አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 12 February 2017

አዳማ የካቲት 5/2009 በየደረጃው የተካሄደው የጥልቅ የተሀድሶ ንቅናቄ የሕብረተሰቡን የቅሬታ ምንጭና መፍትሄውን ለመለየት ማስቻሉን የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ድሪባ ኩማ ገለጹ።

ዛሬ በተካሄደው የአዳማ ከተማና የምስራቅ ሸዋ ዞን የጥልቅ ታሀድሶ ማጠቃለያ መድረክ ላይ የተገኙት ከንቲባ ድሪባ፣ ድርጅቱ ባለፉት 15 ዓመታት የተጓዘበት መንገድና ያመጣቸው ለውጦች የጥልቅ ተሀድሶው መነሻ ናቸው።

ከንቲባው እንዳሉት በእነዚህ ዓመታት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች በመጡት ለውጦች በየደረጃው መብቱን የሚጠይቅና ጥቅሙን የሚያስከብር ሕብረተሰብ መፍጠር ተችሏል።

በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በፍትህና በዴሞክራሲ ሥርእት ግንባታ ረዥም ርቀት ቢኬድም የሚያኩራራ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ያገጠሙ ችግሮች ለህዝቡ ሁሉን አቀፍ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ወቅታዊና ተገቢ ምላሽ ባለመሰጠቱ  የተከሰቱ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

መንግስትና የክልሉ መሪ ድርጅት ኦህዴድ ይህን ችግር በህዝባዊ ተሳትፎና በጥልቅ ተሀድሶ ለመፍታት የችግሩን ምንጭ የመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫ የማስቀመጥ ሥራ መስራታቸውን አስረድተዋል።

በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄው የተገኙትን ለውጦችና ውጤቶች አጠናክሮ ለማስቀጠል ከህዝቡ ጋር በጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ሲባል ይህ መድረክ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ በበኩላቸው፤  በፍትህ እጦት፣ በመልካም አስተዳድር፣ በኪራይ ሰብሳቢነትና በአንዳንድ አመራሮች የተማረረው ህዝብ ወደ አደባባይ ወጥቶ አንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም የተበደለውን ህዝብ ለመካስ በሙሉ አቅም እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ መልካቸውን እየቀየሩ የመጡ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማስወገድ አዳዲስ ሰዎች ወደአመራርነት እንዲመጡ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም ማገልገያ ከማዋል ጀምሮ በየደረጃው የሕብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  ጥያቄዎችን ለመመለስ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መገባቱን ነው የገለጹት።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ኃይሉ በበኩላቸው "በገጠርና በከተማ በሁሉም መስክ ተጨባጭ ለውጦች ቢመዘገቡም የህብረተሰቡን ብሶትና ጥያቄ በአግባቡ ማስተናገድ ባለመቻሉ ዋጋ ተከፍሏል" ብለዋል።

በዞኑ በሚገኙ ከተሞች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ከ330 ሺህ በላይ የድርጅቱን አባላት፣ አመራሮችና ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ጥልቅ ተሀድሶ በማድረግ ለችግሮቹ የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉንም አመልክተዋል።

ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ወለንጪቲ ከተማ ነዋሪ አቶ ሰጪ ቶላ እንደገለፁት፣ በመንግስትና በድርጅቱ የተካሄደው የተሀድሶ ግምገማ ህዝብን ያማርሩ የነበሩ አመራሮችና ፈጻሚዎች በውል እንዲለዩ አድርጓል።

አመራሩን ከቦታ በማንሳት ብቻ የህዝቡ ችግር መፍታት እንደማይቻል የገለጹት አቶ ሰጪ፣ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ተሀድሶው ወደ ቀበሌ እንዲወርድ ጠይቀዋል።

"ተሀድሶ ከመጀመሩ በፊት የከተማ መሬት በጥቂት ግለሰቦችና ባለሃብቶች እጅ ስር ነበር፤ አሁን መሰረታዊ ለውጥ ይመጣል ብለን እንጠብቃለን" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ብርቄ ሀዋስ የተባሉ የአዳማ ከተማ ቀበሌ 05 ነዋሪ ናቸው።

መንግስት ሙሁራንን ወደ አመራርነት ያመጣውና አጥፊዎችን ከቦታቸው ያነሳው በተሀድሶ ምክንያት መሆኑን ገልጸው፣ ለተሀድሶው ውጤታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለይ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የፍትህና የመልካም አስተዳድር ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

በአዳማ ከተማ ዛሬ በተካሄደው ህዝባዊ ኮንፈረንስ ላይ ከምስራቅ ሸዋ ዞን አስር ወረዳዎች እንዲሁም አዳማን ጨምሮ ከአራት የከተማ አስተዳድሮች የተወጣጡ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 5/2009 በቡራዩ ከተማ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥባቸው ነዋሪዎች ጠየቁ።

የከተማዋ አስተዳደር የከንቲባ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ኅብረተሰቡ ላነሳቸው ችግሮች መፍትሄ የማምጣት ስራ እየተተገበረ ነው ብሏል።

በቡራዩ ከተማ ከኅብረተሰቡ ጋር ሲካሄድ የቆየው የጥልቅ ተኃድሶ መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

ነዋሪዎቹ በዚሁ ጊዜ ለኢዜአ እንደተናገሩት በመሬት አስተዳደር፣ በትራንስፖርት፣ በውኃና በኤሌክትሪክ አገልግሎቶች ላይ ችግሮች በመኖራቸው ኅብረተሰቡ እየተጉላላ ነው።

የሚመለከተው አካል ለችግሮቹ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የኅብረተሰቡን ጥያቄ እንዲመልስ ነው ነዋሪዎቹ የጠየቁት።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ሳጂን እያሱ ፈይሳ የከተማዋ የውኃ አቅርቦት ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያላደረገና ችግሮች የሚስተዋሉበት ነው ይላሉ።

ተደጋጋሚ መቆራረጥና መጥፋት እንዳለ ጠቅሰው የከተማዋ የጽዳት አገልግሎትም በተመሳሳይ ችግር ያለበት በመሆኑ ትኩረት እንዲሰጠው አመልክተዋል።

የወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል።

እነዚህና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት መንግሥትና ሕዝብ ተቀራርበው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

አቶ ብርሃኑ ደረብሳ በበኩላቸው በከተማዋ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነት ክፈተት እንደሚስተዋልበት ተናግረዋል።

የትራንስፖርት አቅርቦቱ ከከተማዋ ነዋሪ ቁጥር ጋር ባለመጣጣሙ ህብረተሰቡ በተለይ በሥራ መግቢያና መውጫ ሠዓት እንደሚቸገር ጠቁመዋል። 

በከተማዋ "በመሬት መረጃ አያያዝና በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ" ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ክበበው ቶልቻ ናቸው።

እንደ እርሳቸው ገለጻ በከተማዋ መሬትን በመተለከተ የሚሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶች በአንድ ቦታ መወሰኑ ኅብረተሰቡን ለእንግልት ዳርጎታል።

ለስራው የሚመጥን ሙያተኛ በመቅጠር መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የቡራዩ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በይሳ ከተማ ከኅብረተሰቡ የተነሱት የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎች ትክክለኛ መሆናቸውን አምነዋል።

ጽህፈት ቤቱ ችግሮቹን ለመፍታት ከሚመለከተው የሥራ ክፍል ጋር በመሆን በተለይ የትራንስፖርትና የውኃ አቅርቦቱን ለማስተካከል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከመሬት የመረጃ አያያዝ ጋር የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማስቀረትም ጽህፈት ቤቱ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን በሶስት ቀበሌዎች መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል።

በከተማዋ አሉ የተባሉትን ሌሎች ችግሮች ለመፍታት በቀጣይ ትኩረት በመስጠት አንሰራለን ብለዋል።

 

Published in ፖለቲካ

ሶዶ የካቲት 5/2009 በወላይታ ሶዶ ስታዲየም ዛሬ በተካሄደ ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታ ወላይታ ዲቻ መከላከያን አንድ ለ ባዶ አሸነፈ፡፡ 

በመጀመሪያው የጫዋታ ክፍለ ጊዜ መከላከያ ኳስ በማደራጀት፣ በመከላከል፣ በማጥቃት፣ በጎል ሙከራና ዕድሎችን በመፍጠር የተሻለ ቢንቀሳቀስም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

ባለሜዳው ወላይታ ዲቻ የኳስ ብልጫ ቢወሰድባቸውም አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት የጎል ዕድሎችንና ሙከራዎችን ሲያደርግ ታይቷል፡፡

በሁለተኛው የጫዋታ ክፍለ ጊዜ የወላይታ ዲቻ ቡድን ራሱን አሻሽሎ በመቅረብ በ70ኛ ደቂቃ ላይ በስምንት ቁጥሩ አሸናፊ ዋሎ ተቀይሮ የገባው 10 ቁጥሩ ሳምሶን ደጄነ ጎል አስቆጥሯል፡፡

በ66ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ዲቻ 21 ቁጥሩ ሃፍታለም ታፈሰ በመከላከያው 20 ቁጥር ማቲያስ ወልደአረጋይ ላይ በፈጸመው ጥፋት ከሜዳ በቀይ ካርድ ወጥቷል፡፡

የወላይታ ዲቻ ከ20 ዓመት በታች ዋና አሰልጣኝ ግዛቸው ጌታቸው ''መከላከያ ከባድ ቡድን ቢሆንም በሜዳችን ማሸነፍ አለብን ብለን ነበር የሰራነው ተሳክቶልናል'' ብለዋል፡፡

የመከላከያው ከ20 ዓመት በታች አሰልጣኝ መንግስቱ ዋንጫ ''በመጀመሪያው የጫዋታ ክፍለ ጊዜ የፈጠርናቸውን የጎል ዕድሎች አለመጠቀማችንና የመረጥነው የጫዋታ ዜዴ ዋጋ አሰከፍሎናል'' ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ጨዋታውን በርካታ ደጋፊ በስታዲየሙ ተገኝቶ የተከታተለ ሲሆን ስፖርታዊ ጨዋነቱም የተሻለ ነበር፡፡

Published in ስፖርት

የካቲት 5/2009 ደቡብ ሱዳን ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ፤በአለም አቀፍ ደረጃ ከሶሪያና አፍጋኒስታን ቀጥሎ የስደተኞች ቀውስ የሚስተዋልባት መሆኗን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ ሪፖርት ማመልከቱን ሲጂቲን ዘገበ፡፡ 

በሃገሪቱ በተቀሰቀሰው ግጭት 1.5 ሚሊየን ሰዎች ወደ ጎረቤት ሃገራት የተሰደዱ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ባስቀመጠው ግምት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር  3.5 ሚሊየን ደርሷል፡፡

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ዊሊያም ስፒንድለር እንደገለፁት ካለፈው ሀምሌ ወር ጀምሮ 760 ሺህ ሰዎች ተሰደዋል፡፡

“ከ60 ከመቶ በላይ የሚሆኑት ስደተኞች ህፃናት ሲሆኑ ብዙዎችም አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚሹ ናቸው ፡፡ አሁን በሃገሪቱ ውሥጥ ያለው ግጭትም ዘላቂ ጉዳት የሚያስከትል ነው ብለዋል፡፡”

በየወሩም 63 ሺህ ዜጎች ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የሚገደዱ ሲሆን ከመስከረም 2016 ጀምሮ ግማሽ ሚሊየን ዜጎች ሃገሪቱን ለቀው ወጥተዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት በሰጠው ማስጠንቀቂያ በደቡብ ሱዳን ያለውን ግጭት በፍጥነት ጣልቃ ተገብቶ ማስቆም ካልተቻለ ሊባባስ ይችላል፡፡

 

Published in ፖለቲካ

ሰበታ የካቲት 5/2009 በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየው የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ውጤታማ እንዲሆን ሕብረተሰቡ በሙሉ አቅሙ የልማቱ ተሳታፊ መሆን አለበት ሲሉ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አስቴር ማሞ ተናገሩ።

ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የሰበታ ከተማ ነዋሪዎች ሲካሄድ በቆየው የጥልቅ ተሃድሶ ሂደት ዙሪያ ተወያይተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ጥልቅ ተሃድሶው የከተማዋን ነዋሪዎች መሠረታዊ ችግሮች መፍታት የሚያስችል መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት በከተማዋ ለረጅም ጊዜ የዘለቁት የውኃ፣ የኤሌክትሪክና የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮች በተሃድሶው ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።

ከከተማዋ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በመሬት ይዞታ ማረጋገጫ አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም እልባት ሊያገኙ ይገባል ነው ያሉት።

የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ እንዲሁም የሀሰት ሪፖርት ጉዳይ በከተማዋ ከሚታዩ ችግሮች መካከል ተጠቅሰዋል።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ የአመራሩ የአቅም ውስንነትና የከንቲባዎች መፈራረቅ የመልካም አስተዳደር ችግር እያስከተለ ያለ ጉዳይ ነው።

የከተማዋ ከንቲባ  ለገሰ ነጊሶ በበኩላቸው ከሕብረተሰቡ የተነሱት ችግሮች በጥልቅ ተሃድሶው የታዩና እንደ ችግሮቹ አንገብጋቢነት መፍትሄ እየተፈለገላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

የመሠረተ ለማት አቅርቦት ችግሮቹን ለመፍታት የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ተነድፎ እየተሰራ ነው፤ በአጭር ጊዜ ያለውን ውኃ በአግባቡ ለማከፋፈልም ስራ ተጀምሯል ብለዋል።

የኤሌክትሪክ አቅርቦቱን ለማሻሻልና የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግሮች ለማቃለል ቅድሚያ ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል ከንቲባ ለገሰ።

የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት በመንግስት ጥረት ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ ሙሉ ተሳትፎ ነው ያሉት ደግሞ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሏ ወይዘሮ አስቴር ማሞ ናቸው።

በተሃድሶው መንግስት ብቻ ሳይሆን ሕብረተሰቡም ራሱን ሊያጠራና ከመንግስት ጎን ሆኖ ሊታገል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

መንግስት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ራሱን አጥርቶ ከሕዝቡ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁነቱን እያሳየ መሆኑንም ገልጸዋል።

Published in ፖለቲካ

ሀዋሳ የካቲት 5/2009 በኦሮሚያ ክልል ሕዝቡን በማሳተፍ ከአመራሩ እስከ መንግስት ሠራተኛው በየደረጃው የተካሄደው ጥልቅ የተሀድሶ ንቅናቄ መድረክ ስኬታማ እንደነበር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ፡፡

የጥልቅ ተሀድሶ መድረኩ ማጠቃለያ ዛሬ በሻሸመኔ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በየደረጃው በተካሄዱ ጥልቅ የተሀድሶ ንቅናቄ መድረኮች ላይ ሕብረተሰቡ ባነሳቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ላይ የጋራ መግባባት ተደርሷል።

አመራሩ ከህዝቡ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣቱና ሠራተኛውም በአገልጋይነት ስሜት ሥራውን በአግባቡ አለማከናወኑ ህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን እንዲያነሳ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ለማ እንዳሉት፣ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የሚገኘው አመራር፣ የኦህዴድ አባልና ደጋፊ ፣ የመንግስት ሠራተኛው እንዲሁም ህብረተሰቡ በየደረጃው ባካሄደው ግምገማ በችግሮቹ ላይ በመነጋገር ለመፍትሄዎቹ የጋራ አቅጣጫ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡

በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ለሕዝብ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠትና የሕዝብ እርካታን ለማምጣት አመራሩ፣ የመንግስት ሠራተኛውና ሕዝቡ በጋራ ለመስራት መስማማታቸው የንቅናቄው ስኬት እንደነበር ገልጸዋል።

Published in ፖለቲካ

ደብረ ማርቆስ የካቲት 5/2009 የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት በአገሪቱ የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል እየሰራ መሆኑን የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ አስታወቀ።

ኮሌጅ 200 የፖሊስ እጩ መኮንኖች ትናንት አስመርቋል።

የኮሌጁ ዳይሬክተር ኮማንደር ተስፋው ብሩ እንደገለጹት በአገሪቱ የተጀመረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስቀጠል የሚቻለው ህገመንግስታዊ ስርዓቱ ተከብሮ ህብረተሰቡ በሰላምና በነጻነት ልማቱን ማከናወን ሲችል ነው።

ወንጀልን በመከላከል የህብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ በየደረጃው ያሉ የፖሊስ አመራሮችን በማፍራት ኮሌጁ የተሰጠውን ተልዕኮ በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

የፖሊስ እውቀት ሳይናሳዊና ዘመናዊ ለማድረግም በክህሎት፣ ዕውቀትና አመለካከት በማነጽ ህዝባዊና ህገ መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ የሚያስችል ስልጠና መስጠቱን ተናግረዋል።

ለተከታታይ ሶስት ወራት በንድፈ ሃሳብና በተግባር የታገዘ ፖሊሳዊና ተያያዥነት ባላቸው መርሃ ግብሮች 200 የፖሊስ አባላትን አሰልጥኖ ማስመረቁን ተናግረዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉጌታ ወርቁ ለተመራቂዎች የስራ መመሪያ ሲሰጡ እንደተናገሩት ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማስጠበቅና የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሰሲያዊ መብት ለማስከበር የፖሊስ አመራሩን ማብቃት ያስፈልጋል።

ለክልሉ እንዲሁም ለሀገር ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ለሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ ኮሚሽኑ ከተመራቂዎች ጎን በመሰለፍ ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ከተመራቂዎች መካከል ረዳት ኢንስፔክተር አምባዬ ሙሉነህ በሰጡት አስተያየት በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት፣ አመለካከትና ክህሎት ተጠቅመው ሀገሪቱ የያዘችውን ልማት በፀረ ሰላም ኃይሎች እንዳይደናቀፍ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ረዳት ኢንስፔክተር መልካም ስንሻው በበኩላቸው ''ያገኘሁትን ዕውቀት መሰረት አድርጌ በቀጣይ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የተጣለብኝን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ''ብለዋል።

ኮሌጁ ከተቋቋመበት ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ከ30 ሺህ የሚበልጡ የፖሊስ አባላትና አመራሮችን አሰልጥኖ ማስመረቁን ከኮሌጁ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

 

 

Published in ፖለቲካ

አምቦ የካቲት 5/2009 የአካባቢያቸውን ሰላም፣ ልማትና ዕድገት ለማስቀጠል ከመንግስት ጋር ተባብረው ለመስራት መዘጋጀታቸውን የምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

በሕብረተሰብ ተሳትፎና ንቅናቄ ጥልቅ ተሃድሶውን እናሳካለን በሚል መሪ ቃል በአምቦ ከተማ ዛሬ ህዝባዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ ጥልቅ ተሃድሶን መሰረት አድርገው በየደረጃው በተካሄዱ ህዝባዊ ውይይቶች አብዛኛው የህዝብ ጥያቄዎች ቢመለሱም አሁንም ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎች አሉ።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ከኖኖ ወረዳ የመጣው ወጣት እንዳለ ታከለ በአሁኑ ወቅት መንግስት ለወጣቶች በሚፈጥረው የሥራ ዕድል በማህበር ተደራጅቶ ለመስራት መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡

ወጣቶች ወደሥራ እንዲገቡ መንግስት ከፍተኛ በጀት መመደቡ ለወጣቱ የተሻለ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚያስችል ገልጾ፣ ለውጤታማነቱ ከመንግስት ጋር ሆኖ እንደሚሰራ አመልክቷል።

ከኖኖ ወረዳ የመጣችው ወጣት አታለለች አበራ በበኩሏ የሥራ ዕድል በመፍጠር የወጣቱን ችግር ለመፍታት በመንግስት የጀመረው ጥረት በወጣቶች ላይ የሥራ ተነሳሽነት እየፈጠረ መሆኑን ገልጻለች።

"መንግስት ለወጣቶች የሥራ ዕድል የመደበው ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል የበኩሌን አስተዋጽኦ አደርጋለሁ " በማለትም ተናግራለች።

ከአድአ በርጋ ወረዳ  የመጡት አቶ  ግርማ ታደሰ  በበኩላቸው መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር ባደረገው ጥልቅ የተሃድሶ ንቅናቄ ህዝቡ ያነሳቸው ጥያቄዎች በአብዛኛው ቢመለሱም አሁንም ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ቀሲስ ብርሃኑ ገብረጻዲቅ እና ወይዘሮ ሞሚና ሁሴን የተባሉ ነዋሪዎችም ከተሃድሶው በኋላ ብዙ ለውጥ መምጣታቸውን ቢገልጹም ከተሀድሶ በኋላ በወገናዊነትና በግንኙነት የሚሰሩ ሥራዎች እንዳሉ መታዘባቸውን ጠቁመዋል።

በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

ከመንግስት ጋር ተባብረው በመስራት የአካባቢያቸውን ሰላም፣ ልማትና እድገት ለማፋጠን ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ከአምቦ ከተማ የመጡት ወይዘሮ አስናቀች በቀለ ናቸው፡፡

ከጥልቅ ተሀድሶ በኋላ ከመሰረተ ልማት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጥያያቄዎች እየተመለሱ ቢሆንም በመልካም አስተዳደር በኩል አሁንም ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

መድረኩን የመሩት የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በከር ሻሌ በተሀድሶ አስፈላጊነት ላይ ሕብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ሲባል መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በተሀድሶው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው በድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ሕብረተሰቡም አምኖበት ሲሳተፍ መሆኑን የገለጹት አቶ በከር፣ በቀጣይ ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ መንግስት፣ ሠራተኛውና ሕብረተሰቡ የገቡትን ቃል ወደ ሥራ መተርጎም እንዳለባቸው አስገነዝበዋል፡፡

"ተሃድሶው መንግስት ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራና በሁሉም አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን ከማድረጉም በተጨማሪ የመንግስትን ደካማ ጎን ለመለየትና ወደፊቱን አቅታጫ ለማቀመጥ አግዟል" ብለዋል፡፡

ሕብረተሰቡ በተሃድሶው ወቅት ላደረገው የነቃ ተሳትፎና ኦህዴድ ከስህተቱ እንዲታረም ላደረገው ጥረትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የምዕራብ ሸዋ ዞን ኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክለወልድ በቀለ በበኩላቸው፣ በጥልቅ ተሀድሶው ከሕብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ 236 የዞንና የወረዳ አመረሮች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

አስተዳደራዊ እርምጃ ከተወሰደባቸው አመራሮች በህግ የሚጠየቁትን ወደህግ ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አመልክተዋል።

ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ 150 የኮሌጅ ተመራቂዎች ሥራ ማግኘታቸውንና 25 ሺህ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ሥራ ለማስገባት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋርር ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአምቦ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ የውይይት መድረክ ላይ ከስምንት መቶ በላይ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የሃማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች  የመንግስት ሠራተኞችና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

የካቲት 5/2009 ተዛማችና ድንበር ዘለል የቤት እንስሳት በሽታን በመከላከል አርብቶ አደሩን ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን የእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በሚኒስቴሩ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ መኮነን እንደገለጹት በግማሽ አመቱ በሃገሪቱ ተዛማችና ድንበር ዘለል በሽታዎችን በመከላከል የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከ78 ሚሊዮን 906 ሽህ በላይ እንስሳትን ለማከም የሚያስችል የክትባት መድሃኒት ተሰራጭቷል፡፡

በስድስት ወሩ 38 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶዝ የክትባት መድሃኒት ለማሰራጨት ቢታቀድም  በክልሎች ፍላጎት መሰረት ከእቅድ በላይ 78 ሚሊዮን 906 ሽህ 540 ዶዝ ሊሰራጭ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ይህም አንድ ዶዝ የክትባት መድሃኒት ለአንድ እንስሳ በመርፌ ወይም በጠብታ መልክ የሚሰጠው ክትባት መጠን ነው፡፡

ከ1 ሚሊዮን 131 ሽህ ሊትር በላይ የመድሃኒት መበጥበጫ ጨዋማ ውሃ መሰራጨቱንም ተናግረዋል፡፡

በስድስት ወሩ ለተከናወነው ተግባርም ከ44 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ከመንግስት ወጭ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

የክትባት መድሃኒቱ የአፍሪካ ጋማ ከብት በሽታን፣ የከብት ጉርብርብ በሽታን ፣ የግመል፣  የበግና ፍየል ፈንጣጣ በሽታን ጨምሮ ስምንት አይነት በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ከድርቁ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮችን ለመከላከልም የእንስሳት ክትባትና ህክምና ለመሰጠት ለሶማሌ ክልል፣ለደቡብ ኦሞ ዞንና ለቦረና ዞኖች የመድሃኒት ስርጭት መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በመከላከል ላይ የተመሰረተ ስጋት ተኮር የበሽታ መከላከል መሰረተ ሃሳብን እውን ለማድረግም የዋና ዋና በሽታዎችን ስርጭት የሚያሳይ ካርታ መዘጋጀቱን ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ኃብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስትሆን 57 ነጥብ 83 ሚሊዮን የዳልጋ ከብት፣ 28 ነጥብ 89 ሚሊዮን በግ፣ 29 ነጥብ 7 ሚሊዮን ፍየል እንዲሁም 1 ነጥብ 23 ሚሊዮን ግመል እንዳላት ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ጅማ የካቲት 5/2009 ጥልቅ ተሃድሶው ህብረተሰቡ ለሚያነሳው የመልካም አስተዳደር ችግር መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ለማስተካከል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የጅማ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ከዞኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ ከአንድ ሺ በላይ ነዋሪዎች ከኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር  ዛሬ በጅማ ከተማ ጊቤ አዳራሽ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ናስር አባዱራ እንደገለጹት ባለፉት አስራ አምስት አመታት ከተመዘገበው ሁሉን አቀፍ ዕድገት ጎን ለጎን የመልካም አስተዳደር ችግርና ኪራይ ሰብሳቢነት  አብሮ አድጓል፡፡

ችግሩ በተለይ በኦሮሚያና አማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር እስከመሆን ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

መንግስት ችግሩን ለመፍታት ካለው ቁርጠኛ አቋም የተነሳም አመራሩ በጥልቅ ተሃድሶ እራሱን እንዲፈትሽና የችግሮቹን መነሻ ለይቶ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

ከሊሙ ኮሳ ወረዳ የመጡት ሃጂ ሁሴን በበኩላቸው አንዳንድ አመራሮች የመንግስትን ስልጣን ለግል መበልጸጊያ መሳሪያ በማድረጋቸው ምክንያት የአገሪቱ አንድነት፣ ስላም እና ልማት አደጋ ላይ የሚጥል ሁከት እንዲፈጠር አድርጐ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

''መንግስትም በተረጋጋና ዴሞክራሲያዊ መንገድን በተከተለ መልኩ የተከሰተውን ሁከት ከማብረዱም በላይ ጥልቅ ተሃድሶ በማካሄድ አመራሩን በአዲስ መልክ ማወቀሩ ህዝባዊነቱን የሚያሳይ ነው'' ብለዋል፡፡

''ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ  በሚወጡ የተሳሰቱ መረጃዎች በመመራት የአገሪቱን እድገት ለማይፈልጉ ጸረ ሰላም ሃይሎች መሳሪያ እስከመሆን የደረስንበት ሁኔታ ተከስቶ ነበር'' ያለችው ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ኑሪያ በድሩ ናት፡፡

ለዚህ ችግር መነሻ ደግሞ በወቅቱ በየደረጃው የተመደቡ አመራሮች የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም የወጣቱን የስራ ዕድል ተጠቃሚነት ወደጎን በመተዋቸው እንደሆነም ተናግራለች፡፡

ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ በአዲስ መልክ የተደራጁ አመራሮች ለወጣቱ የልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ የሚል እምነት እንዳላት ገልጻለች፡ 

የኦሮሚያ ገቢዎች ባለስልጣን ኃላፊ አቶ አህመድ ቱሳ ውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንደተናገሩት የጥልቅ ተሃድሶ ትኩረት ''ኪራይ ሰብሳቢነትን በማክሰም መልካም አስተዳደርን አስፍኖ ልማትን ማፋጠን ነው'' ብለዋል፡፡

ይህንንም ለማሳካት የነበሩ ችግሮች ተለይተው በህዝብና በመንግስት የመፍትሄ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን አዲሱ አመራር የመንግስትን ስልጣን ህዝብን ለማገልግል ብቻ እንዲያውል የሚያስገድድ አሰራርን እንደሚከተሉም ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡም በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት ያደረገውን ተሳትፎ ለአገሪቱ ልማትና ሰላም መጠናከር የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

ከጥልቅ ተሃድሶው ጋር በተያያዘ በጅማ ከተማና በጅማ ዞን አስተዳደር 600 አዲስ  አመራሮች መመደባቸው በዚሁ ጊዜ ተገልጿል፡፡

 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን