አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 15 February 2017

መቀሌ፣ የካቲት 8/2009 በትግራይ ክልል 160 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ የደን ሃብት በመንግስት ጥብቅ ደን ለመከለል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ከፍተኛ የደን ልማት ባለሙያ አቶ መሓሪ ገብረመድህን ለኢዜአ እንደገለጡት ባለፉት 25 ዓመታት በክልሉ በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች መልሰው አገግመዋል፡፡

ካገገሙት አካባቢዎች መካከልም በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ስድስት የደን ቦታዎች የክልሉ መንግስት በጥብቅ ደን እንዲያስተዳድራቸው ቢሮው ለክልሉ ምክር ቤት ሃሳብ ማቅረቡን  ገልፀዋል፡፡

በአካባቢዎቹ 160 ሺህ ሄክታር የተሸፈነ ደን መኖሩ መረጋገጡንም አስታውቀዋል፡፡

በደቡባዊ ዞን በራያ ዓዘቦ ወረዳ ፅጋዓ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሃይለ በርሀ በሰጠው አስተያየት ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተራቁቶ የነበረው አካባቢያቸው መልሶ አገግሟል፡፡

አካባቢው መልሶ በማገገሙም መኖ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በእንስሳት እርባታና ማድለብ ስራ ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸውም ገልፀዋል፡፡

‘’ ለተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ በማድረጋችን በሁሉም የግብርና ስራዎቻችንም ለውጥ እያየን ነው’’ ብሏል ወጣት ሃይለ።

በደቡባዊ ዞን የራያ ዓዘቦ ወረዳ የተፈጥሮ ሃብት ልማት አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ፀጋይ በበኩላቸው፣ በወረዳው የአፈርና ውሃ ጥበቃ የተሰራላቸውና እንዲያገግሙ የተደረጉ አካባቢዎች  ወጣቶች  ተደራጅተው በተለያየ የገቢ ማስገኛ የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ እየተደረገ ነው፡፡

እስካሁንም ከ2 ሺህ 500 በላይ ወጣቶች በንብ ማነብና በእንስሳት እርባታ እንዲሰማሩ መደረጉን አስተባባሪው ተናግረዋል።

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ የካቲት 8/2009 በአዲስ አበባ በመገንባት ላይ ያሉ ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃዎች ሲጠናቀቁ መዲናዋ ፅዱና አረንጓዴ እንደምትሆን ከንቲባ ድሪባ ኩማ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን እየተከናወኑ ከሚገኙ ዘመናዊ የፍሳሽ መሰረተ ልማት ሥራዎች የተመረጡ ፕሮጀክቶች ዛሬ ተጎብኝተዋል።

የመካኒሳ ቆጣሪና የቃሊቲ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች፣ የኮዬ ፈጬ ያልተማከለ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ እና የኮዬ ፈጬ የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች ግንባታ ነው የተጎበኘው።

በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ግንባታዎች ሲጠናቀቁ መዲናዋን ፅዱ እና አረንጓዴ ያደርጓታል ብለዋል።

የከተማ ዘመናዊነት የሚረጋገጠው በዘመናዊ የፍሳሽ አገልግሎት በመሆኑ ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት እየተካሄዱ ይገኛሉ ነው ያሉት።

ፕሮጀክቶቹ በከተማዋ 70 በመቶ የሚሆነውን ነዋሪ ሙሉ በሙሉ በቀጥታ ከዘመናዊ የፍሳሽ መስመር ጋር በማገናኘት በመኪና የሚሰጠውን አገልግሎት ያስቀራል ብለዋል ከንቲባው።

"ከተማዋን ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ጋር ከማስተሳሰር ባሻገር አገሪቱ ከሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ግንባር ቀደም እንድትሆንም የሚያግዛት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለማርያም እንዳሉት "ከዚህ ቀደም የነበረው የፍሳሽ ማንሳት አገልግሎት ከከተማዋ ዕድገትና አቅም አንፃር አይመጥንም ነበር"።

በግንባታ ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ግን ከተማዋ የተሻለ የመስመር ፍሳሽ የማንሳት አቅም እንደሚኖር ገልፀዋል።

ፕሮጀክቶቹ በትልልቅ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የህብረተሰቡን የፍሳሽ ማንሳት ጥያቄ በማስተናገድና ተጣርቶ የሚወጣው ውሃ ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውል ይደረጋል።

በቀጣይም በከተማዋ ሀይቆች እንዲፈጠሩ በማድረግ ለከተማዋ መናፈሻና ውበት እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።

"ፕሮጀክቱ በቴክኖሎጂ ደረጃው በአገሪቱና በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች በመስመርም ሆነ በተሽከርካሪ የሚሰበሰበው ፍሳሽ በጥቅሉ 18 ሺህ ሜትር ኪዩብ በሰባት ማጣሪያ ጣቢያዎች እየተጣራና እየተወገደ ይገኛል።

ግንባታው 54 በመቶ የደረሰው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያና የፍሳሽ መስመር በቀን 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ የማጣራት አቅም ሲኖረው ፕሮጀክቱም በ2010 ዓም ይጠናቀቃል። ለፕሮጀክቱ የተመደበው አጠቃላይ በጀትም 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ነው።

በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የሚከናወነው ያልተማከለ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ግንባታም በቀን 27 ሺህ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም ይኖረዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ማስፈፀሚያ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በመንግሥት የተመደበ ሲሆን ግንባታው በ2009 ዓም መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የተመደበለት የኮዬ ፈጬ ያልተማከለ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ፕሮጀክት ደግሞ በቀን 33 ሺህ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም ያለው ሲሆን በመገንባት ላይ የሚገኙ ከ50 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የዘመናዊ የፍሳሽ መስመር ተጠቃሚ ያደርጋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 8/2009 በአገር አቀፉ የህብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽን ባዛርና ሲምፖዚየም ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ለአንድ ወር የሚቆይ የገበያ ትስስር መፍጠር እንደተቻለ የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤግዚብሽን ባዛርና ሲምፖዚየሙ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ የገበያ ትስስር የተፈጠረበት መሆኑ ተገልጿል።

ከየካቲት 2 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ “የህብረት ሥራ ማህበራት ግብይት ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው አራተኛው አገር አቀፍ ኤግዚቢሽን ባዛርና ሲምፖዚየም  ዛሬ ተጠናቋል።

የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ሱሩር እንደተናገሩት፤ ኤግዚቢሽን ባዛርና ሲምፖዚየሙ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ተፈጥሮበታል። ምርጥ ተመክሮዎች የታዩበት፣ አምራቾቹና ሸማቾቹ የገበያ ትስስር የፈጠሩበት ነው።

በባዛርና ሲምፖዚየሙ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገበያ ትስስር መፈጠሩም ተብራርቷል።

በዚህም ከ80 በላይ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከአቻ ማኅበራት፤ ከሸማቾችና ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር ለአንድ ወር የሚቆይ የገበያ ትስስር ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።

ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ምርቶች ለግብይቱ መቅረቡም ተመልክቷል።

በአዲስ አበባ ከተማና በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች በባዛርና ሲምፖዚዬሙ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ያመለከቱት ኃላፊው፤ “ገጠሩንና የከተማውን ህብረተሰብም አስተሳስሯል” ብለዋል።

በኢግዚቢሽን ባዛርና ሲምፖዚየም በተከናወነው የንግድ ልውውጥ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ መገበያየት መቻሉን ተጠቁሟል።

ባዛሩ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱ  የአገሪቷን ኅብረት ሥራ ማህበራት እድገት በተጨባጭ ያሳየ መሆኑን ጠቁመው፤ ማህበራት ለአገር ልማትና ለፍትሃዊ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ያላቸውን የጎላ ሚና ያረጋገጠ እንደሆነም ተናግረዋል።

ከገበያ ትስስሩ ባሻገር በርካታ ብሄሮችና ብሄረሰቦች በአንድ ቦታ የተሰባሰቡበትና ሕብረ ብሔራዊነት የተንጸባረቀበት እንደሆነም እንዲሁ።

በመዝጊያ ስነ ስርዓቱ ላይ የእንስሳትና አሳ ሃብት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች የታደሙ ሲሆን፤ ለባዛርና ሲምፖዚየሙ ስኬት አስተዋጽኦ የነበራቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች የምስጋና ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ  የካቲት  8/2009  በትግራይ ክልል የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን /ማርች ስምንት/ በቦንድ ሽያጭና በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ የሆኑ ሴቶችን በመሸለም እንደሚከበር ተገለፀ፡፡

የክልሉ ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር የትምወርቅ ገብረመስቀልና የትግራይ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ዘነበች ፍስሃ የበዓሉን አከባበር አስመልክተው ትናንት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በተሰጠው መግለጫ መሠረትም በዓሉን ምክንያት በማድረግ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የቦንድ ሽያጭ ይከናወናል፡፡

ከዚሁ የቦንድ ሽያጭም 50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልፀዋል፡፡

የቦንድ ሽያጩ በክልሉ ያለውን የቁጠባ ባህል ለማሳደግና ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በሚደረገው ድጋፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚያስችል የክልሉ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ዘነበች ፍስሃ አስረድተዋል።

ወንዶችም ለሚስቶቻቸው፣ ለእናቶቻቸው፣ ለእህቶቻቸውና ለሴት ልጆቻቸው ቦንድ በመግዛት ክብራቸውንና ፍቅራቸው እንዲገልፁ ጠይቀዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ባለፉት ሁለት ዓመታት የቁጠባ አቅማቸውን ላሳደጉና ተበድረው በተለያዩ የልማት ስራዎች በመሳተፍ ውጤታማ ለሆኑ 54 የልማት ቡድኖች እውቅናና ሽልማት እንደሚሰጥ  የክልሉ ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር የትምወርቅ ተናግረዋል።

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የመንግስትን ስራ ሳይጠብቁ ስራ በመፍጠር ስኬታማ የሆኑ ስምንት ወጣት ሴቶችና በከተሞች በሚካሄድ የፅዳትና ውበት ስራ የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳዩ ሴቶችም እንደሚሸለሙ ገልፀዋል፡፡

በመቀሌ ከተማ በሚካሄደው የሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የተከናወኑ ስራዎችና ያጋጠሙ ችግሮችን የሚዳስስ የውይይት መድረክ ይካሄዳል፡፡

በክልሉ 12 ከተሞችም በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሩጫ ውድድር እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡

ዘንድሮ ለ41ኛ ጊዜ የማርች ስምንት በዓል የሚከበረው  ‘’ የሴቶችን የቁጠባ ባህል ማዳበር የህብረሰተሰብና የህዳሴአችን መሰረት ነው’’  በሚል መሪ ቃል ነው።

Published in ማህበራዊ

ሽሬ እንዳስላሴ የካቲት 8/2009 በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴን ተጠቅመው ማሳቸውን በመስኖ ያለሙ አርሶአደሮች ገቢያቸው እያደገ መሆኑን ገለጹ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱና ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ፀለምት ወረዳ ትናንት የመስክ ጉብኝት አካሂዷዋል።

ማሳቸው የተጎበኘላቸው አርሶ-አደሮች ኩታገጠም የመስኖ ልማት ዘዴን ተጠቅመው ያለሙትን አንድ ጥማድ ማሳ ቀይ ሽንኩርት ከ15 እስከ 23 ሺህ ብር ድረስ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ ጸለምት ወረዳ መድኃኒዓለም ቀበሌ የሚኖረው ወጣት አምባሳደር ተስፋይ እንዳለው፣ በመጀመርያው ዙር በመስኖ ካለማው አንድ ጥማድ የቀይ ሽንኩርት ማሳ 23 ሺህ ብር ማግኘቱን ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ለሁለተኛ ጊዜ ባካሄደው የመስኖ ልማት ማሳውን በቲማቲም መሸፈኑን ጠቁሞ፣ ከምርቱ ከ25 ሺህ ብር በላይ ገቢ አገኛለሁ የሚል ተስፋ እንዳለው አመልክቷል።

ሌላው የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፀጋይ ብርሃነ፣ በመጀመርያው ዙር በቀይ ሽንኩርት ከሸፈኑት አንድ ጥማድ ማሳ ሃያ ኩንታል ምርት መሰብሰባቸውን ነው የተናገሩት።

"ከድካሜ አንጻር ያገኘሁት ምርት በቂ ባይሆንም ከምርቱ ሽያጭ 15 ሺህ ብር ገቢ አግኝቺያለሁ" ብለዋል።

ወደፊት በማህበር በመደራጀት ከምርታቻቸው የተሻለ ዋጋ ለማግኘት አቅደው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አርሶ-አደር ጸጋይ ጠቁመዋል።

ብርክት ብርሃነ የተባለች ሌላዋ ወጣት አርሶአደር በበኩሏ፣ የተከራየችውን አንድ ጥማድ ማሳ በመስኖ በማልማት 20 ሺህ ብር ማግኘቷን ገልጻለች።

በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ፀለምት ወረዳ የመስኖ ግድብ ተጠቅመው በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ ማሳቸውን ያለሙ አርሶአደሮችን ተዘዋውረው የጎበኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ፣ አርሶአደሮች ከልማቱ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ወጣቱን ማዕከል ያደረገ የመስኖ ልማት እንዲጎለብት የክልሉ መንግስት ተጨማሪ የውሃ አማራጮችን ለመገንባት የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ  ያደርጋል።

በልማቱ ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

አርሶአደሮች መሬታቸውን በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ ማልማት እንዳለባቸው አሳስበው ይህም በግብርና ባለሙያ ድጋፍ ለማድረግም ሆነ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

"በክልሉ ቀይ ሽንኩርት በሄክታር እስከ 350 ኩንታል እየተገኘ ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ልማቱ በሁሉም የመስኖ ተጠቃሚ ወረዳዎች መስፋፋት እንዳለበት አመልክተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ጎንደር የካቱት 8/2009 በሰሜን ጎንደር ዞን በእንክብካቤ ጉድለት ጥቅም ያልሰጡ ነባር ተፋሰሶችን በመለየት መልሶ የማልማት ስራ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

አርሶ አደሮች በበኩላቸው ተፋሰሶቹን በተጠናከረ መንገድ አልምተውና ጠብቀው በዘላቂነት ለመጠቀም እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ግዛት ጀመረ ለኢዜአ እንደገለፁት ባለፉት ዓመታት በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከለሙ 1 ሺህ 54 ተፋሰሶች መካከል 994ቱ በእንክብካቤና በጥበቃ ጉድለት ጥቅም ላይ አለመዋላቸው በግምገማ ተረጋግጧል፡፡

ተፋሰሶች ህብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ ተጠብቀውና ዘላቂነት ባለው መንገድ ለምተው ጥቅም እንዲሰጡ በማድረግ በኩል ሰፊ ክፍተት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮ የበጋ ወራት የፈራረሱ እርከኖችና ክትሮች ተመልሰው እንዲሰሩና ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ተጠብቀው በአጭር ጊዜ እንዲያገግሙ ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ርብርብ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ተፋሰሶቹ ለገጠር ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥሩበት፣ በስነ ህይወታዊ ዘዴ የሚጠናከሩበት፣ ለእንስሳት ሀብት ልማት፣ ለአትክልትና ፍራፍሬና ለደን ልማት ግልጋሎት የሚሰጡበት ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የልቅ ግጦሽ መስፋፋት ተፋሰሶች ዘላቂነት ያለው ጥቅም እንዳይሰጡ እንቅፋት መፍጠሩን የተናገሩት አቶ ግዛት ችግሩን ለመቅረፍ አርሶአደሩ የቤት እንስሳቱን አስሮ የመቀለብ ባህል እንዲያጎለብት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በተፋሰሶች ላይ የሚፈጸሙ ጥፋቶችን ለመከላከል በየወረዳው ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተፋሰስ ኮሚቴ እንዲዋቀርና ህገ-ደንብ በማውጣት አጥፊዎችን ለመቅጣትና ለማረም የሚያስችል ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል፡፡ 

ዘንድሮ በህዝብ ንቅናቄ በሚከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ በአንድ ሺህ 54 ነባርና በ60 አዲስ ተፋሰሶች ላይ 10ሺ ሄክታር የሚሸፍን የእርከንና ክትር ስራ ይከናወናል፡፡

የአዲአርቃይ ወረዳ የአባው ማር ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ሙላው ታፈረ  እንዳሉት ''የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራው ጠቅሞናል፤ ምርታችን እንዲጨምርና ለከብቶቻችን የመኖ ሳር እንድናገኝ ረድቶናል'' ብለዋል፡፡

በጃናሞራ ወረዳ የአረጋይ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ትዛዙ ወረታው በበኩላቸው ''የተፈጥሮ ሀብት ልማት በሰራንባቸው ቦታዎች ለሰውም ሆነ ለእንስሳት የሚውል የመጠጥ ውሃ በበጋው ጭምር ማግኘት ጀምረናል'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በጥር አጋማሽ በተጀመረው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ ከ700 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በልማት ቡድን ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን እስከ የካቲት ወር ማብቂያ ድረስ ይቀጥላል፡፡

Published in አካባቢ

ሶዶ የካቲት 8/2009 በትራፊክ አደጋ የሚከሰተውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያስፈልግ የሶዶ ከተማ ተጎጂዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡

በሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል በህክምና ላይ ያሉት አቶ ቢልልኝ ተፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት ሃዋሳ ከተማ ዲያስፖራ ሠፈር ምሽት ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ እግራቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

በወቅቱ ከፊት ለፊት የሚመጣው አሽከርካሪ ረጅም መብራት በመጠቀሙ ምክንያት የተሳፈሩበት መኪና መንገድ ስቶ በመውጣት ባስከተለው አደጋ  ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡

''አሽከርካሪዎች መቼ፣ የትና ምን ዓይነት መብራት መጠቀም እንዳለባቸው ያለማወቅና የጥንቃቄና የኃላፊነት ጉድለት ለአደጋ ዳርጎኛል''  ብለዋል፡፡

ችግሩ እያስከተለ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመቀነስ ከግንዛቤ ትምህርት ጀምሮ በጥፋተኞች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ ማጠናከርና በመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመለየት የቅንጅት ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ከአሰላ ወደ ሳጉሬ የተሳፈረበት የዶልፍን መኪና በመገልበጡ የእግር ስብራት ጉዳት እንደደረሰበት የተናገረው ደግሞ ወጣት ሃሰን አቤ ነው፡፡

መኪናው ከአቅም በላይ እንደጫነና ከፍተኛ ፍጥነት እንደነበረው አስታውሶ ህግን ያለማክበርና የኃላፊነት ጉድለት ለአደጋ እንደዳረገው ገልጿል፡፡

ለህክምና ከ30 ሺህ ብር በላይ መጠየቁን የገለጸው ወጣቱ ሶስት ጓደኞቹ በአደጋው ህይወታቸውን እንዳጡ ተናግሯል፡፡

በመሆኑም የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው በባለቤትነትና በኃላፊነት ስሜት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

ውድ ከሆነው የሰው ልጅ ሕይወት በተጨማሪ እየወደመ ያለው የሃገርና የህዝብ ሃብት ከፍተኛ በመሆኑ ችግሩን ለመከላከል መንግስትና ህዝብ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የሶዶ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አዳነች አያኖ ናቸው፡፡

የወላይታ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል የውስጥ ዴዌ እስፔሻሊስትና የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ለዓለም ዘነበ በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ወራት ከ911 በላይ የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች በሆስፒታሉ ጊዚያዊ ህክምና ተደርጐላቸዋል፡፡

ከ400 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው አልጋ ይዘው ህክምና እየተደረገላቸው ነው፡፡

በአብዛኛው የአደጋው ሰለባ የሚሆኑት ከ15 እስከ 40 የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ችግሩን ለመከላከል ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የትራፊክ አደጋን መቀነስ እንዲቻል ተቋማዊና ቅንጅታዊ አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የወላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር ለማ ላበና ናቸው፡፡

በትምህርት ቤቶች፣ በሃይማኖት ተቋማትና ህዝብ በብዛት በሚገኝባቸው አካባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በጥምረት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት 39 የትራፊክ አደጋ የተከሰተ ሲሆን የአደጋው መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ27 ቀንሷል፡፡ ያስከተለው የጉዳት መጠንና አስከፊነት ግን ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ማይጨው የካቲት 8/2009 በትግራይ ደቡባዊ ዞን ለእርሻ ስራ የሚያጋጥመውን የዝናብ እጥረት ለመቋቋም የውሃ አማራጮችን  በስፋት ለመጠቀም እየተሰራ ነው፡፡

ህወሓት የትጥቅ ትግል የጀመረበትን 42ኛው ዓመት በዓልና የሜጄር ጀነራል ሐየሎም አርአያ 21ኛው ዓመት የመታሰቢያ ቀን በመኸኒ ከተማ ትናንት ተከበሯል።

በበዓሉ ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ተወልደብርሃን ተስፋ አለም እንዳሉት፣ለእርሻ  ስራ  የሚያጋጥመውን የዝናብ እጥረት ለመቋቋም በአካባቢው የሚገኘው እምቅ የከርሰ ውሃ በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ተጀምሯዋል።

" የተጀመረው ስራ የክልሉ መንግስት በከፍተኛ ሰብል አምራችነታቸው የሚታወቁትን የራያ አዘቦና ራያአለማጣ ወረዳዎችን የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ማዕከል ለማድረግ የያዘውን ዕቅድ የሚያሳካ ነው" ብለዋል።

በተለይ በዞኑ ለመስኖ ልማት ታስበው ባለፉት ዓመታት ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተገንብተው ያለ ጥቅም ተቀምጠው የነበሩትን ከአንድ መቶ በላይ ጥልቅ ውሃ ጉድጓዶችን ስራ እንዲጀምሩ እየተደረገ ነው።

የውሃ ጉድጓዶቹ ማልማት ሲጀምሩ በአከባቢው የሚኖሩ ከ16 ሺህ በላይ አባወራና እማወራ አርሶ-አደሮች ከሰብል ምርት ባለፈ የአትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ድርቅን ለመቋቋም እንደሚያስችል አቶ ተወልደብርሃን ተናግረዋል።

የመስኖ ልማቱ በአከባቢው የአግሮ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ከማስቻል ሌላ የአካባቢው አርሶአደሮች ለሰውና ለእንስሳት የሚውል ትርፍ ምርት ያስገኛል፡፡

የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በአካባቢው  ዘመናዊ  የመስኖ ልማት ስራ መሳተፍ  እንዲችሉም ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በበበዓሉ ላይ ከተሳተፉት የመኸኒ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ፋንታየ ገላዬ እንዳሉት፣የካቲት 11 የጭቁኖች መብት የተረጋገጠበት ዕለት በመሆኑ ዕለቱን በልዩ ስሜት እያከበርን ነው "ብለዋል።

ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ለምለም ሓጎስ በበኩላቸው "በቀድሞ ስርዓት ልጆቻችን ለማስተማር ቀርቶ በሰላም ወጥተው እስኪገቡ የምንጨነቅበት የመከራ ጊዜ  አልፎ ለአሁኑ ሰላም ያበቃን ዕለት በመሆኑ ለበዓሉ ልዩ ክብር አለን "ብለዋል።

በዓሉ በመኸኒ ከተማ   የተከበረው " በጥልቅ በመታደስ የመልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የጀመርነው ጥረት ከዳር ለማድረስ የገባነው ቃል በማደስ  ይሆናል " በሚል መሪ ሃሳብ ልማትን በሚያጠናክር ህዝባዊ ውይይት ነው፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 8/2009 የአድዋ ድል ታሪክ የተፈፀመባቸውን የአድዋ ተራሮች የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንደሚሰራ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የአድዋ ድል 121ኛ ዓመት በዓል አከባበርን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት ባደረጉት ጥረት በርካታ የአፍሪካ አገራትን ቅኝ መግዛት ቢችሉም ኢትዮጵያ ሳትደፈር ቆይታለች።

ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ጽኑ ፍላጎት የነበራቸው ጣልያኖች በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት በ1888 ዓ.ም አድዋ ላይ በተደረገውና በኢትጵያውያን ድል አድራጊነት በተጠናቀቀው ጦርነት ህልማቸው እውን ሳይሆን ቀርቷል።

የአድዋ ድል በዓለም ጥቁሮች ነጮችን በጦርነት ማሸነፍ የቻሉበትና የአፍሪካውያን የነፃነት ምልክት ሆኖ ሲዘከር ቆይቷል፤ እየተዘከረም ነው።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም የአድዋ ድል በዓል ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱን አስታውሰው ድሉ የጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ምልክት በመሆኑ ሊዘከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

እስካሁን በነበረው አከባበር የአበባ ጉንጉን ከማስቀመጥና በዕለቱ ስለአድዋ ድል ንግግር ከማድረግ ባለፈ የተሰራ ስራ አለመኖሩን ገልጸው አሁን የአድዋ ተራሮችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

"የአድዋ ድል ድህነትን ለማሸነፍ በምናደርገው ትግል የይቻላል መንፈስ የሚያላብስ ብሄራዊ ክብራችን ነው" ያሉት ሚኒስትሯ "ጀግኖች አርበኞች በአንድ ላይ ተፋልመው ድል ባደረጉበት አካባቢ ሙዚየም ለመገንባትም እንቅስቃሴ ተጀምሯል" ብለዋል።

የሙዚየሙ መገንባት የድሉን ታላቅነት ለመጭው ትውልድ ከማስተላለፉም በላይ ቱሪስቶች ስለ አድዋ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋል ነው ያሉት።

የአድዋ የፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚመራ አብይ ኮሚቴ መቋቋሙንም አክለዋል።

የዘንድሮው 121ኛ ዓመት የአድዋ ድል በዓል ከየካቲት 14 ቀን ጀምሮ የሚከበር ሲሆን ለዜጎች ትክክለኛ መረጃ የሚያስጨብጡ ፕሮግራሞች ይቀርባሉ ብለዋል።

የአገሪቱን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠልና በዓሉ በትውልድ ቅብብሎሽ እንዲቀጥል ሁሉም አካላት አገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

የእግር ጉዞ ወደ አድዋ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የፓናል ውይይት፣ ሲምፖዚዬም፣ የስዕልና ፎቶ ኤግዚቢሽን፣ አዲስ ህብረ ዝማሬ እና የሙዚቃ ኮንሰርት የፕሮግራሙ አካሎች ናቸው።

የዘንድሮው በዓል "የአድዋ ድል ብዝሃነትን ላከበረችው ኢትዮጵያ ድህነትን ለማሸነፍ የሚያስችል ህያው አብነት ነው" በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።

በዓሉ በአድዋ፣ በአዲስ አበባና በክልሎች በተለያዩ ፕሮግራሞች እንደሚከበር በመግለጫው ተብራርቷል።

Published in ማህበራዊ

አዳማ የካቲት 8/2009 የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለአዳማ ከነማ የእግር ኳስ ክለብ ማጠናከሪያ የሚውል የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ከከተማው አስተዳደር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን የተፈራረሙት የዩኒቨርስቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ ከአዳማ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ ጋር ባለፈው እሁድ ነው፡፡

የዩኒቨርስቲው ፕሬዘዳንት በስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት ክለቡ በኢትዮጰያ ፕሪሚየር ሊግ ያሳየውን የመሪነት ሚና አጠናክሮ እንዲቀጥል ዩኒቨርስቲው ዘለቂ ድጋፍ ያደርጋል።

ክለቡን በቁሳቁስና በአቅም ለማጠናከር የገንዘብ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ያመለከቱት ፕሬዘዳንቱ ዩኒቨርሲቲው "በየዓመቱ 2 ሚሊዮን ብር ለክለቡ ይሰጣል "ብለዋል።

ድጋፉ ለአምስት  ዓመታት የሚቆይ ሲሆን በስምምነቱ መሰረት አጠቃላይ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ነው፡፡

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ በበኩላቸው የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለክለቡ ድጋፉን የሚያደርገው በማህበረሰብ አገልግሎት እያከናወነ ካለው ተግባራት በተጨማሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው ያደረገው ድጋፍ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመሪነት ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከነማ ጥንካሬውን ይዞ እንዲቀጥል የሚያግዘው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

አስተዳደሩ ክለቡን ለማጠናከር በሚያደርገው የገንዘብ ፣የቁሳቁስና ሌሎችንም እገዛዎች የከተማዋንም ሆነ የክልሉን መልካም ገጽታ በመገንባት ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ከንቲባዋ ጠቁመዋል፡፡

 

Published in ስፖርት
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን