አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 07 December 2017

ሰመራ ህዳር 28/2010 የሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ በ450 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገለት የማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቆ ተመረቀ።

"ሱልጣን አሊሚራህ ሀንፎሬ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ" ተብሎ እንዲጠራ መወሰኑንም የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አስታውቀዋል።

ርዕሰ መስተዳሩ አቶ ስዩም አወል በምረቃው ላይ እንደተናገሩት የአውሮፕላን ማረፊያው የማስፋፊያ ግንባታ መጠናቀቅ የክልሉን ልማት ለማፋጠን ትልቅ እገዛ ያደርጋል።

አውሮፕላን ማረፊያው በሱልጣን አሊሚራህ መሰየሙም ለህዝቦች ተጠቃሚነት ላደረጉት አስተዋጽኦ መታሰቢያ እንደሆነ ተናግረዋል።

በምረቃው ላይ የተገኙት የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ እንደተናገሩት መንግስት ከሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች መካከል 450ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ አንዱ ነው።

ክልሉ ካለው እምቅ የግብርናና የማዕድን አቅም እንዲሁም ዋነኛ የገቢና ወጪ ንግድ ኮሪደር ከመሆኑ አንጻር አውሮፕላን ማረፊያው ከፍተኛ ሃገራዊ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኤርፖርቶች አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት በበኩላቸው እንደገለጹት የተጠናቀቀው የማስፋፊያ ግንባታ በ45 ሜትር ስፋት እና 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር አስፓልት መንደርደሪያ ያለው ነው።

በተጨማሪም የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ግንባታም በተጀመረ አመት ባልሞላ  ግዜ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ በመጠናቀቁ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰመራ ሱልጣን አሊሚራህ ሀንፎሬ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ  በ2004 ዓ.ም. አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወቃል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ህዳር 28/2010 አዲስ የተቀረጸውን የህገ መንግስቱንና የፌዴራል ሥርዓቱን የአስተምሮ  ስትራቴጂ የበለጠ ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ በትኩረት መስራትእንደሚገባ ጠቅላይ  ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የህገመንግስቱና የፌዴራል ሥርዓቱ አስተምሮ ምን መሆን አለበት በሚል   አዲስ ስትራቴጂ በቅርቡ ተቀርጾ ወጥቷል፡፡ 

የህገ መንግስቱንና የፌዴራል ሥርዓቱን አስተምሮ ስትራቴጂን ይበልጥ በሁሉም ውስጥ ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ መሥራት እንደሚጠይቅና በዚህ የአስተሳሰብ ግንባታ ላይ ባለ ጉድለት ምክንያት የሚስተዋሉ ችግሮችን  መቅረፍም ያስፈልጋል ብለዋል።  

የሀገሪቱ  የቃል ኪዳን ሰነድ የሆነውን ህገ መንግት  የኢትዮጵያ ዜጎች አውቀው እንዲተገብሩና ሌሎች እንዲያከብሩት መስራት እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡

ዜጎች ይሄን ግዴታቸውን  መወጣት እንዲችሉ የፌዴራል ሥርዓቱን ህጎችንና ተግባራቶችን  ጠንቅቆ በማወቅ ብሎም የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለማስወገድ ዴሞክራሲያዊ  ትግልን  ማጠናከር  ይገባል ነው ያሉት፡፡

ዜጎች በፈለጉበት የአገሪቷ አካባቢ በነፃነት ተዘዋውረው የሚሰሩበት ህገ መንግሥታዊ  መብታቸውን ማረጋገጥም እንደሚያስፍልግ አስታውቀዋል፡፡

በአገሪቱን ፈጣን እድገት ለማስመዝገብ  ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶችን ማካሄድ ወሳኝ እንደሆነና  ለእድገቱ ማነቆ የሆኑ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶችንና ተግባራቶችን ማስወገድ እንደሚጠይቅም  ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት አተረጓጎም ላይ ስህተት እንዳይኖር  ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግና ይሄ መብት እሰከተከበረ ድረስ የጋራ እሴቶችንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን ማጠናከር ይቻላል ነው ያሉት።

በአንዳንድ አከባቢዎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንዲጋጩ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ሥርዓቱን አስተካክሎ መቀጠል ወሳኝ  መሆኑንም  አስታውቀዋል፡፡

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የምታደርገው ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳለጥ የሚያስችሉና ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ጥናትና ምርምሮች እንዲያደርጉ ተጠየቀ።

የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት እና የስዊድኑ ጆንሾፒንግ ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ትምህርት ቤት በጋራ ያዘጋጁት ዓለም አቀፍ የቢዝነስና የኢኮኖሚ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው እሸቱ ጮሌ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተጀምሯል።

በኢኮኖሚክስና በቢዝነስ ዘርፍ ያሉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የዘርፉ ምሁራንን በአንድ መድረክ በማገናኘት የእውቀትና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ጥናትና ምርምሮችን ማቅረብ የጉባኤው አላማ ነው።

የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር ዶክተር ይናገር ደሴ እንደተናገሩት፤ አገሪቷ በአሁኑ ወቅት ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሸጋገር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ነው።

በዚህ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ በሚፈለገው መልኩ እንዳይሄድ ማነቆ የሆኑ ችግሮች እንዳሉ ገልጸው፤ ለነዚህ ችግሮች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥናት የተደገፈ መፍትሄ ማቅረብ ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ከአገሪቷ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ድርሻ ከፍተኛውን ቦታ የያዙት የግብርናና የአገልግሎት ዘርፎች መሆናቸውን ጠቁመው፤ "የኢንዱስትሪው በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ድርሻ ዝቅተኛ ነው" ብለዋል።

ኢንዱስትሪው ለአገሪቷ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ ለምን አነስተኛ ሆነ? የዘርፉን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ምን መደረግ አለበት? በሚለው ዙሪያ የኢኮኖሚ ምሁራን በጥናት ላይ የተመሰረተ ሀሳብ ማቅረብ እንዳለባቸው ነው ዶክተር ይናገር ያስረዱት።

በኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩ ላይ ያሉትን ችግሮች በጥናትና ምርምር በመለየት ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦች ማስቀመጥ እንደሚገባና ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከግብርናው ዘርፍ  ወደ ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በሚያደርጉበት ወቅት ተመሳሳይ የሆኑ ችግሮች እያጋጠሟቸው እንደሆነ ነው ኮሚሽነሩ ያብራሩት።

ስለዚህም የአፍሪካ የዘርፉ ተመራማሪዎች በጉዳዩ ላይ ሰፊ ጥናት በማካሄድ መንግስታት በቀጣይ መውሰድ ስለሚገባቸው እርምጃዎች በእውቀትና በመረጃ የተመሰረቱ ጥናቶችን ማድረግ የትኩረት አቅጣጫቸው ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር ይትባረክ ታከለ በበኩላቸው፤ በአገሪቷ ያሉ የኢኮኖሚ ጉዳዮች በየትኞቹ ላይ ጥናት ማድረግ ይገባል? ዋንኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው? የሚለውን ከመለየት አኳያ ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል።

የክፍተቱ ምክንያት መንግስትና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተቀናጅቶና ተናቦ አለመስራት እንደሆነም ነው ዶክተር ይትባረክ ያስረዱት።

ጉባኤው መንግስትና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በማስተሳሰር በኢኮኖሚው ዘርፍ ሊጠኑ የሚገባቸውን ጉዳዮች ለዘርፉ ምሁራን ከማመላከት አኳያ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበርክትም አመልክተዋል።

በጉባኤው ላይ ከሚቀርቡ ጥናታዊ ጽሁፎች መካከል በኤዲቶሪያል ቦርድ ተገምግመው ተገቢውን መስፈርት ያሟሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በአፍሪካ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ጆርናል እንደሚታተሙ ጠቁመዋል።

በጉባኤው ላይ ከ22 አገራት የተወጣጡ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዘርፉ ምሁራን እየተሳተፉ ሲሆን ከ80 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎች እንደሚቀርቡም ተገልጿል።

ጉባኤው ነገ ፍጻሜውን የሚያገኝ ይሆናል።

 

 

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ ህዳር 28/2010 የጊኒ ዎርም በሽታን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃን አሳሰቡ፡፡

 የጊኒ ዎርም በሽታ ማጥፋት ላይ ያተኮረ 22ኛው ሀገር አቀፍ የእቅድ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል ።

 ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት መስሪያ ቤታቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ባከናወናቸው ስራዎች በሽታው ለመጥፋት ተቃርቦ ነበር፡፡

 ሆኖም እንደገና አገርሽቶ በተያዘው ዓመት 14 ሰዎች በሽታው ተጠቅተው ተገኝተዋል፡፡ 

 በሽታው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአራት የአፍረካ ሀገራት በስተቀር በሌሎች የዓለም ሀገራት መጥፋቱን ፕሮፌሰር ይፍሩ ተናግረዋል ።

 ይሁንና በአራቱ የአፍሪካ ሀገራትም ቢሆን በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ቀደም ሲል ከነበረው እየቀነሰ እንደሚገኝ ጠቁመዋል

 መንስኤውም "በበሽታው አምጭ ረቂቅ ህዋስ የተበከለ ውሃ መጠጣት ለበሽታው ተጋላጭ ያደርጋል " ነው ያሉት።

 የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግና የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በሽታውን ከሀገሪቱ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት  ባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶች ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 የዓለም ሎሬትና የአፍሪካ የጊኒ ዎርም ማጥፋት ፕሮግራም በጎ ፍቃድ አምባሳደር ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን በበኩላቸው ባለፈው ዓመት የበሽታውን መጥፋት የመጨረሻ ምዕራፍ ለማየት እቅድ ተይዞ እንደነበር አስታውሰዋል ።

 "ይሁንና በሽታው እንደገና በወረርሽኝ መልክ መከሰቱ አስደንጋጭ ነው"ብለዋል።

 በተለይም ቀደም ሲል በጋምቤላ ክልል በተወሰኑ ወረዳዎች ብቻ ይገኝ የነበረው በሽታው  ዘንድሮ  ወደ ሌሎች አካባቢዎች የመስፋፋት አዝማሚያ ማሳየቱን ጠቁመዋል።

 እንደ ዶክተር ጥበበ ገለፃ በተያዘው የአውሮፓ ዓመት በሽታው ይገኝባቸዋል ከሚባሉት አራት የአፍረካ ሀገራት መካከል በኢትዮጵያና በቻድ 28 ሰዎች ተጠቅተው ተገኝተዋል፤ በደቡብ ሱዳንና በማሊ ግን በበሽታው የተጠቃ ሰው አልተገኘም ።

 "ይህም በኢትዮጵያ በሽታውን በማጥፋት ረገድ ባለፉት ዓመታት የነበረው ስኬት ወደ ኋላ እየተመለሰ ስለመሆኑ አመላካች ነው" ብለዋል።

 የጊኒዎርም በሽታ ከሀገሪቱ  ለማጥፋት ከፌደራል ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በትብብርና በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

 የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት የበሽታው ስርጭት ከክልሉ   ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 "ከህብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስና ከንጹህ መጠጥ ውሃ አቅረቦት ችግር ጋር ተያይዞ በሽታውን የማጥፋቱን ስራ ጊዜ እንዲወስድ አድርጎታል" ብለዋል።

 በተለይም ባለፉት ዓመታት በሽታውን ለማጠፋት በተከናወኑ ስራዎች  የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ወደ ሁለትና ሶስት ዝቅ ብሎ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ የተጠቂዎች ቁጥር እንደገና ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።

 ለሁለት ቀናት በተካሄደው ሀገር አቀፍ  የእቅድ አፈፃፀም መድረክ ባለድርሻ አካላትና የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች ተሳትፈዋል ።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን በተመለከተ የፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ ክፍተት እንዳለበት ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው የአዲስ  አበባ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ "በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል የወንዶችን አጋርነት ማጠናከር" በሚል መሪ ሃሳብ ባካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ነው።

በዚህም ቢሮው በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከልና የወንዶች አጋርነትን ለማጠናከርም የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ሴቶች የፍትህ አሰጣጥ ሂደቱን በተመለከተ ውይይት አካሂደዋል።

የፍትህ አካላት፣ የጤናና የትምህርት ዘርፎች፣ ከንቲባ ጽህፈት ቤት፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ንግድ ቢሮ፣ባህልና ቱሪዝም፣የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኢንዱስትሪ ቢሮና የሃይማኖት ተቋማት በምክክር መድረኩ ከተገኙት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሴቶች ላይ የሚደርሰውን አካላዊና ጾታዊ ጥቃት በተመለከተ ያለው የፍትህ አሰጣጥ ክፍተት የሚታይበት በመሆኑ "በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲባባስ አድርጎታል" ብለዋል።

በከንቲባ ጽህፈት ቤት የህዝብ አደረጃጀት አማካሪው አቶ ሞላ ንጉስ ''ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ላይ ሁሉም ተቋም ትኩረት አድርጎ እርምጃ ቢወስድ ተጽእኖ ማሳረፍ ይችላል በአስተሳሰብ ማውገዝ ይችላል ህጉ አለ ህጉ ሲፈጸም የተዛባ ከሆነ ህጉን  የሚያስፈጽሙት አካላት ላይ ተጽእኖ ማሳረፍ ይገባል።''ብለዋል

የአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊዋ ወይዘሮ አለምጸሃይ ኤሊያስ በበኩላቸው "የፍርድ ቤት ውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱን የሚያጓትቱ የመረጃ አያያዝ ስርዓቶች በአዲስ መልክ መሰራት አለበት" ብለዋል።

በዚህም ጥቃት ፈጻሚው  ከበድ ያለ ውሳኔ እንዲጣልበት የሚያስችል ቅንጅታዊ አሰራር ለማስፈን በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸው፤ የፍርድ ቤት ውሳኔ የሚያሰጡ አንቀጾችም በድጋሚ የሚታዩበት አካሄድ ለመፍጠርም የባለድርሻ አካላት ሚና የላቀ እንደሆነም አንስተዋል።

''ትልቁ ችግራችን ተመጣጣኝ ውሳኔ የማይወሰደው ፍርድ ቤት ላይ ብቻ ሳይሆን መጠቀስ ካለበት ከአንቀጹ ጀምሮ ነው።ተመጣጣኝ ውሳኔ ሊያሰጥ የሚችል የአንቀጽ ልየታ ጭምር ችግር እንዳለ አይተናል።እዚህ ላይ ጥራት ያለው መረጃ ስርአት ኖሮን ይሄንን መረጃ ደግሞ ውሳኔውን ሊያከብድ የሚችል አደረጃጀት ስርአት ሊኖረን የሚያስችል አሰራር እንፈጥራለን። “ነው ያሉት፡፡

በምክክር መድረኩ የተገኙ ባለድርሻ አካላት በቀጣይ የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል ቀልጣፋ አሰራር ለመዘርጋትም የጋራ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን  ከተፈራረሙበት እለት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ በመድረኩ ተነግሯል።

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 በኤች.አይ.ቪ ኤድስ  ዙሪያ የሚሰሩ ክበባት መቀዛቀዝ ለበሽታው ዳግም ማንሰራራት ምክንያት መሆኑ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት ከአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ጋር በመተባበር የአለም የኤድስ ቀንን አስመልክቶ  ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተወጣጡ ሴቶች ጋር ውይይት አካሄዷል።

የፅህፈት ቤቱ የዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ እንደገለፁት ባለፉት አመታት በበሽታው የሚሞቱ ዜጎች ቁጥር መቀነሱ  ህብረተሰቡ እንዲዘናጋና በሽታው ዳግም እንዲያንሰራራ አድርጎታል።

በመሆኑም ከዚህ ቀደም  በየቀበሌውና ወረዳው ተቋቁመው የነበሩ ክበባት በሽታውን በመከላከልና ግንዛቤ በመስጠት የነበራቸው እንቅስቃሴ መዳከሙ ለበሽታው ማንሰራራት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩን ለመከላከል ክበባትን በማጠናከር ረገድ ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበት ተናግረው ህብረተሰቡም ተሳትፎውን በድጋሚ ማጠናከር እንደሚገባው ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ዋና ፀሃፊና የማህበራዊ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ዘነበች አበበ  በበኩላቸው በሽታውን የመርሳት ያህል ችላ በማለታችንና የሚገባውንም ትኩረት ባለመስጠታችን በድጋሚ ሊቀሰቀስ ችሏል ብለዋል።

ወጣት ሴቶች ለበሽታው ተጋለጭ መሆናቸውን አስታውሰው በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው መዘናጋት መቆም አለበት በማለት ተናግረዋል።

ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩ ዜጎች የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑም ተገልጿል፤ ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ መንግስት በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ለሆኑት ሴተኛ አዳሪዎች የተሻለ የስራ እድል የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባ በውይይቱ የተገኙት ሴቶች አስታውቀዋል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአገሪቷ 27 ሺ 288 ሰዎች በየዓመቱ በበሽታው የሚያዙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 16 ሺ 21 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው::  

 

Published in ማህበራዊ

ፍኖተ ሰላም ህዳር 28/2010 ከግብርና የሚገኘውን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በእንስሳት ኃብትና መስኖ ልማት ላይ እየሰራ መሆኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳደር ገለፀ።

በዞኑ ስንዴ፣ጤፍ፣በቆሎና የቢራ ገብስ በኩታ ገጠም አስተራረስ በስፋት እየተሰራበት መሆኑን ነው የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ስሜነህ አያሌው የገለፁት።

የዞኑን ምርታማነት በማሳደግ  የአርሶ አደሩን ምርት ለመጨመር ከመኸር ምርት በተጨማሪ ከሰብል ልማት ወደ ቡናና ፍራፍሬ ልማት ለማሸጋገር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዞኑ ለመስኖ ስራ ወንዞች መኖራቸውን ጠቁመው በዘመናዊ የውሃ መስኖ ግንባታ፣በባህላዊ ወንዝ ጠለፋና አልፎ አልፎ የውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች የውሃ ማቆር ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በተያዘው የምርት ዘመንም በዞኑ 168 ሺህ 609 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ የማልማትና የግንዛቤ ስራ እየተሰራ ነው ተብሏል።

የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለመጨመር እንደ መኸር ሰብሎች ሁሉ ገበያ ተኮር የሆኑ ምርቶች መስኖን በክላስተር የማልማት ስራና የገበያ ትስስር እየፈጠሩ መሆናቸውንም ነው የገለፁት።

ቡናን፣ማንጎና አቮካዶን በተለያዩ ወረዳዎች በክላስተር ለማልማት የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ዞኑ ለእንስሳት እርባታ የተመቸ በመሆኑ በከብት ማድለብና በወተት ምርት ላይ እየሰሩ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጎሹ እንዳላማው ናቸው።

የእንስሳት ኃብት ልማትን ለማሳደግ በዞኑ 363 የገጠር ቀበሌዎች የእንስሳት እርባታ ባለሙያዎች እንዳሏቸውና በሁሉም ቀበሌዎች የእንስሳት ጤና ክሊኒኮች በመክፈት አርሶ አደሩ ዝርያ የማሻሻል፣የማድለብ እና የወተት ኃብት ልማትን የማሳደግ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በዞኑ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የዳልጋ ከብቶች እንደሚገኙ ዋና አስተዳዳሪው አስታውሰዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 በአዲስ አበባ ከተማ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ በየተቋማቱ እየሰሩ የሚገኙ ግለሰቦች በተቀመጠላቸው የይቅርታ የጊዜ ገደብ ውስጥ ራሳቸውን እንዲያጋልጡ ተጠየቀ።

ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በአዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 በሙስና ወንጀል እንደሚያስጠይቅና እስከ 25 ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል።

በመሆኑም በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃና የብቃት ማረጋገጫ እየሰሩ ያሉ ግለሰቦች ራሳቸውን ማጋለጥ እንዳለባቸው ነው የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ የገለጸው።

በአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ይስሃቅ ግርማይ እንደገለጹት፤ ብቃት ያለውና ውጤታማ የሆነ ሲቪል ሰርቪስ ለመፍጠር የትምህርት ማስረጃዎችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

በአዲስ አበባ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ተቀጥረው የሚሰሩ ግለሰቦች መኖራቸው ይታመናል። 

በዚህም በአዲስ አበባ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች "ከህዳር 7 እስከ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ የይቅርታ ጊዜ ገደብ ተቀምጦ ራሳቸውን እንዲያጋልጡና ይቅርታ እንዲጠይቁ ተደርጓል" ብለዋል።

በመሆኑም ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዘው እየሰሩ የሚገኙ ግለሰቦች "በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ራሳቸውን ማጋለጥና ይቅርታ መጠየቅ ይገባቸዋል" ነው ያሉት።

በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሥራ የያዙና የደረጃ እድገት ያገኙ ሰዎች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ራሳቸውን የሚያጋልጡና ይቅርታ የሚጠይቁ ከሆነ በወንጀል እንደማይጠየቁ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ያለ አግባብ የወሰዱትን ጥቅማ ጥቅምና ደመወዝ መልሱ ሳይባሉ በትክክለኛ የትምህርት ማስረጃቸው ዝቅ ብለው እንዲሰሩ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

እንደ ቢሮ ሃላፊው ገለጻ፤ የይቅርታ ጊዜው ከተጀመረበት ከህዳር 7 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ቁጥራቸው ከ10 የማይበልጡ ሰዎች ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው መሆኑን በፈቃዳቸው አረጋግጠዋል።

የይቅርታ ጊዜው ከሚያበቃበት ከታህሣስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም በኋላ መንግሥት በራሱ መንገድ አጣርቶ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲጠቀሙ ከደረሰባቸው ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተገልጿል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎቱን የሚያቀላጥፍ የሞባይል አፕሊኬሽን ይፋ አደረገ።

አዲሱ አሰራር አየር መንገዱ የሚሰጣቸውን የተለያዩ አገልግሎቶችን የያዘ ሲሆን ደንበኞች የበረራ ቀጠሮ ማስያዝና ሌሎች ጉዳዮችን በቀላሉ መከወን ያስችላቸዋል።

በአገልግሎቱ አማካኝነት ደንበኞች በረራቸውን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚያገኙም አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። 

የሞባይል አፕሌኬሽኑን የሚጠቀሙ ደንበኞች ለበረራ ቀጠሮ ሲያሲዙ ከሚከፍሉት ገንዘብ የ10 በመቶ ቅናሽ ያገኛሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንደገለጹት የሞባይል አፕሊኬሽኑ አየር መንገዱ ካለው ስትራቴጂ ውስጥ በዋንኛነት የሚጠቀስ ነው።

በዚህም የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን በመጠቀምና አፍሪካዊ ጣዕም ያለው ኢትዮጵያዊ አገልግሎት በመስጠት የደንበኞችን የበረራ ጊዜ ምቹ ማድረግ እንደሚያስችለው ገልጸዋል።

አየር መንገዱ የደንበኞችን የበረራ ፍላጎት ለማሟላት ደንበኛ ተኮር የሆኑ የተለያዩ አገልግሎቶችን ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም ገልጿል።

ተግባራዊ የሆነው የሞባይል አፕሊኬሽን አየር መንገዱ የደንበኞችን አገልግሎት ለማሻሻል እያከናወነ ላለው ስራ እንደ ማሳያ የሚወሰድ እንደሆነ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የደንበኞችን አገልግሎት እንደሚያሻሽል የታመነበት አዲስ የአቪዬሽን ሕብረት እንዲቋቋም መወሰኑንና ለዛም የሚሆን አዲስ አደረጃጀት ማጽደቁ የሚታወስ ነው።

ሽሬ እንዳስላሴ ህዳር 28/2010 በአራት ክልሎች በመገንባት ላይ ለሚገኙ የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በግብአትነት የሚጠቀሙባቸው ጥሬ ምርቶችን ለማመቻቸት የሚያስችል ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱን የእንስሳትና ዓሳ ኃብት ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

 በስትራተጂክ እቅዱ ዙሪያ በሸሬ እንዳስላሴ ከተማ ውይይት ተካሄዷል፡፡

 ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ገብረእግዛቢሔር ገብረዮውሃንስ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት በትግራይ ክልል የባእከር ኢንዱስትሪ ፓርክን  ጨምሮ በኦሮምያ ክልል  ቡልቡላ ፣ በአማራ ክልል በቡሬ ፣ በደቡብ ደግሞ  በይርጋለም  ከተማ  የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስቱሪ ፓርኮች ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

 ግንባታቸው ከ5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተካሄዱ ያሉት እነዚሁ ፓርኮቹ   ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ የማምረት ሥራ ይጀምራሉ ተብለው ይጠበቃል፡፡

 የፓርኮቹ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ማምረት ሲሸጋገሩ  የሚፈልጉት የግብርና ምርት በመጠን፣ በፍጥነትና በጥራት ዓመቱን ሙሉ ሳይቆራረጥ ማቅረብ የሚያስችል የሦስት ዓመት ስትራተጂክ እቅድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

 ከእቅድ ዝግጅቱ ጋር  ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የግብርና ባለሙያዎችና የህብረት ሥራ ማህበራት ተወካዮች ተሳታፊ የሆኑበት የምክክር መድረክ  በየደረጃው በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ የተካሄደው የውይይት መድረክም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 ፓርኮቹ  የማምረት ስራ ሲጀምሩ አርሶ አደሩ ምርቱን በቀላሉ  በማቅረብ ተጠቃሚ  እንደሚሆን የገለፁት ደግሞ  በኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቱት ዳይሬክተር አቶ ከሊፋ ሁሴን ናቸው።

 አግሮ እንዱስትሪ ፓርኮቹ የሚፈልጉትን እንስስትና የእንስስት ውጤቶች ዓመቱን ሙሉ ሳይቆራረጥ እንዲያገኙ ለአርሶ አደሮች ከወዲሁ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 በትግራይ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ኃብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጀማል ግደይ በበኩላቸው በክልሉ በባእከር እየተገነባ ያለው የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚያስፈልገውን ግብአት በአስተማማኝ መልክ ለማቅረብ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 በአግሮ እንዱስትሪ ፓርኩ አቅራቢያ የሚገኙ  የሦስት ዞኖች አርሶ አደሮችና  የህብርት ሥራ ማህበራት ምርቶቻቸውን በቀላሉ ለማቅረብ የሚያስችላቸው ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 በሽሬ እንዳስላሴ ለአምስት ቀናት  በተካሄደው የምክክር መድረክ  የግብርና ባለሙያዎችና የህብረት ሥራ ማህበራት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል። 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን