አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Saturday, 11 February 2017

መቱ-ጅማ የካቲት 4/2009 የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የተሃድሶ ንቅናቄ መድረኮቹ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ በኢሉአባቦራና በጅማ ዞኖች አስተያየታቸውን የሰጡ የመንግስት ሰራተኞችና ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ 

በኢሉአባቦራ  ዞን አሌ ወረዳ የመንግስት ሰራተኞች ለኢዜአ  እንዳሉት ሁሉም የመንግስት ሰራተኞች በጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ  እንዲያልፉ መደረጉ ራሱን በማየት ድክመቱን ለማረም ያስችለዋል፡፡

ሰራተኛውና አመራሩ ድክመቱን በማረም  ለህብረተሰቡ በቅንነትና በአገልጋይነት መንፈስ ኃላፊነቱን ለመወጣት እድል ይፈጥራል።

የወረዳው ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ሰራተኛ አቶ ጅማ ዳኦ መድረኩ  ኪራይ ሰብሳቢነትን በማስወገድ የተጀመረውን ፈጣን ልማትና እድገት ለማስቀጠል የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተሃድሶ ንቅናቄ መድረኩ ህብረተሰቡ እንዲበደል ያደረጉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት ለመፍታትና ህዝቡን ለመካስ ያዘጋጃቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ  የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ሰራተኛ አቶ ድንቁ ገዛሀኝ ናቸው፡፡

የወረዳው ፐብሊክ ሰርቪስና የመልካም አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሰራተኛ አቶ ተሰማ ውቤ በበኩላቸው መድረኩ  ፀረ- ልማት ኃይሎች ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን  የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች  በመጠቀም ዳግም ድብቅ የጥፋት አላማቸውን እንዳያራምዱ በር የሚዘጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መምህርት ብዙነሽ በቀለ እንዳሉት የተሀድሶ ግምገማው ድክመታቸውንና ህብረተሰቡን የሚበድሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ያዩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለወደፊት ከብልሹ አሰራር ነጻ በመሆን ተገቢና ፍትሀዊ አገልግሎት ለመስጠት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ጠቅሰዋል።

የወረዳው መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ደጀኑ እንዳስታወቁት ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ የተካሄደው ጥልቅ ተሀድሶ መድረክ በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በተለይ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጡና የመልካም አስተዳደር ችግር ሲፈጥሩ በነበሩ 32 የወረዳ አመራሮች ላይ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የማድረግ ርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል።

"በህዝቡ ይሁንታ ያገኙ ፣ በትምህርት ዝግጅታቸውና በስነ-ምግባር የተሻሉ ናቸው የተባሉ 25 አዳዲስ አመራሮች እስካሁን በምትካቸው እንዲመደቡ ተደርጓል "ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በጅማ ዞን ሸቤ-ሰንቦ ወረዳ የሰበቃ ደብዬ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል  አቶ በቀለ አደራ እንዳሉት እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ እየተካሄደ ያለው ተሃድሶ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን መሰረታዊ ለውጥ ያመጣል።

እያንዳንዱ አመራርና ሰራተኛ ያለውን ጥንካሬና ድክመት ተገንዝቦ በቀጣይ ለተሻለ ስራ እንዲነሳሳ  ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ።

"ህዝቡን የበደሉና ኃላፊነታቸውን  በአግባቡ ያልተወጡ አመራሮች እንዲነሱና ተጠያቂ እንዲሆኑ ያስችላል" ብለዋል፡፡

በወረዳው የሸቤ ከተማ ነዋሪ አቶ ደኜ ታዬ በበኩላቸው ለህዝብ ብሶትና ለልማት መደናቀፍ ምክንያቱ  ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጡ  አመራሮች፣ ፈጻሚዎችና ሙያተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እየተደረገ ያለው ጥረት በአንድ ወቅት በሚደረግ ትግል የሚጸዳ ስላልሆነ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠቁመዋል፡፡

ከተሃድሶ በኋላ በከራይ ሰብሳቢነት ተግባር ውስጥ የገቡ አካላትን በመጠቆም ለህግ እንዲቀርቡ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት ለመሳተፍ  መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ በበሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ የጊቤ ቦሳ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ፈቲህ አባነጋ ናቸው፡፡

የጅማ ዞን ዋና አሰተዳደሪ አቶ አብዱልከሪም ሙሉ " ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተካሄደው የጥልቅ ተሃደሶ መድረክ ለውጥ ለማምጣት መነሳሳትን የፈጠረ ነው "ብለዋል።

Published in ፖለቲካ

ሰመራ የካቲት 4/2009 የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት እያደገ ለመጣው የአርብቶ አደሩ የልማት ጥያቄዎች  ምላሽ ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ  የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ፡፡

በክልሉ የመንግስት ሰራተኞች የተሃድሶ ንቅናቄ መድረክ ተጀምሯል፡፡

በመድረኩ ላይ  የክልሉ ርዕስ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሃመድ ሁሴን እንደተናገሩት ክልሉ ባለፉት 15 ዓመታት የአርብቶ አደሩን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

ለዚህም ውጤት  መንግስት የህብረተሰቡን ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ መነሻ አድርጎ የቀረጸዉን ፖሊሲና ስትራቴጂ  ተፈጻሚ በማድረግ የመንግስት ሰራተኛው ሚና ወሳኝ እንደነበርም አመለክተዋል፡፡

ይሁንና ፖሊሲዎቹን በሚገባ ተረድቶ ሳይሸራረፉ በሚፈለገዉ የጥራት ደረጃ በመፈፀምና በማስፈጸም በኩል ከአመራሩ እስከ  ሰራተኛው የአመለካከትና የክህሎት ክፍተቶች ነበሩ፡፡

በዚህም  ህብረተሰቡን ያረካ አገልግሎትና ልማት ከማስመዝገብ አንጻር ክፍተቶች ተሰተውለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት እነዚህን ክፍተቶች በማረም በየሴክተሩ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መነሻ የሆኑ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራትን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እልባት ለመስጠት ቁርጠኛ አቋም ይዞ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል

ሃላፊው እንዳሉት የሰራተኞች የተሃድሶ ንቅናቄ መድረክም የህብረተሰቡን እርካታ የሚፈጥሩ አገልግሎቶች ከመስጠት አኳያ የሚታዩ እንከኖች ላይ የድረሻቸውን በመውሰድ በቀጣይ የተሻለ የልማትና መልካም አስተዳደር ስኬቶችን ለማስመዝገብ መነቃቃትን ይፈጥራል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የርዕሰ መስተዳደር  ጽህፈት ቤት  ሰራተኛ አቶ መሃመድ ኖራ   መድረኩ ሁሉም ሰራተኛ ያለበትን የአመለካከት ችግር በመፍታት የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ እንዲላበስ ለማስቻል አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በተለይም ከመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ አንጻር ያለበትን የግንዛቤ ክፍተት በመሙላት የተጣለበትን ሃላፊነት በሚገባ ለመወጣት አቅም  እንደሚፈጥር  ጠቁመዋል፡፡

መድረኩ ሰራተኛውና  አመራሩ  ፊት ለፊት  ተቀምጠዉ በተቋሙ ተልእኮ ዙሪያ የታዩ አዎንታዊና አሉታዉ ጎኖችን በመፈተሽ ችግሮችን ለማረም እንደሚያግዝ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ሰራተኛ  አቶ የሱፍ እብራሂም ናቸው፡፡

ችግሮችን ፈጥኖ ለማረም  ተመሳሳይ የመወያያ  መድረኮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ለአምስት ቀናት በሚቆየው የተሃድሶ ንቅናቄ መድረክ ላይ የተለያዩ ሴክተር  መስሪያ ቤቶች  ሰራተኞች እየተሳተፉ ናቸው፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 4/2009 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለረጅም ዓመታት ላገለገሉ 202 ሰራተኞች የተለያየ የገንዘብ መጠን ያለው ቼክና የምስክር ወረቀት አበረከተ።

ሽልማቱ የተበረከተው ከ25 ዓመታት በላይ የአገልግሎት ዘመን ላስቆጠሩና በጡረታ ለተገለሉ ነው።

ዕድሜያቸው ለጡረታ በመድረሱ ከተሰናበቱት መካከል ተቋሙን ወክለው ያገለገሉ የሴኔጋል፣ ቶጎ፣ እስራኤል፣ ናይጄሪያ፣ እንግሊዝ እና ህንድ ሠራተኞች ይገኙበታል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንዳሉት ሰራተኞቹ ለድርጅቱ ስኬት የድርሻቸውን አበርክተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል ላበረከቱት አስተዋፆ የሚሰጣቸው ከበሬታ እና እውቅና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ሰራተኞቹ በበኩላቸው ለተበረከተላቸው ሽልማት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

Published in ማህበራዊ

ሽሬእንዳስላሴ የካቲት 4/2009 የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ  ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የሚገኙ የኩናማ ብሔረሰብ ተወላጆች  ገለጹ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ በልማትና ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ከብሔረሰቡ ተወካዮች ጋር ትናንት  በሽራሮ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

ከብሔረሰቡ ተወላጆች መካከል የ57 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ አቶ ብርሃነ ኬኙ እንደገለጹት አርብቶ አደር እንደመሆናቸው ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ኑሯቸውን ይገፉ ነበር፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ በአንድ አካባቢ ተረጋግተው መኖር እንደጀመሩና  ልጆቻችንን በአግባቡ  ለማስተማር መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላው የብሔረሰቡ ተወላጅ ወይዘሮ አኬል አሚኖ በበኩላቸው፣ "በልማት እንቅስቃሴ በስፋት እድንሳተፍ ምቹ ሁኔታ  ተፈጥሮልናል"ብለዋል።

በዚህም ተጠቅመው  በዶሮ እርባታ በመሰማራት ውጤታማ መሆናቸውና ልጆቻቸው በአግባቡ በማስተማር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

የብሄረሰቡ ተወካዮች አሉብን ያሉትን ችግሮች በማንሳት ከርዕሰ መስተደድሩ ጋር  ተወያይተዋል፡፡

ካነሷቸው ችግሮች መካከል በቋንቋቸው እንዲማሩ  ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸው ቢሆንም   በኩናምኛ  ቋንቋ የሚያስተምሩ የመምህራን እጥረት እንዳለባቸው የጠቀሱት ይገኝበታል፡፡  

ርዕሰ መስተዳደር አባይ ወልዱ በበኩላቸው የብሔረሰቡ ተወላጆች በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ያረጋገጡትን ሰላም  ኑራቸውን ለማሻሻል መጠቀም እንዳለባቸውን ተናግረዋል፡

ከሌለው የክልሉ ህዝብ ጋር  ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውና ተሳትፏቸውን እኩል እንዲረጋገጥ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡

በዚህም ተጠቅመው  በተለይ የብሔረሰቡ አባላት እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆቻቸውን ለማስተማር  መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ያለባቸውን የመምህራን  እጥረት ለማቃለል በተለይ ከአንደኛ እስከ የአራተኛ ክፍል የሚያስተምሩ መምህራን በስፋት እንዲሰለጥኑ እንደሚደረግ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

" በሌላ አካባቢ ያሉት የብሔረሰቡ ተወላጅ መምህራን ወደ አካባቢ በማዛውር ብሔረሰቡ በአፍ መፍቻ ቋንቋው እንዲማር ይደረጋል"ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት አሥርኛ ክፍል ያጠናቀቁ የብሔረሰቡ ወጣት ሴቶች በጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ በልዩ ሁኔታ በማስልጠን ብሄረሰቡን የሚያገለግሉበት ሁኔታ ይመቻቸል፡፡

ያለባቸውን የመንገድ ችግር ለመፍታትም በሚመለከተው አካል ተጠንቶ በቅርቡ ግንባታው እንደሚጀመርም  ጠቁመዋል፡፡

የብሄረሰቡ ባህል፣ቋንቋና የአኗኗር ዘይቤው ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ታስቦ ለተገነባው ሙዚየም ማጠናከሪያ  የክልሉ መንግስት  ግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል፡፡ 

በሀገሪቱ   ሰላም፣ልማትና ዲሞክራሲ እንዲረጋገጥ በተካሄደው የትጥቅ ትግል የኩናማ ብሔረሰብ ተወላጆች ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸውም ተመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 4/2009 አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ አሳሰቡ፡፡

ፕሬዝዳንቱ አዲስ ለተሾሙ ስምንት አምባሳደሮች በተዘጋጀ የሽኝት ፕሮግራም ላይ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት አምባሳደሮች በሚሔዱባቸው አገራት ቀድሞ የነበረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ለአገራቸው ጥቅምና ዕድገት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

አምባሳደሮቹ ከአገራቱ ጋር ያለው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ ፣ የዲፕሎማሲ፣ የመግባባትና የወዳጅነት ግንኙነት እንዲቀጥል ከማድረግ ባሻገር ግንኙነቱን በማሳደግም የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ እንደሚገባቸው ነው ያመለከቱት፡፡

ከዚህ ባለፈም አዲስ የግንኙነትና የወዳጅነት ምዕራፍ እንዲኖራቸው ጠንክረው መስራት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

ከተሿሚዎች መካከል አቶ ሬድዋን ሁሴን በአየርላንድ፣ ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ ኢጣልያ፣ አቶ ቶሎሳ ሻጊ ኡጋንዳ፣ አቶ ፀጋዬ በርሄ እስራኤል እና አቶ ረጋሳ ከፍአለ በጋና የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ያገለግላሉ፡፡

በተጨማሪም አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በግብጽ፣ አቶ አብዱልአዚዝ አህመድ በኩዌት እንዲሁም አቶ ግርማ ተመስገን ደግሞ በኮትዲቯር የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ስራቸውን ያከናውናሉ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ "የአገሪቱን የልማት ጉዞ የማስቀጠሉ ስራ በውስጥ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም የውጭ መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች ያላቸው ተጽዕኖም ቀላል አይደለም" ብለዋል፡፡

ስለሆነም ከውጭ የሚመጡ መልካም ዕድሎችን የመጠቀምና ተግዳሮቶችን በጥበብ የመሻገር ኃላፊነት በዋናነት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በስሩ በሚገኙ ኤምባሲዎች ትከሻ ላይ የወደቀ ነው በማለት ነው የገለጹት፡፡

በዛሬው የሽኝት ስነ-ስርዓትም ተሿሚ አምባሳደሮች የተጣለባቸውን የሕዝብና የመንግስት አደራ በብቃት ለመወጣት ተጨማሪ አቅምና መነሳሳት የሚፈጥርላቸው እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ እየተፈጠረ ካለው ተለዋዋጭና አስቸጋሪ ግንኙነት አንፃር አዳዲስ አሰራርና አካሔድን በመከተል የአገሪቱን ጥቅሞች ለማረጋግጥ ተሿሚ አምባሳደሮች ጠንክረው መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡

Published in ፖለቲካ

         እንግዳ መላኩ /ኢዜአ/

እኤአ በ1991 የአምባገነኑ ሰይድ ባሬ አስተዳደር ከተወገደ ጀምሮ የሃገሪቱ ፖለቲካ መረጋጋት እንደተሳነው ሩብ ምዕት ዓመት ያህል ተቆጥሯል፡፡

ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም የሃገሪቱን ፖለቲካ ለማረጋጋትና ሰላምና ደህንነቷን ለማረጋገጥ የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርግም የሚጠበቀውን ያህል ባለመሆኑ ዜጎቿ ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠው ቆይተዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያስረዳው የእርስ በእርስ ጦርነቱን ተከትሎ እስከ 2016 ድረስ 975 ሺህ 951 ዜጎች ወደ ጎረቤት ሃገራት ተሰደዋል፡፡ 1ነጥብ1 ሚሊዮን ተጨማሪ ሶማሌያውያን ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

የሀገሪቱ መንግሥት አልባነት  የዓለም ዓቀፍ አሸባሪዎችን ቀልብ እንድትስብ አድርጓታል፡፡ አሸባሪ ቡድኖቹ  እንደፈለጉ ለመደራጀትና ጥቃቶችንም ለመሰንዘር ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሮላቸው ቆይተዋል፡፡

የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት ሞቃዲሾንና ደቡባዊውን የሃገሪቱ ክፍል በቁጥጥሩ ስር ማዋሉን ተከትሎ እንቅስቃሴውን ለመግታት ከሁሉም በፊት ኢትዮጵያ መከላከያ ኃይሏን ወደ አካባቢው ልካለች፡፡ የኢትዮጵያን ፈለግ ተከትሎ ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት ጦሩን አዝምቷል፡፡

እኤአ በ2006 ዓ.ም የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ሕብረት ደቡባዊውን የሀገሪቱ ክፍል ተቆጣጥሮ የሸሪያ ህግን እስከ መተግበር ቢደርስም የሶማሊያ ሽግግር መንግስትና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጥምረት የሰነዘሩበትን ጠንካራ ጥቃት መቋቋም ባለመቻሉ በታናናሽ አንጃዎች ለመከፋፈል ግድ ሆኖበታል፡፡

የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት ተቀጽላ እንደሆነ የሚነገርለት አልሻባብ እኤአ በ2012 ዓ.ም አልቃኢዳን መቀላቀሉን ይፋ ቢያደርግም ውህደቱን በተመለከተ የተወሰኑ የቡድኑ መሪዎች ከአልቃኢዳ ጋር መግባባት ባለመቻላቸው ውህደቱ ሳይሰምር ቀርቷል፡፡

ያም ቢሆን ቡድኑ “ጸረ እስላም” ባላቸው አካላት ላይ ሃይማኖታዊ ጦርነት ያወጀ ሲሆን የሽግግር መንግሥቱንና በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮን /አሚሶም/ እንደሚፋለምም ይፋ አድርጎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ኢትዮጵያ ሶማሊያን ከአሸባሪ ቡድኑ ለማላቀቅና የሃገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ በግንባር ቀደምትነት በመንቀሳቀስ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተሻለ ውጤት ማግኘት ተችሏል፡፡

አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬት፣ እንግሊዝና አሜሪካም ቡድኑን በአሸባሪነት ፈርጀውታል፡፡

አልሻባብ እስከ 2014 ዓ.ም ከሰባት እስከ ዘጠኝ ሺህ በሚደርሱ ታጣቂዎቹ በርካታ የሃገሪቱን ከተሞች በቁጥጥሩ ስር ቢያደርግም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከከተሞች በማፈግፈግ እንቅስቃሴውን በተወሰኑ የሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ለማድረግ ተገድዷል፡፡

ሶማሊያ ከገጠማት ፖለቲካዊ ቀውስ ሙሉ ለሙሉ ለማገገም የዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሚያሳዩ ምልክቶች ቢኖሩም ተደራራቢ ችግሮችን ተራምዳ መንግሥት ለመመስረትና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ መብቃቷ ግን የሀገሪቱን መጻኢ ብሩህ ተስፋ ያሳያል፡፡

የ2017ቱ የሶማሊያ ብሔራዊ ምርጫ የካቲት 1 ቀን 2009 ዓ.ም በሶማሊያ አስተማማኝ ደህንነት ባለበት አደን አዴ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ተካሂዷል፡፡

በምርጫው የተሸነፉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼኽ ሞሃሙድም ስልጣናቸውን ለአዲሱ ፕሬዝዳንት በሰላማዊ መንገድ አስረክበዋል፡፡

የ55 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ከመደበኛው ስማቸው ይልቅ የሚታወቁት ፋርማጆ በሚለው ቅጽል ስማቸው ነው፡፡ ፋርማጆ ማለት አይብ እንደ ማለት ነው፡፡

የአራት ልጆች አባቱ በሳል ዲፕሎማት፣ የሀገሪቱ የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ከአክቲቪስት ቤተሰብ የተወለዱት እኚሁ ፖለቲከኛ ታሪክና ፖለቲካል ሳይንስ ባጠኑባት አሜሪካ ወጣ ገባ እያሉ ኑሯቸውን አዚያው አድርገውም ነበር፡፡

የሰይድ ባሬ የስልጣን ዘመን ከማብቃቱ በፊት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በአሜሪካ የሶማሊያ አምባሳደር ሆነውም  ሰርተዋል፡፡ የሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እስከሆኑበት ድረስ ደግሞ ኒዮርክ ውስጥ በተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ሰርተዋል፡፡

በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሂደቱ ላይ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረውን የከረረ ግጭት ተከትሎ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን እስከ ለቀቁበት 2011 ዓ.ም ድረስ ደግሞ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል፡፡

ፋርማጆ ስልጣናቸውን ለቀው የምርጫው ሂደት እንዲራዘም ከስምምነት ላይ የደረሱት የሶማሊያውያንን ፍላጎት ለመጠበቅና የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደነበርም ተነግሯል፡፡

በ2012 መጀመሪያ ከቀድሞ ካቢኔያቸው ጋር በመሆን ታዮ (እኩልነት) የተሰኘውን የፖለቲካ ፓርቲ መስርተዋል፡፡

ፓርቲያቸው “ የሀገሪቱ ዳያስፖራ በሀገሪቱ ድህረ ግጭት የግንባታ ሂደት ድጋፍ ማድረግ የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት” ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ በፌስቡክ ገጻቸው ይፋ ማድረጋቸውም አይዘነጋም፡፡

የፋርማጆ አሸናፊነት ሲታወጅ  “ይህ ለሶማሊያ ዜጎች የአንድነት መጀመሪያ ነው፤ ይህ አልሻባብንና ሙስናን ለመዋጋት መሰረት ነው፡፡” የሚል በተስፋ የተሞላ ንግግር አድርገዋል፡፡

ሶማሊያ የ2017ቱንና የ2012ቱን ምርጫዎች በሃገሪቱ ዓለምዓቀፍ አውሮፕላን ጣቢያና በፖሊስ አካዳሚ እንዲሁም የ2007ቱንና የ2004ቱን ምርጫዎች በቅደም ተከተል ኬንያና ጂቡቲ ውስጥ አካሂዳለች፡፡

ምንም እንኳን በሀገር ውስጥ የተከናወኑት ምርጫዎች በከባድ የጸጥታ ቁጥጥር ውስጥ ቢሆንም በሌላ ሀገር ከሚካሄድ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር ግን የተሻለ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ አሁን የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የሀገሪቱን ብሔራዊ ጦር ለማጠናከር በሀገሪቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች ግዳጅ ላይ ከሚገኘው የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ጦር ውጪ ሶማሊያን ማሰብ ለብዙዎቹ ህልም ነው፡፡

አዲሱ ፕሬዝዳንት የአልሻባብን ጉዳይ ጨምሮ በርካታ ችግሮች ከፊታቸው ተደቅነውባቸዋል፡፡ በሃገሪቱ የተንሰራፋው ሙስና፣ድህነትና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም ሌሎች የፋርማጆ ፈተናዎች ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ አዲሱ ፕሬዝዳንት ሀገሪቱ የተጋረጡባትን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ለመቅረፍ ዓለም ዓቀፉን ማሕበረሰብና  ከምንም በላይ ደግሞ የሃገሪቱን ሕዝብ ከጎናቸው አሰልፈው ያላሳለሰ ጥረት ማድረግ ከቻሉ ችግሮቹ የማይቀረፉበት ምክንያት የለም፡፡

በኢትዮጵያና በሌሎች ጎረቤት ሃገራት፣በአፍሪካ ህብረትና በዓለማቀፉ ማህበረሰብ ጥረትሃገሪቱ ለዘመናት ከነበረችበት አስከፊ ግጭትና ጦርነት እንዲሁም መንግስት አልባነት ተላቃ ባለፉት ጥቂት ዓመታት   ወደተሻለ ሰላምና መረጋጋት በመምጣት በተመረጠ መንግስት መተዳደር መጀመሯ ለሰውየው መልካም አጋጣሚ ነው።

በሀገሪቱ ለዓመታት የዘለቁት ችግሮች የሶማሊያውያንን መጻዒ ብሩህ ተስፋ እንዳላጨለሙት የምርጫው ውጤት ይፋ በሆነበት ዕለት ካሳዩት ስሜት ለመረዳት አያዳግትም፡፡ የፋርማጆን አሸናፊነት የሰሙ በሺዎች የሚቆጠሩ የመዲናዋ ነዋሪዎች ደህንነታቸው ሳያሳስባቸው እየዘመሩ መንገዶችን አጥለቅልቀዋል፡፡ ሶማሊያውያን ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባትን ሌላኛዋን ሶማሊያ የማየት ጉጉታቸውን በአደባባይ አሳይተዋል፡፡

አሁን በሃገሪቱ ያለው አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም  ፖለቲካዊ ብስለተታቸው በህዝቡ ዘንድ ካላቸው ተቀባይነት ጋር ተዳምሮ ፕሬዝዳንቱን ለስኬት ያበቃቸዋል የሚሉ አስተያየቶችተሰንዝረዋል።

ፋርማጆም እንዲሁ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች የተተበተበች  ሀገራቸውን ከገባችበት ማጥ የማውጣቱ ነገር ብርቱ ጥረት የሚጠይቃቸው ቢሆንም “ይሳካልኛል”  የሚል ተስፋ መሰነቃቸውን በአደባባይ  ተናግረዋል፡፡ በእርግጥ ይሳካላቸው ይሆን?

Published in ዜና-ትንታኔ

አዲስ አበባ የካቲት 4/2009 በፌደራል መንግሥትና በክልሎች መንግሥታት መካከል የሚፈጠሩ የግንኙነት ክፍተቶችን ለማስተካከል የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ የማውጣት ተግባር መከናወን እንዳለበት ተገለጸ።

የፌደራልና አርብቶአደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስቴር በመንግሥታት ግንኙነት የፖሊሲ ማዕቀፍ  በተዘጋጀው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ተወያይቷል።

በውይይቱ ወቅት እንደተገለጸው፤ በፌዴራል መንግሥትና በክልል መንግሥታት መካከል ባለው የእርስ በእርስ ግንኙነት ክፍተት ይታይበታል።

የግንኙነቶቹ ክፍተት መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ አሠራሮችን ገቢራዊ በማድረጉ በኩል መሆኑን ነው ተወያዮቹ ያብራሩት።

እነዚህን ክፍተቶች ለማስተካከልና ግንኙነቱን የተሳለጠ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት የግድ ይላል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አሰፋ ፍስኃ በወቅቱ ባቀረቡት ጥናት እንደገለጹት፤ በፌዴራሊዝም የመንግሥት አወቃቀር መሰረት መደበኛ የግንኙነት የአሰራር ሥርዓት አለ።

ይህን ግንኙነት በሕግ አስደግፎ ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ባረጋገጠ መልኩ ተግባራዊ አለመደረጉን  ነው የገለጹት።

በክልሎች የእርስ በእርስ ግንኙነቶች መንግሥታት ያላቸውን ማንነትና ባህል እንዲወራረሱ በማድረግ ረገድም ክፍተት በመኖሩ የጋራ እሴት በመገንባት ረገድ “ጫና አሳድሯል” ብለዋል።

በውይይቱ ወቅት የፌዴራሉ መንግሥት የክልሎችን ሥልጣን በማይጋፋ መልኩ የክልሎች ሕጎችና ደንቦች እርስ በእርሳቸው ተጣጥመው እንዲሄዱ ለማስቻል የተዘጋጀ የፖሊሲ ማዕቀፍ ቀርቧል።

በውይይቱ የታደሙ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይ ጸሃዬ በፖለሲ ሰነዱ የተካተቱት ጉዳዮች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ለማድረግ "ወደ ሕግ መቀየር አለበት" ብለዋል።

ይህ ካልሆነ በረቂቁ በመንግሥታት ግንኙነት የተጠቀሱት አበይት ጉዳዮች ተፈጻሚ ሳይሆኑ ወረቀት ላይ ብቻ ተጽፈው ሊቀሩ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ነው አቶ አባይ የተናገሩት።

ሌላው የመድረኩ ታዳሚ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ አማካሪ ዶክተር ፋሲል ናሆም በበኩላቸው፤ ረቂቅ ፖሊሲው በመንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት ከገንዘብ አኳያ አዋጪ በሆነ መልኩ መቃኘት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በመንግሥታት መካከል ያለውን ወቅታዊ የግንኙነት ችግር ለመፍታት የሚያስችልና ወደፊት ከፌዴራሊዝም አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ሊነሱ የሚችሉ ችግሮችን የሚያመላክት መሆን እንዳለበትም አስተያየት ሰጥተዋል።

ግንኙነቱ በሕግ አግባብ የተቃኘና በርግጥም በተግባር ሊታይ የሚችል አሰራር መዘርጋት የሚያስችል ሕግ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ውይይቱን የመሩት የፌዴራልና አርብቶአደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስትር ካሳ ተክለብርሃን በበኩላቸው በረቂቅ ፖሊሲው ውስጥ፣ ፖሊሲና ሕግ መሆን የሚገባቸው ጉዳዮች መለየት አለባቸው ይላሉ።

ከፍ ሲልም ረቂቅ ፖሊሲውን ወደ ሕግ ለመቀየር የአገሪቷን ሕገ-መንግሥት መነሻ በማድረግ የሕግ ጉዳዮችን በግልጽና በማያሻማ መልኩ አብራርቶ ማቅረብና ማመላከት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ረቂቁ ወደ ሕግ ሲለወጥ በሕገ-መንግሥቱ መሰረት በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ማጎልበት በሚቻልበት አግባብ የተቃኘ ሕግ ማውጣት  እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት። 

ረቂቅ ፖሊሲው የመንግሥታትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የማድረስ አስተዋጽኦው የጎላ እንደሆነም አስረድተዋል። 

ዶክተር አሰፋ ፍስኃ ረቂቅ ፖሊሲውን መሰረት አድርገው "የአገሪቷ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በአግባቡ እንዲተገበር በመንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት ሊሰተካከል ይገባል" ብለዋል።

ይህም በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት የተሳለጠ ለማድረግ በሕገ-ደንብ ላይ የተመረኮዘ መሆን እንዳለበትና  ውይይቶች ለማድረግ ጠቃሚ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የተዘጋጀው ረቂቅ ፖሊሲ ይህንና ሌሎች በጋራ ጉዳዮች መግባባት ለመፍጠር እንዲሁም የመንግሥታት ግንኙነቶችን፣ የግንኙነቱን ተጠሪ ተቋማትንና አደረጃጀትን በመወሰን ሚናው ላቅ ያለ መሆኑን ጠቁመዋል።

የመንግሥታት ግንኙነት በፌደራል መንግሥት አወቃቀር ይበልጥ ግልጽና ተጠያቂነት ባሰፈነ መልኩ ማስቀመጥና በጋራ መሥራት የሚያስችል ምቹ መደላድል ያስገኛልም ነው ያሉት።

ይህም የአገሪቷን የፌደራሊዝም ሥርዓት እንደሚያዳብረው በመጠቆም።

ረቂቅ ፖሊሲው በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ወደ ሕግ ይለወጣል ተብሏል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 4/2009 ህብረተሰቡ በስኳር ሕመም ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት እንዲተባበሩ የኢትዮጵያ ስኳር ሕመም ማኅበር ጥሪ አቀረበ።

ማኅበሩ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከሕክምና ባለሙያዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የስኳር ህመምን በመከላከል ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ400 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የስኳር ሕመም ተጠቂዎች ሲሆኑ 800 ሺህ ህጻናት ደግሞ በየዓመቱ ለስኳር ሕመም ይጋለጣሉ።

የስኳር ሕመም የጾታ፣ የዕድሜና የኢኮኖሚ ልዩነት ሳይወስነው በዓለም ዙሪያ ላሉ ሕዝቦች የጤና ስጋት ከሆነ ሰነባብቷል።

በውይይቱ ላይ የስኳር ሕመም በኢትዮጵያ ከፍተኛ የጤና ችግር ቢሆንም ሕመሙ እንደሌሎች በሽታዎች ትኩረት ያልተሰጠው መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ስኳር ሕመም ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ረጃ እንዳሉት ''በርካታ ሕብረተሰብ የስኳር ሕመም የአውሮፓውያንና ያደጉ አገራት ችግር እንደሆነ ያስባል''።

በመሆኑም በትኩረት ማጣት ምክንያት የበርካታ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ባለው የስኳር ሕመም ላይ ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ሊደረግበት ይገባል ብለዋል።

ከሁሉም በላይ በህጻናት ላይ የሚስተዋለው የስኳር ሕመም ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ ትኩረት እንዳልተሰጠው አስረድተዋል።

በተለይም ኅብረተሰቡ በአንድነት ሊዘምትበትና ስለ ሕመሙ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው ሁሉም ባለድርሻ አካለት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ማህበሩ ላለፉት አራት ዓመታት ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሆን በህጻናት ላይ የሚከሰተውን የስኳር ሕመም ለመከላከል ሲሰራ ቆይቷል።

ማህበሩ በአፍሪካ ሕመሙን ለመከላከል የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርገው 'ቼንጂንግ ዲያቤትስ ኢን ቺልድረን' ከተሰኘው ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ አግኝቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱም ከ3 ሺህ 500 በላይ ህጻናት 'የኢንሱሊን' አቅርቦት በማሟላት የህጻናትን ህይወት መታደግ መቻሉን ተናግረዋል።

በሐዋሳ፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ መቀሌና በሌሎችም የዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች በማህበሩ አማካኝነት ለስኳር ሕመም ተጠቂ ህጻናት የመድሃኒትና የጤና እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በውይይት መድረኩ የስኳር ሕመም በህጻናት ላይ እያደረሰ ያለው አካላዊ፣ ስነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተገልጸዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 4/2009 በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከትና ግርግር ጉዳት የደረሰባቸው ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲመለሱ መንግስት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽነሩ አቶ ፍጹም አረጋ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ጉዳት የደረሰባቸው የኢንቨስትመንት ተቋማት በፍጥነት አገግመው ወደ ስራ እንዲመለሱ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል።

ከዚህ ውስጥ ባለሃብቶች ከውጭ የሚያስገቧቸው ዕቃዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲስተናገዱ ማድረግ፣ ባለሃብቶቹን ማወያየት፣ በቀጣይ ችግሮች እንደማይገጥማቸው ማሳመንና የገንዘብ ድጋፍ ይገኙበታል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር በመቀልበስ ረገድ ትልቅ እገዛ ማድረጉንና ባለሃብቶቹም ያለስጋት እንዲንቀሳቀሱ ዋስትና መሆን እንዳስቻለ አቶ ፍጹም ጠቁመዋል፡፡

በተደረገላቸው ድጋፍ መሠረትም በአማራ ክልል ባህርዳር ዙሪያ ያሉ የአበበ እርሻ ልማቶችና በኦሮሚያ ክልል ሰበታ አካባቢ ያሉ የኢንቨስትመንት ተቋማት ከጥቂቶቹ በስተቀር ወደ ስራ ተመልሰዋል።

ተቋማቱ ከፈጠሩት የስራ ዕድልና ለአገር ዕድገት ካላቸው ፋይዳ አንጻር መንግስት ቅድመ-ሁኔታ ሳያስቀምጥ እስካሁን 100 ሚሊዮን ብር በመደገፍ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ አድርጓል ነው ያሉት።

ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ ባለሃብቶቹ በየዕለቱ የሚገጥማቸውን የኤሌትሪክ፣ የውኃና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች ለሟሟላት የቅርብ ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ነው ኮሚሽነሩ ያብራሩት።

በአሁኑ ወቅት ችግሩን አስመልክቶ ጥናቶች እየተካሔዱ ሲሆን በመንግስት የሚደረጉ የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ ሌሎች እገዛዎች ቀጣይ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኮሚሽኑ ባለፉት ስድስት ወራት ባለሃብቶችን የሚያስተናግድበትን አሰራር በመቀየሩ ፍሰቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ሆኗል።

''ከዚህ በፊት ኢንቨስተር ነኝ ያለውን ሁሉ እንቀበል ነበር፣ አሁን ግን በየትኛው ዘርፍ ለመሰማራት እንደሚፈልግ፣ ምን ያህል ካፒታል እንዳለው በአግባቡ ከተረጋገጠ ነው የምንቀበለው'' ብለዋል።

ይህ መሆኑ በኢንቨስትመንት ፍሰቱ ላይ መጠነኛ ቅናሽ ቢያስከትልም በግማሽ ዓመቱ ለማሳካት ከታቀደው 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ  1 ነጥብ 2  ቢሊዮኑ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ነው የገለጹት።

ይህ አካሄድ ጉዳት እንደሌለው የሚጠቅሱት ኮሚሽነር ፍጹም በዓመቱ መጨረሻ ዕቅዱን ለማሳካት ተስፋ ሰጪ ዕድሎች መኖራቸውን አብራርተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 4/2009 በምርቶቻቸው ላይ እሴት ጨምረው ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ምርት ላኪ ኅብረት ሥራ ዩኒዬኖች ገለጹ።

የጨርጨር ኦዳ ቡልቱ ሁለገብ የገበሬዎች ማኅበር ዩኒዬን በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በግብርና ግብዓትና ቴክኖሎጂ፣ በሸማቾች ፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦቶችና በውጭ ግብይት ተግባራት ላይ የተሰማራ ነው።

ከ12 ዓመታት በፊት በ714 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የተመሰረተው ይህ ዩኒዬን በአሁኑ ወቅት የአባላቱን ቁጥርና የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት የካፒታል አቅሙን ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ አሳድጓል።

ዩኒዬኑ የአካባቢውን አርሶና አርብቶ አደሮች ተጠቃሚ ከማድረጉም ባሻገር ጥራት ያለው የሐረር ቡና ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ በውጭ ግብይት ባስመዘገበው ውጤት ከጃፓን የጥራት የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል።

የዩኒዬኖች ሥራ አስኪያጅ አቶ ንጉሴ ለገሰ እንደሚሉት ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ችሏል።

ዩኒዬኑ ለአባላቱ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት የተሻለ ጥራት ያለው ቡና ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንም ተናግዋል።

"ዩኒዬኑ ከዚህ በፊት ካደረጋቸው ግብይቶች ልምዶችን በመውሰድ የተደራሽነት አድማሱን ለማስፋት፣ አገራት በሚፈልጉት መልኩ ቡና ላይ እሴት በመጨመር የተቀነባበረ ቡና ለማቅረብ የማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው" ብለዋል።

በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኘው ፀሐይ ኃላፊነቱ የተወሰነ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒዬን ደግሞ በግብርና ግብዓት አቅርቦት፣ በግብርና ምርቶች ግዢና ሽያጭ፣ በእንስሳት መኖ ማቀነባበር፣ በፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦትና የሰሊጥ ምርትን ወደ ውጭ በመላክ ላይ ነው የተሰማራው።

የዩኒዬኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው ይሁን እንደገለጹት ዩኒዬኑ አቅሙን ለማጎልበት በ50 ሚሊዮን ብር የምግብ ዘይት ፋብሪካ እያስገነባ ሲሆን በምርቶቹ ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ነው። 

ዩኒዬኑ ከሰሊጥና ኑግ ምርት በተጨማሪ በሱፍ፣ በተልባ፣ በጎመን-ዘር፣ በኦቾሎኒ የቅባት ሰብሎችና በጥጥ ምርት የውጭ ግብይት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አቶ እንዳልካቸው ገልጸዋል።

ዩኒዬኑ በአፍሪካ ገበያ ለመሳተፍ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሰው የበቆሎ ምርትን ወደ ኬንያ መላክ መጀመራቸውንና በቅርቡም 100 ሺህ ኩንታል በቆሎ ለመላክ ስምምነት ላይ መድረሱን ለአብነት አንስተዋል።

በምርቶቹ ላይ እሴት በመጨመር ጥራት ያለው ምርት ለውጭ ገበያ በመላክ ከውጭ የሚገኘውን ምንዛሪ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በበኩሉ ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ከሚሰጠው የቁጠባና የብድር አገልግሎት ባሻገር ከማኅበራቱ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ባንኩ በኤግዝረሚትና በዓለም አቀፍ የሐዋላ አግልግሎት የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ መሆኑንም እንዲሁ።

የባንኩ የስትራቴጅክና የለውጥ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ ሊቆ ቶሎሳ እንደገለጹት በውጭ ግብይት በመሳተፍ የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ ያሉ የኅብረት ሥራ ዩኒዬኖች የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ እየሰራ ነው።

ወደ ውጭ ምርቶቻቸውን የሚልኩ መሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒዬኖችን ጨምሮ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ 300 የኅብረት ሥራ ማኅበራት በአራተኛው አገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚዬም ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የውጭ ግብይት ድርሻን ለማሳደግ ወደ ውጭ የሚላኩ የምርት ዓይነቶችን በብዛትና በጥራት በመጨመር የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተግተው እንዲሰሩ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን