አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 14 February 2017

ሃዋሳ የካቲት 7/2009 በደቡብ ክልል በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄውን ተከትሎ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ከአንድ ሺህ 900 በላይ አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አስታወቁ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ደሴ ዳልኬ ዛሬ በተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት በየደረጃው በተካሄደው በጥልቀት የመታደስ መድረክ 496 ሺህ 311 አመራሮችና ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የገጠርና የከተማ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

''የግምገማ መድረኩ በሀገሪቱና በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮች ምንጮችንና አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመለየት ያስቻለ ነው'' ብለዋል፡፡

ግምገማው በህዝቡ የተደራጀ ተሳትፎ የተለዩ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታትና የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ጠቁመዋል፡፡

በሂደቱም ከከፍተኛ ጀምሮ በየደረጃው ያለውን አመራር የማጥራትና መልሶ የማደራጀት ስራ በህዝቡ ተሳትፎ መከናወኑን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

በየመድረኮቹ ከህዝብ የተገኙ አስተያየቶችን መሰረት በማድረግ አንድ ሺህ 920 ከፍተኛ፣ መካከለኛና ጀማሪ አመራሮች እንዲነሱ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም 2 ሺህ 359 ምሁራንና ወጣቶችን በአዲስ መልክ በተዋቀረው አደረጃጀት ውስጥ በከፍተኛና መካከለኛ አመራርነት ማምጣት እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡

''ከፖለቲካዊ እርምጃ በተጨማሪ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በተከናወነው ተግባር በገጠር 3 ሺህ 799 ሄክታር ፤  በከተማ ከ450 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ተመላሽ ተደርጓል'' ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ያለ አግባብ የተመዘበረ ገንዘብ እንዲመለስ የተደረገ ሲሆን የ351 ሰዎች ህገወጥ ቅጥር ተሰርዟል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ 215 አመራሮች ህጋዊ እርምጃና 832 አመራሮች አስተዳደራዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል፡፡

 

Published in ፖለቲካ

አዳማ የካቲት 7/2009 አበረታች መድሃኒት የመውሰድ ተግባራትን ለማስወገድና ግንዛቤ ለመፍጠር ክልሎች ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ተነገረ።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፤ ከክልልና ከከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎችና ባለ ድርሻ አካላት ጋር አዳማ ላይ እየመከረና የመንፈቅ ዓመቱን ዕቅድ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።

የአበረታች መድሃኒት ችግርን ለማስወገድ ክልሎች ለስፖርተኞችና ለህክምና ባለሙያዎች ግንዛቤ መፍጠር እንደሚኖርባቸው በምክክሩ ተነስቷል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው ችግሩ ሳይስፋፋ ለማስቆም ስፖርተኞችን በጉዳዩ ዙሪያ ማሰልጠንና ማስገንዘብ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሎች ስፖርት ቢሮዎች ኃላፊዎች በበኩላቸው ስለ አበረታች መድሃኒት ግንዛቤ ለመፍጠር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የጋምቤላ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዮናስ ተኩምሳ በክልሉ በዞንና በወረዳዎች ጭምር ለሚገኙ ክለቦችና ስፖርተኞች ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ለሚገኙ 50 ያህል የስፖርት ክለቦች በጉዳዩ ዙሪያ ስልጠና መሰጠቱንም ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ቶርባ ቦርሳሞ በበኩላቸው ችግሩ እንዳይስፋፋ በክልሉ ለሚገኙ የስፖርት ማህበራት፣ ክለቦች፣ ቡድኖችና የጤና ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ነው የገለጹት።

ስልጠናው 20 የጤና ባለሙያዎችና በዳኝነትና በአሰልጣኝነት የተሰማሩ 160 የስፖርት ባለሙያዎችን ማካተቱንም አስረድተዋል።

"አበረታች መድሃኒቶችን የመውሰድ ተግባርን ለመከላከል ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞች፣ የቡድን መሪዎችና የስፖርት ባለሙያዎች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል" ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ፍስሃ ገብረሚካኤል ናቸው።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ጠንካራና ተፎካካሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እውቀታቸውን በማዳበርና የአበረታች መድሃኒትን ጉዳት በማሳየት ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረጉን ተናግረዋል።

ክልሉ በዚህ ዙሪያ ከ250 በላይ ለሚሆኑ የስፖርት ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱንም አስታውቀዋል።

ሚኒስቴሩ ክልሎች እያከናወኑት ያለውን ስለ አበረታች መድሃኒት ግንዛቤ የመፍጠር ተግባር አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስቧል።

ምክክሩ ለሶስት ቀናት የሚቀጥል ይሆናል።

Published in ማህበራዊ

መቀሌ የካቲት 7/2009 በትግራይ ክልል ስርጭቱ እየጨመረ ያለውን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ።

የቫይረሱን ስርጭት መግታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሚመክር ውይይት ትናንት በመቀሌ ከተማ ተካሂዷዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጎይቶም ጊጋር በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ59 ሺህ በላይ ሰዎች ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር እንደሚኖሩ በጥናት ተረጋግጧዋል።

ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የስርጭት መጠኑ የዜሮ ነጥብ ሦስት በመቶ ብልጫ እንዳለው አቶ ጎይቶም ተናግረዋል።

"በክልሉ በበሽታው እየተጠቁ ከሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል የነገ ተስፋ የሆኑ ወጣቶች ቀዳሚ ናቸው" ብለዋል።

ለዚህም በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል 49 በመቶ የሚሆኑት ከ15 እስከ 24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደምክትል ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፣ በኤች አይ ቪ/ ኤድስ ምክንያት ወላጅ አልባ የሆኑ ከ300 በላይ ሕጻናት በክልሉ ይገኛሉ።

የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸው፣ በሽታውን ለመግታት ከወዲሁ ካልተሰራ የዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አሳስበዋል።

በክልሉ ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ጠዓመ ዘገየ በበኩላቸው፣ የበሽታው ሥርጭት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ እየተባባሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዘንድሮው ግማሽ የበጀት ዓመት ብቻ በጤና ተቋማት ጽንስ ከስወረዱ ሴቶች መካከል ሰባት ሺህ የሚጠጉት የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህም  ልቅ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት እየተስፋፋ ስለመሆኑ የሚያሳይ መሆኑን አክለው ገልጸል

በመቀሌ ኪሃ ክፍለ ከተማ የሚኖሩት መጋቢ ሃዲስ ቀለመወርቅ፣ "ለበሽታው መባባስ እኛ የሃይማኖት አባቶች ተጠያቂዎች ነን፤ በያንዳንዱ ዜጋ አዕምሮ ላይ ተገቢውን ግንዛቤ አላስጨበጥንም" በለዋል።

"ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት የዕምነት ተከታዮቻቸውን በማስተማር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል።

የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሀጎስ ገብረእግዚብሔር በበኩላቸው፣ ወላጆች ልጆቻቸውን የትና ከማን ጋር እንደሚውሉ የመቆጣጠርና የመምከር ኃላፊነታቸውን በመወጣት የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

"ሁሉም ነገር በመንግስት ይፈታል ከሚል አስተሳሰብ በመውጣት ወላጆችም ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የኤች አይ ቪ/ኤድስ በሽታ ስርጭት መጠን አንድ ነጥብ ሰባት በመቶ መድረሱን የክልሉን ጤና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 7/2009 በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው የሚገኙ ሰነዶችን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ለባለ ጉዳዮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን የመንግስት ልማት ድርጅቶች ባለ አደራ ቦርድ ገለጸ።

ቦርዱ በ2009 ዓ.ም ግማሽ አመት ዕቅድ አፈፃፀሙ ዙሪያ ባካሄደው ውይይት ከግለሰቦችና ወደ ግል ይዞታ ከተዛወሩ ድርጅቶች ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም ተነግሯል።

የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ዛፉ ሰነዶችን ለተገልጋዮች በአንድ ማዕከል ማሰባሰብ በቀጣይም በትኩረት የምንከውነው ተግባር ነው ብለዋል።

የደብረ ብርሃን ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካና የባሮ አኮቦ ሰራተኞችና የፋይናንስ ሰነዶችን ወደ ማዕከል በማምጣት ፋይል ማደራጀት መጀመሩንም ተናግረዋል።

"መስቀል ፍላወር አካባቢ በ40 ሺህ ብር በተከራየነው መጋዘን መደርደሪያዎችን በማስገባት የተገልጋዮችን ፍላጎች ለማርካት እንሰራለን" ነው ያሉት አቶ ዘውዱ።

በተመሳሳይ ቦርዱ ባለፉት ስድስት ወራት ከ57 ግለሰቦችና ወደ ግል ይዞታ ከተዛወሩ 67 ድርጅቶች 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በህግ በመፍረስ ላይ ከሚገኙት ጥቁር ዓባይ ኮንስትራክሽን አክሲዮን ማህበርና ብሄራዊ መሀንዲሶችና ስራ ተቋራጮች ድርጅት የተለያዩ ንብረቶችን በጨረታ በመሸጥ የመንግስት ገቢ እንዳይባክን አድርገናል ብለዋል። 

"ተቋሙ ገቢ ለመሰብሰብ ብቻ ሳይሆን የመንግስትን ዕዳ ለመክፈል ጭምር የተቋቋመ ነው" ያሉት አቶ ዘውዱ ባለፈው ስድስት ወር ለ143 ግለሰቦችና 16 ድርጅቶች ከ6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ መክፈሉን ገልጸዋል።

ቦርዱ ከ1998 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ የ263 ድርጅቶችን ሂሳብ ማስላቱንም ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 7/2009 የቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ-ቱሉ ዲምቱ እና የቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ-ቡልቡላ-ቂሊንጦ አደባባይ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተጀመሩ።

ፕሮጀክቶቹ ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እንደሚከናወኑ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ገልጿል።

መንገዶቹ 20 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመትና ከ40 እስከ 60 ሜትር ስፋት እንደሚኖራቸው የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ተናግረዋል።

የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በሶስት ዓመት የሚጠናቀቅ ሲሆን ወጪው በከተማ አስተዳደሩና ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድር ይሸፈናል።

የመንገድ ፕሮጀክቶቹን የሚያከውነው የቻይና ኮንስትራክሽን ኮሙኒኬሽን ካምፓኒ (ሲሲሲሲ) ነው።

ለአገሪቷ ወጪና ገቢ ንግድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ያለው የቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ-ቱሉ ዲምቱ አደባባይ ፕሮጀክት 2 ነጥብ 45 ቢሊዮን ብር የሚጠይቅ ነው።

መንገዱ 11 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዲሁም 50 ሜትር ስፋት እንዳለው ገልፀዋል ኢንጂነር ሀብታሙ።

የቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ-ቡልቡላ-ቂሊንጦ አደባባይ መንገድ ግንባታም 2 ነጥብ 33 ቢሊዮን ብር የሚፈጅ ሲሆን ከ40 እስከ 60 ሜትር ስፋት እንደሚኖረው ገልጸዋል።

መንገዱ ለቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በቃሊቲ ቡልቡላና ቂሊንጦ ዙሪያ በሚገኙ ቦታዎች ላይ ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለተሸጋገሩ አንቀሳቃሾችና ለአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት ይሰጣል።

የመዲናዋ ከንቲባ ድሪባ ኩማ የፕሮጀክቶቹን መጀመር አስመልክተው ባደረጉት ንግግር መንገዶቹ ከኅብረተሰቡ ሲነሱ የቆዩ ጥያቄዎችን ይመልሳሉ፤ ለከተማዋ መዘመንና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብለዋል።

የአካባቢውን የልማት እንቅስቃሴ ከማፋጠን ባሻገር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ከመሃል ከተማ ጋር የማስተሳሰር ሚናም አላቸው ነው ያሉት ከንቲባው።

የኅብረተሰቡን ፍላጎት ያማከሉ የመሰረተ ልማት ስራዎችና እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ከንቲባ ድሪባ ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ የካቲት 7/2009 ህወሓት የተመሠረተበትን 42ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ ባለፈው ክረምት ለተከሉት ችግኝ እንክብካቤ በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የእንደርታ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ በትግራይ ክልል ለሶስት  ቀናት የሚቆይ የልማት ስራ ከትናንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ መሆኑን የክልሉ እርሻና ገጠር ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡

በእንደርታ ወረዳ የመንበረ ቅዱሳን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አብርሃ በሪሁ  ለኢዜአ እንደገለፁት ልጆቻቸው በከፈሉት መስዋእትነት በተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት የልማት ተቋዳሽ ለመሆን በቅተዋል፡፡

የህወሓት የምስረታ በዓልን በልማት ስራ ማክበራቸው የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠልና በትግሉ የተሰው ልጆቻቸውን ለመዘከር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ብሎ የተተከለውን ችግኝ በመኮትኮትና ውሀ በማጠጣት ፣ የፈራረሱ እርከኖችንም  በመጠገን በዓሉን እያከበሩ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ በወረዳው የዳንዴራ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ዕፃይ አባዲ  ናቸው፡፡

በእንደርታ ወረዳ የለምለም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገብረ ካሕሳይ በበኩላቸው ''ወንድሞቼ መስዋእትነት የከፈሉበትን ህዝባዊ ዓላማ ከግብ ለማድረስ በዓሉን በተለያዩ የልማት ስራዎች በመሳተፍ እያከበርኩት ነው'' ብለዋል፡፡

ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ዘመቻ  በ2 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ  የተተከለ ችግኝ እንክብካቤና የፈራረሰ እርከን ጥገና በመካሄድ ላይ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የእንደርታ ወረዳው እርሻና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋይ ገብረተክለ ናቸው፡፡

በዘመቻውም  ከ39 ሺህ በላይ ህዝብ በመሳተፍ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የህወሓትን የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ የወረዳው አርሶ አደሮች በጀመሩት የሶስት ቀናት ነፃ የስራ ዘመቻ ላይ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ደረጃ የእርሻና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኪሮስ ቢተው  ተገኝተዋል፡፡

አቶ ኪሮስ በዚሁ ጊዜ  ''የተከልናቸውን ችግኞች በመንከባከብና ለም አካበቢ በመፍጠር የሰማዕታት አደራን ማክበርና መጠበቅ አለብን'' ብለዋል፡፡

 

Published in ፖለቲካ

ጂግጂጋ የካቲት 7/2009 የኢትዮጵያ መከላከከያ ሰራዊት ግዳጁን በብቃት በመወጣት በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም በዘላቂነት እንዲሰፍን አስችሏል ሲሉ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ፡፡

አምስተኛው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀን በጅግጅጋ በድምቀት ተከበሯል።

ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ግዳጁን በብቃት በመወጣት በሃገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ አስችሏል በለዋል።

በሚሰጡት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ እየተሳተፈ ግዳጁን በላቀ ጀግንነት በመፈጸም አለም አቀፍ እውቅና አግኝቷል ነው ያሉት፡፡

በተለይም የኢትዮጵያ መከላከከያ ሰራዊት በሶማሊያ ተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት በመወጣት አሸባሪው አልሸባብ ኢትዮጵያን ጨምሮ ቀጠናውን የማተራመስ ህልሙ እንዳይሳካ በማድረግ የሀገራችን ሰላም እንዲቀጥል አስችሏል ብለዋል፡፡

አምስተኛ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀን ዛሬ በጅግጅጋ ሲከበር ለ13ኛ ክፍለ ጦር አራተኛ ሬጅመንት አባላትና አመራሮች የአልሸባብ የሽብር ቡድን በመደምስስ አኩሪ የጀግንነት ገደል በመፈጸማቸው የሁለት ደረጃ የጀግንነት ሽልማት ከፕሬዝደንቱ እጅ ተቀብለዋል፡፡

የሬጅመንት አባላቱ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን አልሸባብ በመደምሰስ በፈፀሙት የጀግንነት ተግባር የኢትዮጵያ ህዝብንና መንግስትን መኩራታቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር በበኩላቸው መከላከያ ሰራዊቱ በከፈለው መስዋዕትነት በክልሉ የተረጋጋ ሰላምን በመምጣቱ በርካታ የልማት ውጤቶች እየተመዝገቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም  ጄኔራል ሰሞራ የኑስ " በህዝባዊ መሰረት ላይ የተገነበው የመከላከያ ሰራዊታችን የሀገራችንን ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በመጠበቅ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በላቀ ጀግንነት ግዳጁን እየተወጣ ነው" ብለዋል፡፡ 

ለ13ኛ ክፍለ ጦር አራተኛ ሬጅመንት የተሰጣቸው የአውዳ ውጊያ ጀግና ሜዳይ ሽልማት "የጅግንነት ውሎ የሰራዊታችን የግዳጅ አፈፃፀም ብቃት ያረጋገጠ ነው'' ብለዋል

"የሬጅምንቱ አባላት አመራሮች ለሽልማት ያበቃቸው አልሸባብ  በሰራዊታችን ላይ ሰኔ 2 ቀን 2008 ዓ.ም የጥፋት ተልዕኮውን ለመፈፀም የሰነዘረው የማጥቃት ሙከራ በማክሽፍ የሰራዊቱ መለያ የሆነውን ፅናትና ጅግንነት በመፈፀማቸው ነው " ያሉት ደግሞ የደቡብ ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ልተናል ጀኔራል አብረሃም ወልደማርያም  ናቸው፡፡

ሬጅመንቱ ያስመዘገበው ድል አሸባሪ ቡድኑ ላይ ከፍተኛ የተዋጊ ኃይልና የመሳሪያ ኪሳራ በማድረስ  ''ሃሊጌን" የተባለችውን ከተማ እና ቁልፍ ወታደራዊ ቦታ በመቆጣጠር የአካባቢውን ሰላም ማስፈን አስችሏል፡፡

"የሬጅመንቱ የግዳጅ ውሎ ለየት ያለ በመሆኑ ለሌሎች የሰራዊቱ አባላት በተሞክሮነት ሊማሩብት የሚገባ ነው "ብለዋል

አልሸባብ የሽብር ቡድን ከቀጠናው ለማጥፋት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ሌተናል ጀኔራሉ በአሁኑ ወቅት አልሸባብ የኢትዮጵያ የሰላም ስጋት የማይሆንበት  ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

የሬጅመንቱ ዋና አዛዥ  ሻለቃ ተወልደ ብርሃን ሃጎስ " ውስጣዊ መተሳሰብና አንድነታችን በማጠናከር  በየጊዜው  የውጊያ ክህሎታችን የሚያሳድጉ የአቅም ግንባታ ስራዎችን በማግኘታችን ለድል አብቅቶናል "ብለዋል::

በዚህም በተሰጣቸው ተልዕኮ መሰረት የሀገሪቱን የሰላም ስጋት የሆነው አልሸባብ በመደምሰስ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስጠበቅ የድርሻቸውን መወጣታቸውንም ተናግረዋል፡፡

በባዓሉ ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ልዩ ልዩ ክፍሎችና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ የሰልፍ እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ተዋጊ አውሮፕላኖች ደግሞ የአየር ላይ ትርኢት አቅርበዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ የያዛቸውን እሴቶች በማጠናከር ከህብረተሰቡ ጋር ያለውን ትስስር ማጎልበትን ዓላማ አድርጎ የሆነው በየአመቱ የካቲት 7 ቀን የሚከበረው የኢፌዴሪ የሰራዊት ቀን፥ በዛሬው ዕለትም ''ህዝባዊ መሰረት ላይ የተገነባው ጀግንነታችን እየታደሰ ይኖራል'' በሚል መሪ ሀሳብ አምስተኛው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀን በጅግጅጋ በድምቀት ተከብሯል::

Published in ፖለቲካ

ባህር ዳር የካቲት 7/2009 ኪራይ ሰብሳቢነትን በተደራጀ አግባብ ለመከላከል አመራሩ የሙስና ተጋላጭነትን በተቋም ደረጃ ለይቶ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

በአማራ ክልል ተቋማዊ የሙስና መከላከል ስትራቴጂ አተገባበር ላይ ያተኮረ ስልጠና ለከፍተኛ አመራሮች ተሰጥቷል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ በስልጠናው ላይ እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል የልማትም ሆነ የመልካም አስተዳደር እንቅፋት የሆነውን ሙስና ለመከላከል ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

በተለይም በመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች፣ በግዥና ጨረታ፣ በከተማ መሬት፣ በገቢ ግብር አሰባሰብና ታክስ የሚስተዋሉ የሙስና ችግሮችን ለመከላከል ሰፊ ጥረት ሲደረግ መቆቱን ነው የገለጹት።

በእዚህም በርካታ የመንግስትና የህዝብ ሀብት በሙስና እንዳይመዘበር የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ይሁንና ከችግሩ ውስብስብነትና አስቸጋሪ ባህሪ ጋር በተያያዘ የሚፈለገውን ያህል ውጤት አለመምጣቱን ገልፀዋል።

ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያለው አመራርም ሆነ ባለሙያ ሙስናና ብልሹ አሰራርን መከላከል የጸረ ሙስና ተቋማት ብቻ አድርገው ማሰባቸው እንደሆነ አብራርተዋል።

ችግሩን ለመፍታት ቀደም ሲል ሲሰራበት ከነበረው አሰራር በተጨማሪ በተቋማት ደረጃ ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል አዲስ አሰራር መተግበር መጀመሩን አቶ ወዶ አስታውቀዋል።

"የተቋም አመራሮች በተቋማት ደረጃ የሙስና አጋላጭ ባህሪያትን በመለየት፣ ዕቅድ በማውጣት፣ አተገባበሩን በመከታታል፣ አጥፊዎች ሲገኙም ፈጥኖ በማረም ያለባቸውን ኃላፊነት በቁርጠኝነት ሊወጡ ይገባል" ብለዋል።

አዲሱ አሰራር በ250 የፌደራል ተቋማት መተግበሩንና በሁሉም ክልሎች ለመተግበር ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዝግአለ ገበየሁ በበኩላቸው የተቀናጀ አሰራር ሙስናን ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ተግባሩ ከመፈፀሙ በፊት የሙስና አጋላጭ ሁኔታዎችን በተቋማት ደረጃ በአግባቡ በመለየት የመከላከሉ ሥራ አዋጭና ተመራጭ መሆኑን ነው የገለጹት።

በተቋማት ደረጃ ለሚተገበረው የሙስና መከላከል ስልትም የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመው፣ ህዝቡም የሚፈጸሙ ሙስናዎችን  ጥቆማ በመስጠት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል።

"ሙስና ሊያደርስ የሚችለውን አገራዊ አደጋ ቀድሞ ያለመተንበይና ጉዳዩን አቅሎና ልማዳዊ አድርጎ የመመልከት ችግር በአመራሩ ላይ ይስተዋላል" ያሉት ደግሞ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ የኔነህ ስመኝ ናቸው።

ሙስናን በተቋማት ደረጃ የመከላከል አሰራር መተግበሩ አመራሩ በተጠያቂነት መንፈስና ከሙስና ጋር ተቆራርጦ እንዲሰራ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል።

ከሙስና የጸዳች አገርና ትውልድ ለመፍጠር የስነ ምግባር ትምህርት ከሙዋለ ሕጻናት ጀምሮ ተገቢው ትኩረት ማግኘት እንዳለበት የገለፁት ደግሞ የፀረ ሙስናና ግልጽነት ቴክኒካል አማካሪ ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ ናቸው።

በባህር ዳር ከተማ ለሁለት ቀን በተሰጠው ሙስናን በተቋማት የመከላከል አሰራርና የስነ ባህሪ ስልጠና የክልሉ የቢሮ ኃላፊዎች፣ ምክትል ቢሮ ኃላፊዎችና የሥራ ሂደት መሪዎች ተካፋይ ሆነዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 7/2009 በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ባለፈው ጥር በተጀመረው የተፋሰስ ልማት 617 ሺህ 740 ሄክታር መሬት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መሸፈኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ገለጸ።

የአገሪቷ ግብርና በዝናብ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የማህበረሰብ ተፋሰስ ልማት በአገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት መከናወን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።

በእነዚህ ዓመታት በተከናወኑ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ስራዎች እጅግ የተጎዱና የተራቆቱ አካባቢዎች ያገገሙበት፤ የደረቁ ምንጮች የጎለበቱበትና አርሶና አርብቶ አደሮችም ተጠቃሚ እንደሆኑበት መረጃዎች ያመለክታሉ።

ባለፈው ዓመት ተከስቶ የነበረውን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባራት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበራቸውም ተገልጿል።

የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለጹት የአርሶና አርብቶ አደሮች ስለ አፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ አስፈላጊነት ግንዛቤአቸው እያደገ መጥቷል።

በማህበረሰብ ተፋሰስ ልማት አስፈላጊነት ላይ ያለው ግንዛቤ መጨመርም ስራው እንደ ባሕል እንዲታይ ማድረጉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ሁሉም ክልሎች የተፋሰስ ልማት ዘመቻውን ለማካሔድ የጊዜ ሰሌዳ አውጥተው ወደ ተግባር እየገቡ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተያዘው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ 6 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ተለይቶ በማህበረሰብ ተፋሰስ ልማት ስራ ለመሸፈንም እቅድ ተይዟል።

በአጠቃላይ የተፋሰስ ልማት ዘመቻው ከ25 ሚሊዮን በላይ የሰው ኃይል ተሳታፊ እንደሚሆንና ከዚህ ውስጥ ከ11 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑ አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።

የተፋሰስ ልማቱን በተቀላጠፈ መንገድ ለማስቀጠልና ውጤታማ ለማድረግ የልማት ቡድኖችና አደረጃጀቶች ተለይተውና ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ስራ መገባቱንም አክለዋል።

በቅድመ ተፋሰስ ልማት ዘመቻው ከ18 ሺህ በላይ አመራሮችና ከ174 ሺህ በላይ ቀያሽ አርሶ አደሮችም ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።

በተፋሰስ ልማቱ ወቅት የሚከናወኑ ስነ-አካላዊና ስነ- ህይወታዊ ክዋኔዎች በእውቀትና በሳይንሳዊ መንገድ እንዲሆኑም ከቀበሌ እስከ ክልል  ባለሙያዎች እንዲሰለጥኑ መደረጉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብ፣ የሐረሪና የትግራይ ክልሎች የማህበረሰብ አቀፍ የተፋሰስ ልማት ዘመቻ ጀምረዋል።

ዘመቻውን ባለፈው ጥር መባቻ ከጀመሩት የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች እስካለፈው ሳምንት ድረስ የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች መረጃ መሰብሰቡንም አቶ አለማየሁ ገልጸዋል።

በተፋሰስ ልማቱ አዳዲስና እድሳት የሚደረግላቸው የስነ-አካላዊና ስነ-ህይወታዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን ጨምሮ ከንክኪ ነጻ የሚደረጉ መሬቶችም ተለይተዋል።

በዚህም በሁለቱ ክልሎች በዓመቱ ለማከናወን ከታቀደው 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 617 ሺህ 740 ሄክታር ላይ አዳዲስ የስነ-አካላዊና ስነ-ህይወታዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተከናውኗል።

ክልሎቹ ያሳዩት አፈጻጸም ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ማሳካት እንደሚቻል አመላካች እንደሆነም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የስነ-አካላዊና ስነ-ህይወታዊ የአፈር ጥበቃ ስራ፣ ጥገናና እድሳት የሚደረግለት 650 ሺህ ሄክታር መሬት ተለይቷል ብለዋል።

እስካሁን በሁለቱ ክልሎች 122 ሺህ ሄክታር መሬት የስነ-አካላዊና ስነ-ህይወታዊ ጥገናና እድሳት ተደርጎለታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በክልሎቹ ከእንስሳት ንክኪ ነጻ እንዲሆኑ የተደረጉ የግጦሽ አካባቢዎችና ቦረቦራማ መሬቶች እንዲያገግሙ ተደርጓል።

በማህበረሰብ ተፋሰስ ልማት ስራዎች የሚመዘገቡ መረጃዎች ትክክለኛ እንዲሆኑ ስልጠና መሰጠቱንና ከፌዴራል እስከ ቀበሌ የሪፖርት ግብረ መልስ አሰጣጥ ስርዓት መዘርጋቱንም አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ

ባህር ዳር የካቲት 7/2009 በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መስፋፋት ለትውልድ ስጋት መሆኑን በዘርፉ የተካሄደ ጥናት አመለከተ ።

የአገራችንን መልካም እሴቶችና ባህሎች ከመጤ ባህል ወረራ በመጠበቅ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “በአሉታዊ መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች” ላይ ያካሄደውን ጥናት መሰረት ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከፍተኛ ባለሙያና የጥናቱ ቡድኑ አባል ወይዘሮ አዳነች ካሳ እንደገለጹት "በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች መጤ ባህሎችና ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፉ መሆኑን የጥናት ግኝቱ አመላክቷል።

ጥናቱ በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ናሙናዎችን በመውሰድ መካሄዱን ጠቅሰዋል ።

"በጥናቱ ግሎባላይዜሽንን ተከትሎ የሚገቡ መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በከፍተኛ ፍጥነት መስፋፋት ለትውልድ ስጋት እንደሆነ  በጥናት ተለይቷል" ብለዋል።

በጥናት ውጤቱ መሰረት ሱስ አስያዥና አደንዛዥ እጾችን መጠቀም፣ የራቁት ዳንስ፣ ከተመሳሳይ ጾታ ጋር ወሲብ መፈጸም፣ በማሳጅ ቤቶች ወሲብ መፈጸም እየተስፋፉ ከመጡ መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በተጨማሪ ያልተገቡ ድረ ገጾችና የወሲብ ፊልሞችን መመልከት እንዲሁም ያልተገቡ አለባበሶች በሁሉም አካባቢ እየተስፋፉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

እነዚህ መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሁሉም ክልሎች እየተስፋፉ መሆኑን ወይዘሮ አዳነች ጠቁመው በተለይም " ፍሪ ዞን፣ ፍሪ ሳተርደይ እና ኖ ሼም ግሩፕ" በሚል ወጣቶች በቡድን የሚፈፅሟቸው መጤ እና ጎጂ ልማዶች በአዲስ አበባና በአንዳንድ ክልሎች በስፋት እንደሚስተዋሉ በጥናቱ መረጋገጡን ጠቁመዋል ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ሰፊና ሁሉን አቀፍ የማስተማር፣ ግንዛቤን የማሳደግና የማስጨበጥ ሥራ በመስራት አደጋውን መከላከል እንዳለበት ጥናቱ መጠቆሙን ተናግረዋል።

የአገሪቱን መልካም እሴቶችና ባህሎችን ከውጪ ከሚመጣ የባህል ወረራ በመጠበቅ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል ።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ረመዳን አሸናፊ በተወካያቸው አማካኝነት ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ቀደምት አባቶች ባህላቸውን፣ ታሪካቸውንና ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ጠብቀው ለትውልድ አስተላልፈዋል።

በአሁኑወቅት የአገሪቱን መልካም እሴቶችና ባህሎች ጠብቆ በመንከባከብ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም በየአካባቢው ያሉ መልካም ባህሎችን በማጥናትና በማስተዋወቅ ለቱሪስት መስህብነት በማዋል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው የገለጹት።

ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በመጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ ያተኮረ ጥናት ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ማካሄዱን ተናግረዋል።

"ግሎባላይዜሽንን መሰረት ያደረጉ የባህል ወረራዎች የሚያሳድሩት ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡን በዘላቂነት በማስተማር መከላከል ያስፈልጋል" ብለዋል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው የተለያዩ መልካም ባህልና እሴቶች እንዳሉን አስታውሰዋል።

"መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በቀጣይ የህዝቡን መልካም እሴቶችና ባህል እንዳያጠፉ ትውልዱ ነቅቶ መጠበቅ አለበት" ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የማህበረሰብ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን