።

በአውደ ጥናቱ ከሚቀርቡት የምርምር ስራዎች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ በወፎች ስደት እያስከተለ ያለውን ተፅኖ፣ በከተሞች የሴቶች የስራ እጥነት ችግር፣ ከአምስተ ዓመት በታች የህፃነት ሞት ቅነሳ የሚሉት ይገኙበታል።

እንዲሁም የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃ ማመጣጠን ያለበት ሁኔታ፣ በእንሰት ሰብል ላይ እየተስተዋለ ያለው በሽታና መከላከያው የሚሉትና ሌሎች የምርምር ስራዎች ናቸው።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው አውደ ጥናት ላይ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ምሁራንና ተማሪዎች እንዲሁም በዘርፉ ተስፋ የተጣለባቸው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

Published in ማህበራዊ

መቀሌ የካቲት 10/2009  የደርግ ስርዓት ከተደመሰሰ በኋላ  በክልሉ ልማት ላይ በመሳተፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የትግራይ ጦር ጉዳተኞች ማህበር አስታወቀ፡፡

የህወሓት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ማህበሩ ለኢዜአ እንደገለጸው የአሁኑ ወጣት ከአካል ጉዳተኞቹ ፅናትና የስራ ታታሪነት መማር አለበት፡፡ 

የማህበሩ  ስራ አስኪያጅ  አቶ አብረሀለይ አስመላሽ  እንዳመለከቱት አሁን የተገኘው ሰላምና ዴሞክራሲ ታጋዮቹ  በከፈሉት መስዋዕትነት ነው፡፡

"ደርግን ለመደምሰስ በተካሄደው ጦርነት የህይወት መስዋእትነት ከከፈሉት ውጭ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 100ሺህ የሚሆኑ ታጋዮች ይገኛሉ" ብለዋል፡፡

ከእነዚህ አብዛኛዎቹ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች መሰማራታቸውን የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ መስኖ ልማትና ንግድ ከተሰማሩባቸው የስራ መስኮች መካከል እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡

ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ከአራት ሺህ በላይ ደግሞ ማህበሩና የክልሉ መንግስት በየወሩ በነፍስ ወከፍ 1ሺህ 200 ብር ድጎማ እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል፡፡

ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው አካል ጉዳተኞች ደግሞ በሚኖሩበት አካባቢ ነፃ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መንግስት አመቻችቶላቸዋል፡፡

የእርሻ መሬታቸውም  በራሳቸው አቅምና በማከራየት እንዲጠቀሙበት  መንግስት ልዩ ድጋፍ እንዳደረገላቸው  አቶ አብረሀላይ አመልክተዋል፡፡

የደርግ ስርዓት ከተደመሰሰ በኋላ የማህበሩ አባላትና ሌሎችም የአካል ጉዳተኞች ፊታቸውን ያዞሩት ድህነትን ለማጥፋት በልማት ላይ በመሰማራት መሆኑን ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡

በማህበሩ የአካል ጉዳት ክፍል አስተባባሪ አቶ ጨርቆስ ወልደሃወርያ በበኩላቸው በንግድ ስራ የተሰማሩ አካል ጉዳተኞች ከ200 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ሀብትና ንብረት ማፍራታቸውን  ተናግረዋል፡፡

"ህወሓት የተመሰረተበትን  የካቲት 11 ስናከብር  የደርግ ስርዓት ለመገርሰስ ያሳዩትን ፅናት   በፀረ ድህነት ትግል መደገም አለበት" ብለዋል፡፡

የትግራይ ጦር ጉዳተኞች ማህበር ከ24ሺህ በላይ አባላት እንዳሉትም ተመልክቷል፡፡

Published in ፖለቲካ

የካቲት 10/2009 በሃገሪቱ ከዘመናዊ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ጋር በተያያዘ ባለፉት ስድስት ወራት ዓለም አቀፍ ግዙፍና ታዋቂ ኩባንያዎች ኢንቨስት ለማድረግ መግባታቸውን  በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

ጽህፈት ቤቱ እንደገለጸው ኩባንያዎቹ  ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከእስያ ሃገራት የመጡ ናቸው ብሏል፡፡

ከኩባንያዎቹ መካከል በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ሶስት የቻይና፣ ሁለት የህንድና የሌሎች አገራት ኩባንያዎች ወደ ሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተዋል፡፡

በዚህም የአገሪቱ የኢንቨስትመንት ተመራጭነት ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የገለጸው፡፡

አገሪቱ የኩባንያዎቹን ቀልብ ለመማረክ የቻለችው ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ሆና በመገኘትዋ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ከዚህም ባሻገር በዋነኛነት በመላ አገሪቱ የሰፈነው አስተማማኝ ሰላም እና መረጋጋት  ለንብረቶቻቸው ዋስትና የተረጋገጠባት አገር መሆኗን በማወቃቸው ነው ሲል ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አብራርቷል፡፡

 

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል

የአገራችን የኢንቨስትመንት ተመራጭነት ተጠናክሮ ይቀጥላል!


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እየወጡ ያሉ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት አገራችን ኢትዮጵያ የኢንቨስተሮችን ትኩረት እየሳበች ትገኛለች። ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሚወጡት መረጃዎች በበኩላቸው እንደሚጠቁሙት በተያዘው የበጀት ዓመት ስድስት ወራት ማለትም ከሃምሌ 1/2008 እስከ ታህሳስ 30/2009ዓ.ም ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የተመዘገበው ካፒታል መጠን 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው።

ይህ አፈፃፀም በ2008 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት እና በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ከተመዘገበው አማካይ አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር በ35 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ በሃገሪቱ ከዘመናዊ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ጋር በተያያዘ ባለፉት ስድስት ወራት ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከእስያ ሃገራት ግዙፍና ታዋቂ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ገብተዋል፡፡ ለአብነትም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ሶስት የቻይና፣ ሁለት የህንድና የሌሎች አገራት ኩባንያዎች በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተዋል፡፡

አንድ የውጭ ባለሃብት ወደ አንዲት አገር ተንቀሳቅሶ በዚያች አገር መዋዕለ ንዋዩን ከማፍሰሱ በፊት በዓለም ላይ ያሉትን አገራት ሁሉ ያነጻጽራል፤ በየአገሮቹ የቀረቡለትንም አማራጮች በሙሉ ይፈትሻል፤ ያወዳድራል። በመረጣት አገር ውስጥ በእርግጥም መዋዕለ ንዋዩን ቢያፈስ ከሌሎቹ አገሮች ሁሉ በተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆን ሳያረጋግጥ ወደተግባር እንደማይገባ ሳይታለም የተፈታ ነው።

ከዚህ አንጻር አገራችን የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የእስያ ግዙፍና ታዋቂ ኩባንያዎችን ቀልብ ለመማረክ የቻለችው በእርግጥም ለኢንቨስትመንት የተሻለ ተመራጭ ሆና በማግኘትዋ ነው። ከነዚህም በዋነኝነት በመላ አገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እና መረጋጋት በመኖሩ ነው። ባለሃብቶቹ ለንብረቶቻቸውም ዋስትና የተረጋገጠባት አገር መሆኗን ጠንቅቀው በማወቃቸው ነው። በፍጥነት እያደገ ያለ መሠረተ ልማትን አገሪቱ እያቀረበች መሆኗንም በማመናቸው ነው። በአጠቃላይ ለኢንቨስትመንት የተመቻቸ ሁኔታ መኖሩን በተከታታይና በተለያየ አግባብና መመዘኛ ሳያረጋግጥ ወደእኛ የሚመጣ የውጭ ባለሃብት የለም፤ አይኖርምም።

ከየክልሎቹ የሚወጡት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የአገር ውስጥ ባለሃብቶችም በኢንቨስትመንት ተግባር ላይ በስፋት እየተሳተፉ ናቸው።
ይህ ውጤት ደግሞ ህዝብና መንግሥት ለዓመታት ያደረጉት የልፋት ውጤት ነው። በመሆኑም በተያያዝነው የተሃድሶ እንቅስቃሴ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለዘለቄታው በመፍታት የኢንዱስትሪ ልማታችን ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር ለሆኑት የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች የተሻለ የኢንቨስትመንት አማራጭ መሆናችንን እንቀጥላለን።

Published in ኢኮኖሚ

ፍቼ/ነቀምቴ የካቲት 10/2009 በገበያ ተፈላጊነት ያላቸውን ሰብል፣ ፍራፍሬና አትክልት በመስኖ በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን በሰሜን ሸዋ ዞን የደብረ ሊባኖስ እና ግራር ጃርሶ ወረዳ አርሶአደሮች ገለጹ።

በምስራቅ ወለጋ ዞን በዘንድሮ የበጋ ወራት 80 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ መሆኑም ተመልክቷል።

በመስኖ ልማት ሥራው ከተሳተፉት አርሶአደሮች አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንዳሉት በመስኖ አልምተው ከሚሸጡት ምርት በዓመት ከ7ዐ ሺህ ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል።

በደብረ ሊባኖስ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር ጌታቸው ገብሬ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት የመስኖ ልማቱ ከቤተሰብ ቀለብ ባለፈ ቋሚ የገቢ ምንጭ እየሆናቸው ይገኛል።

በሁለት ሄክታር መሬታቸው ላይ ከአትክልት በተጨማሪ ገብስና ስንዴን በመስኖ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዓመታዊ የመስኖ ልማት ገቢያቸው ከ70 ሺህ ብር በላይ መሆኑን ገልጸው፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከመስኖና ከሌላ የገቢ ምንጭ 300 ሺህ ብር የሚጠጋ ሀብት ማፍራታቸውን ተናግረዋል።

ዘንድሮ እያካሄዱት ላለው የመስኖ ልማት ሥራ ከባለሙያ ምክር ባለፈ የራሳቸውና የቤተሰባቸውን ጉልበት በመጠቀም ውጤታማ ሥራ እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በወረዳው የአማራ አፍጥን ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ሲሳይ አያሌው በበኩላቸው "ባለፈው ዓመት በመስኖ ልማት ነጭ ሽንኩርትና በርበሬ በማምረት 50 ሺህ ብር ገቢ አግኝቺያለሁ" ብለዋል።

የመስኖ ልማቱን ከጥቅምት ወር ጀምሮ በውሃ መሳቢያ ሞተር ታግዘው በማከናወን ላይ መሆናቸው የተናገሩት ደግሞ በግራር ጃርሶ ወረዳ የቶርባን አሼ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ጉርሜሳ ጉቱ ናቸው።

ባለፈው ዓመት አትክልት፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም በማምረት በአንድ ዙር 71 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

 የሰሜን ሸዋ ዞን መስኖ ልማት ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ምትኩ እንደገለጹት በዘንድሮው የመስኖ ልማት ሥራ በ13 ወረዳዎች የሚገኙ ከ141 ሺህ በላይ  አርሶአደሮች እየተሳተፉ  ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ 121 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት 84 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ገልጸዋል።

ከልማቱም 12 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመው፣ ይህም ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በአንድ ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

ለልማቱ ዘጠኝ መካከለኛ ግድቦችን ጨምሮ በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ የተጠለፉ 71 ወራጅ ወንዞች፣ የከርሰ ምድር ውሃና ጉድጓዶች ጥቅም ላይ ውለዋል።

በመስኖ ከሚለሙት መካከል ገብስ፣ ስንዴ፣ ነጭና ቀይ ሽንኩርት፣ ፍራፍሬና አትክልት የሚገኙባቸው ሲሆን ለእዚህም ከ45 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ቀደም ብሎ መሰራጨቱን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና በምስራቅ ወለጋ ዞን በዘንድሮ የበጋ ወራት 80 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ ነው።

የዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የመስኖ ውሃ አቅርቦት የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ሚልኬሳ ወርቅነህ እንዳሉት የመስኖ ልማት ሥራው እየተካሄደ ያለው ስቡስሬ፣ ዋዮቱቃ፣ ጎቡፈዮን ጨምሮ በ17 ወረዳዎች ነው።

በመስኖ ልማት ሥራው 135 ሺህ የሚሆኑ አርሶአደሮች በግልና በማህበር ተደራጅተው እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸው፣ እስካሁን 274 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ መዋሉን አስታውቀዋል።

በመጀመሪያው ዙር በባህላዊና ዘመናዊ መስኖ እየለሙ ካሉት መካከል ድንች፣ ቲማቲም፣ ካሮት፣ ሽንኩርት፣ በርበሬ፣ በቆሎና ቦሎቄ ይገኙበታል።

ከመስኖ ልማቱም ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ሚልኬሳ ተናግረዋል።

ከዞኑ አርሶአደሮች መካከል በዋዩቱቃ ወረዳ የቦነያሞሎ ቀበሌ አርሶአደር ሰንበቶ ተመስገን በሰጡት አስተያየት ዘንድሮ በአንድ ሄክታር መሬታቸው ላይ ያለሙትን ድንችና ሽንኩርት ለገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን ከ100 ኩንታል በላይ ምርት ለገበያ በማቅረብም 43 ሺህ ብር የሚጠጋ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በሲቡ ወረዳ የለሊሳ ቀበሌ አርሶአደር አዱኛ ሐምቢሳ በዘንድሮ የበጋ ወራት በአንድ ተኩል ሄክታር መሬት ላይ በቆሎና ሽንኩርት ዘርተው በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑወቅት ሊሰበሰብ ከደረሰው የሽንኩርት ምርታቸው ብቻ ሃምሳ ሺህ ብር ገቢ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን