አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 01 February 2017

ከአምስት ዓመት በፊት ወደ  አፍሪካ ህብረት መሪነት ስልጣን የመጡት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶ/ር ኒኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ በስልጣን ዘመናቸው በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት የገቡትን ቃል ፈፅመዋል አልፈጸሙም በሚል በርካታ ሚዲያዎች የተለያዩ ሃሳቦችን አስፍረዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ዘ አፍሪካን ሪፖሪት ዲላሚኒ ዙማ በአፍሪካ ህብረት መሪነታቸው ጥሩ ስራ ሰርተዋልን ሲል ይጠይቃል? በዚህም የአፍሪካ ዲሞክራቲክ ሪፖርት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ  ታቶ ማቱንግ  ዲላሚኒ ዙማ በስልጣን ዘመናቸው ለመስራት ቃል የገቡትን አብዛኛውን አሳክተዋል ትላለች።

ለዚህም እንደማሳያ የምታቀርበው ዲላሚኒ ዙማ በስልጣን ዘመናቸው ከሰሩት ስራዎች መካካል የአፍሪካ ህብረት በወቅታዊ የፀጥታና የሰላም ጉዳዮች ላይ ከመወያየት ተላቆ በአጠቃላይ የአፍሪካ የልማት ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር አድርገዋል ብላለች።

ሴቶች በአፍሪካ ህብረት ስራ ላይ እንዲሳተፉ ጥሩ አርዓያ ነበሩ። ዲላሚኒ ዙማ ባገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ ስለ ሴቶች መብት ሲያቀነቅኑ ነበር፤ የአፍሪካ የስርዓተ ፆታ ስኮር ካርድን ማስተዋዋቅና አፍሪካ ህብረት ያወጣቸዉ የተለያዩ መርሃ ግብሮችና በህብረቱ የተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ በርካታ ሴቶችን በመሾም የሴቶችን የመሪነት ሚና ከፍ ከማድረግ በዘለለ የሴቶችን ስና ልቦና የሚያሳድግ ስራን ሰርተዋል፡፡

ታላቋ አፍሪካ እራስዋን እድትችል ታግለዋል፤ በዙማ የስልጣን ዘመን ከፍተኛ መጠን ያለውን የአህጉሪቱን ሃብት በማንቀሳቀስ አፍሪካ በራስዋ ሃብት ችግሮችዋን መፍታት እንደምትችል አሳይተዋል፡፡ በህብረቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2014 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት ከግል ባላሀብቶች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ የዉይይት መድረክ በማዘጋጀት ኢቦላን ለመከላከል የሚያስችል ሀብት ከንግዱና ከመንግስት በማሰበሳብ ለችግሩ አፈጣኝ ምላሽ ለመስጠት ጥረዋል፡፡

 ከሁሉም በለይ ዲላሚኒ ዙማ በአፍሪካ ህብረት ታሪክ የመጀመሪያዉን የሰብዓዊ  አገልግሎት የሚሰጡ ከ800 በላይ  በጎ ፊቃደኛ የጤና ባላሙያዎችን ከ20 የአፍሪካ ሀገራት በማስተባባር የኢቦላ ቫይራስን ተቆጣጥረዉታል፡፡ በመጨረሻም  የአፈሪካን የቀጣይ 50 ዓመት ረዕይና አቅጣጫ የሚያሰይ  ፍኖተ ካርታ/እቅድ አጀንዳ 2063ን ከ25 የአፍሪካ ሀገራት ብሄራዊ የልማት እቅድ ጋር በማጣጣም ተግባራዊ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ አህጉሪቷ የረዥም ጊዜ እቅድ ባላቤት መሆንዋ  በአጭር ጊዜ ችግሮች  ላይ ከማተኮር ተላቃ በጣም ወሳኝ ወደ ሆነዉ  የስነ ህዝብ ጉዳዮች ወጣቶችና ሴቶች ላይ እንዲሆን አድርገዋል በማለት ታቶ ማቶንግ በዘአፈሪካን ሪፖርት ላይ አስፍራለች፡፡

በሌላ በኩል ኮፊ ማኮኩ የተባለ የደቡብ አፍሪካ የኑድ ሚሊኒያም ፕሮጀክት ዋና ዳይሬክተር የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ትልቅ ክብር ያለዉና በዚያዉ ልክ በበርካታ ፈታናዎችም የተሞላ ነዉ ይላል፡፡ ቦታዉ በጣም አጓጊ፣ ጠንካራ ስራን የሚጠይቅና፤ ተስፋ የሚያስቆርጥ በፖለቲካዉ ዘርፍ ትግስት  አስጨራሽ ጉዳዮች ያሉበት መሆኑ የማያጠያይቅ ነዉ፡፡ ስለዚህ ይላል ፀሃፊው ለምንድነዉ ዲላሚኒ ዙማ ይህን ቦታ ለመያዝ የፈለጉት?  እዉን  ዶ/ር ኒኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ ይህን ስልጣን ከከቀድሞ የህብረቱ ሊቀመንበር ጂን ፒንግ ሲቀበሉ በአፍሪካ ዉስጥ ያለን የፖለቲካ አየር የመቀየር ፍላጎት ነበራቸው?

 

ዲላሚኒ ዙማ የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ህብረት ሴት ሊቀመንበር ሆነዉ ሲመረጡ በህብረቱ ዙሪያ ያሉ አመለካካቶችን በመቀየር አዲስ አስተሳሰቦች እንዲኖሩ ያደርጋሉ የሚል ተስፋ ነበር፡፡

 

በመሆኑም ህብረቱን  በአግባቡ፣ በከፍተኛ ብርታትና ወኔ መምራት እንደሚችሉ ለማሳያት የተለጠጡ አላማዎችንና ግቦችን በመተለም ስራቸውን ጀምረዋል፡፡

 

በመጀመሪያ ደረጃ  በማሊ ያለዉን  ግጭትና በሳህል አካባቢ ያለዉን የኢስላማዊ አክራሪዎች  እንቅስቃሴን መቆጣጠር፤ ሁለተኛ የአፍሪካ ህብረት በገንዘብ እራሱን እንዲችል ማገዝ፣ በሶማሊያ ያለዉን የፖለቲካ ሽግግር በሰላም እንዲጠናቀቅ ማገዝና በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክና ታላላቅ ሃይቆች አካባቢ ያለዉን የሰላም ጥረት መደገፍ ዋና ዋና እቅዶችዋ እንደነበሩ የዘአፍሪካ ሪፖርት ዘገባ ያመላክታል፡፡

 

ይሁን እንጂ  አንዱም ከላይ የተዘረዘሩት ግቦች አልተሳኩምይላል ኮፉ ማኮኩ። ምክንያቱም የአፍሪካ ህብረት ዛሬም በፋይናንስ  ከዉጪ ለጋሾች ጥገኝነት አልተላቀቀም፤ የአፍሪካዊያን ገፅታን ስንመለከት ለእድገት የሚያደርጉት መፍጨርጨር እንዳለ ሆኖ የተሻለ ህይወት ፍለጋ በህገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ  ለመግባት ሲጥሩ ጀልባ ሰጥሞ ህይወታቸዉ የሚያልፉ አፍሪካዊያን  ጉዳይ የሚዲያዎች ዋነኛ መነጋገሪያ እንደሆነ ነዉ፡፡ ስለዚህ ዙማ ሲመረጡ የገቡትን ቃል  አንዱንም አልፈጸሙም ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፡፡    

በሌላ በኩል ኒዉስ 24 ዶ/ር ዲላሚኒ ዙማ በቆይታቸዉ ያሳኩዋቸዉ ሶስት ነገሮችን እንደሚከተለው አስቀምጧል፡፡

አንደኛው እአአ በ2013 ዓ.ም በተከበረዉ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት/ህብረት 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዲላሚኒ ዙማ የአፍሪካን የ50 ዓመት የረዥም ጊዜ ራዕይ የሚያሳይ መሪ እቅድ አጀንዳ 2063ን ይፋ አድርገዋል፡፡ የአጀንዳዉ ዉጤታማነት የሚወሰነዉ በያንዳንዱ አባል ሀገራት አፈፃፃም ላይ የሚመሰረት ቢሆንም ዲላሚኒ ዙማ ግን አጀንዳዉ የፖለቲካ ትኩረት እንዲያገኝና እንዲተዋወቅ ያደረጉት ጥረት ከፍተኛ ነዉ፡፡

ሁለተኛ ዲላሚኒ ዙማ የመጀመሪያዋ  ሴት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር በመሆን  ፋና ወጊ ሴት ያደርጋቸዋል፡፡ ብዙዎች እንደሚስማሙበት አህጉሪቱ የመሪነት ቦታን ሴቶች እንዲይዙ ፍላጎት ባይኖረዉም  በዚህ ዓመት በተካሄደዉ የኮሚሽነርነት ምርጫ ላይ ከተሳተፉ አምስት እጩዎች ሁለቱ ሴቶች መሆናቸዉ  ዙማ  ለሴቶች ጥሩ ዓርዓያ በመሆናቸዉና የእሳቸዉን ፈለግ ለመከተል ካላቸዉ  ፍላጎት የመነጨ  ነዉ፡፡

ዙማ የሴቶች መብት  ለሁለት ተከታታይ ጊዜያት የህብረቱ ዋና አጀንዳ እንዲሆን በማድረግና የአህጉሪቱ የተለያዩ አካላት የሴቶች ያለእድሜ ጋብቻን  ለመከላከል ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመተባባር የንቅናቄ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ በዚህም  የተወሰነ ዉጤት ተገኝቷል፡፡

ሦስተኛ የዲላሚኒ ዙማ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥ ደቡብ አፍሪካዊያን ትኩረታቸዉን ለአህጉራዊ ጉዳዮች እንዲያደርጉ አድርጓል፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ወደ ሀገር ቤት ሲጠሩና ንግግር እንዲያደርጉ ሲጋበዙ ስለአፍሪካ ጉዳዮችና አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን በደቡብ አፍሪካ በነጻነት መንቀሳቀስ እንዳላበቸዉም አፅንኆት ሰጥተዉ   ተናግረዋል፡፡ በዚህም ደቡብ አፍሪካዊያን ድንበር ተሸጋሪ አስተሳሰብ እንዲኖራቸዉ አድርጓል ይላል የኒዉስ 24 ካሪያን ዱ ፕሌሲስ፡፡

እንዲሁም ዲላሚኒ ዙማ ያልሰሯቸዉ ስራዎች ብሎ ኒዉስ 24 የሚከተሉትን ጉዳዮች አቅርቧል፡፡

አንዱና ዋነኛዉ በዲላሚኒ ዙማ ላይ የሚሰነዘርባቸዉ ትችት ሙሉ ጊዜያቸዉን ለህብረቱ ስራ ከማዋል ይልቅ ለኤኤንሲ ጉዳዮች ወደ ደቡብ አፍሪካ በመመላለስ አጥፍተዋል ሲል ይተቻሉ፡፡

ሁለተኛ ዲላሚኒ ዙማ ወደ ስልጣን ለመምጣት ባደረጉት የምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት አፍሪካን አንድ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዉ ነበር። ነገር ግን በገቡት ቃል መሰረት አፍሪካን አንድ የማድረግ ስራዉ አልተሳካላቸዉም ይላል የኒዉስ 24 ዘገባ፡፡

ሦስተኛ በአፍሪካ ላሉ ችግሮች አፋጣኝ  መፍትሄ ለመስጠት ከሚሰሩት ስራዎች በዘለለ  በአህጉሪቱ የሚስተዋሉ ግጭቶች ዛሬም መፍትሄ አልተገኘላቸዉም፡፡

የናይጄሪያ የቀድሞ ብሄራዊ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሊቀመንበር ቺዲ አንስለም ኦዲንካሉ ዲላሚኒ ዙማ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ሚናቻዉን በአግባቡ አልተወጡም ይላል፡፡ ዙማ በስልጣን ዘመናቸዉ የሰሩትን ስራ የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ የሚችል ሰዉ የለም ብሏል፡፡

አንድ ሰዉ አንድን ስራ ሃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት እንዲችል ዝግጅት ማድረግ አለበት፡፡እንዲሁም ዙማ ወደ አዲሰ አባባ የመጡት የአፍሪካ ህብራት ስራን ለመስራት ሳይሆን ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንትነት የምረጡኝ ቅስቀሳ የመጡ ነዉ የሚመስለዉ ሲል ቺዲ አንስላም ዲላሚኒ ስራቸዉን አልሰሩም ብሏል፡፡

በለንደን ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ስቴፈን ቻን ዲላሚኒ ዙማ አህጉሪቷ ያለችበትን ፈታኝ ጉዳዮች ግጭቶችና ወታደራዊ አስተዳዳሮችን በማስተካከል ወደ ህዝቡ መድረስ ያልቻሉ መሪ ናቸዉ ብሏል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን ዲላሚኒ ዙማ በደቡብ ሱዳን ያለዉን ጦርነት ለማስቆም የሰሩት ስራ አነስተኛ ነዉ ይላሉ፡፡የሱዳንን ጉዳይ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ እንዲሆን ሰብሮ ይዞ የወጣ አንድም አክቲቪስትም አልነበረም ብሏል፡፡

ጋናዊዉ ፀሃፊና ተንታኝ ኢማኑኤል ዶግቤቪ በቻንና ኦዲንካሉ ሀሳብ አይስማማም። ዲላሚኒ ዙማ እንደሴትነታቸው በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት በጣም ጥሩ ስራዎችን እንደሰሩ ይገልፃል፡፡

ዶግቤቪ ዙማ አብራዋቸዉ ከሚሰሩ ወንዶች ጋር ጥሩ ግንኙነት በመፍጠር ረገድም የተዋጣላቸዉ ነበሩ ይላል ተንታኙ፡፡

የአፍሪካ ህብረት ያፀደቃቸዉን አጀንዳዎችና ስምምነቶችን እያንዳንዱ ሀገር ወደ ተግበር እንዲቀይሩት የሚያስገድድ ስልጣን የለውም፡፡ ስለዚህ ሀገራት አንዳንድ ህጎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉና ተግባራዊ ያላደረጉትን ሀገራት ተጠያቂ ማድረግ የሚያስችል ህግ የለም፡፡

መሪዎቹ በስበሰባ ተገናኝተዉ በሚወጡ ህጎች ላይ ፊርማቸዉን ከማኖር በስተቀር ህጉን ተግባራዊ የማድረግና ያለማድረግ የእያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገራት ጉዳይ ነዉ ብለዋል፡፡

በእርግጥም ዲላሚኒ የደቡብ ሱዳንን ችግር እና የዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎን ጉዳይ መፍታት አልቻሉም፤ ነገር ግን በአፍሪካ ታሪክ ከመጀመሪያ ዙር ምርጫ በኋላ ስልጣን የለቀቁት የናይጄሪያዉ ጉድ ላክ ጆናታን በእሳቸዉ የስልጣን ዘመን መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም በማለት ይከራከራሉ ጋናዊዉ ፀሃፊና ተንታኝ ኢማኑኤል፡፡

የአፈሪካ ህብረት በፋይናንስ እራሱን እንዲችልም ጥረት አድርገዋል፡፡

የህገ ወጥ ገንዘብ ዝዉዉር በአፍሪካ ምጣኔ ሃብት ላይ የሚያደርሰዉን ተጽዕኖ የሚያጠና  ከፍተኛ ፓናል በማዋቀር አፍሪካ የምታጣዉን ከፍተኛ መጠን ያለዉን ገንዘብ በማስቀረትና በአፍሪካ ምጠኔ ሃብት ላይ ያለዉን ተጽዕኖ በማስቀረት ለራስዋ እድገት ማዋል የምትችልበትን ሁኔታ በመለየት መልካም ስራ ማበርከታቸውን አመልክቷል፡

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ 24/2009 ኢትዮጵያ በግሎባል ኢንቫሮመንት ፋሲሊቲ ድርጅት የውሳኔ ሰጪ አካል ውስጥ ተሳታፊ እንድትሆን ግብዣ ቀረበላት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የ"ግሎባል ኢንቫሮመንት ፋሲሊቲ" ዋና ስራ አስፈጻሚ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የግሎባል ኢንቫሮመንት ፋሲሊቲ ከለጋሽ አገሮች ገንዘብ በማሰባሰብ በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ አገሮችን በገንዘብና በቴክኒክ በመደገፍ ይታወቃል።

አገሪቷ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እያገኘች ከመጣቸው ተጽዕኖ ፈጣሪነት አኳያ በድርጅቱ የውሳኔ ሰጪ አካል ውስጥ ተሳትፎ ቢኖራት የተሻለ መሆኑ ተገልጿል።

በዚሁ መሠረት ድርጅቱ "ለኢትዮጵያ ግብዣ አድርጎላታል" ነው የተባለው።

ውይይቱን የተከታተሉት የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብር ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ እንደገለጹት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለግብዣው አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል።

ግሎባል ኢንቫሮመንት ፋሲሊቲ በቀጣይ ዓመት ጥቅምት ላይ የሚያዘጋጀው ጉባኤም በኢትዮጵያ እንዲደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መስማማታቸውንም ተናግረዋል።

ጉባኤ በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ ለጋሽ አገሮች ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የሰራችውን ሥራ በተግባር አይተው የበለጠ ድጋፍ እንዲያደርጉ "እድል ይፈጥራል" ተብሏል።

እስካሁን ባለው ተመክሮም "ኢትዮጵያ ከለጋሽ አገሮች የምታገኘውን ገንዘብ በአግባቡ ስራ ላይ በማዋል ትታወቃለች" ብለዋል ሚኒስትሩ።

ግሎባል ኢንቫሮመንት ፋሲሊቲ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አሁን ካለበት እንዲጨምርና በሶስተኛ ወገን በኩል የሚደርሰው ድጋፍ በቀጥታ እንዲሆን ጥያቄ መቅረቡን ገልጸዋል።

ድርጅቱ አትዮጵያ የአካባቢ መራቆቱን በመከላከል ረገድ እያከናወነች ያለውን ተግባር እንዲደግፉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጠየቃቸውን አመልክተዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ናኦኮ ኢሺ  እንደተናገሩት  በፋሲሊቲውና በኢትዮጵያ መንግሰት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር ውይይት አድርገዋል።

''ከዚህ በፊትም ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ አጋሮች ነን'' ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ በቀጣይም ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለተኛው የድርጅቱ ጉባኤ በቀጣይ ጥቅምት በአዲስ አበባ እንዲካሄድም ቃል እንደተገባም አስታውቀዋል።

ድርጅቱ 183 የዓለም አገሮችን በአጋርነት የያዘ ሲሆን፤ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የሲቪል ማህበራትና የግል ድርጅቶች በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በጋራ የሚንቀሳቀሱበት ነው።

Published in አካባቢ

                                                         ግረማቸው ተስፋዬ (ኢዜአ)

 

የአፍሪካ ኅብረት መዲና፣ አዲስ አበባ 28ኛውን የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ለማካሄድ ሽረ ጉድ ስትል መሰንበቷ በስኬት የተጠናቀቀውን ጉባዔ በዋቢነት መጠቀስ ይቻላል።

እነሆ! እንግዶቿን ያለምንም ኮሽታ አስተናግዳ ወደመጡበት መሸኘት ችላለች።

"ከፍተኛ አምራች ኃይል ለመጠቀም፣ ወጣቶች ላይ መዋዕለ ነዋይ እናፍስስ" በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የቆየው ጉባዔ በርካታ ውሳኔዎች ተላልፈውበታል።

በተለይ “በአህጉሪቷ የወጣቶች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አለብን” የሚለው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት መሪዎቹ የመከሩበት ነው። መሪዎች በየአገራቸው የስራ አጥነት ችግርን ለመፍታትና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመፍተሄ አቅጣጫዎች ለማስቀመጥ የቻሉበት ጉባዔ ነው ማለት ይቻላል።

ከአባልነት ወጥታ ዓመታትን ከወንድሞቿ የተለየችው ሞሮኮ በአባልነት ተመልሳ መቀላቀሏ የጉባኤው አዲስ ክሰተት ሲሆን፤ "የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍታት" ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

ሞሮኮ ከ33 ዓመታት ቆይታ በኋላ ነው ወደ አፍሪካ ኅብረት የተመለሰችው።

አገሪቷ እኤአ በ1984 ራሷን ከወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በይፋ ማግለሏ ይታወሳል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቷ ሞሮኮ “ግዛቴ” የምትላትን ሰሃራዊ ዴሞክራቲክ ዓረብ ሪፐብሊክን በወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአባልነት መቀበሉ እንደነበር ይወሳል።

የአትላንቲክ ውቅያኖስን ተንተርሳ ያለችውን ትንሿን ሰሃራዊ ዴሞክራቲክ ዓረብ ሪፐብሊክን በ1980ቹ ስፔን ለቃ ስትወጣ ሞሮኮ “የአገሬ አንዷ ግዛት ናት” በማለት እስከ አሁን ድረስ የአገሪቷን 60 ከመቶ በቁጥጥሯ ስር እንዳደረገች ነው።

በዚህም ከአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ተነጥላ ብቻዋን ለ33 ዓመታት አሳልፋለች። ይሁን እንጂ ብቸኝነቱ የበረታባት ሞሮኮ “መልሱኝ” ብላ ባለፈው ሐምሌ በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ጥያቄዋን በይፋ አቅርባለች።

ከ53ቱ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች 39ኙ “ለመመለስ ከፈልግሽ ቤትሽ ነው” ብሎ ድጋፍ ሰጥተው ሲቀበሏት፤ አልጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ግን መመለሷን በይፋ ተቃውመዋል።

ሌላው ደግሞ የኅብረቱን ኮሚሽን በሊቀ መንበርነት ማን ይምራ? የሚለው ዋነኛውና በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው ጉዳይ ነው። የኬንያዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር አሚና መሐመድ “ከዶክተር ንኮሶዛና ድላሚኒ ዙማ ሊቀ መንበርነቱን ይረከባሉ” ተብሎ ሲጠበቅ ሳይታሰብ የቻዱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሳ ፋቂ መሃማት የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ሆነው ተመረጡ።

በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ያገኙት የምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የሊቀ መንበርነቱን ቦታ በመያዝ “ኅብረቱን በተከታታይነት ሴቶች በሊቀ መንበርነት ሊመሩት ይችላሉ” ተብሎ ሲጠበቅ ሳይታሰብ የቻዱ ሙሳ ከኅብረቱ ድጋፍ በማግኘት ቦታውን ይዘዋል።

በዘንድሮው ምርጫ ለኮሚሽኑ ሊቀመንበርነት ኬንያዊቷ ዶክተር አሚና መሐመድ፣ የቀድሞዋ ጋዜጠኛ ቦትስዋናዊቷ ፔሎኖሚ ቬንሰን - ሞታይ፣ የኢኳቶሪያል ጊኒ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አጋፒቶ ምባ ሞኩይንና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ የመካከለኛው አፍሪካ ልዩ ተወካይ የነበሩት ሴኔጋላዊው ዶክተር አብዱላይ ባዚልይ እና የምርጫው አሸናፊ የቻዱ ሙሳ ፋቂ መሃማት በዕጩነት መቅረባቸው ይታወሳል።

ኮሚሽኑን በሊቀ መንበርነት የመሩት ዶክተር ንኮሶዛና ድላሚኒ ዙማን ጨምሮ አማራ ኤሲ፣ አልፋ ኦማር ኮናሬና ዣን ፒንግ ሲሆኑ፤ አሁን ደግሞ ሙሳ ፋቂ መሃማት ተረኛ ሆነዋል።

ሌላኛው የጉባዔ ክስተት ኅብረቱን ለአንድ ዓመት በሊቀ-መንበርነት ለመምራት የጊኒው ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ከማሊው ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቤ ስልጣኑን መቀበላቸው ነው።

ለአንድ ዓመት በሊቀ -መንበርነት የመምራቱ ስራ በየቀጣናው በዙር የሚደርስ ሲሆን፤ የዘንድሮው ተረኛ ምዕራብ አፍሪካ ሆናለች። የባለፈው ዓመት የመካከለኛ አፍሪካዋ አገር ማሊ ዘመኗን ጨርሳ ለተረኛዋ አስረክባለች።

የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በዚሁ በ28ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተገኝተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካውያንን ጥቅሞች በሚያስቀድሙ ጉዳይች ላይ በቅርበት ለመስራት ትብብሩን እንደሚያጠናክር የሚገልጽ ንግግር ማድረጋቸው ለአህጉሩ ተስፋ የሰጠ የጉባዔ አበይት ጉዳይ ሆኖ አልፏል።

በመሪዎቹ ጉባዔ ላይ የታደሙት ዋና ጸሃፊው እንደገለጹት፤ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰላምና ጸጥታ ማስከበር ተልዕኮ ትልቁን ድርሻ እየተወጣች ነው።

በርካታ አገሮች በሮቻቸውን በዘጉበት በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ አገሮች በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ስደተኞችን ማስጠለላቸውን አድንቀዋል። “አፍሪካ በፈጣን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እየገሰገሰች በመሆኗ ሁላችን ልንማር ይገባል” ብለዋል ዋና ጸሃፊው።

በዓለም ላይ ዘላቂ የልማት ግቦች ስኬታማ ለማድረግ በአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ በአህጉሪቷ ከሚገኙ ልዩ ልዩ “የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ጋር ግንኙነታችንን እናጠናክራለን” ያሉት በዚሁ በ28ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ነው።

የአፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ድርጅቶች በአህጉሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠርና ዴሞክራሲ እንዲጎለብት ያደረጉት እንቅስቃሴ የዓለም የጋራ ጉዳይ በመሆኑ የሚበረታታ ነው።

“በአህጉሪቱ ዘላቂ ልማትና ብልጽግና የሚፈጠረው ሰላምና ጸጥታ ሲሰፍን በመሆኑ የአፍሪካ ህብረት መዋቅር እንዲሻሻልና የህብረቱ ጸጥታ ምክር ቤት እንዲጠናክር የመንግስታቱ ድርጅት ዘላቂነት ያለው የገንዘብ ድጋፍ ይለግሳል” ብለዋል።

በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 28ኛ የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ የተሻለች አህጉር ለመፍጠር የሚያግዙ ውሳኔዎችን ማሳለፉ የተገለጸውም ለዚሁ ነው።

ኢትዮጵያ ጉባዔውን በተሳካ መልኩ አስተናግዳ እንግዶችዋን ወደ የአገራቸው መሸኘት ችላለች።

Published in ዜና-ትንታኔ

አዲስ አበባ ጥር 24/2009 "በኢትዮጵያ ያለው ሰላም፤ አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ያለች አላስመሰላትም" ሲሉ የ28ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ታዳሚዎች ተናገሩ።

የመሪዎቹ ስብሰባም በተለያዩ ኩነቶች ለየት ባለ መልኩ እንደተካሄደ የስብሰባው ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባጋጠማት ሁከትና ግርግር ከመስከረም 28 ጀምሮ የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጇ የሚታወስ ነው።

በመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ልዩ አማካሪ ማገድ አብድላዚዝ ለኢዜአ እንዳሉት "አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ያለች አትመስልም፤ ምንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምልክት የለም"።

በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች በመሄድ ምንም አይነት የጸጥታ ችግር እንዳላጋጠማቸውና ሌሎችም ወደፈለጉበት ቦታ ያለምንም ገደብና ቁጥጥር በመሄድ አገልግሎት ሲያገኙ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

"ከዚህ በመለስ ስብሰባውም በሰላም ተጠናቋል፤ ሰላምን የሚያደፈርስ ምንም አይነት ችግር አላየሁም" በማለት አስተያየት ሰጥተዋል። 

"ኢትዮጵያ ሕብረ-ብሄራዊት አገር ብትሆንም ሁሉም በአንድ ላይ የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው" ያሉት አማካሪው "የተለያዩ አመለካከቶች በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ይደመጣሉ፤ ይሁንና ይህም ኢትዮጵያን አልጎዳትም "ብለዋል።

28ኛው የመሪዎች ስብሰባ የተለየ እንደሆነና ስብሰባው የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን መቀበሉን ለአብነት አንስተዋል። 

የመንግሥታቱ ድርጅትና የአፍሪካ ኅብረት በሰላምና ደኅንነት፣ በልማት እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ላይ ተቀራርበው እንዲሰሩ የሚያስችሉ ውሳኔዎች ተላልፈውበታል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝቦች ለስብሰባው ታዳሚዎች የተደረገውን እንግዳ አቀባበልም ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በአፍሪካ ኅብረት የኢንዱስትሪ ክፍል ኃላፊ ሃሰን ሁሴን በበኩላቸው "በኢትዮጵያ ሰላም አለ፤ በአገሪቱ ያለው ሁኔታም መልካም ነው" ብለዋል።

ይህም አገሪቱ ሰላምና ልማት በማረጋገጥ ረገድ በትክክለኛ ጎዳና ላይ መሆኗን አመላካች እንደሆነ ጠቁመዋል።

ስብሰባው በሰላም እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎችን በተገቢው መልኩ በመመደብ የተደረገው ርብርብ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ስብሰባው በሰላም ለማጠናቀቅ መቻሉን ነው ያስረዱት።

28ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ፤ የኅብረቱን ሊቀ መንበርና ሌሎች በርካታ አህጉራዊ ውሳኔዎችን በማሳለፍ በትላንትናው ዕለት ተጠናቋል።

Published in ፖለቲካ

አምቦ ጥር 24/2009 በምእራብ ሸዋ ዞን ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የሰብል ምርታማነት እያደገ መምጣቱን በምእራብ ሸዋ ዞን የሊበን ጃዊ ወረዳ አርሶአደሮች ገለጹ፡፡

በዞን ደረጃ በ262 ሺህ 500 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚካሄደው የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በሊበን ጃዊ ወረዳ ሮጌ ዳኒሳ ቀበሌ ተጀምሯል፡፡

የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ንጉሴ አበበ በሰጡት አስተያየት  ባለፉት አመታት በማሳቸው ላይ የሰሩት እርከን በጎርፍ ተጠርጎ የሚሄደውን አፈር በማስቀረቱ ከመደበኛና ከመስኖ እርሻ ከሚዘሩት የሰብልና አትክልት ምርት መጠን ሊጨምር ችሏል ።

ዘንድሮም የመኸሩን ምርት በማንሳት በመስኖ በመታገዝ ጥቅል ጎመንና  ቀይ ሽንኩርት በማልማት ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል ።

ባለፈው አመት በመስኖ ካለሙት የጓሮ አትክልት ሽያጭ 75 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ አግኝተው እንደነበር አስታውሰዋል ።

ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር አበበ እንሰርሙ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ የድንጋይ እርከን በመስራታቸው ከመኽሩ እርሻ  ከሰበሰቡት የገብስና የስንዴ ሰብል የተሻለ ምርት ማግኘት እንደቻሉ ገልፀዋል ።

ከዚህ ቀደም ከማሳቸው ላይ ያገኙት የነበረው አነስተኛ ምርት በወቅቱ ወደ 20 ኩንታልና ከዚያ በላይ ማደጉን ጠቅሰዋል ። 

የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራውን ያስጀመሩት  የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊና የዞኑ መስተዳደር ምክትል ኃላፊ አቶ ፉፋ ቴሶ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል ።

እየተገኘ ያለውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠልም በዚህ አመት 262 ሺህ 500 ሔክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው እንደሚካሄድ ተናግረዋል ።

ለሰላሳ ቀናት በሚካሄደው የአካባቢ ጥበቃና ልማት ስራ 541 ሺ 250 ህዝብ ተሳታፊ እንደሚሆን ጠቅሰዋል ።

በአካባቢ ጥበቃና ልማት ስራው 124ሺ 426 ኪሎ ሜትር  እርከንና 149 ሺህ ሜትር ኪዩብ የክትር ስራ እንደሚከናወን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በዞኑ ባለፉት አምስት አመታት 761 ሺህ 812 ሄክታር መሬት ላይ ልማቱ መካሄዱን  አቶ ፉፋ አስታውቀዋል።

Published in አካባቢ

መቀሌ ጥር 24/2009 " በንግድ ዘርፍ ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን በመፍታት ህዝቡ በጥልቅ መታደሳችን ማረጋገጫ እንዲያገኝ በትኩረት ሊሰራ ይገባል" ሲሉ  የንግድ ሚኒስትሩ ዶክተር በቀለ ጉላዶ አሳሰቡ፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በንግድ ዘርፍ የነበረውን አፈፃፀም የሚገመግም አገር አቀፍ የውይይት መድርክ ዛሬ በመቀሌ ተጀምሯዋል፡፡

በውይይቱ መክፈቻ ላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ በጥልቅ ተሀድሶ ወቅት ለህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ማጣት መነሻ የሆኑ ችግሮችን በመለየት ለማስተካከል የሚያስችል ግብአት ተገኝተዋል፡፡

በዘርፉ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድም በተለይ በድጎማ የሚገቡ ሸቀጣ ሸቀጦችና የነዳጅ ምርቶችን በአግባቡ ወደ ህብረተሰቡ እንዲደርሱ ተገቢ የቁጥጥር ስርዓት  መዘርጋት  እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ኮንትሮባድና ህግ ወጥ ንግድን በመቆጣጠርም ህጋዊ ነጋዴዎችን መታደግና በንግዱ ዘርፉ የሚሰጡ የአገልግሎት መብቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፣ በተሟላና በተቀላጠፈ መንገድ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡

''በንግድ ዘርፍ ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን በመፍታትና በዘርፉ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን በማድረግ ህዝቡ በጥልቅ መታደሳችን ማረጋገጥ ይኖርበታል'' ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳሉት አገሪቱ  ከምታስገኘው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ግኝት 75 ከመቶ ከንግድ ዘርፍ ነው።

ለአገር ውስጥ ከሚቀርበው የብድር መጠን ደግሞ 35 ከመቶ የንግድ ዘርፉ መሆኑን አመልክቷዋል።

ዘርፉ  ከሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች የተሳሰረ በመሆኑ በንግዱ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ደግሞ የተቀናጀ ጥረት ይፈልጋል።

በንግድ ምዝገባና እድሳት አምስት ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በአገር አቀፍ ደረጃ በኔት ዎርክ መተሳሰራቸውን የገለፁት ደግሞ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አሰድ ዝያድ ናቸው፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ከአምስቱ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች አንድ ነጥብ ሦስት  ሚሊዮን የንግድ ማህበረሰብ የንግድ ፍቃድ አሳድሰዋል፡፡ 800ሺህ ሰዎች ደግሞ የንግድ ምዝገባ አካሂዷዋል፡፡

እስከ አሁን በመረጃ መረቡ ያልተሳሰሩ አራት ክልሎች ወደ አንድ የንግድ መረጃ ቋት  እንዲገቡ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን መኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል፡፡

በንግድ ዘርፉ ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችና ችግሮች ለማስወገድ ባለፈው ዓመት አዲስ የንግድ አዋጅ በመውጣቱ ውጤተማ ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል፡፡ ፡፡

ቀደም ሲል ብቸኛ አስመጪና አከፋፋይ በማለት የህብረተሰቡን አማራጭ ሲያሳጡ የነበሩ አሰራሮች በአዲሱ አዋጅ እንዲቀሩ ተደረገዋል።

የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር  ተወካይ አቶ ጥላሁን ታረቀ በበኩላቸው፣ በክልሉ የንግድ ሪፎርሙ ተግባራዊ ለማድርግ በርዕስ መስተዳድሩ የሚመራ ኮማንድ ፖስት  ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ዓለም ወደ አንድ የገበያ ማዕከል በተሰባሰበበት ወቅት የንግድ ስርዓታችን ዘመናዊና ተወዳዳሪ ለማድርግ ቀጣይነት ያለው  ክትትልና የልምድ ልውውጥ ያስፈልጋል "ብለዋል፡፡

ለሶስት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ ላይ ሁሉም ክልሎች የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀማቸውን አቅርበው እንደሚወያዩም ተመልክቷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 24/2009 በአራት ማሰልጠኛ ጣቢያዎች የተሃድሶ ሥልጠና ተከታትለው ነገ የሚመረቁ ሠልጣኞች “በልማት በመሳተፍና ማህበራዊ አገልግሎት በመስጠት በህዝብ ዘንድ በጎ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል”  ሲሉ የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬቴሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ገለጹ።

በሁከትና ግርግሩ ተጠርጥረው በሁለተኛ ዙር የተሃድሶ ሥልጠና የወሰዱ 11 ሺ 352 ሰልጣኞች በነገው ዕለት ተመርቀው ይለቀቃሉ።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስትርና የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬቴሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በመጀመሪያ ዙር አስር ሺ የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች ተመርው ከህብረተሰቡ ጋር መቀላቀላቸው ይታወሳል። 

በወቅቱ ሠልጣኞቹ ሲመረቁ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የማይነጣጡሉ የአንድ አገር ህልውና መሰረት መሆናቸውን ወጣቱ ተገንዝቦ እነዚህን እሴቶች የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መገለጹ የሚታወስ ነው።

የመጀመሪያ ዙር ተመራቂዎችም በሰላምና በልማት መስክ በጎ ሚና እየተጫወቱ መሆኑ ነው የተመለከተው።

የሁለተኛ ዙር ሥልጠና የተከታተሉት በኦሮሚያ ሰንቀሌ፣ ጦላይ፣ በይርጋለም አቦስቶ እንዲሁም በአማራ ክልል ብር ሸለቆ ማዕከላት ነው።

ተመራቂዎቹ ለ20 ቀናት የተከታተሉትን ሥልጠና ጨርሰው ነገ ወደ ህብረሰተቡ እንዲቀላቀሉ ይደረጋል።

ሥልጠናውን ተከታትለው ወደ ኅበረተሰቡ የሚቀላቀሉት “ተመራቂዎቹ ባገኙት ሥልጠና በልማት ተሳትፎናና በማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ በህብረተሱ ዘንድ በጎ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል” ብለዋል።

ሠልጣኞቹ ስለህገ - መንግስቱ፣ አገሪቷ ስለምተከተለው ስርዓት፣ ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም ቀጣይ አገራዊ ጉዞ ምን እንደሚመስል በቂ ግንዛቤ እንዲይዙ መደረጉን አቶ ሲራጅ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ሲራጅ ገለጻ፤ ነገ የሚመረቁት ሠልጣኞች የግንዛቤ እጥረት ያለባቸውን ሰዎች ስለ አገራቸው በቂ ግንዛቤና መረዳት እንዲኖራቸው ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመጀመሪያው ዙር ሥልጠና ወቅት የተለያዩ ችግሮች እንደታዩ አስታውሰው፤ በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ በተወሰደው ልምድና ተመክሮ መሰረት የሁለተኛው ዙር ስልጠና ችግሮች እንዳይከሰቱ መደረጉን ተናግረዋል።

በተሃድሶ ሥልጠና ተከታትለው የተመረቁት ሲለቀቁ የመንግስት ሰራተኞች ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

አሁን አገሪቷ ካለችበት ሰላም አኳያ ሶስተኛ ዙር የተሃድሶ ስልጠና የሚገቡ ተጠርጣሪዎች እንደማይኖሩ አመልክተው፤ “በቁጥጥር ስር የሚገኙ ቀሪዎቹ ተጠርጣሪዎች እንደፈጸሙት ወንጀል ተግባር በሕግ የሚጠየቁ ይሆናል” ብለዋል።

ኮማንድ ፖስቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ ስለለው አጠቃላይ ሂደት፣ አፈፃፀምና ቀጣይ ሁኔታ እንዲሁም የሶስት ወር ግምገማ በቅርቡ ለህዝብ መረጃ እንደሚሰጥም አቶ ሲራጅ ገልጸዋል።

ሠልጣኞቹ በማዕከሉ ቆይታቸው "የተፈጠረው አመፅ አይደገምም፣ የቀለም አብዮት፣ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ እንዲሁም ወጣቶች ሚና" በሚሉ ርዕሶች ላይ የተዘጋጀውን ስልጠና ተከታትለዋል።

የአገሪቷን ህልውና ለማስጠበቅና የሕዝብ ሠላም፣ ፀጥታና ደህንነት ላይ የተደቀነውን ከፍተኛ ስጋት ለመቀልበስ በመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወቃል።

Published in ፖለቲካ

መቀሌ ጥር 24/2009 " ባንኩ ያስቀመጥኩትን ገንዘብ ያለአግባብ ለሌላ ግለሰብ አሳልፎ በመስጠት በድሎኛል "ሲሉ  የወጋገን ባንክ ደንበኛ የሆኑ አንድ አርሶ አደር ቅሬታቸውን ገለጹ ፡፡

ባንኩ በበኩሉ"  ጉዳዩን የፈጸምኩት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው "  ብሏል።

በጉዳዩ ላይ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የህግ ባለሙያ ፍርድ ቤቱና ባንኩ በፈፀሙት ስህተት በግለሰቡ መብት ላይ  የህግ ጥሰት መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡

አቶ መለስ ገብረመድህን አብርሃ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ዓድዋ ወረዳ የላዕላይ ለጎምቲ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሲሆኑ፤ ገንዘብ በመቆጠብ  ዓድዋ ከተማ በሚገኘው ወጋገን ባንክ ከአስር ዓመታት በላይ በደንበኝነት መቆየታቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በባንኩ ከ40ሺህ ብር በላይ ማስቀመጣቸውን ጠቁመው ከዚህ ገንዘብ  ውስጥ  14 ሺህ የሚጠጋ  ብር በማያውቁት ሁኔታ ባንኩ  አለግባብ  ለሌላ ግለሰብ አሳልፎ በመስጠት በደል እንዳደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡

ለማያውቁት ግለሰብ ገንዘቡን የከፈለው ባንኩ  እንዲመልስላቸው በተደጋጋሚ እየተመላለሱ ቢጠይቁም " እኛ የከፈልነው በፍርድ ቤት ትእዛዝ ስለሆነ ግለሰቡን ፈልገህ መክሰስ ያንተ  ፋንታ  ነው” በማለት ከአስር ወራት በላይ ተገቢውን ምላሽ እንደነፈጋቸው አቶ መለስ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ መለስ እንዳሉት የህግ ባለሙያዎችን አማክረው ባንኩን መከሰስ እንዳለባቸው በተነገራቸው መሰረት መጋቢት 2008 ዓድዋ በሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መስረተዋል፡፡

ይሁንና ፍርድ ቤቱ " ባንኩ በፍርድ ቤት ታዞ የፈፀመው ስለሆነ ሊከሰስ አይገባውም"  በማለት መዝገቡ እንዲዘጋ በማድረግ ሌላ ተጨማሪ በደል እንደፈፀመባቸው አመልክተዋል።

የወጋገን ባንክ ጉዳይ አስፈፃሚና የህግ ባለሙያው አቶ ተስፉ ታደለ ስለጉዳዩ ተጠይቀው  በሰጡት ምላሽ የሁለት ግለሰቦች ጉዳይ ሲያከራክር የነበረው የዓድዋ ወረዳ ፍርድ ቤት በአቶ መለስ ገብረመድህን አብርሃ የሚታወቅ የባንክ ሂሳብ ካለ ተጣርቶ እንዲቀርብ በጠየቀው መሰረት በግለሰቡ ስም ሂሳብ መኖሩን አረጋግጠው ማሳወቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ተከራካሪ ወገኖች ለአራት ወራት ያህል ሲከራከሩ መቆየታቸውን የጠቀሱት አቶ ተስፉ  እስከዚህ ጊዜ ድረስ ለባንኩ ደንበኛ ገንዘባቸው የታገደ መሆኑን እንዲያውቁት ያልተደረገበት ምክንያት  ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ለደንበኛው ለማሳወቅ በተደጋጋሚ ስልክ ደውለው  በኔትወርክ ችግር ምክንያት ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የአቶ መለስ ገብረመድህን አብርሃ ሂሳብ መኖሩን አጣርታችሁ እንድትልኩ ስትጠየቁ  በባንኩ የሚገኘውን የግለሰቡ ሙሉ መረጃ የያዘ አድራሻ፣ ፎቶግራፋቸውና የሚኖሩበት አካባቢ ተጠቅሶ ለምን እንዳልተላከ ለአቶ ተስፉ ኢዜአ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ብለዋል፡፡

በአቶ መለስ ገብረመድህን አብርሃ ስም ያለ ሂሳብ እንጂ ሌላ ማስረጃ እንዲልኩ  በፍርድ ቤቱ ባለመጠየቃቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

" በስመ ሞክሼ  የተከፈለ መሆኑን ያረጋገጥነው ደንበኛችን ወደ ባንካችን ከመጡ በኋላ ነው ፤  ፍርድ ቤቱ የተሳሳተ ትእዛዝ በማስተላለፉ የወሰደው ግለሰብ በድጋሚ በክስ ተጣርቶ ሊመልስላቸው ማድረግ እንጂ  ባንካችን ሊጠየቅ አይገባም "ብለዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ኢዜአ  ያነጋገራቸው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ  ነፃ የህግ ድጋፍ ማዕከል አስተባባሪና የህግ ባለሙያ አቶ ተስፋስላሴ ሃይሉ ባንኩ በፈፀመው ቸልተኝነትና የግለሰቡ ባለመብትነት የወረዳው ፍርድ ቤት በመጣሱ የተፈፀመ የህግ ጥሰት መሆኑን ገልጸዋል።

የህግ ባለሙያው እንዳሉት ፍርድ ቤቱ አቶ መለስ ገብረመድህን አብርሃ የተባሉ በባንኩ ሂሳብ ስለመኖራቸው ሳይሆን መጠየቅ የነበረበት ለተከሳሹ በየትኛው ባንክ ሂሳብ እንዳላቸው ጠይቆ የሚሰጠው ምላሽ መሰረት በማድረግ ለባንኩ ማሳወቅ ነበረበት።

" ሌላው የህግ ስህተት ፍርድ ቤቱ ከባንኩ የተሰጠው ማስረጃም ለተከሳሹ በመስቀለኛ ጥያቄዎች የማጣራት ስራ ሳያካሂድ እንዲታገድ ማድረጉ የህግ አግባብነት የለውም "  ብለዋል፡፡

ማዕከሉ የሙያና የምክር ድጋፍ በማድረግ በግለሰቡ የተፈፀመውን በደልና የህግ ጥሰት ለማጣራትና ገንዘባቸውን ለማስመለስ ጥረት የሚያደርግ መሆኑን አቶ ተስፋስላሴ ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥር 24/2009 ጉባኤው የአፍሪካ ህብረት አቅሙን በማሳደግ በራሱ እንዲቆም የሚያስችሉ ውሳኔዎች የተላለፉበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት “የአፍሪካ ህብረት ከተመሰረተ ጀምሮ ስትራቴጂካዊ የሆኑ ውሳኔዎች የተወሰኑበት መድረክ ቢኖር ይሄ ጉባኤ ነው”።

ኋላቀር የነበረውን የህብረቱ አሰራር ለማሻሻል የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጅቶ በሁሉም አገሮች ስምምነት መፅደቁ አንዱ የጉባኤው ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።

በፕሬዚዳንት ካጋሜ መሪነት በተዘጋጀው የማሻሻያ ሰነድ "አገራቸውን ሪፎርም በማድረግ የሚገኙ መሪዎች ግብአት የሰጡበትና የአህጉሩ ምሁራን የተሳተፉበት መሆኑም ትልቅ ውጤት ነው" ብለዋል።

"በርግጥ ሰነድ መፅደቁ ብቻ በቂ አይደለም ወደ ተግባር መሸጋገር አለበት" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለተግባራዊነቱ እንታገላለን” ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ህብረቱን ከጥገኝነትና ጣልቃ ገብነት ለማላቀቅ የአፍሪካ አገራት የህብረቱን ወጪ በራስ አቅም ለመሸፈን ከስምምነት መድረሳቸው ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ከአባላቱ በመዋጮ የሚገኘው የህብረቱ ከ60 እና 70 በመቶ በላይ ገቢ ከውጭ አገሮችና ከለጋሾች ይሸፈን ነበር።

ይሁን እንጂ ድጋፍ ሰጪዎቹ ጣልቃ እየገቡ የአፍሪካ ህብረት በራሱ እንዳይቆም ሲያደርጉት ቆይተዋል ነው ያሉት።

አሁን ግን የህብረቱ የፋይናንስ ፍላጎት በራስ አቅም መሸፈን አለበት የሚል ውሳኔ በጉባኤው መወሰኑ አንድ እርምጃ ወደፊት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለፁት የህብረቱን ወጪ በራስ አቅም ለመቻል ሁሉም አባል አገራት ከውጪ ከሚያስገቡት ገቢ ዜሮ ነጥብ ሁለት በመቶውን ለህብረቱ እንዲያስገቡ ተስማምተዋል።

ይህም ህብረቱ በዓመት ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማግኘት የተወሰነ ትርፍ ኖሮት ራሱን በራሱ እንዲያስተዳደር ያስችለዋል ነው ያሉት።

ባለፈው ዓመት ስምምነት ላይ ባለመደረሱ የኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር ሳይመረጥ መቅረቱን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በአሁኑ ጉባኤ የነበሩ ችግሮችን በማስወገድ በመግባባት ህብረቱን በሊቀመንበርነት የሚመራ ኮሚሽነር በመምረጣችን ተደስተናል" ብለዋል።

ልዩነቶችን በመፍታት ሞሮኮ ወደ ህብረቱ መምጣቷም የህብረቱ ጉባኤ ስኬት ነው በማለት ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በአህጉሩ የወጣቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግ የህብረቱ አጀንዳ ሆኖ መወያየታችንና መስማማታችን ሌላው ስኬት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የህብረቱን ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ ማድረጓንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

Published in ፖለቲካ

ዲላ /ነቀምቴ ጥር 24/2009 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ልማትን በማስቀጠል ዕድገቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረጉን የጌዴኦ ዞን ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።

የጌዴኦ ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ኮሎኔል ጀማል ሻለ ለኢዜአ እንደገለጹት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ መንግስት አዋጁን አውጥቶ ተግባራዊ ካደረገ በኋላ የፀረ ሠላም ኃይሎችን እንቅስቃሴን መከላከል ተችሏል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የሕብረተስቡን ሠላምና ፀጥታ ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ከአስተዳደር አካላት ጋር በመሆን የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡

በፀረ ሠላም ኃይሎች ፕሮፓጋንዳ ወደ ጥፋት ገብቶ የነበረው ወጣቱ ኃይል በሚፈጠርለት የሥራ ዕድል የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡

አዋጁ ባለፉት ሦስት ወራት በጌዴኦ ዞን ባስገኛቸው ሰላም የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸው፣ ለተገኘው ሰላም ሕብረተሰቡ የነበረው አስተዋዕኦ ከፍተኛ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በሁከትና ግርግሩ የተሳተፉትንና ከጀርባ ሆነው ሲመሩ የነበሩትን በማጋለጥና ለፀጥታ ኃይሉ በማስረከብ ረገድ ህብረተሰቡ የጎላ አስተዋጽኦ አድርጓል ፡፡

በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው በቂ ማስረጃ የተገኘባቸው ግለሰቦች በፍጥነት ለፍርድ አልቀረቡም የሚል ቅሬታ በአንዳንድ ወገኖች ይነሳ እንደነበር ያስታወሱት ኮለኔሉ፣ መረጃዎችን የማጣራትና መሰል ሥራዎች ጊዜ መፍጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ግለሰቦቹን በቅርቡ ለፍርድ ለማቅረብ የቅደመ ዝግጅት ሥራው መጠናቀቁን ኮሎኔል ጀማል አክለው ገልጸዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ዩኒት አስተባባሪ አቶ ታሪኩ ዋቆ በበኩላቸው፣ በዞኑ በርካታ ኢንዱስትሪዎች በጸረ ሰላም ኃይሎች ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይህም በባለሀብቱ ዘንድ ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሮ እንደነበር ገልጸው፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባመጣው ሠላምና መረጋጋት ሥጋቱ ቀርቶ ባለሀብቶቹ ወደቀድሞ የልማት ሥራቸው መግባታቸውን አስረድተዋል፡

ባለፉት ሰደስት ወራት በዞኑ ለባለሀብት ሊሰጡ ከታቀዱ ስድስት አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶች አራቱን ማሳካት መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

በዲላ ከተማ በአሰሪና ሠራተኛ አገናኝነት በማህበር ታቅፎ እየሰራ የሚገኘው ወጣት ዝናቡ ቱሼ በበኩሉ፣ በሁከትና ግርግሩ ደንበኞቻቸው ቀንሰው እንደነበርና አዋጁን ተከትሎ በሰፈነው ሰላም ሥራቸው ወደ ነበረበት መመለሱን ተናግሯል፡፡ 

በዞኑ ተፈጥሮ በነበረው ሁከት ምክንያት በቁጥጥር ሥር ውለው በይርጋአለም ተሀድሶ ማዕከል የቆዩ አንድ ሺህ 813 ሠልጣኞች የበደሉትን ህዝብ ይቅርታ በመጠየቅ መቀላቀላቸው ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ ዜና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአካባቢያቸው ልማቱን በማስቀጠል በኩል ጠቀሜታው የጎላ እንደነበር አንዳንድ የደምቢ ዶሎ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል የቀበሌ 04 ነዋሪ አቶ ቡራዩ ቶለሳ በሰጡት አስተያየት በአዋጁ ምክንያት በተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም ከመግባቱ በተጨማሪ ልማቱን በማስቀጠል ዕድገቱ እንዲቀጥል ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

አዋጁ  ሁሉም  የዕለት ተዕለት ሥራውን በሠላም  እንዲያከናውንና ለአካባቢው ልማት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተገኘው  ሠላምና መረጋጋት  መዘናጋት አንዳይፈጠር መንግሥትና ሕዝብ የአካባቢያቸውን ሠላም ነቅተው መጠበቅ እንዳላባቸውም አቶ ቡራዩ መክረዋል፡፡

በከተማው ቀበሌ 05 ነዋሪ አቶ ያዳቹ ተረፈ በበኩላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ወዲህ የመማር ማስተማር ሥራውና ገበያው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

"የመንግስት ሠራተኛውም ባለጉዳዮችን በአግባቡ እያስተናገደ  ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የከተማው ከንቲባ ድሪባ አብዲሳ በበኩላቸው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በከተማቸውና በአካባቢያቸው አስተማማኝ ሠላምና መረጋጋት ማስፈኑን ተናግረዋል።

በዚህም የከተማው የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ቀጣይነት ባለው  ሁኔታ እየተካሄዱ መሆናቸውንና ሕብረተሰቡም ያለምንም ስጋት በልማት ሥራው ላይ እየተሰማራ መሆኑን አስረድተዋል።

የዞኑ ኮማንድ ፖስትና ሕዝቡ በጋራ በመሆን የአካባቢያቸውን ሠላም ለማስጠበቅ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲያደርጉት የነበረውን እንቅስቃሴ  አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመልክተዋል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን