አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 10 February 2017

አዲስ አበባ የካቲት 3/2009 የአፍሪካ ቀዳማዊት እመቤቶች የሴቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በአህጉሪቷ ሁለንተናዊ እድገት ለማምጣት በጋራ እየሰሩ መሆኑን ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ገለጹ። 

ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ሴቶች ለአህጉሪቷም ሆነ ለአገሮቻቸው እድገት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆኑና የጾታ አኩልነትም አለመስፈኑን ተናግረዋል።

የሴቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጡ ኃላፊነት የሴቶች  ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመንግስታትም አጀንዳ እንዲሆን የቀዳማዊት እመቤቶች ማህበር ተጽዕኖ የመፍጠር ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

"ሴቶች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ለሚያስገድዱ ችግሮች ትኩረት በመስጠት ማህበሩ መፍትሄ ይፈልጋል" ነው ያሉት ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ።

መንግስታት ለሴቶች ኢኮኖሚያዊ እድገት በጀት እንዲመድቡ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።  

ቀዳማዊት እመቤቶቹ የሴቶችን የንግድ ክህሎት ለማሳደግ ፕሮግራሞችን ቀርፀው ስልጠና የሚያገኙበትን መንገድ እያመቻቹ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

"መሪዎች ለጾታ እኩልነት ትኩረት እንዲሰጡ ግፊት እናደርጋለን" ሲሉም አክለዋል።

የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማሳደግ የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ቀዳማዊት እመቤቶቹ "ቅድሚያ ሰጥተን እንሰራለን" ብለዋል።

የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቀደም ሲል የተሰሩ ስራዎች የሚፈለገውን ውጤት ባያስገኙም ጥረቱና ጅምሩ መቀጠሉን አመልክተዋል። 

"የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ኃላፊነት ላይ ያለን ሴቶች ድምጻቸው ያልተሰማ እህቶች ዕድሉን እንዲያገኙ የነቃ ተሳተፎ ልናደርግ ይገባል" ብለዋል ቀዳማዊት እመቤቷ።

ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የወጡ ፕሮግራሞች ተፈጻሚ እንዲሆኑ "ግንዛቤ የመፍጠር፣ የመቀስቀስና ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል" ሲሉም አስገንዝበዋል:: 

የአፍሪካ ቀዳማዊት አመቤቶች ማህበር አህጉሪቷን ከኤች.አይ.ቪ ኤድስ ነጻ ለማድረግ፣ የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ፣ ሴቶችን ለማብቃትና እኩልነታቸውን ለማረጋገጥ ላለፉት 15 ዓመታት ሲሰራ ቆይቷል።

Published in ማህበራዊ
Friday, 10 February 2017 23:28

የአፍሪካ ትስስር ጅማሮ

ከሰለሞን ተሰራ /ኢዜአ/

ከጅቡቲ መዲና የተነሳው ባቡር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያሉትን ታላላቅ ሰዎች አትኩሮት መሳቡ የተነገረው ባለፈው ወር አካባቢ ነበር፡፡በጅቡቲ የባህል ድምፃውያን የታጀበውና የአፍሪካና የአውሮፓ ዲፕሎማቶች የተካፈሉበት የምረቃ ስነስርአት ደማቅ እንደነበረ የዘገበው ቻናል አይ አር ኦንላይን ድረ ገፅ ነው፡፡

 “ለአገራችን ህዝብና መንግስት ኩራት ሲሆን ታሪካዊነቱ ደግሞ የማያጠያይቅ ነው“ በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ በወቅቱ መናገራቸውን አስታውሷል፡፡በአፍሪካ በኤሌክትሪክ ሐይል የሚሰራ ባቡር የመጀመሪያ  ጉዞውን የሚያደርገው ወደ አዲስ አበባ ነው፡፡“ ይህ መስመር የሁለቱን አገራት የማህበራዊና የኢኮኖሚ ነባራዊ ሁኔታ የሚለውጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በዚህ እለት ዋነኛዋ ተዋናይ ሆና የቀረበችው ደግሞ ቻይና ናት፡፡ቻይና የባቡሩን አሰራር በመዘርጋት፣ባቡሮቹን በማቅረብ እና ባለፉት ስድስት አመታት በሺ የሚቆጠሩ ኢንጅነሮችን በማስመጣት የመስመሩን ግንባታ እውን አድርጋለች፡፡ አራት ቢሊዮን የሚጠጋውን ወጪ በአብዛኛው የሸፈነችው ቻይና ናት፡፡

በአለም ውዱና ዘመናዊውን የባቡር መስመር በአገሯ  የገነባችው ቻይና ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎቿን ወደ ውጭ አገራት በመላክ አጋርነቷን እያስመሰከረች ነው፡፡በቻይና የተመረቱ የምድር ውስጥ ባቡሮች በቅርቡ በአሜሪካኖቹ ቦስተንና ቺካጎ እንደሚታዩ ዘገባው አስነብቧል፡፡ቤጂንግ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ፈጣን የባቡር መስመር ኢንዶኔዢያ ላይ እየገነባች ነው፡፡ከዚህ ባለፈ በቤጂንግና በለንደን መካከል የባቡር የጭነት አገልግሎት ጅማሮ እውን ሊሆን ተቃርቧል፡፡ሌላው አስደማሚ ግንባታ ደግሞ 2 ሺ 400 ማይል የሚረዝመው የፓን ኤሽያ የባቡር መስመር ትስስር ሲሆን ቻይናን፣ላኦስን፣ታይላንድንና ሲንጋፖርን ያገናኛል፡፡

እንደ አፍሪካ ያሉ የተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ የቻይናን ድጋፍ በላቀ ሁኔታ እያገኙ ነው፡፡አህጉሪቱ ያላት የባቡር መስመር በጣም አነስተኛ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ከሰሐራ በታች ያሉት አገራት ተከታታይና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ቢሆንም አሁንም የመሰረተ ልማት እጥረት አለባቸው፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ከአህጉሪቱ መንገዶች መካከል ግማሹ ብቻ አስፋልት የተነጠፈለት ሲሆን 600 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝቧ የኤሌክትሪክ ሐይል አቅርቦት አያገኝም፡፡

 በጆብ ሆፕኪንስ የአለም አቀፍ ጥናት አድቫንስድ ክፍል የቻይና አፍሪካ የምርምር ኢኒሼቲቭ በቻይና መንግስት እገዛ የሚንቀሳቀሱት ኩባንያዎች በአመት  50 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በመመደብ በአህጉሪቱ አዳዲስ ወደቦችን፣የቀለበት መንገዶችንና የአውሮፕላን ማረፊያዎችን እየገነቡ መሆኑን በጥናት ተመርኩዞ አቅርቧል፡፡

ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች የቤጂንግ አዲሱ የሲልክ ሮድ ኢኒሼቲቭ አካል ሲሆኑ ቻይና 1 ትሪሊዮን ዶላር በመመደብ በማደግ ላይ ካሉ አገራት ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ የምትጠቀምበት ነው፡፡

ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ገንዘብ ለባቡር መስመር ዝርጋታ የሚውል ሲሆን ግንባታው የአፍሪካውያንን የጉዞ እንግልት በመቀነስና ከተቀረው አለም ጋር ያላቸውን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ እንደሚያግዛቸው ታምኖበታል፡፡

በቻይና መንግስት የገንዘብና የግንባታ ባለሙያዎች እገዛ ከተሰሩት ፕሮጀክቶች መካከል በኢትዮጵያ የሚገኘውና ሁለት አመት የፈጀው የቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታ፣13 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጀውና የኬንያዋን ዋና ከተማ ናይሮቢን ከወደብ ከተማዋ ሞምባሳ ጋር የሚያገናኘው የባቡር መስመር እንዲሁም በናይጀሪያ እየተከናወነ ያለው ዘመናዊ የባቡር መስመር ግንባታ ይጠቀሳሉ፡፡

“ ለረጅም አመታት በአፍሪካ ያለው የመንገድ አገልግሎት እየፈራረሰና እየቀነሰ መጥቷል ነገር ግን በቻይና እገዛ ይህ እውነታ እየተቀየረ መምጣቱን ” በሬል ዌይ የባቡር መስመር ጋዜጣ የዜና ኤዲተር የሆነው አንድሪው ግራንትሀም ተናግሯል፡፡

ቻይና በአፍሪካ በቁርጠኛነት እያከናወነች ያለችው የባቡር መስመር፣የትምህርት ቤትና የስታዲየም ግንባታ ከአሜሪካ አንፃር ሲታይ ለየቅል የቆመ ነው፡፡.አሜሪካ በአፍሪካ የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የመደገፍ ፍላጎቷ ፍፁም የወረደ መሆኑን ፀሐፊው ጠቅሷል፡፡

በባራክ ኦባማ የአመራር ዘመን በ2013 ይፋ የተደረገውና 9 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት የፓወር አፍሪካ ኢኒሸቲቭ በአምስት አመታት ውስጥ 20 ሚሊዮን አፍሪካውያንን የኤሌክትሪክ ሐይል  ተጠቃሚ ለማድረግ ቢያልምም ፈቅ ሳይል ቀርቷል፡፡

ንግድን በተመለከተ ደግሞ ቻይና በ2009 አሜሪካን በመቅደም የአፍሪካ ዋነኛዋ የንግድ አጋር ሆናለች፡፡ይህ ሒሳብ በዶናልድ ትራምፕ ዘመን እንዴት ሊቀለበስ እንደሚችል የሚያሳይ ምንም ፍንጭ አለመኖሩን ዘጋቢው አስነብቧል፡፡ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቀረጥ ነጻ የንግድ እድል ተጠቃሚነት ወይም አጎዋን ጥያቄ ውስጥ ከትተውታል፡፡ከወራት በፊት ያዋቀሩት የሽግግር ቡድን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በላከው መጠይቅ በአፍሪካ ያለውን የእድገት መፍጨርጨርና የውጭ እርዳታ አጠራጣሪ አድርጎ አሳይቶበታል፡፡

ይህ ደግሞ አንዳንድ የአፍሪካ ከፍተኛ ባለስልጣኖችንና ኤክስፐርቶችን ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡የአሜሪካ ተፅእኖ የጎላ መሆኑ የማይካድ ሲሆን የመሰረተ ልማት ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚውተረተሩ አገራት ስጋት ቢገባቸው አያስደንቅም፡፡

.በብሮኪንግ ኢንስቲቲዩት የአጎዋ ዳይሬክተር የሆኑት አማዱ ሳይ አሜሪካ ታማኝ ደንበኞችን ለማፍራት ያገኘችውን አጋጣሚ እያጣች ነው ብለዋል፡፡

”አዲስ ገበያ የምትፈልግ ከሆነ ቦታው አፍሪካ ነው፡፡ ነገር ግን አሜሪካ የአፍሪካን እምቅ አቅም እየተጠቀመችበት አይደለም፡፡በንፅፅር ቻይናውያን እዛ ናቸው ማንኛውንም አደጋ ለመጋፈጥ ተዘጋጅተዋል ”ሲሉ ሙያዊ ምልከታቸውን አንጸባርቀዋል፡፡

ቻይና ድህነትንና ስራ አጥነትን ለማስወገድ እየተጋች ባለችው ጅቡቲ ብቻ 14 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ በመመደብ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ከያዘቻቸው ፕሮጀክቶች መካከል የሶስት ወደቦች፣የሁለት አውሮፕላን ማረፊያ  ይጠቀሳሉ፡፡ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ የከሰል ሐይል ማመንጫ ለመገንባት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡

የኢትዮጵያ 90 በመቶ የወጪ ንግድ በጅቡቲ በኩል የሚወጣ በመሆኑ የአገራቱ ትስስር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

የጅቡቲ ወደብ ሊቀመንበር የሆኑት አቡበከር ኦማር ሀዲ ሁለቱን አገራት የሚያገናኘው አዲሱ የባቡር መስመር ከህንድ ውቅያኖስ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ለሚዘረጋውና የረጅም ጊዜ ህልም ለነበረው የአፍሪካ የጉዞ ትስስር ቀለበት መንደርደሪያ ነው ብለዋል፡፡

”ባቡሩ በአሁኑ ሰአት ጨዋታ ቀያሪ ሆኗል በማለት ቀደም ባለው ጊዜ አራት ቀን አካባቢ ይፈጅ የነበረውን የመኪና ጎዞ ወደ 12 ሰአት ማሳጠሩን ማሳያ በማድረግ ሐሳባቸውን ለዘጋቢው አካፍለውታል፡፡”

ቻይና ለአገራቸው እያደረገች ያለውን የገንዘብ ድጋፍም አድንቀዋል፡፡

”አሜሪካኖችን ብንቀርባቸውም ራዕይ የላቸውም,፡፡30 አመት ወደፊት ቀድመው ማሰብ አይችሉም፡፡ የእነሱ ራዕይ አፍሪካ አሁንም በእርስ በእርስ ጦርነትና በርሐብ ውስጥ እንዳለች አድርጎ ማሰብ ነው፡፡ ቻይናውያን ግን ራዕይ አላቸው፡፡” ማለታቸውን ዘግቧል፡፡

ሁሉም በቻይና ራዕይ ደስተኛ ላይሆን ይችላል፡፡አገራት በብድር ባህር እንዳይሰጥሙ የሚሰጉ አሉ፡፡ የጅቡቲ ብድር ከፍ ያለ ቢሆን የመክፈል አቅም እንዳላት የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ኢሊስ ሙሳ ዳውላህ ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትሩ ጅቡቲ በማስመዝገብ ላይ ያለችው 6 ነጥብ 7 በመቶ አገራዊ እድገት ብድሯን ለመክፈል ያስችላታል ማለታቸውን ዘገባው በማሳያነት አስቀምጦታል፡፡

” አደጋውን ተጋፍጠን መሰረተ ልማታችን ካላስፋፋን በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀን እንቀራለን፡፡ከጥቂት አመታት በኋላ ስትመለሱ ጅቡቲን የአህጉሪቱ የሎጀሰቲክ መናኽሪያ ሆና ታገኟታላችሁ ብለዋል፡፡ ”

 የባቡር መስመር ዝርጋታው ከግንባታው ይልቅ ጥገናው አሳሳቢ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ ቀደም ያሉ ማሳያዎችን በመጥቀስ የአፍሪካ ፍሪደም ሬል ዌይ መፅሐፍ ፀሐፊዋ ጄሚ ሞንሶን ትናገራለች፡፡

” አስተማማኝ የሆነ ጥገና ከሌለ ችግር መፈጠሩ አይቀርም፡፡ይህ ደግሞ በአህጉሪቱ ኢኮኖሚና መደበኛ ነዋሪ ላይ ከባድ ተፅእኖ ያሳርፋል ብላለች፡፡”

ለአሁኑ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት በኢትዮ ጅቡቲ ዘመናዊ  የባቡር መስመር ግንባታ መጠናቀቅ ደስተኛ ሆነዋል፡፡ቻይናውያን የቴክኒኩንና የኢንጅነሪንግ ስራውን ሲከዉኑት ኢትዮጵያውያንና ጅቡቲያውያን ሰራተኞች ደግሞ በጉልበትና በቀላል የቴክኒክ ስራዎች ላይ በመሳተፍ አዲስ እውቀት ለመቅሰም በቅተዋል፡፡

አጠቃላይ አሰራሩ ለአምስት አመታት በቻይናውያን እጅ ውስጥ ከቆየ በኋላ በቻይና በሰለጠኑትና በመሰልጠን ላይ ለሚገኙት ለአገራቱ ዜጎች ይተላለፋል፡፡

ለጅቡቲ መንግስት የሚሰራው የቴክኖለጂ ስፔሻሊስት ዳሀ አህመድ ኦስማን አዲሱ የባቡር መስመር ከጅቡቲና ከኢትዮጵያ ባለፈ አህጉሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግራት እምነት እንዳለው ለፀሐፊው ነግሮታል፡፡በዚህ ስራቸው ቻይናውያንን ማመስገን አለብን፡፡ ምክንያቱም ገንዘባቸውንና እውቀታቸውን ከእኛ ጋር ተካፍለዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ልናመሰግናቸው የሚገባው በእኛ ላይ እምነት በማሳደራቸው  ነው ማለቱን ጠቅሶ ድረ ገፁ ዘገባውን አጠናቋል፡፡

Published in ዜና ሓተታ

አዲስ አበባ የካቲት 3/2009 ድርቁን ለዘለቄታው በራስ አቅም ለመቋቋም የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አሳሰበ።

ፅህፈት ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳለው መንግስትና ባለድርሻ አካላት ድርቁን በራስ አቅም ለመፍታት በሚደረገው ጥረት በጋራ መስራት አለባቸው።

በአንዳንድ ቆላማና የአርብቶ አደር አካባቢዎች ያጋጠመውን ድርቅ ለመቋቋም መንግስት፣ የክልል መንግስታትና ህብረተሰቡ የጋራ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉም ብሏል።

መንግስት በድርቁ ለተገጎዱ ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቁሟል።

በኤልኒኖ የአየር መዛባት በአገሪቷ ታሪክ ተከስቶ የነበረውን ከባድ ድርቅ በራስ አቅም በመፍታት ድርቁ ምንም አይነት ሰብዓዊ ቀውስና ጉዳት ከማድረሱ በፊት መቆጣጠር እንደተቻለም ነው ፅህፈት ቤቱ ያስታወሰው።

ድርቁን በመቋቋም ረገድ ካለፈው ዓመት የተገኙ በጎ ተሞክሮዎችን በማስፋት የድርቁን ተጽዕኖና ዘላቂ ጉዳት የመቋቋም አቅምን ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑንም በመግለጫው አትቷል። 

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

በኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ

የካቲት 3 ቀን 2009 ዓ.ም

ድርቅን ለዘለቄታው በራሳችን አቅም ለመቋቋም እንረባረብ!

በዓለማችን በተከሰተው የተፈጥሮ አየር መዛባት ሳቢያ ባለፈው ዓመት በ50 ዓመት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ድርቅ አጋጥሞን እንደነበር አይዘነጋም። በወቅቱ የኢፌዴሪ መንግሥት ችግሩን በወሳኝነት በራስ አቅም ለመፍታት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በተደረገ ርብርብ በድርቁ አንዳችም ዓይነት ሰብዓዊ ቀውስ እና ጉዳት ከመድረሱ በፊት አደጋውን መቋቋም ተችሏል፡፡ ያለፈው ዓመት ድርቅን የመቋቋም ተግባራችንን ከዚያ በፊት ከነበረው ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎቻችን የተለየ ያደረገውም ይኸው በወሳኝነት በራሳችን ሀገራዊ አቅም አደጋውን መቋቋም መቻላችን ነበር።

ይኸው ተፈጥሮአዊ ክስተት ዘንድሮም  በአንዳንድ ቆላማ የአርብቶ አደር አካባቢዎች አጋጥሞናል። ድርቁ የሚያስከትለውን አደጋ ለመቋቋምም የኢፌዴሪ መንግሥት፣ የክልል መንግሥታት፣ የየአካባቢው ማህበረሰብ እና መላ ህዝቡ የጋራ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ።

የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በጋራ ለ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህዝብ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎችን እያቀረቡ ይገኛሉ። የመጠጥ ውሃ በቦቴ በማመላለስ፣ የእንስሳት መኖ አቅርቦት እና የህክምና አገልግሎትም ለድርቁ ተጠቂዎች እየተሰጠ ይገኛል። በድርቅ በተጠቁት አካባቢዎች የሚኖሩ የአርብቶ አደር ልጆች ከቀያቸው ሳይርቁ ትምህርታቸውን መቀጠል እንዲችሉም ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህም የፌዴራል መንግሥት ከመደበው ሀብት በተጨማሪ ክልሎች የየራሳቸውን በጀት በመጨመር የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም በመጀመሩ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ ተችሏል። ድርቅን በመቋቋም ረገድ ባለፈው ዓመት የተገኙ በጎ ተሞክሮዎችን  በማስፋትም የድርቅን ተጽዕኖና ዘላቂ ጉዳት የመቋቋም አቅምን ለማጎልበት እየተሰራ ይገኛል። ለአብነትም መስኖ ባለባቸው አካባቢዎች በፍጥነት የሚደርሱ የእንስሳት መኖዎችን የማልማት ሥራ እየተካሄደ ነው።  ከዚህ ጎን ለጎን በመላ አገሪቱ ለዘለቄታው ድርቅን መቋቋም የሚችል አቅም ለመፍጠር እየተካሄደ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል። በአሁኑ ወቅት ከ22 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በተፋሰስ ልማት ስራ ላይ ተሰማርቶ እየሰራ ይገኛል።

የኢፌዴሪ መንግስት ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያለውን ችግር በጊዜያዊነት ለመፍታት በዋናነት በራሱ አቅም የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ወዳጅ ሀገራትም ችግሩን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ማስተባበሩን ይቀጥላል፡፡  ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያለው ማህበረሰብ እና መላው ህዝባችን እያደረጉት ያለውን ርብርብ እንዲሁም ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚደረገው የልማት ስራዎች ርብርብ እያሳዩ ያሉትን የነቃ ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ በዚህ አጋጣሚም  ጥሪውን ያስተላልፋል።

ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 3/2009 ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን የማልማትና የመጠቀም አቅም እየፈጠረች መምጣቷን ያረጋገጠ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

የጋራ ምክር ቤቱ አራት የአባልነትና አንድ ወደ አባልነት የመመለስ ጥያቄዎች ከአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀርበውለታል።

የጋራ ምክር ቤቱ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ አባል ፓርቲዎች በህዳሴው ግድብ ያደረጉትን የመስክ ጉብኝት ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክሯል።

ፓርቲዎቹ ባካሄዱት ጉብኝት የግድቡ ግንባታ በቀን ለ24 ሠዓታት ያለማቋረጥ እየተከናወነ መሆኑን በስፍራው ተገኝተው መመልከታቸው በሪፖርት ቀርቧል።

የግድቡ ግንባታ በአገር ውስጥ አቅም በጥራትና በፍጥነት እየተከወነ መሆኑን መገንዘቡን የገለፀው ምክር ቤቱ ይህም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን በራሷ አቅም አልምታ መጠቀም መጀመሯን ያሳያል ብሏል።

ይህም ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተምሳሌት የሚሆን ተግባር እንደሆነ ነው የገለጸው።

የምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች በሰጧቸው አስተያየቶች የግድቡ ግንባታ ያለ ዕረፍት መካሄድ መቀጠሉ የኢትዮጵያውያን ድጋፍ በተግባር ታሪክ ለመስራት እየዋለ መሆኑን አስገንዝቦናል ብለዋል።

በግድቡ አካባቢ በቂ የሰራተኞች መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም የባንክ፣ የፖስታ፣ የሞባይልና የህክምና አገልግሎቶች መዘርጋታቸውን እንደተመለከቱም ተናግረዋል።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚካሄዱ የመንደር ማሰባሰብና የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን የገለፁት ፓርቲዎቹ በተለይ የግብርና ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስተያየት ሰጥተዋል።

ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሰባው ከአራት አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀረበለት የአባልነት ጥያቄ ላይ መክሯል።

ጥያቄ ያቀረቡት ፓርቲዎች ሰነዶቻቸውን አሟልተው ሲቀርቡ እልባት ለመስጠትም ውሳኔ አሳልፏል።

ከምክር ቤቱ አባልነት ወጥቶ የነበረ አንድ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ላቀረበው የልመለስ ጥያቄም ፓርቲው በይፋ ይቅርታ ሲጠይቅ ጉዳዩ እንደሚታይ ከስምምነት ተደርሷል።

በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች የተፈጠረውን ድርቅ የምክር ቤቱ አባላት በአካል ተገኝተው መመልከት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።

በጋራ ምክር ቤቱ ዓመታዊ ዕቅድ መሰረት በአገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመከራከር መድረኮች እንደሚዘጋጁ ተመልክቷል።

የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 9 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈ ነው።

Published in ፖለቲካ

ባህርዳር የካቲት 3/2009 በአማራ ክልል ለልዩ ፍላጎት ትምህርት ትኩረት በመሰጠቱ የተማሪዎች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

በቢሮው የልዩ ፍላጎት ትምህርት ባለሙያ ወይዘሮ ስንታየሁ እምሩ ትናንት ለኢዜአ እንደገለጹት ትምህርት ለሁሉም በሚለው መርህ መሰረት  የአካል ጉዳት ያለባቸው ሕጻናት ትኩረት እንዲያገኙ ተደርጓል።

በተያዘው የትምህርት ዘመን በክልሉ በ605 ትምህርት ቤቶች ከ14 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎች የልዩ ፍጎት ትምህርት በመከታተል ላይ ናቸው።

ከነዚህ መካከል ከስድስት ሺህ 500 የሚበልጡት  ሴት ተማሪዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ዘንድሮ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከአንድ ሺህ 700 በላይ ብልጫ እንዳለው ባለሙያዋ ተናግረዋል።

"ተማሪዎቹ ከአንድ እስከ አራተኛ ክፍል በሙያው በሰለጠኑ መምህራን ለብቻቸው እንዲማሩ ይደረጋል" ያሉት ወይዘሮ ስንታየሁ፤ ከ5ኛ ክፍል በኋላ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በአካቶ ትምህርት እንዲማሩ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደባለሙያዋ ገለጻ፣ በልዩ ፍላጎት ትምህርት የሚሳተፉት ዓይነስውራን፣ መስማት የተሳናቸው፣ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው፣ የእጅ ወይም የእግር ጉዳትና ሌሎች ችግሮች ያሉባቸው ተማሪዎች ናቸው።

ለእነዚህ ተማሪዎችም በመጀመሪያ ዲግሪና በዲፕሎማ የሰለጠኑ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ መምህራን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተመድበው ትምህርቱን እየሰጡ ይገኛሉ።

የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ቢመጣም የበጀት፣ የማጣቀሻ መጻህፍትና የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን ወይዘሮ ስንታየሁ ተናግረዋል።

የሰርጸ ድንግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ተፈራ መንገሻ በበኩላቸው፣ በትምህርት ቤቱ 78 የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለልዩ ፍላጎት ትምህርት ከወርልድ ቪዥን ከ50 ሺህ ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታቸውን ገልጸው፣ በዚህም የመቅረጸ ድምጽ፣ የብሬልና ሌሎች የትምህርት ግብአቶች ተገዝተው ለተማሪዎች መታደሉን ተናግረዋል።

ያለምንም የትምህርት ግበአት ችግር ትምህርቱን እየተከታተለ መሆኑን የገለጸው ደግሞ በትምህርት ቤቱ የሰባተኛ ክፍል የልዩ ፍላጎት ተማሪው አብየ ብርሃኑ ነው።

"አይነስውር ብሆንም የብሬልና የመቅረጸ ድምጽ ችግሬ ተቀርፎልኛል፤ በአካቶ ትምህርት ከሌሎች ተማሪዎች ጋር  በመሆን እየተማርኩ ነው። መንግስትም በየወሩ የሚያደርግልኝ የ350 ብር ድጋፍ በትምህርቴ እንድበረታ አግዞኛል" ብሏል።  

በዚሁ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ክፍል ተማሪው ሃብተማርያም ሞላ በበኩሉ ዓይነስውር መሆን ከመማርና ሌሎች የደረሱበት ደረጃ ከመድረስ የሚያግደው ነገር እንደሌለ ገልጿል።

ወደፊት ጥሩ ደረጃ ላይ ለመድረስ ትምህርቱን በትኩረት እየተከታተለ መሆኑንም ተማሪው ተናግሯል። 

የሰርፀ ድንግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የልዩ ፍላጎት መምህር ወይዘሮ አትጠገብ ቢረሳው በበኩላቸው፣  ዓይነስውራን ተማሪዎች ትምህርቱን በመቀበል በኩል ከሌሎች ፈጣን መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተማሪዎቹ ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቁ ቢደረግ ትምህርታቸውን ያለደጋፊ አንባቢ በኮምፒዩተር መከታተልና ማጥናት እንደሚችሉም  አመልከተዋል።  

በ2008 የትምህርት ዘመን በአማራ ክልል 13 ሺህ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተላቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ የካቲት 3/2009 በንግድና ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያጋጥሙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የማጠናከር ስር እንደሚካሄድ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሀዝቦች ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ገለጸ፡፡

ቢሮው የ2009 የመጀመሪያው ግማሽ የበጀት ዓመት አፈጻጸምን በሃዋሳ ከተማ ገምግሟል፡፡

"ኪራይ ሰብሳቢነት፤ የምርት እጥረት በመፍጠር ዋጋን ማናር፣ ኋላቀር የመረጃ ስርዓት፣ ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በዘርፉ የተስተዋሉ ችግሮች ናቸው" ሲሉ የቢሮው ሃላፊ  ዶክተር ጌትነት በጋሻው ተናግረዋል፡፡

በግማሽ የበጀት ዓመቱ ውስጥ ክልሉ ከፍተኛ የሆነ የግብርና ምርት ቢኖረውም ለውጭ  ገበያ የሚውሉ የቅባት፣ ጥራጥሬ፣ የቁም እንስሳትና የመሳሰሉት የግብርና ምርቶች ግብይት ያልተሰራበት ዘርፍ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ዘርፉ በኢኮኖሚው እድገት ውስጥ ሚናውን በብቃት እንዲወጣ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ውድድርን መሰረት ያደረገ የንግድ ስርዓት እንዲኖር የሚሰራ መሆኑን  ዶክተር ጌትነት ገልጸዋል፡፡ 

የንግዱ ማህበረሰብ በነጻ የገበያ ስርዓት የሸማቾችን ፍላጎት የሚያረኩ ምርቶችንና አገልግሎት ማቅረብ ሌላው ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

እንዳሃላፊው ገለጻ በህዝቡ የሚነሳው ቅሬታ የዘይት፣  ስኳርና  የስንዴ ዱቄት እጥረት የሚፈጠረው ለክልሉ የሚሰጠው ከህዝቡ ፍላጎት ጋር የማይጣጣምና  የስርጭት ፍትሃዊነት ያለመሆን ነው፡፡

ችግሩን ለመፍታት ከንግድ ሚኒስትር ጋር በመነጋገር ማሻሻያ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ፍኖተ ካርታ ከተዘጋጀ 10 ዓመታትን ቢያስቆጥርም ተጨባጭ ለውጥ አልተመዘገበም፡፡

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የበቁ ማህበራትን ደግፎ አለማሳተፍ፣ የማምረቻ ቦታዎችን አለማዘጋጀትና የማዋቅሩ ተደራሽ አለመሆንን እንደምክንያት የጠቀሱት ሃላፊው "ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት የኢንዱስትሪ  ፓርኮች ልማት ኮርፓሬሽን ተቋቁማል" ብለዋል፡፡

ቢሮው የንግድና ማንፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያጋጥሙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ዘርፉን የማጠናከር ስራ ለማካሄድ ትኩረት ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ 

የከፋ ዞን ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ልሳነ ተሾመ የግምገማው መድረክ "ድክመቶቻችንና ጥንካሬዎቻችንን ያሳየን በመሆኑ ለቀጣይ ስራችን አነሳስቶናል "ብለዋል፡፡

መምሪያው ማህበራት በቡና ኢንዱስትሪ እንዲሳተፉና ህገ ወጥ የቡና ንግድ ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ለማህበራት ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ረገድ ክፍተት እንዳለ የተናገሩት ደግሞ የየም ልዩ ወረዳ ንግድና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ  አቶ ሽመልስ እጅጉ ናቸው፡፡

ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍና የሸማቾችን መብት ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም ጠቁመዋል፡፡

በሀዋሳ ለሁለት ቀናት የተካሄደውና ትናንት በተጠናቀቀው የግምገማ መድረክ ላይ ከሁሉም የዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተወጣጡ የዘርፉ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ የዘርፉን ችግሮች በመፍታት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገም በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም አመልክተዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ድሬደዋ የካቲት 3/2009 የሀገሪቱን የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተግባራትና ውጤቶችን ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር ለላቀ ውጤት መስራት እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስቴር አመለከተ።

አራተኛው ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ  ትስስር አውደ ጥናት በድሬዳዋ ተጀምሯል።

በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ምርምርና አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ዘሪሁን ከበደ  በአውደ ጥናቱ ላይ እንደገለጹት የሀገሪቱ የህዳሴን ጉዞ  ለማሳካት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከኢንዱስትሪ ጋር ማስተሳሰር ወሳኝ ጉዳይ ነው።

ከድህነት  ለመውጣት ሌሎች አገሮች የሰሩትን ቴክኖሎጂ ባግባቡ ተጠቅሞ በማምረትና አገልግሎት በመስጠት በዘላቂነት በአለም ገበያ መወዳደር ይገባል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሌሎችን ቴክኖሎጂዎች በመቅዳትም ሆነ በመፍጠር የህዳሴውን ጉዞ ማሳካትና ከድህነት ለመላቀቅ ተግተው መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

ይህ የሚሆነው የቴክኖሎጂ አቅም በመገንባት መሆኑን ዶክተር ዘሪሁን ጠቅሰው የዩኒቨርሲቲ ኢንዳስትሪ ትስስር ተወዳዳሪ ምርትና አገልግሎት በመስጠት ሀገሪቱ የተያያዘችውን ዘላቂ ልማት እድገት  ለማረጋገጥ  ከፍተኛ ትርጉም እንደሚሰጠው ተናግረዋል።

ለዚህም ብቃት ያለውን የሰው ኃይል በማፍራት ለሀገሪቱ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት አስፈላጊነት ላይ ኢንዱስትሪዎችና  ዩኒቨርሲቲዎች ተሳስረው ከመጓዝ አንጻር መሰረታዊ ክፍተቶች አሉ፡፡

ክፍተቶችን ለመሙላት በቁርጠኝነት ወደ ስራ መግባት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ኢንዱስትሪዎችም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር አብረው መስራታቸውና በምርምር ውጤት መደገፋቸው የድርጅታቸው ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በመገንዘብ ተቀራርበው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ዶክተር ዘሪሁን ጠቁመዋል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ግርማ ጎሮ በበኩላቸው አራተኛው የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር አውደ ጥናት የተሻለ ተሞክሮና ልምድ በመለዋወጥ  ትስስሩን ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በምስራቁ ክፍል ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር ፎረም በመመስረት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን የመፍታት ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው "በቀጣይ ይህን ትስሰር ለማጎልበት  አውደ ጥናቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው" ብለዋል።

በድሬደዋ ትናንት በተጀመረው አውደ ጥናት ላይ ከሀገሪቱ የተለያዩ  ዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዱስትሪዎች የተወጣጡ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ናቸው፡፡

ተሳታፊዎቹ ዛሬ  የሐረማያና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ኢንዱስትሪ  ባሸጋገሯቸው የምርምር ውጤቶች ላይ ውይይት እያካሄዱ ይገኛሉ።

በተለያዩ የምርምር ውጤቶች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን የሚሞሉ  አቅጣጫዎች በማስቀመጥ አውደ ጥናቱ ነገ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፤  በተማሪዎች የተከናወኑ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶችን የሚያመለክት አውደ ርዕይም ይካሄዳል።

 

 

Published in ማህበራዊ

አዳማ የካቲት 3/2009 መልካም አስተዳደርን በማስፈን ፍትሃዊና ፈጣን አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ለመስጠት እንደሚሰሩ የአዳማና ሻሻመኔ ከተማ ከንቲባዎች ገለጹ።

ከንቲባዎቹ ሰሞኑን ለኢዜአ እንደገለጹት ህዝቡ ወደ አደባባይ እንዲወጣ ያደረጉ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ብልሹ አሰራር፣ ስልጣንን ለግል ጥቅም ማዋልና የፍትህ መጓደል ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት በትኩረት ይሰራሉ።

የአዳማ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ እንዳሉት ለሕብረተሰቡ ቅሬታ በወቅቱ ተገቢ ምላሽ አለመሰጠቱ ወደ ሁከትና ግርግር እንዲያመራ አድርጓል።

"ከዚህ ቀደም በነበረው አካሄድ ሁሉንም የሕብረተሰቡን ጥያቄ መመለስ አይቻልም" ያሉት ወይዘሮ አዳነች በመሬትና በፍትህ እጦት፣ በገቢ፣ በከተማ ጽዳትና ውበት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የከተማዋ የፋይናንስ ምንጭ ለልማት ብቻ እንዲውል በማድረግ በኩል ያለውን ክፍተት ለማስወገድም በሙሉ አቅም እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል።

ኪራይ ሰብሳቢ ባለሀብቶችና ግለሰቦች ቀደም ሲል ከአመራሮች ጋር ተመሳጥረው የያዙትን መሬት፣ የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾች የማምረቻ ማዕከላትን ወደ ግል ያዛወሩ፣ ሳይለሙ ታጥረው የተቀመጡ ይዞታዎችን የመለየትና የማስመለስ ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በመለየት ሂደት ውስጥ ከሕብረተሰቡ፣ ከፍትህና ከፖሊስ አካላት፣ በየደረጃው ከሚገኙ አዳዲስ አመራሮች የተዋቀረ ኮሚቴ ተቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ወይዘሮ አዳነች ገልጸዋል።

" የከተማዋ መሬት ለህዝብ ልማትና ጥቅም ብቻ እንዲውል በህዝብና በመንግስት እምነት የተጣለባቸውን አመራሮች ሙሉ በመሉ በአዲስ መልክ በማደራጀት ወደ ተጨባጭ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ተደርጓል" ብለዋል

የሻሻመኔ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው፣ ጥልቅ ተሀድሶውን ተከትሎ በከተማዋ በልማትና በመልካም አስተዳድር መሰረታዊ ለውጥና ውጤት ለማምጣት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የህዝቡን የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ለመመለስና የመልካም አስተዳድር ችግሮችን ለማስወገድ በትኩረት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ወይዘሮ ጠይባ እንዳሉት፣ በከተማዋ እስከ ቀበሌ ድረስ በጥልቅ ተሀድሶ ተገምግመው ያለፉት አዳዲስ አመራሮች በህዝብና በኦህዴድ አባላት እንዲተቹ ተደርጓል።

በተጨማሪም በትምህርት ዝግጅትና በፖለቲካ ቁርጠኝነታቸው ተመዝነው ብቃታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ወደሥራ እንዲገቡ መደረጉን  ነው የገለጹት።

በተሀድሶ ግምገማው በኪራይ ሰብሳቢነት መዘፈቃቸው የተለዩ አመራሮች፣ ፈጻሚዎችና ሙያተኞች ላይ አስተዳደራዊና ህገዊ እርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም የሕብረተሰቡ ቅሬታ ጎልቶ በሚሰማባቸው ሰባት ሴክተር መስሪያቤት አመራሮች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ከስልጣን እንዲነሱ መደረጉን ገልጸዋል።

የሕዝቡን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ከአገልግሎት መስጠት ጀምሮ በጥቅም የተቆላለፉ፣ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት የተሰማሩ አመራሮች፣ ሙያተኞችና ሠራተኞችን ለህግ ለማቅረብ በጥናት የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

አስተዳደሩ ሕብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ቅሬታ የሚያነሳባቸውን አገልግሎቶች በተለይ ከውሃ፣ ከመብራት፣ ከመሰረተ ልማት ጥራት መጓደል፣ ከፍትህና መሰል አገልግሎቶች ጋር የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ወይዘሮ ጠይባ አስረድተዋል።

Published in ፖለቲካ

አምቦ የካቲት 3/2009 በምዕራብ ሸዋ ዞን ከ26 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ አምስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የኮንትራት አስተዳደርና የግንባታ ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጂሬኛ ዶርስስ እንዳስታወቁት የመስኖ አውታር ግንባታው እየተካሄደ ያለው በዞኑ ዘመናዊ የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት ነው።

የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሥራ በዳኖ፣ ቶኬ-ኩታዬ፣ አቡና ግንደበረት፣ ኖኖና ጨሊያ ወረዳዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸው፣ የግንባታ ሥራው ከ26 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ግንባታው ከ46 እስከ 80 በመቶ መድረሱን የጠቆሙት አቶ ጂሬኛ፣ ፕሮጀክቶቹን በተያዘው ዓመት ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅ ሥራ ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ፣ ሁሉም ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ በአንድ ጊዜ ከ260 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት የሚቻል ሲሆን በዚህም 700 አርሶአደሮች ተጠቃሚ ይሆናሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ዘመናዊ የመስኖ ልማትን በማስፋፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ለመሰኖ ልማት አመቺ የሆኑ አካባቢዎችን ለይቶ የማጥናት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡  

በምዕራብ ሸዋ ዞን የጨሊያ ወረዳ አርሶ አደር ሚሬሳ ፉፋ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ዓመታት በአካባቢያቸው በተገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶች የተለያዩ አትክልቶችን፣ ሙዝና በቆሎ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በግማሽ ሄክታር መሬታቸው ላይ ያለሙትን ከቤተሰብ ቀለብ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ በአንድ ዙር ብቻ እስከ 12 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በዳኖ ወረዳ የመስኖ ልማት ተጠቃሚ  አርሶአደር መርጋ ፉታሳ በበኩላቸው፣ በአካባቢያቸው ክረምት ከበጋ የሚፈሰውን ወንዝ በባህላዊ መንገድ ጠልፈው ቢያለሙም ብዙም ውጤታማ እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት በአቅራቢያቸው ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክት እየተገነባ መሆኑን ጠቁመው፣ ፕሮጀክቱ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ ማቀዳቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በዞኑ በተገነቡ 65 ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶች ዘጠኝ ሺህ 752  አርሶአደሮች ተጠቃሚ መሆናቸው ተመልክቷል።

በተያዘው የበጋ ወራትም 77 ሺህ 815 ሄክታር መሬት በዘመናዊና ባህላዊ መስኖ ለማልማት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ  የካቲት 3/2009 የስፖርት ማህበራትና ፌዴሬሽኖች መረጃ ለመስጠት ክፍት ባለመሆናቸው የህብረተሰቡን ፍላጎት ማርካት እንዳልቻሉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ገለጹ።

የመረጃ አሰጣጣቸውን በማዘመንና በአግባቡ ተደራሽ በማድረግ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥሩም ጠይቀዋል።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ የአገር ውስጥ የስፖርት መረጃዎችን ተደራሽነት ለማስፋት ከፌዴሬሽኖችና ከስፖርት ማህበራት ጋር እየሰራሁ ነው ብሏል።

በአገሪቷ የመገናኛ ብዙሃን ቁጥር እያደገ ቢሆንም በተለይም በስፖርቱ ዘርፍ አብዛኛው ጊዜያቸውን በውጭ ዘገባዎች ላይ በማተኮር እንደሚያሳልፉ የስፖርት ቤተሰቦች ተናግረዋል።

ስለ አገር ውስጥ ስፖርት ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት የኃላፊዎች ፍቃደኛ አለመሆንና የማህበረሰቡም ፍላጎት ወደ ውጭ ስፖርት ማመዘን ለመገናኛ ብዙሃኑ ሽፋን ዝቅተኛ መሆን አስተዋጽኦ ማድረጉን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

መገናኛ ብዙሃን ለስፖርቱ ዕድገት ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶችን በማሳየት መፍትሔ እንዲያገኙና ህብረተሰቡም ስፖርትን ባህሉ አድርጎ እንዲያሰርጸው የማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ነው የገለጹት።    

የብስራት 101 ነጥብ 1 ኤፍ.ኤፍ ራዲዮ ጣቢያ የስፖርት ጋዜጠኛ ኃይለእግዚያብሔር አድሃኖም የአገር ውስጥ የስፖርት መረጃዎችን ማግኘት ፈተና እየሆነ ነው ብሏል።

ጋዜጠኛው መረጃዎችን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት አድርጎም በቂ ምላሽ የማያገኝ በመሆኑ ወደ ውጭ ስፖርት ዘገባ እንዲያመዝን አድርጎታል ነው ያለው።

የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን የስፖርት ጋዜጠኛ ዮናስ ሞላ በበኩሉ ጋዜጠኞች የአንድን አገር ስፖርት የማሳደግ ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ገልጿል።

ሆኖም ይህን አቅም ለመጠቀም በስፖርቱ ዘርፍ ያሉ ኃላፊዎች መቀያየርና መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆን ማነቆ ሆኗል ብሏል።

እግር ኳስ ጋዜጠኛች በስፋት ስለሚሰሩት በህዝብ ጆሮ መግባቱን ጠቅሶ፤ በአንጻሩ አትሌቲክስ፣ ቴኳንዶና ሌሎች ስፖርቶች የሚሰጣቸው ትኩረት በቂ አለመሆኑን ለአብነት አንስቷል።

የአገሪቱን ስፖርት በበላይነት የሚመራው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር የጋዜጠኞችን ግንዛቤ በማሳደግና ድጋፍ በማድርግ ረገድ ሃላፊነቱን መወጣት አለበት ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

የዛሚ 90 ነጥብ 7 ኤፍ.ኤም የአገራዊ ስፖርት አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዮሴፍ ከፈለኝም የአገር ውስጥ ስፖርት መረጃዎችን እንደ ውጪው በቀላሉ ለማገኘት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጿል።

አብዛኞቹ ፌዴሬሽኖችና የስፖርት ማህበራት ያሉትን የመገናኛ ብዙሃን እንደማያውቋቸውና ከእነሱም ጋር ተቀራርበው የመስራት ልምድ እንደሌላቸው ነው የተናገረው።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር የኮሙኒኬሽን ዳሬክተር አቶ ናስር ለገሰ በበኩላቸው በስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማህበራት በኩል ሚዲያው በሚፈልገው መልኩ መረጃ የመስጠት ችግር እንደሚስተዋል አምነዋል።

ችግሩን ለመፍታት ከማህበራትና ፌዴሬሽኖች ጋር በመተባበርና ዘመናዊ አሰራሮችን በመጠቀም መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙሃን ለማድረስ እየሰራን ነው ብለዋል።

የተወሰኑት የስፖርት ሚዲያዎች ውድድርና ስብሰባዎችን ብቻ መሰረት አድርገው መዘገብና ለአገር ውስጥ መረጃዎች ትኩረት አለመስጠት ችግሮች እንዳሉባቸውም ጠቅሰዋል።

ሚኒስቴሩ መረጃዎችን ከመገናኛ ብዙሃን በተጨማሪ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ለማህበረሰቡ ለማድርስ እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።

 

 

Published in ስፖርት
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን