አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Monday, 13 February 2017

ማይጨው የካቲት 6/2009 የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለማስወገድ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን የትግራይ ደቡባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ።

ህወሓት የትጥቅ ትግል የጀመረበት የካቲት 11  በዓል ትናንት በኮረም ከተማ  ተከብሯል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ተወልደብርሃን ተስፋአለም በበዓሉ ላይ  እንደገለጹት ፣ በዞኑ እስከ ቀበሌ ድረስ የጥልቅ ተሃድሶ  ንቅናቄ መድረክ ተካሄዷል፤ በዚህም  የአደረጃጀት ለውጥ ፣   የአመራር ሽግሽግና  ድልድል ተጠናቋል።

በአሁኑ ጊዜ በዞኑ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባራት በመዋጋት የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

በዞኑ ፍትሕና መልካም አስተዳደርን በማስፈን የአካባቢው ህዝብ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን  የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ተሳትፎውን ማጠናከር እንዳለበት ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል፡፡

"መንግስት በአካባቢው የሚደርሰውን  የድርቅ ችግር  በዘላቂነት ለመፍታት ዞኑን  የአግሮ ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል ስራ እየሰራ ነው "ብለዋል።

በዞኑ ባለፉት ዓመታት ተቆፍረው የቆዩትን ከ100 በላይ ከፍተኛ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን ለዘመናዊ የመስኖ ልማት አገልግሎት በማዋል አርሶአደሩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

በትምህርት ፣ በጤናና በሌሎችም ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች በማከናወን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን   አቶ ተወልደብርሃን ገልጸዋል፡፡

የኮረም ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አልጋነሽ ሕሸ በሰጡት አስተያየት ፣ የየካቲት 11 በዓል የሴቶችን መብት ያረጋገጠልን ቀን በመሆኑ በዓሉን በልዩ ስሜት እንደሚያከብሩት ተናግረዋል፡፡

"የካቲት 11 ልጆቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው ሰላማችን ያረጋገጡበት ዕለት በመሆኑ በደስታ እያከበርን ነው" ያሉት ደግሞ ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ካሰች ፍቃዱ ናቸው፡፡

ህወሓት የትጥቅ ትግል የጀመረበትን 42ኛው ዓመት በዓል በኮረም የተከበረው በህዝባዊ ውይይት ሲሆን በዕለቱ  የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች  በአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጡበትና በ21 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ባለ አራት ፎቅ ህንፃ ተመርቋል።

Published in ፖለቲካ

መቐለ የካቲት 6/2009 በድል የተጠናቀቀው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ/ህወሓት/የትጥቅ ትግል ወጣቶች ሀብት ማፍራት እንዲችሉ መደላድል መፍጠሩን አንዳንድ የክልሉ ወጣቶች ተናግረዋል፡፡

የህወሓትን የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል የዓድዋ ከተማ ነዋሪው ወጣት ዓወት በርሀ እንደገለጸችው የትጥቅ ትግሉ በድል መጠናቀቁን ተከትሎ ወጣቶች  ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ይሄውም  ወጣቱ ወደ ጦርነት   ሳይሆን የሀብት ባለቤት ወደሚሆንበት  የልማት ስራ ለመሰማራት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል፡፡

ወጣቷ እንዳለችው የዚህ እድል ተጠቃሚ በመሆን  የሴቶች የፀጉር ስራ ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከልና የሌላም ገቢ  ማስገኛ ደርጅት ባለቤት ናት፡፡

ከደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በ5 ሺህ ብር መነሻ ብድር  በጀመረችው ስራ አሁን ላይ የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር  ሀብት እንዳላት ወጣቷ ገልጻለች፡፡

" ያለፉት ዓመታት ለወጣቱ የተሻለ ትኩረት የተሰጠበት ነው " ያለው ደግሞ የመቀሌ ከተማ ነዋሪው ወጣት  ኢድሪስ ዓብደላ  ነው፡፡

በዚህም ተቀጥሮ ይሰራበት ከነበረው የግል የልብስ ስፌት ስራ በመውጣት ለ65 ሌሎች ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የሀብትና የንብረት ባለቤት ለመሆን መብቃቱን ተናግሯል፡፡

" የካቲት 11 በዓል ስናከብር ሰላም፣  ዴሞክራሲና ልማት ለማምጣት ህይወታቸውን የሰው ታጋይ አባቶችና እናቶችን የትግል መነሻ ሳንዘነጋ መሆን ይገባል "ብሏል፡፡

ባለፉት ዓመታት በተፈጠረላትው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም  የብሎኬት ማምረቻና መሸጫ ድርጅት ለመቋቋም መብቷን የተናገረችው ደግሞ  በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የዕዳጋ ዓርቢ ከተማ ነዋሪ ወጣት ንግስቲ ገብረመድህን ናት፡፡

" የታጋይ አባትና እናቶችን ታሪክ በመውረስ  የትግል ፅናታቸውን ለቀጣዩ  ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል "ብላለች፡፡

በህወሓት ጽህፈት ቤት የገጠር ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሀላፊ  አቶ አማኑኤል አማረ  በበኩላቸው ህወሓት የትጥቅ ትግል የጀመረበትን 42ኛ ዓመት በዓል የካቲት 11 የሚከበር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሃላፊው እንዳመለከቱት በዓሉ የሚከበረው " የተጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በየካቲት 11 ዳግም ቃል በመግባት ተጠናክሮ ይቀጥላል" በሚል መሪ ሀሳብ በፓናል ውይይት ነው፡፡

Published in ፖለቲካ

ሽሬ እንዳስላሴ የካቲት 6/2009 በትግራይ ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የማይ-ሓንሰ እና ደደቢት ከተማ ነዋሪዎች በማህበራዊ አገልግሎት መስጫት ተቋማት ያሉባቸው ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ ከከተሞቹ ነዋሪዎች ጋር  በልማትና በተነሱ ችግሮች ላይ ትናንት በማይ-ሓንሰ ከተማ መክረዋል።

ነዋሪዎቹ በውይይቱ ላይ እንዳሉት በከተሞቻቸው የመብራትና የመጠጥ ውሃ ችግር ከመኖሩ በተጨማሪ ቀደም ብሎ ግንባታው የተጀመረው ሆስፒታል ባለመጠናቀቁ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደነዋሪዎቹ ገለጻ፣ በሁሉቱም ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል አለመኖር የተለያዩ ሥራዎችን ለማናወን እንቅፋት እየሆነባቸው ነው።

በማይ-ሓንሰ ከተማ ግንባታው የተጀመረው ሆስፒታል እስካሁን ባለመጠናቀቁ ነዋሪዎች የተሻለ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት እየተቸገሩ መሆናቸውንም በውይይቱ ላይ አንስተዋል።

በአካባቢው የሚገኝ ጤና ጣቢያም በቂ የሕክምና መሳሪያና መድኃኒት ያልተሟላለት በመሆኑ ችግራቸው አለመቀረፉን ተናግረዋል።

በባንክ አገልግሎት፣ በትምህርትና በእናቶች ጤና አገልግሎት ላይ  የተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ከነዋሪዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

የማህበራዊ ረድኤት ትግራይ (ማረት) ዋና ዳይሬክተር አቶ ተክለወይኒ አሰፋ፣ ድርጅቱ ለከተማው አገልግሎት የሚውል ተጨማሪ የመጠጥ ውሃ ጉድጓድ በመቆፈር ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሀጎስ ጎዲፋይ በበኩላቸው ነዋሪዎች ያነሷቸው ችግሮች ትክክለኛ መሆናቸውን በመገንዘብ ሆስፒታሉን በቅርብ ጊዜ አገልግሎት ለማስጀመር የባለሙያዎች ቅጥር እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት በሚታይባቸው ጤና ጣቢያዎች መድኃኒት እንዲሟላ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በደደቢት ከተማ ተጨማሪ ጤና ጣቢያ ለመገንባት መታቀዱን ጠቁመዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ በበኩላቸው፣ በደደቢትና ማይ-ሐንሰ ከተሞች ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ለመፍታት የትራንስፎርመር ግዢ እንደሚፈጸም ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከውይይቱ በኋላ በትግራይ ክልላዊ መንግስት በ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በማይ-ሐንሰ ከተማ የተገነባውን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መርቀዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 6/2009 ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው ዓለማት የሠላም አምባሳደር በመሆን አገራቸውን እንዲያስተዋውቁ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘ ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በተደረገላቸው ጥሪ በስዊዘርላንድና ኢጣሊያ ይፋዊ ጉብኝት አድርገዋል።

ፓትርያርኩ በአገራቱ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ባካሄዱት ውይይት ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት ዓለም ሁሉ የሠላም አምባሳደር በመሆን ኢትዮጵያዊነትን እንዲያስተዋውቁ ጠይቀዋል።

ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር በመሆንም በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የምክር ቤቱን ጽህፈት ቤት ጎብኝተዋል።

ፅህፈት ቤቱ በሠላም፣ በፍቅርና በእኩልነት ላይ እያከናነወ ስላለው ዓለም አቀፍ ተግባርም በምክር ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ፓትርያርኩ ምክር ቤቱ በተለይም በዓለም ሠላም ጉዳይ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል።

"የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የምክር ቤቱ መስራች አባል እንደመሆኗ፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊነቷን አክብራ ምክር ቤቱ በሚሰራባቸው በሠላም፣ በትህትናና በአንድነት ላይ በጋራ ለመስራት ዝግጁ ናት" ብለዋል ፓትሪያርኩ።

በኢጣሊያ ሮም ባደረጉት ጉብኝትም ከመላው ዓለም በህገ ወጥ ስደትና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በተቋሙ ለተጠለሉ ስደተኞች የሚደረገውን የበጎ አድራጎት ስራ ተመልክተዋል።

ከድርጅቱ ፕሬዝዳንትና የስራ ኃላፊዎች ጋርም ስለ ስደት አስከፊነትና ስለ ዓለም ሠላምና ጸጥታ ጉዳይ ተወያይተዋል።

በስዊዘርላንድና ኢጣሊያ ጉብኝታቸው በአገራቱ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋርም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

በፓትሪያርኩ የተመራው የቅዱስ ሲኖዶስ የልዑካን ቡድን በጄኔቫና በሮም ለአምስት ቀናት ያካሄደውን ጉብኝት አጠናቆ መመለሱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙሃን አገልግሎት ስርጭት ለኢዜአ ገልጿል።

Published in ማህበራዊ

ፍቼ የካቲት 6/2009 በየደረጃው የተካሄደው የጥልቅ የተሃድሶ መድረክ ለመብቱ ተሟጋች ህብረተሰብ እንዲፈጠር ማገዙን በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

ከዞን የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የጥልቅ ተሀድሶ ማጠቃለያ የውይይት መድረክ ትናንት በፍቼ ከተማ ተካሄዷል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የአብቹ ኘአ ወረዳ የሀገር ሽማግሌ ተወካይ አቶ ጌታቸው ጥላ እንደገለፁት በየደረጃው የተካሄደው የጥልቅ ተሀድሶ መድረክ በመንግሥትና በህዝብ መካከል መቀራረብ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

''ይህም ህብረተሰቡ ፍትሀዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ከማስቻሉም በላይ ለመብቱ ተሟጋች ህብረተሰብ እንዲፈጠር  አስችሏል'' ብለዋል፡፡ 

የግራር ጃርሶ ወረዳ ሴቶች ተወካይ ወይዘሮ በላይነሽ ሀይሉ በበኩላቸው በአካባቢያቸው በርካታ የአሰተዳደርና የመሰረተ ልማት ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከህዝቡ ጋር የበለጠ ተቀራርቦ ሊሰራ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

በውይይቱ ላይ በጥልቅ ተሀድሶ የተለዩ ችግሮች መፍትሄ ያገኛሉ የሚል እምነት እንዳላቸው የገለፁት ደግሞ የደር ወረዳ የሀገር ሽማግሌ ተወካይ አቶ ብርሃኑ ደሜ ናቸው፡፡

መድረኩን የመሩት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ አቶ እሸቱ ደሴ እንደገለፁት በክልሉ በየደረጃው የተካሄደው በጥልቅ የመታደስ መድረክ ለቀጣይ ስራዎች የለውጥ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል።

መድረኩ በየደረጃው የሚታዩ የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራር ምንጮችን በመለየት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት መሰረት መጣሉን ጠቁመዋል፡፡

ህዝባዊ ችግሮች የሚፈቱት ለተወሰነ አካል ብቻ ኃላፊነት በመስጠት ሳይሆን ሁሉም የድርሻውን  በመወጣትና በመታገል መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በዞኑ በየደረጃው በተካሄደ ጥልቅ ተሀድሶ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ተቀምጦ ወደተግባር መገባቱን የገለፁት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ  አቶ ተክለፃዲቅ ሬባ ናቸው፡፡

በተለይ ለተለዩ ችግሮች ላይ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እስካሁን አሰራሮችን በማሻሻል ከዞን እስከ ወረዳ  አዳዲስ አደረዳጀቶች እንዲዋቀሩ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በዞኑ 13 ወረዳዎችና ከተሞች ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነትና አደራ በአግባቡ ያልተወጡ 558 አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

ሁለት ሺህ 626 የሚሆኑ አመራሮች ደግሞ የመዋቅር ሽግግር የተደረገ ሲሆን 35 የዞን አመራሮች በአዲስ እንዲተኩ ተደርጓል፡፡

በተለይ ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ ወንጀል የፈጸሙ አካላት በህግ እንዲጠየቁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በመድርኩ ማጠቃለያ ላይ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሱሌማን ደደፎ እንዳስገነዘቡት መብትን በገንዘብ ለመግዛት ከመደራደር ይልቅ በህጋዊ መንገዶች መታገል ይገባል።

በፍቼ ከተማ ሁለገብ አዳራሽ በተካሄደው የማጠቃለያ የውይይት መድረክ ከዞኑ 13 ወረዳዎች የተውጣጡ 6ዐዐ የሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 6/2009 በባቡር መስረተ ልማት ዝርጋታ የተሻለ ልምድና ዕውቀት እያገኙ መሆኑን በስራው እየተሳተፉ የሚገኙ አገር በቀል የስራ ተቋራጮች ገለጹ።

ኢትዮጵያ በባቡር መሰረተ ልማት ዝርጋታ ያገኘችውን ልምድና እውቀት ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ለማካፈል በዝግጅት ላይ መሆኗን የገለጸው ደግሞ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ነው።

አገር በቀል ተቋራጮቹ የባቡር መስመር ዝርጋታው በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ ዕውቀትና ክህሎትን መጨበጥ እንዳስቻላቸው ነው የሚናገሩት።

ከነዚህ ተቋራጮች መካከል በአዋሽ ወልዲያ የባቡር መስመር ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው 'ኦርኪ ቢዝነስ ግሩፕ' አንዱ ነው።

የኩባኒያው 'ኤርዝ ሙቪንግ' ስራዎች ኃላፊ ኢንጂነር መሳይ ይመኑ እንደሚሉት ስራውን እያከናወነ ከሚገኘው ያፒ መርከዚ ከተሰኘው የቱርክ ኩባንያ ኮንትራት በመውሰድ በፕሮጀክቱ ተሳታፊ ሆነዋል።

''በኮንትራቱ መሰረት ላለፉት ሁለት ዓመታት 70 ኪሎ ሜትር የአፈር ቆረጣና ሙሌት ስራ በመስራት ጥሩ ልምድና የስራ ባሕል ማዳበር ችለናል'' ነው የሚሉት።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ኩባኒያው ካገኘው የ700 ሚሊዮን ብር ገቢ በላይ በዘርፉ ያካበተው ዕውቀትና የስራ ልምድ በሌሎች ተመሳሳይ ስራዎችም በስፋት ለመሳተፍ ያግዘዋል።

ሌላው በግንባታው ተሳታፊ የሆነው 'ቢአይካ ጀነራል ፒ.ኤል.ሲ' የተሰኘው አገር በቀል ተቋራጭ ነው 

የኩባኒያው የኮንስትራክሽን ስራዎች ኃላፊ ኢንጂነር ጀመረ ምስጋናው ''በፕሮጀክቱ ከተሳተፍንባቸው ስራዎች መካከል 27 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የሬዲዮ ኮሚኒኬሽን የመንገድ ግንባታ ስራዎች ሰርተን አጠናቀናል'' ብለዋል።

የግንባታውን ኮንትራት በንኡስ የስራ ተቋራጭነት መውሰዳቸውን የሚገልጹት ኃላፊው ''በስራ ላይ ያገኘነው የዘመናዊና አዳዲስ ቴክኖሎጂ  ዕውቀቶች ወደፊት በዘርፉ ራሳችንን ችለን በዋና ስራ ተቋራጭነት እንድንሰራ የሚያደርገን ነው'' ይላሉ።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በበኩሉ የባቡር መስመር ዝርጋታው ከአገር በቀል ኩባንያዎች አልፎ ኢትዮጵያ ልምዷን ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም ለማካፈል የሚያስችላት እየሆነ ነው ይላል።

በአገሪቱ የባቡር መስመር ዝርጋታ መጀመሩ ኢትዮጵያ በዘርፉ አዳዲስ ዕውቀትና ቴክኖሎጂን እንድትገበይ አድርጓል የሚሉት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ኢንጂነር ጌታቸው በትሩ ናቸው።

በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰልጣኞችና የአገር ውስጥ ተቋራጮች ዘመናዊ የባቡር መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ የካበተ ልምድ እንዲያገኙ አስችሏል ብለዋል። 

በአገሪቱ የተከፈተው የባቡር መሰረተ ልማት አካዳሚ ሰልጣኞች ከዲዛይን ጀምሮ ድልድዮችና የውስጥ ለውስጥ ዋሻዎች ግንባታ ዕውቀቶችን ቦታው ድረስ ሔደው እንዲቀስሙ በር መክፈቱን ነው የገለጹት። 

በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 500 የሚደርሱ ሰልጣኞች የባቡር መሰረተ ልማት ላይ ስልጠና እየተከታተሉ ይገኛሉ ነው ያሉት።

ኮርፖሬሽኑ ይህን ዕውቀት ለሌሎች አገራትም ለማካፈልና ወደ ገቢ ማስገኛነት ለመቀየር እየሰራ መሆኑን ተናግረው ''በቅርቡም የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ በዘርፉ ያገኘችውን ዕውቀት እንድታካፍላቸው ጥያቄ አቅርበዋል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያን ልምድ ለመውሰድ ጥያቄ ካቀረቡት መካከል ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና ናይጄሪያ ይጠቀሳሉ።

በእስካሁኑ ሂደት የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ወደ ኬንያ ሔደው ከዲዛይን ጀምሮ የቅየሳና ሌሎች ሙያዊ ስራዎችን ለማከናወን ዝግጅት አድርገዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በባቡር መሠረተ ልማት ሕዝቦቿን ለማስተሳሰር ከምታደርገው ጥረት በላይ ራሷን ከጎረቤት አገራት ጋር ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት አድናቆትን እያተረፈላት መጥቷል።

Published in ማህበራዊ

ጅማ-/ ሶዶ የካቲት 6/2009 በጅማ ከተማ በተካሄደው 12ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ጨዋታ ጅማ ከተማ ከስልጤ ወራቤ ጋር ባደረጉት የእግር ኳስ ቡድን  አንድ እኩል ተለያዩ፡፡

በወላይታ ሶዶ ስታዲየም በተካሄደው የቦሊ ቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታም ወላይታ ዲቻ የፌደራል ማረሚያ ቤቶችን 3 ለ 0 አሸነፏል።

በጅማ ከተማ በተካሄደው የከፍተኛ ሊግ ጨዋታ ጎሎቹ በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተቆጠሩ ሲሆን ለጅማ ከተማ አክሊስያስ ግርማ፤  ለስልጤ ወራቤ ደግሞ ከድር ታረቀኝ ጎል አስቆጥረዋል፡፡

ጨዋታው ያለመግባባት የታየበት ሲሆን በወራቤ ከተማ ላይ የተቆጠረው ጎል ከፍተኛ ውዝግብ ከማስነሳቱም በላይ ለ10 ደቂቃ ጨዋታው እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡

ወራቤዎች ኳስ ከጎል መስመር ሳያልፍ መመለስ በመቻላችን ጎል ሁኖ  ሊጸድቅ  አይገባም ሲሉ ቢከራከሩም የእለቱ ዳኛ ኳሷ ከመስመር ካለፈ በኋላ ነው የተመለሰው በሚል ጥያቄያቸውን ሳይቀበሉ ጎሉን አጽድቀዋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የጅማ ደጋፊዎች ድንጋይና የውሃ መያዣ ፕላስቲኮችን ወደሜዳ ሲወረውሩ የተስተውሉ ሲሆን ከደጋፊዎች በተጨማሪ ስፖርቱን የሚመሩ አካላት ሜዳ ላይ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ሲደባደቡ ተስተውሏል፡፡

የጅማ ከተማ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና "ኳስ ተቆጣጥርን ብንጫወትም ወደጎል መቀየር ላይ ስኬታማ አልነበርንም " ብለዋል፡፡

"በጨዋታው የዳኝነት ክፍተት ሰፊ ነበር፤ በርካታ ኳሶች ከግብ ክልል የሚርቁት በእጅ እየተነኩ ነበር" ብለዋል፡፡

አንዳንድ የጅማ ክለብ ደጋፊዎች በግል ተጫዋቾችን ሲደግፉ መስተዋላቸውን ገልጸው፣ መደገፍ የሚገባቸው ቡድኑን እንጂ ተጨዋቾችን በተናጠል መሆን እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡

የስልጤ ወራቤ አስልጣኝ ይዘዲን አብደላ በበኩሉ በጨዋታው ውጤት ቢደሰትም በዳኝነቱ ላይ "ከፍተኛ ቅሬታ አለኝ" ብሏል፡፡

"ዳኛው ፊትለፊት ቁመው እያዩ ያልገባ ኳስ ገብቷል ብለው መወሰናቸው ተገቢ አይደለም። በጨዋታው እስከ ድብድብ የደረሱ በርካታ ጥፋቶች የተፈጸሙ ቢሆንም ምንም አይነት የማስጠንቀቂያ ካርድ ባለመሰጠቱም አዝኛለሁ" ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ  የምድብ "ለ"ን ጨዋታ ጅማ ከተማ በ22 ነጥብ አንደኛ ሁኖ ሲመራ ስልጤ ወራቤ በ14 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ ዜና በመረብ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ወላይታ ዲቻ የፌደራል ማረሚያቤቶችን 3 ለ 0 አሸነፏል።

የወላይታ ዲቻ ቡድን ተጋጣሚውን ያሸነፈው ትናንት ከቀኑ በ8፡00 ሰዓት በሜዳው በተካሄደው 7ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ መርብ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጫዋታ ነው።  

የዲቻ ቡድን ኳስ በመቆጣጠር በተጋጣሚው ላይ ብልጫ በመውሰድ ለማሸነፍ ችሏል፡፡

በወላይታ ሶዶ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ በርካታ ደጋፊ ባይገኝም ሁለቱም ቡድኖች አዝናኝ የኳስና የጨዋታ እንቅስቃሴ አሳይተዋል፡፡

የወላይታ ዲቻ አሰላጣኝ ሻምበል ጳውሎስ ሹኬ "የተጋጣሚያችንን የጨዋታ ዜዴ ስለምናውቅ በሜዳችን ላይ ጨዋታውን በበላይነት ተቆጣጥረን ለማሸነፍ ተዘጋጅተን ነበር፤ አሳክተናል፡፡" ብለዋል።

"ለዋንጫ ስለምንጫወት ነጥቡ ከምንም በላይ ያስፈልገናል፤ በጨዋታው ተጋጣሚያችን ሊፈትነን ሞክሯል" ብለዋል፡፡

"የተመልካችና የብዙሀን መገናኛ ለስፖርቱ ትኩረት አለመስጠት በዕድገቱ ላይ አሉታዊ ጫና እንዳያሳድር እፈራለሁ" ብለዋል፡፡

የፌዴራል ማረሚያቤቶች አሰልጣኝ ዋና ኦፊሰር ተሾመ ለማ የልምድና የትኩረት ማነስ ለቡድናቸው መሸነፍ ዋነኛ ምክንያቶች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

" ወላይታ ዲቻ ጠንካራ ቡድን ነው፤ ከስህተታችን ተምረን በቀጣይ ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን" ብለዋል፡፡

በዳኝነቱ ላይ ቅሬታ እንደተሰማቸው የተናገሩት አሰልጣኙ፣ "ሞራል የሚነካ ነገር የጨዋታውን ድባብ ስለሚያበላሽ ሊታሰብበት ይገባል" ብለዋል፡፡

Published in ስፖርት

ባህር ዳር የካቲት 6/2009 በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው የጣና ፍሎራ ኩባንያ ባለፉት ስድስት ወራት ያመረተውን አበባ ወደ ተለያዩ የውጭ ሃገራት በመላክ ከሁለት ሚሊዮን  ዩሮ በላይ ገቢ ማስገኘቱን አስታወቀ።

የኩባንያው የእቅድና ክትትል ባለሙያ አቶ በላይ ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት የአበባ ልማቱን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ለገበያ የማቅረብ ስራው እንደቀጠለ ነው፡፡

ገቢው የተገኘው ከ14 ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ 21 ዓይነት የአበባ ዘንግ ወደ አውሮፓ ገበያ በመላክ እንደሆነ አስታውቀዋል።

በዓመቱ መጀመሪያ በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው  ግርግር በአበባ ልማቱ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም ችግሩን ፈጥኖ በመፍታት ከቀድሞ በተሻለ ምርት በመሰብሰብ መላክ መቻሉን ባለሙያው ጠቁመዋል።

ባለሙያው እንዳመለከቱት በግማሽ ዓመቱ የተላከው የአበባ ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ የአበባ ዘንግ ጭማሪ አለው።

ከሽያጩ  የተገኘው ገቢም በ675 ሺህ 849 ዩሮ ብልጫ እንዳለው ባለሙያው ጠቁመው፤ ለጭማሪውም ኩባንያው የአበባ ምርት ጥራቱን በማሻሻል በገበያ ተወዳደሪ ሆኖ የማሸነፍ አቅሙ  እያደገ በመምጣቱ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጣና ፍሎራ የአበባ ልማቱን በ40 ሄክታር መሬት እያከናወነ ሲሆን በ84 ሄክታር መሬት ላይ ደግሞ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት መጀመሩን አቶ በላይ ተናግረዋል።

በልማቱም ዘጠኝ መቶ ለሚጠጉ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከልም የአበባ ምርት ተቆጣጣሪዋ ወይዘሮ ተስፋ መኩሪያ በሰጡት አስተያየት "ኩባንያው የአዳዲስ ቴክኖሎጂና ልምድ ባለቤት አድርጎኛል " ነው ያሉት።

በዚህም በቀጣይ ወደ አካባቢው ለሚመጡ የአበባ ኢንዱስትሪዎች"  የተሻለ እውቀትና ክህሎት በመጨበጥ ለዘርፉ ውጤታማነት የበኩሌን እንድወጣ ያግዘኛል" ብለዋል።

በተለይም የአበባ ልማት አዲስ ኢንዱስትሪና  የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማስገኛ ምንጭ በመሆኑ የበለጠ ጠንክረው እንዲሰሩ የሚያነሳሳቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

በኩባንያው ተቀጥረው በሚያገኙት የተሻለ ገቢም  ራሳቸውንና  ቤተሰባቸውን በመርዳት ተጠቃሚ እንደሆኑም ጠቅሰዋል።

የጣና ፍሎራ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት ከ44 ሚሊዮን በላይ የአበባ ዘንግ በመላክ ከስድስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ዩሮና 26 ሺህ 700 ዶላር  ገቢ ማስገኘቱም ተመልክቷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 6/2009 የመዲናዋ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የአበበ ቢቂላ ስታዲየምን ጥገናና ጣሪያ ማልበስ ከሚከውነው የቻይና ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራረመ። 

የቻይናው ዙዋንግንሚን ኩባንያ ስራውን በ105 ሚሊዮን ብር ወጪ በ18 ወራት ለማከናወን ተስማምቷል።

ስምምነቱን የቢሮው ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸውና የኩባንያው ተወካይ ዋንግ ሁ ተፈራርመዋል።

ለጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ መታሰቢያነት የተገነባው ስታዲየም ለበርካታ ዓመታት የመሮጫ ትራክ፣ ጣሪያና መቀመጫ ወንበር ሳይገጠምለት ቆይቷል።

የጥገናና ጣሪያ የማልበስ ስራውን ለመስራት ከታቀደም እንዲሁ ዓመታት ተቆጥረዋል።

በመሆኑም የስታዲየሙን ጥገናና ጣሪያ የማልበስ ስራ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለማከናወን የዲዛይን ጥናቱን ካሸነፈው የቻይና ኩባንያ ጋር  ዛሬ ስምምነቱ ተፈርሟል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው እንደተናገሩት ጥገናውን ለማከናወን በተደጋጋሚ ጨረታ ቢካሄድም በዲዛይን ጥራት ችግር ዘግይቷል።

ቀደም ሲል የትራክ (የመም) ንጣፍ ሊካሄድ ታስቦ የነበረ ቢሆንም በድጋሚ ታይቶ ሁሉን አቀፍ የትራክ፣ የመቀመጫ ወንበር ጥገናና የጣሪያ ማልበስ ስራ እንዲከናወን 105 ሚሊዮን ብር ተበጅቶለታል ብለዋል።

የዙዋንግንሚን ኩባንያ ተወካይ ሚስተር ዋንግ ሁ በበኩላቸው የጣሪያ ማልበስና ጥገናው ጥራት ተጠብቆ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ እንሰራለን ብለዋል።

የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ስራው ጥራቱን ጠብቆ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

Published in ስፖርት

ጎባ-ነገሌ-መቱ የካቲት 6/2009 የተሃድሶ ንቅናቄ መድረኩ መንግስት የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግር አዳምጦ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት መሆኑን በኦሮሚያ ክልል የባሌ፣ ጉጂና ኢሉአባቦራ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የየዞኑ ነዋሪዎች ተወካዮች የተሰተፉበት የጥልቅ ተሀድሶ የማጠቃለያ መድረክ በባሌ ሮቤ፣ ነገሌና መቱ ከተሞች ትናንት ተካሄዷል፡፡

በክልሉ ባለፉት 15  ዓመታት በርካታ የልማት ስኬቶች ቢመዘገቡም ህብረተሰቡን ለቁጣ ያነሳሱ ችግሮች እንደነበሩም የየዞኑ የውይይት ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡

በባሌ ሮቤ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ  ተሳታፊዎች መካከል የጊኒር ወረዳ ተወካይ ሃጂ ሙክታር ሙሀመድ እንደተናገሩት በየደረጃው የተካሄደው የተሃድሶ ንቅናቄ መድረክ መንግስት የህብረተሰቡን ችግር በማዳመጥ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዲንሾ ወረዳ የመጣው ወጣት አዱኛ ከተማ በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የመልካም አስተዳድር ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፍ ገልጿል።

በተለይ በዞኑ የአርብቶ አደር ወረዳዎች ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ጋር ያለው የወሰን ችግር እልባት እንዲበጅለት ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር፣  በዞኑ ግንባታቸው ተጀምሮ የተጓተቱ የመደ ወላቡ የባህል ማእከልና የጊኒር ከተማ የመጠጥ ውኃ ግንባታ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

የውይይት መድረኩን የመሩት በሚኒስትር ማዕረግ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ተቋማት ጉዳዮች አስተባባሪ አቶ አብዱልአዚዝ መሀመድ እንደተናገሩ በየደረጃው በተካሄዱ የተሃድሶ መድረኮች የመንግስትን ደካማ ጎን ለመለየትና የወደፊቱን አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚያስችል ግብዓት ተገኝቷል፡፡

የተሀድሶ መድረኩ የተፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንዲችል የመንግስት ጥረት ብቻ  በቂ አለመሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት  ሕብረተሰቡ  የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ  አቶ አብዱልአዚዝ አሳስበዋል፡፡

ከህብረተሰቡ የተነሳውን የወሰን ጥያቄ በተመለከተም “የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከፌዴራልና ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል መንግስት ጋር በጉዳዩ ላይ እየመከረበት” ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደም ቃሲም በበኩላቸው ''መንግስት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በቁርጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛል'' ብለዋል፡፡

ከጉጂ ዞን ነዋሪዎች ተወካዮች መካከል የአዶላ ከተማ ነዋሪ ቄስ ቶማስ ቦሩ በሰጡት አስተያየት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመፍታት ጅምር ቢኖርም የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መጓተት ችግሮች ፈጣን ምላሽ የሚሹ ህዝባዊ ጥያቄዎች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በተለይ ግንባታቸው የተጀመሩ  ሆስፒታሎች ስራ አለመጀመር፣ የመጠጥ ውሀና የአስፋልት መንገድ ግንባታ መጓተት አሳሳቢ እንደሆነ በዞኑ የኡራጋ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ሽምብራ ዱጎ ገልጸዋል፡፡

መድረኩን የመሩት የእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ "በ15 አመታት የህዳሴ ጉዞ የተመዘገበውን ሰላም፣ ልማትና እድገት ለማስቀጠል የህዝብ ድጋፍና ትብብር ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳሉት መንግስት የኪራይ ሰብሳበነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የራሱ አድርጎ በመውሰድ ከህዝብ ለቀረቡ  ጥያቄዎች በጥልቅ ተሀድሶ ምላሽ እንደሚሰጥ በተግባር አረጋግጧል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ዋደራ የኪራይ ሰብሳቢነት ብልሹ አሰራርን ለማስተካከል በጥልቅ ተሀድሶ የተወሰዱ የአዳዲስ አመራሮችን ሹመት ለውይይቱ ተሳታፊዎች ይፋ አድርገዋል፡፡

በኢሉአባበራ ዞን የህዝብ ተወካዮች መካከል  ከዳሪሙ ወረዳ የተገኙ አቶ ሙዘሚል አብዱረህማን  እንዳሉት መንግስት የመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን ለመቅረፍ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ያካሄደው የጥልቅ ተሀድሶ ህዝባዊነቱን ያሳየ ነው፡፡

በዞኑ ባለፉት ዓመታት ተጀምረው የተስተጓጎሉና የተጓተቱ የልማት ኘሮጀክቶች በአዲሶቹ አመራሮች መፍትሄ ያገኛሉ ብለው እንደሚጠብቁ ገልፀዋል፡፡

''ባለፉት ዓመታት መንግስትና ህዝብ ያስመዘገቧቸው  የልማት ውጤቶች ከቅርብ አመታት ወዲህ በኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ሳቢያ በሚፈለገው መልኩ ተጠቃሚ እንዳንሆን አድጎናል'' ያሉት ደግሞ የዶረኒ ወረዳ የሀገር ሽማግሌ አቶ ታደሰ ሁንዴ ናቸው፡፡

የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸናፊ ሞሲሳ በበኩላቸው የጥልቅ ተሀድሶውን ውጤት መሠረት በማድረግ  ከዞን እስከ ቀበሌ ያለውን አመራር እንደገና የማዋቀር ስራ ተሰርቷል፡፡

መድረኩን የመሩት የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች  ሚኒስትር ወይዘሮ ደሚቱ አምቢሳ እንደተናገሩት በጥልቅ ተሀድሶው  የተለዩትን ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን እቅድ አውጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡፡

 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን