አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 16 February 2017

መቀሌ የካቲት 9/2009 የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ከሌሎች ብሔሮች ብሔረሰቦች ጋር በመሆን የህዳሴውን ጉዞ እውን ለማድረግ ትግሉን በፅናት እንደሚቀጥሉ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ማዕከላዊ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

ህወሓት የትጥቅ ትግል የጀመረበትን 42ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ማዕከላዊ ኮሚቴው  ለኢዜአ በላከው መግለጫ የ42 ዓመታት የትግል  ጉዞ ምንጭ በየመድረኩ እየጠራና እየፋፋ መምጣቱን ገልጿል፡፡

በመግለጫ ላይ እንደተመለከተው  የውስጥና የውጭ ጠላቶች ህገ መንግስታዊ ስርዓቱና የህዳሴ ጉዞውን ለማደናቀፍ የሚያደርጉት ጥረት አይሳካላቸውም፡፡

የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት በጋራ በመሆን የህዳሴ ጉዟችን ለማሳካት ዳግም ቃል እንገባለን  ሲል ድርጅቱ በመግለጫው ላይ  አመልክቷል፡፡

ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ለ17 ዓመታት ያካሄዱት መራራ የትጥቅ ትግል የሀገሪቱ ህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲመሰርቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጿል፡፡

"በዚህም በድህነት የዓለም ተምሳሌት ተደርጋ ትታይ የነበረችው አገራችን አሁን ፈጣን ፣ፍትሃዊ  ልማትና ሰፊ መሰረት ያለው ዲሞክራሲ ለመገንባት  ርብርብ ላይ ነን " ብሏል ህወሓት በመግለጫው፡፡

ህወሓት በሰፊ ህዝባዊ መሰረት የጸና ፣  በሳይንሳዊና ስነ ሀሳባዊ የበለፀገ ፖለቲካዊ ብቃቱን ያስመሰከረ መሪ ድርጅት መሆኑ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡ 

በየጊዜው የሚያጋጥሙትን   ፈተናዎች  በብቃት በመሻገር አንፀባራቂ ድሎችን እያስመዘገበ  መጥቷል ብሏል፡፡

የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ከሌሎች ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች  ጋር በመሆን የህዳሴውን  ጉዞ  እውን ለማድረግ ትግሉን  በፅናት እንደሚቀጥሉ  ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው  አስታውቋል፡፡

ህወሓት 42ኛ ዓመቱን ሲያከብር ያለፉት የ15 ዓመታት የህዳሴ ጉዞ በጥልቀት በገመገመበት  ማግስት መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

ህወሓት  ካለፉት  ዓመታት የህዳሴ ጉዞ ልምድና ትምህርት በመውሰድ "አሁንም ድርጅታችን በጥልቀት በማደስ ለተልዕኮው ብቁ እናደርገዋለን" በሚል መሪ ሀሳብ በዓሉ እንደሚከበር ተገልጿል፡፡

በገጠርና በከተማ የሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎች እንደትላንቱ ከመሪ ድርጅቱ ጎን በመሰለፍ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር የፈጠራቸውን እድሎች በመጠቀም ኑሮውን ለማሻሻል እያደረጋቸው ባለው ጥረት ለውጥ እያስመዘገበ ነው፡፡

"አርሶ አደሩ ትላንት የማያውቀውን አሁን ሀብትና ጥሪት እያፈራ መሆኑ ማረጋገጫ ነው " ብሏል ህወሓት በመግለጫው፡፡

መስመሩ ለከተማው ነዋሪ ህዝብም የኑሮው መሻሻል  ዋስትና መሆኑንም በርካታ ማረጋገጫ እንዳሉትም ድርጅቱ አብራርቷል፡፡

ህወሓት ለትግራይ ህዝብ፣ለእህትና አጋር ድርጅቶች ፣ ለኢህአደግ አባላት፣ ለብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንኳን ለ42ኛ አመት የልደት በዓል አደረሳችሁ ብሏል፡፡

 

 

Published in ፖለቲካ

ሀዋሳ የካቲት 9/2009 የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ሶስት አዋጆችን፣ ተጨማሪ በጀትና ሹመት በማጽደቅ ዛሬ ተጠናቀቀ፡፡

ጉባኤው ዛሬ ያጸደቃቸው አዋጆች የታክስ አስተዳደር፣ የከተሞች አስተዳደርና የገቢ ግብርን የተመለከቱ ናቸው፡፡

የክልሉ ታክስ አስተዳደር ስርዓት ራሱን ችሎ የበለጠ ቀልጣፋና  ውጤታማ እንዲሆን  የታክስ አስተዳደር አዋጁ መውጣቱ ተገልጿል፡፡

አዋጁ በታክስ ህጎች አተረጓጎም ረገድ በታክስ አስተዳደሩ ውስጥ በሚፈጠር ልዩነት ምክንያት ታክስ ከፋዩ ሲያጋጥመው የነበረውን እንግልት በማስቀረት ወጥነት ያለው  እንዲሆን ያስችላል፡፡ 

የከተሞች አስተዳደር አዋጅ ደግሞ በክልሉ  መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ሁሉን አቀፍ ልማት በማረጋገጥ ከተሞች የምርት የአገልግሎትና የገበያ ማዕከላት ሆነው የክልሉን ኢንዱስትሪ ልማት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያችል ተመልክቷል፡፡

እንዲሁም የገቢ ግብር አዋጅ የግብር አከፋፈል ስርዓቱ ፍትሀዊነት ያለው እንዲሆንና ግብር የማይከፈልባቸውን ገቢዎች በግብር መረብ ውስጥ ለማስገባት እንደሚያስችል በጸደቀው አዋጅ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡

የክልሉ ኢኮኖሚ ዕድገት ከደረሰበት ደረጃ ጋር የተጣጣመና ኢኮኖሚውን የሚያግዝ ዘመናዊና ቀልጣፋ የግብር ስርዓት ለመዘርጋት በማስፈለጉ አዋጁ መውጣቱ ተጠቁሟል፡፡

የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር የስራ ቆይታቸው በማብቃቱና የስራ መልቀቂያ በማስገባታቸው በቦታቸው አቶ ተስፋዬ ታፈሰን ዋና ኦዲተር በማድረግ ምክር ቤቱ ሾሟል፡፡

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የቦርድ አባል በነበሩት ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን ምትክ አቶ ሰለሞን ኃይሉ እንዲተኩ ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡

የሀድያ ብሔረሰብን ወክለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካይ እንዲሆኑ አቶ ስንታየው ወልደሚካኤልን ምክር ቤቱ ወክሏል፡፡

ምክር ቤቱ የተሰጣቸውን የዳኝነት ስልጣን ለግል ጥቅም በማዋል በስነ ምግባር ጉድለት ምክንያት 18 ዳኞችን እንዲነሱ ሲያደርግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ለከፍተኛ ፍርድ ቤትና ለወረዳ ፍርድ ቤቶች የ116 ዳኞችን ሹመት አጽድቋል፡፡  

በተጨማሪም ለመምህራን የደሞዘ ጭማሪ በክልል ማዕከል ለሚገኙ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ፣ለተለያዩ ኮሌጆችና ሌሎችን ተግባራት የሚውል ከአንድ ቢሊዮን 682 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት በማጽደቅ ጉባኤው ተጠናቋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ደብረ ማርቆስ የካቲት 9/2009 በቅድመ ወሊድ ክትትል የኤች አይቪ ኤድስ ምርመራና የምክር አገልግሎት በማግኘታቸው ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ልጅ መውለድ እንደቻሉ በምስራቅ ጎጃም ዞን አንዳንድ የአገልግሎቱ  ተጠቃሚ እናቶች ገለጹ። 

በዞኑ ዘንድሮ ከ42ሺህ በላይ እናቶች ነጻ የኤች አይቪ ኤድስ ምርመራና የምክር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ወይዘሮ እርስቴ አለሙ  በባሶሊበን ወረዳ የየጁቤ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ "በሰፈር የጤና ልማት ቡድን ውይይት ባገኘሁት ግንዛቤ በእርግዝና ጊዜዬ የቅድመ ወሊድ ህክምና ክትትል እንዳደርግ አስችሎኛል" ሲሉ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

የህክምና ክትትል በሚያደርጉበት ወቅት  ቫይረሱ በደማቸው እንዳለ ቢነገራቸውም  ቫይረሱ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ የሚወሰደውን መዳሐኒት እየተጠቀሙ በህክምና ተቋም በመውለድ ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ልጅ መውለድ እንደቻሉ ተናግረዋል።

" ከወለድኩ በኋላም  ራሴን ጠብቄ በመኖርና በጥንቃቄ ጉድለት ቫይረሱ ወደ ልጄ እንዳይተላለፍ የእናትነት ሀላፊነቴን እየተወጣሁ  እገኛለሁ" ብለዋል፡፡

የደብረኤሊያስ ወረዳ ዜሮ አንድ ቀበሌ ነዋሪ  ወይዘሮ   በለጡ ሙሉ  በበኩላቸው ከስድስት ዓመት በፊት የመጀመሪያው ባለቤታቸው በሞት እንደተለያቸው አመልክተዋል፡፡

ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ እንደገና ትዳር መስርተው በመጸነሳቸው የእርግዝና ክትትል እንዲያደርጉ በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ግፊት ወደ ጤና ጣቢያ በሄዱበት ወቅት ነው ቫይረሱ በደማቸው መኖሩን እንዳወቁ የገለፁት፡፡

ከመጀመሪያ ባለቤታቸው የወለዷትን የሰባት ዓመት ልጃቸውን በማስመርመር ቫይረሱ በደሟ እንደተገኘባት ጠቁመው  ይህም ባለማወቅ በእርግዝና ጊዜያቸው ተገቢውን ክትትል ባለማድረጋቸው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

"ሁለተኛውን ልጄን እንዳረገዝኩ ባደረግሁት የህክምና ክትትል ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ልጅ መውለድ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ " ብለዋል፡፡

በደብረማርቆስ ከተማ የዜሮ ስድስት ነዋሪዋ ወይዘሪት ራሄል ተፈሪ እንዳሉት በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩ ቢሆንም ከቫይረሱ  ነጻ እንደሆኑ ይገምቱ ነበር፤  ባጋጣሚ  አርግዘው  የቅድመ ወሊድ ክትትልና ምርመራ ሲያደርጉ ቫይረሱ በደማቸው እንዳለ ያረጋግጣሉ፡፡ 

ከዚህ በኋላም ቢሆን  ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ባደረጉት የህክምና ክትትልና  የባለሙያ ድጋፍ ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ልጅ መውለድ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ጤና መምሪያ የእናቶችና  ወጣቶች የጤና ክትትል ባለሙያ አቶ ሰይድ ኡስማን እንዳመለከቱት  በተጠናቀቀው ግማሽ የበጀት ዓመት ከ42ሺህ በላይ እናቶችን ነጻ የኤች አይቪ ኤድስ ምርመራና የምክር አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

ከእነዚህም መካከል ከ400 በላይ የሚሆኑት ቫይረሱ በደማቸው ተገኝቶባቸው ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን መድሃኒት በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

ወደ ጤና ተቋማት በመምጣት በባለሙያ የታገዘ የወሊድ አገልግሎት በማግኘት ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ለጅ እንዲወልዱ አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት እየተደረገላቸው መሆኑንም ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመትም  ከ420 በላይ ነፍሰ ጡር እናቶች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን በተደረገላቸው ክትትልና ድጋፍ ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ልጅ መውለዳቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 9/2009 ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመሯቸውን ተግባራት አጠናክረው እንዲቀጥሉ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አሳሰበ።

ሚኒስቴሩ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮቹን የወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎች የመንፈቅ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ገምግሞ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጧል።

በግምገማው በከተሞቹና በክልሎች እየተከናወኑ የሚገኙ መልካም ጅምሮች እንዲጠናከሩና ክፍተቶች እንዲታረሙ አስገንዝቧል።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ርስቱ ይርዳው ስራ አጥ ወጣቶችን በመለየትና በማደራጀት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ምሩቃንና ከዛ በታች የትምህርት ዝግጅት ላላቸው ስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ  የተደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ወጣት ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ወጣቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ የተሰራው ስራ አመርቂ አለመሆኑን ጠቅሰው ትኩረት ሰጥቶ መስራት ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ ሚኒስትር ርስቱ ገለፃ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፖርኮች ወጣቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት ተገቢ ነው።

ከስራ ዕድል ፈጠራ ባሻገርም የስፖርት ማዘውተሪያና የወጣት ማዕከላትን የማስፋፋቱ ተግባር ሊጠናከር እንደሚገባም አውስተዋል።

ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን አስመልክቶ በተለይም ክልሎች ለወጣቶቻቸው ስልጠና በመስጠት ግንዛቤ ለማስጨበጥ አበክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አክለዋል።

ሚኒስቴሩ "ሰፊ ተሳትፎና ቀጣይ እንቅስቃሴ ለንቁ ትውልድ" በሚል መሪ ሃሳብ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎችና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር አዳማ ላይ ለአራት ቀናት ሲያካሂድ የቆየው ምክክር ተጠናቋል።

የፈዴራልና የክልል ወጣት አደረጃጀት ኃላፊዎች፣ የስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማህበራት ተወካዮች፣ የክልሎች የወጣት ስራ ዕድል ፈጠራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በምክክር መድረኩ ተሳትፈዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አክሱም የካቲት 9/2009 በትግራይ ክልል ሶስት ዞኖች የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የአክሱም ደም ባንክ አስታወቀ፡፡

የደም ባንኩ ከበጎ ፈቃደኞች የተለገሰውን ደም በትግራይ ማእከላዊ፣ ሰሜን ምእራብና ምእራባዊ ዞኖች ለሚገኙ 16 መለስተኛና አጠቃላይ ሆስፒታሎች ያሰራጫል፡፡

ቀደም ሲል ከህብረተሰቡ የግንዛቤ እጥረት የተነሳ በሦስቱ ዞኖች በበጎ ፈቃድ ደም የሚለግሱ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ እንደነበር የደም ባንኩ ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን የማነ ለኢዜአ ገልፀዋል፡፡

ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ የደም ለጋሾች ቁጥር እየጨመረ እንዲመጣ አስችሏል፡፡

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ከአንድ ሺህ 800 ዩኒት በላይ ደም ተለግሷል፡፡

የተለገሰው ደም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ800 ዩኒት ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡

ከተሰበሰበው ደም ውስጥ አንድ ሺህ 165 ዩኒቱ ለ16ቱም ሆስፒታሎች  ተከፋፍሏል፡፡

የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችን ቁጥር የበለጠ ለማሳደግም ክበባት በመቋቋም ላይ መሆናቸውን ገልፀው ከእነዚሁ ውስጥ በአክሱም ዩኒቨርሲቲና በከተማው የሚገኙ ኮሌጆች የመሠረቱት 15 የደም ክበብ ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይኸው እንቅስቃሴ በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል፡፡

ከሶስት አመት በፊት ከነበረባቸው የደም እጥረት ጋር በተያያዘ በየዓመቱ ከአራት እናቶች በላይ ህይወታቸው ያልፍ እንደነበር የገለፁት ደግሞ የአክሱም ቅድስት ማሪያም ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረሚካኤል ወልደገብርኤል ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን የተሻለ የደም አቅርቦት በመኖሩ በደም እጥረት ምክንያት ህይወቱ የሚያልፍ ታካሚ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

በሆሰፒታሉ በተደረገላቸው የህክምና እርዳታና የደም ልገሳ በመልካም  ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የገለፁት ደግሞ  ነፍሰ ጡሯ ወይዘሮ አለም ብዙአየነ ናቸው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 9/2009 ''በአገር ዓቀፍ ደረጃ የትምህርት ቤቶችን የመረጃ አያያዝ ስርዓት የሚያዘምን ሶፍት ዌር ለምቶ እያለ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እና አይ ሲ ቲ ልማት ኤጀንሲ ሌላ ዓለም አቀፍ ጨረታ አውጥተዋል'' ሲል 'ፋርካ አይ. ሲ. ቲ' ሶሉሽን የተባለ ድርጅት ቅሬታውን ገለጸ።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ የለማውን ሶፍት ዌር እንደማያውቀው ተናግሯል፡፡

የአዲስ አበባ አይ ሲ ቲ ልማት ኤጀንሲ ደግሞ የወጣው ጨረታ “ከለማው ሶፍት ዌር ጋር ግንኙነት የለውም” ብሏል።

'ፋርካ አይ. ሲ .ቲ ሶሉሽን' ከትምህርት ሚኒስቴርና ከዩኒሴፍ ጋር በ2007 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ቤቶችን የመረጃ አያያዝ ስርዓት የሚያዘምን ''የትምህርት ቤት መረጃ አስተዳደር ስርዓት'' ወይም 'ኤስ ኤም አይ ኤስ' የተባለ ሶፍት ዌር በማልማት በሙከራ ተግባር ላይ ይገኛል።

ሶፍት ዌሩ ተማሪዎች በተሰጣቸው የይለፍ ቃል መሠረት ውጤታቸውን የሚያዩበት፣ መምህራንም እንዲሁ የተማሪዎችን ውጤት የሚያስገቡበትና ወላጆችም በተሰጣቸው የይለፍ ቃል የልጆቻቸውን ሁኔታ በቀላሉ እንዲደርሳቸው ማድረግ የሚችል ነው።

ሶፍት ዌሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በትግራይ፣ በድሬደዋና በአፋር ክልሎች በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ተዘርግቶ በሙከራ ላይ ይገኛል።

በተለይም በመዲናዋ በሚገኙ 67 የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ሶፍት ዌሩ ተዘርግቶላቸው እየተጠቀሙበት መሆኑ ነው የሚነገረው።

ከነዚህ ትምህርት ቤቶች መካከል የምንሊክ፣ አዲስ ከተማና ዶክተር ሃዲስ አለማየሁ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይጠቀሳሉ።

የትምህርት ቤቶቹ ኃላፊዎች  እንደገለጹት፤ የተዘረጋው ሶፍት ዌር ከዚህ በፊት የነበረውን የተንዛዛ አሰራር ያስተካከለ፣ ጊዜና ጉልበትን መቆጠብ ያስቻለ ነው።

ይህ ሆኖ ሳለ ትምህርት ቢሮው “ከመጠሪያ ስያሜው ውጪ ሌላ ልዩነት የሌለው ሶፍት ዌር ለመግዛት ዓለም ዓቀፍ ጨረታ ማውጣቱ ትክክል አይደለም” ይላሉ 'የፋርካ አይ ሲ ቲ' ሶሉሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሔኖክ ኪሮስ።

በፌዴራል መንግስት የግዥ አፈጻጸም ተሻሽሎ በወጣው መመሪያ ስር የሌሎች አገልግሎቶች ግዥን አስመልክቶ የተጠቀሰው ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዥ ለመፈጸም ግልጽ ጨረታ ይወጣል። ይህም ቢሆን ጥያቄው የለማን ሶፍት ዌር እያለ ጨረታ ለማውጣት ለምን አስፈለገ የሚለው ነው።

አቶ ሔኖክ ሁለቱ የከተማ አስተዳደሩ ቢሮዎች የተዘረጋውን ሶፍት ዌር ጥቅም እያወቁ ''እኛንም አላግባብ ሲያመላልሱን ነበር'' ነው ያሉት።

የሙከራ ትግበራ የጀመሩ ትምህርት ቤቶች በዚህ ዓመት ብቻ የሶፍት ዌር ሥርዓቱን ተጠቅመው 40 ሺ ተማሪዎችን መመዝገባቸውንም እንዲሁ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃይለስላሴ ፍሰሃ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ በተቋሙ ስለለማው ሶፍት ዌር ምንም የሚያውቁት ነገረ እንደሌለ አመልክተዋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኃይለስላሴ በዚህ መልኩ ምላሽ ቢሰጡም ትምህርት ሚኒስቴር በታህሳስ 2008 ዓ.ም በጻፈው ደበዳቤ ሶፍት ዌሩን የማልማት ሂደት መጠናቀቁን በመግለጽ በከተማዋ በኔት ወርክ የተገናኙ ትምህርት ቤቶች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ትብብር ጠይቋል።

ከዚህ በኋላም ትምህርት ቤቶቹ ሶፍት ዌሩን በሙከራ ደረጃ እየተጠቀሙበት መቆየታቸውንና አሁን ግን በኔት ዎርክ ችግር ምክንያት መቋረጡን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬን ኤጀንሲ  በበኩሉ፤ የወጣው ዓለም ዓቀፍ ጨረታ አሁን ከለማው ሶፍት ዌር ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ገልጿል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ኃይሌ እንዳሉት፤ ለመዲናዋ ትምህርት ቤቶች የተዘረጋው ሶፍት ዌር 'ዩኒሴፍ' ለራሱ ጥቅም ብሎ ያሰራው ነው እንጂ ለትምህርት ቢሮው ፋይዳ የለውም።

በዚሁ መሠረት ኤጀንሲው “አዲስ ዓለም ዓቀፍ ጨረታ እንዲወጣ ተደርጓል ነው” ያሉት።

ትምህርት ሚኒስቴር ሁሉንም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ታሳቢ ያደረገ ሶፍት ዌር ማዘጋጀቱንና የሙከራ ጊዜው እየተጠናቀቀ መሆኑን የሚያብራሩት ደግሞ የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ጣፋ ናቸው።

አቶ ወርቅነህ እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱ ተገቢ አይደለም። ሚኒስቴሩም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው ነው።

እንዲህ አይነት ተግባር ማከናወን ያለበት “ትምህርት ሚኒስቴር ነው እንጂ ቢሮዎች አይደለም” ብለዋል - ዳይሬክተሩ።

አንድ የዘርፉ ባለሙያ በሰጡን አስተያየት እንደገለጹት፤ ሶፍት ዌሩን ለማልማት አልም ዓቀፍ ጨረታ ማወጣቱ ተገቢነት የጎደለው ነው። ዋጋውም የተጋነነ ነው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 9/2009 ሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያ አምስት ክልሎች ለሚያካሄዳቸው የተለያዩ የልማት ሥራዎች 300 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት መመደቡን አስታወቀ።

የድርጅቱ የቦርድ ሊቀ መንበር ሚስተር ክርስቲያን ኡዴ ድርጅቱ እ.አ.አ 2017 በኢትዮጵያ የሚያከናውናቸውን የልማት ሥራዎች አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

የተመደበው በጀት ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ለንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ለአካባቢ ንፅህና፣ ለሰው ኃይል ልማትና ለዘላቂ የመሬት አጠቃቀም መርሃ ግብር እንደሚውል አስታውቀዋል።

የልማት ሥራዎቹ በደቡብ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሐረሪና በትግራይ ክልሎች የሚካሔዱ ሲሆን በጀቱ በዋናነት ለልማትና ለሰብዓዊ አገልግሎቶች ይውላል ብለዋል።

ድርጅቱ ከመደበው በጀት 130 ሚሊዮን ብር የሚጠጋው ለሰባት አዳዲስና 13 በጅምር ላይ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እንደሚውልም ጠቅሰዋል።

በግንባታ ላይ የሚገኙት ትምህርት ቤቶች ሲጠናቀቁ ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎች የትምህርት እድል ያገኛሉም ብለዋል።

በተጨማሪም በተመደበው በጀት 83 የጥልቅ ጉድጓድ ውሃ ቁፋሮና 76 ምንጮችን የማጎልበት ተግባራትን ጨምሮ 159 የንጹህ መጠጥ ውሃ ማዕከላት እንደሚገነቡ ተናግረዋል።

ከአምስት ሺህ በላይ የሚሆኑ የገጠር ሴቶችን ተጠቃሚ ለሚያደርጉ የብድርና ቁጠባ ማህበራት ድጋፍ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

የተለያዩ ስልቶችን በመከተል 50 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ የተቦረቦሩ የመሬት አካላት እንዲያገግሙ፣ 15 ሚሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉና ፍራፍሬዎችና የቡና ተክሎችም እንደሚለሙ ጠቅሰዋል።

በእነዚህ የልማት ሥራዎች 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉም አክለዋል።

የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያ ባለፉት 35 ዓመታት ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረጉ ተገልጿል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

የካቲት 09/2009 ኢትዮጵያን ጨምሮ 9 ሀገራት  በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በቀላሉ የሚድኑ በሽታዎችን በመከላከል የነፍሰ ጡር እናቶች እና ህፃናት ሞትን በግማሽ ይቀንሳሉ ተብለው መለየታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ፡፡

ድርጅቱ እንደገለጸው ኢትዮጵያ፤ባንግላዴሽ፤ጋና፤ማላዊ፤ናይጄሪያ፤ታንዛኒያ፤ህንድ፤ኮትዲቯር እና ዩጋንዳ የእናቶች እና ህፃናት ሞትን በግማሽ ለመቀነስ ቁርጠኝነት አሳይተዋል፡፡

የአለም ጤና ድርጅት እና ዩኒሴፍ በጋራ ባወጡት ሪፖርት ሀገራቱ በሚቀጥሉት 5 አመታት ውስጥ ለእናቶች እና ህፃናት የሚያደርጉት እንክብካቤ ጥራት ይሻሻላል ብለዋል፡፡

ድርጅቶቹ በሀገራቱ የሚደረገውን ሊድኑ የሚችሉ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ የሚያደርጉትን ጥረት ለማሻሻል እና ጥራት እንዲኖረው ለማድረግ እንደግፋለን ብለዋል፡፡

አዲስ በሚዘረጋው የመረጃ መረብ ድጋፍ አማካኝነት በ9ኙ ሀገራት ሊድኑ የሚችሉ በሽታዎችን ሙሉ በሙሉ በማጥፋት በ2030 የነፍሰ ጡር እናቶች እና ጨቅላ ህፃናት ሞትን ለማስቀረት ታቅዷል፡፡

የጤና ባለሞያዎች አቅም፤ ተነሳሽነት፤፤ የመረጃ አያያዝ ፤አሰባሰብና አጠነቃቀር ላይ በስፋት ይሰራል፡፡

“እናቶችና ጨቅላ ህፃናት በሄዱባቸው ጤና ተቋማት ከፍተኛ ጥራት ያለው አገልግሎት ማግኘት አለባቸው “ ያሉት የአለም ጤና ድርጅት የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር አንቶኒ ኮስቴሎ ናቸው፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ 303, 000 ሺህ ሴቶች በእርግዝና እና ወሊድ ወቅት ህይወታቸው ያልፋል በመሆኑም ይህን አሃዝ ለማስቀረት መስራት አለብን ብለዋል፡፡

ዶ/ር አንቶኒ ባለፉት አስርት አመታት ወደ ጤና ጣቢያ መጥተው የሚወልዱ እናቶች ቁጥር መጨመሩንም አስታውሰዋል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

የካቲት 9/2009 ዓ.ም በሁሉም ንግድ ባንኮች 1 የአሜሪካን ዶላር በ22ብር 5906 ሳንቲም እየተገዛ በ23 ብር ከ0424 ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡የእንግሊዝ ፓውንድ ስተሪሊንግ በ28 ብር ከ0372 ሳንቲም እየተገዛ በ28 ብር ከ5979 ሳንቲም እየተሸጠ ነው፡፡
የወርቅ ዋጋን ስንመለከት ደግሞ 24 ካራት አንድ ግራም ወርቅ በ935ብር ከ5516ሳንቲም ሲሸጥ ባለ14 ካራት ደግሞ በ545ብር ከ7384ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡የሌሎችን ሃገራት የምንዛሬ ዋጋና የወርቅ ዋጋ በተከታዩ ሰንጠረዥ ይመልከቱ፡፡

No automatic alt text available.

Published in ኢኮኖሚ

የካቲት 9/2009 በአዲስ አበባ አሸዋ ሜዳና ቡራዩ የገበያ ማእከላት ዛሬ የዋለውን የእህል ዋጋ መረጃ የኦሮሚያ ግብርና ምርት ገበያ ድርጅት አድርሶናል፡፡

No automatic alt text available.

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን